የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ

የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ

በዮሐንስ አድማሱ

(1961 ዓ.ም)

.

“እፍጻሜ ለማድረስ የምሞክረው ተግባሬ በተጻፈው ኃይለ ቃል እንድታዳምጡ፣ እንዲሰማችሁ፣ ከሁሉም ይልቅ እንድታዩ ማድረግ ነው። ከሱ ወዲያ ሌላ ተግባር የለኝም። በሱም ውስጥ ሁሉም ነገር ይካተታል። ከተቃናልኝ በሚገባችሁ መጠን መበራታት፣ መጽናናት፣ ፍርሀት፣ ሞገስ – የምትፈልጉትንም ሁሉ – ታገኛላችሁ። ትሿት ዘንድ የምትገባችሁን ግና የዘነጋችኋትንም እውነት በጨረፍታ ታይዋታላችሁ። ” 

ዮሴፍ ኮንራድ፣ “ኒገር ኦፍ ዘ ናርሲሰስ” ከተባለው መጽሐፍ መቅድም

.

ሥነ ጽሑፍ የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነት ኀይል ግዘፍ ነሥቶ፣ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው። የአማናዊ ሥነ ጽሑፍም ምንጩ የሰው ልጅ እውነታ (ሪአሊቲ) ነው። እውነታውም በልደትና በሞት መካከል የተዘረጋው ህላዌ ነው።

ሥነ ጽሑፍ ጠቅላላ ዓላማው ማስደሰት ነው። ይኽንንም ጉልህ አላማ የሚፈጽመው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕይወት ሒስ በማቅረብ ነው። ሥነ ጽሑፍ ጉልህ ዓላማውን ለመፈጸም ጥራትና ወጥነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። “በኑኀ ዘመን በቀን ብዛት፣ የማይነቅዝና የማይሻግት” መሆን አለበት። አለዚያ አጉል ጉሕና ወይም ብስና እንጂ ሥነ ጽሑፍ ሊሆን አይችልም። ሥነ ጽሑፉን ሥነ ጽሑፍ የሚያደርገው የደራሲው የኪነት ኀይሉ፣ የማስተዋልና የማንጠር ስጦታው፣ ያስተዋለውንና ያነጠረውን ከሰው ልጅ እውነታ ጋር በቋንቋ ኀይል አገናዝቦና አዋሕዶ እነሆኝ ብሎ የሚያቀርብበት ልዩ ችሎታው ነው። ግልብ ደራሲ ግልብ ተመልካች ነው። ጽሑፉም በዚያው ልክ ግልብ፣ የችርቻሮ ጽሑፍ ይሆናል።

ይህን አባባል መሠረት በማድረግ ከሠላሳ ሦስት እስከ ስድሳ አንድ ዓመተ ምሕረት (1933-1961) ድረስ ስላለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ አንዳንድ ነገር ለማውሳት እወዳለሁ።

በጠቅላላው በነዚህ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ አማርኛ ያፈራው ሥነ ጽሑፍ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። ከጥልቀት ይልቅ ግልብነት፣ ከውበት ይልቅ አስቀያሚነት (አስቀያሚነት ውበት ነው ወይንም ውበት አለው ካልተባለ በቀር)፤ ከሥነ ጽሑፋዊ እውነት ይልቅ የአንቀጸ ብፁዓን ምኞት ይገኝበታል። ሥነ ጽሑፍ የሕይወት ሒስ በመሆን ፈንታ የወሸነኔ ስሜት መግለጫ ሁኗል። እስከ አሁን ድረስ አካሄዱ አጉል ነው፤ የጎድን ነው። አቅጣጫም ያለው አይመስል። የወደፊት አካሄዱን መተንበይ ባይቻልም፣ እስከ አሁን ድረስ ተመልክተን የተገነዘብነው አካሄዱ ለወደፊት አካሄዱ አብነት ለመሆን የሚችል አይደለም።

በአጭሩ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ ቀደም ካለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ አዝመራ ጋር ሲነጻጸር ደረጃው፣ ጥራቱና ወጥነቱ፣ በዚያውም መጠን ውበቱና አስደሳችነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። እያደር ይጫጫል፤ እየሰነበተ ይደገድጋል፤ እየባጀ፣ እየከረመም ይመነምናል። ለዚህ አሳዛኝ፣ ከቶም ድቀታዊ ሁነት ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ነገሮች ሦስቱን ጠቅሼ ከመዘርዘሬ አስቀድሞ ጥራት፣ ወጥነት፣ ጥልቀትና ውበት ያላቸው ሁለት መጻሕፍት መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሁለቱ መጻሕፍት “እንደ ወጣች ቀረች” እና “ፍቅር እስከ መቃብር” ናቸው። (ከነዚህ ከሁለቱ ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች መጻሕፍት በመጠኑ አሉ።)

እነዚህ ሁለቱ መጻሕፍት የኪነት ውጤት ናቸው፤ ጥልቀታቸውም፣ ውበታቸውም፣ ሌላውም መልካም የምንለው ጥራታቸውም ከዚሁ ከኪነት መንፈሳቸው ይሠርጻል። በ”ቴክኒክ” (ቅርጽ) በኩል ከሞላ ጎደል ምሉዕ ናቸው – በትልም፣ በባሕርያት አቀራረጽ፣ በአተራረክ፣ በቋንቋ … ወዘተ። እነዚህ ሁለት የልብ ወለድ መጻሕፍት በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች የሰነዘርኋቸውን ሐሳቦች በሙሉም ባይሆን በከፊል አቀናብረው ይዘዋል። ሁለቱም ሁለት ልዩ እውነታ ያቀርባሉ። በአንድ ነገር ይተባበራሉ፤ ይገናኛሉ። ሁለቱም ያቀረቡልን የሕይወት ሒስ ነው። ሁለቱም በየገጾቻቸው በሚገኙት ቃላት ኀይል እንድናዳምጥ፣ እንዲሰማን፣ በተለይም እንድናይ ለማድረግ ሞክረዋል።  ይኸም ሙከራቸው በሙሉም ባይሆን በከፊል ስለተቃናላቸው የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ አድርገዋል። በዚሁም እኛ አንባብያኑ ሐሤት እናደርጋለን።

በጠቅላላው ከሠላሳ ሶስት ዓመተ ምሕረት ወዲህ ጥሩ የምንላቸው የአማርኛ (የኪነት) መጻሕፍት ጥቂት ናቸው። ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ “ብላሽ” ናቸው። ለምን?

ደራስያኑ በደፈናው ወይንም በጠቅላላው ስለ ልዩ ልዩ የኪነት ጽሑፍ ቴክኒክ አያውቁም፤ ቢያውቁም አይጨነቁም። ጽሑፋቸውን የቴክኒክ ግብዝነት አለልክ ያጠቃዋል። የጽሑፍ ቴክኒክ ለኪነት ጽሑፍ ዓቢይ ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። የሀገራችን የኖረ፣ የቆየ የጽሑፍ ቴክኒክ አለ፤ የውጭ ሀገርም የጽሑፍ ቴክኒክ አለ። ደራስያኑ የውጭውንም ሆነ የሀገራችንን የጽሑፍ ቴክኒክ አብስለውና ጠንቅቀው አያውቁትም።

በሀገራችን (ለምሳሌ ያህል) የታወቀ፣ የተለመደ፣ ከሙያ የዋለ የገድል አጻጻፍ ቴክኒክ አለ። ገድል የአንድ ሰማዕት ወይንም የአንድ ጻድቅ የሕይወት ታሪክ ነው። ገድል በጠቅላላው የሚያወጋው ወይንም የሚተርከው የሰማዕቱን ወይንም የጻድቁን ተጋድሎ ነው … ስለሰማያዊ ልዕልና፤ ለሰማያዊ ክብር መንፈሳዊ የሆነ ምድራዊ ተጋድሎ። አተራረኩ በመንፈሳዊ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ትልምና ባሕርያት የአተራረክ ስልትም አለው። የአተራረክ ፈሊጥም አለው። ብሎም “ገድለ ተክለ ሃይማኖትን” መጥቀስ ይበቃል። አንቱ የሚባል ወይንም ለመባል የሚሻም ደራሲ የገድልን አጻጻፍ አጥርቶ ማወቅ ግዴታው ነው። ብዙ ነገር ይማራል፤ አያሌ ጥበብ ይቀስማል። በቴክኒክም ይበለጽጋል።

የቅኔ ቴክኒክ አለ። ይኽንንም ቴክኒክ ማወቅ የማንኛውም ደራሲ፣ በተለይም የገጣሚ ተግባርና ግዴታ ነው። (የቀረውን እንዳለፈው ያነቧል።) ሌሎችም ብዙ የጽሑፍ ቴክኒኮች በሀገራችን በብዛት ይገኛሉ – የተረት፣ የሙሾ፣ የእንቆቅልሽ፣ የእንካስላንቲያ፣ የቀረርቶ … ወዘተ። እነዚህን ሁሉ አንቱ የሚባል ወይንም ለመባል የሚሻ ደራሲ አጠናቆ ማወቅ ግዴታው ነው።

ከውጭውም ዓለም የተገኙ የጽሑፍ ቴክኒኮች አሉ፤ የተውኔት፣ የረጅም ልብ ወለድ፣ የአጭር ልብ ወለድ … ወዘተ። ደራስያናችን የውጭውንም የጽሑፍ ቴክኒክ አጥርተው አያውቁትም። በአጭሩ፣ የሚጽፉት አገኝ አጣቸውን ነው። የሚጽፉት በንዝሕላልነት፣ ብዙ ጊዜም በግዴለሽነት፣ በማን አለብኝ መንፈስ ነው። ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ብዙ መጻሕፍት አሉ። ለጊዜው ግን አንዱን መመልከት ይበቃል።

“አድልዎን በሰይፍ” መጽሐፉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ “ብላሽ” ነው። ጉድለቱ ወሰን ዲካ የለውም። ጥራቱ ጉድለቱን ጉልህ አድርጎ ማሳየቱ ነው። ታሪኩ የሚተረከው በአንደኛ መደብ፣ ነጠላ ቁጥር (እኔ) ነው። አንድ ታሪክ በአንደኛ መደብ መተረክ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ታላቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አደገኛ ነው። በተለይም ለጀማሪ ደራሲ ክፉ፣ አዚመኛ አንጋዳ ነው። እላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ በአንደኛ መደብ ይተርክና መጽሐፉ ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው “ሞትኩ” ይላል። ይኽን የሚለው የታሪኩ ዋና ባሕርይ ነው። ባሕርዩ መደቡ አንደኛ መደብ ነው። “ሞትኩ” ካለም በኋላ ታሪኩን ይተርካል። ሙቷል፣ በአጸደ ሥጋ አይገኝም ማለት ነው። ይኽ ንስሐ የሌለው ታላቅ የቴክኒክ በደል ነው።

እንደዚህ ያለው በደል የሚፈጸመው ምናልባት ካለማወቅ ይሆናል፤ ምናልባትም ከንዝሕላልነት፣ ወይም ከንቀት። ምክንያቱ የትኛው እንደሆነ አላውቅም። ከደራሲው ጋር መነጋገር ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳ ይሆናል። ይኽንንና ይኽን የመሰለ የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው መጻሕፍት እጅግ ብዙ ናቸው። የሚከተሉትን ይመለከቷል፤ “ውብ ነበረች”፣ “ሥራ ገንዘቡና ጓደኛው”፣ “የጉድጓዱ ምሥጢር”፣ “ንስሐ”፣ “እውነት ስትጠፋ”፣ “የሐሳብ እስረኛ”፣ “ከማን አንሼ”፣ “እኛም ይድረሰን” … ወዘተ። እነዚህ መጠቀስ ከሚገባቸው መካከል በጣም ጥቂቱ ናቸው።


የዘመናችን ደራሲያን በጽሑፍ ቴክኒክ በኩል ከሀገራቸውም አልሆኑ፤ ከውጭውም አልሆኑ። የሀገራችንንና የውጭን አዳቅለውም መጢቃ ቴክኒክ አላቀረቡልንም። ወይንም ከሁለት አንዱን ብቻ ተከትለው ወጥ ጽሑፍ አላበረከቱም። እስከ አሁን ድረስ ቴክኒካቸው ውጥንቅጥ፣ የልብ ትኩሳት፣ የልብ ቃር የሚሆን አጉል ቅይጥ ነው። ከሥርዓት ይልቅ ምስቅል የሰፈነበት ነው።

ምናልባት ከዚህ ውጥንቅጥ፣ ከዚህ ምስቅል ኢትዮጵያዊ የሆነ ወጥ ቴክኒክ – እንደ ብሂል፣ እንደ ሠረዝ፣ እንደ ጎዳና ቅኔ ያለ ይጸነስ ይሆናል። ይኽ መቸም ምኞት ነው። ምኞቱ እውነት እንዲሆን የኔ ብቻ ሳይሆን ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ማደግ፣ መዳበርና ኀያል መሆን የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፍላጎት ነው።

ሁለተኛው ነቁጥ የሒስ ጥበብ አለመለመድና የሐያሲ አለመኖር ነው። በባህላችን የሒስ ጥበብ አልነበረም፤ የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከዚህም የተነሳ ደራስያኑ መጻሕፍታቸው በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ሲተቹ (በቀጥተኛ ሒስ) አንዳንዶቹ ያኮርፋሉ፤ አንዳንዶቹ ይዝታሉ፤ አንዳንዶቹ በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ይሳደባሉ። ይኽ መንፈስ ከየት እንደመጣ አላውቅም። ጉዳዩ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ይሁን እንጂ አንድ የማውቀው ነገር አለ። ሒስ በቅኔ ቤት የተለመደ ነው። የቅኔው ተማሪ፣ ከቅኔው ትምህርት ሌላ፣ በጥበቡ የሚጎለምሰው፣ የኪነት ተውህቦውን የሚያተባው፣ የሚያራቅቀውና የሚያደራጀው በሒስ ጥበብ ነው። የተማሪውን ቅኔ የቀለም ጓደኞቹና መምህሩ ይተቻሉ። እሱም እንደዚሁ ያደርጋል። ተማሪዎቹ የመምህራቸውን ቅኔ ይተቻሉ፤ አንዳንዴም ብትንትኑን ያወጡታል። ኩርፊያና ስድብ፣ ዛቻና ቅያሜ የለም፤ ይህ መልካም ጥበብ እያለ ደራስያናችን ለምን በሒስ (በደንበኛ ሒስ) ይቆጣሉ?

ሒስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛና ፍቱን መድኃኒት ነው። ሒስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ ነው። ማስተማሪያም ነው። እንደ ስድብ፣ እንደ ነውር መቆጠር የለበትም። በሒስ መስተዋትነት ስኃውን የማይከላ ሥነ ጽሑፍ ሆነ ደራሲ ከበድን አንድ ነው። ተገቢ ቦታውም ቤተ መዘክር ነው።

ሦስተኛው ነቁጥ፣ ያለፉት የሃያ ሰባት ዓመታት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሦስተኛ ጉድለቱ የቋንቋ ነው። በጠቅላላው ቋንቋው ውበት፣ ጥራትና ተጠየቅ  የተለየው  በጸያፍ (ሰዋስው) የተበከለ በቃላት እጥረት የተሞሸረ ነው። ይኽን ጉድለት የፈጠሩ ደራስያኑ ናቸው እንጂ ቋንቋው አይደለም። ቋንቋው ማለፊያ ባለሙያ፣ ልባም ደራሲ ካገኘ ብዙ ሰነፍ የሚያስገባ አይመስለኝም። ለዚህም አብነት የሚሆኑ የሚከተሉት ቀደምት ደራስያን ናቸው፤ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አለቃ ታዬ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ … ወዘተ። በመጻሕፍት በኩል (እላይ የተጠቀሱት ደራስያን ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ) መጽሐፈ መነኰሳትን፣ አርባዕቱ ወንጌልን መመልከት ይበቃል።

  afework-tobya heruy-wedaje kidane-hizqel

የአሁኑ ዘመን ደራስያን አማርኛ ለምን ተበላሸ? በዚሁስ የሚቀጥለው ለምንድር ነው? ሁለት ምክንያት መስጠት ይቻላል። አንደኛ ደራስያኑ፣ ትምህርት ቤት በነበሩበት ጊዜ ጥሩ አማርኛ እንዲማሩ አልተደረገም። ሁለተኛ ደራስያኑ የሚያነቡ አይመስልም። ጥሩ ጥሩ የሆኑ፣ ተነበው በቋንቋቸው ጥራት፣ በዘይቤያቸው ውበት የሚሰዩ መጻሕፍት ጠፍተው አይደለም፤ አሉ። ከፍ ብዬ የጠቀስኋቸው መጻሕፍት ጥቂቱ ናቸው፤ እነሱን የመሳሰሉ በብዛት አሉ። ፈልጎ ማንበብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። መጻሕፍቱን የጠቀስኋቸው ስለ ይዞታቸው ሳይሆን (ይዞታቸውን የማይፈቅዱ ይኖሩ ይሆናል)፣ በጠቅላላው ስለቋንቋቸው ጥሩነት ነው፤ ስለምናባቸው (ኢማጂኔሽን) ስፋት ነው፤ ስለ ዘይቤያቸው አስገራሚነትና ውበት ነው። ዛሬ ያሉንም ሆኑ ወደፊት የሚነሡት ደራስያን እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን መጻሕፍት በየጊዜው ቢያነቡ ቋንቋቸው ይዳብራል፤ አስተሳሰባቸው ይተባል፤ ሐሳባቸውን – ጃ ሳይላቸው – እንደ ልባቸው መግለጽ ይችላሉ። የማይሰለች፣ ለዛና ወዝ ውበትና ጥራት ያለው፣ “ዞሌ” ጽሑፍ መጻፍ ይችላሉ።

የጽሑፌ ኀይለ ቃል በድርሞ መልክ የሚከተለው ነው። በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በጠቅላላው ጥራቱና ወጥነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። ይኽም የሆነበት ምክንያት፣

/ በቴክኒክ ጉድለት፤ / በሒስና በሐያሲ እጦት፤ / በደራስያኑ አማርኛ መበላሸት።

ከነዚህም ምክንያቶች ለሁለቱ (“” እና ““) ኀላፊዎቹ በከፊል ደራስያኑ ናቸው። አያነቡም፤ የማወቅና የማጥናት ጉጉት የላቸውም። ለሁለተኛው ምክንያት (““) ኀላፊነታቸው ኢርቱዕ ነው። ሒስ አለመቀበላቸው ወይንም በሒስ መበርገጋቸው።

የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የተሻለ ደረጃ እንዲይዝ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ተጽዕኖው ለመላው ዓለም እንዲተርፍ ከተፈለገ ደራስያናችን (ዛሬ ያሉትም ሆኑ ወደፊትም የሚነሱት) ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው። የተጋድሎው ጎዳና ረዥም ሆኖ ጎዳጉድ የበዛበት፣ ቅርቅፍት ነው፤ ተስፋ መቁረጥ ግን አያስፈልግም። እንደጥንታውያኑ ለሀገራቸው ነጻነት ሕይወታቸውን፣ በየጎራው፣ በየሜዳው፣ በየአረሁ እንደሠዉት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ባጭር ታጥቆ ፣ የሥነ ጽሑፍ ዘገር ነቅንቆ፣ የሥነ ጽሑፍ ጋሻ መክቶ ለሥነ ጽሑፍ መጋደል የየእያንዳንዱ ደራሲ ፈንታ ነው።

ኢትዮጵያውያን ደራስያን በዓለም የሥነ ጽሑፍ ሸንጎ ላይ ተሰልፈው የሚወዳደሩበትን ዕለት በናፍቆት እጠባበቃለሁ።

.

.

.

.

.

ዮሐንስ አድማሱ

[ምንጭ] – “መነን” መጽሔት፤ ግንቦት ፲፫፣ ፲፱፻፷፩ (ገጽ ፲፪-፲፬)።

4 thoughts on “የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ

  1. አጃኢብ ነው ፡ እንዴት ያለ ግሩም ፀሐፊ ነው ፡ በእውነቱ የቋንቋ ባለፀጋ ነው ፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ይሄ እይታው ያሁኑንም ጊዜ ይመለከታል፡ እርግጠኛ ነኝ ወደፊት (በቅርቡ) የዚህን ደማም ብዕረኛ ስራዎች በዚህ ገፅ ላይ እንደምንመለከት፡ ለሂሱ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡

    Like

አስተያየት ለመስጠት