“ሙሉጌታ አለባቸው” (ቃለመጠይቅ)

“ቆይታ ከሙሉጌታ አለባቸው ጋር”

(ቃለመጠይቅ)

.
[ከአንድምታ ጋር የተደረገ ውይይት]

.

[ሙሉጌታ አለባቸውን በርካቶቻችን የምናውቀው በያዝነው ዓመት ባሳተመው “መሐረቤን ያያችሁ” የተሰኘ የልብወለድ መጽሐፉ ነው። አንዳንዶቻችንም በተወዳጁ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ እና በቀድሞው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት አጭር ልብወለዶቹን እና ትርጉሞቹን አንብበናል። ምናልባት ጥቂቶቻችን ደግሞ “መቅረዝ የኪነጥበብ አፍቃሪያን ማኅበር” ውስጥ አብረነው ተወያይተን ይሆናል።

ሙሉጌታ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በወልዲያ፣ ከፍተኛ ደረጃውን ደግሞ በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ ተከታትሏል። በሥራ በኩልም በጋዜጠኝነት፣ በተርጓሚነት፣ በአርታዒነት እና በሕዝብ ግንኙነት ዘርፎች በማገልገል ላይ ይገኛል። በትርፍ ጊዜውም ሥነጽሑፋዊ መጣጥፎችን እና ድርሰቶችን እያቀረበ ነው። አንድምታ ሙሉጌታን በቅርቡ በሥነጽሑፍ ዙርያ አነጋግራው ነበር።]

በቤታችሁ የነበረው የትረካ ንባብ ባህል ምን ይመስል ነበር?

ልጅነቴ በትረካ የተሞላ ነበር። ያሳደገችኝ አደይ ብዬ የምጠራት አያቴ ናት። የእሷን ሩብ ያክል እንኳን መተረክ ብችል እንደ እኔ ያለ ጸሐፊ አይገኝም ነበር። ከተረከችልኝ ውስጥ “የየዋህ ባልና ሚስቶቹን”፣ እንዲሁም “የአያ ድቡልቡሌን” ታሪክ ሳስታውስ አሁን ራሱ ምናቤ በግልፅ በተሳለ ጣፋጭ ትውስታ ይሞላል። አባቴ እና እናቴ ደሞ አስተማሪዎች ነበሩ። አባቴ ጠዋት የእንግሊዝኛ ተረቶች እያነበበ ይተረጉምልኝ ነበር። “The Axe Porridge” አስታውሳለሁ። ርዕሳቸው የጠፋብኝ ሌሎች ብዙ ተረቶችም አሉ። እሱ ጠዋት በእንግሊዝኛ ተረት የከፈተውን ቀኔን ማታ አደይ በአማርኛ ተረት ትዘጋዋለች።

ፊደል መቁጠር ከጀመርኩ በኋላ የመጀመሪያው ሰፊ የንባብ ጊዜዬ የክረምት ወቅት ነበር። በእርግጥ ሁለቱም ወላጆቼ አስተማሪዎች ስለነበሩ ሳልወድ ከዓመት እስከ ዓመት ወረቀት ላይ ማፍጠጥ ነበረብኝ። አንደኛ ደረጃን እስክጨርስ ልክ ሰኔ ላይ ትምህርት እንደተዘጋ የሚቀጥለው ክፍል መጽሐፎች ቤት ድረስ ይመጡልኛል። ከመደበኛ የትምህርት ጥናት ሸፍቼ ልቦለድ እና ታሪክ ንባብ ውስጥ ሳልሠወር በፊት የክረምት ንባቤ ሳይንስ፤ ኅብረተሰብና ስነ-ሕይወት ነበር።

ቆይቶ ግን ከትምህርት ውጪ ያሉ መጽሐፎች ይመጡልኝ ጀመር። አማርኛ መማሪያ መጽሐፎች ውስጥ ያሉትን ታሪኮችም እወዳቸው ስለነበር የሌሎች የክፍል ደረጃዎችን መጽሐፎች እየተዋስኩ አነባለሁ። “መጀመሪያ የመቀመጫዬ ይውጣ” ያለችው ዝንጀሮ ታሪክ በግጥም ሁሉ ነበር። አሁን ድረስ አልረሳውም። መማሪያ መጽሐፎቻችን ውስጥ ከ“ደማሙ ብዕረኛ” (መንግሥቱ ለማ)፣ ከታደሰ ሊበን፣ ከበአሉ ግርማ ሥራዎች የተቀነጨቡ ታሪኮች ነበሩ።

ተወልጄ ያደግኩባት የወልዲያ ከተማ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ይመስገንና “ላጠና ነው” በሚል ሰበብ ሄጄ ብዙ አነብ ነበር። ሥራዎቹን በአማርኛ ትርጉም አንብቤ በሼክሲፒር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደመምኩት እዚያ ነው። አሁን የዘነጋኋቸውን ግጥሞች ከመጻሕፍት እየገለበጥኩ ቤት ተመልሼ ለአደይ አነብላት ነበር። የኪራይ መጽሐፍትም ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ሁለት ወር ክረምት ከክፍሌ የምወጣው ሌላ መጽሐፍ ተከራይቼ ለማምጣት ብቻ ነበር ብል ያጋነንኩት ትንሽ ብቻ ነው። በጊዜው መጽሐፍት ማከራያ ቤቱ ውስጥ የነበሩትን ሁሉ አንብቤያቸው ነበር። ሆኖም እንደ አሁኑ መራጭ አንባቢ አልነበርኩም።

እስቲ ስለትምህርት ቤት እና ልጅነት ትውስታዎችህ አካፍለን።  

አምስተኛ ክፍል ስገባ አባቴ እንግሊዝኛ እናቴ ደሞ አማርኛ አስተማሪዎቼ ነበሩ። ያኔ ይሆናል ሳላስበው በቋንቋ የተመሰጥኩት። ከአማርኛ አስተማሪዎቼ የማስታውሰው የአሥራ ሁለተኛ ክፍል አማርኛ አስተማሪዬ ነው። የታዋቂ ሰዎች የሕይወት ታሪክ እንዲያመጣልኝ እየጠየቅኩት በእንግሊዝኛ የሚያመጣልኝን ጽሑፍ እየተረጎምኩ በሚኒሚዲያ አቀርብ ነበር። በቁም ነገር የሚሠራ ትልቁ የክበብ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባሁት ግን “ራዕይ” የተባለ የአማተር የስነ-ጽሑፍ እና የጋዜጠኞች ማሕበርን ስቀላቀል ነው። እዚያ ውስጥ ያሉ ሰዎች በጣም ጠንካራ ናቸው። በሳል ከያኒያን ናቸው። እኔ በዕድሜም ትንሽም ነበርኩ። በእውነት ሳስበው በዚያ ዕድሜዬ እነሱ መካከል መገኘት ባይገባኝም እንድገኝ አድርገውኛልና አመሰግናቸዋለሁ። አስበው ዛሬ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን የማይደረገውን ያኔ አንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ ወቅቱን እየጠበቀ የሚወጣ ጋዜጣ ነበረን!

ከእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ጋር እንዴት ተዋወቅክ?

እንግሊዝኛ አንብቤ መረዳት ስጀምር አባቴ ያነብልኝ የነበረውን የተረት መጽሐፍ በራሴ ማንበብ ጀመርኩ። ከዚያም ወልዲያ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ሄጄ “Short Story International” የተባለ በተከታታይ የሚወጡ የዘመናዊ ጸሐፊዎችን ሥራዎች የያዙ በርካታ መጻሕፍት አገኘሁ። “The Penguin Book of Very Short Stories” የሚልም ነበረ። ከእነዚህ ጥቂቱን ተርጉሜያቸዋለሁ።

ኮስተር ብዬ ማንበብ የጀመርኩት ግን ዘግይቼ ነው። በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (አአዩ)። በተለይ በአአዩ ቆይታዬ ሰፊ የማንበቢያ ጊዜ ነበረኝ። ኬኔዲ ቤተ-መጻሕፍት ብዙ መጽሐፎቹ ጠፍተውበት እንኳን ብዙ ሰጥቶኛል። በኋላ ላይ የተወሰኑትን ወደ አማርኛ የተረጎምኳቸውን የጄምስ ጆይስን ሥራዎች፤ ቻርለስ ዲከንስ፤ እና የግሪክ ጸሐፌ ተውኔቶችን ሥራዎች የእነ ሶፎክለስ፣ የእነ አሪስቶፌንስ፣ የሌሎችም። ፈራ ተባ እያልኩ ፍሮይድ እና ያንግን ማንበብ የጀመርኩትም እዚያው ነው። ጸጋዬ ገብረ መድኅን በዋናነት በአማርኛ እንደተጻፉ አድርጎ ያቀረበቸውን የሼክስፒር ተውኔቶች አንብቤ በተአምራዊ ቋንቋው የማለልኩትም በዚህ ጊዜ ነበር።

ዋሳ ኒቨርስቲ ሥነጽሑፍ እንድትማር እን ወሰንክ?

አስቤው አልነበረም። ፍላጎቴ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነት መማር ነበር። አሁን ሳስበው እዚህ የትምህርት ክፍል ውስጥ ባለመመደቤ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥራለሁ። ምክንያቱም የተመደብኩበት የትምህርት ክፍል በዋናነት ሥነ-ጽሑፍ ላይ ቢያተኩርም ከጋዜጠኝነት ጋር ስለሚያያዙ ጉዳዮች ሁሉ በቂ እውቀት ጠቅለል አድርጎ ሰጥቶኛል። ጋዜጠኝነት፣ የሕዝብ ግንኙነት፣ አርትኦት፣ ማስታወቂያ ወዘተ…

ዋሳ ሳለህ “መቅረዝ የኪነጥበብ አፍቃሪያን ማኅበር ውስጥ ምን አይነት እንቅስቃሴ ደረ ነበር?

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የነበረኝን ቆይታ የማይዘነጋ እንዲሆን ካደረጉልኝ ነገሮች አንዱ መቅረዝ ነው። በየሳምንቱ አንዴ እንገናኝና ሁሉም የጻፈውን ያነባል። ጠንካራ የሂስ ባህል ነበረን። በተማሪነት ዘመኔ እንደዛ ዓይነት ቀጥተኛ እና ክሪቲካል ሂስ መሰጣጠት ለምጄ በኋላ ሰፊው ዓለም ውስጥ ስገባ ግን በተቃራኒው ሆኖብኝ ሁኔታውን ለመረዳት ተቸግሬ ነበር። በአብዛኛው በግል ትውውቅ መረብ እና ካብ ለካብ በመተያየት ደንብ እንደሚዘወር ሲገባኝ እውነታው ይሄ ነው ብዬ ለመቀበል ጥቂት ጊዜ ወስዶብኛል።

መቅረዝ ውስጥ የተመረጡ ሥራዎችን የምናቀርብባቸው ዝግጅቶችም ነበሩን። መቅረዝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል አቻ ነበር። አብዛኞቹ አባላቱ በአሁኑ ሰዓት ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎች እና ገጣሚዎች ሆነዋል። ራሳቸውን ቢደብቁም ውብ ግጥሞችና አስደማሚ ትረካዎችን የሚጽፉም አሉ።

ዋሳ ሳለህ የአማርኛ ሥነጽሑፍ ንባብህ በምን መልኩ ተቀየረ? የእንግሊዝኛስ?

አንድ የንባብ ቡድን ነበረን፤ በየወሩ ገንዘብ እያዋጣን በአባላቱ ጥቆማ መሠረት መጽሐፍት ገዝተን እሱን በተራ እናነባለን። በአብዛኛው የአማርኛ መጻሕፍት ነበሩ። በዋናነት ታሪክ እና ስነ-ጽሑፍ። መጻሕፍት ከማገኘትም በላይ ጓደኞቼ ምን ዓይነት መጽሐፍ ማንበብ እንዳለብኝ አቅጣጫ ይሰጡኛል። እንደ በፊቱ በአግበስባሽት ማንበብ አይቀጥልም።

የተማርኩት ትምህርት የእንግሊዝኛ ስነጽሑፍ ውስጥ የትኞቹን ግጥሞች፤ የትኞቹን ልቦለዶች እና የትኞቹን ትያትሮች ማንበብ እንዳለብኝ መንገዱን መርቶኛል። አሁን ድረስ አንብቤ ያልጨረስኩት መለሎ የርዕሶች ዝርዝር አለኝ። የምማረው ትምህርት ራሱ ሥነ-ጽሑፍን ማንበብና መረዳት ስለነበር በደስታ ብዙ አነባለሁ። አንብብ ተብዬ በአስተማሪዎቼ ከታዘዝኩት ዘልዬ ሁሉ የዩኒቨርሲቲው ቤተ-መጻሕፍት የደረደራቸውን መጻሕፍት እገላልጣለሁ። የሄሚንግዌይን A Farewell to Arms እና የቼኑ አቼቤን No Longer at Ease በባዶ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተቀምጬ ሳነብ አስታውሳለሁ። የጄኬ ሮውሊንግስ መሳጭ ፋንታሲ Harry Potter Seriesን ከአንድ ወዳጄ ጋር እየተሽቀዳደምን ደጋግመን እናነብ ነበር።

የትርጉም ሥራዎችስ በዚህ እድሜህ ወቅት ሞካክረህ ነበር

ትርጉም መስራት የጀመርኩት በ1998 ዓ.ም. ነው። አስራ ሁለተኛ ክፍል ነበርኩ። ለትምህርት ቤታችን ሚኒ ሚዲያ ከማዘጋጀው ውጪ በጊዜው እሳተፍበት በነበረው የሥነ-ጽሑፍ እና የጋዜጠኞች ማሕበር አቀርብ ነበር።  የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ሄጄ ሙሉውን ታሪክ በእጄ ጽፌ ከገለበጥኩ በኋላ የምተረጉመው ቤቴ ሄጄ ነበር። በእንደዚህ ‘ጥንታዊ’ ዘዴ የሠራኋቸው እንደ “Shoboksh and the Hundred Years” (የግብጽ አገር ልቦለድ) ያሉ አጫጭር ልቦለዶች ነበሩ።

ከዚያ በኋላም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ደግሞ የስነ ጽሑፍ ኮርሶች ውስጥ መማሪያ ሆነው የሚመጡ ግጥሞችና አጫጭር ልቦለዶችን መተርጎም ደስ ይለኝ ነበር። እነ ጆን ኪትስ፣ ወርድስወርዝ፣ ሼሊ፣ ቴኒሰን እና የሌሎችም ገጣሚያን ሥራዎች። La Bella Dame Sans Merci (“ምሕረት የለሿ ልዣገረድ”) እና Ode to a Nightingale በተለይ አይረሱኝም። ከአጫጭር ልቦለዶችም የልዩ ልዩ አገራት ጸሐፊዎችን ድርሰቶችን እተረጉም ነበር። የእነ ጆቫኒ ቦካሺዮ እና የእነ አንቶን ቼኮቭ። የቼኮቭን “ቫንካ” ተርጉሜ ዶርም ውስጥ ስናነብ አስታውሳለሁ። ከቼኑ አቼቤ አጫጭር ልቦለዶችም እንደዚሁ ለመቅረዝ አቀርብ ነበር።

በአዲስ አበባ ርስቲ የድኅረ ምረቃ የመመረቂያ ጽሑፍህን ርእስ እን መረጥክ?

ርእሴን (Stream of Consciousness) የመረጥኩበት ምክንያት በቴክኒኩ ፍቅር ስለወደቅኩ ነው። ሆኖም አሁን ላይ ሳየው የመመረቂያ ጽሑፌ በኩራት የማቀርበው ሰነድ አይደለም። የሠራሁት አዳም ረታ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ላይ ነበር። ብዙ የተመሰጥኩት በመጽሐፉ ቅርጽ ላይ ነበር፤ ይዘቱን ስቼዋለሁ ሁሉ! ከመጀመሪያ ዲግሪዬ የመመረቂያ ጽሑፍ በተቃራኒ፤ የድኅረ ምረቃ ትምህርት የመመረቂያ ጽሑፌ በአሳዛኝ ሁኔታ እንጭጭ የግብር ይውጣ ሥራ ነበር። ለዚህ በዋናነት ተጠያቂው የግል ስንፍናዬ ቢሆንም ዛሬ ላይ ቆሜ ሳየው ግን ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ።

አሁን ዓለም አቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ጆርናሎች ላይ የሚወጡ ጽሑፎችን የማየት ዕድል አግኝቻለሁ። መሥፈርታቸው እና የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ ሳይ ‘ከዚህ ቢፊት የሠራሁት ምንድን ነበር?’ የሚል ማወዳደር ውስጥ እገባለሁ። ተማሪዎች ምርጥ የምርምር ጽሑፎችን ማዘጋጀት የማይችሉት የእኛ ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ምን ቢጎድለው ነው? ብዬ እጠይቃለሁ።

ባለፉት ዓመታት ስቡክ ውስጥ ስለተጀመረው የኪነጥበብ ውይይት ምን ትውስታ አለህ?

አአዩ ውስጥ ሳለሁ በፌስቡክ ኪነ ጥበባዊ ውይይቶችን የሚያደርጉ ጥቂት ግለሰቦችን አይቻለሁ። መጀመሪያ ላይ ጠንካራ ሊባሉ ለሚችሉ ሥነ-ጽሑፋዊ ክርክሮች ምቹ ቦታ ነበር። በደራሲዎቻችን ስሞች በተከፈቱ የፌስቡክ ቡድኖች ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር ብዙ መረጃዎችን የሚለዋወጥ፣ ጠባብ ቢሆንም ጠንካራ እንቅስቃሴ ነበር። አሁን ከስሟል።

የሳይበር ግንኙነት በጊዜ እና በቦታ በተራራቁ ሰዎች መካከል እንዲካሄድ ስለሚያስችል በባሕሪው ኀይለ ቃል መለዋወጥና መዘረጣጠጥን ይፈቅዳል። ሥነ-ጽሑፋችን ውስጥ ከጥንት የነበረውን በግል የትውውቅ መረብ የመደናነቅ/የመነቃቀፍ ልማድም አጉልቶቷል። በቃላት ከተደረተ ጽንፈኛ ትችት በስተቀር ውኃ የሚያነሳ ሀሳብ ይዞ የሚሞግት የሥነ-ጽሑፍ ሂስ እና ውይይት ያነበብኩበት ጊዜ እጅግ ጥቂት ነው።

የጋዜጠኝነት ዘመንህ የሥነጽሑፍ ፍቅርህን አደበዘዘው ወይ አጠነከረው?

ጋዜጠኝነት ሥነ-ጽሑፍን ሊተካልኝ አልቻለም። ተርጓሚነትም እንደዛው። ስለዚህ ሥራዬም እረፍቴም ሥነ-ጽሑፍ ነበር ለማለት አልደፍርም። በጋዜጠኝነት ዋና ሥራዬ መረጃ መሰብሰብና አቀናጅቶ ማሰራጨት ነበር። ጋዜጠኝነት ተጨባጭ መረጃን በማነፍነፍ ተጠምዷል። ስለዚህ ሥነ-ጽሑፍን ሊተካልኝ አይችልም። ከጋዜጠኝነት ደረቅ የመረጃ ስርጭት ለማምለጥ የሚረዱኝ ስልቶች ግን ነበሩ … አንደኛው የመጻሕፍት ዳሰሳዎችን መሥራት ሁለተኛው ደሞ ለሌሎች ጋዜጦችና መጽሔቶች መጻፍ። እነ “አዲስ አድማስ” እና “አዲስ ጉዳይ” ማምለጫ ቀዳዳዎቼ ነበሩ።

ሙሉ ጊዜህን ለሥራ ዓለም ብትሰጥም ባለህ ትርፍ ጊዜ ጥበባዊ ድርሰቶችን እየሰራህ ነው። የእንጀራ እና የጥበብ ነገር እንዴት ነው?

የተለመደ አባባል ልጠቀምና “ጥበብ ጠራችኝ” ብልም የእንጀራ ጥሪ ጎልቶ ይሰማኛል። ምንዳ ስለሚከፈለኝ አይደለም። ጽሑፍን እንደምወደው ሁሉ ሥራንም እወዳለሁ። ስለአንድ ፕሮጄክት ዝርዝር ጉዳይ ተጨንቄ ሥራውን በስኬት ማጠናቀቅ አንድ አጭር ልቦለድ ጽፎ ከመጨረስ የማያንስ ደስታ ይሰጠኛል። በአጭሩ ለሥነ-ጽሑፍ ፍቅር ብዬ የእንጀራ ገመዴን አልበጥስም ማለት ነው።

የስብሐት እና የበአሉ ግር ሥራዎች በአንተ ውስጥ ስለተዉት አሻራ የምትለው አለ?

የስብሐት እና የበአሉን ሥራዎች በጣም እወዳለሁ። ከስብሐት ሥራዎች በተለይ “አምስት ስድስት ሰባት” አንጀቴን ያርሰኛል። ፋንታሲው ጠቅልሎ ወደ ሌላ ዓለም ይወስደኛል። ሁልጊዜም ሲጽፍ ሕይወትን ነው። በአሉም እንደዛው። በተለይ “ከአድማስ ባሻገር” ልብ ላይ የሚደርስ ሥራ ነው። ደሞ በሌላ መጽሐፉ ውስጥ ያቺ ውብ የበአሉ ግጥም አለች!

“የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር

የሰው ልጅ ልብ ነው፤

የሌለው ዳርቻ፣ የሌለው ድንበር!”

ከልብወለድ እኩል የግጥም ፍቅር ያለህ ይመስላል።

ቃላትን ወድጄ የግጥም ፍቅር ባይኖረኝ ግዙፍ ምጸት ይሆን ነበር። ሆን ተብለው በተመረጡ ቃላት የተዋቀረች አንዲት ስንኝ ካነበብኩ መጽሐፉን ዘግቼ በሀሳብ ጭልጥ እላለሁ። ግነት አይደለም። አንዳንዱ ቀኔ ጠዋት አንብቤው በምወጣው ነገር ይወሰናልና ምን ማንበብ እንዳለብኝ እጠነቀቃለሁ። እንደ ዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” ዓይነት ነገር በጠዋት ካነበብኩ ቀኑን ሙሉ ተረብሼ እውላለሁ።

“አዋሽ ማዶ አብረን እንውረድ” ሲል ጸጋዬ፣ ወይም ገብረክርስቶስ “የፍቅር ሰላምታ” ሲል ፍቅር ካልተሰማኝ ቃላት መውደዴን መጠራጠር መጀመር አለብኝ። የደበበንም “ጊዜ በረርክ በረርክ” ሳነብ ልቤን ካልነዘረው። በእውቀቱ ደግሞ ድንቁን ሀሳብ በውብ ቋንቋ አሽሞንሙኖ በልዩ የስንኝ ምጣኔው ሲያስቀምጥ ካልተገረምኩ “በድንቅ አብቃይ ምድር” ሳይገርመኝ እየኖርኩ የማልፍ ትውልድ ሆንኩ ማለት ነው።

እንደመታደል ሆኖ የአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በዝርው ከሚያቀርብልኝ አማራጮች በላይ በሥነ-ግጥም ሰጥቶኛል። ከምወዳቸው ደራሲያን ቁጥር የምወዳቸው ገጣሚያን ቁጥር ይበልጣል።  ደበበ ሰይፉ፣ ነቢይ መኮንን፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ሰለሞን ዴሬሳ፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ጌትነት እንየው፣ የሻው ተሰማ፣ ቴዎድሮስ ፀጋዬ … መአት ናቸው። በመጽሐፍ መልክ ባይሆንም እንኳን የዘፈን ግጥም አለልኝ። በብዛት አለመገኘቱ እንጂ ዝርው ግጥምም አለ!

ከአዳም ረታ ሥራዎች ጋር ስለተዋወቅክበት ኔታ እስቲ ትውስታህን ብታጋራን

በ2000 ዓ.ም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማደሪያ ክፍላችን ውስጥ በሚገኘው ሎከር ከተደረደሩት መጻሕፍት መካከል አንድ ወፈር ያለ “ግራጫ ቃጭሎች” የተሰኘ ልቦለድ መዝዤ ማንበብ ስጀምር እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ሁሉም ቦታ ይዤው የምዞረው ጥራዝ ይሆናል ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር።

የቅርጽ እና የይዘት ድንቅ ውሕደቱ ምን ጊዜም አይጠገብም። ከእንጀራ የተቀዳው ቅርጹ ልቦለዱን ከዓይን እስከ ሰበከቱ እየደጋገምኩ እንድበላው/እንዳነበው ያደርገኛል። በገጸ ባሕሪያቱ ተደንቄ ሳልጨርስ በጣፋጭ ቋንቋው እገረማለሁ። ጎልቶ በማይታይ ሤራ መሳጭ ልቦለድ እንደሚጻፍ ሌላ ማሳያ ነው። ይሄው እስከ ዛሬ ድረስ ዋና ገጸ ባሕሪው መዝገቡ ሥጋ እንደለበሰ ሰው እንጂ በመጽሐፍ ገጾች መካከል እንደሚገኝ ምናብ ብቻ አልቆጥረውም።

ግራጫ ቃጭሎችን ደግሜ ባነበብኩት ቁጥር ከዚህ በፊት ያላየሁት ነገር አገኛለሁ። በጥቅሉ በአማርኛ ቋንቋ እንደዚህ ሊታሰብ እና ሊጻፍ መቻሉ አስደመመኝ።

እጅህ ላይ ስላሉት ድርሰቶች እና ውጥኖች ጥቂት ብትነግረንስ?

የአጫጭር ልቦለድ ቢጋሮች አሉኝ። ሆኖም አሁን ትኩረቴ እሱ ላይ አይደለም። አምርሬ ከመጀመሬ በፊት ማንበብ አለብኝ። ከልቦለድ ውጪ ግን የጀማመርኳቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንድ ልዩ መጽሐፍ አለበት – ለአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ያልተለመደ ዓይነት መዝገበ ቃላት ነው። በቅርቡ ይታተማል ብዬ ተስፋ አለኝ …

ለቆይታው እናመሰግናለን።

 እኔም አመሰግናለሁ።

.

ሙሉጌታ አለባቸው

(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)

ሐምሌ 2009 ዓ.ም

.

“ማሪበላ” (ልብወለድ)

“ማሪበላ”

ከሙሉጌታ አለባቸው

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

… ዞብል። ዞብል። ዞብል። …

ስጠራው አፌ ላይ ቅልል ስለሚለኝ ነው መሰል ይሄን ቃል እወደዋለሁ። የምወደው አባቴ (እሱም ከልጆቹ ሁሉ የሚወደኝ) የተወለደበት ዛፋማ አገር ስለሆነ፤ ዛጎል ከሚለው ቃል ጋር  ስለሚመሳሰልብኝም ይሆናል። እንቆአርያ እወዳለሁና። ይሄ የዞብል እና የዛጎል ድምፅ መመሳሰል መርቶኝ ሳይሆን አይቀርም ያኔ ዛጎሎች ከአሸንጌ ሐይቅ የሚለቀሙ ሳይሆኑ ከዛፍ የሚሸመጠጡ ቀንድ አውጦች ይመስሉኝ ነበር። አንዳንዴ በሥራ ፈት ምናቤ አያይዤ የማስኬደው የአባቴ ትረካ ያነሳሳው የሀሳቤ ባቡር እነኚህን የቃላት ፉርጎ አስከትሎ ይነጉዳል፡ ዞብል፣ዛጎል፣ማዘል፣ወተት፣ጸጉር፣ማር፣አርሒቡ፣ኮንሶ፣ሰተት፣ፍቅር

.

ዞብል፣ዞብል፣ዞብል …

ሄጄበት የማላውቀው የዞብል ሰፊ ምድር የጃምዮ፟ ሰብል ለብሶ ይታየኛል።  አናቴ መሀል የምታቀልጥ ፀሐይ እንደ ጋለ ቆብ፣ ጥላ ሞቴ እንደ ጥቁር ምንጣፍ እግሮቼ ሥር፣ በውሃ እጦት የተሰነጣጠቀ ምድር ላይ፤ እኔ በማሽላ ማሳ መካከል እንደ መንድብ ሰንጥቄ ሳልፍ ግራና ቀኝ እየታከኳቸው የሚያልፉ ሞተው የደረቁ ቅጠሎች እየተንሿሹ። የጎመራ የማሽላ ቅጠል እንደ አፋር ጊሌ በሰላ ጠርዙ ስስ ቆዳዬን “እያረደኝ”። (ታናሽ ወንድሜ ቆቦ አካባቢ የሚኖር አንድ የአባቴ የቅርብ ዘመድ ያመጣልንን የጥንቅሽ አገዳ ሲያኝክ ልጣጩ አውራ ጣቱን ሰንጥቆት ደሙ እየተንጠባጠበ ሲያለቅስ ምን እንደሆነ ብጠይቀው “ጥንቅሹ አረደኝ” እንዳለኝ ያክል ባይሆንም)።

.

ዞብል፣ዞብል፣ዛጎል

ከደረታቸው መሃል ለመሃል ለሁለት ተከፍለው፣ አካፋያቸውም ውሽልሽል ስፌት እንደፈጠረው ሽብሽብ መስሎ፣ ወይ በጥቁር ጭራ እኩል ቦታ ላይ ተሰፍተው እንደተያያዙ ሁለት የእርጎ ቁራጮች። ታናሽ ወንድሜ ከሚታዘልበት በለፋ ቆዳ ከተሰራ ባለ ቡናማ ቀለም አንቀልባ ግርጌ በቀጫጭኑ ተተልትሎ እንደ ነጠላ ዘርፍ ከተንዘረፈፈ ሌጦ ጫፍ ላይ የተንጠለጠሉትን ዛጎሎች በልስልስ ጥፊ መታ መታ እያደረግኩ ሆጨጭ ሲሉ ስሰማ የሚሰማኝ መረጋጋት ወደር አልነበረውም። ጡት አስጣዬ በጨዋታ ደክሞ ሲነጫነጭ እናቴ ሰርኬ እሹሩሩ ብላ ልታስተኛው ስትፈልግ በመጀመሪያ ልዩ ስሜን በልዩ ቁልምጫ ጠርታ አንቀልባውን እንዳቀብላት ትጠይቀኛለች፣

“…ይሄ ልጅ ተብሰከሰከ… እንቅልፉ መጣ መሰል። እስቲ ያን ማዘል አቀብለኝ”

.

ዛጎል፣ማዘል፣ወተት

እኔንም ያሳደገ ያ ማዘል ከፈፉ በጨሌ ያጌጠ ነበር። አንድ ዛር አንጋሽ አንገቱ ላይ የጨሌ ማተብ አንጠልጥሎ ስላየሁ እነኛን ደቃቅ ዶቃዎች አልወዳቸው፣ እፈራቸውም ነበር። ከዚህ አንቀልባ ወርጄ ገና ወፌ ቆመቼን ሳልጨርስ ከሥሬ ለተወለደው ታናሽ ወንድሜ ተራውን አልለቅም ያልኳት እማ፤ ጡቷን እንደ ልሃጭ በሚዝለገለግ የእሬት ደም ለቅልቃ ስታቀርብልኝ እየመረረኝም ቢሆን መለግለጌን አልተው ብላት ከዞማዋ አንድ ሁለት ሰበዝ ነጭታ፤ የጡቷ ጫፍ ላይ ጠምጥማ “በላህ! በላህ!” ስትለኝ…. አሁን ሳስበው ያኔ ይመስለኛል ለጭገር ያለኝ ፍርሃት የተፀነሰው።

.

ማዘል፣ወተት፣ጸጉር

መፍርሄ ጸጉር ሳያጠቃኝም አልቀረም። በብብቶቼ ሁሉ ጸጉር ማብቀል ከጀመርኩ አንስቶ በየሳምንቱ መንትዮቹ ጸጉር ቆራጮች ምናሴ እና ኤፍሬም ጋ እገኛለሁ። ገና የፂም ቁጥቋጦ ፊቴ ላይ ኑግ መስሎ መፍሰስ ሲጀምር ዘወትር ጠዋት መስታዎት ፊት ቆሜ ሙልጭ አድርጌ እላጫለሁ። ብችል ቅንድቤንና የዐይን ጭራዬን ሁሉ ከሥራቸው ነቅዬ ብጥላቸው በወደድኩ።

.

ወተት፣ጸጉር፣ማር

ያደግኩበት ቤት ዘወትር በአባቴ ወዳጆችና በእናቴ ቡና አጣጮች የተሞላ መንገድ ዳር ያለ ቤት ነው። ቤታችንን ከሚያዘወትሩ የአባቴ ወዳጆች ሁሉ የምወደው ዳውድ የተባለ ሹፌር ነበር። ነጭ ፒካፕ መኪና የሚነዳ። ለሽርሽር የሚወስደኝ። ከእማማ ዘምዘም ጣፋጭ የሰሊጥ እንክብል/ፎፎን የሚገዛልኝ። የሰፈሬን ጣፋጭ ጥምዝ ኬኮችም የሚያስገምጠኝ።

ከዳውድ የሚያስጠላኝ ነገር በሚያጎፍረው ጢሙ ፊቴን ሲነካኝ ነው። ማር ጸጉር ከነካ ያሸብታል ይባል የለ? ዳውድ ሳሕን ሙሉ ኑግ ከመሰለው ጥቁር ጸጉሩ ተለይታ ከግንባሩ ከፍ ብሎ በግራ በኩል የተቀመጠች ትንሽዬ ጨረቃ የመሰለች ክብ ሽበት ነበረችው። ልክ ጨረቃን በቴስታ እንደመታ ሁሉ።

ከጋሽ አቦሰጥ ቤት በየዓመቱ የሚላክልንን የጥቅምት ማር ውስጥ ልክ እንደሞተ ንብ ተዘፍቄ ስወጣ አግኝቶኝ ወለላ የለበሰ ፊቴን በጸጉሩ ሲዳብስ የነካው ይሆናል ብዬ አስብ ነበር።

.

አርሒቡ

ከገነቴ ከተማ ነዋሪዎች አባቴን የማያውቅ ያለ አይመስኝም ነበር። ከሁሉ ጋር አርቦሽ የሆነ፣ ሁሉን የሚጋብዝ፣ ሰውን ሁሉ በእኩል ዓይን የሚያይና ሰው ሁሉ የሚወደው አባት ነበረኝ። የግራ እጁ የማርያም ጣት ላይ የሚያስራትን ባለ አረንጓዴ ፈርጥ የብር ቀለበት እያሻሸ “የደጃች ብጡል ዘር ነኝ” ስለሚል አንዳንዴ የከተማውን ሰው ሰብስቦ ግብር ማብላት ሁሉ ሳያምረው አይቀርም እያልኩ አስባለሁ። አውራ ጎዳናው ዳር ያለው ቤታችን ውስጥ ቁጭ ብሎ ኮረፌውን እየጨለጠ ከግራ ቀኝ ሲመላለሱ ከውስጥ ሆኖ ጎራ እንዲሉ ይጋብዛል፣

“አርሒቡ!”

“እንኳንም ዳገቱን አልፈን ግራካሶን ወጣን አንተዬ፤ ይሄን የእናት ጡት የመሰለ ኮረፌ ከየት እናገኘው ነበር ነውኮ የሚያስብለኝ ጃን” ይላል በማርማላት ጣሳ ለእንግዳው እየቀዳ። ይሄ አባባሉ ቃል ሳይቀየር በመደጋገሙ ጭንቅላቴ ውስጥ እንደሆነ የተረሳ የልጅነት መዝሙር በሥራ ፈትነት ተጋድሞ አሁን ድረስ ሲገላበጥ ይሰማኛል። ወዲያው ደግሞ ቀጥሎ “ያዝ በል ይቺን ያዝ” ይላል ጣሳውን ሲያቀብል።

ታዲያ አባቴ “አርሒቡ” ባለ ቁጥር “አትራቡ!” ብሎ እጅ ነስቶ የሚያልፈው ጥቂት ሰው ብቻ ነበርና አንዳንዴ እናቴ ግብዣ አበዛህ ብላ ስታማርር “ሁሉ በዚህ ዓለም ቀሪ ነው፤ ይዘንው አንሄድ” ይል ነበር። ብቻ አንድ ወይንጠጅ ቆብ የሚደፉና ሁሌ ጥቁር ጃንጥላ የሚይዙ፣ መስቀል ሲያሳልሙን ወርደን ጉልበታቸውን ካልሳምን የጽንሃ ዥዋዥዌ ባቆረፈደው እጃቸው ደረቅ ቁንጥጫ የሚያቀምሱን እጃቸው ከርቤ ከርቤ አፋቸው ጌሾ ጌሾ የሚሸት አባ ገብረ ኪዳን የተባሉ የንስሐ አባታችን የሆኑ ቄስ ጋር ሲደርስ ጋባዥነቱ ይጠፋል። ሆደ ሻሹ አባቴ ቄስ እንደማይወድ በግልፅ እየተናገረ “አባ ገብረ ኪዳን ውሽማሽ ናቸው መሰለኝ፤ እግሬ ወጣ እንዳለ አድራሻቸው በድንገት ወደዚህ ቤት ይለወጣል” እያለ ሰርኬን ይተርባል። “አማረልኝ መስሎሃል” ትላለች ከጓዳ ውስጥ።

የቄስ ደንብ ነው መሰለኝ አባ ገብረ ኪዳን ጥቅስ፣ ግዕዝና አግቦ መናገር ያበዛሉ። ቆለኛው አባቴ ነገሩ ሁሉ ፊት ለፊት ነው። የማይጥመው ነገር ካጋጠመው እዚያው ቦታው ላይ በግልፅ ዐማርኛ እንዳልጣመው ተናግሮ ያልፋል። አንድ ቀን ግን በሚገባቸው ቋንቋ ላናግራቸው ብሎ ነው መሰል የሚደነቃቀፍ ግዕዝ ሸምድዶ ተናገራቸው።

የዚያን ዕለት ትዝ ይለኛል መልካ-ቆሌ ከተባለች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቴ ተዛውሬ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ወደ ተባለ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የገባሁበት የመጀመሪያ ቀን ነው። የጠዋት ፈረቃ ትምህርቴን ጨርሼ መጥቼ አባቴ ጎን ተቀምጫለሁ። ትምህርት ቤቱን ወድጄው እንደሆነ እያሳሳቀ ይጠይቀኛል።

“ብቻ አልወደድኩትም ካልከኝ አማራጭ የለም ቄስ ትምህርት ቤት ትገባለህ። ከዚያ እንደዚህ ሰውዬ (ወደ እኛ ቤት አቅጣጫ የሚመጡትን አባ ገብረ ኪዳን እየጠቆመ) ፂምህን ታሳድግና ጥቁር ጃን ጥላ ይዘህ ቤት ለቤት እየዞርክ መቀላወጥ ነው”

“ኧረ ደስ ይላል። ግን ሩቅ ነው”

“በል እንደ ቅድመ አያቶችህ ፈረስ ይገዛልህና ደንገላሳ እየጋለብክ ወፋ ውጊያ ትወርዳለህ። ሃሃሃ። ልጅ እያሱን መስለሽ ልትገቢ ነዋ ተማሪ ቤትሽ። ማን እንበልዎ እርስዎንስ … ልጅ ማሪበላ እንበልዎት ይሆን?”

“ሩቅ ነው ነው ያልኩት።”

“መጋል ይሁንልህ ዳለቻ?”

“ምኑ?”

“ፈረሱ ነዋ ልጅ ማሪበላ … ፈረሱ” ተነስቶ በሹፈት እጅ ነሳኝ።

“አታሹፍብኝ” እያሳቀኝ ያናድደኛል።

በመንገድ ሲያልፉ አይቶ እንዳላየ ዝም ቢላቸውም ራሳቸውን ጋብዘው ገቡና ገና ቂጣቸው መቀመጫ ሳይነካ እንግዳ ተቀባይ ስለመሆን፣ የሆነ አብርሃም የተባለ የድንኳን ቪላ ውስጥ የሚኖር ሰውዬን እንደ አብነት እያነሱ ብዙ ብዙ አወሩ። ሰርኬ ልታስተናግዳቸው ጓዳ ውስጥ ትንደፋደፋለች። እስከዚያው ማዳረሻ እንዲሆን ብላ ኮረፌ ስትቀዳላቸው “አይ ወለተ ጴጥሮስ፤ ኮረፌሽ አምሮኝ ነውኮ የመጣሁት፤ ሌላ ሌላውማ የትም አለ” እያሉ ተቀበሏት። ከእሱ ፉት ብለው “ከእናት ጡት እንደሚፈስ ወተት ማለት ነው የኮረም ኮረፌ” ሲሉ ባልጠበቁት ፍጥነት አባቴ በነገር ያዛቸው።

“ደሞ ዘፈንም ያዳምጡ ጀመር?”

ሰርኬ ጆጉን አስቀምጣ ወደ ጓዳ ስትመለስ በአጠገቡ የምታልፍ መስላ ጎሸም አደረገችው።

“ምን አገሩ ሁሉ የሚለው ነው” በሀፍረት መለሱ

“ባለፈው ስንፈልግዎት ምነው ጠፉ ግን? እዚህ ቤት ውስጥ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ነበሩ ለወትሮው”

“ብፁዕ አባታችን ይመጣሉ ተብሎ ተኸር በዝቶብናል” ወደ ቤት ሲገቡ የነበራቸው ኀይል ደክሟል።

“አልመሰለኝም” አለ አባቴ። ቀና ብለው አዩት። “ለነገሩ ግዕዙ ጨርሶታል” አለና የሆነ ነገር ለማስታወስ ለአፍታ አሰብ አድርጎ እንዲህ አለ፣

“ኦካህንእንተሀገርከመርቄ

በጊዜማሕሌትበግዕወበጊዜመክፈልትዐንቄ”

ይሄን ተናግሮ ዞብል ድረስ የሚሰማ ታላቅ ሣቅ ሣቀ።

አንዳንዴ አባቴ “ውሽማሽ” የሚላት ነገር አንዴ ካጋጠመኝ ነገር ጋር ይያያዝ እንደሆነ አስብ ነበር። አይደር የተባለ ከተማ ውስጥ ሕጻናት ትምህርት ቤት ላይ ከአውሮፕላን ቦምብ ተጥሎ ብዙ ልጆች የሞቱበት የጦርነት ሰሞን ነበር። የሆነ ጄት ምናምን አየር ላይ ሲያንዣብብ ታይቷል ተብሎ በእረፍት ሰዓት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እንድንሄድ ተነግሮን አዲስ ያፈራኋቸው ጓደኞቼ እዚያው ቆይተን እንድንጫወት ቢለምኑኝም እምቢ ብዬ ወደ ቤት መጣሁ።

ሰርኬ እና አባ ገብረ ኪዳን ቤት ነበሩ። በጣም ተቀራርበው ቆመው ነበር። ደስ አይልም። እኔን እንዳዩኝ ደንገጥ ብለው መስቀላቸውን አወጡና አሳለሟት። ደበረኝ። የሆነ ደስ የማይል ነገር ግን ይሄ ነው ብዬ ላብራራው ያልቻልኩት ድብርት። ከዚያ እያሳለሟት ከእናቴ ጋር ብቻ ሲሆኑ እየደጋገሙ የሚናገሯትን ግዕዝ ተናገሩ።

“ብቻ ወለተ ጴጥሮስ፤ ʻኢያጸድቆ ለሰብእ ጸሎት እንበለ ፍቅርʼ ነው የሚለው መጽሐፉም”

.

ኮንሶ

በተወለድኩበት ዕለት ረቡዕ ለኀሙስ አጥቢያ ቤታችን ደጃፍ ያለች የኮንሶ ዛፍ ላይ የንብ መንጋ ሰፍሮ ይገኛል። ያው መቼም ያሉኝን ነው። ታዲያ ወንድ ልጅ የተወለደለት አባቴ ማርያምን ሲለማመኑ ያመሹ ሴቶች ከተዘጋ ላንቃቸው የሚወጣ ሻካራ እልልታቸው ተሰምቶ ሳያልቅ ይወጣና ሙክት ፍየል አርዶ ቆዳውን ይገፋል። ፍየሉን አንጠልጥሎ ብልቱን ለመገነጣጠል ወደ ኮንሶ ዛፏ ሲጠጋ የሚርመሰመሰውን የንብ ክምር ያያል። ከሴቶቹ አንዷን ጠርቶ የተገሸለጠ ፍየሉን እንድትጠብቅለት ያደርግና ጋሽ አቦሰጥ የተባሉ እማማ ዘምዘም ሰሊጥ ቤት ጎን የሚኖሩ ንብ አንቢ ሰውዬ ጋ ሄዶ ስለ ሁኔታው ያስረዳቸዋል። ጋሽ አቦሰጥም ጊዜ ሳይወስዱ ስፋቱ የመቻሬን ሜዳ የሚያክል የመሶብ ክዳን እና በትንሽዬ ቅል ወተት ይዘው ከተፍ ይሉና ደጅ ላይ ቆመው፣ እናቴን “እንኳን ማርያም ማረችሽ” ብለው፣ ወተቱን ወስከምቢያው ላይ ረጨት ረጨት አድርገው የሚተራመሰው የንቦች ክምር ላይ ይደፉታል። ትንሽ ቆይቶ ወስከምባዩን የያዙበት እጃቸው ከበድ ሲላቸው ቀስ ብለው በግራ እጃቸው ደግፈው ገልበጥ አድርገው ሲያዩ የንብ ዘር ሠራተኛና ድንጉላ ሳትቀር ግልብጥ ብላ እፊያው ላይ ሰፍራለች። ጋሽ አቦሰጥ አባቴን አመስግነው ቀፎ የሚሞላ መንጋቸውን ይዘው በቀስታ እርምጃ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።

አራሷ ጥቂት አረፍ እንዳለችም ብንያም የሚሉት ትልቁ ልጃቸውን ልከው “አደራ ይሄን ልጅ በማር አቀማቅሙት። ንግር ቢኖረው ነው እንጂ ንብ ቀፎዋን ትታ ከተማ መሃል ጎጆ ልስራ አትልም። አደራ” ከሚል ቃል ጋር ጭንቁላ ሙሉ ማር አስይዘው ላኩ። ከዚያ በኋላ በየዓመቱ ከዚያ ቀፎ ማር በቆረጡ ቁጥር “የጥቅምት ማር መድኀኒት ነው” እያሉ ስልቻ ሙሉ መላካቸውን አላስታጎሉም።

ከዚያ የነፍስ አባታችን አባ ገብረ ኪዳን “ተው ልጄ፤ ይሄ ነገር ቅዱሳንን መዳፈር ነው። ይቅርብህ” እያሉት አልሰማም ብሎ ስሜን ላሊበላ አለኝ። ቄሱ ቤት በመጡ ቁጥር (በየቀኑ ማለት ነው)

እስመኀበሀሎትዕቢትህየሀሎኀሳር

እስመኀበሀሎትዕቢትህየሀሎኀሳር

እስመኀበሀሎትዕቢትህየሀሎኀሳር

እያሉ ቢያስፈራሩት እንኳ አልተመለሰም።

ቆይቶ የእናቴ ጸጉር የእናቴን ጡት ካስጣለኝ በኋላ ስሜን ቀየር አድርጎ ማሪበላ አለኝ።

.

ሰተት

የኮረም ተወላጇ እናቴ ሰርኬ ቤታችን ግራና ቀኝ በሚኖሩ ቡና አጣጮቿ ተከባ ማንም ቡና አውቃለሁ የሚል ሁሉ የመሰከረላትን ቡና ከአቦል እስከ በረካ ታጠጣለች። ከቡናዋ ጣዕም የሥነ-ሥርዓቷ። እያንዳንዷን ነገር በዝርዝርና በእርጋታ ስታሰነዳ ትልቅ ድግስ ያለባት ትመስላለች። ታዲያ ሁሉን አዘጋጅታ ልትጨርስ ስትል “በል እስቲ ሂድ ቡና ጠጡ ብለህ ጥራልኝ ጎሽ” ብላ ትልከኛለች። ስመለስ ረከቦቷ ጀርባ እንደ ሰሊክ የሚሰራው እጣኗን እያጨሰች አድባር መስላ ተቀምጣ አገኛታለሁ። ውጭ ቆይተው ሲገቡ ለዓይን ያዝ በሚያደርገው ቤት ውስጥ በእርጋታ በሚተራመሰው የመዓዛ ጭጋግ መካከል ማየት የሚቻለው ድፍን ጨረቃ የሚያካክሉ ዓይኖቿንና እንግዶቿን በሣቅ የሚቀበለውን ልሙጥ ወረቀት የመሰለ ጥርሷን ብቻ ነው።

“እማማ አስረበብና እታለምን ሉሉን ጠርቻለሁ። ዘውዲቱ ቤቷ የለችም” አልኩ ወለሉ ላይ ከተጎዘጎዘው የኮንሶ ዛፍ አንድ ቅጠል ላነሳ እያጎነበስኩ።

“በላይነሽንስ ጠራህልኝ?”

“እማማ አስረበብ ቤት ነበረች”

“የኬጃ ሚስትስ?”

“እሷን አልጠራኋትም፤ ረሳኋት”

“ምን እያሰብክ ነው ከቶ ልብህ ካንተ ጋር የለለው? በል ሂድ አሁን ቶሎ ብለህ ጥራልኝ። ከጎረቤት ልታጣላኝ ነው? እንደው ምን ባደርገው ይሻለኛል እናንተ”

ረከቦቱ አጠገብ ባለግራም ሳሕን በመሰለ ስፌት/ቆለምሽሽ ላይ በግማሽ በኩል ፈንድሻ በግማሽ በኩል ደግሞ የጠመዥ ቆሎ ተቀምጧል። ቆሎዎቹ ላይ ደግሞ እንደ ባልጩት የሚያበራ ልጥልጥ ኑግ በሞላላ በሞላላ ቅርጽ ሆኖ ተጋድሟል። ይሄን የመሰለ የቡና ቁርስ እንዴት እንደምፈጨው እያሰብኩ የሐመልማል ዝንጣፊ እንደ ባንዲራ ከግራ ቀኝ እያውለበለብኩ የኬጃን ሚስት ልጠራ በምሬት ወጣሁ።

ስመለስ “እንደው ምን ባደርግህ ይሻላል፤ የቁራ መላክተኛ የሆንክ ልጅ” አለች። ትክክለኛውን ተረት የተረተች አይመስለኝም። ምክንያቱም፣ እኔ እንደሚመስለኝ ቁራው የቅጠል ዝንጣፊ ይዞ አልተመለሰም። በራሷ ውትወታ አባ ገብረ ኪዳን በግዕዝ ያስተማሩኝን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አጣቅሼ ላርማት ብሞክር ምን እንደምትመልስልኝ ስለማውቅ ዝም አልኩ። ጨዋታ ያሰኘኝ ቀን ቢሆን ግን፣ “ግንኮ ሰርኬ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቁራው አልተመለሰም። እኔ ግን ተመልሼ መጥቻለሁ” እላት ነበር።

መልሷንም ምንም ሳይዛነፍ፣ ምንም ቃል ሳይቀየር መገመት እችላለሁ። “አቤት አቤት፤ ወግ ወጉማ ተይዞልናል። ቁራ ደሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ሊሠራ ገባ? ቀባጣሪ!”

እማማ አስረበብ እና በላይነሽ መጡ። ጉበኑ ላይ ቆሜ በአጠገቤ ሲያልፉ በላይነሽ ኩበት ኩበት ትሸታለች። እንደ ድመት ግልገል ኩሽና ውስጥ ተወልዳ ኩሽና ውስጥ ያደገች መሰለኝ። የእማማ አስረበብ ቀይ ጥለት ያለው መቀነት ፊቴን ጠረገኝ። ከባዳ እጃቸው ደግሞ አናቴን። በጉርምስናዬ ከደባሪ ሚሲሌኒየስ ኤክሰርሳይስ ለመሸሽ ሳነባቸው በነበሩ ልቦለዶች በአንዱ ውስጥ እትዬ አልታየ የተባሉ ገፀ ባሕሪ ሲያጋጥሙኝ ምናቤ ውስጥ የተፈጠረው የእሳቸው ምስል ነበር። እማማ አስረበብ የራሳቸውን ስኒ ይዘው ባይመጡም ረከቦት ላይ ከሚደረደሩ ስኒዎች መካከል መርጠው ለራሳቸው የሰየሟት ሸራፋ ስኒ ነበረቻቸው። ሰርኬ ተሳስታ በሌላ ስኒ የሰጠቻቸው እንደሆነ “በራሴ ፍንጃል ካልሆነ ባልጠጣ ይሻለኛል” ብለው ይመልሳሉ።

“እንዴት ዋላችሁ?” አሉ እማማ አስረበብ/እትዬ አልታዬ። እጃቸው በጸጉሬ ተቦርሾ ተነሳ። ዓይናቸው ደከም ስላለ አግዳሚ ወንበሩን በዳበሳ አግኝተው ቁጭ አሉ። በላይነሽ አጠገባቸው ተቀመጠች።

“እንዴት ዋላችሁ? እህትሽ የለችም እንዴ በላይ?”

“አሁንማ የት ትሄዳለች ብለሽ ነው። ጦቢያ እንደሆነች አባራታለች። አብሽሎ፟ እየጋገረች ነው። ሳለ ጉልበቷ ሰርታ ትበላለች። ግርድና ነው ያስቀረችላት። እኔምኮ እማማ አስረበብ ጠርተውኝ አቋርጬ እንጂ የማክሰኞ ጠላ መች ፋታ ይሰጣል። ትመጣለች አሁን ወዲህ ስናልፍ ጠርቻታለሁ”

“እኔማ ያው የመባቻ ቡና ሰው ሲጎድል አልወድም። ደሞ ለወሩ አድርሳን። እንዲችው ሳንጎድል ደሞ ለወሩ ታድርሰን ብለን መለያየት ነው እንጂ”

“ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ” አሉ እማማ አስረበብ። የማይጨርሷት ተረታቸው ነች። “የዛሬ ወርማ ግንቦት ልደታ ናት። መንደሩ ሁሉ ተሰብስቦ ነው …”

“አይ … እንዴት ረሳኋት እናንተ … ያቺን ተናኘን ሳልጠራት”

“ተናኘ የትኛዋ?” በላይነሽ ግንባሯን ከስክሳ።

“እህ … ይቺ ተናኘ ናታ። የሳራ እናት”

“እኮ ተናኘ ይህደጎ?”

“አሁን ለታ ገነቴ ገበያ አግኝቻት ‘እንደው እንዳንቺ ያለ ቡና ቀምሼም አላውቅ። በዓመት አንዴ ግንቦት ልደታን እየጠበቅኩ ያንቺን እጠጣለሁ እንጂ ሌላ ቡና በአፌም አይዞር ዓመት ሙሉ። ምናል አንዳንዴ እንኳ ብትጠሪኝ ስትለኝ እንደው አንጀቴን በላችው”

“ትዝ ቢልሽ ኖሮ ልትጠሪያት ኖሯል?” በላይነሽ

“መቸም ወላድ ቀልብ የለውምና ዘነጋኋት እንጂ እንዴት አልጠራት?”

“ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ። ደሞ ከመቸ ጀምሮ ነው ከሴተኛ አዳሪ ጋር ተርቲበኛ የሆንሽው?” አፋቸውን አሽሟጠጡ። በላይነሽ ሂጂልኝ እንደማለት አይነት እጇን አራገበች።

“እማማ አስረበብ ደግሞ …” ሰርኬ የእጣን ዕቃውን ከፍታ በሦስት ጣቶቿ ዘግና እጇን ሰነዘረችና ማጨሻው ላይ አስቀመጠች። ከጋቻው ላይ ጥቁር እንፋሎት በእርጋታ መነሳት ጀመረ።

“እሱን ከተወች ስንት ዘበን ሆናት?”

“እሷ ተውኩ ትላለች እንጂ ሰፈርተኛው ሌላ ሌላ ነው የሚለው”

“የገነቴ ሰውማ ያወራል። ምን አለ ደሞ?”

“ሰውማ ምን ይላል? ይቺን አባቷ የማይታወቅ ልጇን እየጎተተች፣ ጌጥ ይመስላታል እንዴ እላለሁ እኔማ ሳያት … በየላጤው ቤት አይደል እንዴ አንሶላ ስትጋፈፍ የምትገኘው? እኔማ እንደው ይቺን ልጅ ገና ቂጧን እንኳ ሳትጠርግ የማይሆን ነገር አስተማረቻት እላለሁ፤ ምነው በእንቁላሌ በቀጣሽኝ ብላ እንዳትተርት እንኳ እንቁላሉንም እሷው ናት የሰጠቻት”

“ደሞ ይሄን አሉ?” አለች ሰርኬ ጀበናውን እያወረደች።

“እኔኮ ያንቺ ጋሻ ጃግሬ መሆን ነው የሚገርመኝ። ቆይ እንደው ሴተኛ አዳሪነቱን ተውኩ ብትልስ ቤቷ ውስጥ ስንትና ስንት ኮማሪት ቀጥራ እያሰራች እሷ ልትተወው ነው? ደሞ ልማድ መቸም አይለቅ” አለች በላይነሽ።

“አይ … አሁን ገና የማይጥም ነገር አወራሽ በላይ። እኔ መቸም ያለፈ አልፏል ነው የምለው። ማርያም ይቺ የመቅደላዋን አይደለም ወይ ጌታችን እንኳ ይቅር ያላት? ስንት ዘመን በግልሙትና ኖራም አይደል እግሩ ሥር ተደፍታ በእንባዋ ብታጥበው ያለፈ ታሪክሽን አልቆጥርብሽም ብሎ ነጣ ያወጣት መድኃኔአለም? እኛም ያው ያዳም ዘር ነን። ማንም ሰሃ የሌለበት አይገኝ። ደሞ ዓይናችን ውስጥ ምሰሶ አጋድመን በሌላው ሰው ዓይን ውስጥ ባለች ይቺን የምታክል ጉድፍ መዘባበት ለሰሚም ደስ አይል”

የማርያም ጣቷን በአውራ ጣቷ እየጫረች የተናገረቻት ይቺ የመጨረሻዋ አባባል ግቧን መታች። ከዚህ በኋላ የኬጃ ሚስት፣ የበላይነሽ እህት፣ ተናኘ ከነልጇ፤ እታለም ሉሉ፤ የእታለም ሉሉ የመጨረሻ ልጅ መጥተው ሲሄዱ ሁሉ በላይነሽ አንድ ቃል አልተናገረችም።

እትዬ አልታዬ ብቻ “ህም … ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ” አሉ።

እናቴ ከፈንድሻው ዘግና ወደ በሩ አቅጣጫ የተነሰነሰው ቅጠል ላይ እየበተነች “ለቆሌዋ” አለች። ከዚያ ወደ እኔ ዞራ “እስቲ ና አስዘግናቸው” አለች።

ቆለምሽሹን አንስቼ ሴቶቹ ፊት ቆምኩ። “ሴት ሆኖልሽ ቢሆን ሸጋ ነበር” አሉ እማማ አስረበብ ከፈንድሻው ዘግነው መቀነታቸው ላይ እያስቀመጡ። ሁሌ የሚያናድደኝ አባባላቸው ነው።

“ኧረ ወዲያ፤ ደሞ ሴት ልጅ ብሎ ነገር። ፋፎ ቆሎውን በደንብ ዝገኑ እንጂ እማማ አስረበብ፣ እንኳንም ወንድ ሆነልኝ፤ ጣጣዋ ብዙ ነው ሴት” አለች ሰርኬ።

እማማ አስረበብ ሊናገሩ አፋቸውን ከፈት ሲያደርጉ “ሠላም ለዚህ ቤት” ብላ ገባች የኬጃ ሚስት።

“እንዴት ዋልሽ የኬጃ ሚስት፤ ደርሰሻል ዛሬስ አቦሉ ላይ። በይ ያዥ በቁምሽ የቡና ቁርሱን፤ ጠመዥ ትወጂ የለ? ላንቺ ነው የቆላሁት”

“እሰይ ሰርክዬ ደሞ ወዙ ማማሩ” ሁለቱ ሴቶች ፊት ለፊት ግራ እጇን ተመርኩዛ በርጩማ ላይ እየተቀመጠች በቀኝ እጇ ዘገነችና ተቀምጣ ሳትጨርስ መቆርጠም ጀመረች። “አቤት አቤት እንደው እንዴት አድርገሽ ብትቆዪው ነው ልጄ እንደ እንትንኮ ነው ፍርኩት ፍርኩት ሲል ቆሎም አይመስል”

“ምን ታረጊዋለሽ፤ ከትከሻዬ ነው እንግዲህ” አለች ሰርኬ

ከበላይነሽ በቀር ሁሉም ሳቁ።

አንዱን (ሰው) ሲያነሱ ሌላውን ሲጥሉ ቶናውን ጠጥተው ጨረሱ። ጭሱ እየደከመ ጨዋታቸው እየሞቀ ሄደ።

ለሦስተኛ ጊዜ ቀድታ ጀበናውን ከማስቀመጧ እታለም ሉሉ መጣች። ከበርካታ ልጆቿ መሀል በላይ የሚባለው በእድሜ እኩያዬ ስለሆነ ጓደኞች ነገር ነን። ለቡና ስትመጣ የምትይዘውን እንዝርት አልያዘችም። እጁን ይዛ በቀስታ እየጎተተች የምታስከትለው ዳዴ ዘለል ልጇም የለም። ገና እንደገባች ደህና ዋላችሁም ሳትል በረጅሙ ተነፈሰችና፣

“እንደው ድካም ድካም እያለኝ ነው ሰሞኑን …” ብላ በላይነሽ ጎን ተቀመጠች።

“አይ አንበሲት፤ ደሞ ቋጠርሽ እንዴ? መቸም አንቺ ሽለ ሙቅ ነሽኮ” አለች ሰርኬ የእታለምን ሆድ እያየች። ወዲያው ደሞ ከተቀመጠችበት ወደ ቀኝ ጋደል ብላ ወደ በሩ እያየች ተጣራች “ተናኘ! ተናኘ!”

“ልጅ መቸስ ሀብት ነው …” ብላ በረጅሙ ሳቀች እታለም።

“ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ” አሉ እማማ አስረበብ። ይሄ መልሳቸው ለሰርኬ ይሁን ለእታለም አልገባኝም።

እታለም አሳኢታ የሚባል አገር ስለሚኖር ልጇ ማውራት ጀምራ ሌሎች ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ልጆቿን መዘርዘር ጀመረች። እያንዳንዱን ልጇን በስም እየጠቀሰች እድሜውን፣ ሥራውን፣ የሚኖርበትን አገር ስትዘረዝር ተናኘ ከነ ልጇ ገብታ ኬጃ ሚስት አጠገብ እስክትቀመጥ፣ በረካው ተቀድቶ እስኪሰጣቸው፤ ሰርኬ ማጨሻው ላይ እጣን ጨምራ ቤቱ ከእንደገና እስኪታፈን፣ ተናኘና ሳራ ከቡና ቁርሱ እስኪዘግኑ ድረስ እንኳ አልጨረሰችም። ተመስጣ በምታደርገው ንግግር መሀል በቀኝ እጇ የያዘችውን ቡና ቀመሰችና ሬት የለበሰ የጡት ጫፍ ምላሱ ላይ እንዳረፈበት ሕፃን ፊቷን አጨማድዳ ስኒውን ለመመለስ እጇን ወደ ሰርኬ እየዘረጋች።

“ምነው ስታውቂው፤ ቡና በአሻቦ ነው የምጠጣው። ለምን በስኳር ሰጠሸኝ?” አለች

“ውይ … አፈር በበላሁ … አምጭው አምጭው” ብላ ተቀበለቻት ሰርኬ።

እማማ አስረበብ የተናኘ መምጣት ምቾት ነስቷቸው ዝም ብለዋል። በላይነሽ በፊትም ቀንዷን ተብላ በጥልቅ ጸጥታ ተቀምጣለች። የኬጃ ሚስት ጠመዥ ትፈጫለች። እታለም ቡናዋ በጨው እስኪቀርብላት ትጠብቃለች። ሰርኬ ቡና ታማስላለች። እንዲህ ሲሆን ለአንድ ደቂቃ ለሚሆን ያክል ጊዜ ሁሉም ነገር ዝም አለ።

ልክ በዚህ ጊዜ ነበር የእታለም ሉሉ ትንሹ ልጅ፤ ይሄ ወፌቆመቹን አጠናቅቆ ደንበኛ እርምጃ መራመድ ከጀመረ አንድ ሳምንት ያላለፈው ባለ ቁንጮ፤ በእጁ ፌስታል አንጠልጥሎ የገባው። ፌስታሉ ውስጥ እንዝርትና ጥጥ አለ። ለመጫወቻ እንዲሆነው ደመና ቋጥሮ የመጣ ይመስል ይዞ የመጣውን እቃ ለእናቱ ማድረሱን ትቶ ልክ ሲገባ ፊት ለፊቱ ያየውን ረከቦቱ አጠገብ ያለውን የቡና ቁርስ ሊቀምስ ግራና ቀኝ ሳይገላምጥ ቀጥ ብሎ ገባ። ቆለምሽሹ አጠገብ ደርሶ የቡና ቁርሱ አጠገብ ሊቀመጥ እያጎነበሰ መሀል መንገድ ላይ ሲደርስ የተናኘ ልጅ ሳራ አንድ ዐረፍተ ነገር ተናገረች። ሰዋሰውን የጠበቀ። ባለቤት ተሳቢና ግስ ያለው። በዘይቤ የታሸ። ሰሚን በማሳፈር የሰለጠነ አንድ ቀላል ዐረፍተ ነገር፣

“ሰተት ብሎ ገባ እንደ ቁላ”።

ይህቺ ልጅ የስንዝሮና የቢልጮን ተረቶች እየሰማች አላደገችምና አይፈረድባትም። እሹሩሩዋ የተሰራው እናትህ ከገበያ ስትመጣ ይሄንና ያን ታመጣልሃለች ከሚባል መሸንገያ አልነበረምና ማንም አይከፋባትም። ምናልባትም “እናትሸ ስትመጣ …” እያለች ያባበለቻት ለሃያ አንድ ፈሪ የሆነች ኮረዳ እሷም እናቷ መጥተው እንዲያፅናኗት የምትመኝ ነበረች ይሆናል። ይህቺ ሳራ የእናቷ ቅጥረኛ ኮማሪቶች ትናንትና ማታ የገጠማቸው ወንድ እንዴት እንዴት እንዳደረጋቸው በትናንሽ ጆሮዎቿ እየሰማች አደገች እንጂ የቅጥራን ፏፏቴ የመሰለ ጸጉሯን እየደባበሰ ሞራል የሚሰብክ ትርክት የሚነግራት አባት አልነበራትም። ለዚህም በእናቷ አባት ስም ሳራ ይህደጎ ተብላ የምትጠራ ይቺ ወንድም አልባ፣ እህተ ቢስ ልጅ እንካ ስላንቲያን ዘልላ፣ እንቆቅልሽ ምን አውቀልሽን ሳትነካ፣ “ተረት ተረት የላም በረት ሆድሽ ተተርትሮ ተይዟል በብረት” ብላ ተረት ለመስማት የጓጓች ታናሿን ሳትሸውድ፣ እንዲህ ሳታደርግና እንዲያ ሳይሆን በፊት “የአፍሽ የቂጥሽ ወሬ” የለመደች ነበረች።

ረፋዱ ላይ የእናቷ ሠራተኞች የምሽት ውርጭ የገረፈው ፊታቸው ገርጥቶ፣ ታችኛው የዓይናቸው ቆብ ፊታቸው ላይ ማህደረ ቆለጥ መስሎ ተንጠልጥሎ፣ ሲመቱ በጮሁበት፣ ሲረገጡ ባላዘኑበት፣ ሲጠለዙ ባቃሰቱበት በዚያ በጩኸት በሰለለ ድምጻቸው ተተርከው የልጅነት ስስ ታምቡሯ ላይ እንደ ዘላቂ ኩክ የተለሰኑት “ማታ ያጋጠመኝ ሰውዬ ደሞ …” ብለው የሚጀምሩ ጨዋታዎች ነበሩ። ማንም ይህን አያምንም እንጂ ሳራ ይህደጎ ለመጫወቻ አንዲሆናት ኮንዶም እንደ ፊኛ እየተነፋ የሚሰጣት ልጅ ነበረች። ሳራ እንዲህ ስላደገች ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስታውሳት እረዳታለሁ። ያኔ በአምስት ቃላት የመሰረተችው ዐረፍተ ነገር ግን “ሰተት” የሚለውን ቃል በሰማሁ ቁጥር ትዝ ይለኛል።

ያኔ በንፅፅር የተቀመጠው ነገር የገባው ወዴት እንደሆነ ባላውቅም ልክ ተናግራ ስትጨርስ እናቷ ተናኘ በሀፍረት ተነስታ ፊቷን ስታጮላት፣ በእኩል ሰዓትም እማማ አስረበብ ጮክ ብለው “ከሤራ ዲና” ሲሉ፣ በዚያችው ደቂቃ በላይነሽም አፏን አፍና ስትሥቅ፣ በዚያችው ሴኮንድ ልጇ ያመጣውን ባዘቶ ልትቀበል የተነሳቸው እታለም መሀል መንገድ ላይ ቆም ብላ ወደ ሳራ ስትገላመጥ፣ በዚያችው ቅጽበት ሰርኬ ወደ እኔ ዐየት አድርግ “በቃ ጆሮህ እዚህ ነው አይደል፤ አያነበውምኮ ወረቀቱን ለላንቲካ ነው ፊቱ የዘረጋው” ስትል፣ እኔ በጣቁሳ ለተወለዱ ቅኔ ምናቸው ነው/ የማሽላ ቂጣን በኑግ ይጉመዱ እንጂ እያልኩ የኑግ ልጥልጤን እያልጎጠጎጥኩ ለይስሙላ የዘረጋሁት የአማርኛ ትምህርት መጽሐፌ ውስጥ ተደበቅኩ። (በዘይቤ ከታሸ ከዚህ ዐረፍተ ነገር ወዲያ አማርኛ ትምህርት አለ?) አፍሬ የሰቀልኩት ቅንድቤ ያለ ምንም ማጋነን እስካሁን ወደ ቦታው አልተመለሰም፤ የፈጠጠው ዓይኔ እስካሁን አልሟሸሸም። ጭራሽ “ሰርኬን ነውኮ የሚመስለው እስቲ እዩት ዓይኑን፤ ዛጎል የመሰለ” እየተባልኩበት።

.

ፍቅር

ከዚህ አጋጣሚ በላይ የሚያሳፍረኝ ሌላ አጋጣሚም ነበረ።

“ጸሎት ያለ ፍቅር ሰውን አያጸድቀውም ሲልሽ ይሄ ዲያቢሎስ ያቀማቀመው ጠምጣሚ እውነት መሰለሽ?” አባቴ ይሄን በጩኸት ሲናገር እናቴ ካቀረቀረችበት ቀና አለች። ይሄንን አባባል ማወቁ አስገርሟታል። አሁን አሁን ሳስበው ይሄን ማወቁ ለእኔም ይገርመኛል። እንኳን ሰው ፊት በኀይለ ቃል ሊናገራት ብቻቸውን ሲሆኑ እንኳን የጎደለው ነገር እንዲሟላ ሲጠይቅ እያሳሳቀ፤ በጨዋታ እያደረገ ነበርና በጩኸት መናገሩ ብቻ አስፈርቶኛል።

ትዝ ይለኛል ቅዳሜ ቀን ነው። አባቴ ከእናቴ ጋር ተጋጭቶ ከቤት ከወጣ ሁለት ሳምንት ሆኖት ነበር። አባቴና እናቴ ተፋትተው የተጣሉበትን ምክንያት የሰፈር ሰው እኔ እንድሰማው አድርጎ በአብሻቂ ሹክሹክታ ሲያወራ እንደሰማሰሁትና በኋላ አባቴ ነፍስ ሳውቅ እንደነገረኝ እናቴ ይናፋ፟/ኢናፋ ስለተያዘች ነው፡፡፟

ደባሪ የሂሳብ ትምህርት ሜክ አፕ ክላስ ጨርሼ ቤት ስገባ አባትና እናቴ ሽማግሌዎች መሀል ተቀምጠዋል። ዳውድ ምናምን። አባ ገብረ ኪዳንና ሌላም ቄስ ነበሩ። ሌላኛው ቄስ የአባ ገብረ ኪዳን የንሰሐ አባት ይሆኑ ይሆናል፤ ለእኛ ደግሞ የንሰሐ አያታችን ናቸው ማለት ነው?

አባቴ ዓይኑ ቀልቶ ነጎድጓድ ድምፁ በንዴት እየተንቀጠቀጠ ይናገራል፣

“አመንሽው ሰርካለም? አይደለም በሁለት በሠላሳ ቋንቋ ቢያወሩ እንኳን ለደብተራ ሤራ ለጳጳሱ ግዝት የምትበገሪ አይመስለኝም ነበር። አመንሺው ይሄን ዘኬ ለቃሚ? አመንሺው ሰርኬ? ይሄን ዛር አንጋሽ አመንሺው? አመንሺው?!”

ሰርኬ ከተቀመጠችበት ተነስታ ሰዎች መሀል መሬት ላይ ተደፍታ ማልቀስ ጀመረች። ምን እየተደረገ እንደሆነ እንኳ ሳይገባኝ ገና በር ላይ ሆኜ እንባዬ ይወርዳል። የናፈቀኝ አባቴን እንኳ አቅፌ ለመሳም አልቻልኩም።  ሰርኬ ጸሎት እንደሚያደርግ ሰው እጇን ወደ ላይ እየዘረጋች በሳግ የተዋጠ ለመስማት የሚያስቸግር የሆነ ነገር ትናገርና መልሳ ትደፋለች።

“አንድኛሽን ለምን እንደ ኀምሳ አለቃ ይህደጎ ልጅ መሸታ ቤት አትከፍቺም?…”

የሽማግሌዎች ምክር ጣልቃ ገባ።

“ተው እንጂ ወልደ መስቀል እንደዛ አይባልም ተው …”

“ምንስ ቢሆን የልጆችህ እናት አይደለች፣ ተው እንጂ …”

ድምፁን ጨምሮ ቀጠለ።

“…አዎ! ‘ለሰው ፍቅር መስጠት ደግ ነው፤ ቡና ሳፈላ አንዳንዴ ብጠራት ምን ችግር አለው’ ስትዪ አልነበረም? ጥሩ ነው። ጠጡ! ፍቅር ስጫት፤ አሰጣጥ ታስተምርሻለች። አየሽ ቢያንስ ሀብታም ትሆኚበታለሽ …”

ድምፁ እየጨመረ መጣ። የሚናገረው እያንዳንዱ ቃል ሲሰብራት ይታየኛል። ዐረፍተ ነገር ሲጨርስ እንደተጎሸመች ሁሉ ታቃስታለች። ሰዎቹ አቀርቅረዋል።

“ተው እንጂ አወል፤ ሁለት ሳምንት ሙሉ ስንት ነገር ስንነጋገር ከርመን እንደገና ወደ ኋላ ትመለሳለህ? … ስንት ነገር አጫውቼህ … ትዳር ውስጥ ስንቱን ችሎ ነው …” አለ ዳውድ ቀና ብሎ አባቴን እያየ።

ከተቀመጠበት ተነስቶ እኔ ወዳለሁበት ወደ በሩ አቅጣጫ መጣ። እንደዚህ ረጅም ጊዜ ጠፍቶ መጥቶ ሊያቅፈኝ ይቅርና አጠገቡ መቆሜን ልብ ሳይል ወጥቶ ሄደ። ከኋላው የቀሳውስት ግዝትና የሰርኬ ሳግ የለበሰ ልመና ተከተሉት።

ይህ ከሆነ በኋላ፤ ይሄው አባ ገብረ ኪዳን የተባሉ መዘዘኛ ቄስ ጉሮሯቸውን ስለው፤ ልክ በድርጊቱ ተከፋይ እንዳልሆኑ፤ ልክ ለማስታረቅ ብቻ እንደመጣ ሽማግሌ ሆነው ራሳቸውን ነፃ የሚያወጣ አንድ ጥቅስ ተናገሩ፣

እግዚአብሔርወሀበወእግዚአብሔርነሥአ

በቃ … ቄስና ግዕዝ ጠላሁ።

.

ሙሉጌታ አለባቸው

2009 ዓ.ም

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “መሐረቤን ያያችሁ”። ፳፻፱። ገጽ 56-73።

“ፍቅር እና ሆሄ” (ልብወለድ)

“ፍቅር እና ሆሄ”

በአዳም ረታ

.

[ይሄ ጽሑፍ በ1999 ዓ.ም አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች (በመስፋቱም ጭምር) በመጀመሪያ ንድፍ ላይ ከደረሰ ‘ፍቅርና ሆሄ’ ከተባለ ግን ሳይታተም ከቀረ የ2500 ገጽ ልብወለድ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ነው። ጽሑፉ የተቆረሰው አርባ ገጾች አካባቢ ብዛት ካለው ‘ዑር እናት’ ከተባለ የመጽሐፉ መግቢያ ምዕራፍ ነው።]

.

Adam Inside Photo

.

(አገሪቱ በፀሐይ ሙቀት ለነደደች ጊዜ፣ በከተማውና በከተማው ዙሪያ ያሉ ባሕር ዛፎች በጠል መጥፋት ቢጫ ለነበሩ ጊዜ፣ የሚቀመስ እህል ጠፍቶ ለነበረ ጊዜ፣ በተለይ የአገሪቷ ተወዳጅ ምግብ ዱባ የተባለው ፍሬ ዘር ማንዘሩ ለጠፋ ጊዜ፣ ብቻ ከዛሬ ልጅ ለነበረ ጊዜ ……… አያቱ እናኑ የተመቻቸው ቦታ ተቀምጠው ሲያያቸው ገላው ለመታቀፍ ይቁነጠነጥ ነበር። እቅፋቸው ውስጥ በረዶ በመሰለ ጋቢያቸው ሲጠቀለል የሚያደርገው ዓይኖቹን ጨፍኖ ለማይቆም ጊዜ መተኛት ነው። ‘እናና!’ ብሎ ሲጠራቸው ለሌሎች ሰዎች ጎምዛዛ የሚሆኑት ሴትዮ እንደ አበባ ይከፈታሉ። ጉንጭና አፉን ሲስሙ ሁለመናቸው ወተት ይሆናል። አንዳንዴም አላዛር እንደሚወደው ጋቢያቸውን ድንኳን አስመስለው በላያቸው ላይ ይዘረጉና እንደ ልጅ ይላፉታል ……… ከረሜላ ይወዱ ነበር። ሲያውቃቸው ጀምሮ ከአፋቸው የማይጠፋው ከረሜላ ነበር። የሳምንቱን ቅዳሜ ጠብቆ አባቱ በሚሰጠው ገንዘብ ብዙ ማር ከረሜላና ደስታ ከረሜላ ገዝቶላቸው ይሄዳል። ለእሱ የሚፈልገውን በሱሪ ኪሱ፣ ለእሳቸው የመደበውን ደሞ በእጁ ጨብጦ ይቀርባቸውና ‘ትልቋ እማማ ከረሜላ አመጣሁልሽ’ ይላቸዋል። ከረሜላ የያዘበት እጁን በሁለት እጆቻቸው ያቅፉና በምራቃቸው ረጥቦ እስኪያብረቀርቅ ቡጢውን ይስሙለታል።)

… ለምን ትልቅዋ አያቴ ትለኛለህ? ማን አስተማረህ? እኔ ተአያትህ ተሰብለ ብዙ አላረጅም እኮ … ግን ኑሮ ቀደም ብሎ በጥቁር እጁ ሲነካኝ ምን ይሁን? ነካ ነካ ያደርግሃል ኑሮ። ይነጅስሃል። እስዋ የፊታውራሪ ልጅ ነበረች። እኔ በጉዲፈቻ ሞጆ ያደግሁ አባትና እናቴ በስልቱ የማይታወቁ። በእናትህ በኩል ቅድመ አያትህ ፊታውራሪ መሸሻ የሚባሉ የጎጃም ሰው ስማቸው የተጠራ ነበሩ በዋላ ስሰማ። ሰብለ ዲማ ነው እንግዲህ የወለደችው። ለአቅመ ሔዋን የደረሰችው እዛ ነው። የሚገርም ታሪክ ነበራት በዋላ ስትነግረኝ … እሱማ ሰሚ ካገኘ የማንም ታሪክ አይገርምም? እንደው እየመረጥነ እንጂ። ሀሁ ተሚያስተምራት ዲያቆን ይሁን ደብተራ የትኛው እንደሆነ እንጃ በዛብህ ተሚባል ጎረምሳ … ጎረምሳ ነው … ፍቅር ይይዛታል። አባትዋ ሲቀብጡና ሲኮሩ ባል ሲመርጡ ትልቅ እስትትሆን ቤት ዘግተውባት ይኖራሉ … እና አልኩህ እንዳለችኝ ይሄ በዛብህን ወደደች። ታዲያ ያኔ እንደ ዛሬ ዘመን ማንም ከማንም አይጋባም። ዘር አለ ምን አለ … ጦረኛ የጦረኛ ልጅ ነው የሚያገባ … ባለመሬት ባለመሬትን። ፍቅር ማን ያውቃል? ፍቅር አብረው ሲኖሩ ነው … እስቲ አትደብቀኝ አላዘር ዓለምዬ እንደው ያቺ የጎረቤታችሁ ልጅ ማን ነበር ስምዋ? እ? …

(ሊመልስላት አልፈለገም። ገና ቅልስልስነቱን ባልጨረሰ ልጅነቱ ጊዜ ለምን እንዲህ እንደምትጠይቀው ግራ ይገባዋል። እየሳቀች በአፏ ከተባረኪ ጋር ባልና ሚስት ስታጫውተው ትወዳለች። እየተሽኮረመመ አያት። አታየውም። ሊመልስላት አልፈለገም። ድምፁ ውስጥ የመሽኮርመም ዜማ እንዲሰማበት አልፈለገም። ወደ እሱ ያዞረችው ፊቷ ሳያቋርጥ ያሳዝነዋል። ልመልስላት አልመልስላት ሲያስብ …)

ተባረኪ? ወይ ስም እቴ አይ የስም ማማር … ለመሆኑ አባትዋ ይመጣል? … አይመጣም … አይ እቴ ያልሸገረኝን። እና ሰብለ ዲያቆን ለምዳ በዋላ መሰማቱ ይቀራል እግዜር ሲያቅደው። አባት ‘ካልገደልኩት ይሄን ቅማላም ደሃ’ ሲሉ ይፈራና ነፍሱን ሊያድን አምልጦ ወደ ሸዋ ይመጣል። መሄዱን ስትሰማ እስዋ ተከትላ እግሬ አውጭኝ … ወደ ሸዋ እግሩን ተከትላ። መንገድ ላይ ሽፍቶች ደብድበውት … መቼም የሰማሁትን መደበቅ ምን ያደርግልኛል? … ብዙ ነበር የምትለው ሊሞት ሲል የባላገር ቤት አርፎ በጠና ቆስሎ ትደርሳለች። ግጥጥሙ አይገርምም? ምን ይደረጋል እግዜር ያቀደውን … አይታገሉት። ክንድዋ ላይ ደም መቶት ይሞታል። አያሳዝንም? እንዲህ ስታወራኝ በጉንጭዋ ዕንባ እየወረደ። የሰማት ሁሉ ነው የሚያለቅስ … እስቲ ያን ውሃ አቀብለኝ … ያቺ ልጅ አልመጣችም? መድሃኒቴን የት ነው ያስቀመጠችው? ጊዜው ተላለፈ እኮ። ሰዓት ስንት ሆነ? አምስት? ያ አባትህ እኮ ገና በልጅነትህ ሰዓት መስጠቱ ለእኔ ሳይጠቅመኝ አልቀረም። ለመሆኑ አያድርግና ስትጫወት ብትሰብረውስ? እ? አምስት አልከኝ? አንድ ሰዓት አለኝ። አምስት ተሩብ? ያው ነው … ስለ አያትህ ስለ ሰብለ ልቀጥልልህ። ሰብለ መሸሻ። የእኔ እህት… የእኔ እመቤት። አራዳው ካገኘሁዋት ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀን አለቀሰች። ተዚያ ተሁለት ሰንበት በዋላ ተሻላት። መብላት ጀመረች መጠጣት ጀመረች። አልፎ አልፎ እንደው ቢደብታትም። እኔ ምን ነበረኝ ያኔ? ምንም። ሴት ነኝ የሁለታችንንም ሆድ መሙላት አልችል። በደህናው ጊዜማ የንግሥት ጣይቱ ወጥ ቤት ነበርኩ። አይ ጣይቱ እናቴ። አንቺም አፈር ይበላሻል። ንግሥት ገና ጠዋት ብቅ ሲሉ ‘የት ናት እናኑ? የእኔ ጎራዳ’ ይላሉ። ‘ያቺ አገጫም የታለች?’ እንደ እኔ ጎረድረድ ያሉ ሴትዩ ነበሩ። ‘ለእሳቸው’ ለሚኒሊክ ማለታቸው ነው ‘ቁርሳቸውን አድርሺ መመለሻቸው ነው’ ይሉኛል። ሁልጊዜ ፊቴን ያዩና ወደ ማታ ተሆነ ‘ደክሞሻል?’ ይሉኛል። አልደከመኝም ካልኳቸው ‘በይ ትንሽ ንፍሮ ቢጤ ይዘሽለኝ ነይ ተብርዝ ጋር’ ይሉኛል። እመቤት እኮ ናቸው። ምላሳቸው ግን አይጣል ነው ተከፉ። መኝታ ቤታቸው ይዤላቸው እሄዳለሁ … ንፍሮውን በቁልቢጥ ብርዙንም በቀንድ አድርጌ። ገና እሱን መሬት እንዳስቀመጥኩ ይጠቅሱኝና ጋቢያቸውን ወረድ ያደርጋሉ። ድንቡሽ ያሉ ናቸው። ተዛ ጀርባቸውን አክላቸዋለሁ። … ምግብ አቅራቢያቸውና አካኪያቸው ነበርኩ። አንገታችው ትዝ ትለኛለች። አንገታቸው በመወፈራቸው የተጣጠፈች ሥጋ ነበረች። ‘ማከኩን ተወት አድርጊና እሱን እሺኝ ሳይጣምነኝ አልቀረም’ ይሉና እሱን ሳሽላቸው በቀስታ ያንጎራጉራሉ። ‘ልጅ እያለሁ እዘፍነው ነበር’ ይሉኛል። ወረሂመኑ ለነበሩ ጊዜ … ለመሆኑ ወረሂመኑ የሚባል ቦታ ሰምተሃል?

(አልመለሰላትም። እንደሚያይ ሁሉ ወደ ተቀመጠበት ዞር ትልና ‘ታየዋለች’ … ወደ ተጋደመችበት ሄዶ ከአፏ ዳርና ዳር ቆበር በኩታዋ ጠርጎ ያነሳላታል … አሁንም አሁንም)

አላልኩም አላልኩም አገራችሁን ትንቁዋታላችሁ እንጂ የት ታውቁዋታላችሁ። ወረሂመኑን የመሰለ አገር አታውቅም … አውሮባ ምናምን ቢሏቸሁ ይሄኔ ታታታታ ታደርጋላችሁ። የዚህን የጣይቱን ነገር ለአንተ ብቻ ነው የምነግርህ። ወሬ ምን ይታወቃል ማን ጋ እንደሚደርስ። እስተ ዛሬ ንጉሡ እኮ አለቀቁኝም። ንግሥት ጣይቱ ጀርባቸውን ያሳክኩ ነበር ተብሎ ቢጣፍስ? ሁሉ በየቤትዋ ታሳክካለች እኮ። ተፈሪ ጣይቱን ያሸነፋቸው እኮ ስም በማጥፋት ነው። እንደ ወንድ መቸ ችሎበት። ወንድ ቢሆን ኖሮ እዝህ ለሰላቶ ለፋሺስት ትቶን ይሄድ ነበር? ወንድ ሆኖ ክንድ የለውም። ክንድ ተፈረንጅ ሊበደር ይሄዳል። ለአንተ ብቻ ነው የምነግርህ። ጣይቱ አምባላጌ ሲያዋጉ ባዶ እግራቸውን ወንዶች ፊት ፊት ሲሮጡ ተሩቅ ጥልያን አይቶ መትረየስ ቢያዘንብባቸው ይህቺ የግራ እግራቸው ትንሽ ጣት ተቆረጠች። በቃ የለችም። አራት ጣት ነው ያላቸው። አንድ ጎበዝ እላያቸው ላይ ወድቆ ነው ያዳናቸው። ጎናቸውን ደሞ ሲወድቁ ጫንቃቸው ላይ የተሸከሙት የዓላማ ሰንደቅ ወግቶአቸው አሁን ድረስ እስቲሞቱ ያማቸው ነበር። እዚህ ከብብታችው ዝቅ ብሎ። ገና ብርድ ሲሆን ውሃ አሙቄ ጨርቅ ይዤ ማደሪያቸው እሄዳለሁ። አንዳንዴ ‘እሱን ተይ’ ይሉኝና በጋቢ ተከናንበው ይቀመጡና እኔም ተከናንቤ አቅፋቸዋለሁ። ‘የሰው ሙቀት ይሻላል’ ይላሉ። ምን ላይ ነበርኩ ዓለምዬ? … አድዋ ዘመቻ ጊዜ ከተማ ጠባቂና ፀሎተኛ ነበርኩ። በቀን ሶስቴ እንፀልያለን። አሸነፍን ሲባል ልጄ ተንጦጦ ባቡር ጣቢያ በእልልታ ቀለጠ። ዛፍ ተቃጠለ። ደን አለቀ ልበልህ። ምን ላይ ነበርኩ ዓለምዬ?…

(እምን ላይ እንዳቆመች ሊነግራት አልፈለገም። በዝምታ በተመስጦ ግርማው ያልጠፋ ረዥም ፊቷን ማየት ብቻ ነው የሚፈልገው። ጨዋታዋን ያቆመችበት ጠፍቷት “በል ሂድልኝ የሚቀጥለው ሳምንት ና” ብትለውም ይወዳል። የቆመችበት እንደጠፋው ሁሉ ዝም አላት)

… አዎ የጀመርኩልህ? ምን ነበር? አዎ። ስለ ዱባ ወጥ። ስለ መሐሌ ወለላ። ሚኒሊክ አያውቁም። ንግሥትነታቸውን እስቲነጠቁ ድረስ እስከ ሺህ አስር እስከ ሺህ ዘጠኝ መቶ አስር ድረስ ዱባ ወጥ ለጣይቱ መስራቴን ወጥ ቤት እንኳን አያውቅም። አየህ አላዛር ሞጆ በነበርኩ ጊዜ እንዲህ ሆነ። እረሳለሁ እንጂ የማይረሳ እረሳለሁ። የማይረሳ። ነሲቡ አሳዳጊዬ ሞተው እሳቸውን ቀብሬ ስመለስ ደብረዘይት ቢሾፍቱ ከመድረሴ በፊት ዝናብ ጣለ። የሚገርም የሚገርም ዝናብ። ምን? በለኝ። ምን? በለኝ። የተሰባበረ ዱባና የዱባ ዘር። እንደውልህ ከሰማይ እየመጣ የተፈናጠጥናቸው ከብቶች ላይ አናታችን ላይ አይለጠፍብን። ቀና ብዬ ሳይ ወርቅ የመሰለ ቢጫቴ ደመና። የዛ ዓይነት ደመና አይቼ አላውቅ ከተወለድኩ። ‘ሚካኤል ከዚህ ካወጣኸን በየወሩ ጠበል አደርግለሃለሁ’ አልኩት። ቁጥቁዋጦ ግራር ነገር ፈልገን ተጋረድን። የዘነበው ብዙ ቦታ አልነበረም። እንደው እኛ ጉድ ሊያሳየን ይሁን እንጃ። እንደው እኮ ሶስት ቀበሌ ቢዘንብ ነው፣ ቢሾፍቱ ስንደርስ ‘እህ’ አልን የዛን አገር ሰዎች። ‘በሉ አትቀልዱ’ አሉን። ‘እንዴ ከሰማይ ዱባ ዘነበ’ ስንላቸው እብድ አደረጉን። አብረውኝ የነበሩ መንገደኞች ነበሩ አንድዋ ጣይቱ ቤት ልትወስደኝ አንድዋ ዘመድ ጥየቃ ሞጆ ደርሳ የዓመቱ አቦ መሰለኝ ትዝ አይለኝም ስገምት ማለቴ ነው፣ እንደው እምቢ ሲሉ እኔ በመቀነቴ ርጥቡን የዱባ ፍሬ ሰብስቤ አዲስ አባ ገባሁ። አንድ ቀን መቀነቴን ላጥብ ስል ረስቼው ኖሮ … የቤተመንግስት ሥራ ጊዜ መች ይሰጣል? ማስተዳደር በለው፣ የመኩዋንንቱ ሆድ አያርፍም። ሁልጊዜ የሚበላ ያስፈልጋል መቆያም ይሁን። ጠዋት መስራት ማታ መስራት፣ እና በመቀነቴ እንደያዝኩት ዘሩ ሳይበላሽ ወር ከርሞ አገኘሁት። ያኔ እንደ ዛሬው ልብስ በየቀኑ አይታጠብም፣ ሳጥብ ደርቆ ልፋጩ መቀነቴ ቋጠሮ ውስጥ ተገፎ ረግፎ አገኘሁት። ሲሸት ነበር አንድ ሰሞን መተኛዬ ስገባ ይሸተኛል። ግን ልብ ሳልል እንጂ። እሱን ዘር ወሰድኩና ቤቴ ግቢ ሰፊ ቦታ ነበር፣ እዛ አጥር ሥር ፎገል ፎገል አድርጌ ቀበርኩት። ዝናብ ነበር ትዝ ይለኛል፣ ወሩን እንጃ … ምን ትዝ ይለኛል ወሩ። ዝናብ ነበር። ‘ያ ዱባ ከሰማይ የወረደ ዱባ ነው’ ብዬ ስናገር የሚያምነኝ አልነበረም። ተጫዋች ነበርኩ፣ እና ጨዋታ ይመስላቸዋል። ቀምሰው ዱባዬን … ቀምሰው እንኩዋን አያምኑኝም ነበር። ልጄ ሕዝባችን የተለየ ሕዝብ ነው። የማያዩትን የሚያምኑ፣ ያዩትን የማያምኑ ሕዝቦች ነን። ትደርስበታለህ። የማወርስህ ብችል እሱን የዱባ ዘር ነበር። ጥልያን ሲመጣ ትቸው ሄድኩ። ቤቴ የተሰጣቸው ባንዶች ቆፍረው ሌላ ነገር ሎሚና ወይን አብቅለውበት ደረስኩ። እቴጌ ጣይቱ ‘ዘር ስጪኝ’ ብለው እሳቸው ብቻ ያመኑኝ ወሰዱ። ያኔ እንጦጦ በቁም እስር እያሉ። ቁም እስር ታውቃለህ? ቁም እስር ማለት እንግዲህ አሳሪዎችህ እነሱ ዳገት ላይ ተቀምጠው አንተን ሜዳ ላይ ይለቁሃል እና ‘እንዳሻው ለቀቅነው’ ይሉሃል እሱ ቁም እስር ነው። ግሼን አምባም አይደለ። ማጣት ነው ያለበት። አውቆ ማጣት ነው። የዱባ ዘሬን በወሰዱ በሳምንቱ ጣይቱ እናቴ ከእንጦጦ ጠፉ። የተባለው ሞቱ ነው … እና ብፈልግ ብፈልግ መጠጫቸው ካቦና ያቺ የዱባ ቋጠሮ ለመሆኑ ካቦ ታውቃለህ? መጠጫ ጥዋ ነገር … የት ነበር ያቆምኩት ልጄ? የተነሳሁበት ይጠፋኛል። ለምን ይሄን አወራሃለሁ? የተነሳህበት እንዳይጠፋህ ነው ልጄ … እናልህ እስኪጠፉ እንደተባለው እስኪሞቱ ድረስ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ አብረን ከንግሥት ጋር ዱባ እንበላ ነበር። ዛሬ የተረፉ ወጥ ቤቶች አይጠፉም ቢጠየቁ ይህቺን የእኔንና የጣይቱን ሚስጢር አያውቁም። ማታ ማታ ወጥ ቤት ሁሉ ሲተኛ ቀን ደብቄ ያመጣሁትን ዱባ እልጥና አሳምሬ እሰራላቸዋለሁ። ጣታቸውን የሚልሱት ተእኔ ጋር ነበር። ምግብ ሲበሉ ‘ለመሆኑ የእናኑ እጅዋ አለበት?’ ይላሉ። የለበትም ተተባሉ ‘በሉ አስቀምጡትና ሂዱ ተራበኝ እበላለሁ’። አይበሉትም። ንክች። ‘ለመሆኑ የት ሄደች’ ይሉና መታመሜን ያውቁ የለ ይነገራቸውና መድሃኒት የሚያቅ ቤቴ ይልካሉ። አንድ ጊዜ ቅቤ ሳነጥር ከባድ ምች መቶኝ ሁለት ቀን ተኛሁ። በሁለተኛው ቀን ቤቴ መጡና እዝሁ ጎላ የደሃ ጎጆዬ ግማሽ ቀን ውለው ዳማ ከሴ ቆርጠው፣ አጥሚት ሰርተው አልጋዬ ጎን የተኛሁበትን ቁርበት ወርውረው ጨርቅ አንጥፈው … ዛሬ ድረስ አለ ያ ጨርቅ … ትንሽ ሲሻለኝ በበነጋታው መጥተው ገላዬን አጥበው … ማን ነበረኝ? ማን? ይሄ ሁሉ ልጄ በንግሥት እጅ። ዛሬ እንዲያ የሚያደርግ ንግሥት ቀርቶ እንደው ተራ ሰውስ አለ? ችሎታ ብላችሁት … የክፋት ችሎታ …

(ፈገግ አለ። የሚያስፈግግ ነገር አልነበረም። ስለ ንግሥት ቀባጢሶ ማውራት ወይም መስማት አይፈልግም። አሁን ወደ ውጭ መሄድ ይፈልጋል። ስታወራው ሳይቋርጥ የሚያየው ነገር ጠይም ፊቷን፣ ትልቅ አፏንና መውጫ በሩን ነው። ሲኒማ መግቢያው ጊዜ ደርሷል። ትንሽ ከቆየ ሊዘጋ ይችላል። ሊሞላ ይችላል። ፒያሳን ያስባል … አምፒር፣ የቡና በወተት ጠረን፣ የባቅላባ ጠረን፣ የእርጎ ጠረን፣ በቁንጅናቸው የሚያማልሉት ትናንሽ የጂንስ ቤልቦተም ሱሪዎች ያደረጉ ያኮረኮሩ ልጃገረዶች)

… አንድ ጊዜ ተአድዋ ዘመቻ በዋላ ትልቅ ግብር ያዘጋጃሉ። የእኛ መኩዋንንት ጦር ስላሸነፈ ብቻ ሁሉን ነገር ያወቀ ይመስለዋል። ‘መኩዋንንቱን ሁሉ እስቲ የሃበሻ ሴትን ሙያ እናሳየው’ ብለው ጣይቱ ምን የመሰለ ድግስ ያዘጋጃሉ። ከብት አለቀ ልበልህ። ተአምስት ሺህ በላይ ከብት። ብዙው መጋበዝ የሚመስለው ሥጋ ብቻ ነው። በመጨረሻ ዕለት ንግሥት ጠጋ አሉኝና ‘ለመሆኑ ያንን ዱባሽን በትልቁ ለብዙ ሰው መስራት ትችያለሽ?’ ይሉኛል። ተጠራጠርኩ። ‘እንዴ አንቺ ጎራዳ እናደርገውና እምቢ ካለን ዝም ነው’ አሉ … ሂሂሂሂ …

(ሳል ስላጣደፋት ከተኛችበት በክርኗ ደገፍ ብላ ተነሳችና ባዶ አየር ውስጥ በጭንቀት አፈጠጠች። ተረጋግቶ የነበረው ፊቷ ቁጣ እንደነካው ሁሉ ተኮማተረ። የምትስል ሳይሆን ብስጭት የሚሰማት ትመስላለች። እንደ አጋጣሚ በእጁ የያዘውን የኩታ ጫፍ ወደ አፏ ወሰደና ከአፏ ወደ ውጭ እየተገፋ የሚፈናጠቀውን ምራቅ መቅለብ ጀመረ። ከመሃል ትንፋሽ ስላጠራትና ዓይኖቿ ስለፈጠጡ ደንግጦ ለእርዳታ ሠራተኛዋን ሊጠራት ሲል መሳልዋን አቁማ ዝም አለች። የሚፈራው ይሄን ነው … )

…. ሲያምር ተንግሥት ጋር መዶለት። ዱባ ወጥ ሰራነ። አስቸገረ። አይ ሲጣፍጥ እቴ … አስቸጋሪው ደሞ በሰታቴ የተሰራ ያ ሁሉ ዱባ እንዴት ሳይፈርስ ተምድጃ ይወጣል ነው። ቀላል ይመስላል። እኔ እናትህ ማማሰያ ሳላስገባ እተጌን አስደሰትኩዋ። ጠረኑ ራሱ ‘የዛሬስ ወጥ ምን ቅመም ቢገባበት ነው?’ ተባለ። እኔና ንግሥት እንተዋወቃለን። ተራራው ላይ እንጦጦ ሳትወጣ ታች እዛ አሁን ሰፈራችሁ ያለበት ገደል ጋ ይሸትሃል … ስዋሽህ አይደለም። መኩዋንንት ተሰብስቦ ሲበላ ‘ምንድነው’ አለ? ‘የምን ሥጋ ነው? በምን ሰራችሁት?’ ሁሉ ተበልቶ አልቆ ‘ዱባ ነው’ ተብሎ ቢነገራቸው ‘አሁን ተሥጋው የበለጠ ጥሞአችሁ የበላችሁት እሱ ዱባ ነው’ ሲባሉ አላመኑም። አላዛር ሙት አላመኑም። እተጌ ሲናገሩአቸው አላመኑም። አምነናል ያሉትም ‘እንዴ ታዲያ መኩዋንንቱን ዱባ ታበያለሽ እንዴ? የሚበላ ጠፋ?’ አሏቸው። ብቻ ዱባ መሆኑ ሲነገራቸው ስለበሉት ነገር ማውራት አቆሙ። በዋላ ሲያስሩአቸው ‘ይህቺ እኮ ትንቀናለች ያ ዱባ ትዝ ይላችሁዋል?’ እያሉ ነበር። ‘መኩዋንንቱን ንቃ ዱባ ደብቃ የምታበላ’ እያሉ። እኔ እናኑ እውነቴን ነው የምልህ የዚያ ወጥ ጠረን ተማድቤት ቀርቶ ተራራው ራሱ ላይ ‘ስንት ጊዜ ምን የሚያምር ነገር ይሸተናል’ እየተባለ። ያን ሰሞን ቢበሽቁ እተጌ መኩዋንንቱን አዘፈኑባቸው።

አገሬን ወዳለሁ ሕዝቤን እወዳለሁ

አፈርዋን ዱባዋን ጠብሼ እበላለሁ

ደም አፍሰው ሥጋ ቢነጩት ቢነጩት

ልብ ይደፍናል እንጂ አይሆን ለሰው አንጀት

የጦብያ ሴቶች ሙያቸው ትላልቅ

በጦር ሜዳ ይሁን በማድ ቤት እናስንቅ

እናልህ እሳቸው በተፈሪ ሲታሰሩ ማድ ቤት የነበርነውም ተበተንን። እኔ በዋላ በዋላ ታዘነልኝና ባሌም ስለ ሞተ ዘውዲቱም ስለምትወደኝ ትንሽ መሬት ተቆርጦልኝ … አንድ መኩዋንንት ናቸው አሉ ‘ሴት ልጅ አትበድሉ’ ብለው ተከራክረውልኝ … ጣይቱ የቁም እስር ባሉበት ተዚህች ዓለም እስቲያልፉ ድረስ ተእኔ እንዳይገናኙ ቢከለከሉም አንዳንዴ እየጠሩኝ በአቅራቢ በአቅራቢ … እንግዲህ እኔ ተፈርቼ መሆኑ ነው … ከጓሮዬ ቀንጥሼ ዱባ ወጥ ሰርቼ እወስድላቸዋለሁ ወይ እልክላቸዋለሁ … ‘አረፉ’ ሲባል አለቀስኩ ልጄ … አሁን እኔ ኖሬ እሳቸው ይሞታሉ? የእግዜርን ነገር አየህ። አሁን ዘጠና አለፈሽ እባላለሁ ግን እመቤቴ እሳትዋ በአጭር ተጠለፈች። እግዜር ሚስጢሩ አይገባም …

(ብዙ ነገር ቢረሳም ይሄን አይረሳም። አባቱ ብርሃነመስቀል እናኑ ጋ አድርሶት ወደ ሚሄድበት ሊሄድ ታኑስ መኪናውን ግቢ አቁሞ፣ ዝናቡን እያማረረ፣ ሐምሌን እየረገመ፣ በጫማው የሰበሰበውን ጭቃ ድንጋይ ላይ ለመጥረግ ሲለፋ፣ አላዛር አባቱን ትቶት እየሮጠ ወደ ቤት ውስጥ ይገባል ……… ከፊት ለፊቱ ትራስ ተደግፈው ሶፋ ላይ ጋደም ያሉት እናኑ ላይ ወደቀ። እናኑ አላዛር ከረሜላ ያመጣልኛል ብለው የመጨረሻዋን የማር ከረሜላ አፋቸው ከተው እየመጠጡ ነበር። ያን ቀን ከረሜላ አልገዛም። ጭናቸው ላይ ተቀምጦ እንደ እንቦሳ እየተገላበጠ፣ አባቱ ገንዘብ አልሰጥህም ብሎት ከረሜላ ስላልገዛ ከሚበሉት ከረሜላ እንዲሰጡት ይጠይቃቸዋል። ‘እምቢ አፌ ከገባ አልሰጥህም’ ይሉታል። አልሰማም። ጣቶቹን አፋቸው ውስጥ ከቶ ከረሜላውን ለማውጣት ብዙ ለፋ። እምቢ ቢሉትም ጭናቸው ላይ በጀርባው ተኝቶ ካልሰጠሽኝ እያለ መነዝነዙን ቀጠለ ……… አላዛር ጭናቸው ላይ እንደ ቡችላ ሲሆን ሲያዩት፣ የወርቅ ሐብሉ ከነመስቀሏ የሚያምር አንገቱ ላይ ተልፈስፍሳ ሲያዩት፣ ወተት የመሰሉ ትናንሽ ጥርሶቹና እህል ገብቶበት የማያውቅ የመሰለ የአፉን ጽዳት ደሞ የቆዳውን ልስላሴ ሲያዩት … ብቻ ሁሉ ነገሩ ስቧቸው፣ የወለዱት ሁሉ መስሏቸው፣ ወደ አፉ እንደሚስሙት ሁሉ ቀርበው በምራቃቸው የመለገውን ከረሜላ በተከፈተ ለፍላፊ አፉ ጠብ አደረጉለት። ዓይኖቻቸውን በእርካታ ጨፈኑ። ልባቸው የምትቆም መሰላቸው። አላዛር በአፉ የገባው ከረሜላ አስደስቶት ያሉበትን ክፍል በትንሽ ልጅ ሳቁ ሞላው ……… አላዛር ይሄ ሲታወሰው ለእናኑ የዱባ ተረትና አይቶትም ይሁን ቀምሶት የማያውቀው የዱባ ወጥ ጣዕም አፉ ውስጥ ይሰማዋል። ከረሜላ አይደለም ምንም አይደለም ራሱንም ይጠይቃል እንዴት ያልቀመስኩት ትዝ ይለኛል? እንዴትስ ይጣፍጠኛል?)

.

አዳም ረታ

.

ዘመን ቊጥርና ስሌት

“ዘመን ቊጥርና ስሌት”

(ክፍል 1) 

በኅሩይ አብዱ

.

የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች ጥንታዊ ሰነዶችን እንደ መረጃ ሲጠቀሙ፣ ሰነዱ የተጻፈበትን ጊዜ ማወቅ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር መንገዶች ካሁኑ ስለሚለዩ የጽሑፉን ዘመን በቀላሉ ማወቅ ያዳግታል። ለምሳሌ በ14ኛው ክ/ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ ላይ የተጻፈው የዐጼ ዓምደ ጽዮን ታሪክ እንዲህ ይላል፣

ዓምደ ጽዮን ንጉሠ ኢትዮጵያ … በዓሠርቱ ወሠመንቱ ዓመተ መንግሥቱ እምዘ ነግሠ ወዓመተ ምሕረትሂ ፭፻፲ወ፮።

[ትርጉም] የኢትዮጵያ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን … በነገሠ በ 18 ዓመት፣ በ516 ዓመተ ምሕረት።

(516 ዓመተ ምሕረት?! ይህ እንዴት ይሆናል? ያኔ የአክሱም ዘመን አልነበር? የጸሓፊው ስሕተት ነው ወይስ ያልተረዳነው ነገር አለ?)

ሌላ ምሳሌ ደግሞ፣

በ፴ወ፭ ዓመተ ምሕረት ወበመዋዕሊሁ ለንጉሥነ ዘርአ ያዕቆብ … ወእምአመ ነግሠ በ፳ወ፭ ዓመት ..

[ትርጉም] በ35 ዓመተ ምሕረት በንጉሣችን በዘርአ ያዕቆብ ዘመን … ከነገሠ በ25 ዓመት

(የ15ኛው ክ/ዘመን አፄ ዘርአ ያዕቆብስ ወደ አንደኛው ክ/ዘመን ምን ሊሰራ ሄደ?)

ይባስ ብሎ ሌላ በ14ኛ ክ/ዘመን የተዘጋጀ ብራና፣

ዓመተ ምሕረት በ፷፻፰፻፸፬ … (በ6874 ዓመተ ምሕረት)

(ይህንስ ማለቱ ስምንተኛው ሺ የሚያስብል ነው።)

እነዚህን አደናጋሪ የዘመን አቆጣጠር ምሳሌዎች ወደፊት ለመፍታት ይሞከራል። በመጀመርያ በዚህኛው ክፍል ስለ ግዕዝ ቁጥሮችና ስሌቶች አጭር ገለጻ አቀርባለሁ።

በሚቀጥሉት ወራት በሚቀርቡ ክፍሎች ደግሞ ከዘመነ አክሱም እስከ 20ኛው ምዕት ዓመት የዘመን አቆጣጠር ታሪካዊ ቅኝት ቀርቦ፣ በመጨረሻም የተወሰኑ የዘመን አቆጣጠር ዓይነቶች ከታሪካዊ ምሳሌዎችና የሒሳብ ስሌቶች ጋር ይታያሉ።

 .

የግእዝ ቊጥር (አኀዝ)

በግእዝ ሰዋስው አኀዝ የተባለ ራሱን የቻለ ክፍል አለ። ስለ አኀዝ ሰፋ ያለ ትንተና ከምናገኝባቸው ቀደምት ሥራዎች መካከል፣ አባ ገብረ ሚካኤል በ1850ዎቹ አዘጋጅተውት በኋላ በ1872 ዓ.ም. በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ አርታዒነት በላዛሪስት ሚሽን ማተምያ ቤት ከረን የታተመው መጽሐፈ ሰዋስው ነው።

በ1882 ዓ.ም. በአለቃ ታዬ የተዘጋጀውም መጽሐፈ ሰዋስው ተመሳሳይ ትንተና ስለ አኀዝ ምንነት ያቀርባል። ጽሑፉም እንደሚለው አኀዝ መጀመሪያ፣ መቋሚያ፣ መያዣ ዋስ፣ ቊጥር እና ድምበር ተብሎ ይተረጎማል። የአኀዝንም ፍቺ በአንድምታ የትንተና ስልት እንደዚህ አቅርበውታል።

aleqa taye
አለቃ ታየ ገብረማርያም

መጀመሪያ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ ሁሉ በቊጥር ይጀመራል ይጨርሳልና መጀመሪያ ተባለ።

አኀዝን መቋሚያ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ የነገር ሁሉ መቋሚያ አለው፤ አኀዝም የነገር ሁሉ መቋሚያ ነውና…።

መያዣ ዋስ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ በመያዣ በዋስ ያለ እንዳይጠፋ በቊጥርም ያለ አይጠፋምና መያዣ ዋስ ተባለ።

አኀዝን ቊጥር ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ በቊጥር የተወሰነ ይወሳል። ያልተወሰነ ይረሳልና ቊጥር ተባለ።

ድምበር ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ ድምበር የእህል የሣር መለያ ነው። ቊጥርም የሁሉ መታወቂያ ነውና ድምበር ተባለ። አንድም ከአኀዝ ወዲያ ቅጽል የለምና ድምበር ተባለ።”

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በታላቁ መጽሐፋቸው፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ስለ አኀዝ ጠለቅ ያለ ትንተና ያቀርባሉ። ስለ የተለያዩ የአኀዝ ዓይነቶች ሲያስረዱ፣ አኀዝ በጥቅሉ መዘርጋት፣ መተርተር፣ መከፈል፣ መታጠፍ፣ መጠቅለል እንደሚችል ይገልጻሉ። ሲተነተኑም፣

Kidane Photo
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ

መዘርጋት፣ ብዛትንና ስንትነትን እንደ ነዶና እንደ ችቦ አስሮ ሰብስቦ የሚያሳይ የጅምላ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ ፩፣ ፪፣ ፲፣ እንዲሁ።

መተርተር፣ ስንትነታቸው ከታወቀ ከብዙዎች ማኽል ስንተኛነትን ለይቶ የሚያሳይ የተራ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ ፩ኛ፣ ፪ኛ፣ ፲ኛ፣ እንዲሁ።

መክፈል፣ የክፍሎችን ስም እንደ ተራ ቊጥር እየለየ በየማዕርጉ የሚያሳይ ክፋለዊ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ መንፈቅ፣ ሣልሲት፣ ራብዒት።

ማጠፍ፣ ጅምላውን ቊጥር ዐጥፎ ደርቦ እያሳየ በመንታ መንገድ የሚወስድ ያጸፋ ቊጥር ነው። ምሳሌ፣ አሐዳት፣ አው ካዕበተ አሐዱ፣ ፩ ዕጽፍ። ክልኤታት፣ አው ካዕበተ ክልኤቱ፣ ፪ ዕጽፍ፣፬ ነጠላ፤ ወከማሁ።

መጠቅለል፣ እንዳራቱ ክፍሎች አኀዝ ሳይኖረው፣ በቅጽልነቱ ማነስና መብዛት ሕጸጽና ምልአት የሚያሳይ፣ የአኀዝ ቅጽሎች ሰብሳቢና ከታች የሚኾን መድበል ቊጥር ነው፤ ያውም ኅዳጥ ብዙኅ ኵሉ፣ ይህን የመሰለ።

የግእዝ ቊጥሮችንም ከአንድ እስከ ምእልፊት (መቶ ሚልዮን) ይዘረዝሩና፣ ከተፈለገም እስከ እልፍ  ምእልፊት (ትሪልዮን)  … እንዲሁም ከዛም በላይ መቊጠር (መጻፍ) እንደሚቻል ያስረዳሉ። አለቃ ኪዳነወልድ ከአንድ (1) እስከ እልፍ ምእልፊት (በአሁኑ አቆጣጠር ትሪልዮን 1‚000‚000‚000‚000) በግእዝ አኀዝ ለመጻፍ እንደ ቊጥር የሚያገለግሉ አስራ ዘጠኝ የተለያዩ ምልክቶችን ተጠቅመዋል። እነዚህም በአሁኑ ባላቸው መልክ የሚከተሉት ናቸው።

፩ ፪ ፫ ፬ ፭ ፮ ፯ ፰ ፱ ፲ ፳ ፴ ፵ ፶ ፷ ፸ ፹ ፺ ፻

(1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 20 30 40 50 60 70 80 90 100)

እነዚህን 19 ምልክቶች በተለያየ መልክ በማጣመርም ሌሎች ቁጥሮችን መፍጠር ይቻላል።

ለምሳሌ ፳፻፲፯፣ 2017 (20 መቶ እና 10 እና 7) ይሆናል።

ስለዚህ የግዕዝ የቊጥር ስርዓት በ19 ምልክቶች ላይ የተመሰረተ ነው (በአንፃሩ በዓለም በሰፊው የተሰራጨው የሂንዱ-አረብ የቊጥር ስርዓት አስር ምልክቶችን ይጠቀማል።)

የግዕዝ የቊጥር ስርዓት ለዜሮ ቊጥር ምልክት የለውም፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ ለአስር፣ ለሀያ … እስከ መቶ ላሉት ቁጥሮች ተጨማሪ ምልክቶች ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ የዜሮ ምልክት በቁጥሩ ስርዓት ውስጥ ባይኖርም፣ የዜሮ ጽንሰ ሐሳብ ግን ለብዙ መቶ ዓመታት አልቦ (ሲያጥር አል ወይም ) በሚለው ቃል ውስጥ ተካቶ እናያለን፣ በተለይ የማካፈል ስሌት ውጤቶች ውስጥ።

.

የቊጥሮች መልክ መቀያየር

ከላይ የሚታዩት ያሁኑ ዘመን የቊጥር ምልክቶች በመደበኝነት በዚህ ቅርጻቸው የጸኑት በ19ኛው ክ/ዘመን ለኅትመት ሲባል በብረት መቀረጽ ሲጀምሩ ነው፣ አሁን ደግሞ በኮምፕዩተር ፕሮግራሞች ያንኑ መልክ ይዘው ቀጥለዋል። ከታች የቀረበው ሰንጠረዥ የተወሰኑ የግዕዝ ቁጥሮችን የጊዜ ሂደት ለውጥ ያሳያል።

Hiruy Numbers Evolution

ከሰንጠረዡ ማየት እንደሚቻለው በዋነኝነት በጊዜ ሂደት መልካቸው ሊያሳስት የሚችለው ቊጥር 1 እና 4፣ እንዲሁም ቊጥር 6 እና 7 ናቸው።

የአክሱም ዘመን፣ የ14/15 ምዕት ዓመት እና በ17ኛ ክ/ዘመን ሉዶልፍ ያስቀረጸው ቊጥር 1 ያሁኑን ዘመን ቊጥር 4 (፬) ይመስል ነበር፣

የቀድሞው ቊጥር 4  ሦስት ማዕዘናዊ ነበር።

ስለዚህ ሁለቱን ለመለየት ሲባል ያሁኑ ዘመን ቊጥር 1 (፩) ከላዩ ትንሽ ቅጥያ ተጨምሮለታል።

የአክሱም ዘመን፣ የ14/15 ምዕት ዓመት እና በ17ኛ ክ/ዘመን ሉዶልፍ ያስቀረጸው ቊጥር 6 ያሁኑን ዘመን አነስተኛ ቊጥር 7 (፯) ይመስል ነበር፣ ስለዚህ ሁለቱን ለመለየት ሲባል ያሁኑ ዘመን ቊጥር 6 (፮) የስረኛው ቅጥያ ወደ ቀለበት ተቀይሯል።

 .

የሒሳብ ስሌቶች

በጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት ባሕረ ሐሳብ የሚባል የዕውቀት ክፍል አለ። የትምህርቱም ዓላማ ከዓመት ዓመት ተንቀሳቃሽ የሆኑ በዓላትና አጽዋማት (ፋሲካ፣ የሁዳዴ ጾም … ወዘተ)  መቼ እንደሚውሉ ማስላት ነው። የባሕረ ሐሳብ ዐዋቂ ለመሆን የሚያስፈልገው የአራቱ መደብ የቊጥር ስሌት (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈል) እንዲሁም የአንዳንድ የዘመን መለኪያ የስሌት ቃላትን ትርጉም መረዳት ነው።

የስሌትን አጠቀላይ ተግባር ለመግለጽ የተለያዩ የግዕዝና የአማርኛ ቃላት በሥነ ጽሑፍ ይገኛሉ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፣

ቈጠረ፣ ቀመረ፣ ሠፈረ፣ መጠነ፣ ሐሰበ (ዐሰበ) – ሒሳብ፣ አሰላ – ስሌት፣ …

በተጨማሪም፣

በዘተአምር (እንድታውቅ)፣

አእምሮ አዝማን (ዘመንን ማወቅ)፣

ትእኅዝ (ትይዛለህ)፣

ተኀሥሥ (ትፈልጋለህ፣ ትሻለህ) … የሚባሉ ሙያዊ ቃላቶችም አሉ።

የስሌቱ ውጤት እንዲህ ይሆናል ለማለት ደግሞ፣

ይዔሪ (ይተካከላል፣ እኩል ይሆናል)፣

ይከውነከ (ይሆንልሃል) … የመሰሳሉትን እናገኛለን።

ከታች ያለው ሰንጠረዥ አራቱ መደበኛ የቊጥር ስሌቶች (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈል) በግዕዝ እና አማርኛ የባሕረ ሐሳብ ብራናዎች በምን ቃላት እንደሚገለጹ ዝርዝር ያቀርባል።

Terms Table

.

ማካፈል

በባሕረ ሐሳብ ትምህርት በመደጋገም የምናገኘው ስሌት ማካፈል ነው፤ በተለይም መግደፍ ለሚባለው ስሌት በጣም አስፈላጊ ነው። ማካፈልን በዘመናዊ መልኩ ስናየው፣ አንድ ቊጥር በሌላ ሲካፈል የማካፈሉ ውጤት ድርሻ (quotient) እና ቀሪ (remainder) ይሰጣል።

ለምሳሌ ሰላሳን በሰባት ብናካፍል

Division Figure

የማካፈሉ ውጤት – ድርሻ አራት (4) ይደርስና (4 × 7 =28) ቀሪው ሁለት (2) ይሆናል።

.

መግደፍ 

በባሕረ ሐሳብ ትምህርት ላይ መግደፍ የሚባል ከአራቱ መደብ የቊጥር ስሌት ትንሽ ለየት ያለ የሒሳብ ስሌት አለ። መግደፍ ማለት አንድን ቊጥር በሌላ አካፍሎ የሚተርፈውን ቊጥር (ቀሪ) እንደ ውጤት መያዝ ነው። የላይኛውን ምሳሌ ከእንደገና ብናይ፣ ሰላሳን (30) በ ሰባት (7) መግደፍ ቢያስፈልግ፣ መጀመርያ ሰላሳን በሰባት እናካፍላለን – የዚህም ውጤት አራት ይደርስና (4 × 7 =28) ቀሪው ሁለት (2) ይሆናል።

ስለዚህ ቀሪው ሁለት (2)፣ ሰላሳን በሰባት መግደፍ ለተባለው የሒሳብ ስሌት ውጤት መሆኑ ነው። በዘመናዊ የሒሳብና የኮምፒዩተር ስሌት መግደፍ Modulo (MOD) ከሚባለው ስሌት ጋር አቻ መሆኑ ነው።

የመግደፍን ውጤት የሚተነትኑ ቃላትም አሉ፤

ጥንቁቀ ተከፍለ (በትክክል ተከፍሏል – ቀሪ የለውም ለማለት)፣

ወዘተርፈከ (የተረፈህም)፣

ወዘዘኢከለ (ያልበቃውም – የተረፈውም)፣

እስከ ትዌድእ (እስከ ትጨርስ ድረስ … ‹ማካፈሉን›)፣ (ይህን ያህል) …ደርሶ …(ይህን ያህል) ይቀራል፣ ይተርፋል ….

መግደፍ በሰፊው በባሕረ ሐሳብ ስሌቶች ውስጥ፣ እንዲሁም ከ16ኛ ክ/ዘመን ጀምሮ በተስፋፋው በዓውደ ነገሥት የዕጣ-ፈንታ ስሌት ውስጥም ይገኛል።

.

መጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት፣  … መጠነ _ _ _

ከማካፈል ስሌት ጋር በተገናኘ፣ ቀሪው እላይ እንደታየው መግደፍ ለተባለው ስሌት ሲጠቅም፣ ድርሻው ደግሞ አሁን ለምናያቸው መጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት … ስሌቶች ይጠቅማል። መጠነ ሳብዒት የአንድን ቊጥር በሰባት የማካፈል ድርሻ ሲይዝ፣ መጠነ ራብዒት ደግሞ የአንድን ቊጥር በአራት የማካፈል ድርሻ ይወስዳል። የላይኛውን ምሳሌ ከንደገና ብናይ፣

የሰላሳ መጠነ ሳብዒት፣ ሰለሳን በሰባት አካፍሎ (30 ÷ 7፣ ድርሻው 4፣ ቀሪው 2)  ድርሻውን አራት (4) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰለሳ መጠነ ሳብዒት አራት (4) ነው።

የሰላሳ መጠነ ራብዒት፣ ሰለሳን ባራት አካፍሎ ድርሻውን ሰባት (7) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰለሳ መጠነ ራብዒት ሰባት (7) ነው።

ይህ መጠነ — የሚለው ስሌት ከአራት እና ሰባት በተጨማሪ ለሌላ ቁጥሮችም ማስላት ይቻላል። ለምሳሌ፣ መጠነ ሳድሲት በስድስት የማካፈልን ድርሻ ይይዛል። የሰላሳ መጠነ ሳድሲት (30 ÷ 6፣ ድርሻው 5፣ ቀሪው 0) ድርሻውን አምስት (5) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰላሳ መጠነ ሳድሲት አምስት (5) ነው።

.

(ውጤቱ) እንዲህ ከሆነ … ይህን አድርግ … 

አለዚያ … ያንን አድርግ

በዘመናዊ የሒሳብና የኮምፒዩተር ስሌት Conditional IF ከሚባለው ስሌት ጋር አቻ መሆኑ ነው።

If 1 Then  Do A,

If 2 Then  Do B …

Else … Do X

የአንድ የመግደፍ ስሌት ውጤት ከታወቀ በኋላ፣ እንደውጤቱ ዓይነት የተለያዩ የድርጊት ምርጫዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ በባሕረ ሐሳብ፣ መስከረም 1 በምን ዕለት እንደሚውል በሚደረገው ስሌት፣ ድምሩ በሰባት ይገደፍና፣ ቀሪው ውጤት አበቅቴ ፀሐይ ተብሎ ይያዛል። የሚገደፈው በሰባት ስለሆነ ያሉትም ምርጫዎች ሰባት ይሆናሉ። ሰነዱ እንደሚለው፣

            ወእምዝ ትገደፍ በበ፯ ወዘተረፈከ ውእቱኬ አበቅቴ ፀሐይ።

(ከዛም በ7 ትገደፋልህ፤ የተረፈህም (ውጤት) አበቅቴ ፀሐይ ነው።)

ለእመ ኮነ ኍልቈ አበቅቴ ፀሐይ

የአበቅቴ ፀሐይ ልኬት (ቊጥር) 1 ከሆነ)

ይከውን ቀዳሚተ ሠርቀ መስከረም በዕለተ ረቡዕ

(መስከረም 1 ረቡዕ ዕለት ይሆናል (ይውላል)።)

       ለእመ ኮነ ኍልቈ አበቅቴ ፀሐይ

(የአበቅቴ ፀሐይ ልኬት (ቊጥር) 2 ከሆነ)

 ይከውን ቀዳሚተ ሠርቀ መስከረም በዕለተ ኀሙስ

(መስከረም 1 ሐሙስ ዕለት ይሆናል (ይውላል)።)

… እያለ እስከ ቊጥር ሰባት ድረስ ይዘልቃል።

ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ባሳተሙት ሐተታ መናፍስት ወዓውደ ነገሥት ደግሞ፣ ለምሳሌ ሓሰበ ኑሮ ወዕድል የሚለውን ክፍል ብንወስድ፤ በመጀመርያ፣ ‹ስምና የእናትን ስም በ፱ ግደፍ› ይላል። የሚገደፈው በዘጠኝ ሰለሆነ ያሉትም ምርጫዎች ዘጠኝ ናቸው። ከዛም እንደ ሎተሪ፣

፩፤ ሲወጣ በሹመት ይኖራል።

፪፤ በንግድ ይኖራል።

በዙረት ይኖራል።

በእጀ ስራ ይኖራል

በወታደርነት ይኖራል።

በብክንክን ይኖራል።

በቤተ መንግሥት ይኖራል።

በዙረትና ልፋት ይኖራል።

በንግድና በእርሻ ይኖራል።›

.

ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገደብ (ወሰን)

የአንድ ስሌት ውጤት ከዚህ ቊጥር መብለጥ ወይንም ከዚህ ቊጥር ማነስ የለበትም፣ የሚለውን ሐሳብ ለማስረዳት በባሕረ ሐሳብ ትምህርት የሚከተሉት ቃላት ይገኛሉ። ዝቅተኛው ገደብን (በሒሳብ እና ኮምፕዩተር ትምህርት Lower Limit) ለመግለጽ፣

ኢይውኅድ (አይቀንስም)፣

ኢይወርድ (አይወርድም)፣

ኢይቴሐት (አያንስም)፤

ከፍተኛውን ገደብ (በሒሳብ እና ኮምፕዩተር ትምህርት Upper Limit) ለመግለጽ ደግሞ፣

ኢይበዝኅ (አይበዛም)፣

ኢይዐዱ (አያልፍም)፣

ኢይትሌዐል (አይተልቅም)።

እላይ ካየናቸው ከአራቱ መደበኛ ስሌቶች፣ ከመግደፍመጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት …፣ ከ ‹(ውጤቱ) እንዲህ ከሆነ … ይህን አድርግ‹ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገደብ› በተጨማሪ ሌሎች የሒሳብ ስሌቶችና ብያኔዎች አሉ።

ሁሉንም ለመዘርዘር እና ለመተንተን ግን ሰፋ ያለ ጥናት ያስፈልጋል። የ14ኛው ክ/ዘመን የባሕረ ሐሳብ ሊቅ እንዳለው፣

ዘንተ ዕቀቡ

በጥንቃቄ ሐስቡ 

ጥያቄ አዝማን ከመ ትርከቡ። 

(የዘመንን ምርመራ ታገኙ ዘንድ፣ ይህንን ያዙ፤ በጥንቃቄ አስሉ።)

.

ኅሩይ አብዱ

ሐምሌ ፳፻፱