“ፍቅር እና ሆሄ” (ልብወለድ)

“ፍቅር እና ሆሄ”

በአዳም ረታ

.

[ይሄ ጽሑፍ በ1999 ዓ.ም አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች (በመስፋቱም ጭምር) በመጀመሪያ ንድፍ ላይ ከደረሰ ‘ፍቅርና ሆሄ’ ከተባለ ግን ሳይታተም ከቀረ የ2500 ገጽ ልብወለድ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ነው። ጽሑፉ የተቆረሰው አርባ ገጾች አካባቢ ብዛት ካለው ‘ዑር እናት’ ከተባለ የመጽሐፉ መግቢያ ምዕራፍ ነው።]

.

Adam Inside Photo

.

(አገሪቱ በፀሐይ ሙቀት ለነደደች ጊዜ፣ በከተማውና በከተማው ዙሪያ ያሉ ባሕር ዛፎች በጠል መጥፋት ቢጫ ለነበሩ ጊዜ፣ የሚቀመስ እህል ጠፍቶ ለነበረ ጊዜ፣ በተለይ የአገሪቷ ተወዳጅ ምግብ ዱባ የተባለው ፍሬ ዘር ማንዘሩ ለጠፋ ጊዜ፣ ብቻ ከዛሬ ልጅ ለነበረ ጊዜ ……… አያቱ እናኑ የተመቻቸው ቦታ ተቀምጠው ሲያያቸው ገላው ለመታቀፍ ይቁነጠነጥ ነበር። እቅፋቸው ውስጥ በረዶ በመሰለ ጋቢያቸው ሲጠቀለል የሚያደርገው ዓይኖቹን ጨፍኖ ለማይቆም ጊዜ መተኛት ነው። ‘እናና!’ ብሎ ሲጠራቸው ለሌሎች ሰዎች ጎምዛዛ የሚሆኑት ሴትዮ እንደ አበባ ይከፈታሉ። ጉንጭና አፉን ሲስሙ ሁለመናቸው ወተት ይሆናል። አንዳንዴም አላዛር እንደሚወደው ጋቢያቸውን ድንኳን አስመስለው በላያቸው ላይ ይዘረጉና እንደ ልጅ ይላፉታል ……… ከረሜላ ይወዱ ነበር። ሲያውቃቸው ጀምሮ ከአፋቸው የማይጠፋው ከረሜላ ነበር። የሳምንቱን ቅዳሜ ጠብቆ አባቱ በሚሰጠው ገንዘብ ብዙ ማር ከረሜላና ደስታ ከረሜላ ገዝቶላቸው ይሄዳል። ለእሱ የሚፈልገውን በሱሪ ኪሱ፣ ለእሳቸው የመደበውን ደሞ በእጁ ጨብጦ ይቀርባቸውና ‘ትልቋ እማማ ከረሜላ አመጣሁልሽ’ ይላቸዋል። ከረሜላ የያዘበት እጁን በሁለት እጆቻቸው ያቅፉና በምራቃቸው ረጥቦ እስኪያብረቀርቅ ቡጢውን ይስሙለታል።)

… ለምን ትልቅዋ አያቴ ትለኛለህ? ማን አስተማረህ? እኔ ተአያትህ ተሰብለ ብዙ አላረጅም እኮ … ግን ኑሮ ቀደም ብሎ በጥቁር እጁ ሲነካኝ ምን ይሁን? ነካ ነካ ያደርግሃል ኑሮ። ይነጅስሃል። እስዋ የፊታውራሪ ልጅ ነበረች። እኔ በጉዲፈቻ ሞጆ ያደግሁ አባትና እናቴ በስልቱ የማይታወቁ። በእናትህ በኩል ቅድመ አያትህ ፊታውራሪ መሸሻ የሚባሉ የጎጃም ሰው ስማቸው የተጠራ ነበሩ በዋላ ስሰማ። ሰብለ ዲማ ነው እንግዲህ የወለደችው። ለአቅመ ሔዋን የደረሰችው እዛ ነው። የሚገርም ታሪክ ነበራት በዋላ ስትነግረኝ … እሱማ ሰሚ ካገኘ የማንም ታሪክ አይገርምም? እንደው እየመረጥነ እንጂ። ሀሁ ተሚያስተምራት ዲያቆን ይሁን ደብተራ የትኛው እንደሆነ እንጃ በዛብህ ተሚባል ጎረምሳ … ጎረምሳ ነው … ፍቅር ይይዛታል። አባትዋ ሲቀብጡና ሲኮሩ ባል ሲመርጡ ትልቅ እስትትሆን ቤት ዘግተውባት ይኖራሉ … እና አልኩህ እንዳለችኝ ይሄ በዛብህን ወደደች። ታዲያ ያኔ እንደ ዛሬ ዘመን ማንም ከማንም አይጋባም። ዘር አለ ምን አለ … ጦረኛ የጦረኛ ልጅ ነው የሚያገባ … ባለመሬት ባለመሬትን። ፍቅር ማን ያውቃል? ፍቅር አብረው ሲኖሩ ነው … እስቲ አትደብቀኝ አላዘር ዓለምዬ እንደው ያቺ የጎረቤታችሁ ልጅ ማን ነበር ስምዋ? እ? …

(ሊመልስላት አልፈለገም። ገና ቅልስልስነቱን ባልጨረሰ ልጅነቱ ጊዜ ለምን እንዲህ እንደምትጠይቀው ግራ ይገባዋል። እየሳቀች በአፏ ከተባረኪ ጋር ባልና ሚስት ስታጫውተው ትወዳለች። እየተሽኮረመመ አያት። አታየውም። ሊመልስላት አልፈለገም። ድምፁ ውስጥ የመሽኮርመም ዜማ እንዲሰማበት አልፈለገም። ወደ እሱ ያዞረችው ፊቷ ሳያቋርጥ ያሳዝነዋል። ልመልስላት አልመልስላት ሲያስብ …)

ተባረኪ? ወይ ስም እቴ አይ የስም ማማር … ለመሆኑ አባትዋ ይመጣል? … አይመጣም … አይ እቴ ያልሸገረኝን። እና ሰብለ ዲያቆን ለምዳ በዋላ መሰማቱ ይቀራል እግዜር ሲያቅደው። አባት ‘ካልገደልኩት ይሄን ቅማላም ደሃ’ ሲሉ ይፈራና ነፍሱን ሊያድን አምልጦ ወደ ሸዋ ይመጣል። መሄዱን ስትሰማ እስዋ ተከትላ እግሬ አውጭኝ … ወደ ሸዋ እግሩን ተከትላ። መንገድ ላይ ሽፍቶች ደብድበውት … መቼም የሰማሁትን መደበቅ ምን ያደርግልኛል? … ብዙ ነበር የምትለው ሊሞት ሲል የባላገር ቤት አርፎ በጠና ቆስሎ ትደርሳለች። ግጥጥሙ አይገርምም? ምን ይደረጋል እግዜር ያቀደውን … አይታገሉት። ክንድዋ ላይ ደም መቶት ይሞታል። አያሳዝንም? እንዲህ ስታወራኝ በጉንጭዋ ዕንባ እየወረደ። የሰማት ሁሉ ነው የሚያለቅስ … እስቲ ያን ውሃ አቀብለኝ … ያቺ ልጅ አልመጣችም? መድሃኒቴን የት ነው ያስቀመጠችው? ጊዜው ተላለፈ እኮ። ሰዓት ስንት ሆነ? አምስት? ያ አባትህ እኮ ገና በልጅነትህ ሰዓት መስጠቱ ለእኔ ሳይጠቅመኝ አልቀረም። ለመሆኑ አያድርግና ስትጫወት ብትሰብረውስ? እ? አምስት አልከኝ? አንድ ሰዓት አለኝ። አምስት ተሩብ? ያው ነው … ስለ አያትህ ስለ ሰብለ ልቀጥልልህ። ሰብለ መሸሻ። የእኔ እህት… የእኔ እመቤት። አራዳው ካገኘሁዋት ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀን አለቀሰች። ተዚያ ተሁለት ሰንበት በዋላ ተሻላት። መብላት ጀመረች መጠጣት ጀመረች። አልፎ አልፎ እንደው ቢደብታትም። እኔ ምን ነበረኝ ያኔ? ምንም። ሴት ነኝ የሁለታችንንም ሆድ መሙላት አልችል። በደህናው ጊዜማ የንግሥት ጣይቱ ወጥ ቤት ነበርኩ። አይ ጣይቱ እናቴ። አንቺም አፈር ይበላሻል። ንግሥት ገና ጠዋት ብቅ ሲሉ ‘የት ናት እናኑ? የእኔ ጎራዳ’ ይላሉ። ‘ያቺ አገጫም የታለች?’ እንደ እኔ ጎረድረድ ያሉ ሴትዩ ነበሩ። ‘ለእሳቸው’ ለሚኒሊክ ማለታቸው ነው ‘ቁርሳቸውን አድርሺ መመለሻቸው ነው’ ይሉኛል። ሁልጊዜ ፊቴን ያዩና ወደ ማታ ተሆነ ‘ደክሞሻል?’ ይሉኛል። አልደከመኝም ካልኳቸው ‘በይ ትንሽ ንፍሮ ቢጤ ይዘሽለኝ ነይ ተብርዝ ጋር’ ይሉኛል። እመቤት እኮ ናቸው። ምላሳቸው ግን አይጣል ነው ተከፉ። መኝታ ቤታቸው ይዤላቸው እሄዳለሁ … ንፍሮውን በቁልቢጥ ብርዙንም በቀንድ አድርጌ። ገና እሱን መሬት እንዳስቀመጥኩ ይጠቅሱኝና ጋቢያቸውን ወረድ ያደርጋሉ። ድንቡሽ ያሉ ናቸው። ተዛ ጀርባቸውን አክላቸዋለሁ። … ምግብ አቅራቢያቸውና አካኪያቸው ነበርኩ። አንገታችው ትዝ ትለኛለች። አንገታቸው በመወፈራቸው የተጣጠፈች ሥጋ ነበረች። ‘ማከኩን ተወት አድርጊና እሱን እሺኝ ሳይጣምነኝ አልቀረም’ ይሉና እሱን ሳሽላቸው በቀስታ ያንጎራጉራሉ። ‘ልጅ እያለሁ እዘፍነው ነበር’ ይሉኛል። ወረሂመኑ ለነበሩ ጊዜ … ለመሆኑ ወረሂመኑ የሚባል ቦታ ሰምተሃል?

(አልመለሰላትም። እንደሚያይ ሁሉ ወደ ተቀመጠበት ዞር ትልና ‘ታየዋለች’ … ወደ ተጋደመችበት ሄዶ ከአፏ ዳርና ዳር ቆበር በኩታዋ ጠርጎ ያነሳላታል … አሁንም አሁንም)

አላልኩም አላልኩም አገራችሁን ትንቁዋታላችሁ እንጂ የት ታውቁዋታላችሁ። ወረሂመኑን የመሰለ አገር አታውቅም … አውሮባ ምናምን ቢሏቸሁ ይሄኔ ታታታታ ታደርጋላችሁ። የዚህን የጣይቱን ነገር ለአንተ ብቻ ነው የምነግርህ። ወሬ ምን ይታወቃል ማን ጋ እንደሚደርስ። እስተ ዛሬ ንጉሡ እኮ አለቀቁኝም። ንግሥት ጣይቱ ጀርባቸውን ያሳክኩ ነበር ተብሎ ቢጣፍስ? ሁሉ በየቤትዋ ታሳክካለች እኮ። ተፈሪ ጣይቱን ያሸነፋቸው እኮ ስም በማጥፋት ነው። እንደ ወንድ መቸ ችሎበት። ወንድ ቢሆን ኖሮ እዝህ ለሰላቶ ለፋሺስት ትቶን ይሄድ ነበር? ወንድ ሆኖ ክንድ የለውም። ክንድ ተፈረንጅ ሊበደር ይሄዳል። ለአንተ ብቻ ነው የምነግርህ። ጣይቱ አምባላጌ ሲያዋጉ ባዶ እግራቸውን ወንዶች ፊት ፊት ሲሮጡ ተሩቅ ጥልያን አይቶ መትረየስ ቢያዘንብባቸው ይህቺ የግራ እግራቸው ትንሽ ጣት ተቆረጠች። በቃ የለችም። አራት ጣት ነው ያላቸው። አንድ ጎበዝ እላያቸው ላይ ወድቆ ነው ያዳናቸው። ጎናቸውን ደሞ ሲወድቁ ጫንቃቸው ላይ የተሸከሙት የዓላማ ሰንደቅ ወግቶአቸው አሁን ድረስ እስቲሞቱ ያማቸው ነበር። እዚህ ከብብታችው ዝቅ ብሎ። ገና ብርድ ሲሆን ውሃ አሙቄ ጨርቅ ይዤ ማደሪያቸው እሄዳለሁ። አንዳንዴ ‘እሱን ተይ’ ይሉኝና በጋቢ ተከናንበው ይቀመጡና እኔም ተከናንቤ አቅፋቸዋለሁ። ‘የሰው ሙቀት ይሻላል’ ይላሉ። ምን ላይ ነበርኩ ዓለምዬ? … አድዋ ዘመቻ ጊዜ ከተማ ጠባቂና ፀሎተኛ ነበርኩ። በቀን ሶስቴ እንፀልያለን። አሸነፍን ሲባል ልጄ ተንጦጦ ባቡር ጣቢያ በእልልታ ቀለጠ። ዛፍ ተቃጠለ። ደን አለቀ ልበልህ። ምን ላይ ነበርኩ ዓለምዬ?…

(እምን ላይ እንዳቆመች ሊነግራት አልፈለገም። በዝምታ በተመስጦ ግርማው ያልጠፋ ረዥም ፊቷን ማየት ብቻ ነው የሚፈልገው። ጨዋታዋን ያቆመችበት ጠፍቷት “በል ሂድልኝ የሚቀጥለው ሳምንት ና” ብትለውም ይወዳል። የቆመችበት እንደጠፋው ሁሉ ዝም አላት)

… አዎ የጀመርኩልህ? ምን ነበር? አዎ። ስለ ዱባ ወጥ። ስለ መሐሌ ወለላ። ሚኒሊክ አያውቁም። ንግሥትነታቸውን እስቲነጠቁ ድረስ እስከ ሺህ አስር እስከ ሺህ ዘጠኝ መቶ አስር ድረስ ዱባ ወጥ ለጣይቱ መስራቴን ወጥ ቤት እንኳን አያውቅም። አየህ አላዛር ሞጆ በነበርኩ ጊዜ እንዲህ ሆነ። እረሳለሁ እንጂ የማይረሳ እረሳለሁ። የማይረሳ። ነሲቡ አሳዳጊዬ ሞተው እሳቸውን ቀብሬ ስመለስ ደብረዘይት ቢሾፍቱ ከመድረሴ በፊት ዝናብ ጣለ። የሚገርም የሚገርም ዝናብ። ምን? በለኝ። ምን? በለኝ። የተሰባበረ ዱባና የዱባ ዘር። እንደውልህ ከሰማይ እየመጣ የተፈናጠጥናቸው ከብቶች ላይ አናታችን ላይ አይለጠፍብን። ቀና ብዬ ሳይ ወርቅ የመሰለ ቢጫቴ ደመና። የዛ ዓይነት ደመና አይቼ አላውቅ ከተወለድኩ። ‘ሚካኤል ከዚህ ካወጣኸን በየወሩ ጠበል አደርግለሃለሁ’ አልኩት። ቁጥቁዋጦ ግራር ነገር ፈልገን ተጋረድን። የዘነበው ብዙ ቦታ አልነበረም። እንደው እኛ ጉድ ሊያሳየን ይሁን እንጃ። እንደው እኮ ሶስት ቀበሌ ቢዘንብ ነው፣ ቢሾፍቱ ስንደርስ ‘እህ’ አልን የዛን አገር ሰዎች። ‘በሉ አትቀልዱ’ አሉን። ‘እንዴ ከሰማይ ዱባ ዘነበ’ ስንላቸው እብድ አደረጉን። አብረውኝ የነበሩ መንገደኞች ነበሩ አንድዋ ጣይቱ ቤት ልትወስደኝ አንድዋ ዘመድ ጥየቃ ሞጆ ደርሳ የዓመቱ አቦ መሰለኝ ትዝ አይለኝም ስገምት ማለቴ ነው፣ እንደው እምቢ ሲሉ እኔ በመቀነቴ ርጥቡን የዱባ ፍሬ ሰብስቤ አዲስ አባ ገባሁ። አንድ ቀን መቀነቴን ላጥብ ስል ረስቼው ኖሮ … የቤተመንግስት ሥራ ጊዜ መች ይሰጣል? ማስተዳደር በለው፣ የመኩዋንንቱ ሆድ አያርፍም። ሁልጊዜ የሚበላ ያስፈልጋል መቆያም ይሁን። ጠዋት መስራት ማታ መስራት፣ እና በመቀነቴ እንደያዝኩት ዘሩ ሳይበላሽ ወር ከርሞ አገኘሁት። ያኔ እንደ ዛሬው ልብስ በየቀኑ አይታጠብም፣ ሳጥብ ደርቆ ልፋጩ መቀነቴ ቋጠሮ ውስጥ ተገፎ ረግፎ አገኘሁት። ሲሸት ነበር አንድ ሰሞን መተኛዬ ስገባ ይሸተኛል። ግን ልብ ሳልል እንጂ። እሱን ዘር ወሰድኩና ቤቴ ግቢ ሰፊ ቦታ ነበር፣ እዛ አጥር ሥር ፎገል ፎገል አድርጌ ቀበርኩት። ዝናብ ነበር ትዝ ይለኛል፣ ወሩን እንጃ … ምን ትዝ ይለኛል ወሩ። ዝናብ ነበር። ‘ያ ዱባ ከሰማይ የወረደ ዱባ ነው’ ብዬ ስናገር የሚያምነኝ አልነበረም። ተጫዋች ነበርኩ፣ እና ጨዋታ ይመስላቸዋል። ቀምሰው ዱባዬን … ቀምሰው እንኩዋን አያምኑኝም ነበር። ልጄ ሕዝባችን የተለየ ሕዝብ ነው። የማያዩትን የሚያምኑ፣ ያዩትን የማያምኑ ሕዝቦች ነን። ትደርስበታለህ። የማወርስህ ብችል እሱን የዱባ ዘር ነበር። ጥልያን ሲመጣ ትቸው ሄድኩ። ቤቴ የተሰጣቸው ባንዶች ቆፍረው ሌላ ነገር ሎሚና ወይን አብቅለውበት ደረስኩ። እቴጌ ጣይቱ ‘ዘር ስጪኝ’ ብለው እሳቸው ብቻ ያመኑኝ ወሰዱ። ያኔ እንጦጦ በቁም እስር እያሉ። ቁም እስር ታውቃለህ? ቁም እስር ማለት እንግዲህ አሳሪዎችህ እነሱ ዳገት ላይ ተቀምጠው አንተን ሜዳ ላይ ይለቁሃል እና ‘እንዳሻው ለቀቅነው’ ይሉሃል እሱ ቁም እስር ነው። ግሼን አምባም አይደለ። ማጣት ነው ያለበት። አውቆ ማጣት ነው። የዱባ ዘሬን በወሰዱ በሳምንቱ ጣይቱ እናቴ ከእንጦጦ ጠፉ። የተባለው ሞቱ ነው … እና ብፈልግ ብፈልግ መጠጫቸው ካቦና ያቺ የዱባ ቋጠሮ ለመሆኑ ካቦ ታውቃለህ? መጠጫ ጥዋ ነገር … የት ነበር ያቆምኩት ልጄ? የተነሳሁበት ይጠፋኛል። ለምን ይሄን አወራሃለሁ? የተነሳህበት እንዳይጠፋህ ነው ልጄ … እናልህ እስኪጠፉ እንደተባለው እስኪሞቱ ድረስ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ አብረን ከንግሥት ጋር ዱባ እንበላ ነበር። ዛሬ የተረፉ ወጥ ቤቶች አይጠፉም ቢጠየቁ ይህቺን የእኔንና የጣይቱን ሚስጢር አያውቁም። ማታ ማታ ወጥ ቤት ሁሉ ሲተኛ ቀን ደብቄ ያመጣሁትን ዱባ እልጥና አሳምሬ እሰራላቸዋለሁ። ጣታቸውን የሚልሱት ተእኔ ጋር ነበር። ምግብ ሲበሉ ‘ለመሆኑ የእናኑ እጅዋ አለበት?’ ይላሉ። የለበትም ተተባሉ ‘በሉ አስቀምጡትና ሂዱ ተራበኝ እበላለሁ’። አይበሉትም። ንክች። ‘ለመሆኑ የት ሄደች’ ይሉና መታመሜን ያውቁ የለ ይነገራቸውና መድሃኒት የሚያቅ ቤቴ ይልካሉ። አንድ ጊዜ ቅቤ ሳነጥር ከባድ ምች መቶኝ ሁለት ቀን ተኛሁ። በሁለተኛው ቀን ቤቴ መጡና እዝሁ ጎላ የደሃ ጎጆዬ ግማሽ ቀን ውለው ዳማ ከሴ ቆርጠው፣ አጥሚት ሰርተው አልጋዬ ጎን የተኛሁበትን ቁርበት ወርውረው ጨርቅ አንጥፈው … ዛሬ ድረስ አለ ያ ጨርቅ … ትንሽ ሲሻለኝ በበነጋታው መጥተው ገላዬን አጥበው … ማን ነበረኝ? ማን? ይሄ ሁሉ ልጄ በንግሥት እጅ። ዛሬ እንዲያ የሚያደርግ ንግሥት ቀርቶ እንደው ተራ ሰውስ አለ? ችሎታ ብላችሁት … የክፋት ችሎታ …

(ፈገግ አለ። የሚያስፈግግ ነገር አልነበረም። ስለ ንግሥት ቀባጢሶ ማውራት ወይም መስማት አይፈልግም። አሁን ወደ ውጭ መሄድ ይፈልጋል። ስታወራው ሳይቋርጥ የሚያየው ነገር ጠይም ፊቷን፣ ትልቅ አፏንና መውጫ በሩን ነው። ሲኒማ መግቢያው ጊዜ ደርሷል። ትንሽ ከቆየ ሊዘጋ ይችላል። ሊሞላ ይችላል። ፒያሳን ያስባል … አምፒር፣ የቡና በወተት ጠረን፣ የባቅላባ ጠረን፣ የእርጎ ጠረን፣ በቁንጅናቸው የሚያማልሉት ትናንሽ የጂንስ ቤልቦተም ሱሪዎች ያደረጉ ያኮረኮሩ ልጃገረዶች)

… አንድ ጊዜ ተአድዋ ዘመቻ በዋላ ትልቅ ግብር ያዘጋጃሉ። የእኛ መኩዋንንት ጦር ስላሸነፈ ብቻ ሁሉን ነገር ያወቀ ይመስለዋል። ‘መኩዋንንቱን ሁሉ እስቲ የሃበሻ ሴትን ሙያ እናሳየው’ ብለው ጣይቱ ምን የመሰለ ድግስ ያዘጋጃሉ። ከብት አለቀ ልበልህ። ተአምስት ሺህ በላይ ከብት። ብዙው መጋበዝ የሚመስለው ሥጋ ብቻ ነው። በመጨረሻ ዕለት ንግሥት ጠጋ አሉኝና ‘ለመሆኑ ያንን ዱባሽን በትልቁ ለብዙ ሰው መስራት ትችያለሽ?’ ይሉኛል። ተጠራጠርኩ። ‘እንዴ አንቺ ጎራዳ እናደርገውና እምቢ ካለን ዝም ነው’ አሉ … ሂሂሂሂ …

(ሳል ስላጣደፋት ከተኛችበት በክርኗ ደገፍ ብላ ተነሳችና ባዶ አየር ውስጥ በጭንቀት አፈጠጠች። ተረጋግቶ የነበረው ፊቷ ቁጣ እንደነካው ሁሉ ተኮማተረ። የምትስል ሳይሆን ብስጭት የሚሰማት ትመስላለች። እንደ አጋጣሚ በእጁ የያዘውን የኩታ ጫፍ ወደ አፏ ወሰደና ከአፏ ወደ ውጭ እየተገፋ የሚፈናጠቀውን ምራቅ መቅለብ ጀመረ። ከመሃል ትንፋሽ ስላጠራትና ዓይኖቿ ስለፈጠጡ ደንግጦ ለእርዳታ ሠራተኛዋን ሊጠራት ሲል መሳልዋን አቁማ ዝም አለች። የሚፈራው ይሄን ነው … )

…. ሲያምር ተንግሥት ጋር መዶለት። ዱባ ወጥ ሰራነ። አስቸገረ። አይ ሲጣፍጥ እቴ … አስቸጋሪው ደሞ በሰታቴ የተሰራ ያ ሁሉ ዱባ እንዴት ሳይፈርስ ተምድጃ ይወጣል ነው። ቀላል ይመስላል። እኔ እናትህ ማማሰያ ሳላስገባ እተጌን አስደሰትኩዋ። ጠረኑ ራሱ ‘የዛሬስ ወጥ ምን ቅመም ቢገባበት ነው?’ ተባለ። እኔና ንግሥት እንተዋወቃለን። ተራራው ላይ እንጦጦ ሳትወጣ ታች እዛ አሁን ሰፈራችሁ ያለበት ገደል ጋ ይሸትሃል … ስዋሽህ አይደለም። መኩዋንንት ተሰብስቦ ሲበላ ‘ምንድነው’ አለ? ‘የምን ሥጋ ነው? በምን ሰራችሁት?’ ሁሉ ተበልቶ አልቆ ‘ዱባ ነው’ ተብሎ ቢነገራቸው ‘አሁን ተሥጋው የበለጠ ጥሞአችሁ የበላችሁት እሱ ዱባ ነው’ ሲባሉ አላመኑም። አላዛር ሙት አላመኑም። እተጌ ሲናገሩአቸው አላመኑም። አምነናል ያሉትም ‘እንዴ ታዲያ መኩዋንንቱን ዱባ ታበያለሽ እንዴ? የሚበላ ጠፋ?’ አሏቸው። ብቻ ዱባ መሆኑ ሲነገራቸው ስለበሉት ነገር ማውራት አቆሙ። በዋላ ሲያስሩአቸው ‘ይህቺ እኮ ትንቀናለች ያ ዱባ ትዝ ይላችሁዋል?’ እያሉ ነበር። ‘መኩዋንንቱን ንቃ ዱባ ደብቃ የምታበላ’ እያሉ። እኔ እናኑ እውነቴን ነው የምልህ የዚያ ወጥ ጠረን ተማድቤት ቀርቶ ተራራው ራሱ ላይ ‘ስንት ጊዜ ምን የሚያምር ነገር ይሸተናል’ እየተባለ። ያን ሰሞን ቢበሽቁ እተጌ መኩዋንንቱን አዘፈኑባቸው።

አገሬን ወዳለሁ ሕዝቤን እወዳለሁ

አፈርዋን ዱባዋን ጠብሼ እበላለሁ

ደም አፍሰው ሥጋ ቢነጩት ቢነጩት

ልብ ይደፍናል እንጂ አይሆን ለሰው አንጀት

የጦብያ ሴቶች ሙያቸው ትላልቅ

በጦር ሜዳ ይሁን በማድ ቤት እናስንቅ

እናልህ እሳቸው በተፈሪ ሲታሰሩ ማድ ቤት የነበርነውም ተበተንን። እኔ በዋላ በዋላ ታዘነልኝና ባሌም ስለ ሞተ ዘውዲቱም ስለምትወደኝ ትንሽ መሬት ተቆርጦልኝ … አንድ መኩዋንንት ናቸው አሉ ‘ሴት ልጅ አትበድሉ’ ብለው ተከራክረውልኝ … ጣይቱ የቁም እስር ባሉበት ተዚህች ዓለም እስቲያልፉ ድረስ ተእኔ እንዳይገናኙ ቢከለከሉም አንዳንዴ እየጠሩኝ በአቅራቢ በአቅራቢ … እንግዲህ እኔ ተፈርቼ መሆኑ ነው … ከጓሮዬ ቀንጥሼ ዱባ ወጥ ሰርቼ እወስድላቸዋለሁ ወይ እልክላቸዋለሁ … ‘አረፉ’ ሲባል አለቀስኩ ልጄ … አሁን እኔ ኖሬ እሳቸው ይሞታሉ? የእግዜርን ነገር አየህ። አሁን ዘጠና አለፈሽ እባላለሁ ግን እመቤቴ እሳትዋ በአጭር ተጠለፈች። እግዜር ሚስጢሩ አይገባም …

(ብዙ ነገር ቢረሳም ይሄን አይረሳም። አባቱ ብርሃነመስቀል እናኑ ጋ አድርሶት ወደ ሚሄድበት ሊሄድ ታኑስ መኪናውን ግቢ አቁሞ፣ ዝናቡን እያማረረ፣ ሐምሌን እየረገመ፣ በጫማው የሰበሰበውን ጭቃ ድንጋይ ላይ ለመጥረግ ሲለፋ፣ አላዛር አባቱን ትቶት እየሮጠ ወደ ቤት ውስጥ ይገባል ……… ከፊት ለፊቱ ትራስ ተደግፈው ሶፋ ላይ ጋደም ያሉት እናኑ ላይ ወደቀ። እናኑ አላዛር ከረሜላ ያመጣልኛል ብለው የመጨረሻዋን የማር ከረሜላ አፋቸው ከተው እየመጠጡ ነበር። ያን ቀን ከረሜላ አልገዛም። ጭናቸው ላይ ተቀምጦ እንደ እንቦሳ እየተገላበጠ፣ አባቱ ገንዘብ አልሰጥህም ብሎት ከረሜላ ስላልገዛ ከሚበሉት ከረሜላ እንዲሰጡት ይጠይቃቸዋል። ‘እምቢ አፌ ከገባ አልሰጥህም’ ይሉታል። አልሰማም። ጣቶቹን አፋቸው ውስጥ ከቶ ከረሜላውን ለማውጣት ብዙ ለፋ። እምቢ ቢሉትም ጭናቸው ላይ በጀርባው ተኝቶ ካልሰጠሽኝ እያለ መነዝነዙን ቀጠለ ……… አላዛር ጭናቸው ላይ እንደ ቡችላ ሲሆን ሲያዩት፣ የወርቅ ሐብሉ ከነመስቀሏ የሚያምር አንገቱ ላይ ተልፈስፍሳ ሲያዩት፣ ወተት የመሰሉ ትናንሽ ጥርሶቹና እህል ገብቶበት የማያውቅ የመሰለ የአፉን ጽዳት ደሞ የቆዳውን ልስላሴ ሲያዩት … ብቻ ሁሉ ነገሩ ስቧቸው፣ የወለዱት ሁሉ መስሏቸው፣ ወደ አፉ እንደሚስሙት ሁሉ ቀርበው በምራቃቸው የመለገውን ከረሜላ በተከፈተ ለፍላፊ አፉ ጠብ አደረጉለት። ዓይኖቻቸውን በእርካታ ጨፈኑ። ልባቸው የምትቆም መሰላቸው። አላዛር በአፉ የገባው ከረሜላ አስደስቶት ያሉበትን ክፍል በትንሽ ልጅ ሳቁ ሞላው ……… አላዛር ይሄ ሲታወሰው ለእናኑ የዱባ ተረትና አይቶትም ይሁን ቀምሶት የማያውቀው የዱባ ወጥ ጣዕም አፉ ውስጥ ይሰማዋል። ከረሜላ አይደለም ምንም አይደለም ራሱንም ይጠይቃል እንዴት ያልቀመስኩት ትዝ ይለኛል? እንዴትስ ይጣፍጠኛል?)

.

አዳም ረታ

.

One thought on ““ፍቅር እና ሆሄ” (ልብወለድ)

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s