“በራሪ ወፎች” – የሥዕል ኤግዚቢሽን
በሕይወት ከተማ
በየካቲት ወር፣ በብሔራዊ ሙዚየም ጋለሪ የስናፍቅሽ ዘለቀ “በራሪ ወፎች” የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ተዘጋጅቶ ነበር። ትዕይንቱንም ለአንድ ሰዓት ያህል ከአንድ ወዳጄ ጋር ተመልክተን ስንወጣ ራሷን ስናፍቅሽን በር ላይ አገኘናት።
ስለ ሥዕሎቿ አንዳንድ ነገሮችን አወራርተን እንዳበቃን፣ ስናፍቅሽ (ዐውደ ርዕዩን በማስመልከት ነው መሰለኝ) “ሰው የደገሰውን መጥተው ሲበሉለት ደስ ይለዋል” አለችን። ወዳጄ ግን፣ “አይ ሰው እንኳ ባይመጣ እኔስ እራሴ እበላዋለሁ” ብሏት ተሳሳቅን።
ስናፍቅሽ ዘለቀ በ1977 ዓ. ም. ከአዲስ አበባ የሥነጥበብ ት/ቤት በቀለም ቅብ ተመረቀች። በ1979 የመጀመሪያዋን የግል ኤግዚብሽን በአልያንስ (Alliance Ethio–Française) አሳየች። በርካታ ዐውደ ርዕዮችንና የሥነ ጥበብ ውይይቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለማዘጋጀትም በቃች። እንዲሁም “ፏ ብዙነን” የተባለውን የሴቶች ሰዓሊያን ማህበር አቋቁማለች። በሕንድ ት/ቤትም (Indian National School) የሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ መምህርት ሆና ለረጅም ዓመታት አስተምራለች።
ስናፍቅሽ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ለሠላሳ አመታት ያህል ስታቀርብ የቆየች ባለሙያ ናት። በማህበራዊ ጉዳይ ባተኮሩ ስራዎቿም ስትታወቅ በተለይም የሴቶችን ትግል የሚያሳዩ በርካታ ሥዕሎችን ለእይታ አቅርባለች። በራሷም አገላለጽ “…ሴት ልጅ የቤተሰብ ኃላፊ ከሆነች እንደ እናትም ብዙ ኃላፊነት አለባት። ልጅ ሲወለድ ብሩሽና ሸራ መቀመጥ የለበትም” ትላለች።
በአሁኑ ዐውደ ርዕይ ግን ስናፍቅሽ በከፊል አዲስ አትኩሮት የያዘች ይመስላል። እራሷ እንደነገረችኝም፣ ካለፈው አመት ጀምሮ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተለየ መልክ እየያዘ ሄዷል። “በጨለማ ውስጥ ብርሃንን፣ በመኖር ውስጥ አለመኖርን፣ በማጣት ውስጥ ማግኘትን … አብረው ተቆላልፈው ማየት ጀምርያለሁ” ትላለች።
እናም የሕይወት “ዙር ጥምጥም” (ሙሉ ክብነት) በብዛት እየታያት መምጣት እንደጀመረ ትናገራለች። ይህንንም ፍልስፍናዋን በሥዕሎቿ ላይ ለማሳየት እንደሞከረች ይታያል።
በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡት ወደ 40 ከሚጠጉ ሥዕሎቿ ውስጥ ግማሾቹ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ ግማሾቹ ደግሞ “ምናባዊ” (Abstract) ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በአዲሱ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተቀረጹት ደንገዝና ጨለም ብለው “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) የሆኑት ሥዕሎቿ ቀልቤን ስበውታል።
መቼም የሥዕል ፎቶ ቅጂዎች የዋናውን ሥዕል ግርማ ሞገስ እንደማይገልጹ የታወቀ ነው። የዚህም ዐውደ ርዕይ በብዛት የተሰራበት አክሪሊክ (Acrylic) ቀለም ደግሞ በተፈጥሮው በፎቶ ሲታይ ልጥፍ (Flat) የመሆን ባሕርይ አለው። በዚህ ምክንያት የሥዕሉን መልክ በትክክል ማሳየት የሚችል ምስል ማንሳት አስቸጋሪ ነው። እናም፣ ሁሌም ቢሆን ሥዕሎችን ራሳቸውን በአካል ሄዶ ማየት አጥብቆ ይመከራል።
እስቲ፣ ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹን “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) ሥዕሎቿን እንያቸው።
ይህ ሥዕል ጨለም ያለ ድባብ (Background) ላይ የተመሰረተ ሲሆን በቀጥታ መስመሮችና ክቦች ተገንብቶ የተለያዩ ቀለማትን በመስመር ፈርጆ ያሳያል። የቅርጾቹ ቀላልነት (Simplicity)፣ የክቦቹ አቀማመጥ፣ የመስመሮቹ ጥራት፣ እና የቅርጾቹ አነባበር (Depth) ደስ የሚል የመውደቅን ወይም የማሽቅልቆልን ስሜት ይሰጣል። ሠዓሊዋ አስቸጋሪ የሆነውን ጥቁር ቀለም ስትጠቀም ገጽታው ልጥፍ እንዳይሆንና ንብብር እንዲኖረው በተለያዩ ቀለማት መደገፏ ይታያል። ከሥዕሉ በታች በኩል የሚታየውን ጭስ ጠገብ ሰማያዊ ምሕዋሩን (Space) ያስተውሏል። ይህ ተንጠልጣይ ቦታ የመንሳፈፍን፣ የመምጠቅን ስሜት አሳድሮብኛል … ብቻ የሥዕል እይታ እንደተመልካች ይለያያልና ለእናንተ የተለየ ስሜት ይፈጥርባችሁ ይሆናል።
“መስመሮችና ቅርጾች በምሽት”
Acrylic on Canvas
100 x 75 cm
ይህኛውም ከላይ እንዳየነው በጥቁር ድባብ የተመሰረተ፣ ብዙ የተለያየ መጠን ያላቸውን ክቦች ያዋቀረ ነው። የተለያዩት ቀለሞች ግን እንደፊተኛው በመስመሮች የታገዱ ሳይሆን በነጻነት የሚፈሱ ናቸው። ሥዕሉም በውስጡ ውስብስብ ድርብርብነት (Layering) ይታይበታል። እነዚህ ድርብርብ ቀለማት ከክቦቹ ጋር ተዋህደው የሥዕሉን ሙሉነት ይገልጻሉ። እያንዳንዱ ክብ ሆነም ወፍ የራሱ የሆነ ገጽታ (Expression) በፊቱ ላይ ይታያል። ለምሳሌ፣ በመሀል ያለውን ትልቁን ክብ/ወፍ ብንመለከት፣ የወፉ አይን ውስጥ የሚታየው እይታ ምሰጣ ውስጥ መግባትን የሚገልጽ ይመስላል።
“በራሪ ወፎች”
Acrylic on Canvas
95 x 50 cm
ይህኛው ደግሞ በአፈርማ (መሬታዊ) ቀለማት ተገንብቶ አንድ ክብን በማማከል ወደ ውጭ የሚፈሱ (Radiating) መስመሮችን የያዘ ነው። የመስመሮቹ ጥራት አሁንም የሚደነቅ ነው። እዚህ ላይ ስናፍቅሽ የተጠቀመችው ስልት ቀለማቱን ከመደራረብ ይልቅ እያንዳንዱን “መስኮት” የተለያየ ቀለም ወይም “ጥለት” (Pattern) መስጠት ነው። ህብረ ቀለሙ በመስመሮቹ ቢታሰርም ከመስመሮቹ መፍሰስ ጋር በጋራ ሲታይ የተሟላ ሥዕል እንዲሆን አድርጎታል። የሥዕሉ አሰዳደር (Composition) እንዲሁም የመስመሮቿ አካሄድ ሌጣ ቢመስልም ምሕዋሩን በሚገባ ተጠቅማበታለች።
.
“ክብና መስኮቶች”
Acrylic on Canvas
95 x 71 cm
ይህ ሥዕል ከአሁኑ “ዙር ጥምጥም” የአሰራር ስልቷ ወጣ ብሎ የ“ሴትነት” እይታ የያዘ ይመስላል። ሥዕሉ የጠንካራ ሴትን ገጽታ የሚገልጽ ይመስላል። ሴቲቷ “ኮስታራነት” ተላብሳ ዓለሟን አሸንፋ በራሷ መንገድ መሄድን የመረጠች መስላ ትታያለች። አሁንም የሥዕሉ መስመሮች እንደተለመደው ግልጽ ናቸው። ይህችንም ሴት ለመሳል የተጠቀመችው እኒህኑ ጠንካራ መስመሮቿን ነው። ባጠቃላይ የሴትየዋን ፊት “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) በማድረግ ጠንካራ የፊት ገጽታ ለመፍጠር ችላለች። በሴቲቷ ፊት ላይ የሚታዩትን ቀጫጭን መስመሮች ያስተውሏል። በእሳታማ ቀለማት አጠቃቀሟም ተጨማሪ ሙቀት ለሥዕሉ ሰጥታዋለች።
.
.
“Concentration”
Acrylic on Canvas
92 x 62 cm
ይህኛውም የፊት ገጽን በቅርጽ እያሳየ በመሬታማ ቀለማት የተሰራ ነው። ጥሩ የብርሃንና ጥላ አጠቃቀም ይታይበታል። የእናትነት ገጽታ በሚገባ በመቀረፁ ደግነትንና እንክብካቤን በአንገቷና በአይኖቿ እናያለን። አሁንም የስናፍቅሽ አቀራረብ በተለየ ሁኔታ “ቅርጻዊ” ነው። በመስመሮችና በቅርጾች የምትፈልገውን ሁሉ በሥዕሎቿ ማስተላለፍን የተካነችበት ይመስላል።
.
.
.
“እናትና ልጅ”
Acrylic on Canvas
72 x 63 cm
የስናፍቅሽ የአሳሳል ጥንካሬ በ“ቅርጻዊ” ስልት ሸራዋን ማድመቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። መስመሮቿን በሚገባ ትስላለች። ቀለሞቿን ደግሞ አነባብራ ትጠቀማለች። ሰፋ ያለ ምሕዋር (Space) መፍጠርንም የግሏ አድርጋዋለች።
ዛሬም ቢሆን ስናፍቅሽ የምትሰራው በዚህ “ምናባዊ” (Abstract) ስልት ብቻ አይደለም። ዐውደ ርዕዩ ላይ በመጠኑ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ አንዳንዴም “ገጽታዊ” (Expressionist) የሆኑ ሥዕሎችም ለእይታ ቀርበዋል። እነዚህ ሥዕሎቿ ግን ከተለመደው የአሳሳል ስልት እምብዛም ወጣ ያላሉ በብዛትም “ጌጣዊ” (Decorative) የሚመስሉ ናቸው። የሰዎቹ ፊትና ገጽታ ተመሳሳይና ስሜት አልባ ይመስላሉ። የሥዕሎቿን ጥንካሬ እምብዛም አናይባቸውም።
እስቲ ከእነዚህ ሥዕሎች ለምሳሌ አንድ እንይ፦
“ወደ ገበያ”
Acrylic on Canvas
92 x 62 cm
.
በአዲስ መልክ እየተጠቀመችው ያለው “ቅርጻዊ” የሆነው “ዙር ጥምጥም” ስልቷ ግን ቀልብ ይስባል። በዚህ ስልት ክቦቿ እውነትም መስመር የያዙላት ይመስላሉ፤ የምትስላቸው ገጻዊ ሥዕሎችም እጅግ ገላጭ ናቸው።
ስናፍቅሽን ለምን ይህን አዲስ አቅጣጫ እንደቀየሰችም ጠይቄአት ነበር። “ምናልባትም በሰል ማለት ይሆናል … ለምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም … አሁን ግን የሚሰማኝ እንደሱ ነው” አለችኝ።
እግረ መንገዴን ስለ ጥቁር ቀለም አጠቃቀሟ ጠይቄአት ስትናገር፣ “ትምህርት ቤት እያለን ጥቁር ቀለምን እንድንጠቀም አያበረታቱንም ነበር። አንደኛ፣ ‘ያቆሽሻል’ ይሉናል፤ ሁለተኛ፣ የተለያዩ ቀለሞችን በመደበላለቅ የሚመጣ ስለሆነ እምብዛም በቀጥታ አንጠቀምበትም። አሁን ግን ለመድፈር ወስኜ እየሰራሁበት ነው። የተለያየ የጨለማ ደረጃም ላመጣበት ችያለሁ” ትላለች።
በመጨረሻም፣ ከስናፍቅሽ ጋር በሥዕል አርእስት አወጣጥ ዙርያ ተወያይተን ነበር። እኔም፣ “መጀመሪያ አርእስት አስበሽ ነው ሥዕሉን የምትሰሪው? ወይስ ከሰራሽው በኋላ ነው የምትሰጭው?” ብዬ ጠየኳት። እሷም በተራዋ፣ “እንደሁኔታው … አንዳንዴ መጀመሪያ፣ አንዳንዴ መሃል አንዳንዴም መጨረሻ ነው” አለችኝ።
የጥበብ ሰዎች በሥራቸው ፍልስፍና ላይ ብዙ ሲንገላቱ አያለሁ። የትኛው ይሆን የሚቀድመው … ጥበብን መፍጠር? ወይስ ለመፍጠር ፍልስፍናን ማጠንከር? … አንድ የጥበብ ሥራ መልዕክት ሊኖረው የግድ ነውን? … ጥበብ ያለ ፍልስፍና ወይም መልዕክት ሌጣውን በራሱ ብቻ መደነቅስ ይችላል? … አንዳንድ ጊዜ “ሥዕሎች ምነው አርእስት ባይኖራቸው?” ያስብለኛል።
ስናፍቅሽ ብዙ የጥበብ ውይይቶችን እንደምታዘጋጅ፣ የህዝቡንም የሥዕል ንቃተ ኅሊና ከፍ ለማድረግ (እንደ መምህርነቷ) ሃላፊነት እንደሚሰማት ትናገራለች። ስለዚህም በዐውደ ርዕዮቿ ላይ በመገኘት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ተመልካች ያልገባውን ለማስረዳት እንደምትሞክር ገልጻልኛለች። የጥበብ ሰዎች የሥዕል ድግሳቸውን ስለሚቋደሱ ተመልካቾች ምን ያህል መጨነቅ እንዳለባቸው ያሳስበኛል።
ወደፊት ሥራዋ ወዴት እንደሚመራት ለማየት ጓጉቻለሁ።
.
ተጨማሪ
ቃለመጠይቅ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ‹‹ሥዕልን ያን ያህል የተገነዘበ ማኅበረሰብ አለን ለማለት ያስቸግራል››
የኤግዚቢሽን ዘገባ ከሪፖርተር ጋዜጣ በ‹‹በራሪ ወፎች›› ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ
“በራሪ ወፎች Catalogue” የካቲት 2009
እጅግ በጣም ውብ ሥራዎች ናቸው። እናመሰግናለን!!!
LikeLike
endemen senabetachu enai betame dehina neghi
ye berare wefoch exhibition enanteneme des selasegachuna endetestfulet seladeregachui betame des belogali/i am v.happy/
1- beakababew yale sew bekelalu lemelketew yechilal gen bebota reket yeal degmo mayet eyefelege sayayew yekerebetal selzhi enante kelal ye hone menged sertacholi.
2-sela artistu genizabe endenor yadergal tiru mastewawekeya menged new .
3-ye artistu document /merega/ sever new .
4-selene serawoch yetebalut /yetesafut /menem yemelew neger yelgeme mekenyatum hulm endetesemaw /endeteredaw/selehone yemelew
betechemari yebelete endesera eyaderegachugi new .
lela geza degmo enaweralen
betame amesegenalhu
bertu
i appreciate u
with regrades
senafkish zeleke
artist
LikeLiked by 1 person
ARTIST SENAFKISH IS A PROMINENT PAINTER IN AFRICA AS WELL AS THE WORLD. FIND HER TO GIVE HER RECOGNITION AND SHE WILL HAVE A BETER CHANCE TO SHOW HER ART TROUGHOUT THE WORLD. I WISH FOR HER TO BE A FAMOUS ARTIST. KEEP IT UP
LikeLike
Senafkish is one of my all time favourite artists. Thank you so much for featuring her art works! I feel that she is one of the most underrated and yet highly talented professionals in our country. She has consistently created high quality art works representing the lives of ordinary Ethiopians with all the glories and the struggles included. Now also so pleased to see her latest abstract collections. How beautiful it is to be able to tell so much stories with circles scattered across the canvas – beautiful!!! I hope her works get the opportunity to reach a larger audience in the US and across the globe.
LikeLike
I can not see the paintings in person as I live in a distance but here I loved them all. Senafkish is a great artist but under rated. Great works but unknown by most Ethiopians. Let her works speak about her gifted hands and pure vision.
LikeLike