“የሺንጋ መንደር”
በሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም
.
[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]
.
፩
ሺንጋ ተወለደ
ጊዜው ደንገዝገዝ ብሏል። ከእልፍኙ ምድጃ መሐል የደረቅ ወይራ እሳት ይንቀለቀላል። የእናታቸውን ጡት የናፈቁ ትናንሽ ጥጆች ጋጣቸው ውስጥ ቆመው እምቤ ይላሉ። የሠፈሩን ከብት የሚያግደው እረኛ መንጋውን እየነዳ የሚመላለስበት ሰዓት ስለሆነ ከብቶቹ በሩቁ ‘እምቧ’ ሲሉ ከቤት ዘልቆ ሰው ጆሮ ውስጥ ያስተጋባል … (ድርሰቱን በጉራጊኛ ለመቀጠል)
ማተቤት የምሽት ቡና ለመጣድ እውጭ ወጥታ ጀበናዋን ታለቀልቃለች። ኬርወጌ ደግሞ ስለተጫጫናት ምድጃው አጠገብ ጋደም ብላ እሳት ትሞቃለች። ድርስ ነፍሰጡር ስለሆነች በዛሬና በነገ ትገላገል ይሆናል የሚል ስሜት ትፈጥራለች። ባለቤቷ ባላ በአባወራው ሥፍረ ኬሻ ላይ ተቀምጦ የቤት ጋያውን ያንቦቀቡቃል። ዝም ብሎ ሲያዩት “ሚስቴ ወንድ ልጅ ትገላገልልኝ ይሆን ወይስ ሴት ልጅ?” እያለ የሚያሰላስል ይመስላል።
ከትንሽ ጊዜ በኋላ ከብቶች ከደጅ ሲደርሱ ባላ ጋያውን መሬት ላይ አኑሮ፣ ትምባሆ በቃጫ ጠቅልሎ ቀኝ ጉንጩ ውስጥ ወሽቆ ከብቶቹን ለመቀበል ወደ ደጅ አመራ። ነጭቷ ላም ትምባሆ ጎርሰው ካልተቀበሏት በስተቀር ቀኑን ሙሉ ሣር ስትግጥ እንዳልዋለች ሁሉ ምሽት ላይ ምናምን ፍለጋ መኰብለሏን ልማዷ አድርጋዋለች። ይህን አመሏን ትተዋለች በማለት ጆሮዋን ብትበጣም አልተው አለች። አሁንም ወደ ጓሮ ዘው ለማለት ስትከጅል ባላ “ነጪት!” ሲል ተጣራ። የጌታዋን ድምጽ ስትሰማ ለትምባሆ ጭማቂ መሆኑ ገብቷት መለስ አለች። ከብቶቹ በመላ ወደ ውስጥ ከዘለቁ በኋላ ማተቤት በእየጋጣቸው አስገብታ አሠረቻቸው። ከዚያ በኋላ ቀደም ብላ ጣደችው።
ባላ ሱሪውን አውልቆ ቡሉኮውን ተከናንቦ በአባወራው ማረፊያ ቦታ ጋደም አለ። ትንሺቷ ሴት ልጁ ተሬዛ፤ እየሮጠች መጥታ በአጠገቡ ቁጭ አለች። አባቷም “እስቲ በትናንሽ እጆችሽ ጀርባዬን አሸት አሸት አርጊልኝ” አላት። እሷም የአባቷን ጉንጭ ሳም አድርጋው ጀርባው ላይ የነበረውን ቡልኮ ወደ ታች ቀልብሳ ጀርባውን ታሻሸው ጀመር።
ኬርወጌ ምጥ የጀመራት ይመስላል፤ ከተኛችበት ሆና ‘እህ’ እያለች ስታቃስት ትሰማለች። ተሬዛን የወለደች ጊዜ ምጡ እጅግ በጣም አሰቃይቷት ስለነበረ ከአሁን ወዲያ እግዚአብሔር ልጅ አይስጠኝ ብላ ተመኝታ ነበር። ነገር ግን ወንድ ልጅ ስላልነበራት ምኞቷ የምር ነው ብሎ የተቀበላት ሰው አልነበረም።
እመቤቷ እህ ባለች ቁጥር ርኅሩኋ ማተቤት “እኔን እናቴ!” እያለች ትንሰፈሰፍ ነበር። እዚያ ከነበረ ሰው ሁሉ ከሷ በስተቀር ሌላ የወለደች ሴት አልነበረችምና የምጥን አስከፊነት ደህና አድርጋ የምታውቅም እሷ ነበረች።
ማተቤት እየተንሰፈሰፈች እያለች፤ ቡናውም ለመድረስ ሲቃረብ፤ ይብጊየታ የተባለው ጎረቤት ወጣት ልጅ በሁለት ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ለምሽት ሸንጎ ባላ ዘንድ ከተፍ አለ።
“ደህና ዋላችሁ?” ብሎ ገባ ሲል ባላ ከተኛበት ቀና ብሎ፣
“ይብጊየታ ነህ እንዴ? ሰሞኑን ወዴት ጠፍተህ ኖሯል? አላየንህም!” አለው።
ኢብጊየታ መልስ እስኪሰጠው ሳይጠብቅ አያይዞ፤
“ያች ሙሽራህ ጥላህ እንደሔድች ቀረች? ወይስ ተመልሳልሃለች?” ሲል ጠየቀው።
ኢብጊየታ ወጣት ልጅ በመሆኑ አፈር እያለ፤
“ዛሬ ተመልሳልኛለች” አለው ።
ባላም ቀጠል አድርጎ፣
“ለዚህ ነዋ ዛሬ ለምሽት ሸንጎ ብቅ ያልከው! ቤት የሚጠብቅልህ ሰው አግኝተሃላ!” አለው።
ባላና ኢብጊየታ እንዲሁ ሲጨዋወቱ እያሉ ቡናው ደረሰ። ማተቤት ማቶት ይዛ መጥታ ጀበናውን ከእሳቱ አንስታ እዚያ ላይ አኖረችው። ሲኒዎቹን አጣጥባ ረከቦቱ ላይ ደረደረቻቸው። ይህን ጊዜ አትሼወ ከሁለተኛው ጎጆ የሚገቡትን ከብቶች በረታቸው ውስጥ አስገብቶ፣ አልቦ፣ በሌአቸውን ሰጥቷቸው ሲያበቃ ለቡና ወደ እልፈኙ ገባ።
ሰው ተሰባስቦ ቡናው እየተጠጣ እያለ ኬርወጌ ከተኛችበት አልተነሳችም። አልፎ አልፎ እህ እያለች ታቃስታለች እንጂ ምንም አትናገርም። “ቡና በወተት ልስጥሽ” ብትባል እምቢ አለች።
ይኼኔ ትንሿ ተሬዛ፣
“ስኒ አልጠፋ፤ ቡና ለምን ተከለከልኩ” አለች።
ማተቤት ቆጣ ብላ፤
“አንች ውሪ! ትልልቆቹ ሳይደግሙ ላንቺ ቡና ልስጥሽ?” አለቻት።
ባላ ግን ሰምቷት ለእሱ የተሰጠውን ስኒ ቡና ጎንጨት አለለትና፣
“እንቺ የኔን ውሰጂ” አላት።
ተሬዛም ደስ ብሏት ፈገግ አለችና ሲኒውን ተቀበለችው።
ቡናው ሲጠናቀቅ ኬርወጌ፤ “ሰው ጥሩልኝ” አለች። የሰፈር ሴቶች በምጧ እንዲያግዟት። ይኽን ጊዜ ርኅሩኋ ማተቤት መንሰፍሰፏን ቀጠለች። ጉልቻዎቹን በታተነቻቸው፤ ጀበናውን ወደ ጓዳ መለሰቸው፤ ማቶቱንና ሲኒዎቹን በእየቦታቸው መለሰቻቸው።
ባላ በበኩሉ ባለቤቱ በምጥ መያዟን ሲያረጋግጥ “በዚያኛው ጎጆ አረፍ ለማለት እፈልጋለሁ፤ ማረፊያ አበጃጁልኝ” አለ። ኢብጊየታ ዱላውን አንስቶ በምሥራቅ አቅጣጫ የነበሩትን የሠፈር ሴቶች ለመጥራት ሲወጣ አትሼወ በበኩሉ ጦሩን ጨብጦ በስተምዕራብ የነበሩትን የሠፈር ሴቶች ለመጥራት ወደዚያ አመራ።
ከትናንት በስቲያ በሠፈሩ ለተስካር የሚሆን ሠንጋ ታርዶ ነበር። በዚህ ምክንያት ደም የሸተታቸው ጅቦች ይርመሰመሱ ነበር። ማተቤት ባዶ እጇን ወደ ሁለተኛው ጎጆ ለማምራት ስለፈራች አንዳች የሚያህል ገጀራ ትከሻዋ ላይ አጋድማ ለባላ ማረፊያ ለማዘጋጀት ወደ ሁለተኛው ጎጆ አመራች።
ኬርወጌ በምጥ መያዟን የሠፈሩ ሴቶች ሲሰሙ ወዲያውኑ እየተንሰፈሰፉ ከእየቤታቸው ወጡ። ምሽቱ ዓይን ቢወጉ አይታይ ጨለማ ስለነበር አንዳንዶቹ የሚነድ ክፋይ ይዘው፣ ሌሎቹ የስንደዶ ችቦ አብርተው እየተጣደፉ መጡ። እነሱም እንደደረሱ ባላ ትንሿን ልጁን አንስቶ ታቀፋት። እውጭም መሬቱ ቅዝቃዜ ስለነበረው የእንጨት መጫምያውን እየረገጠ ወደዚያኛው ጎጆ አመራ። አብጊየታና አትሼወም የሠፈሩን ሴቶች እግር በእግር ተከታትለው ከመጡ በኋላ ባላን ለማጓደን ወደዚያኛው ጎጆ አመሩ።
መንፈቀ ሌሊት ላይ ሰማይ ምድሩ ጭጭ አለ። የላሞች እምቧታ የለም፤ የፍየል የአህያ ጩኸት የለም፤ የዶሮ ወይም የውሻ ድምጽ እንኳን አይሰማም። እውጭ ነፋስ ሲነፍስ ብቻ ሽውታው ጆሮ ውስጥ ያስተጋባል።
ምጡ ሲከፋባት ኬርወጌ አልፎ አልፎ “ወይኔ!” እያለች ስትጮህ በትንሹ ይሰማል። “ወይኔ!” ብላ በጮኸችም ቁጥር ከእሷ ጋር ያሉት የሠፈር ሴቶች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ኦ! ማርያም!” እያሉ ይማጸናሉ።
ባላ የሚስቱን የስቃይ ድምጽ በሰማ ቁጥር ጭንቀት ላይ ይወድቃል። ሆኖም ወንድ ነውና ጭንቀቱ እንዳይታወቅበት አፍኖ ይዞ ሌላ ጨዋታ ያመጣል። አልፎ አልፎም በአጠገቡ የተኛችውን ትንሿ ልጁን ባይበሉባው ጉንጯን ይዳስሳታል።
እንዲሁ እየተጠባበቁ እያሉ በሩቁ ጅብ እያላዘነ ሲጮህ ሰሙ። ጅብ እንዲህ ሲያላዝን በመንደር የታመመ ሰው ካለ ሊሞት ነው የሚል ፍራቻ ያሳድራል። ኬርወጌም ምጥ ከፍቶባት ስለነበረ እቤት ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ፤ ወንዱም ሴቱም በጣም ተደናገጠ።
ይኸኔ አትሼው፣ “ጅቦ ለራስህ አልቅስ!” ሲል ተራገመ። ኢብጊየታም ተከትሎ፤ “አዎን ለራሱ ያልቅስ!” አለ።
ባላ ግን ካቶሊክ ክርስቲያን ስለነበረ በዚህ ዓይነት እምነት አይረታም ነበር። ስለሆነም አትሼወና ኢብጊየታ ሲራገሙ ሰማቸውና “ቃዥታችኋል?” አላቸው። በልቡ ግን እሱም ቢሆን ሳይደነግጥ አልቀረ ይሆናል፤ ማን ያውቃል!
በዶሮ ጩኸት ሴቶቹ ካሉበት እልፍኝ ውስጥ ጫጫታ ይሰማ ጀመር። ማተቤት ገጀራዋን በትከሻዋ ላይ እንዳጋደመች እየሮጠችና እያለከለከች ከእልፍኙ ወደዚህኛው ቤት መጣች።
ባላ በባለቤቱ ላይ አንዳች ክፉ ነገር ደርሷል ብሎ በመጠርጠር ተደናግጦ፤
“አንቺ … ምን ወሬ ይዘሽ መጣሽ?” አላት።
“አባ … እማ ተገላግላለች” አለችው።
“ፈጣሪዬ ምስጋና ላንተ ይሁን” በማለት እንደወናፍ ተነፈሰ። ቀጠል አድርጎም፤
“ወንድ ነው ወይስ ሴት?” አላት
“እኔ እንጃ አባ…” ብላ ለመጠየቅ በጥድፊያ አመራች።
በመንገድ ድንጋይ አደናቅፏት፤ መች ወድቃ መች እንደተነሳች ሳታውቅ የተወለደውን ሕጻን ጾታ ጠይቃ እንደበፊቱ እያለከለከች ተመልሳ መጥጣ፣
“ወንድ ነው አባ …” አለችው።
ባላ መልሶ፤
“ፈጣሪዬ ምስጋና ላንተ ይሁን” ሲል ተነፈሰ።
አትሼወና አብጊየታ የማተቤትን የመራወጥ ሁኔታ ተመልክተው ከት ከት ብለው ሲስቁ ተሬዛ ከእንቅልፏ ነቃች። ይኸን ጊዜ ባላ ሕጻን ልጁን አንስቶ ታቅፏት ወደ እልፍኙ ተመለሰ።
በዚያ የነበሩትም ሁሉ ወንዶቹም ሴቶቹም አራሷን ተሰናብተው ወጥተው ወደየጎጆዎቻቸው ለመተኛት አመሩ።
ጠዋት ሲነጋ በርካታ ሰዎች አራሷን ‘እንኳን ማርያም ማረችሽ’ ለማለት መጡ። የኬርወጌ የልብ ወዳጅ የሆነችው ዝምወት ተማሪ ልጇን ደገሙን አስከትላ ከአጣጥ መንደር መጣች።
እቤት ስትገባም፣
“እኔ ፍርክስ … ፍርክስክስ ልበልልሽ፤ ደግመሽም ሌላ ወንድ ልጅ ውለጂ” ብላ ኬርወጌ ከተኛችበት ሥፍራ ሔዳ ሳመቻት።
ኬርወጌም እንደሷ እንዲህ እንዲያ ተፍጨርጭራ ተነስታ ግድግዳውን ተደግፋ ቁጭ አለችና በሞተ ድምጽ፤
“መገላገሌን ማን ነገረሽ ዝም? ወይስ በዛሬው ጊዜ ወሬ የሚደርሰው በነፋሽ በራሱ ነው?” ስትል ጠየቀቻት።
“የኔዋ … እኔስ ድርስ መሆንሽን አውቄ ልጠይቅሽ ስመጣ መገላገልሽን የሰማሁት እዚሁ ከጐረቤትሽ ነው እንጂ ዜናውስ ገና ከአጣጥ አልደረሰም” አለቻት።
“ቢሆንም ማልደሽ መውጣትሽ ደግ አይደለም። እራስሽ ባትጨነቂ እንኳ ለዚህ ጨቅላ ልጅሽ ማሰብ ነበረብሽ፤ በማለዳ ብርድ አስመታሽውኮ!”
ኬርወጌ እቤት ውስጥ ስለቆየች ውጩ ይበርዳል ብላ አሰበች እንጂ ውጩ ሞቃት ነበር። ሰማዩም ጥርት ያለ ነበር። ውጭ ያለው ሣር ጤዛውን አራግፎ ሽታው ከቤት ውስጥ ገብቶ ያውድ ነበር። የቤቱ ውስጥ ግን ጨለምለም ብሎ ነበር። እራሷና ጨቅላዋ የፀሐይ ጨረር እንዳያያቸው የበሩ መዝጊያ ገርበብ ተደርጎ ነበር።
የፀሐይ ጨረር ካረፈባቸው ምች ይመታቸዋል ተብሎ ይታመን ነበርና።
.
ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም
(ሣህሌ አናንቃ)
1955 ዓ.ም
.
(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)
.
I takes me to my village where i grew up to the age of 10 years old. Great memory it was real and we lived in it; currently it may be a little bit different due to the high rate of urbanization. But how could i get the book to read the full story? Please indicate where could i get it.
LikeLike
በጣምአሪፍነው
LikeLike