አለቃ ዘነብ (፲፰፻፲፯-፲፰፻፷፱)

አለቃ ዘነብ (1817-1869)

ከብሩክ አብዱ

.

“ቅቤ ለመጽሐፍ ዘመዱ አይደለም … መጽሐፍ ግን ለሰው ቅቤ ነው” (መጽሐፈ ጨዋታ)

በ1924 ዓ.ም “መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” የተባለ አንድ ወግ-አዘል ድርሰት አዲስ አበባ ከተማ ታተመ። የመጽሐፉ አሳታሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የተቋቋመው ‘ጎሀ ጽባሕ ማተሚያ ቤት’ ነበር። ደራሲው ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጽሑፎቻቸው የታወቁት አለቃ ዘነብ ነበሩ። መቶ ሃምሳ አመት በላይ ያስቆጠረው ይህ የአለቃ ዘነብ ድርሰት እስከዛሬ ድረስ የአማርኛ ሥነጽሑፍ እድገት መነሻ ተደርጎ ይታያል።

ሆኖም፣ ስለኚህ ደራሲ ሕይወት ከምናውቀው የማናውቀው ያመዝናል። በመቀጠል፣ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ምንጮች (የዘመኑ ድርሰቶች፣ ደብዳቤዎች) እና ከባሕር ማዶ መረጃዎች (የጐብኚዎች ትረካ እና የሚስዮን መዛግብት) የቃረምኩትን የአለቃ ዘነብን የሕይወት ታሪክ አቀርባለሁ።

.

ከይፋት እስከ ደብረ ታቦር (1817-1847)

Bernatz Ankober
የመንደር ኑሮ በ1820ዎቿ ሸዋ

“አንድ ዓይንና አንድ ዓይን ያላቸው ተጋብተው ሁለት ዓይን ያለው ልጅ ወለዱ። ይህ ነገር ምንድር ነው? … አንድ ካባቱ አንዱ ከናቱ ነዋ” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 2 – አንቀጽ 8)

አለቃ ዘነብ በ1810ዎቹ አጋማሽ (እንዳንድ ሰነዶች 1817 ዓ.ም) በሸዋ በይፋት አካባቢ ተወለዱ። በ1820ዎቹ የልጅነታቸውንና የትምህርት ዘመናቸውን በዚያው በሸዋ ይሁን በሌላ የአገሪቱ ማዕከላት እንዳሳለፉ ለጊዜው መረጃው የለንም። ቢሆንም በአካል ያገኟቸው ሰዎች እንደሚመሰክሩት አለቃ ጠለቅ ካለ የማወቅ ጉጉት በተጨማሪ የግእዝ ሰዋስው፣ የአቡሻክር (ቀን አቆጣጠር) እና የጽሕፈት ሙያ ነበራቸው። አለቃ ዘነብን የያዛቸው ይህ የትምህርት እና የቋንቋ እውቀት ጥማትም፣ ወደፊት እንደምናየው፣ በብዙ የድርሰት መስኮች (ታሪክ፣ ወግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ፈር-ቀዳጅ እንዲሆኑ ያገዛቸው ይመስላል።

ደብተራ ዘነብ በ1830ዎቹ ግድም እንደመነኰሱ የተወሰኑ የውጪ ሰነዶች ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ መጠሪያቸው አንድም ከመነኩሴነታቸው፣ አንድም ደግሞ የባሕር ማዶ ሰዎች ያገራችንን የባህልና የማዕረግ ሥርዓት በሚገባ ካለመረዳታቸው የመነጨ ሊሆን ይችላል። ‘አባ’ ዘነብ ባዮቹም በደብረ ታቦር አካባቢ ጋፋት የሰፈሩት ‘መድፍ ሠሪ’ ሚስዮናውያን (St. Chrischona Pilgermission) ነበሩ።

tewodros
አፄ ቴዎድሮስ ከነአጃቢዎቻቸው

በ1840ዎቹ ደብተራ ዘነብ በማናውቀው ሁኔታ እጣቸው ከአባ ታጠቅ ካሳ ጋር መጣመር ይጀምራል። የቋራው ደጃዝማች ካሳም አፄ ቴዎድሮስ ተሰኝተው በ1847 ዓ.ም አገሪቱን ሲገዙ ዜና መዋዕላቸውን እንዲጽፉ የሾሟቸው ደብተራ ዘነብን ነበር። ደብተራ ዘነብም ከልጅነት ጀምሮ እስከ 1852 ዓ.ም ድረስ ያለውን የቴዎድሮስን ታሪክ (በመቅደላ ከመሞታቸው ከስምንት አመት በፊት) ውብ በሆነ አማርኛ ጽፈውታል። ይህም ፈር-ቀዳጅ ድርሰታቸው ቀዳሚው የአማርኛ ዜና መዋዕል ተደርጎ በሰፊው ይጠቀሳል።

.

ከደብረ ታቦር እስከ መቅደላ (1847-1860)

“ዝናም ከዘነመ በኋላ ቡቃያ ያበቅላል። ንጉሥም ከወደደ በኋላ ይሾማል” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 1 – አንቀጽ 10)

አለቃ ዘነብ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ስመጥር የቤተመንግሥት ባለሟል የነበሩ ይመስላሉ። በጸሐፌ ትእዛዝነታቸው እስከ 1850ዎቹ መጀመሪያ ድረስም አገልግለዋል። ከ1852 አጋማሽ እስከ መጋቢት 1860 ዓ.ም ደግሞ የመዝገብ ቤት ሹም ሆነው በመቅደላ ቆይተዋል። የዘመኑን ታሪክ ከጻፉት መሐል አንዱ የሆኑት አለቃ ወልደማርያም እንደሚሉትም አለቃ ዘነብ የድርሰት ብቻ ሳይሆን ሌላም ሙያ ነበራቸው፣

“በዚህ ዘመን በሰው ሁሉ ብዙ መከራ ነበረበት። በየሀገሩ በመቅደላም ሌሊት እየገባ የቡዳ ጅብ ሲበላ ሰውን ሁሉ አስጨነቀ። በዚህም ጭንቅ ነፍጠኛ ሁሉ መክሮ በየደጁ ሲተኩስ ብዙ ጅብ አለቀ። አለቃ ዘነብ የሚባልም ለአፄ ቴዎድሮስ የተወደደ ጸሐፊ የሸዋ ሰው ነበረ ለብቻው 11 ጅብ ከደጁ ላይ ገደለ።” (የቴዎድሮስ ታሪክ፣ ገጽ ፵፮)

Tewodros house Meqdela 2
የመቅደላ አምባ አፋፍ

ከላይ የሚነበበው ቃልም በተራው “መጽሐፈ ጨዋታ” ላይ አለቃ ዘነብ በነፍጥ ዙርያ ያነሷቸውን ወጎች በመጠኑ ያስታውሰናል፣

“ተጌጥ መልካም ማነው ወርቅና ብር፤ ለሰልፍስ መልካም ባሩድና አረር … ለሰውስ መልካም ማነው አገር፤ ለወገብስ መልካም ማነው ዝናር … ካረህ ማን ይውላል ነፍጠኛ፤ ከሜዳ ማን ይውላል ፈረሰኛ … ፍቅር ዘውድ ነው፤ መልካም ጠባይ ዝናር ነው።” (ክፍል 4፤ አንቀጽ 4-9)

እንዳጋጣሚ ሆኖ ከ1850ዎቹ እስከ 1869 ዓ.ም ላሉት አመታት ስለ አለቃ ዘነብ በርከት ያሉ መረጃዎችን እናገኛለን። ለዚህም ዋናው ምክንያት ከ1850 ዓ.ም መባቻ ጀምሮ አለቃ ዘነብ በሚስዮናውያን ሰነዶች ውስጥ መጠቀስ መጀመራቸው ነው።

captives 2
በ1860 ዓ.ም በመቅደላ የነበሩት ሚስዮናውያን እስረኞች

በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሚስዮኖች በቀላሉ ለመንቀሳቀስ አይችሉም ነበር። በአንድ በኩል፣ ወንጌልን በአደባባይ መስበክ ስለማይፈቀድላቸው በየቤታቸው ትምህርት በመስጠት እና በአገሪቷ ቋንቋዎች የታተሙ ወንጌሎችን በማከፋፈል ይሰሩ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አዳዲስ አማኞችን ወደ ሚስዮኑ እምነት (ወንጌላዊ ወይም ካቶሊክ) ሳይሆን ወደ ኦርቶዶክስ ክርስትና ማስጠመቅ ይገደዱ ነበር።

እናም፣ ሰነዶቹ እንደሚገልጹት፣ በ1850 ዓ.ም መባቻ አፄ ቴዎድሮስ በጋፋት ያሉትን ባለሙያ ሚስዮናውያን አማርኛ የሚያስጠና አንድ ሊቅ ይመድባሉ። መምህር ሆነው የተመረጡትም የያኔው ደብተራ/አለቃ ዘነብ ነበሩ። እሳቸውም እኒህን ሚስዮናውያን ቋንቋ በማስተማር ሳሉ እግረመንገዳቸውን በቅርቡ ታትሞ የተሰራጨውን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ማንበብ ሳይጀምሩ አይቀርም። በዚህም ምክንያት ብዙ ሳይቆዩ ወንጌልን የመስበክ ጠንካራ ፍላጎት አድሮባቸው ከ1851 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን ተልእኮ የተያያዙት ይመስላል።

በ1852 ዓ.ም አለቃ ዘነብ የአፄ ቴዎድሮስ ጸሐፌ ትእዛዝነታቸው አበቃ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እሳቸው የደረሱት “የቴዎድሮስ ታሪክ” በዚሁ አመት ዘገባ የሚያቋርጠው። አፄ ቴዎድሮስም በተራቸው አለቃ እንግዳን አዲሱ ጸሐፌ ትእዛዛቸው አድርገው ሲሾሙ፣ አለቃ ዘነብን ደግሞ (በግዞት ይሁን በሹመት) የመዝገብ ቤት ሹም አሰኝተው ወደ መቅደላ ላኳቸው። መቅደላም በነበሩባቸው ዓመታት (1852-1860 ዓ.ም) አለቃ ዘነብ ለአምባው ወታደሮች ወንጌልን በአማርኛ መስበክ የጀመሩ ይመስላል።

Zeneb Dawit 2
የአለቃ ዘነብ ዳዊት (መቅደላ፤ ፲፰፻፶፪)

አለቃ ዘነብ መቅደላ ሳሉ ከመዝገብ ቤት ኀላፊነታቸውም ባሻገርም በጸሐፊነት ሙያቸው ቀጥለዋል። በጊዜው ከቀዷቸው በርካታ ብራናዎችም ቢያንስ አንዱ ለትውልድ ተርፏል። ይህንንም የዳዊት ብራና በመቅደላ ሳሉ በእጃቸው የጻፉት አለቃ ዘነብ እና መልአከ ገነት ወልደ መስቀል ሲሆኑ ወቅቱም በ1852 ዓ.ም ነበር። (ወደፊት የአለቃን እና የመልአከ ገነትን እጅ ለይቶ ለማጥናት መሞከር የበለጠ ውጤት ሳይሰጥ አይቀርም።)

ChewataTewodros Tarik

አለቃ ዘነብ መቅደላ ሳሉ በርካታ ድርሰቶችን ለአገራችን ሥነጽሑፍ አበርክተዋል – “የቴዎድሮስ ታሪክ” (1852 ዓ.ም)፣ “መጽሐፈ ጨዋታ” (1856 ዓ.ም)፣ እንዲሁም “የኦሮምኛና አገውኛ መዝገበ ቃላት” (1860 ዓ.ም ግድም)። በዚህም ዘመን አለቃ ዘነብ ከሚስዮናውያኑ (Martin Flad እና Johannes Meyer) እንግሊዝኛን መማር ጀምረው ነበር። በተራቸውም ኦሮምኛን ያስተምሩ ነበር። የዘመኑ ሰነዶች እንደሚሉት አለቃ ወደፊት ወንጌልን በኦሮምኛ ለመስበክ እንዲችሉ እየተዘጋጁ የነበረ ይመስላል።

.

ከመቅደላ እስከ አድዋ (1860-1864)

“በርበሬ ላይን ቀይ ሆኖ ይታያል ምነው ቢሉ በብልሐት ገብቶ ሊለበልብ። ክፉ ሰውም ቀስ ብሎ ገብቶ ኋላ ነገሩን ያመጣል” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 1 – አንቀጽ 9)

ብዙም ሳይቆይ በ1860 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ አረፉ። አለቃ ዘነብም የደጃች ዓለማየሁ ሞግዚት ሆነው በእንግሊዙ ጦር ተመደቡ። በሞግዚትነት የተመረጡበትንም ሁኔታ በወቅቱ የእንግሊዝን መንግሥት ወክሎ በአስተርጓሚነት ያገለግል የነበረው ሶርያዊው ራሳም (Hormuzd Rassam) ሲገልጽ፣

“በኔው አመልካችነት አለቃ ዘነብ የሚባለው ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ክርስቲያን ያፄ ቴዎድሮስ የመዝገብ ቤት ሀላፊ የነበረው፣ ለዓለማየሁ ሞግዚት ሆኖ አብሮት እንዲሄድ ተፈቀደ። በኋላ ግን በየምክንያቱ አብሮት ሊሄድ አልቻለም።” (ትርጉም – ተክለጻድቅ መኩሪያ)

ምክንያቱም እንዲህ ነበር። አለቃ ዘነብ ከእንግሊዞች ጋር የጌታቸውን ልጅ ደጃች አለማየሁን ተከትለው ሰንአፈ ድረስ ተጓዙ። ሰንአፈም ላይ ከደጃች አለማየሁ ጋራ በመርከብ ተሳፍረው በግብጽ የስዌዝ ካናል ሊደርሱ ሲሉ አንድ ችግር ተፈጠረ። ስለዚህም ሁኔታ አለቃ የጻፉት የብሶት ደብዳቤ ኦርጅናሌው አማርኛ ቢጠፋም እንግሊዝኛ ቅጂው ግን ሊተርፍ ችሏል፣

NPG Ax30351; Prince (Dejatch) Alamayou of Abyssinia (Prince Alemayehu Tewodros of Ethiopia); Tristram Charles Sawyer Speedy by (Cornelius) Jabez Hughes
Capt. Speedy (ባሻ ፈለቀ) እና ደጃች ዓለማየሁ

“… Before we arrived at Suez and when we were still at sea, Captain Speedy told us ‘Alam-Ayahoo does not like you, remove, do not come near him’ … When we said, ‘Why do you separate us from the son of our Lord Theodoros?’ Basha Falaka (Capt. Speedy) replied ‘When man has too much blood, he dislikes his friend … I shall buy a vessel and take you until his heart returns to you and Alam-Ayahoo likes you again.’ And saying this Falaka took his oath by himself saying, ‘May Falaka die!’ …

 

“On the following day … Basha Falaka came and said ‘Give to me the baggage of Dedjadj Alam-Ayahoo’ and when we were delivering it fully we said to him, ‘Why, if we have offended, let us be judged in a judicial way, why do you separate us?’ … We returned without having received from him any money and paper …

Speedy Pose
‘ባሻ ፈለቀ’ አንዱን አሽከሩን አጊጦ ‘ሲማርክ’

“We have been wrong treated with great injustice. Is it then right in your country to oppress a man by subtility? To be sure the face of an Abyssinian is black, but has he not been created in the resemblance of the Trinity and been redeemed by the blood of Christ? … And now, I have written this that the Christians of England might know it.”

 

[“ታላቅ ግፍና ታላቅ በደል ደርሶብናል። በአገራችሁ አንድን ሰው አባብሎ ማታለል ነውር አይደለምን? ምንም እንኳን ሐበሻ ጥቁር ቢሆን መልኩ በአርአያ ሥላሴ አልተፈጠረምን? በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነጻ አልወጣምን? … ይህንንም አሁን የጻፍኩት የእንግሊዝ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲያውቀው ብዬ ነው።” (ትርጉም – ብ.አ)]

አለቃ ዘነብ ለ Krapf፤ ኅዳር 8፣ 1861 ዓ.ም፤ ምጽዋ።

.

በዚህም ምክንያት አለቃ ዘነብ ግብጽ ድረስ ደርሰው ደጃች ዓለማየሁን ሳይሰናበቱ፣ ኢየሩሳሌምንም ሳይሳለሙ በመመለስ ለበርካታ ወራት በምጽዋ ለእንግልት ተዳረጉ። በምጽዋ ቆይታቸውም ወቅት ከፈረንሳይ ምክትል ቆንስሉ ሙንዚገር (Werner Münzinger) ዘንድ አርፈው የተወሰኑ መጻሕፍትን የጻፉ ይመስላል። በሙንዚንገር ገፋፊነትም (እስከዛሬ ድረስ ሊገኝ ያልተቻለ) ሁለተኛውን የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ያኔ ሳያዘጋጁ አይቀርም።

Dawit 1871
“Farsoota Mottin Daawiid” 1864 ዓ.ም

በመቀጠልም ለሚስዮናዊ ሥራ እንዲሆን አራቱን ወንጌላት ወደ ኦሮምኛ በትጋት ተርጉመው ወደ ጀርመን አገር ላኩ። ለአመት ያህል ምጽዋ ከቆዩም በኋላ በመጋቢት 1861 ዓ.ም ከሁለት ሚስዮናውያን ጋር በመሆን በእንግሊዝ የታተመውን የአማርኛ ወንጌልን ለማሠራጨት British Foreign Bible Society ስር ተቀጥረው ወደ አድዋ አመሩ።

በአድዋ ቆይታቸው ወቅት (1861-1864 ዓ.ም) አለቃ ዘነብ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለአካባቢው ነዋሪዎች በማሰራጨት እና የኦሮምኛ ቋንቋ እውቀታቸውን በጥናት በማዳበር ጊዜያቸውን ያሳለፉ ይመስላል። ብዙም ሳይቆይ እሳቸው ተርጉመው (ወይም የመጽሐፉ ሽፋን እንደሚለው ‘ጽፈው’) የጨረሱት ኦሮምኛው ዳዊት አድዋ ሳሉ ታተመ።

መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የመተርጎሙንም ሥራ በማስፋፋት ከሌሎች የቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር (ዋሬ፣ ሩፎ፣ ሾለን፣ ጀገን እና ገብረሚካኤል) በመተባበር ሙሉውን አዲስ ኪዳን ወደ ኦሮምኛ ተርጉመው በሰኔ 1862 ዓ.ም አገባደዱ። ይህም ትርጉማቸው ለኦሮምኛ ሥነጽሑፍ የመጀመሪያው አዲስ ኪዳን መሆኑ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሚስዮኑ ክራጵፍ (J.L. Krapf) በ1869 ዓ.ም በራሱ ስም ያሳተመው ይህንኑ የነአለቃ ዘነብን ሥራ ነበር።

ታዲያ የአለቃ ዘነብ እና የባልደረቦቻቸው ትርጉም እንደ ፈር ቀዳጅነቱ ያህል በአንዳንድ የቋንቋው ምሁራን ግን ብዙውን የተወደደ አይመስልም። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኦሮምኛ የመለሰው ታታሪው ኦነሲሞስ ነሲብ ሥራውን ሲጀምር የነአለቃ ዘነብን ትርጉም መሠረት ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ሆኖም የነአለቃ ዘነብ የአዲስ ኪዳን ትርጉም በርካታ የፊደል ስሕተቶች፣ የቃላት አመራረጥ እና የግስ እርባታ አካሄድ ችግሮች ስለነበሩበት ኦነሲሞስ መጽሐፍ ቅዱሱን ከእንደገና ወደ ኦሮምኛ ለመተርጐም እንደተገደደ ይናገራል።

Menelik and his chiefs
ንጉሥ ምኒልክ ከመኳንንቶቻቸው ጋር

አለቃ ዘነብ አድዋ በገቡ ባመታቸው (በሚያዝያ 1862) ያልጠበቁት ደብዳቤ ከንጉሥ ምኒልክ ደረሳቸው። በመቅደላ በእስረኝነታቸው ዘመን ያውቋቸው የነበሩት የዛሬው “ንጉሠ ሸዋ” ከደብዳቤው ጋር 2,000 ጠገራ ብር ለአለቃ ዘነብ ልከው ነበር። ንጉሥ ምኒልክም በደብዳቤያቸው ውስጥ አለቃ ዘነብ በድጋሚ ግብጽ ድረስ ሄደው (ከዚህ በፊት ከዛ መድረሳቸውን ያውቃሉና) የተለያዩ መሣሪያዎችን እና የእጅ ባለሙያዎችን ቀጥረው ወደ ሸዋ እንዲያመጡ ጠየቋቸው።

.

ከአድዋ እስከ ልቼ (1864-1869)

“መልካምን መብል መልካምን መጠጥ ዓለምንም ሁሉ ቢወዱት ምን ይሆናል?

ሞት ድንገት መጥቶ አስጨንቆ በግድ ይወስዳልና” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 4 – አንቀጽ 16)

ከጥቂት አመታትም በኋላ አለቃ ዘነብ በመጋቢት 1864 ዓ.ም በሸዋ ሚስዮን ለማቋቋም አድዋን ለቀው ከሁለት ሚስዮናውያን ጋር ንጉሥ ምኒልክ ዘንድ አመሩ። መንገዳቸው ግን በችግር የተሞላ ነበር። ተከዜን ከመሻገራቸው፣ ሰቈጣ ላይ የወቅቱ የየጁ ባላባት (አሊ ብሩ) ለሁለት ወር ሙሉ አስሮ አገታቸው። ከብዙ እንግልትም በኋላ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ወረኢሉ ተገናኙ።

አለቃ ዘነብ አመጣጣቸው መቅደላ ላይ ሳሉ እንዳቀዱት ወንጌልን በኦሮምኛ ለመስበክ ነበር። ንጉሥ ምኒልክ ለካቶሊኩ አባ ማስያስ እንደፈቀዱት ሁላ፣ አለቃ ዘነብና አብረዋቸው የመጡት ሚስዮናውያንም ተመሳሳይ ወንጌልን የመስበክ ነጻነት እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገው ነበር። ሆኖም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያቀዱት ሊሳካላቸው አልቻለም። አለቃም ባላሰቡት መንገድ ቆይታቸው በያኔዋ ሸዋ ዋና ከተማ በነበረችው ልቼ እና በአንኮበር ውስጥ ሊሆን ቻለ።

አለቃ ዘነብ ልቼ ሳሉ ከንጉሥ ምኒልክ አዳራሽ ብዙም አልራቁም ነበር። ሸዋ በገቡ በሦስተኛ አመታቸው የፈረንሳይ ዜጎች ከሸዋ ወደ አፋር ሲጓዙ አንድ አደጋ ተከሰተ። በዚህም ምክንያት የፈረንሳይ መንግሥትን ለማረጋጋት በልቼ ከተማ በታኅሣስ 1867 ዓ.ም በተፈረመው ሰነድ ላይ ከውጭ አገር ነዋሪዎች፣ ከሚስዮናውያን እና ከቤተመንግሥት ባለሟሎች መሐል የምስክርነት ፊርማቸውን አለቃ ዘነብ አውለው ነበር።

አለቃ ዘነብ በሸዋ ተቀምጠው በነበረበት ወቅት “መጽሐፈ ጨዋታ” እና ሌሎች ድርሰቶቻቸው በቤተ መንግሥት እና በመኳንንት መሐል በብዛት ተቀድተው የተሰራጩ ይመስላል። በዛሬም ዘመን በእጃችን የሚገኙት የ“መጽሐፈ ጨዋታ” ቅጂዎች ሊበረክቱ የቻሉት በሸዋ ቆይታቸው ድርሰቱ ተወዳጅነትን አትርፎ ስለነበረ ሳይሆን አይቀርም።

depositphotos_13297287-stock-photo-abyssinian-warriors

ሸዋ በገቡ በአምስተኛ አመታቸው፣ በጥቅምት 1869 ዓ.ም በጉራጌ ምድር ቸሃ አካባቢ የንጉሥ ምኒልክ ጦር ዘምቶ ነበር። በዚህም ዘመቻ አብረው ተጉዘው የነበሩት አለቃ ዘነብ ባልታወቀ ሁኔታ ሕይወታቸው አለፈች። የአለቃ ዘነብን “መጽሐፈ ጨዋታ” ከማሳተማቸው ከአስር አመት በፊት ብላታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአንዱ መጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ነበር፣

“አለቃ ዘነብ የተማሩ ሊቅ ነበሩ … እርሳቸውም በውስጡ እጅግ የረቀቀ ምስጢር ያለበት መጽሐፈ ጨዋታ የሚባል መጽሐፍ ትተው ስለሞቱ ስማቸው አልጠፋም።”

.

ብሩክ አብዱ

ሰኔ 2009 ዓ.ም

.

የመረጃ ምንጮች

.

ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ)። [፲፱፻፲፯]። “የኢትዮጵያ ታሪክ” አርታዒ፤ ስርግው ገላው (2002 ዓ.ም)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፴፮]። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ“፤ (9ኛ እትም፤ ገጽ ፮-፯)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፹፩]። “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት“።

ኅሩይ ወልደሥላሴ (ብላታ)። [፲፱፻፲፭]። “የሕይወት ታሪክ”፤ ገጽ ፸፰።

ወልደማርያም (አለቃ)። [፲፰፻፸፭]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Mondon-Vidailhet, Cassimir (1904)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፪]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Littmann, Enno (1902).

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፮]። “ሐፈ ጨዋታ/ መጽሐፈ ጥበብ” አርታዒ፤ ኅሩይ ወልደሥላሴ (፲፱፻፳፬)።

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷]። የኦሮምኛና አገውኛ ግስ” (ያልታተመ)።

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷፩]። ደብዳቤ ለክራጵፍ” ውስተ “Acta Aethiopica – Vol II” Rubenson, Sven [Ed.] (1996)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷፪]። “ቁልቁሎታ መጣፎታ ከኩ ሐረዋ” (Kaku Harrawaa) አርታዒ፤ Krapf, J.L (1876)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷፬]። “ፈርሶታ ሞቲን ዳዊድ” (Farsoota Motin Dawid) አርታዒ፤ Krapf, J.L (1872)

(ያልታወቀ ደራሲ)። [፲፰፻፸ዎቹ]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Fusella, Luigi (1959).

Aren, Gustav (1978). “Evangelical Pioneers in Ethiopia”

Smidt, Wolbert (2014) “Zännäb” ውስተ Encyclopaedia Aethiopica Vol V ገጽ 140-142 

Rubenson, Sven [Ed.] (2000) “Acta Aethiopica – Vol III”

4 thoughts on “አለቃ ዘነብ (፲፰፻፲፯-፲፰፻፷፱)

  1. እጅግ ማለፊያ ሥራ ነው። እግዚአብሔር ያክብርልን። በአንተ እና በሌሎች ምሁራን ጥረት፣ “አንድምታ” በጣም ተወዳጅ እየሆነች እንደምትቀጥል አልጠራጠርም።
    ጌቴ ገላዬ ከሀገረ ጌርመንያ።

    Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s