የደራስያኑ ጦርነት

የደራስያኑ ጦርነት – መንግሥቱና ጸጋዬ

ከብርሀኑ ዘሪሁን

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ እንቅስቃሴ ይልቅ፣ በጥቂቶች ኢትዮጵያውያን የሥነ ጥበብ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተፋፍሞ ይገኛል። ያልታወጀ ጦርነት ነው። አንዱ ቡድን እግር ይበጥሳል። ሌላው አንገት ለመቁረጥ ይሞክራል።

ሰሎሞን ደሬሣን በ“Addis Reporter”፣ ተቃዋሚውን አንባቢ በ“አዲስ ዘመን”፣ አሁንም ሰሎሞንን በ“African Arts” የሦስት ወር መጽሔት፣ መንግሥቱ ለማን እና ጸጋዬ ደባልቄን በ“የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ያነበበ፣ አልፎ አልፎም የእነ ዓለማየሁ ሞገስን የእነ ዮሐንስ አድማሱን ንግግር ያዳመጠ ሁሉ፣ ከመደነቅ ጋር ምናልባት ግራ ሳይጋባ አልቀረም። ስለምንድን ነው ትንቅንቁና ፍጅቱ?

ከመሠረቱ በሥነጥበብ አካባቢ የአስተያየት ግጭት አዲስ ነገር አይደለም። የመናናቅና የመቀናናት ስሜት አለ። የሥነጥበብ ሰዎችም፣ እንደሌላው ሁሉ ደካማ ፍጡሮች ናቸውና። ከዚህ ጋር ደግሞ፣ የሐሳብና የአስተሳሰብ ልዩነት ሲታከልበት መጨፋጨፍ ነው። ደግነቱ የሥነጥበብ ሰዎች በሰይፍ አይፋለጡም። በዚያው በብዕር ጫፍ መቦጫጨር ነው።

ቤርናርድ ሾው (Bernard Shaw) ቶልስቶይን “ማጫራ እንጅ ደራሲ አይደለም” ይል ነበር። በሀገራችን (ሁለቱንም በሰማይ ነፍሳቸውን ይማርና) አለቃ ታየ እና ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለገላጋይ አስቸግረው ነበር ይባላል።

ሟቹ ፕሮፌሰር ተአምራት እና ቋሚው አስረስ የኔሰው በ“ኤርትራ ድምፅ” ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ በመቃ ብዕር (እንደዛሬው ጭቃ ቀለም አልመጣም ነበርና) የሚሸቃሸቁበት ዓምድ ነበራቸው። ታዲያ፣ አንዱ እጁን አንስቶ ተማርኮ ወይም ወድቆ ድሉ የማን እንደሆነ በሚገባ ሳይለይ ሁለቱም ተዳክመው ውጊያውን ተዉት።

ምናልባት አቀራረቡ የተለየ ይመስል እንጅ የአሁኑም የሥነጥበብ አካባቢ ጦርነት በመሠረቱ ያለፈው ዓይነት ነው።

እንደጊዜያችን ዓለም ሁሉ፣ የሥነጽሑፍ ጦርነትም አራጋቢዎችና አስታራቂዎች፣ ዝምተኛ ተመልካቾች፣ ሦስተኛ ኀይል ለመሆን የሚፈልጉ ገለልተኞች አሉበት። ከዚያም ሁለቱ ኀያላን ይመጣሉ። ይህ ምናልባት ትንሽ የተጋነነ አገላለጽ ሊመስል ይችላል። ግን ከእውነተኛው በጣም የራቀ አይደለም።

እርግጥ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣

“ምን ዓይነቱ ነው! ጦርነት አትበሉት! ለማባባስ ነው!” ይላል።

አቶ መንግሥቱ ለማ ደግሞ በዚያ የለሰለሰ የዲፕሎማሲ አንደበት፣

“ኤዲያ እንዲያው እናንተ ደግሞ ነገር መጐርጐር ትወዳላችሁ! አሁን ምን ያስፈልጋል!” ይላል።

ጸጋዬ ገብረመድኅን ሦስተኛውን፣ መንግሥቱ ለማ አራተኛውን የሥነጽሑፍ ሽልማት ባይወስዱ፣ ሁለቱም ከናካቴው ባይሸለሙ ኖሮ ምናልባት ጦርነታቸው ባልተካረረ ነበር። መንግሥቱ ለማ “ከኔ ቀድሞ ማግኘት አልነበረበትም” ቢል፣ ጸጋዬ ደግሞ “ከኔ መከተል አልነበረበትም” ባይ ነው። አንደኛው ሽልማቱን በተቀበለበት ጊዜ ሌላው ምን ያህል እንዳረረና እንደተከዘ እግዚአብሔር ይወቅ። ምናልባትም ብዙ የአረቄ ጠርሙሶች ተንጠፍጥፈው አድረው ይሆናል። መሳሳብ መገፋተር፣ መቀራረብ መራራቅ፣ መፋቀር መጣላት፣ ይህ ሁሉ በሰው ተፈጥሮ የደካማነትም ባይሆን የተለመደ ባሕርይ ነው። ተፈጥሮ ነው እንበል?

ጸጋዬ ገብረመድኅን እና መንግሥቱ ለማ (ወይም በስም አወሳስ አደላችሁ እንዳንባል) መንግሥቱ ለማ እና ጸጋዬ ገብረመድኅን የመጀመርያ ግንኙነታቸውም ቢሆን እስከዚህም ድረስ የመቀራረብ ወይም የመሳሳብ ኀይል አልነበረበትም።

IMG_4943Menge portraitሁለቱ የሥነጽሑፍ ሰዎች በብዙ ረገድ አይመሳሰሉም። ጸጋዬ ጠይም ረጅም ነው። በበጋውም በክረምቱም ወፍራም ድሪቶ ሹራብ ከማዘውተሩ በቀር፣ ስለ አለባበሱና ስለ አነጋገሩ ጥንቃቄ የለውም። ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ከአፉ የሚወጡት ቃላት የእረኛ ስድቦች ናቸው። ጳውሎስ ኞኞ አንድ ጊዜ “አንደበተ እረኛ” ሲል ጠቅሶት ነበር። ብቻ በክፋት አይደለም። መሳደቡም ማቆላመጡ ሊሆን ይችላል። ንግግር ሲያደርግ ተሞልቶ እንደተለቀቀ ሞላ ይተረተራል። የሚለውን ሁሉ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ታዲያ “ምን ትንተባተባለህ!” ቢሉት ግድ የለውም።

መንግሥቱ ደግሞ ቀይ፣ ቁመናው ወደ እጥረቱ የሚያደላ፣ በሙያውም በአነጋገሩም በሁናቴውም ዲፕሎማት ነው። ከሚያዜመው ድምፁ ጋር ቀስ ብሎ ሲናገር፣ ሲጫወት፣ ሲተርብ ያውቅበታል። ይራቀቅበታል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ “ማሽሟጠጡን ያውቁበታል” ነው ያለው? አዎ! እንደ ዜማው፣ እንደ ዘይቤው፣ እንደ ቅኔው ትርጓሜ … የመንግሥቱ ለማ ምስጋና … ነቀፋና ስድብ ሊሆን ይችላል።

ተቃራኒ የማግኔት ጫፎች ይሳሳባሉ እንደሚለው የፊዚክስ ሥርዓት ቢሆን ኖሮ የሁለቱ ደራስያን ባሕርይ ሁናቴ አለመመሳሰል ሊያወዳጃቸው በተገባ ነበር። ግን ከመጀመርያው አንስቶ፣ በመካከላቸው የመቀራረብ ስሜት የተፈጠረ አይመስልም። የተዋወቁት የጸጋዬ “ቴዎድሮስ” ቴአትር (በእንግሊዝኛ) ስለመታየቱ ዶክተር ካፕላን ባዘጋጀው ግብዣ ላይ ነበር። ከዚያ በፊት አንዱ ስለሌላው ሳይሰማ አልቀረም።

የመንግሥቱ “የግጥም ጉባኤ” ዝነኛ ሆኖ ነበር። ጸጋዬም በመጀመርያ ቴአትሩ አቶ አሐዱ ሣቡሬ በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ ካደፋፈሩትና “የሾህ አክሊል”ንም ካቀረበ ወዲህ ስሙ በጋዜጣ ላይ እየተደጋገመ መውጣት ይዞ ነበር። ምናልባት ያን ጊዜ ለወጉ ለማዕረጉ እጅ ተጨባብጠው አንዳንድ መልካም ቃላት ተለዋውጠው ይሆናል። ዛሬ ጸጋዬ፣ “ያን ቀን ‘እንዴ እንዴ ደኅና ሥር የያዝክ ይመስለኛል’ (በእንግሊዝኛ) ሲል መንግሥቱ የተናገረው ትዝ ይለኛል” ይላል። ልዩ ስሜትና ትርጓሜ በማሳደር የታወሰው ከጊዜ በኋላ ሳይሆን አይቀርም።

ምክንያቱም፣ ከዚያ በኋላ ለአጭር ጊዜ መቀራረብ ጀምረው ነበር። ሁለቱ ብቻ አይደሉም። ሁለቱን ጨምሮ፣ ጥቂቶች ዘመናውያን ደራሲዎች የሥነግጥም ምንባብ ብጤ አቋቁመው ነበር። እንደ ሀገራችን ማኅበር ሁሉ አንድ ቀን ከአንዱ ቤት፣ ሌላ ቀን ከሌላው ቤት ይሰበሰባሉ። ጠላ ባይጠመቅ ዳቦ ባይጋገር ውስኪው፣ አረቄው፣ ቢራው፣ ለስላሣ መጠጡ ፉት እየተባለ አንዱ ቅኔውን ወይም ሥነግጥሙን ያነባል። በኋላም ይተቻቹበታል። የክበቡ ተግባር ይህ ነበር። በኋላም የሥነግጥም ምንባቡ በቀ.ኃ.ሥ ኪነጥበባት ወቲያትር ቤት ውስጥ እንዲደረግ ታስቦ ነበር። በመካከሉ የክበቡ አቋም እንደ በረዶ ሟሸሸ። ጸጋዬ እንደሚለው ለመሟሸሹ ዋናው ምክንያት መንግሥቱ ነው።

በመካከሉ፣ ጦርነቱን ያባባሰው የዳካሩ “የጥቁር ዓለም ሕዝብ የሥነ ጥበብ በዓል” መጣ። ምናልባት ስለ በዓሉ በመጀመርያ ያወቀ እሱ ብቻ ሊሆን ቢችል ባይችል፣ ስለ ተካፋይነቱ ጉዳይ በመጀመርያ ወደ ዳካር ሂዶ ከሴንጎር (Léopold Sédar Senghor) ጋር የተነጋገረው ጸጋዬ ነበር።

Senghorበዚያን ጊዜ ጸጋዬ “Oda Oak Oracle” የተባለውን የእንግሊዝኛ ድራማ አዘጋጅቶ ነበር። ስለ በዓሉ አስቀድሞ ስላወቀ አዘጋጅቶት ለበዓሉ አቅርቦት እንደሆን አስተያየት የማንሰጥበት ሌላ ጥያቄ ነው። ያን ጊዜ መንግሥቱ በውጭ ሀገር ቋንቋ የተጻፈ ድራማ አልነበረውም። በኋላም የአቶ ከበደ ሚካኤል “አኒባል” እንዲሄድ መደረጉ ይታወሳል። ወዲያውም በውጭ ሀገር ቋንቋ ተተርጉሞ ነበር።

ጸጋዬ እንደሚለው “Oda Oak Oracle” እንዳይሄድ በዚህም በዚያም ብሎ ያስቀረው መንግሥቱ ለማ መሆኑ ነው። ያን ሰሞን በሥነጥበብ ሰዎች አካባቢ የሚሰማው ሁሉ ራሱ አንድ ረጅም ሐተታ ይወጣዋል።

አንዱ ወገን፣

“በውጭ ሀገር ቋንቋ ማቅረብ ግድ ከሆነ ‘Oda Oak Oracle’ ግሩም ሥነጽሑፍ ነው። የእንግሊዝ ማሳተሚያ ድርጅት ሳይቀር የተቀበለው። ያም ባይሆን እንግሊዝኛው ‘ቴዎድሮስ’ አለ። የአኒባል ታሪክ ታሪካችን አይደለ። ባህላችን አይደል! ምንድነውኮ የሚሰራው?” ይላል።

የሌላው ወገን ደግሞ ሥራ አልፈታም፣

“እስቲ እግዜር ያሳያችሁ! ዋርካ የሚመለክበት፣ ሕፃን በአምልኮ የሚታረድበት የኢትዮጵያን ባህል፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ይወክላል እንዴ? የምዕራብ አፍሪቃ ታሪክ ከሆነ እነርሱው አሳምረው ያቀርቡታል” ይሉ ነበር።

ከግል የሰብአዊነት ስሜት በቀር በሁለቱ ደራስያን የአማርኛ ሥነጽሑፍ አስተሳሰብና አቀራረብ መካከል ልዩነት አለ።

Shilimat

በመጀመርያ የአስተሳሰብን ጉዳይ እንውሰድ። አስተሳሰባቸውም የወጡበትን አካባቢ የሚጠቅስ ሊሆን ይችላል። መንግሥቱ ለማ፣ አነጋገሩ የአማራ አማርኛ፣ ግዕዝ አዋቂ፣ ባይዘርፍም ቅኔ የቀማመሰ፣ የሰዋስው ሥርዓት አክባሪ ነው። ታዲያ የአማርኛ ሥነጽሑፍ በአማራ ሥነባህል፣ የአማራ ሥነባህል በቤተክህነት ሥነጥበብ፣ የቤተክህነት ሥነጥበብም በግዕዝና በቅኔ በሰዋስውና በአግባቡ የተመሠረተ ስለሆነ መጠበቅ አለበት ቢል ያስኬደዋል ማለት ነው።

በጸጋዬ አስተሳሰብ ደግሞ ቅኔን ለማወቅ መቃብር ቤት ማደር አያስፈልግም፣ “ቅኔ ከግዕዝ የተወለደ ነው። ቅኔና ሥነግጥም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ደግሞ ዛሬ ጊዜ አማርኛ ኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ሆኖ መታየት አለበት። ኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያዊኛም በመሆኑ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሜትና አስተሳሰብ፣ ምኞትና ፍላጎት ህልውናና አኗኗር የሚገልጥ የሚተረጐም መሆን አለበት። ስለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ስናስብ ከጠባብ አስተያየት መውጣት አለብን” ይላል።

Tsegaye_Gabre-Medhin

ጸጋዬ ስለ ቅኔ ችሎታው እጥረት ሼክስፒርን ይጠቅሳል፣

“ሼክስፒር በዚያን ጊዜ በሥነጽሑፍ ዓለም እንደ ትልቅ ቁምነገር በሚታየው በላቲንና በግሪክ በጣም ደካማ ችሎታ ነበረው። ነገር ግን ቃላት ፈጥሮ፣ ቃላት ከየትም ወርሶና አዋርሶ፣ የሚያፍነውንና የሚያስጨንቀውን የሰዋስው ደንብ ጥሶ፣ የእንግሊዝን ሥነጽሑፍ ከፍተኛ ብቃት ሰጠው።

“ለምሳሌ፣ ‘ጉዲፈቻ’ የሚለው ቃል በአማርኛ ምትክ አይገኝለትም። ‘ማደጎ’ የሩቅ ተመሳሳዩ ነው። ታዲያ ከኦሮምኛ መጣ ከወላይትኛ ለምን አንጠቀምበትም? ዞሮ ዞሮ ሥነጽሑፋችንን ያበለጽግልናል” ይላል ጸጋዬ።

እንደ ዳካሩ በዓል በቅርቡ አልጀርስ ላይ የሚደርገው የፓን አፍሪቃን የሥነጥበብ በዓል ደግሞ ለሁለቱ ደራስያን አንድ ሌላ የጦርነት መስክ ሳይሆን አልቀረም።

ብቻ አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። መንግሥቱ ለማ “ያላቻ ጋብቻ”ን በእንግሊዝኛ ተርጉሞ ተጨዋቾቹን በማሠልጠን ላይ ይገኛል። ካሁን ቀደምም በአንዳንድ የውጭ ዩኒቨርስቲዎች ቴአትሩ ታይቷል አሉ።

“እኔ አቀርባለሁ። መቸም መምረጡ የዳኞች ፈንታ ነው” ካለ በኋላ፣ “ለነገሩ ግን፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቴአትር ወደ አልጀርስ መላኩ ለፖለቲካ የሚበጅ ይመስልሃል? ሰማኸኝ ወይ፣ በእኔ ቴአትር ስንኳ አንድ ሐጅ ካለበት” ሲል በቴሌፎን ያጫውታል።

ጸጋዬ ለአልጀርሱ በዓል ያሰበው ቴአትር ደግሞ ገና ለሕዝብ ያልቀረበ፣ “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የሚል ነው። በጸጋዬ ግምት፣ ኢትዮጵያ የምትመካበት ዋና ሥነባህል፣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነፃነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ ነው። የጴጥሮስ አሟሟት ያኮራናል።

“ግን ቴአትሩን ያዘጋጀሁት ከመንግሥቱ ጋር ለመወዳደር ወይም አልጀርስ ለመሄድ አይደለም” ይላል።

“ ‘የከርሞ ሰው’ን ከፒንተር (Harold Pinter) ወስደህ ነው፤ ሼክስፒርንም በደንብ አልተረጐምክም ይልሃል” አልነው ጸጋዬን።

“ከየትም አምጥቶ፣ ሌላ ‘የከርሞ ሰው’ ይጻፍ እስቲ! እርሱም ይቅር፣ ‘ሐምሌት’ን ይተርጉምና እንይለት። ይተያይ። እንዲሁ ከመንቀፉ የሚያዋጣው ይኸው ነው” ሲል መለሰልን።

Mengistu smiling 2

ለማበላለጥና ለማባለጥ ሳይሆን፣ የጸጋዬ ድርሰት ቁምነገር ሲጫነው፣ የመንግሥቱ ለማ ወደ ቀልድ ያጋድላል። የጸጋዬ ጽሑፍ ስሜትን ይወጋል። ጸጋዬ በድርሰቱ ስሜት ውስጥ ራሱ ገብቶ እየተሰማው የሚጽፍ ይመስላል። በተመልካችና በአንባቢ ላይም ተመሳሳይ ስሜት ያሳድራል።

ለምሳሌ፣ ‘ጴጥሮስ ያችን ሰዓት’ን እንውሰድ። ጸጋዬ የጴጥሮስ ጭንቀት፣ የጴጥሮስ ሰቀቀን የተሰማው ይመስላል። የቴአትሩ ተመልካችም ሳይወድ በግድ ወደ አቡነ ጴጥሮስ የጭንቀትና የሰቀቀን ዓለም ውስጥ መግባት አለበት።

የመንግሥቱ ለማ አቀራረብ ደግሞ የተመልካችና የታዛቢ ዓይነት ነው። ሊያስቅ ሊያስደስት ይችላል። ግን የተካፋይነት ስሜት አያሳድርም። ለምሳሌ፣ ‘መጽሐፈ ትዝታ’ን ስናነብ የማናውቀው ሌላ ዓለም ይታየናል። በስሜት በዚያ ዓለም ውስጥ እንድንኖር ግን አያደርገንም። ‘ያላቻ ጋብቻ’ም እንዲሁ ነው። ታላቋ እሜቴ ሲቆጡ፣ በለጤ ቡና ስታቀርብ፣ ባሕሩና በለጤ ሲሽኮራመሙ እያየን ከመደሰትና ከመሳቅ በቀር ወደ ስሜት ዓላማቸው ውስጥ አንገባም።

 

ታዲያ የሁለቱም ዓይነት ሥነጽሑፍ ዓለም ውስጥ ቦታ አላቸው። ተፈላጊዎች ናቸው። በየፊናቸው በየተሰጥኦዋቸው መወዳደር ይችላሉ።

የሚበጀው ግን ቀና ውድድር እንጅ አጉል ፉክክር አልነበረም።

.

ብርሃኑ ዘሪሁን

1961 ዓ.ም

.

(በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “መነን” መጽሔት። ግንቦት ፲፫፣ ፲፱፻፷፩። ገጽ ፲፮-፲፰።

One thought on “የደራስያኑ ጦርነት

Leave a Reply to ምትኩ አዲሱ Cancel reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s