የግዕዝ ሊቃውንት እና አዲሱ ዘመን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 5)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል አራት የቀጠለ)

 

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትውልዳቸው ሸዋ ትምህርታቸው ጎንደር ነው። ዕድሜያቸው 60 ዓመት ይሆናል። በኢትዮጵያ መጻሕፍት ካላቸው ከሰፊው ዕውቀታቸው በላይ፣ ላገራችን መጻሕፍት ምሥጢርና ታሪክ አስፈላጊ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ዕብራይስጥ ጨምረውበታል። የሕዝቅኤልን ትንቢት ዕብራይስጡን ወደ አማርኛ ገልብጠው ባማርኛ የጨመሩበት መግለጫ፣ ከሁሉ በፊት ላገራችን ሊቃውንት ከግሪክ ተተርጕሞ በግዕዝ ተቀብለውት የሚኖሩትን የብሉያትን መጻሕፍት፣ ዋናውን አብነት ዕብራይስጡን እያዩ ማቃናት እንዳለባቸው አነቃቅተዋቸዋል። ዳግመኛ ትምህርቱም መጠነኛ ቢሆን አማርኛ ያወቀ ሁሉ ሊያስተውለውና ሊያጣጥመው በሚችል ንግግር በመግለጣቸው ተራውን ሕዝብ ሳይቀር ከሊቃውንቱ ዕውቀት እንዲካፈል አድርገውታል። እግረ መንገዳቸውንም ልዩ ለሆነው ከባድ ዕውቀት፣ ልዩ የሆነና ያጌጠ አማርኛ ፈጥረውለታል።

kidane-photo

እርሳቸው ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት ኢየሩሳሌም ሒደው ዕብራይስጥ የተማሩበት ዘመን የነበረውን ችግር ያስተዋለ ሰው ብቻ ድካማቸውን ሊመዝነውና ሞያቸው ትልቅ መሆኑን ሊረዳ ይችላል። ፍቅርና አንድነት በተሰበከበት አገር በኢየሩሳሌም ጠብና መለያየት ተዘርቶበት ነበር። ዛሬውንም ገና አላለፈበትም። ከዚያ የነበረው የኢትዮጵያ መነኮሳት ማኅበር፣ ከጸሎት በቀር፣ ትምህርት መቀጠል የማያስፈልግ ሥራ ሁኖ ሲታየው፣ እስራኤላዊ ደግሞ በዓለም ያለ ሕዝብ አሥር ቢማር እንደማያፈቅረው ተረድቶት ቋንቋውን ሊማርለት የመጣውን ክርስቲያን መርዳት፣ እባብን ከመቀለብ ይቆጥረው ነበር። ስለዚህም አለቃ ኪዳነ ወልድ ዕብራይስጥ የተማሩት በሁለት ፊት ሥቃያት እያዩ ነው። ይህ ሁሉ ድካማቸው በክርስቲያን ሊቃውንት ጭምር ስለ ብሉያት መጻሕፍትና ታሪክ ያመጡትን አዲስ መግለጫ ለመከታተል ቢቸግራቸው፣ አማርኛው ከተሰናዳው መግለጫቸውም በክርስቲያንነታቸው የጸኑት ሊቃውንት ከደረሱበት የታሪክና የትርጕም አዲስ አካሔድ ለመድረስ ቢያቅታቸው አይፈረድባቸውም።

kidane-hizqel

የኢትዮጵያን የጥንቱን ትምህርት ከሚያውቁት ሊቃውንት አማርኛንና ግዕዝን ለማጣራት፣ ያለቃ ኪዳነ ወልድን ያህል የሚደክም ብዙ አልተገኘም። አማርኛ ለግዕዝ ልጁ በመሆኑ፣ ከግዕዝ የተቀበላቸውን ቃላት ልክ እንደ ግዕዝ አድርጎ መያዝ አለበት የሚል አሳብ ስላለባቸው፣ ይህንኑ ውሳኔ ለመግለጥ የታተመና ያልታተመ ብዙ መጽሐፍ ጽፈዋል። አሳባቸውን ተቀብሎም ለማስተዋል የሚጣጣር በያገሩ ብዙ ደቀመዛሙርት አውጥተዋል። ሠላሳ ዓመት ያህል የደከሙበት ዋናው መጽሐፋቸው ግዕዙን ባማርኛ የሚተረጕም መዝገበ ቃላት ነው።

ጠላት አገራችንን በወረረበት ዘመን እርሳቸው ሲታሠሩ ሲጋዙ ያን ያህል የደከሙበት ሥራ የሚከውነው አጥቶ የብልና የምስጥ ምግብ ሁኖ መቆነጻጸሉ ጕዳቱ የራሳቸውና የመላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወሰን ሳያግደው ሰንደቅ ዓላም ሳይለየው፣ ወገን ለሆነው በዓለም ላለው የትምህርት ወዳጅ ለሆነው ሰው ሁሉ ነው። ከሰው ተለይተው፣ ፈቃድ አጥተው ሲኖሩ ሳለ ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ከችግር አስጥለዋቸው የነበሩ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ዛሬም ንጉሠ ነገሥታችን የኢትዮጵያን አልጋ መልሰው ሲይዙ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድን አስፈልገው የዕለት እንጀራቸውን በመዓርግ እንዲያገኙና ያቋረጡትን ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋልና ፈቃዱ ሁኖ የኢትዮጵያ ወጣቶች የግዕዝን ቋንቋ ከሥር እስከ መሠረቱ ለማወቅ ከገዛ አገራቸው ሊቅ በተጻፈው መዝገበ ቃላት ይመረምሩታል እያልን ተስፋ እናደርጋለን።kidane-dictionary

የግጥም ባሕል

በግጥም ወይም ቤት ሳይመታ፣ ቃሉ ያላጋደለ፣ የተመዛዘነ በሆነ ንግግር አሳብን መግለጥ፣ ሰው አንደበት ከፈታ ጀምሮ የነበረ ልማድ ነው። በጽሕፈት ያልገባው ያገራችን የጥንት ወግና ታሪክ፣ ብዙ ግጥም አለበት። ሌላ የቀድሞ ሕዝብ የቤተ መንግሥቱን ሕግ ሳይቀር ቤት እያስመታ ጽፎ፣ በተማሪ ቤት በዜማ እንዲማሩት አድርጓል። በኢትዮጵያ ማናቸውንም የግዕዝ መጽሐፍ ስንኳ በዜማ ማንበብ ልምድ ቢሆን፣ ሕግን በግጥም መጻፍ አልተለመደም። ነገር ግን ቤት የሚመታ የሕግ ዓይነት ምሳሌ አይጠፋም። “ይካስ የበደለ፣ ይሙት የገደለ”፣ “ያባት ዕዳ ለልጅ፣ ያፍንጫ እድፍ ለእጅ”፣ “አልሞት ባይ፣ ተጋዳይ”።

ይህንንም የሚመስል ባንድ ፊት ምሳሌ፣ እግረ መንገዱን ደግሞ ሕግ ሁኖ የሚጠቀስ፣ ቤት የሚመታ ብዙ ንግግር አለ። በቀድሞ ዘመን አንዳንድ ጊዜ ከሳሽና ተከሳሽ ተከራክረው ሲጨርሱ፣ አጭር ሁኖ ቤት የሚመታ ንግግር ጉዳያቸውን ለዳኛ ያቀርቡ ነበር። ከትችት ላይ ዛሬውንም ቢሆን በግጥም የሚተች አለ። የበገናና የመሰንቆ፣ ልዩ ልዩ ዝማሬ፣ ባላገሩ ለአምላክና ለድንግል ማርያም፣ ለመልአክና ለጻድቅ የሚያቀርበው ልመናና ምስጋና በግጥም ነው። ቀረርቶና ዘፈን፣ እንጕርጕሮና ልቅሶ ሁሉም በግጥም ነው።

ነገር ግን ልዩ ልዩ ሕዝብ ፊት አስቀድሞ ቤት እየመታ ወይም በሕግ በተወሰነ ሚዛን አሳቡን የሚገልጥበትን ጽሑፍ ሥራው ሲደራጅ፣ ባገራችን ጽሑፍ ሥራ ግጥም የኋሊት ቀርትዋል። ስለሆነም አሁን በቅርቡ ጊዜ ብዙዎች ሰዎች በግጥም መጻፍ ጀምረዋል። አብዛኛው ስላልታተመ ስለ አማርኛ ግጥም ብዙ የምናመለክተው የለንም።

ያሳተሙትና ያላሳተሙት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች በግጥም የሚገልጡት አሳብ አብዛኛውን ጊዜ ምክር ነው። የሰውን ኀዘንና ደስታ የሚገልጠው እጅግ በጥቂቱ ሁኖ፣ የወንድንና የሴትን ፍቅር የሚያነሳ በጭራሽ የለበትም። የጣልያኖች ወረራ፣ ስለ አገርና ስለ ንጉሠ ነገሥት ፍቅር፣ ዓመፀኝነት ስለሚሠራው ግፍ፣ ስለነፃነትም ናፍቆት በግጥም የሚያናግር አሳብ ቀስቅስዋል። የተጻፈው ገና ስላልተመረመረ፣ የሚያምረውን ከማያምረው ለመለየት ለጊዜው አልተቻለኝም።

ስለ አማርኛ የቅኔ ባሕርይ ግን ከዚህ በፊት እንዳመለከትነው፣ ብዙ “ስለምን” ወይም “አማርኛ” ይወዳል። አብዛኛውን ጊዜ አያሌውን መስመር ባንድ ፊደል ቤት ያስመታል። አንዱን መስመር በሁለት ሐረግ ከፍሎ፣ ላንዳንዱ ሐረግ ፮፣ ለሁለቱ ሐረግ (ላንዱ መስመር) ፲፪ ፊደል ይሰጣል። ፊደል ሲቆጥር አብዛኛውን ጊዜ እንደ ዕብራይስጡ ቅኔ ሳድሱን ከሌለ ይቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሳቡና በንግግሩ ስንኳ ቅኔ ወዳጅና ቅኔ ፈጣሪ ሁኖ ቢታይ፣ ባማርኛ እስከ ዛሬ ጽፈው ካሳተሙት ግጥም ገጣሚዎች፣ ትዕግሥት ሰጥትዋቸው፣ ሽሕ መቶ ሽሕ መሥመር የጻፉና ያሳተሙ ያሉ አይመስሉንም። በርከት አድርጎ የጻፈ ቢኖርባቸው ለፍርድ ይመች ነበር።

ወጣቱ ከበደ ሚካኤል

ይሁን እንጂ አጭርም ቢሆን፣ እኔ ለራሴ ሥራቸውን የማደንቅላቸውና የማመሰግንላቸው ብዙ ወጣቶች አሉ። ከነዚህም አንዱ ከበደ ሚካኤል ነው። ቅኔ፣ ምሳሌ፣ ተረት ከውጭ አገር ደራሲ (ከፈረንሳይ) በሚተረጕምበት ጊዜ አሳቡና ንግግሩ አማርኛ ሁኖ ከተረጐመበት ቋንቋ ጋር ሲያስተያዩት አንዳንድ ጊዜ ተወዳዳሪው፣ አንዳንድ ጊዜም አርሞ ያቃናው ሁኖ ይገኛል።

ምክንያቱን ከራሱ አፍልቆ የሚፈጥረው ግጥም ከልብ የወጣ ከልብ ይገባል እንደተባለው ሁሉ፣ ልብን የማይነካ የሚገኝበት ሁኖ አልታየኝም። አብዛኛውን ጊዜ ካገራችን ባለ ቅኔዎች ግዕዝን ወይም የውጭ አገርን ቋንቋ እጅ ያደረጉ ሲሆኑ ወደዚያው እየሳባቸው ንግግራቸውን ለማስተዋል እንቸገርበታለን። ወይም ደግሞ፣ ሌላ ባለ ግጥም ያወጣውን ንግግር፣ አማርኛው ካማረ ብለው ያለ ቦታው ሲጥሉት ቅር ያሰኛሉ። “ስለምን” ያልሁትን ንግግር አምጥተው አንባቢ በቶሎው እንዳያስተውለው ያደረጉ እንደሆን፣ ሰው ሊያስተውለው ያልቻለ ጥልቅ ጥበብ የተገለጠላቸው ይመስላቸዋል። ከበደ ሚካኤል፣ ሌሎች ካበጁት ወይም ከውጭ አገር ንግግር ሳይጨምር በራሱ አማርኛ፣ ሁሉም ሊያስተውለው የሚችል አገላለጥ በመምረጡ ለወደፊት ለሚነሱት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች አብነታቸው ለመሆን ተስፋ የሚያስደርግ ልጅ ነው።

kebede-berhane-hilinakebede-nibab

ማጠቃለያ

ለንግግራችን ፍጻሜ ስንሰጥም ደግመን የምናስታውሰው፣

  1. በአማርኛ መጻፍ ከጀመርን ስድስት መቶ ዓመት ስንኳ ቢሆን፣ በብዙው የተጻፈበት ዘመን ከ1600 ዓ.ም. በኋላ መሆኑን።
  2. ከ1600 ዓ.ም. ጀምሮ ባማርኛ የሚጻፈው አብዛኛው የሃይማኖት መጽሐፍ ሁኖ ከንግግሩና ከአሰካኩ ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ ብዙ አካሔድ እንደነበረበት፤ ይህንም የአጻጻፍና የንግግር አካሔድ ዛሬውን ሳይቀር አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደሚከተሉት።
  3. አማርኛን ራሱን አስችለው መጻፍ የጀመሩት ደራስያን በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን (1847-1860) መሆኑን ጭራሽ እየተጣራ የሔደበት ግን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን።
  4. አማርኛ ጽሑፍ ሥራውን በግጥም ጀምሮ፣ ይኸው የግጥም ሥራ ዛሬ የኋሊት መቅረቱን።
  5. የዛሬ ዘመን ደራስያን ከሚጽፉት አብዛኛው መጽሐፋቸው የታሪክና፣ የሃይማኖት፣ የልብ ወለድ ታሪክም መሆኑን፣ የሁሉን አሳብ ትምህርትን ሥራንና ልማድን እያሻሻሉ መሔድ ዋና መሆኑን።
  6. የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍጥረቱ የቅኔ መንፈስ ያደረበትና በግጥም አሳቡን እንደገለጠ መኖሩን፣ ሙግቱንና ትቹን ሳይቀር በግጥም ማምጣት ልማዱ መሆኑን በዚኸውም የተፈጥሮ ልማዱ ቤት እያስመታ የሚሔድ ደራሲ በብዙው መገኘቱን፣ ነገር ግን ባማርኛ ያወጣውን ግጥም ያሳተመ ደራሲ ጥቂት መሆኑን ነው።

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም

7 thoughts on “የግዕዝ ሊቃውንት እና አዲሱ ዘመን

  1. ጊዜ የማይሽራቸው የትውልድ ቅርሶች! በጠንካራ አለት ላይ የተገነቡ! ስለ አሁኑ ለመናገር ያለፉት የጣሉትን መሠረት ማየት በእጅጉ ተገቢ ነው! ተዝቆ የማያልቅ የጥበብ ሀብት! የማይደበዝዝ አሻራ! በርቱ

    Like

  2. ያወቃችሁትን አሳውቁን ከተቻለ በፒዲኤፍ የምናገኝበትን አግባባቡ ብታመቻቹ። አሀንም ድንቅ ናችሁ።

    Like

  3. Thanks ‘Andemtas” for letting me to know all those who had done their part in the past. And, in fact, they done pretty job. Keep it up Andemtawoch, glad I found you!

    Like

  4. ቤተ እስራኤላዊ ፕሮፌሶር ተአምራት አማኑኤል ነ/ይ. የቤተ እስራኤላውያን ታላቅ መሪ ነበሩ። ለኢትዮጵያም በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። ስለ እሳቸው የሕይወት ታሪክ በዕብራይስጥ ቋኑቋ መጽሐፍ ለማሳተም ጥናት እያደረኩ ነው። ስለ እሳቸው ማንኛው መርጃ ያለው ወይም የሚያቅ ሰው፡ ብታካፍሉኝ ደስ ይለኛል

    Like

አስተያየት ለመስጠት