ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ጋር

“ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን ጋር”

ከግርማ መኮንን

.

በአካልም በስሜትም ከሀገሬ በጣም መራራቅ ጀመርኩ መሰለኝ ትዝታዎቼ ከአምስቱም የስሜት ሕዋሳቶቼ መፍለቅ ጀምረዋል።

ሰው ሁሉ አፍንጫውን ዘግቶ መንገድ ለመሻገር እንደመንጋ ሲንጋጋ እኔ እርምጃዬን ገታ አደርግና ፖሊሱ ወደተቀመጠበት ፈረስ አቅራቢያ ስደርስ ደረቴ እስኪወጠር ድረስ አየሩን እስባለሁ። የፋንድያው ሽታ እኔን የሚያስታውሰኝ ሰፈሬን ሽሮሜዳን ነዋ! እሱም ቢሆን እኮ ይናፍቃል። አዘውትሬ የምሄድበት ቡና ቤትም በአንድ ጥግ በኩል ኮርኒሱ ተቦርድሷል … ያደግኩበት ቤትም እንደዚሁ።

ጆሮዬም ቢሆን የሚናፍቀው የራሱ የሆነ ትዝታ አለው።

አሁን አሁን የእግር ኳስ ጨዋታን እምብዛም ባልከታተልም አንዳንዴ የስፖርት ዘጋቢዎቹ “ጎል!” ብለው ሲጮሁ ለመስማት እጓጓለሁ። እሷን በሰማኹ ቁጥር ትዝ የሚለኝ አባቴ ነው። እኔና ወንድሜ ሕፃን እያለን በሳምንት እንዴ የሚተላለፈው የእንግሊዞች ኳስ ጨዋታ እንዳያመልጠን ተንደርድረን ከሶፋው ላይ ጉብ እንላለን። የኛም ልብ እንደተሰቀለ አይቀርምና አንድ ጎል ይገባል። ደስታችን ገና በጩኸት ሳይመነዘር በፊት አባታችን ጎል ብሎ ይጀምራል …

“… እንዲያ ነው ጎል! …

ከዚያማ ጎል አባ ቁርጡ

ያንን ሁዳድ ሙሉ ጀግና፥ ከገላገለው ከምጡ …

ምኑ ቅጡ! ምኑ ቅጡ!”

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፻፲፩)

አባታችን ዘወትር ቅድሜና እሑድ ጠዋት፣ መኝታ ቤታችን ድረስ እየመጣ ከሚያነብልን ግጥሞች መሐል ተቀንጥባ እንደወጣች እናውቃለን። ሁሌም ጎል በገባ ቁጥር ስለሚላት ጭፈራ ወይ ሐዘን ከመጀመራችን በፊት የሱን አፍ እንጠብቅ ነበር።

Esat wey Abebaተለቅ ስንል ግን እሱን መጠበቅ አቆምን። ታዲያ የሁለት ሳምንቱን ሸመታ ለማካሄድ በሶማሌ ተራ አድርገን፣ የተክለ ሃይማኖትን መንገድ አሳብረን፣ በጠመዝማዛ መንገድ ተጠማዘን፣ ቅቤና ቡላ ከሚቸረቸርበት መደዳ ደርሰን፣ እናቴ ለብቻዋ ከመኪና ስትወርድ እኔ የአባቴን አፍ መከታተል እጀምራለሁ። እንደለመደው ግራና ቀኙን ካየ በኋላ አንድ ቁም ነገር እንዳስታወሰ ሁሉ ወሬ ሊጀምር ሲል እቀድምና፣

“መርካቶ ያገር ድግሱ

የገጠር ስንቅ አግበስብሱ

ለከተሜው ለአባ ከርሱ …” እላለሁ።

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፴፩)

አባቴም ኮራ እያለ፣

“እሱን ግጥም ምን እንደጻፈው ታውቃለህ?” ብሎ ይጠይቃል ።

“አፍንጮን የጻፈው ሰውዬ ነዋ” ብዬ መሳቅ እጀምራለሁ።

አባቴም “አንበሳ ሲያረጅ…” እንደሚባለው ቀልዱ በሱ ላይ መሆኑ ይገባዋል። የሱም ጥየቃ የዘልማድ ሆኖ እንጂ ጋሽ ጸጋዬን እንደማውቃቸው ያውቃል – ዳዊት ሳልደግም አይደል “እሳት ወይ አበባን” ያስደገመኝ!

IMG_4952እኔም አውቃቸዋለሁ ስል እንደ አሕዛብ ሁሉ አንዳንድ ሥራዎቻቸውን አንብቤ ወይም ሰምቼ እንጂ በቁም አይቻቸውም አላውቅም ነበር። ታዲያ አሜሪካ ከመጣሁ ከደርዘን ዓመታት በኋላ እምግብ ቤት በራፍ ላይ በቁም አገናኘን።

እሳቸው ከምግብ ቤቱ ሲወጡ፣ እኔ ደሞ ሊጐበኘኝ ከመጣው ታናሽ ወንድሜና ከጓደኞቼ ጋራ ርሃባችንን ለማስታገስ ስንቻኮል። በራፍ ላይ ስለነበርን ሁላችንን ሰላም ብለው ሊያልፉ ሲሉ ከኛው መሐል አንዱ ወደኔና ወንድሜ እየጠቆመ፣

“እነዚህ ደሞ ወንድማማቾች ናቸው። አይመሳሰሉም?” ብሎ ሲያዳንቅ፣

“ለመመሳሰልማ አይጦች ሁሉ ይመሳሰሉ የለ እንዴ?” ብለውን አለፉ።

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ነክ የሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ስሄድ በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ አያቸው ነበር። ሦስት ዓመታት ያኽል እንዲህ አለፉና እንደገና እሳቸውን የማገኝበት ሁኔታ ተፈጠረ። “አንድምታ” የመጽሐፍ ክበብን ወክዬ ጋሽ ጸጋዬን እንዳነጋግር ተጠየኩኝ። እኔም በተራዬ በልጃቸው በኩል ቀጠሮ ያዝኩኝ።

IMG_4942ጋሽ ጸጋዬ ጋር ከቡና ቤት እንድንገናኝ ነበርና ቀጠሮ የተያዘው እኔም እንዳይረፍድብኝ በማሰብ ከቤቴ ቀደም ብዬ ወጣሁ። ግና ሌሊቱን ሰማዩ የበረዶ ገለባ ሲበትን አድሮ ኖሮ፣ ጠዋት ከቤት ስወጣ መንገዱና መኪናው ሁሉ ይህንኑ ሦስት አራት ድርብ ጥጥ ለብሷል። ቀጠሮዬ መሰናከሉ ገብቶኝ አጠገቤ ያየሁትን ነገር ሁሉ መስደብ ስጀምር ከቀበቶዬ ያነገብኩት ስልክ ጥሪ እንዳለ አስታወቀኝ።

“ሃሎ፣ የምጽአት ቀን ዛሬ ናት መሰለኝ….” አልኩ ልጃቸውን።

“የቀጠሮውን ሰዓት ብትረሳው ይሻላል። ግን ቤት ድረስ መምጣት ትችላለህ?” አለችኝ።

የተቃጠርነው ከጠዋቱ 4 ሰዓት መሆኑን ሳልዘነጋ እኔም በ6 ሰዓት ከቤታቸው። የጋሽ ጸጋዬን ባለቤት ወይዘሮ ላቀችን ከሳሎን እንደተቀመጡ ሰላም ብዬ የምትመራኝን ልጃቸውን ተከትዬ በስተቀኝ በኩል ወዳለው መኝታ ቤት ዘው ብዬ ገባሁ።

በቀኝ በኩል ጠረጴዛ፣ በላዩ ላይ ደግሞ ኮምፒውተር – በግራ በኩል አመቺ ወንበር፣ በላዩ ላይ ደግሞ ጋሽ ጸጋዬ፣ ከእጃቸው ላይ ደግሞ ስልክ ተቀምጠዋል። አንድ ወንበር ጐተት አደረኩና ከፊታቸው ቁጭ ብዬ የስልክ ጥሪውን እስኪጨርሱ መጠበቅ ጀምርኩ።

TSEGAYE GEBRE-MEDHINየምሽት ልብሳቸውን እንደለበሱ ነው ቁጭ ያሉት። ቤቱ ውስጥ ባይበርድም ጋቢ ደርበዋል። ከጭንቅላታቸው የደፏት የሹራብ ኮፍያ ለአመል እንጂ በአግባቡ የተደረገች አትመስልም። ይህን የመሳሰሉትን የአለባበስ ዘዬዎች ሳስተውል ስልክ ጥሪያቸውን ጨርሰው ኖሮ አተኩረው ተመልክተውኝ፤

“ከዚህ በፊት ተገናኝተን አናውቅም?” አሉኝ

“እናውቃለን እንጂ ቂም ብይዝ እኮ ነው ቤቶ ድረስ የመጣሁ።”

“እንዴት?”

“ከሦስት ዓመታት በፊት ወንድሜንና እኔን ከአይጦች ጋራ አመሳስለው ነበር። ረሱት እንዴ?”

ፈገግ አሉና፣

“እሱማ የኛኑ ቤተሰብ ትመስላለህ ለማለት ነበር … አንዳንዴ ሰው አይቼ እኔን ይመስሉኝና እደነግጣለሁ። እንዲሁ አንድ ጊዜ የሆነ ልጅ ስድስት ኪሎ አካባቢ አይቼ የኛን ቤተሰብ መምሰሉ በጣም ገረመኝና ተጠግቼ ጠየቅኩት” ብለው ዝም አሉ።

ብጠብቅ አሁንም ዝም።

“ምን ብለው ጠየቁት” አልኩኝ መጠበቅ አላስችል ቢለኝ።

“እናትህ ጐረቤት ነበረች ወይ ነዋ!” ብለው በራሳቸው ቀልድ ራሳቸውንም እኔንም አስቀው ወሬያችንን ቀጠልን።

በደንቡ መሠረት ወደ ቁም ነገር ሰተት ተብሎ አይገባምና እኔና እሳቸውም የባጥ የቆጡን ማውራት ቀጠልን – ወቅቱ ስላመጣው ዝናብና በረዶ፤ ስለ ሰፈሬ እንጦጦ ብርድ፣ ከኒው ዮርክ በፊት ስለኖርኩበት ከተማ፣ በአሁኑ ጊዜ ምን እንደምሰራ ወዘተ… ይኽንንም ያንንም እየዳሰስን ቀስ በቀስ ወደመጣሁበት ጉዳይ ማዘንበላችን አልቀረም።

እኔም ያለመዳዳት “አንድምታ ክበብ” ከሐሳበ ጽንሰት እስከ ጉርምስና እንዴት እንደደረሰ አስረዳሁ። በጥሞና ከሰሙኝ በኋላ፣

“በኛ ቋንቋ ከተጻፉ ሥራዎች በቅርቡ ያነበብከው ጥሩ ነው የምትለው አግኝተሃል?” በማለት ጥያቄ አቀረቡ።

ለአባቴ ድሮ እንደምመልስለት አፍንጮ ልላቸው አሰብኩና ቀልዱን ለማስረዳት ብዙ ጊዜ እንደሚወስድብኝ ገምቼ ተውኩት። ሆኖም የሳቸው ጥያቄ ለ15 ደቂቅ ያኽል ራሱን የቻለ ውይይት ውስጥ ከተተን። ለጥያቄያቸው ቀጥተኛ መልስ ባልሰጣቸውም የፈላስፋው ዘርአ ያዕቆብን ሥራ ለራሴ አንብቤ መገምገም በመቻሌ ጽሑፉን ተርጉመውና አቀነባብረው ላቀረቡልን ምስጋናዬን እንደማቀርብ ተናገርኩ።

እሳቸውም አጠፋውን ሲመልሱ፣

“አየህ ሼክስፒር ለእንግሊዝ ትልቅ ቅርስ ነው። እንደ ትልቅነቱም ቅርሱ እንዳይበላሽ በመንግሥት ደረጃ ይጠበቃል። የሼክስፒር ሥራዎች ሌላ ሀገር በመድረክ ላይ ሲቀርቡ በትክክል ካልተሰሩ፣ ባህሉን አቃውሰው ካሳዩ፣ ዝግጅታቸው ጥሩ ካልሆነ፣ ጉዳዩ በአምባሳደሩ ደረጃ ተመክሮበት ነገሩ እንዲስተካከል ተብሎ ‘እርዳታ እናድርግላችሁ’ ብለው እንግሊዞች ይጠይቃሉ። ይኽም የሚሆንበት ምክንያት የሼክስፒር ሥራዎች የእንግሊዝን ታሪክና ባህል ስለሚወክሉ እንደ ቅርስ ተቆጥረው ነው። ምነው የኛ ሀገር ቅርሶች ታዲያ እንዲያ አይያዙም? እነ ያሬድን እነ ዘርአ ያዕቆብን ማን እንደዚህ የሚንከባከባቸው አለ?”

ሊሰነዝሩት ያሰቡት ነጥብ አላመለጠኝም። እሳቸው ግን ቀጠሉ፣

IMG_4943

“ትልቅ ዋጋ እንሰጣቸው የነበሩ ነገሮች በጣም ረክሰው ስናያቸው መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅም ይታክታል። በአፄ ምኒልክ ጊዜ እንግሊዞች ቱርካና ሐይቅ አካባቢ ዝሆን ያድኑ ነበርና አንዴ አደናቸውን ተከትለው ሲገሰግሱ ከኢትዮጵያ ኬላ ደርሰው ኖሮ ድንበር አላሳልፍ ካሉ የኬላ ጠባቂዎች ጋራ ተኩስ ይከፈትና ከአዳኞች አንዱ በዚሁ ምክንያት ይሞታል። እንግሊዞችም አቤቱታ ያሰሙና ነገሩ የጦር የሚስቴር ከነበሩት ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዘንድ ይደረሳል። እንግሊዞቹ ያላግባብ ሰው እንደተገደለባቸው አመልክተው የደም ካሳ እንዲሆናቸው ከኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው ነበር የጠየቁት።

“ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ነገሩን ያጠኑና ችግር እንደሌለው ለእንግሊዞች ይገልጻሉ። ‘ነገሩ ከመፈጸሙ በፊት ግን ይኽ ሕግ እናንተ ሀገርም እንደሚሰራበት ማየት ስለምንሻ በሰነድ መልክ ረቂቁ ካለ እስቲ እንየው። እውነት የእንግሊዝ ሰው የዌልስን ሰው ቢገድል እንግሊዝ ከመሬቷ ለዌልስ የምትሰጥ ከሆነ እኛም እንሰጣለን። እሱም የሚሆነው ለተገደለብን የኬላ ጠባቂ ካሳ የሚሆን ከቱርካና ሐይቅ አካባቢ መሬት ከተረከብን ይሆናል።’ ብለው መለሷቸው” አሉ።

እንዲህ እንዲያ እያልን የተጀመረው ወሬ በኢትዮጵያ ቅርስ ደጃፍ አቋርጦ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ጓሮ ዞሮ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያንን ነካ ነካ አድርጎ ከራሴው ቤት ፊት ለፊት ጣለኝ። ወሬያችን ከአንድ ርእስ ወደ ሌላ ሲሸጋገር በተያያዙ ነጥቦች ስለቤተሰቤ ድንገት ሲጠይቁኝ ምን አስመርኩዘው እንደሆነ አልታወቀኝም። አባቴ የሳቸውን ግጥም ያነብልን እንደነበር ተገልጾላቸው ይሆን?

ያም ሆነ ይኽ ስለቤተሰቤ ተናግሬ ስጨርስ እስቲ የኔን ጽዋ ይቅመሱት ብዬ በምትኩ አዲስ የተጻፈች እንዲት አጭር ታሪክ አነበብኩላቸው – ታሪኩ መኸል እሳቸው የጻፏት “ሕይወት ቢራቢሮ” የተሰኘችው ግጥም ቅንጣቢ ነበረች። የራሳቸው ግጥም አንድ ነገር አስታውሷቸው ልክ ታሪኩን አንብቤ ስጨርስ፣

“እሷ ግጥም በጋዜጣ ታትማ በወጣች ማግስት መንግስቱ ለማ ከቢሮዬ መጥቶ ‘ቢራውን እስቲ አምጣው ወይስ ዝም ብለህ ነው ቢራ ቢሮ ያልከው’ ብሎ እንደቀለደብኝ ትዝ ይለኛል” አሉኝ።

ትንሽ ተከዝ አሉና፣

“ምን የመሰለ ደማም ቋንቋ የነበረው ሰው ነበር። አሁን እኮ ደማም ቋንቋ የሚናገር ሰው ሁሉ ጠፋ።” ብለው እንደገና ትክዝ አሉ።

እኔም አዝማሚያው አላማረኝም። ምክንያቱም የመንግስቱ ለማን ሥራዎችም ቢሆን አባቴ ቅዳሜና እሑድ እንደ ዳዊት ይደግምልን ስለነበር በጣም እያደነቅኩት ነው ያደግኩት። ስለዚህ ስለሱ ማውራት ብንጀምር አዳሬም ከሳቸው ቤት እንደሚሆን በመረዳት እዚህ ላይ ልሰናበታቸው ወሰንኩ።

የአንድምታን መሥራች አባላት ይዤ መጥቼ እንደገና በሰፊው እንደምንወያይ ነግሬያቸው ልወጣ ስል ያዝ አረጉኝና ግንባሬ ላይ ሳሙኝ። ብዙ ባላስቀይማቸው ነው ብዬ ገምቼ ነበር።

IMG_4953

ግን ለካ ወደ ፊት ወጣ ያለው ግንባሬ ቀድሞ ከንፈራቸውን አግኝቶት ኖሯል።

… እኛኑ ትመስላለህ ብለውኝ የለ!

.

ግርማ መኰንን

1998 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “አንድምታ” ቅፅ ፫ – መጋቢት-ግንቦት ፲፱፻፺፰። ገጽ 1፣ 4፣ 10።

 

3 thoughts on “ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ጋር

 1. አለቀ ልትሉ እንዳይሆን ብቻ ወይንስ ክፍል ሁለት አለው? ቃለ መጠይቁ የቅድሚያ መግባቢያው ብቻ ነው እኮ ይሄ::

  Like

 2. ጋሽ ጸጋዬን በጎልዳፋ ብዕሬ ለማወደስ ሞክሬ ነበር፡፡ አስር አመት አለፈው፡፡ በህይወት እያለ የተጻፈ ነው፡፡

  ራስጌ እና ግርጌ

  ‹‹ እናም እንደ እኔ እና እነዳንቺ የጥበብ ዐይኑ የታወረ እግረ ህሊናው የከረረ፤
  ባህረ ሐሳቡን ያልታደለ››
  ፀጋዬ ባለቅኔ እንጂ ነብይ እኮ አይደለም አለ፡፡ ያልታደለ፡፡
  የዘመንን ትብታብ ቋጠሮ ፤ ሲፈታታው ዘርዝሮ ፤
  የትውልድን ውድቀት ፤ የጊዜን ትንሳዔ ፤
  ሲያሻው በግጥም በጉባዔ፤
  አሊያም በተውኔት በድርሰቱ፤
  ሲያንበለብል ካንደበቱ፡፡
  አይቶ ፤ ሰምቶ፤ ያላስተዋለ !!
  ፀጋዬ ሰው እንጂ ነብይ እኮ አይደለም አለ፡፡ ያልታደለ!!
  የተፈጥሮን እንባ እና ሳቅ፤
  የትዝታን የተስፋን ስንቅ
  ስንኝ ቋጥሮ ባስነበበ፤
  ጥጋብ ረሐብን ፣ ጭንቀት ፍርሀትን ፣ ውስጡ ዘልቆ በከተበ፤
  ማስተዋል ቢነሳው ፣ ሊገባው ያልቻለ ፤
  ጸጋዬ ባለቅኔ እንጂ ፣ ነብይ እኮ አይደለም አለ፡፡ ያልታደለ!!
  የግሸኗ ማሪያም ፤ የባሌዋ አቴቴ ፤
  የኩሽ አባት ዋቃ ፣የኢትዮጵያ አምላክ ጌታ፤
  በብዕሩ ሲናግሩ ፤ ባንደበቱ ሲዘምሩ፤
  ሰምቶ ማዳመጥ ያልቻለ ፤
  ጸጋዬ ገጣሚ እንጂ ፣ ነብይ እኮ አይደለም አለ፡፡

  ጴጥሮስን ፣ በዚያች ሰዐት ፤
  ቴዎድሮስን ፣ በዚያች አምባ፤
  በመንፈሱ ጠልቆ ገብቶ፤
  የዘመንን እንባ እና ሳቅ ፣ እንካ ቢለው ፈትፍቶ፤
  ማሽተት ፤ መዳሰሱን ፤ ማጣጣም ያቃተው ፤
  ነብዩ ጸጋዬን ፣ ገጣሚ ነው አለው፡፡

  በእናት ዐለም ጠኑ ፣ ነገሮች ሲጠኑ፤
  በ ሀ ሁ በ ስድስት ወር ፣ትንቢት ሲወረወር ፤
  ደግሞም ባቡጊዳ በ መልዕክተ ወዛደር፤
  የዘመን ቋጠሮን ፣በወግ ሲተረትር፤
  ሀ ሁ ፐ ፑ ብሎ ትንቢተ ዘመንን ፣ በፊደል ሲያስቆጥር፤
  ባበባና በእሳት ፣ዘመንን ሲያሳየው፤
  ልቡን በድን አድርጎ ፣አልታይህ ያለው፤
  ነብዩን አቅሎ ፣ገጣሚ አደረገው፡፡
  አዋሽን ከመጫ፣ ከምንጩ ጀምሮ፤
  ከሴቴ ሸረሪት ፣ባህሪውን ፈጥሮ፤
  አሸዋ ላሸዋ አፋር ምድር ድረስ ፣ተከትሎ ሰምጦ፤
  እንዲህ ናችሁ ቢለን ፣ ውስጣችንን ገልጦ፤
  መቀበል ቢያቅተው ማንነቱን ውጦ፤
  ነብዩን ኮነነው ፣ማዕረጉን ለውጦ፡፡
  ከ ኩሽ ስልጣኔ ፣ከፈርዖን ደጃፍ፤
  ከ አክሱሞች ቀዬ ቅኔውን ሲዘርፍ፤
  ግሪክ ዘመን ዘልቆ ከኤዞፕ ሲስማማ፤

  ካቴቴ ኦሮሞ ካባ ጋዳው ጋልማ፤
  ከግማደ መስቀሉ ደፍ ከ ታቦቱ ደጃፍ፤
  የተነገረውን የሰማውን ቢፅፍ፤
  አይቶ ፤ ሰምቶ ፤ ያላስተዋለ ፤
  ፀጋዬ ገጣሚ እንጂ ነብይ እኮ አይደለም አለ፡፡ ያልታደለ!!
  የሰውን አመጣጥ የዘሩን ምጣኔ፤
  ገደቡን ልቀቱን ውድቀት ስልጣኔ፤
  ስረ መሰረቱን ማንነቱን ዘልቆ፤
  ቢነግረው ያልገባው ያልተረዳው ጠልቆ፤
  ገጣሚ ነው አለው ማዕረጉን አውልቆ ፡፡
  እሱም ታውቆት ኖሯል ነብይ መች ይስታል ፤
  በ ዕስትንፋሱ ማብቂያ ለዘመኑ ጽፏል ፤
  የማይሰማ ወጭት ጥዶ ፤
  የከሰመ ፍም እፍ እንደሚል……..፡፡

  ስለሺ ሽብሩ
  1998
  ነፍስህን ይማርልን ፡፡

  Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s