ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ

“ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ”

በሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ማንኛውንም መጽሐፍ ገዝቼም ሆነ ተውሼ ከማንበቤ በፊት ማን እንደጻፈው፣ በኋላው አጎበር ምን እንደተጻፈ፣ መግቢያ ወይም መቅድም ካለው እዚያ ውስጥ ምን እንደተባለ፣ ማውጫ ካለውም በዚያ የሠፈረውን ገረፍ ገረፍ አድርጌ እመለከታለሁ።

ይህንን የማደርገው መጽሐፉን ከአጎበር እስከ አጎበር ማንበብ ከመጀመሬ በፊት “መነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው ወይንስ አይደለም?” የሚል ግምት ለመውሰድ ያህል ነው። አብዛኛውን ጊዜም ግምት ወስጄ በማነባቸው መጻሕፍት ከሞላ ጐደል እደሰታለሁ፤ የአእምሮ ብርሃን የሚሰጡ፣ ስለ ሕይወት ብዙ ነገር የሚያስተምሩ፣ የሚያዝናኑና የሚያስደስቱ ናቸው።

ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹን ብጠቅስ እወዳለሁ።

የሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” (1958)፣ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” (1962)፣ የአፈወርቅ ገብረየሱስ “ልብወለድ ታሪክ [ጦቢያ]” (1900) እና “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ” (1901)፣ የገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” (1916)፣ የአሰፋ ገብረማርያም “እንደወጣች ቀረች” (1946) … እና ሌሎችም።

ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የአገራችን ደራስያን የማውቃቸው በጽሑፎቻቸው አማካኝነት እንጂ በግንባር አይደለም። በግንባር ላያቸው ፍላጎት ቢኖረኝ ኖሮ እንኳ ባልተቻለኝም ነበር፤ እነሱ የኖሩበትና እኔ የምኖርበት ዘመን በጣም የተራራቁ በመሆናቸው።

ዳኛቸው ወርቁ ግን የዕድሜ አቻዬ በመሆኑና ሁለታችንም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመሆናችን እሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ብዙ ጊዜ የመገናኘትና የመጨዋወት ዕድል አጋጥሞናል።

የማልረሳው የመጀመሪያው ግንኙነታችንን ነበር።

ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ቀን፣ የቀድሞው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባልደረባዬና ወዳጄ የሆነውን ሰው ለመጠየቅ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እሄዳለሁ። ያ ወዳጄ በዚያን ሰዓት ከዳኛቸው ወርቁ ጋር ነበር፤ በቢሮው ውስጥ።

“እገሌ”፣ “እገሌ” ብሎ አስተዋወቀንና የ“አደፍርስ” ደራሲ መሆኑን ገለጸልኝ። “አደፍርስ” ስለሚባል መጽሐፍ ከዚያን ቀን በፊት ሰምቼ አላውቅም። ከታተመ አንድ አመት እንኳ የሞላው አይመስለኝም።

“በዚህ ርዕስ የሚታወቅ መጽሐፍ ካለ ምነው መጽሐፍ መሸጫ መደብር ውስጥ አይቼው አላውቅም?” ስል ጠየቅሁት ዳኛቸውን።

“ቀደም ብሎ እንኳ ከመጽሐፍ መሸጫ መደብር ይገኝ ነበር፤ አሁን ግን እኔ ዘንድ እንጂ ሌላ ቦታ አታገኘውም” አለኝ።

ሦስታችንም የመጻሕፍት አፍቃሪያን ስለነበርን ስለሥነጽሑፍና በጊዜው ታትመው ይወጡ ስለነበሩት መጻሕፍት ስንጨዋወት ቆየንና በመጨረሻም ዳኛቸውና እኔ ወዳጃችንን ተሰናብተን ወጣን።

“መጽሐፍህን ልገዛው እፈልግ ነበር። ነገር ግን እንዴት ነው የማገኘው?” አልኩት።

“ማግኘት እንኳ ታገኘዋለህ። ነገር ግን ዋጋው እንደቀድሞው አይደለም” አለኝ።

“ስንት ነው?” አልኩት።

“መጀመሪያ በአምስት ብር ነበር የሚሸጠው። ነገር ግን አልሄድ ስላለ አስር ብር አደረግሁት። አሁንም እንደገና አልሄድ አለ። ስለዚህ መሸጫ ዋጋውን አስራ አምስት ብር አድርጌዋለሁ” አለኝ።

ይህንን ስሰማ ሳቅ ወጥሮ ያዘኝ። ነገር ግን ከዚያ በፊት የማልተዋወቀውን ዳኛቸውን እንዳላስቀይመው በመፍራት ሳቄን ታግዬ አስቀረሁትና፣

“ለማንኛውም አንድ ኮፒ እፈልጋለሁ” አልኩት።

“እንግዲያውስ ተከተለኝ” ብሎኝ መኪናው ውስጥ ገባ። እኔም በያዝኩት መኪና ተከተልኩት።

በፒያሳ አድርገን አራት ኪሎ ስንደርስ ወደታች ተጠምዘን ወደ ምኒልክ ግቢ አቅጣጫ አመራን። እዚያ ሳንደርስ ከፓርላማ ወደ እሪ በከንቱ የሚያመራውን መንገድ አቋርጠን ትንሽ ከሄድን በኋላ ወደ ቀኝ ታጥፈን በጠባብ ኮረኮንች መንገድ ተጓዝን። ከዚያም በኋላ ከመኪናችን ወርደን በእግራችን ወደ መኖርያ ቤቱ አመራን።

ከጽሕፈት ቤቱ ስንገባ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ በብዙ ረድፍ የተደረደሩ የመጻሕፍት ክምር ይታያል። ሄድ ብሎ ከአንዱ እሽግ አንድ ኮፒ መዞ አወጣና “ይኸውልህ” አለኝ። ተቀብዬው፣ ሂሳቡንም ከፍዬ ተሰናብቼው ወጣሁ።

ዳኛቸው ወርቁ ልዩ ባህሪ ያለው ሰው መሆኑን ያን ቀን ነው የተረዳሁት።

ከዚያም በኋላ ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል፤ ተቀራርበናልም። እኔ እንደማውቀው በጣም ሰዓት አክባሪ ሰው ነበር። አንድ ቀን እቢሮው ተቃጠርንና ከዚያ ስሄድ እሱ ከቢሮው ወጥቶ ወደ መኪናው ሲያመራ አየሁና፤

“ዳኛቸው! ዳኛቸው!” ብዬ ተጣራሁና፤ “ምነው? እረሳህ እንዴ? ቀጠሮ ነበረንኮ!” አልኩት።

“ቀጠሮውንማ አፍርሰህብኝ ወደ ሌላ ጉዳዬ መሄዴ ነበር” አለኝ፤ መለስ ብሎ።

እጅግ በጣም ተገርሜ ሰዓቴን ብመለከት ያሳለፍኩት ጊዜ ሦስት ደቂቃ ብቻ ነበር!

በሌላ ቀንም ኩራዝ መጻሕፍት መደብር እንድንገናኝ ተቃጠርን። በቀነ ቀጠሮው ከዚያ ብሄድ ዳኛቸው የለም። አስራ አምስት ደቂቃ ያህል ጠበቅሁትና አለመምጣቱን ሳይ አንዳች እክል ቢያጋጥመው ነው እንጂ አይቀርም ነበር አልኩና ወደ ሌላ ጉዳዬ ሄድኩ።

ከዚያ በኋላ በሌላ ቀን በአጋጣሚ ስንገናኝ በቀጠሮአችን ቀን ለምን ሳይመጣ እንደቀረ ጠየቅሁት።

“እኔማ ከተቃጠርንበት መጻሕፍት መሸጫ መደብር ሄጄ ነበር። እንዲያውም ሰዓት አሳልፋለሁ ብዬ ስከንፍ መኪናዬን ገጨኋት። አንተ ግን በቀጠሮው ቦታ አልነበርክም” አለኝ።

“ኧረ እኔስ ከዚያ ነበርኩ! አንተ ነህ ቀጠሮ ያፈረስከው” አልኩት።

“ወደ የትኛው መደብር ነበር የሄድከው?”

“ኤንሪኮ ባር ፊት ለፊት ያለው … ቸርችል ጐዳና”

“አዬ! ለካስ ያልተግባባነው ከቦታው ኖሯል! እኔ ደሞ የሄድኩት አምስት ኪሎ ካለው መደብር ነው” አለኝና ሁለታችንም በሠራነው ስሕተት ተሳስቀን ተለያየን።

ዳኛቸውን ከሌሎች ሰዎች ለየት የሚያደርገው ሰዓት አክባሪነቱ ብቻ አልነበረም። እኔ እንደማውቀው እውነተኛ ሰው ሆኖ ተጠራጣሪም ነበር – “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” እንደሚባለው አይነት!

የሆነ ሆኖ ወደ መጻሕፍት እናምራ።

“አደፍርስ” በርካታ ምሁራንን በሰፊው ያነታረከ መጽሐፍ ስለሆነ እኔም ተጨማሪ ንትርክ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለሁም። ስለምንነቱ ጥቂት ሳልል ግን ለማለፍ አይቻለኝም።

“አደፍርስ” በሌሎች ልብ ወለዶች የምናየው ዓይነት አንድ ወጥ የሆነና የጐለበተ ፈጠራ ታሪክ የለውም። በዚህ ፈንታ ቁርጥራጭ ትርኢቶች ነው የሚታዩበት።

ትረካውን ይፋትንና ጥሙጋን ከጣርማ በር ተራራ ላይ ሆነው ሲመለከቱት ምን እንደሚመስል የሙዚቃ ቃና ባለው ቋንቋ ይጀምራል፤

“ቁንዲ አንገቷን አስግጋ ቃፊርነት የቆመች መስላለች። የዓዋዲና የጀውሃ ጅረቶች ደረታቸውን ለፀሐይ ሰጥተው ይምቦገቦጋሉ። ሰማይና ምድር የተገናኘበት፣ ሕይወት ያሸለበችበት የሚመስለውን በስተግርጌ የሚታይ ሜዳ አቧራ ረግቶበታል … የይፋትና ጥሙጋ አውራጃን ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከቱት እግዚአብሔር ዓለምን ሠርቶ ሲያበቃ የተረፈውን ትርክምክም ያጐረበት እቃ ቤቱ ይመስላል – ሸለቆው፣ ጉባው፣ ተራራው፣ ገመገሙ፣ ጭጋጉ፣ አቧራው ሕይወትን አፍኗት ተኝታለች – ያቺ በሌላው አገር የምትጣደፈው፣ የምትፍለቀለቀው፣ የምትምቦለቦለው ሕይወት እዚህ እፎይ ብላለች – በርጋታ፣ በዝግታ ታምማለች፤ በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ …” (ገጽ ፭)

ገጠሩን በተዋበ ቋንቋ ከገለጸልን በኋላ ወ/ሮ አሰጋሽ የተባሉ የገጠር እመቤት ከጢሰኛቸው ጋር ቲያትር መሰል የንግግር ልውውጥ ሲያደርጉ ያሳየናል። ጢሰኛው የዘንጋዳ ዘር አጥቶ ሊበደር ወደ እመቤቱ ዘንድ መጥቶ ይለምናል። ወ/ሮ አሰጋሽ በተባ አንደበት የጢሰኛቸውን ሞራል አንኮታኩተው ከሰበሩት በኋላ ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ ሰጥተውት በመኸር ወራት አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይነግሩታል።

የ”አደፍርስ” ጀርባ ሥዕል (በታዬ ወልደ መድኅን)

አራጣው በጣም የበዛ መሆኑ በተሰበረ ድምፅ ይገልጽላቸውና እንዲራሩለት ይማጸናቸዋል። ወ/ሮ አሰጋሽ ግን በአራጣው ከተስማማ ዘጠኙን ቁና እንዲወስድ፣ አራጣው በዛ ካለም እንዲተወው ርህራሄ በሌለው አንደበት ቁርጥ አድርገው ይነግሩታል።

ሌላ ምርጫ ስለሌለው እመቤቱ ለሚሰጡት ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይስማማል። ወ/ሮ አሰጋሽም ይህንን ገፈፋ ውለታ እንደዋሉለት በመቁጠር በመሬታቸው ላይ የበቀለውን የድርቆሽ ሳር (ሰማንያ ሸክም ይሆናል) አጭዶ፣ ተሸክሞ አምጥቶ ከደጃቸው እንዲከምረው ይነግሩታል። እሱም ትእዛዛቸውን ለመፈጸም የቃል ውል ከገባ በኋላ ዘንጋዳው ተሰፍሮለት አህያውን እየነዳ ከግቢያቸው ይወጣል።

በዚህ ክፍል ያለው ድንቅ ትርኢት በመድረክ ላይ የሚታይ ትርኢት እንጂ ሌላም አይመስል።

ታሪኩ በዚሁ ይቀጥላል ብለን ስንጠባበቅ ሳለን የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ ይከፈትና ሌሎች ባህርዮች ሲጨዋወቱ እናያለን።

ምሽት ይሆንና “የፌንጣ ሲርሲርታ፣ የዝንብ ዝዝታ፣ የንቦች እምምታ” እንሰማለን። ጨረቃ ትወጣለች። የወ/ሮ አሰጋሽ አገልጋይ የሆነውን የወርዶፋ ዋሽንት ሙዚቃ እናዳምጣለን።

በዚህ መልክ የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ እንደገና እየተከፈተ እስከ መጨረሻው ድረስ የተለያየ ትርኢት እናያለን።

ከዚህ ቀደም እንዳልኩት መጽሐፉ ከልብ ወለድነት ይልቅ ወደ ድራማነት የተጠጋ ነው … አንዳንዴ አስቸጋሪ ቢሆንም በውብ ቋንቋ የተደረሰ ድራማ።

የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ዐቢይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት እንግሊዝ አገር የታተመውና “The Thirteenth Sun” የተሰኘው መጽሐፍ በብዙ የአውሮጳውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንደታተመም ዳኛቸው ራሱ አጫውቶኛል።

መሠረተ ሀሳቡ ከ“አደፍርስ” ጭብጥ እጅግም የራቀ አይደለም።

በጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተሳሰብና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ (በቀድሞው ትውልድ እምነትና በዛሬው ትውልድ አመለካከት) መሀከል ባለው ግጭት ላይ የተገነባ ልብወለድ ነው። በእኔ አስተያየት በትረካው ረገድ “The Thirteenth Sun” ከ“አደፍርስ” ላቅ ያለ ሲሆን በቋንቋው ውበት ግን አደፍርስ ይበልጣል።

ከዳኛቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበትን ቀን ምንጊዜም አልረሳውም ብዬ ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ አስከሬኑን የሸኘኹበትንም ቀን አልረሳውም።

ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ምሽት ላይ ሁለት ደራሲያን ወዳጆቼ በተለያየ ሰዓት ስልክ ደውለው ዳኛቸው ወርቁ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱንና በማግስቱ ማለዳ ከ11 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ አስከሬኑ ወደ ትውልድ አገሩ፣ ደብረሲና እንደሚሸኝ ገለጹልኝ።

ከሌሊቱ በ11 ሰዓት ተነስቼ ምኒልክ ግቢ አጠገብ ወደሚገኘው ቤቱ አመራሁ።

እዚያ ስደርስ አምስት የሚሆኑ የግል አውቶሞቢሎችና ከሠላሳ የማይበልጡ በጣም ጥቂት ሰዎች (አብዛኞቹ የሠፈር ሴቶች መሰሉኝ) በአካባቢው ቆመው አየሁ። ሌሎች አስር የሚሆኑ ሰዎች ደሞ ከዚያው አጠገብ ከቆመው መለስተኛ አውቶቡስ ውስጥ ገብተው ተቀምጠዋል።

የአስከሬኑ ሳጥን በአውቶቡሱ ጣርያ ላይ በሸራ ተሸፍኖ ታስሯል። በአካባቢው አንድ ሰው ብቻ ሲነፋረቅና እንባውን ሲጠርግ ተመለከትሁ። ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ ብመለከት አንድም የማውቀው ሰው የለም። ትናንትና ደውለው ያረዱኝ ወዳጆቼም በዚያ የሉም።

እጅግ በጣም ተገረምኩ፤ አዘንኩም።

“አደፍርስ” እና “The Thirteenth Sun” የሚያህሉ ድርሰቶችን ያቀረበልን የብዕር ሰው አስከሬኑ የሚሸኘው በዚህ ሁኔታ ነው ወይ? ወይንስ ዳኛቸው ወርቁ ራሱን አግልሎ ስለሚኖር ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹና ደራስያኑ ጭምር ዜና ዕረፍቱን በጊዜ ሳይሰሙ ቀሩ? ስል አሰብኩ።

የሆነ ሆኖ ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ ሲሆን አስከሬኑን የጫነው መለስተኛ አውቶቡስ ወደ ደብረሲና ለመጓዝ መንቀሳቀስ ሲጀምር በሀሳቤ፣

“ነፍስህን ይማረው። የዘላለም እረፍት አግኝ” ብዬ ተሰናብቼው ወደ ቤቴ አቅጣጫ አመራሁ።

ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

(1988 ዓ.ም)

በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – “ሹክታ” (፲፱፻፺፪)፤ ገጽ 6-20።

.

.

 

5 thoughts on “ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ

  1. የዳኛቸው ወርቁን ሥራዎች ፈልጌ እንዳነባቸው የሚያስገድድ አይነት አቀራረብ ነውና ምስጋናችንን ቃላት አይገልፀውም።

    Like

  2. ኢትዮጵያውያን እስከመቼ ነቢዮቻቸውን ችላ ይላሉ? ደግም አይደል! ጀግኖቻችንን እናክብር!!!

    የነቢይ ሕልውና
    ትላንት ነቢይ በአገሩ አይከበርም።
    ዛሬ ነቢይ በአገሩ አይፈጠርም።
    ነገ ነቢይ በአገሩ አይኖርም።
    (በዕውቀቱ ሥዩም)

    Like

  3. አይ ሃገሬ የሚገርም ነው በስንቱ ነገር ተጠብሰናል ጎበዝ፣ ዳኛቸው ወርቁን ሚያህል የጥበብ ሰው የሚያዝንለት ሰው ሲያጣ በዕረፍቱ እጅግ ያሳዝናል፣ ዳኛቸው ክህሎት እጅግ ልቅ ማለቱን የምናየው በመጻፍ ችሎታው ብቻ አይመስልኝም ጥሩ የኔታም ነበር ዕውቀቱን ጥበብን በቋንቋችን አንጀት በሚያርስ ገለፃ ሚያስተምር፣ አደፍርስን እንደ ልዩ ቅርስ የማየው መጻፌ ነው አሁንም ሳነበው ያረካኛል፣ በጥበብ ስራ ቀንብቦ የሰራው ነው፣ ለማመሳከር የጽሑፍ ጥበብ መመሪያን መረዳት ይበቃል፣ ማንም መፃፍ የሚፈልግ፣ ሰው መመሪያውን ካነበበ፣ ከተረዳ በደንብ መጻፍ ይችላል። ላንድምታ ታዳሚ እመሰክራለሁ። አደፍርስን ካርባ ዓመት በኋላ እንኳ መረዳት ሲያቅት ሥነ ፅሑፋችን እንዴት የኋሊት እንደ ሄደ መረዳት አይከብድም። ጀግናውን ግን ሁሌ ሳስበው ያኮራኛል፣ ነፍሱን ይማር።

    Like

  4. አደፍርስ የምንግዜም ምርጥ መፅሀፌ ነው።የቁዋንቁዋ አጠቃቀሙ ገለፃው እንዲሁም ይዘቱ የተለየ ቦታ ያሰጠዋል ብየ አምናለሁ። ክብር ለዳኛቸው!!!

    Like

Leave a Reply to ምንሊክ ኅ/ማ Cancel reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s