“ማሪበላ” (ልብወለድ)

“ማሪበላ”

ከሙሉጌታ አለባቸው

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

… ዞብል። ዞብል። ዞብል። …

ስጠራው አፌ ላይ ቅልል ስለሚለኝ ነው መሰል ይሄን ቃል እወደዋለሁ። የምወደው አባቴ (እሱም ከልጆቹ ሁሉ የሚወደኝ) የተወለደበት ዛፋማ አገር ስለሆነ፤ ዛጎል ከሚለው ቃል ጋር  ስለሚመሳሰልብኝም ይሆናል። እንቆአርያ እወዳለሁና። ይሄ የዞብል እና የዛጎል ድምፅ መመሳሰል መርቶኝ ሳይሆን አይቀርም ያኔ ዛጎሎች ከአሸንጌ ሐይቅ የሚለቀሙ ሳይሆኑ ከዛፍ የሚሸመጠጡ ቀንድ አውጦች ይመስሉኝ ነበር። አንዳንዴ በሥራ ፈት ምናቤ አያይዤ የማስኬደው የአባቴ ትረካ ያነሳሳው የሀሳቤ ባቡር እነኚህን የቃላት ፉርጎ አስከትሎ ይነጉዳል፡ ዞብል፣ዛጎል፣ማዘል፣ወተት፣ጸጉር፣ማር፣አርሒቡ፣ኮንሶ፣ሰተት፣ፍቅር

.

ዞብል፣ዞብል፣ዞብል …

ሄጄበት የማላውቀው የዞብል ሰፊ ምድር የጃምዮ፟ ሰብል ለብሶ ይታየኛል።  አናቴ መሀል የምታቀልጥ ፀሐይ እንደ ጋለ ቆብ፣ ጥላ ሞቴ እንደ ጥቁር ምንጣፍ እግሮቼ ሥር፣ በውሃ እጦት የተሰነጣጠቀ ምድር ላይ፤ እኔ በማሽላ ማሳ መካከል እንደ መንድብ ሰንጥቄ ሳልፍ ግራና ቀኝ እየታከኳቸው የሚያልፉ ሞተው የደረቁ ቅጠሎች እየተንሿሹ። የጎመራ የማሽላ ቅጠል እንደ አፋር ጊሌ በሰላ ጠርዙ ስስ ቆዳዬን “እያረደኝ”። (ታናሽ ወንድሜ ቆቦ አካባቢ የሚኖር አንድ የአባቴ የቅርብ ዘመድ ያመጣልንን የጥንቅሽ አገዳ ሲያኝክ ልጣጩ አውራ ጣቱን ሰንጥቆት ደሙ እየተንጠባጠበ ሲያለቅስ ምን እንደሆነ ብጠይቀው “ጥንቅሹ አረደኝ” እንዳለኝ ያክል ባይሆንም)።

.

ዞብል፣ዞብል፣ዛጎል

ከደረታቸው መሃል ለመሃል ለሁለት ተከፍለው፣ አካፋያቸውም ውሽልሽል ስፌት እንደፈጠረው ሽብሽብ መስሎ፣ ወይ በጥቁር ጭራ እኩል ቦታ ላይ ተሰፍተው እንደተያያዙ ሁለት የእርጎ ቁራጮች። ታናሽ ወንድሜ ከሚታዘልበት በለፋ ቆዳ ከተሰራ ባለ ቡናማ ቀለም አንቀልባ ግርጌ በቀጫጭኑ ተተልትሎ እንደ ነጠላ ዘርፍ ከተንዘረፈፈ ሌጦ ጫፍ ላይ የተንጠለጠሉትን ዛጎሎች በልስልስ ጥፊ መታ መታ እያደረግኩ ሆጨጭ ሲሉ ስሰማ የሚሰማኝ መረጋጋት ወደር አልነበረውም። ጡት አስጣዬ በጨዋታ ደክሞ ሲነጫነጭ እናቴ ሰርኬ እሹሩሩ ብላ ልታስተኛው ስትፈልግ በመጀመሪያ ልዩ ስሜን በልዩ ቁልምጫ ጠርታ አንቀልባውን እንዳቀብላት ትጠይቀኛለች፣

“…ይሄ ልጅ ተብሰከሰከ… እንቅልፉ መጣ መሰል። እስቲ ያን ማዘል አቀብለኝ”

.

ዛጎል፣ማዘል፣ወተት

እኔንም ያሳደገ ያ ማዘል ከፈፉ በጨሌ ያጌጠ ነበር። አንድ ዛር አንጋሽ አንገቱ ላይ የጨሌ ማተብ አንጠልጥሎ ስላየሁ እነኛን ደቃቅ ዶቃዎች አልወዳቸው፣ እፈራቸውም ነበር። ከዚህ አንቀልባ ወርጄ ገና ወፌ ቆመቼን ሳልጨርስ ከሥሬ ለተወለደው ታናሽ ወንድሜ ተራውን አልለቅም ያልኳት እማ፤ ጡቷን እንደ ልሃጭ በሚዝለገለግ የእሬት ደም ለቅልቃ ስታቀርብልኝ እየመረረኝም ቢሆን መለግለጌን አልተው ብላት ከዞማዋ አንድ ሁለት ሰበዝ ነጭታ፤ የጡቷ ጫፍ ላይ ጠምጥማ “በላህ! በላህ!” ስትለኝ…. አሁን ሳስበው ያኔ ይመስለኛል ለጭገር ያለኝ ፍርሃት የተፀነሰው።

.

ማዘል፣ወተት፣ጸጉር

መፍርሄ ጸጉር ሳያጠቃኝም አልቀረም። በብብቶቼ ሁሉ ጸጉር ማብቀል ከጀመርኩ አንስቶ በየሳምንቱ መንትዮቹ ጸጉር ቆራጮች ምናሴ እና ኤፍሬም ጋ እገኛለሁ። ገና የፂም ቁጥቋጦ ፊቴ ላይ ኑግ መስሎ መፍሰስ ሲጀምር ዘወትር ጠዋት መስታዎት ፊት ቆሜ ሙልጭ አድርጌ እላጫለሁ። ብችል ቅንድቤንና የዐይን ጭራዬን ሁሉ ከሥራቸው ነቅዬ ብጥላቸው በወደድኩ።

.

ወተት፣ጸጉር፣ማር

ያደግኩበት ቤት ዘወትር በአባቴ ወዳጆችና በእናቴ ቡና አጣጮች የተሞላ መንገድ ዳር ያለ ቤት ነው። ቤታችንን ከሚያዘወትሩ የአባቴ ወዳጆች ሁሉ የምወደው ዳውድ የተባለ ሹፌር ነበር። ነጭ ፒካፕ መኪና የሚነዳ። ለሽርሽር የሚወስደኝ። ከእማማ ዘምዘም ጣፋጭ የሰሊጥ እንክብል/ፎፎን የሚገዛልኝ። የሰፈሬን ጣፋጭ ጥምዝ ኬኮችም የሚያስገምጠኝ።

ከዳውድ የሚያስጠላኝ ነገር በሚያጎፍረው ጢሙ ፊቴን ሲነካኝ ነው። ማር ጸጉር ከነካ ያሸብታል ይባል የለ? ዳውድ ሳሕን ሙሉ ኑግ ከመሰለው ጥቁር ጸጉሩ ተለይታ ከግንባሩ ከፍ ብሎ በግራ በኩል የተቀመጠች ትንሽዬ ጨረቃ የመሰለች ክብ ሽበት ነበረችው። ልክ ጨረቃን በቴስታ እንደመታ ሁሉ።

ከጋሽ አቦሰጥ ቤት በየዓመቱ የሚላክልንን የጥቅምት ማር ውስጥ ልክ እንደሞተ ንብ ተዘፍቄ ስወጣ አግኝቶኝ ወለላ የለበሰ ፊቴን በጸጉሩ ሲዳብስ የነካው ይሆናል ብዬ አስብ ነበር።

.

አርሒቡ

ከገነቴ ከተማ ነዋሪዎች አባቴን የማያውቅ ያለ አይመስኝም ነበር። ከሁሉ ጋር አርቦሽ የሆነ፣ ሁሉን የሚጋብዝ፣ ሰውን ሁሉ በእኩል ዓይን የሚያይና ሰው ሁሉ የሚወደው አባት ነበረኝ። የግራ እጁ የማርያም ጣት ላይ የሚያስራትን ባለ አረንጓዴ ፈርጥ የብር ቀለበት እያሻሸ “የደጃች ብጡል ዘር ነኝ” ስለሚል አንዳንዴ የከተማውን ሰው ሰብስቦ ግብር ማብላት ሁሉ ሳያምረው አይቀርም እያልኩ አስባለሁ። አውራ ጎዳናው ዳር ያለው ቤታችን ውስጥ ቁጭ ብሎ ኮረፌውን እየጨለጠ ከግራ ቀኝ ሲመላለሱ ከውስጥ ሆኖ ጎራ እንዲሉ ይጋብዛል፣

“አርሒቡ!”

“እንኳንም ዳገቱን አልፈን ግራካሶን ወጣን አንተዬ፤ ይሄን የእናት ጡት የመሰለ ኮረፌ ከየት እናገኘው ነበር ነውኮ የሚያስብለኝ ጃን” ይላል በማርማላት ጣሳ ለእንግዳው እየቀዳ። ይሄ አባባሉ ቃል ሳይቀየር በመደጋገሙ ጭንቅላቴ ውስጥ እንደሆነ የተረሳ የልጅነት መዝሙር በሥራ ፈትነት ተጋድሞ አሁን ድረስ ሲገላበጥ ይሰማኛል። ወዲያው ደግሞ ቀጥሎ “ያዝ በል ይቺን ያዝ” ይላል ጣሳውን ሲያቀብል።

ታዲያ አባቴ “አርሒቡ” ባለ ቁጥር “አትራቡ!” ብሎ እጅ ነስቶ የሚያልፈው ጥቂት ሰው ብቻ ነበርና አንዳንዴ እናቴ ግብዣ አበዛህ ብላ ስታማርር “ሁሉ በዚህ ዓለም ቀሪ ነው፤ ይዘንው አንሄድ” ይል ነበር። ብቻ አንድ ወይንጠጅ ቆብ የሚደፉና ሁሌ ጥቁር ጃንጥላ የሚይዙ፣ መስቀል ሲያሳልሙን ወርደን ጉልበታቸውን ካልሳምን የጽንሃ ዥዋዥዌ ባቆረፈደው እጃቸው ደረቅ ቁንጥጫ የሚያቀምሱን እጃቸው ከርቤ ከርቤ አፋቸው ጌሾ ጌሾ የሚሸት አባ ገብረ ኪዳን የተባሉ የንስሐ አባታችን የሆኑ ቄስ ጋር ሲደርስ ጋባዥነቱ ይጠፋል። ሆደ ሻሹ አባቴ ቄስ እንደማይወድ በግልፅ እየተናገረ “አባ ገብረ ኪዳን ውሽማሽ ናቸው መሰለኝ፤ እግሬ ወጣ እንዳለ አድራሻቸው በድንገት ወደዚህ ቤት ይለወጣል” እያለ ሰርኬን ይተርባል። “አማረልኝ መስሎሃል” ትላለች ከጓዳ ውስጥ።

የቄስ ደንብ ነው መሰለኝ አባ ገብረ ኪዳን ጥቅስ፣ ግዕዝና አግቦ መናገር ያበዛሉ። ቆለኛው አባቴ ነገሩ ሁሉ ፊት ለፊት ነው። የማይጥመው ነገር ካጋጠመው እዚያው ቦታው ላይ በግልፅ ዐማርኛ እንዳልጣመው ተናግሮ ያልፋል። አንድ ቀን ግን በሚገባቸው ቋንቋ ላናግራቸው ብሎ ነው መሰል የሚደነቃቀፍ ግዕዝ ሸምድዶ ተናገራቸው።

የዚያን ዕለት ትዝ ይለኛል መልካ-ቆሌ ከተባለች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቴ ተዛውሬ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ወደ ተባለ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የገባሁበት የመጀመሪያ ቀን ነው። የጠዋት ፈረቃ ትምህርቴን ጨርሼ መጥቼ አባቴ ጎን ተቀምጫለሁ። ትምህርት ቤቱን ወድጄው እንደሆነ እያሳሳቀ ይጠይቀኛል።

“ብቻ አልወደድኩትም ካልከኝ አማራጭ የለም ቄስ ትምህርት ቤት ትገባለህ። ከዚያ እንደዚህ ሰውዬ (ወደ እኛ ቤት አቅጣጫ የሚመጡትን አባ ገብረ ኪዳን እየጠቆመ) ፂምህን ታሳድግና ጥቁር ጃን ጥላ ይዘህ ቤት ለቤት እየዞርክ መቀላወጥ ነው”

“ኧረ ደስ ይላል። ግን ሩቅ ነው”

“በል እንደ ቅድመ አያቶችህ ፈረስ ይገዛልህና ደንገላሳ እየጋለብክ ወፋ ውጊያ ትወርዳለህ። ሃሃሃ። ልጅ እያሱን መስለሽ ልትገቢ ነዋ ተማሪ ቤትሽ። ማን እንበልዎ እርስዎንስ … ልጅ ማሪበላ እንበልዎት ይሆን?”

“ሩቅ ነው ነው ያልኩት።”

“መጋል ይሁንልህ ዳለቻ?”

“ምኑ?”

“ፈረሱ ነዋ ልጅ ማሪበላ … ፈረሱ” ተነስቶ በሹፈት እጅ ነሳኝ።

“አታሹፍብኝ” እያሳቀኝ ያናድደኛል።

በመንገድ ሲያልፉ አይቶ እንዳላየ ዝም ቢላቸውም ራሳቸውን ጋብዘው ገቡና ገና ቂጣቸው መቀመጫ ሳይነካ እንግዳ ተቀባይ ስለመሆን፣ የሆነ አብርሃም የተባለ የድንኳን ቪላ ውስጥ የሚኖር ሰውዬን እንደ አብነት እያነሱ ብዙ ብዙ አወሩ። ሰርኬ ልታስተናግዳቸው ጓዳ ውስጥ ትንደፋደፋለች። እስከዚያው ማዳረሻ እንዲሆን ብላ ኮረፌ ስትቀዳላቸው “አይ ወለተ ጴጥሮስ፤ ኮረፌሽ አምሮኝ ነውኮ የመጣሁት፤ ሌላ ሌላውማ የትም አለ” እያሉ ተቀበሏት። ከእሱ ፉት ብለው “ከእናት ጡት እንደሚፈስ ወተት ማለት ነው የኮረም ኮረፌ” ሲሉ ባልጠበቁት ፍጥነት አባቴ በነገር ያዛቸው።

“ደሞ ዘፈንም ያዳምጡ ጀመር?”

ሰርኬ ጆጉን አስቀምጣ ወደ ጓዳ ስትመለስ በአጠገቡ የምታልፍ መስላ ጎሸም አደረገችው።

“ምን አገሩ ሁሉ የሚለው ነው” በሀፍረት መለሱ

“ባለፈው ስንፈልግዎት ምነው ጠፉ ግን? እዚህ ቤት ውስጥ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ነበሩ ለወትሮው”

“ብፁዕ አባታችን ይመጣሉ ተብሎ ተኸር በዝቶብናል” ወደ ቤት ሲገቡ የነበራቸው ኀይል ደክሟል።

“አልመሰለኝም” አለ አባቴ። ቀና ብለው አዩት። “ለነገሩ ግዕዙ ጨርሶታል” አለና የሆነ ነገር ለማስታወስ ለአፍታ አሰብ አድርጎ እንዲህ አለ፣

“ኦካህንእንተሀገርከመርቄ

በጊዜማሕሌትበግዕወበጊዜመክፈልትዐንቄ”

ይሄን ተናግሮ ዞብል ድረስ የሚሰማ ታላቅ ሣቅ ሣቀ።

አንዳንዴ አባቴ “ውሽማሽ” የሚላት ነገር አንዴ ካጋጠመኝ ነገር ጋር ይያያዝ እንደሆነ አስብ ነበር። አይደር የተባለ ከተማ ውስጥ ሕጻናት ትምህርት ቤት ላይ ከአውሮፕላን ቦምብ ተጥሎ ብዙ ልጆች የሞቱበት የጦርነት ሰሞን ነበር። የሆነ ጄት ምናምን አየር ላይ ሲያንዣብብ ታይቷል ተብሎ በእረፍት ሰዓት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እንድንሄድ ተነግሮን አዲስ ያፈራኋቸው ጓደኞቼ እዚያው ቆይተን እንድንጫወት ቢለምኑኝም እምቢ ብዬ ወደ ቤት መጣሁ።

ሰርኬ እና አባ ገብረ ኪዳን ቤት ነበሩ። በጣም ተቀራርበው ቆመው ነበር። ደስ አይልም። እኔን እንዳዩኝ ደንገጥ ብለው መስቀላቸውን አወጡና አሳለሟት። ደበረኝ። የሆነ ደስ የማይል ነገር ግን ይሄ ነው ብዬ ላብራራው ያልቻልኩት ድብርት። ከዚያ እያሳለሟት ከእናቴ ጋር ብቻ ሲሆኑ እየደጋገሙ የሚናገሯትን ግዕዝ ተናገሩ።

“ብቻ ወለተ ጴጥሮስ፤ ʻኢያጸድቆ ለሰብእ ጸሎት እንበለ ፍቅርʼ ነው የሚለው መጽሐፉም”

.

ኮንሶ

በተወለድኩበት ዕለት ረቡዕ ለኀሙስ አጥቢያ ቤታችን ደጃፍ ያለች የኮንሶ ዛፍ ላይ የንብ መንጋ ሰፍሮ ይገኛል። ያው መቼም ያሉኝን ነው። ታዲያ ወንድ ልጅ የተወለደለት አባቴ ማርያምን ሲለማመኑ ያመሹ ሴቶች ከተዘጋ ላንቃቸው የሚወጣ ሻካራ እልልታቸው ተሰምቶ ሳያልቅ ይወጣና ሙክት ፍየል አርዶ ቆዳውን ይገፋል። ፍየሉን አንጠልጥሎ ብልቱን ለመገነጣጠል ወደ ኮንሶ ዛፏ ሲጠጋ የሚርመሰመሰውን የንብ ክምር ያያል። ከሴቶቹ አንዷን ጠርቶ የተገሸለጠ ፍየሉን እንድትጠብቅለት ያደርግና ጋሽ አቦሰጥ የተባሉ እማማ ዘምዘም ሰሊጥ ቤት ጎን የሚኖሩ ንብ አንቢ ሰውዬ ጋ ሄዶ ስለ ሁኔታው ያስረዳቸዋል። ጋሽ አቦሰጥም ጊዜ ሳይወስዱ ስፋቱ የመቻሬን ሜዳ የሚያክል የመሶብ ክዳን እና በትንሽዬ ቅል ወተት ይዘው ከተፍ ይሉና ደጅ ላይ ቆመው፣ እናቴን “እንኳን ማርያም ማረችሽ” ብለው፣ ወተቱን ወስከምቢያው ላይ ረጨት ረጨት አድርገው የሚተራመሰው የንቦች ክምር ላይ ይደፉታል። ትንሽ ቆይቶ ወስከምባዩን የያዙበት እጃቸው ከበድ ሲላቸው ቀስ ብለው በግራ እጃቸው ደግፈው ገልበጥ አድርገው ሲያዩ የንብ ዘር ሠራተኛና ድንጉላ ሳትቀር ግልብጥ ብላ እፊያው ላይ ሰፍራለች። ጋሽ አቦሰጥ አባቴን አመስግነው ቀፎ የሚሞላ መንጋቸውን ይዘው በቀስታ እርምጃ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።

አራሷ ጥቂት አረፍ እንዳለችም ብንያም የሚሉት ትልቁ ልጃቸውን ልከው “አደራ ይሄን ልጅ በማር አቀማቅሙት። ንግር ቢኖረው ነው እንጂ ንብ ቀፎዋን ትታ ከተማ መሃል ጎጆ ልስራ አትልም። አደራ” ከሚል ቃል ጋር ጭንቁላ ሙሉ ማር አስይዘው ላኩ። ከዚያ በኋላ በየዓመቱ ከዚያ ቀፎ ማር በቆረጡ ቁጥር “የጥቅምት ማር መድኀኒት ነው” እያሉ ስልቻ ሙሉ መላካቸውን አላስታጎሉም።

ከዚያ የነፍስ አባታችን አባ ገብረ ኪዳን “ተው ልጄ፤ ይሄ ነገር ቅዱሳንን መዳፈር ነው። ይቅርብህ” እያሉት አልሰማም ብሎ ስሜን ላሊበላ አለኝ። ቄሱ ቤት በመጡ ቁጥር (በየቀኑ ማለት ነው)

እስመኀበሀሎትዕቢትህየሀሎኀሳር

እስመኀበሀሎትዕቢትህየሀሎኀሳር

እስመኀበሀሎትዕቢትህየሀሎኀሳር

እያሉ ቢያስፈራሩት እንኳ አልተመለሰም።

ቆይቶ የእናቴ ጸጉር የእናቴን ጡት ካስጣለኝ በኋላ ስሜን ቀየር አድርጎ ማሪበላ አለኝ።

.

ሰተት

የኮረም ተወላጇ እናቴ ሰርኬ ቤታችን ግራና ቀኝ በሚኖሩ ቡና አጣጮቿ ተከባ ማንም ቡና አውቃለሁ የሚል ሁሉ የመሰከረላትን ቡና ከአቦል እስከ በረካ ታጠጣለች። ከቡናዋ ጣዕም የሥነ-ሥርዓቷ። እያንዳንዷን ነገር በዝርዝርና በእርጋታ ስታሰነዳ ትልቅ ድግስ ያለባት ትመስላለች። ታዲያ ሁሉን አዘጋጅታ ልትጨርስ ስትል “በል እስቲ ሂድ ቡና ጠጡ ብለህ ጥራልኝ ጎሽ” ብላ ትልከኛለች። ስመለስ ረከቦቷ ጀርባ እንደ ሰሊክ የሚሰራው እጣኗን እያጨሰች አድባር መስላ ተቀምጣ አገኛታለሁ። ውጭ ቆይተው ሲገቡ ለዓይን ያዝ በሚያደርገው ቤት ውስጥ በእርጋታ በሚተራመሰው የመዓዛ ጭጋግ መካከል ማየት የሚቻለው ድፍን ጨረቃ የሚያካክሉ ዓይኖቿንና እንግዶቿን በሣቅ የሚቀበለውን ልሙጥ ወረቀት የመሰለ ጥርሷን ብቻ ነው።

“እማማ አስረበብና እታለምን ሉሉን ጠርቻለሁ። ዘውዲቱ ቤቷ የለችም” አልኩ ወለሉ ላይ ከተጎዘጎዘው የኮንሶ ዛፍ አንድ ቅጠል ላነሳ እያጎነበስኩ።

“በላይነሽንስ ጠራህልኝ?”

“እማማ አስረበብ ቤት ነበረች”

“የኬጃ ሚስትስ?”

“እሷን አልጠራኋትም፤ ረሳኋት”

“ምን እያሰብክ ነው ከቶ ልብህ ካንተ ጋር የለለው? በል ሂድ አሁን ቶሎ ብለህ ጥራልኝ። ከጎረቤት ልታጣላኝ ነው? እንደው ምን ባደርገው ይሻለኛል እናንተ”

ረከቦቱ አጠገብ ባለግራም ሳሕን በመሰለ ስፌት/ቆለምሽሽ ላይ በግማሽ በኩል ፈንድሻ በግማሽ በኩል ደግሞ የጠመዥ ቆሎ ተቀምጧል። ቆሎዎቹ ላይ ደግሞ እንደ ባልጩት የሚያበራ ልጥልጥ ኑግ በሞላላ በሞላላ ቅርጽ ሆኖ ተጋድሟል። ይሄን የመሰለ የቡና ቁርስ እንዴት እንደምፈጨው እያሰብኩ የሐመልማል ዝንጣፊ እንደ ባንዲራ ከግራ ቀኝ እያውለበለብኩ የኬጃን ሚስት ልጠራ በምሬት ወጣሁ።

ስመለስ “እንደው ምን ባደርግህ ይሻላል፤ የቁራ መላክተኛ የሆንክ ልጅ” አለች። ትክክለኛውን ተረት የተረተች አይመስለኝም። ምክንያቱም፣ እኔ እንደሚመስለኝ ቁራው የቅጠል ዝንጣፊ ይዞ አልተመለሰም። በራሷ ውትወታ አባ ገብረ ኪዳን በግዕዝ ያስተማሩኝን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አጣቅሼ ላርማት ብሞክር ምን እንደምትመልስልኝ ስለማውቅ ዝም አልኩ። ጨዋታ ያሰኘኝ ቀን ቢሆን ግን፣ “ግንኮ ሰርኬ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቁራው አልተመለሰም። እኔ ግን ተመልሼ መጥቻለሁ” እላት ነበር።

መልሷንም ምንም ሳይዛነፍ፣ ምንም ቃል ሳይቀየር መገመት እችላለሁ። “አቤት አቤት፤ ወግ ወጉማ ተይዞልናል። ቁራ ደሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ሊሠራ ገባ? ቀባጣሪ!”

እማማ አስረበብ እና በላይነሽ መጡ። ጉበኑ ላይ ቆሜ በአጠገቤ ሲያልፉ በላይነሽ ኩበት ኩበት ትሸታለች። እንደ ድመት ግልገል ኩሽና ውስጥ ተወልዳ ኩሽና ውስጥ ያደገች መሰለኝ። የእማማ አስረበብ ቀይ ጥለት ያለው መቀነት ፊቴን ጠረገኝ። ከባዳ እጃቸው ደግሞ አናቴን። በጉርምስናዬ ከደባሪ ሚሲሌኒየስ ኤክሰርሳይስ ለመሸሽ ሳነባቸው በነበሩ ልቦለዶች በአንዱ ውስጥ እትዬ አልታየ የተባሉ ገፀ ባሕሪ ሲያጋጥሙኝ ምናቤ ውስጥ የተፈጠረው የእሳቸው ምስል ነበር። እማማ አስረበብ የራሳቸውን ስኒ ይዘው ባይመጡም ረከቦት ላይ ከሚደረደሩ ስኒዎች መካከል መርጠው ለራሳቸው የሰየሟት ሸራፋ ስኒ ነበረቻቸው። ሰርኬ ተሳስታ በሌላ ስኒ የሰጠቻቸው እንደሆነ “በራሴ ፍንጃል ካልሆነ ባልጠጣ ይሻለኛል” ብለው ይመልሳሉ።

“እንዴት ዋላችሁ?” አሉ እማማ አስረበብ/እትዬ አልታዬ። እጃቸው በጸጉሬ ተቦርሾ ተነሳ። ዓይናቸው ደከም ስላለ አግዳሚ ወንበሩን በዳበሳ አግኝተው ቁጭ አሉ። በላይነሽ አጠገባቸው ተቀመጠች።

“እንዴት ዋላችሁ? እህትሽ የለችም እንዴ በላይ?”

“አሁንማ የት ትሄዳለች ብለሽ ነው። ጦቢያ እንደሆነች አባራታለች። አብሽሎ፟ እየጋገረች ነው። ሳለ ጉልበቷ ሰርታ ትበላለች። ግርድና ነው ያስቀረችላት። እኔምኮ እማማ አስረበብ ጠርተውኝ አቋርጬ እንጂ የማክሰኞ ጠላ መች ፋታ ይሰጣል። ትመጣለች አሁን ወዲህ ስናልፍ ጠርቻታለሁ”

“እኔማ ያው የመባቻ ቡና ሰው ሲጎድል አልወድም። ደሞ ለወሩ አድርሳን። እንዲችው ሳንጎድል ደሞ ለወሩ ታድርሰን ብለን መለያየት ነው እንጂ”

“ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ” አሉ እማማ አስረበብ። የማይጨርሷት ተረታቸው ነች። “የዛሬ ወርማ ግንቦት ልደታ ናት። መንደሩ ሁሉ ተሰብስቦ ነው …”

“አይ … እንዴት ረሳኋት እናንተ … ያቺን ተናኘን ሳልጠራት”

“ተናኘ የትኛዋ?” በላይነሽ ግንባሯን ከስክሳ።

“እህ … ይቺ ተናኘ ናታ። የሳራ እናት”

“እኮ ተናኘ ይህደጎ?”

“አሁን ለታ ገነቴ ገበያ አግኝቻት ‘እንደው እንዳንቺ ያለ ቡና ቀምሼም አላውቅ። በዓመት አንዴ ግንቦት ልደታን እየጠበቅኩ ያንቺን እጠጣለሁ እንጂ ሌላ ቡና በአፌም አይዞር ዓመት ሙሉ። ምናል አንዳንዴ እንኳ ብትጠሪኝ ስትለኝ እንደው አንጀቴን በላችው”

“ትዝ ቢልሽ ኖሮ ልትጠሪያት ኖሯል?” በላይነሽ

“መቸም ወላድ ቀልብ የለውምና ዘነጋኋት እንጂ እንዴት አልጠራት?”

“ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ። ደሞ ከመቸ ጀምሮ ነው ከሴተኛ አዳሪ ጋር ተርቲበኛ የሆንሽው?” አፋቸውን አሽሟጠጡ። በላይነሽ ሂጂልኝ እንደማለት አይነት እጇን አራገበች።

“እማማ አስረበብ ደግሞ …” ሰርኬ የእጣን ዕቃውን ከፍታ በሦስት ጣቶቿ ዘግና እጇን ሰነዘረችና ማጨሻው ላይ አስቀመጠች። ከጋቻው ላይ ጥቁር እንፋሎት በእርጋታ መነሳት ጀመረ።

“እሱን ከተወች ስንት ዘበን ሆናት?”

“እሷ ተውኩ ትላለች እንጂ ሰፈርተኛው ሌላ ሌላ ነው የሚለው”

“የገነቴ ሰውማ ያወራል። ምን አለ ደሞ?”

“ሰውማ ምን ይላል? ይቺን አባቷ የማይታወቅ ልጇን እየጎተተች፣ ጌጥ ይመስላታል እንዴ እላለሁ እኔማ ሳያት … በየላጤው ቤት አይደል እንዴ አንሶላ ስትጋፈፍ የምትገኘው? እኔማ እንደው ይቺን ልጅ ገና ቂጧን እንኳ ሳትጠርግ የማይሆን ነገር አስተማረቻት እላለሁ፤ ምነው በእንቁላሌ በቀጣሽኝ ብላ እንዳትተርት እንኳ እንቁላሉንም እሷው ናት የሰጠቻት”

“ደሞ ይሄን አሉ?” አለች ሰርኬ ጀበናውን እያወረደች።

“እኔኮ ያንቺ ጋሻ ጃግሬ መሆን ነው የሚገርመኝ። ቆይ እንደው ሴተኛ አዳሪነቱን ተውኩ ብትልስ ቤቷ ውስጥ ስንትና ስንት ኮማሪት ቀጥራ እያሰራች እሷ ልትተወው ነው? ደሞ ልማድ መቸም አይለቅ” አለች በላይነሽ።

“አይ … አሁን ገና የማይጥም ነገር አወራሽ በላይ። እኔ መቸም ያለፈ አልፏል ነው የምለው። ማርያም ይቺ የመቅደላዋን አይደለም ወይ ጌታችን እንኳ ይቅር ያላት? ስንት ዘመን በግልሙትና ኖራም አይደል እግሩ ሥር ተደፍታ በእንባዋ ብታጥበው ያለፈ ታሪክሽን አልቆጥርብሽም ብሎ ነጣ ያወጣት መድኃኔአለም? እኛም ያው ያዳም ዘር ነን። ማንም ሰሃ የሌለበት አይገኝ። ደሞ ዓይናችን ውስጥ ምሰሶ አጋድመን በሌላው ሰው ዓይን ውስጥ ባለች ይቺን የምታክል ጉድፍ መዘባበት ለሰሚም ደስ አይል”

የማርያም ጣቷን በአውራ ጣቷ እየጫረች የተናገረቻት ይቺ የመጨረሻዋ አባባል ግቧን መታች። ከዚህ በኋላ የኬጃ ሚስት፣ የበላይነሽ እህት፣ ተናኘ ከነልጇ፤ እታለም ሉሉ፤ የእታለም ሉሉ የመጨረሻ ልጅ መጥተው ሲሄዱ ሁሉ በላይነሽ አንድ ቃል አልተናገረችም።

እትዬ አልታዬ ብቻ “ህም … ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ” አሉ።

እናቴ ከፈንድሻው ዘግና ወደ በሩ አቅጣጫ የተነሰነሰው ቅጠል ላይ እየበተነች “ለቆሌዋ” አለች። ከዚያ ወደ እኔ ዞራ “እስቲ ና አስዘግናቸው” አለች።

ቆለምሽሹን አንስቼ ሴቶቹ ፊት ቆምኩ። “ሴት ሆኖልሽ ቢሆን ሸጋ ነበር” አሉ እማማ አስረበብ ከፈንድሻው ዘግነው መቀነታቸው ላይ እያስቀመጡ። ሁሌ የሚያናድደኝ አባባላቸው ነው።

“ኧረ ወዲያ፤ ደሞ ሴት ልጅ ብሎ ነገር። ፋፎ ቆሎውን በደንብ ዝገኑ እንጂ እማማ አስረበብ፣ እንኳንም ወንድ ሆነልኝ፤ ጣጣዋ ብዙ ነው ሴት” አለች ሰርኬ።

እማማ አስረበብ ሊናገሩ አፋቸውን ከፈት ሲያደርጉ “ሠላም ለዚህ ቤት” ብላ ገባች የኬጃ ሚስት።

“እንዴት ዋልሽ የኬጃ ሚስት፤ ደርሰሻል ዛሬስ አቦሉ ላይ። በይ ያዥ በቁምሽ የቡና ቁርሱን፤ ጠመዥ ትወጂ የለ? ላንቺ ነው የቆላሁት”

“እሰይ ሰርክዬ ደሞ ወዙ ማማሩ” ሁለቱ ሴቶች ፊት ለፊት ግራ እጇን ተመርኩዛ በርጩማ ላይ እየተቀመጠች በቀኝ እጇ ዘገነችና ተቀምጣ ሳትጨርስ መቆርጠም ጀመረች። “አቤት አቤት እንደው እንዴት አድርገሽ ብትቆዪው ነው ልጄ እንደ እንትንኮ ነው ፍርኩት ፍርኩት ሲል ቆሎም አይመስል”

“ምን ታረጊዋለሽ፤ ከትከሻዬ ነው እንግዲህ” አለች ሰርኬ

ከበላይነሽ በቀር ሁሉም ሳቁ።

አንዱን (ሰው) ሲያነሱ ሌላውን ሲጥሉ ቶናውን ጠጥተው ጨረሱ። ጭሱ እየደከመ ጨዋታቸው እየሞቀ ሄደ።

ለሦስተኛ ጊዜ ቀድታ ጀበናውን ከማስቀመጧ እታለም ሉሉ መጣች። ከበርካታ ልጆቿ መሀል በላይ የሚባለው በእድሜ እኩያዬ ስለሆነ ጓደኞች ነገር ነን። ለቡና ስትመጣ የምትይዘውን እንዝርት አልያዘችም። እጁን ይዛ በቀስታ እየጎተተች የምታስከትለው ዳዴ ዘለል ልጇም የለም። ገና እንደገባች ደህና ዋላችሁም ሳትል በረጅሙ ተነፈሰችና፣

“እንደው ድካም ድካም እያለኝ ነው ሰሞኑን …” ብላ በላይነሽ ጎን ተቀመጠች።

“አይ አንበሲት፤ ደሞ ቋጠርሽ እንዴ? መቸም አንቺ ሽለ ሙቅ ነሽኮ” አለች ሰርኬ የእታለምን ሆድ እያየች። ወዲያው ደሞ ከተቀመጠችበት ወደ ቀኝ ጋደል ብላ ወደ በሩ እያየች ተጣራች “ተናኘ! ተናኘ!”

“ልጅ መቸስ ሀብት ነው …” ብላ በረጅሙ ሳቀች እታለም።

“ከሤራ ዲና ይወድልሻል አሉ” አሉ እማማ አስረበብ። ይሄ መልሳቸው ለሰርኬ ይሁን ለእታለም አልገባኝም።

እታለም አሳኢታ የሚባል አገር ስለሚኖር ልጇ ማውራት ጀምራ ሌሎች ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ልጆቿን መዘርዘር ጀመረች። እያንዳንዱን ልጇን በስም እየጠቀሰች እድሜውን፣ ሥራውን፣ የሚኖርበትን አገር ስትዘረዝር ተናኘ ከነ ልጇ ገብታ ኬጃ ሚስት አጠገብ እስክትቀመጥ፣ በረካው ተቀድቶ እስኪሰጣቸው፤ ሰርኬ ማጨሻው ላይ እጣን ጨምራ ቤቱ ከእንደገና እስኪታፈን፣ ተናኘና ሳራ ከቡና ቁርሱ እስኪዘግኑ ድረስ እንኳ አልጨረሰችም። ተመስጣ በምታደርገው ንግግር መሀል በቀኝ እጇ የያዘችውን ቡና ቀመሰችና ሬት የለበሰ የጡት ጫፍ ምላሱ ላይ እንዳረፈበት ሕፃን ፊቷን አጨማድዳ ስኒውን ለመመለስ እጇን ወደ ሰርኬ እየዘረጋች።

“ምነው ስታውቂው፤ ቡና በአሻቦ ነው የምጠጣው። ለምን በስኳር ሰጠሸኝ?” አለች

“ውይ … አፈር በበላሁ … አምጭው አምጭው” ብላ ተቀበለቻት ሰርኬ።

እማማ አስረበብ የተናኘ መምጣት ምቾት ነስቷቸው ዝም ብለዋል። በላይነሽ በፊትም ቀንዷን ተብላ በጥልቅ ጸጥታ ተቀምጣለች። የኬጃ ሚስት ጠመዥ ትፈጫለች። እታለም ቡናዋ በጨው እስኪቀርብላት ትጠብቃለች። ሰርኬ ቡና ታማስላለች። እንዲህ ሲሆን ለአንድ ደቂቃ ለሚሆን ያክል ጊዜ ሁሉም ነገር ዝም አለ።

ልክ በዚህ ጊዜ ነበር የእታለም ሉሉ ትንሹ ልጅ፤ ይሄ ወፌቆመቹን አጠናቅቆ ደንበኛ እርምጃ መራመድ ከጀመረ አንድ ሳምንት ያላለፈው ባለ ቁንጮ፤ በእጁ ፌስታል አንጠልጥሎ የገባው። ፌስታሉ ውስጥ እንዝርትና ጥጥ አለ። ለመጫወቻ እንዲሆነው ደመና ቋጥሮ የመጣ ይመስል ይዞ የመጣውን እቃ ለእናቱ ማድረሱን ትቶ ልክ ሲገባ ፊት ለፊቱ ያየውን ረከቦቱ አጠገብ ያለውን የቡና ቁርስ ሊቀምስ ግራና ቀኝ ሳይገላምጥ ቀጥ ብሎ ገባ። ቆለምሽሹ አጠገብ ደርሶ የቡና ቁርሱ አጠገብ ሊቀመጥ እያጎነበሰ መሀል መንገድ ላይ ሲደርስ የተናኘ ልጅ ሳራ አንድ ዐረፍተ ነገር ተናገረች። ሰዋሰውን የጠበቀ። ባለቤት ተሳቢና ግስ ያለው። በዘይቤ የታሸ። ሰሚን በማሳፈር የሰለጠነ አንድ ቀላል ዐረፍተ ነገር፣

“ሰተት ብሎ ገባ እንደ ቁላ”።

ይህቺ ልጅ የስንዝሮና የቢልጮን ተረቶች እየሰማች አላደገችምና አይፈረድባትም። እሹሩሩዋ የተሰራው እናትህ ከገበያ ስትመጣ ይሄንና ያን ታመጣልሃለች ከሚባል መሸንገያ አልነበረምና ማንም አይከፋባትም። ምናልባትም “እናትሸ ስትመጣ …” እያለች ያባበለቻት ለሃያ አንድ ፈሪ የሆነች ኮረዳ እሷም እናቷ መጥተው እንዲያፅናኗት የምትመኝ ነበረች ይሆናል። ይህቺ ሳራ የእናቷ ቅጥረኛ ኮማሪቶች ትናንትና ማታ የገጠማቸው ወንድ እንዴት እንዴት እንዳደረጋቸው በትናንሽ ጆሮዎቿ እየሰማች አደገች እንጂ የቅጥራን ፏፏቴ የመሰለ ጸጉሯን እየደባበሰ ሞራል የሚሰብክ ትርክት የሚነግራት አባት አልነበራትም። ለዚህም በእናቷ አባት ስም ሳራ ይህደጎ ተብላ የምትጠራ ይቺ ወንድም አልባ፣ እህተ ቢስ ልጅ እንካ ስላንቲያን ዘልላ፣ እንቆቅልሽ ምን አውቀልሽን ሳትነካ፣ “ተረት ተረት የላም በረት ሆድሽ ተተርትሮ ተይዟል በብረት” ብላ ተረት ለመስማት የጓጓች ታናሿን ሳትሸውድ፣ እንዲህ ሳታደርግና እንዲያ ሳይሆን በፊት “የአፍሽ የቂጥሽ ወሬ” የለመደች ነበረች።

ረፋዱ ላይ የእናቷ ሠራተኞች የምሽት ውርጭ የገረፈው ፊታቸው ገርጥቶ፣ ታችኛው የዓይናቸው ቆብ ፊታቸው ላይ ማህደረ ቆለጥ መስሎ ተንጠልጥሎ፣ ሲመቱ በጮሁበት፣ ሲረገጡ ባላዘኑበት፣ ሲጠለዙ ባቃሰቱበት በዚያ በጩኸት በሰለለ ድምጻቸው ተተርከው የልጅነት ስስ ታምቡሯ ላይ እንደ ዘላቂ ኩክ የተለሰኑት “ማታ ያጋጠመኝ ሰውዬ ደሞ …” ብለው የሚጀምሩ ጨዋታዎች ነበሩ። ማንም ይህን አያምንም እንጂ ሳራ ይህደጎ ለመጫወቻ አንዲሆናት ኮንዶም እንደ ፊኛ እየተነፋ የሚሰጣት ልጅ ነበረች። ሳራ እንዲህ ስላደገች ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስታውሳት እረዳታለሁ። ያኔ በአምስት ቃላት የመሰረተችው ዐረፍተ ነገር ግን “ሰተት” የሚለውን ቃል በሰማሁ ቁጥር ትዝ ይለኛል።

ያኔ በንፅፅር የተቀመጠው ነገር የገባው ወዴት እንደሆነ ባላውቅም ልክ ተናግራ ስትጨርስ እናቷ ተናኘ በሀፍረት ተነስታ ፊቷን ስታጮላት፣ በእኩል ሰዓትም እማማ አስረበብ ጮክ ብለው “ከሤራ ዲና” ሲሉ፣ በዚያችው ደቂቃ በላይነሽም አፏን አፍና ስትሥቅ፣ በዚያችው ሴኮንድ ልጇ ያመጣውን ባዘቶ ልትቀበል የተነሳቸው እታለም መሀል መንገድ ላይ ቆም ብላ ወደ ሳራ ስትገላመጥ፣ በዚያችው ቅጽበት ሰርኬ ወደ እኔ ዐየት አድርግ “በቃ ጆሮህ እዚህ ነው አይደል፤ አያነበውምኮ ወረቀቱን ለላንቲካ ነው ፊቱ የዘረጋው” ስትል፣ እኔ በጣቁሳ ለተወለዱ ቅኔ ምናቸው ነው/ የማሽላ ቂጣን በኑግ ይጉመዱ እንጂ እያልኩ የኑግ ልጥልጤን እያልጎጠጎጥኩ ለይስሙላ የዘረጋሁት የአማርኛ ትምህርት መጽሐፌ ውስጥ ተደበቅኩ። (በዘይቤ ከታሸ ከዚህ ዐረፍተ ነገር ወዲያ አማርኛ ትምህርት አለ?) አፍሬ የሰቀልኩት ቅንድቤ ያለ ምንም ማጋነን እስካሁን ወደ ቦታው አልተመለሰም፤ የፈጠጠው ዓይኔ እስካሁን አልሟሸሸም። ጭራሽ “ሰርኬን ነውኮ የሚመስለው እስቲ እዩት ዓይኑን፤ ዛጎል የመሰለ” እየተባልኩበት።

.

ፍቅር

ከዚህ አጋጣሚ በላይ የሚያሳፍረኝ ሌላ አጋጣሚም ነበረ።

“ጸሎት ያለ ፍቅር ሰውን አያጸድቀውም ሲልሽ ይሄ ዲያቢሎስ ያቀማቀመው ጠምጣሚ እውነት መሰለሽ?” አባቴ ይሄን በጩኸት ሲናገር እናቴ ካቀረቀረችበት ቀና አለች። ይሄንን አባባል ማወቁ አስገርሟታል። አሁን አሁን ሳስበው ይሄን ማወቁ ለእኔም ይገርመኛል። እንኳን ሰው ፊት በኀይለ ቃል ሊናገራት ብቻቸውን ሲሆኑ እንኳን የጎደለው ነገር እንዲሟላ ሲጠይቅ እያሳሳቀ፤ በጨዋታ እያደረገ ነበርና በጩኸት መናገሩ ብቻ አስፈርቶኛል።

ትዝ ይለኛል ቅዳሜ ቀን ነው። አባቴ ከእናቴ ጋር ተጋጭቶ ከቤት ከወጣ ሁለት ሳምንት ሆኖት ነበር። አባቴና እናቴ ተፋትተው የተጣሉበትን ምክንያት የሰፈር ሰው እኔ እንድሰማው አድርጎ በአብሻቂ ሹክሹክታ ሲያወራ እንደሰማሰሁትና በኋላ አባቴ ነፍስ ሳውቅ እንደነገረኝ እናቴ ይናፋ፟/ኢናፋ ስለተያዘች ነው፡፡፟

ደባሪ የሂሳብ ትምህርት ሜክ አፕ ክላስ ጨርሼ ቤት ስገባ አባትና እናቴ ሽማግሌዎች መሀል ተቀምጠዋል። ዳውድ ምናምን። አባ ገብረ ኪዳንና ሌላም ቄስ ነበሩ። ሌላኛው ቄስ የአባ ገብረ ኪዳን የንሰሐ አባት ይሆኑ ይሆናል፤ ለእኛ ደግሞ የንሰሐ አያታችን ናቸው ማለት ነው?

አባቴ ዓይኑ ቀልቶ ነጎድጓድ ድምፁ በንዴት እየተንቀጠቀጠ ይናገራል፣

“አመንሽው ሰርካለም? አይደለም በሁለት በሠላሳ ቋንቋ ቢያወሩ እንኳን ለደብተራ ሤራ ለጳጳሱ ግዝት የምትበገሪ አይመስለኝም ነበር። አመንሺው ይሄን ዘኬ ለቃሚ? አመንሺው ሰርኬ? ይሄን ዛር አንጋሽ አመንሺው? አመንሺው?!”

ሰርኬ ከተቀመጠችበት ተነስታ ሰዎች መሀል መሬት ላይ ተደፍታ ማልቀስ ጀመረች። ምን እየተደረገ እንደሆነ እንኳ ሳይገባኝ ገና በር ላይ ሆኜ እንባዬ ይወርዳል። የናፈቀኝ አባቴን እንኳ አቅፌ ለመሳም አልቻልኩም።  ሰርኬ ጸሎት እንደሚያደርግ ሰው እጇን ወደ ላይ እየዘረጋች በሳግ የተዋጠ ለመስማት የሚያስቸግር የሆነ ነገር ትናገርና መልሳ ትደፋለች።

“አንድኛሽን ለምን እንደ ኀምሳ አለቃ ይህደጎ ልጅ መሸታ ቤት አትከፍቺም?…”

የሽማግሌዎች ምክር ጣልቃ ገባ።

“ተው እንጂ ወልደ መስቀል እንደዛ አይባልም ተው …”

“ምንስ ቢሆን የልጆችህ እናት አይደለች፣ ተው እንጂ …”

ድምፁን ጨምሮ ቀጠለ።

“…አዎ! ‘ለሰው ፍቅር መስጠት ደግ ነው፤ ቡና ሳፈላ አንዳንዴ ብጠራት ምን ችግር አለው’ ስትዪ አልነበረም? ጥሩ ነው። ጠጡ! ፍቅር ስጫት፤ አሰጣጥ ታስተምርሻለች። አየሽ ቢያንስ ሀብታም ትሆኚበታለሽ …”

ድምፁ እየጨመረ መጣ። የሚናገረው እያንዳንዱ ቃል ሲሰብራት ይታየኛል። ዐረፍተ ነገር ሲጨርስ እንደተጎሸመች ሁሉ ታቃስታለች። ሰዎቹ አቀርቅረዋል።

“ተው እንጂ አወል፤ ሁለት ሳምንት ሙሉ ስንት ነገር ስንነጋገር ከርመን እንደገና ወደ ኋላ ትመለሳለህ? … ስንት ነገር አጫውቼህ … ትዳር ውስጥ ስንቱን ችሎ ነው …” አለ ዳውድ ቀና ብሎ አባቴን እያየ።

ከተቀመጠበት ተነስቶ እኔ ወዳለሁበት ወደ በሩ አቅጣጫ መጣ። እንደዚህ ረጅም ጊዜ ጠፍቶ መጥቶ ሊያቅፈኝ ይቅርና አጠገቡ መቆሜን ልብ ሳይል ወጥቶ ሄደ። ከኋላው የቀሳውስት ግዝትና የሰርኬ ሳግ የለበሰ ልመና ተከተሉት።

ይህ ከሆነ በኋላ፤ ይሄው አባ ገብረ ኪዳን የተባሉ መዘዘኛ ቄስ ጉሮሯቸውን ስለው፤ ልክ በድርጊቱ ተከፋይ እንዳልሆኑ፤ ልክ ለማስታረቅ ብቻ እንደመጣ ሽማግሌ ሆነው ራሳቸውን ነፃ የሚያወጣ አንድ ጥቅስ ተናገሩ፣

እግዚአብሔርወሀበወእግዚአብሔርነሥአ

በቃ … ቄስና ግዕዝ ጠላሁ።

.

ሙሉጌታ አለባቸው

2009 ዓ.ም

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “መሐረቤን ያያችሁ”። ፳፻፱። ገጽ 56-73።

7 thoughts on ““ማሪበላ” (ልብወለድ)

  1. ጥሩ ድርሰት ነው:: ነገር ግን በሚከተለው ዓ\ነገር ውስጥ ‘ፍንጃል’ ተጠቅስዋል::

    …..ሰርኬ ተሳስታ በሌላ ስኒ የሰጠቻቸው እንደሆነ “በራሴ ፍንጃል ካልሆነ ባልጠጣ ይሻለኛል” ብለው ይመልሳሉ።

    ‘ፍንጃል’ ማለት ምንድን ነው??

    በጽሁፋ ላይ እንደታየው ‘ፍንጃል’ ማለት ‘ስኒ’ ማለት ነው እንዴ?

    ለኔ ‘ፍንጃል’ ማለት ‘ጀበና’ ማለት ይመስለኛል::

    የትኛው ነው ትክክል?????

    Liked by 1 person

  2. ከብዙ ጊዜ በኋላ ምርጥ የአማርኛ አጭር ልቦለድ ሳነብ፤ ተባረክ ሙሌ ፤ ስንቴ እንዳነበብኩት ፡ ያላስታወሰኝ ሥራዎች የለም የስብሃት ፭ ፮ ሰባት፡ የአዳም ረታ ማህሌት እና ሌሎችም። በእውነቱ የድህነታችን ሥር ዘልቆ ፡ መልካሙን ባህላችን፡ ሃይማኖታችን ውስጥ የሚሽሎከሎኩትን ክፋቶች፣ ስስቶች፡ የማህበረሰብችን ምስኪን እንስቶችን ውይም እናቶችን ከሥር ፈልፍሎ ማሳየት ጀግንነት ነው። ዛሬ ለተንሸዋረረው ማንነታችን አኗኗሯችን ‘ነውርነቱ’ ቢገፈፍ ስንት ጉድ አለ፤ ይህንን ነው ደራሲው በምርጥ ቋንቋ ያስቃኘን። በርታ ወንድሜ። አንድምታዎችንም ሳላመሰግን አላልፍም።

    Liked by 1 person

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s