“ጅብ ነች” (ልብወለድ)

“ጅብ ነች”

ከታደሰ ሊበን

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ቀኑ ቅዳሜ ነበር። አሰፋ ያዲስ አበባ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ተማሪ፣ እድሜው ሃያ አመት የሆነ፣ እናቱን ለመጠየቅ ካዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር በምሥራቅ በኩል ርቃ ከምትገኘው ከተማ ሸኖ ሄዶ፣ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እናቱ ቤት ነበር።

ይመጣል ብለው ያልተጠባበቁት እናት፣ ለጊዜው ቤት ያፈራውን በተቻለ መጠን አጣፍጠው ከሸነገሉት በኋላ፣ ለራቱ የሚሆን የዶሮ ወጥ ሊሰሩ፣ ዶሮ አሳርደው፣ የፈላው ውሀ ከሱ የሚጠበቀውን ካደረሰ በኋላ፣ እሳቸው ደግሞ መንፋቱንና መለብለቡን፣ ከዚያም በኋላ መፋቁንና መገነጣጠሉን፣ ተራ በተራ ይዘው ነበር። ታናሽ እኅቱም አየለች፣ ውሀ በመጥለቅና ዕቃን በማቀበል እናቷን ለመርዳት እዚያው እስራቸው ነበረች።

አሰፋም ከመጣ ጀምሮ ወደ ውጭ ሳይል ሥስት ሰዓት ሙሉ ከቤት ቁጭ ብሎ፣ የናፈቁትን እናቱን ትንሹንም ትልቁንም ሲያጫውታቸው ነበርና የቆየው፣ ዘጠኝ ሰዓት እንደሆነ፣ አገሩን ውጭውን ለማየትና ወዲያውም ለመናፈስ በማሰብ ሊወጣ ብድግ አለ።

እናቱም ወይዘሮ አሰገደች ዓይናቸውን በሥራቸውና በልጃቸው ላይ ጣል አድርገው ኖሮ፣ ልጃቸው መነሳቱን እንዳዩ ሥራውን ቆም አድርገው፤

“ምነው አሰፋ የት ልትሄድ ነው?” ብለው ጠየቁት።

አሰፋም በዚህ ጊዜ ከበሩ ደርሶ ነበርና ከዚያው ከቆመበት መለስ ብሎ፤

“አገሩን ልይ ብዬ ነው” ብሎ መለሰ።

“ቆይ እኮ። በኋላ ጥላው በረድ ሲል ነዋ ልጄ፣ በዚህ ጠራራማ ሰዓት ደግ አይደለም።”

“ምን ይለኛል ብለሽ ነው?”

“እንዴ! አይሆንም። ሽታው፣ ደግሞ ይኸ ምና ምኑ፣ ምን ይታወቃል ብለህ ነው። የኛ አገር እንዳዲስ አበባ አይደለም ልጄ። አተላው፣ አመዱ፣ በያለበት ነው የሚፈሰው። በዚህ ሰዓት ሽታው ደግ አይደለም።”

አሰፋም የእናቱን ሀሳብ በመቀበል እርምጃውን ወደፊት ሳይቀጥል እዚያው ከናቱ ደጃፍ ላይ ቆሞ ውጭውን ይመለከት ጀመር።

የእናቱ ቤት ከከፍተኛ ቦታ ላይ የተሠራ በመሆኑ፣ ከበር አፉም ላይ ሆኖ የሚታዩ ብዙ ነገሮች ነበሩ። በአንጻሩ ቡልጋና መገዘዝ ጠፈሩን የነኩ መስለው፣ ከሩቅ በጭጋግ ተውጠው፣ እንደ ህልም ይታዩ ነበር። ከዚያም ወዲህ ተራሮች በየኮረብታቸው ያገሬውን ቤት ሾመው፣ በወገባቸውም አዝመራን አዝለው፣ የሚወጡና የሚወርዱት አያሌ ነበሩ። ከዚያም በጣም ወዲህ ወደ ሸኖ ቀረብ ሲሉ ደግሞ፣ የሚታየው ከከተማው ጥቂቱ ክፍል ነበር። በዚሁ ክፍል የሚታዩት ቤቶች፣ በድንጋይ ካብ ግድግዳና በሰንበሌጥ ክዳን የተሠሩ ነበሩ።

የአሰፋም ዓይን ይህንኑ ትርኢት ከሩቅ ሲከታተል ከመጣ በኋላ፣ በእናቱ አጥር ግቢ አዋሳኝ ካለው አጥር ግቢ ውስጥ ከሚታየው ሰቀላ ቤት በር፣ ወደ ውጭ ሲወጣ የሚታየው ነገር፣ እውነተኛ ወይም ህልም መሆኑን ለማረጋገጥ አስቦ፣ ደህና ሆኖ እንዲታየው በተመቸው አቅጣጫ አንጋዶ፣ ወደዚሁ በር አተኩሮ ነበር።

ይህም ቤት ከሌሎቹ ቤቶች ትንሽ ለመለየትና፣ ግማሽ በግማሽም ያዲስ ዘመን አቅድ ነክ በመሆን፣ ጣሪያው አዲስ አበባን (ቆርቆሮ)፣ ግድግዳው ሸኖን (የድንጋይ ካብ) የሆነ ነበር። ሆኖም አሰፋ አሁን በበሩ ብቅ ሲል ያየው ነገር፣ እውነተኛ እንጂ ህልም አልነበረም። ከቤት ውስጥ በበሩ ብቅ ያለችው፣ አንድ ነጭ የቤት ፈትል ቀሚስ የለበሰች ሴት ልጅ ነበረች።

እሱም በዚያ ርቀት እንደሚያያት ልጅቷ ብስል ቀይ፣ ዓይኗ ጥራቱ ኩል የመሰለ፣ ፀጉሯ ዞማ፣ ከዘመናዊው ይዞታ አንዱም አይነት ሳይነካው፣ እንደዚሁ በተፈጥሮው ብቻ፣ ትከሻዋ ላይ ነጥሮ ለቀቅ ካለው ሽንጧ ላይ እንዲዘናፈል የተተወ፣ ቅንድቧና ሽፋሏ፣ አፍንጫዋና ከንፈሯ ይህ ቀራቸው የማይባሉ፣ የጡቷም አጐጠጐጤ ከቀሚሱ ውስጥ መፈናጠሩ፣ የተፈጥሮ ሳይሆን ልብሷን ከሰሩት ልቃቂቶች መሀል፣ ሁለት የዳበሩት ተመርጠው ቀርተው እንደ ወጋግራ እንዲወጥሩት የቆሙበት የሚመስል፣ ቁመቷ ደልዳላ፣ ዕድሜዋ ቢበዛ ሃያ፣ ቢያንስ አሥራ ዘጠኝ የሚሆን ነበረች።

አሰፋም ወጥታለት እንዲህ ሙሉ በሙሉ እንዳያት፣ ልቡ አለመጠን መታ። ዓይኖቿም ከዓይኖቹ ላይ ሲያርፉ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ነዘረው። ዓይኖቹንም ከሷው ላይ ሳያነሳ እናቱን፣

“እማማ ይቺ ማን ናት?” ብሎ ጠየቀ።

ቁጭ ያሉትም እናት እዚያው እንደሆኑ ቀና ብለው፣

“የቷ ልጄ?” ብለው ጠየቁ።

አሰፋ አሁንም ወደ እናቱ ዘወር ሳይል፣ እዚያው ሰውነት ላይ ዓይኖቹን ድርቅ አድርጎ፣

“ይ … ይቺ!” አለ።

እናቱም በዚህ መልስ ብድግ ብለው፣ የልጃቸውን ዓይን እንዲህ የፈዘዘበትን አቅጣጫ ይዘው፣ የተጠቀሰችውን ሴት ልጅ እንዳዩ፣ ስቅጥጥ ብለው፣

“አሰፋ! በል ቀስ ብለህ ግባ። ይህችን ልጅ ከእንግዲህ ወዲህ፣ ዓይንህ ፈጽሞ እንዳላያት ሁን”

ብለው አዘዙ። እሱም በዚህ ጊዜ ወደናቱ አይቶ፣

“ምነው! ለምን እማማ?” ብሎ ጠየቀ።

“ቡዳ ነች! ልጄ። ያውም እንዲህ እንዳትመስልህ ዋና ቀርጣፊዋ።”

አሰፋም የእናቱን ነገራቸውን በማቃለል ሳቅ ብሎ፣

“አይ እማማ! አሁን ይ-ይቺ!” ብሎ በፈገግታ ጠየቀ።

እናትየዋም በፈገግታው ከመበገር ይልቅ ይበልጥ አምረው፣

“አዎን እሷ። በዚሁ በመልኳ እያታለለች ነው ብዙውን ጀግና ያበላሸችው። ስማና እረፈው እንግዲህ ከፈለግህ፣ ማታ ማታ ጅብ ትሆናለች” አሉት።

አሰፋም በማዘን አኳኋን ወደ እናቱ ሙሉ በሙሉ ዘወር ብሎ፣

“እማማ! እማማ! እንደዚህ አትበይ። ሰው የሰው ልጅ አንቺስ ብታስቢው እንዴት ጅብ መሆን ይችላል? ይህ እማማ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ያገራችን አፈ ታሪክ ነው። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ተመልሶ ጅብ ሊሆን እንደማይችል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞም ሌሎች ከፍ ያሉ ትምህርቶች ያስረዱናል። እርግጥ አንዳንድ ሰዎች የዓይናቸው ኀይል አያዪ ሆኖ፣ ደከም ባለ ሰው ላይና በሕፃናት ላይ ሲያርፍ፣ ሊጎዳ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ከዚህ አልፎ ተርፎ ሰው ማታ ጅብ፣ ቀን ደግሞ ተመልሶ ሰው ይሆናል ማለት የማይሆን ነገር ነው” አለ።

እናትየዋ በዚህ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ቱግ ብለው፣

“ልጄ እንግዲህ ትሰማ እንደሆነ፣ የወለድኩህ እኔ ነኝ አንተ አይደለህም፣ ስማኝ! ጅብ ትሆናለች ስልህ፣ ጅብ ትሆናለች ነው። ይህን የአንተን አትሆንም የሚለውን መጽሐፍ ለዚያው ላዲስ አበባህ አድርገው” አሉ።

አሰፋ በዚህ ጊዜ እሱም በበኩሉ ናር ብሎ፣

“እሺ! አንቺስ ጅብ መሆኗን እንዴት ታስረጂኛለሽ?” ብሎ ጠየቀ።

እናትየዋም እንዲሁ እሳቸውም በበኩላቸው በቁጣ የደም ስሮቻቸው ተገታትረው፣

“እንዴት ታስረጂኛለሽ ይላል! ህም! ሊያቅተኝ። ምነው አሁን በቀደም ለት፣ ከስምንት ቀን በፊት፣ ድፍን ሸኖ አልተረዳውም እንዴ! መገርሳ የሚባለውን ወዳጅዋን አልጋዋ ላይ በመድኀኒቷ አፍዝዛ አስተኝታ፣ እሷ ከጅቦቹ ጋር ስትጋልብ አንግታ፣ ስትመለስ እሱስ መድኀኒቱ ሳይበቃ ቀርቶ፣ አይነቃም ብላ ካሰበችበት ጊዜ በፊት መገርሳ ነቅቶ፣ አውልቃ የደበቀችው የራስ ቅሏን አግኝቶ አልደበቀውም! እሺ እሱም ይቅር፣ ሦስት ቀን ሙሉ አልመልስላት ብሎ፣ በሯን ዘግታ ስታለቅስ አልከረመችም! እሺ እሱም ደግሞ ይቅር፣ ይህንኑ አሁን እንዲህ እላዩዋ ላይ ወድቆ ያየኸውን ፀጉሯን ራሱኑ፣ ከነራስ ቅሏ በመገርሳ እጅ፣ ሰኞ ገበያ ውስጥ ሲዞር አላየነውም! ህም! ደግሞ እንዴት ታስረጂኛለሽ! ባየህ አገር ግልብጥ ብሎ ወጥቶ እግዚዎ ብሎ ለምኖት ነው የመለሰላት። ምነው አንቺ አየለች አትነግሪውም ለዚህ ለወንድምሽ? በይ እኮ። የወይኒቱን ፀጉር እመገርሳ እጅ አላየሽውም? እሷስ በሯን ዘግታ ሦስት ቀን ሙሉ ስታለቅስ አልሰማሻትም?” አሉ።

አየለችም የእናቷን ማምረር ተገንዝባ እንዳሏትም ወዲያው ወንድሟን አይታ፣

“አዎን ጋሼ፣ እማማ ያለችው ሁሉ እውነት ነው። ፀጉሯን ጋሼ መገርሳ ሲያዞረው ሁላችንም አይተነዋል” አለችው።

አሰፋም ከዚያ በኋላ ምንም ሊል አልቻለም። ደንግጦ ገብቶ ቁጭ አለ። ከሰውም ሰው የዚች ልጅ ጭንቅላት፣ ከራሷ ላይ ወልቆ ተገኝቶ፣ በገበያ ሲዞር ነበር አሉት። እስቲ ለዚህ ምን ይመለሳል! ዝም ብሎ ተቀምጦ ቆይቶ ጥላው በርዶ አሥራ አንድ ሰዓት እንደሆነለት፣ ብቻውን ለመሆን በማሰብ፣ በዚያው ፊት አገሩን ላይ ነው ብሎ አቅርቦት በነበረው ምክንያት፣ አሁንም በሱው አማኻኝቶ ሊወጣ ተነሳ።

እናቱም እደጅ ድረስ ተከትለውት ወጥተው፣

“እንግዲህ እንዲያው አደራህን ልጄ፣ ወደዚያ ቤት ፈጽመህ ዝር እንዳትል?” ብለው ለመኑት።

አሰፋም የእናቱን ማምረር ተገንዝቦ፣

“እሺ እማማ” ብሎ መለሰ።

“እስቲ እንዲያው ይኸው ሙች አልሄድም በልና እጄን ምታኝ?”

“እማማ ሙች።”

.

አሰፋም ከዚህ በኋላ ለይምሰል አገሩን እውነት እንደሚያይ ሰው፣ ከተማው በሞላ ወለል ብሎ ከሚታይበት ከፍተኛ ቦታ ላይ ወጥቶ ነበር። ነገር ግን ዓይኑ ከዋለበት ላይ ልቡ ስላልነበረ፣ አንዱንም አላየም ነበር። ልቡ በዚያችው ልጅ ላይ ነበር።

በሕይወቱ ሙሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ልቡን የማረከችው እሷው ልጅ ነበረች። አሰፋ በጣም ወዷት ነበር። ታወቃላችሁ? የመጀመሪያ ፍቅራችሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታዩዋት፣ ልባችሁ አለመጠን ይመታል። አካላታችሁንም በሞላ አንዳች ነገር ሲወራችሁ ይሰማችኋል። ይህም ይበልጡን ጊዜ የሚሆነው፣ ፍቅሩና መሳሳቡ ከሁለቱም በኩል የመጣ ሲሆን ነው። አሰፋንም ቅድም ዓይኖቿ በዓይኖቹ ላይ ሲያርፉ፣ እንደዚያ የነዘረው፣ ይኸው ሆኖ ነበር። አሰፋ አውቆታል። ልጅቷም ወዳዋለች።

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እንደዚሁ እንዳልነው፣ ፍቅሩና መሳሳቡ እሁለቱም ዘንድ ይኖርና፣ ልጅቷ ለክፋት ያገባች፣ ወይም የታጨች፣ ወይም ክብሯ፣ ዘሯ ከተራ ሰው ጋር የማይቀላቅላት ሆኖ ራሷን ገዝታ፣ ፊቷን መልሳ ዞራ ትሄዳለች። በዚህ ጊዜም ሐዘን፣ ደግሞም ትካዜና ቅርታ በተገፊው ልክ ላይ ይሰፍራሉ።

አሰፋንም አሁን እንደዚህ ያስተከዘው ነገር፣ ከነዚሁ መሰናክሎች አንዱ በሆነ ጥሩ ነበር። ምነው እናቱ ቅድም ያገባች ናት፣ ወይም ታጭታለች፣ ወይም የራስ ልጅ ናት ባሉት ኖሮ። አሰፋ ደፋር ነው። እንደሚሉት ደግሞ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም። ነገር ግን እናቱ አልፈው ተርፈው፣ ጅብ ነች አሉት።

አሰፋ ይህንን በኅሊናው ሊያምነው፣ ወይም ሊቀበለው ከቶ አልቻለም። ለብቻው በሐሳቡ፣ እንዴት እሷ ጅብ ትሆናለች? እሷ ከሰብአዊነት ወደ ሌላ ነገር ለመለወጥ ብትችል፣ መልአክ ብትሆን እንጂ፣ ጅብ አትሆንም ይል ጀመር። ደግሞስ የሰው ልጅ እንዴት የራስ ቅሉን አውልቆ፣ አስቀምጦ፣ ጅብ ሆኖ ይሄዳል? ይህ በፍጹም እልም ያለ ዓይን ያወጣ ውሸት ነው። ስንት የደም ሥሮች፣ ስንት ጅማቶች፣ መበጣጠስ እንዳለባቸው፣ ማን ለነማማ በነገራቸው።

እነሱ ግን ሲያወሩት ልክ አንድ ባርኔጣ፣ ከሰው ራስ ወልቆ እንደተቀመጠ ያኽል አድርገው ነው። ሆኖም ይኸው ንግግራቸው ሁሉም፣ ጨርሶ ውሸት ነው ለማለት ደግሞ አይቻልም። ያ መገርሳ ያሉት ሰውዬ፣ የልጅቷን ስም ማጥፋቱን ጥርጥሩ የለውም አጥፍቶታል። የታባቱ! ይህን ጊዜ እምቢ ብላው ይሆናል። እሱን እውነትም እንዴት ብላ እሺ ትበለው። ስሙ እንኳን ደስ አይልም። አንዳንድ ሰዎች እንደዚህ ናቸው። የገዛ ነውራቸውን ለመደገፍ ሲሉ፣ የሰውን ስም ያጠፋሉ።

“እገሌ፣ እገሊትን ለምን ተውካት?”

“አዬ የኔ ወንድም፣ እሷማ ይኸውልህ እንደዚህ ነች።”

መገርሳም አይጠረጠርም የዚሁ ብጤ ነው። እንዲያው እሷን ጠይቄያት። አግኝቼው። ነገር ግን እንዴት አድርጌ ልጠይቃት እችላለሁ? እማማ እንዳልሄድ አስምላኛለች። እማማ እንዳልሄድ ያስማለችኝ፣ ጅብ ናትና ልጄን ትበላብኛለች ብላ ነው። አይ እማማ! እነዚህ እናቶች! ነገር ግን እኔ ሰው ጅብ እንደማይሆን፣ ይህችም ልጅ ጅብ እንዳይደለች አውቃለሁ። ምን አለ ታዲያ ብሄድ? አምላኬ! እባክህ ልሂድ? ዛሬ እንዲያው እሷን አንድ ጊዜ ስሜያት፣ ነገ ጧት ንስሐ እገባለሁ።

እሺ፣ አንተንስ አስፈቀድሁ። እማማንስ እንደምን አድርጌ እሄዳለሁ? ወደዚያ እንኳን ሄጄና ዞር ብዬ ብታይ፣ በእሪታ አገር ታስነሳለች። ማታ!

“አዎን ማታ!” አለ አሰፋ ለብቻው ጮህ ብሎ።

ማታ ሁላችንም እንደተኛን፣ ሮባን የጓሮውን በር ክፈትልኝ ብዬ ሄጄ፣ ከሷው ጋራ አድሬ፣ ጧት በሌሊት ደግሞ እማማ እንዳታይ፣ ሳትነሳ ተመልሼ እቤት እንዳደረ ሰው ገብቼ እተኛለሁ።

አሁን እንግዲያውስ እቤት ሄጄ፣ ሮባን ልጅቷን ሄደህ ማታ እመጣለሁ ብሎሻል፣ በልና ንገራት ልበለው። ምናልባት ሮባም እንደነሱው ጅብ ናት፣ እኔ ምንም ቢሆን አልነግራትም፣ እናትህ ይገድሉኛል ይለኝ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ብር ከሰጠሁትና፣ አንድ ኮት እሸልምሃለሁ ካልኩት ወዲያውኑ ይሄዳል።

አሰፋም በዚህ ሐሳቡ ጸንቶ ከዚያም ወዲያውኑ ወደ ቤት ተመልሶ ለእናቱ ገበሬ ለሮባ ጉርሻውን አስቀድሞ ሰጥቶ፣ የሚያደርገውን ሁሉ ነገረው። አቅዱም እንደተፈለገው ካንድ እስከ መጨረሻ፣ ወዲያውኑ እየተከታተለ መሥመር መሥመሩን ያዘ። እራት በልተው እንደተኙም፣ እናትየዋ እፎይ ተመስገን ጌታዬ፣ ልጄን አለባብሼ አስተኝቸዋለሁ ብለው፣ የማታ ጸሎታቸውን አድርሰው፣ ወገባቸውን መሬት እንዳስነኩ፣ አሰፋ ሸለብ ለማድረጊያቸው አሥር ደቂቃ ብቻ ሰጥቶ፣ ከዚያ በኋላ ወደ ወይኒቱ ቤት፣ ኰቴውን ሳያሰማ ሹልክ ብሎ ሄደ።

.

ወይኒቱ እሱ አንኳኩቶ ሲገባ ደህና ደህና ልብሷን ለባብሳ አልጋዋ አጠገብ ቁጭ ብላ ነበር።

“ቅድም ልክ ሳይሽ ……………!”

“እኔም ገና ሳይህ …………….!”

“ሮባን ስልከው በእውነት እሺ ና የምትይኝ አልመሰለኝም ነበር።”

“እኔም ቅድም እናትህ ከበሩ ላይ ወደ ውስጥ ሲያስገቡህ ሁለተኛ የምንተያይ አልመሰለኝም ነበር።”

እንደዚህ ነበር ለጥቂት ጊዜ ሆኖ የቆየው፣ የአሰፋና የወይኒቱ የፍቅር ንግግር። በኋላም ይህ ሁሉ አልፎ፣ ለአሰፋም የቀኑ ህልም ተፈጽሞ፣ ጐን ለጐን ተቀምጠው፣ ስሟት ስማው፣ እንደዚሁም ደግሞ ሌላ ቁምነገር ሁሉ ሲያወሩና ሲጫወቱ ቆይተው፣ ሌሊቱ እንደተራመደባቸው እንዳስተዋሉ ደግሞ፣ ኩራዙን አጥፍተው ተኝተው ነበር።

አሰፋንም ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ ከባድ እንቅልፍ ወስዶት፣ ወይኒቱ እጐኑ እክንዱ ላይ ተኝታ፣ እሱ በህልሙ ከሷው ጋራ፣ በደስታና በዓለም በብዙ አገር፣ በብዙ ቦታ ሲጓዝ ያይ ነበር። ነገር ግን አሰፋ በዚሁ በያዘው ሁኔታ ሌሊቱን በሞላ ሳያነጋ፣ ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ሲሆን፣ በርዶት ከእንቅልፉ ብንን አለ። ብርዱም ደግሞ ያለ ምክንያት አልነበረም። ህልሙ፣ ቅዠቱ፣ ፍቅሩ፣ ወይኒቱ ከጎኑ አልነበረችም።

እናቱም ያሉት ነገር ወዲያውኑ ትዝ አለው። ‘ጅብ ነች!’ ጥርጣሬ ሆዱን አሸበረው። ከብርዱ ጋራ ወባው እንደተነሳበት ሰው ተርገፈገፈ። በሚንቀጠቀጠውም እጁ ዳብሶ፣ ክብሪቱን እንደ ምንም ደረሰበት። እየተርበደበደም ጭሮ ኩራዙን አበራው። በዓይኑም ጨለማውን ባስወገደለት ኩራዝ ብርሃን ኀይል፣ እሷን ፍለጋ ጀመረ።

አሁንም ወይኒቱ ከቤቱ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ አልነበረችም። ፈጥኖም ወደ በሩ ተመለከተ። እነሆ! በሩም መቀርቀሪያው ወልቆ ክፍቱን ተንገርብቦ ነበር። ለአሰፋም ይኸው በቃው። አስተኝታኝ ከዚያው ከጅቦቿ ዘንድ ሄዳለች አለ። ልብሱንም በጥድፊያ አጠላልቆ፣ ወደ እናቱ ቤት ሩጦ ሊሄድ አሰበ። ሱሪውንም ማታ አውልቆ ካኖረበት ወንበር ላይ ሊያነሳ፣ ዘወር ብሎ እጁን ሰደደ።

እዚያም ባየው ነገር ኮረንቲ እንደጨበጠ ሰው፣ እጁን ነዝሮ ካልጋው ላይ ነጥሮ፣ በሌላው ጐን በኩል ከመሬት ወርዶ ወደቀ። ሱሪው ከነበረበት ወንበር፣ በሱሪው ላይ፣ የወይኒቱ ፀጉር እንዳለ ወልቆ ተቀምጦ ነበር።

ብርድ፣ ፍርሀት፣ ድንጋጤ አሰፋን ሰበቁት። ከዚያም ቀስ ብሎ ተነሥቶ ላቡን እያንጠባጠበ፣ ግድግዳውን ጥግ አድርጎ ቆመ። ግድግዳውም ዙሪያውን ሁሉ የጅቦች ሹክሻኬ የሚያዘምት መሰለው። “አሁን እንበላዋለን … እንበላዋለን … ለን!”

በዚሁ ሁኔታው ምንም ያህል ሳይቆይ፣ ወዲያውኑ ደግሞ፣ በሩ ሊከፈት ተንሳጠጠ። አንድ መልክም ወዲያውኑ እቤት ውስጥ ገባ። አሰፋም ይህንኑ መልክ ትክ ብሎ አየው። መልኩም ግማሽ ወገኑ የወይኒቱን ይመስል ነበር። አዎን። አፍንጫው፣ ከንፈሩ፣ ዓይኑ፣ ሽፋሉ፣ ቅንድቡ፣ ቁመቱ፣ ሽንጡ የሷው የወይኒቱ ነበር። ነገር ግን እራሱ፣ ቅቤ የተቀባ ድፍን ቅል ይመስል ነበር። አንድም ፀጉር አልነበረበትም።

የአሰፋና የዚሁ መልክ ዓይን ተገጣጠመ። መልኩም ወዲያውኑ ቀስ እያለ፣ እርምጃውን ወደ አሰፋ በኩል ቀጠለ። አሰፋም በዚህ ጊዜ የሽሽት ግድግዳውን የሙጥኝ በሁለት እጆቹ ይዞ፣ በፍርሀት ድምፅ ጮኾ፣

“አትጠጊኝ! አትጠጊኝ ኋላ … ኡኡ! እላለሁ!” አለ።

መልኩም ዛቻውን ፈርቶ ሳይቆም፣ አሁንም ዝም ብሎ እንደዚያው እየቀረበ በቀስታ፣

“ለምን?” ብሎ ጠየቀው።

አሰፋ አሁን ደግሞ ድምፁ የማን እንደሆነ ወዲያውኑ ለየ። ድምፁም የሷው የወይኒቱ ነበር።

“ጅብ ነሽ! እናቴ ስላንቺ የነገረችኝ ነገር ሁሉ እውነት ነው። አትጠጊኝ፣ አትጠጊኝ ብያለሁ ኋላ!”

ወይኒቱም በዚህ ጊዜ ከአሰፋ ዘንድ ተመልሳ፣ ወደ አልጋዋ እያዘገመች ሄዳ፣ በግርጌው ላይ ቁጭ አለች። እንባም በጉንጮቿ ላይ ወዲያውኑ ይወርድ ጀመር። ትንሽም በዚሁ ሁኔታ ዝም ብላ፣ አንገቷን ደፍታ፣ ስትንሰቀሰቅ ከቆየች በኋላ፣ ወደ አሰፋ ተመልክታ፣

“አሰፋ አንተም እንደ ሰዎቹ ጅብ ነሽ አልከኝ? ምን ኑሯል ሌሊት አቀፈኸኝ በክንዶችህ ላይ ሳለሁ የነገርኸኝ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሳይንስ፣ ሰው ጅብ እንደማይሆን ያስረዳኛል፣ ማንም ጅብ ነሽ ቢልሽ፣ እኔ ከቶ አልልሽም አላልከኝም? አሁን ታዲያ ………!”

“አዎን ሌሊት እርግጥ እንደሱ ብዬሻለሁ። ነገር ግን ማየት ማመን ነው። አሁን እራሴ በዓይኔ አየሁሽ። ጅብ ነሽ።”

በዚህ ጊዜ ወይኒቱ ከልቧ ተንሰቅስቃ፣

“የለም አሰፍዬ አይደለሁም” አለችው።

“እንዴት አይደለሽም? እሺ፣ ምንድነው ይኸ እራስሽ? ፀጉርሽስ እንዴት ቢሆን እንደዚህ ወለቀ? አንቺስ አሁን የት ነበርሽ?”

አሁን ደግሞ ወይኒቱ ቀና ብላ እንባዋን ከፊቷ ላይ ጠራርጋ፣

“እሺ። ስማኝ አሰፍዬ ልንገርህ እንግዲያውስ የት እንደነበርኩ። ፀጉሬም እንዴት እንደዚህ እንደወለቀ።  አሁን ከአጠገብህ ያጣኸኝ፣ ወደ ጓሮ ወጥቼ ነው። ፀጉሬም እንዲህ የወለቀው፣ የራሴ የተፈጥሮ አይደለም” አለችው።

በዚህ ንግግር አሰፋ ደንግጦ፣

“አ!” አለ።

አሁን ደግሞ ወይኒቱ በጣም አልቅሳ፣

“አዎን አሰፍዬ፣ ስማኝ ታሪኬ ይህ ነው። እናቴ፣ ባሏ የእኔ የልጅዋ አባት፣ ወዲያው እንደተወለድኩ ሞቶባት፣ ችግርና ማጣት በዚህ ዓለም ክፉኛ ያንገላታት ድኻ ሴት ነበረች። የሚላስ የሚቀመስ ስላልነበረ፣ እየዞረች ትለምን ነበር። አንድ ቀን በተወለድኩ በዓመቴ፣ እኔን ብቻዬን ከቤት ውስጥ ዘግታብኝ፣ እሷ ቃርሚያ ሄዳ ነበር። ለካስ ፈቀቅ ብሎ ከተኛሁበት መደብ ሥር የተዳፈነ ረመጥ ኖሮ፣ ተንከባልዬ በአናቴ ወድቄበት፣ ራሴ በሞላ ተጠበሰ።

“እንደ አጋጣሚ በዚያ በኩል ከሚያልፉ ሰዎች አንዱ፣ ጩኸቴን ሰምቶ ባይደርስና ባያተርፈኝ ኖሮ፣ ነድጄ እቀር ነበር። ከዚያም አገር እናቴ ወዲያውኑ ይዛኝ ጠፍታ አዲስ አበባ ገባች። እዚያም ብዙ ሐኪሞች ዘንድ እየለመነች ደርሳ ራሴን አሳየቻቸው። ሁሉም ይኸ ፈጽሞ ተቃጥሏል፣ ሁለተኛ ፀጉር የሚሉት ነገር አያበቅልም አሏት። እሷም እኔን ያለልክ ትወደኝ ነበርና፣ መጨረሻ የሄደችበት ሐኪም እግሩ ላይ ወድቃ፣ ምርር ብላ ብታለቅስበት፣ ትልቅ ስትሆን ወደ እኔ ዘንድ አምጪያት አላት።

“እናቴም ሳትርቅ ለዚያው ለሐኪም ግርድና ገብታ ትሰራ ጀመር። እኔም ሌላ ቦታ ላይ እሳቱ ስላልነካኝ፣ ይህንኑ ራሴን ብቻ በቆብና በሻሽ እየተሸፈንኩ አደግሁ። በአሥራ አምስት ዓመቴም፣ ሐኪሙ ለእናቴ በሰጣት ተስፋ መሰረት፣ ይህንን ፀጉር ካገሩ ተላልኮ አምጥቶ ሰጠኝ። ስለዚህ ማታ ማታ ስተኛ፣ ከቀን ብዛት ከመኝታ የተነሳ፣ ተሰባብሮ እንዳያልቅብኝ አውልቄ አኖረዋለሁ” አለችው።

አሰፋም በዚህ ንግግር ልቡ ተነካ።

ወዲያውኑ ወደ አልጋው ጠጋ ብሎ፣ ፀጉሩን ከሱሪው ላይ አንስቶ በኩራዙ መረመረው። እውነትም ፀጉሩ ወይኒቱ እንዳለችው፣ በሰው እጅ የተጐነጐነ፣ ሰው ሰራሽ ነበር። የአሰፋም እንባው ተንቆረዘዘ። ፀጉሩን አልጋው ላይ አስቀምጦ፣ ራሷን ደግሞ ሊያይ ኩራዙን ይዞ ወይኒቱን ተጠጋት።

እነሆ! እሱም እንደዚያው እሷው እንዳለችው፣ በሞላ በእሳት የተቃጠለ ጠባሳ ነበር። አሰፋንም እንባ አነቀው። ከንፈሩም ተንቀጠቀጠ። ኩራዙንም ከቦታው አስቀምጦ መጥቶ፣ ወይኒቱን በደረቱ ላይ ጥብቅ አድርጎ አቀፋት።

ሁለቱም አንገት ላንገት ተያይዘው፣ እኩል ተንሰቅስቀው አለቀሱ።

.

ታደሰ ሊበን

1949 ዓ.ም

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] – “መስከረም” ፲፱፻፵፱። ገጽ 11-28።

6 thoughts on ““ጅብ ነች” (ልብወለድ)

  1. It is great. I read it for the first time. I didn’t know any thing about the book. But, Ato Tadesse Liban was my boss in the Bank for several years. I did have high regard and respect for him. When he retired, I was a branch manager. He humbled himself to come to my office, Arada Branch and gave me pieces of advice which were very useful to me and unforgettable.

    Like

  2. What a nice short story I love it. I read it in the past, still nice. Characters are vivid we can see them, their motives, lives and cultures. Words like classical old Amharic sayings, also narrative style, is so catching. Theme/substance/ also powerful, mocking on old beliefs but respecting elders and appreciating humanity, through Love.

    Like

  3. እንግዲህ ይህ ታሪክ የዛረ 40-100 አመት ታሪክ ይመስለናል ፡፡ እነን ያሚገርመን አሁንም በዚህ ሃሳብ የሚሆኑ ስዎች መኖራቸው ነው፡፡ የአገራችን ህዝብ በታም ያሳዝናል ሁሉን የፈታረ አምላኩን እያመነ ይህንንም ያምናል ይገርመናል፤፤፤

    Like

  4. Thank you very much for posting one of Ato Tadesse Liben’s short stories “Jib Nat”. I believe he is one of the prominent Ethiopian short story writers. I tried to find this book in Addis when I visited a few years ago but I couldn’t find it anywhere. My favorite story was “Yetebetese Fre”. I would appreciate if I someone post the author’s biography and if possible “Yetebetese Fre”.

    Thank you.

    Like

  5. Wow! What a flawless story … The story develops with systematic progress; and, the language is awesome.

    I met Tadesse, the author, at Addis Ababa University. He was a dignified speaker in ILS.
    He was too shy and gentle. Using my opportunity, I tried to visualize his literary work. Eventually, now, I read his beautiful short story listening the melodic music behind eac word. Mesmerizing!

    Like

አስተያየት ለመስጠት