“እንዳለጌታ ከበደ” (ቃለመጠይቅ)

ቆይታ ከእንዳለጌታ ከበደ ጋር

(ከታኅሣሥ 1998 ዓ.ም እትማችን የተወሰደ)

.

ባለፉት አመታት ከደመቁት የስነጽሑፍ ኮከባት መሀል ወልቂጤ ያፈራችው እንዳለጌታ ከበደ አንዱ ነው። በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ፣ በ”እፍታ” እና “ክንፋም ህልሞች” መድበሎች ካቀረበው ሥራዎቹ ሌላ በ1996 ዓ.ም “ከጥቁር ሰማይ ሥር” እንዲሁም በ1998 “ዛጎል” የተሰኘ ረጅም ልብወለድን አቅርቦልናል። እንዳለጌታን በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በስልክ አግኝተነው ነበር።

እንዴትወደስነጽሑፍአለምገባህ? ከየትስጀመርክ?

ለመጀመሪያ ጊዜ ግጥም የጻፍኩት ሰባተኛ ክፍል እያለሁ ነው። አንድ ጓደኛችን ግጥም መድረክ ላይ አቀረበ። እና ያኔ ተጨበጨበለት፤ በጣም ሙገሳ በዛለት። እኔ ደግሞ ያቺ ግጥም ከጋዜጣ እንደተወሰደች አውቃለሁና እንዴት ባልሰራው ስራ የኔ ነው እያለ ጉራውን ይቸረችርብናል ብዬ ተናደድኩ። ጓደኞቼ ደግሞ “ታዲያ በዚህ እድሜው ከየት ሊያመጣ ይችላል፤ ከባድ እኮ ነው” ብለው መልሰው እኔን ተቆጡኝ። እኔም ይህን ያህል ከባድ አይደለም ብዬ አንድ ግጥም ጽፌ ለመምህሩ ሰጠሁ። መምህሩ ግን ከድርሰቱ ይልቅ የወደደው እጅ ጽሑፌን ነበር። ቢሆንም አበረታቶኝ ለወላጆች ቀን ዝግጅት አቀረብኩት።

እንዲሁም ቤት የምሰማውን ተረትና ታሪክ ቀይሬ አሻሽዬ ለሰው አወራ ነበር። አሁን ሳስበው ወደ ድርሰት ማዘንበሉ ያኔ የተጀመረ ይመስለኛል። ቤተ ክርስቲያንም አካባቢ እሄድ ስለነበር የቅዱሳን ገድልና ታሪካዊ ነገሮች አነብ ነበር – በተለይ ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ የሚያሳትሟቸውን። የጸሎት መጽሐፎቹ ግን የዛን የአራተኛ ክፍል ያለሁበትን ምኞቴን አልያዙም ነበር። ያኔ ምኞቴ በትምህርቴ በጣም ጎብዤ አባቴን ማስደሰት ነበር። የጸሎት መጽሐፎቹ ግን የሚሉት ጳጳሱን ባርክ እንዲያ የመሳሰለውን ነው። በልጅነት አእምሮዬ የጳጳሱ መባረክ ጥቅሙ ሰላልገባኝ ትናንሽ የጸሎት መጽሐፎች እጽፍ ጀመር – እኔ መሆን የምፈልገውን ቤተሰቦች ከኔ የሚጠብቁትን። “እግዚአብሔርዬ ከተማሪዎች ሁሉ የተሻለ ውጤት እንዲኖረኝ አባቴም በኔ ደስ እንዲለው አድርግልኝ” እያልኩ እጽፍ ነበር። ከዛም ቀስ በቀስ ወደ ልብወለድ ንባብ ገባሁ።

የትኞቹንየልብወለድጽሑፎችታነብነበር?

መጀመሪያ ያነበብኩት “ሽልንጌን” የሚል አማርኛ መጽሐፋችን ውስጥ የሚገኝ አጭር ልብወለድ ነበር። ከዛም ሳንቲም ሳገኝ – ያኔ መጽሐፎች 3.50 ወይም 4.50 ያወጡ ነበርና – ያገኘሁትን ሳላማርጥ አነብ ነበር። መጀመሪያ በጣም የወደድኩት አጭር ልብወለድ የስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን “አምስት ስድስት ሰባት” ነበር። እሱ ግን ታዋቂ መሆኑን ያወቅኩት አስረኛ ክፍል እያለሁ የአማርኛ መምህራችን ከታዋቂ ደራሲዎች አንዱ ስብሐት ነው ብሎ ሲነግረን ነው። ያኔ መምህሩ እኔ የምወደውን ደራሲ ሰላደነቀልኝ በጣም ደስ አለኝ። ቀጥሎም ወደእነ በዓሉ ግርማ …

ያኔበአካባቢህየስነጽሑፍክበብነበር?

እኔ ተወልጄ ያደግኩት ወልቂጤ ነው። እና ያኔ እንኳን ላይብረሪ ይቅርና መጽሐፍ መሸጫ መደብሮች  አልነበሩም። በየስንት ወሩ አንዴ ብቅ የሚል እየዞረ የሚሸጥ አንድ ሰው ነበር። እና ከሱ ነበር መጽሐፍ የምንገዛው። ታዲያ ሰው ቤት ስሄድ የመጀመሪያ ትኩረቴ መደርደሪያዎችን ማየት ነበር። ከዛም ካላነብኳቸው መጽሐፎች አንዱን መርጨ አነብ ነበር። በማንበብ ረሀብ ውስጥ ሰላደግኩ ነው መሰለኝ፣ ቆይ ሳድግ ትንሽም ቢሆን ቤተ መጻሕፍት እከፍታለሁ የሚል ስሜት ነበረኝ። አስራ ሁለተኛ ክፍል ስጨርስም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባ ነጥብ አልነበረኝም። እና ያኔ ትንሽዬ ክፍል ውስጥ መጽሐፎቼን አሰባስቤ ማከራየት ጀመርኩ – ለ24 ሰአት 25 ሳንቲም። እዛም ብዙ ሰዎች – ተማሪዎች መምህራን – ይመጣሉ፤ መወያየት ጀመርን። ከዛም “ተስፋ ቡክ ክለብን” ከፈትን፤ የስነጽሑፍ ሰዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም የቀለም ተማሪዎችን የሚያግዝ አንዳንድ ስራዎችን መስራት ላይ አተኩረን ነበር።

ወደአዲስአበባእንዴትመጣህ?

መጽሐፍ በማከራየት የሰበሰብኩትን ገንዘብ ይዤ ዕቁብ በመግባት አንድ ሶስት ሺ ብር ሲሞላ ወደ አዲስ አበባ ተጓዝኩ። ፍላጎቴ ስነጽሑፍ መማር ቢሆንም ይህን ዘርፍ የሚያስተምር የግል ተቋም ሰላልነበረ ዩኒቲ ኮሌጅ በመግባት ጆርናሊዝም እና ኮምዩኒኬሽን ተማርኩ።

የመጀመሪያመጽሐፍህስ?

መጀመሪያ ገንዘብ ስሰበስብ መማር ላይ አተኮርኩ። ቀጥሎ ደግሞ ወልቂጤ የነበረውን ስራ ወንድሞቼ ያግዙኝ ነበረ እና ገንዘቡ ሲጠራቀም የኔን ስም የያዘ መጽሐፍ ለማሳተም የነበረኝን ፍላጎት እውን ለማድረግ አሰብኩ። አንዳንድ አጫጭር ልብወለዶቼ ከዚህ በፊት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ወጥተው ነበር፤ ጓደኞቼ እንዲሁም የማከብራቸው ሰዎች ጥሩ አስተያየት ሰጥተውኝ ነበር። ነገር ግን እነዚህ አጫጭር ልብወለዶች ተሰባስበው አንድ የራሴ የሆነ ቀለም ማሳየት እፈልግ ነበር። እንዴት እንደማስብ ማሳየት እፈልግ ነበር። መጀመሪያ ግጥም ለማሳተም አሰብኩ። ያኔ ግን ብዙ ገጣሚዎች ስራዎቻቸውን ለንባብ ያበቁበት ጊዜ ነበረና አይ አጫጭር ልብወለድ ቢታተም በአመት አንዴ ነውና ለምን የኔዎቹን ሰብስቤ አላሳትማቸውም ብዬ አሰብኩ። ከዚህ በፊት ለንባብ ከበቁትና ከአዳዲሶቹም ጨምሬ አሥራ ስድስቱን አብሬ አሳተምኩ። “ከጥቁር ሰማይ ሥር”ንም ለማሳተም የፈጀብኝ 12 ሺ ብር ነው። ግማሹን ከኔ ግማሹን ተበድሬ።

ምንያህልኮፒአሳተምክ?

ሶስት ሺ። ሰዎች፣ እኔም ጭምር፣ አይሸጥም ብለን ፈርተን ነበር። መጀመሪያ የተበደርኩትን ገንዘብ ካስመለስኩ ጥሩ ይሆናል ብዬ አሰብኩ፤ ከዛም ካልከሰርኩ ጥሩ ነው አልኩ። ቀስ በቀስ ጋዜጦች ሰለመድበሉ መጻፍ ሲጀምሩ እንዲሁም ሰው ሲነጋገርበት ስመለከት አይ ትንሽ እንኳን ማትረፍ ብችል ማለት ጀመርኩ። አሁን መጽሐፉ ከወጣ ሁለት ዓመት አልፎታል። እና ገበያ ላይ አለ ማለት ያስቸግራል። ባለፈው አንድ ሱቅ ውስጥ ሁለት ሶስት አይቼ እራሴ ገዛኋቸው። እና አሁን አብዛኛው ጸሐፊ አንድ ወይም ሁለት ሺ በሚያሳትምበት ጊዜ ሶስት ሺ ማሳተሜ ብዙ ቢመስልም ከሰባ ሚልዮን ህዝብ በላይ ባለበት ሀገር እንዲህ መሆኑ ንባብ በጣም ማሽቆልቆሉን ያሳያል።

ከጥቁርሰማይሥርዋጋውአስርብርነው።ለመሆኑየአከፋፋዮቹድርሻእንዴትነው?

አከፋፋዮቹ 30 ከመቶ ያገኛሉ። የሽፋን ስዕሉንና Layout ለማሰራት፣ ታይፕ ለማስደረግ፣ እንዲሁም ለማሳተም ለእያንዳንዱ መጽሐፍ 4 ብር ወጥቷል። አከፋፋዮቹ ደግሞ 3 ብር ያገኛሉ። እኔ ደግሞ ለሰዎች በነፃ የሰጠሁትን እንዲሁም የተበላሹትን ኮፒዎች አስበህ ከእያንዳንዱ መጽሐፍ 2.80 አገኛለሁ።

በአንድጋዜጣላይምኞትህአንድአገራዊድርሰትበሚልዮንኮፒእንዲታተምመሆኑንገልጸህነበር።እዛለመድረስምንማድረግያስፈልጋል?

ምን መሰለህ! ብዙ ሰዎች መጽሐፍ የሚያነቡት በሌላው ጎትጓችነት ነው። በአሁኑ ሰዓት መጽሐፎች ውድ ናቸውና “ሳንቲሜን አውጥቼ ከገዛሁ በኋላ የፈለኩትን ያህል ደስታ ባላገኝበትስ? ዝም ብሎ እንቶ ፈንቶ ቢሆንስ?” የሚል አስተያየት አለ። አንዳንዶች “ለመሆኑ በአሁኑ ዘመን ጥሩ ደራሲ አለ ወይ?” ይላሉ። እናም በዚህ ጥርጣሬ አይገዛም ማለት ነው። የሰዉን ስሜት ስመለከት መምህሩ አንብቡ ያላቸውን መጽሐፍ ውለው ሳያድሩ ያነባሉ። ምክንያቱም ካላነበቡ የሚጎድልባቸው እንዳለ ሰለሚያውቁ ነው።

ሁለተኛ ደግሞ ያሉን የቤተ መጻሕፍት ቁጥር ብዛታቸው ስንት ነው ብንል መልሱ ያሳዝነናል። መጽሐፍ ሻጮችንም የሚያበረታታ አካል የለንም። ከሚልዮን በላይ ኮፒ ቢታተም ደስ ይለኛል ያልኩት ከምን አንጻር ነው ቢባል? እንግዲህ የህዝቡን ብዛት አስብ! በየጊዜው ደግሞ የመኃይማኑ ቁጥር ቀንሷል ነው የሚባለው። ይህን ህልም እውን ለማድረግ የንባብንና የውይይት ክበቦችን ማብዛት የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ምክንያቱም ብዙዎቹ ያነቡና የሚያዋራቸው ሰው የለም። የሚያወያያቸው ሰውም የለም። በአሁኑ ሰዓት  የአንባቢው ቁጥር አንሷል ማለት አስቸጋሪ ነው። ሰዉ ወደ ጋዜጣና መጽሔት፣ የዕለት ተዕለት ወደሆነ ኑሮ የሚያተኩሩ ዜናዎችን ለማንበብ ነው የሚረባረበው። መንግሥት በየቀበሌው ካሉት የመዝናኛ ማዕከሎች መሐል የተወሰኑትን ለንባብ አገልግሎት እንዲውሉ ቢያደርግ የአንባብያንን ቁጥር ማብዛት ይቻላል። ምክንያቱም ወመዘክር ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብትሄድ ሰልፉ ሌላ ነው። እንኳንስ ቁጭ ብለህ ልታነብባቸው ይቅርና ሰው በዝቶባቸው የማይመቹ ቦታዎች ሆነዋል።

ከደራሲው ብዙ የሚጠበቅ አይመስለኝም – ማለት እንዲነበብለት። የውይይትና የንባብ ክበባት ይህንን ነገር ማጉላትና ማራመድ ይችላሉ። በመገናኛ ብዙኃን የጥበባት ፕሮግራምም አዳዲስ መጻሕፍት ሲወጡ በማስተዋወቅ የአንባብያን ቁጥር እንዲበዛ ማድረግ ይቻላል። የቴሌቪዥን ሚዲያ ስናይ የስዕል ኤግዚቢሽን ሲከፈት ሮጠው ያቀርባሉ። ጥሩ ነው ደስ ይላል። ደራሲያን መጽሐፍ በሚያስመርቁበት ሰዓት ግን ብዙ አይመጡም። አንባቢንና ድርሰትን ለማገናኘት የሚያደርጉት ጥረት የደከመ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። እነዚህ ሁሉ ድክመቶች መቀረፍ ቢችሉ በተወሰነ መንገድ የአንባብያንን ቁጥር ማብዛት እንደሚቻል አስባለሁ።

ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም አንድ ዝግጅት ላይ ጥናት አቅርበው በደርግ ዘመን ብዙ አንባቢዎች ነበሩ ብለዋል። ለምሳሌ የሲሳይ ንጉሡ “ሰመመን” 70-80 ሺ ኮፒ ታትሞ ተሽጧል። አሁን ግን ደራሲዎች የሚያሳትሟቸው መጽሐፎች ከ5 ሺ ኮፒ ብዙም ፈቀቅ አይሉም። ለምንድነው? አስበው እንግዲህ የህዝብ ቁጥር ጨምሯል። ነገር ግን የአንባቢያን ቁጥር እየቀነሰ ነው። ያኔ ጎትጓች ነበረው። ያሁኑ ያህል ጋዜጦች አልነበሩም። ሚዲያ አልነበረም፤ ኢንተርኔት ጊዜን አያጣብብም ነበር። ሲኒማዎችም አልተበራከቱም። አቶ ሣህለሥላሴ ሲናገሩ ያኔ ጋዜጦች “ወታደሩ ሰለማያነብ ንቃተ ህሊናው አልዳበረም” እያሉ ይወርፉ ነበር። ወታደሩም እኛ ነን ወይ የማናነበው፤ እኛ ነን ወይ ንቃተ ህሊናችን ያልዳበረው በማለት መጽሐፍ ይገዛ ነበር። ይላክለትም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ወታደሩ እንዲያነብ ግፊት ስለሌለው የተወሰነ አንባቢዎችን አጥተናል ሲሉ ሰምቻለሁ።

አንተ፣ በዕውቀቱሥዩምናአማኑኤልመሃሪስትረዳዱይታያል።ከጥቁርሰማይስርውስጥያሉትንስዕሎችየሳለውምበዕውቀቱነው።የደራሲዎችመተባበርናአብሮመስራትንእንዴትታየዋለህ ?

አብሮ መስራት ስራውን የተሸለ ለማድረግ ምንም ጥርጥር በሌለው መልክ ያግዛል። ለምሳሌ በዕውቀቱ “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” የሚለውን መጽሐፉን ከማውጣቱ በፊት አንዳንድ ግጥሞቹን እንዲያወጣ መክረነው ሀሳባችንን ተቀብሏል። ይህ ትውልድ ውስጥ መንፈሳዊ የሆነ ስሜት አለ። እርስ በእርስ የመተጋገዝ ነገር አለ። ከሶስተኛው መጽሐፌ ቀደም ብሎ በዕውቀቱ መጽሐፍ ቢያወጣ ደስ ይለኛል። ሙሉ ትኩረታችንንም እዛ ላይ አድርገን ብንሰራም በጣም ደስ ይለኛል። ምክንያቱም እሱ የሚጽፋቸውን ነገሮች እወዳቸዋለሁ። የኔ መጽሐፎችንም ሳሳትም በዕውቀቱ የራሱ የሆነ እገዛዎች ነበሩት፤ አብዛኛዎቹን ሀሳቦቹን ተቀብያቸዋለሁ። ሰለዚህ የምጽፈው ጽሑፍ ወደ ህዝብ እንዲደርስ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በእኛ መሀከል መተጋገዙ ጥሩ ነገር ለህዝብ ለማቅረብ ከመጓጓት ስሜት ነው። ፍቅርህን የምትገልጸው የምትወደውን ነገር የሚወዱ ሰዎች በማብዛት ነው። እኔና ጓደኞቼ ጥበብን እንወዳለን። ኪነትም የተለየ ስሜት ይሰጠናል። በጣም ጥሩ ነገር ስናዘጋጅ እንቀባበላለን። ለምን ይሄ ነገር ጋዜጣ ላይ አይወጣም እንላለን። የህብረት መዝሙር ላይ ከሚሳተፉ ሰዎች መሃል እንደ አንዱ ነን። እያንዳንዱ ዘማሪ የራሱ የሆነ ድምጽ አለው። በሁሉም ባንመሳሰልም አንድ ላይ ስንደረደር ግን እራሱን የቻለ ጥዑመ ዜማ ሊወጣ እንደሚችል እንገምታለን። መተባበራችን እገዛ እንደሚያደርግ እገምታለሁ። ቢያንስ ቅንነትን ለተተኪው ትውልድ ማሳየት ነው።

እናመሰግናለን።

“በሰንበት የተፀነሰው” (ልብወለድ)

“በሰንበት የተፀነሰው”

በእንዳለጌታ ከበደ

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

“ምነው በጊዜ መጣህ? የኔታ የሉም እንዴ?” አለች ምንትዋብ፤ ቄስ ትምህርት ቤት የላከችው ልጇ ያለ ሰዓቱ መመለሱን አይታ።

“ወላጅ አምጣ አሉኝ” አላት፣ የስድስት ዓመቱ አቦቸር – ብልጣብልጥ ዓይኖቹ ላይ ሐዘኔታን ለማስነበብ እየጣረ።

“የሠራኸው ተንኮል አለ?”

“የኔታ የማላውቀው ጥያቄ ሲጠይቁኝ ኤክስ ሆንኩና ጓደኞቼ ሳቁብኝ”

“ምንድነው ጥያቄው?”

“‘እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ ከጨረሰው በኋላ ወደ ገነት ወስዶ ምን ብሎ አስጠነቀቀው’ ብለው አፍጥጠው ጠየቁኝ”

“ምን መለስክላቸው?” አለች እናቱ መልሱን ለመስማት ጓጉታ።

“’አልሰማሁም’ አላልኳቸውም። ‘እግዚአብሔር አዳምን ወደ ገነት ወስዶ  ምን አለው?’ ሲሉኝ ጊዜ፤ ‘ለሕይወትህ ዋጋ ስጥ ብሎ አስጠነቀቀው’ ስላቸው፤ ተቆጡኝና፤ ብዙ አይነት የሚያስበሳጭ ስድብ ሰደቡኝ …”

ሌላ ቀን

“ዛሬ ደግሞ ለምንድን ነው ት/ቤት ያልሄድከው?” ብላ ተቆጣች፣ ምንትዋብ። ገበያ ሄዳ ብቅልና ጌሾ ገዝታ ስትመለስ ነው አቦቸርን ሠፈር ውስጥ ያገኘችው። በዕድሜ ከሚተካከሉት ጋር ሆኖ፣ በጣቶቹ መሃል ያለችውን ብይ ወደ ጉድጓዱ አፍ ለመክተት ሲፍጨረጨር ነበር የደረሰችበት።

“የኔታ አባረሩኛ!! ‘እዚህች ደጅ ብትደርስ በአለንጋ እዠልጥሃለሁ’ አሉኝ” አለ አቦቸር “ዛሬም ‘ይሄ በሰንበት የተፀነሰ’ ብለው፤ ሌላ ሰው እንዲሰማላቸው ብለው – ጮክ ብለው ሰደቡኝ …”  አለ ጠይም ፊቱ ቅያሜ እየተስተዋለበት።

“ለምን?” ተቆጣች – ምንትዋብ።

“አለንጋቸውን ደብቄባቸው አላውቅም። ከጫፉ ቆርጬ ቦርሳዬ ውስጥ የደበቅሁትም እኔ አይደለሁም። ሁሌ ሳልሰድባቸው ይሰድቡኛል፤ ‘ጥፋ ከፊቴ! ባለንጋ ነው የምዠልጥህ’ እያሉ ያስቦኩኛል”

“የማንን ልጅ ማን ይቀጣል?” አመረረች፣ ምንትዋብ።

በፊትም ቢሆን የሃይማኖት ሰዎችን አትወድም። ምክንያትሽ ምንድን ነው? ቢሏት ‘አባቴ’ ትላለች። አባቷ መጾም መፀለይ የሚያበዙ ነበሩ፤ ሰው እፊታቸው ቀርቦ ‘ይፍቱኝ አባ’ ብሎ የሠራውን በደል የሚናዘዝላቸው አይነት ሰው ነበሩ። ቀን ቀን ‘ሐዋርያዊ ተልእኮአቸው’ን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ይውላሉ። ጀምበር አሽቆልቁላ ወደ ማደሪያዋ ስታዘግም – የሚቀመሰውን ቀማምሰው – ሞቅ ይላቸውና ጥምጣማቸውን ፈተውና ቀበቶአቸውን አላልተው በመሸበት ያድራሉ።

የምንትዋብ አባት በመሸበት በማደራቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሠፈር መንደርተኛም ለመወገዝ የበቁበት ምክንያት አለ። በስደተኛው መድኃኒያለም ስም ዣንጥላ ዘርግተውና፣ ምስል ደረታቸው ላይ አንጠልጥለው ያለ ቤተ ክህነት ፈቃድ ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር። ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው እስር ቤት ቤታቸው እንዲሆን ሲፈረድባቸው የእነምንትዋብ ስምም የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ርዕስ ሆነ።

በዚህን ጊዜ ምንትዋብና እናቷ ሳር ቅጠሉ፤ ዘመድ ጎረቤቱ ጣት የሚቀስርባቸውና ሰድቦ ለሰዳቢ አሳልፎ የሚሰጣቸው መሰላቸው። ከማታውቃቸው ወንዶች ጋር መሄድ የጀመረችውም ያን ሰሞን ነው፤ ቤተሰቦቿን ለመርዳት።

ምንትዋብ ወደ ቤት ገባችና ጥቁርና የረዘመ ሻሿን አውጥታ አሰረች። ቀሚሷን አስተካከለች። መበስበስ ከጀመረ – መቀመጫው ከተበላ ካርቶን ውስጥ ያደፈ ነጠላዋን አውጥታ ትከሻዋ ላይ አኖረች።

ቤቱን ለቅቀው ከመውጣታቸው በፊት፣ ጠላ መኖሩን የሚጠቁመውን ቂጡን ለሰማይ የሚያሳይ ጣሳ (አፉን ከመሬት ባገናኘ ሙቀጫ ላይ ተቀምጦ የሚያሳየውን) አርማ አስገባችው።

ቤቱ ተቆለፈ።

“ምንትዬ!”

“እ?”

“አሳይሻለሁ እሺ?!”

“የኔታህን?”

“አይ የማይመጣውን ልጅ! እኛ ስንማር ከኛ ጋር የማይኖረውና ብዙ ንፍጥ የሚወጣው ልጅ!”

“ሰነፍ በለው”

“ከማይመጣው ልጅ የበለጠ የማይመጣው ትልቁ ልጅ ዛሬም አልመጣም” ይላል አቦቸር ያሳሰበው ይመስል – አመዳም – ጠይም ፊቱን እያሻሸ።

“ወላጅ አሰዳቢ በለው”

“ላይመጣ ነዋ የሄደው! አንድ ቀን የኔታ ከሽንት ቤት እስኪመጡ ድረስ ብድግ አለና እሳቸው ሰክረው ጎርፍ ውስጥ እንዴት ተንገዳግደው እንደሚወድቁ እያሳየ ሲያስቀን፤ ደረሱበትና እስከ ሩቅ ቦታ ድረስ አባረሩት። ‘ይህን አሳዳጊ የበደለው ውጫጭ በድንጋይ በሉት’ አሉንና ሁላችንንም ላኩን። እኛ ግን ፈንክተን ከጭንቅላቱ ደም እንዳናስወጣበት ብለን እሱ ወዳልሄደበት ቦታ ድንጋይ ወረወርን። ከዚያ ቶሎ ቶሎ መሸና ወደየቤታችን ተበታተንን”

ለምንትዋብ አቦቸር ልጇ ብቻ ሳይሆን ጓደኛዋም ጭምር ነው። ጥያቄዎቹን አትሰለቻቸውም።

“ምንትዬ … ሳድግ ቁመቴ ከሁሉም የሚበልጥ አይሆንልኝም? ወደ ላ-ይ አያድግልኝም?” ይጠይቃል እናቱን።

“ያድግልሃል። ምነው አሽቆልቁሎ ማየት አማረህ እንዴ?”

“ጥቁርስ አልሆንም?”

“ትፈልገዋለህ እንዴ ጥቁረትን?” ትለዋለች፤ ደንቡሽቡሽ ያለ ፊቱ ላይ እያተኮረች።

“አዎ። እንትንስ …” ጣቱን ከንፈሩ ላይ አኑሮ የረሳውን ለማስታወስ ድምጹን እየጎተተ፤ “ፀጉሬ – ግንባሬ አጠገብ ያለው ፀጉሬ – ነጭ አይሆንልኝም?”

“ምን ያደርግልሃል ሽበት?”

“ጋሼ አበራ ሞላን ለመሆን ነዋ! የኛን ሰፈር አዲስ አረገዋለሁ። አረገውና አንድ ነገር እጽፍበታለሁ። ጠላ የምትጠምቂበት ጋን ሲሰበር ደግሞ እንዳትጥይው። ያስተማርኳቸው ሁሉ አስተማሪ ሆኑልኝ የሚሉሽ የድሮ አስተማሪ አንቺ ጋ ሲመጡ ደግሞ – ‘ለልጄ ቶሎ የማያልቅ ቾክ አምጡለት’ በያቸው። እጽፍበታለሁ። ‘የሸና ይነሸነሻል’ ብዬ። ይነሸነሻል አይደለም ‘የሸና ይሸነሸናል ብዬ ነው የምጽፈው። እንዳይረሳኝ እሺ?”

“እሺ!”

ሌላ ቀን

“እኔ ስሞት ምንድነው የምሆነው?” ይላታል፤ ያለ አባት ለምታሳድገው ምንትዋብ።

“ሚጢጢ መልአክ ትሆናለህ!” ትለዋለች እናቱ።

“ከዚያስ?” ያመጣዋል ጥያቄውን።

“ሰዎች ጉዳይ ሲኖራቸው ወዳንተ ይጸልያሉ” ትለዋለች – ምን ይመልስልኝ ይሆን? ብላ – ዓይኗን በሚመስለው ዓይኑ ላይ አተኩራ።

ሌላ ቀን

“ሳድግ አንድ ነገር አረግልሻለሁ እሺ?! የእግዚአብሔር ሚጢጢ መልአክ እሆንና እንደገና አስፈጥርሻለሁ” አላት።

(ሸራተን ሆቴልን – በምሽት – ምን እንደሚመስል ከርቀት ጐብኝቶ በሚንቦገቦገው ብርሃን የተመሰጠ ለታ ነው ይሄ ሀሳብ ውስጡ የተወለደው)

“ምናልክ? እንደገና አስፈጥርሻለሁ?!” ትለዋለች ድንጋጤዋ እየታየ።

“አዎ ቆንጅዬ አስደርጌ – ደስ የሚል ልብስ አስለብሼ – ሽቶ አርከፍክፌሽ፣ አሪፍ አስደርጌ አሳድግሻለሁ…’

እናት ትስቃለች።

“ኧይ አቦቸር! እሺ ከዚያስ?”

“ከዚያ ምን?!”

“አቆንጅተህ ካሳደግከኝ በኋላ …”

“ከአላሙዲን ጋር አጋባሻለሁዋ!”

“ከአላሙዲን?!”

“ከዚያም… እናቴን አግባት ስለው እምቢ ስላላለኝ ብዙ ዓመት እንዲያስኖረው እግዚአብሔርን እለምንለታለሁ እንጂ አላስሞተውም። ደግሞ ካጠፋችሁ ስለምታናድዱኝ – እንዳልገድላችሁ ብዬ – ስትሳሳቱ ላላይ – እንቅልፌን እተኛለሁ። ብዙ ቀን እስኪሆነኝ ድረስ…”

“ኧይ አንተ!”

“… የኔታ ጸሎት ሲያደርጉ፤ ‘አታስርበኝ’ ብለው ሲለምኑኝ ‘አልሰማዎትም’ እላቸዋለሁ። ‘ድሮ ለምን በሰንበት የተፀነሰው ብለው ሰደቡኝ፤ ትንሽ እያለሁ ለምን በአለንጋ ዠልጠው አሳመሙኝ’ እላቸዋለሁ። ለሠይጣን እነግረውና፤ ‘ሂድና ፂማቸውን በእሳት አቃጥለውና ራሳቸውን አግማቸው’ እለዋለሁ!’

ምንትዋብ ሳቋን መቆጣጠር ያቅታታል።

*  *  *

አንድ ቀን ደግሞ ከገበያ ስትመለስ ያቺ ዥንጉርጉር ቀለም ያላት ጭር ያለችዋን ዶሮ አባርሮ እንቁላሎቿን ሲሰባብር ደረሰችበት፡-

“እንዴ? ምን እየሆንክ ነው?” አለችው ቁጣዋ እየመጣ።

“እንቁላል ውስጥ ያሉትን ጫጩቶች እያስወጣሁዋቸው …” ይላል – በአስኳል የበጨጨ መዳፉን በእራፊ ጨርቅ እያፀዳ።

“ኧይ የልጅ ነገር! ከሳምንት በኋላ የሚፈለፈሉትን ባጭር ትቀጫቸዋለህ እንዴ?!”

“ብዙ ቀን እስኪሆን ድረስ ጫጩቶቹ እንቁላል ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ ታፍነው ይሞታሉ ብዬ እኮ ነው!”

“አጥፍተሃል አቦቸር” ከኩርፊያ ጋር።

“ዶሮዋ ናት ጥፋተኛ! እንቁላሏ ውስጥ ከትታ ከምታስጨንቃቸው፤ ላያቸው ላይ ከምትቀመጥባቸው፤ መጀመሪያውኑ ለምንድነው ጫጩቶቿን እንቁላል ውስጥ ከትታ የምትወልዳቸው?”

ኩርፊያዋ እየተገፈፈ ይመጣና እቅፍ አድርጋ ትስመዋለች።

“እናት ልጆቿን ታስጨንቃለች? አታስጨንቅም አይደል?!…”

አቤት ሀሳቦቹ ሲያዝናኗት!

ሌላ ልጅ የመጨመር ሀሳብ የላትም ‘ሃምሳ ቢወልዱ ሃምሳ ነው ጉዱ፤ ከተባረከ ይበቃል አንዱ’ …ማለትን ታዘወትራለች።

ልጇን ያልወደደ ባይወለድ ትመርጣለች። ከጎረቤቶቿ ጋር (‘ውሽማዬን ወሰድሺብኝ’፣ ‘ዶሮሽ ስጥ በተነብኝ’ በሚሉ ሰበብ አስባቦች) በተጋጨች ቁጥር እሷን ለማበሳጨት አቦቸር ላይ ይወርዱበታል። “… ይኼ ከየትኛው ቱቦ እንደፈሰሰ የማይታወቅ ቆሻሻ!” እያሉ።

አቦቸርም አንዳንዴ ያልተጠበቀና አስደማሚ ሀሳቦች ይመጡበታል።

“አንቺ እማ!” ይላል ቲቪ ሲያይ ቆይቶ ለምሳ ቤቱ ሲገባ።

“… እ?”

“…ለአለቤቾው ‘ባል የለኝም’ ብለሽ አልቅሰሽ ካስለቀስሺው አባት አያስመጣልኝም?”

“ከየት?” ብላ ትጠይቃለች፣ መገረም ልቧን እየሞላው!

“እኔንጃ” ይመልሳል – ውስብስብ ያለ ሂሳብ እንደሚያሰላ ተማሪ ፊቱን አኮምጭጮ!

… አቦቸር አባቱን አያውቅም። እናቱም አባቱን አታውቅም። አባቱም ልጁን የሚያውቅ አይመስልም።

“የኔታ ሁልጊዜ ቀን በቀን ይጠይቁኛል”

“የምን ጥያቄ ነው’ሱ?”

“‘የአባትህ ስም’ እያሉ ነዋ!”

“ምንትዋብ አትላቸውም?”

“ስላቸው ጊዜ ልጆች ይስቁብኛል። ‘የሴት ልጅ’ እያሉ! እነሱ ግን አባት ከየት ነው የሚያስመጡት? ስም ሲጠራ ያንቺን ስም ሲሰሙ የማያልቅ ሳቅ ስለሚስቁብኝ፣ ቆይቼ ቆይቼ ነው፤ ሁሉም ሰው ገብቶ ካለቀ በኋላ ለትምህርት የምገባው። እያልወደድኳቸው ነው። ለብዙ ልጆች ሀ- ሁ- ያስጠናኋቸው እኔ ነኝ። እንዳይረሳቸው አርጌ። ግን ይሳደባሉ። ስድብድብ ነው የሚያረጉኝ። እናደድና እደበድባቸዋለሁ” በእልህ ከንፈሩን እየነከሰ – በወሰደባቸው እርምጃ እየተደሰተ።

ምንትዋብ የሀሳብ መርከብ ይዟት ይሄዳል። በጥያቄ ባሕር ላይ እየተንሳፈፈች – በጥርጣሬ ካፒቴን እየተሾፈረች።

ይሄ ልጅ የማነው? የትኛው ወዳጄን ነው የሚመስል?!…

*  *  *

“ሸበላ ነበርኩ” ትላለች እናቱ። “ዳሌዬ ሲሞናደል የአልፎ አግዳሚውን ዓይን ጠልፎ የሚያስቀር። ተማሪ አልቀረኝ መምህር! ሎሌ አልቀረኝ ጌታ! ወታደር አልቀረኝ ኮለኔል! መነኩሴውስ ቢሆን?! ያላመላለስኩት ቀበቶ ታጣቂ አልነበረም” ትላለች … ስለ ትላንት በተወሳ ቁጥር።

“… ይህንን ሰፈር እንደ ጉድ ጭሰንበት አልፈናል፣ ተጫጭሰንበታል” ማለትን ታዘወትራለች ምንትዋብ።

“ኧረ? … !” ብሎ ወሬውን ላሟሟቀ “እንዴታ! የዚያን ዘመን ፍንዳታዎች ፍም ሆነው ይመጡና ‘የታለች ሉባንጃ? ልናጫጭሳት ነው’ ይላሉ ‘ሉባንጃዬ’ ነበር የሚሉኝ! በግሩም መዓዛዋ የሚወዳደራት የለም – ሉባንጃን እጣን። ውበት ብቻ አይደለም ዋናው ነገር፤ ውበት አይደለም ጠረን ነው። ጠረን ብቻ አይደለም ያልጋ ላይ ጨዋታ ነው”

ሠፈራቸውም ለየት ነው የሚል። ጥዋት ጥዋት ቃል ከሚገልጸው በላይ ሠፈሩ ፀጥ ይላል። ከሰዓት በኋላ ደግሞ ጭርታውን አስደንግጠው ለማባረር ሠፈርተኞቹ በአስነዋሪ ቃላት ይሰዳደባሉ።

ምድር ጥቁር ቆቧን አናቷ ላይ ከደፋች በኋላ ግን የሁሉም ምላስ ለስልሶ ፍቅርን ለማዜም የቸኮለ ይመስላል። አካባቢውም የገበያ ያህል ግርግር ይበዛዋል። ንግድ ይጧጧፍበታል። የሚያድንም የሚታደንም ሞልቷል። ማታ ማታ ያው የሚነገር አይደለም። በጨዋ አነጋገር ሆድ ጾሙን ውሎ እንዳያድር – ከማያውቁት ገላ ጋርም ቢሆን – አንሶላ ይጋፈፉበታል።

ይህን ይመስላል የእነ አቦቸር ሠፈር … (ከብዙ በጥቂቱ ይነገርለት ከተባለ)

“ምንትዬ…”

“እ?”

“ወደዛ እንዳታዪ …” አላት፤ ጎረምሶች ተሰብስበው አላፊ አግዳሚውን የሚለክፉበት ‘ድድ ማስጫ’ ተብሎ የሚጠራ ቦታ እያሳያት።

“ለምን ግን?” አለችው።

“ይለክፉሻል። ሸምሱ ሻይ ቤት ቁጭ ብለን ፊልም ስናይ … የመዐት ወንዶች የሚወዷትና እሷም ወደ መኝታ ቤት የምትወስዳቸው ሴት ያሳዩኝና፤ ‘እናትህን ትመስላለች’ ይሉኛል! አንድ ቀን ግን ተናድጄ ሌላ ሰው ሻይ በጠጣበት ብርጭቆ ቲቪውን ላንኮታኩተው ነበር”

“የጨዋ ልጅ እንዲህ አያደርግም”

“እነሱ ዝም አያስብሉኝማ! እኔን ሳትወልጂኝ በፊት፤ ቆንጆ የሆነችዋን ጄኔፈር ሎፔዝ የምትባለዋን አክተር ትመስይ እንደነበር፤ ለሁሉም እንዲሰማ ጮክ ብዬ ስነግራቸው፤ ጎረቤት እስኪሰማ ድረስ ሳቁብኝ። ‘ከመወለድህ በፊት እናትህን አይተሃት ነበር ወይ?!’ ይሉኛል። ባላይሽስ? እናቴ አይደለሽ እንዴ? ሳልወለድ በፊት ምን እንደምትመስይ ማወቅ ያቅተኛል?!”

“አያቅትህም” ትላለች፣ እናት ሳቋ እየመጣ።

“ፊልሙ ሳያልቅ ወጣሁላቸዋ! እነሱኮ ተሳድበው ተሳድበው እኔም ስሰድባቸው እቆይና ስድብ ሲያልቅብኝ ደግሞ ማለቅስ መስሏቸዋል…” ይላል፤ አቦቸር ብልጠት የሚታይባቸው ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ።

ቄስ ትምህርት ቤት ደረሱ።

“ይሄ ነው ትምህርት ቤታችን። እዚህ ሰፈር ካሉ ቤቶች አንደኛ አሮጌ የኛ ቄስ ትምህርት ቤት ነው” አለ ዘመም ወዳለና ጭቃ ወደተመረገበት ቤት ጣቱን ሰዶ እየጠቆመ።

“የአስተማሪህ ስም ማን ይባላል?”

የሰማት አይመስልም።

“‘በሰንበት የተፀነሰ’ ብለው አይስደቡት በያቸው። አንድ ቀን ከሌላ ሰው ጋር ሲያወሩ አጠገባቸው ቆሜ ነበር። አዩኝ አዩኝና በአለንጋ ዠለጡኝ። ‘ጆሮ ጠቢ’ ብለው ሰደቡኝ። እኔ ግን የማንንም ጆሮ ጠብቼ አላውቅም። ጆሮ ሲጠባ ግን አይጣፍጥም አይደል?”

ምንትዋብ ስትስቅ ቆየችና፣

“ምስጢር ስለሰማህኮ ነው እንደዚያ ያሉህ”

“እያልሰማኋቸው ነበራ!”

“ስማቸው ማነው?”

“የየኔታ?” ጠየቀ አቦቸር።

“አዎ የፊደል አስተማሪህ?”

“የኔታ ነዋ! ሌላ ስም አልወጣላቸውም። አንድ ቀን ግን ሰከሩና በጠላ ከበሰበሱ በኋላ፤ ‘ከእንግዲህ እኔ የዚህ ቄስ ተማሪ ቤት ዳይሬክተር ነኝ’ አሉን። ትንሽ ቆዩና ‘ምናችሁ ነኝ?’ ብለው ጠየቁን። አሁንም አሁንም ጠየቁን። ስንረሳ ገረፉን። ሌላ ቀን እንዳይረሳኝ፤ አስታውሺኝ እሺ?!”

የሕፃናት ድምፅ ይሰማ ጀመር።

ሀ – ሁ – ሂ – ሃ – ሄ – ህ – ሆ!

አ – ቡ – ጊ – ዳ – ሄ – ው – ዞ!

መልእከተ ዮሐንስ  . . . ወንጌል . . .

በአንድ ክፍል ውስጥ በተለያየ ዜማ የሚደመጡ ድምጾች።

የኔታ፣ የምንትዋብን ድምፅ ሰምተው ከመማሪያው ቤት ወጡ፤ የሚቋጩትን ነጠላ ይዘው። ጺማም ሽማግሌ።

ሁለቱም ሲተያዩ ደነገጡ። አቦቸርን ሊያስደነግጠው የቻለ ድንጋጤ። እናም ትንሽዬ ፊቱ ላይ ላብ ታየ። እየበዛ መጣ። የኔታ፣ ዓይናቸውን ዓይኑ ውስጥ እየፈለጉ ያሉ እስኪመስል ድረስ አዩት።

በቀስታና በቀዝቃዛ ድምፅ –

“ከስድስት ዓመት በፊት መሆኑ ነው? …” አሉ፤ “በበዓለ ጊዮርጊስ?! አይደል?” ብለው እናቱን ጠየቁ።

“ልክ ነዎት!” አለች ምንትዋብ፤ በመገረም አናቷን እየነቀነቀች፤ “ያኔ ዶሮ ማነቂያ ነበር ያለሁት”

*  *  *

ምንትዋብ፣ ነጠላዋን ለባብሳ አስፋልት ዳር ቆማለች። አልፎ አግዳሚውን ስትማትር ከሩብ ሰዓት በላይ አሳልፋለች። ሃምሳዎቹን ያጋመሱ የሚመስሉ አንድ ጠምጣሚ በአጠገቧ ሊያልፉ ሲሉ አየቻቸውና “አባ ያሳልሙኝ” አለቻቸው።

ቄሱ ጥያቄዋን ተግብረው ሊሄዱ ሲሉ፤

“እንዲያው ማስቸገር ባይሆንብኝ ያዘጋጀኋት ፀበል ጸዲቅ ነበረችኝ፤ እና እርስዎ ማዕዱን ቢባርኩልኝ . . .”

የቄሱ ምላሽ እምቢታ አልሆነም። ተያይዘው ወደ ምንትዋብ ቤት ሄዱ።

“ዳቦውን ከመቁረስዎ በፊት፤ መጀመሪያ ቤቴን ፀበል ቢረጩልኝ እንዴት ደስ ይለኝ ነበር? ጤናዬ መታወክ ከጀመረ ሰነባብቷል!” አለቻቸው “ሌቱን ደግሞ በቅዠት ነው የማሳልፈው!”

ፀበሉ ተዘገጃጅቶ መርጨት ጀመሩ። ሳሎኑ ተረጭቶ ሲያበቃ ‘መኝታ ቤቱም ይድረሰው’ አለችና መግቢያውን አመላከተቻቸው። መራቻቸውም።

“እንዲህ ያለ እምነት እያለሽ እንዲህ ባለ ርካሽ ቦታ መገኘትሽ ቅር ያሰኛል” ብለው መርጨታቸውን ሲቀጥሉ –

ምንትዋብ ከአልጋው ክፍል ወጣችና የመኝታ ቤቱን በር ዘጋችው።

የቤተክህነት ሰዎችን አትወዳቸውም። መሳቂያና መሳለቂያ ሲሆኑ ስታይ ነው ልቧ የሚረካው። በቀሳውስት ላይ የሚስቁ ጥርሶች እንዲበዙ ባደረገች ቁጥር አባቷን የተበቀለች ይመስላታል፤ አኗኗሯ እንዲበላሽ ያደረገውን አባቷን።

ቄሱ የበር መቆለፍ ድምፅ ሰምተው ዘወር ሲሉ ብቻቸውን ናቸው። መገረም ልባቸውን ገዛው።

“የኔ እህት . . .”

ዝም።

“የቀረኝ ቦታ የለም፤ ሁሉም ቦታ ረጭቼልሻለሁ”

ዝም።

“የኔ እህት … ምን እያደረግሽ ነው?”

“አንድ ያጠፉት ጥፋት አለ – ዋስ ካልጠሩ ልፈታዎ አልችልም!”

“እንዴ? ምነው? ምን አጥፍቼ? ማንን በድዬ …” ይለምኗት ገቡ።

“ምነው የሔዋን ልጅ? ምነው የእመብርሃን እህት? እንዲህ ያለውን እኩይ ሀሳብ ያሳደረብሽን መንፈስ ‘እክሕደከ’ በይው? … ምነው ልጄ ምን በደልኩ?… ሰተት ብዬ ተከትዬሽ ቤትሽን ፀበል ከመርጨት በቀር?”

“የሚያውቁት ሰው ካለ – ዘመድዎ ወይ የንስሐ ልጅዎ – ደውዬ ልጥራውና ባስጠሩት ሰው ፊት ሐጥያትዎን እናዘዛለሁ”

“የቅርብ ዘመድ ከየት አባቴ ልውለድ? ለራሴ በገንዘብም በዘመድም ምንም የሌለኝ መናጢ! በኪሴ ውስጥ ድር ማድራት ከጀመረ ስንትና ስንት ቀኑ!”

“እንግዲህ የሚበጅዎትን ለመምረጥ ምርጫው በእጅዎ ነው”

“የማይመስል ነገር መጠየቅሽ ነውር አይሆንብሽም የኔ እህት? ኧረ የማይሆን ቀልድ ይዘሻል…”

“ፍላጎቴን ካላሟሉ ያለ እህል ውሃ እንደተከረቸመብዎ ይቆያሉ”

“ኧረ ልጄ!…”

የቄሱ ተማፅኖ እየበረታ ሲመጣ ልቧ ሐሴት እያደረገ ነበር።

ቄሱ በሆነው ነገር እየተደናገጡ፤ ህልም እንዲሆንም እየተመኙ አንድ ነገር ተናገሩ።

“ይኸውልሽ! አሁን የምልሽን የምትፈጽሚ ከሆነ የምትፈልጊው ነገር በእጅሽ ይገባል” አሏት፤ እልህ ተናንቋቸው።

“ምን ይፈለግብኛል?” ተረጋግታ ጠየቀች። የቄሱ መርበትበት ምንትዋብን ደስ ማሰኘት ቀጥሏል።

“የምሰጥሽን ቁጥር ልብ ብለሽ ስሚ። ማሙሸት የሚባል የወንድሜ ልጅ አለ – ማሙሸት የሚባል! ስልኩን ሲያነሳ የዚህን ሠፈር ቤትና ትክክለኛ አድራሻ ስጪውና እንዲያገኘኝ አድርጊ!”

ማሙሸት ተደውሎለት መጣ።

“አጎቴ ምን ሆኗል?” አላት ተደናግጦ።

“በእዳ ተይዘው ነው። ‘በነፃ የተሰጣችሁን በነፃ ስጡ’ ይላል መጽሐፉ ብለው አልከፍልሽም አሉኝ”

“የጠጣበትን?!” አለ ማሙሸት።

“አልኮል እንኳ በአፋቸውም ደጅ አልዞረ!”

“ታዲያ የምን እዳ ነው ያለበት?”

“እንደዚህ ላለው ቀላል ጥያቄ መልስ መስጠት አለመደብኝም”

“ስትዪ …”

“መኝታ ቤት አልጋዬ ክፍል ገብተው አይደል ያገኘሃቸው? ምን ሲሰሩኝ የቆዩ ይመስልሃል?”

ቄሱ ድምፃቸውን አሰሙ። “ኧረ አንች ሴት ጡር ፍሪ! ምንድነው እንዲህ የሚያወሻክትሽ? ይኸውልህ ልጄ ነገሩ እንዲህ ነው…” አሉና ከመጀመሪያው ጀምረው ይተርኩለት ገቡ።

ይህ ሁሉ ሲሆን የተዘጋባቸው በር አልተከፈተም። በማሙሸት ፊት ላይ የማመንም ሆነ ያለማመን ነገር አይታይም። “ስንት ብከፍልሽ ነው አጎቴ ነፃ የሚሆነው?” አለ ኪሱን እየደባበሰ።

“ሃያ አምስት ብር ከሰባ አምስት ነው እሺ ያልኳቸው”

“ሰባ አምስቷ ደግሞ ምንድን ናት?”

“አንተን ደውዬ የጠራሁበት ነዋ! ሴት ካገኘሁ ቆይቻለሁ ብለው አስተዛዝነው ባይነግሩኝ ኖሮ ለሃያ አምስት ብር ብዬ …”

ቄሱ የርግማን ዶፍ ያዘንቡባት ጀመር። ወጡ።

አመሻሽ ላይ ቄሱ ራሳቸውን ለውጠው የተከፈለበትን ገላ ሊጎበኙ ሞቅ ብሏቸው መጡ።

* * *

ይህ ሁሉ ከሆነ ስድስት ዓመት አልፎታል። በማግስቱ የቄስ ትምህርት አልነበረም። በማግስቱ ማግስትም እንዲሁ … ሳምንት … ወር …ትምህርቱ ተቋረጠ። ለምን ቢባል የፊደል አስቆጣሪውን ዓይን አየሁ የሚል በመጥፋቱ።

አንድ ቀን ምንትዋብ “ያ ነገር እኮ አጣርቼ ደረስኩበት” አለችው አቦቸርን።

“የቱን?!…”

“የየኔታን ስም …”

“ማን ነው?”

“ገብረ መስቀል” አለች – እያንዳንዱን ፊደል ረገጥ አድርጋ።

ጭቃማ ወራት አለፉ። … ወደ ት/ቤት ሊመዘገብ ስትወስደው “ምንቴ …” አለ አቦቸር፤ በአዲሱ ሹራብ የእጅ ጫፍ ንፍጡን እየጠረገ።

“እ?”

“አንደኛ ክፍል ተመዝግቤ ስማር – አጠገቤ አስተማሪ የሚያስቀምጣቸው የማላውቃቸው ልጆች ‘የጨርቆስ ሠፈር ልጅ ነህ ወይ?’ ሲሉኝ፤ ‘አይደለሁም’ ነው አይደል የምለው?”

“ለምን? ‘ነኝ’ በል እንጂ!” ትላለች እናቱ፤ የሠፈሩን ስም የሚያስክድ ምን ተገኘ ብላ …

“ያበሽቁኛላ!”

“እነማን?!…”

“የጨርቆስ ሠፈር ያልሆኑ ልጆች”

“ምን ይሉሃል?”

“እንግዳ ሲመጣባችሁ የፎቶ አልበም ከጎረቤት ተውሳችሁ ነው ለእንግዳ የምታሳዩት ይሉናል። ምንቴ …” አላት ዓይንዋን ቀና ብሎ እያየ።

“አንድ ልጅ ደግሞ ምን አለኝ መሰለሽ? ‘የእናንተ እናቶች – አስራ ሁለት እስኪሞሉ ድረስ ይሰባሰቡና – ባለ ሁለት ብር ከአርባ አልበም ይገዛሉ። ከገዙ በኋላ ያዋጡ ሰዎች ሦስት ሦስት ፎቶ ያመጡና ይከቱበታል። ከዚያ እሁድ እሁድ እጣ የወጣለት ሰው እስከ ሳምንት ድረስ አልበሙን ቤቱ ይወስደዋል’ ብሎ እየሳቀ አበሸቀኝ”

“ሲያበሽቁህ አትብሸቅላቸው እሺ?!”

“ብሽሽቅ አስለምጂኛ! እንዳልበሽቅላቸው። … አንዳንዴ እንባ ያስመጡብኛል። አንድ ቀን ጋዜጣ ገዙና እኔን የማይመስል ሥዕል አዩና – ትላልቆች ናቸው እኮ! – ሲጋራ አስገዝተውኝ፣ መልሱን ውሰደው እንዲሉኝ ብዬ አጠገባቸው ስቆም፤ በጋዜጣው ላይ ሥዕል አዩና ‘አቦቸር ይኸውና’ ብለው የተጻፈ ነገር አንብበው አሳቁብኝ”

“ምንድነው ያነበቡት?”

“ሥዕሉን አይተውኮ ነው። አስተማሪው ባዶ ቦታዎችን ሙሉ ብሎ ጥያቄ ጠየቀ። ‘እናቴ ውሃ ጠጣች ካለ አባቴ ክትፎ  ’ ተብሎ ሲጠየቅ፤ ዳሽ በሚለው ቦታ ‘ክትፎ ናፈቀው’ ብሎ መልሱን ጻፈ ብለው ያላልኩትን አስወሩብኝ”

“ኧይ አቦቸር! ዛሬ በሳቅ ልታፈርሰኝ ታጥቀህ ተነስተሃል” አለች ምንትዋብ።

በልጇ ስም የሚቀለዱ ቀልዶች እየበዙ በመምጣታቸው አትቆጭም። ይልቁንስ -ትንሽ ትልቁ – ሴት ወንዱ ከአፉ የሚወጣውን ቃል ለመስማት ጆሮዎች ሲቀሰሩ ስታይ ደስ ይላታል።

“‘አባቴ ክትፎ በላ’ ነው መልሱ እሺ”

“አባቴ ክትፎ በላ ብዬ ስመልስ፤ ውሸታም ተብዬ በአለንጋ አልዠለጥም? አስተማሪያችን አያስበረክኩኝም?”

“ይጨበጨብልሃል”

ትንሽ ቆይቶ “አባቴ ክትፎ ነበር የሚበላው?” አለ ምራቁን እየዋጠ። “አንቺን ያስበላሽ ነበር? ወይስ ውሃ ብቻ እያስጠጣሽ ክትፎ ያስናፍቅሽ ነበር?”

“ማን?”

“አባቴ ነዋ! የማላውቀው አባቴ”

የምትመልስለት ስለማይኖራት ያልሰማች መስላ ፊቷን ታዞርበታለች። ረዣዥም ሳሮች የሞሉበት ግቢ ውስጥ ሕፃናት ይሯሯጣሉ። አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው።

እናት ከልጇ ጋር ሆና ስትጠባበቀው የነበረው ሰልፍ አልቆ ተራዋ ስለደረሰ ወደ ውስጥ ገባች።

“ስም? . . . ” ተነገራት ለመዝጋቢዋ።

“የአባት?”

አቦቸር ‘ምንትዋብ’ የሚል ጠበቀ፤ ግን አልሆነም።

“የአባቱ ስም?!” መዝጋቢዋ ዝምታ ሲበዛ መልሳ መጠየቅ ግድ ሆነባት።

“ገብረመስቀል” ኩራት በበዛበት ድምፅ ምንትዋብ መለሰች። ቀና ብሎ እናቱን አየ። በፈገግታ ጠይም ፊቱን አበራው።

እንባው መጣ።

ያ ቀን – ፀሐይዋ በደመና ሳትጋረድ … በሚርከፈከፈው ካፊያ መሃል … ትናንሽ እግሮቹን እያሮጠ … ለበርካታ ሕፃናት (ለሚያውቁትም ለማያውቁትም) የጨዋታው ርዕስ ይሄ ሆነ።

‘አባቴን እኮ አገኘሁት’ እያለ – ‘የኔታ ገርበመስቀል ይባላል’ እያለ –

‘ደስ የሚል የሚያሳምም ቁስል የሚያስመጣ አለንጋ ነበራቸው’ እያለ – ‘ደስ ደስ የሚል እናቴን የሚያናድዳት ስድብ ይሰድበኝ ነበር’

እያለ … እያለ … እያ … እ …

በእንዳለጌታ ከበደ

(1995 ዓ.ም)

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

[ምንጭ] – “ከጥቁር ሰማይ ስር” (፲፱፻፺፮)፤ ገጽ 39 – 64።

.

[ምስል] – በዕውቀቱ ሥዩም።

 

የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ

የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ

በዮሐንስ አድማሱ

(1961 ዓ.ም)

.

“እፍጻሜ ለማድረስ የምሞክረው ተግባሬ በተጻፈው ኃይለ ቃል እንድታዳምጡ፣ እንዲሰማችሁ፣ ከሁሉም ይልቅ እንድታዩ ማድረግ ነው። ከሱ ወዲያ ሌላ ተግባር የለኝም። በሱም ውስጥ ሁሉም ነገር ይካተታል። ከተቃናልኝ በሚገባችሁ መጠን መበራታት፣ መጽናናት፣ ፍርሀት፣ ሞገስ – የምትፈልጉትንም ሁሉ – ታገኛላችሁ። ትሿት ዘንድ የምትገባችሁን ግና የዘነጋችኋትንም እውነት በጨረፍታ ታይዋታላችሁ። ” 

ዮሴፍ ኮንራድ፣ “ኒገር ኦፍ ዘ ናርሲሰስ” ከተባለው መጽሐፍ መቅድም

.

ሥነ ጽሑፍ የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነት ኀይል ግዘፍ ነሥቶ፣ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው። የአማናዊ ሥነ ጽሑፍም ምንጩ የሰው ልጅ እውነታ (ሪአሊቲ) ነው። እውነታውም በልደትና በሞት መካከል የተዘረጋው ህላዌ ነው።

ሥነ ጽሑፍ ጠቅላላ ዓላማው ማስደሰት ነው። ይኽንንም ጉልህ አላማ የሚፈጽመው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕይወት ሒስ በማቅረብ ነው። ሥነ ጽሑፍ ጉልህ ዓላማውን ለመፈጸም ጥራትና ወጥነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። “በኑኀ ዘመን በቀን ብዛት፣ የማይነቅዝና የማይሻግት” መሆን አለበት። አለዚያ አጉል ጉሕና ወይም ብስና እንጂ ሥነ ጽሑፍ ሊሆን አይችልም። ሥነ ጽሑፉን ሥነ ጽሑፍ የሚያደርገው የደራሲው የኪነት ኀይሉ፣ የማስተዋልና የማንጠር ስጦታው፣ ያስተዋለውንና ያነጠረውን ከሰው ልጅ እውነታ ጋር በቋንቋ ኀይል አገናዝቦና አዋሕዶ እነሆኝ ብሎ የሚያቀርብበት ልዩ ችሎታው ነው። ግልብ ደራሲ ግልብ ተመልካች ነው። ጽሑፉም በዚያው ልክ ግልብ፣ የችርቻሮ ጽሑፍ ይሆናል።

ይህን አባባል መሠረት በማድረግ ከሠላሳ ሦስት እስከ ስድሳ አንድ ዓመተ ምሕረት (1933-1961) ድረስ ስላለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ አንዳንድ ነገር ለማውሳት እወዳለሁ።

በጠቅላላው በነዚህ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ አማርኛ ያፈራው ሥነ ጽሑፍ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። ከጥልቀት ይልቅ ግልብነት፣ ከውበት ይልቅ አስቀያሚነት (አስቀያሚነት ውበት ነው ወይንም ውበት አለው ካልተባለ በቀር)፤ ከሥነ ጽሑፋዊ እውነት ይልቅ የአንቀጸ ብፁዓን ምኞት ይገኝበታል። ሥነ ጽሑፍ የሕይወት ሒስ በመሆን ፈንታ የወሸነኔ ስሜት መግለጫ ሁኗል። እስከ አሁን ድረስ አካሄዱ አጉል ነው፤ የጎድን ነው። አቅጣጫም ያለው አይመስል። የወደፊት አካሄዱን መተንበይ ባይቻልም፣ እስከ አሁን ድረስ ተመልክተን የተገነዘብነው አካሄዱ ለወደፊት አካሄዱ አብነት ለመሆን የሚችል አይደለም።

በአጭሩ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ ቀደም ካለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ አዝመራ ጋር ሲነጻጸር ደረጃው፣ ጥራቱና ወጥነቱ፣ በዚያውም መጠን ውበቱና አስደሳችነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። እያደር ይጫጫል፤ እየሰነበተ ይደገድጋል፤ እየባጀ፣ እየከረመም ይመነምናል። ለዚህ አሳዛኝ፣ ከቶም ድቀታዊ ሁነት ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ነገሮች ሦስቱን ጠቅሼ ከመዘርዘሬ አስቀድሞ ጥራት፣ ወጥነት፣ ጥልቀትና ውበት ያላቸው ሁለት መጻሕፍት መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሁለቱ መጻሕፍት “እንደ ወጣች ቀረች” እና “ፍቅር እስከ መቃብር” ናቸው። (ከነዚህ ከሁለቱ ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች መጻሕፍት በመጠኑ አሉ።)

እነዚህ ሁለቱ መጻሕፍት የኪነት ውጤት ናቸው፤ ጥልቀታቸውም፣ ውበታቸውም፣ ሌላውም መልካም የምንለው ጥራታቸውም ከዚሁ ከኪነት መንፈሳቸው ይሠርጻል። በ”ቴክኒክ” (ቅርጽ) በኩል ከሞላ ጎደል ምሉዕ ናቸው – በትልም፣ በባሕርያት አቀራረጽ፣ በአተራረክ፣ በቋንቋ … ወዘተ። እነዚህ ሁለት የልብ ወለድ መጻሕፍት በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች የሰነዘርኋቸውን ሐሳቦች በሙሉም ባይሆን በከፊል አቀናብረው ይዘዋል። ሁለቱም ሁለት ልዩ እውነታ ያቀርባሉ። በአንድ ነገር ይተባበራሉ፤ ይገናኛሉ። ሁለቱም ያቀረቡልን የሕይወት ሒስ ነው። ሁለቱም በየገጾቻቸው በሚገኙት ቃላት ኀይል እንድናዳምጥ፣ እንዲሰማን፣ በተለይም እንድናይ ለማድረግ ሞክረዋል።  ይኸም ሙከራቸው በሙሉም ባይሆን በከፊል ስለተቃናላቸው የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ አድርገዋል። በዚሁም እኛ አንባብያኑ ሐሤት እናደርጋለን።

በጠቅላላው ከሠላሳ ሶስት ዓመተ ምሕረት ወዲህ ጥሩ የምንላቸው የአማርኛ (የኪነት) መጻሕፍት ጥቂት ናቸው። ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ “ብላሽ” ናቸው። ለምን?

ደራስያኑ በደፈናው ወይንም በጠቅላላው ስለ ልዩ ልዩ የኪነት ጽሑፍ ቴክኒክ አያውቁም፤ ቢያውቁም አይጨነቁም። ጽሑፋቸውን የቴክኒክ ግብዝነት አለልክ ያጠቃዋል። የጽሑፍ ቴክኒክ ለኪነት ጽሑፍ ዓቢይ ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። የሀገራችን የኖረ፣ የቆየ የጽሑፍ ቴክኒክ አለ፤ የውጭ ሀገርም የጽሑፍ ቴክኒክ አለ። ደራስያኑ የውጭውንም ሆነ የሀገራችንን የጽሑፍ ቴክኒክ አብስለውና ጠንቅቀው አያውቁትም።

በሀገራችን (ለምሳሌ ያህል) የታወቀ፣ የተለመደ፣ ከሙያ የዋለ የገድል አጻጻፍ ቴክኒክ አለ። ገድል የአንድ ሰማዕት ወይንም የአንድ ጻድቅ የሕይወት ታሪክ ነው። ገድል በጠቅላላው የሚያወጋው ወይንም የሚተርከው የሰማዕቱን ወይንም የጻድቁን ተጋድሎ ነው … ስለሰማያዊ ልዕልና፤ ለሰማያዊ ክብር መንፈሳዊ የሆነ ምድራዊ ተጋድሎ። አተራረኩ በመንፈሳዊ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ትልምና ባሕርያት የአተራረክ ስልትም አለው። የአተራረክ ፈሊጥም አለው። ብሎም “ገድለ ተክለ ሃይማኖትን” መጥቀስ ይበቃል። አንቱ የሚባል ወይንም ለመባል የሚሻም ደራሲ የገድልን አጻጻፍ አጥርቶ ማወቅ ግዴታው ነው። ብዙ ነገር ይማራል፤ አያሌ ጥበብ ይቀስማል። በቴክኒክም ይበለጽጋል።

የቅኔ ቴክኒክ አለ። ይኽንንም ቴክኒክ ማወቅ የማንኛውም ደራሲ፣ በተለይም የገጣሚ ተግባርና ግዴታ ነው። (የቀረውን እንዳለፈው ያነቧል።) ሌሎችም ብዙ የጽሑፍ ቴክኒኮች በሀገራችን በብዛት ይገኛሉ – የተረት፣ የሙሾ፣ የእንቆቅልሽ፣ የእንካስላንቲያ፣ የቀረርቶ … ወዘተ። እነዚህን ሁሉ አንቱ የሚባል ወይንም ለመባል የሚሻ ደራሲ አጠናቆ ማወቅ ግዴታው ነው።

ከውጭውም ዓለም የተገኙ የጽሑፍ ቴክኒኮች አሉ፤ የተውኔት፣ የረጅም ልብ ወለድ፣ የአጭር ልብ ወለድ … ወዘተ። ደራስያናችን የውጭውንም የጽሑፍ ቴክኒክ አጥርተው አያውቁትም። በአጭሩ፣ የሚጽፉት አገኝ አጣቸውን ነው። የሚጽፉት በንዝሕላልነት፣ ብዙ ጊዜም በግዴለሽነት፣ በማን አለብኝ መንፈስ ነው። ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ብዙ መጻሕፍት አሉ። ለጊዜው ግን አንዱን መመልከት ይበቃል።

“አድልዎን በሰይፍ” መጽሐፉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ “ብላሽ” ነው። ጉድለቱ ወሰን ዲካ የለውም። ጥራቱ ጉድለቱን ጉልህ አድርጎ ማሳየቱ ነው። ታሪኩ የሚተረከው በአንደኛ መደብ፣ ነጠላ ቁጥር (እኔ) ነው። አንድ ታሪክ በአንደኛ መደብ መተረክ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ታላቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አደገኛ ነው። በተለይም ለጀማሪ ደራሲ ክፉ፣ አዚመኛ አንጋዳ ነው። እላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ በአንደኛ መደብ ይተርክና መጽሐፉ ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው “ሞትኩ” ይላል። ይኽን የሚለው የታሪኩ ዋና ባሕርይ ነው። ባሕርዩ መደቡ አንደኛ መደብ ነው። “ሞትኩ” ካለም በኋላ ታሪኩን ይተርካል። ሙቷል፣ በአጸደ ሥጋ አይገኝም ማለት ነው። ይኽ ንስሐ የሌለው ታላቅ የቴክኒክ በደል ነው።

እንደዚህ ያለው በደል የሚፈጸመው ምናልባት ካለማወቅ ይሆናል፤ ምናልባትም ከንዝሕላልነት፣ ወይም ከንቀት። ምክንያቱ የትኛው እንደሆነ አላውቅም። ከደራሲው ጋር መነጋገር ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳ ይሆናል። ይኽንንና ይኽን የመሰለ የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው መጻሕፍት እጅግ ብዙ ናቸው። የሚከተሉትን ይመለከቷል፤ “ውብ ነበረች”፣ “ሥራ ገንዘቡና ጓደኛው”፣ “የጉድጓዱ ምሥጢር”፣ “ንስሐ”፣ “እውነት ስትጠፋ”፣ “የሐሳብ እስረኛ”፣ “ከማን አንሼ”፣ “እኛም ይድረሰን” … ወዘተ። እነዚህ መጠቀስ ከሚገባቸው መካከል በጣም ጥቂቱ ናቸው።


የዘመናችን ደራሲያን በጽሑፍ ቴክኒክ በኩል ከሀገራቸውም አልሆኑ፤ ከውጭውም አልሆኑ። የሀገራችንንና የውጭን አዳቅለውም መጢቃ ቴክኒክ አላቀረቡልንም። ወይንም ከሁለት አንዱን ብቻ ተከትለው ወጥ ጽሑፍ አላበረከቱም። እስከ አሁን ድረስ ቴክኒካቸው ውጥንቅጥ፣ የልብ ትኩሳት፣ የልብ ቃር የሚሆን አጉል ቅይጥ ነው። ከሥርዓት ይልቅ ምስቅል የሰፈነበት ነው።

ምናልባት ከዚህ ውጥንቅጥ፣ ከዚህ ምስቅል ኢትዮጵያዊ የሆነ ወጥ ቴክኒክ – እንደ ብሂል፣ እንደ ሠረዝ፣ እንደ ጎዳና ቅኔ ያለ ይጸነስ ይሆናል። ይኽ መቸም ምኞት ነው። ምኞቱ እውነት እንዲሆን የኔ ብቻ ሳይሆን ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ማደግ፣ መዳበርና ኀያል መሆን የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፍላጎት ነው።

ሁለተኛው ነቁጥ የሒስ ጥበብ አለመለመድና የሐያሲ አለመኖር ነው። በባህላችን የሒስ ጥበብ አልነበረም፤ የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከዚህም የተነሳ ደራስያኑ መጻሕፍታቸው በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ሲተቹ (በቀጥተኛ ሒስ) አንዳንዶቹ ያኮርፋሉ፤ አንዳንዶቹ ይዝታሉ፤ አንዳንዶቹ በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ይሳደባሉ። ይኽ መንፈስ ከየት እንደመጣ አላውቅም። ጉዳዩ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ይሁን እንጂ አንድ የማውቀው ነገር አለ። ሒስ በቅኔ ቤት የተለመደ ነው። የቅኔው ተማሪ፣ ከቅኔው ትምህርት ሌላ፣ በጥበቡ የሚጎለምሰው፣ የኪነት ተውህቦውን የሚያተባው፣ የሚያራቅቀውና የሚያደራጀው በሒስ ጥበብ ነው። የተማሪውን ቅኔ የቀለም ጓደኞቹና መምህሩ ይተቻሉ። እሱም እንደዚሁ ያደርጋል። ተማሪዎቹ የመምህራቸውን ቅኔ ይተቻሉ፤ አንዳንዴም ብትንትኑን ያወጡታል። ኩርፊያና ስድብ፣ ዛቻና ቅያሜ የለም፤ ይህ መልካም ጥበብ እያለ ደራስያናችን ለምን በሒስ (በደንበኛ ሒስ) ይቆጣሉ?

ሒስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛና ፍቱን መድኃኒት ነው። ሒስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ ነው። ማስተማሪያም ነው። እንደ ስድብ፣ እንደ ነውር መቆጠር የለበትም። በሒስ መስተዋትነት ስኃውን የማይከላ ሥነ ጽሑፍ ሆነ ደራሲ ከበድን አንድ ነው። ተገቢ ቦታውም ቤተ መዘክር ነው።

ሦስተኛው ነቁጥ፣ ያለፉት የሃያ ሰባት ዓመታት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሦስተኛ ጉድለቱ የቋንቋ ነው። በጠቅላላው ቋንቋው ውበት፣ ጥራትና ተጠየቅ  የተለየው  በጸያፍ (ሰዋስው) የተበከለ በቃላት እጥረት የተሞሸረ ነው። ይኽን ጉድለት የፈጠሩ ደራስያኑ ናቸው እንጂ ቋንቋው አይደለም። ቋንቋው ማለፊያ ባለሙያ፣ ልባም ደራሲ ካገኘ ብዙ ሰነፍ የሚያስገባ አይመስለኝም። ለዚህም አብነት የሚሆኑ የሚከተሉት ቀደምት ደራስያን ናቸው፤ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አለቃ ታዬ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ … ወዘተ። በመጻሕፍት በኩል (እላይ የተጠቀሱት ደራስያን ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ) መጽሐፈ መነኰሳትን፣ አርባዕቱ ወንጌልን መመልከት ይበቃል።

  afework-tobya heruy-wedaje kidane-hizqel

የአሁኑ ዘመን ደራስያን አማርኛ ለምን ተበላሸ? በዚሁስ የሚቀጥለው ለምንድር ነው? ሁለት ምክንያት መስጠት ይቻላል። አንደኛ ደራስያኑ፣ ትምህርት ቤት በነበሩበት ጊዜ ጥሩ አማርኛ እንዲማሩ አልተደረገም። ሁለተኛ ደራስያኑ የሚያነቡ አይመስልም። ጥሩ ጥሩ የሆኑ፣ ተነበው በቋንቋቸው ጥራት፣ በዘይቤያቸው ውበት የሚሰዩ መጻሕፍት ጠፍተው አይደለም፤ አሉ። ከፍ ብዬ የጠቀስኋቸው መጻሕፍት ጥቂቱ ናቸው፤ እነሱን የመሳሰሉ በብዛት አሉ። ፈልጎ ማንበብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። መጻሕፍቱን የጠቀስኋቸው ስለ ይዞታቸው ሳይሆን (ይዞታቸውን የማይፈቅዱ ይኖሩ ይሆናል)፣ በጠቅላላው ስለቋንቋቸው ጥሩነት ነው፤ ስለምናባቸው (ኢማጂኔሽን) ስፋት ነው፤ ስለ ዘይቤያቸው አስገራሚነትና ውበት ነው። ዛሬ ያሉንም ሆኑ ወደፊት የሚነሡት ደራስያን እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን መጻሕፍት በየጊዜው ቢያነቡ ቋንቋቸው ይዳብራል፤ አስተሳሰባቸው ይተባል፤ ሐሳባቸውን – ጃ ሳይላቸው – እንደ ልባቸው መግለጽ ይችላሉ። የማይሰለች፣ ለዛና ወዝ ውበትና ጥራት ያለው፣ “ዞሌ” ጽሑፍ መጻፍ ይችላሉ።

የጽሑፌ ኀይለ ቃል በድርሞ መልክ የሚከተለው ነው። በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በጠቅላላው ጥራቱና ወጥነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። ይኽም የሆነበት ምክንያት፣

/ በቴክኒክ ጉድለት፤ / በሒስና በሐያሲ እጦት፤ / በደራስያኑ አማርኛ መበላሸት።

ከነዚህም ምክንያቶች ለሁለቱ (“” እና ““) ኀላፊዎቹ በከፊል ደራስያኑ ናቸው። አያነቡም፤ የማወቅና የማጥናት ጉጉት የላቸውም። ለሁለተኛው ምክንያት (““) ኀላፊነታቸው ኢርቱዕ ነው። ሒስ አለመቀበላቸው ወይንም በሒስ መበርገጋቸው።

የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የተሻለ ደረጃ እንዲይዝ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ተጽዕኖው ለመላው ዓለም እንዲተርፍ ከተፈለገ ደራስያናችን (ዛሬ ያሉትም ሆኑ ወደፊትም የሚነሱት) ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው። የተጋድሎው ጎዳና ረዥም ሆኖ ጎዳጉድ የበዛበት፣ ቅርቅፍት ነው፤ ተስፋ መቁረጥ ግን አያስፈልግም። እንደጥንታውያኑ ለሀገራቸው ነጻነት ሕይወታቸውን፣ በየጎራው፣ በየሜዳው፣ በየአረሁ እንደሠዉት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ባጭር ታጥቆ ፣ የሥነ ጽሑፍ ዘገር ነቅንቆ፣ የሥነ ጽሑፍ ጋሻ መክቶ ለሥነ ጽሑፍ መጋደል የየእያንዳንዱ ደራሲ ፈንታ ነው።

ኢትዮጵያውያን ደራስያን በዓለም የሥነ ጽሑፍ ሸንጎ ላይ ተሰልፈው የሚወዳደሩበትን ዕለት በናፍቆት እጠባበቃለሁ።

.

.

.

.

.

ዮሐንስ አድማሱ

[ምንጭ] – “መነን” መጽሔት፤ ግንቦት ፲፫፣ ፲፱፻፷፩ (ገጽ ፲፪-፲፬)።

አስኮ ጌታሁን እና ‘ዝምታ’

አስኮ ጌታሁን እና ‘ዝምታ’

በአዳም ረታ

.

አስኮ ጌታሁን” የተባለው የጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል የአጭር ታሪኮች መድብል በውስጡ ሰባት ትረካዎችን ይዟል። በእነዚህም ትረካዎች ውስጥ ገኖ የሚታየው ሸካራ እውነታና እነዚህን ለመግለጽ የፈሰሰው አስገራሚ የገለጻ ቋንቋ ነው።

የጃርሶ ትረካዎች መቼት ከ1966 ዓ.ም በፊት ነው። በዚያን ጊዜ ወጣት ወይም ልጅ የነበረ ምን ያህል እነዚህ ታሪኮች ውበትና የዘመን ውክልናን እንዳቀፉ ሊሳተው አይችልም። ትረካዎቹ በሆነ መልክ የባህላችን ታሪክ፣ በሌላ መልክ ደግሞ የትዝታ እና የናፍቆታችን ሩካቤዎች (Communications of Nostalgia) ናቸው።

እነዚህ ውበትና ማህበራዊ ሀላፊነት የተመዘገበባቸው ትረካዎች ከተለያዩ የሥነጽሑፍ ሂስ ትወራ፣ የስነልቡናና የፍልስፍና መስመሮች አንጻር ሊታዩ ይችላሉ። ሆኖም ሁሉንም በዚህ መልክ ለማንበብ መሞከር ራሱን የቻለ ግዙፍ ስራ ነው። በከፊል ከጊዜ፣ በከፊል ከሀያሲነት ዕውቀት እጥረት ለማስታረቅ የመጽሐፉን “መሪ ታሪክ” (አስኮ ጌታሁን) ብቻ በመውሰድ፣ እንደገናም ከዚህ ትረካ ውስጥ አንድ ሴማ (Theme) ብቻ በማውጣት ንባብ ለማድረግ እሞክራለሁ።

ከሰባቱ ትረካዎች “አስኮ ጌታሁን”ን የመረጥኩበት ምክንያት የመጽሐፉ ማሰባሰቢያ አርእስት ስለሆነ ሳይሆን የ“አስኮ” ትረካ አጻጻፍ ከሌሎቹ የተለየ በመሆኑ ነው። በዚህም (ትረካ የተለየ መሆኑ) ደራሲው/ተራኪው ምን ሊነግረን ፈልጎ እንደሆነ ከመጠርጠር የመጣ ነው። አንድ የኪነት ስራ ከደራሲው እጅ ወጥቶ አንባቢ ዓይን ስር ሲያርፍ ባለው ማህበራዊ ዐውድ፣ በግለሰቦች የባህርይ ዝንባሌና አድልዎ የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። ይሄ ንባብ በመጠኑ የእኔም አድልዎ ነው።

አስኮ ጌታሁን” 12 ገጾች ሲኖሩት በሰላሳ አንቀጾች የተከፋፈለ ነው። የትረካው አንጻር ገለልተኛ፣ ከፊል ሁሉን አወቅ ነው። አስጨናቂ የደይን ክስተቶችን ተራኪው ሲጽፋቸው ቋንቋው ውስጥ ሐዘን የለም። ራሱም ምን እንደሚሰማው አይገልጽም። ትረካው በስፋት ነገሮችን ከውጭ ስለሚገልጽ ተራኪው ስለአስኮ ስነልቦና ከእኛ የተለየ ብዙ ነገር አያውቅም ብለን እንድንጠረጥር ያደርገናል።

ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ (አስኮ ጌታሁን) ከገጠር አዲስ አበባ ይመጣሉ። አስተማሪነት ይቀጠሩና ወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ወ/ሮ ስህን ት/ቤት ይሄዳሉ። እዛ በአስተማሪነት ብቻ ሳይሆን በትርፍ ጊዜያቸው ጫማ ጠጋኝ በመሆን ራሳቸውን ይጠቅማሉ፤ ሕብረተሰቡንም ያገለግላሉ። ከሚሰሩበት የትምህርት አስተዳደር መዋቅር ወጥተው በሐሳብ ከሚመስሏቸው ወገኖቻቸው ጋር በመሆን በየገጠሩ ገበሬ ወገናቸውን ፊደል ያስቆጥራሉ። በተጨማሪም ስለ ትምህርት አስፈላጊነት የሚሰብክ ፍልስፍናቸውን በተመቻቸው ቦታ ያነሳሉ፣ ይከራከራሉ።

እኒህ ድርጊቶቻቸው ግን “አገር እናስተዳድራለን” በሚሉ ግለሰቦች አልተወደዱም። በሥርዓቱም ማሳደኛ ጥበብ አስኮ ጌታሁን በአካባቢው ነዋሪዎች እንዲጠሉ፣ እንዲጠረጠሩና እንዲሸሹ ይደረጋል። አልፎ ተርፎ በመገለል መቀጣቱ ሳይበቃቸው የአካልና የሕግ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። በአንድ ወቅት በተፈጠረ ቀላል አምባጓሮ መሀል ጣልቃ የገቡ እናታቸው ይሞታሉ። አስኮም ለአጭር ጊዜ ይታሰራሉ። ከዚህ አጭር እስር እንደወጡም ብዙ ሳይቆይ ሰበብ ተሰርቶ በሐሰት ተወንጅለው ሃያ ዓመት ተፈርዶባቸው አዲሳባ ከርቸሌ ይወርዳሉ።

ከአስራ ስምንት አመታት በኋላ ከከርቸሌ ነፍስ ይማር ይፈታሉ። የአስተማሪነት ነገር ተረስቶ፣ ጤንነታቸውም ተቃውሶ አዲሳባ ተክለሃይማኖት አደባባይ በጫማ ሠሪነት ‘እየተዳደሩ’ ይኖራሉ።

አንድን አጭር ታሪክ አንብበን ስንጨርስ የተራኪውን ሃሳብ ወይም የታሪኩን መልእክት ለማወቅ “ተራኪው/ደራሲው ምን ለማለት ፈልጓል?” የሚል ጥያቄ መጠየቃችን አይቀርም። በእኔ ግምት ደራሲው ስለ ‘ዝምታ’ ለመጻፍ መሞከሩ ነው። ምንም እንኳን በራሴ አድልዎ የድርሰቱ መልእክት ዝምታ ነው ብዬ ብነሳም የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም አስሰናል ሊሉ ይችላሉ።

ጥቂት ምሳሌዎች እነሆ፤ አንዳንድ አንባቢ “በጥቅሉ ስለ አንድ ሥርዓት ጭቆና ያሳያል” ብሎ ይደመድማል። አንዳንዱ “ባለታሪኩ የነበረበት የፊውዳል ሕብረተሰብ ብዙ ዜጎችን ምሕረት በሌለው ተመሳሳይ መንገድ በሚጨቁንበት ወቅት እምቢተኛ ግለሰቦች መኖራቸው አይቀርም። ግን እነዚህን እምቢተኞች ስለምን መሰል ተጨቋኞች ያገሏቸዋል? እኩል እየተጨቆኑ ለምን እኩል እምቢ አይሉም?” አይነት ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል።

ሌላው ደግሞ “አስኮ ጌታሁን ራሱን በነጠላ ለአደጋ በማጋለጡ ፍዳ ዘንቦበታል፣ ስለሆነ ይኼም ስለ ፖለቲካ ድርጅትና ስለ መሰሉ ድርጅቶች መኖር ጠቀሜታ ያሳየናል። አለበለዚያ ‘ብቻውን የታገለ ብቻውን ይሞታል’ አይነት ይሆናል፤ ትረካውም ስለዚህ አይነት ነጠላ መሥዋዕትነት ሊያሳየን የተነገረ ነው” ሊለን ይችላል።

አንዳንድ አንባቢዎች ደሞ “ለሚያምኑበት ዓላማ ፊት ለፊት ተጋፍጠው በዚህ ሰበብ የሚመጣባቸውን መሥዋዕትነት ስለሚቀበሉና ስለሚጠፉ ግለሰቦች አጢነናል” ሊሉ ይችላሉ። አንዳንዱ “ስለ ተዛባ ማህበራዊ ሩካቤና ሕብረተሰቡ ደካማ አሉባልተኛ በመሆኑ ለፍሬ የታገለለትን ግለሰብ ታሪክ የተዛባ መንገድ ተጠቅሞ መረዳት እንደሚሞክር (‘አስኮ ትልቅ የከሰረ ነጋዴ ነው’ ወይ ‘ሚስኪን’ ወይ ‘እብድ’ ነው) ለማሳየት የተጻፈ ነው” ሊሉ ይችላሉ።

እነዚህ ሁሉ አማራጭ አተረጓጎሞች ግን እንደሚመስለኝ ከሚፈለገው በላይ አድልዎ ባለበት ግፊት የሚነቃነቁና ጠባብ የሆኑ ናቸው። “ደራሲው ለምን ለአተረጓጎም እንዲቀለን እሱ ራሱ ልንረዳለት የሚፈልገውን አንድ ማዕከላዊ ሴማ በሚጎርፍ ቋንቋ አውጥቶ አያሳየንም ነበር?” ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ለምሳሌ፣ ድርሰቱ መጀመሪያ ላይ ጃርሶ ስለ አስኮ ተክለቁመና/መልክ በስፋት ገልጿል። ስለ ሥራው አካላዊ አካባቢ ብዙ የተብራራ ነገር አበጅቷል። “ለምን ታዲያ የዝምታን ጉዳይ በስፋት አልተናገረውም?” ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

ግን ሴማዎች የሚቀናበሩበት ደረጃ ይኖራል። በግልጽ እንዲህ ነው ከሚለው ጀምሮ በትንሽ ልፋት እስከሚገኝ ትርጉም ድረስ። የኋለኛውን ጥልቅ ሴማ (Deep Theme) እንበለው። የዝምታን ሴማ መዝዤ ሳወጣ “በአንተ ፍላጎት የመጣ አተረጓጎም ምኞት ነው” እንኳን ብባል (በተለያየ መልክ በደግግሞሽ ንባብ የሚከሰቱ) ደጋፊ ምልክቶችንና ይሄን ሴማ አጥረው የያዙ የመረጃ እብነ ወሰኖችን ድርሰቱ ውስጥ እናገኛለን።

ትረካው ውስጥ ወዳለው የዝምታ አወቃቀር ለመግባት ግን የሆነ ቀዳዳ ያስፈልገኛል። ዝምታን ተርትሬ ለመረዳትና የድርሰቱ “ዋና አጥንት” እሱ ነው ለማለት የሆነች ቁጢት ቆንጥጨ መያዝ ነበረብኝ። ይህቺ ቁጢት ‘ታስፈሩኛላችሁ’ የምትለዋ ቃል ናት።

የአስኮ ታሪክ በአስራ ሁለት ገጽ ብቻ መቅረቡ ‘አንዱ’ ምክንያት ንግግር ድርሰቱ ውስጥ አለመኖሩ ነው። ይሄ የተሰወረው ወይም ተሸርፎ የቀረበው ከፊል ንግግር የአስኮ ነው። የአስኮ ጌታሁን ዝምታ ወይም ጸጥታ የድምጽ አለመኖርን ወይም መሰወርን ይጠቁማል። ዝምታ ማለት (በሳይንሳዊ ትርጉሙ) በጆሮ የስሜት ሕዋሳት ልንቀበላቸው የሚቻሉ የድምፅ ሞገዶችን ከአፋችን አለማውጣት ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሰፋና ከበረታ ከአፍ የወጣውን የራስ ድምፅ መስማት አለመቻል ወይም በሌላ የውጭ አካል ወይም የግል አቋም መከተርንም ይጨምራል። የዝምታን ትርጉም ትንሽ ለማብራራት አንዳንድ ጥያቄዎች በመጠየቅ እነሳለሁ።

አንደኛ እዚህ የምንነጋገረው ስለ ሰው ልጅ ነው። በዓለም ላይ ደሞ ድምፅ የሚያወጣው የሰው ልጅ ብቻ አይደለም። በራሳቸው የተፈጥሮ ግፊት ድምፅ ማውጣት የሚችሉና የማይችሉ አሉ። ሰው የሰራቸው ሜካኒካዊ ነገሮች ሁሉ ከራሳቸው ግፊት (Volition) ድምፅ አያወጡም። ይሄን ልዩነት የሚያሳይ የቃል አጠቃቀም ይኑረን አይኑረን አላውቅም። ምናልባት ሊኖር ይችል እንደሆነ በማለት ከቃላት ትርጉምና አጠቃቀም በመነሳት ልዩነት ለማበጀት ሞክሬ ነበር።

በመዝገበ ቃል ፍቺ ‘ዝምታ’ እና ‘ጸጥታ’ እንዲህ ይተረጐማሉ፤

 1. ዝም፤ – መጨረ (ቁጥር)
 2. ዝምታ፤ – ጭጭ፣ ቃል አለመስጠት፣ አለመናገር
 3. ዝም አለ፤ – አረመመ፣ ከመናገር ተከለከለ
 4. ጸጥታ፤ – መርጋት፣ ማረፍ፣ መቆም፣ መጨመት

(“ዐዲስ መዝገበ ቃላት” በደስታ ተክለወልድ ፲፱፻፷፪)

‘ደኑ ዝም ያለ ነው’ ማለት እንችላለን? ‘ደኑ ጸጥ ያለ ነው’ስ? አንድ በዕቃ የተሞላ ባዶ ክፍል ውስጥ ብንገባ የሚያጋጥመን ዝምታ ነው ጸጥታ?

ለምሳሌ፣ በአማርኛ ፊደል ጸጥታ የሚጻፈው በ‘ፀ’ አይደለም። ምክንያት ይኖረው ይሆን? በደስታ ተክለወልድ አባባል የጸጥታ ሥሩ ግዕዝ ነው። ከዛ ወደ አማርኛ የገባ የትርጉም ልዋጤ ይኖር? ብዙ የማይናገር ሰው ‘ዝምተኛ’ ይባላል (‘ጸጥተኛ ነው’ አይባልም)። ከአንደበት ጋር የተያያዘ ነው (ምላሳም፣ አፋም፣ አፈኛ እንደመሳሰሉ ቃላት)።

‘ዝም’ የሚለው ቃል ለሰው የሚቀርብ ነው። ምክንያቱም አብሮት ቋንቋ መናገርና ቁጥር ይጠቀሳሉ። ‘ጸጥታ’ የሚሰጠው ፍቺ በመጠኑ ሰፊ ነው ብለን ልንጠረጥር እንችላለን። ምንም እንኳን ይሄ ፅንሰ ሃሳብ የበረታ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም እኔ በመጠኑ አድልዎ ላስገባና እዚህ ንባብ ውስጥ የምጠቀመው ‘ዝምታ’ የሚለውን ቃል ይሆናል።

ዝምታን ከሰው ልጅ ካያያዝነው ባህላዊ እሴት ይሆናል። እንደማንኛውም ባህላዊ እሴት ይተረጎማል። ዝምታ በባህላችን አሻሚ ወይም አያኖአዊ ቦታ አለው። የአነጋገር ምሳሌዎች በመውሰድ ማረጋገጥ እንችላለን።

ደማሪ መልኩ፤ (“ካልተናገሩ ደጃዝማችነት ይቀራል”/ “መልካም ምላስ መልሕቅ ነው”/ “ዝም አይነቅዝም”)

ቀናሽ መልኩ፤ (“በለፈለፉ አፍ ይጠፉ”/ “አፍ ሲከዳ ከሎሌ ይብሳል”)

እዚህ ንባብ ውስጥ የምንነጋገርበት ዝምታ ሰዎች እየተወያዩ እያሉ ተራ ለመጠበቅ የሚወስዱትን እፎይታ አይደለም። በተጨማሪም በባህል አወዳዳሪ ጥናት እንደሚደረገው አንዱን ባህል ከሌላው ‘ዝምታ ያደንቃል’/‘ማውራት ያደንቃል’ በሚለው አፈራረድ ስር የሚገባም አይደለም።

እዚህ የማነሳው የዝምታ ፅንሰ ሃሳብ ልቀት ያለውን፣ ግለሰቦች በቋንቋ ከመሰል የሕብረተሰብ አባላት ለመገለል የወሰዱትን የጓነ መገንጠል (Radical Split) ለመጥቀስ ነው።

.

(በክፍል 2 ይቀጥላል)

አዳም ረታ

አስኮ ጌታሁን እና ‘ዝምታ’ (ክፍል 2)

አስኮ ጌታሁን እና ዝምታ

(ክፍል ሁለት)

በአዳም ረታ

.

(ከክፍል 1 የቀጠለ)

አስኮ ጌታሁን አጭር ታሪክ ኪነ አገነባብ ሁለት ፈርጆች አሉት። የቦታና ተውላጣዊ/ሰዋስዋዊ አንጻር። በቦታ ደረጃ ድርሰቱ በሁለት ስፍራዎች ዙርያ (ወሎና አዲስ አባ) የሚያውጠነጥን ነው። የመጀመሪያው ክፍል እንደ አሁን ጊዜ ሆኖ የሚያነሳው ተክለ ሃይማኖት/አዲስ አባን ነው (ሰሌዳ )። ከመሐል በምልሰት (ሰሌዳ ) ትረካው ወሎ ይገባል፤ መደምደሚያ ላይ (ሰሌዳ ሀ’) አዲስ አባ ይመልሰናል።

ሌላው የድርሰቱ ማራኪ ኪን ተራኪው በወሰደው ሁሉን አወቅ ግን ገለልተኛ አንጻር መነሾ የተፈጠረ (እላይ ከተነሳው የስፍራ አሸናሸን ጋር የተያያዘ) በ‘አንተ’ እና በ‘አንቱ’ ተውላጠ ስሞች መከፈሉ ነው። በዚህ የአገነባብ ስልት አስኮ ጌታሁንን በሁለተኛ መደብ ተውላጠ ስም ‘አንተ’ እያለ እየጠራ የሚተርከው የመጀመሪያው ክፍል (ሰሌዳ /ሀ’) ሲሆን፣ ሌላው ደሞ በምልሰት የጊዜ ክበብ የሚነቃነቀው አስኮ ‘አንቱ/እሳቸው’ እየተባለ የሚጠራበት ሁለተኛው ክፍል (ሰሌዳ ) ነው።

‘አንተ’ እና ‘አንቱ’ በስብእናው ዝቅተኛነት፣ የአካባቢው ኗሪ ለአስኮ ጌታሁን የሚሰጠው ስያሜ ነው። አስተማሪ ሆኖ እያለ ‘አንቱ’ ሲባል፣ ከእስር ተፈቶ እንደ እብድ በተቆጠረ ጊዜ ‘አንተ’ ይባላል። ደራሲው በዚህ ግንዛቤ መሐል ገብቶ ሊያርመው አልሞከረም። አንቱና አንተ ካለመተዋወቅና ከመከባበር ጉዳይ ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም። የተራኪው/ደራሲው ገለልተኛነትና አስኮን ‘እንደሚኖረው’ ለማሳየት የተደረገ ጥረትም ነው።

እርዝመታቸው እንዲህ ነው። የመጀመሪያው ክፍል (ሰሌዳ ) በአስራ ሰባት አንቀጾች ሲቀርብ ሁለተኛው የምልሰት ክፍል ደሞ (ሰሌዳ ) በአስራ ሁለት አንቀጾች ይቀርባል። ሶስተኛው ‘መዝጊያ’ ክፍል (ሰሌዳ ሀ’) አንድ አናሳ አንቀጽ አለው። በጊዜ እቅድ ከአሁን-ጊዜ ወደ ፊት-ጊዜ መስመራዊ (Linear) በሆነ መንገድ ተራኪው ድርሰቱን ማዋቀር ቢፈልግ በቀላሉ የክፍሎችን (ሰሌዳዎችን) ቦታ ወደ (ሀ’) ማለዋወጥ ይችላል።

ግን እንዲህ አላደረገም፤ ምክንያት ይኖረዋል። ምናልባት ወደ ኋላ ለምን እንዳደረገ ግምት እወረውራለሁ።

በትረካ ትወራ (Narrative Theory) ስለ መተረክ ዘዴዎች ብዙ ዓይነት ክርክር አለ። አንዳንድ መሠረታዊም ይሁን አይሁን አለመግባባት ቢኖርም ብዙ ጊዜ በተለያየ አመዳደብና የአትኩሮት ደረጃ የሚያነሷቸው አራት ዘዴዎች አሉ። ገለጻ (Description)፣ ሪፖርት (Report)፣ ንግግር (Speech) እና ግምገማ (Comment)።

በ”አስኮ ጌታሁን” ውስጥ ያሉትና የተገነዘብኳቸው የትረካ ሞዶች (ዘዴዎች/ስልቶች) ሶስት ናቸው። እነሱም ገለፃ፣ ሪፖርትና ንግግር ናቸው። ይሄ አመዳደብ ወሳኝነት/መጣኝነት ቢኖረውም አስኮ ጌታሁንን ለማንበብ የሚለግሰኝ እርዳታ በቂ ስለሆነ ተፎካካሪ አመዳደቦችን ላነሳና የማያስፈልግ ንትርክ ውስጥ ራሴን ልዶል አልሻም።

ከነዚህ ከሶስቱ በአስኮ ጌታሁን አጭር ታሪክ ውስጥ በጣም በዝቅተኛ ቦታ የተመዘገበው ንግግር ነው። ስለ ዝምታ ካነሳሁ ላጤናቸው የሚገቡኝ ሞዶች ንግግርና ሪፖርት ይሆናሉ። ሪፖርት ስል ምን ማለቴ ነው? ንግግርስ?

ሪፖርት ስል በሰው ልጅ የተደረገ ነገር በተራኪው ሲገለጽ ነው። እነዚህ ድርጊቶች ጉልህ የሆነ ወይም ያለሆነ መቼት ሊኖራቸው ይችላል። ንግግር ስል ደግሞ የልብወለድ ገጸ ባሕርይው (አስኮ) ሲናገር በትእምርተ ጥቅስ (“…”) የሚቀመጠው ነው። እንዲህ በቀጥታ የሚናገረው ብቻ ሳይሆን በሃሳቡ የሚያስበውና ስለ ሃሳቡም የሚያስበው (Perception/Apperception) በዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ።

ንግግር በጊዜ ውስጥ የሚሆን ነው፤ ንግግር የቅርብ እርቀት ነው። ሪፖርት ግን ሩቅ ነው።

ንግግርና ሪፖርት ከዘዴዎቹ ሁሉ ንቁ (Active) የሚባሉት ናቸው። ምክንያቱም ባህርያቸው ውስጥ ድርጊት (Action) አለ። የትረካ ፍሰት ዝርዝር በሌላቸው (ዝርዝር አዘግዪ ነውና) ሪፖርትና ንግግር ሲቀርብ ፈጣን ይሆናል። በ”አስኮ ጌታሁን” ትረካ ውስጥ ሪፖርትና ንግግር ተያይዘውና ተወስውሰው የተሰሩ ናቸው። የጌታሁን ደቃቃ ንግግሮች ከሌሎች ዘይቤዎች ጋር ያለ ማስጠንቀቂያ ይመጣሉ።

የ”አስኮ ጌታሁን” 30 አንቀጾችን በነዚህ ዘዴዎች/ሞዶች ስር ልንመድባቸው እንችላለን። በአንቀጽ ብቻ ሳይሆን ድርሰቱን በሐረግና በቃላት ደረጃ በመክተፍ/በመሸንሸን ዝርዝር ሥራ መስራት ይቻላል። የዚህ ንባብ ዓላማ ግን ስለ አጭር ድርሰቱ አጠቃላይ ስሜት ለመውሰድ ብቻ የምናደርገው ስለሆነ ትርፍርፍ ዝርዝር ውስጥ አንገባም።

ከላይ በጠቀስኩት የሞድ ስየማ ንባቤን ስጀምርና የአስኮን ዝምታ በተጠቀሰው አመዳደብ ልፈትሽ ስሞክር ከታች ያለውን አይነት የመረጃ አሰባሰብ መንገድ ተጠቅሜ ነው። ድርሰቱ በሰላሳ (30) አንቀጾች የተከፋፈለ ነው ብለናል። እነዚህን አንቀጾች የትንታኔ አሐድ አድርገን በመውሰድ በመጀመሪያ በእያንዳንዱ አንቀጽ የትኛው ዘዴ (‘ንግግር’ ወይ ‘ሪፖርት’) ተጠቃሽ እንደሆነ የሚያሳይ ሰንጠረዥ እንሰራለን።

የሞድ ካርታ ሰንጠረዥ

ከላይ በሰንጠረዥ የቀረበው በመጠኑ የተጣራ መረጃ ስለተነሳንበት ጉዳይ የሚነግረን ሀሳብ አለ። በየአንቀጾቹ ‘ንግግር’ የሚቀርብባቸው መንገዶች ሁለት ናቸው። አንደኛው፤ በቀጥታ ተራኪው “አስኮ እንዲህ አለ” ብሎ በትእምርተ ጥቅስ የሚያስቀምጠው (“አስኮ አለ”)፣ ሁለተኛው፤ በሌላ ሰው ወይም ሰዎች በኩል አስኮ ‘እንዲህ አለ’ ወይም ‘ተባለ’ ወይም ‘ይባላል’ ተብሎ የተደነገገውን ነገር ነው (“ ‘አስኮ አለ’ ተባለ”)።

በሰንጠረዡ ውስጥ የምናየው የ‘ሪፖርት’ ገናናነትን ነው። የአስኮ ንግግር የሚመዘገበው በአብዛኛው በዚህ ዘዴ ስር ነው። አስኮ መናገሩ ብቻ አይደለም። ‘ምን ያህል ተናግሮአል?’ ብለን መጠየቅም አለብን። በሌላ በኩል አኀዝ (Quantity) ለብቻው የጥልቀትም መለኪያ አይደለም። የጥራታዊ ፈረጁንም (Quality) መርሳት የለብንም።

ጃርሶ አትኳሪ ጸሐፊ ነው። ደስ የሚል ገላጭም ነው። ግን አስኮን ከንግግር ያወጣው ምክንያት ቢኖር ነው አልኩ። ገጾቹን በመጨመር ስለ አስኮ በተዘረዘረ መልክ ሊነግረን ይችል አልነበር? ከአዲስ አባ በኋላ ወ/ሮ ስህን ሲያስተምር በትምህርት ቤት፣ በመንደሮች፣ በፍርድ ቤቶች በእስር ቤቶች ስለነበረው ሕይወቱ ጥልቅ ወሬ ማምጣት ይችል አልነበር? ለምን አላደረገውም?

ጌታሁን አስተማሪ ነበሩ/ነበረ። ከብዙ ሰዎች ጋር በሀሳብ ተከራክረዋል፣ ተጣልተዋል፣ ተኮራርፈዋል ፍርድ ቤት ተከሰው ቆመዋል። አስራ ስምንት አመት እስር ቤት አሳልፈዋል። መቼም ሳይከራከሩ ዘብጥያ አልወረዱም። ለማስተማር ሲቆሙ ቃላት ከአፋቸው ሳይወጣ አልቀረም። ለምን ግን አስኮ ሲነጋገር እንድንሰማው አልተደረገም? በአስራ ሁለት ገጾች ውስጥ ድምጹን የምንሰማው ጥቂት ቦታዎች ነው።

በቃላት ደረጃ ቆጠራ ብናደርግ ደሞ ከ2,520 በላይ ቃላት ባሉት ድርሰት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ (አሉ/አለ የተባለው ሁሉ ተጨምሮ) የተናገራቸው በቃላት ብዛት 133 ይሆናሉ። በመቶኛ አምስት (5%) ቢሆን ነው። ይሄ አንጻራዊ አኀዝ የሚያሳየን የንግግርን ጠባብ ቦታ ነው።

የዚህ ጽሑፍ ንባብ ማዕከልም ‘ለምን ይሄ/እንዲህ ሆነ?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሞከር ነው።

ረዥም የተባለው ንግግሩ በመጀመሪያው ክፍል (ሰሌዳ ) ውስጥ በመንገድ ላይ ከአንድ ባልና ሚስት ጋር ያደረገው (በአንቀጽ 10 እና 11) በአንደበት መላከፍ ነው። እንዲህ ስል የንግግሩን ዘይቤ ዘንግቼም አይደለም። በተራኪው ሪፖርት ካልተደረገ በስተቀር አስኮ ጌታሁን ተክለሃይማኖት ጫማ ሰሪ ሆኖ ከመቀመጡ በፊት ስለነበረው ሕይወቱ አንዲት ቃል እንኳን አይተነፍስም።

አስኮ ተናገራቸው የተባሉት ይዘታቸው የተለያየ ነው።

በአስተማሪነት ዘመናቸው (ሰሌዳ ) የሚናገሩት ቁም ነገር እንደሆነ ቢነግረንም በተራኪው ቀጥታ ሪፖርት የተዘገበው ለልጃቸው የተናገሩት አንዲት አረፍተ ነገር ብቻ ናት፤ “እዛ ጓዳ ሂድና አጥና” (አንቀጽ 21)። ይሄ ቀላል አባባል ስለ ትምህርት አስፈላጊነት (“አጥና”)፣ ትምህርት ገለል ያለ ትኩረት የሚጠይቅ ልፋት እንደሆነ (“እዛ ጓዳ”) እና ስለ አኗኗራቸው/ቤታቸው ፕላን (“ጓዳ”) የሚነግረን ነው።

በሌላኛው ክፍል (ሰሌዳ ) ግን አስኮ ንክ በመሆናቸው ሳይሆን አይቀርም (‘እብድና ዘመናይ የፈለገውን ይናገራል’ በሚባል ስልት) ንግግሮቹ በአብዛኛው ‘ግልፅ’ እና ‘አሽሟጣጭ’ ናቸው። ሁለት ምሳሌዎች እንውሰድ፤

 1. “ዓለም ሰፊ አፍ፣ ሰዎች ሁሉ ጥርሶቿ ይመስሉኛል” (አንቀጽ 12)
 2. “እንዴት ሁለት የግራ እግር ጫማ ታደርጊያለሽ ልጄ? እግዜር በቅጡ አልፈጠረሽም ልበል?” (አንቀጽ 15)

እነዚህ የተለያየ ዘይቤ ያላቸውን መልእክቶች በአንድ አኀዝ ውስጥ አስተባብሮ አንጻራዊ መቶኛቸውን ማውጣት ደግ አይደለም። ቢሆንም ንግግር ናቸውና ቆጠራው ሲሰራ አንድ ላይ ከመደበል አያመልጡም። ብዙ ጊዜ የአስኮ ንግግር በውይይት (ዲያሎግ) መሀል ስለማይከሰት “ምን አጋጥሞት ወይም ተብሎ ነው ይሄን የተናገረው” ብለን ወደ ኋላ ስንሄድ ጽንብር የለሽ (Indeterminate) ጉዳይ ይሆንብናል።

ለምሳሌ፣ ከላይ በቁጥር ሁለት (አንቀጽ 15) የተናገረው የሰፈሩን ሰው ጠቅሎ ስለሚጠላ ነው? ልጅቷን ስለማይወዳት ነው? ልጅቷስ በእርግጥ ሁለት የግራ ጫማ አምጥታ ነው ወይስ ሊተርባት ፈልጎ? ከልጅቷ ጋር ቀደም ሲል በመንገድ ላይ ተሰዳድበው ይሆን? ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እንድናነሳ እንገደዳለን። ታዲያ በአስኮ ታሪክ አሳዛኝነት (በትረካው ውስጥ) ተገፋፍተን ለእሱ የሚያዳላ መደምደሚያ ላይ መድረስም የለብንም።

.

(በክፍል 3 ይቀጥላል)

አዳም ረታ

አስኮ ጌታሁን እና ‘ዝምታ’ (ክፍል 3)

አስኮ ጌታሁን እና ዝምታ

(ክፍል ሦስት)

በአዳም ረታ

.

(ከክፍል 2 የቀጠለ)

የፈጠራ ሥራ ከተጨባጭ ዓለም አንዳንድ እውነታዎች መውሰድ እና በነዚህ ላይ (የምናብ ችሎታና ቴክኒክ በሚፈቅደው መሠረት) አማራጭ ምትሀታዊ እውነታ ወረቀት ላይ በፊደላትና በቃላት መገንባት ነው። ይህ ማለት መጀመሪያ እውነታ ነበር፤ ወይም ተጨባጭ ዓለም የሚባለው። የመጻፍ ድርጊት አሰፋፉና አጠላለቁ ይለያይ እንጂ በስሜት ሕዋሶቻችን የመዘገብነው እውነታ ነው።

የፈጠራ ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕይወት ራሷ በድግግሞሽ የተሞላች ናት። እዚህ ጋ ተራራ አለ፣ ደሞ እዛጋም አለ። እዚህ ጋ አውቶቡስ ማቆሚያ አለ ደግሞ ፈቀቅ ብሎ ሌላ አለ ይቀጥላል። እዚህ ይዘፈናል እዚያም ይዘፈናል። አንዳንድ የፈጠራ ስራዎች እንደውም በድግግሞሽ የተናጡ ናቸው። ብዙ ጊዜ በተራኪው ችሎታ የመድገም ግዴታዎች ተቀናብረው ስልት ተበጅቶላቸው ትክክል እንዲሆኑ ይደረጋል፤ ይከየናሉ። ድግግሞሾች በቃላት ደረጃ፣ በሀረግ ደረጃ፣ በአንቀፅ ደረጃ፣ በኩነት ደረጃ ሊመጡ ይችላሉ።

አስኮ ጌታሁን” ድርሰት ውስጥ የተቀናበረ ምት (Rhythm) አለ። ይህም የአጭር ታሪኩን አገነባብ ግጥማዊ ያደርገዋል። በኪነ አገነባብ ብቻ ሳይሆን በቦታ ደረጃ ሲሜትሪ እናያለን። ስለ ቦታ ሲሜትሪ ጥቂት ልበል።

የኢትዮጵያ ከተሞች አሰታተር በአንድ ትልቅ ከተማ (አዲስ አባ) ቁንጮነት ይጀምራል። የተቀሩት ከተሞች አነሰም በዛም በዚህ በቀዳማዊት ከተማ (Primate City) የሚደረገውን ኮፒ የሚያደርጉ ቀሽምነታቸውና እርፍናቸውን ከዚህ ዋና ከተማ እድገትና መበላሸት ጋር የሚያያይዙ ናቸው። በዚህ አገነባብ ውስጥ ጠቃሚ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ሕብረተሰብ ማፈኛ መሠረተ ልማቶች በተቀናበረ የተዋረድ መረብ ይሰራሉ።

ይሄ የመቆጣጠሪያ ተዋረድ በተብራራም ይሁን ባልተብራራ የስራ ክፍፍል መደጋገፍ ያለበት ነው። በትልቁ ከተማ የአገልግሎት ተቋሞች ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው ድረስ ያሉበት ነው። ከክሊኒክ እስከ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል። ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች። ከጠላ ቤት እንከ ታላላቅ ሆቴሎች። ትንንሽ የተባሉ ማዕከሎች (የጠቅላይ ግዛት ከተሞች፣ የአውራጃ ከተሞች፣ የወረዳ ከተሞች) ድርሻቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በስራ ክፍፍሉ መሰረትና የተለየ የቁጥጥር ስርዓት ወደሚያነቃንቀው ወደ አዲስ አባ ይሸጋግራሉ።

አለም በቃኝ ያለው አዲስ አባ ከርቸሌ ነው (ምንም እንኳን በዘወትር ቃል አጠቃቀም ‘እከሌ ከከርቸሌ ወጣ’ አንልም። ‘ወረደ’ ነው። አዘቅት ነው)። ከከርቸሌ በኋላ አስኮ የሰዎችን የአሰፋፈር ስልት ተከትሎ በየትም ደረጃ ባሉ ከተሞች ይኖራል ብለን በምንገመተው የቁጥጥር ጫማ ስር ያርፋል። በአጭሩ የጭቆና ሪትም ወይም ምት አለ።

አስኮ ጌታሁን “አንዳንዴ እንኳን ሳላስበው ዓለም ሰፊ አፍ፣ ሰዎች ሁሉ ጥርሶቿ ይመስሉኛል” (አንቀጽ 12) ሲል ዓለም ማለቱ አገሩን ነው። የልምዱ ስፋት ፕላኔታዊ አይደለም።

በተዋረድ በሚሰራ ዘመናዊ አስተዳደር ባለው አንድ ሉዓላዊ ክልል የተክለሃይማኖት አደባባይ የተለዋጭነት እሴት (Metaphorical Value) ሰፊ ነው። ተክለ ሃይማኖት ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ናቸው። ከእስር ቤት ሲወጣ የተጠለለው እሳቸው በተሰየሙበት ደጀ ሰላም ነው። ህብረተሰቡ ከገነባቸው መንፈሳዊም ይሁን ዓለማዊ መሸሸጊያዎች ለአስኮ ያዳላ ወይም በሩን የከፈተ የለም። አላመለጠም። አስኮ ቦታ ቢለዋውጥም ያለበት የህልውና ስፍራ አንድ ነው። በሕይወት ጎዳና ሲጓዝ ተመልሶ የመጣው ወደነበረበት አዲስ አባ ነው። ክብ ነው።

ይሄ ስለ ጭቆና ሁሉ ቦታ መኖር (Omnipresence) ብቻ ሳይሆን ስለ ቦታ ምት ይነግረናል።

ከታሪኩ ጀርባና ፊት እየተወሰወሰ ከመጣው የጭቆና ስልት ጋር አብረው የሚነቃነቁ ድርጊቶች አሉ። አንዱ ጫማ ስራ ነው። ሁለተኛው የማይሳትና ቁልፍ የሆነው ‘ታስፈሩኛላችሁ’ የሚለው ቃል ነው። ይሄ ቃል ውይይት (Dialogue) ተከትሎ አልመጣም። ምክንያቱም ውይይት ሊደረግ የሚቻልበት ሁኔታ አይደለም። በዚያን ‘ነጠላ’ ወቅት ባየው ነገር ተገርሞም አይደለም። ከሃያ አመት ልምዱ ነጥሮ የወጣ ቃል ነው።

ይሄ ቃል ታሪኩ ውስጥ አራቴ አለ።

አንደኛው በክፍል አንድ (ሰሌዳ ) ላይ (ሁለት ጊዜ)፣ ሁለተኛው ታሪኩ መዝጊያ ላይ (ሰሌዳ ሀ’) (ሁለት ጊዜ)። በዚህ ሂደት በሁለት ሰሌዳዎች ( እና ) ላይ የሰፈረው ታሪክ ውህደት ያገኛል። ተራኪው ትረካውን በ ለ-ሀ-ሀ’ ሞዴል ቢሰራው ኖሮ በድርሰቱ ውስጥ ያለው ጥብቀትና ትስስር ይጠፋ ነበር።

ድግግሞሽ እዚህ የቋንቋና የኩነት ነው። ‘ታስፈሩኛላችሁ’ ቃል ነው። በተደራቢም በአካላዊ ንቅናቄ የሚሰራ በመሆኑም ኩነት ነው። አንዱ ምዕራፍ ወይም ሰሌዳ ከሌላ ሰሌዳ የመጣውን ድምጽ ተቀብሎ ማሚቶ እንደሰራም ይቆጠራል። ኤሚሌ ዞላ ‘ምት ለድርሰት አካልና ጠንካራ ትስስሮሽ ይሰጠዋል’ ይላል፤ ወይም አንድ ሀሳብን ወይም ስሜትን ያጠናክራል።

ጫማ ስራ በሁለቱም ሰሌዳዎች (ሀ/ለ) ለአስኮ ችግር መቅረፊያ የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ናቸው። ከሰሌዳ “” ላይ ግን የተለየ ሁኔታ ይከሰታል። ጫማ መስራቱን እንደ ሰሌዳ “” ለራሱ መጠቀሚያ አያደርግም። ለሚሰራው ስራ የሚቀበለው ክፍያ ለምስማሮቹ መግዣ የሚበቃውን ያህል ብቻ ነው (አስኮ እንደሚለው)።

የሰው ልጅ ከዛፍ ወርዶ ቆሞ ለመሄድና ተፈጥሮን እያወቀና እየታገለ ለራሱ ጥቅም እያዋለ እንዲመጣ የረዳው አንዱ ብልቱ ወይም የአካሉ ክፍል እግር እንደነበረ ሳይንስ ይነግረናል። በአምልኮ ውስጥ እግርን ካሳከከ ‘ጉዞ አለብህ’ ይባላል።

ጫማ ከእግር ጋር የተያያዘ ነው። እግር ጉዞ ነው። ጫማ ምን ተምሳሌት እንዳለው በአገራችን በበቂ ባይታወቅም (በህልም አፈታትና በዘይቤ) ጌታሁን ሁሉን ነገር አጥቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ግን የጫማ ነገር እየተከተለው መምጣቱ አንድ ፍቺ ቢኖረው ነው ብዬ እገምታለሁ።

አንዱ ፍቺ በቴክኒክ ደረጃ ታሪኩ እንዳይረግብ የያዘው ሞቲፍ ቢሆንም ከምንነጋገርበት የዝምታ ጉዳይ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማግኘት መጣሬ አልቀረም። አስኮ የግል ቦታ (Personal Space) አለው። ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ እዚህ ጠባብ የግል ስፍራ ውስጥ ቀዶ ለመግባት የሚፈልግ የለም። የጭቆና እና የማዋረድ መሳሪያው አካላዊ መሆኑ አንሶ (እስር ቤትና ከቦታ ቦታ መንከራተት) የድምጽና የቋንቋ ጉዳይ ይደረብበታል። የሚናገራቸውና የሚያናግሩት ሰዎች ጥቂት ስለሆኑ የግል ስፍራው ባብዛኛው ጸጥታ የወረሰው ነው። ጫማ ሰሪ በመሆኑ ምስማርና ቆዳ ሲቀጠቅጥ ድርጊቱ ከእሱ የበለጠ ድምጽ እንዲኖረው አያደርገውም?

ካለፈው ታሪኩ አብሮት የመጣው ጫማና ዝምታ ነው። ጫማ የሚሰራው ችላ ለሚሉት ያልፈለገውን፣ ያልተከመረበትን ቅጽል ለሚሰጡት በርቀት ንቀው ለሚያዩት ሰዎች ነው። አስኮ ከጫማው ጋር ሲነጋገር ይውላል ብለን እንኳን ማለት አንችልም።

አስኮ ለራሱ ጫማ እንደማይሰራ ለሚሰራላቸው ሰዎች ጉዞ አስቦ ነው? ወይስ በንግግር እንዳደረገው ሂሳብ ሲሰጡት በቋንቋው እንደሚያሽሟጥጣቸውን በኩነት ማሽሟጠጡ ነው? ወይስ የታሰረ ቋንቋውን ወደ ፊት ነጻ የሚያወጣበት አንድ ድርጊቱ? ማለት አብዶ ከጠፋ በኋላ “ይሄን ጫማ አስኮ ነው የሰራው። ጥሩ አልሰራውም?” ዓይነት ሲናገሩ አንደበታቸው ውስጥ ስሙን ለማስቀረት ነው? በእነሱ ድምፅ ውስጥ የመኖር።

ይሄ አፅናኝ ቢሆንም የአስኮ ድምፅ ጉዲፈቻ ከመሆን አያልፍም። በጊዜ እርዝመትም እሱ የሰራቸው ጫማዎች በማለቃቸው ወይም የሰራላቸው ሰዎች ትውስታ በመረበሹ (ስለሚረሱት ወይም የእሱን ስራ ከሌላ ጫማ ሰሪ ስራ ጋር ስለሚያምታቱት) ስሙ የሚጠፋ ይሆናል።

አስኮ ለሠፈረተኛው ደሃ ጫማ ይጠግናል። ያውም በዋጋ አይጎዳቸውም። ይሄ ለውለተኛነት ቦታ ቢከፍትም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን አገልግሎቱን በርካሽ እየተጠቀሙ አይቀርቡትም። ሥርዓቱ የሰጠውን ጠባሳ አያዩለትም። እንደውም ሰዎቹና ስርዓቱ የመጠቃቀም ግንኙነት አላቸው። ስርዓቱ የህልውናውን ጣዕም አጎምዝዟል። ይሄ ሁኔታ በቀላሉ የሚታለል ወይም ግድ የማይሰጠው አስኮን ወልዷል። ይሄ ሙያውን ርካሽ ያደርገዋል። ምንም እንኳን አስኮ የወደቀለት አላማ በቦታ ደረጃ ሌላ ስፍራ ቢሆንም (ወሎ ስህን ት/ቤት) ሁሉም ዜጎች ግን የሚሹት ነው። ኑዋሪዎቹ ይማራሉ፣ ይሰራሉ ከእነዛም ውስጥ ለአገር የሚያስቡ ይኖሩ ይሆናል።

ግን የተጣመመው ስርዓት የተስተካከለ እንዲሆን ሲዋጋ የነበረውን ወንድማቸውን ያጣጥሉታል። ከአሁን በኋላ መንግስታዊ የሆኑ ቀጥተኛ የጭቆና መሰረተ ልማቶች አያስፈልጉም። ሕዝቡ ራሱ ያካሂደዋል። በመንግስት እስር ቤት መከተት ግድ አይልም። ሕዝቡ ራሱ አስኮን እንደ ጠላት በወሬውና በአገልግሎት ጥበቡ ያስረዋል። ከላይ የጠቀስነው ከአዲስ አባ እስከ ጭቃ ሹሞች የተዘረጋው የመንግስት መቆጣጠሪያ መዋቅር መሬት ላይ (ታች) ገንዘብ የማይከፍለው ስራ አስፈጻሚ አግኝቷል።

አስኮ የሲጋራ ፓኮ ሲለቃቅም አንዲት ሴትና ባሏ የሚለቃቅማቸው ወረቀቶቹን በጫማዎቻቸው ይረግጡበታል። ለመጀመሪያ ጊዜ የአስኮ ርዕዮት በቀጥታ ንግግር የሚገለጸው እዚህ ነው። ዝምታው በኮስታራ ቋንቋ የሚገሰሰው አሁን ነው። የተናገረው ሃይለ ቃል ልቧን ያራራበት ዘመናይ (ዘመናይ ፓ-ፓ-ፓ- ባለዘመን፣ የጊዜው ሰው) ወይዘሮ ልትክሰው እርጥባን ውራጅ ቀይ ካፖርት ትሰጠዋለች (ለምን ቀይ ካፖርት? ለምን ሌላ ቀለም አልሆነም? ለአዲስ አባ ለባሽ ቀይ ካፖርት እንግዳ ስለሆነ ለልዋጭነት ወይም ምሳሌነት እንደቀረበ ልጠረጥር ዘንድ እገፋፋለሁ። ግን ይሄን የቀለም አይነት በምን ልተረጉመው እንደሚገባኝ አላውቅም። የስሜት ሃያልነት? አደጋ?)

አስኮ ላገሩ በለፋው ልፋት ኦሪጂናሌ ብናደርገውም ወይም እንደዛ ብለን ብናስበውም የሚለብሰው ግን ሳልቫጅ ነው። ሳልቫጅ ሌላው ስሙ ‘ነፍስ ይማር’ ነው። የሞተው ማነው? ስለ ሴትዬዋ ሳይሆን ስለ አስኮ በጥልቅ ስለምናውቅ ሟቹ እሱ ሊሆን አይችልም? ጊዜ ታጥፎ የራሱን የድሮ ልብስ የለበሰ ሊሆን አይችልም? የሙት ቋሚ ሊሆን አይችልም? እነዚህ ስር ነቀል ግምቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የህልውና ምት አይመስልም?

የመጨረሻው ክፍል (ሰሌዳ ሀ’) በቀጥታ መስመራዊ አተራረክ የመጀመሪያው ክፍል (ሰሌዳ ) ተከታይ ነው። አጨራረስ (Ending) በተራኪው ቁጥጥር ስር ነው። አዘጋግ (Closure) ግን በተራኪና በአንባቢ መሀል ያለውን ውጥረት የምናይበት ነው። ፍርሰቱ የተዘጋው በመጨረሻው አንቀጽ (ሀ’) አስኮ በተናገረው ‘ታስፈሩኛላችሁ’ በተባለው ቃል ማዕከላዊነት ነው።

adam1

የዚህን ትርጉም የምናገኘው ዐውድ ፈልገን ነው። ዐውድ ቀደም ሲል የነበረው ትረካ ውስጥ ነው (ሰሌዳ ሀ-ለ)። ምን ያህል የቋንቋ ክህሎቱ ቢናጋ ነው ‘እናንተ’ የሚለውን ተውላጠ ስም ሸውኮ በአጭር የተናገረው? ከቃል በታች ሊኖረው የሚችል ምን አይነት ቃል ነው?

የአስኮ የአነጋገር ጥልቀት ቢገባንም እዚህ ላይ ሁሉ ነገሩን በአንድ ቃል አስሮ ማለፍ የፈለገ ይመስላል። ቃልዋ ሲጢታ ትመስላለች። ሲጢታ ንኡስ ድምጽ ናት። የቋንቋ ጽንብር (Limit) ላይ የደረሰ ይመስላል። ‘ምን ማለትህ ነው?’ ተብሎ ማብራሪያ የማይሰጥበት የደከመበት ደረጃ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥልቅ የሆነን የአእምሮን ወይም የስሜት ልምድን ለመግለጽ የሚከብድበት ጊዜ አለ። የአረጋሽ ሰይፉ አንድ ግጥም ትዝ ይለኛል፤

ቃል አልቦ

“… ከቋንቋ የላቀ፣

ከቃል የመጠቀ፣ …

ሲባዛ ገደቡ ዝም … ዝም … ዝም … ዝም …

እንዲያ ነው ሚገለጥ …

ጥላቻም፤ ፍቅርም።

(አረጋሽ ሰይፉ፤ (፲፱፻፺) “እኛ 170 ግጥሞች”)

በባህላችን ከቋንቋ መራቅ የተለመደ ነው። ምንኩስና (ለምሳሌ) ከዓለማዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን የቋንቋ ተፈጥሯዊ ስፍራ ከሆነው ማሕበረሰብ ርቆ ቋንቋን በዋሻና (በአካል) አርምሞ (ኢ-ቦታዊ/አእምሮአዊ) አጥሮ ከሩካቤ ማሸሽ ነው። ሰዎቹ የረቀቀና የላቀ መንፈሳዊ ስብዕና እናገኛለን የሚሉት በዚህ ዓይነት የጸጥታ ገደብ በነገሰበት ዐውድ ውስጥ ነው። አስኮ ምንኩስና ላይ አይደለም። ገለልተኛነቱና ዝም ተባልነቱ ምን ያህል ንቃት እንደሚሰጠው ባንገምትም በአንድ ቃል ያልቃል ብለን መገመት ይከብደናል።

እዚህ ሁኔታና አጨራረስ ለመድረስ ግን አስኮ በብዙ ነገር ውስጥ አልፏል። ከዚህ ካለፈበት የህይወቱ ጉዞ ጋር አዝጋሚ ከሩካቤ የመራቅ የዝምታ ዝግመተ ምልዋጥ (A Process of Evolving Silence) እናያለን። ይሄን የምልዋጥ ሂደት ከላይ በሰየምኳቸው ሰሌዳዎች አሰራር ተራኪው የሰጠንን በምልሰት የተገነባ ድራሳን (ሰሌዳ ሀ-ለ-ሀ’) ወደ መስመራዊ አካሄድ (ሰሌዳ ለ-ሀ-ሀ’) ለመለወጥ በስምንት ተርታ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።

 1. [ማህበረሰብ አካል] – መሰማትና መነቀፍ (አንቀጽ 19)
 2. [ኢ-ሰብአዊ ማድረግ] – “የወፍ ቋንቋ” (አንቀጽ 23)
 1. [ራስን ሳንሱር ማድረግ] – “ከንግግራቸው መጠን ማለት ጀመሩ” (አንቀጽ 25)
 1. [ባይተዋርነት] – “እንደ ደረቀ ግንድ … ተለይተው ይታዩ ጀመር” (አንቀጽ 25) (“የአስኮ ጌታሁን ፊት የሸበተ አሮጌ ጉቶ ላይ የሰው መልክ የተቀረጸበት ይመስላል” (አንቀጽ 1) ከሚለው ጋር የተስማማ ንፅፅር እናያለን።)
 1. [ማህበረሰቡ ተጠቃሎ መሰረዙ] – “የለም፣ የለም ወዲህ ነው፤ ከራሴ ጋር ነው” (አንቀጽ 25)
 1. [ለቅሶ] – “እንጉርጉሮ ነገር ያሰማል” (አንቀጽ 15) እና “አያለቅስም፣ ድምጽ የለውም። እንዲሁ ብቻ ያነባል።” (አንቀጽ 13)
 1. [ማግለል] – “አጠገቡ ሲደርሱ የሱን ወሬ ለመከላከል (ደንበኞቹ) እርስ በርሳቸው ማውራታቸው የተለመደ ነው” (አንቀጽ 15)
 2. [መዝጊያ] – ከዚህ ወደ ፀጥታና ወደ ፍጹም መሰወር ጉዞ ላይ እያለ “ከቶም የማይረሳ ነገር ተናገር” (አንቀጽ 30)

በዚህ የአስኮ ጉዞ የምናየው ቀስ በቀስ ቋንቋ እየተሰወረ መሄዱንና አስኮ ያለበት ኢ-ሰብአዊ ሁኔታ መክረር ነው። ይሄ የቋንቋ መጥፋት ከሕብረተሰቡ በፍጹም ለመለያየት ፍጥጥሞሽ ማድረጉ ነው። አማራጭ አልነበረውም? ሌላውን መስሎ መኖር?

አስኮ ‘ታስፈሩኛላችሁ!’ ብሎ ሲናገር ያዳመጡት “ከቶም የማይረሳ ነገር ተናገረ” ይሉታል (አንቀጽ 30)። የምንጠይቀው የተለመደ ጥያቄ ለመሆኑ እንዲህ ከተናገረ በኋላ የአባባሉ ተጽዕኖ አካባቢው ላይ ምን ያህል ነው? የሚመስለኝ ይሄ ነው።

ድምጽ ድርጊት ነው። ድምጽ ማውጣት በምልክትነቱ ጫማ ከመስራት፣ ከመሳደብ፣ እየዞሩ ከመተረብ፣ ከዝምታ የሚለየው ነገር እንጂ የዕድሜው ጊዜያትን በአንድ ቃል ውስጥ ሰብስቦ የተነፈሰው ነው። አዘጋጉ የሚጠቅሰው አስኮ በመናገሩ የተጣለበትን የዝምተኛነት ፍርድ መጣሱ ሲሆን (እንደ አንድ ግለሰብ ‘ወንዳታ’ ቢሆንም) የቃሉ መሰማት ከማሚቶ የበለጠ አይሆንም።

ቃሉ በትምህርተ ጥቅስ በመታቀፉ ራሱ ውስጥ የቀረ አይሆንም? ማሚቶ አይሆንም? ይኼ ማሚቶ በቅርጽ ደረጃ ሰሌዳዎቹም በራሳቸው ውስጥ የሚያደርጉት ቅብብል ነው። የህልውናው ምት እንደ ማሚቶ ነው። የቦታው ምት የማሚቶ ጸባይ አለው። ማሚቶ ከራሷ ሌላ የምትረባው አዲስ ነገር የለም። ተዳክማ ከመሰወር ወይም ኅቡዕ ከመሆን ሌላ ግብ የላትም።

አስኮ አንዲትን ለመሰወር የደረሰች ቃል ጮሆ ከምንምነት ቢያመልጥም አካባቢው ላይ ያለው ተጽዕኖ አይገለጽም። ቃሉ በረዥም የጊዜ ሂደት ተቀናቃኝ የስር ነቀል ድርጊት ማስነሻ ይሆናል ብለን ለመገመት የቀረበልን ሌላ ተፃራሪ የትረካ መስመር የለም። ካፖርት የለገሰችው ሴትዮ ከእርጥባን ዘልቃ መሄድ የምትችል አልነበረችም። ከዛ ውጭ ያን ድምጽ የሚጠብቀው አዛኝ ልቡና፣ ተንታኝ አእምሮ የለም። ዝምታ አይሆንም?

‘ከቶም የማይረሳ’ ብንባልም ዋስትና የለንም። የዛ የመጨረሻ ጩኸት መነሻ ምክንያት ለኗሪው እስከ መቼም ሳይብራራ ይቀራል። ያቺ ጩኸት ለእነሱ አንድ አካላዊ ክስተት (Physical Phenomenon) ብቻ ናት። ዴሲቤል ናት። ለእነሱ ያ ቃል አስገራሚ የሆነበት ምክንያት ብቻውን ከታሪክ፣ ከሂደት የተፋታ ቃል ስለ ሆነባቸው ነው።

መስማታቸው አንድ ጉዳይ ሳይሆን ባይቀርም ስለ እነሱ ካለን ዕውቀት የትም እንደማይደርስ ነው። ምናልባት ቢብስ ይሄን ጩኸት ያብራራል የሚሉት ሌላ የከተማ ትውፊት (Urban Legend) ይፈጥሩለት ይሆናል። የዛ ማሕበረሰብ ልዩ ስጦታ ይሄ ነው።

ተራኪው የፈለገው “ታስፈሩኛላችሁ” የምትባለዋን ቃል በማንሳት አስገራሚ አጨራረስ ወይም ንሮሽ (ከመ ታደሰ ሊበን) ሊከስትልን አይደለም። ይሄን ቃል ቀድሞ ሌሎች ገጾች ላይ አንድ ሁለቴ አንብበነዋል። አስኮ ምንም ነገር ቢደራረብበት የተቻለውን መልስ ሳይሰጥ እንዳላለፈ ተራኪው ሊነግረን ነው።

ጃፓናዊው ገጣሚ ሶቢ ሺጌቺ የሚለውን ያስታውሷል፤

“I may be silent but

I am thinking

I may not talk, but

Do not mistake me for a wall.”

ሚስቱን እናቱን ልጁን አስተማሪነቱን አጥቷል። አስኮ ምንም የለውም። ከውስጡ ሁሉ ነገር ተጎልጉሎ ተዘርፏል። እዚህ ባዶ ውስጥ ድምፅ ይኖራል? ከዚህ አሟጦ ከጨረሰ ህልውና፣ ከዚህ ‘ገዋ’፣ ከዚህ ጨለማ ድምፅ ለመምጣት የግድ ይላል።

ትናንትና በትውስታ ውስጥ ሳትሞት አለች – የቁጭት ዕንቁላል የጣለች። ተክለ ሃይማኖት አደባባይ የአስኮ ጌታሁን ማመጫው ናት – ያቺ የመጨረሻ ቃሉን የሚወልድባት (አለነገር ወዲያ ወዲህ ለምን አለ? አለነገር ለምን ተቁነጠነጠ?)

‘በመጀመሪያ ቃል ነበር’ ሲል መጽሐፉ ዐቢይ ነገር ሲጠቅስ ነው። ሲጀመርና ሲጀምር ያምላክ የሩካቤው ማዕከል ቃል ነው። ባቢሎን ላይ ያደረገው ስልጣኔ የማፍረስ የመጀመሪያው ቅጣቱ የተሰራው በቋንቋ ማማከያነት ነው። ምርቃትና እርግማን ቋንቋ ናቸው።

ስም ቃል ነው። ግለሰቦችንም አንዱን ከአንዱ መለያ ነው። በሕብረተሰባችን ሁለት አለማት አሉ። የደግና የክፉ። የእግዚአብሔርና የሳጥናኤል። በዓለማዊው ዓለም ውዥንብርና መምታታት እንዳይፈጠር ዓለማዊ የሰርክ ስማችንን እንይዛለን። ከመልካም መንፈስ ጋር ታሻርከን እኩይ መናፍስትን ለመዋጋትና ከእነሱ ንጀሳ ለመከላከል የሚስጥር ክርስትና ስም ይኖረናል።

ይሄ በሆነ መልክ የዶስ (Power) ጨዋታ ነው። ጀግኖችና ጠቢባን በፈረሶቻቸውና (አባ ነፍሶ፣ አባ ታጠቅ፣ ወዘተ) በሊቅነታቸው ጥልቀት (አራት አይናው ማንትስ፣ ወዘተ) ይጠራሉ። በተጨማሪም በየቀኑ ድርጊታቸው/ሁኔታቸው የተቀሰቀሰ በወዳጆቻቸው ወይም በሚቀርቧቸው ሰዎች አማካኝነት ቅጽል ስም ሊወጣላቸው ይችላል።

አዲስ አባ ውስጥ ‘አስኮ የጫማ ፋብሪካ’ የሚባል ነበር። ባለቤቱ የውጭ አገር ሰው መሰሉኝ። ለአቶ ጌታሁን የቅጽል ስሙ ‘አስኮ’ የማሾፍ አባባል ነው። “ጌታ ለመሆን ነው እንደ አስኮ ጫማ” ብሎ ይመልሳል (አንቀጽ 29) ለምን ይሄን ሙያ እንደያዘ ሰዎች ሲጠይቁት። ምንም እንኳን በማሾፍ ቢናገረውም፣ እሱ የሚናገረውን ፋይዳ ሳይሰጥ ራሱን ይሰውር የነበረው የሰፈር ጆሮ አባባሉን ዘርፎና አዙሮ ቅጽል ለጥፎበታል።

‘አስኮ’ የሚለው ስያሜ ገለልተኛ ይመስላል እንጂ አይደለም። አስኮን በዚህ ቅጽል መጥራት ሁለት ጥቅም አለው። አንደኛ፤ የባዕድ ስም ፊቱ በመገተር ባይተዋርነቱን አጥብቆ የስደተኛነት ጋቢ የማልበስ ሲሆን፣ ሁለተኛም፤ የማሾፍ ነው። ሁልጊዜ የአስኮ ጫማ የሚያደርግ ጎረምሳ ወይም ሰው ወይም በመሰለ ሁኔታ የተያያዘ ‘አስኮ’ ተብሎ ስሙ ቢቀጸል እውነተኛነት ስለሚኖረው ያስቀን ይሆናል። ጌታሁን ‘ሁልጊዜ በአስኮ ፋብሪካ የተሰሩ ግን የተቀደዱ ጫማዎችን ብቻ ነው የምጠግነው’ ብሎ ቢል ኖሮ መልካም ቅጽል ይሆን ነበር።

አስኮ የተሰጠው ቅጽል ከመውደቁ ከባይተዋርነቱ ከአንቱ ወደ አንተ ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ ነው። አዝናኝነት፣ አሳቂነት የለውም። ስያሜ ከውጭ ሲመጣ ደፋሪና ነውረኛ ነው። በሌላው ሰው በማይገባው ልንቀበለው በማንችል ርዕዮት የተቀመመ ማንነትን መመጠኛ ስልት ነው። ለራስ ጌታ መሆንን ማጣት ነው። ስያሜ ቋንቋ ስለሆነ ለራስ የተከለለን ቋንቋ በሌላ ሀይል መወረስ ነው። ድምፅንም መነጠቅ ነው።

ግን ስለ ዝምታ ሲጻፍ አያኖ ይሆናል። ድምጽ ስለሌላቸው ሰዎች ሲጻፍ ሰዎቹ በሆነ መልክ አልሞቱም። በሆነ መልክ ድምጽ አላቸው።

አለቃ ዘነብ ‘ቀለም በቀንድ ሳለ ድዳ ነው፣ በተጻፈ ጊዜ ግን ምላሰኛ ነው’ ይላሉ። አስኮ ጫማ ሰሪውና አስተማሪው መልካሙ ሰውዬ ያለ ድምጽ ቢያልፉም በትረካው አማካይነት በኅሊናችን እንዲቀሩ ሆነዋል። ያለ ዝምታ ወደ እብደት እንደገባ ሪፖርት ተደርሶልናል።

የአስኮ ድርጊት ሰው በቦክስ ማስፈራራት፣ ተኩሶ መግደል ወይም የመሳሰለ ቅጣት አይደለም። አስኮ ያ አቅም የለውም። ያለው አቅም ዝምታውን ማፍረሱ ነው። ለተራኪው አስኮ ‘የሚነገርለት’ የሆነው ለዚህ ነው። የዚህ ታሪክ ወረቀት ላይ መስፈሩ የግድ ይላል።

የአስኮ ዝምታ ወረቀት ላይ በሰፈሩ ቃላቶች ድምጽ ይካሳል።

.

አዳም ረታ

 

“አስኮ ጌታሁን” (ልብወለድ)

አስኮ ጌታሁን

ከጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል

.

[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]

.

የሚገርመው ነገር፣ አስኮ ጌታሁንን አንዴ አይቶ መልኩን ለሰሞናት ከዓይነ ህሊና ማጥፋት አለመቻሉ። የሚያስደነግጥ፣ የሚሰቀጥጥና ለአንዳንዱም የሚያሳዝን ገጽ ያለው ሰው ነው። ይሄን ፊቱን ከተመለከቱት፣ አእምሮ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ፊትም ላይ ተቀርጾ ይቀራል። በአንዳች አጋጣሚ ተመልክተውት ሲያበቁ ፊታቸውን በፍራቻ የሚደባብሱ ጥቂት አይደሉም። በግድ መጥቶ ፊት ላይ የሚተሻሽና ቅሪተ አካሉን የሚተው ገጽ ነው። የአስኮ ጌታሁን ፊት የሸበተ አሮጌ ጉቶ ላይ የሰው መልክ የተቀረጸበት ይመስላል። አንድ ዓይኑ ለብቻዋ ሙታለች። ብርሃን አልተሳናትም፤ ግን ሞታለች። ብይ ትመስላለች፤ ጠጠር ትመስላለች። ዓይነስቡ በበለዘ ጥቁር ሰማያዊ ሲከበብ፣ ሽፋሽፍቱን ባንቀሳቀሰ ቁጥር የምትላወስ እንሽላሊት የመሰለች ጠባሳ ከግንባሩ ወደዓይነ ቆቡ ተጋድማለች። የፊቱን መጨማደድ ከላይ የተጠቀሰው አሮጌ ጉቶ በበቂ ሁኔታ ይገልጸዋል። ፀጉሩ እንደሙጃ ቀጥ ብሎ ከመቆሙ በላይ እውስጡ ተባዮችን ትተን የዳቦ ፍርፋሪ፣ አሸዋ፣ የፀጉሩ ማስያዣና አንዳንዴም አንድ ሳንቲም ይኖሩበታል።

ከአገጩ የሚወርደው ባለአንድ ግምድ ፍየል ጢም፣ እንዲጐተት የተፈጠረ ጥንተ አካሉ እንጂ ከጊዜ በኋላ አቀምቅሞ ቸፍርጐ የተገመደ ፀጉር አይመስልም። ቁመናው ረዥም ነው። ከወገቡ በላይ ያለው አካል አለመመጣጠኑን ቢያሳይም፣ የፊቱ እንደአንዳች መርዘም ሸፍኖታል።

“ጫማ ሰፊ ሆኖ እንዴት ባዶ እግሩን ይሄዳል” በሚለው መታበል ከቶም ከእግሩ የአንድ እግር ጫማ አይጠፋም። ይሄ ማለት የቀኝ፣ ቀኝ ላይ ይውላል ማለት አይደለም። ግን የግራም ቀኝ ላይ ቢውል፣ አንድ እግር ጫማ ለመኖሩ ያህል አለ ማለት ነው።

አስኮ የሚኖረው ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ነው። ቀደም ብሎም የደብር አለቃው ከአቃቢቶች ጋር ባነሱት አምባጓሮ ተባረረ እንጂ መቃኞው ውስጥ ጥቂት ለማይባል ጊዜ አድሯል። እያደር የአካባቢው ህዝብ ለምዶት፣ የሠፈሩ ህፃናት አሹፈውበት፣ እንደጥጃ በመሸ በየፖሊስ ጣቢያው ታስሮ ካበቃ በኋላ ዛሬ አስኮ ለሠፈሩ ህዝብ የአውራጐዳና ባለስልጣን ጥሎት እንደሄደ የሬንጅ በርሜል ያህል እንኳን ለዓይን አይቆረቁርም። እሱ ግን “አገር ሰለቸኝ” ይላል። አገርም እሱን እንደሰለቸው አያስብም። እንደአበደ ባሕታዊ ድንጋይ ከአናቱ ጭኖ፣ “እግዜር የሰውን ልጅ ሲፈጥር፣ ለጭቃ ማቡኪያ ሰባት ባልዲ ውሃ ያቀበልኩት እኔ ነኝ። ከፈለጋችሁ ሰማይ ቤት ስትገቡ፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጠይቁ። እማኜ ናቸው” ሲል አስተዋይ ነኝ ያለ ጭንቅላቱን ይነቀንቃል። ስላቁ የነካቸው ኮስተር ይላሉ። ህፃናትም እንደተጠመደ አውሬ ይዞሩታል።

ይህ ሰው ህብረተሰብ “ወፈፌ፣ አውቆ አበድ፣ ንክ” እና ሌላም ከሚሏቸው አንዱ ነው። አንዳንዴ ከዛጉት ጥርሶቹ ተስፈትልከው የሚወጡት ቃላት፣ አጥንት ሰብረው ከመዝለቃቸውም አስባለሁ ያለን አዕምሮ ለቀናት ወጥረውት ይቆያሉ። ስለዚህም በሙሉ “እብድ” ሊለው የቻለ ሰው አልነበረም። በዚህም ላይ ደግሞ ምክር እንደገባው ሰው አንድ ሳምንት ሰጥ ለጥ ብሎ በአሮጌ ዣንጥላ በተገጠመች መጠለያው ሥር ጫማ ስፌቱን ይያያዘዋል። ጫማ ለማሰፋት የሚመጡትን ሠፈርተኞች ከነፃ በላይ፣ እሱው እንደሚለው “ለሚስማር መግዣ” ብቻ ነው የሚያስከፍላቸው። እናም “አስኮ ተቀምጧል” ከተባለ ሰልፉ አጭር አይደለም።

ፊታቸውን አዙረው ጫማ የሚሰጡት፣ በሀይለኛ ጉንፋን አሳበው ደፋ፣ ደፋ የሚሉት፣ መልኩን ላለማየት እንደሆነ ያውቃል። “ባለ አሥራ ሁለት ሳንቲም ሚስማር ውጬ ደረቴን ወጥሮታል” ሲል፣ በድንጋጤ ቀና ብለው ቢያዩ ያቺን ሙት ዓይኑን ያበራባቸዋል።

ይህ ሰው “ንብረትና ሀብት አለኝ” ብሎ አስቧል። “ከዋናው ባንክ ቅርንጫፍ”፣ “ከሰላም ምግብ ቤት”፣ “ከኦስማን የህንፃ መሣሪያ አስመጪዎች”፣ “ከአጂፕ ቤንዚን ማደያ” እና ከተቀሩትም አገሩን ያጫነቁ የገቢ ምንጮቹ ሳያዛንፍ አርብ አርብ ከሰዓት በኋላ ደረሰኙን ይዞ ይሄድና በቀጥታ ወደመደገፊያው ሥፍራ በመጠጋት፣ “ጤና ይስጥልኝ ባልደረቦች፤ እስቲ ከገቢ ወጪ እንተሳሰብ። ቅርንጫፍ ፀሐፊውን ንገርልኝ፤ አስኮ ጌታሁን መጥቷል ብለህ” ይላል።

ቀደም ሲል ብዙ ጊዜ ታስሮ ተፈታ። በኋላ ላይ ግን የባንኩ ሠራተኞች የጫት መግዣ ሰጥተውት ደረሰኙን “ፈርመው” ሲሸኙት፣ ባለ ሆቴል ቤቶች ራት አብልተው ይለቁታል። አንዳንዴ ሠራተኞቹን “ንግድ በማበላሸታቸው፣ ትርፍ በማዳከማቸው” እየተቆጣ ሲሄድ፣ አልፎ አልፎም “ሁሴን መሀመድን የአቃቂው ቅርንጫፍ ሹም ያላደረግሁት እንደሆነ ታዘቡኝ። አንጀቴን ያራሰኝ ሠራተኛ ነው” በማለት ለህልሙ ንግድ የህልም ተስፋ አልሞ ይወጣል።

የሆነውን ገሀድ ለራሱ እንደፈለገው ማውራት የሚወደውና የሚችለው ሕዝብም ለአስኮ ልብወለድ ፈጥሮለታል። “የጭነት መኪናዎች የነበሩት እንዴት ያለ ቱጃር ነበር መሰላችሁ” ሲል፤ ሌላው ደግሞ “በማር ንግድ የደለበ ነጋዴ ነበር። ዛሬ ጉድ ሆነ” ይላል። ግን እውነቱን ማግኘት የሚቻለው ከራሱ ከአስኮ ነበር። ታዲያ ምን ይሆናል?! እሱም አያውቀውም። ዛሬን እንደማያስብ፣ ነገን እንደማያልም ሁሉ፣ ትላንትናም ጨርሶ ከአእምሮው ጠፍታለች።

ወታደርን ሲያስቡ አለመለዮ ልብሱ ማየት እንደማይቻል ሁሉ፣ አስኮን አለረዥም ቀይ ካቦርታው ማሰብ አይሞከርም። ልብስ ሲሰፋ “እንደአስኮ ጌታሁን ካፖርት ተንቦረቀቀ” ይባላል። ለሱ ግን የቀን ልብሱ፣ የሌሊት ልባሱ ነች። የዚህ ካፖርት አመጣጥ ታሪክ አለው። አንድ ማለዳ አስኮ የሲጃራ ባኮ ከመሬት ሲለቃቅም፣ የአንዲት ሴት ጫማ ሹል ታኮ አንዱን በስቶ ቢይዝበት፣ “በሕግ አምላክ ንብረቴን ተዘረፍኩኝ!” ሲል ጮኸ። ባል ይሁን ወዳጅ አልለየም ድንገት ሽክ ብሎ የለበሰ ጐበዝ ደረሰ። አስኮን ለመምታት ቢቃጣው፣ መልሶ እጅን የሚሞርድ ፊት እንዳለው አስተውሎ ስንዝሩን መለሰና በሰላሙ መንገድ ጀመረው። አንድ ሁለት ሲባል፣ የአስኮ ጌታሁን ወሬ ሙሉውን የእብድ አለመሆኑን ያዩት ሴትና ወንድ፣ እንደመማረክ ብለው ያደምጡት ጀመር።

“እናንተ ቤት አላችሁ፤ ንብረት አላችሁ። ካልጠፋ አገር እዚህ ድረስ መጥታችሁ፤ ከመሬት የምለቃቅመውን ባኮ እንደምትበሉት ማካሮኒ በመጫሚያችሁ ሹካ የምትወስዱብኝ ለምንድነው? እንዳው ለመሆኑ የሰው ግፍ ገደብ የለውም ጌታ? እንደው ለነገሩ በቃኝን አልፈጠረብንም ማለት ነው?” ወንድየው ተገረመ እንጂ አልራራም። ሴትየዋ ግን እቤት ቅርጫት ውስጥ ያለውን የእናቷን ካቦርታ ‘ነብስ ይማር’ አምጥታ፣ ሀፍረቱን እንዲሸፍንበት ለመስጠት ታሰባትና በማግስቱ ተመልሳ ብትፈልገው አልተገኘም። ባለ መደብሮችን በምልክት ስትጠይቅ በመገረም፣ “እዚሁ ሠፈር ነው የሚውለው። አንድ ቦታ የሚቀመጥ ፍጡር አይደለም። እስቲ ወደጫት ተራ ፈላልጉት” እያሉ ተጠቃቀሱባት። አግኝታ ስትሰጠው፣ “እሜትዬ፣ አርብ ሂሳብ እንደተረከብሁኝ ከነወለዱ እከፍላለሁ” ብሎ ካፖርታውን ለአንዴም ለሁሌም አጠለቀው።

“አንዳንዴ’ኮ ሳስበው” ይላል አሉ፤ “ዓለም ሰፊ አፍ፣ ሰዎች ሁሉ ጥርሶቿ ይመስሉኛል። እና እኔን እያኘኩኝ ነው።” እዚህ መርካቶ ይሄ የሰው አሸን የሚፈላበት፣ የሚያወጣው እጅ አጥቶ እንደሚንተከተክ የተጣደ ነገር ሁሉ የሚንጨረጨርበት የትርምስና ሁካታ ዓለም፤ የመርካቶ ዓለም ውስጥ፤ ይህ ሰው አንዲት ጥግ ይዞ በካፖርታው ተጀቡኖ እንደጅብ የሚያስፈራ ጭንቅላቱን ብቅ አድርጎ ሁሉን ነገር ይቃኝ፣ ይቃኝና ሲያበቃ፣ “ታስፈሩኛላችሁ!!!” ብሎ ይጮኻል። እዚህ የጆሮና የአፍ ደን ውስጥ የሚሰማውም የሚመልስለትም አያገኝም። ተመልሶ ይተክዛል።

ታላቁ የቤተስኪያን ደወል እንደጮኸበት የጸናጽሉ ሻሻታ፣ የቃጭሉ ድምፅ፣ የሰዉ ወሬ ሁሉም በአንዴ ሲወሩት በሁለት መዳፎቹ ጭንቅላቱን ይይዛል። በአጠገቡ የሚያልፍ ለአፍታ መልከት ሲል ህፃናት ይመጡና፣ “አስኮ፣ እንካ ይሄንን ቦንዳ ብላ እስቲ፣ የእነቡጡ ሰፈር ልጆች ብረትና ሚስማር ይበላል ብለው ተወራርደዋል” ይሉታል። አያለቅስም፣ ድምጽ የለውም። እንዲሁ ብቻ ያነባል።

ይህ ሰው በርግጥ ለአካባቢው ከወደቀ ግንድ፣ ወይም ካረጀ ውሻ የበለጠ አይከብድም። የውስጡን የስቃይ ቡጥጫ፣ ናላው ውስጥ የሚንተከተከውን እንዲህ የሕያው ሙት ያደረገውን ነገር የሚያውቅለት የለም። ለነሱ አስኮ ጌታሁን “አውቆ አበድ” ነው ወይም “ሚስኪን” ነው። ወይም ለቤት ህፃናት ማስፈራሪያ የሚያገለግል ምስል ነው። ሰብአዊ ህልውናውን ከአካሉ ለይተው አንዱን ብቻ በመቀበል፣ በአስፈሪ መልኩ ወይም አስደንጋጭ ሁለመናውን ብቻ የሚያውቁትም አሉ።

“አስኮ ሲቀመጥ” አቅመ ደካማዎችና ሳንቲም ማትረፍ የሚፈልጉ ይሰለፋሉ። አጠገቡ ሲደርሱ የሱን ወሬ ለመከላከል እርስ በርሳቸው ማውራታቸው የተለመደ ነው። ሆኖም፣ ጫማ ሰፊው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ አያውቅም። “እንዴት ሁለት የግራ እግር ጫማ ታደርጊያለሽ ልጄ? እግዜር በቅጡ አልፈጠረሽም ልበል?” ሲል፣ ንግግሩ ሳቅን ቢገፋፋም፣ ወሬ ላለማበርከት ሲሉ ጉንጫቸውን በአየር ነፍተው ያጐነብሳሉ። “የእዚህ ጫማ ጌታ ውስጡ አንዲት የታጠፈች ብር ረስቶ አግኝቻለሁና ታውቁት እንደሆነ ንገሩት። የእግር ቁጥር አርባ ሁለት፣ ቀለሙ ጥንት ጥቁር፣ አሁን አመድ” በማለት ጫማውን ለትዕይንት ብድግ ሲያደርግ፣ ጫማውን ብቻ ከፊቱ ለይተው ለማየት ጨረር እንዳስቸገራቸው ያህል በመዳፋቸው ዓይነ ጥላ ያበጃሉ። እሱም ወደ ተግባሩ አቀርቅሮ ጫማውን ከትንሽ ብረት ላይ እያዟዟረ ሲቀጠቅጥ እንጉርጉሮ መሰል ነገር ያሰማል። ዜማውን አውቃለሁ የሚል ሰው እስካሁን ባይገኝም፣ በቃላቱ መሀከል … “የእርኩም ሥጋ አበሉኝ፣ ዕድሜ ታገኝ ብለው” የሚል ሀረግ ይገኝበታል።

ከገጹ መከራና ስቃይ የሚነበበው ይህ ሰው የተጨማተረች ልቡን በሳጠራ ደረቱና በአሮጌው ዲሪቶ ሸፍኖ ሲኖር “እህ?” ብሎ በደሉን የጠየቀው፣ “በጄ” ብሎ በቁም ነገር ያደመጠው አይገኝም። ድምፁን ግን ይሰማሉ።

ጐህ ሲቀድ፣ ከወደቀበት ተነስቶ ረዥሙን ቁመና ያንጠራራና ባለ ድምጹ፣ “ታስፈሩኛላችሁ! ታስፈሩኛላችሁ እኮ ነው የምለው!” ሲል ያጓራል። የጠገበ ነጋዴ ቦርጩን ሲያገላብጥ፣ ሸቃጮች መንጋቱን አውቀው ለዕለት ተግባራቸው ስምሪት ፊታቸውን ሲያሻሹ፣ ቤት የለሾቹ ደግሞ በድምጹ ተረብሸው “ይሄ የሰፈር ጋኔል ይህችኑ እንቅልፋችንን ነሳን’ኮ” እያሉ በየወደቁበት ይገላበጣሉ። አስኮም ሀገር ምድር አልቀበል እንዳለው እርኩስ መንፈስ፣ የመንጠራወዣ ዕለቱን ለመጀመር ሁሉን ነገር በትዝብትና ፍራቻ ይቃኝና ያደረ አክታውን ይተፋል። ለአስኮ ጌታሁን ዛሬና ነገን የሚለየው፣ በመሀከሉ ያለው ምሽትና ሌሊት የተባለ ጨለማ ነው።

አቶ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ፣ የወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ሲከፈት በመምህርነት የመቀጠር ዕድል አግኝተው ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ ፋናቸውን ሲነቅሉ፣ ስንቅ ለማዘጋጀት ጠብ እርግፍ ያሉት ወላጅ እናታቸውን እና ገና “ረ” ማለትን ምላሱ ያልለመደች አንድ ልጃቸውን አስከትለው ነበር። ሥራ ተጀምሮ፣ እንደ ሰዎች ሁሉ ኑሮውን ከተያያዙት በኋላ ከሥራ ባልደረቦቻቸው መግባባትን፣ ከተማሪዎቻቸው አድናቆትንና ክብርን ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባቸውም። እኚህ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው፣ መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው ያወቁ ሰው፣ ባደሩበት በዋሉበት፣ ሰውን በጥንቃቄና በትህትና መያዝን ሕይወት ያስተማራቸው ነበሩ። አንገታቸውን አቀርቅረው ቢሄዱም ልባቸውን ከሰው የመሰወር ባህርይ አልፈጠረባቸውም። በውስጥ ሀሳባቸው የመጠመድ፣ የህይወትን እንቆቅልሽ አግባብ ካላቸው ወዳጆቻቸው መወያየትን እንደዘወትር ተግባራቸው ከያዙት ቆይተዋል። አቶ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ከራሳቸው አፍልቀው፣ ከመጽሐፍ አጣቅሰው የሚያቀርቡት በወግና በዘዴ የቀረበ ትምህርታቸው፣ ልብ ብሎ ያደመጠን ሁሉ እንዳሳሰበው ይኖራል።

የመረረ የገረረ ባህሪዋን፣ ውስብስብ መልኳን “ይሁን” ብሎ የተቀበላትን ሁሉ ባለ አቅሟ የምትቀጣው ህይወትም፣ እኚህን ሰው በየወቅቱ መሸንቆጥና ማጋጨትን ለመጀመር አልዘገየችም። “ልፈላሰፍ ይላል … ሁለገብ ነው፤ አፉ አያርፍም” የመሰሉ አስተያየቶች ከየሰዉ መሰማት ሲጀመር፣ አቶ ጌታሁን ግን በራሳቸው በመተማመንና የልቡና ቅንነታቸውን አጥርተው ስለሚያውቁ ደንግጠው ዝም ያሉ፣ ፈርተው ያልመለሱ ሰው አልነበሩም።

ከሥራ መልስ ደጃፋቸውን ሳይኮተኩቱ፣ ካረቧቸው ዶሮዎች የታቀፈችውን፣ ጭር ያለችውን ሳይመለከቱ ወደ ንባባቸው አይዞሩም። በሥራ ላይ የነበራቸው እምነት ብርቱ ነበርና ጫማ ሰፍተው ሳንቲም ሲሰበስቡ ከአያሽር-አያገድፍ ደሞዛቸው አናት ታክላ ጉዳይ እንደምትሞላ ስላወቁ፣ ነዋሪውን እስቲገርመው ድረስ መስፋታቸውን ይቀጥላሉ። እጭናቸው አስገብተው ሲቀጠቅጡ ሀሳባቸው ግን የህልውናን ምንነት ከማጠንጠን አያርፍም። እናት ቤት ያፈራውን ሲያበሳስሉ፣ ትንሹ ፍሬው ከቤት ሥራው ጋር በማሾ ብርሃን ሲታገል፣ ኑሮን ህይወት ብለው ተያይዘውት ቆዩ። ከጓደኛቸው ጋር የሚያደርጉት ውይይት እስከ ንጋቱ በሚዘልቅበት ወቅት፣ እናት ስለማሾው ክር ማለቅ ማንገርገራቸው አልቀረም።

ጨዋታ መሀከል የሚስት ነገር ሲነሳ ተከዝ ማለታቸውን ያስተዋለ ጓደኛ ምክንያቱን ቢጠይቃቸው፣ ፍሬውን “እዛ ጓዳ ሂድና አጥና” በማለት ከአጠገባቸው አርቀው ሲያበቁ፣ ትንሽ ተከዝ አሉና፤ በሬ ግንባር በማታህል ማሳ መዘዝ በተነሳ የርስት ክርክር፣ የልጅነት ሚስታቸውን የዘመድ ባላንጣዎች መርዝ አብልተው እንደገደሏትና የዚህም መሪር ሀዘን ከቶም ከልባቸው ሊጠፋ ያልቻለ ነበልባል እንደሆነ አጫወቱት። ለልጃቸው ያላቸው ፍቅርም የዚሁ ጭምር ውጤት እንደሆነ ሲናገሩ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው ነበር። ያዳመጣቸው ቻይነታቸውን አድንቆ በሀዘናቸው አዝኖ ተለያቸው። ፍሬውን ጠርተው፣ ከጭናቸው ላይ አስቀምጠው ብርቱ ተማሪ እንዲሆን ሲመክሩት የነገሩ ድንገተኛነት ገርሞት የህፃን ልቡ ጠየቀች።

እያደር የተሰማው የኚህ ሰው ማንነት በጐን መታየትን ሲያስከትልባቸው፣ አለቆቻቸውም “በአጉል እምነት የታበየ ግብዝ ነው” የማለትን አነጋገር በየአጋጣሚው ሳይሰነዝሩባቸው አላለፉም። “አቶ ጌታሁን ለመሆኑ ‘ህግና ሰው’ የሚልን ነገር ለህፃናት ማስተማር ምንን ለማትረፍ ይሆን? ለወሬው እንደሆነ ሀገሬው አይበቃም?” ሲሉ አለቅየው የተናገሩትን ለመመለስ አፋቸውን እንደከፈቱ አለቅየው ቀድመው በሩን ከፍተው፤ “ውጣልኝ!” አሏቸው። መውጣቱን ወጡ፣ ነገሩ ግን ከልባቸው አልወጣም። የመምህርነት ሙያ ምግባረ ቀናና የተማሩትን የተገነዘቡ ሰዎችን ማፍራት እንጂ ለደሞዝ ማግኛ ብቻ የሚፈጸም የግብር ይውጣ መሆን እንደሌለበት ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር “ከልፈፋቸው አንዱ” ተብሎ ቢወሰድም ያዳመጠ ህሊና ውስጥ መቀረጹ ግን አልቀረም።

ደሴ ዙሪያ ከአንድ ወረዳ የሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ እንዲፈርስ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ተማሪዎችን ሰብስበው ወረዳ ገዥው ዘንድ ለአቤቱታ ሲሄዱ ያየ ሁሉ፣ “ይሄ ሰው ብሎ፣ ብሎ በገዛ እጁ እጁን መስጠቱ ነው” ያላለ አልነበረም። ለፈረንጅ ላሞች ማርቢያነት አስበውት የነበረው መሬት በሌሉበት በግብረ ጠል የተወረሰባቸው በዥሮንድ ማንትሴ ከሄዱበት መጥተው ከብዙ ዘመን ክርክር በኋላ ረቱ። አቶ ጌታሁን ስለ ትምህርት ገበታ፣ ስለ ዕውቀትና ታዳጊ ትውልድ፣ ሰፊ ድርሳን ቢያቀርቡም ለወረዳ ገዥው የወፍ ቋንቋ እንጂ፣ ሌላም ሆኖ አልተሰማቸውም። ትምህርት ቤቱም ፍርስራሽ ላይ የእርሻ መኪና እንቲንዳዳበት ሳምንት አልፈጀም።

ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ እያደር ከዓይንና ከአፍ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ሹማምንት የሚሰነዝሩት አስተያየት ጓደኞቻቸውን ማራቅ ጀመረ። ከሁለቴም ሦስቴ ማስጠንቀቂያና ግሳጼ ተሰጣቸው። እሳቸው ግን እየጐላ ከመጣው መነጠላቸው ጋራ እየታገሉ፣ ከበፊቱ ማንነታቸው ላለመለወጥ መፍጨርጨራቸውን ቀጠሉ። በራስ አነሳሽነት የጀመሩት ተማሪዎችን ይዞ በየገጠሩ በመሄድ ቅዳሜና እሑድን ፊደል ማስቆጠር ከሀገሬው ምስጋና ሲያተርፍላቸው፣ ከወደ አውራጃ ጽሕፈት ቤት ወታደር ተላከባቸው። ጫማቸውን ይጠቀጥቁ የነበሩት ሰው ድንገት የመጣውን ሀይል ማንነት ለመጠየቅ ማብራሪያ በመሻታቸው ቃል ከርሮ በተነሳው ውዝግብ እናት መሀከል እገባለሁ ሲሉ፣ ሰደፍ ደረታቸውን ብሎ ምድጃ ስር ጣላቸው። ጌታሁንም በዚሁ ሳቢያ ለአንድ ወር እንዲታሰሩ ሲደረግ፣ የእናታቸው ሁኔታ እያደር መባስና የፍሬው መውደቅ ሲያሳስባቸው፤ እናት የጐድን አጥንታቸው ተሰብሮ ኖሮ ደም ተፍተው፣ የልጃቸው ስም ከአፋቸው ሳይለይ እንደአረፉ ተሰማ።

ጌታሁን ከእስር ሲወጡ ዓይናቸውም አብሮ ደፍርሶ ወጣ። ከንግግራቸው መጠን ማለትን ጀመሩ። ከግብሩ ግን ይህ ነው የተባለ ለውጥ አይታይባቸውም ነበር። ፍሬውን የበለጠ ወደ ጉያቸው አስጠግተው በርሱና በብርቱ መምህርነታቸው ተጽናንተው ከቆሙበት ጀመሩ። የቅርብ ጓደኞቻቸው አብሮ መዋልንና መታየትን ፈርተው እንደሸሹ የሚያወራው ጥቂት አይደለም። ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ የሚቀርቧቸው ተማሪዎችና ጥርጣሬ ላይ የማይወድቁ ሌሎች ሠራተኞች ብቻ ሆኑ። ለብቻው እንደ ደረቀ ግንድ፣ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ተለይተው ይታዩ ጀመር። ሀዘናቸውን ከሀሳባቸው አሰናስለው በጽናት ለመኖር ሁሌ እንደማሉ ሲኖሩ፣ የልባቸው መሀላ ይንርና ጐልቶ ሲሰማ ፍሬው፣ “ምናልክ አባዬ፣ እኔን ነው?” ይላል። ከሀሳባቸው የባነኑት ሰው፣ “የለም፣ የለም ወዲህ ነው፤ ከራሴ ጋር ነው” በማለት ይመልሱለታል።

በመንፈቁ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ቤት ደጃፍ ሬሳ ታይቶ ሀገር ግልብጥ ብሎ ይመለከታል። ከሥራ የተመለሱት መምህር አጀቡን አልፈው ቢጠጉት፣ ከአፈር የወጣ ሬሳ ተጋድሟል። “የመንደሩ ውሾች ናቸው ፈልፍለው ያወጡት። አይ ሲያጋልጥ፤ አይ የሰው ደም!” ሲል አንዱ፣ ሌላው ተመልካች፣ “ይሄንዬ ወዳጅ ዘመድ ጉዱን አልሰማም” ይላል። ጌታሁን አፋቸውን ከፍተው ሬሳውን ሲመለከቱ፣ አፋቸው እየገቡ የሚወጡትን ዝንቦች ለምን እንደማይከላከሉ የተመለከተ ገረመው።

በረቀቀ ሸር፣ በግፍ ግፍ የተወነጀሉት ዶሮ አርቢው ጫማ ሰፊ መምህር፣ ያለ ፍርድ አሥራ አንድ ወራት ከታሰሩ በኋላ በሁለት፣ ሦስት ምስክሮችና በእብሪተኛ ዳኞች ሀይል ሃያ አመት ተፈርዶባቸው ወደ አዲስ አበባው ዓለም በቃኝ እንዲዛወሩ ተደረገ። የማወጣጫው ግርፋትና ቅጥቀጣው ያደረቃቸው ሰው ወደ ወህኒ መኪና ሲዘዋወሩ፣ ፍሬውን ከአንድ ጐረቤታቸው ሥር ተለጥፎ አዩት። የመጨረሻው ነበር።

ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ዓለም በቃኝ አሥራ ስምንት ዓመታት ታስረው ሲወጡ አዲስ አበባን እንደ ስደተኛ አዲስ መጥ እንጂ፣ ጥንት እንደሚያውቀው ሰው ለማየት አልቻሉም። እኚህ ከሥር መሠረታቸው የተነቀሉ፣ በብዙ ጦር የተወጉ የግፍ ብካይ፣ እግራቸው ወደ ወሰዳቸው ሲሄዱ ውለው፣ ሲመሽ ማደሪያ ፍለጋ አንዱን ኩሊ ቢጠይቁት ተክለ ሃይማኖትን በጣቱ ጠቆመላቸው። ገብተው ወደቁ።

የገቡበትን ትርምስ በመጠኑ ሊገነዘብ የሚችል ትንሽ የህሊና ጭላንጭል ቀርቷቸው ነበርና ከቀን ብዛት አንድ አጥር ጥግ፣ በአሮጌ ዣንጥላ የተገጠመች ጠለላ አበጅተው ጫማ መቀጥቀጥ ጀመሩ። ጫማ አሰሪውም በየአጋጣሚው ለምን ይሄንን ሙያ ብለው እንደያዙት ሲጠይቃቸው በቁስል ፈገግታ፣ “ጌታ ለመሆን ነው እንደ አስኮ ጫማ” ማለትን ጀመሩ ይባላል። በዚሁም “አስኮ ጌታሁን” የሚለው ቅጥል ላያቸው ላይ እንደታተመ ቀረ።

ጀምበር በጠለቀች የአስኮ ጌታሁን ፊት እየተጨማተረ፣ በንዴት ምራቁን በተፋ ቁጥር ፊቱን እየጠረገ፣ እሳት ውስጥ እንደወደቀ ጉበት ያለፈውና የአሁኑ ሥቃይ ወላፈን ሲገርፈው ኩምትርትር እያለ ሄደ። የቀረችው የአእምሮ ጭላንጭል ጨርሶ ከስማ ጨርቅ ጥሎ መሄድ የጀመረ ዕለት፣ አንድ ከቶም የማይረሳ ነገር ተናገረ እየተባለ ይወራል። ይሄውም፣ “ታስፈሩኛላችሁ!” የሚል ነበር።

ጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል

(1973 ዓ.ም)

.

በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

[ምንጭ] – “አስኮ ጌታሁን እና ሌሎች ታሪኮች” (፲፱፻፺፪)፤ ገጽ 106-117።

አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ”

“ቪላ አልፋ” አዲሱ መልክ

ከበዓሉ ግርማ

(1961 ዓ.ም)

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገውን፣ በመደረግ ላይ ያለውንና ወደፊት የሚደረገውን ሁሉ እንደመጠጥ ብርጭቆ አንስተው የማስቀመጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከተሜዎች አሉ። ሰሞኑንም ከሰላምታ በኋላ አርዕስተ ነገር አድርገው የያዙት ትችት ቢኖር ስለ አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጐድጓድ) አዲሱ የቪላ አልፋ መልክ ነው።

ትችቱ እንደተቺዎቹ የበዛ ቢሆንም አንዳንዶቹ፣

“ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ (በተለይ የፍሮይድን ሳይኮሎጂ ከእጅ ጣታቸው እንደዋዛ የሚያንቆረቁሩት ተቺዎች) የዚህን ዓለም ጉዳይ ወደጎን ብለው፣

“አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ።

“ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነገር ነው” የሚሉም አሉ።

ያም ሆነ ይህ የነቀፌታዎቹ መነሾ ሠዓሊው አፈወርቅ ቪላ በመሥራቱ አይደለም። ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን የገነቡት በሰው አፍ አልገቡም። በግል መኖሪያቸው የሰማኒያና የመቶ ሺህ ብር ዘመናይ ቪላዎችን የሠሩት ዓይን አልበላቸውም።

“ታዲያ የአፈወርቅ ስም እንደ ትኩስ ድንች እያንዳንዱ አፍ ውስጥ የሚገላበጥበት ምክንያት ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።

ጐንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነው ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው።

የዚህ አይነት ቤት (ወይም ካስል) በመሥራት አፈወርቅ በዘመናችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ቤቱን የቀየሰው መሐንዲስ G. Boscarino እንዳለው፤

“እንዲህ ያለው ቤት ውስጥ ከአፈወርቅ በስተቀር ሌላ ሰው ቢኖርበት፣ ቤቱ አሁን ያለውን ዋጋና ጥቅም ሊሰጥ አይችልም”።

አዎን፣ ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ የመሰለውን ቤት አልሞ የሚሰራ የለም። የሚሰጠውን ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱው ብቻ ነው።

እንዲህ የመሰለውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ምን እንዳሳሰበው፣ ከተሰራ በኋላ የሚሰጠውንም ጥቅም እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበር። ለማናገር ፈቃደኛ ቢሆንም ጊዜ አልነበረውም።

አናጢዎቹ በየደቂቃው ይጠሩታል።

በተመለሰ ቁጥር “የአገራችን አናጢዎች ለምን አንድ መስመር በትክክል ለመሥራት አይችሉም?” በማለት ይገረም ነበር።

እነሱም በበኩላቸው እሱ አሁን በቅርብ ጊዜ የሠራውን የእንሥራ ተሸካሚ ሥዕል፤ በተለይ ወተት መስሎ በጃኖ ጥለት የታጠረውን ቀሚሷን፣ አለንጋ የመሳሰሉትን ጣቶቿንና ሕልም መሳይ ውበቷን አይተው መገረማቸው አልቀረም።

ገና ተመልሶ ቁጭ ከማለቱም ቀለም ቀቢዎች ይጠሩታል።

አዎን፣ “የሰሜን ተራራ” የተባለውን ሥዕል (ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ሰላም የሚፈጥረውን) የሠራ ሰው ለተራ ቀለም ቀቢዎች ችሎታ ልዩ አድናቆት ሊኖረው አይችልም።

አሁንስ አፈወርቅን የሚጠራው ሰው የለም ብዬ በመተማመን ጥያቄዬን ወርውሬ፣ ብዕሬን ከወረቀት ለማገናኘት ስቃጣ፣ አንድ ጽጌረዳ አበባ የት እንደሚተክሉ የቸገራቸው፣ ወይም አበባ የያዘውን ሳጥን የት እንደሚያስቀምጡ ግራ የገባቸው ለምክር ይጠሩታል። ሳያማክሩት ያስቀመጡት፣ ወይም የተከሉት እንደሆነ ኋላ ማንሳታቸው አይቀርም።

አፈወርቅ ደጋግሞ እንደሚለው፣

“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው”።

ሠራተኞቹም ደከሙ። ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ያራውጣቸው ነበር።

ጥሪው እያነሰ ሄደ። ቁጭ ለማለት ቻልን።

“ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊው የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል” አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ።

በሁለት ወር ያልቃል ተብሎ የታሰበው ቤት አሁን አራተኛ ወሩን ሊጨርስ ነው። በአራት ወር ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕሎች ብቻ ነበር ለመሥራት የቻለው። የቀረውን ጊዜ ያዋለው በቤቱ ሥራ ላይ ነበር።

“ቪላ አልፋ” የተሠራው በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን ቤቱን ለመሥራት አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥቦ ነበር። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል።

ይሁንና በኔ በጠያቂው በኩል ሃያ ስድስት በሃያ ስድስት ሜትር ካሬ መሬት ላይ የተሠራው አዲሱ ቤት ይህን ያህል የሚያስደንቅ ወጭ የሚጠይቅ መስሎ አልታየኝም። አፈወርቅም ስንት ገንዘብ እንደጨረሰ ትክክለኛ ዋጋውን ሊገልጽልኝ አልፈቀደም።

ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስሎ ለመስራት ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽልኝ እንዲህ አለ፣

“ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም።”

አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው።

በቤቱ ውስጥ ያለ ምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው እሱ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። የቤቱ ቆርቆሮ ቀይ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። ቤቱ ነጭ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው።

አንድ ሥዕል አንድ ግድግዳ ላይ በአንድ በኩል እንዲሰቀል የተደረገበት ያለ ምክንያት አይደለም። ቤቱ የተሠራው ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ሌላ ምክንያት አለው። ቤቱም ቀለሙም አቀማመጡም – ሁሉም ባንድነት ተዋህደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው።

“ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ። የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ አውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር።”

“አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው።”

“ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ላንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትዕይንት ጠቃሚው ነው።”

አዎን፣ ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

ቤቱ አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው።

ሦስቱ መስኮቶች ሦስት አይነት ቀለማት የተቀቡበት ምክንያት አለው። የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንጸባርቁ ለማድረግ ነው።

የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው። እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሱም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው።

የምሥጢር በሩ ያለ ምክንያት አልተሠራም። አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው።

የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው።

አዎን፣ በአፈወርቅ ቤት ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

በዓሉ ግርማ

በዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – መነን (ሚያዝያ ፳፱፣ ፲፱፻፷፩)፤ ገጽ ፲፮-፲፯።

ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ

“ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ”

በሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ማንኛውንም መጽሐፍ ገዝቼም ሆነ ተውሼ ከማንበቤ በፊት ማን እንደጻፈው፣ በኋላው አጎበር ምን እንደተጻፈ፣ መግቢያ ወይም መቅድም ካለው እዚያ ውስጥ ምን እንደተባለ፣ ማውጫ ካለውም በዚያ የሠፈረውን ገረፍ ገረፍ አድርጌ እመለከታለሁ።

ይህንን የማደርገው መጽሐፉን ከአጎበር እስከ አጎበር ማንበብ ከመጀመሬ በፊት “መነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው ወይንስ አይደለም?” የሚል ግምት ለመውሰድ ያህል ነው። አብዛኛውን ጊዜም ግምት ወስጄ በማነባቸው መጻሕፍት ከሞላ ጐደል እደሰታለሁ፤ የአእምሮ ብርሃን የሚሰጡ፣ ስለ ሕይወት ብዙ ነገር የሚያስተምሩ፣ የሚያዝናኑና የሚያስደስቱ ናቸው።

ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹን ብጠቅስ እወዳለሁ።

የሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” (1958)፣ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” (1962)፣ የአፈወርቅ ገብረየሱስ “ልብወለድ ታሪክ [ጦቢያ]” (1900) እና “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ” (1901)፣ የገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” (1916)፣ የአሰፋ ገብረማርያም “እንደወጣች ቀረች” (1946) … እና ሌሎችም።

ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የአገራችን ደራስያን የማውቃቸው በጽሑፎቻቸው አማካኝነት እንጂ በግንባር አይደለም። በግንባር ላያቸው ፍላጎት ቢኖረኝ ኖሮ እንኳ ባልተቻለኝም ነበር፤ እነሱ የኖሩበትና እኔ የምኖርበት ዘመን በጣም የተራራቁ በመሆናቸው።

ዳኛቸው ወርቁ ግን የዕድሜ አቻዬ በመሆኑና ሁለታችንም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመሆናችን እሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ብዙ ጊዜ የመገናኘትና የመጨዋወት ዕድል አጋጥሞናል።

የማልረሳው የመጀመሪያው ግንኙነታችንን ነበር።

ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ቀን፣ የቀድሞው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባልደረባዬና ወዳጄ የሆነውን ሰው ለመጠየቅ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እሄዳለሁ። ያ ወዳጄ በዚያን ሰዓት ከዳኛቸው ወርቁ ጋር ነበር፤ በቢሮው ውስጥ።

“እገሌ”፣ “እገሌ” ብሎ አስተዋወቀንና የ“አደፍርስ” ደራሲ መሆኑን ገለጸልኝ። “አደፍርስ” ስለሚባል መጽሐፍ ከዚያን ቀን በፊት ሰምቼ አላውቅም። ከታተመ አንድ አመት እንኳ የሞላው አይመስለኝም።

“በዚህ ርዕስ የሚታወቅ መጽሐፍ ካለ ምነው መጽሐፍ መሸጫ መደብር ውስጥ አይቼው አላውቅም?” ስል ጠየቅሁት ዳኛቸውን።

“ቀደም ብሎ እንኳ ከመጽሐፍ መሸጫ መደብር ይገኝ ነበር፤ አሁን ግን እኔ ዘንድ እንጂ ሌላ ቦታ አታገኘውም” አለኝ።

ሦስታችንም የመጻሕፍት አፍቃሪያን ስለነበርን ስለሥነጽሑፍና በጊዜው ታትመው ይወጡ ስለነበሩት መጻሕፍት ስንጨዋወት ቆየንና በመጨረሻም ዳኛቸውና እኔ ወዳጃችንን ተሰናብተን ወጣን።

“መጽሐፍህን ልገዛው እፈልግ ነበር። ነገር ግን እንዴት ነው የማገኘው?” አልኩት።

“ማግኘት እንኳ ታገኘዋለህ። ነገር ግን ዋጋው እንደቀድሞው አይደለም” አለኝ።

“ስንት ነው?” አልኩት።

“መጀመሪያ በአምስት ብር ነበር የሚሸጠው። ነገር ግን አልሄድ ስላለ አስር ብር አደረግሁት። አሁንም እንደገና አልሄድ አለ። ስለዚህ መሸጫ ዋጋውን አስራ አምስት ብር አድርጌዋለሁ” አለኝ።

ይህንን ስሰማ ሳቅ ወጥሮ ያዘኝ። ነገር ግን ከዚያ በፊት የማልተዋወቀውን ዳኛቸውን እንዳላስቀይመው በመፍራት ሳቄን ታግዬ አስቀረሁትና፣

“ለማንኛውም አንድ ኮፒ እፈልጋለሁ” አልኩት።

“እንግዲያውስ ተከተለኝ” ብሎኝ መኪናው ውስጥ ገባ። እኔም በያዝኩት መኪና ተከተልኩት።

በፒያሳ አድርገን አራት ኪሎ ስንደርስ ወደታች ተጠምዘን ወደ ምኒልክ ግቢ አቅጣጫ አመራን። እዚያ ሳንደርስ ከፓርላማ ወደ እሪ በከንቱ የሚያመራውን መንገድ አቋርጠን ትንሽ ከሄድን በኋላ ወደ ቀኝ ታጥፈን በጠባብ ኮረኮንች መንገድ ተጓዝን። ከዚያም በኋላ ከመኪናችን ወርደን በእግራችን ወደ መኖርያ ቤቱ አመራን።

ከጽሕፈት ቤቱ ስንገባ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ በብዙ ረድፍ የተደረደሩ የመጻሕፍት ክምር ይታያል። ሄድ ብሎ ከአንዱ እሽግ አንድ ኮፒ መዞ አወጣና “ይኸውልህ” አለኝ። ተቀብዬው፣ ሂሳቡንም ከፍዬ ተሰናብቼው ወጣሁ።

ዳኛቸው ወርቁ ልዩ ባህሪ ያለው ሰው መሆኑን ያን ቀን ነው የተረዳሁት።

ከዚያም በኋላ ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል፤ ተቀራርበናልም። እኔ እንደማውቀው በጣም ሰዓት አክባሪ ሰው ነበር። አንድ ቀን እቢሮው ተቃጠርንና ከዚያ ስሄድ እሱ ከቢሮው ወጥቶ ወደ መኪናው ሲያመራ አየሁና፤

“ዳኛቸው! ዳኛቸው!” ብዬ ተጣራሁና፤ “ምነው? እረሳህ እንዴ? ቀጠሮ ነበረንኮ!” አልኩት።

“ቀጠሮውንማ አፍርሰህብኝ ወደ ሌላ ጉዳዬ መሄዴ ነበር” አለኝ፤ መለስ ብሎ።

እጅግ በጣም ተገርሜ ሰዓቴን ብመለከት ያሳለፍኩት ጊዜ ሦስት ደቂቃ ብቻ ነበር!

በሌላ ቀንም ኩራዝ መጻሕፍት መደብር እንድንገናኝ ተቃጠርን። በቀነ ቀጠሮው ከዚያ ብሄድ ዳኛቸው የለም። አስራ አምስት ደቂቃ ያህል ጠበቅሁትና አለመምጣቱን ሳይ አንዳች እክል ቢያጋጥመው ነው እንጂ አይቀርም ነበር አልኩና ወደ ሌላ ጉዳዬ ሄድኩ።

ከዚያ በኋላ በሌላ ቀን በአጋጣሚ ስንገናኝ በቀጠሮአችን ቀን ለምን ሳይመጣ እንደቀረ ጠየቅሁት።

“እኔማ ከተቃጠርንበት መጻሕፍት መሸጫ መደብር ሄጄ ነበር። እንዲያውም ሰዓት አሳልፋለሁ ብዬ ስከንፍ መኪናዬን ገጨኋት። አንተ ግን በቀጠሮው ቦታ አልነበርክም” አለኝ።

“ኧረ እኔስ ከዚያ ነበርኩ! አንተ ነህ ቀጠሮ ያፈረስከው” አልኩት።

“ወደ የትኛው መደብር ነበር የሄድከው?”

“ኤንሪኮ ባር ፊት ለፊት ያለው … ቸርችል ጐዳና”

“አዬ! ለካስ ያልተግባባነው ከቦታው ኖሯል! እኔ ደሞ የሄድኩት አምስት ኪሎ ካለው መደብር ነው” አለኝና ሁለታችንም በሠራነው ስሕተት ተሳስቀን ተለያየን።

ዳኛቸውን ከሌሎች ሰዎች ለየት የሚያደርገው ሰዓት አክባሪነቱ ብቻ አልነበረም። እኔ እንደማውቀው እውነተኛ ሰው ሆኖ ተጠራጣሪም ነበር – “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” እንደሚባለው አይነት!

የሆነ ሆኖ ወደ መጻሕፍት እናምራ።

“አደፍርስ” በርካታ ምሁራንን በሰፊው ያነታረከ መጽሐፍ ስለሆነ እኔም ተጨማሪ ንትርክ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለሁም። ስለምንነቱ ጥቂት ሳልል ግን ለማለፍ አይቻለኝም።

“አደፍርስ” በሌሎች ልብ ወለዶች የምናየው ዓይነት አንድ ወጥ የሆነና የጐለበተ ፈጠራ ታሪክ የለውም። በዚህ ፈንታ ቁርጥራጭ ትርኢቶች ነው የሚታዩበት።

ትረካውን ይፋትንና ጥሙጋን ከጣርማ በር ተራራ ላይ ሆነው ሲመለከቱት ምን እንደሚመስል የሙዚቃ ቃና ባለው ቋንቋ ይጀምራል፤

“ቁንዲ አንገቷን አስግጋ ቃፊርነት የቆመች መስላለች። የዓዋዲና የጀውሃ ጅረቶች ደረታቸውን ለፀሐይ ሰጥተው ይምቦገቦጋሉ። ሰማይና ምድር የተገናኘበት፣ ሕይወት ያሸለበችበት የሚመስለውን በስተግርጌ የሚታይ ሜዳ አቧራ ረግቶበታል … የይፋትና ጥሙጋ አውራጃን ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከቱት እግዚአብሔር ዓለምን ሠርቶ ሲያበቃ የተረፈውን ትርክምክም ያጐረበት እቃ ቤቱ ይመስላል – ሸለቆው፣ ጉባው፣ ተራራው፣ ገመገሙ፣ ጭጋጉ፣ አቧራው ሕይወትን አፍኗት ተኝታለች – ያቺ በሌላው አገር የምትጣደፈው፣ የምትፍለቀለቀው፣ የምትምቦለቦለው ሕይወት እዚህ እፎይ ብላለች – በርጋታ፣ በዝግታ ታምማለች፤ በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ …” (ገጽ ፭)

ገጠሩን በተዋበ ቋንቋ ከገለጸልን በኋላ ወ/ሮ አሰጋሽ የተባሉ የገጠር እመቤት ከጢሰኛቸው ጋር ቲያትር መሰል የንግግር ልውውጥ ሲያደርጉ ያሳየናል። ጢሰኛው የዘንጋዳ ዘር አጥቶ ሊበደር ወደ እመቤቱ ዘንድ መጥቶ ይለምናል። ወ/ሮ አሰጋሽ በተባ አንደበት የጢሰኛቸውን ሞራል አንኮታኩተው ከሰበሩት በኋላ ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ ሰጥተውት በመኸር ወራት አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይነግሩታል።

የ”አደፍርስ” ጀርባ ሥዕል (በታዬ ወልደ መድኅን)

አራጣው በጣም የበዛ መሆኑ በተሰበረ ድምፅ ይገልጽላቸውና እንዲራሩለት ይማጸናቸዋል። ወ/ሮ አሰጋሽ ግን በአራጣው ከተስማማ ዘጠኙን ቁና እንዲወስድ፣ አራጣው በዛ ካለም እንዲተወው ርህራሄ በሌለው አንደበት ቁርጥ አድርገው ይነግሩታል።

ሌላ ምርጫ ስለሌለው እመቤቱ ለሚሰጡት ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይስማማል። ወ/ሮ አሰጋሽም ይህንን ገፈፋ ውለታ እንደዋሉለት በመቁጠር በመሬታቸው ላይ የበቀለውን የድርቆሽ ሳር (ሰማንያ ሸክም ይሆናል) አጭዶ፣ ተሸክሞ አምጥቶ ከደጃቸው እንዲከምረው ይነግሩታል። እሱም ትእዛዛቸውን ለመፈጸም የቃል ውል ከገባ በኋላ ዘንጋዳው ተሰፍሮለት አህያውን እየነዳ ከግቢያቸው ይወጣል።

በዚህ ክፍል ያለው ድንቅ ትርኢት በመድረክ ላይ የሚታይ ትርኢት እንጂ ሌላም አይመስል።

ታሪኩ በዚሁ ይቀጥላል ብለን ስንጠባበቅ ሳለን የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ ይከፈትና ሌሎች ባህርዮች ሲጨዋወቱ እናያለን።

ምሽት ይሆንና “የፌንጣ ሲርሲርታ፣ የዝንብ ዝዝታ፣ የንቦች እምምታ” እንሰማለን። ጨረቃ ትወጣለች። የወ/ሮ አሰጋሽ አገልጋይ የሆነውን የወርዶፋ ዋሽንት ሙዚቃ እናዳምጣለን።

በዚህ መልክ የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ እንደገና እየተከፈተ እስከ መጨረሻው ድረስ የተለያየ ትርኢት እናያለን።

ከዚህ ቀደም እንዳልኩት መጽሐፉ ከልብ ወለድነት ይልቅ ወደ ድራማነት የተጠጋ ነው … አንዳንዴ አስቸጋሪ ቢሆንም በውብ ቋንቋ የተደረሰ ድራማ።

የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ዐቢይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት እንግሊዝ አገር የታተመውና “The Thirteenth Sun” የተሰኘው መጽሐፍ በብዙ የአውሮጳውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንደታተመም ዳኛቸው ራሱ አጫውቶኛል።

መሠረተ ሀሳቡ ከ“አደፍርስ” ጭብጥ እጅግም የራቀ አይደለም።

በጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተሳሰብና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ (በቀድሞው ትውልድ እምነትና በዛሬው ትውልድ አመለካከት) መሀከል ባለው ግጭት ላይ የተገነባ ልብወለድ ነው። በእኔ አስተያየት በትረካው ረገድ “The Thirteenth Sun” ከ“አደፍርስ” ላቅ ያለ ሲሆን በቋንቋው ውበት ግን አደፍርስ ይበልጣል።

ከዳኛቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበትን ቀን ምንጊዜም አልረሳውም ብዬ ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ አስከሬኑን የሸኘኹበትንም ቀን አልረሳውም።

ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ምሽት ላይ ሁለት ደራሲያን ወዳጆቼ በተለያየ ሰዓት ስልክ ደውለው ዳኛቸው ወርቁ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱንና በማግስቱ ማለዳ ከ11 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ አስከሬኑ ወደ ትውልድ አገሩ፣ ደብረሲና እንደሚሸኝ ገለጹልኝ።

ከሌሊቱ በ11 ሰዓት ተነስቼ ምኒልክ ግቢ አጠገብ ወደሚገኘው ቤቱ አመራሁ።

እዚያ ስደርስ አምስት የሚሆኑ የግል አውቶሞቢሎችና ከሠላሳ የማይበልጡ በጣም ጥቂት ሰዎች (አብዛኞቹ የሠፈር ሴቶች መሰሉኝ) በአካባቢው ቆመው አየሁ። ሌሎች አስር የሚሆኑ ሰዎች ደሞ ከዚያው አጠገብ ከቆመው መለስተኛ አውቶቡስ ውስጥ ገብተው ተቀምጠዋል።

የአስከሬኑ ሳጥን በአውቶቡሱ ጣርያ ላይ በሸራ ተሸፍኖ ታስሯል። በአካባቢው አንድ ሰው ብቻ ሲነፋረቅና እንባውን ሲጠርግ ተመለከትሁ። ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ ብመለከት አንድም የማውቀው ሰው የለም። ትናንትና ደውለው ያረዱኝ ወዳጆቼም በዚያ የሉም።

እጅግ በጣም ተገረምኩ፤ አዘንኩም።

“አደፍርስ” እና “The Thirteenth Sun” የሚያህሉ ድርሰቶችን ያቀረበልን የብዕር ሰው አስከሬኑ የሚሸኘው በዚህ ሁኔታ ነው ወይ? ወይንስ ዳኛቸው ወርቁ ራሱን አግልሎ ስለሚኖር ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹና ደራስያኑ ጭምር ዜና ዕረፍቱን በጊዜ ሳይሰሙ ቀሩ? ስል አሰብኩ።

የሆነ ሆኖ ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ ሲሆን አስከሬኑን የጫነው መለስተኛ አውቶቡስ ወደ ደብረሲና ለመጓዝ መንቀሳቀስ ሲጀምር በሀሳቤ፣

“ነፍስህን ይማረው። የዘላለም እረፍት አግኝ” ብዬ ተሰናብቼው ወደ ቤቴ አቅጣጫ አመራሁ።

ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

(1988 ዓ.ም)

በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – “ሹክታ” (፲፱፻፺፪)፤ ገጽ 6-20።

.

.

 

“በራሪ ወፎች” (የሥዕል እይታ)

“በራሪ ወፎች” – የሥዕል ኤግዚቢሽን

በሕይወት ከተማ

 

በየካቲት ወር፣ በብሔራዊ ሙዚየም ጋለሪ የስናፍቅሽ ዘለቀ “በራሪ ወፎች” የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ተዘጋጅቶ ነበር። ትዕይንቱንም ለአንድ ሰዓት ያህል ከአንድ ወዳጄ ጋር ተመልክተን ስንወጣ ራሷን ስናፍቅሽን በር ላይ አገኘናት።

ስለ ሥዕሎቿ አንዳንድ ነገሮችን አወራርተን እንዳበቃን፣ ስናፍቅሽ (ዐውደ ርዕዩን በማስመልከት ነው መሰለኝ) “ሰው የደገሰውን መጥተው ሲበሉለት ደስ ይለዋል” አለችን። ወዳጄ ግን፣ “አይ ሰው እንኳ ባይመጣ እኔስ እራሴ እበላዋለሁ” ብሏት ተሳሳቅን።

ስናፍቅሽ ዘለቀ በ1977 ዓ. ም. ከአዲስ አበባ የሥነጥበብ ት/ቤት በቀለም ቅብ ተመረቀች። በ1979 የመጀመሪያዋን የግል ኤግዚብሽን በአልያንስ (Alliance EthioFrançaise) አሳየች። በርካታ ዐውደ ርዕዮችንና የሥነ ጥበብ ውይይቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለማዘጋጀትም በቃች። እንዲሁም “ፏ ብዙነን” የተባለውን የሴቶች ሰዓሊያን ማህበር አቋቁማለች። በሕንድ ት/ቤትም (Indian National School) የሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ መምህርት ሆና ለረጅም ዓመታት አስተምራለች።

ስናፍቅሽ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ለሠላሳ አመታት ያህል ስታቀርብ የቆየች ባለሙያ ናት። በማህበራዊ ጉዳይ ባተኮሩ ስራዎቿም ስትታወቅ በተለይም የሴቶችን ትግል የሚያሳዩ በርካታ ሥዕሎችን ለእይታ አቅርባለች። በራሷም አገላለጽ “…ሴት ልጅ የቤተሰብ ኃላፊ ከሆነች እንደ እናትም ብዙ ኃላፊነት አለባት።  ልጅ ሲወለድ ብሩሽና ሸራ መቀመጥ የለበትም” ትላለች።

በአሁኑ ዐውደ ርዕይ ግን ስናፍቅሽ በከፊል አዲስ አትኩሮት የያዘች ይመስላል። እራሷ እንደነገረችኝም፣ ካለፈው አመት ጀምሮ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተለየ መልክ እየያዘ ሄዷል። “በጨለማ ውስጥ ብርሃንን፣ በመኖር ውስጥ አለመኖርን፣ በማጣት ውስጥ ማግኘትን … አብረው ተቆላልፈው ማየት ጀምርያለሁ” ትላለች።

እናም የሕይወት “ዙር ጥምጥም” (ሙሉ ክብነት) በብዛት እየታያት መምጣት እንደጀመረ ትናገራለች። ይህንንም ፍልስፍናዋን በሥዕሎቿ ላይ ለማሳየት እንደሞከረች ይታያል።

በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡት ወደ 40 ከሚጠጉ ሥዕሎቿ ውስጥ ግማሾቹ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ ግማሾቹ ደግሞ “ምናባዊ” (Abstract) ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በአዲሱ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተቀረጹት ደንገዝና ጨለም ብለው “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) የሆኑት ሥዕሎቿ ቀልቤን ስበውታል።

መቼም የሥዕል ፎቶ ቅጂዎች የዋናውን ሥዕል ግርማ ሞገስ እንደማይገልጹ የታወቀ ነው። የዚህም ዐውደ ርዕይ በብዛት የተሰራበት አክሪሊክ (Acrylic) ቀለም ደግሞ በተፈጥሮው በፎቶ ሲታይ ልጥፍ (Flat) የመሆን ባሕርይ አለው። በዚህ ምክንያት የሥዕሉን መልክ በትክክል ማሳየት የሚችል ምስል ማንሳት አስቸጋሪ ነው። እናም፣ ሁሌም ቢሆን ሥዕሎችን ራሳቸውን በአካል ሄዶ ማየት አጥብቆ ይመከራል።

እስቲ፣ ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹን “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) ሥዕሎቿን እንያቸው።

ይህ ሥዕል ጨለም ያለ ድባብ (Background) ላይ የተመሰረተ ሲሆን በቀጥታ መስመሮችና ክቦች ተገንብቶ የተለያዩ ቀለማትን በመስመር ፈርጆ ያሳያል። የቅርጾቹ ቀላልነት (Simplicity)፣ የክቦቹ አቀማመጥ፣ የመስመሮቹ ጥራት፣ እና የቅርጾቹ አነባበር (Depth) ደስ የሚል የመውደቅን ወይም የማሽቅልቆልን ስሜት ይሰጣል። ሠዓሊዋ አስቸጋሪ የሆነውን ጥቁር ቀለም ስትጠቀም ገጽታው ልጥፍ እንዳይሆንና ንብብር እንዲኖረው በተለያዩ ቀለማት መደገፏ ይታያል። ከሥዕሉ በታች በኩል የሚታየውን ጭስ ጠገብ ሰማያዊ ምሕዋሩን (Space) ያስተውሏል። ይህ ተንጠልጣይ ቦታ የመንሳፈፍን፣ የመምጠቅን ስሜት አሳድሮብኛል … ብቻ የሥዕል እይታ እንደተመልካች ይለያያልና ለእናንተ የተለየ ስሜት ይፈጥርባችሁ ይሆናል።

“መስመሮችና ቅርጾች በምሽት”

Acrylic on Canvas

100 x 75 cm


ይህኛውም ከላይ እንዳየነው በጥቁር ድባብ የተመሰረተ፣ ብዙ የተለያየ መጠን ያላቸውን ክቦች ያዋቀረ ነው። የተለያዩት ቀለሞች ግን እንደፊተኛው በመስመሮች የታገዱ ሳይሆን በነጻነት የሚፈሱ ናቸው። ሥዕሉም በውስጡ ውስብስብ ድርብርብነት (Layering) ይታይበታል። እነዚህ ድርብርብ ቀለማት ከክቦቹ ጋር ተዋህደው የሥዕሉን ሙሉነት ይገልጻሉ። እያንዳንዱ ክብ ሆነም ወፍ የራሱ የሆነ ገጽታ (Expression) በፊቱ ላይ ይታያል። ለምሳሌ፣ በመሀል ያለውን ትልቁን ክብ/ወፍ ብንመለከት፣ የወፉ አይን ውስጥ የሚታየው እይታ ምሰጣ ውስጥ መግባትን የሚገልጽ ይመስላል።

“በራሪ ወፎች”

Acrylic on Canvas

95 x 50 cm


ይህኛው ደግሞ በአፈርማ (መሬታዊ) ቀለማት ተገንብቶ አንድ ክብን በማማከል ወደ ውጭ የሚፈሱ (Radiating) መስመሮችን የያዘ ነው። የመስመሮቹ ጥራት አሁንም የሚደነቅ ነው። እዚህ ላይ ስናፍቅሽ የተጠቀመችው ስልት ቀለማቱን ከመደራረብ ይልቅ እያንዳንዱን “መስኮት” የተለያየ ቀለም ወይም “ጥለት” (Pattern) መስጠት ነው። ህብረ ቀለሙ በመስመሮቹ ቢታሰርም ከመስመሮቹ መፍሰስ ጋር በጋራ ሲታይ የተሟላ ሥዕል እንዲሆን አድርጎታል። የሥዕሉ አሰዳደር (Composition) እንዲሁም የመስመሮቿ አካሄድ ሌጣ ቢመስልም ምሕዋሩን በሚገባ ተጠቅማበታለች።

.

“ክብና መስኮቶች”

Acrylic on Canvas

95 x 71 cm


ይህ ሥዕል ከአሁኑ “ዙር ጥምጥም” የአሰራር ስልቷ ወጣ ብሎ የ“ሴትነት” እይታ የያዘ ይመስላል። ሥዕሉ የጠንካራ ሴትን ገጽታ የሚገልጽ ይመስላል። ሴቲቷ “ኮስታራነት” ተላብሳ ዓለሟን አሸንፋ በራሷ መንገድ መሄድን የመረጠች መስላ ትታያለች። አሁንም የሥዕሉ መስመሮች እንደተለመደው ግልጽ ናቸው። ይህችንም ሴት ለመሳል የተጠቀመችው እኒህኑ ጠንካራ መስመሮቿን ነው። ባጠቃላይ የሴትየዋን ፊት “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) በማድረግ ጠንካራ የፊት ገጽታ ለመፍጠር ችላለች። በሴቲቷ ፊት ላይ የሚታዩትን ቀጫጭን መስመሮች ያስተውሏል። በእሳታማ ቀለማት አጠቃቀሟም ተጨማሪ ሙቀት ለሥዕሉ ሰጥታዋለች።

.

.

“Concentration”

Acrylic on Canvas

92 x 62 cm


ይህኛውም የፊት ገጽን በቅርጽ እያሳየ በመሬታማ ቀለማት የተሰራ ነው። ጥሩ የብርሃንና ጥላ አጠቃቀም ይታይበታል። የእናትነት ገጽታ በሚገባ በመቀረፁ ደግነትንና እንክብካቤን በአንገቷና በአይኖቿ እናያለን። አሁንም የስናፍቅሽ አቀራረብ በተለየ ሁኔታ “ቅርጻዊ” ነው። በመስመሮችና በቅርጾች የምትፈልገውን ሁሉ በሥዕሎቿ ማስተላለፍን የተካነችበት ይመስላል።

.

.

.

“እናትና ልጅ”

Acrylic on Canvas

72 x 63 cm


የስናፍቅሽ የአሳሳል ጥንካሬ በ“ቅርጻዊ” ስልት ሸራዋን ማድመቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። መስመሮቿን በሚገባ ትስላለች። ቀለሞቿን ደግሞ አነባብራ ትጠቀማለች። ሰፋ ያለ ምሕዋር (Space) መፍጠርንም የግሏ አድርጋዋለች።

ዛሬም ቢሆን ስናፍቅሽ የምትሰራው በዚህ “ምናባዊ” (Abstract) ስልት ብቻ አይደለም። ዐውደ ርዕዩ ላይ በመጠኑ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ አንዳንዴም “ገጽታዊ” (Expressionist) የሆኑ ሥዕሎችም ለእይታ ቀርበዋል። እነዚህ ሥዕሎቿ ግን ከተለመደው የአሳሳል ስልት እምብዛም ወጣ ያላሉ በብዛትም “ጌጣዊ” (Decorative) የሚመስሉ ናቸው። የሰዎቹ ፊትና ገጽታ ተመሳሳይና ስሜት አልባ ይመስላሉ። የሥዕሎቿን ጥንካሬ እምብዛም አናይባቸውም።

እስቲ ከእነዚህ ሥዕሎች ለምሳሌ አንድ እንይ፦

“ወደ ገበያ”

Acrylic on Canvas

92 x 62 cm

.

በአዲስ መልክ እየተጠቀመችው ያለው “ቅርጻዊ” የሆነው “ዙር ጥምጥም” ስልቷ ግን ቀልብ ይስባል። በዚህ ስልት ክቦቿ እውነትም መስመር የያዙላት ይመስላሉ፤ የምትስላቸው ገጻዊ ሥዕሎችም እጅግ ገላጭ ናቸው።

ስናፍቅሽን ለምን ይህን አዲስ አቅጣጫ እንደቀየሰችም ጠይቄአት ነበር። “ምናልባትም በሰል ማለት ይሆናል … ለምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም … አሁን ግን የሚሰማኝ እንደሱ ነው” አለችኝ።

እግረ መንገዴን ስለ ጥቁር ቀለም አጠቃቀሟ ጠይቄአት ስትናገር፣ “ትምህርት ቤት እያለን ጥቁር ቀለምን እንድንጠቀም አያበረታቱንም ነበር። አንደኛ፣ ‘ያቆሽሻል’ ይሉናል፤ ሁለተኛ፣ የተለያዩ ቀለሞችን በመደበላለቅ የሚመጣ ስለሆነ እምብዛም በቀጥታ አንጠቀምበትም። አሁን ግን ለመድፈር ወስኜ እየሰራሁበት ነው። የተለያየ የጨለማ ደረጃም ላመጣበት ችያለሁ” ትላለች።

በመጨረሻም፣ ከስናፍቅሽ ጋር በሥዕል አርእስት አወጣጥ ዙርያ ተወያይተን ነበር። እኔም፣ “መጀመሪያ አርእስት አስበሽ ነው ሥዕሉን የምትሰሪው? ወይስ ከሰራሽው በኋላ ነው የምትሰጭው?” ብዬ ጠየኳት። እሷም በተራዋ፣ “እንደሁኔታው … አንዳንዴ መጀመሪያ፣ አንዳንዴ መሃል አንዳንዴም መጨረሻ ነው” አለችኝ።

የጥበብ ሰዎች በሥራቸው ፍልስፍና ላይ ብዙ ሲንገላቱ አያለሁ። የትኛው ይሆን የሚቀድመው … ጥበብን  መፍጠር? ወይስ ለመፍጠር ፍልስፍናን ማጠንከር? … አንድ የጥበብ ሥራ መልዕክት ሊኖረው የግድ ነውን? … ጥበብ ያለ ፍልስፍና ወይም መልዕክት ሌጣውን በራሱ ብቻ መደነቅስ ይችላል? … አንዳንድ ጊዜ “ሥዕሎች ምነው አርእስት ባይኖራቸው?” ያስብለኛል።

ስናፍቅሽ ብዙ የጥበብ ውይይቶችን እንደምታዘጋጅ፣ የህዝቡንም የሥዕል ንቃተ ኅሊና ከፍ ለማድረግ (እንደ መምህርነቷ) ሃላፊነት እንደሚሰማት ትናገራለች። ስለዚህም በዐውደ ርዕዮቿ ላይ በመገኘት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ተመልካች ያልገባውን ለማስረዳት እንደምትሞክር ገልጻልኛለች። የጥበብ ሰዎች የሥዕል ድግሳቸውን ስለሚቋደሱ ተመልካቾች ምን ያህል መጨነቅ እንዳለባቸው ያሳስበኛል።

ወደፊት ሥራዋ ወዴት እንደሚመራት ለማየት ጓጉቻለሁ።

.

ተጨማሪ

ሌሎች ሥዕሎቿን ለማየት

 ቃለመጠይቅ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ‹‹ሥዕልን ያን ያህል የተገነዘበ ማኅበረሰብ አለን ለማለት ያስቸግራል››

የኤግዚቢሽን ዘገባ ከሪፖርተር ጋዜጣ  በ‹‹በራሪ ወፎች›› ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ

“በራሪ ወፎች Catalogue” የካቲት 2009