ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን

ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን

(ሂሳዊ ንባብ)

በተአምራት አማኑኤል

(1926 ዓ.ም)

.

የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይን “ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን” የሚባለውን መጽሐፍ ባነበብሁ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ ውጭ ያለውን አገራችንን (ተማሪ ቤት፣ ስልክ፣ ባቡር የሌለበትን)፣ እንኳንስና ከውቅያኖስ ማዶ ያሉትን አገሮች የኢትዮጵያን ወሬ የማያገኝበትን ወረዳ ነው ያሰብሁ።

እኒህን ቃላት ለመጻፍ ያነሳሳኝም ለተራበ ሕዝብ ጐተራውን ከፍቶ እህሉን እንደሚናኝ ባለጸጋ፣ ደራሲው ያዩትን የሰሙትን ያወቁትን ላገራቸው ልጆች ለማካፈል የጻፉትን መጽሐፍ በሩቅ አገር የሚኖሩት አንባቢዎች ወሬውን እንዲሰሙት፣ ሰምተውም መጽሐፉን እንዲያነቡት ስል ነው እንጂ “ሰብሕዎ ለኅሩይ” ለማለት አይደለም።

ይህን ብል ኃጢአት ኑሮበት አይደለም። ነገር ግን አመስጋኝ ያላጡትን ሰዎች፣ ይልቁንም ከቤተ መንግሥት ከፍ ካለ ማዕረግ የደረሱትን ሰዎች፣ በሚገባቸው ጊዜ ስንኳ ቢሆን እነሱን ማሞገስ (ያውም በጋዜጣ) ከከንቱ ድካም እቈጥረዋለሁ። “ሥራህ ጥሩ ነው አይዞህ በርታ ግፋበት” የሚባል እግር እንዳልተከለ ልጅ ታቴ የሚለውን ድኃ ነው።

በዓለም አንድ ተብለው ከሚቆጠሩት ቅኔ አዋቂዎች ፍሪዱዚ ያገሩን የፋርስን ነገሥታት ታሪክ “ሻ ናሜ” ብሎ ሰይሞ በግጥም ጽፎት መጽሐፉ በፈረንሣይ ቋንቋ በተተረጐመበት ዘመን ስለዚሁ መጽሐፍ አንድ የፈረንሣይ ደራሲ ጋዜጣ ሲያወጣ እንዲህ ይላል፣

“አንዳንድ ጊዜ ደጅ መውጣት ያላዩትን አገር ማየት ደግ ነው፤ አእምሮህን ያሰፋልሃል። ከማን አንሳለሁ የሚያሰኝህን ተራራ የሆነውን ትዕቢትህን አንስቶ ከመሬት ያፈርጠዋል። ካገርህ ሳትወጣ ከቤትህ ተሸጉጠህ ትልቅነት ገናናነት አንደኛ ነው እንጂ የምትለው አሳብህ ሁሉ ምስኪን መሆኑንና የሌላውን ነገር ሁሉ ልኩን የምታገኘው ደጅ ስትወጣ ነው።”

ዋና ሰው ነኝ እያሉ በሚመናቸኩበት ሰዓት ትዕቢትን ለማብረድ ስለ ፋርስ ስለ ሺን አገር መንገደኞቹ የጻፉትን መጽሐፍ ከማንበብ በቀር ሌላ መድኃኒት አይታየኝም። ያውልህ እልፍ አእላፋት ሕዝብና ነገድ ወሬህን ሰምተው የማያውቁ ለወደፊቱም ዜናህን ሳይሰሙት እድሜያቸውን የሚያሳልፉ ወሬህን ባለመስማታቸውም ጠጠት የማያድርባቸው … ያንጊዜም በገዛ እጅህ እንደ ፈላስፋው ብሌዝ ፓስካል “ስንትና ስንት መንግሥታት ሳያውቁ ይኖራሉ” ከማለት ትደርሳለህ።

አዲስ አበባን ቅሉ ካላዩት ካንዳንድ ያገሬ ልጆች መኳንንትና ወይዛዝር (እንጀራና ሹመት መሳይ ካላቸው ሰዎች ጋራ) ስነጋገርበት በነበረ ጊዜ እኒህ ሰዎች ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያለው ፍጥረት ሁሉ ያወቃቸው፣ የሚኮሩበትን አባትና ሹመትም ዓለም ሁሉ የተረዳላቸው ይመስላቸው እንደነበረ ስላየሁት ነው። ከዚህ በላይ ያለውን ቃል የጠቀስኩ ከጐንደር ተነሥታ ባምብሎ ስትደርስ “ትግሬ ማለት ይኸ ነው?” አለች እየተባለ ባንዲት ሴት ወይዘሮ ሲተረት አውቃለሁ።

በውነት እብድ ይመስል ሰው ሁሉ ቤቱን እየጣለ ይዙር ይንከራተት ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ካለበት ሁኖም ትምህርቱ ይስፋ፣ “ጌታ ነኝ ወይዘሮ ነኝ ጀግና ነኝ” የምትለው ሁሉ ተማር … ትምህርትህ ጌትነትህን ውይዝርናህን ጀግንነትህን አያጐልብህም። ይህ ሁሉስ ቢቀር ከትምህርት የበለጠን መሰለህ? “ጉልበት ማለት እውቀት ነው” ይሉሃል ላቲኖችና እውቀትን አታጐጥጠው እባክህ።

አሁንም “ማኅደረ ብርሃን” መጽሐፋቸውን አንብብና ብዙ ሳትደክም አንገረብን ሳትሻገር በብዙ ደስታ ከምድር ዳር ደርሰህ ትመለሳለህ። ደራሲውን ተከተላቸው … በባሕሩ በየብሱ በተራራው በደሴቱ ይመሩሃል። ተግተህ ከሰማሃቸውም ከቤትህ ሳትወጣ ጃፓን ርስት ልታካፍል ስንትም አይቀርህ። “እሳት ተነሳ፣ ቋያ ተቃጠለ” ስትል ቅጠለ-ቀይ ዛፍ ነው ይሉሃል፤ “ጥጥ ነው አመልማሎ ነው” ስትል ነጭ አበባ ነው ይሉሃል።

“እሺ ይሁን” በላቸው … ቀሚሱን እስከ እግር ጣቱ ሰዶ ወንዱንም ሴቱንም በቶኪዩ ጐዳና ድምቡል ድምቡል ሲል ያሳዩሃል። እንዲህ አስተዋውቀውህ ከቤቱ ሲወስዱህ ተንበርክኮ ይቆይሃል፤ “ንበር ሊለኝ ነው ሊነሳልኝ ነው” ስትል ፍግም ብሎ መሬት ይስምልሃል። አደግድግ አንተም … እንዳገርህ ‘ክበር ተከባበር’ ነውና እጅ ንሳ።

ከዚያ አልፈህ ከነቡዳሃ ከነሽንቶ ሽራይን (መቅደስ) ስትገባ አልባሳታቸው ብቻ የሚያስገርምህ ካህናትንና ደናግልን ሲያለዝቡ ሲያመረግዱ ታገኛለህ። አንተም አሸብሽብ … በሞቱ ከምድር አድማስ ነው ደርሰህ ያለ። ደራሲው በጠራ በማይሰለች አማርኛ ንግግር፣ አጭር ሳለ ብዙ ፍሬ ነገር በያዘ ቃል ያዩትን የሰሙትን ነገር ሁሉ ይነግሩሃል። ጃፓን ከተባለ እስከዛሬ ድረስ ያለውን ታሪኩንና ሕግጋቱን ሃይማኖቱንና ሥርዓቱን ይገልጹልሃል። ታሪኩ ይሰለችህ እንደሆነ ዝም ብለህ ተከተላቸው።

በኢትዮጵያና በጃፓን ሰንደቅ ዓላማ ተጋርደህ በሕዝብና በተማሪ ታጅበህ “ባንጃሂ ባንጃሂ” እየተባለልህ የደስታ ውካታና ጭደራ እየቀለጠ በየት አለፈ እስቲ እንየው እየተባልህ በብዙ ደጅ ጥናት ከማታገኘው ከነገሥታት እልፍኝ ያገቡሃል። መሳፍንቱና ወይዛዝሩ፣ የውስጥ አሽከሮቹና ደንገጥሮቹ ገና አይተው ሳይጠግቡህ እጅ ነሥተህ ዘወር በል። ለራት ለምሳ ግብዣ ተጠርተሃልና ካንዱ ሁሉ ግንብ መግባት አለብህ።

ከዚያም ከፍራሽ ላይ እየተዘናፈልክ፣ ክራር እየተመታልህ ባንድ እጅህ ሳኬ የሞላበትን ጽዋህን ጨብጠህ፣ ሹል ሁኖ አጊጦ በተበጀ ዝሆን ጥርስ (ወይም ድብልብል እንጨት) እየያዝህ ልጃገረዶች የሚያቀርቡልህን ምግብ ኮምኩም። ጃፓን እንግዳህ ቢሆን አንተም ለጃፓን ብርቁ ነህና ብዙ የምትጠይቀው አለብህ። አንተም በተራህ ጠይቅ። የጃፓን ሕዝብ ከባለጌነት በጣም የራቀ ጨዋ የጨዋ ልጅ ነውና በጠየቀኸው ሁሉ በፍቅር በማክበር ይመስልሃል።

ያገሩ፣ የወንዙ፣ የሰዉ ስም ላንደበትህ የቸገረ ፍጹም ግራ ሁኖ ይታይሃል። ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ወድያው ይለመድሃል። የሃይማኖቱ አሳብ እንግዳ ይሆንብሃል – ላንተ እንግዳ ይሁንብህ እንጂ ደራሲው ከሰሎሞን ጋራ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ይሉሃል። ይህን ብለውም አይቀሩ ጃፓን በሃይማኖቱ ሰማንያ አሐዱን ከተቀበለ ሕዝብ ጋራ በብዙ ነገር እንዲስማማ ያስረዱሃል። መጽሐፋቸውን አንብብው። ካነበብኸው ጃፓንን አየኸው ያዝኸው ጨበጥኸው።

ጃፓን ሥራ ወዳጅ ነው። በፋብሪካ የሚሠራው ወንዱም ሴቱም በሚሊዮን ነው የሚቆጠር። የሠራውም እቃ ከብዛቱ የተነሳ ገበያ አልበቃው ብሎ መድረሻ አጥቶ ተቀምጧል። ጃፓን ጀግና ነው። እንኳንስና ሊሰጋ ሕዝቡ ሰላማዊ ነው እንጂ እንዳይመጣብን እያሉ የሚፈሩት አይጠፉም። ጃፓን ብልህ፣ ቁም ነገረኛ፣ ፍቅሩ የሚፈለግ ሕዝብ ነው። ጃፓን ሊቅ ነው። በትምህርት ራሱን ችሎ ለሌላ ሊተርፍ ስንትም ያልቀረው ደቀ መዝሙር ነው። የሥልጣኔው ታሪክ የትላንትና ይባላል እንጂ እንደ እውነቱ የዛሬ ሺህ ተስድስት መቶ ዓመት ባገሩ ሲሰራ የነበረው እቃና የተደረሰው ቅኔ ረቂቅ ሕዝብ እንደነበረ ይመሰክርለታል።

የድርሰቱን የቅኔውን ሥራ ያገሬ ባላገር የደካማ ሥራ ብሎ ለደብተራ ብቻ ንቆ እንደሚተውለት ብልሁን ጃፓን ቃትቶት አያውቅም። የመጻሕፍቱን ታሪክ ብታየው ወይዛዝሩና መኳንንቱ፣ ንግሥታቱና ነገሥታቱ፣ ጀግኖች ወታደሮቹና መንፈሳውያን ካህናቱ “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ” የሚፈካከሩበት ነው የሚመስልህ። ጥሩ ቅኔና ድርሰት የጀመሩ ከልደት በኋላ በ285 ዓመት ነው ይሉናል። ከዚያ አንስቶም እስከ ዛሬ ደራሲና ባለቅኔ አቋርጦ አያውቅም።

ንጉሠ ነገሥቱ ሙሺሂቶ ዘመነ መንግሥታቸው ሜይጂ ዖ (ሰላማዊ ብርሃን) የተባለው፣ የዛሬው ንጉሠ ነገሥት አባት ዋና ባለ ቅኔ ነበሩ። ቢሆንም የትርጉም ትርጉም ሲሆን የቅኔያቸው መልኩ ሊበላሽብኝ ሆነ እንጂ፣ ከግርማዊ ሙሺሂቶ ቅኔ አንዲቱን አጭሯን ከጣልያን ቋንቋ ልተርጉምልህና “ማኅደረ ብርሃን“ን አንብብ እያልሁ ፍቀድልኝ ልሰናበትህ፤

ጐበዝ ላገርህ ለወንዝህ

እኔ ንጉሥህ ጌታህ

ውጋ ምታ ስል አዘዝሁህ

በለው አሁንም ውጋ

ዋናውን ፍቅርን አትዘንጋ

ቢሆንብህ የግድ

ላገርህ ለወንዝህ ማረድ

ፍቅርን መውደድን አትካድ።

.

ተአምራት አማኑኤል

1926 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ፤ መስከረም ፲፰፣ ፲፱፻፳፮

One thought on “ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s