ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

በተአምራት አማኑኤል

(ክፍል 1)

.

የጥንቱ የኢትዮጵያ አፈ ታሪክ “አንድ ሽሕ ዓመት ያህል ከልደተ ክርስቶስ በፊት፣ ባገራችን ሊቃውንትና መምህራን ነበሩበት … እስከ ዛሬ ድረስም ሊቅ፣ መምህርና ደራሲ አልጠፉበትም” ይላል። ቢሆንም አፈ ታሪኩ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከብሉያት በቀር ሌላ ዓይነት መጻሕፍት መኖር አለመኖራቸውን አያመለክትም።

አፈ ታሪካችን በሰሎሞን ዘመን ከሕዝበ እስራኤል ጋራ ግንኙነት እንደነበረን፣ ንግሥተ ሳባ ዛሬ ኢትዮጵያ (ሐበሻ) የምንለውንና ከዓረብ አገር የደቡቡን ክፍል ትገዛ እንደነበረች፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ሒዳ ከሰሎሞን ጋር ተዋውቃ ከርሱ ቀዳማዊ ምኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ እንደወለደች፣ ቀዳማዊ ምኒልክም እስከ ዛሬ ድረስ ላሉት ነገሥታቶቻችን አባት መሆኑን፣ እርሱም አባቱን ሰሎሞንን ለማየት ሒዶ ከኢየሩሳሌም ሲመለስ፣ ጽላተ ሙሴንና እስከ ሰሎሞን ዘመን ከእስራኤላውያን የተጻፉትን መጻሕፍተ ብሉያትን ይዞ እንደመጣ ይነግራል።

ይህን አፈ ታሪክ የሚነግሩ መጻሕፍት ባገራችን መጻፍ የጀመሩት ከ1300ኛው ዓመተ ምሕረት ወዲህ ነው። ሽሕ ዓመት ከዚያ በፊት ለሕዝቡ ወንጌል ተሰብኮለት ነበር። በሽሕ ዓመት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ፣ በአሕዛብነት የነበረበትን ዘመን እንዲጠየፈው፣ የሕዝበ እሥራኤልን መጻሕፍትና አሳብ እንዲወድ አድርጎት ስለ ነበረ፣ ጥቂት በጥቂት የገዛ ራሱን ታሪክ እየዘነጋ፣ የእስራኤል ልጅ ነኝ ከማለትና የእስራኤል ሕዝብ የጻፋቸውን መጻሕፍት፣ አያቶቼ የጻፏቸው ናቸው ከማለት ደርሷል።

በሰሎሞን ዘመን የእስራኤልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ኖሯቸው ይሆናል ቢባል፣ ማስረጃው እንኳ ባይገኝ፣ ሳይሆን አይቀርም በማለት በተቀበልነው። በሰሎሞን ዘመን ከብሉያት መጻሕፍት አንዳንዶቹ እስከ ኢትዮጵያ ደርሰው በዚያው ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀብሎ የሃይማኖት ሥራ አስይዟቸዋል ለማለት ግን ማስረጃው እስኪገኝ ድረስ ልብ ወለድ የመጣ አሳብ ነው እንላለን።

የዛሬው ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሙሴ የሚባሉት አምስቱ ብሔረ ኦሪት ተሰብስበው ባንድነት መገኘት የጀመሩት በሰሎሞን ዘመን ብቻ ነው ይለናል። የዚህ ክርክር ገና ሳይጨረስ፣ አፈ ታሪካችን፤ “መጽሐፈ ኦሪት በሰሎሞን ዘመን ካገራችን ደርሰው ነበር” ሲል፣ ለራሱ ክብር በመጓጓት፣ ታሪክ ጥሶ የተራመደ ሁኖ ይታየናል። ይህም ከወገን ለጊዜው የበለጠ መስሎ የታየውን እየመረጡ “ወገኔ ነው” ማለት፣ የዛሬ ሳይሆን የጥንት፣ የኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የደረሰና፣ ታሪክ ተመርምሮ ወሬው ትክክለኛ አለመሆኑ ሲታይ የሚቀር ነው።

በግሪኮች ሥልጣኔ ንጹሕ ቅናት ያደረባቸው ሮማውያን፣ የግሪኮች መዓረግ ተካፋይ ለመሆን፣ የ”ኤኔአ”ን ተረት ፈጥረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕዝበ እስራኤል የተነገረው ሁሉ ደስ ሲያሰኛቸው ከነበሩት እንግሊዞች፣ አንዳንዱ ባለ ታሪክ፣ “ስደት የሔዱት የአስሩ ነገደ እስራኤል የልጅ ልጆች ነን” ሲል ነበር። ዛሬ ግን፣ ሮማውያንም ከግሪኮች ጋር ዝምድና እንኳ ቢኖራቸው፣ ባለ ታሪክ ሌላ ማስረጃ ያመጣል እንጅ የ”ኤኔአ”ን ተረት መሠረት አያደርገውም። የባለ ታሪክ ስምና መዓረግ ያለው ሰው ደግሞ፣ “በእንግሊዝ ደሴቶች ከምሥራቅ የመጣ ሕዝብ ሰፍሮበት ኑሮ ይሆናል” እንኳ ቢል፣ “አንግሎ ሳክሶን የአስሩ ነገደ እስራኤል ልጆች ናቸው” አይልም።

እንደዚኸው ሁሉ የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲሱ የምርመር አካሔድ የሚከታተል ሰው፣ ታሪኩን በሌላ መንገድ ያስረዳል እንጂ፣ ስለ ንግሥት ሳባና ስለ ሰሎሞን የሚነገረውን መሠረት አያደርግም። ስለዚህም ከልደተ ክርስቶስ በፊት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ኑረው እንደሆነ የደረሱበትን ለማወቅ ቸግሮናል እንላለን እንጅ (ሕዝበ እስራኤል በሰሎሞን ዘመን የሙሴን መጻሕፍት መሰብሰብ ገና ሲጀምር) እነዚህ መጻሕፍት ድሮ ባገራችን ነበሩ ለማለት ይቸግረናል።

በውቅሮ አቅራቢያ የተገኘው የአልሙቃሕ ቤተ ጸሎት

ጽሑፍ ሥራ በኢትዮጵያ ገና ከልደተ ክርስቶስ በፊት ተጀምሮ ነበር እንላለን። ማስረጃው ግን በጣም ችግር ነው። እርግጥ የምናውቀው ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን አቅራብያ በትግሬ አውራጃ ከሐውልትና ከጸሎት ቤት የተጻፈ አንዳንድ ቃል መገኘቱን ነው። ቀደምት የተባሉት ጽሕፈቶች የሚገኙት በሳባና በግሪክ ቋንቋ ነው። ከክርስቶስ ልደት በኋላ 300ኛው ዘመን ሲጀምር ግን፣ ጽሕፈቱና ንግግሩ የተጣራ፣ በግዕዝ ቋንቋ ከሐውልት ላይ የተጻፈ መታሰብያ አለ። ስለዚህም ከሊቃውንት አንዳንዱ እንዲህ ይላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፣

           ፊት፤                ግሪክ፣

          ቀጥሎ፤              ሳባ፣

           ኋላ፤                ግዕዝ

king-ezana-s-inscription
የንጉሥ ኤዛና የድል ሐውልት በአክሱም

ለዚህ አሳብ ብዙ ተቃራኒ አልተነሣበትም። ነገር ግን ገና የመንን ሳይለቅ ባገሩ ቋንቋና ፊደል ሲጽፍ የነበረ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለምን በግሪክ ጻፈ? ደግሞም እስከ ዛሬ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ሥራ የተያዘበት ሴማዊ የሆነው የግዕዝ ቋንቋ እጅግ የተጣራ በመሆኑ፣ ለግሪክና ለላቲን ቋንቋ ተወዳዳሪ ሊሆን ይቃጣዋል። ይህን የመሰለ ቋንቋ እያለው ባገር ውስጥ ላለው ጕዳይ ለምን በግሪክ ይጽፋል? የዚህ ምክንያቱ እስኪገለጥ ድረስ ከዚህ በላይ የተነገረው አሳብ ትክክለኛ ነው ላይባል ነው።

በርሱ ፈንታም ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን አሳብ መናገር ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፤

           ፊት፤                ሳባ፣

           ቀጥሎ፤            ግዕዝ

የግሪክ ቋንቋ ከእስክንድር ጀምሮ ሮማውያን ግብጽን እስከያዙበትና ከዚያም በኋላ እስከ ብዙ ዘመን ለግብፅና ለታናሽ እስያ ሕዝብ ዋና ቋንቋ ሁኖ ነበረ። ለኢትዮጵያ ደግሞ ከሠለጠነው ዓለም ጋር መገናኛ ቋንቋ ሁኖላት ለደብዳቤ፣ አላፊ አግዳሚ ለሚያየው ሐውልትዋ፣ ባሕር ተሻግሮ ለሚገበያዩበት ገንዘብዋ፣ ይህንንም ለመሰለ ልዩ ጕዳይ የጽሕፈት ቋንቋዋ ኑሮ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ከ400ኛው ዓመተ ምሕረት በፊት (ይህ ማለት ወንጌል ባገሩ ሳይሰበክ) በሳባ ሆነ በግሪክ፣ በግዕዝም ሆነ ወይም በሌላ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ኑሮ እንደሆን ወሬው ከኛ አልደረሰም። ዛሬ በጃችን ያሉት መጻሕፍት ከ400ኛው እስከ 1700ኛው ዓ ም በግዕዝ፣ ከዚያ እስከ ዛሬ በግዕዝና በአማርኛ የተጻፉ ናቸው። ግዕዝ የሴም ቋንቋ መሆኑን ከዚህ በፊት አመልክተናል። ከዓረብ በስተደቡብ ከነበሩት ሴማውያን ያንዱ ነገድ ቋንቋ ኑሮ ይሆናል ይባላል። ምናልባትም ከዚሁ ነገድ አንድ ክፍል ዛሬ ዓጋሜ በምንለው አውራጃ ግድም ይኖር ኖሯል። ድንገት ደግሞ ከትግሬ አውራጃ ካሉት ነገዶች አንዳንዶች ይነጋገሩበት ኑረው ይሆናል። “በኢትዮጵያ ያሉት የሴም ቋንቋዎች (ትግርኛ፣ ትግረ፣ አማርኛ፣ ወዘተ) ከርሱ የመጡ ናቸው” የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ይህን አሳብ የማይቀበሉ በዚህ ፈንታም፣ “ከዓረብ በስተደቡብ ሲኖሩ ከነበሩት የሴም ነገዶች አንዳንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ ኖሯቸው፣ የእያንዳንዱ ነገድ ቋንቋ ራሱን እንደቻለ፣ በሆነለት መጠን እየደረጀ ሄዷል እንጅ፣ ግዕዝ በኢትዮጵያ ላለው ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ አባቱ አይደለም” የሚሉ አሉ።

img0042
በቀደምትነቱ የሚታወቀው የአባ ገሪማ ወንጌል

በግዕዝ ከተጻፉት በብዙ ሽሕ ከሚቆጠሩት መጻሕፍቶቻችን ጥቂቶች ሲቀሩ፣ አብዛኛው ከክርስትያናዊ ግሪክና ዓረብ ከሌላም ቋንቋ የተተረጐሙ ናቸው። ደግሞም የዓለምንና የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚነግሩት ከጥቂቶች መጻሕፍት በቀር ሁሉም የሃይማኖት መጻሕፍት ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያዊነታችንን አሳብ የሚገልጥ መጽሐፍ በብዛት አይገኝባቸውም። ዋናው መጽሐፋችን “መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። ይኸውም ብሉይና ሐዲሱ እግዚአብሔር በዓለምና በእስራኤል ላይ የሠራውንና የሚሠራውን እስራኤላውያን በታያቸው ዓይነት የሚገልጽ መጽሐፍ መሆኑን፣ ሁሉ ያውቀዋል። ምስጋና ለዚህ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በሃይማኖትና በምግባር ከፍ ካለ ደረጃ ደርሶ፣ በያዘው መንገድ እየገፋበት እንዲሔድ ብርቱ ኃይል ተሰጥቶታል።

ደግሞም የግዕዝ ቋንቋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወዳገራችን ሳይመጣ ገና ፊት አስቀድሞ ራሱን የቻለ እንደነበረ በሐተታ እንኳ ብንረዳው፣ የግዕዝ ቋንቋ ጽሑፍ ምስክሩ ባለቤቶቹ የጻፉት መጽሐፍ መሆኑ ቀርቶ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የሌሎች መጻሕፍት ትርጕም ነው። ማናቸውም የሠለጠነ ሕዝብ ለቋንቋው፣ ለሰዋስው ማስረጃ ባለቤቶቹ የጻፉትን ሲጠቅስ፣ ግዕዝ ለሰዋስው ማስረጃ የሚጠቅስ ከባዕድ ቋንቋ የተተረጐሙትን መጻሕፍት ነው። በግዕዝ ከጻፉት ካገራችን ደራስያን ይቅርና በአሳብ፣ በአጻጻፍ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል ሳይከተሉ የጻፉ የሚገኙ አይመስለኝም። ይህም ልምድ የሃይማኖት አሳባቸውን የሚገልጹበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ አገራችን ታሪክና ማናቸውንም ጕዳይ በሚጽፉበት ጊዜ ጭምር ነው። ይህም የአጻጻፍ አካሔድ ኢትዮጵያ ገንዘብ ካደረገችው ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር የተስማማ ንግግር ለማምጣት የተመቸ ከመሆኑ በላይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሳንቀበል ከነበረብን አሕዛባዊ ከሆነ ምሳሌና ንግግር አርቆናል።

ይሁን እንጅ ኢትዮጵያዊ የሆነ አሳብ፣ ኢትዮጵያዊ በሆነ ንግግር የመግለጹ ዕድል ለግዕዝ ቀርቶበት ለአማርኛ ሆኗል። ዛሬ ዘመን በግዕዝ እግር ተተክቶ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ጕዳይ የሚሠራበት የአማርኛ ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባማርኛ መጻፍ ከጀመረ ስድስት መቶ ዓመታት ሁኖታል። አማርኛ ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን አካሔድ በ፫ ዘመን ቢከፍሉት ይሆናል።

፩ኛውን ዘመነ ዓምደ ጽዮን (1336-1599 ዓ ም)

፪ኛውን ዘመነ ሱስንዮስ (1599-1847 ዓ ም)

፫ኛውን ዘመነ ቴዎድሮስ (1847-1936 ዓ ም)

በ፩ኛው ዘመን በአማርኛ የተጻፈው ሥራ እጅግ ጥቂት ነው። የተጻፈውም ላንዳንድ ነገሥታት ምስጋና ደራሲው ባልታወቀ የተገጠመ ቅኔ ነው። ቅኔውም በዘመናት ውስጥ አንድ ቋንቋ እንደምን ሁኖ እየተለዋወጠ ለመሄዱ ዋና ምስክር ከመሆኑ በላይ በዚያ ዘመን የነገሥታቱ ሥልጣን የተዘረጋበት የሰፊው አገር ሁኔታ እንዴት እንደነበረ፣ ለታሪክም ለዦግራፊም ማስረጃ ለመሆን ይረዳል።

pages-from-bruce-88-bodleian-library-oxford
በአማርኛ የተጻፈ የነገሥታት ግጥም (የ1600ዎቹ ቅጂ)

አማርኛው ዛሬ ዘመን የማንናገርበትና የማንጽፈው፣ ለማስተዋሉም የሚያስቸግረንና የሰዋስው አካሔዱ የተለዋወጠ ብዙ ቃልና አገባብ አለበት። እርሱን የመሰለ አማርኛም በየዘመኑ እየተጻፈ ምናልባት እስከ 1599 ደርሶ ይሆናል። ነገር ግን ከ1555 እስከ 1599 ዓ.ም ባማርኛ የተጻፈ ምስክር አይገኝም፤ ቢገኝም ከዚህ በፊት ያመለከትሁትን የመሰለ ግጥም ሳይሆን አይቀርም።

ከ1500ኛው ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወገን ለይቶ አልጋ ለመያዝ እርስ በርሱ ሲዋጋ፣ ባንድ ወገን ደግሞ ቱርኮችና ፖርቱጋሎች በቀይ ባሕር ሥልጣናቸውን ለመዘርጋት ይፈካከሩ ነበር። ቱርኮች በቀይ ባሕር ዙርያ ላለው ፖሊቲካቸው የኢትዮጵያን እስላም ሲረዱ፣ ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የፖርቱጋልን እርዳታ መለመን ግድ ሆነበት። አራት መቶም ያህል ጠበንጃ የያዙ ፖርቱጋሎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተዋጉበት ጊዜ፣ ድል ለክርስቲያኑ ወገን ሆነ።

የፖርቱጋል መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋራ ግንኙነት ሲጀምር ያገሩ ካህናት በኢትዮጵያ ለማስተማር እንዲፈቀድላቸው ተነጋግሮ ነበርና በስምምነታቸው የካቶሊክ ካህናት በኢትዮጵያ ማስተማር ጀመሩ። የሚያስተምሩበትና የሚጽፉበት ቋንቋ አማርኛ ነበርና የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ደግሞ ሕዝቡ ካቶሊክ እንዳይሆንበት ግዕዝን ሳይተው ባማርኛ መተርጐምና መጻፍ ጀመረ። በዚያው ዘመን ለመጻሕፍት ትርጕምና ለስብከት የተጀመረው አማርኛ ገና ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ፣ አንዳንዱም ንግግር ግዕዝ ላልተማረ ሰው በፍጹም የማይሰማ ነበር። እንደዚኽው ሁሉ በዚያው ዘመን ሲጻፍ የነበረው የነገሥታት ታሪክ ግዕዙ አማርኛ ቅልቅል ነበር።

old-amharic
በ1760ዎቹ የተጻፈ የአማርኛው መሐልየ መሐልይ ዘሰሎሞን

ያም ሁሉ ሁኖ እንኳንስና ለውጭ አገር ሕዝብ የሚተርፍ፣ ካገራችን ውስጥ ከፍተኛ አሳብ የሚያሳድር በታረመ አማርኛ የተጻፈ መጽሐፍ ለማግኘት ችግር ነው። መጻሕፍቱ የፈጸሙት ጕዳይ፣ በሕዝቡ ላይ ከመጣበት ከሃይማኖት ተወዳዳሪ መከላከልና የባላገር ቋንቋ የነበረውን አማርኛን ጽሑፍ ሥራ ለማስያዝ መጀመራቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ለትሕትና ሲል ስሙን አያመለክትም ነበርና የመጻሕፍቱን ፍሬ ነገር መዘርዘር፣ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ማን እንደነበር መርምሮ የሕይወቱን ታሪክ ማመልከት ይቸግረናል።

(በክፍል ሁለት ይቀጥላል …)

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም

የግዕዝ ሊቃውንት እና አዲሱ ዘመን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 5)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል አራት የቀጠለ)

 

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትውልዳቸው ሸዋ ትምህርታቸው ጎንደር ነው። ዕድሜያቸው 60 ዓመት ይሆናል። በኢትዮጵያ መጻሕፍት ካላቸው ከሰፊው ዕውቀታቸው በላይ፣ ላገራችን መጻሕፍት ምሥጢርና ታሪክ አስፈላጊ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ዕብራይስጥ ጨምረውበታል። የሕዝቅኤልን ትንቢት ዕብራይስጡን ወደ አማርኛ ገልብጠው ባማርኛ የጨመሩበት መግለጫ፣ ከሁሉ በፊት ላገራችን ሊቃውንት ከግሪክ ተተርጕሞ በግዕዝ ተቀብለውት የሚኖሩትን የብሉያትን መጻሕፍት፣ ዋናውን አብነት ዕብራይስጡን እያዩ ማቃናት እንዳለባቸው አነቃቅተዋቸዋል። ዳግመኛ ትምህርቱም መጠነኛ ቢሆን አማርኛ ያወቀ ሁሉ ሊያስተውለውና ሊያጣጥመው በሚችል ንግግር በመግለጣቸው ተራውን ሕዝብ ሳይቀር ከሊቃውንቱ ዕውቀት እንዲካፈል አድርገውታል። እግረ መንገዳቸውንም ልዩ ለሆነው ከባድ ዕውቀት፣ ልዩ የሆነና ያጌጠ አማርኛ ፈጥረውለታል።

kidane-photo

እርሳቸው ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት ኢየሩሳሌም ሒደው ዕብራይስጥ የተማሩበት ዘመን የነበረውን ችግር ያስተዋለ ሰው ብቻ ድካማቸውን ሊመዝነውና ሞያቸው ትልቅ መሆኑን ሊረዳ ይችላል። ፍቅርና አንድነት በተሰበከበት አገር በኢየሩሳሌም ጠብና መለያየት ተዘርቶበት ነበር። ዛሬውንም ገና አላለፈበትም። ከዚያ የነበረው የኢትዮጵያ መነኮሳት ማኅበር፣ ከጸሎት በቀር፣ ትምህርት መቀጠል የማያስፈልግ ሥራ ሁኖ ሲታየው፣ እስራኤላዊ ደግሞ በዓለም ያለ ሕዝብ አሥር ቢማር እንደማያፈቅረው ተረድቶት ቋንቋውን ሊማርለት የመጣውን ክርስቲያን መርዳት፣ እባብን ከመቀለብ ይቆጥረው ነበር። ስለዚህም አለቃ ኪዳነ ወልድ ዕብራይስጥ የተማሩት በሁለት ፊት ሥቃያት እያዩ ነው። ይህ ሁሉ ድካማቸው በክርስቲያን ሊቃውንት ጭምር ስለ ብሉያት መጻሕፍትና ታሪክ ያመጡትን አዲስ መግለጫ ለመከታተል ቢቸግራቸው፣ አማርኛው ከተሰናዳው መግለጫቸውም በክርስቲያንነታቸው የጸኑት ሊቃውንት ከደረሱበት የታሪክና የትርጕም አዲስ አካሔድ ለመድረስ ቢያቅታቸው አይፈረድባቸውም።

kidane-hizqel

የኢትዮጵያን የጥንቱን ትምህርት ከሚያውቁት ሊቃውንት አማርኛንና ግዕዝን ለማጣራት፣ ያለቃ ኪዳነ ወልድን ያህል የሚደክም ብዙ አልተገኘም። አማርኛ ለግዕዝ ልጁ በመሆኑ፣ ከግዕዝ የተቀበላቸውን ቃላት ልክ እንደ ግዕዝ አድርጎ መያዝ አለበት የሚል አሳብ ስላለባቸው፣ ይህንኑ ውሳኔ ለመግለጥ የታተመና ያልታተመ ብዙ መጽሐፍ ጽፈዋል። አሳባቸውን ተቀብሎም ለማስተዋል የሚጣጣር በያገሩ ብዙ ደቀመዛሙርት አውጥተዋል። ሠላሳ ዓመት ያህል የደከሙበት ዋናው መጽሐፋቸው ግዕዙን ባማርኛ የሚተረጕም መዝገበ ቃላት ነው።

ጠላት አገራችንን በወረረበት ዘመን እርሳቸው ሲታሠሩ ሲጋዙ ያን ያህል የደከሙበት ሥራ የሚከውነው አጥቶ የብልና የምስጥ ምግብ ሁኖ መቆነጻጸሉ ጕዳቱ የራሳቸውና የመላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወሰን ሳያግደው ሰንደቅ ዓላም ሳይለየው፣ ወገን ለሆነው በዓለም ላለው የትምህርት ወዳጅ ለሆነው ሰው ሁሉ ነው። ከሰው ተለይተው፣ ፈቃድ አጥተው ሲኖሩ ሳለ ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ከችግር አስጥለዋቸው የነበሩ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ዛሬም ንጉሠ ነገሥታችን የኢትዮጵያን አልጋ መልሰው ሲይዙ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድን አስፈልገው የዕለት እንጀራቸውን በመዓርግ እንዲያገኙና ያቋረጡትን ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋልና ፈቃዱ ሁኖ የኢትዮጵያ ወጣቶች የግዕዝን ቋንቋ ከሥር እስከ መሠረቱ ለማወቅ ከገዛ አገራቸው ሊቅ በተጻፈው መዝገበ ቃላት ይመረምሩታል እያልን ተስፋ እናደርጋለን።kidane-dictionary

የግጥም ባሕል

በግጥም ወይም ቤት ሳይመታ፣ ቃሉ ያላጋደለ፣ የተመዛዘነ በሆነ ንግግር አሳብን መግለጥ፣ ሰው አንደበት ከፈታ ጀምሮ የነበረ ልማድ ነው። በጽሕፈት ያልገባው ያገራችን የጥንት ወግና ታሪክ፣ ብዙ ግጥም አለበት። ሌላ የቀድሞ ሕዝብ የቤተ መንግሥቱን ሕግ ሳይቀር ቤት እያስመታ ጽፎ፣ በተማሪ ቤት በዜማ እንዲማሩት አድርጓል። በኢትዮጵያ ማናቸውንም የግዕዝ መጽሐፍ ስንኳ በዜማ ማንበብ ልምድ ቢሆን፣ ሕግን በግጥም መጻፍ አልተለመደም። ነገር ግን ቤት የሚመታ የሕግ ዓይነት ምሳሌ አይጠፋም። “ይካስ የበደለ፣ ይሙት የገደለ”፣ “ያባት ዕዳ ለልጅ፣ ያፍንጫ እድፍ ለእጅ”፣ “አልሞት ባይ፣ ተጋዳይ”።

ይህንንም የሚመስል ባንድ ፊት ምሳሌ፣ እግረ መንገዱን ደግሞ ሕግ ሁኖ የሚጠቀስ፣ ቤት የሚመታ ብዙ ንግግር አለ። በቀድሞ ዘመን አንዳንድ ጊዜ ከሳሽና ተከሳሽ ተከራክረው ሲጨርሱ፣ አጭር ሁኖ ቤት የሚመታ ንግግር ጉዳያቸውን ለዳኛ ያቀርቡ ነበር። ከትችት ላይ ዛሬውንም ቢሆን በግጥም የሚተች አለ። የበገናና የመሰንቆ፣ ልዩ ልዩ ዝማሬ፣ ባላገሩ ለአምላክና ለድንግል ማርያም፣ ለመልአክና ለጻድቅ የሚያቀርበው ልመናና ምስጋና በግጥም ነው። ቀረርቶና ዘፈን፣ እንጕርጕሮና ልቅሶ ሁሉም በግጥም ነው።

ነገር ግን ልዩ ልዩ ሕዝብ ፊት አስቀድሞ ቤት እየመታ ወይም በሕግ በተወሰነ ሚዛን አሳቡን የሚገልጥበትን ጽሑፍ ሥራው ሲደራጅ፣ ባገራችን ጽሑፍ ሥራ ግጥም የኋሊት ቀርትዋል። ስለሆነም አሁን በቅርቡ ጊዜ ብዙዎች ሰዎች በግጥም መጻፍ ጀምረዋል። አብዛኛው ስላልታተመ ስለ አማርኛ ግጥም ብዙ የምናመለክተው የለንም።

ያሳተሙትና ያላሳተሙት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች በግጥም የሚገልጡት አሳብ አብዛኛውን ጊዜ ምክር ነው። የሰውን ኀዘንና ደስታ የሚገልጠው እጅግ በጥቂቱ ሁኖ፣ የወንድንና የሴትን ፍቅር የሚያነሳ በጭራሽ የለበትም። የጣልያኖች ወረራ፣ ስለ አገርና ስለ ንጉሠ ነገሥት ፍቅር፣ ዓመፀኝነት ስለሚሠራው ግፍ፣ ስለነፃነትም ናፍቆት በግጥም የሚያናግር አሳብ ቀስቅስዋል። የተጻፈው ገና ስላልተመረመረ፣ የሚያምረውን ከማያምረው ለመለየት ለጊዜው አልተቻለኝም።

ስለ አማርኛ የቅኔ ባሕርይ ግን ከዚህ በፊት እንዳመለከትነው፣ ብዙ “ስለምን” ወይም “አማርኛ” ይወዳል። አብዛኛውን ጊዜ አያሌውን መስመር ባንድ ፊደል ቤት ያስመታል። አንዱን መስመር በሁለት ሐረግ ከፍሎ፣ ላንዳንዱ ሐረግ ፮፣ ለሁለቱ ሐረግ (ላንዱ መስመር) ፲፪ ፊደል ይሰጣል። ፊደል ሲቆጥር አብዛኛውን ጊዜ እንደ ዕብራይስጡ ቅኔ ሳድሱን ከሌለ ይቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሳቡና በንግግሩ ስንኳ ቅኔ ወዳጅና ቅኔ ፈጣሪ ሁኖ ቢታይ፣ ባማርኛ እስከ ዛሬ ጽፈው ካሳተሙት ግጥም ገጣሚዎች፣ ትዕግሥት ሰጥትዋቸው፣ ሽሕ መቶ ሽሕ መሥመር የጻፉና ያሳተሙ ያሉ አይመስሉንም። በርከት አድርጎ የጻፈ ቢኖርባቸው ለፍርድ ይመች ነበር።

ወጣቱ ከበደ ሚካኤል

ይሁን እንጂ አጭርም ቢሆን፣ እኔ ለራሴ ሥራቸውን የማደንቅላቸውና የማመሰግንላቸው ብዙ ወጣቶች አሉ። ከነዚህም አንዱ ከበደ ሚካኤል ነው። ቅኔ፣ ምሳሌ፣ ተረት ከውጭ አገር ደራሲ (ከፈረንሳይ) በሚተረጕምበት ጊዜ አሳቡና ንግግሩ አማርኛ ሁኖ ከተረጐመበት ቋንቋ ጋር ሲያስተያዩት አንዳንድ ጊዜ ተወዳዳሪው፣ አንዳንድ ጊዜም አርሞ ያቃናው ሁኖ ይገኛል።

ምክንያቱን ከራሱ አፍልቆ የሚፈጥረው ግጥም ከልብ የወጣ ከልብ ይገባል እንደተባለው ሁሉ፣ ልብን የማይነካ የሚገኝበት ሁኖ አልታየኝም። አብዛኛውን ጊዜ ካገራችን ባለ ቅኔዎች ግዕዝን ወይም የውጭ አገርን ቋንቋ እጅ ያደረጉ ሲሆኑ ወደዚያው እየሳባቸው ንግግራቸውን ለማስተዋል እንቸገርበታለን። ወይም ደግሞ፣ ሌላ ባለ ግጥም ያወጣውን ንግግር፣ አማርኛው ካማረ ብለው ያለ ቦታው ሲጥሉት ቅር ያሰኛሉ። “ስለምን” ያልሁትን ንግግር አምጥተው አንባቢ በቶሎው እንዳያስተውለው ያደረጉ እንደሆን፣ ሰው ሊያስተውለው ያልቻለ ጥልቅ ጥበብ የተገለጠላቸው ይመስላቸዋል። ከበደ ሚካኤል፣ ሌሎች ካበጁት ወይም ከውጭ አገር ንግግር ሳይጨምር በራሱ አማርኛ፣ ሁሉም ሊያስተውለው የሚችል አገላለጥ በመምረጡ ለወደፊት ለሚነሱት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች አብነታቸው ለመሆን ተስፋ የሚያስደርግ ልጅ ነው።

kebede-berhane-hilinakebede-nibab

ማጠቃለያ

ለንግግራችን ፍጻሜ ስንሰጥም ደግመን የምናስታውሰው፣

 1. በአማርኛ መጻፍ ከጀመርን ስድስት መቶ ዓመት ስንኳ ቢሆን፣ በብዙው የተጻፈበት ዘመን ከ1600 ዓ.ም. በኋላ መሆኑን።
 2. ከ1600 ዓ.ም. ጀምሮ ባማርኛ የሚጻፈው አብዛኛው የሃይማኖት መጽሐፍ ሁኖ ከንግግሩና ከአሰካኩ ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ ብዙ አካሔድ እንደነበረበት፤ ይህንም የአጻጻፍና የንግግር አካሔድ ዛሬውን ሳይቀር አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደሚከተሉት።
 3. አማርኛን ራሱን አስችለው መጻፍ የጀመሩት ደራስያን በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን (1847-1860) መሆኑን ጭራሽ እየተጣራ የሔደበት ግን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን።
 4. አማርኛ ጽሑፍ ሥራውን በግጥም ጀምሮ፣ ይኸው የግጥም ሥራ ዛሬ የኋሊት መቅረቱን።
 5. የዛሬ ዘመን ደራስያን ከሚጽፉት አብዛኛው መጽሐፋቸው የታሪክና፣ የሃይማኖት፣ የልብ ወለድ ታሪክም መሆኑን፣ የሁሉን አሳብ ትምህርትን ሥራንና ልማድን እያሻሻሉ መሔድ ዋና መሆኑን።
 6. የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍጥረቱ የቅኔ መንፈስ ያደረበትና በግጥም አሳቡን እንደገለጠ መኖሩን፣ ሙግቱንና ትቹን ሳይቀር በግጥም ማምጣት ልማዱ መሆኑን በዚኸውም የተፈጥሮ ልማዱ ቤት እያስመታ የሚሔድ ደራሲ በብዙው መገኘቱን፣ ነገር ግን ባማርኛ ያወጣውን ግጥም ያሳተመ ደራሲ ጥቂት መሆኑን ነው።

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 4)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል ሶስት የቀጠለ)

 

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ትውልዳቸው ሸዋ የሞቱበት አገር (+1931) በባት ከተማ በእንግሊዝ አገር ነው። በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ትምህርት ፈጽመው በቤተ ክህነት ሲያገለግሉ ኑረው ሠላሳ ዓመት ያህል በቤተ መንግሥት ልዩ ልዩና ከፍ ያለ ሹመት ተቀብለው ከባድ የሆነ የኀላፊነት ሥራ የፈጸሙ ሰው ናቸው። የአሁኑ ማስታወሻ ስለ ደራሲነታቸው ብቻ የሚናገር በመሆኑ በሹመታቸው ስላስኬዱት ትላልቅ ሥራ ከዚህ ማንሣት የለብንም።

heruy-medal

ከጽሑፍ ሥራቸውም ዋና ሁነው የሚታዩን “ወዳጄ ልቤ”፣ “ጎሐ ጽባሕ” እና “ሀገረ ጃፓን” በመሆናቸው የቀሩት መጻሕፍቶቻቸው ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስንኳ በብዙው ቢጠቅሙት፣ አሳባቸውንና ደራሲነታቸውን በሦስቱ መጻሕፍት ማግኘት ስለ ተቻለ ስለነርሱ ብቻ ባጭሩ እናመለክታለን።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ በጻፉት ሁሉ ዋና አሳባቸው፤

 1. በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው ሁሉ በፈጣሪውና በመንግሥት ዘንድ አኳያ መሆኑን ነው። የውነት ነው። ሲፈጠር ብልህና ሞኝ ሁንዋል፤ በሥራ ዕውቀትና ዕድለኛ በመሆን ከሰው የተሠራ አስፈላጊ የሆነ የመዓርግ ከፍተኝነትና ዝቅተኝነት ይህንንም የመሰለ ብዙ ልዩነት አለ። ነገር ግን በምንፈርድለትና በምንፈርድበት ጊዜ መሠረት ልናደርገው የሚገባን ሁሉም ትክክል መሆኑን ነው።
 2. በዘርና በሃይማኖት የመጣውን ልዩነትም እርስ በርሳችን ተቻችለን ከሌለ መቍጠር ይገባናል።
 3. የክርስቲያን ሃይማኖት በዓለም ከታወቁት ሃይማኖቶች ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ኑሮ የሚስማማ ነው።
 4. ሰው በማናቸውም ሰዓት ሞት እንደሚመጣበት ማሰብ ይገባዋል።
 5. ሰው የልማድ ባርያ ሳይሆን በነፃነት ሕጉንና ሥርዓቱን እያሻሻለ መሔድ አለበት።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከጻፍዋቸው መጻሕፍት ከሁሉ ይልቅ ዕድለኛ ሁኖ ሕዝቡ አንብቦ የማይጠግበው “ወዳጄ ልቤ” ነው። እንዲህ ያለውን መጽሐፍ የሚጽፍ የእንግሊዙን ደራሲ የዮሐንስ ቡንያንን መጽሐፍ ያነበበ ሰው ብቻ መሆኑን የምንረዳው የዚሁኑ ደራሲ “የክርስቲያን መንገድ” የተባለውን መጽሐፉን ስናነብ ነው። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ግን ንድፉን ስንኳ ከእንግሊዙ ደራሲ ቢቀበሉ፣ የጽሑፋቸውን ሕንፃ መልክና ጠባይ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ያውም የሚያምር ኢትዮጵያዊ አድርገውታል።

heruy-wedaje

ባሳባቸው የፈጠሩት “ወዳጄ ልቤ” የተባለው ሰው የርሳቸው ራሳቸው ወይም ክርስቲያን ሁኖ የክርስቲያንን ሕግ ለመጠበቅ የሚታገል ሰው ምሳሌ ነው። ወዳጄ ልቤ ለብቻው ሁኖ የእግዚአብሔርን ህላዌና የሕዝበ አዳምን፣ በተለየም የነፍስን ሁኔታ በሚያስብበት ጊዜ፣ ወይም እግር ጥሎት ከልዩ ልዩ ሰዎች ጋር ተገናኝቶ ክፋታቸውንና በጎነታቸውን በሚገልጥበት ጊዜ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ በተለየም በክርስቲያን ላይ የሚመጣበትን መከራ ሲያስታውስ፣ ተስፋ ሊቆርጥ ሲቃጣና፣ በርትቶ ሲታገል፣ ከባልንጀሮቹ ጋርና ለብቻው መሰንቆውን ይዞ ሲያንጐራጕር፣ በሠርግ አስመስሎ ስለ ክርስቲያን ሃይማኖት አጀማመርና፣ ድል እየነሣ በሔደበት፣ በሚሔድበትም ዘመን ሁሉ ያለበትን መከራ ሲተርክ፣ ፍጹም ክርስቲያናዊ ነው።

ወዳጄ ልቤ፣ “ሰው በየሱስ ክርስቶስ ካመነ በኋላ ከኃጢአት ላለመውደቅ ምን ቢሠራ ይሻላልን?” ብሎ የሚጠይቅ ወይም የዚህን አሳብ የሚያሳድር ሁኖ ይታያል። አንባቢው፣ ቁልፉን ወይንም መልሱን አገኘሁ! መጽሐፉ ሊነግረኝ ነው! ብሎ ሲጓጓ፣ “ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ” ብሎ ያሰናብተዋል።

heruy-goh

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስለ ሃይማኖትና ስለ ፖሊቲካ ስለ ልዩ ልዩ ጉዳይም ያሰቡትን ሁሉ ካንድ ላይ ሰብስበው ጽፈው ያወጡትን መጽሐፍ “ጎሐ ጽባሕ” ብለው ሰይመውታል። ጎሐ ጽባሕ ስለ ሃይማኖት የሚገልጠው አሳብ ንግግሩም ልዩ ቢሆን ከ”ወዳጄ ልቤ” አይለይም። ሕግንና ልማድን ማሻሻል ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ሥራዬ ብለው የቆሙበት ዋና አሳብ በመሆኑ፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ቍጥር፣ ስለ ምንኵስናና ስለ ጋብቻ ሥርዓት፣ ስለ ጸሎትና ስለ ንስሐ ከጻፉት ክፍል፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ሥርዓት እየተሻሻለ የሚሔድበትን መንገድ መሠረት ባለው አካሔድ አስረድተዋል። ከቤተ ክህነት፣ ቤተ መንግሥትን መምራት ይገባኛል እያለ፣ በመንፈሳዊና በሥጋዊ ጕዳይ ሁሉ የበላይ አስተዳዳሪ ልሁን የሚል እንደማይጠፋ ስለ ተረዱት፣ የሁለቱንም ሥልጣን ወስነው ሁሉም በየክፍሉ፣ በየሥራው አላፊነት እንዳለበት፣ የሁሉ በላይ ግን መንግሥት መሆኑን አደላድለው ወስነዋል። ወገን ለሌለው፣ በዘር በሃይማኖት ለተለየ ሰውና ለእንስሳ ርኅራኄ እንዲገባ በብዙው ሰብከዋል። ለዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያዊ አንዳንዱ ስንኳ የዚህ ዓይነት ምክር ባያስፈልገው፣ ካገራችን ሕዝብ ላብዛኛው አዲስ ነገር ሁኖ ታይቶት ከአሳባቸው አንዳንዱ ለመቀበል የሚያስቸግር ሁኖ ሳይታየው የማይቀር ነው፣ መጽሐፉ ለእንዲህ ያለው ክፍል ብርቱ አሳብ የሚያሳድርበትና ጥቅም ያለው ክርክር የሚያነሣ ነው።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ገና ወደ ጃፓን አገር የመንግሥት መልእክተኛ ሁነው ሳይሔዱና ከዚያ በኋላ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ስላይዋቸው አገሮች ሁነታ የጻፉዋቸው መጻሕፍት አሉ። በተስተካከለ አማርኛና ያላዩትን አገርና ሕዝብ ካዩት በሚያስቆጥር አነጋገር የመንገዳቸውን አካኋን የገለበጡበት መጽሐፍ ግን “ማኅደረ ብርሃን” (ሀገረ ጃፓን) ብለው የሰየሙት ነው።

heruy-japan

መጽሐፉ ከማያስፈልግና ከሚያታክት ዝርዝር ሳይገባ በወሬ የምናውቀው የጃፓን አገርና ሕዝቡ፣ ሃይማኖቱ፣ ያገሩ ልማድ፣ ሥልጣኔውና አስተዳደሩ ምን እንደሆነ ነግሮ የሚያጠግብ ነው። ደራሲው የተላኩበት ሥራ ከሕዝብና ከትላልቅ ሰው፣ ከንጉሠ ነገሥቱና ከንግሥቲቱ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የሆቴሉንና የባላገሩን፣ የሚኒስትሮችንና የቤተ መንግሥቱን እልፍኝ ታዳራሽ ወገኑንና ሥርዓቱን አይተዋል። ያዩትንም ላላየነው፣ ካየነው እንድንቆጥረው አድርገው ጽፈዋል። ከዚህም ሁሉ ጋራ ጃፓን ሕዝብ መሆን ከጀመረበት ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታሪኩን እንድናውቀው ከሌላ ባለ ታሪክ እየጠቀሱ ባጭሩ ተርከውልናል። የባሕሩንና የመሬቱን፣ የጫካውንና ያትክልቱን ሁኔታ የሚነግረው ክፍል፣ ደኅና ሥዕል ሳይ፣ በሚስማማ ቀለም ነድፎ ያቀረበው ሰሌዳ ይመስላል። ክርስቲያኑ ኅሩይ፣ ክርስቲያን ያይደሉትን ወገኖች የአምልኮና ባህል የሚያዩት እጅግ ከፍ ባለ አስተያየት ነው። የጃፓን አምልኮም እንደ ሌላው አምልኮ፣ የእግዚአብሔርን ምስጢር ለማግኘት የሚጣጣር ሁኖ ስለታያቸው፣ ያገራችን ሕዝብ ደግሞ ባይቀበለውም በሰፊው እንዲመለከተው አድርገው ገልጠውታል።

ከዚያ በፊት ልዩ ልዩ መጻሕፍት በመጻፍ ብዙ ትግል ያየው የብላቴን ጌታ አእምሮና አማርኛ፣ “ሀገረ ጃፓን”ን በጻፈበት ጊዜ፣ ደርጅቶ ከፋ ካለ ደረጃ የደረሰ ሁኖ ይታያል።

አማርኛ ማሠሪያ አንቀጹን አርቆ፤ ከማህሉ ልዩ ልዩ አሳብ ጣልቃ ማግባት የተፈጥሮ ጠባዩ ነው ብለናል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ አብዛኛውን ጊዜ ይህን ሳይከተሉ ንግግሩን ባጭር ባጭሩ ማሠር ልዩ ባሕርያቸው ነው። ከአማርኛ መርማሪዎች አንዳንድ ሰው ብላቴን ጌታ ኅሩይ አማርኛን በውጭ አገር (በኤውሮጳ) ንግግር ዓይነት እንጂ በተፈጥሮ ጠባዩ አያስኬዱትም ብሎ ጽፎባቸዋል። ነገሩም እውነት ይሆናል፤ ግን ደግሞ ደራሲ መከተልና ማሻሻል የሚገባው የሚጽፍበትን ቋንቋ ጠባይ ነው ስለ ተባለ፣ ይኸው ደራሲ የሚጽፈው፣ የንግግር ጣዕም ያለውና በፍጥነት የሚያስተውሉት ከሆነ፣ ከተራው ሕዝብ ተለይቶ መዓርግ ያለው ደራሲ ነው መባልን አያግደውም።

heruy-sikwarብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሕፃናትና አእምሮ ለዋጭ የሚሆኑ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ትተውልናል። እንዲያውም ከመጻሕፍት ዓይነት በጽሕፈት ለመግለጥ ያልሞከሩት ጥቂት ነው ለማለት ይቻላል። በሥራ የተፈተነው የተፈጥሮ ባሕርያቸው ትዕግሥተኛ ሲሆን፣ ጽሕፈት ሲልዋቸው ፍጥነታቸው የመኪና ያህል ስለ ነበረ፣ ካማርኛቸው በቀር በወጣቱ ኢትዮጵያዊ ላንዳንዱ የጻፉት ታሪክና ልብ ወለድ ታሪክ፣ ሌላውም ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ ውዝፍ ሁኖ ይታየዋል።

ምክንያቱም በቤተ መንግሥት የነበረባቸው ከባድ ሥራ፣ ለሚጽፉት መጽሐፍ የተገባውን ምርመራ ለማጥለቅና ለማስፋፋት ፋታ አልሰጣቸው ስላለና ላገራቸው ሕዝብ በነበረባቸው ፍቅር፣ እርሳቸው ካወቁት ከብዙው ጥቂቱን ሳያስታውቁት ቢቀሩ “ዘደፈነ ወርቀ እግዚኡ” እንዳይሆኑ ሲሉ ይሆናል።

የሒሳብና የፍልስፍና የሕክምና የሥነ ፍጥረት ይህንንም የመሰለው ልዩ ልዩ ዕውቀት የተጻፈበትን ጽሑፍ ሥራ ቋንቋው የተጣራ ቢሆን፣ ያንኑ ዕውቀት የተማረ ሰው ካልሆነ በቀር፣ በሌላ ዕውቀትም ሊቅ የሆነ ሰው አያስተውለውም። የድርሰት ስጦታቸው አንዳንድ ሰዎች ግን፣ እንኳንስና የተማረ ሰው ተራው ሕዝብ ሳይቀር በሚያስተውለው ንግግር ልዩ ዕውቀታቸውን ለመጻፍ ተችልዋቸዋል። ቃለ እግዚአብሔር የሚያስተምሩና የሃይማኖትን መጻሕፍት የሚተረጕሙ፣ ስለ ሃይማኖትም የሚጽፉት ሊቃውንት፣ ምሥጢሩ ግድ እያላቸው ንግግራቸው ወይም አጻጻፋቸው አማርኛ አወቅሁ ለሚል ሁሉ የማይደፈር ሁኖ ይኖራል። ደግሞም ትምህርት ሲባል፣ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ያገር፣ የመንግሥት ወሰን የማያግደው አገሩና መንግሥቱም ቢለያዩ ሰንደቅ ዓላማው፣ ወይም ወገኑ አንድ የሆነ ነው። ለጊዜው ያገራችን ሊቃውንት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ያለው ትምህርትና ዕውቀት ባዕድ ሁኖባቸዋል።

 

(በክፍል አምስት ይቀጥላል …)

ማቲክ ኬዎርኮፍ – አርመኑ ነጋዴ

 የፒያሳው ኬዎርኮፍ ሕንጻ

(ክፍል 3)

በሕይወት ከተማ

(… ከክፍል ሁለት የቀጠለ)

አራዳ የመዲናችን ንግድ ማዕከል በነበረችበት ዘመን ትላልቆቹን ሱቆች የሚያስተዳድሩት የውጭ ዜጎች (ግሪኮች፣ አረቦች፣ አርመኖችና ህንዶች) ነበሩ። ከነዚህም የናጠጡ ነጋዴዎች መካከል አርመናዊው Matig Kevorkoff (እንዳገሬው አጠራር ማቲክ ኬዎርኮፍ) አንዱ ነበር።

ጥቂት ስለ ማቲክ ኬዎርኮፍ

 

ኬዎርኮፍ በ1859 ዓም ኢስታምቡል ውስጥ ተወለደ። በቆንስጣንጢኖስም (Constantinople) በአርመን ትምህርት ቤት ተምሮ ወደ ግብጽ ተጓዘ። ለአጭር ጊዜ ግብጽ ውስጥ ቆይቶ በ1888 (በአድዋ ድል ወቅት) ወደ ጅቡቲ አመራ። በጅቡቲም ቆይታው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ እና የፈረንሳይም ዜጋ ለመሆን በቃ።

16463652_1413657838645249_4225349741114144258_o
ማቲክ ኬዎርኮፍ  (ምንጭ – “L’Empire D’Ethiopie” by Adrien Zervos)

ኬዎርኮፍም ከአጎቱ ጋር በመሆን ከጅቡቲ ትንባሆ ወደ ፈረሳይ ሐገር በመላክ ትልቅ ንግድ ጀመሩ። ቀስ እያለም ንግዱን ወደ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ እና አዲስ አበባ አስፋፋ። ጎራዴ፣ ሰይፍ፣ ጩቤ እና የመሳሰሉትን በ1890ዎቹ በሐረር ያመርት እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

picture 19
የኬዎርኮፍ ጎራዴ (የኢንተርኔት ምንጮች)

ጥይትና መሳሪያም በማስመጣት በአዲስ አበባ ሱቁ ይሸጥ እንደነበር የቀድሞ ደብዳቤዎች ያሳያሉ፤

“ይድረስ ከነጋድራስ ይገዙ – ማቲክ ጊዎርኮፍ መቶ ሳጥን የፉዚግራ ጥይት ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ አምቷልና እንዳይከለከል ይሁን።”

[ግንቦት 4 ቀን 1899 ዓ.ም. አዲስ አበባ]

በጣልያን ወራራ ዋዜማ ግንቦት 29, 1927 ዓ.ም. የወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣም ይህንንኑ ይጠቁማል።

guns
የመሳርያ ማስታወቂያ  (ብርንሃና ሰላም ጋዜጣ፣ ግንቦት 29 1927)

የትንባሆ ንግድ በጣም አዋጪ ሆኖም ስላገኘው በአዲስ አበባ የትንባሆ ብቸኛ አስመጪ ሞኖፖል ይዞ ንግዱን በሰፊው ተያያዘው። በመጋቢት 1921 ዓ.ም. አእምሮ ጋዜጣ ስለ አገሪቱ የትንባሆ ሞኖፕል ለተጻፈበት ትችት መልስ ሲሰጥም እዚህ ይነበባል።

ከዚህም በተጨማሪ ጥጥ፣ ሐር፣ መጠጥ፣ ዘይት፣ ሳሙና፣ የህንጻ መሳሪያዎች፣ ብትን ጨርቅ፣ ስጋጃ፣ ሰዓት እና የመሳሰሉትን አስመጭና ላኪ ሆኖ ይሰራ ነበር።

picture 26
ማቲክ ኬዎርኮፍ በሱቁ ውስጥ (ምንጭ – Fasil & Gerald – Plate 504)

 

 

omega 2.JPG
የኬዎርኮፍ ሰዓት ማስታወቂያ (ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ፤ መጋቢት 29፣ 1919)
cognac
የኮኛክ ማስታወቂያ (ብርንሃና ሰላም ጋዜጣ፤ ሐምሌ 21፣ 1919)

እንዲሁም ኬዎርኮፍ የኮኛክና የተለያዩ መጠጦች ዋነኛ አስመጪ እንደነበር ምንጮች ያሳያሉ።

“መገን ያራዳ ልጅ ጠመንጃም የላቸው፤

በየደረሱበት ብርጭቆ ግምባቸው።

… ውስኪና ኮኛኩ ሲረጭ እንደውሃ፤

እንዴት ነሽ አራዳ የውቤ በረሃ።”

ለዚህ ሁሉ የንግድ ሥራው ይሆን ዘንድ ነበር በአራዳ የሚገኘውን ኬዎርኮፍ ህንጻ ያሰራው። ይህም የኬዎርኮፍ ሕንጻ የትምባሆ ሞኖፖል (“Tobacco Regie”) ዋና ቢሮ ሆኖ አገልግሏል። (ሕንጻው በአሁኑ ጊዜ “ሮያል ኮሌጅ”፣ “አቢሲኒያ ባንክ” ፣ “ካስቴሊ ሬስቶራንት” እና ሁለት ቡቲኮችን በመያዝ እያገለገለ ነው።)

ኬዎርኮፍ ሕንጻ

የኬዎርኮፍ ህንጻ ከመሰራቱ በፊት ኬዎርኮፍ አራዳ ውስጥ በሁለት ሌሎች ሱቆች ውስጥ ንግዱን ያካሂድ እንደነበር ምንጮች ያሳያሉ። ከደጎል አደባባይ ፊት ለፊት ከአያሌው ሙዚቃ ቤት በስተቀኝ በነበረ (አሁን የፈረሰ) ጥንታዊ ህንጻ ውስጥ ኬዎርኮፍ ሱቅ እንደነበረው ይታያል።

cp-michel-29-recto-2
የቀድሞ የኬዎርኮፍ ሱቅ  (ከፖስትካርድ የተገኘ)

ከዚህም በተጨማሪ እስከ 1920ቹ የፖስታ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ህንጻ የነበረው (የአሁኑ “ሲኒማ ኢትዮጵያ” እና “ትራያኖን ካፌ”) በ1900ዎቹ ዓ.ም. መጀመሪያ የኮዎርኮፍ ሱቅ እንደነበረ ይታያል።

picture 24
የቀድሞ የኬዎርኮፍ ሱቅ (ከፖስትካርድ የተገኘ)

ኬዎርኮፍ ከዚህም ሌላ የሚታወቀው በፈረንሳይ ሌጌሲዎን ውስጥ የዲፕሎማሲና የማስተርጎም ስራዎችን በመሥራት ነበር። ከአንደኛው አለም ጦርነት በኋላም የትውልድ ሃገሩ አርሜንያ ስትመሰረት ብዙ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። በ1911 ዓ.ም. ከጓደኞቹ ጋር በመሆን 1000 የእንግሊዝ ባውንድ አዋጥተው ለአዲሲቷ አርሜንያ አውሮፕላን አበርክተው ነበር። በ1911 ዓ.ም. ደግሞ ለአርሜኒያ በኢትዮጵያ ተወካይ (እንደ አምባሳደር) ሆኖ ተመርጦ ነበር። ኬዎርኮፍ የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ መንግሥቶች የክብር ኒሻን ተሸላሚ እንደነበርም የወቅቱ ጋዜጦች ዘግበዋል።

በ1919 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ውስጥ አርመን ኮሚኒቲ ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል። ቀደም ብሎም በ1915 ዓ.ም. በአርመን ፖለቲካ ልዩነት የተነሳ ሶስት ቦታ ተከፋፍሎ የነበረውን የአርመን ትምህርት ቤቶች በማዋሃድ አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት (National Armenian Kevorkoff School) ብሎ ሰይሞ አቋቁሞት ነበር። እስካሁንም ይህ ትምህርት ቤት በአራት ኪሎ አርመን ሰፈር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ባንክ (Bank of Abyssinia) ቦርድ አባል እና የሎተሪ ኮሚሽን አማካሪ ሆኖ አገልግሏል።

በጣልያን ወረራ ዋዜማ ኬዎርኮፍና ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጋ ነጋዴዎች በአንድነት ግማሽ ሚሊዮን ብር አዋጥተው ለኢትዮጵያ የጦርነት ወጪ ድጋፍ ይሆን ዘንድ ለቀዳማዊ ኀይለሥላሴ አበርክተው ነበር። ይህንንም ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ በታህሳስ 2 1928 ዓ.ም. እትሙ ዘግቦታል።

በ1928 ዓ.ም. ጣልያን አዲስ አበባ በገባ ጊዜ በፈረንሳዊነቱ ምክንያት ንብረቱ በሙሉ “የጠላት ንብረት” ተብሎ እንደተወረሰበት ይነገራል። በዚህም የተነሳ ወደ ፈረንሳይ ተሰዶ፣ በማርሴይ ውስጥ እንደሞተ ይነገራል።

ታዲያ እሱ ቢያልፍም፣ አሻራውን በአዲስ አበባችን ኪነ ሕንጻ ላይ ትቶልን አልፏል።

.

የጽሑፍ ምንጮች

 1. “The City and Its Architectural Heritage Addis Ababa 1886-1941” by Fasil Giorghis and Denis Gerard
 2. “Old Tracks in the New Flower – A Historical Guide to Addis Ababa” by Milena Batistoni and Gian paolo Chiari
 3. “L’Empire D’Ethiopie : le Miroir de l’ethiopie moderne 1906-1935”  by Adrien Zervos
 4. “ይምጡ በዝና፤ አዲስ አበባ” በያሬድ ገብረ ሚካኤል (1958 ዓ.ም)
 5. “Urban Africa: Changing Contours of Survival in the City”  by Abdou Maliq Simone & Abdelghani Abouhani
 6. “Out of Africa and into America, The Odyssey of Italians in East Africa” by Enzo Centofanti
 7. “Moderns Abroad: Architecture, Cities and Italian Imperialism” by Mia Fuller
 8. “La fanfare du Négus”  by Boris Adjemian
 9. “The Dramatic History of Addis Ababa  The Capital’s Armenians” by Richard Pankhurst
 10. “ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ” – ግንቦት 29 1927፣ መጋቢት 29 1919፣ ሐምሌ 21 1919 እትሞች
 11. “አእምሮ ጋዜጣ” – መጋቢት 14፣ 1921 እትም
 12. “አጤ ምኒልክ በሐገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች” በጳውሎስ ኞኞ 2003 ዓ.ም.

የኢንተርኔት ምንጮች

 1. http://armenianweekly.com/2015/05/06/remembering-the-armenians-of-ethiopia/
 2. http://www.failedarchitecture.com/le-corbusiers-visions-for-fascist-addis-ababa/
 3. http://www.africantrain.org
 4. https://gasparesciortino.wordpress.com/
 5. http://senato.archivioluce.it/senato-luce/home.html
 6. http://www.samilitaria.com/SAM/

የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ደራሲዎች

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 3)

በተአምራት አማኑኤል

[1936 ዓ.ም]

(… ከክፍል ሁለት የቀጠለ)

የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ደራሲዎች

፩ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ የሱስ

አለቃ ታየ ሲጽፉና ሲያስተምሩ በነበሩበት ጊዜ፣ ፊት ኤውሮጳ ኋላም ኢትዮጵያ ሁነው ላማርኛ አጻጻፍና ንግግር ብዙ ትጋት ያሳዩ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ የሱስ ናቸው። በወጣትነታቸው ለትምህርት ወደ ኤውሮጳ በመሔዳቸው፣ በነገር አስተያየትም መልክ ባለው ንግግር አሳብን በጽሕፈት በመግለጥ ልዩ ስጦታ ያላቸው ደራሲ ናቸው። የሕይወታቸው ታሪክ ግን እጅግ የሚያሳዝን ነው።

የዛሬ 50 ዓመት አቅራብያ ዕድለኛ ሁነው ከጃንሆይ ካጤ ምኒልክ ተመርጠው ለትምህርት ወደ ኤውሮጳ ተላኩ። የጣልያን የጦር አለቃ ባራቲዬሪ (1888 ዓ.ም) መልሶ ወደ ሮማ እስኪልካቸው ድረስ፣ ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ተሰልፈው ዓዲግራት ድረስ መጡ። ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሳትረሳ፣ ይቅርታ አድርጋ፣ በልጅ ኢያሱ አልጋ ወራሽነት ጊዜ ለትልቅ ሥራ አጨቻቸው።

ለዚህ ወረታ ወጣቱን የኢትዮጵያን አልጋ ወራሽ ልጅ ኢያሱን በሚያምር ንግግር በማሞገስ ደስታቸውን ገለጡ። በእውነትም ልጅ ኢያሱ ባልሆኑ ካጤ ምኒልክ ጋራ የሠሩት መሳፍንትና መኳንንት ሁሉ ተቀይመዋቸው ነበር። አሳባቸውም የነበረ በቤተ መንግሥት ሥራ ለማስያዝ ይቅርና የኢትዮጵያን መሬት እንዳይረግጡ ለማድረግ ነበር። የኢትዮጵያ ባላባቶች የልጅ ኢያሱ ሥራ አጀማመር ብዙ የሚያሠጋ ሁኖ ታይትዋቸው ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ባስገደድዋቸው ጊዜ፣ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከዚያ ሁሉ ሰው አብልጠው ለኢትዮጵያ የተቈረቈሩ መሆናቸውን ለማስረዳት፣ የሚያምረውን ግጥማቸውን የልጅ ኢያሱ መስደቢያ በማድረጋቸው አበላሹት።

እንኳን ይህን፣ ከጠላት ጋር አገራቸውን ሊወጉ የተሰለፉትን በደል የቤተ መንግሥት አስተዳደሮች ትተውላቸው ነበር። አሁንም ንግሥት ዘውዲቱና ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ ሁነው የመንግሥቱን ሥራ ሲያካሒዱበት በነበረ ጊዜ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ተቀበሉ። ከቶውንም በሚኒስትርነት ሥራ ወደ ሮም ተላኩ። ጠላት አገራችንን ሲያጠፋት፣ አሁንም ተመልሰው ለጣልያን ዋና ሠራተኛ ሆኑለት። አገርን ለያዘ ጠላት ሳያስፈልግ ማገልገል እንኳ ከመነቀፍ ቢያደርስ፣ ይህ አልበቃ ብሎ ለጠላት ታማኝነታቸውን ለመግለጥ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ጀምረው እስከ ተራው አርበኛ ድረስ የማይጠጋውና ያልሆነ ቃል በመጻፍ ብዕራቸውን አበላሹ።

ተራ ጸሐፊ ቢሆኑ የሚያሳዝነውን የሕይወታቸውን ታሪክ ሳላነሣው በቀረሁ። ነገር ግን ፕሮፌሰር አፈወርቅ እኛ ላለንበት ትውልድ ዋና ደራሲው ናቸው።

afework-grammarafework-grammar-2

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ባማርኛ ከጻፍዋቸው መጻሕፍት፣ “የአጤ ምኒልክ ታሪክ” እና “ልብ ወለድ ታሪክ” ዋና ሁነው ይታዩናል። የነርሱን አኳኋን ከማስታወቃችን በፊት የአማርኛ ቋንቋ ሕጉንና ሕዝቡ የሚወደውን የንግግር ወይም ያጻጻፍ ዓይነት እናመልክት። ከሕጉም ርቀው አዲስ አካሔድ የሰጡን ደራስያንና የተለምዶውን ንግግርና አጻጻፍ ሳይለቁ ጣዕም ያለበት ለማድረግ የቻሉትን ካልቻሉት ለመለየት ይረዳናል።

የአማርኛ ቋንቋ ከብዙው ሕገጋቱ አንዱ፣ ማሰርያ አንቀጽን ከንግግር መጨረሻ ማግባት ነው። ከጽሕፈት ላይ ባንድ ማሰርያ አንቀጽ ውስጥ ባሉት ቃላት ማኽል ጣልቃ እያገባ ልዩ ልዩ አሳብና ንግግር በሚጨምርበት ጊዜ፣ ዋናውንና ጣልቃ የገባውን ከውኖ ለማስተዋል እንዲመች ሊያደርጉ የቻሉ ስጦታ ያላቸው ደራስያን ብቻ ናቸው። ደራሲው ሙሉውን ንግግር ባማርኛ ባሕርይ በሚያስኬድበት ጊዜ ደግሞ ሰነፍ አንባቢ እንዳይታክተው ለማድረግ ያሰበበት እንደሆነ፣ ንግግሩን ባጭር ባጭሩ በማሰሩ ላንባቢ መመቸቱ እርግጥ ነው።

ቢሆንም ደራሲ በፊተኛው (በረጅሙ) አካሔድ ሲጽፍ አንባቢው በውጥን ጭርስ አካሔድ አስሮ ለንግግሩ ደራሲው ያላሰበውን አሳብ ከመስጠት የሚደርስበት ጊዜ አለ። ደራሲው በሁለተኛው አካሔድ (ባጭሩ) ሲጽፍ አንባቢው አሁን ካመለከትነው ስሕተት አይደርስም። ግን ንግግሩን ባንድ ማሰሪያ አንቀጽ ሊጠቀልል ሲሽል ደራሲው እያቋረጠ በመናገር አንደበቱን ያልረታ ሕፃን ሊመስል ነው። ንግግሩንም በመጠኑ ካማርኛ ባሕርይ የራቀ ሊያደርገው ነው። ዋና ደራሲ የምንለው፣ በረጅሙም ሆነ ባጭሩ አካሔድ ጽፎ፣ ንግግሩ ግልጽ እና ጣዕም ያለው ሲሆን ነው።

afework-guide
የአፈወርቅ ገብረየሱስ “Guide de Voyage”

በኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ሲበዛም ሲያንስም በልዩ ልዩ ሕዝብ (ይልቁንም በምሥራቃውያን) የተለመደ አካሔድ በሁለት፣ በሦስት ፍች የሚተረጎም ቃል እየፈለጉ ከንግግር ማግባት ነው። እንዲህ ያለው አካሔድ “አማርኛ” ወይም “ስለምን” ይባላል። ይህም በኢትዮጵያ እጅግ የተወደደና የተለመደ ንግግር ነው። እንዲህ ያለውን ንግግር የሚያመጣንም ሰው ሁሉ የንግግር ዕውቀት ያለው ሰው በመሆኑ የሚከራከርበት አይገኝም።

ሁለተኛ፣ በአሳብ ከልብ ፈጥሮ ደጉንና ክፉውን በምሳሌ በሚገልጽበት ጊዜ፣ ክፉውንና ደጉን የሚገልጡበትን ሰዎች አንባቢው በግብራቸው ባሕርያቸውን እንኳ ቢለይ፣ ደራሲው በ”ምሳሌ ስም” በአሳቡ የፈጠራቸውን ሰዎች “አቶ ክፉ ሰው”፣ “አቶ ደግ ሰው”፣ “ወይዘሮ ዓለሚቱ” ይህንንም በመሰለ ስም ይሰይማቸዋል። እንዲህ ያለው አካሔድ አብዛኛውን ጊዜ ችክ ይላል። ስለሆነም በደራሲዎችና በሕዝቡ ተለምዷል፤ ተወዷልም።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከዚህ በላይ “ስለምን” እና “ምሳሌ ስም” ያልነውን አካሔድ በብዙው አይከተሉትም። በተከተሉበት ጊዜም፣ አንባቢው ሳይሰለች አሳባቸውን እንዲያስተውል አድርገዋል። ሙሉው ንግግራቸው ያማርኛን ባሕርይ እየተከተለ በረዘመበት ጊዜም ቢሆን፣ ግልጥና ያማረበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ብቻ ቅጽል ሲያበዙ ነገሩ ጉት ይሆንባቸዋል። ፕሮፌሰር አፈወርቅ በደራሲነታቸው ሙቀት ያለበት ንግግር ማምጣት ዋና ባሕርያቸው ነው። ሙቀቱም የሚገባ ወይም ተሸጋጋሪ በመሆኑ፣ አንባቢው አሳባቸውንም በማይቀበልበት ጊዜ መሞቁ አይቀርም። በጽሑፍ ሥራቸው የሚያነሡት ሰው ወይም እንስሳ፣ ጫካ ወይም በረኻ ሁሉም ሕይወት ያለበት ሁኖ ይታያል።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ “የአጤ ምኒልክ ታሪክ” እና አንድ ልብ ወለድ ታሪክ ጽፈዋል። የቀሩት በጣልያንና በፈረንሳይ ቋንቋ የጻፏቸው መጻሕፍት የአማርኛን ሰዋስውና የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያስታውቁ ናቸው።

afework-menelik

ፕሮፌሰር አፈወርቅ የአጤ ምኒልክን ታሪክ ሲጽፉ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ከደረሰባቸውና ከሠሩት ዝርዝር ሳይገቡ ዋና ዋናውን ብቻ አመልክተዋል። ጥቂት ዝርዝር ያለበት፣ ስለ አጤ ምኒልክና የኢጣልያ መንግሥት መልእክተኞች የሚናገረው ክፍል ነው። የአጤ ምኒልክን ታሪክ ባጭሩ ካመለከቱ በኋላ የጣልያን መንግሥት መልእክተኞች ፕሮፌሰር አፈወርቅን እንዲረዷቸው በገንዘብ ሳይቀር ሊያባብልዋቸው እንደሞከሩ፣ እርሳቸው ግን ሳይታለሉላቸው በመቅረታቸው የንጉሣቸውን ፖለቲካ እንደደገፉ ለማስረዳት ይጣጣራሉ። በንግግራቸው ለምኒልከና ለሸዋ ሲሆን፣ ቁልምጫውንና ቃለ አጋኖውን ማብዛታቸው፣ ለሌላው ወረዳ ባላባትና ሕዝብ ሲሆን፣ ማዋረዳቸውና መሳቂያ ለማድረግ መታገላቸው፣ ለባለ ታሪክ የተገባውን እውነተኛ ሚዛን የያዙ በመሆን ፈንታ፣ ከዳተኛ ካለቻቸው አገራቸው ጋር ለመቃረብና የመንግሥቱን ሥራ የያዙትን ደስ ለማሰኘት የተነሡ ያስመስላቸዋል። ግን ደግሞ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከባለ ታሪክ ልዩ ሥራ አንዳንዱን እንዳልዘነጉትና ለታሪክ ንግግር አዲስ መንገድ እንደ ጠረጉለት አጭሩ የምኒልክ ታሪክ እንደሚያስረዳ ማስታወቅ ይገባናል።

afework-tobya

“ልብ ወለድ ታሪክ” ለኢትዮጵያ የፈጠራ መጀመሪያ መጽሐፍዋ ነው። ከዚህ በፊት እንዳመለከትሁት ያገራችን ደራሲ አሳቡን በጽሕፈት ለመግለጥ ባሰበበት ጊዜ ባሳቡ የሚፈጥራቸው ሰዎች የግብራቸውን ስም የተጸውዖ ስም አድርጎ “አቶ መልካም ሰው”፣ “አቶ ክፉ ሰው” የሚሉትን አካሔድ ብቻ ይከታተል ነበር። የዛሬው ሰው የፕሮፌሰር አፈወርቅንና የኤውሮጳን መጻሕፍት በማንበቡ ልብ ወለድ ታሪክ ለመጻፍ ይጣጣራልና በር ከፋቹ ፕሮፌሰር አፈወርቅ በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋል።

የፕሮፌሰር አፈወርቅ ልብ ወለድ ታሪክ የሚነግረን የሁለት ወጣቶችን ፍቅር ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁነው፣ ሃይማኖታቸው የወንድየው እስላም የሴቲቱ ክርስቲያን ነው። ከሁለቱ በፍቅር ድል ሁኖ የወዳጁን ሃይማኖት የተቀበለ ወንድየው ነው። መጽሐፉ የፍቅር ኃይል ብርቱ መሆኑንና የንጹሕ ፍቅር አካሔድ እንዴት መሆን እንደሚገባው ይተርካል። እግረ መንገዱን ደግሞ፣ የዛሬ ሰባት ወይም ስምንት መቶ ዓመት በኢትዮጵያ ሲደረግ ከነበረው ሥራ ከብዙው ጥቂቱን ያመለክተናል።

ደራሲው የጽሕፈት አገላለጣቸው ደግ ሲሆን፣ ምክንያት ለመፍጠር ብዙ መንገድ አልተገለጠላቸውም። ባሳባቸው የፈጠሯቸው ሰዎች ለሚፈጽሙት ሁለት ሦስት ልዩ ልዩ ሥራ አንድ ምክንያት ሰጥተው፣ ያንኑ አንዱን ምክንያት ሳይለውጡ፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ደጋግመውታል። ይህንና ሌላውን ያደራረግ ብልሐት (የቴክኒክ ጣጣ) የዋናው ሥራቸው ንድፍ ተስተካክሎ በመሔዱ አንባቢው እንደሌለ ይቆጥረዋል። ይህም አንድ ኪነ ጥበብ ነው።

ፕሮፌሰር አፈ ወርቅ ሁለት ሦስት ያህል ቲያትር ጽፈዋል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሰው በቲያትር ጨዋታ አላያቸውም ደግሞም አልታተሙም።

እንደዚኸው ሁሉ ብዙ ደራስያን ጽፈው ያላሳተሙ አሉና ሥራቸው በሕዝብ ስላልታወቀ ስለነርሱ ለመጻፍ ከዚህ ሥፍራው አይደለምና እንተወዋለን። ቢሆንም ከነዚህ ያንዱን የበጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትን ስም ማስታወስ የተገባ ነው።

፪ በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም

teklehawaryat-photo-2

አገራቸው ሸዋ፣ የተወለዱበት ዘመን ደግሞ 1875 ዓ.ም ግድም ነው። እርሻና የወታደርነት ሥራ በሞስኮብና በፈረንሳይ አገር ተምረው በኢትዮጵያ መንግሥት ከፍ ባለ ልዩ ልዩ ሹመት ላይ ኑረዋል። በመጨረሻ ጊዜም በፓሪስና በዤኔቭ የኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስትር ሁነው ነበር። ፍጹም አማርኛ በሆነ ግጥም ጥቂት ተረት ጽፈው ካሳተሙና በተረት ዓይነት ቲያትር ከጻፉ በኋላ፣ አሁንም ንጹሕ በሆነ አማርኛ ስለ እርሻ ትምህርት ጽፈዋል።

teklehawaryat-ershaበዚህም መጽሐፍ በአማርኛ ቃል ላልተገኘለት ለኬሚስትሪና ለሌላው ዕውቀት የተመረጠ ቃል በመገኘቱ ዕውቀትን በእውነት እጅ ካደረጉት ለደራሲ ቋንቋን እንደልቡ ማዘዝ እንደማያስቸግር ያስረዳል። በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ለኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መግለጫ የተናገሩትና የጻፉት ደግሞ የተሰወረን አሳብ ለመግለጥ ችሎታ እንዳላቸው ያስረዳል።

፫ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ

ነጋድራስ ገብረሕይወት ትውልዳቸው ትግሬ ሲሆን ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ሙተዋል። በልጅነታቸው ነምሳ (ኦስትሪያ) አገር ብዙ ተቀምጠው በትምህርታቸው ተጠቅመዋል። ከጻፉት አብዛኛው ጠፍቶ በሕይወታቸው ሳሉ ስለ አጤ ምኒልክና የኢትዮጵያ ሕዝብ በኤርትራ ሲታተም ከነበረ ጋዜጣ አሳትመዋል። “የመንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” ብለው የሰየሙትን መጽሐፍ ከሞቱ በኋላ ወዳጆቻቸው አሳትመውታል።

በሁለቱም ሁሉ መጻሕፍት ኢትዮጵያዊ በሚረዳው አካሔድ የቤተ መንግሥቱ ሥራ ማሻሻል እንዳለበት ሰብከዋል። ሁለቱም መጻሕፍት ደራሲው በልበ ሙሉነት ስለሚገልጡት ከፍተኛ አሳብና ስለ ንግግራቸው ጥራት ምስክር ናቸው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ብዙ ጉዳይ ለማሠራትና፣ ለወደፊት ሕግንና ልማድን እያሻሻሉ ለማደስ ስላለብን ሥራ፣ ብርቱ አሳብ የሚያሳድሩ የሚያስፈጽሙም መጻሕፍት ናቸው።

(በክፍል አራት ይቀጥላል …)

የፒያሳው ኬዎርኮፍ ሕንጻ

የፒያሳው ኬዎርኮፍ ህንጻ

(ክፍል 2)

በሕይወት ከተማ

(… ከክፍል አንድ የቀጠለ)

 

በ1900ዎቹ መጨረሻ ማቲክ ኬዎርኮፍ በተባለ ነጋዴ ለሱቅነት የተገነባው ሕንጻ ለሃያ አመታት ያህል በዚሁ በመደብርነቱ ሲያገለግል ቆየ። ከስድስቱ የሕንጻ ክፍሎችም ሁለቱ (የዛሬዎቹ “ካስቴሊ” እና “አንበሳ ባንክ”) በዛን ዘመን የሕንጻው አካል አልነበሩም። ከ1928 ዓ.ም በኋላ ግን ይህ ታሪከኛ ሕንጻ ብዙ መሰናክል አጋጠመው። ሆኖም፣ ሕንጻውም በበኩሉ በርካታ አይነት ለውጦችን በማድረግ ከዘመኑ ጋር ለመሄድ ጥሯል።

Casa Littoria (1928-1933 ዓ.ም.)

በሚያዝያ 1928 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ (ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ በባቡር ሲሰደዱና ጣልያን ገስግሶ መዲናችን ሲገባ) የአዲስ አበባ ሕዝብ አራዳን መዝረፍ እና ማውደም ጀመረ። በሚቀጥሉት አራት ቀናት ውስጥ ብዙ ንብረት ጠፋ፤ እጅግ ብዙ ሱቆች፣ ሆቴሎችና ንግድ ቤቶችም ተቃጠሉ። የኬዎርኮፍ ሱቅም ይህ እጣ አልቀረለትምና ከአካባቢው ሕንጻዎች ጋር ተቃጥሎ በአጥንቱ ቀረ።

picture 08
ህንጻው በቃጠሎ ጊዜ  (ምንጭ – Fasil & Gerard – Plate 505)

ጣልያንም ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የሕንጻ ባለሙያዎቹ የኬዎርኮፍን ሕንጻ ውበት ለማየት አልተቸገሩም። አፍርሰው በሌላ በመተካት ፋንታ እንዳለ ለማደስ ወሰኑ። አንዳንድ ለውጦችን ግን ማድረጋቸው አልቀረም።

Capture
የኬዎርኮፍ ሕንጻ ፕላን
picture 10
በጣልያን እድሳት ጊዜ  (ምንጭ – Cine ITTA` Luce Instituto)

ከጎን በምስሉ እንደሚታየው ፣ ዋነኛው ለውጥ “ሕ4” እና “ሕ5” ከህንጻው ጋር መቀላቀላቸው ነው። የሕንጻው አካል ለማድረግ የተጠቀሙበትም ዋነኛው መንገድ በቀኝ በኩል ላለው “ሕ5” (የዛሬው ካስቴሊ) የላይኛውን ፎቅ መስኮቶች ቅስት ማድረግ ነበር። በተጨማሪም ቀድሞ በ”ሕ1” እና “ሕ3” አናት እና ወገብ ላይ የነበረውን ተደራራቢ መስመር ወደ “ሕ5” እንዲቀጥል አደረጉ።

“ሕ2” እና “ሕ4” (ምንጭ – Cine ITTA` Luce Instituto)

በግራ በኩል ላለው “ሕ4” ግን እምብዛም ለማመሳሰል ጥረት የተደረገ አይመስልም። የውስጡ ፕላን እንዲገናኝና እንደ አንድ ወጥ ሕንጻ እንዲዋሐዱ ቢደረግም፣ ለአይን ግን እስካሁን ልዩነታቸው ጎልቶ ይታያል። “ሕ4” የሌላውን ሕንጻ ክፍሎች ዋነኛ ጸባይ (ከጥርብ ድንጋይ መሠራቱን) እንኳን አላሟላም።

በተጨማሪም፣ (ከእድሳት በኋላ) ጣራው ተነስቶ ወደውጭ ወጣ ብሎ የነበረው ገባ ተደርጎ የጣራው ተዳፋት በጣም አጭር ሆነ። እንዲሁም፣ የጣራው ቆርቆሮ እንዳይታይ ግድግዳው በትንሹ ወደላይ ከፍ ብሎ እንዲቀጥል ተደረገ።

የላይኛዋም ህንጣ (“ሕ6”) ከስሯ ጓደኛ ተፈጥሮላት አዲሲቷ እንጎቻ የራሷ ጣራና ትንንሽ መስኮቶች እንዲኖራት ተደረገ። የቀድሞዋ እንጎቻም ወደላይ ከፍ ብላ በአምስት ማእዘን ጎኖቿ ላይ የራሷ ቅስት መስኮቶች ተሰሩላት።

“ሕ6” ከእድሳት በኋላ
sketch 09
የመስኮቶች አቀማመጥ ከእድሳት በኋላ

እነዛ ትናንሽ አራት ማዕዘን መስኮቶችም ተደፍነው በግራ በኩል (“ሕ2” ክፍል) ያሉት በርና መስኮት ሁለቱም ዝቅ ብለው እንዲታዩ ተደረገ። በቀኝ በኩል (“ሕ3” ክፍል) ደግሞ አንደኛው መስኮት ከፍ ብሎ ከ“ሕ1” ጋር ሲቀላቀል፣ በሩ ግን ዝቅ እንዳለ በተዛነፈ ዲዛይን ተሠራ።(ምስል 21 – የመስኮቶች አቀማመጥ ከእድሳት በኋላ)

በመጨረሻም፣ መስኮቶቹ በሙሉ ያራት ማዕዘን ጠርዝ ባላቸው መስታወቶች ተቀይረው ከፎቁ ላይ “Casa Littoria” የሚል ጽሑፍ ካናቱ በትልቁ ተቀመጠበት። ህንጻውም በዚህ አዲሱ የፋሽስት ኢጣልያ አስተዳደር ቢሮነቱ ከ”ፒያሳ ሊቶሪዮ” አደባባይ ፊት ደረቱን ነፍቶ ቆሞ ካራት አመት በላይ አገለገለ።

kervekoff
ካዛ ሊቶሪያ  (ምንጭ – Berhanou Abebe Collection)

 

 የኢትዮጵያ የርሻ ባንክ (1930ዎቹ-1960ዎቹ)

 

ምንም እንኳን ጣልያን ወጥቶ ነፃነት ቢመለስም፣ ህንጻው ወደ ቀድሞው ባለቤት ወደ ኬዎርኮፍ ቤተሰቦች የተመለሰ አይመስልም። በኒህም ዓመታት፣ ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች (እርሻ ባንክ፣ ንግድ ምክር ቤት) በቢሮነት ማገልገል ጀመረ።

picture 14
የኢትዮጵያ የርሻ ባንክ  (ምንጭ – Postcards by “George Talanos, Addis Ababa”)

በ1950ዎቹ አካባቢ አሁንም አነስ ያለ እድሳት ተደረገበት። ይህም የሚታየው በተለይ ከላይኛዋ እንጎቻ ህንጣ ላይ ነው። አምስት ማዕዘኗ በጎባጣ መስኮቶች ፋንታ በአራት ማዕዘን መስኮቶች ተተኩ። ሶስቱ መግቢያ በሮችም የበር ፍሬም ለውጦች ተደርገውባቸዋል።

በእርሻ ባንክነቱ ዘመን
010-Haile-Selassie-Square
ህንጻው [በግራ] በእርሻ ባንክነቱ  ዘመን  (ምንጭ – Postcards by “George Talanos”)
043-Traffic-policeman
ሕንጻው  በርሻ ባንክነቱ ዘመን  (ምንጭ – Postcards by “Edit. National Photo Studio” )

 

ከኤልያስ ሆቴል እስከ ሮያል ኮሌጅ (1970ዎቹ-2000ዎቹ)

 

photo-1-5
ሕንጻው በቅርቡ ይዞታው  (ፎቶ በአንድምታ)
photo 2 (2)
ተመሳስሎ የተሰራው የመስኮት ድጋፍ  (ፎቶ በአንድምታ)

ከ1960ዎቹ በኋላ የተደረገው ዋነኛ ለውጥ “ሕ1” መሀል ላይ የነበሩት ሶስት ዋና መግቢያ በሮች ወደ ሁለት መስኮትና አንድ በር መቀየራቸው ነው። ይህንንም ለማድረግ ባለሙያዎች ከቀድሞው ሦስት በሮች ግራና ቀኝ የነበሩትን መስኮቶች አስመስለው በር 1 እና 3 ግርጌ የመስኮት ድጋፍና ጌጥ ከተመሳሳይ ድንጋይ አበጅተዋል።

ከመስኮት ወደ በር  (ፎቶ በአንድምታ)

በተጨማሪም፣ የ”ሕ1” አንዱን መስኮት (በግራ ያለውን) ወደ በር ለመቀየር ተወስኗል። ይህንንም ለማድረግ የቀድሞውን መስኮት ታችኛ ድጋፍ እና ጌጥ ጥርብ ድንጋዮች ሙሉ በሙሉ ነቅለው (ቆርጠው) ለማውጣት ተገደዋል። ከዚህም ሂደት የተረፈው የአሁኑ በር ጠርዝ በሊሾ ሲሚንቶ ለማስተካከል ሞክረዋል።

በህንጻው ሁለተኛ ፎቅ ወደ ባንኮኒ ያስወጡ የነበሩት ሰባት በሮች ከአንዱ በስተቀር (በቀኝ በኩል መጨረሻ ያለው) ሁሉም ወደ መስኮትነት ተቀይረዋል። የላይኛውም ህንጣ (“ሕ6”) እንደገና ሌላ እድሳት ተደርጎበት የመስኮቱ ማዕዘን በመጠኑ ሰፍቷል።

sketch 13
“ሕ6” በአሁኑ ይዞታ

በተጨማሪ ግን፣ ከግልጋሎትና አንዳንድ የቀለም ለውጥ ውጭ እምብዛም ለውጥ አይታይም። ከመጠቀም ብዛትና ከጥገና እጦትም እንደ ብዙዎቹ የሀገራችን ታሪካዊ ሕንጻዎች ጃጅቶ ይታያል።

በአሁኑ ጊዜ ይህ ህንጻ በቅርስነት ተመዝግቧል። በአሁኑም ይዞታው ህንጻው ሮያል ኮሌጅን፣ አቢሲኒያ ባንክን እና ካስቴሊ ሬስቶራንትን በውስጡ ያስተናግዳል። የካስቴሊ ቤተሰብ በጣልያን ወረራ ጊዜ በ1928 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደገቡ ይነገራል። ኋላም ጣልያን ካገር ሲወጣ አዲስ አበባ ቀርተው በ1940ዎቹ መጨረሻ ካስቴሊ ምግብ ቤትን ከፈቱ። ታዲያ ይህ ምግብ ቤት በምርጥ የጣልያን ምግብ አዘገጃጀቱ የአለም አቀፍ ተወዳጅነት አትርፏል። ብራድ ፒት እና ጂሚ ካርተርም ሳይቀሩ ስፓጌቲያቸውን በዚሁ ምግብ ቤት እንደጠቀለሉ ይወራል!

የኬዎርኮፍ ህንጻ ስልቶች

 

የኬዎርኮፍ ሕንጻ

discription-kevበመጀመሪያው የአሰራሩ ውጥን ብናየው የህንጻው ስልት (Architectural Style) በአጠቃላይ “እንዲህ ነው” ብሎ ለመፈረጅ ያስቸግራል። ነገር ግን ለያይተን ብንመለከት፤ (ሀ) ድርድር ቅስት መስኮቶች (Arched Windows)፣ (ለ) የጣራ ክፈፍ ስር ያለው ጌጥ (Entablature)፣ (ሐ) የህንጻው ወገብ እና ግርጌ ላይ የሚዞሩት ተደራራቢ መስመሮች (Stone Bands)፣ (መ) ቋሚ-መሳይ አምዶች (False Columns)፣ (ሠ) ሙሉ የጥርብ ድንጋይ ህንጻ ስራ፣ (ረ) ወጣ ገባ ማዕዘን ስራ (Quoins)፣ እንዲሁም (ሰ) የባንኮኒው አጋጌጥ መንገድ በአውሮፓ ከ1832-1911 በሰፊው ይሰራበት የነበረውን “Renaissance Revival” የተሰኘውን የሥነ ህንጻ ስልት ያስታውሰናል።

kev-descበተመሳሳይ መልኩ ደግሞ፤ (ሸ) የጣራው ክፈፍ ወጣ ብሎ አሰራር፣ (ቀ) የጣራው ተዳፋት ስፋት፣ (በ) የመስታዎቶቹ ፍሬም አሰራር፣ (ተ) የጣራው ክፈፍ ጌጥና ጉልላት (Fascia Board Ornamentation) (ቸ) የጣራ ስር ፎቅ (Dormer Floor)፣ እና (ኀ) ከአናት ያለችው ህንጣ አሰራር፤ የ “እስያ” የሥነ ህንጻ ጥበብ እና በተለይም ከ1829–1893 በአውሮፓ የነበረውን እስያ-ገረፉን “Victorian Architecture” ያስታውሰናል።

በአጭሩ ኬዎርኮፍ ህንጻ የተለያዩ የኪነ-ህንጻ ስልቶችን ያንጸባርቃል::

በጣልያን እድሳት ጊዜ ብዙዎቹን የ “Victorian Architecture” የሚያሳዩትን ስልቶች አስወግዶ ወደ  “Renaissance Revival” እንዲጠጋ ያደረገው ይመስላል። ማለትም (1) የጣራውን ክፈፍ ማስወገድ፣ (2) የጣራውን ተዳፋት አጭር አድርጎ ግድግዳውን ወደላይ በመቀጠል እንዳይታይ ማድረግ (3) የመስታወቶቹን ፍሬሞች በሙሉ በአራት መዓዘን መቀየር፣ (4) የጣራ ስር ፎቅን (Dormer Floor) ማስወገድ፤ ወደዚህ ስልት እንዲጠጋ ያደርገዋል። አሁንም ግን ሙሉ ለሙሉ ይህን የኪነ-ህንጻ ስልት ይከተላል ለማለት ያስቸግራል። በተጨማሪም ጣልያን ከህንጻው ፕላን ጋር ካቀላቀላቸው ህንጻዎች መካከል “ሕ4” ከጠቅላላው ስልት ጋር እንዲጣረስ አድርጎታል።

በአሁኑ ይዞታው ከጣልያን እድሳት እምብዛም የተለወጠ ነገር ባይኖርም፣ አንዳንድ በግዴለሽነት እንዲሁም ለግልጋሎት መመቸት ተብለው የተቀየሩ ነገሮች ከአጠቃላይ የህንጻው ቢጋር ጋር የማይሄዱ ሆነው እናገኛቸዋለን።

ለምሳሌ፣ አናት ላይ ያለችው እንጎቻ ህንጣ ከጎባጣ መስኮቶች ወደ አራት መአዘን መቀየሯ ከየትኛውም የህንጻው ቢጋር ጋር አይሄድም። እንዲሁም የግራና የቀኙ “ሕ2” እና “ሕ3” አለመመሳሰል የህንጻውን ሚዛናዊ እይታ ያዛባዋል። ወደ ባንኮኒው የሚያስወጡት በሮችም ወደ መስኮት መቀየር ባንኮኒውን ጥቅም ያሳጡታል።

በአጠቃላይ ይህ የመቶ አመት እድሜ ጠገብ ህንጻ ሂደታዊ ለውጥ ከሌሎች የአዲስ አበባ ህንጻዎች በልዩ መልኩ የሚታይ አይደለም። ማንኛውም ህንጻ ሕይወት ያለው ፍጡር ይመስል ያድጋል፣ ይጎረምሳል፣ ያረጃል፣ ይታደሳል፣ ይሞታል። የመዲናችንን ህንጻዎች በተመሳሳይ መልክ በቅርበት ብናስተውላቸው ተዘርዝሮ የማያልቅ የከተማችንን ታሪክ መልሰው ያንጸባርቁልናል።

(በክፍል ሶስት ይቀጥላል …)

“በዕውቀቱ ሥዩም” (ቃለመጠይቅ)

ቆይታ ከበዕውቀቱ ሥዩም ጋር

(ከመስከረም 1998 ዓ.ም እትማችን የተወሰደ)

.

በዕውቀቱ ሥዩም የስነጽሑፍ ተስፋችንን ከጣልንባቸው ወጣት ጸሐፊዎች አንዱ ነው። “በክንፋም ህልሞች” ውስጥም የመጽሐፉን ርዕስ የያዘውን አጭር ልብወለድ ደራሲ ነው። ስለሱም ከመጽሐፉ ያገኘነው እንዲህ ይላል – “… በጎጃም ማንኩሳ በምትባል ገጠር ቢጤ ከተማ ተወለደ። ደብረ ማርቆስም ተማረ። በ1995 ዓ.ም. ‘ኗሪ አልባ ጎጆዎች’ የሚል የግጥም ስብስብና በ 1996 ‘በራሪ ቅጠሎች’ የሚል የሽርፍራፊ ታሪኮች መድበል አሳትሟል። … በ1993 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን በጽሑፍ ስራ ይተዳደራል።” በ1997 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በስልክ አግኝተነው ነበር።

አንብበህየወደድከውየመጀመሪያውመጽሐፍምንነበር?

ትዝ የሚለኝ የሐዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ነው። ከውጭ ደግሞ 3ኛ ነው 4ኛ ክፍል ያነበብኩት አንድ የኬንያ ጽሑፍ … አርእስቱ ጠፋኝ … ኸ … ታሪኩ ስለ ማሳዮች ነበር። አዎ ‘The Chiefs Shadow’ መሰለኝ።

የምትወደውየሐገርደራሲ?

ሀዲስ አለማየሁና ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር።

ገጣሚስ?

ዮፍታሔ ንጉሤና ዮሐንስ አድማሱ።

ኢትዮጵያውያንማንበብአለባቸውየምትላቸውሶስትመጽሐፎችየትኞቹናቸው?

መጀመሪያ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ን እመርጣለሁ። መጽሐፉ የኢትዮጵያን ስነጽሑፍ ወደፊት አሻግሯል። የአለም ስነጽሑፍ ደረጃን የጠበቀ የአገራችን የመጀመሪያው ድርሰት ነው – ግን ኢትዮጵያዊነቱን ሳይለቅ። ቀጥሎ የምመርጠው የስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን ‘ሌቱም አይነጋልኝ’ን ነው። ብዙ ሰው ስብሐትን የሚያውቀው Controversial ነገሮችን ስለሚያነሳ ነው። ነገር ግን አጻጻፉ ራሱ ጥንካሬ አለው ፤ ነፃ ሆኖ የጊዜውን የስነጽሑፍ ህግጋቶች Transcend አድርጓል – አልፏል። ከግጥም መጽሐፎች የዮሐንስ አድማሱን ‘እስኪ ተጠየቁ’ን እመርጣለው። በተጨማሪም የዕጓለ ገብረ ዮሐንስን “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተዋጣለት ሐተታ አቀራረቡ እመርጠዋለሁ።

ከውጭጸሐፊዎችእነማንንትወዳለህ?

ሚላን ኩንዴራን አደንቃለሁ፤ ‘The Unbearable Lightness of Being’ እና ‘Book of Laughter and Forgetting’ የሚባሉ መጽሐፎች አሉት – አራት አምስት ጊዜ ደጋግሜ ነው ያነበብኳቸው። ከዛ በፊት ረጅም ልብወለድ ደጋግሞ የሚነበብ አይመስለኝም ነበር። አንዴ ከተነበበ ታሪኩ ስለሚታወቅ ለምን ይደገማል እል ነበር። እንዲሁም ቪክቶር ሁጎን፣ ቻርልስ ዲክንስን እና ፍሬዴሪክ ኒቸን እወዳለሁ።

ለመሆኑለማነውየምትጽፈው? አንባቢህማነው?

እኔ እንኳ ለአንባቢ ብዬ ሳይሆን ለራሴ ነው የምጽፈው። ከዛም ጓደኞቼን አስነብባለሁ። እነሱ ከወደዱት እንዲወጣ ይደረጋል።

ዮሐንስአድማሱንብዙጊዜበጽሑፎችህታነሰዋለህ።የምትወደውንምያህልአንዳንዴትቀልድበታለህ።እንዴትነውነገሩ?

(ሳቅ ብሎ) የምቀልድበት ስለምወደው ይመስለኛል። ዮሐንስ ሀያሲነቱን በጣም አደንቃለሁ፤ ሂሶቹን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች አቅርቧል። ዘመናዊ ገጣሚነቱንም እስከነድክመቶቹ አደንቃለሁ።

ድክመቶቹ?

ድክመቶቹ – ለምሳሌ እንደነ ‘እስኪ ተጠየቁ’ የመሳሰሉት ግጥሞች ከመጠን በላይ ረዝመዋል፤ ስሰማ በዛ ጊዜ የነበሩ ጸሐፊዎች የአማርኛ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ዘዴ ነበር። በዛው ልክ የአማርኛ ግጥምን አሳድጓል። ከሱ በፊት የነበሩ ዘመናዊ ገጣሚዎች (እንደነ ከበደ ሚካኤል የመሳሰሉት) አንብበው ወይም ሰምተው የሳባቸውን ሀሳብ ቅርፁን ወደ ወል ግጥም ቀይረው ለሰው ያቀርቡ ነበር። ዮሐንስ ግን የራሱን የሚገርሙ እይታዎች በራሱ ቅርፅ!

መጽሐፎችህበራስህስእሎችየታጀቡናቸው።በአገራችንያልተለመደነገርነው፤እንዴትጀመርከው?

ወደ ሥነጽሑፍ ከመግባቴ በፊት ሥዕል እሞክር ነበር። አሁንም አቢሲኒያ ሥዕል ኮሌጅ ገብቼ እማራለሁ። ሥዕሎችን ከጽሑፋቸው ጋር በማዋሃድ የሳቡኝ ካሊል ጊብራንና በተለይም ዊልያም ብሌክ ናቸው። ሥዕሎቹ ለግጥሞቹ ወይም ለታሪኩ እንደ ማስረጃ ወይንም ምትክ እንዲሆኑ ብዬ አይደለም። በራሳቸው መንገድ እንደ ቅኔ እንደ ሀሳብ እንዲታዩ ነው።

እንደክንፋምህልሞችገጸባህሪያትከማንኩሳወደደብረማርቆስከዛምወደአዲስአበባተሸጋግረሃል።አሁንስአሜሪካልትመጣነወይ?

(እየሳቀ) አይመስለኝም። አሜሪካን ለናንተ ትቻለሁ። አዎ ‘ክንፋም ህልሞች’ን ስጽፍ ከተወለድኩበት ማንኩሳ እስከ አዲስ አበባ ያለፍኩበትን የሕይወት ልምድ ተጠቅሜበታለሁ። የፈራሁት ግን የአሜሪካውን ደብዳቤ ነበር።

እንዴት?

አይ ለአሜሪካ መንፈስ ባእድ ስለሆንኩ በትክክል ላላቀርበው እችላለሁ ብዬ ፈርቼ ነበር።

እናመሰግናለን።

እኔም አመሰግናለሁ።

የአስናቀች ወርቁ ኪነጥበባዊ ሕይወት

የአስናቀች ወርቁ ኪነጥበባዊ ሕይወት

በኅሩይ አብዱ

“አስናቀችና ሙዚቃ”

ከቅጽበታዊው የተውኔት መድረክ ይበልጥ አብዛኞቻችን አስናቀችን የምናያይዛት ከክራሯና ከምታንጎራጉራቸው ዘፈኖቿ ጋር ነው። እንደ ኢየሩሳሌምን እንደምታስታውሱ ተስፋ አደርጋለሁ።

“እንደ ኢየሩሳሌም እንደ አኩስም ፅዮን ፣

ተሳልሜው መጣሁ አይንና ጥርሱን …”

asnakech-ethiopiquesየኢትዮጵክስ 16 – “The Lady With the Krar” – ሲዲ አስናቀች በ1966ና 1968 ዓ. ም. ያወጣቻቸውን ሸክላ ዘፈኖች የድምጽ ጥራት አሻሽሎ ለገበያ ቀርቧል። ኢትዮጲክስ 16 ሃያ ሁለት ዘፈኖችን አሰባስቧል፣ ዘፈኖቹ በሕዝባዊ ዜማዎች ላይ ተመስርተው ሰባቱ ግጥሞች በአስናቀች ሲደረሱ ሌሎቹ በጌታቸው ደባልቄ፣ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ተስፋዬ ለማና፣ ሸዋልዑል መንግስቱ የተገጠሙ ናቸው።

አስናቀች በክራር ራሷን አጅባ በምታንጎራጉራቸው ዘፈኖች የምታተኩረው ተቀጣጥሎ ያልተፋፋመ ወይንም የሰከነ ፍቅር ላይ ነው። ለአብነት ‘እንደ ኢየሩሳሌምን’ና ‘እሱ ርቆ ሄዶ’ን መመልከት ነው። የፍቅር ጉዞዋ በዘፈኖቿ ውስጥም ይታያል። የምታፈቅራቸው ሰዎች አያዛልቋትም፤ የሰው ሰው ሊሆኑ ይችላሉ ወይንም ስሜታቸው አብሯት አይፈካም። ለዚህም ነው ፍቅረኞቿን “ይፋ የማይወጣ ሰው”፣ “ፍቅር የማይገባው አጉል ሰው” እያለች የምትጠራቸው። አስናቀች ለወደደችው ፍቅሯን ከመግለጽ አትቆጠብም፣ ከመለማመጥም አትመለስም። አንዴ ፍቅሩ ከሰከነ ግን እርግፍ አድርጋ ትተዋለች። ሕይወቷም ዘፈኖቿም ምስክሮች ናቸው።

“መሞከር ይሻላል ሁሉንም መሞከር፣

ይፈጠር ይሆናል አንድ ደህና ነገር።”

መንገደኛው ልቤ 1966 ዓ. ም.

asnakech-musicአስናቀች ወርቁ እነዚህን ስንኞች ስታንጎራጉር የሕይወቷን ሚስጥር የምታካፍለን ይመስላል። አስናቀች ዘወትር ሕይወቷን ወደ አዲስ መንገድ እንደመራችው ነው። ከልጅነት ወደ ትዳር፣ ከአንዱ ትዳር ወደ ሌላ፣ ያም ሲፈርስ ወደ አዲስ ፍቅረኛ፣ ከዛም ወደ ሌሎች ፍቅረኞች ተሻግራለች። ብዙ ነገር ሆናለች፤ ማንም ያልደፈረውን የሴት ተዋናይ፣ ከዛም አልፋ የሙዚቃ (ክራር) ተጨዋች ፣ ዘፋኝ (አንጎራጓሪ)፣ እንዲሁም የባሕልና የዘመናዊ ሙዚቃ ተወዛዋዥ፣ ሁሉንም ሆናለች።

“አስናቀችና ቴያትር”

አስናቀች “የፍቅር ጮራ” ተውኔት ውስጥ ከመሳተፏ በፊት የሴትን ገጸባህሪ የሚጫወቱት ወንዶች ነበሩ። የሚመረጡትም ጺም ገና ያላወጡ ፣ መልከ መልካም ወጣቶች – እንደ ተስፋዬ ሣህሉ (አባባ ተስፋዬ)፣ መርአዊ ስጦት፣ ተፈራ አቡነወልድ … የመሳሰሉት – ነበሩ። ምንም መልከ መልካም ቢሆን፣ ድምጽንም እንደፈለገ መቀያየር ቢችል፣ ወጣቱ አባባ ተስፋዬ (ወይንም ሌላ ወንድ ተዋናይ) የቧልት እንጂ ውስብስብ የሴት ገጸባህሪይ መጫወት የሚችል አይመስለኝም። በአስናቀች ፋና ወጊነት የሴቶችን ገጸባህሪ ሴቶች ራሳቸው ይጫወቱት ጀመረ፤ የሚሰሩትም ተውኔቶች ተአማኒነታቸው እየጨመረ ሄደ።

img_4762የዚህችን ሁለገብ ጠበብት ሕይወት የሚዳስስ መጽሐፍም በቅርቡ ታትሟል። አስናቀች መድረክ ላይ የምትጫወተውን የባለታሪክ ባህርይ ሙሉ በሙሉ እንደምትላበስ ደራሲው ይናገራል። ለምሳሌ የፍቅር ጮራ ላይ ከመድረክ ፍቅረኛዋ ጋር የነበራት ግንኙነት እውነተኛ በመምሰሉ ትርኢቱን የምትመለከተው የተዋናዩ ፍቅረኛ እያለቀሰች ዝግጅቱን አቋርጣ ወጥታለች (ገጽ 23)። በሌላ መድረክ ላይ “ሴተኛ አዳሪዋ” አስናቀች ኑሮዋን የመረጠችው እንደሌላው ስራ ዘመድ፣ ትምህርት ወይንም ጉቦ ስለማያስፈልገው እንደሆነ ትናገራለች። እውነታው የከነከናቸው የውቤ በረሃ ቆነጃጅት እንዲሁም ሌላው ተመልካች ገጸባህሪዋን (ወይንስ አስናቀችን?) በጭብጨባ ደግፈዋታል (ገጽ 36)።

አስናቀች ምን ያህል ተውኔቶች ውስጥ እንደተሳተፈች አላውቅም። መጽሐፉም አይናገርም። ደራሲው የፍቅር ጮራ ፣ እኔና ክፋቴ ፣ ዳዊትና ኦሪዮን ፣ ስነ ስቅለት ፣ ኦቴሎ ፣ እናት አለም ጠኑና ኤሪስ በጎንደር የተባሉትን ዘርዝሯል። የነዚህን ከአምስት እጥፍ በላይ እንደሰራች አልጠራጠርም። ነገር ግን ተጽፎ ካልተቀመጠ ይረሳልና፣ ደራሲው የወደፊት እትም ላይ ቦታ ቢሰጠው መጽሐፉን ያሳድገዋል። ገጣሚውና ጸሐፌ ተውኔቱ ጸጋዬ ገብረ መድህን በበልግ መጽሐፉ ፣ “በመስከረም 19 ቀን 1954 ዓ. ም. ዓርብ ማታ በተከፈተ (የበልግ ተውኔት) ጊዜ፣ … ጌታቸው ደባልቄ እንደ ወፈፌው ሰዓሊ እንደ ኅሩይ፣ … አስናቀች ወርቁ እንደ ብኩኗ ቆንጆ እንደ ጽዮን ሆነው ተጫውተው ነበር” በማለት ዘግቧል። በተጨማሪም አውራስ መጽሔት 1985 ዓ.ም. ቁጥር 1 ላይ እንዳየሁትም “ደመ መራራ”ና “ዋናው ተቆጣጣሪ” የተባሉ ተውኔቶች ውስጥ ተሳትፋለች።

“መጽሐፉ”

img_4761የአስናቀች ትዝታዎቹን በጽሑፍ አዘጋጅቶ ያቀረበልን ጌታቸው ደባልቄ ነው። ጌታቸው ላለፉት 50 አመታት ከዘመናዊ የኢትዮጵያ ቴያትር አብሮ ድኾ፣ አድጎ፣ ጎልምሷል – እንደ ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ደራሲ እንዲሁም አስተዳዳሪ። በተጨማሪም ጌታቸው ስለ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃና ቴያትር አጀማመርና ሂደት ማወቅ ለፈለጉ የመረጃ ምንጭ ኧረ ወንዝም ነው። የሰበሰባቸው ፎቶዎችና ሰነዶች፣ እንዲሁም ለጠየቁት በደስታ የሚያወጋቸው ትዝታዎቹ፣ ከመጽሔቶች ተርፈው ሙሴ ፋልሴቶ አዘጋጅቶ የሚያቀርባቸውን የኢትዮጲክስ (Ethiopiques) ሲዲዎች እያጀቡ ነው።

ደራሲው ከባለታሪኳ ጋር የተዋወቀው በ1945 ዓ.ም. ነበር። ጌታቸውም እንደሚለው፣ “ስለሷ ሕይወት መጠነኛ ታሪክ ለማስቀረት ምኞት ካደረብኝ ቆይቷል” ለምንስ መጽሐፉን ጻፈ? “… ለነገዎቹ የኪነጥበብ ሰዎችና ታሪክ ጸሐፊዎች” ለማስተላለፍ ይመስላል።

asniመጽሐፉ አራት ክፍሎች አሉት፤ እነሱም ልደትና እድገት – ውስብስብ ሕይወት ፣ የጥበብ ጮራ ፣ ከጠባቡ ወደ ሰፊው የኪነጥበብ አለምና፣ ጡረታና ትዝታ ናቸው። አባቷን የማታውቅ፣ እናቷም በሕጻንነቷ የሞቱባት አስናቀች፣ ልጅነቷን ያሳለፈችው አንዱ ዘመድ ወደ ሌላው እየተቀባበላት ነበር። በብቸኛው የአዲስ አበባ የሴቶች ት/ቤት የመማር እድሏን ስለተነፈገች፣ ምርጫ ሆኖ የታየው ለትዳር መዘጋጀት ብቻ ነበር። አክስቷም ጣሊያን አገር ሚስትና ልጆቹን ላስቀመጠው ለአንዱ ዳሯት። ልጅነቷን ያልጠገበችው አስናቀች ግን የትዳር ማተብ ሊያስራት እንዳልቻለ በመጀመሪያው ክፍል እናያለን።

ሁለተኛው ክፍል የዘመናዊን ቴያትር አጀማመር በትንሹ ዳስሶ አስናቀችም በምን መልክ “የፍቅር ጮራ” ተውኔት ላይ የመጀመሪያዋ የሴት ተዋናይት እንደሆነች ይተርካል። የሚቀጥለው ክፍል የአስናቀችን በ“ዳዊትና ኦሪዮን” (ለአፄ ኃይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዮ የተዘጋጀ ተውኔት) የተዋጣለት ትወና፣ እንዲሁም ከክራሯ ጋር የመሰረተችውን ፍቅር አጀማመር ያወሳል። የመጨረሻው ላይ ክፍል ከጡረታ ይልቅ ሁሌ የሚፋጀው የአስናቀች ፍቅር ላይ ያተኩራል፤ የፍቅር ሕይወቷ ለብቻው አንድ ተውኔት ሳይወጣው አይቀርም። በኢትዮጲክስ አዘጋጅ ከቀረበው አጭር የሕይወት ታሪክ በኋላም መጽሐፉ በሁለት የታወቁ የአስናቀች የዘፈን ግጥሞች ይደመደማል።

asnaketch-costume

የሽፋኑም ምስሎች ፣ የደራሲውንም ጉርድ ፎቶ ጨምረን መጽሐፉ ከሃያ በሚበልጡ ፎቶዎች አሸብርቋል። የናንተን ባላውቅም እኔ በበኩሌ ፎቶ ወይንም ምስሎች የተነሰነሱበት መጽሐፍ ይስበኛል። ምስሎች ከታሪክ ጋር በአግባቡ ሲዋሀዱ ጽሑፍን ያጣፍጣሉ፤ ምናባችንንም “በፈረሱም ይኸው ሜዳውም ይኸው” እያሉ ያደፋፍራሉ። አዘወትረን በሀገራችን መጽሐፎች እንደምናየው ፎቶዎቹ ደብዝዘው ሰው ከሰው የማይለይበት ደረጃ አልደረሱም። እነዚህዎቹ ጥርት ብለው ወጥተዋል ፤ ደራሲውና አሳታሚው ምስሎቹን ታሪካዊነት ፋይዳ ስለሰጡ ፎቶዎቹን ከደህና ምንጭ ቀድተው ለፎቶ በሚስማማ ወረቀት አሳትመዋል።

የፊት ሽፋኑን ፎቶ ብትመልከቱት፤ ለብቻው ስንት ታሪክ ይናገራል! መቸስ አስናቀች ባሕላዊነትን ከዘመናዊነት ጋር ያለ ግጭት ካዋሐዱ ጥቂቶች አንዷ መሆን አለባት። የእድሜ ባለፀጋዋ ወጣትነት ከልብ ትኩሳት እንጂ ከቁጥር ማነስ እንደማይገኝ የምታምን ትመስላለች፤ ወይንስ ትዝታዋን የሙጥኝ መያዟ ነው? የአይኖቿ ከኛ መደበቅስ? ብዙ ሚስጥር በሆዷ ይዛ ነውን? እኛን አፍራ ሳይሆን ሸክሙ እንዳይከብደን ያዘነች ትመስላለች። ይሄ በሙላ ከአንድ ፎቶ!

asnakech-kirar

ፎቶዎቹ ሌላም ብዙ ታሪክ ያወሳሉ። አስናቀች የመጀመሪያዋ የሴት ተዋናይ ከመሆኗ በፊት የሴትን ገጸባህሪ ማን ይጫወት ነበር? ገጽ 19 ያለውን ፎቶ ይመልከቱ። በ1945 ዓ. ም. ሁለተኛ ማዕረግ ተቀምጦ ቴያትር ለመመልከት ስንት ብር ያስፈልግ ነበር? ምን ያህልስ የተውኔት ማስተዋወቂያ ይታተም ነበር? መልሱን ገጽ 21 ያገኙታል። ሞኝና ወረቀት … ልበል መሰለኝ።

ጌታቸው ደባልቄ በዚህ አነስተኛ መጽሐፍ ስለሚወዳት ጓደኛው ያሉትን ትውስታዎች አስተላልፎልናል። በተጨማሪም ስለ ቴያትርና ሙዚቃ አጀማመር፣ ወጣቷንም አዲስ አበባን ለመተዋወቅ ለሚፈልጉ ጥሩ እይታ ይሰጣል። ይህን መጽሐፍ እንደተለመዱት በዓመተ ምህረትና በመረጃዎች እንደተሞሉ የሕይወት ስራዎች አላየሁትም። ከዚያ ይልቅ በትውስታ/ትዝታ ዘርፍ ቢመደብ አንባቢውንም አያደናግርም።

ምን ይጨመር? ምንስ ይቀነስ? አስናቀች የተሳተፈችባቸውን ተውኔቶች፣ የዘፈነችባቸውን የሙዚቃ ሸክላዎች ቢዘረዘሩ የበለጠ የምናውቃት ይመስለኛል። የመጽሐፉ መጀመሪያና አራተኛው ክፍል በባለታሪኳ ድምጽ ቢተረክ ቋንቋዋም ስሜቷም የሚዋሐደን ይመስለኛል። መጽሐፉ በመታተሙ እጅግ ተደስቻለሁ፤ በሕይወት ያሉ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጊዜ መጽሐፍ አይጻፍላቸውምና!

እንደ መጽሐፉ መዝጊያ ዓረፍተ ነገሮች …

“ይህ የኔ ጽሑፍ ለመጭዎች ጸሐፊዎች መግቢያ በር ይሆናል። ሊያባዙት ሊያሳጥሩት ቀና መንገድ ይሆናል። በበኩሌ የዘለልኩትን ዘልዬ ያሳጠርኩትን አሳጥሬ በዚህ ሁኔታ ደምድሜዋለሁ።”

አራዳና ቀደምት ሕንጻዎቿ

የፒያሳው ኬዎርኮፍ ሕንጻ

(ክፍል 1)

በሕይወት ከተማ

አራዳና ፒያሳ

አራዳ ከአዲስ አበባ ምስረታ ጀምሮ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ (1879-1928 ዓ.ም) የመዲናችን ዋነኛ የንግድ ማዕከል ነበረች። ከጊዮርጊስ ፊት ለፊት ያለው የሜዳ ገበያ እና በዙሪያውም የተገነቡት ሱቆች በኒህ ሃምሳ አመታት የአራዳን ገበያ አጠናክረውት ነበር።

picture-01
አራዳ ገበያ  (ከፖስትካርድ የተገኘ)

“አራዳ ሲወጣ ምን ይላል ነጋዴው፤

ልቃቂት ካሞሌ የሚደረድረው።

እስቲ ተነስቼ እግሬን ላንቀሳቅሰው

ይምጣ ያራዳ ልጅ፣ እንደ መልካም እናት ጎን የሚዳብሰው።”

በጣልያንም ጊዜ (1928-1933ዓ.ም.) የጥቁርና የነጭ መኖሪያ እንዲለይ ሲደረግ አራዳ የአውሮፓውያን ክልል ተቀላቀለች። የሀገሬው መገበያያም ወደ አሁኑ መርካቶ (በጣልያንኛ Mercato de Indigeno) ዞረ። ብዙም ሳይቆይ፣ በአራዳ ፈንታ መርካቶ የመዲናችን ዋነኛ የገበያ ማዕከል ለመሆን በቃች።

በኒህ ዓመታት፣ ጣልያን ክፍት ቦታዎችን አስታኮ አደባባዮችን “Piazza Roma”፣ “Piazza V Maggio”፣ “Piazza Imperio”፣ “Piazza Littorio” እያለ ይሰይም ጀመር። ታዲያ ነፃነት ሲመለስ ብዙዎቹ አደባባዮች ስማቸውን መልሰው (ምኒልክ አደባባይ፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ) ቀየሩ።

picture-02
ፒያሳ ሊቶሪዮ  (ምንጭ – Cine ITTA` Luce Instituto )

“Piazza Littorio” የተባለችው የጣልያን አደባባይ ግን አሻራዋን ጣለች። እናም ያች የጥንቷ አራዳ ሰፈር፣ የድሮ ዘመን ስሟ ቀርቶ ዛሬ በጣልያን ዘመኑ “ፒያሳ” እየተባለች ትጠራለች። “ፒያሳ ሊቶሪዮ” ተብሎ ይጠራ የነበረው ስፍራ፣ ቀድሞ (ከጣልያን በፊት) የሥላሴ አደባባይ (Star Square) የነበረበት፣ አሁን ደግሞ፤ ከቼንትሮ ካፌ አናት ላይ የሚገኘው “የመነፅር ተራ” የሆነው ሶስት ጎን ክፍት ቦታ ነው። ፒያሳ ሊቶርዮ (የህብረት አደባባይ) የተባለውም ስያሜ ከፊት ለፊቱ ካለው ግራጫ “Casa Littoria” (የህብረት ቤት) ከተሰኘ የድንጋይ ህንፃ የመጣ ይመስላል።

ይህ ታሪከኛ ህንጻ በ1900ዎቹ መጨረሻ አመታት፣ በአርመናዊው ነጋዴ በማቲክ ኬቮርኮፍ (እንዳገሬው አጠራር ኬዎርኮፍ) (Matig Kevorkoff) እንደተገነባ ይነገራል። የህንጻውን ዲዛይን የሠራው ማን እንደሆነ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም። ሆኖም በጊዜው የነበሩት የሥነ ህንጻ ባለሙያዎች አርመኖች፣ ህንዶችና፣ የአውሮፓ ሰዎች ስለነበሩ ከነዚሁ ባንዱ እንደሆነ ይታሰባል። ህንጻው ተሠርቶ እንዳለቀም የኬዎርኮፍ ሱቅ እና ግምጃ ቤት ሆኖ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ አገልግሏል።

ጣልያን በገባበትና ጃንሆይ ካገር በወጡበት መካከል በነበረው የአለመረጋጋት ዕለታት (ሚያዝያ 1928) አራዳ በሌቦች ተዘርፋና ተቃጥላ ነበር። አራዳንም የፈጀው ዝርፊያና ቃጠሎ ለኬዎርኮፍም ሱቅ ተርፎ ህንጻውን አቃጥሎ በአጥንቱ አስቀርቶት ነበር።

ይህ አልበገሬ ህንጻ ሙሉ በሙሉ ነዶ ባዶውን ድንጋዩ ቢቀርም፣ ጣልያኖች (ከአንዳንድ ጥቃቅን ለውጥ በስተቀር) ግርማውን እንደተጎናጸፈ ቅርጹን፣ ጌጡን እና ውጫዊ ገጽታውን ጠብቀው ሊያድሱት ቻሉ። ጣልያንም ይህንን ህንጻ ከኬዎርኮፍ ወርሶ የጣልያን ፋሺስት ፓርቲ ዋና መምሪያ “Casa Littoria” (የኅብረት ቤት) ብሎ ሰይሞ ሲጠቀምበት ቆየ።

በ1933 ዓም ጣልያን ካገር ሲወጣ ህንጻው በመጀመሪያ “የኢትዮጵያ የእርሻ ባንክ” እና “የንግድ ምክር ቤት” ቢሮ ሆነ። በመቀጠልም፣ “ኤልያስ ሆቴል” ተሰኝቶ ለበርካታ ዓመታት ቆየ። አሁን ደግሞ “አቢሲኒያ ባንክ”፣ “ሮያል ኮሌጅ”፣ “ካስቴሊ ሬስቶራንት” እና ሁለት ቡቲኮችን በመያዝ እያገለገለ ነው።

በመቀጠል፣ የህንጻውን ታሪክና ውጫዊ ገጽታ (ከ1900ዎቹ ግንባታው እስከ 2000ዎቹ) ከፋፍዬ አቀርባለሁ። ከዚያም የኪነ-ህንጻውን አጠቃላይ ስልት እና የህንጻውን ባለቤት (ማቲግ ኬዎርኮፍ) ታሪክ በአጭሩ አቀርባለሁ።

የመጀመሪያው ኬዎርኮፍ ህንጻ (1909-1928)

picture-05
ኬዎርኮፍ ህንጻ ከመሰራቱ በፊት  (ምንጭ – Fasil & Gerard – Plate 58)

የኬዎርኮፍ ህንጻ የሚገኘው በዛሬዎቹ መሃትማ ጋንዲና ከኒንግሃም መንገዶች መገናኛ ላይ ነው። ህንጻው ከመሰራቱ ከ10 ዓመታት በፊት በቦታው ላይ አነስ ያለ የሳር ህንጻ እንደነበረበት (ባለ ጥንድ አሞራ ክንፉ ህንጻ እና ጎጆ ቤቶቹ መሀል ያለው) የዘመኑ ምስሎች ያሳያሉ።

በ1909 ግድም የተገነባው የኬዎርኮፍ ህንጻ ግድግዳው ጠቆር ባለ ግራጫ ጥርብ ድንጋይ (ከረጭ) የተሰራ ነው። በጊዜው የተገነቡት አንዳንድ ህንጻዎች (የግሪክ ቤተክርስቲያን፣ የአሁኑ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እና አራዳ ፖስታ ቤቶች) ይህንን ድንጋይ እንደተጠቀሙበት ይታያል። ጣራው ወፈር ካለ ቆርቆሮ፣ የጣራው ክፈፍና የመስኮቱ ፍሬም ደግሞ የእንጨት ሥራዎች ይታይባቸዋል። የባንኮኒው (በረንዳው) መደገፊያ ደግሞ ከብረት የተሠራ ነው።

picture-03
የመጀመሪያው ኬዎርኮፍ ህንጻ (ከፖስትካርድ የተገኘ)

የኮዎርኮፍ ህንጻ ውበት ሥነ-ቅርፃዊ (Sculptural) ነው ለማለት ያስደፍራል። እያንዳንዱ አካል (ማዕዘን፣ ጌጥ፣ መስኮት፣ ባንኮኒ…) ለብቻውም ሆነ በጋራ ሲታይ በጥንቃቄ ታስቦበት ለዓይን እንዲያረካ ሆኖ ተሰርቷል። የህንጻው ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታደሰ (አንዳንዴም እየተበላሸ) አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። እንዲያም ሆኖ ግን የመነሻ ቅርፁን ብዙም ሳይቀይር ከነውበቱ አሁንም አለ።

ህንጻው በአሁኑ ይዞታው ስናየው ከኋላው በ‘ረ’ ቅርጽ (L-Shaped) ትራፒዞይድ ይጀምርና ፊት ለፊቱን በክብ (Oval) ቅርጽ ይጨርሳል። የተሠራውም በ ሶስት መንገዶች መገናኛ ጫፍ ላይ በመሆኑ የመንገዱን መስመር ተከትሎ ተሰርቷል።

Capture
አካባቢ ፕላን

በመቀጠል፤ ለገለጻ እንዲመች ከላይ ባለው ፕላን እንደሚታየው ስድስት ቦታ (“ሕ1”፣ “ሕ2”፣ “ሕ3”፣ “ሕ4”፣ “ሕ5” እና “ሕ6”) እንከፋፍለዋለን

picture-06
የህንጻው ግንባታ  (ምንጭ – Fasil & Gerard – Plate 502)

በህንጻው ግንባታ ፎቶ ላይ እንደምንመለከተው ዙሪያውን በቅስት (Arched) መስኮቶች እና በሮች ተከቧል። በተመሳሳይ ጊዜ ይሠሩ እንጂ፣ የሕንጻው አራተኛ እና አምስተኛ ክፍሎች (“ሕ4” እና “ሕ5”) ራሳቸውን የቻሉ የተለዩ ሕንጻዎች እንደነበሩ ይታያል። ሕ5 (በአሁኑ ይዞታ ካስቴሊ ምግብ ቤት) ቀድሞ የእቴጌ ሱቅ ህንጻ የነበረ ሲሆን፣ በጣልያን ወረራ ጊዜ ሲታደስ የኬዎርኮፍን ህንጻ ተቀላቅሎ እንዲያገለግል ተደርጓል።

ስለዚህ፣ (በመጀመሪያ) አራቱን ኦሪጅናሌ የህንጻው ክፍሎች (ሕ1፣ ሕ2፣ ሕ3 እና ሕ6) እንመለከታለን።

የህንጻው መሀከለኛ ክፍል (“ሕ1”)

የፊት ለፊቱ የሕንጻ ክፍል (ሕ1) መጀመሪያው ፎቅ (Ground Floor) በግራና በቀኝ ሁለት ሁለት መስኮቶች ሲኖሩት፣ ክብ ቅርጹ የሚጋነንበት ቦታ ላይ ደግሞ ሶስት በሮች ይገኙበታል። ሁለተኛው ፎቅ (First Floor) ላይ “ሕ1”ን ባጠቃላይ የሚሸፍን ዙሪያውን ወጣ ያለ ባንኮኒ (Cantilever Balcony) ተሠርቷል። ሁለተኛውም ፎቅ ወደ ባንኮኒው የሚያመሩ ሰባት በሮች አሉት።

sketch-03
የሕ1 መስኮት በቅርበት

የዚህ “ሕ1” ህንጻ አጋጌጥ ስልት (Ornamentation) ከሌሎቹ የሕንጻው ክፍሎች በመጠኑ ለየት ያለ ነው። እስቲ በትነን (መስኮትና በር፣ ባንኮኒና ጣራ) እንመልከት።

በምስሉ እንደሚታየው፣ በሕንጻው መካከለኛ ክፍል የሚገኙት መስኮቶች (እያንዳንዳቸው) ለየራሳቸው በአንድ አንድ ቋሚ-መሳይ አምዶች (Rectangular False Columns) በቀኝና በግራ ታጥረዋል። ሁሉም በሮች በተመሳሳይ መልኩ በሁለት ቋሚ-መሳይ  አምዶች ታጥረዋል። በተጨማሪም፣ ከመስኮቱ ድጋፍ እስከ መሬት ያለው ቁመት በትንሹ ወደ ውስጥ ገባ በማለቱ መስኮቱን እንደ በር የሙሉነት መልክ (Illusion) አላብሶታል። ከመስኮቱ በታችም በልዩ ጌጥ የተቀረጸ ማስጌጫ ተሠርቶለታል።

sketch 04
የ “ሕ1” መስኮት ስር ማስጌጫ በቅርበት

ታዲያ ከሁሉም በበለጠ መልኩ የህንጻውን ባንኮኒ (በረንዳ) ለመሥራት ብዙ ጊዜ እንደፈሰሰበት አያጠራጥርም። ወጣ ወጣ ብለው ባንኮኒውን የተሸከሙት ድጋፎች (Beams) እያንዳንዳቸው ከውስጥ በጥምዝምዝ ቅርጽ አምረዋል። ጫፋቸውም በእንጨት መሰል ዲዛይን አጊጦ ደረታቸው በቅጠልያ ተሸልሟል። የባንኮኒውን የድንጋይ ሳንቃ (Slab) ከታች ወደላይ ስንመለከት እያንዳንዱ ክፍት ቦታ ውብ ቅርጽ ወጥቶለታል። ከላይም የባንኮኒው ድጋፍ (Rail) የብረት ባለሙያዎች ተጠበውበታል።

ባንኮኒው በቅርበት ሲታይ

የ”ሕ1” ሁለተኛ ፎቅ (First Floor) ሰባት በሮች ሙሉ ለሙሉ ወደባንኮኒ መውጫ ሆነው ያገለግላሉ። የዚህ ህንጻ ክፍል ጣራ ክቡን ተከትሎ በሰፊ ተዳፋት (Slope) ወደላይ ይቀጥላል።

የሕንጻው ግራ እና ቀኝ ክፍሎች (“ሕ2” እና “ሕ3”)

የህንጻው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ክፍሎች (“ሕ2” እና “ሕ3”) በግራና በቀኝ ከመሀሉ ክፍል (“ሕ1”) በትንሹ ወጣ ብለው ይጀምራሉ። ሁለቱም ክፍሎች የመንትያነት ጸባይ ቢኖራቸውም ቀረብ ብለን ስንመለከታቸው ልዩነታቸውን ማስተዋል ይቻላል። ይህ የመንትያነት ጸባያቸው ህንጻውን ባጠቃላይ ሚዛናዊ መንፈስ (Symmetry) ይሰጡታል። በሁለቱም በኩል የመሬቱ ስሪት ወደታች ዝቅ እንደሚል ታዲያ እናስተውል (የቀኙ ከግራው የበለጠ ዝቅ ይላልና)።

sketch 06
የ”ሕ3″ (ቀኝ) መስኮቶች አቀማመጥ ከእድሳት በፊት

ይህንንም የከፍታ ልዩነት የሕንጻው ጠበብቶች ሲፈቱት፤ በመጀመሪያ፣ የሕንጻውን አሠራር እራሳቸውን በቻሉ ሶስት ክፍሎች በመከፋፈል የመሬቱ ዝቅታ ልዩነት የሚፈጥረውን መጣረስ ለመቅረፍ ሞክሩ። በሁለተኛ ደረጃ፣ በቀኝ በኩል ላለው “ሕ3” ክፍል ዝቅ ያለበትን ያህል አንድ ሙሉ ፎቅ ጨመሩበት። በመጀመሪያው ፎቅ (Ground floor) ያሉት ሁለት ቅስት በሮች ወደታች ዝቅ እንዲሉ ተደረገ። ሁለተኛው ፎቅ ላይ ግን አራት መአዘን መስኮቶች በቅስቶቹ የአናት እርከን ላይ ተሰሩ። ይህም ከሕንጻው የፊተኛ ክፍል (“ሕ1”) መስኮቶች ጋር የመዋሐድ ስሜትን (Continuity) እንዲሰጥ አስበውበት ይመስላል።

picture-04
የ “ሕ2” [ግራ] መስኮቶች አቀማመጥ (ምንጭ – Martin Rikli Photographs)

በግራ ያለው “ሕ2” ግን አንድ ሙሉ ፎቅ ለመጨመር በቂ ቦታ ስላልነበረው ግማሽ ፎቅ (Mezzanine) እንዲጨመር አደረጉ። የበሮቹ እና መስኮቶቹ አቀማመጥም ልክ እንደ “ሕ3” (ከአራት መአዘን መስኮቶቹ በትንሹ ማነስ በቀር) ተመሳስሎ ተሰርቷል። የ“ሕ2” ሶስተኛ ፎቅ በሁለቱም ክፍሎች ሁለት ሁለት ቅስት መስኮቶችን ይዞ ከ”ሕ1” ሁለተኛ ፎቅ ጋር ተያይዞ የሚቀጥል ይመስላል።

የህንጻው “ሕ2” እና “ሕ3” ክፍሎች የአጋጌጥ ስልት ከ“ሕ1” በመጠኑ ይለያል። ይኸውም በቋሚ-መሳይ አምዶች (False Columns) ፋንታ በወጣ ገባ የድንጋይ አገነባብ ስልት (Quoins) መስኮቶች እና በሮች በመገንባታቸው ነው። ማዕዘኖች በተመሳሳይ ሁኔታ በወጣ ገባ ስልት አጊጠዋል።

እንዲሁም “ሕ2” እና “ሕ3” ከጣራው ተዳፋት ስፋት የተነሳ አንድ ተጨማሪ የጣራ ስር ፎቅ (Dormer Floor) ያስተናገዱ ይመስላል።

ለጣራቸውም (ከዋናው ጣራ በተጨማሪ) ለብቻው ወጣ ያለ አሞራ ክንፍ ጣራ (Intersecting Gable Roof) እና የጣራ መስኮት (Dormer Window) ተሠርቶለታል። ዙሪያውንም የጣሪያው ክፈፍ በእንጨት ስራ (Fascia Board Ornamentation) እንዲያጌጥ ተደርጎ ሁለቱም ጣራዎች በጉልላት (Finial) ተሸልመዋል።

picture-12
“ሕ2” ጣራ አሰራር በቅርበት (ከፖስትካርድ የተገኘ)
sketch 07
ከጣራው ክፈፍ ስር ያለው ጌጥ በቅርበት

ሶስቱም የህንጻ ክፍሎች በአንድነት እንዲታዩ በመጨረሻው ፎቅ ከጣራው ክፈፍ ስር ያለው ጌጥ (Entablature) ሶስቱንም ክፍሎች ይዞራል።

ከዚህም ሌላ፣ የህንጻውን ወገብ እና ግርጌ የሚዞሩት ተደራራቢ መስመሮች (Stone Bands) ሕንጻው በአንድነት እንዲታሠር ያደርጋሉ። በተጨማሪም፣ እያንዳንዱን ፎቅ የራሱ ማንነት ይሰጡታል። የ“ሕ1” ሁለተኛ ፎቅ በሮችና የ“ሕ2” እና “ሕ3” ሶስተኛ ፎቅ መስኮቶች በተመሳሳይ እርከን (Level) ላይ መሆናቸውና ቅስትነቱን መቀጠላቸው አንድነትን ይፈጥራል።

‘በህንጣ ላይ ህንጣ’ (“ሕ6”)

ከጣራው በላይ አንዲት ትንሽ ህንጣ ትታያለች። ይህችም ህንጣ፣ እንደ እንጎቻ የታችኛውን ሕንጻ ክፍል ተመሳስላ በትንሹ ተሠርታለች። ልክ እንደ ዋናው ሕንጻ መሀከለኛ ክፍል (“ሕ1”) ክብ ቅርጽ አላት። በግራና በቀኝ ደግሞ ትንሽ ወጣ ያለ አሞራ ክንፍ ዝንቦ ጣራ (Mini-Gable Roof) ሳታስቀር ህንጻውን ከአናቱ ትጨርሰዋለች። ይህች ህንጣ አመታት ባለፉ ቁጥር ስትቀያየር ከርማለች።

sketch 10
በህንጣ ላይ ህንጣ

(በክፍል ሁለት ይቀጥላል…)

አለቃ ታየ እና የዘመኑ ደራሲዎች

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 2)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል አንድ የቀጠለ)

 

ዘመነ ቴዎድሮስ

አማርኛ ከዚህ በላይ ባመለከትነው አኳኋን ሲጐላደፍ ቆይቶ ፫ኛ ብለን ወደ ሰየምነው ዘመን ይደርሳል። ይሁን እንጂ ፪ኛ ብለን ከሰየምነው ዘመን አካሔድ፣ በጭራሽ ነፃ ወጥቶ ደራሲ የሆነ ሁሉ ግዕዝ ባልተቀላቀለበት አማርኛ ብቻ መጻፍ የጀመረ አሁን በቅርቡ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው።

ነገር ግን ፊተኛ ሆኖ ንጹሕ በሆነ አማርኛ የተጻፈው መጽሐፍ የአጤ ቴዎድሮስ (1847-1860 ዓ.ም) ታሪክ ነው። ደራሲው ያጤ ቴዎድሮስ ጸሐፌ ትእዛዝ አለቃ ዘነብ የተባለው የሸዋ ሰው ነው። የሞተበት ዘመን ለማወቅ አልተቻለኝም፤ ነገር ግን በ1880 ዓ.ም ግድም ወደ ትግሬ ሁኖ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ሲጻጻፍ እንደ ነበር እርግጥ ነው።

“የቴዎድሮስ ታሪክ” በአለቃ ዘነብ
woldemariam-book
“የቴዎድሮስ ታሪክ” በአለቃ ወልደማርያም

እንደዚኸው ሁሉ፣ ባጤ ቴዎድሮስ ዘመን የነበረ የሸዋ ሰው፣ አለቃ ወልደማርያም፣ አጤ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ ታሪካቸውን ባማርኛ ጽፏል። ሁለቱም ባለታሪኮች የሚመሰገኑበት፣ ፊተኞች ሁነው በተቻለ መጠን አጣርተው ባማርኛ መጻፋቸው ነው። ቃል ለማሳመር እንኳ ብዙ ባይጣጣሩ፣ ግዕዝ ሳይጐትታቸው፣ አማርኛን ራሱን እያስቻሉ ከተፈጥሮ በተቀበለው ጠባይ አስኪደውታል።

አጤ ቴዎድሮስ አእምሮዋቸው በትክክል ባልሠራበት ሰዓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ያወረዱት ጭካኔ፣ እንዲሁም ከ1792 ዓ.ም ጀምራ በብዙ መሳፍንት ስትገዛ ለነበረችው ኢትዮጵያ ባንድ ንጉሠ ነገሥት እንድትስተዳደር፣ በእርሻና በንግድ፣ በትምህርትና በአስተዳደርም እንድትሻሻል የነበረባቸውን ድካም ብዙ ነበር። ይኸውም ሥራ ጀማሪው እርሳቸው ሁነው፣ ለወደፊት ሊከታተሉት የሚገባ ሰፊ ፕሮግራም መሆኑን ባለታሪኮቹ በሚገባ መጠን አልተገነዘቡትም። ስለዚህም ካጻጻፋቸው ላይ ደህና አድርገው አላጐሉትም። ግን ደግሞ በሰላም መኖርን ልምድ አድርጎ የኖረ ሕዝብ፣ ሳያስበው እንደ መብረቅ መዓት ያወረደበትን ንጉሥ ደግነቱንና ጨካኝነቱን ለማመዛዘን ባይቻል አይፈረድበትም።

fitegnayitu
የአለቃ ዘወልድ (ፍስሐ ጊዮርጊስ ዐብየ እግዚ) መጽሐፍ

የተወለደበትንና የሞተበትን ዘመን ለማወቅ ያልተቻለኝ አለቃ ዘወልድ በ1891 ዓ.ም አቅራብያ “ፊተኛይቱና ኋለኛይቱ ኢትዮጵያ” ብሎ ሰይሞ ከዚህ በፊት በግዕዝና ባማርኛ ታሪክ ከጻፉት ደራሲዎቻችን በተለየ አስተያየት ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ጽፏል።

አቶ ዐፅመ ጊዮርጊስ ገብረ መሲሕ

asme-giyorgis
በጦር ልብስ ያጌጡት ዐፅመ ጊዮርጊስ

አቶ ዐፅሜ (+1907) የሸዋ ሰው ናቸው። ስለ ኦሮሞዎች የጻፉት ታሪክ እንግዲህ ወደ አርባ ዓመቱ ተቃርቦታል። ኦሮሞዎች ወደ መሀል ኢትዮጵያ የመጡበትን ዘመንና አኳኋናቸውን ለመግለጥ በብዙው ደክመውበታል። አፈ ታሪኩን በብዙ ሥፍራ አጣርተውታል። ደግሞም በጻፉበት ዘመን የኤውሮጳ ሊቃውንት ስለ ኦሮሞዎች ታሪክ ማጣራት የጀመሩትን አንዳንድ ጊዜ መሠረት አድርገውታል። ከኤውሮጳ ትምህርት ቤት በጣም ርቆ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ፣ በዚያ ዘመን ከርሳቸው በበለጠ አገላለጥ መጻፍ ይገባው ነበር ለማለት አይቻልምና ካገላለጣቸው አንዳንዱ ትክክለኛ ሁኖ እንኳ ባይታይ፣ የመጽሐፋቸው ረዳትነት የማይካድ ነው።

በካቶሊክ ሃይማኖት ያዲሱ ትውልድ ዘመን ሰው ስለነበሩ ለሃይማኖታቸው የነበረባቸው ቅንዓት በኦርቶዶክሳዊው ወገን ላይ ምክንያት ባገኙ ቍጥር ከልክ ያለፈ የተግሣፅ ቃል አስጽፏቸዋል። አንዳንድ ጊዜም ታሪኩ መንገድ ሳይሰጣቸው በኦርቶዶክሳውያን ላይ የኃይል ቃል ለመጻፍ ምክንያቱን በግድ ፈልገው ያመጡት ይመስላል። ከዚህ በቀር ባገራችን በነበሩበት ዘመን የባለ ታሪክ ስም የተገባቸው ደራሲ ናቸው።

አለቃ ታየ ገብረማርያም

አለቃ ታየ (+1916) በጌ ምድሬ ናቸው። በኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ተምረው የጨረሱትን እንኳ ለማወቅ ባይቻል የስብከትና የድርሰት ስጦታ እንደነበራቸው የታተሙትና ያልታተሙት መጻሕፍቶቻቸው ይመሰክሩላቸዋል። እርሳቸውም ለፕሮተስታንት ሃይማኖት አዲስ ምእመን ነበሩና የያዙትን ሃይማኖት እውነተኛነት ለማስረዳት “መዝገበ ቃላት” የሚባል መጽሐፍ ጽፈዋል።

በዚህ መጽሐፍ ጦርነት ያነሡበት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋራ የማይስማማ ሁኖ የታያቸውን፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ባገራችን ውስጥ ያለውን ልዩ ልዩ ባህል፣ እንደዚኸውም ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በፕሮተስታንት አካሔድ ባልተመለከተ የሊቃውንትና አዋልድ በምንላቸው መጻሕፍት ላይ ነው። በመዝገበ ቃላቱ እንደ አቶ ዐፅሜ ያለ የዘለፋ ቃል የለበትም። ቢኖርም መጽሐፉ የተጻፈ ለታሪክ ሳይሆን ለሃይማኖት ማስረጃ ነውና ሥፍራው ነው ያሰኛል። መጽሐፉ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ቢጻፍም ንግግሩ አብዛኛውን ጊዜ ሰው የማያስቀየም የሊቅ አነጋገር ነውና ስለ ሃይማኖት ክርክር ለሚጽፍ ሰው አብነት የሚሆን ነው።

aleqa-taye
አለቃ ታየ ገብረማርያም

አለቃ ታየ ከጥንት እስከ 1910 ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክም ጽፈዋል። መጽሐፉ ባለመታተሙ ከጥቂቶች ሊቃውንት በቀር የመረመረው የለም። “መዝገበ ቃላት”ና ይህ ታሪክ ጠላት አገራችንን ከወረረው ወዲህ (1928-1933) የደረሱበት አልታወቀም።

ሕዝቡ የሚያነበው አለቃ ታየ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከብዙው በጥቂቱ የጻፉትን ነው። በዚህ መጽሐፍ መሠረት አድርገው የሚከታተሉት ፩ኛ መጽሐፍ ቅዱስን፣ ፪ኛ በኢትዮጵያ ስለ ታሪክ የሚናገሩትን መጻሕፍትና ከሁሉ ይልቅ ክብረ ነገሥትን፣ ፫ኛ የግሪክን፣ የላቲንን፣ የዓረብን ሊቃውንት፣ ፬ኛ በዛሬ ዘመን በኤውሮጳ የተጻፉትን ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የቀድሞ ሰዎች ባስተዋሉት መንገድ ስለ ተከለተሉት መንፈሳዊውን እንጂ ታሪካዊውን ጥቅሙን በጭራሽ አላገኙትም።

እንደዚኸው ሁሉ፣ ክብረ ነገሥታችንንና የቀሩትን የኢትዮጵያን መጻሕፍት የግሪክንና የላቲንን፣ የዓረብን፣ እንዲሁም የአውሮጳ ሊቃውንት አጣርተው የደረሱበት ፍጻሜ ከነወሬው ሳይደርስላቸው ቀርቶ ቃል በቃል ተከታትለውታል። በቅርብ ዘመንና ዛሬውኑ በኤውሮጳ ስለ ኢትዮጵያ መሠረት ባለው አካሔድ የገለጡትን ሊቃውንት ግን ያንዳንዶቹን እንኳ ስማቸውን ቢጠሩ ከነዚሁ ሊቃውንት አሳብ አንድዋ ከጆሮዋቸው እንዳልደረሰች መጽሐፋቸው ድንቅኛ አድርጎ ይመሰክራል። በሊቃውንቶቹ ፈንታ የታሪክ ሊቃውንት መስለዋቸው ከኤውሮጳ ከዲፕሎማሲና ከጋዜጣ መልእክተኞች ያንዳንዱን አሳብ ተከትለዋል። ይህ ሁሉ ቢሆን በሃይማኖት እንዳደረጉት በታሪክ ደግሞ እውነት ሆኖ በታያቸው አሳብ አንዳች ሥጋት ሳያድርባቸው በቅንነት አሳባቸውን ያስታወቁ ሰው ናቸው።

ነገር ግን ኅሊናቸው የተረዳውን የሚቃወም ታሪክ ሲገጥማቸው፣ ባንደበታቸው ጥራት መጠን ማስረጃ መስጠትን ያህል፣ “የልጆች ጨዋታ የባልቴት ተረት” እያሉ አልፈውታል። እንዲህ ከሚሉት አብዛኛውንም ተረት ነው ቢሉት የተገባ ነው። ነገር ግን የሚናገርና የሚጽፍ ሰው፣ የማይስማማውን አሳብ ተረት እያለ ቢሔድ፣ ሰሚና አንባቢ ደግሞ ማፍረሻውን አስረዳን ማለት እንዳለባቸው አለመዘንጋት ነው። እንዲሁም ለታሪክ ጻፊ እውነት ሁኖ ከሚታየው አንዳንዱ ለሰሚው ግራ ሁኖ የሚታየው ይኖር ይሆናል። ባለታሪክ በእንዲህ ያለው ጊዜ፣ የሚመታውን መላ ወይም ታሪኩን የሚመሠርትበትን ማስረጃ ማመልከት ዋና ሥራው ነበር።

taye-book

በዚህ ፈንታ አለቃ ታየና እስከ ዛሬ ከተነሱት ታሪክ ጸሐፊዎች አንዳንዶቹ፣ አንባቢው ሳይረዳው እነርሱ ለብቻቸው የተረዱትን “እንደ ሃይማኖት ተቀበሉ!” ይላሉ። ያልተረዱትን አሳብ ደግሞ፤ “እኛ ተረት ካልነው አትቀበሉት!” ብለው የሚያዙ ሁነው ይታዩናል። አንዳንድ ጊዜ ማስረጃ ብለው የሚያመጡት ንግግር ግን ከዚህ በፊት እንዳልኩት የታሪክን አካሔድ ያጣሩትን ሊቃውንት ሥራ ዙረው እንዳላዩት ንግግራቸው ያስረዳል።

ይሁን እንጅ የመጽሐፍ አካሔድና መልክ ላለው ሥራቸው፣ ለመጽሐፍ አጻጻፍም ንድፍ በመስጠታቸው ለአለቃ ታየና በዚህ ጽሑፍ ስማቸውን ለማነሳቸው ደራስያን ሁሉ ያገራችን ሕዝብ ባለወረታቸው ነው።

(በክፍል ሶስት ይቀጥላል …)