“በሰንበት የተፀነሰው” (ልብወለድ)

“በሰንበት የተፀነሰው”

በእንዳለጌታ ከበደ

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

“ምነው በጊዜ መጣህ? የኔታ የሉም እንዴ?” አለች ምንትዋብ፤ ቄስ ትምህርት ቤት የላከችው ልጇ ያለ ሰዓቱ መመለሱን አይታ።

“ወላጅ አምጣ አሉኝ” አላት፣ የስድስት ዓመቱ አቦቸር – ብልጣብልጥ ዓይኖቹ ላይ ሐዘኔታን ለማስነበብ እየጣረ።

“የሠራኸው ተንኮል አለ?”

“የኔታ የማላውቀው ጥያቄ ሲጠይቁኝ ኤክስ ሆንኩና ጓደኞቼ ሳቁብኝ”

“ምንድነው ጥያቄው?”

“‘እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ ከጨረሰው በኋላ ወደ ገነት ወስዶ ምን ብሎ አስጠነቀቀው’ ብለው አፍጥጠው ጠየቁኝ”

“ምን መለስክላቸው?” አለች እናቱ መልሱን ለመስማት ጓጉታ።

“’አልሰማሁም’ አላልኳቸውም። ‘እግዚአብሔር አዳምን ወደ ገነት ወስዶ  ምን አለው?’ ሲሉኝ ጊዜ፤ ‘ለሕይወትህ ዋጋ ስጥ ብሎ አስጠነቀቀው’ ስላቸው፤ ተቆጡኝና፤ ብዙ አይነት የሚያስበሳጭ ስድብ ሰደቡኝ …”

ሌላ ቀን

“ዛሬ ደግሞ ለምንድን ነው ት/ቤት ያልሄድከው?” ብላ ተቆጣች፣ ምንትዋብ። ገበያ ሄዳ ብቅልና ጌሾ ገዝታ ስትመለስ ነው አቦቸርን ሠፈር ውስጥ ያገኘችው። በዕድሜ ከሚተካከሉት ጋር ሆኖ፣ በጣቶቹ መሃል ያለችውን ብይ ወደ ጉድጓዱ አፍ ለመክተት ሲፍጨረጨር ነበር የደረሰችበት።

“የኔታ አባረሩኛ!! ‘እዚህች ደጅ ብትደርስ በአለንጋ እዠልጥሃለሁ’ አሉኝ” አለ አቦቸር “ዛሬም ‘ይሄ በሰንበት የተፀነሰ’ ብለው፤ ሌላ ሰው እንዲሰማላቸው ብለው – ጮክ ብለው ሰደቡኝ …”  አለ ጠይም ፊቱ ቅያሜ እየተስተዋለበት።

“ለምን?” ተቆጣች – ምንትዋብ።

“አለንጋቸውን ደብቄባቸው አላውቅም። ከጫፉ ቆርጬ ቦርሳዬ ውስጥ የደበቅሁትም እኔ አይደለሁም። ሁሌ ሳልሰድባቸው ይሰድቡኛል፤ ‘ጥፋ ከፊቴ! ባለንጋ ነው የምዠልጥህ’ እያሉ ያስቦኩኛል”

“የማንን ልጅ ማን ይቀጣል?” አመረረች፣ ምንትዋብ።

በፊትም ቢሆን የሃይማኖት ሰዎችን አትወድም። ምክንያትሽ ምንድን ነው? ቢሏት ‘አባቴ’ ትላለች። አባቷ መጾም መፀለይ የሚያበዙ ነበሩ፤ ሰው እፊታቸው ቀርቦ ‘ይፍቱኝ አባ’ ብሎ የሠራውን በደል የሚናዘዝላቸው አይነት ሰው ነበሩ። ቀን ቀን ‘ሐዋርያዊ ተልእኮአቸው’ን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ይውላሉ። ጀምበር አሽቆልቁላ ወደ ማደሪያዋ ስታዘግም – የሚቀመሰውን ቀማምሰው – ሞቅ ይላቸውና ጥምጣማቸውን ፈተውና ቀበቶአቸውን አላልተው በመሸበት ያድራሉ።

የምንትዋብ አባት በመሸበት በማደራቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሠፈር መንደርተኛም ለመወገዝ የበቁበት ምክንያት አለ። በስደተኛው መድኃኒያለም ስም ዣንጥላ ዘርግተውና፣ ምስል ደረታቸው ላይ አንጠልጥለው ያለ ቤተ ክህነት ፈቃድ ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር። ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው እስር ቤት ቤታቸው እንዲሆን ሲፈረድባቸው የእነምንትዋብ ስምም የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ርዕስ ሆነ።

በዚህን ጊዜ ምንትዋብና እናቷ ሳር ቅጠሉ፤ ዘመድ ጎረቤቱ ጣት የሚቀስርባቸውና ሰድቦ ለሰዳቢ አሳልፎ የሚሰጣቸው መሰላቸው። ከማታውቃቸው ወንዶች ጋር መሄድ የጀመረችውም ያን ሰሞን ነው፤ ቤተሰቦቿን ለመርዳት።

ምንትዋብ ወደ ቤት ገባችና ጥቁርና የረዘመ ሻሿን አውጥታ አሰረች። ቀሚሷን አስተካከለች። መበስበስ ከጀመረ – መቀመጫው ከተበላ ካርቶን ውስጥ ያደፈ ነጠላዋን አውጥታ ትከሻዋ ላይ አኖረች።

ቤቱን ለቅቀው ከመውጣታቸው በፊት፣ ጠላ መኖሩን የሚጠቁመውን ቂጡን ለሰማይ የሚያሳይ ጣሳ (አፉን ከመሬት ባገናኘ ሙቀጫ ላይ ተቀምጦ የሚያሳየውን) አርማ አስገባችው።

ቤቱ ተቆለፈ።

“ምንትዬ!”

“እ?”

“አሳይሻለሁ እሺ?!”

“የኔታህን?”

“አይ የማይመጣውን ልጅ! እኛ ስንማር ከኛ ጋር የማይኖረውና ብዙ ንፍጥ የሚወጣው ልጅ!”

“ሰነፍ በለው”

“ከማይመጣው ልጅ የበለጠ የማይመጣው ትልቁ ልጅ ዛሬም አልመጣም” ይላል አቦቸር ያሳሰበው ይመስል – አመዳም – ጠይም ፊቱን እያሻሸ።

“ወላጅ አሰዳቢ በለው”

“ላይመጣ ነዋ የሄደው! አንድ ቀን የኔታ ከሽንት ቤት እስኪመጡ ድረስ ብድግ አለና እሳቸው ሰክረው ጎርፍ ውስጥ እንዴት ተንገዳግደው እንደሚወድቁ እያሳየ ሲያስቀን፤ ደረሱበትና እስከ ሩቅ ቦታ ድረስ አባረሩት። ‘ይህን አሳዳጊ የበደለው ውጫጭ በድንጋይ በሉት’ አሉንና ሁላችንንም ላኩን። እኛ ግን ፈንክተን ከጭንቅላቱ ደም እንዳናስወጣበት ብለን እሱ ወዳልሄደበት ቦታ ድንጋይ ወረወርን። ከዚያ ቶሎ ቶሎ መሸና ወደየቤታችን ተበታተንን”

ለምንትዋብ አቦቸር ልጇ ብቻ ሳይሆን ጓደኛዋም ጭምር ነው። ጥያቄዎቹን አትሰለቻቸውም።

“ምንትዬ … ሳድግ ቁመቴ ከሁሉም የሚበልጥ አይሆንልኝም? ወደ ላ-ይ አያድግልኝም?” ይጠይቃል እናቱን።

“ያድግልሃል። ምነው አሽቆልቁሎ ማየት አማረህ እንዴ?”

“ጥቁርስ አልሆንም?”

“ትፈልገዋለህ እንዴ ጥቁረትን?” ትለዋለች፤ ደንቡሽቡሽ ያለ ፊቱ ላይ እያተኮረች።

“አዎ። እንትንስ …” ጣቱን ከንፈሩ ላይ አኑሮ የረሳውን ለማስታወስ ድምጹን እየጎተተ፤ “ፀጉሬ – ግንባሬ አጠገብ ያለው ፀጉሬ – ነጭ አይሆንልኝም?”

“ምን ያደርግልሃል ሽበት?”

“ጋሼ አበራ ሞላን ለመሆን ነዋ! የኛን ሰፈር አዲስ አረገዋለሁ። አረገውና አንድ ነገር እጽፍበታለሁ። ጠላ የምትጠምቂበት ጋን ሲሰበር ደግሞ እንዳትጥይው። ያስተማርኳቸው ሁሉ አስተማሪ ሆኑልኝ የሚሉሽ የድሮ አስተማሪ አንቺ ጋ ሲመጡ ደግሞ – ‘ለልጄ ቶሎ የማያልቅ ቾክ አምጡለት’ በያቸው። እጽፍበታለሁ። ‘የሸና ይነሸነሻል’ ብዬ። ይነሸነሻል አይደለም ‘የሸና ይሸነሸናል ብዬ ነው የምጽፈው። እንዳይረሳኝ እሺ?”

“እሺ!”

ሌላ ቀን

“እኔ ስሞት ምንድነው የምሆነው?” ይላታል፤ ያለ አባት ለምታሳድገው ምንትዋብ።

“ሚጢጢ መልአክ ትሆናለህ!” ትለዋለች እናቱ።

“ከዚያስ?” ያመጣዋል ጥያቄውን።

“ሰዎች ጉዳይ ሲኖራቸው ወዳንተ ይጸልያሉ” ትለዋለች – ምን ይመልስልኝ ይሆን? ብላ – ዓይኗን በሚመስለው ዓይኑ ላይ አተኩራ።

ሌላ ቀን

“ሳድግ አንድ ነገር አረግልሻለሁ እሺ?! የእግዚአብሔር ሚጢጢ መልአክ እሆንና እንደገና አስፈጥርሻለሁ” አላት።

(ሸራተን ሆቴልን – በምሽት – ምን እንደሚመስል ከርቀት ጐብኝቶ በሚንቦገቦገው ብርሃን የተመሰጠ ለታ ነው ይሄ ሀሳብ ውስጡ የተወለደው)

“ምናልክ? እንደገና አስፈጥርሻለሁ?!” ትለዋለች ድንጋጤዋ እየታየ።

“አዎ ቆንጅዬ አስደርጌ – ደስ የሚል ልብስ አስለብሼ – ሽቶ አርከፍክፌሽ፣ አሪፍ አስደርጌ አሳድግሻለሁ…’

እናት ትስቃለች።

“ኧይ አቦቸር! እሺ ከዚያስ?”

“ከዚያ ምን?!”

“አቆንጅተህ ካሳደግከኝ በኋላ …”

“ከአላሙዲን ጋር አጋባሻለሁዋ!”

“ከአላሙዲን?!”

“ከዚያም… እናቴን አግባት ስለው እምቢ ስላላለኝ ብዙ ዓመት እንዲያስኖረው እግዚአብሔርን እለምንለታለሁ እንጂ አላስሞተውም። ደግሞ ካጠፋችሁ ስለምታናድዱኝ – እንዳልገድላችሁ ብዬ – ስትሳሳቱ ላላይ – እንቅልፌን እተኛለሁ። ብዙ ቀን እስኪሆነኝ ድረስ…”

“ኧይ አንተ!”

“… የኔታ ጸሎት ሲያደርጉ፤ ‘አታስርበኝ’ ብለው ሲለምኑኝ ‘አልሰማዎትም’ እላቸዋለሁ። ‘ድሮ ለምን በሰንበት የተፀነሰው ብለው ሰደቡኝ፤ ትንሽ እያለሁ ለምን በአለንጋ ዠልጠው አሳመሙኝ’ እላቸዋለሁ። ለሠይጣን እነግረውና፤ ‘ሂድና ፂማቸውን በእሳት አቃጥለውና ራሳቸውን አግማቸው’ እለዋለሁ!’

ምንትዋብ ሳቋን መቆጣጠር ያቅታታል።

*  *  *

አንድ ቀን ደግሞ ከገበያ ስትመለስ ያቺ ዥንጉርጉር ቀለም ያላት ጭር ያለችዋን ዶሮ አባርሮ እንቁላሎቿን ሲሰባብር ደረሰችበት፡-

“እንዴ? ምን እየሆንክ ነው?” አለችው ቁጣዋ እየመጣ።

“እንቁላል ውስጥ ያሉትን ጫጩቶች እያስወጣሁዋቸው …” ይላል – በአስኳል የበጨጨ መዳፉን በእራፊ ጨርቅ እያፀዳ።

“ኧይ የልጅ ነገር! ከሳምንት በኋላ የሚፈለፈሉትን ባጭር ትቀጫቸዋለህ እንዴ?!”

“ብዙ ቀን እስኪሆን ድረስ ጫጩቶቹ እንቁላል ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ ታፍነው ይሞታሉ ብዬ እኮ ነው!”

“አጥፍተሃል አቦቸር” ከኩርፊያ ጋር።

“ዶሮዋ ናት ጥፋተኛ! እንቁላሏ ውስጥ ከትታ ከምታስጨንቃቸው፤ ላያቸው ላይ ከምትቀመጥባቸው፤ መጀመሪያውኑ ለምንድነው ጫጩቶቿን እንቁላል ውስጥ ከትታ የምትወልዳቸው?”

ኩርፊያዋ እየተገፈፈ ይመጣና እቅፍ አድርጋ ትስመዋለች።

“እናት ልጆቿን ታስጨንቃለች? አታስጨንቅም አይደል?!…”

አቤት ሀሳቦቹ ሲያዝናኗት!

ሌላ ልጅ የመጨመር ሀሳብ የላትም ‘ሃምሳ ቢወልዱ ሃምሳ ነው ጉዱ፤ ከተባረከ ይበቃል አንዱ’ …ማለትን ታዘወትራለች።

ልጇን ያልወደደ ባይወለድ ትመርጣለች። ከጎረቤቶቿ ጋር (‘ውሽማዬን ወሰድሺብኝ’፣ ‘ዶሮሽ ስጥ በተነብኝ’ በሚሉ ሰበብ አስባቦች) በተጋጨች ቁጥር እሷን ለማበሳጨት አቦቸር ላይ ይወርዱበታል። “… ይኼ ከየትኛው ቱቦ እንደፈሰሰ የማይታወቅ ቆሻሻ!” እያሉ።

አቦቸርም አንዳንዴ ያልተጠበቀና አስደማሚ ሀሳቦች ይመጡበታል።

“አንቺ እማ!” ይላል ቲቪ ሲያይ ቆይቶ ለምሳ ቤቱ ሲገባ።

“… እ?”

“…ለአለቤቾው ‘ባል የለኝም’ ብለሽ አልቅሰሽ ካስለቀስሺው አባት አያስመጣልኝም?”

“ከየት?” ብላ ትጠይቃለች፣ መገረም ልቧን እየሞላው!

“እኔንጃ” ይመልሳል – ውስብስብ ያለ ሂሳብ እንደሚያሰላ ተማሪ ፊቱን አኮምጭጮ!

… አቦቸር አባቱን አያውቅም። እናቱም አባቱን አታውቅም። አባቱም ልጁን የሚያውቅ አይመስልም።

“የኔታ ሁልጊዜ ቀን በቀን ይጠይቁኛል”

“የምን ጥያቄ ነው’ሱ?”

“‘የአባትህ ስም’ እያሉ ነዋ!”

“ምንትዋብ አትላቸውም?”

“ስላቸው ጊዜ ልጆች ይስቁብኛል። ‘የሴት ልጅ’ እያሉ! እነሱ ግን አባት ከየት ነው የሚያስመጡት? ስም ሲጠራ ያንቺን ስም ሲሰሙ የማያልቅ ሳቅ ስለሚስቁብኝ፣ ቆይቼ ቆይቼ ነው፤ ሁሉም ሰው ገብቶ ካለቀ በኋላ ለትምህርት የምገባው። እያልወደድኳቸው ነው። ለብዙ ልጆች ሀ- ሁ- ያስጠናኋቸው እኔ ነኝ። እንዳይረሳቸው አርጌ። ግን ይሳደባሉ። ስድብድብ ነው የሚያረጉኝ። እናደድና እደበድባቸዋለሁ” በእልህ ከንፈሩን እየነከሰ – በወሰደባቸው እርምጃ እየተደሰተ።

ምንትዋብ የሀሳብ መርከብ ይዟት ይሄዳል። በጥያቄ ባሕር ላይ እየተንሳፈፈች – በጥርጣሬ ካፒቴን እየተሾፈረች።

ይሄ ልጅ የማነው? የትኛው ወዳጄን ነው የሚመስል?!…

*  *  *

“ሸበላ ነበርኩ” ትላለች እናቱ። “ዳሌዬ ሲሞናደል የአልፎ አግዳሚውን ዓይን ጠልፎ የሚያስቀር። ተማሪ አልቀረኝ መምህር! ሎሌ አልቀረኝ ጌታ! ወታደር አልቀረኝ ኮለኔል! መነኩሴውስ ቢሆን?! ያላመላለስኩት ቀበቶ ታጣቂ አልነበረም” ትላለች … ስለ ትላንት በተወሳ ቁጥር።

“… ይህንን ሰፈር እንደ ጉድ ጭሰንበት አልፈናል፣ ተጫጭሰንበታል” ማለትን ታዘወትራለች ምንትዋብ።

“ኧረ? … !” ብሎ ወሬውን ላሟሟቀ “እንዴታ! የዚያን ዘመን ፍንዳታዎች ፍም ሆነው ይመጡና ‘የታለች ሉባንጃ? ልናጫጭሳት ነው’ ይላሉ ‘ሉባንጃዬ’ ነበር የሚሉኝ! በግሩም መዓዛዋ የሚወዳደራት የለም – ሉባንጃን እጣን። ውበት ብቻ አይደለም ዋናው ነገር፤ ውበት አይደለም ጠረን ነው። ጠረን ብቻ አይደለም ያልጋ ላይ ጨዋታ ነው”

ሠፈራቸውም ለየት ነው የሚል። ጥዋት ጥዋት ቃል ከሚገልጸው በላይ ሠፈሩ ፀጥ ይላል። ከሰዓት በኋላ ደግሞ ጭርታውን አስደንግጠው ለማባረር ሠፈርተኞቹ በአስነዋሪ ቃላት ይሰዳደባሉ።

ምድር ጥቁር ቆቧን አናቷ ላይ ከደፋች በኋላ ግን የሁሉም ምላስ ለስልሶ ፍቅርን ለማዜም የቸኮለ ይመስላል። አካባቢውም የገበያ ያህል ግርግር ይበዛዋል። ንግድ ይጧጧፍበታል። የሚያድንም የሚታደንም ሞልቷል። ማታ ማታ ያው የሚነገር አይደለም። በጨዋ አነጋገር ሆድ ጾሙን ውሎ እንዳያድር – ከማያውቁት ገላ ጋርም ቢሆን – አንሶላ ይጋፈፉበታል።

ይህን ይመስላል የእነ አቦቸር ሠፈር … (ከብዙ በጥቂቱ ይነገርለት ከተባለ)

“ምንትዬ…”

“እ?”

“ወደዛ እንዳታዪ …” አላት፤ ጎረምሶች ተሰብስበው አላፊ አግዳሚውን የሚለክፉበት ‘ድድ ማስጫ’ ተብሎ የሚጠራ ቦታ እያሳያት።

“ለምን ግን?” አለችው።

“ይለክፉሻል። ሸምሱ ሻይ ቤት ቁጭ ብለን ፊልም ስናይ … የመዐት ወንዶች የሚወዷትና እሷም ወደ መኝታ ቤት የምትወስዳቸው ሴት ያሳዩኝና፤ ‘እናትህን ትመስላለች’ ይሉኛል! አንድ ቀን ግን ተናድጄ ሌላ ሰው ሻይ በጠጣበት ብርጭቆ ቲቪውን ላንኮታኩተው ነበር”

“የጨዋ ልጅ እንዲህ አያደርግም”

“እነሱ ዝም አያስብሉኝማ! እኔን ሳትወልጂኝ በፊት፤ ቆንጆ የሆነችዋን ጄኔፈር ሎፔዝ የምትባለዋን አክተር ትመስይ እንደነበር፤ ለሁሉም እንዲሰማ ጮክ ብዬ ስነግራቸው፤ ጎረቤት እስኪሰማ ድረስ ሳቁብኝ። ‘ከመወለድህ በፊት እናትህን አይተሃት ነበር ወይ?!’ ይሉኛል። ባላይሽስ? እናቴ አይደለሽ እንዴ? ሳልወለድ በፊት ምን እንደምትመስይ ማወቅ ያቅተኛል?!”

“አያቅትህም” ትላለች፣ እናት ሳቋ እየመጣ።

“ፊልሙ ሳያልቅ ወጣሁላቸዋ! እነሱኮ ተሳድበው ተሳድበው እኔም ስሰድባቸው እቆይና ስድብ ሲያልቅብኝ ደግሞ ማለቅስ መስሏቸዋል…” ይላል፤ አቦቸር ብልጠት የሚታይባቸው ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ።

ቄስ ትምህርት ቤት ደረሱ።

“ይሄ ነው ትምህርት ቤታችን። እዚህ ሰፈር ካሉ ቤቶች አንደኛ አሮጌ የኛ ቄስ ትምህርት ቤት ነው” አለ ዘመም ወዳለና ጭቃ ወደተመረገበት ቤት ጣቱን ሰዶ እየጠቆመ።

“የአስተማሪህ ስም ማን ይባላል?”

የሰማት አይመስልም።

“‘በሰንበት የተፀነሰ’ ብለው አይስደቡት በያቸው። አንድ ቀን ከሌላ ሰው ጋር ሲያወሩ አጠገባቸው ቆሜ ነበር። አዩኝ አዩኝና በአለንጋ ዠለጡኝ። ‘ጆሮ ጠቢ’ ብለው ሰደቡኝ። እኔ ግን የማንንም ጆሮ ጠብቼ አላውቅም። ጆሮ ሲጠባ ግን አይጣፍጥም አይደል?”

ምንትዋብ ስትስቅ ቆየችና፣

“ምስጢር ስለሰማህኮ ነው እንደዚያ ያሉህ”

“እያልሰማኋቸው ነበራ!”

“ስማቸው ማነው?”

“የየኔታ?” ጠየቀ አቦቸር።

“አዎ የፊደል አስተማሪህ?”

“የኔታ ነዋ! ሌላ ስም አልወጣላቸውም። አንድ ቀን ግን ሰከሩና በጠላ ከበሰበሱ በኋላ፤ ‘ከእንግዲህ እኔ የዚህ ቄስ ተማሪ ቤት ዳይሬክተር ነኝ’ አሉን። ትንሽ ቆዩና ‘ምናችሁ ነኝ?’ ብለው ጠየቁን። አሁንም አሁንም ጠየቁን። ስንረሳ ገረፉን። ሌላ ቀን እንዳይረሳኝ፤ አስታውሺኝ እሺ?!”

የሕፃናት ድምፅ ይሰማ ጀመር።

ሀ – ሁ – ሂ – ሃ – ሄ – ህ – ሆ!

አ – ቡ – ጊ – ዳ – ሄ – ው – ዞ!

መልእከተ ዮሐንስ  . . . ወንጌል . . .

በአንድ ክፍል ውስጥ በተለያየ ዜማ የሚደመጡ ድምጾች።

የኔታ፣ የምንትዋብን ድምፅ ሰምተው ከመማሪያው ቤት ወጡ፤ የሚቋጩትን ነጠላ ይዘው። ጺማም ሽማግሌ።

ሁለቱም ሲተያዩ ደነገጡ። አቦቸርን ሊያስደነግጠው የቻለ ድንጋጤ። እናም ትንሽዬ ፊቱ ላይ ላብ ታየ። እየበዛ መጣ። የኔታ፣ ዓይናቸውን ዓይኑ ውስጥ እየፈለጉ ያሉ እስኪመስል ድረስ አዩት።

በቀስታና በቀዝቃዛ ድምፅ –

“ከስድስት ዓመት በፊት መሆኑ ነው? …” አሉ፤ “በበዓለ ጊዮርጊስ?! አይደል?” ብለው እናቱን ጠየቁ።

“ልክ ነዎት!” አለች ምንትዋብ፤ በመገረም አናቷን እየነቀነቀች፤ “ያኔ ዶሮ ማነቂያ ነበር ያለሁት”

*  *  *

ምንትዋብ፣ ነጠላዋን ለባብሳ አስፋልት ዳር ቆማለች። አልፎ አግዳሚውን ስትማትር ከሩብ ሰዓት በላይ አሳልፋለች። ሃምሳዎቹን ያጋመሱ የሚመስሉ አንድ ጠምጣሚ በአጠገቧ ሊያልፉ ሲሉ አየቻቸውና “አባ ያሳልሙኝ” አለቻቸው።

ቄሱ ጥያቄዋን ተግብረው ሊሄዱ ሲሉ፤

“እንዲያው ማስቸገር ባይሆንብኝ ያዘጋጀኋት ፀበል ጸዲቅ ነበረችኝ፤ እና እርስዎ ማዕዱን ቢባርኩልኝ . . .”

የቄሱ ምላሽ እምቢታ አልሆነም። ተያይዘው ወደ ምንትዋብ ቤት ሄዱ።

“ዳቦውን ከመቁረስዎ በፊት፤ መጀመሪያ ቤቴን ፀበል ቢረጩልኝ እንዴት ደስ ይለኝ ነበር? ጤናዬ መታወክ ከጀመረ ሰነባብቷል!” አለቻቸው “ሌቱን ደግሞ በቅዠት ነው የማሳልፈው!”

ፀበሉ ተዘገጃጅቶ መርጨት ጀመሩ። ሳሎኑ ተረጭቶ ሲያበቃ ‘መኝታ ቤቱም ይድረሰው’ አለችና መግቢያውን አመላከተቻቸው። መራቻቸውም።

“እንዲህ ያለ እምነት እያለሽ እንዲህ ባለ ርካሽ ቦታ መገኘትሽ ቅር ያሰኛል” ብለው መርጨታቸውን ሲቀጥሉ –

ምንትዋብ ከአልጋው ክፍል ወጣችና የመኝታ ቤቱን በር ዘጋችው።

የቤተክህነት ሰዎችን አትወዳቸውም። መሳቂያና መሳለቂያ ሲሆኑ ስታይ ነው ልቧ የሚረካው። በቀሳውስት ላይ የሚስቁ ጥርሶች እንዲበዙ ባደረገች ቁጥር አባቷን የተበቀለች ይመስላታል፤ አኗኗሯ እንዲበላሽ ያደረገውን አባቷን።

ቄሱ የበር መቆለፍ ድምፅ ሰምተው ዘወር ሲሉ ብቻቸውን ናቸው። መገረም ልባቸውን ገዛው።

“የኔ እህት . . .”

ዝም።

“የቀረኝ ቦታ የለም፤ ሁሉም ቦታ ረጭቼልሻለሁ”

ዝም።

“የኔ እህት … ምን እያደረግሽ ነው?”

“አንድ ያጠፉት ጥፋት አለ – ዋስ ካልጠሩ ልፈታዎ አልችልም!”

“እንዴ? ምነው? ምን አጥፍቼ? ማንን በድዬ …” ይለምኗት ገቡ።

“ምነው የሔዋን ልጅ? ምነው የእመብርሃን እህት? እንዲህ ያለውን እኩይ ሀሳብ ያሳደረብሽን መንፈስ ‘እክሕደከ’ በይው? … ምነው ልጄ ምን በደልኩ?… ሰተት ብዬ ተከትዬሽ ቤትሽን ፀበል ከመርጨት በቀር?”

“የሚያውቁት ሰው ካለ – ዘመድዎ ወይ የንስሐ ልጅዎ – ደውዬ ልጥራውና ባስጠሩት ሰው ፊት ሐጥያትዎን እናዘዛለሁ”

“የቅርብ ዘመድ ከየት አባቴ ልውለድ? ለራሴ በገንዘብም በዘመድም ምንም የሌለኝ መናጢ! በኪሴ ውስጥ ድር ማድራት ከጀመረ ስንትና ስንት ቀኑ!”

“እንግዲህ የሚበጅዎትን ለመምረጥ ምርጫው በእጅዎ ነው”

“የማይመስል ነገር መጠየቅሽ ነውር አይሆንብሽም የኔ እህት? ኧረ የማይሆን ቀልድ ይዘሻል…”

“ፍላጎቴን ካላሟሉ ያለ እህል ውሃ እንደተከረቸመብዎ ይቆያሉ”

“ኧረ ልጄ!…”

የቄሱ ተማፅኖ እየበረታ ሲመጣ ልቧ ሐሴት እያደረገ ነበር።

ቄሱ በሆነው ነገር እየተደናገጡ፤ ህልም እንዲሆንም እየተመኙ አንድ ነገር ተናገሩ።

“ይኸውልሽ! አሁን የምልሽን የምትፈጽሚ ከሆነ የምትፈልጊው ነገር በእጅሽ ይገባል” አሏት፤ እልህ ተናንቋቸው።

“ምን ይፈለግብኛል?” ተረጋግታ ጠየቀች። የቄሱ መርበትበት ምንትዋብን ደስ ማሰኘት ቀጥሏል።

“የምሰጥሽን ቁጥር ልብ ብለሽ ስሚ። ማሙሸት የሚባል የወንድሜ ልጅ አለ – ማሙሸት የሚባል! ስልኩን ሲያነሳ የዚህን ሠፈር ቤትና ትክክለኛ አድራሻ ስጪውና እንዲያገኘኝ አድርጊ!”

ማሙሸት ተደውሎለት መጣ።

“አጎቴ ምን ሆኗል?” አላት ተደናግጦ።

“በእዳ ተይዘው ነው። ‘በነፃ የተሰጣችሁን በነፃ ስጡ’ ይላል መጽሐፉ ብለው አልከፍልሽም አሉኝ”

“የጠጣበትን?!” አለ ማሙሸት።

“አልኮል እንኳ በአፋቸውም ደጅ አልዞረ!”

“ታዲያ የምን እዳ ነው ያለበት?”

“እንደዚህ ላለው ቀላል ጥያቄ መልስ መስጠት አለመደብኝም”

“ስትዪ …”

“መኝታ ቤት አልጋዬ ክፍል ገብተው አይደል ያገኘሃቸው? ምን ሲሰሩኝ የቆዩ ይመስልሃል?”

ቄሱ ድምፃቸውን አሰሙ። “ኧረ አንች ሴት ጡር ፍሪ! ምንድነው እንዲህ የሚያወሻክትሽ? ይኸውልህ ልጄ ነገሩ እንዲህ ነው…” አሉና ከመጀመሪያው ጀምረው ይተርኩለት ገቡ።

ይህ ሁሉ ሲሆን የተዘጋባቸው በር አልተከፈተም። በማሙሸት ፊት ላይ የማመንም ሆነ ያለማመን ነገር አይታይም። “ስንት ብከፍልሽ ነው አጎቴ ነፃ የሚሆነው?” አለ ኪሱን እየደባበሰ።

“ሃያ አምስት ብር ከሰባ አምስት ነው እሺ ያልኳቸው”

“ሰባ አምስቷ ደግሞ ምንድን ናት?”

“አንተን ደውዬ የጠራሁበት ነዋ! ሴት ካገኘሁ ቆይቻለሁ ብለው አስተዛዝነው ባይነግሩኝ ኖሮ ለሃያ አምስት ብር ብዬ …”

ቄሱ የርግማን ዶፍ ያዘንቡባት ጀመር። ወጡ።

አመሻሽ ላይ ቄሱ ራሳቸውን ለውጠው የተከፈለበትን ገላ ሊጎበኙ ሞቅ ብሏቸው መጡ።

* * *

ይህ ሁሉ ከሆነ ስድስት ዓመት አልፎታል። በማግስቱ የቄስ ትምህርት አልነበረም። በማግስቱ ማግስትም እንዲሁ … ሳምንት … ወር …ትምህርቱ ተቋረጠ። ለምን ቢባል የፊደል አስቆጣሪውን ዓይን አየሁ የሚል በመጥፋቱ።

አንድ ቀን ምንትዋብ “ያ ነገር እኮ አጣርቼ ደረስኩበት” አለችው አቦቸርን።

“የቱን?!…”

“የየኔታን ስም …”

“ማን ነው?”

“ገብረ መስቀል” አለች – እያንዳንዱን ፊደል ረገጥ አድርጋ።

ጭቃማ ወራት አለፉ። … ወደ ት/ቤት ሊመዘገብ ስትወስደው “ምንቴ …” አለ አቦቸር፤ በአዲሱ ሹራብ የእጅ ጫፍ ንፍጡን እየጠረገ።

“እ?”

“አንደኛ ክፍል ተመዝግቤ ስማር – አጠገቤ አስተማሪ የሚያስቀምጣቸው የማላውቃቸው ልጆች ‘የጨርቆስ ሠፈር ልጅ ነህ ወይ?’ ሲሉኝ፤ ‘አይደለሁም’ ነው አይደል የምለው?”

“ለምን? ‘ነኝ’ በል እንጂ!” ትላለች እናቱ፤ የሠፈሩን ስም የሚያስክድ ምን ተገኘ ብላ …

“ያበሽቁኛላ!”

“እነማን?!…”

“የጨርቆስ ሠፈር ያልሆኑ ልጆች”

“ምን ይሉሃል?”

“እንግዳ ሲመጣባችሁ የፎቶ አልበም ከጎረቤት ተውሳችሁ ነው ለእንግዳ የምታሳዩት ይሉናል። ምንቴ …” አላት ዓይንዋን ቀና ብሎ እያየ።

“አንድ ልጅ ደግሞ ምን አለኝ መሰለሽ? ‘የእናንተ እናቶች – አስራ ሁለት እስኪሞሉ ድረስ ይሰባሰቡና – ባለ ሁለት ብር ከአርባ አልበም ይገዛሉ። ከገዙ በኋላ ያዋጡ ሰዎች ሦስት ሦስት ፎቶ ያመጡና ይከቱበታል። ከዚያ እሁድ እሁድ እጣ የወጣለት ሰው እስከ ሳምንት ድረስ አልበሙን ቤቱ ይወስደዋል’ ብሎ እየሳቀ አበሸቀኝ”

“ሲያበሽቁህ አትብሸቅላቸው እሺ?!”

“ብሽሽቅ አስለምጂኛ! እንዳልበሽቅላቸው። … አንዳንዴ እንባ ያስመጡብኛል። አንድ ቀን ጋዜጣ ገዙና እኔን የማይመስል ሥዕል አዩና – ትላልቆች ናቸው እኮ! – ሲጋራ አስገዝተውኝ፣ መልሱን ውሰደው እንዲሉኝ ብዬ አጠገባቸው ስቆም፤ በጋዜጣው ላይ ሥዕል አዩና ‘አቦቸር ይኸውና’ ብለው የተጻፈ ነገር አንብበው አሳቁብኝ”

“ምንድነው ያነበቡት?”

“ሥዕሉን አይተውኮ ነው። አስተማሪው ባዶ ቦታዎችን ሙሉ ብሎ ጥያቄ ጠየቀ። ‘እናቴ ውሃ ጠጣች ካለ አባቴ ክትፎ  ’ ተብሎ ሲጠየቅ፤ ዳሽ በሚለው ቦታ ‘ክትፎ ናፈቀው’ ብሎ መልሱን ጻፈ ብለው ያላልኩትን አስወሩብኝ”

“ኧይ አቦቸር! ዛሬ በሳቅ ልታፈርሰኝ ታጥቀህ ተነስተሃል” አለች ምንትዋብ።

በልጇ ስም የሚቀለዱ ቀልዶች እየበዙ በመምጣታቸው አትቆጭም። ይልቁንስ -ትንሽ ትልቁ – ሴት ወንዱ ከአፉ የሚወጣውን ቃል ለመስማት ጆሮዎች ሲቀሰሩ ስታይ ደስ ይላታል።

“‘አባቴ ክትፎ በላ’ ነው መልሱ እሺ”

“አባቴ ክትፎ በላ ብዬ ስመልስ፤ ውሸታም ተብዬ በአለንጋ አልዠለጥም? አስተማሪያችን አያስበረክኩኝም?”

“ይጨበጨብልሃል”

ትንሽ ቆይቶ “አባቴ ክትፎ ነበር የሚበላው?” አለ ምራቁን እየዋጠ። “አንቺን ያስበላሽ ነበር? ወይስ ውሃ ብቻ እያስጠጣሽ ክትፎ ያስናፍቅሽ ነበር?”

“ማን?”

“አባቴ ነዋ! የማላውቀው አባቴ”

የምትመልስለት ስለማይኖራት ያልሰማች መስላ ፊቷን ታዞርበታለች። ረዣዥም ሳሮች የሞሉበት ግቢ ውስጥ ሕፃናት ይሯሯጣሉ። አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው።

እናት ከልጇ ጋር ሆና ስትጠባበቀው የነበረው ሰልፍ አልቆ ተራዋ ስለደረሰ ወደ ውስጥ ገባች።

“ስም? . . . ” ተነገራት ለመዝጋቢዋ።

“የአባት?”

አቦቸር ‘ምንትዋብ’ የሚል ጠበቀ፤ ግን አልሆነም።

“የአባቱ ስም?!” መዝጋቢዋ ዝምታ ሲበዛ መልሳ መጠየቅ ግድ ሆነባት።

“ገብረመስቀል” ኩራት በበዛበት ድምፅ ምንትዋብ መለሰች። ቀና ብሎ እናቱን አየ። በፈገግታ ጠይም ፊቱን አበራው።

እንባው መጣ።

ያ ቀን – ፀሐይዋ በደመና ሳትጋረድ … በሚርከፈከፈው ካፊያ መሃል … ትናንሽ እግሮቹን እያሮጠ … ለበርካታ ሕፃናት (ለሚያውቁትም ለማያውቁትም) የጨዋታው ርዕስ ይሄ ሆነ።

‘አባቴን እኮ አገኘሁት’ እያለ – ‘የኔታ ገርበመስቀል ይባላል’ እያለ –

‘ደስ የሚል የሚያሳምም ቁስል የሚያስመጣ አለንጋ ነበራቸው’ እያለ – ‘ደስ ደስ የሚል እናቴን የሚያናድዳት ስድብ ይሰድበኝ ነበር’

እያለ … እያለ … እያ … እ …

በእንዳለጌታ ከበደ

(1995 ዓ.ም)

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

[ምንጭ] – “ከጥቁር ሰማይ ስር” (፲፱፻፺፮)፤ ገጽ 39 – 64።

.

[ምስል] – በዕውቀቱ ሥዩም።

 

8 thoughts on ““በሰንበት የተፀነሰው” (ልብወለድ)

  1. “አንድ ቀን ከሌላ ሰው ጋር ሲያወሩ አጠገባቸው ቁሜ ነበር አዩኝ አዩኝና በአለንጋ ዠለጡኝ ጆሮ ጠቢ ብለው ሰደቡኝ እኔ ግን የማንንም ጆሮ ጠብቸ አላውቅም ጆሮ ሲጠባ ግን አይጣፍጥም አይደል” … ቂቂ አይ አቦችር

    Like

  2. በጣም ደስ የሚል ድርሰት ነው። ልጅነቴን፣ የኖርኩበት ማህበረሰብ፣ የእውቀት በኩራታችንን ያቋደሱንን የኔታና በትራቸውን አስታውሶኛል።

    Like

Leave a reply to kelali Cancel reply