“የጃፓን ባህል ቅኝት”
ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ
(1924 ዓ.ም)
.
የጃፓን አገር ቀስት መስሎ ከምሥራቅ ወደ ሰሜን ምዕራብ በቀጭኑ የተዘረጋና የተከፋፈለ ደሴት ነው። እየዞርን ያየናቸው አውራጃዎች ሁሉ የሚበዙት ተራራሞች ናቸው። በየተራሮቹም ቄድሮስ (Cedar) የሚባለው ዛፍና ሌላም ልዩ ልዩ ዛፎች በብዙ ይታያሉ። ስለ ተራሮችም ብዛት ትልልቆች ወንዞች ሞልተዋል። ስለዚህም በየዘብጡ መሬት ሩዝ ለመዝራትና ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶች ለመትከል ይመቻቸዋል።
አሁን እኛ ወደ ጃፓን በደረስንበት ወራት የሩዝ አጨዳ ነበር። ስለ መሬቱም እርጥባምነት የታጨደው ሩዝ እንዳይበሰብስ በየነዶው እያሰሩ ረጃጅም እንጨት በባላ እያጋደሙ እንደ ሥጋ ቋንጣ ይሰቅሉታል እንጂ በመሬት ላይ አይከምሩትም። አንዳንዱም በገመድ እያሰሩ በየዛፉ ላይ ያንጠለጥሉታል።
እኛ በዞርንበት በጃፓን ምዕራብና ደቡብ በግና ፍየል ሌላም የቀንድ ከብት በዱር ተሰማርቶ የሚበላ አላየንም። ምናልባት እነዚህን የመሰሉት እንስሶች የሚረቡት በጃፓን ምሥራቅና ሰሜን ይሆናል እንጂ ባገሩ ውስጥ በግና የቀንድ ከብት የለም ለማለት አይቻልም።
በጃፓን አገር በያውራጃው የሚከበረው በዓል ብዙ ነው። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ የገብርኤል፣ የራጉኤል፣ የጊዮርጊስ፣ የተክለ ሃይማኖት፣ የገብረመንፈስ ቅዱስ ታቦት ባለበት አገር በየሰበካው እንደሚከበረው ነው። አሁን የምጽፈው ግን በመላው ጃፓን አገር የሚከበረውን ትልልቁን በዓላት ብቻ ነው። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ መስቀል፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ፋሲካ እንደሚባለው ነው።
ኅዳር 23 ቀን የሩዝ መከር በዓል ነው። በዚህም ቀን ከሩዙ ጥቂት ጥቂት እየያዙ ወደ ሽራይን (Shrine) እየሄዱ እንደ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበት ቀን ነው። በቤተ መንግሥቱም ከአዲሱ ሩዝ የሚቀመሰው በዚሁ ቀን ነው።
ጥር 1 ቀን የዘመን መለወጫ በዓላቸው ነው። የካቲት 3 ቀን የክረምት ማጋመሻ በዓል ይባላል። በዚህም በዓል ቤተ ዘመዱ ሁሉ በየቤቱ እየተሰበሰበ ቆሎ እየተቆላ ቆሎውን እየዘገነ ‘ሰይጣንና ክፉ ነገር ውጣ’ እያለ ወደ ውጭ ይበትናል። ‘ሲሳይና ጤና ወደ ቤት ግባ’ እያለ ወደ ቤት ውስጥ ይበትናል፤ የተረፈውንም ይበሉታል። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ በየባላገሩ ለእንቁጣጣሽና ለግንቦት ልደታ እንደሚደረገው ነው።
መጋቢት 3 ቀን ‘ያሻንጉሊት በዓል’ የሚባለውን ያከብራሉ። በዚህም ቀን ከነገሥታቱ ልጆች ጀምሮ እስከ ሕዝቡ ድረስ ያሉት ሴቶች ልጆች ዋጋው ውድ የሆነ አሻንጉሊት እየገዙ ለንጉሠ ነገሥቱና ለእቴጌይቱ፣ ለሚኒስትሮችና ለመኳንንቶች፣ ለየትልልቁም ሰው ሁሉ እየወሰዱ ይሰጣሉ። ይኸውም እየተሰበሰበ እንደ አንቲካ በክብር እየሆነ ይቀመጣል። ባገራችን በኢትዮጵያ ሴቶች ልጆች ለእንቁጣጣሽ እንግጫ፣ ለመስቀል ደግሞ አበባ እየወሰዱ ለየትልልቁ ሰው እንደሚሰጡት ነው።
ግንቦት 5 ቀን ‘የባንዲራ በዓል’ ይባላል። ይኸውም በሙሉ በጃፓን አገር ይከበራል። በዚህም ቀን ወንዶች ልጆች ሁሉ የልብስ፣ ያላገኙም የወረቀት ባንዲራ እያበጁ ይይዛሉ። የወረቀት ባሎንም እያበጁ ወደ ሰማይ ይወረውራሉ። ደግሞ ካንዱ ቤት ወዳንዱ ቤት ገመድ እየተዘረጋ የወረቀት ባንዲራ ይደረደራል። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ በየቆላው አገር ሁሉ ወንዶች ልጆች የማሽላ አገዳ (አሜራ) እየላጡ በክር እየሰኩ አላማ እያሉ ለከተራ ታቦት ሲወጣ እየያዙ ወደ ጥምቀተ ባሕር እየወረዱ በማግሥቱ ታቦት ሲመለስ ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያኖሩት ነው።
ሐምሌ 13 ቀን የሰው ሁሉ የሞቱት ዘመዶች ነፍሳት መታሰቢያ በዓል ነው። በዚሁም ቀን የሞቱት መቃብራቸውንና የድሮ ቤታቸውን ይጎበኛሉ ይባላልና ሕያዋኑ ዘመዶቻቸው የመቃብሩን ስፍራ ሁሉ ንጹሕ ያደርጋሉ። ቤታቸውንም ሁሉ ያስጌጣሉ። ድግስም እየተደገሰ በየመቅደሱ ይላካል። ካህናቱም ጸሎት ያደርጋሉ፤ በየደጃቸውም ላይ ነፍሳትን ለመቀበል የጪስ እንጨት ያጨሳሉ። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ ክብረ ቅዱሳን ተዝካረ ሙታን እንደሚባለው ነው።
በተረፈ በሽንቶ ሽራይንም በቡድሃ መቅደስም አንዳንድ የቅዱሳኖቻቸው በዓላት ይከበራሉ። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ ታቦት በተተከለበት ስፍራ ሁሉ የታቦቱን በዓል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆኑ የሰበካው ሕዝብ ብቻ እንደሚያከብሩት ነው።
በጃፓኖች ቤት ሁለት ዓይነት መብል ይዘጋጃል። አንደኛው ዓይነት ያገራቸው መብል፣ ሁለተኛው ዓይነት የአውሮጳ ወጥ ነው። የአገራቸው መብል ከአታክልት፣ ከዓሳ፣ ከሥጋ፣ ከሩዝ የሚሰናዳ ነው። ዳቦ ወይም ሌላ ዓይነት እንጀራ የለም። መብሉ ለስላሳና ጣፋጭ ነገር ነው። ለውጭ አገር ሰው እጅግ ደስ አያሰኝም። የዓሳና የዶሮ ሥጋ ኮምጣጤ የሚመስል ከቅመም የተሰራ መረቅ ቀርቦ በዚያ እየተነከረ እርጥቡን ይበላል።
መብል ሲቀርብ ለያንዳንዱ ሰው በተለየ እቃ ነው እንጂ ለብዙ ሰዎች ባንድ እቃ አይቀርብም። ወጡም በትንንሽ ሳህን ለየብቻው እየቀረበ ባለቤቱ እየመረጠ ይበላል። የሚበላውም በማለፊያ ሆኖ በታነጸ በሁለት ድብልብል እንጨት (Chopstick) እየተጣበቀ ነው እንጂ እጅ አይነካውም። ጌታ ጌታው ከዝሆን ጥርስ የተሰራ ማጣበቂያ አለው።
የጃፓን ነገሥታት ታሪክ በጣም የሚያስደንቅ ነው። መጀመሪያ በጃፓን የነገሠው ‘ጂሙ ቴኖ’ ይባል ነበር። ‘ቴኖ’ ማለት በቋንቋቸው ንጉሠ ነገሥት ማለት ነው። ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩትን የነገሥታቱን ስም ሲጠይቋቸው “አማልክት ይገዙን ነበር” ይላሉ። ትርጓሜው ግን ታሪኩ አልተገኘም አልታወቀም ማለት ይመስላል።
የዚህ ንጉሥ ዘር ከወዴት የመጣ ነው ሲሏቸው “ፀሐይ ‘አማቴራሱ’ የተባለች ሴት ልጅ ነበረቻትና ከእሷ ዘር የመጣ ሰባተኛ ትውልድ ነው። ፀሐይም አምላክ ናትና ነገሥታቶቻችን የአምላክ ልጆች ስለ መሆናቸውና ሰውነታቸው የተቀደሰ ስለ መሆኑ እንሰግድላቸዋለን” ይላሉ። ምናልባት ይህች ‘አማቴራሱ’ ያሏት እኛ ሔዋን የምንላትን ይሆናል።
ይህም ልማድ በጃፓን አገር ብቻ አይደለም። ነገር ግን በቀድሞ ዘመን በምሥራቅ አገር፣ በባቢሎንና በፋርስ፣ በህንድም በሽንም የነበሩ ሰዎች አምላካችን ፀሐይ ነው እያሉ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። ባገራችን በኢትዮጵያም ምንም እንኳን በብሉይ ኪዳን ተጽፎ ባናገኘው ካባቶቻችን ቃል ለቃል ተያይዞልን እንደመጣው ታሪክ አብርሃም እንደ አባቶቹ በፀሐይ ለማምለክ ኅሊናው እምቢ ቢለው “አምላከ ፀሐይ ተናበበቢ (የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ)” አለ ይባላል።
በጃፓን አገር ነገሥታቱም የፀሐይ ልጆች ናቸው እየተባሉ በታላቅ ክብር እየተከበሩ ይሰገድላቸዋል። ከቀድሞ ካባቶቻቸው ጀምሮ እንደ ዘውድ እየተወራረሰ የመጣላቸው ያልማዝ ቀለበታቸውና ሰይፋቸው፣ መስተዋታቸውም እንደ ንዋየ ቅድሳት ይቆጠራል። የሰውነታቸውም መከበር ይቅርና ፎቶግራፋቸው በታየ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይሰግዳሉ።
ስለ ክብሩም ማንም ቢሆን የንጉሠ ነገሥቱን ፎቶግራፍ ደፍሮ በቤቱ የሚሰቅል አይገኝም። ለየትልልቅ ሰዎችም እንደ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ እንደሆነ በትልቅ የብረት ሳጥን ውስጥ እያገቡ ቆልፈው ያስቀምጡታል። በውጭ አገርም ለተሾሙት የጃፓን አምባሳደሮችና ሚኒስትሮች የተሰጠ እንደሆነ ነፋስ እንዳይነፍስበት፣ ትቢያ እንዳይበንበት፣ የእሳትም አደጋ እንዳያገኘው እየተባለ በብረት ሳጥን ውስጥ ይቀመጣል እንጂ በሌጋሲዮኑ አይሰቀልም። ያለፈቃድም ፎቶግራፉን ኮፒ ለማንሳት አይቻልም።
ይህም በእኔ በራሴ ደርሶብኛል።
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መልእከተኛ ስለ መሆኔ የጃፓን ንጉሠ ነገሥትና እቴጌይቱ ፎቶግራፋቸውን እየፈረሙ ሰጥተውኝ ነበር። ያገሩንም ሕግ ሳላውቅ ወደ አንድ ሠራተኛ ወስጄ “ይኸን ፎቶግራፍ ኮፒ አንስተህ በመጽሐፍ የሚገባ ክሊሼ ስራልኝ” ብለው ፎቶግራፉን ተቀብሎ አይቶ፣ “የተቀደሰውን የንጉሣችንን ፎቶግራፍ ክሊሼ ለመስራት ከግርማዊነታቸው ልዩ ፈቃድ ካላገኘሁ አልችልም” ብሎ ፎቶግራፉን መልሶ ሰጠኝ።
የዛሬው የጃፓን ንጉሥ ነገሥት የእንግሊዝና የፈረንሣዊ ቋንቋ ያውቃሉ። ነገር ግን የኦፌሴል ጉዳይ የሆነውን ሁሉ በአስተርጓሚያቸው ካልሆነ በቀር አውቃለሁ ብለው በውጭ አገር ቋንቋ አያነጋግሩም።
ይኸውም የጃፓንን ቋንቋ ለማስከበር የተደረገ ይመስላል።
.
ኅሩይ ወልደሥላሴ
(1924 ዓ.ም)
.
[ምንጭ] – “ማኅደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን”። ፲፱፻፳፬። ገጽ ፻፴፭-፻፶፭።