“መጽሐፈ ጨዋታ” (ቅንጫቢ)

“መጽሐፈ ጨዋታ” (ቅንጫቢ)

አለቃ ዘነብ

(አንድምታ መጻሕፍት – 2010 ዓ.ም – ገጽ 27-30። )

.

[ይሄ ድርሰት ከ150 አመታት በፊት የተጻፈ ውብ የአማርኛ ወግ መጽሐፍ ነው … ለቅምሻ ያህል ከአዲሱ የአንድምታ እትም እነሆ  …]

.

ክፍል 1

እግዚአብሔር እስቲሻር ሚካኤል እስቲሞት ምነው በኖርሁኝ? ገብርኤል ሲያንቀላፋ ሩፋኤል ሲደክም ሐሰተኛው ዲያብሎስ ንስሐ ይገባል።

ክረምት ሲመጣ ሰማይ እንዲከብድ የጠሉትም ሰው ሲመጣ እንደዚያ ይከብዳል። ዘወትር ከሚያጋድል አህያ ተሸክሞ መሄድ ይሻላል። ከማያስተካክል መላክተኛ የማለዳ ወፍ ትሻላለች ምነው ቢሉ ንጋቱን ትነግራለችና።

ድንጋይና ጭቃ ቢቀጣጠሉ ታላቅ ቤት ረጅም ቅጥር ይሆናሉ። እናንተም መሬታውያን ሰዎች እንደዚህ ብትረዳዱ ጥበባችሁና ኀይላችሁ ከሰማይ በደረሰ።

ኮሶና ክረምት ፊት ይመራል ኋላ ግን ደስ ያሰኛል። ድሪ ምንድር ነው ገንዘብን ለመቆራኘት የተሠራ ሰንሰለት ነው። እሬት መብላት ቢለመድ ባልተለቀቀም ነበር። ዝሙትም ላለመደው ሰው እንደዚህ ነው።

ጣዝማ እጅግ ብልሕ ናት። መሬት ቀዳ ገብታ እንደዚያ ያለ መድኃኒት የሚሆን ማር ትሠራለች። ምነው እናንተ ሰዎች ወይ ከፈጣሪ ወይም ከሰው ብልሐትን አትፈልጉምን?

የምሥራች ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ የሰው ልብ በደስታ ባሕር ይሰጥማል። እርጎን ከፍቶ ቢተውት ዝንብና ድመት ይጫወትበታል። አገርንም አቅንቶ ሰው ካላስቀመጡበት ተመልሶ ዱር ይሆናል።

ባባቱ የሚኮራ ሰው ጅል ነው። የሰው አባቱ አንድ አዳም አይደለምን? ሴትን ወንድ አንድ ጊዜ ይደርስባታል መንታ ትወልዳለች። እህልም አንዲት ፍሬ ተዘርታ ብዙ ታፈራለች። ይህ ነገር ከቶ እንዴት ነው? እንጃ ማን ያውቀዋል። ያ የጠቢቦች ጠቢብ ያውቀው እንደሆነ ነው እንጂ።

ፈረስ በብረት ልጓም ይገታል። የሕዝብም ልጓሙ ንጉሥ ነው። መቃብር መልካም ጐታ ነው ብስሉንና ጥሬውን ይከታልና። ወዳጅ ቢወዱት ይወዳል መሬትም ቢበሉት ይበላል።

በርበሬ ላይን ቀይ ሆኖ ይታያል ምነው ቢሉ በብልሐት ገብቶ ሊለበልብ። ክፉ ሰውም ቀስ ብሎ ገብቶ ኋላ ነገሩን ያመጣል።

ቸር ሰው ለወዳጁ ጠጅ ነው ፍቅሩ ያሰክራልና። ዝናም ከዘነመ በኋላ ቡቃያ ያበቅላል። ንጉሥም ከወደደ በኋላ ይሾማል።

ሸክላ እጅግ ክፉ ነው ውሀ አርሶ አሠርቶት መከታ እየሆነ እሳትን ያስወጋዋል። ክፉም ሰው እንደዚያ ነው። ወንፊት ዱቄትን እንዲነፋ ዘርዛራም ሸማ ጠጅን እንዲያወርድ ባለቤቱም ያልቻለውን ምሥጢር ሌላው ሰው አይችለውም።

ቅቤ ካይብና ካጓት እንዲለይ በላይም እንዲሆን ጻድቅም ሰው እንደዚያ ነው።

.

ክፍል 2

ደመና ሰማይን እንዲሸፍነው ንጉሥም በሰራዊቱ እንደዚያ ነው። ሳማና አብላሊት ለምለም መስለው እንዲለበልቡ መናፍቃንም ሲቀርቧቸው እንደዚያ ናቸው።

በቀስታና በዝግታ የተበጀ መዘውር ኋላ ጉልበት ይሆናል። ወረቀት መልካም እርሻ ነው ብዙ ነገር ይዘራልና። ጐታም አይሻ እርሱ ከቶት ይኖራልና።

ማር ሁለት ጊዜ ያገለግላል አንድ ጊዜ መጠጥ አንድ ጊዜ መብራት ሆኖ። ምነው ቢሉ የብልሕ ሥራ ነውና አሰርም የለው።

ሕዝብና ሕዝብ ደጋና ቆላ ናቸው ንጉሡ ግን ገበያ ነው ሁሉን ያገናኛልና። ሸክላ ከተሰበረ በኋላ ገል ነው መኳንንትም ከተሻሩ በኋላ ሕዝብ ናቸው።

ክፉ ሰው ሽንቱን በሸና ጊዜ ኋላ ጉንፋን ይሆናል ምነው ቢሉ ግብሩ ተጉድፍ የተዋሐደ ነውና። ማርና እሬትን ቢመዝኑ ማን ይደፋል እሬት ምነው ቢሉ ክፉ መራራ ነውና።

ከብዙ ቀን ደስታ ያንድ ቀን መከራ ይበልጣል። ንጉሥ ምሰሶ ነው ሠራዊት ግድግዳ ናቸው መኳንንት ግን ማገር ናቸው። ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው።

ጨው በዓለሙ ሁሉ ይዞራል ምናልባት ሰልችተው ይተውኛል ብሎ ነውን? ከሬት ጋራ ይጋባ እንደሆነ ነው እንጂ የሚለቀው የለም።

አንድ ዓይንና አንድ ዓይን ያላቸው ተጋብተው ሁለት ዓይን ያለው ልጅ ወለዱ። ይህ ነገር ምንድር ነው? አንድ ካባቱ አንዱ ከናቱ ነዋ። የዚህ ዓለም ትርፉ ምንድር ነው? መብላት መጠጣት ጥጋብና ኩራት ነው። ኩራት ምንድር ነው? እንደርሱ ሆኖ የተፈጠረውን ሰው መናቅ ነው።

ሰው ፍሪዳን አብልቶ አብልቶ ያሰባዋል በመጨረሻውም ይበላዋል። ምነው ቢሉ አብልቶ መብላት እንጂ ገበያ ነው። ወርቅ ቢያብረቀርቅ ብር ያብለጨልጫል ምነው እናንት መናፍቃን ጥቂት ጥቂት ብልሐት አታዋጡምን።

የዝንብ ብልሐቷ ምንድር ነው ሌላው የሠራውን መብላት ነው። ሰነፎች ሰዎችም እንደዚሁ ሌላ ሰው የሠራውን መብላት ይወዳሉ።

ድሀ ከመሆን ሀብታም መሆን ይሻላል ምነው ቢሉ አይቸግርምና። በምድር ከመኖር በሰማይ መኖር ይሻላል ምነው ቢሉ የዚህ ዓለም መከራው ብዙ ነውና።

ከባለጌ ፍቅር የንጉሥ ቁጣ ይሻላል። የረሀብ ጌትነቱ መቼ ነው እህል በታጣ ጊዜ ነው ምነው ቢሉ የሌለውን አምጡ ይላልና። የማጣትስ ጌትነቱ መቼ ነው የፈለጉት ነገር በታጣ ጊዜ ነው። የጥጋብስ ጌትነቱ መቼ ነው መብልና መጠጥ በተገኘ ጊዜ ነው። የመብላትስ ትርፉ ምንድር ነው ጥጋብ ነው።

.

አለቃ/ደብተራ ዘነብ

1856 ዓ.ም.

[ምንጭ] – “መጽሐፈ ጨዋታ”። አንድምታ መጻሕፍት። ፳፻፲። ገጽ 27-30።

.

(የቃላት መፍቻ)

[ከሣቴ] = ተሰማ ሀብተ ሚካኤል። (፲፱፻፶፩)። “ከሣቴ ብርሃን የዐማርኛ መዝገበ ቃላት”

.

ለንቋጣ = የሚምለገለግ፣ ልጥ ያለው አንድ አይነት ሐረግ መሳይ [ከሣቴ፤ ገጽ ፲፱]

“ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው” (ክፍል 2፤ አንቀጽ 6)

ማለገ = ሳይፈተግ ተቆልቶ የተወቀጠውና የተበጠበጠው ተልባ ተዝለገለገ፣ ልሀጭ የሚመስል ዛህል ወጣው [ከሣቴ፤ ገጽ ፻፵]

“ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው” (ክፍል 2፤ አንቀጽ 6)

.

8 thoughts on ““መጽሐፈ ጨዋታ” (ቅንጫቢ)

 1. ምስጋናዬ ይድረሳችሁ!
  የምወደውን ፅሁፍ አስነበባችሁኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
  በአለቃ ዘነብ ወግ ላይ በአንዳንድ ጠጣር ቃላት ላይ ትርጓሜውን አድርሳችሁን በዝህች ቃል ላይ ፋደት ፥ ምን እንደሚመስላችሁ እስቲ እናንተው አሳውቁን ባላችሁት መሰረት የበኩሌን ድርሻ ላካፍል።

  ከተፈራ ወርቅ አርምዴ ያአማርኛ ሥነ ቃላት በተሰኘው በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም ከታተመው አጭር መፅሀፍ ላይ ይህን የሚል ትርጓሜ በግርድፉ ይገኛል።
  ፋደት፥ መጠማጥ ፤ ሙጭጭላ(ሙጭልጭላ)።

  በ አቢሲኒያ መዝገበ ቃላት ላይ ደግሞ ይህን የሚል ትርጓሜ ያለው ፅሁፍ አገኘሁ።

  የመጐጥ (ጦች) ፤ ትግ ሙጭጭላ) ትርጉም – ዥራተ ጐፍላ ታናሽ አውሬ መጠኑ የሸሌ መጠማጥ ፤ የገሳ የዛፍ ፍሬ የሚበላ ኑሮው ቈላ ፤ መልኩ ዐመድማና ጥቍር። እሱንም አንዳንድ ሰዎች ዐይጠ መጐጥ ይሉታል።

  ምን ያህል እንደጠቀማችሁ ባላውቅም ያገኘሁት ይሄን ነው።
  ሰላማችሁ ይብዛ!

  Like

 2. አንድምታዎች…. አንጀት አርሶች፤ የልብ አድርሶች!!
  ፋደት፦ እኔ ባደግኩበት አካባቢ “ፋሮ” የሚባል ተመሳሳይ ባህሪ ያለው እንሳ አለ። ቤት ውስጥ ሾልኮ በመግባት ዶሮ እና እንቁላል ይበለል። ውሻ ወይም ሰው ሊያጠቃው ሲቀርብ ፈሱን ይፈሳል። የፈሱ ግማት አፍንጫ የሚያደነዝዝ፣ ለሳንባ የሚጎመዝዝ …እጅግ መጥፎ ሽታ አለው። ስለዚህ ፋደትም ከፋሮ ጋር ዝምድና አለው…. ወይም አካባቢያዊ መጠሪያው ተለያይቶ እንስሳው አንድ አይነት ይሆናል።

  Like

 3. እናመሰግናለን። ፅሁፉ እያዝናናኝ ነበር። ግን በዘመኑም ሆነ አሁንም ያሉ እና ስለሴቶች ደካማን ጎን ብቻ እየጠቆሙ የሚሄዱ ፅሁፎች የሚቀየሩበት ጊዜ ይናፍቀኛል። “የስስት መልክና የሴት ልብ አንድ ነው ምነው ቢሉ ወዲያው ይለዋወጣልና።” የሚለው አረፍተነገር እስካነብ ድረስ በፅሁፉ እየተደሰትኩ ነበር…ምን ያረጋል …

  Like

 4. ከአገባቡ ይሆናል ብየ እንዳሰብኩት “ፋደት” ውሻ ሲመጣባት ፈሷን በመፍሳት የምታስመልሰው ቀበሮ ናት።የፈለገ ጉልበታምና ደፋር ውሻ ቢሆን ሮጦ ከጠገቧ ሲደርስ ይመለሳል እንጅ አይነክሳትም።በሌላ በኩል በመጥፎ ጠረን የምትታወቀው ጥርኝ የምትባል በህይወት እያለች የምትጠነባ እንስሳ አውቃለሁ።

  Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s