ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን
በተአምራት አማኑኤል
(ክፍል 1)
.
የጥንቱ የኢትዮጵያ አፈ ታሪክ “አንድ ሽሕ ዓመት ያህል ከልደተ ክርስቶስ በፊት፣ ባገራችን ሊቃውንትና መምህራን ነበሩበት … እስከ ዛሬ ድረስም ሊቅ፣ መምህርና ደራሲ አልጠፉበትም” ይላል። ቢሆንም አፈ ታሪኩ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከብሉያት በቀር ሌላ ዓይነት መጻሕፍት መኖር አለመኖራቸውን አያመለክትም።
አፈ ታሪካችን በሰሎሞን ዘመን ከሕዝበ እስራኤል ጋራ ግንኙነት እንደነበረን፣ ንግሥተ ሳባ ዛሬ ኢትዮጵያ (ሐበሻ) የምንለውንና ከዓረብ አገር የደቡቡን ክፍል ትገዛ እንደነበረች፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ሒዳ ከሰሎሞን ጋር ተዋውቃ ከርሱ ቀዳማዊ ምኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ እንደወለደች፣ ቀዳማዊ ምኒልክም እስከ ዛሬ ድረስ ላሉት ነገሥታቶቻችን አባት መሆኑን፣ እርሱም አባቱን ሰሎሞንን ለማየት ሒዶ ከኢየሩሳሌም ሲመለስ፣ ጽላተ ሙሴንና እስከ ሰሎሞን ዘመን ከእስራኤላውያን የተጻፉትን መጻሕፍተ ብሉያትን ይዞ እንደመጣ ይነግራል።
ይህን አፈ ታሪክ የሚነግሩ መጻሕፍት ባገራችን መጻፍ የጀመሩት ከ1300ኛው ዓመተ ምሕረት ወዲህ ነው። ሽሕ ዓመት ከዚያ በፊት ለሕዝቡ ወንጌል ተሰብኮለት ነበር። በሽሕ ዓመት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ፣ በአሕዛብነት የነበረበትን ዘመን እንዲጠየፈው፣ የሕዝበ እሥራኤልን መጻሕፍትና አሳብ እንዲወድ አድርጎት ስለ ነበረ፣ ጥቂት በጥቂት የገዛ ራሱን ታሪክ እየዘነጋ፣ የእስራኤል ልጅ ነኝ ከማለትና የእስራኤል ሕዝብ የጻፋቸውን መጻሕፍት፣ አያቶቼ የጻፏቸው ናቸው ከማለት ደርሷል።
በሰሎሞን ዘመን የእስራኤልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ኖሯቸው ይሆናል ቢባል፣ ማስረጃው እንኳ ባይገኝ፣ ሳይሆን አይቀርም በማለት በተቀበልነው። በሰሎሞን ዘመን ከብሉያት መጻሕፍት አንዳንዶቹ እስከ ኢትዮጵያ ደርሰው በዚያው ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀብሎ የሃይማኖት ሥራ አስይዟቸዋል ለማለት ግን ማስረጃው እስኪገኝ ድረስ ልብ ወለድ የመጣ አሳብ ነው እንላለን።
የዛሬው ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሙሴ የሚባሉት አምስቱ ብሔረ ኦሪት ተሰብስበው ባንድነት መገኘት የጀመሩት በሰሎሞን ዘመን ብቻ ነው ይለናል። የዚህ ክርክር ገና ሳይጨረስ፣ አፈ ታሪካችን፤ “መጽሐፈ ኦሪት በሰሎሞን ዘመን ካገራችን ደርሰው ነበር” ሲል፣ ለራሱ ክብር በመጓጓት፣ ታሪክ ጥሶ የተራመደ ሁኖ ይታየናል። ይህም ከወገን ለጊዜው የበለጠ መስሎ የታየውን እየመረጡ “ወገኔ ነው” ማለት፣ የዛሬ ሳይሆን የጥንት፣ የኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የደረሰና፣ ታሪክ ተመርምሮ ወሬው ትክክለኛ አለመሆኑ ሲታይ የሚቀር ነው።
በግሪኮች ሥልጣኔ ንጹሕ ቅናት ያደረባቸው ሮማውያን፣ የግሪኮች መዓረግ ተካፋይ ለመሆን፣ የ”ኤኔአ”ን ተረት ፈጥረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕዝበ እስራኤል የተነገረው ሁሉ ደስ ሲያሰኛቸው ከነበሩት እንግሊዞች፣ አንዳንዱ ባለ ታሪክ፣ “ስደት የሔዱት የአስሩ ነገደ እስራኤል የልጅ ልጆች ነን” ሲል ነበር። ዛሬ ግን፣ ሮማውያንም ከግሪኮች ጋር ዝምድና እንኳ ቢኖራቸው፣ ባለ ታሪክ ሌላ ማስረጃ ያመጣል እንጅ የ”ኤኔአ”ን ተረት መሠረት አያደርገውም። የባለ ታሪክ ስምና መዓረግ ያለው ሰው ደግሞ፣ “በእንግሊዝ ደሴቶች ከምሥራቅ የመጣ ሕዝብ ሰፍሮበት ኑሮ ይሆናል” እንኳ ቢል፣ “አንግሎ ሳክሶን የአስሩ ነገደ እስራኤል ልጆች ናቸው” አይልም።
እንደዚኸው ሁሉ የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲሱ የምርመር አካሔድ የሚከታተል ሰው፣ ታሪኩን በሌላ መንገድ ያስረዳል እንጂ፣ ስለ ንግሥት ሳባና ስለ ሰሎሞን የሚነገረውን መሠረት አያደርግም። ስለዚህም ከልደተ ክርስቶስ በፊት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ኑረው እንደሆነ የደረሱበትን ለማወቅ ቸግሮናል እንላለን እንጅ (ሕዝበ እስራኤል በሰሎሞን ዘመን የሙሴን መጻሕፍት መሰብሰብ ገና ሲጀምር) እነዚህ መጻሕፍት ድሮ ባገራችን ነበሩ ለማለት ይቸግረናል።

ጽሑፍ ሥራ በኢትዮጵያ ገና ከልደተ ክርስቶስ በፊት ተጀምሮ ነበር እንላለን። ማስረጃው ግን በጣም ችግር ነው። እርግጥ የምናውቀው ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን አቅራብያ በትግሬ አውራጃ ከሐውልትና ከጸሎት ቤት የተጻፈ አንዳንድ ቃል መገኘቱን ነው። ቀደምት የተባሉት ጽሕፈቶች የሚገኙት በሳባና በግሪክ ቋንቋ ነው። ከክርስቶስ ልደት በኋላ 300ኛው ዘመን ሲጀምር ግን፣ ጽሕፈቱና ንግግሩ የተጣራ፣ በግዕዝ ቋንቋ ከሐውልት ላይ የተጻፈ መታሰብያ አለ። ስለዚህም ከሊቃውንት አንዳንዱ እንዲህ ይላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፣
ፊት፤ ግሪክ፣
ቀጥሎ፤ ሳባ፣
ኋላ፤ ግዕዝ

ለዚህ አሳብ ብዙ ተቃራኒ አልተነሣበትም። ነገር ግን ገና የመንን ሳይለቅ ባገሩ ቋንቋና ፊደል ሲጽፍ የነበረ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለምን በግሪክ ጻፈ? ደግሞም እስከ ዛሬ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ሥራ የተያዘበት ሴማዊ የሆነው የግዕዝ ቋንቋ እጅግ የተጣራ በመሆኑ፣ ለግሪክና ለላቲን ቋንቋ ተወዳዳሪ ሊሆን ይቃጣዋል። ይህን የመሰለ ቋንቋ እያለው ባገር ውስጥ ላለው ጕዳይ ለምን በግሪክ ይጽፋል? የዚህ ምክንያቱ እስኪገለጥ ድረስ ከዚህ በላይ የተነገረው አሳብ ትክክለኛ ነው ላይባል ነው።
በርሱ ፈንታም ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን አሳብ መናገር ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፤
ፊት፤ ሳባ፣
ቀጥሎ፤ ግዕዝ
የግሪክ ቋንቋ ከእስክንድር ጀምሮ ሮማውያን ግብጽን እስከያዙበትና ከዚያም በኋላ እስከ ብዙ ዘመን ለግብፅና ለታናሽ እስያ ሕዝብ ዋና ቋንቋ ሁኖ ነበረ። ለኢትዮጵያ ደግሞ ከሠለጠነው ዓለም ጋር መገናኛ ቋንቋ ሁኖላት ለደብዳቤ፣ አላፊ አግዳሚ ለሚያየው ሐውልትዋ፣ ባሕር ተሻግሮ ለሚገበያዩበት ገንዘብዋ፣ ይህንንም ለመሰለ ልዩ ጕዳይ የጽሕፈት ቋንቋዋ ኑሮ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ከ400ኛው ዓመተ ምሕረት በፊት (ይህ ማለት ወንጌል ባገሩ ሳይሰበክ) በሳባ ሆነ በግሪክ፣ በግዕዝም ሆነ ወይም በሌላ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ኑሮ እንደሆን ወሬው ከኛ አልደረሰም። ዛሬ በጃችን ያሉት መጻሕፍት ከ400ኛው እስከ 1700ኛው ዓ ም በግዕዝ፣ ከዚያ እስከ ዛሬ በግዕዝና በአማርኛ የተጻፉ ናቸው። ግዕዝ የሴም ቋንቋ መሆኑን ከዚህ በፊት አመልክተናል። ከዓረብ በስተደቡብ ከነበሩት ሴማውያን ያንዱ ነገድ ቋንቋ ኑሮ ይሆናል ይባላል። ምናልባትም ከዚሁ ነገድ አንድ ክፍል ዛሬ ዓጋሜ በምንለው አውራጃ ግድም ይኖር ኖሯል። ድንገት ደግሞ ከትግሬ አውራጃ ካሉት ነገዶች አንዳንዶች ይነጋገሩበት ኑረው ይሆናል። “በኢትዮጵያ ያሉት የሴም ቋንቋዎች (ትግርኛ፣ ትግረ፣ አማርኛ፣ ወዘተ) ከርሱ የመጡ ናቸው” የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ይህን አሳብ የማይቀበሉ በዚህ ፈንታም፣ “ከዓረብ በስተደቡብ ሲኖሩ ከነበሩት የሴም ነገዶች አንዳንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ ኖሯቸው፣ የእያንዳንዱ ነገድ ቋንቋ ራሱን እንደቻለ፣ በሆነለት መጠን እየደረጀ ሄዷል እንጅ፣ ግዕዝ በኢትዮጵያ ላለው ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ አባቱ አይደለም” የሚሉ አሉ።

በግዕዝ ከተጻፉት በብዙ ሽሕ ከሚቆጠሩት መጻሕፍቶቻችን ጥቂቶች ሲቀሩ፣ አብዛኛው ከክርስትያናዊ ግሪክና ዓረብ ከሌላም ቋንቋ የተተረጐሙ ናቸው። ደግሞም የዓለምንና የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚነግሩት ከጥቂቶች መጻሕፍት በቀር ሁሉም የሃይማኖት መጻሕፍት ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያዊነታችንን አሳብ የሚገልጥ መጽሐፍ በብዛት አይገኝባቸውም። ዋናው መጽሐፋችን “መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። ይኸውም ብሉይና ሐዲሱ እግዚአብሔር በዓለምና በእስራኤል ላይ የሠራውንና የሚሠራውን እስራኤላውያን በታያቸው ዓይነት የሚገልጽ መጽሐፍ መሆኑን፣ ሁሉ ያውቀዋል። ምስጋና ለዚህ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በሃይማኖትና በምግባር ከፍ ካለ ደረጃ ደርሶ፣ በያዘው መንገድ እየገፋበት እንዲሔድ ብርቱ ኃይል ተሰጥቶታል።
ደግሞም የግዕዝ ቋንቋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወዳገራችን ሳይመጣ ገና ፊት አስቀድሞ ራሱን የቻለ እንደነበረ በሐተታ እንኳ ብንረዳው፣ የግዕዝ ቋንቋ ጽሑፍ ምስክሩ ባለቤቶቹ የጻፉት መጽሐፍ መሆኑ ቀርቶ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የሌሎች መጻሕፍት ትርጕም ነው። ማናቸውም የሠለጠነ ሕዝብ ለቋንቋው፣ ለሰዋስው ማስረጃ ባለቤቶቹ የጻፉትን ሲጠቅስ፣ ግዕዝ ለሰዋስው ማስረጃ የሚጠቅስ ከባዕድ ቋንቋ የተተረጐሙትን መጻሕፍት ነው። በግዕዝ ከጻፉት ካገራችን ደራስያን ይቅርና በአሳብ፣ በአጻጻፍ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል ሳይከተሉ የጻፉ የሚገኙ አይመስለኝም። ይህም ልምድ የሃይማኖት አሳባቸውን የሚገልጹበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ አገራችን ታሪክና ማናቸውንም ጕዳይ በሚጽፉበት ጊዜ ጭምር ነው። ይህም የአጻጻፍ አካሔድ ኢትዮጵያ ገንዘብ ካደረገችው ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር የተስማማ ንግግር ለማምጣት የተመቸ ከመሆኑ በላይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሳንቀበል ከነበረብን አሕዛባዊ ከሆነ ምሳሌና ንግግር አርቆናል።
ይሁን እንጅ ኢትዮጵያዊ የሆነ አሳብ፣ ኢትዮጵያዊ በሆነ ንግግር የመግለጹ ዕድል ለግዕዝ ቀርቶበት ለአማርኛ ሆኗል። ዛሬ ዘመን በግዕዝ እግር ተተክቶ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ጕዳይ የሚሠራበት የአማርኛ ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባማርኛ መጻፍ ከጀመረ ስድስት መቶ ዓመታት ሁኖታል። አማርኛ ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን አካሔድ በ፫ ዘመን ቢከፍሉት ይሆናል።
፩ኛውን ዘመነ ዓምደ ጽዮን (1336-1599 ዓ ም)
፪ኛውን ዘመነ ሱስንዮስ (1599-1847 ዓ ም)
፫ኛውን ዘመነ ቴዎድሮስ (1847-1936 ዓ ም)
በ፩ኛው ዘመን በአማርኛ የተጻፈው ሥራ እጅግ ጥቂት ነው። የተጻፈውም ላንዳንድ ነገሥታት ምስጋና ደራሲው ባልታወቀ የተገጠመ ቅኔ ነው። ቅኔውም በዘመናት ውስጥ አንድ ቋንቋ እንደምን ሁኖ እየተለዋወጠ ለመሄዱ ዋና ምስክር ከመሆኑ በላይ በዚያ ዘመን የነገሥታቱ ሥልጣን የተዘረጋበት የሰፊው አገር ሁኔታ እንዴት እንደነበረ፣ ለታሪክም ለዦግራፊም ማስረጃ ለመሆን ይረዳል።

አማርኛው ዛሬ ዘመን የማንናገርበትና የማንጽፈው፣ ለማስተዋሉም የሚያስቸግረንና የሰዋስው አካሔዱ የተለዋወጠ ብዙ ቃልና አገባብ አለበት። እርሱን የመሰለ አማርኛም በየዘመኑ እየተጻፈ ምናልባት እስከ 1599 ደርሶ ይሆናል። ነገር ግን ከ1555 እስከ 1599 ዓ.ም ባማርኛ የተጻፈ ምስክር አይገኝም፤ ቢገኝም ከዚህ በፊት ያመለከትሁትን የመሰለ ግጥም ሳይሆን አይቀርም።
ከ1500ኛው ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወገን ለይቶ አልጋ ለመያዝ እርስ በርሱ ሲዋጋ፣ ባንድ ወገን ደግሞ ቱርኮችና ፖርቱጋሎች በቀይ ባሕር ሥልጣናቸውን ለመዘርጋት ይፈካከሩ ነበር። ቱርኮች በቀይ ባሕር ዙርያ ላለው ፖሊቲካቸው የኢትዮጵያን እስላም ሲረዱ፣ ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የፖርቱጋልን እርዳታ መለመን ግድ ሆነበት። አራት መቶም ያህል ጠበንጃ የያዙ ፖርቱጋሎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተዋጉበት ጊዜ፣ ድል ለክርስቲያኑ ወገን ሆነ።
የፖርቱጋል መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋራ ግንኙነት ሲጀምር ያገሩ ካህናት በኢትዮጵያ ለማስተማር እንዲፈቀድላቸው ተነጋግሮ ነበርና በስምምነታቸው የካቶሊክ ካህናት በኢትዮጵያ ማስተማር ጀመሩ። የሚያስተምሩበትና የሚጽፉበት ቋንቋ አማርኛ ነበርና የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ደግሞ ሕዝቡ ካቶሊክ እንዳይሆንበት ግዕዝን ሳይተው ባማርኛ መተርጐምና መጻፍ ጀመረ። በዚያው ዘመን ለመጻሕፍት ትርጕምና ለስብከት የተጀመረው አማርኛ ገና ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ፣ አንዳንዱም ንግግር ግዕዝ ላልተማረ ሰው በፍጹም የማይሰማ ነበር። እንደዚኽው ሁሉ በዚያው ዘመን ሲጻፍ የነበረው የነገሥታት ታሪክ ግዕዙ አማርኛ ቅልቅል ነበር።

ያም ሁሉ ሁኖ እንኳንስና ለውጭ አገር ሕዝብ የሚተርፍ፣ ካገራችን ውስጥ ከፍተኛ አሳብ የሚያሳድር በታረመ አማርኛ የተጻፈ መጽሐፍ ለማግኘት ችግር ነው። መጻሕፍቱ የፈጸሙት ጕዳይ፣ በሕዝቡ ላይ ከመጣበት ከሃይማኖት ተወዳዳሪ መከላከልና የባላገር ቋንቋ የነበረውን አማርኛን ጽሑፍ ሥራ ለማስያዝ መጀመራቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ለትሕትና ሲል ስሙን አያመለክትም ነበርና የመጻሕፍቱን ፍሬ ነገር መዘርዘር፣ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ማን እንደነበር መርምሮ የሕይወቱን ታሪክ ማመልከት ይቸግረናል።
ተአምራት አማኑኤል
1936 ዓ.ም
ተረት ተረት ነው። አማርኛ ከግእዝ አልተወለደም። ከግእዝ የተወለደው ትግርኛ እና ትግረ ነው።
LikeLike
ይበል!
LikeLike
በዙ መረጃወችን አስደግፈህ ብታቀርብ መልካም ነበር። ሙሉ ሀተታህ የግል አስተያየት ይበዛዋል።
ምሁር ከሆንክ በመረጃ አስደግፍና አቅርብ እሱንም ደግሞ ሌሎች ምሁራን ይደግፉልሃል ወይንም በሌላ መረጃ ይሞግቱሃል።
ስለዚህ የጻፍከውን ሀሳብ ለህትመት የበቃል ወይን ብለህ ማሰብ አለብህ! ያ ካልሆነ ደግሞ እነደነገርኩህ ስሜትህን ነው የገለጽከው እንጅ አዲስ ነገር አልጨመርክበትም።
LikeLike
Your view is clear and strategically pointed on showing the difference of history and story; for me, this is cogent, keep it up.
LikeLike