“ዓለም እና ጊዜ” (ግጥም)

“ዓለም እና ጊዜ”

በከበደ ሚካኤል

.

.

እኔማ አቶ ጊዜ፥ ከጥንት ዠምሬ፣

ለፍጥረት ታዛቢ፥ ሆኜ በመኖሬ፣

እጅግ በረዘመው፥ በራቀው መንገዴ፣

ቸኩዬ በፍጥነት፥ ሳልፍ እንደ ልማዴ፣

መቼም አይቀርና፥ አይቶ መመልከት፣

ትልቅ ግቢ አይቼ፥ ባለ ብዙ ቤት፣

ከደጅ ሲተራመስ፥ ሰዉ ከቤት ተርፎ፣

ይመስል ነበረ፥ ንብ ያለበት ቀፎ።

ያጥሮቹ አሠራር፥ የግቢውም መድመቅ፣

የቤቶቹም ብዛት፥ በጣም የሚደነቅ፣

እንደዚህ ግቢውን፥ ሠርቶ ያሳመረ፣

ማን ይሆን? አልኩና፥ ከዚህ የሰፈረ፣

ደንቆኝ ስመለከት፥ በጣም ተገርሜ፣

ሰው አገኘሁና፥ አልኩት “በል ወንድሜ፣

የዚህ የውብ ግቢ፥ ባለቤቱ ማነው?”

“ያባት ያያቱ ርስት፥ ያንድ ከበርቴ ነው፣

ርስቱም ዘላለም፥ አለ ሳይነካ”፣

ብሎ መለሰልኝ፥ ኰርቶ እየተመካ።

 

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

 

ከዚያ ካጥር ግቢ፥ ከዚያ ሁሉ ቤት፣

ከቁመቱ ርዝመት፥ ከጐኑ ስፋት፣

አንድ ድንጋይ እንኳን፥ ጠፍቶ ምልክት፣

ያ ያየሁት ሁሉ፥ እንዳልነበር ሆኖ፣

ከግቢው ቦታ ላይ፥ አየሁ ትልቅ መስኖ።

የለመለመበት፥ አንድ ትልቅ ጨፌ፣

ተመለከትኩና፥ ልሄድ ስል አልፌ፣

አንድ ትልቅ ዛፍ ሥር፥ ተጠግቶ ጥላ፣

አንድ እረኛ አገኘሁ፥ ከብቶች ሣር ሲያበላ።

“እንደዚህ ያለ ሣር፥ የበቀለበት፣

ከመቼ ወዲህ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤

እሱም ቁጭ እንዳለ፥ ቀና ብሎ አይቶኝ፣

“ዘለዓለም ለከብቶች፥ ግጦሽ የሚገኝ፣

ከዚሁ መስኖ ነው” ሲል መለሰልኝ።

 

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

 

መስኖውም ጠፋና፥ ጨፌነቱ ቀርቶ፣

ከመስኩ ቦታ ላይ፥ ከተማ ተሠርቶ፣

የቤቱ መበርከት፥ የመንገዱ ማማር፣

የከተማው ጥዳት፥ የግንቡም አሠራር፣

የሕዝቡ አበዛዝ፥ የገበያው መድመቅ፣

ታይቶ እማይጠገብ፥ እጅግ የሚደነቅ።

ያማረች ከተማ፥ የጥበብ መዝገብ፣

ጠንተው የቆሙባት፥ ዐዋጅና ደንብ፣

ውበቷን አድንቄ፥ ስመለከታት፣

ዕድሜው የጠና ሰው፥ አግኝቼ ድንገት፣

“መች ነው የተሠራች?” ብዬ ጠየቅሁት።

እሱም መለሰልኝ፥ በጣቱ አመልክቶ፣

“ይች ትልቅ ከተማ፥ ከጥንትም አንሥቶ፣

መልኳ እየታደሰ፥ ውበቷ እያበራ፣

ይኖራል ዘለዓለም፥ ሥልጣኗ እንደ ኰራ”።

 

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

 

ከዚያች ከከተማ፥ ጠፍቶ ምልክት፣

አየሁ ከዚያ ቦታ፥ ጫካ በቅሎበት፤

ሲተራመሱበት፥ ዥብ ነበር አንበሳ፣

በያይነቱ አውሬ፥ አዕዋፍ እንስሳ፣

ሁሉም በየቋንቋው፥ ድምፁን እያሰማ፣

ለጫካው ሲሰጡት፥ የሚያስፈራ ግርማ፣

የዛፉ አበዛዝ፥ ያውሬው መበርከት፣

እጅግ አስደናቂ፥ ሆኖ አገኘሁት።

ደኑን ተመልክቼ፥ እያየሁ ስሄድ፣

አገኘሁ ያገር ሰው፥ ድንገት በመንገድ፤

“ዛፍ እንጨቱ፥ በቅሎ ጫካው የደመቀው፣

ከመቼ ወዲህ ነው?” ብዬ ብጠይቀው፣

ትክ ብሎ እያየ፥ ጫካ ጫካውን፣

እንዲህ መለሰልኝ፥ እሱም ተራውን፤

“ይህን መጠየቅህ፥ እንግዳ ነህ ለካ፣

ጥድ የሚበቅልበት፥ ግራርና ወርካ፣

ጥንቱንም ደን ነው፥ የዘላለም ጫካ”።

 

አንዱ ስፍራ ሲለቅ፥ አንዱ እየተተካ፣

ሁሉም ርስቴ ነች፥ እያለ ሲመካ፣

ሞኝነት አድሮብን፥ ሳናስበው እኛ፣

ዓለም ሰፈር ሆና፥ ሕዝቡ መንገደኛ፣

ትውልድ ፈሳሽ ውሃ፥ መሬቷም ዥረት፣

መሆኑን ዘንግቶ፥ ይህ ሁሉ ፍጥረት፣

ስትመለከቱት፥ በሰልፍ ተጉዞ፣

ሁሉም በየተራው፥ ያልፋል ተያይዞ።

.

ከበደ ሚካኤል

(1936 እና 1956 ዓ.ም)

.

[ምንጭ] – “የቅኔ አዝመራ”። ፲፱፻፶፮። ገጽ 4-8።

የበአሉ ግርማ ገጸባሕርያት

“የበአሉ ግርማ ገጸባሕርያት”

ከብሩክ አብዱ

.

በአሉ ግርማ (1931-1976 ዓ.ም) ልጅነቱን ያሳለፈው በሱጴ (ኢሉባቦር)፣ ጉርምስናውን ደግሞ በአዲስ አበባ (“ልዕልት ዘነበወርቅ” እና “ጀነራል ዊንጌት” ት/ቤቶች) ነበር። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና በMichigan State University የጋዜጠኝነትና የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቱን ተከታትሏል። የሥራ ዘመኑንም ባብዛኛው ያሳለፈው በማስታወቂያ ሚኒስትር በተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች ነበር።

በአሉ ስድስት ተወዳጅ ልቦለድ ሥራዎችን አሳትሟል። እኒህም “ከአድማስ ባሻገር” (1962 ዓ.ም)፣ “የህሊና ደወል” (1966 ዓ.ም)፣ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” (1972 ዓ.ም)፣ “ደራሲው” (1972 ዓ.ም)፣ “ሀዲስ” (1975 ዓ.ም) እና “ኦሮማይ” (1975 ዓ.ም) ናቸው። ከኒህም በተጨማሪ በርካታ መጣጥፎችን፣ ቃለ-መጠይቆችን እና ርእሰ አንቀጾችን ጽፏል።

በዚች ጽሑፍ፣ በአሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” መጽሐፉ ላይ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ የገጸባሕርያት አሳሳል ስልቶች በቅርበት ለማሳየት እሞክራለሁ።

.

“ከአድማስ ባሻገር”

ይህ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ የበቃው በ1962 ዓ.ም ነበር። ምንም እንኳን ዳግመኛ እስኪታተም ሁለት አመት ቢፈጅበትም በወጣበት ዘመን በሰፊው ተነቧል (ከ1962 እስከ 2004 ዓ.ም ዘጠኝ ጊዜ ታትሟል)። ከ1980ዎቹ ጀምሮ ደግሞ በሬድዮ ትረካ ቀርቧል።

ከአድማስ ባሻገር” የበአሉ ግርማ የመጀመሪያ የልብ ወለድ መጽሐፍ ቢሆንም በኩር የፈጠራ ሥራው አልነበረም። ከዚያ በፊት በአሉ በተለያዩ የተማሪ መጽሔቶች (የጄነራል ዊንጌቱ “Chindit” እና የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ “News and Views”) ግጥሞቹን ማቅረብ ለምዶ ነበር። ከፈጠራ ድርሰት ባሻገርም በጋዜጣና መጽሔት አዘጋጅነት (“News and Views”፣ “Addis Reporter”፣ “መነን” እና “አዲስ ዘመን”) የበርካታ አመታት ልምድ ነበረው። በኒህም አመታት በተቻለው መጠን የአዘጋጅነቱን ሚና በመጠቀም (በተለይ በ”መነን” እና “አዲስ ዘመን”) በርካታ ኪነጥበባዊ አምዶችን (ለምሳሌ “አጭር ልብወለድ”፣ “ከኪነጥበባት አካባቢ”) አስጀምሮ  ነበር።

ስለዚህ ከመጀመሪያው ልብወለዱ ኅትመት በፊት በአሉ ቢያንስ ለአስር አመታት ያህል ኪነጥበባዊ ጽሑፎችን ሲያነብ፣ ሲጽፍና ሲያዘጋጅ የከረመ ደራሲ ነበር። እናም የበኩር መጽሐፉ እምብዛም የጀማሪ ድርሰት የጀማሪ ድርሰት ባይሸት ብዙ ሊያስደንቀን አይገባም።

ከአድማስ ባሻገር” ታሪኩ በግርድፉ የሚከተለውን ይመስላል። እድሜውን በዘመናዊ ትምህርት ያሳለፈ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት (አበራ) የምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በአንድ ወገን፣ ብዙም ስሜት በማይሰጠው ሥራ በመትጋት ንብረትና ልጆች እንዲያፈራ ወንድሙ (‘ጋሽ’ አባተ) ቤተሰባዊ ግዴታውን ያስታውሱታል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ጥሪውን” በመስማት ሥራውን ለቆ ሙሉ ሕይወቱን በሰአሊነት እንዲያሳልፍ አብሮ አደጉ (ሀይለማርያም) እና አዲሲቷ ፍቅረኛው (ሉሊት) ይገፋፉታል። አበራ ግን የሚፈልገውን የሚያውቅ አይመስልምና መምረጥ ይቸግረዋል።

የአበራም ወላዋይነት በራሱ፣ በቤተሰቡ፣ በጓደኛውና በፍቅረኛው ሕይወት ውስጥ የሚያስከትሉትን ለውጦችና መዘዞች ድርሰቱ በጥልቀት ይተርካል። እግረመንገዱንም፣ ደራሲው የዛሬ ሀምሳ አመት ግድም በነበረው የአዲስ አበባ ማኅበረሰብ ውስጥ ይፋጩ የነበሩትን “ባህላዊነት” እና “ዘመናዊነት”፣ “ሀላፊነት” እና “ጥሪ”፣ “መተማመን” እና “ቅናት” በገጸባሕርያቱ በኩል ያሳየናል።

ይህ ልብወለድ ከ50 በላይ ገጸባሕርያትን አቅፎ ይዟል። ከእነዚህም አራቱ ዋና ገጸባሕርያት (አበራ፣ ሀይለማርያም፣ ሉሊት፣ ‘ጋሽ’ አባተ)፥ ሰባቱ ጭፍራ (‘እሜቴ ባፈና፣ ሰናይት ‘ሱቅ በደረቴ’ …)፥ ሃያዎቹ አዳማቂ (ሱዛን ሮስ፣ ትርንጐ፣ ሚኒስትሩ …)፥ እና ከሃያ በላይ ደግሞ ስውር ገጸባሕርያት (ወፍራም ዝንብ፣ ባይከዳኝ …) ናቸው።

‘ዋና’ ገጸባሕርያትን እንደድርሰቱ አጥንት፣ ‘ጭፍራ’ ገጸባሕርያትን ደግሞ እንደትረካው ሥጋ ልናያቸው እንችላለን። ያለኒህ አስር ግድም ገጸባሕርያት “ከአድማስ ባሻገር”ን አንብቦ ለመረዳት በጣም ያስቸግራል (አንድ ተማሪ “መጽሐፉን ወደ ተውኔት ለውጠህ ጻፍ” ወይም “ልብወለዱን ላናበቡ ጓደኞችህ በአጭሩ ተርክ” ቢባል እኒህኑ ዋና እና ጭፍራ ገጸባሕርያት መጠቀሙ አይቀርም)። በተመሳሳይ መልኩ “አዳማቂ” ገጸባሕርያትን እንደ ክት አልባሳት ብናያቸው ያስኬዳል፤ እጅጉን ባያስፈልጉም ድርሰቱን በሚገባ ያስጌጡታልና።

ታዲያ የደራሲውን ጥበብ ለመረዳት አንዱ መንገድ የፈጠራቸውን ገጸባሕርያት በምን መልኩ ተንከባክቦ እንዳሳደጋቸው ለመረዳት መሞከር ነው። በመቀጠልም፣ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ወሳኝ ባይሆንም ጠቃሚ ሚና ከሚጫወቱት ሃያ “አዳማቂ” ገጸባሕርያት አምስቱን መርጬ እንዴት አድርጎ በአሉ ግርማ እንደሳላቸው ለማሳየት እሞክራለሁ።

እኒህንም አዳማቂ ገጸባሕርያት የመረጥኩበት ምክንያት እንደሚከተለው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደራሲዎች የዋና እና ጭፍራ ገጸባሕርያት አሳሳል ላይ ልዩ አትኩሮት (እንዲሁም በርካታ ገጾችን) ይሰጣሉ። በዚህም ምክንያት፣ የገጸባሕሪ አሳሳል ችሎታቸውን በሚገባ ለመመዘን ያስቸግረናል … ብዙም ባልተካነ ደራሲ እጅ እንኳን የዋና ገጸባሕርያት አሳሳል የስኬት ሚዛን ሊደፋ ይችላልና።

በአንጻሩ፣ በልብወለዱ ወሳኝ ሚና የማይጫወቱትን “አዳማቂ” ገጸባሕርያትን ለመሳል ደራሲው በአማካይ ከአንድ ገጽ በላይ ቀለም አያጠፋም። እኛም እንደ አንባቢነታችን እኒህን መስመሮች በቅርበት በማስተዋል “ደራሲው ባለው ውስን እድል ገጸባሕሪውን በሚገባ አዳብሮታልን?”፣ “የገጸባሕሪው ልዩ የሆነ ምስል በምናባችን ሊሳል ተችሏልን?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከር እንችላለን። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ደራሲ በበርካታ ገጾች ገለጻ እና ንግግር አንድን ገጸባሕሪ በጉልበት ምናባችን ውስጥ ቢያስገባውም፣ ጥበበኛ ደራሲ ግን በአንዲት አንቀጽ ብቻ አይረሴ ምስል በአእምሯችን ሊቀርፅ ይችላል።

እናም የዚህ መጣጥፍ ጥያቄ፤ “በገጸባሕርያት አሳሳል ረገድ በአሉ ግርማ ምን አይነት ደራሲ ነው?” የሚል ይሆናል።

.

የአዳማቂ ገጸባሕርያት አሳሳል

የአንድ ልብወለድ ገጸባሕርያት ደራሲው በፈጠረላቸው ህዋ እና ባበጀላቸው ምሕዋር ይሽከረከራሉ። ይህም በሞላ ጎደል የሚቀየሰው በገጸባሕርያቱ ንግግርና በተራኪው ገለጻ ነው። የተራኪው ገለጻ የገጸባሕሪውን አጠቃላይ ገጽታ ሲወስንልን፣ የገጸባሕሪው ንግግር ደግሞ አስተሳሰቡንና ስሜቱን ቀንጭቦ ያሳየናል። በኒህም ሁለት ስልቶች በመደጋገፍ ደራሲው በኛ ባንባቢዎች ላይ የገጸባሕርያትን ምስል ለመቅረጽ ይሞክራል።

በ“ከአድማስ ባሻገር” በአሉ በርካታ የፈጠራ ህዋዎችንና ምሕዋሮችን ቀይሷል፤ የተራኪው “ሁሉን አውቅ” ባይ መለኮታዊ እይታ፣ የአበራ ውጥንቅጥ ሀሳቦችና ምኞቶች፣ የገድሉ “ሉሊት-ከበብ” ምሕዋር፣ የሀይለማርያም “አበራ-ተኮር” እሽክርክሪት … ወዘተ። በሌላ አነጋገር፣ በልብወለዱ ውስጥ አበራ የድርሰቱ “ፀሐይ” ሲሆን፣ እነ ሀይለማርያም እና ሉሊት ደግሞ ከአበራ ስበት ማምለጥ አቅቷቸው እሱኑ የሚሽከረከሩት ዓለማት ናቸው። በልብወለድም ውስጥ አብዛኛው ፍትጊያና ግጭት ያለው በነዚሁ በዋና እና በጭፍራ ገጸባሕርያቱ መሀል ነው።

በተቃራኒ መልኩ፣ በድርሰቱ ወሳኝ ሚና የሌላቸው “አዳማቂ” ገጸባሕርያት ግን ብዙ ጊዜ የተረጋጋ ህልውና ያሳያሉ። አንድም፤ ምሕዋራቸው ከዋናው ገጸባሕሪ (አበራ ወርቁ) እጅግ የራቀ በመሆኑ፣ አንድም ደግሞ፤ እንደተወርዋሪ ኮከብ ብቅ ብለው ስለሚጠፉ የጭፍራ ገጸባሕርያትን ያህል የድርሰቱ እሳትና ፍትጊያ ብዙም አያሳስባቸውም። በዚህም ምክንያት የደራሲውን ጥበብ ለመለካት ጥሩ መስፈርት ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

በመቀጠል፣ በነዚህ ለታሪኩ ወሳኝ ሚና በማይጫወቱ አዳማቂ ገጸባሕርያት ላይ ደራሲው የተጠቀመውን የአሳሳል ስልት እዳስሳለሁ።

1. ሱዛን ሮስ

“ከአድማስ ባሻገር” ትረካው የሚጀምረው ዋና ገጸባሕሪው አበራ ብቻውን በሀሳብ ባሕር እየዋኘ ማንነቱን ሲፈትሽ፣ ከዛም የድሮ ፍቅረኛውን (ሱዛን) ሲያስታውስ ነው። ተራኪው ስለዚች ገጸባሕሪ የሚከተለውን ዘርዘር ያለ ገለጻ በጥቂት ገጾች ይሰጣል (በመጽሐፉ ገጽ 8-12)፤

‘የሰላም ጓድ ልኡካን ባልደረባ’፣ ‘ያለሙዚቃ ሰውነቷ አይፍታታም’፣ ‘ውርጭ ውስጥ እንዳደረ ብረት የሚቀዘቅዝ ጭን’፣

‘ረጅም ጠጉሯ ስር ውሎ እንደዝሆን ጥርስ የነጣ ማጅራት’፣ ‘የታጠፈ ቀሚስ’፣ ‘ሲቃ የያዘው ድምጽ’፣

‘ጉንጮቿ ላይ የነበረው ደም ቁልቁል የወረደ’፣ ‘ጸሀይ ያልነካው በሽተኛ ይመስል የገረጣች’፣

‘ከሩቅ ሲመለከቱት ነጭ ከቅርብ ሲያዩት ሽሮ የሚመስል ጥርስ’፣ ‘በረጅሙ ተንፍሳ’፣

‘ረጅም ጠጉሯን በሁለት እጆቿ ጭምድድ አድርጋ’፣ ‘እጆቿ ላይ ያሉት የደም ስሮች እንደሽምጥ አጥር ተገትረው’፣

‘የቀሉት ትናንሽ ውብ አይኖቿ’፣ ‘እንባ እየፈለቀ የገረጡትን ጉንጮቿን ያርሰው’፣

‘የየሙዚቃውን ስልት በግለት በስሜት … ትጠብቅ’፣ ‘ጸሀይ እንዳየች የጽጌረዳ እምቡጥ ወከክ ትርክክ’

ከላይ የምናየው ተራ ገለጻ አይደለም። ደራሲው የተራኪውን ድምጽ በሚገባ በመጠቀም የሱዛንን ሰውነት ብቻ ሳይሆን ስሜቶቿንም በሰፊው ስሎልናል። ቢሆንም በአሉ በዚህ አላበቃም። የራሷንም አንደበት በመጠቀም የአስተሳሰቧን ህዋ ይስልልናል። ሱዛንም ስትናገር ከሌሎች አዳማቂ ገጸባሕርያት ተለይታ የምትሽከረከርባቸውን የቃላት ምሕዋር መለየት እንችላለን። እኒህም “መስጠት”፣ “ሙዚቃ”፣ “ትዝ”፣ “አብረን”፣ “ደስ/ደስታ”፣ “ደንታ”፣ “ጽጌረዳ” እና “ፍጹም” ናቸው። እስቲ ለምሳሌ ያህል ሦስቱን በቅርበት እንመልከት፤

ሙዚቃ

ሙዚቃ ስጠኝና ፍቅር ልስጥህ።”

ሙዚቃ ስጠኝ ነው የምልህ።

ያለሙዚቃ አይሆንልኝም ፍጹም አይሆንልኝም።”

ትዝ

“አብረን የሰማናቸው ጥኡም ሙዚቃዎች ትዝ ይሉኛል።”

“እያንዳንዷ ደቂቃ ትዝ ትለኛለች።”

ደስ/ደስታ

“ብልጫ ያለውን ነገር የሚመርጡ ወንዶች ደስ ይሉኛል።”

“ወንዶችን ማሞላቀቅ ደስ ይለኛል።”

“እንዳንተ ያሉ … ሳገኝ ደግሞ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል።”

ሱዛን ደምቃ የምትታይ “አዳማቂ” ገጸባሕሪ ናት። ከ“ሽሮ” ጥርሷ ጀምሮ እስከ “ደስ” የሚሏት ወንዶች በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል። በአሉ በጥቂት መስመሮች ይህን ሁሉ በምናባችን መሳሉ የሚያስደንቅ ነው። እንዲያውም ተጨማሪ ገጾች እና ሚና ቢጨምርላት “ጭፍራ” ገጸባሕሪ ሆና መመደብ ትችል ነበር።

2. ትርንጐ

ትርንጐ በድርሰቱ የአበራ የልጅነት የቤት ሠራተኛ የነበረች ናት። ተራኪው ስለዚች አዳማቂ ገጸባሕሪ የሚከተለውን ይገልጻል (በመጽሐፉ ገጽ 13)፤

‘እድሜዋ ከእርሱ እድሜ ገፋ ያለ’፥ ‘ፊቷ እንደውድቅት ጨለማ ጠቁሮ በወዝ የተንጨፈጨፈ’

‘ጠጉሯ አንድ ባንድ የሚቆጠር’፥ ‘ፍርጥምጥም ያለች ጉጭማ’

‘መደብ ላይ ተጋድማ’፥  ‘ከባይከዳኝ ጋር ስትዳራ’፥ ‘ደንግጣ ከላይዋ ላይ ስትወረውረው’

ይህ ጥሩ ምስል-ሳይ አካላዊ ገለጻ ነው። ቢሆንም ስሜቷን በሚገባ አይገልጽልንም፤ የምናውቀው ድንጋጤዋን ብቻ ነው። ታዲያ ከአንድ ገጽ ባነሰች ስፍራ ደራሲው ስሜቶቿን ከዚህ ይበልጥ ሊገልጽ ቢያዳግተው ሊያስደንቀን አይገባም (ለ“ሱዛን” አራት ገጽ መመደቡን እያስታወስን)። በተጨማሪም፣ ከአንደበቷ የምንሰማው ንግግር ተለይቶ የሚሽከረከረው በሁለት ቃላት (“ና ” እና “እንጫወት“) ዙርያ ነው፣

ና እንጫወት።”

ምን ቸገረህ እኔ አሳይሀለሁ።”

የኒህም ቃላት ምናባዊ ሀይል በንግግሯና በተራኪው ገለጻ በመደጋገፉ (‘ታጫውተዋለች’፣ ‘ከባይከዳኝ ጋር ስትዳራ’) ሳይጠነክር አልቀረም። እናም ትርንጐን ስናይ፤ እንደሱዛን ያልደመቀች፣ ግን የራሷ የሆነ ልዩ ፍካት ያላት ገጸባሕሪ ሆና እናገኛታለን። ደራሲው ይህችን ገጸባሕሪ በሚገባ ለማድመቅ ያልመረጠበትን ምክንያት ግን (የቦታ ማጠር ይሁን ለታሪኩ ሂደት ከዚህ በላይ መግለጽ አለማስፈለጉ) በእርግጠኝነት ለማወቅ ያስቸግራል።

3. ሴተኛ አዳሪ

“ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ አበራ ስሜቱን “ለማውጣት” (ለመወጣት) በተደጋጋሚ ሴተኛ አዳሪ ፍለጋ ይሰማራል። በድርሰቱ ላይ ተራኪው የሚከተለውን ገለጻ ይሰጠናል (በመጽሐፉ ገጽ 45-46፣ 88)፤

‘ቀያይ መጋረጃዎቹን እየገለጡ ከየደጃፉ ብቅ ብቅ’፥ ‘ድምጿ ጨለማውንና ጸጥታውን ቀደደው’

‘ከየሴቶቹ ቤት የሚመጣ የእጣንና የከርቤ ጢስ’፥ ‘በቀይ መብራት አንዷን ከሌላዋ መለየት አስቸጋሪ’

‘ሁለቱ ያገር ልብስ የተቀሩት … ሰውነት ላይ ልክክ የሚሉ ቀሚሶች ለብሰው’፥ ‘ዳሌዋ ሰፋ ብሎ የታየችው’

‘ሲገባ እንደሌሎቹ ወከክ ያላለችለት’፥ ‘በቅናት አይን ቆዳዋን ገፈፏት’፥ ‘የተቀባችው ሽቶ የተስማማው አይመስልም’

‘የሸማኔ መወርወሪያ ይመስል ወዲህና ወዲህ ይሯሯጣሉ’፥ ‘አንገቷን እንደእስክስታ ወራጅ እንክት’

በአሉ የሴተኛ አዳሪዎችን ገጸባሕሪያት በአንድ ክርታስ በጅምላ የሳላቸው ይመስላል። ከገለጻው ውስጥ በሚገባ ተነጥላ የምትታይ ሴተኛ አዳሪ የለችም፤ “መጋረጃ እየገለጡ”፣ “ወዲህና ወዲህ ሲሯሯጡ”፣ “በቀይ መብራት ሲዋሀዱ” ነው የምናስተውለው። በንግግራቸውም ቢሆን ሴተኛ አዳሪ ገጸባሕርያት በተወሰነላቸው የቃላት ምሕዋር (“አንቱ” እና “ኡኡቴ”) ነው የሚሽከረከሩት።

አንቱ

አንቱ ዛሬ ደግሞ ዉስኪ ይዘው መዞር ጀመሩ እንዴ?”

“ጋሼ አንቱ ምን እንጋበዝ ታዲያ?”

“ምን የሚያስቅ ነገር አገኙብኝ አንቱ?”

ደራሲው እዚህ ላይ ግለሰባዊ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ መልክ ያለው የሴተኛ አዳሪዎችን ምስል (በገለጻ እና ንግግር ታግዞ) ለመቅረጽ የመረጠ ይመስላል። በአሉም ይህን ያደረገበት ምክንያት በልብወለድ ድርሰቱ ውስጥ የሴተኛ አዳሪ ገጸባሕርያት በታሪኩ ፍሰት ላይ ወሳኝ ሚና ስለማይጫወቱ ይሆናል። ዋናው ገጸባሕሪ አበራም ቢሆን “ስሜቱን ለማውጣት” ብቻ እንደፈለጋቸው ስናስታውስ ደራሲው በጅምላ ለምን እንደሳላቸው መረዳት እንችላለን።

4. በቀለ “ሽክታ”

በቀለ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ከአበራ የመስሪያ ቤት ባልደረቦች አንዱ እና አይረሴው ነው። ተራኪው ይህን ገጸባሕሪ በሚከተለው መልክ ይገልጸዋል (ገጽ 70-73፣ 97)፤

‘ረጅም ቀጭን ቁመናውን እንደ ሽመል እያውዘገዘገ’፥ ‘የተቀባው ሽቶ ክፍሉን ሁሉ አውዶ’፥ ‘የሚናገረው በጥድፊያ’

‘ሲናገር እንደሴት ይቅለሰለሳል’፥ ‘ሲሄድም ይውዘገዘጋል’፥ ‘ልብሱ ዳለቻ ሆኖ ከሀር ጨርቅ የተሰራ’

‘ቀይ ክራቫት አስሮ’፥ ‘የፈነዳ ጽጌረዳ ቅርጽ ያለው … መሀረብ የደረት ኪሱ ላይ ሰክቶ’

‘ረዥም ዞማ ጠጉሩ በቅባት ወደኋላ ተለጥጦ’፥ ‘ዘወትር ሙሽራ’፥ ‘ሴታ ሴት መልኩ ላይ የሚወራጭ ስሜት’

‘ረጃጅም አርጩሜ መሳይ ጣቶች’፥ ‘ጀብዱ ለማውራት … ልብሱን ለማሳየት ከቢሮ ቢሮ መዞር ግዴታው’

‘እዩኝ የሚል’፥ ‘በመስኮቱ መስተዋት የክራቫት አስተሳሰሩንና የጠጉሩን አበጣጠር እያየ ሲመጻደቅ’

በአንደበቱ ንግግርም በኩል የበቀለ “ሽክታነት” በአስተሳሰቡም መሆኑን በሚከተሉት ቃላት ይታየናል።

አላማረብኝም?

“ስላንዷ ሴት የሰባ ወሬ ነበረኝ።”

ታዲያ የበቀለ “ሽክታነት” እና ጀብዱ ለወግ ያህል እንደመሆኑ፣ ሌሎች ገጸባሕርያት ንግግሩን እና ጀብዱዎቹን ከምር የወሰዱት አይመስልም። (እንዲያውም በሕይወቱ ሴት ነክቶ የማያውቅ ቢሆን አያስደንቅም!)

5. ሚኒስትሩ

በስማቸው የማይጠቀሱት “ሚኒስትሩ” በልብወለዱ ውስጥ የአበራ የበላይ በላይ አለቃ እንዲሁም የታላቅ ወንድሙ የ’ጋሽ’ አባተ ወዳጅ ናቸው። ገጸባሕሪውን ተራኪው በሚከተለው መልክ ይገልጻቸዋል (ገጽ 79-80)፤

‘የቢሯቸው ስፋትና የጠረጴዛው ግዙፍነት … የማነስ ስሜት ያሳድራል’፥ ‘ግርማ ሞገስ ሳይወዱ በግድ ያስደገድጋል’፥

‘ወፍራም ድምጽ’፥ ‘ጥያቄአቸውን ከትእዛዝ ለይቶ ለማወቅ ያዳግታል’፥ ‘ቀና ብለው ሰው አለማየት ልማድ’

‘ሰው የሚያስበውን አስቀድመው የማወቅ ችሎታ ያላቸው የሚመስላቸው’

‘ቁጭ በል ማለት አያውቁም’፥ ‘ዝም ካሉ ማሰናበታቸው’

ይህን ገለጻ ስናነብ አንዳንዶቻችን ሳንወድ በደመነፍስ የምንሽቆጠቆጥላቸውን ሰዎች ሊያስታውሰን ይችል ይሆናል – ጠንካራ ምስል-ሳይ ገለጻ ነውና። በዚህም ሳያበቃ ደራሲው በገጸባሕሪው አንደበት በርካታ የቃላት ምሕዋሮችን (“ለመሆኑ”፣ “ለማንኛውም”፣ “ልጅ/ልጅነት”፣ “ብቻ”፣ “ችሎታ”፣ “አልሰማህም?”) በምናባችን ያሽከረክራል። እስቲ ሦስቱን እንመልከት፤

ለመሆኑ

ለመሆኑ ስንት አመትህ ነው?”

ለመሆኑ ሚስት አግብተሀል?”

ብቻ

ብቻ ያስጠራሁህ ለዚህ አልነበረም።”

ብቻ አንድ ቦታ ረግተህ ለመስራት አትችልም።”

ብቻ እናንተ ወጣቶች ሁሉንም ባንዴ ለማድረግ ትጣደፋላችሁ።”

አልሰማህም?

“የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ሲባል አልሰማህም?

“ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል የሚለውን ምሳሌስ አልሰማህም?

እኒህ ተደጋጋሚ ቃላት ከተራኪው ምናባዊ ገለጻ ጋር አንድ ከራሳቸው ጋር የሚነጋገሩ “ምክር አከፋፋይ” ባለስልጣንን ምስል ይፈጥራሉ።

.

ማሳረጊያ

ደራሲው ከላይ በመጠኑ በተዳሰሱት አምስት ገጸባሕርያት አማካኝነት፤ ነጥሮ የወጣ ግለሰባዊነትን (“ሱዛን”)፣ ቡድናዊ ባህሪን (“ሴተኛ አዳሪዎች” እና “ሚኒስትሩ”)፣ አዝናኝነትን (“በቀለ ሽክታ”)፣ እንዲሁም የብዥታን ምስል (“ትርንጐ”) በሚገርም መልኩ በምናባችን በቀላሉ ለመሳል ችሏል።

በአሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ እኒህን እና የተቀሩትን 50 ገጸባሕርያት ሲስል እጅጉን ተጠቦበት እንደነበር ለማስተዋል አያዳግትም። ይህም ልብወለድ ዘመን-ተሻጋሪ ተወዳጅነትን ለማግኘት ካስቻሉት ምክንያቶች አንዱ የገጸባሕርያት አሳሳል ስልቱ ሳይሆን አይቀርም። ለበአሉ የመጀመሪያው ልብወለድ መጽሐፉ መሆኑን ስናስታውስ ደግሞ የድርሰት ጥበቡን ብስለት ያሳየናል።

ታዲያ ድርሰቱ ውስጥ የሚገኙትን የገጸባሕርያት አሳሳል ስልቶች ሙሉ በሙሉ ገና አልተገነዘብንም። የበአሉ ግርማን ጥበብ በሚገባ ለመረዳት “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ያሉትን ዋና፣ ጭፍራ እና ስውር ገጸባሕርያትንም በቅርበት ማጥናት ያስፈልጋል። በዚሁ ድርሰትም ያየነውን የገጸባሕሪ አሳሳል ስልት በሌሎቹ አምስት ልብወለዶች (“የህሊና ደወል”፣ “የቀይ ኮከብ ጥሪ”፣ “ደራሲው”፣ “ሀዲስ” እና “ኦሮማይ”) ዳብሮ ወይ ቀንጭሮ እንደሄደ ማየት ይኖርብናል። ይህንንም ለመረዳት እያንዳንዱን ልብወለድ በተናጠል፣ ከዚያም ስድስቱን የፈጠራ ድርሰቶች በንፅፅር ማጥናት ሳይጠቅመን አይቀርም።

ምናልባት ያኔ፣ የበአሉ ግርማን የገጸባሕርያት አሳሳል ጥበብ በሚገባ ተረድተናል ለማለት እንችል ይሆናል።

.

ብሩክ አብዱ

ሐምሌ 2009

.

አባሪ

(የ“ከአድማስ ባሻገር” አዳማቂ ገጸባሕርያት ንግግርና ቃላት)

.

ሱዛን

“ብልጫ ያለውን ነገር የሚመርጡ ወንዶች ደስ ይሉኛል። ምክንያቱም ለውድና ለከፍተኛ ነገሮች የሚጣጣሩ ወንዶች ሲያጋጥሙኝ እኔ ስለራሴ ያለኝ አስተያየት ውሃ እንዳገኘ ጽጌረዳ ይለመልማል።” (ገጽ 8)

ሙዚቃ ስጠኝና ፍቅር ልስጥህ።”

ሙዚቃ ስጠኝ ነው የምልህ።”

“እውር ነህ ለማየት አትችልም።” (ገጽ 9)

“ያለሙዚቃ አይሆንልኝም ፍጹም አይሆንልኝም። ፍቅሬን ለወንድ አሳልፌ ከመስጠቴ በፊት ነፍሴ ወደ ሙዚቃ አለም መግባት አለባት። ከዚያ በኋላ ነጻነት ይሰማኛል። ውስጤ እንደ ጽጌረዳ እምቡጥ ይከፈታል። ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ዝግጁ እሆናለሁ።” (10)

“አበራ ለምን እንዲህ ትላለህ? ለቀለም ደንታ እንደሌለኝ እዚህ መምጣቴ ሊያረጋግጥልህ አይችልም?” (ገጽ 10)

“መልካም ፋሲካ ስኳር ወለላዬ። የትም ብሆን አብረን የሰማናቸው ጥኡም ሙዚቃዎች ትዝ ይሉኛል። የማዝነው አንተ ለጋብቻ ፍጹም ደንታ ስለሌለህና ብዙ ሙዚቃዎችን አብረን ሳናዳምጥ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በመለያየታችን ነው። ሆኖም ቅሬታ የለኝም። እያንዳንዷ ደቂቃ ትዝ ትለኛለች።” (ገጽ 10)

“ወንዶችን ማሞላቀቅ ደስ ይለኛል። እንዳንተ ያሉ የእግር ጥፍራቸውን መቁረጥና የብብት ጠጉራቸውን መላጨት የማይችሉ ሳገኝ ደግሞ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል።” (ገጽ 12)

ትርንጐ

እንጫወት።”

ምን ቸገረህ እኔ አሳይሀለሁ።” (ገጽ 13)

የጣልያን ገረድ

“ብስብስ የወንድ ።” (ገጽ 16)

የበግ ነጋዴ

“ሀምሣ ብር።”

“ስድሳ ብር።” (ገጽ 25)

“ጮማነታቸው ላይ።”

“ከስድስት ባውንድ አይቀንስም።”

“ፋሲካ።”

“ታዲያ በግ ተራ ለምን መጡ?” (ገጽ 26)

ሴተኛ አዳሪዎች

አንቱ ዛሬ ደግሞ ዉስኪ ይዘው መዞር ጀመሩ እንዴ?” (ገጽ 45)

“ጋሼ አንቱ ምን እንጋበዝ ታዲያ?” (ገጽ 46)

“ምን የሚያስቅ ነገር አገኙብኝ አንቱ። ሄደው መሳቂያዎን ይፈልጉ።”

“ታዲያ በማን ነው?”

ኡኡቴ እርስዎ ከማን በለጡና!” (ገጽ 88)

እንጀራ አባት

“አንተ ወስላታ ተነስተህ በሩን አትከፍትም?” (ገጽ 51)

ባልቻ

“ማን ነው የቀደመኝ? ስሮጥ የመጣሁት ለተሰማ ክብሪት ልሰጥ ነበር።” (ገጽ 69)

“አበራ ምን ነው ዛሬ የከፋህ ትመስላለህ? ሀዘኑንና ብስጭቱን ለኔ ተውና ይልቅ ቡና በለን። ተሰማ እንደሆን ዛሬ እማማ የኪስ ገንዘብ አልሰጡትም መሰለኝ። (ገጽ 70)

“አርፌ ሲጃራ እንዳልቃርምበት ነው ይህ ሁሉ። ደሞዝ ጭማሪ መጥታለች መሰለኝ።” (ገጽ 72)

“ለመሆኑ ሰርግሽን መቼ ነው የምንበላው?” (ገጽ 76)

“እንዲያው ስለእግዚአብሔር ብላችሁ ሰላሳ ብር አበድሩኝ።” (ገጽ 98)

በቀለ “ሽክታ”

“ይህንን ልብስ በስንት ገዛሁት? እስቲ ገምቱ። አላማረብኝም?” (ገጽ 70)

“ፋሲካን ያሳለፍኩት ከአንዲት አገር አሸነፈች ከየምትባል ኮረዳ ጋር ነበር። ታዲያ ምን ይሆናል እያለቀሰች ስቃዪዋ ደስታ ላይሆነኝ። (ገጽ 71)

“አበሳ ነው እንጅ። ስለአንዷ ሴት የሰባ ወሬ ነበረኝ። ለሹመት ታጭተሀል እንዴ?” (ገጽ 73)

“ሉሊት ታደሰ ማን ናት?” (ገጽ 97)

“እንደኔ ያለው ወንድ ባያጋጥማት ነው። ግን ማን ነው ያልከው? አዎን ገድሉ የአበራ ጓደኛ ከሆነ አንተን ከመላክ እሱ ራሱ ለምን አይነግረውም?” (ገጽ 98)

ተላላኪ

“ሚኒስትሩ በአስቸኳይ ይፈልጉሀል።” (ገጽ 78)

ሚኒስትሩ

“ያንን ጥናት ምን አደረስከው?” (ገጽ 79)

“የእምቧይ ካብ ይሆናል ለማለት ነው? ችግሩ ሳይገባህ አይቀርም። ብቻ ያስጠራሁህ ለዚህ አልነበረም። የአባተ ወንድም አይደለህም? አዎን ትመሳሰላላችሁ። ጥሩ ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ። እኔም ራሴ ደርሼበታለሁ። ብቻ አንድ ቦታ ረግተህ ለመስራት አትችልም። ስህተት ነው። የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ሲባል አልሰማህም? ብቻ እናንተ ወጣቶች ሁሉንም ባንዴ ለማድረግ ትጣደፋላችሁ። ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል የሚለውን ምሳሌስ አልሰማህም? ብቻ ለማንኛውም ነገር ብዙ ታስቦልሀል። ልጅ እንደሆኑ ዘለአለም አይኖርም። ረጋ ብለህ ስራ። ለመሆኑ ስንት አመትህ ነው?” (ገጽ 79)

“በጣም ልጅ ትመስላለህ። ግን አርጅተሀል። ለመሆኑ ሚስት አግብተሀል?” (ገጽ 79)

“ታዲያ ምን ትጠብቃለህ? ሁሉም በልጅነት ሲሆን ያምራል። ለእድገትም ሆነ ለማንኛውም ነገር የቤተሰብ ሀላፊነት ጥሩ ዋስትና አለው። አባትህ ስመ ጥር ጀግና ነበሩ። ታዲያ አስብበት እንጂ። ችሎታ ብቻውን መቼ ይበቃልና።” (ገጽ 80)

 

“ከአድማስ ባሻገር” (ልብወለድ)

“ከአድማስ ባሻገር”

በአሉ ግርማ

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ] 

.

ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል። ከዚያ ዝምታ በዝምታ የሚመነጨው የሙዚቃ ቃና መጨረሻ የለውም። ነፍስን በሀሴት ሊያወራጭ አእምሮን ኮርኩሮ ሀሳብን በስልት ሊያስደንስ ይችላል።

አበራ ወርቁ፣ በዚያ መጨረሻ በሌለው ዝምታ ተውጦ ሙሉ የሌሊት ልብሱን ለብሶ እንደልማዱ የጣት ጥፍሩን በጥርሱ እየከረከመ ወዲህና ወዲያ በመንጐራደድ ለገላው ያሞቀው ውሀ ወደ ገንዳው እስኪወርድለት ድረስ የወትሮው ባልሆነ ትእግስት ይጠባበቃል።

ቧንቧው እንፋሎት ብቻ ስለሚተፋ ወደገንዳው የሚወርደው ውሀ ዝናብ ዘንቦ ካባራ በኋላ ከሰንበሌጥ ላይ ኮለል ኮለል እያለ እንደሚወርድ ጠፈጠፍ ስልት እየጠበቀ አንድ ባንድ ይንጠባጠባል።

“ትኩስ የህይወት ጠብታ፣ ትኩስ፣ ወፍራም የህይወት ጠብታ” የሚል ሀሳብ ላንዳፍታ አእምሮው ውስጥ እንደመብረቅ ብልጭ ብሎ መልሶ ድርግም አለ። የአበራ አእምሮ ካንድ ሀሳብ ወደሌላ ሀሳብ ስለሚጋልብ አንድ ነገር በተለይ ወስዶ እስከ መጨረሻው ድረስ ሊያስብበት አይችልም። ለዚህ ነበር ባለቅኔ፣ ወይም ደራሲ፣ ወይም ሰአሊ የመሆን ተስፋውን ውስጡ ቀብሮ ያስቀረው። ነፍሱ ግን ራሷን ባንድ ነገር ለመግለጥ ዘለአለም እንደዋተተች፣ እንደቃተተች ትኖራለች። አእምሮው ወዲያና ወዲህ እንደሚባክን ስለሚያውቅ አዘውትሮ፣ “ሀሳብ መጨረሻ የለውም፤ ቁም ነገሩ መኖር ነው፤ የኑሮን ጣእም ማወቅ። ሀሳብ የፈጠረው ግብ ካልደረሰ ውጤቱ ያው ነው፤ ምሬትና ብስጭት። አዎን፣ ሌላ ምናለና!” ይላል።

አንድ ትልቅ ወፍራም ጥቁር ዝንብ ከየት መጣ ሳይባል እንግዳ ቤት ገብቶ ጥዝዝ – እያለ አንዴ ከኮርኒሱ ጋር፣ አብዛኛውን ጊዜ ከመስኮቱ መስተዋት ጋር፣ አንዳንዴ ደግሞ ከተንጠለጠሉት ባለአራት ጡት መብራቶች ጋር እየተጋጨ ክፍሉን ውጦት የነበረውን ከባድ ዝምታ ባንዳፍታ አደፈረሰው። የዝምታው ሙዚቃ ስልቱን አጣ። አበራ መንጐራደዱን ትቶ ዝንቡን ለመግደል ይሯሯጥ ጀመር። የጧት ካቦርቱን አውልቆ፣ ዝንቡ መስኮትና ኮርኒሱ ላይ ሲያርፍ ለመግደል አንድ ሁለት ጊዜ ከሞከረ በኋላ ጥዝዝ … እያለ ሂዶ መብራቱ ላይ በማረፉ የሚያደርገው ነገር ጠፍቶት ወደላይ አንጋጦ ለጥቂት ጊዜ ተመለከተውና ተስፋ እንደመቁረጥ ብሎ ራሱን ነቀነቀ። “አሀ!” አለና ሂዶ መስኮቱን ከፍቶ ይጠብቀው ጀመር። እሱም እንዳሰበው፣ ዝንቡም በበኩሉ ይጠብቅ የነበረውን መውጫ ቀዳዳ ያገኘ ይመስል ጥዝዝ … እያለ ሹልክ ብሎ ወጣ። ከውጭ የሚመጣው ሁካታ ተወርውሮ ጆሮውን መታው። የመኪና ጋጋታ፣ ጡሩምባ፣ የበጎች ጩኸትና የሰዎች ድምጽ ባንድነት ሲሰማ የአማኑኤል ሆስፒታል እብዶች ተሰብስበው ያቋቋሙት የሙዚቃ ጓድ ይመስል ጆሮ ይጠልዛል። ቶሎ መስኮቱን ዘጋ። “እኔ ግን መውጫ ቀዳዳ የለኝም!” አለ ዝንቡን አስታውሶ።

አበራ ለጊዜው የሚኖርበት ሰፈር በየበአላቱ ቀን የበግ ገበያ ሆኖ ይውላል። የሚኖረው በመስፍነ ሀረር መንገድ ከሾላው በላይ ተስፋዬ ቀጄላ ቤት ፊትለፊት ሲሆን፣ ይሄኛው ቤት በአምስት አመት ውስጥ ዘጠነኛ ቤቱ መሆኑ ነው። ከወንድሙ ምክር መሀል አበራ ልብ ውስጥ በመጠኑ የሚገባው የቤት መስራት ጉዳይ ነው። አበራ ወርቁ ቤት አጠገብ ወይም ፊትለፊት የሚባልበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ጊዜው ሩቅ መስሎ ታየው።

ለመጀመሪያ ጊዜ በኩራት አይን የቤቱን እቃ አንድ ባንድ ይመለከት ገባ። ውጭ የደመቀ የጸሀይ ብርሀን ቢኖርም የዝምታው አዘቅትና ጽላሎት በስውር መንገድ ተዋህደው የእንግዳ ቤቱን ብርሀን ደበብ አድርገውታል። በብርሀን አይን የሚያሞቀው የምንጣፉና የሶፋዎቹ ደማቅ ቀይ ቀለም አሁን የረጋ ደም መስሏል። ወርቅማ ሆነው በጥቁር ጥለት ያጌጡት የመስኮት መጋረጃዎች በብርሀን ያላቸውን ድምቀት አጥተው ፈዝዘዋል። ከውጭ ወደ ውስጥ ሲገቡ በስተቀኝ ካለው ግድግዳ ላይ የተሰቀለው በህብረ ቀለማት ስለቀለማት የተሰራው ስእል ብርሀን በማጣቱ የቅኔው ውበት ጠፍቷል። ትኩር ብሎ ተመለከተው። ፍዝዝ ብሎ በተመሰጠ አእምሮ አየው። ስእሉን ሳይሆን በስእሉ ውስጥ አልፎ የሚመለከተው ራሱን ነበር። በከንቱ ያሳለፈውን ህይወቱን ነበር – ያለፈውንና ወደፊትም ቢሆን ሊያገኘው የሚችለው መስሎት የማይታየውን ህይወት።

“ማን ነኝ? ምንስ ነኝ? እቃ። ለዚያውም ዋጋ የሌለው የበሰበሰ እቃ። እቃ ሆኜ እንድቀር ያደረገኝ ማንነው? እኔው ራሴ? ወይስ ያፈራኝ ህብረተሰብ? ወይስ አልፌው የመጣሁት የትምህርት አቋም? የምን የትምህርት አቋም! የአቋሙ አላማስ ምን ይሆን? ላይ ላዩን የሽምጥ ለማስጋለብ! ለምን አላማ! የትምህርት አላማው እያንዳንዱ ሰው ራሱን፣ ማንነቱን፣ የተፈጥሮ ችሎታውን እንዲያውቅ ማድረግ ነበር። እኔ ግን ማንነኝ?” እያለ፣ አይኖቹን ስእሉ ላይ ተክሎ ሲያስብ ፍዝዝ ብሎ ቀርቶ ነበር። ደንዝዞ ነበር።

በስተግራ ያለው ግድግዳ ጽላሎቱን አሳርፎበት ተንጣሎ የሚታየው ራዲዮግራም የሬሳ ሳጥን መስሏል። ሱዛን ሮስ የተባለችው የሰላም ጓድ ልኡካን ባልደረባ ህይወቱ ውስጥ በድንገት ለጥቂት ወራት ባትገባ ኖሮ አበራ ይህን ራዲዮግራም ለመግዛት ሀሳብ አልነበረውም። ነገር ግን፣ ከገዛ ላይቀር የሚገዛው ነገር ሁሉ ከባድና ዋጋ ያለው መሆን አለበት። “የምቆጥበው ለነገ የሚሆነኝ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በርግጥ ስለማላውቅ ለምን ርካሽ ነገር እገዛለሁ? በርግጥ የማውቀው ዛሬን ብቻ ነው!” በማለት ሁልጊዜ ውድ እቃዎችን ይገዛል። ቤቱ ርካሽ እቃ አይገኝም።

ሱዛን ሮስ፣ “ብልጫ ያለውን ነገር የሚመርጡ ወንዶች ደስ ይሉኛል፤ ምክንያቱም ለውድና ለከፍተኛ ነገሮች የሚጣጣሩ ወንዶች ሲያጋጥሙኝ እኔ ስለራሴ ያለኝ አስተያየት ውሀ እንዳገኘ ጽጌረዳ ይለመልማል” እያለች ደጋግማ ትነግረው ነበር። ሆኖም አልጋ ውስጥ ገብታ ያለሙዚቃ መንቀሳቀስ ፈጽሞ እንደማትችል አስታወሰ። ያለሙዚቃ ሰውነቷ አይፍታታም። ያለሙዚቃ ፍቅር ሰጥታ ፍቅር መውሰድ ጨርሶ አይሆንላትም። ከስንት ማግባባት በኋላ ቤቱ የወሰዳትን ወንድ አስቀድማ የምትሰጠው ምርጫ “ሙዚቃ ስጠኝና ፍቅር ልስጥህ” የሚል ነበር። ታዲያ፣ አበራ ቤቱ ባመጣት ምሽት እንደዚያ ያለውን ምርጫ ስታቀርብለት አላመናትም። ውርጭ ውስጥ እንዳደረ ብረት የሚቀዘቅዘውን ጭኗን እየደባበሰ፣ ረጅም ጠጉሯ ስር ውሎ እንደዝሆን ጥርስ የነጣውን ማጅራቷን አንዴ በጥፍሩ እየቧጠጠ፣ አንዴ በጥርሱ እየነከሰ፣ ከንፈሯን አሁንም እየሳመ፣ ካሁን አሁን ተሸነፈችልኝ በማለት ልቡ ድው ድው፣ የደም ስሮቹ ትር ትር እያሉ ሲጠብቅ ከላዪዋ ላይ ገፍትራው ተነሳች።

የታጠፈውን ቀሚሷን እያስተካከለች፣ “ሙዚቃ ስጠኝ ነው የምልህ!” አለችው በቁጣ ቃል፣ ሲቃ በያዘው ድምጽ። ጉንጮቿ ላይ የነበረው ደም ቁልቁል ወረደ። ባንዳፍታ ጸሀይ ያልነካው በሽተኛ ይመስል ገረጣች። ከሩቅ ሲመለከቱት ነጭ፣ ከቅርብ ሲያዩት ሽሮ የሚመስለውን ጥርሷን ታፋጭ ጀመር።

“ስለግዜር ብለሽ አሁን ሙዚቃ ምን ያደርግልሻል? ልባችንን አንድ ብናደርገው እኛው ራሳችን ውብ ሙዚቃ ልንፈጥር እንችላለን – የተፈጥሮ ዳንኪራ እየረገጥን።”

“እውር ነህ፤ ለማየት አትችልም!” አለችው፤ በረጅሙ ተንፍሳ፣ ረጅም ጠጉሯን በሁለት እጆቿ ጭምድድ አድርጋ ይዛለች። እጆቿ ላይ ያሉት የደም ስሮች እንደሽምጥ አጥር ተገትረዋል። እና ከቀሉት ትናንሽ ውብ አይኖቿ እንባ እየፈለቀ የገረጡትን ጉንጮቿን ያርሰው ነበር።

“ምን!”

“ያለሙዚቃ አይሆንልኝም፤ ፍጹም አይሆንልኝም። ፍቅሬን ለወንድ አሳልፌ ከመስጠቴ በፊት ነፍሴ ወደ ሙዚቃ አለም መግባት አለባት። ከዚያ በኋላ ነጻነት ይሰማኛል፤ ውስጤ እንደጽጌረዳ እምቡጥ ይከፈታል፤ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ዝግጁ እሆናለሁ።”

“እሱን ተይው! ፍቅርሽን ለመስጠት ነፍስሽን አስቀድመሽ ለሙዚቃ መለወጥ የምትፈልጊው ለጥቁሮች ብቻ ነው? ወይስ ከብጤዎችሽም ጋር እንዲሁ ነሽ?”

“አበራ፣ ለምን እንዲህ ትላለህ? ለቀለም ደንታ እንደሌለኝ እዚህ መምጣቴ ሊያረጋግጥልህ አይችልም?”

አበራ ጊዜ አላጠፋም። በሚቀጥለው ቀን ሂዶ ራዲዮግራም ገዛ። ከዚያ በኋላ ሱዛን የየሙዚቃውን ስልት በግለት፣ በስሜት እስከተለየችው ቀን ድረስ ትጠብቅ ነበር። ጸሀይ እንዳየች የጽጌረዳ እምቡጥ ወከክ፣ ትርክክ ትልለት ነበር።

ከኒውዮርክ፣ ከሱዛን ዘንድ ትናንት የደረሰው ካርድ “መልካም ፋሲካ፣ ስኳር ወለላዬ፣ የትም ብሆን አብረን የሰማናቸው ጥኡም ሙዚቃዎች ትዝ ይሉኛል። የማዝነው አንተ ለጋብቻ ፍጹም ደንታ ስለሌለህና ብዙ ሙዚቃዎችን አብረን ሳናዳምጥ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በመለያየታችን ነው። ሆኖም ቅሬታ የለኝም፤ እያንዳንዷ ደቂቃ ትዝ ትለኛለች” የሚል ነበር። ራዲዮግራሙ ላይ አስቀምጦታል። “እሳቱ አልፎ ረመጥ፣ ረመጡ በርዶ አመድ የሆነ ትዝታ ነው” ሲል አሰበና የጧት ካቦርታውን ትከሻው ላይ ጣል አድርጐ ወደ መታጠቢያ ቤት ሄደ።

መታጠቢያ ቤቱን ያጥለቀለቀው እንፋሎት ያፍናል። የፊት መስተዋቱም፣ የመስኮት መስተዋቱም፣ ግድግዳውን ያለበሱት ነጭ ሸክላዎችም በሙሉ በላብ ደፍቀው ወርዝተዋል። ገንዳው ውስጥ የወረደው ውሀ ግን ይህን ያህል አይፋጅም። እንደፍላጐቱ ቢሆን ውሀው መፋጀት አለበት። አበራ ገላውን አሽቶ ለመታጠብ ስለሚሰንፍ ገንዳው ውስጥ በጀርባው ተንጋሎ መቀቀልን ይወዳል። በተለይ የጀርባው ነገር ጭንቁ ነው። ጀርባውን አሽቶ የሚታጠብበት ዘዴ ሊገባው አልቻለም። ለሌላ ሳይሆን ለዚህ ብቻ ሚስት ቢያገኝ አይጠላም።

የሌሊት ልብሱን አውልቆ እርቃነ ስጋውን አንድ ሁለት ጊዜ ከተንጐራደደ በኋላ በእንፋሎት ወርዝቶ የጧት ጭጋግ የመሰለውን የፊት መስተዋት በፎጣው ወለወለና ላንዳፍታ ፊቱን ተመለከተ። የቀይ ዳማ ቢሆንም ጸሀይ ያልመታው ፊቱ ገርጥቷል። የአበራ መልክ ቁንጅና ትላልቅ አይኖቹ ላይ ነው። ችርችም ያሉት ቅንድቦቹ ከኮፈናቸው ወጣ ወጣ ላሉት አይኖቹ ልዩ ውበት ይለግሷቸዋል። ሽፋሎቹ በምላጭ የተስተካከለ ይመስላሉ። በራው በመጠኑ ገለጥ ባያደርገው ኖሮ የግንባሩ ማጠር ጐልቶ በታየ ነበር። አፍንጫው ሰልከክ ብሎ ወርዶ ቀዳዳዎቹ በመጠኑ ሰፋ ሰፋ ያሉ ናቸው።

መቀስ አንስቶ ካፍንጫው ውስጥ እንደ ራዲዮ አንቴና ረዘም ብለው የወጡትን አንዳንድ ጠጉር ከርክሞ ሲያበቃ፣ አፉን በመክፈት ምላሱን ወደ ውስጥ ቀልሶ፣ ተዋጊ በሬ ይመስል ያንገት ስሮቹ እስኪያብጡ ድረስ ወደታች አቀርቅሮ፣ የታችኛዎቹ ጥርሶቹን ከውስጥ በኩል ሲጃራ ምን ያህል እንዳበለዛቸው ተመለከተ። የዛገ ቆርቆሮ መስለዋል። ሽንት እንዳሸተተ በግ ስስ ከንፈሮቹን ብልጥጥ አድርጐ ተመለከተ። ጥርሶቹ እንደወተት ባይነጡም ጸአዳ ናቸው።

ጢሙ አድጐ እንደሆን ለማየት በሁለት እጆቹ ጉንጮቹን ከታች ወደላይ መላልሶ ደባበሰ። ጢሙ አላደገም፤ ጉንጮቹ እንደህጻን ልጅ ገላ ለስልሰዋል። ብብቶቹ ውስጥና ጉያው መካከል ያለው ጠጉር ግን እንደባህታዊ ጠጉር አድጐ ተገማምዷል። የእግሩ ጥፍሮች አድገው ገሚሶቹ ተጣጥፈው ገሚሶቹ ደግሞ ተሰባብረዋል። ሱዛን የብብቱንና የጉያውን ጠጉርም ሆነ የእግር ጥፍሮቹን በየጊዜው ታስተካክልለት ነበር። እርሱ ለራሱ ሊያደርግ የማይችለውን ስታደርግለት ልዩ ደስታ ይሰማት ነበር።

“ወንዶችን ማሞላቀቅ ደስ ይለኛል። እንዳንተ ያሉ የእግር ጥፍራቸውን መቁረጥና የብብት ጠጉራቸውን መላጨት የማይችሉ ሳገኝ ደግሞ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል” የምትለው ሁሉ ትዝ አለውና፣ “ምንነው አሁን በተገኘሽ!” ብሎ በመመኘት ገንዳው ውስጥ ገብቶ በጀርባው እንደልማዱ ተንጋለለ።

የገንዳው ርዝመት ለአበራ መካከለኛ ቁመት ይህን ያህል አስቸጋሪ ሁኖ አልተገኘም። የስፖርትን ነገር እርግፍ አድርጐ የተወው ከሰባት አመት በፊት ካዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንደወጣ ቢሆንም፣ የትከሻው ስፋት፣ የወገቡ ቅጥነትና የዳሌው ስልክክ ማለት ከስፖርት አለም ተለይቶ የኖረ ሰው አያስመስሉትም።

ሰውነቱን በስንፍና ለማሸት ሲሞክር ደረቱ ላይ በቀኝ በኩል ያለውን ለሀያ አምስት አመታት አብሮት የኖረውን ትልቅ ጠባሳ ነካ። ትርንጐ ትዝ አለችው። በነፍስ ትኖር ይሆን? ሞታ ይሆን? አያውቅም። የሚያውቀው አንድ ነገር ብቻ ነው።

እድሜዋ ከእርሱ እድሜ ገፋ ያለ ነበር። ፊቷ እንደውድቅት ጨለማ ጠቁሮ በወዝ የተንጨፈጨፈ ነበር። ጠጉሯ አንድ ባንድ የሚቆጠር፣ ፍርጥምጥም ያለች ጉጭማ ነበረች። እናቱ ወይዘሮ ባፈና ሞልቶት ቡና ለመጠጣት የግል ሲኒአቸውን ይዘው መንደር ሲሄዱ፣ ትርንጐ አበራን ትጠራውና መደብ ላይ ተጋድማ፣ “ና እንጫወት” ትለው ነበር።

“ምን አይነት ጨዋታ?”

“ና ምን ቸገረህ፣ እኔ አሳይሀለሁ”

ታጫውተዋለች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከጨዋታው የሚያገኘው ደስታ እየጣመው ስለሄደ የእናቱን ከቤት መውጣት በናፍቆት ይጠባበቅ ነበር። እንዲያውም አንዳንዴ ትርንጐ ስራ ይዛ አላጫውትህም ስትለው ምርር እያለ ያለቅስ ነበር። በተለይ ከባይከዳኝ ጋራ ስትዳራ ያየ እንደሆነ ትንሿ ልቡ እርር፣ ድብን ትል ነበር። ቆየት ብለው እሱን አስወጥተው በር ሲዘጉበትማ አይጣል – ትርጉሙን ለይቶ የማያውቀው ስሜት በሰራ አካላቱ እየተሰራጨ ያብከነክነው ነበር … ያብሰለስለው ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን ጧት እናቱ ቡና ለመጠጣት ከቤት እንደወጡ አበራና ትርንጐ መደብ ላይ ወጥተው ጨዋታቸውን ቀጠሉ። ወይዘሮ ባፈና አንዴ ከቤት ከወጡ በየቤቱ ቡና አክትመው ቤት እስኪመለሱ ድረስ ጥላው ቤት ስር ክትት እንደሚል ያውቃሉ። ነገር ግን፣ ያን ቀን ለካ ስኒአቸውን ረስተው ሂደው ኖሮ ወዲያውኑ ተመልሰው መጥተው የአጥረ ግቢውን በር “ትርንጐ፣ ትርንጐ” እያሉ ሲያንኳኩ፣ ትርንጐ ደንግጣ አንዴ ከላዪዋ ላይ ስትወረውረው ጊዜ ሽንኩርት ለመክተፍ ያስቀመጠችው ቢላዋ ላይ ሂዶ በደረቱ ወደቀ። ጠባሳው አብሮት ይኖራል – ማስታወሻ ሆኖ። አሁን የት ትሆን?

የትርንጐ ትዝታና የውሀው ሙቀት ሰውነቱን አዝናንቶት ኖሮ ፍትወት አደረበት። አበራ አንድ ስሜት ካደረበት ያንን ስሜት ሳያረካ ለመቆየት አይችልም … ከዚያ በኋላ ራሱን እየጠላ አይኖቹን ከድኖ ከህሊናው ጋር ሲሟገት የመታጠቢያው ቤት በር ተንኳኳ።

“ማንነው?” ሲል ጠየቀ፣ በጐረና ድምጽ። አድሮበት የነበረው ምትሀት ከመቅጽበት አለፈ። በፍትወት ስሜት አብጦ የነበረው ሰውነቱ ባንዳፍታ ሙሽሽ አለ።

“ከእቁባቶችህ አንዷ መስዬህ ደነገጥክ እንዴ?” ሲል ውጭ የቆመው ሰው መልሶ ጠየቀው። ከፍ ዝቅም ሳይል አንድ አቅጣጫ ይዞ የሚሄድ፣ ለአበራ ጆሮ እንግዳ ያልሆነ ወፍራም ድምጽ ነበር …

.

በአሉ ግርማ

(1962 ዓ.ም)

.

(በበአሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “ከአድማስ ባሻገር”። ፲፱፻፷፪። ገጽ 5-14።

 

 

የደራስያኑ ጦርነት

የደራስያኑ ጦርነት – መንግሥቱና ጸጋዬ

ከብርሀኑ ዘሪሁን

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ እንቅስቃሴ ይልቅ፣ በጥቂቶች ኢትዮጵያውያን የሥነ ጥበብ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተፋፍሞ ይገኛል። ያልታወጀ ጦርነት ነው። አንዱ ቡድን እግር ይበጥሳል። ሌላው አንገት ለመቁረጥ ይሞክራል።

ሰሎሞን ደሬሣን በ“Addis Reporter”፣ ተቃዋሚውን አንባቢ በ“አዲስ ዘመን”፣ አሁንም ሰሎሞንን በ“African Arts” የሦስት ወር መጽሔት፣ መንግሥቱ ለማን እና ጸጋዬ ደባልቄን በ“የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ያነበበ፣ አልፎ አልፎም የእነ ዓለማየሁ ሞገስን የእነ ዮሐንስ አድማሱን ንግግር ያዳመጠ ሁሉ፣ ከመደነቅ ጋር ምናልባት ግራ ሳይጋባ አልቀረም። ስለምንድን ነው ትንቅንቁና ፍጅቱ?

ከመሠረቱ በሥነጥበብ አካባቢ የአስተያየት ግጭት አዲስ ነገር አይደለም። የመናናቅና የመቀናናት ስሜት አለ። የሥነጥበብ ሰዎችም፣ እንደሌላው ሁሉ ደካማ ፍጡሮች ናቸውና። ከዚህ ጋር ደግሞ፣ የሐሳብና የአስተሳሰብ ልዩነት ሲታከልበት መጨፋጨፍ ነው። ደግነቱ የሥነጥበብ ሰዎች በሰይፍ አይፋለጡም። በዚያው በብዕር ጫፍ መቦጫጨር ነው።

ቤርናርድ ሾው (Bernard Shaw) ቶልስቶይን “ማጫራ እንጅ ደራሲ አይደለም” ይል ነበር። በሀገራችን (ሁለቱንም በሰማይ ነፍሳቸውን ይማርና) አለቃ ታየ እና ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለገላጋይ አስቸግረው ነበር ይባላል።

ሟቹ ፕሮፌሰር ተአምራት እና ቋሚው አስረስ የኔሰው በ“ኤርትራ ድምፅ” ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ በመቃ ብዕር (እንደዛሬው ጭቃ ቀለም አልመጣም ነበርና) የሚሸቃሸቁበት ዓምድ ነበራቸው። ታዲያ፣ አንዱ እጁን አንስቶ ተማርኮ ወይም ወድቆ ድሉ የማን እንደሆነ በሚገባ ሳይለይ ሁለቱም ተዳክመው ውጊያውን ተዉት።

ምናልባት አቀራረቡ የተለየ ይመስል እንጅ የአሁኑም የሥነጥበብ አካባቢ ጦርነት በመሠረቱ ያለፈው ዓይነት ነው።

እንደጊዜያችን ዓለም ሁሉ፣ የሥነጽሑፍ ጦርነትም አራጋቢዎችና አስታራቂዎች፣ ዝምተኛ ተመልካቾች፣ ሦስተኛ ኀይል ለመሆን የሚፈልጉ ገለልተኞች አሉበት። ከዚያም ሁለቱ ኀያላን ይመጣሉ። ይህ ምናልባት ትንሽ የተጋነነ አገላለጽ ሊመስል ይችላል። ግን ከእውነተኛው በጣም የራቀ አይደለም።

እርግጥ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣

“ምን ዓይነቱ ነው! ጦርነት አትበሉት! ለማባባስ ነው!” ይላል።

አቶ መንግሥቱ ለማ ደግሞ በዚያ የለሰለሰ የዲፕሎማሲ አንደበት፣

“ኤዲያ እንዲያው እናንተ ደግሞ ነገር መጐርጐር ትወዳላችሁ! አሁን ምን ያስፈልጋል!” ይላል።

ጸጋዬ ገብረመድኅን ሦስተኛውን፣ መንግሥቱ ለማ አራተኛውን የሥነጽሑፍ ሽልማት ባይወስዱ፣ ሁለቱም ከናካቴው ባይሸለሙ ኖሮ ምናልባት ጦርነታቸው ባልተካረረ ነበር። መንግሥቱ ለማ “ከኔ ቀድሞ ማግኘት አልነበረበትም” ቢል፣ ጸጋዬ ደግሞ “ከኔ መከተል አልነበረበትም” ባይ ነው። አንደኛው ሽልማቱን በተቀበለበት ጊዜ ሌላው ምን ያህል እንዳረረና እንደተከዘ እግዚአብሔር ይወቅ። ምናልባትም ብዙ የአረቄ ጠርሙሶች ተንጠፍጥፈው አድረው ይሆናል። መሳሳብ መገፋተር፣ መቀራረብ መራራቅ፣ መፋቀር መጣላት፣ ይህ ሁሉ በሰው ተፈጥሮ የደካማነትም ባይሆን የተለመደ ባሕርይ ነው። ተፈጥሮ ነው እንበል?

ጸጋዬ ገብረመድኅን እና መንግሥቱ ለማ (ወይም በስም አወሳስ አደላችሁ እንዳንባል) መንግሥቱ ለማ እና ጸጋዬ ገብረመድኅን የመጀመርያ ግንኙነታቸውም ቢሆን እስከዚህም ድረስ የመቀራረብ ወይም የመሳሳብ ኀይል አልነበረበትም።

IMG_4943Menge portraitሁለቱ የሥነጽሑፍ ሰዎች በብዙ ረገድ አይመሳሰሉም። ጸጋዬ ጠይም ረጅም ነው። በበጋውም በክረምቱም ወፍራም ድሪቶ ሹራብ ከማዘውተሩ በቀር፣ ስለ አለባበሱና ስለ አነጋገሩ ጥንቃቄ የለውም። ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ከአፉ የሚወጡት ቃላት የእረኛ ስድቦች ናቸው። ጳውሎስ ኞኞ አንድ ጊዜ “አንደበተ እረኛ” ሲል ጠቅሶት ነበር። ብቻ በክፋት አይደለም። መሳደቡም ማቆላመጡ ሊሆን ይችላል። ንግግር ሲያደርግ ተሞልቶ እንደተለቀቀ ሞላ ይተረተራል። የሚለውን ሁሉ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ታዲያ “ምን ትንተባተባለህ!” ቢሉት ግድ የለውም።

መንግሥቱ ደግሞ ቀይ፣ ቁመናው ወደ እጥረቱ የሚያደላ፣ በሙያውም በአነጋገሩም በሁናቴውም ዲፕሎማት ነው። ከሚያዜመው ድምፁ ጋር ቀስ ብሎ ሲናገር፣ ሲጫወት፣ ሲተርብ ያውቅበታል። ይራቀቅበታል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ “ማሽሟጠጡን ያውቁበታል” ነው ያለው? አዎ! እንደ ዜማው፣ እንደ ዘይቤው፣ እንደ ቅኔው ትርጓሜ … የመንግሥቱ ለማ ምስጋና … ነቀፋና ስድብ ሊሆን ይችላል።

ተቃራኒ የማግኔት ጫፎች ይሳሳባሉ እንደሚለው የፊዚክስ ሥርዓት ቢሆን ኖሮ የሁለቱ ደራስያን ባሕርይ ሁናቴ አለመመሳሰል ሊያወዳጃቸው በተገባ ነበር። ግን ከመጀመርያው አንስቶ፣ በመካከላቸው የመቀራረብ ስሜት የተፈጠረ አይመስልም። የተዋወቁት የጸጋዬ “ቴዎድሮስ” ቴአትር (በእንግሊዝኛ) ስለመታየቱ ዶክተር ካፕላን ባዘጋጀው ግብዣ ላይ ነበር። ከዚያ በፊት አንዱ ስለሌላው ሳይሰማ አልቀረም።

የመንግሥቱ “የግጥም ጉባኤ” ዝነኛ ሆኖ ነበር። ጸጋዬም በመጀመርያ ቴአትሩ አቶ አሐዱ ሣቡሬ በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ ካደፋፈሩትና “የሾህ አክሊል”ንም ካቀረበ ወዲህ ስሙ በጋዜጣ ላይ እየተደጋገመ መውጣት ይዞ ነበር። ምናልባት ያን ጊዜ ለወጉ ለማዕረጉ እጅ ተጨባብጠው አንዳንድ መልካም ቃላት ተለዋውጠው ይሆናል። ዛሬ ጸጋዬ፣ “ያን ቀን ‘እንዴ እንዴ ደኅና ሥር የያዝክ ይመስለኛል’ (በእንግሊዝኛ) ሲል መንግሥቱ የተናገረው ትዝ ይለኛል” ይላል። ልዩ ስሜትና ትርጓሜ በማሳደር የታወሰው ከጊዜ በኋላ ሳይሆን አይቀርም።

ምክንያቱም፣ ከዚያ በኋላ ለአጭር ጊዜ መቀራረብ ጀምረው ነበር። ሁለቱ ብቻ አይደሉም። ሁለቱን ጨምሮ፣ ጥቂቶች ዘመናውያን ደራሲዎች የሥነግጥም ምንባብ ብጤ አቋቁመው ነበር። እንደ ሀገራችን ማኅበር ሁሉ አንድ ቀን ከአንዱ ቤት፣ ሌላ ቀን ከሌላው ቤት ይሰበሰባሉ። ጠላ ባይጠመቅ ዳቦ ባይጋገር ውስኪው፣ አረቄው፣ ቢራው፣ ለስላሣ መጠጡ ፉት እየተባለ አንዱ ቅኔውን ወይም ሥነግጥሙን ያነባል። በኋላም ይተቻቹበታል። የክበቡ ተግባር ይህ ነበር። በኋላም የሥነግጥም ምንባቡ በቀ.ኃ.ሥ ኪነጥበባት ወቲያትር ቤት ውስጥ እንዲደረግ ታስቦ ነበር። በመካከሉ የክበቡ አቋም እንደ በረዶ ሟሸሸ። ጸጋዬ እንደሚለው ለመሟሸሹ ዋናው ምክንያት መንግሥቱ ነው።

በመካከሉ፣ ጦርነቱን ያባባሰው የዳካሩ “የጥቁር ዓለም ሕዝብ የሥነ ጥበብ በዓል” መጣ። ምናልባት ስለ በዓሉ በመጀመርያ ያወቀ እሱ ብቻ ሊሆን ቢችል ባይችል፣ ስለ ተካፋይነቱ ጉዳይ በመጀመርያ ወደ ዳካር ሂዶ ከሴንጎር (Léopold Sédar Senghor) ጋር የተነጋገረው ጸጋዬ ነበር።

Senghorበዚያን ጊዜ ጸጋዬ “Oda Oak Oracle” የተባለውን የእንግሊዝኛ ድራማ አዘጋጅቶ ነበር። ስለ በዓሉ አስቀድሞ ስላወቀ አዘጋጅቶት ለበዓሉ አቅርቦት እንደሆን አስተያየት የማንሰጥበት ሌላ ጥያቄ ነው። ያን ጊዜ መንግሥቱ በውጭ ሀገር ቋንቋ የተጻፈ ድራማ አልነበረውም። በኋላም የአቶ ከበደ ሚካኤል “አኒባል” እንዲሄድ መደረጉ ይታወሳል። ወዲያውም በውጭ ሀገር ቋንቋ ተተርጉሞ ነበር።

ጸጋዬ እንደሚለው “Oda Oak Oracle” እንዳይሄድ በዚህም በዚያም ብሎ ያስቀረው መንግሥቱ ለማ መሆኑ ነው። ያን ሰሞን በሥነጥበብ ሰዎች አካባቢ የሚሰማው ሁሉ ራሱ አንድ ረጅም ሐተታ ይወጣዋል።

አንዱ ወገን፣

“በውጭ ሀገር ቋንቋ ማቅረብ ግድ ከሆነ ‘Oda Oak Oracle’ ግሩም ሥነጽሑፍ ነው። የእንግሊዝ ማሳተሚያ ድርጅት ሳይቀር የተቀበለው። ያም ባይሆን እንግሊዝኛው ‘ቴዎድሮስ’ አለ። የአኒባል ታሪክ ታሪካችን አይደለ። ባህላችን አይደል! ምንድነውኮ የሚሰራው?” ይላል።

የሌላው ወገን ደግሞ ሥራ አልፈታም፣

“እስቲ እግዜር ያሳያችሁ! ዋርካ የሚመለክበት፣ ሕፃን በአምልኮ የሚታረድበት የኢትዮጵያን ባህል፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ይወክላል እንዴ? የምዕራብ አፍሪቃ ታሪክ ከሆነ እነርሱው አሳምረው ያቀርቡታል” ይሉ ነበር።

ከግል የሰብአዊነት ስሜት በቀር በሁለቱ ደራስያን የአማርኛ ሥነጽሑፍ አስተሳሰብና አቀራረብ መካከል ልዩነት አለ።

Shilimat

በመጀመርያ የአስተሳሰብን ጉዳይ እንውሰድ። አስተሳሰባቸውም የወጡበትን አካባቢ የሚጠቅስ ሊሆን ይችላል። መንግሥቱ ለማ፣ አነጋገሩ የአማራ አማርኛ፣ ግዕዝ አዋቂ፣ ባይዘርፍም ቅኔ የቀማመሰ፣ የሰዋስው ሥርዓት አክባሪ ነው። ታዲያ የአማርኛ ሥነጽሑፍ በአማራ ሥነባህል፣ የአማራ ሥነባህል በቤተክህነት ሥነጥበብ፣ የቤተክህነት ሥነጥበብም በግዕዝና በቅኔ በሰዋስውና በአግባቡ የተመሠረተ ስለሆነ መጠበቅ አለበት ቢል ያስኬደዋል ማለት ነው።

በጸጋዬ አስተሳሰብ ደግሞ ቅኔን ለማወቅ መቃብር ቤት ማደር አያስፈልግም፣ “ቅኔ ከግዕዝ የተወለደ ነው። ቅኔና ሥነግጥም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ደግሞ ዛሬ ጊዜ አማርኛ ኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ሆኖ መታየት አለበት። ኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያዊኛም በመሆኑ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሜትና አስተሳሰብ፣ ምኞትና ፍላጎት ህልውናና አኗኗር የሚገልጥ የሚተረጐም መሆን አለበት። ስለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ስናስብ ከጠባብ አስተያየት መውጣት አለብን” ይላል።

Tsegaye_Gabre-Medhin

ጸጋዬ ስለ ቅኔ ችሎታው እጥረት ሼክስፒርን ይጠቅሳል፣

“ሼክስፒር በዚያን ጊዜ በሥነጽሑፍ ዓለም እንደ ትልቅ ቁምነገር በሚታየው በላቲንና በግሪክ በጣም ደካማ ችሎታ ነበረው። ነገር ግን ቃላት ፈጥሮ፣ ቃላት ከየትም ወርሶና አዋርሶ፣ የሚያፍነውንና የሚያስጨንቀውን የሰዋስው ደንብ ጥሶ፣ የእንግሊዝን ሥነጽሑፍ ከፍተኛ ብቃት ሰጠው።

“ለምሳሌ፣ ‘ጉዲፈቻ’ የሚለው ቃል በአማርኛ ምትክ አይገኝለትም። ‘ማደጎ’ የሩቅ ተመሳሳዩ ነው። ታዲያ ከኦሮምኛ መጣ ከወላይትኛ ለምን አንጠቀምበትም? ዞሮ ዞሮ ሥነጽሑፋችንን ያበለጽግልናል” ይላል ጸጋዬ።

እንደ ዳካሩ በዓል በቅርቡ አልጀርስ ላይ የሚደርገው የፓን አፍሪቃን የሥነጥበብ በዓል ደግሞ ለሁለቱ ደራስያን አንድ ሌላ የጦርነት መስክ ሳይሆን አልቀረም።

ብቻ አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። መንግሥቱ ለማ “ያላቻ ጋብቻ”ን በእንግሊዝኛ ተርጉሞ ተጨዋቾቹን በማሠልጠን ላይ ይገኛል። ካሁን ቀደምም በአንዳንድ የውጭ ዩኒቨርስቲዎች ቴአትሩ ታይቷል አሉ።

“እኔ አቀርባለሁ። መቸም መምረጡ የዳኞች ፈንታ ነው” ካለ በኋላ፣ “ለነገሩ ግን፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቴአትር ወደ አልጀርስ መላኩ ለፖለቲካ የሚበጅ ይመስልሃል? ሰማኸኝ ወይ፣ በእኔ ቴአትር ስንኳ አንድ ሐጅ ካለበት” ሲል በቴሌፎን ያጫውታል።

ጸጋዬ ለአልጀርሱ በዓል ያሰበው ቴአትር ደግሞ ገና ለሕዝብ ያልቀረበ፣ “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የሚል ነው። በጸጋዬ ግምት፣ ኢትዮጵያ የምትመካበት ዋና ሥነባህል፣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነፃነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ ነው። የጴጥሮስ አሟሟት ያኮራናል።

“ግን ቴአትሩን ያዘጋጀሁት ከመንግሥቱ ጋር ለመወዳደር ወይም አልጀርስ ለመሄድ አይደለም” ይላል።

“ ‘የከርሞ ሰው’ን ከፒንተር (Harold Pinter) ወስደህ ነው፤ ሼክስፒርንም በደንብ አልተረጐምክም ይልሃል” አልነው ጸጋዬን።

“ከየትም አምጥቶ፣ ሌላ ‘የከርሞ ሰው’ ይጻፍ እስቲ! እርሱም ይቅር፣ ‘ሐምሌት’ን ይተርጉምና እንይለት። ይተያይ። እንዲሁ ከመንቀፉ የሚያዋጣው ይኸው ነው” ሲል መለሰልን።

Mengistu smiling 2

ለማበላለጥና ለማባለጥ ሳይሆን፣ የጸጋዬ ድርሰት ቁምነገር ሲጫነው፣ የመንግሥቱ ለማ ወደ ቀልድ ያጋድላል። የጸጋዬ ጽሑፍ ስሜትን ይወጋል። ጸጋዬ በድርሰቱ ስሜት ውስጥ ራሱ ገብቶ እየተሰማው የሚጽፍ ይመስላል። በተመልካችና በአንባቢ ላይም ተመሳሳይ ስሜት ያሳድራል።

ለምሳሌ፣ ‘ጴጥሮስ ያችን ሰዓት’ን እንውሰድ። ጸጋዬ የጴጥሮስ ጭንቀት፣ የጴጥሮስ ሰቀቀን የተሰማው ይመስላል። የቴአትሩ ተመልካችም ሳይወድ በግድ ወደ አቡነ ጴጥሮስ የጭንቀትና የሰቀቀን ዓለም ውስጥ መግባት አለበት።

የመንግሥቱ ለማ አቀራረብ ደግሞ የተመልካችና የታዛቢ ዓይነት ነው። ሊያስቅ ሊያስደስት ይችላል። ግን የተካፋይነት ስሜት አያሳድርም። ለምሳሌ፣ ‘መጽሐፈ ትዝታ’ን ስናነብ የማናውቀው ሌላ ዓለም ይታየናል። በስሜት በዚያ ዓለም ውስጥ እንድንኖር ግን አያደርገንም። ‘ያላቻ ጋብቻ’ም እንዲሁ ነው። ታላቋ እሜቴ ሲቆጡ፣ በለጤ ቡና ስታቀርብ፣ ባሕሩና በለጤ ሲሽኮራመሙ እያየን ከመደሰትና ከመሳቅ በቀር ወደ ስሜት ዓላማቸው ውስጥ አንገባም።

 

ታዲያ የሁለቱም ዓይነት ሥነጽሑፍ ዓለም ውስጥ ቦታ አላቸው። ተፈላጊዎች ናቸው። በየፊናቸው በየተሰጥኦዋቸው መወዳደር ይችላሉ።

የሚበጀው ግን ቀና ውድድር እንጅ አጉል ፉክክር አልነበረም።

.

ብርሃኑ ዘሪሁን

1961 ዓ.ም

.

(በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “መነን” መጽሔት። ግንቦት ፲፫፣ ፲፱፻፷፩። ገጽ ፲፮-፲፰።

“ባሻ አሸብር በአሜሪካ” (ግጥም)

“ባሻ አሸብር በአሜሪካ”

ከመንግሥቱ ለማ

.

 

የዛሬ አሥር ዓመት፥ በታላቅ ሹመት

አሜሪካ ልኮኝ፥ ነበረ መንግሥት፤

ዋሽንግቶን ገብቼም፥ ዋልሁ አደርሁኝና

ሽር ሽር ስል ሳለ፥ ባንድ አውራ ጐዳና

አላፊ አግዳሚውን፥ ጥቁሩን ነጩን

ሳይ ስመለከተው፥ በኢትዮጵያዊ ዐይን

የውሀ ጥም ደርሶ፥ ስላረገኝ ቅጥል

ከመንገድ ዳር ካለች፥ ካንድ ትንሽ ውቴል

ጐራ አልኩና፥ ገና ከወምበር ላርፍ ስል

ተንደርድሮ መጣ፥ የውቴሉ ጌታ

አማረው ቋመጠ፥ ከጀለው ሊማታ፤

“አብዷል ሰክሯል እንዴ? ምንድን መሆኑ ነው?

በል ንካኝ በዱላ፥ ግንባርህን ላቡነው!”

ብዬ ስነጋገር፥ ሰምቶ ባማርኛ

አሳላፊው ሆነ፥ አስታራቂ ዳኛ፤

ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፥ እንዳገራችን ሕግ

አክብሮ ጠየቀኝ፥ ምን እንደምፈልግ፤

እኔም ጐራ ያልሁት፥ የሚጠጣ ነገር

ለመሻት መሆኑን፥ ነግሬ ከወንበር

“ይቅርታዎን ጌታ፥ አዝናለሁ በጣሙ

ምናምኒት የለም፥ በከንቱ አይድከሙ”

አለና እጅ ነሣኝ፥ ሳቁን እየቻለ

“ውሀም የለ?” ብለው፥ በሳቅ ገነፈለ፤

ቤቱን የሞላው ሰው፥ ሁሉም አጨብጭቦ

“ብራቮ!” ተባለ፥ “ብራቮ! ብራቮ!”

በጣም ተገርሜ፥ ደንቆኝ ‘ያየሁት

ከዘራየን ይዤ፥ ሄድሁኝ ወጣሁት፤

ሀሳብ ገብቶኝ እደጅ፥ ሳሰላስል ቁሜ

ያን ቂዛዛ መስኮት፥ ባስተውለው አግድሜ

አራዳ ግሪኮች፥ እንደሚሸጡት

ያለ በያይነቱ፥ አየሁኝ ብስኩት፤

ትዝ አለኝ “አራዳ አዲሳባ ሆይ

አገርም እንደ ሰው፥ ይናፍቃል ወይ?” …

አጐመዠኝ በሉ፥ ሳይርበኝ ጠግቤ

አስተውለው ጀመረ፥ መስኮቱን ቀርቤ፤

የምገዛውንም፥ በልቤ ቆጥሬ

ዳግም ልገባ ስል፥ በስተበሩ ዞሬ

ዘወር ብዬ አያለሁ፥ የውቴሉ ጌታ

ተኩሮ  ያየኛል፥ ወደኔም ተጠጋ

“ስንት ነው ሰውዬ፥ ያንዱ ብስኩት ዋጋ?”

የያዘው አባዜ፥ ብሎት አላናግር

ዐይኑ ደም ለበሰ፥ ይጉረጠረጥ ጀመር፤

“ዓለም ሁሉ ያውቃል፥ መሆኔን ታጋሽ …

ትግሥቴ አሁን አልቋል

ጥፋ ብረር ሽሽ! …

አገጭህን በቦክስ፥ ሳላፈራርሰው

ይህ ፈጠጤ ዐይንህን፥ እዚህ ሳላፈሰው

እሱቄ መግባትህ፥ አንሶህ አሁንስ

መስኮቴ ፊት ደሞ፥ ልትልከሰከስ?!

ገበያ አላገኝም! ደምበኛዎቼም

እዚህ አንተን ካዩ፥ ዳግመኛ አይመጡም

ሥራ ሥራ እኮ ነው፥ አይገባህም እንዴ?

ወግድ! አትገተር፥ ይቋረጣል ንግዴ!”

ይህንን እንዳለ፥ ቁጣው ጠና ጋለ

አገጨና ጉንጨም፥ በቡጢ ነገለ

በቦክስም አይለኝም፥ መልሶ መልሶ!

እስኪሸረፍ ድረስ፥ ጥርሴ በደም ርሶ!

ዠለጥ አደረግሁት፥ በያዝሁት ከዘራ

ግና አልጠቀመውም፥ ዘበኛ ተጣራ፤

ፖሊስ ቢሮ ሄድን

እሱ ተለቀቀ

አሸብር ከልካይ ግን፥ እወህኒ ማቀቀ፤

ማን ሊሰማኝ እዚያ፥ ዘሬን ብቆጥር

ብሸልል ባቅራራ፥ ወይስ ብፈክር

ደረቴ ላይ ያለው፥ ያገሬ ባንዲራ

ያምራል ተባለ እንጂ፥ ከብሮም አልተፈራ!

የሞጃው ተወላጅ፥ የጠራሁት መንዜ

ሸጐሌ ሻንቅላ፥ ተብዬ መያዜ

በግፍ እንደሆነ፥ ባሰት በውሸት

አቃተኝ ማነንም፥ ከቶ ማስረዳት፤

ሲቸግረኝ ጊዜ፥ አንዱን ተጠግቼ

‘ሻንቆን’ እንዲህ አልሁት፥ ነገሬን አስልቼ፤

“ሰማኸኝ ወንድሜ፥ አላሳዝንህም

በሰው ጠብ ገብቼ፥ በከንቱ ስደክም?

“አውቃለሁ ከጥንትም፥ ነጭና ሻንቅላ

በቂም እንደኖረ፥ ሲዋጋ ሲጣላ

እኔ ግን ሐበሻው፥ ምን ወገን ልለይ

በማይነካኝ ነገር፥ ለምን ልሰቃይ?

እንካ … ጠጉሬን እየው፥ … ሸጐሌ አይደለሁም

ፊቴን ተመልከተው … እንዳንት አልጠቆርኩም

ቀይ ዳማ ነኝ … እየኝ፥ ይሁን ጠይም ልባል …

እኔን መቁጠሪያ ራስ፥ የሚለኝ ሰው አብዷል!

“ዘራችንም ቢሆን፥ ከነገደ ሴም

ሲወርድ የመጣ ነው፥ ከዳዊት ካዳም

የንግሥተ ሳባን ታሪክ፥ ሰምተህ የለ?

ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ ተባለ …

ዛጔማ ከገረድ፥ ነው የተወለደ …

አያወጣው ወጥቶ፥ ከዙፋን ወረደ፤

የካም ልጆች ናችሁ፥ እናንተ ጥቁሮች

ፈንጆችም ናቸው፥ የያፌት ልጆች …”

ብዬ እንደጀመርኩኝ፥ ታሪክን ላስጠናው

ባጭሩ አቋረጠኝ፥ ትግሥት አጣ ሰሚው፤

“እንዲህ ያል ንግግር፥ ያሰኛል አላቲ!

ባሻ አሸብር ከልካይ፥ ልጠይቅህ እስቲ

ገና አንተ ነህና፥ ኢትዮጵያዊ

አይደለሁም ልትል፥ ጥቁር አፍሪካዊ?!

“ምን ይሆናል እንጂ፥ አንተን ላይዘልቅህ

ነበረኝ ባያሌው፥ ብዙ እምነግርህ …

“ቁጥርህ ከማን እንደሁ፥ ከነጭ ወይ ጥቁር

ማወቅ ቢፈልግህ፥ ወዳጄ አሸብር

እነጮች ቡና ቤት፥ ገብተህ ቡና ጠጣ

ወይ በባቡር ስትሄድ፥ አብረህ ተቀመጣ!

ይህም ባይቻልህ፥ ሞክር ባልደረባ

ነጮች እገቡበት፥ ሆቴል ልትገባ፤

“ባንተ አልተጀመረም፥ ያዳሜ ምኞት

ከተጠቃው ‘መራቅ’፥ አጥቂን ‘መጠጋት’

ኀይለኛውን ‘መውደድ’፥ ደካሙን ‘መጥላት’ …

ሰው ባያቱ ይምላል፥ አባቱ ሳይከብር

ማነው የድሀ ልጅ፥ ዘሩን የማይቆጥር?”

እስከ ዛሬ ድረስ፥ ይህ አነጋገር

ሲታወሰኝ አለ፥ ባሰብሁት ቁጥር፤

ይመስገነው ገባኝ፥ ከጊዜ በኋላ

‘አማራ’ ‘ጊሚራ’፥ ቢባልም ‘ሻንቅላ’

‘ሱማሌ’ ‘ኪኩዩ’፥ ‘ሡዋሂሊ’ ‘ባንቱ’

‘ኩኑኑሉሉ’ ‘ማሣይ’፥ ‘ኔግሮ’ ‘ባማንጓቱ’

ማለት እንደሆነ፥ ስልቻ ቀልቀሎ፤

ቀልቀሎ ስልቻ፥ ስልቻ ቀልቀሎ

ስልቻ ስልቻ፥ ቀልቀሎ ቀልቀሎ።

.

መንግሥቱ ለማ

(1950ዎቹ)

.

[ምንጭ] – “ባሻ አሸብር ባሜሪካ”። ፲፱፻፷፯። ገጽ ፲-፲፫።

 

ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ጋር

“ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን ጋር”

ከግርማ መኮንን

.

በአካልም በስሜትም ከሀገሬ በጣም መራራቅ ጀመርኩ መሰለኝ ትዝታዎቼ ከአምስቱም የስሜት ሕዋሳቶቼ መፍለቅ ጀምረዋል።

ሰው ሁሉ አፍንጫውን ዘግቶ መንገድ ለመሻገር እንደመንጋ ሲንጋጋ እኔ እርምጃዬን ገታ አደርግና ፖሊሱ ወደተቀመጠበት ፈረስ አቅራቢያ ስደርስ ደረቴ እስኪወጠር ድረስ አየሩን እስባለሁ። የፋንድያው ሽታ እኔን የሚያስታውሰኝ ሰፈሬን ሽሮሜዳን ነዋ! እሱም ቢሆን እኮ ይናፍቃል። አዘውትሬ የምሄድበት ቡና ቤትም በአንድ ጥግ በኩል ኮርኒሱ ተቦርድሷል … ያደግኩበት ቤትም እንደዚሁ።

ጆሮዬም ቢሆን የሚናፍቀው የራሱ የሆነ ትዝታ አለው።

አሁን አሁን የእግር ኳስ ጨዋታን እምብዛም ባልከታተልም አንዳንዴ የስፖርት ዘጋቢዎቹ “ጎል!” ብለው ሲጮሁ ለመስማት እጓጓለሁ። እሷን በሰማኹ ቁጥር ትዝ የሚለኝ አባቴ ነው። እኔና ወንድሜ ሕፃን እያለን በሳምንት እንዴ የሚተላለፈው የእንግሊዞች ኳስ ጨዋታ እንዳያመልጠን ተንደርድረን ከሶፋው ላይ ጉብ እንላለን። የኛም ልብ እንደተሰቀለ አይቀርምና አንድ ጎል ይገባል። ደስታችን ገና በጩኸት ሳይመነዘር በፊት አባታችን ጎል ብሎ ይጀምራል …

“… እንዲያ ነው ጎል! …

ከዚያማ ጎል አባ ቁርጡ

ያንን ሁዳድ ሙሉ ጀግና፥ ከገላገለው ከምጡ …

ምኑ ቅጡ! ምኑ ቅጡ!”

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፻፲፩)

አባታችን ዘወትር ቅድሜና እሑድ ጠዋት፣ መኝታ ቤታችን ድረስ እየመጣ ከሚያነብልን ግጥሞች መሐል ተቀንጥባ እንደወጣች እናውቃለን። ሁሌም ጎል በገባ ቁጥር ስለሚላት ጭፈራ ወይ ሐዘን ከመጀመራችን በፊት የሱን አፍ እንጠብቅ ነበር።

Esat wey Abebaተለቅ ስንል ግን እሱን መጠበቅ አቆምን። ታዲያ የሁለት ሳምንቱን ሸመታ ለማካሄድ በሶማሌ ተራ አድርገን፣ የተክለ ሃይማኖትን መንገድ አሳብረን፣ በጠመዝማዛ መንገድ ተጠማዘን፣ ቅቤና ቡላ ከሚቸረቸርበት መደዳ ደርሰን፣ እናቴ ለብቻዋ ከመኪና ስትወርድ እኔ የአባቴን አፍ መከታተል እጀምራለሁ። እንደለመደው ግራና ቀኙን ካየ በኋላ አንድ ቁም ነገር እንዳስታወሰ ሁሉ ወሬ ሊጀምር ሲል እቀድምና፣

“መርካቶ ያገር ድግሱ

የገጠር ስንቅ አግበስብሱ

ለከተሜው ለአባ ከርሱ …” እላለሁ።

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፴፩)

አባቴም ኮራ እያለ፣

“እሱን ግጥም ምን እንደጻፈው ታውቃለህ?” ብሎ ይጠይቃል ።

“አፍንጮን የጻፈው ሰውዬ ነዋ” ብዬ መሳቅ እጀምራለሁ።

አባቴም “አንበሳ ሲያረጅ…” እንደሚባለው ቀልዱ በሱ ላይ መሆኑ ይገባዋል። የሱም ጥየቃ የዘልማድ ሆኖ እንጂ ጋሽ ጸጋዬን እንደማውቃቸው ያውቃል – ዳዊት ሳልደግም አይደል “እሳት ወይ አበባን” ያስደገመኝ!

IMG_4952እኔም አውቃቸዋለሁ ስል እንደ አሕዛብ ሁሉ አንዳንድ ሥራዎቻቸውን አንብቤ ወይም ሰምቼ እንጂ በቁም አይቻቸውም አላውቅም ነበር። ታዲያ አሜሪካ ከመጣሁ ከደርዘን ዓመታት በኋላ እምግብ ቤት በራፍ ላይ በቁም አገናኘን።

እሳቸው ከምግብ ቤቱ ሲወጡ፣ እኔ ደሞ ሊጐበኘኝ ከመጣው ታናሽ ወንድሜና ከጓደኞቼ ጋራ ርሃባችንን ለማስታገስ ስንቻኮል። በራፍ ላይ ስለነበርን ሁላችንን ሰላም ብለው ሊያልፉ ሲሉ ከኛው መሐል አንዱ ወደኔና ወንድሜ እየጠቆመ፣

“እነዚህ ደሞ ወንድማማቾች ናቸው። አይመሳሰሉም?” ብሎ ሲያዳንቅ፣

“ለመመሳሰልማ አይጦች ሁሉ ይመሳሰሉ የለ እንዴ?” ብለውን አለፉ።

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ነክ የሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ስሄድ በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ አያቸው ነበር። ሦስት ዓመታት ያኽል እንዲህ አለፉና እንደገና እሳቸውን የማገኝበት ሁኔታ ተፈጠረ። “አንድምታ” የመጽሐፍ ክበብን ወክዬ ጋሽ ጸጋዬን እንዳነጋግር ተጠየኩኝ። እኔም በተራዬ በልጃቸው በኩል ቀጠሮ ያዝኩኝ።

IMG_4942ጋሽ ጸጋዬ ጋር ከቡና ቤት እንድንገናኝ ነበርና ቀጠሮ የተያዘው እኔም እንዳይረፍድብኝ በማሰብ ከቤቴ ቀደም ብዬ ወጣሁ። ግና ሌሊቱን ሰማዩ የበረዶ ገለባ ሲበትን አድሮ ኖሮ፣ ጠዋት ከቤት ስወጣ መንገዱና መኪናው ሁሉ ይህንኑ ሦስት አራት ድርብ ጥጥ ለብሷል። ቀጠሮዬ መሰናከሉ ገብቶኝ አጠገቤ ያየሁትን ነገር ሁሉ መስደብ ስጀምር ከቀበቶዬ ያነገብኩት ስልክ ጥሪ እንዳለ አስታወቀኝ።

“ሃሎ፣ የምጽአት ቀን ዛሬ ናት መሰለኝ….” አልኩ ልጃቸውን።

“የቀጠሮውን ሰዓት ብትረሳው ይሻላል። ግን ቤት ድረስ መምጣት ትችላለህ?” አለችኝ።

የተቃጠርነው ከጠዋቱ 4 ሰዓት መሆኑን ሳልዘነጋ እኔም በ6 ሰዓት ከቤታቸው። የጋሽ ጸጋዬን ባለቤት ወይዘሮ ላቀችን ከሳሎን እንደተቀመጡ ሰላም ብዬ የምትመራኝን ልጃቸውን ተከትዬ በስተቀኝ በኩል ወዳለው መኝታ ቤት ዘው ብዬ ገባሁ።

በቀኝ በኩል ጠረጴዛ፣ በላዩ ላይ ደግሞ ኮምፒውተር – በግራ በኩል አመቺ ወንበር፣ በላዩ ላይ ደግሞ ጋሽ ጸጋዬ፣ ከእጃቸው ላይ ደግሞ ስልክ ተቀምጠዋል። አንድ ወንበር ጐተት አደረኩና ከፊታቸው ቁጭ ብዬ የስልክ ጥሪውን እስኪጨርሱ መጠበቅ ጀምርኩ።

TSEGAYE GEBRE-MEDHINየምሽት ልብሳቸውን እንደለበሱ ነው ቁጭ ያሉት። ቤቱ ውስጥ ባይበርድም ጋቢ ደርበዋል። ከጭንቅላታቸው የደፏት የሹራብ ኮፍያ ለአመል እንጂ በአግባቡ የተደረገች አትመስልም። ይህን የመሳሰሉትን የአለባበስ ዘዬዎች ሳስተውል ስልክ ጥሪያቸውን ጨርሰው ኖሮ አተኩረው ተመልክተውኝ፤

“ከዚህ በፊት ተገናኝተን አናውቅም?” አሉኝ

“እናውቃለን እንጂ ቂም ብይዝ እኮ ነው ቤቶ ድረስ የመጣሁ።”

“እንዴት?”

“ከሦስት ዓመታት በፊት ወንድሜንና እኔን ከአይጦች ጋራ አመሳስለው ነበር። ረሱት እንዴ?”

ፈገግ አሉና፣

“እሱማ የኛኑ ቤተሰብ ትመስላለህ ለማለት ነበር … አንዳንዴ ሰው አይቼ እኔን ይመስሉኝና እደነግጣለሁ። እንዲሁ አንድ ጊዜ የሆነ ልጅ ስድስት ኪሎ አካባቢ አይቼ የኛን ቤተሰብ መምሰሉ በጣም ገረመኝና ተጠግቼ ጠየቅኩት” ብለው ዝም አሉ።

ብጠብቅ አሁንም ዝም።

“ምን ብለው ጠየቁት” አልኩኝ መጠበቅ አላስችል ቢለኝ።

“እናትህ ጐረቤት ነበረች ወይ ነዋ!” ብለው በራሳቸው ቀልድ ራሳቸውንም እኔንም አስቀው ወሬያችንን ቀጠልን።

በደንቡ መሠረት ወደ ቁም ነገር ሰተት ተብሎ አይገባምና እኔና እሳቸውም የባጥ የቆጡን ማውራት ቀጠልን – ወቅቱ ስላመጣው ዝናብና በረዶ፤ ስለ ሰፈሬ እንጦጦ ብርድ፣ ከኒው ዮርክ በፊት ስለኖርኩበት ከተማ፣ በአሁኑ ጊዜ ምን እንደምሰራ ወዘተ… ይኽንንም ያንንም እየዳሰስን ቀስ በቀስ ወደመጣሁበት ጉዳይ ማዘንበላችን አልቀረም።

እኔም ያለመዳዳት “አንድምታ ክበብ” ከሐሳበ ጽንሰት እስከ ጉርምስና እንዴት እንደደረሰ አስረዳሁ። በጥሞና ከሰሙኝ በኋላ፣

“በኛ ቋንቋ ከተጻፉ ሥራዎች በቅርቡ ያነበብከው ጥሩ ነው የምትለው አግኝተሃል?” በማለት ጥያቄ አቀረቡ።

ለአባቴ ድሮ እንደምመልስለት አፍንጮ ልላቸው አሰብኩና ቀልዱን ለማስረዳት ብዙ ጊዜ እንደሚወስድብኝ ገምቼ ተውኩት። ሆኖም የሳቸው ጥያቄ ለ15 ደቂቅ ያኽል ራሱን የቻለ ውይይት ውስጥ ከተተን። ለጥያቄያቸው ቀጥተኛ መልስ ባልሰጣቸውም የፈላስፋው ዘርአ ያዕቆብን ሥራ ለራሴ አንብቤ መገምገም በመቻሌ ጽሑፉን ተርጉመውና አቀነባብረው ላቀረቡልን ምስጋናዬን እንደማቀርብ ተናገርኩ።

እሳቸውም አጠፋውን ሲመልሱ፣

“አየህ ሼክስፒር ለእንግሊዝ ትልቅ ቅርስ ነው። እንደ ትልቅነቱም ቅርሱ እንዳይበላሽ በመንግሥት ደረጃ ይጠበቃል። የሼክስፒር ሥራዎች ሌላ ሀገር በመድረክ ላይ ሲቀርቡ በትክክል ካልተሰሩ፣ ባህሉን አቃውሰው ካሳዩ፣ ዝግጅታቸው ጥሩ ካልሆነ፣ ጉዳዩ በአምባሳደሩ ደረጃ ተመክሮበት ነገሩ እንዲስተካከል ተብሎ ‘እርዳታ እናድርግላችሁ’ ብለው እንግሊዞች ይጠይቃሉ። ይኽም የሚሆንበት ምክንያት የሼክስፒር ሥራዎች የእንግሊዝን ታሪክና ባህል ስለሚወክሉ እንደ ቅርስ ተቆጥረው ነው። ምነው የኛ ሀገር ቅርሶች ታዲያ እንዲያ አይያዙም? እነ ያሬድን እነ ዘርአ ያዕቆብን ማን እንደዚህ የሚንከባከባቸው አለ?”

ሊሰነዝሩት ያሰቡት ነጥብ አላመለጠኝም። እሳቸው ግን ቀጠሉ፣

IMG_4943

“ትልቅ ዋጋ እንሰጣቸው የነበሩ ነገሮች በጣም ረክሰው ስናያቸው መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅም ይታክታል። በአፄ ምኒልክ ጊዜ እንግሊዞች ቱርካና ሐይቅ አካባቢ ዝሆን ያድኑ ነበርና አንዴ አደናቸውን ተከትለው ሲገሰግሱ ከኢትዮጵያ ኬላ ደርሰው ኖሮ ድንበር አላሳልፍ ካሉ የኬላ ጠባቂዎች ጋራ ተኩስ ይከፈትና ከአዳኞች አንዱ በዚሁ ምክንያት ይሞታል። እንግሊዞችም አቤቱታ ያሰሙና ነገሩ የጦር የሚስቴር ከነበሩት ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዘንድ ይደረሳል። እንግሊዞቹ ያላግባብ ሰው እንደተገደለባቸው አመልክተው የደም ካሳ እንዲሆናቸው ከኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው ነበር የጠየቁት።

“ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ነገሩን ያጠኑና ችግር እንደሌለው ለእንግሊዞች ይገልጻሉ። ‘ነገሩ ከመፈጸሙ በፊት ግን ይኽ ሕግ እናንተ ሀገርም እንደሚሰራበት ማየት ስለምንሻ በሰነድ መልክ ረቂቁ ካለ እስቲ እንየው። እውነት የእንግሊዝ ሰው የዌልስን ሰው ቢገድል እንግሊዝ ከመሬቷ ለዌልስ የምትሰጥ ከሆነ እኛም እንሰጣለን። እሱም የሚሆነው ለተገደለብን የኬላ ጠባቂ ካሳ የሚሆን ከቱርካና ሐይቅ አካባቢ መሬት ከተረከብን ይሆናል።’ ብለው መለሷቸው” አሉ።

እንዲህ እንዲያ እያልን የተጀመረው ወሬ በኢትዮጵያ ቅርስ ደጃፍ አቋርጦ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ጓሮ ዞሮ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያንን ነካ ነካ አድርጎ ከራሴው ቤት ፊት ለፊት ጣለኝ። ወሬያችን ከአንድ ርእስ ወደ ሌላ ሲሸጋገር በተያያዙ ነጥቦች ስለቤተሰቤ ድንገት ሲጠይቁኝ ምን አስመርኩዘው እንደሆነ አልታወቀኝም። አባቴ የሳቸውን ግጥም ያነብልን እንደነበር ተገልጾላቸው ይሆን?

ያም ሆነ ይኽ ስለቤተሰቤ ተናግሬ ስጨርስ እስቲ የኔን ጽዋ ይቅመሱት ብዬ በምትኩ አዲስ የተጻፈች እንዲት አጭር ታሪክ አነበብኩላቸው – ታሪኩ መኸል እሳቸው የጻፏት “ሕይወት ቢራቢሮ” የተሰኘችው ግጥም ቅንጣቢ ነበረች። የራሳቸው ግጥም አንድ ነገር አስታውሷቸው ልክ ታሪኩን አንብቤ ስጨርስ፣

“እሷ ግጥም በጋዜጣ ታትማ በወጣች ማግስት መንግስቱ ለማ ከቢሮዬ መጥቶ ‘ቢራውን እስቲ አምጣው ወይስ ዝም ብለህ ነው ቢራ ቢሮ ያልከው’ ብሎ እንደቀለደብኝ ትዝ ይለኛል” አሉኝ።

ትንሽ ተከዝ አሉና፣

“ምን የመሰለ ደማም ቋንቋ የነበረው ሰው ነበር። አሁን እኮ ደማም ቋንቋ የሚናገር ሰው ሁሉ ጠፋ።” ብለው እንደገና ትክዝ አሉ።

እኔም አዝማሚያው አላማረኝም። ምክንያቱም የመንግስቱ ለማን ሥራዎችም ቢሆን አባቴ ቅዳሜና እሑድ እንደ ዳዊት ይደግምልን ስለነበር በጣም እያደነቅኩት ነው ያደግኩት። ስለዚህ ስለሱ ማውራት ብንጀምር አዳሬም ከሳቸው ቤት እንደሚሆን በመረዳት እዚህ ላይ ልሰናበታቸው ወሰንኩ።

የአንድምታን መሥራች አባላት ይዤ መጥቼ እንደገና በሰፊው እንደምንወያይ ነግሬያቸው ልወጣ ስል ያዝ አረጉኝና ግንባሬ ላይ ሳሙኝ። ብዙ ባላስቀይማቸው ነው ብዬ ገምቼ ነበር።

IMG_4953

ግን ለካ ወደ ፊት ወጣ ያለው ግንባሬ ቀድሞ ከንፈራቸውን አግኝቶት ኖሯል።

… እኛኑ ትመስላለህ ብለውኝ የለ!

.

ግርማ መኰንን

1998 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “አንድምታ” ቅፅ ፫ – መጋቢት-ግንቦት ፲፱፻፺፰። ገጽ 1፣ 4፣ 10።