“አስኮ ጌታሁን” (ልብወለድ)

አስኮ ጌታሁን

ከጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል

.

[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]

.

የሚገርመው ነገር፣ አስኮ ጌታሁንን አንዴ አይቶ መልኩን ለሰሞናት ከዓይነ ህሊና ማጥፋት አለመቻሉ። የሚያስደነግጥ፣ የሚሰቀጥጥና ለአንዳንዱም የሚያሳዝን ገጽ ያለው ሰው ነው። ይሄን ፊቱን ከተመለከቱት፣ አእምሮ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ፊትም ላይ ተቀርጾ ይቀራል። በአንዳች አጋጣሚ ተመልክተውት ሲያበቁ ፊታቸውን በፍራቻ የሚደባብሱ ጥቂት አይደሉም። በግድ መጥቶ ፊት ላይ የሚተሻሽና ቅሪተ አካሉን የሚተው ገጽ ነው። የአስኮ ጌታሁን ፊት የሸበተ አሮጌ ጉቶ ላይ የሰው መልክ የተቀረጸበት ይመስላል። አንድ ዓይኑ ለብቻዋ ሙታለች። ብርሃን አልተሳናትም፤ ግን ሞታለች። ብይ ትመስላለች፤ ጠጠር ትመስላለች። ዓይነስቡ በበለዘ ጥቁር ሰማያዊ ሲከበብ፣ ሽፋሽፍቱን ባንቀሳቀሰ ቁጥር የምትላወስ እንሽላሊት የመሰለች ጠባሳ ከግንባሩ ወደዓይነ ቆቡ ተጋድማለች። የፊቱን መጨማደድ ከላይ የተጠቀሰው አሮጌ ጉቶ በበቂ ሁኔታ ይገልጸዋል። ፀጉሩ እንደሙጃ ቀጥ ብሎ ከመቆሙ በላይ እውስጡ ተባዮችን ትተን የዳቦ ፍርፋሪ፣ አሸዋ፣ የፀጉሩ ማስያዣና አንዳንዴም አንድ ሳንቲም ይኖሩበታል።

ከአገጩ የሚወርደው ባለአንድ ግምድ ፍየል ጢም፣ እንዲጐተት የተፈጠረ ጥንተ አካሉ እንጂ ከጊዜ በኋላ አቀምቅሞ ቸፍርጐ የተገመደ ፀጉር አይመስልም። ቁመናው ረዥም ነው። ከወገቡ በላይ ያለው አካል አለመመጣጠኑን ቢያሳይም፣ የፊቱ እንደአንዳች መርዘም ሸፍኖታል።

“ጫማ ሰፊ ሆኖ እንዴት ባዶ እግሩን ይሄዳል” በሚለው መታበል ከቶም ከእግሩ የአንድ እግር ጫማ አይጠፋም። ይሄ ማለት የቀኝ፣ ቀኝ ላይ ይውላል ማለት አይደለም። ግን የግራም ቀኝ ላይ ቢውል፣ አንድ እግር ጫማ ለመኖሩ ያህል አለ ማለት ነው።

አስኮ የሚኖረው ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ነው። ቀደም ብሎም የደብር አለቃው ከአቃቢቶች ጋር ባነሱት አምባጓሮ ተባረረ እንጂ መቃኞው ውስጥ ጥቂት ለማይባል ጊዜ አድሯል። እያደር የአካባቢው ህዝብ ለምዶት፣ የሠፈሩ ህፃናት አሹፈውበት፣ እንደጥጃ በመሸ በየፖሊስ ጣቢያው ታስሮ ካበቃ በኋላ ዛሬ አስኮ ለሠፈሩ ህዝብ የአውራጐዳና ባለስልጣን ጥሎት እንደሄደ የሬንጅ በርሜል ያህል እንኳን ለዓይን አይቆረቁርም። እሱ ግን “አገር ሰለቸኝ” ይላል። አገርም እሱን እንደሰለቸው አያስብም። እንደአበደ ባሕታዊ ድንጋይ ከአናቱ ጭኖ፣ “እግዜር የሰውን ልጅ ሲፈጥር፣ ለጭቃ ማቡኪያ ሰባት ባልዲ ውሃ ያቀበልኩት እኔ ነኝ። ከፈለጋችሁ ሰማይ ቤት ስትገቡ፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጠይቁ። እማኜ ናቸው” ሲል አስተዋይ ነኝ ያለ ጭንቅላቱን ይነቀንቃል። ስላቁ የነካቸው ኮስተር ይላሉ። ህፃናትም እንደተጠመደ አውሬ ይዞሩታል።

ይህ ሰው ህብረተሰብ “ወፈፌ፣ አውቆ አበድ፣ ንክ” እና ሌላም ከሚሏቸው አንዱ ነው። አንዳንዴ ከዛጉት ጥርሶቹ ተስፈትልከው የሚወጡት ቃላት፣ አጥንት ሰብረው ከመዝለቃቸውም አስባለሁ ያለን አዕምሮ ለቀናት ወጥረውት ይቆያሉ። ስለዚህም በሙሉ “እብድ” ሊለው የቻለ ሰው አልነበረም። በዚህም ላይ ደግሞ ምክር እንደገባው ሰው አንድ ሳምንት ሰጥ ለጥ ብሎ በአሮጌ ዣንጥላ በተገጠመች መጠለያው ሥር ጫማ ስፌቱን ይያያዘዋል። ጫማ ለማሰፋት የሚመጡትን ሠፈርተኞች ከነፃ በላይ፣ እሱው እንደሚለው “ለሚስማር መግዣ” ብቻ ነው የሚያስከፍላቸው። እናም “አስኮ ተቀምጧል” ከተባለ ሰልፉ አጭር አይደለም።

ፊታቸውን አዙረው ጫማ የሚሰጡት፣ በሀይለኛ ጉንፋን አሳበው ደፋ፣ ደፋ የሚሉት፣ መልኩን ላለማየት እንደሆነ ያውቃል። “ባለ አሥራ ሁለት ሳንቲም ሚስማር ውጬ ደረቴን ወጥሮታል” ሲል፣ በድንጋጤ ቀና ብለው ቢያዩ ያቺን ሙት ዓይኑን ያበራባቸዋል።

ይህ ሰው “ንብረትና ሀብት አለኝ” ብሎ አስቧል። “ከዋናው ባንክ ቅርንጫፍ”፣ “ከሰላም ምግብ ቤት”፣ “ከኦስማን የህንፃ መሣሪያ አስመጪዎች”፣ “ከአጂፕ ቤንዚን ማደያ” እና ከተቀሩትም አገሩን ያጫነቁ የገቢ ምንጮቹ ሳያዛንፍ አርብ አርብ ከሰዓት በኋላ ደረሰኙን ይዞ ይሄድና በቀጥታ ወደመደገፊያው ሥፍራ በመጠጋት፣ “ጤና ይስጥልኝ ባልደረቦች፤ እስቲ ከገቢ ወጪ እንተሳሰብ። ቅርንጫፍ ፀሐፊውን ንገርልኝ፤ አስኮ ጌታሁን መጥቷል ብለህ” ይላል።

ቀደም ሲል ብዙ ጊዜ ታስሮ ተፈታ። በኋላ ላይ ግን የባንኩ ሠራተኞች የጫት መግዣ ሰጥተውት ደረሰኙን “ፈርመው” ሲሸኙት፣ ባለ ሆቴል ቤቶች ራት አብልተው ይለቁታል። አንዳንዴ ሠራተኞቹን “ንግድ በማበላሸታቸው፣ ትርፍ በማዳከማቸው” እየተቆጣ ሲሄድ፣ አልፎ አልፎም “ሁሴን መሀመድን የአቃቂው ቅርንጫፍ ሹም ያላደረግሁት እንደሆነ ታዘቡኝ። አንጀቴን ያራሰኝ ሠራተኛ ነው” በማለት ለህልሙ ንግድ የህልም ተስፋ አልሞ ይወጣል።

የሆነውን ገሀድ ለራሱ እንደፈለገው ማውራት የሚወደውና የሚችለው ሕዝብም ለአስኮ ልብወለድ ፈጥሮለታል። “የጭነት መኪናዎች የነበሩት እንዴት ያለ ቱጃር ነበር መሰላችሁ” ሲል፤ ሌላው ደግሞ “በማር ንግድ የደለበ ነጋዴ ነበር። ዛሬ ጉድ ሆነ” ይላል። ግን እውነቱን ማግኘት የሚቻለው ከራሱ ከአስኮ ነበር። ታዲያ ምን ይሆናል?! እሱም አያውቀውም። ዛሬን እንደማያስብ፣ ነገን እንደማያልም ሁሉ፣ ትላንትናም ጨርሶ ከአእምሮው ጠፍታለች።

ወታደርን ሲያስቡ አለመለዮ ልብሱ ማየት እንደማይቻል ሁሉ፣ አስኮን አለረዥም ቀይ ካቦርታው ማሰብ አይሞከርም። ልብስ ሲሰፋ “እንደአስኮ ጌታሁን ካፖርት ተንቦረቀቀ” ይባላል። ለሱ ግን የቀን ልብሱ፣ የሌሊት ልባሱ ነች። የዚህ ካፖርት አመጣጥ ታሪክ አለው። አንድ ማለዳ አስኮ የሲጃራ ባኮ ከመሬት ሲለቃቅም፣ የአንዲት ሴት ጫማ ሹል ታኮ አንዱን በስቶ ቢይዝበት፣ “በሕግ አምላክ ንብረቴን ተዘረፍኩኝ!” ሲል ጮኸ። ባል ይሁን ወዳጅ አልለየም ድንገት ሽክ ብሎ የለበሰ ጐበዝ ደረሰ። አስኮን ለመምታት ቢቃጣው፣ መልሶ እጅን የሚሞርድ ፊት እንዳለው አስተውሎ ስንዝሩን መለሰና በሰላሙ መንገድ ጀመረው። አንድ ሁለት ሲባል፣ የአስኮ ጌታሁን ወሬ ሙሉውን የእብድ አለመሆኑን ያዩት ሴትና ወንድ፣ እንደመማረክ ብለው ያደምጡት ጀመር።

“እናንተ ቤት አላችሁ፤ ንብረት አላችሁ። ካልጠፋ አገር እዚህ ድረስ መጥታችሁ፤ ከመሬት የምለቃቅመውን ባኮ እንደምትበሉት ማካሮኒ በመጫሚያችሁ ሹካ የምትወስዱብኝ ለምንድነው? እንዳው ለመሆኑ የሰው ግፍ ገደብ የለውም ጌታ? እንደው ለነገሩ በቃኝን አልፈጠረብንም ማለት ነው?” ወንድየው ተገረመ እንጂ አልራራም። ሴትየዋ ግን እቤት ቅርጫት ውስጥ ያለውን የእናቷን ካቦርታ ‘ነብስ ይማር’ አምጥታ፣ ሀፍረቱን እንዲሸፍንበት ለመስጠት ታሰባትና በማግስቱ ተመልሳ ብትፈልገው አልተገኘም። ባለ መደብሮችን በምልክት ስትጠይቅ በመገረም፣ “እዚሁ ሠፈር ነው የሚውለው። አንድ ቦታ የሚቀመጥ ፍጡር አይደለም። እስቲ ወደጫት ተራ ፈላልጉት” እያሉ ተጠቃቀሱባት። አግኝታ ስትሰጠው፣ “እሜትዬ፣ አርብ ሂሳብ እንደተረከብሁኝ ከነወለዱ እከፍላለሁ” ብሎ ካፖርታውን ለአንዴም ለሁሌም አጠለቀው።

“አንዳንዴ’ኮ ሳስበው” ይላል አሉ፤ “ዓለም ሰፊ አፍ፣ ሰዎች ሁሉ ጥርሶቿ ይመስሉኛል። እና እኔን እያኘኩኝ ነው።” እዚህ መርካቶ ይሄ የሰው አሸን የሚፈላበት፣ የሚያወጣው እጅ አጥቶ እንደሚንተከተክ የተጣደ ነገር ሁሉ የሚንጨረጨርበት የትርምስና ሁካታ ዓለም፤ የመርካቶ ዓለም ውስጥ፤ ይህ ሰው አንዲት ጥግ ይዞ በካፖርታው ተጀቡኖ እንደጅብ የሚያስፈራ ጭንቅላቱን ብቅ አድርጎ ሁሉን ነገር ይቃኝ፣ ይቃኝና ሲያበቃ፣ “ታስፈሩኛላችሁ!!!” ብሎ ይጮኻል። እዚህ የጆሮና የአፍ ደን ውስጥ የሚሰማውም የሚመልስለትም አያገኝም። ተመልሶ ይተክዛል።

ታላቁ የቤተስኪያን ደወል እንደጮኸበት የጸናጽሉ ሻሻታ፣ የቃጭሉ ድምፅ፣ የሰዉ ወሬ ሁሉም በአንዴ ሲወሩት በሁለት መዳፎቹ ጭንቅላቱን ይይዛል። በአጠገቡ የሚያልፍ ለአፍታ መልከት ሲል ህፃናት ይመጡና፣ “አስኮ፣ እንካ ይሄንን ቦንዳ ብላ እስቲ፣ የእነቡጡ ሰፈር ልጆች ብረትና ሚስማር ይበላል ብለው ተወራርደዋል” ይሉታል። አያለቅስም፣ ድምጽ የለውም። እንዲሁ ብቻ ያነባል።

ይህ ሰው በርግጥ ለአካባቢው ከወደቀ ግንድ፣ ወይም ካረጀ ውሻ የበለጠ አይከብድም። የውስጡን የስቃይ ቡጥጫ፣ ናላው ውስጥ የሚንተከተከውን እንዲህ የሕያው ሙት ያደረገውን ነገር የሚያውቅለት የለም። ለነሱ አስኮ ጌታሁን “አውቆ አበድ” ነው ወይም “ሚስኪን” ነው። ወይም ለቤት ህፃናት ማስፈራሪያ የሚያገለግል ምስል ነው። ሰብአዊ ህልውናውን ከአካሉ ለይተው አንዱን ብቻ በመቀበል፣ በአስፈሪ መልኩ ወይም አስደንጋጭ ሁለመናውን ብቻ የሚያውቁትም አሉ።

“አስኮ ሲቀመጥ” አቅመ ደካማዎችና ሳንቲም ማትረፍ የሚፈልጉ ይሰለፋሉ። አጠገቡ ሲደርሱ የሱን ወሬ ለመከላከል እርስ በርሳቸው ማውራታቸው የተለመደ ነው። ሆኖም፣ ጫማ ሰፊው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ አያውቅም። “እንዴት ሁለት የግራ እግር ጫማ ታደርጊያለሽ ልጄ? እግዜር በቅጡ አልፈጠረሽም ልበል?” ሲል፣ ንግግሩ ሳቅን ቢገፋፋም፣ ወሬ ላለማበርከት ሲሉ ጉንጫቸውን በአየር ነፍተው ያጐነብሳሉ። “የእዚህ ጫማ ጌታ ውስጡ አንዲት የታጠፈች ብር ረስቶ አግኝቻለሁና ታውቁት እንደሆነ ንገሩት። የእግር ቁጥር አርባ ሁለት፣ ቀለሙ ጥንት ጥቁር፣ አሁን አመድ” በማለት ጫማውን ለትዕይንት ብድግ ሲያደርግ፣ ጫማውን ብቻ ከፊቱ ለይተው ለማየት ጨረር እንዳስቸገራቸው ያህል በመዳፋቸው ዓይነ ጥላ ያበጃሉ። እሱም ወደ ተግባሩ አቀርቅሮ ጫማውን ከትንሽ ብረት ላይ እያዟዟረ ሲቀጠቅጥ እንጉርጉሮ መሰል ነገር ያሰማል። ዜማውን አውቃለሁ የሚል ሰው እስካሁን ባይገኝም፣ በቃላቱ መሀከል … “የእርኩም ሥጋ አበሉኝ፣ ዕድሜ ታገኝ ብለው” የሚል ሀረግ ይገኝበታል።

ከገጹ መከራና ስቃይ የሚነበበው ይህ ሰው የተጨማተረች ልቡን በሳጠራ ደረቱና በአሮጌው ዲሪቶ ሸፍኖ ሲኖር “እህ?” ብሎ በደሉን የጠየቀው፣ “በጄ” ብሎ በቁም ነገር ያደመጠው አይገኝም። ድምፁን ግን ይሰማሉ።

ጐህ ሲቀድ፣ ከወደቀበት ተነስቶ ረዥሙን ቁመና ያንጠራራና ባለ ድምጹ፣ “ታስፈሩኛላችሁ! ታስፈሩኛላችሁ እኮ ነው የምለው!” ሲል ያጓራል። የጠገበ ነጋዴ ቦርጩን ሲያገላብጥ፣ ሸቃጮች መንጋቱን አውቀው ለዕለት ተግባራቸው ስምሪት ፊታቸውን ሲያሻሹ፣ ቤት የለሾቹ ደግሞ በድምጹ ተረብሸው “ይሄ የሰፈር ጋኔል ይህችኑ እንቅልፋችንን ነሳን’ኮ” እያሉ በየወደቁበት ይገላበጣሉ። አስኮም ሀገር ምድር አልቀበል እንዳለው እርኩስ መንፈስ፣ የመንጠራወዣ ዕለቱን ለመጀመር ሁሉን ነገር በትዝብትና ፍራቻ ይቃኝና ያደረ አክታውን ይተፋል። ለአስኮ ጌታሁን ዛሬና ነገን የሚለየው፣ በመሀከሉ ያለው ምሽትና ሌሊት የተባለ ጨለማ ነው።

አቶ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ፣ የወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ሲከፈት በመምህርነት የመቀጠር ዕድል አግኝተው ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ ፋናቸውን ሲነቅሉ፣ ስንቅ ለማዘጋጀት ጠብ እርግፍ ያሉት ወላጅ እናታቸውን እና ገና “ረ” ማለትን ምላሱ ያልለመደች አንድ ልጃቸውን አስከትለው ነበር። ሥራ ተጀምሮ፣ እንደ ሰዎች ሁሉ ኑሮውን ከተያያዙት በኋላ ከሥራ ባልደረቦቻቸው መግባባትን፣ ከተማሪዎቻቸው አድናቆትንና ክብርን ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባቸውም። እኚህ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው፣ መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው ያወቁ ሰው፣ ባደሩበት በዋሉበት፣ ሰውን በጥንቃቄና በትህትና መያዝን ሕይወት ያስተማራቸው ነበሩ። አንገታቸውን አቀርቅረው ቢሄዱም ልባቸውን ከሰው የመሰወር ባህርይ አልፈጠረባቸውም። በውስጥ ሀሳባቸው የመጠመድ፣ የህይወትን እንቆቅልሽ አግባብ ካላቸው ወዳጆቻቸው መወያየትን እንደዘወትር ተግባራቸው ከያዙት ቆይተዋል። አቶ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ከራሳቸው አፍልቀው፣ ከመጽሐፍ አጣቅሰው የሚያቀርቡት በወግና በዘዴ የቀረበ ትምህርታቸው፣ ልብ ብሎ ያደመጠን ሁሉ እንዳሳሰበው ይኖራል።

የመረረ የገረረ ባህሪዋን፣ ውስብስብ መልኳን “ይሁን” ብሎ የተቀበላትን ሁሉ ባለ አቅሟ የምትቀጣው ህይወትም፣ እኚህን ሰው በየወቅቱ መሸንቆጥና ማጋጨትን ለመጀመር አልዘገየችም። “ልፈላሰፍ ይላል … ሁለገብ ነው፤ አፉ አያርፍም” የመሰሉ አስተያየቶች ከየሰዉ መሰማት ሲጀመር፣ አቶ ጌታሁን ግን በራሳቸው በመተማመንና የልቡና ቅንነታቸውን አጥርተው ስለሚያውቁ ደንግጠው ዝም ያሉ፣ ፈርተው ያልመለሱ ሰው አልነበሩም።

ከሥራ መልስ ደጃፋቸውን ሳይኮተኩቱ፣ ካረቧቸው ዶሮዎች የታቀፈችውን፣ ጭር ያለችውን ሳይመለከቱ ወደ ንባባቸው አይዞሩም። በሥራ ላይ የነበራቸው እምነት ብርቱ ነበርና ጫማ ሰፍተው ሳንቲም ሲሰበስቡ ከአያሽር-አያገድፍ ደሞዛቸው አናት ታክላ ጉዳይ እንደምትሞላ ስላወቁ፣ ነዋሪውን እስቲገርመው ድረስ መስፋታቸውን ይቀጥላሉ። እጭናቸው አስገብተው ሲቀጠቅጡ ሀሳባቸው ግን የህልውናን ምንነት ከማጠንጠን አያርፍም። እናት ቤት ያፈራውን ሲያበሳስሉ፣ ትንሹ ፍሬው ከቤት ሥራው ጋር በማሾ ብርሃን ሲታገል፣ ኑሮን ህይወት ብለው ተያይዘውት ቆዩ። ከጓደኛቸው ጋር የሚያደርጉት ውይይት እስከ ንጋቱ በሚዘልቅበት ወቅት፣ እናት ስለማሾው ክር ማለቅ ማንገርገራቸው አልቀረም።

ጨዋታ መሀከል የሚስት ነገር ሲነሳ ተከዝ ማለታቸውን ያስተዋለ ጓደኛ ምክንያቱን ቢጠይቃቸው፣ ፍሬውን “እዛ ጓዳ ሂድና አጥና” በማለት ከአጠገባቸው አርቀው ሲያበቁ፣ ትንሽ ተከዝ አሉና፤ በሬ ግንባር በማታህል ማሳ መዘዝ በተነሳ የርስት ክርክር፣ የልጅነት ሚስታቸውን የዘመድ ባላንጣዎች መርዝ አብልተው እንደገደሏትና የዚህም መሪር ሀዘን ከቶም ከልባቸው ሊጠፋ ያልቻለ ነበልባል እንደሆነ አጫወቱት። ለልጃቸው ያላቸው ፍቅርም የዚሁ ጭምር ውጤት እንደሆነ ሲናገሩ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው ነበር። ያዳመጣቸው ቻይነታቸውን አድንቆ በሀዘናቸው አዝኖ ተለያቸው። ፍሬውን ጠርተው፣ ከጭናቸው ላይ አስቀምጠው ብርቱ ተማሪ እንዲሆን ሲመክሩት የነገሩ ድንገተኛነት ገርሞት የህፃን ልቡ ጠየቀች።

እያደር የተሰማው የኚህ ሰው ማንነት በጐን መታየትን ሲያስከትልባቸው፣ አለቆቻቸውም “በአጉል እምነት የታበየ ግብዝ ነው” የማለትን አነጋገር በየአጋጣሚው ሳይሰነዝሩባቸው አላለፉም። “አቶ ጌታሁን ለመሆኑ ‘ህግና ሰው’ የሚልን ነገር ለህፃናት ማስተማር ምንን ለማትረፍ ይሆን? ለወሬው እንደሆነ ሀገሬው አይበቃም?” ሲሉ አለቅየው የተናገሩትን ለመመለስ አፋቸውን እንደከፈቱ አለቅየው ቀድመው በሩን ከፍተው፤ “ውጣልኝ!” አሏቸው። መውጣቱን ወጡ፣ ነገሩ ግን ከልባቸው አልወጣም። የመምህርነት ሙያ ምግባረ ቀናና የተማሩትን የተገነዘቡ ሰዎችን ማፍራት እንጂ ለደሞዝ ማግኛ ብቻ የሚፈጸም የግብር ይውጣ መሆን እንደሌለበት ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር “ከልፈፋቸው አንዱ” ተብሎ ቢወሰድም ያዳመጠ ህሊና ውስጥ መቀረጹ ግን አልቀረም።

ደሴ ዙሪያ ከአንድ ወረዳ የሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ እንዲፈርስ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ተማሪዎችን ሰብስበው ወረዳ ገዥው ዘንድ ለአቤቱታ ሲሄዱ ያየ ሁሉ፣ “ይሄ ሰው ብሎ፣ ብሎ በገዛ እጁ እጁን መስጠቱ ነው” ያላለ አልነበረም። ለፈረንጅ ላሞች ማርቢያነት አስበውት የነበረው መሬት በሌሉበት በግብረ ጠል የተወረሰባቸው በዥሮንድ ማንትሴ ከሄዱበት መጥተው ከብዙ ዘመን ክርክር በኋላ ረቱ። አቶ ጌታሁን ስለ ትምህርት ገበታ፣ ስለ ዕውቀትና ታዳጊ ትውልድ፣ ሰፊ ድርሳን ቢያቀርቡም ለወረዳ ገዥው የወፍ ቋንቋ እንጂ፣ ሌላም ሆኖ አልተሰማቸውም። ትምህርት ቤቱም ፍርስራሽ ላይ የእርሻ መኪና እንቲንዳዳበት ሳምንት አልፈጀም።

ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ እያደር ከዓይንና ከአፍ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ሹማምንት የሚሰነዝሩት አስተያየት ጓደኞቻቸውን ማራቅ ጀመረ። ከሁለቴም ሦስቴ ማስጠንቀቂያና ግሳጼ ተሰጣቸው። እሳቸው ግን እየጐላ ከመጣው መነጠላቸው ጋራ እየታገሉ፣ ከበፊቱ ማንነታቸው ላለመለወጥ መፍጨርጨራቸውን ቀጠሉ። በራስ አነሳሽነት የጀመሩት ተማሪዎችን ይዞ በየገጠሩ በመሄድ ቅዳሜና እሑድን ፊደል ማስቆጠር ከሀገሬው ምስጋና ሲያተርፍላቸው፣ ከወደ አውራጃ ጽሕፈት ቤት ወታደር ተላከባቸው። ጫማቸውን ይጠቀጥቁ የነበሩት ሰው ድንገት የመጣውን ሀይል ማንነት ለመጠየቅ ማብራሪያ በመሻታቸው ቃል ከርሮ በተነሳው ውዝግብ እናት መሀከል እገባለሁ ሲሉ፣ ሰደፍ ደረታቸውን ብሎ ምድጃ ስር ጣላቸው። ጌታሁንም በዚሁ ሳቢያ ለአንድ ወር እንዲታሰሩ ሲደረግ፣ የእናታቸው ሁኔታ እያደር መባስና የፍሬው መውደቅ ሲያሳስባቸው፤ እናት የጐድን አጥንታቸው ተሰብሮ ኖሮ ደም ተፍተው፣ የልጃቸው ስም ከአፋቸው ሳይለይ እንደአረፉ ተሰማ።

ጌታሁን ከእስር ሲወጡ ዓይናቸውም አብሮ ደፍርሶ ወጣ። ከንግግራቸው መጠን ማለትን ጀመሩ። ከግብሩ ግን ይህ ነው የተባለ ለውጥ አይታይባቸውም ነበር። ፍሬውን የበለጠ ወደ ጉያቸው አስጠግተው በርሱና በብርቱ መምህርነታቸው ተጽናንተው ከቆሙበት ጀመሩ። የቅርብ ጓደኞቻቸው አብሮ መዋልንና መታየትን ፈርተው እንደሸሹ የሚያወራው ጥቂት አይደለም። ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ የሚቀርቧቸው ተማሪዎችና ጥርጣሬ ላይ የማይወድቁ ሌሎች ሠራተኞች ብቻ ሆኑ። ለብቻው እንደ ደረቀ ግንድ፣ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ተለይተው ይታዩ ጀመር። ሀዘናቸውን ከሀሳባቸው አሰናስለው በጽናት ለመኖር ሁሌ እንደማሉ ሲኖሩ፣ የልባቸው መሀላ ይንርና ጐልቶ ሲሰማ ፍሬው፣ “ምናልክ አባዬ፣ እኔን ነው?” ይላል። ከሀሳባቸው የባነኑት ሰው፣ “የለም፣ የለም ወዲህ ነው፤ ከራሴ ጋር ነው” በማለት ይመልሱለታል።

በመንፈቁ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ቤት ደጃፍ ሬሳ ታይቶ ሀገር ግልብጥ ብሎ ይመለከታል። ከሥራ የተመለሱት መምህር አጀቡን አልፈው ቢጠጉት፣ ከአፈር የወጣ ሬሳ ተጋድሟል። “የመንደሩ ውሾች ናቸው ፈልፍለው ያወጡት። አይ ሲያጋልጥ፤ አይ የሰው ደም!” ሲል አንዱ፣ ሌላው ተመልካች፣ “ይሄንዬ ወዳጅ ዘመድ ጉዱን አልሰማም” ይላል። ጌታሁን አፋቸውን ከፍተው ሬሳውን ሲመለከቱ፣ አፋቸው እየገቡ የሚወጡትን ዝንቦች ለምን እንደማይከላከሉ የተመለከተ ገረመው።

በረቀቀ ሸር፣ በግፍ ግፍ የተወነጀሉት ዶሮ አርቢው ጫማ ሰፊ መምህር፣ ያለ ፍርድ አሥራ አንድ ወራት ከታሰሩ በኋላ በሁለት፣ ሦስት ምስክሮችና በእብሪተኛ ዳኞች ሀይል ሃያ አመት ተፈርዶባቸው ወደ አዲስ አበባው ዓለም በቃኝ እንዲዛወሩ ተደረገ። የማወጣጫው ግርፋትና ቅጥቀጣው ያደረቃቸው ሰው ወደ ወህኒ መኪና ሲዘዋወሩ፣ ፍሬውን ከአንድ ጐረቤታቸው ሥር ተለጥፎ አዩት። የመጨረሻው ነበር።

ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ ዓለም በቃኝ አሥራ ስምንት ዓመታት ታስረው ሲወጡ አዲስ አበባን እንደ ስደተኛ አዲስ መጥ እንጂ፣ ጥንት እንደሚያውቀው ሰው ለማየት አልቻሉም። እኚህ ከሥር መሠረታቸው የተነቀሉ፣ በብዙ ጦር የተወጉ የግፍ ብካይ፣ እግራቸው ወደ ወሰዳቸው ሲሄዱ ውለው፣ ሲመሽ ማደሪያ ፍለጋ አንዱን ኩሊ ቢጠይቁት ተክለ ሃይማኖትን በጣቱ ጠቆመላቸው። ገብተው ወደቁ።

የገቡበትን ትርምስ በመጠኑ ሊገነዘብ የሚችል ትንሽ የህሊና ጭላንጭል ቀርቷቸው ነበርና ከቀን ብዛት አንድ አጥር ጥግ፣ በአሮጌ ዣንጥላ የተገጠመች ጠለላ አበጅተው ጫማ መቀጥቀጥ ጀመሩ። ጫማ አሰሪውም በየአጋጣሚው ለምን ይሄንን ሙያ ብለው እንደያዙት ሲጠይቃቸው በቁስል ፈገግታ፣ “ጌታ ለመሆን ነው እንደ አስኮ ጫማ” ማለትን ጀመሩ ይባላል። በዚሁም “አስኮ ጌታሁን” የሚለው ቅጥል ላያቸው ላይ እንደታተመ ቀረ።

ጀምበር በጠለቀች የአስኮ ጌታሁን ፊት እየተጨማተረ፣ በንዴት ምራቁን በተፋ ቁጥር ፊቱን እየጠረገ፣ እሳት ውስጥ እንደወደቀ ጉበት ያለፈውና የአሁኑ ሥቃይ ወላፈን ሲገርፈው ኩምትርትር እያለ ሄደ። የቀረችው የአእምሮ ጭላንጭል ጨርሶ ከስማ ጨርቅ ጥሎ መሄድ የጀመረ ዕለት፣ አንድ ከቶም የማይረሳ ነገር ተናገረ እየተባለ ይወራል። ይሄውም፣ “ታስፈሩኛላችሁ!” የሚል ነበር።

ጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል

(1973 ዓ.ም)

.

በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

[ምንጭ] – “አስኮ ጌታሁን እና ሌሎች ታሪኮች” (፲፱፻፺፪)፤ ገጽ 106-117።

6 thoughts on ““አስኮ ጌታሁን” (ልብወለድ)

  1. የጃርሶ ሞት ባይኖር ኪሩቤልን የተወሰኑ መጣጥፍና ወግ በዶችቬሌ ሬድዮ በልጅነቴ አዳምጥ ነበር። ትዝታው በውስጤ አለ። ዛሬ ደግሞ ከ30 አመት በኋላ ጽሑፉን ስላገኘሁት ደስ እያለኝ አነበብኩት ታሪኩን። ቀጥሉበት ከተቻለም በድምፅ አድርጉት።

    Like

  2. እግዜር ይባርካችሁ፣ ይጨምርላችሁ፣ ያቆያችሁ፣ ያገልግሎት ዘመናችሁን ያርዝምላችሁ።ገና ዛሬ ስለሆነ የጎበኘኋችሁ ይቅርታ አሰተያየት የለኝም።

    Like

  3. ejig betam dessssss yemil neger new abo egziabher mignotachihun hulu yasakalachihu edmeyen bemulu simegnew yenebere neger new jarso ejig betam yemiwodew derasi,social scientist, philosopher etc new ebakachihu eyandandun tireka lemakreb mokiru thank you very much Adam Reta.

    Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s