I
በልጅነት ምን ዓይነት መጻሕፍትን ታነቢ ነበር?
በልጅነት መጀመሪያ ያነበብኳቸው የልጆች መጻሕፍት አልነበሩም። በስምንት ወይም በዘጠኝ አመቴ ያነበብኩትን የመጀመሪያ መጽሐፍን (“ግርዶሽ” በሲሳይ ንጉሡ) ጨምሮ በዚያን ጊዜ አካባቢና ከዚያ በኋላ ሁሉ ይታተሙ የነበሩትን ያካትታል።
ቤታችን ውስጥ በርካታ ልብወለድ፣ የታሪክና ጥቂት የሚባሉ ከዚህ ውጪ የሆኑ መጻሕፍት ነበሩ። ልብወለዶቹ የሀገር ውስጥ ወጥ ስራዎች፣ ብዛት ያላቸው ትርጉሞችና ጥቂት በእንግሊዘኛ የተጻፉ ልብወለዶች ናቸው። በሀገራችን ታሪክ ዙሪያ በተለያየ ጊዜ የተጻፉ መጻህፍትም ቤት ውስጥ ነበሩ። እንዲሁም በይዘታቸው ለየት ያሉ በዚያ እድሜዬ የሚገርሙኝ አንዳንድ መጻሕፍት ነበሩበት፤ በቤት ውስጥ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ላይ የሚያተኩር ወደል የእንግሊዘኛ መጽሐፍና ‘ባሃኡላህና አዲሱ ዘመን’ የሚል አንድ ደቃቃ መጽሐፍ ለምሳሌ ያህል ትዝ ይሉኛል።
በተጨማሪ በትምህርት ቤት ደግሞ እንደው ለይስሙላ በክፍል ውስጥ ይሰጡ የነበሩ እንደ ‘እጅ ስራ’ ያሉ ትምህርት ክፍለጊዜዎች ላይ የልጆች መጻሕፍትን የምታነብልን ታሪክ የምትባል መምህርት ነበረች። ለኔ በበኩሌ ባለውለታዬ ናት።
‘የተኛችው ቆንጆ፣ ሲንደሬላ፣ አንድ ሺህ አንድ ሌሊት፣ ቲሙርና ቡድኑ ወዘተ’ በሙሉ መኖራቸውን ያወቅኩት በእሷ ምክንያት ነው። ብዙዎቹ እነዚህ መጻሕፍት ትርጉሞች ናቸው። ከትምህርት ቤት ተመልሼ ማታ ማታ እነዚያን ታሪኮች ለእህቶቼና ለእናቴ ስተርክ አመሻለሁ። ሳላስብበት ትረካን (story telling) ወደድኩ።
ቤት ውስጥ የነበሩትን ልብወለዶች በተለይ ትርጉሞቹን በሙሉ አንብቤያቸዋለሁ። ኢንተርኔት፣ ጉግል የመሳሰለውን በማላውቅበት ለአቅመ የብእር ጓደኛ ባልበቃሁበት እድሜ ላይ ስለነበር ያነበብኳቸው፣ በርካታ አስደናቂ ዓለማትን ለምናቤ ከፍተዋል። ከ1983 በኋላ ደግሞ ከዚያ በፊት ያለፈውን አስራ ሰባት አመት ታሪክ በተለያየ አኳኋን የሚዘክሩ መጻሕፍት መጡና ቀልቤን ማረኩት።
ከዚህ በኋላ ደግሞ እናቴ የBritish Council ቤተመጻሕፍት የአባልነት መታወቂያ አወጣችና የተለያዩ የእንግሊዘኛ መጻሕፍትን ማንበብ አስቻለችኝ። አባቴም የእንግሊዝ ሥነጽሑፍ ቁንጮ ጸሐፍትን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች፣ ለታዳጊ ወጣቶች እንዲሆኑ አጠር ተደርገው የተዘጋጁትን፣ ከፍ ስንልም እንደዚያው ጠንከር ያሉ መጻሕፍትን ገዝቶ ያስነብበን ነበር።
በትምህርት ቤታችሁ የነበረው የንባብ ባህልስ ምን ይመስል ነበር?
እስከ ስምንተኛ ክፍል በተማርኩበት የገዳመ ሲታውያን ማርያም ጽዮን ትምህርት ቤት (Cistercian Monastery Mariam Tsion School) የማስታውሰው የተለመደው የአማርኛ ቋንቋችንን የማዳበሪያ ተግባራት ይሰጡን እንደነበረ ነው፤ ግጥም መጻፍ፣ ክርክር ማከናወን የመሳሰሉት። ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ላይ ግን የአማርኛ መምህራችን ከዚህ በላይ ገፍቶ ያተጋን ነበር። ተውኔት ደርሰን አዘጋጅተን በክፍል ውስጥ ስናቀርብ አስታውሳለሁ። በአማርኛ ሥነጽሑፍ ውስጥ እስካሁንም የሚጠቀሱ አውራ ደራስያንና ስራዎቻቸው ላይ ሂሳዊ ንባብ እንዲሁም ግምገማዎችንም እንድናካሂድ ያደርገን ነበር። በዚህ መልኩ መምህራችን (አቶ ታሪኩ) የአማርኛ ሥነጽሑፍን እንደው ዝም ብሎ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ማጣጣምንም አስተምሮናል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በተከታተልኩበት ሰላም የሕጻናት መንደር ትምህርት ቤት ደግሞ መደበኛ የመማሪያ መጽሐፉ ከሚጠቁመው በተጨማሪ ለማትሪክ የበለጠ ዝግጁ ያደርጋል ብለው ያሰቡትን ይዘት አክለው የሚያስተምሩን ሁለት የአማርኛ መምህራን ነበሩ። ስለዚህ ከተማርነው ይዘት ፈሊጣዊ አነጋገሩ፣ ቅኔው፣ ምሳሌያዊ አነጋገሩና ይህን የመሳሰለው ይበዛ ነበር። እና ደግሞ ቁጥር የለሽ (መምህራኑ ‘ጥሬ’ የአማርኛ ቃላት የሚሏቸው) በተለምዶ በሚነገረው አማርኛችን ውስጥ እምብዛም የማንገለገልባቸው አስገራሚ ቃላትን አጥንተናል።
ድራማና ጭውውት ደርሶ አዘጋጅቶ መተወን በክፍል ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍሎች መካከል በውድድር መልክ የሚካሄድና፣ በየማለዳው ቀኑን በጸሎት በምንጀምርበት አዳራሽ (ቻፕል) ውስጥ ለተማሪዎችና ወላጆች በሚቀርቡ ዝግጅቶችም ላይ የምንሳተፍበት ሁኔታ ነበር።
በቤት ውስጥስ ምን አይነት ሥነጽሑፋዊ ተጽዕኖ ነበር?
ወላጆቼ ራሳቸውም ማንበብ የሚወዱ ሰዎች በመሆናቸው፣ መጻሕፍትን ይሰበስባሉ። እኔም በግላጭ አግኝቼ ኮምኩሜያቸዋለሁ። ቤት ውስጥ በርካታ የትርጉም እንዲሁም ታሪክ ነክ መጻሕፍት የነበሩ መሆናቸው የራሱን ተጽዕኖ አድርጎብኛል ብዬ አስባለሁ።
እናቴ ገጣሚም ነች፤ ትደብቃቸዋለች እንጂ ግጥሞችን ትጽፋለች። አባቴም በበኩሉ ያነበብኳቸውን መጻሕፍት ይዘት ጨምቄ እንድጽፍ ወይም በቃል እንዳቀርብ ሲያደርገኝ አስታውሳለሁ። በተጨማሪም በስራው ምክንያት ለወራት መስክ ላይ በሚቆይበት ወቅት የተለዋወጥናቸው ደብዳቤዎች በእንግሊዘኛ ነበሩ። አንዳንዴ ሳከናውን የሰነበትኩትን ጉዳይ ለእሱ ለመግለጽ የሚረዳኝ የእንግሊዘኛ ቃል ፍለጋ ስለፋ ትዝ ይለኛል።
ከዚህ ይልቅ ግን በእርግጠኝነት ከወላጆቼ የወሰድኩት መጻሕፍትን የማፍቀርን ነገር ነው። ስለ ሁለቱም የማይረሱኝን ሁለት አጋጣሚዎች ልግለጽ።
‘ምጽአተ እስራኤል’ የተባለ የማሞ ውድነህ የትርጉም መጽሐፍ የወጣ ሰሞን ነው። መኖሪያ ቤታችን ያን ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ድንበር የሚባል ቦታ ላይ ነበር። ማንኛውም አይነት ትራንስፖርት ከሚገኝበት ዋና አስፋልት መንገድ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል በከባድ ኮሮኮንች መንገድ ወደ ውስጥ ያስገባል።
እናቴ ወጋየሁ ከስራ ወጥታ መጥታ እዚህ አስፋልት መንገድ ዳር፣ የመጽሐፍ መደብር ጎራ ስትል ይህን አዲስ መጽሐፍ ታገኛለች። ትጓጓለች። ነገር ግን ዋጋውን ስታየው ከቦርሳዋ በቂ ገንዘብ አልያዘችም። እስከ ነገ መጠበቅ ሊኖርባት ነው። እሷ ግን ያን ኮሮኮንች መንገድ ሰላሳ ደቂቃ ሄዳ ቤት ገብታ፣ ገንዘቡን ይዛ፣ ተመልሳ ወደ መደብሩ ሄዳ መጽሐፉን ገዝታ አደረች። በድምሩ በማግስቱ መግዛት ለምትችለው መጽሐፍ ያን ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል በእግሯ ተጓዘች ማለት ነው። እናቴን ያሸነፋት ጉጉቷ ነው።
ሌላ ጊዜ ነው፤ ካልተሳሳትኩ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይመስለኛል። እኔና አባቴ ፒያሳ አካባቢ በእግር እየተጓዝን በየሱቁ መስኮት አንዳንድ ነገር እናያለን፤ በትክክል ምን ልናደርግ እዚያ እንደሄድን አላስታውስም። ይህንን ግን አስታውሳለሁ። አንድ መጽሐፍ መደብር የመስታወት መስኮት ውስጥ Lords of Poverty የተሰኘውን የግራሃም ሃንኮክ መጽሐፍ እናያለን። አባቴም እኔም ይህንን ጸሐፊ እንወደዋለንና የመጽሐፉን ዋጋ አጣራን። መቶ ብር ነው።
መቶ ብር የዛሬ ኻያ አመት ገደማ ቀላል የሚባል ብር አልነበረም። ቢያንስ ቢያንስ ለእኔ ደህና ቆዳ ጫማ ይገዛል። አመነታን። እንግዛው አንግዛው እየተባባልን ጥቂት ደቂቃዎችን አባከንን። ከጀርባው የተጻፉ ነገሮችን፣ ማውጫውንና የመሳሰለውን እያየን ጥሩ መጽሐፍ ነው ተባብለን የዋጋው ጉዳይ ግን ያዝ አደረገን። ከተወሰኑ ደቂቃዎች መንቆራጠጥ በኋላ ገንዘቡን ከኪሱ የሚያወጣው አባቴ ወሰነ። ለወትሮው አማረን ግዛልን የምንለው ነገሮች ላይ ቆጣቢ ቢሆንም ዛሬ ግን ‘እንግዛው ባክሽ፣ ድህነት እንደሆን ቂሙን አይረሳም’ አለኝ። እኔም አሁን ድረስ አንዳንዴ ዋጋቸው ቆንጠጥ የሚያደርጉ መጻሕፍትን ለመግዛት ወኔ ሲያንሰኝ ‘ድህነት ቂሙን አይረሳም’ የምትለዋን ቀረርቶ ለራሴ አሰማለሁ።
II
ሕግን ለማጥናት እንዴት ወሰንሽ?
ወፍራም እንጀራ ያወጣል፣ ያስተማምናል ስለተባልኩና፣ የተባልኩትን ስለሰማሁ!
ጉጉት፣ ጥያቄ፣ ቀጥታ ንግግር እና ትንሽ ድፍረት የምታሳይ፣ በትምህርት ቤት ደህና ውጤት ያላት ታዳጊ ስትሆን ጸሐፊ ወይም ተዋናይት መሆን ትችላለች ብሎ የሚመኝልህ ብዙ ሰው አይኖርም፤ ነገረ ፈጅ እንጂ!
ዩኒቨርሲቲ ስገባ ምን ማጥናት እንዳለብኝ ብዙዎችን ሳማክር ተመሳሳይ ምላሽ ስላገኘሁ፣ ይህንኑ በመከተል ሕግን መረጥኩ።
የሕግ ሙያ ተምረው በርካታ የኪነጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ምሩቃን ለምን ያሉ ይመስልሻል?
እውነት ነው። ሕግ ተምረው የኪነጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ምሩቃን ጥቂት አይደሉም። በተለይ ከመነሻው ትንሽም ቢሆን ኪነጥበባዊ ፍላጎት (interest) የነበራቸው ሰዎች ከሆኑ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳስብ የሚከተለው ይታየኛል፤ በተለይ በራሴው ልምድ ከተገነዘብኩት በመነሳት።
አንደኛ የሕግ ትምህርት የቋንቋ እና የግንዛቤ ክህሎትን ይሞርዳል ብዬ አስባለሁ። የሕግ ትምህርት የግድ ከባድ አይደለም፤ ግን እጅግ ሰፊ ነው። የሚነበበው ብዙ ነው፣ የሚተነተነው ብዙ ነው፣ የሚጻፈው ብዙ ነው። የምታነባቸው መጻሕፍት አይነትና ብዛት ቋንቋህ እና እውቀት አዘል ግንዛቤህ ላይ አይነተኛ ተጽዕኖ አላቸው። በትምህርት እንዲሁም በስራ ወቅት እንድታዘጋጃቸው የሚጠበቁብህ የጽሑፍ አይነቶች የመተንተን፣ የማሰናሰልና የማስረዳት ክህሎትህ ላይ እንዲሁ ተጽዕኖ አላቸው።
ሁለተኛ ሕግ ራሱ ሁሉን ጠለቅ (pervasive) ባሕሪይ አለው። ሕግ የማይመለከተው ወይም የማይገዛው የሕይወታችን ክፍል የለም። ሕግ የሚባለው ምን እንደሆነ እና እንደምን እንደመጣ ለመረዳት መጀመሪያ ላይ የፍልስፍና ትምህርት፣ በመቀጠል የሕግ ፍልስፍና ትምህርት ስትወስድ ዘላለማዊ የሚባሉትን የሰው ልጅ ኀሠሣዎች ገረፍ አድርገህ ታልፋለህ። ከዚያ በኋላ በሕግ ግምትና በሕግ አተያይ ሰው ከመሆን አንስቶ፣ የግለሰብን ሕይወትና ከግለሰብ፣ ከማህበረሰብ እና ከመንግስት ጋር የሚኖር መስተጋብር፣ የሀገር እና የአለም አቀፍ ህብረተሰብን መስተጋብር፣ በየፈርጁ የሚፈትሹ ሃሳቦችን፣ የሚገዙ መርሆችን ታያለህ።
በአጭሩ ሕግ መቼ ተፀነስክ ከሚለው የማህፀን ውስጥ ሀቅ ጀምሮ ቤትህን፣ ምድርን፣ ባህርን፣ አየርን እና አሁን ደግሞ ‘ቨርቹዋል’ የምንለውንም አለም እንዲሁም እዚህ ሁሉ ውስጥ ያለውን ክንውን ይቃኛል። ኪነትስ? በአንዳች አይነት መልኩ ይህንኑ አታደርግም?
የኔ ፍላጎት ሥነጽሑፍና ቴአትር ስለነበር፣ አባቴ አበበ ባልቻን ምሳሌ አድርጎ ሕግ ትምህርት ቤት እንድገባ አሳመነኝ። እኔ አብዛኛዎቹን አመታት ክፍል ውስጥ ግጥም እየጻፍኩ አሳለፍኳቸው። ቴዎድሮስ ሞሲሳ ዘፈን ሲያወጣ ጓደኞቼ ‘የሒዊ መጨረሻ’ ብለው ለወራት ተዝናኑብኝ።
በአአዩ የነበረው ኪነጥበባዊ ድባብ ምን ይመስል ነበር?
አአዩ በነበርኩበት ጊዜ፣ እኔና ጓደኞቼ እንሳተፍበት የነበረው የባህል ማእከሉን የግጥም ምሽት ነበር። በሳምንት አንድ ቀን የሚጽፉ ልጆች ግጥሞቻቸውን እና ወጎቻቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ ነው። በወቅቱ የነበረው የመብራት መጥፋት ወረፋ እንኳን ሳያግደው በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ በሻማ ብርሃን ይከናወን ነበር። በ1993 በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተነሳው ግርግር ምክንያት ተቋርጠ።
ከዚያ በኋላም ተማሪዎች በቡድን ተሰባስበው መገኘት ስለተከለከሉ የሥነጽሁፍ ምሽቱን ማስቀጠል አልተቻለም። ለወትሮውም ቢሆን ከሚቀርቡት ጽሁፎች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ይዘታቸው ፖለቲካዊ እንደሆነ የታወቀ ነውና።
በ1993 የትምህርት ዘመን የሁለተኛውን ሴሚስተር ተምሮ ላለመጨረስና ፈተና ላለመውሰድ የወሰኑት መደበኛ ተማሪዎች በሙሉ ለአንድ አመት በትምህር ገበታ ላይ እንዳይገኙ ተደርገው ተቀጡ። በመሆኑም በ1994 እንኳን እንደወትሮው የደመቀ የሥነጽሁፍ ምሽት ሊካሄድ፣ በግቢው ውስጥ የቀሩት እኛ የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በዚሁ አመት የገቡ አዲስ ተማሪዎች ብቻ ነበሩ። ምናልባት በሌሎች መርሃ ግብሮች የሚማሩ ተማሪዎችም ነበሩ ይሆናል፣ በትክክል አላስታውስም። የማስታውሰው እንደ ድንጋይ የሚካበደውን ጭርታ ብቻ ነው።
በ1995 ተማሪዎች ከተመለሱና ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ግን እኔና የክፍል ጓደኛዬ የሆነው ይርጋ ገላው (ገጣሚና ደራሲ)፣ የተቋረጠው መድረክ መቀጠል እንዳለበት ስላሰብን በወቅቱ ወደ ነበሩት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንቶችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በመሄድ የግጥም ምሽቱ በድጋሚ እንዲጀመር ጠየቅን። ግልጽና ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶን ተፈቀደ።
መድረኩም በሌሎች እገዛ እንደገና ጀመረ። ልጆች አሁንም ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን በስራዎቻቸው መግለጽ አላቆሙም ነበርና ከባህል ማእከሉ ተቆጣጣሪዎች ተግሳጽና ምክር አንዳንዴም የ‘እባካችሁ ሁላችንንም እንዳታሳስሩን’ ልመናን አስተናግደናል።
ከባህል ማእከል ባለፈ ደግሞ ተለቅ ያሉ የሥነጽሁፍ መድረኮችን ከሌሎችም ጓደኞቻችን ጋር በመሆን እናዘጋጅ ነበር።
በተለመደው በሳምንት አንዴ በሚዘጋጀው መድረክ ከሌሎቹ ካምፓሶች የሚመጡት ተማሪዎች ቁጥር እምብዛም ስላልነበረ፣ አልፎ አልፎ እያዘጋጀን ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ አዳራሽ የምናቀርበው መድረክ እነዚህንና ሌሎችንም ይስብ ነበር። በስድስት ኪሎና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከይርጋ ጋር እየተዘዋወርን ትምህርት ቤቶቹ ከተማሪዎቻቸው መካከል መርጠው በእኛ ዝግጅት ላይ ግጥም የሚያነቡ ታዳጊዎችን እንዲልኩልን ስንጠይቅ ሁሉ አስታውሳለሁ።
እኔና ጓደኞቼ እንደሌሎች ብዙዎች ከግጥም ምሽቱ በኋላ የምናዘወትረው ልማድ ነበረን። ተያይዘን ‘አሴ ቤት’ ወይም ‘ማዘር ቤት’ እንሄዳለን። በዚያም ምሽቱን መድረክ ላይ በቀረቡት ስራዎች መንስዔነት የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ይንሸራሸራሉ። በመሆኑም በተለያዩ ርእሰ ሃሳቦች ላይ በልዩ ሁኔታ ስምም የሆንነውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀራረብን የመጣን ልጆች አንዲት ማኅበር መሰረትን።
ማህበሯም በተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት እውቅና አግኝታ በግቢው ውስጥ አንዳንድ ዝግጅቶችን በማከናወን መንቀሳቀስ ጀመረች። አላማዋ ለተማሪዎች/ለወጣቶች በሃገር በቀል ባህሎችና ማንነት፣ በአፍሪካዊ ማንነትና ትልሞች እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር። የክዋሜ ንክሩማ ልጅ ጋማል ንክሩማ ተገኝቶ ለተማሪዎች ንግግር ያደረገበት በማህበሯ የተዘጋጀው መድረክ ከማይረሱኝ አንዱ ነው።
በኋላ ላይ የመስራቾች የመመረቂያ ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ፣ ማኅበሯን ከግቢ ውጪ እንደ ድርጅት የማስመዝገብ ሃሳብ መጣ፤ ተመዘገበችም። ከጊዜ በኋላ የነበርነው ነባር መስራቾች በተለያየ የግል ምክንያት ብንጎድልም፣ ከመካከላችን ጎበዛዝትና ምርጦች የሆኑት ግን ይዘዋት፣ ደግፈዋት ቀጥለዋል፤ ዛሬም ድረስ እየሰራች ነው።
በዚህ ዘመን የንባብሽ ምርጫ ምን ይመስል ነበር?
ከላይ እንዳልኩት በልጅነት በአብዛኛው ልብወለዶችን ከፍ ካልኩ በኋላ ደግሞ ጊዜው የከሰታቸውን የታሪክና ታሪክ ነክ መጻሕፍት አነብ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ ዩኒቨርሲቲ የገባሁ ሰሞን ድረስ፣ ልብወለዶችን በተለይ የሩሲያ ጸሐፍትን ስራዎች ትርጉም ሳነብ አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ከመሰልቸት ይሁን፣ ወይም ‘አድጌያለሁ እኮ፣ እስካሁን ልብወለድ እንዴት አነባለሁ?’ የምትል ሚጢጢ ትምክህት ከልቤ አጎንቁላ፣ ልብወለድ የሚባል ማንበብ ተውኩ።
ኢ-ልብወለድ የሆኑ ጽሑፎች በይበልጥ ይማርኩኝ ጀመር። ምናልባት እየዳበረ የመጣው ስብእናዬ በወቅቱ ከነበርኩበት የመማርና የልምድ ንፍቀ ክበብ (ዩኒቨርሲቲ) ጋር ተባብሮ ፈርጀ ብዙ እውቀት የማጋበስ ፍላጎት ፈጥሮብኝ ይሆናል። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ታሪክ፣ ስነልቦና፣ ሃይማኖት፣ የሃይማኖት ታሪክ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ኢ-ልብወለድ መጻሕፍትን ጊዜ፣ ተደራሽነትና አቅም በፈቀደ መጠን ለማንበብ ሞከርኩ።
ከዚያ፣ ‘ግራጫ ቃጭሎች’ የተሰኘ ትንግርት ተከሰተ።
በግራጫ ቃጭሎች መንስዔነት ፊቴን ወደ ልብወለድ መለስኩኝ፤ የአማርኛም የእንግሊዘኛም። አሁን ሁሉንም አቀላቅዬ ለማንበብ እሞክራለሁ። በተለይ ግን ግለ ታሪክ፣ የህይወት ታሪክና፣ ማስታወሻዎች በይበልጥ ቀልቤን ይገዙታል። በብዛት እና በተስማሚ ዋጋ ባለመገኘታቸው ምክንያት ከውጭ ሀገር መጻሕፍት ይልቅ በብዛት የሀገር ውስጦቹ ላይ የምበረታ ይመስለኛል።
III
የሐማ ቱማን “The Case of the Socialist Witchdoctor” እና የሕይወት ተፈራን “Mine to Win” እንዴት ለመተርጐም ወሰንሽ?


“The Case of the Socialist Witchdoctor” (“የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”) ጋር የተገናኘሁት በአጋጣሚ ነው። መጽሐፉ በሀገር ውስጥ እንደልብ የማይገኝ በመሆኑ ፎቶ ኮፒውን አግኝታ ያነበበች ጓደኛዬ ደጋግማ ስላነሳችብኝ ተውሺያት አነበብኩት። የመጀመሪያውን ክፍል ሙሉ በሙሉ ሳልጨርሰው ለመተርጎም ወስኜያለሁ።
እንደ ሀገር እንደ ህዝብ ስለራሳችን ያልተቀበልናቸውና፣ ዘወትር ሸፋፍነን የምናልፋቸውን አስቀያሚ ገጽታዎቻችን እንዲሁም እርስ በእርስ የተደራረስነው ግፍ፣ የተገብርነውን ክፋት እያዋዛ ሆጭ አድርጎ ማሳየቱን ወደድኩት። ሰው ሁሉ እንዲያነበው ፈለግኩ። ስለዚህ ልተረጉመው ወሰንኩ። የደራሲውን አድራሻ ከጉግል ላይ አፈላልጌ ፍቃዱን ጠየቅኩት። የተቀረው፣ … እንደሆነው ነው።


በሌላ በኩል “Mine to Win” ደግሞ፣ ሕይወት ተፈራ ለማስተርጎም ፈልጋ ወዳጅ ጓደኞቿን ተርጓሚ እንዲጠቁሟት ስትጠይቅ፣ የኔ ስም በሁለት ወገን ይደርሳታል። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ትርጉም ብዙ ሰው ወዶት ስለነበር ነው እኔን መጠቆማቸው። ነገር ግን ሕይወት ሶስት ሰዎችን ለማወዳደር ነበር የፈለገችው። በተለይም ደግሞ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን አላነበበችውም ነበርና፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ስንነጋገር፣ ይህንኑ ገልጻ ከ“Mine to Win” አንድ ምእራፍ ብቻ ሰጥታኝ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር እንደምታወዳድረኝ ነገረችኝ። ተወዳደርኩ። ዳኞች እኛ ተወዳዳሪዎች ያላውቅናቸው ሰዎች ናቸው፤ እራሷም አልዳኘችም።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የመጽሐፉ ታሪክ የሚያጠነጥንበትን መቼትና ሁኔታ የሚመጥን ረቂቅ በማቅረቤ እኔ እንዳለፍኩ ተነገረኝና ስራውን ጀመርኩ። በእርግጥ ሙሉ የትርጉም ስራውን ከመጀመሬ በፊት የእንግሊዝኛውን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ገጸ ባሕሪይ ከተውኔ (ተዋነይ) ጋር ልባዊ ቁርኝት መፍጠር ያስቻሉኝን በርካታ ነገሮች አገኘሁና፣ ተወዳድሬ እንዳገኘሁት ስራ ሳይሆን ፈልጌ፣ ጠይቄ የተረጎምኩት ያህል አቅሜ የቻለውን ሁሉ ለማድረግ በቂ ውስጣዊ ግፊት ነበረኝ።
ከኒህ ሥራዎች በፊት የነበረሽ የትርጉም ልምድ ምን ይመስል ነበር?
ከዚህ በፊት የነበረኝ የትርጉም ልምድ በአብዛኛው ግጥሞችን መተርጎም ነበረ። ሙሉ ስራ ሳይሆን፣ እንዲሁ እዚህም እዚያም ሳነባቸው የወደድኳቸውን እና ስሜቴን የነኩትን አንዳንድ ግጥሞች ተርጉሜያለሁ።
“የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ተርጉሜ ስጨርስ ጉዳዩ ለራሴውም ጥያቄ ሆነብኝ። አንብቤው እዚያው ለመተርጎም የወሰንኩበትን ቁርጠኝነት ከየት አመጣሁት? እስካሁን ለምን ሙሉ ስራ ለመስራት አልተነሳሁም ነበር? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ውስጤ ይመላለሱ ነበር። ይህን ጊዜ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ትርጉም የሞከርኩበት አጋጣሚ ታልሞ እንደተረሳ ህልም ትውስ ያለኝ።
አምስተኛ ክፍል ነበር። I am Legend የተበለውን የሪቻርድ ማቴሰን መጽሐፍ ቤት ውስጥ አግኝቼ አንብቤዋለሁ፤ እንግዲህ በአምስተኛ ክፍል እንግሊዘኛ ምን ያህል ገብቶኝ እንደሆነ አሁን በዝርዝር መግለጽ አልችልም። የማስታውሰው ግን አንዲት ጓደኛዬን “እንተርጉመው” ብያት በጠራራ ፀሐይ ይዘነው ሜዳ ላይ ቁጭ ብለን እንደሞከርን ነው። እንደሚጠበቀው አንድ አረፍተ ነገር እንኳን አልተሳካልንም።
ሥነጽሑፍን በተመለከተ፣ ግጥም እጽፍ ነበር፤ አብዛኛዎቹ በአአዩ ቆይታዬ የተጻፉና ባህል ማእከል የቀረቡ ናቸው። ገጣሚ እንዳልሆንኩ የገባኝ ለታ ግን መጻፍ ተውኩ። ባለፈው አስራ ሁለት አመት ውስጥ፣ እጅግ በጣም ስሜቴን የነኩት ነገሮች ገጥመውኝ አንድ ሶስት ግጥም ሳልጽፍ አልቀረሁም። ፌስቡክ ላይ ተለጥፈዋል። ድሮ የሞካከርኳቸው አጫጭር ልቦለዶችም ነበሩኝ።
ብዙ ጊዜ የምትጠቀሚው የትርጉም ስልት ምን የመሰለ ነው?
ስለ ትርጉም ስልቴ ለማብራራት “ኀሠሣ” ላይ የአርትኦት ስራ የሰራው ይኩኖአምላክ መዝገቡ በአንድ ወቅት ያለኝን ላካፍል። ስለ “ኀሠሣ” አንዳንድ ነገር ለመነጋገር እኔና ሕይወት ተፈራ አግኝተነው ነው። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ቀድሞ አንብቦት ነበረና ስለ ትርጉም ስልቴ የሚያስበውን እንደሚከተለው አጫወተኝ። ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት የሚነበብ ነገር ሲያገላብጥ አንድ ሰው ስለ ተርጓሚዎች በጣልያንኛ የተናገረውን ነገር አግኝቷል። ሰውየው “Traduttore traditore” ነው መሰለኝ ያለው። Translator, traitor ለማለት ነው በእንግሊዘኛ፤ “ተርጓሚ ከሃዲ ነው” እንደማለት።
ማለትም አንድ ሰው የትርጉም ስራ ሲሰራ የሚከናወን የፈጠራ ስራ አለ፣ ምንም ያህል እናት/ምንጭ ስራውን ተቀራርቦ ሊተረጉም ቢሞክር እንኳን፣ የቋንቋ ብቃት፣ የራሱ አመለካከትና ንቃተ ህሊና፣ የራሱ ባህልና ስነልቦና የመሳሰሉት ነገሮችን ይጨምርበታል። ስለዚህ ትርጉሙ ዋናውን ሊመስል አይችልም። ተርጓሚው የራሱን አረዳድ ነው የሚጽፈው፤ በመሆኑም ከሃዲ ነው። ዋናው ባለስራ ወይም ዋናው ስራ ላይ የሚፈጽመው ክህደት አለ የሚል ነገር አጫወተኝና፣ “አንቺ ግን ከሃዲ አይደለሽም” አለኝ በስተመጨረሻ።
ትክክል ነው፤ እናት ጽሑፉ የግድ መጨመርን ወይም መቀነስን ካልጠየቀ በስተቀር (ለሚተረጎምበት ቋንቋ አንባቢዎች ስምም ለማድረግ ሲባል) እንደተጻፈው መተርጎምን እመርጣለሁ። ይህንን ስልት አስቤበት መርጬው አይደለም። እስከዛሬ ትርጉም ስሞክር ልቦናዬ የመራኝ በዚያ መንገድ ስለነበረ፣ መጠቀም የቀጠልኩበት ስልት ነው።
ዕለታዊ አሰራሬ ጠዋት ራሴን ከማስደሰት ይጀምራል። ቁርስ፣ ቡና በትልቅ ኩባያ፣ ትንሽ ፌስቡክ። ከዚያ ስራ፣ ምሳ፣ ለኻያ ደቂቃ ማሸለብ፣ ተነስቶ ስራ መቀጠል፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ስራ አቁሞ ሌሎች የሚያስደስቱኝን ነገሮች ማድረግ።
በሌሎች የስራ ወይም የማህበራዊ ኑሮ ጉዳዮች ያልተረበሸ የስራ ቀኔ ይህን ይመስላል። በእርግጥ በየመሃሉ ቤቴ ውስጥ በተሰናዱት የዘቢብ፣ የቴምር፣ የሱፍ ፍሬ፣ የኦቾሎኒ እና የመሳሰሉት ጣቢያዎች ቆም እያልኩ ነዳጅ እሞላለሁ!
በልብወለድ ትርጉም ሥራ በርካታ የሀገራችን ደራሲዎች ተሰማርተዋል … እኒህን ሥራዎች እንዴት ታያቸው ነበር?
ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ለአማርኛ የትርጉም ስራዎች ከልጅነቴ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ልዩ ስፍራ አለ። በብዛት ስላገኘኋቸውና ተስገብግቤ በማነብበት ወቅት ስለተዋወቅኳቸው፣ አድማሳትን ስላስቃኙኝ ተያይዞም ለተርጓሚዎቻችን ትልቅ አክብሮት አለኝ። እነዚያን ጣዕም የነበራቸው ቀናት የኖርኳቸው በእነሱ ስራዎች ውስጥ ነውና።
ቅርብ ጊዜ እንደገና ያነበብኳቸው እንኳን ጥቂት ናቸው። ደግሜ እንዳየኋቸው ከማስታውሳቸው ውስጥ፣ የከበደ ሚካኤል “ሮሜዮና ዡልየት”፣ የአውግቸው ተረፈ “የትውልድ እልቂት”፣ የለማ በላይነህ “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” እና የሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያምን “የኢየሱስ ሕይወት” በድጋሚ ቃኘት ቃኘት አድርጌያቸዋለሁ።
አሁን እንደተርጓሚ ሳነባቸው ብዙ ሃሳቦች በጭንቅላቴ ውስጥ ይንጋጋሉ፤ ምንን እንዴት እንደተረጎሙት ብልጭታዎች ይታዩኛል። ብዙውን ጊዜ ግን ተርጓሚ መሆኔን ረስቼው እንደአንባቢ ሌላ ቦታ ይወስዱኛል። በተለይ “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” … ስራ አስትቶኝ ያውቃል።
IV
“ኀሠሣ”ን ስትተረጉሚ ከእናቱ ድርሰት (Mine to Win) ወጣ ብለሽ ላለመሄድ እንዴት ሞከርሽ?
ከላይ እንዳልኩት ‘traditore’ ላለመሆን የተቻለኝን ያህል ሞክሬያለሁ። እናት ድርሰቱ የተጻፈበት ዘመን መንፈስ (Zeitgest)፣ የተገለጸው የአኗኗር ሁኔታ፣ የአነጋገር ዘዬ፣ የአመለካከት አጥናፍ እንዳለ ወደ አማርኛ ቢመለስ፣ ትርጉሙ የመጣፈጥ እድሉ ይጨምራል። ደግሞ ይዘቱ ውስጥ የሚገኘው ቅኔ ነው፣ ትምህርት ነው፣ ኢትዮጵያዊ ጥበብና ፍልስፍና ነው ሕግጋትና ማፈንገጦች ናቸው። ለምን ወጣ ብዬ ለመሄድ እሞክራለሁ? ለዛውን ማሳጣት ይሆናል።
የዘመኑን (19ኛ ክ/ዘመን) የንግግር ዘዬ ለማምጣት ምን ስልት ተጠቀምሽ?
ያደረግኩት ዝግጅት የተጠቀምኩትን ስልት ይገልጻል ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ የሥነጽሁፍና የታሪክ ምሁር በሆነ ውድ ጓደኛዬ ትጋት ለዚህ ስራ ዝግጅት ላነባቸው የሚገባኝ መጻሕፍት ዝርዝር ወጣ። እኔም የራሴን አከልኩበት። ከዚህ በኋላ ዝርዝሩ ላይ ያሉትን መጻሕፍት አሰባሰብኩ።
መጻሕፍቱ በአብዛኛው በ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የነበሩ/ያሉ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ዲያቆናት፣ ጸሐፌ ዜና መዋዕሎች፣ ደራሲዎች የጻፏቸው፣ ወይም ስለእነሱ የተጻፉ ናቸው። አንዳንዶቹ እኔ ራሴ ቤት ውስጥ ነበሩኝ፣ ሌሎች በግዢ፣ በውሰት ወይም ከበይነ መረብ በማውረድ (ለምሳሌ: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መጻሕፍት) የተገኙ ናቸው።
ቀን ቀን መሰረታዊ የትርጉም ስራውን እየሰራሁ ማታ ማታ እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ ጀመርኩ። እያነበብኩም ሊጠቅሙኝ የሚችሉ ቃላትን በማስታወሻ እየሰበሰብኩ የራሴን ትንሽዬ ሙዳየ ቃላት አዘጋጀሁ። በእርግጥ ከዚህ በፊት የቤተሰብ አባላት ሲነጋገሩ በምሰማበት ወቅት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወቅት፣ በንባብ ወቅት፣ ካገኘኋቸው ቃላት በትውስታዬ የተገኙትን ሁሉ በረቂቁ ውስጥ ተጠቅሜባቸዋለሁ።
በመቀጠል ረቂቁን የማበልጸግ የመጀመሪያ ዙር ስራ ስሰራ ያጠራቀምኳቸውን ቃላት እንደሁኔታው ቦታ ቦታ አገኘሁላቸው። ከገጠር የኑሮ ዘይቤና ከቤተክርስቲያን ስርዓት ጋር የተያያዙ ብዙ ቃላትን እናቴ ጠቁማኛለች። በአቅራቢያችን ከሚገኘው ሰዓሊተ ምህረት ቤ/ክ የነበሩ ካህን አገናኝታኝ በቃለመጠይቅ ብዙ መረጃ ሰጥተውኛል።
በዚህ ጊዜ በብዛት ያገኘኋቸው መጻሕፍት የተጻፉት በሸዋ ልሂቃን እንደመሆኑ የረቂቁ አማርኛ የሸዋ አማርኛ ያመዘነበት ይመስለኛል። ጥንታዊዎቹን መዛግብተ ቃላትና ተጨማሪ መጻሕፍትን በመጠቀም በበኩሌ የተቻለኝን ያህል የጎጃምን ዘዬ ለማምጣት ከሰራሁ በኋላ የቀረውን አርታኢዎች እንዲያዩት ተውኩላቸው። ያጎደልኩትን ሞሉልኝ፣ ያጣመምኩትን አቀኑልኝ።
ገና የእንግሊዘኛውን መጽሐፍ ማንበብ ስጀምርና ታሪኩ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ እንደሚያጠነጥን ስረዳ፣ የተገለጸልኝ ነገር የሚተረጎምበት አማርኛ የገጠር አማርኛ ብቻ ሳይሆን፣ የድሮ የገጠር አማርኛ መሆን እንዳለበትም ጭምር ነው። በዘመን ሂደት ቃላትም ጡረታ ይወጣሉና የተገኘው የገጠር አማርኛ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፤ የቆየ መሆን አለበት፣ አሁን እምብዛም የማንሰማው፣የማንናገረው። ስለዚህ ‘ወደፊት’ ሳይሆን ‘ግፋኝ’ ጊዜውን የበለጠ ያሳያል …
ቅድመ አያቴም፣ አያቴም ለምሳሌ “ተነስተሽ የማትሄጅ?” ሲሉ ሰምቼ አላውቅም። “ተነስተሽ እማትሄጅ?” ግን ይሉ ነበር። አርታኢዎችም በዚህ መንገድ የመጻፉን ሃሳብ አቅርበው ተቀብዬዋለሁ።
“ከ = ተ/ኸ” (ተአፋቸው፣ ታልኾነ፣ ኸቤታቸው)
“መ = ም” (ምንደር)
“ሄ = ኸ” (መኸድ)
“ሂ = ኽ” (እንኽድ)
መጀመሪያ ላይ በንግግሮች ላይ ብቻ ነበር እንዲህ አይነቱን አደማመጽ የተጠቀምኩት። በኋላ ግን መጽሐፉ የሚተረክልን በአንደኛ መደብ፣ በተዋነይ በራሱ ስለሆነ፣ ለተዋነይ የራሱን የአነጋገር ዘዬ (accent) ብሰጠውስ ብዬ አሰብኩና ነው። ሌሎች ሰዎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከእሱ ጋር ሲያወሩ የተናገሩትንም የሚጽፍልን እሱው ስለሆነ በተመሳሳይ መንገድ እዚያም ላይ ተጠቅሜዋለሁ።
መጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው እንደ ዐወቀ፣ አባ እና ሠረገላ ብርሃን ያሉ ሌሎች አውራ ገጸባሕሪያት ደግሞ፣ እንደው ሁሉም አንዳይነትና ልሙጥ እንዳይሆኑ ትንሽ የአነጋገር ልዩነት ቀለም ልቀባባቸው ሞክሬያለሁ።
“ሁ = ኹ” (ኹለት፣ ተነሳኹ)
“ሆ = ኾ” (ታልኾነ)
“አ = ዐ” (ዐዘንሁኝ፣ ዕርሻ)
መቼም 100% ተሳክቷል ብዬ አፌን ሞልቼ ባልናገርም፣ አማርኛ እንዳሁኑ ሳይሆን፣ ከሞላ ጎደል በግዕዝ ፊደላት በሚጻፍበት ጊዜ ቃላቱ የሚጻፉበትን መንገድ ለመከተል ስለመረጥኩ ነው፤ ትርጉሙ ጊዜውን እንዲመስል። እንዳልኩት ታሪኩ የሚተረክልን በአንደኛ መደብ፣ በዋናው ገጸባሕሪ በተዋነይ ነው፤ ተዋነይ ደግሞ ሐዲስን ጠንቅቆ ጸሐፌ ዜና መዋዕል ለመሆን የታጨ ሊቅ ነው። አማርኛውን ዛሬ እኛ እንደምንጽፈው እያቀላቀለ ወይም የግዕዝን ድምጾች ባስወገደ መንገድ ይጽፈዋል ተብሎ መቼም አይጠበቅም ብዬ በማሰብ ነው።
የቻልኩትንም ያህል ዋና ዋናዎቹን መዛግብተ ቃላት በመመልከት ለቅሜ ለመጠቀም ጥረት አድርጌያለሁ።
ከላይ እንዳልኩት ለጊዜውና ለቦታው እውነተኛ (authentic) በሆኑ ቃላት ነገሮችን ለመግለጽ መሞከሬ እንዳለ ሆኖ፣ አንዳንድ ቃላት በጣም ዘመናዊ (modern) ወይም ዘመነኛ (contemporary) ሲመስሉኝ ቆየት ያለውን እቻቸውን ለመፈለግ ሞክሬያለሁ። አንዳንዴ አሁን ባለንበት ጊዜ እስኪሰለቹ ድረስ የምንጠቀማቸውን ቃላት በደራሲዋ ሕይወት ምክር የቀየርኳቸው ይኖራሉ፤ ለምሳሌ: ታዳሚው፣ ታዳሚያንን ትተን ‘እድምተኛው’ን መጠቀም መረጥን።
ከሕይወት ተፈራ ጋር የነበራችሁ የአሠራር ሂደቱስ?
ትርጉሙን ጨርሼ ነው የሰጠኋት። ያው የመጀመሪያው ምእራፍ የተወዳደርኩበት ነው። ሌሎቹን ጨርሼ፣ በተደጋጋሚ አንብቤና አርሜ ሙሉውን ነው የሰጠኋት።
የስራው ሂደት እጅግ አስደሳች ነበር። ሕይወት ተፈራ በጣም አስተዋይ ናት፤ የረሳሁት መስመር ወይም በተሳሳተ መልኩ ተረድቼው የተረጎምኩት መስመር አያመልጣትም፤ የራሷን መጽሐፍ በልቧ ታውቀዋለች። በመሆኑም ረቂቁን አንድ ሶስቴ ኦዲት አድርጌዋለው፤ የጠፉ አናቅጽና መስመሮች እንዳሉ ቆጠራ።
ያልመሰላት ጉዳይ ላይ በግልጽ ታዋየኛለች፣ ታደምጠኛለች። ወይ አሳምናታለሁ፣ ወይ ታሳምነኛለች። የመጨረሻ ውሳኔ የእሷ ቢሆንም፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ እስከመጨረሻ ድረስ እንከራከር ነበር። ስለዚህ ራሴን ለመግለጽና ለማስረዳት ምንም ገደብ አላበጀችብኝም። አንዳንዴ እንዴት አድርጌ ሳዋራት እንደነበር ቤት ገብቼ ሳስበው፣ እንደ እኩያዋ እንዳዋራት ያስቻለኝን ድባብ እንደምን እንደፈጠረችው ይደንቀኛል።
የትርጉሙን የመጀመሪያውን ረቂቅ አንብባ በመደሰቷ የራሷን መጽሐፍ “ለካ እንዲህ ቆንጆ መጽሐፍ ነበርንዴ?” ያለችኝ ዕለት፣ እኔም እጅግ ደስ ተሰኝቼበታለሁ።
መጽሐፉን አሁን መለስ ብለሽ ስታይው ትርጉምሽ ላይ ምን ማስተካከል ትፈልጊ ይሆን?
አንዳንድ አሁንም መስተካከል የሚችሉ ነገሮች አይጠፉም። ያው ለረጅም ጊዜ ከእጅህ ሳታወጣ ልታስተካክለው፣ ልታሰማምረው የምትችል ይመስልሃል። ግን የሆነ ቦታ ይህ ሂደት መቋረጥ አለበትና ነው እርማት ማድረግን የምታቆመው። በመሆኑም ትርጉሙን ያነበቡ እንዲሁም የገመገሙ ሰዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ባለማወቅ፣ በእንዝህላልነት ወይም በተሳሳተ ምክር ምክንያት የተፈጠሩ መስተካከል የሚችሉ ነገሮች ታይተውኛል። ከነዚህ ውጪ ምንም ማከልም ሆነ ማንሳት አልፈልግም።
በሁለተኛው እትም ላይ ያስተካከልነው የተወሰኑ የፊደል ግድፈቶችን፣ እና አንድን ቃል በተለያዩ ሆሄዎች በመጻፍ የተሰሩ ስህተቶችን ነው። በተጨማሪ፣ ኀሠሣ ላይ የእንግሊዘኛው ርእስ (Mine to Win) ሳይካተት ነበርና የታተመው፣ እንግሊዘኛው መውጣቱን ያላወቁ ሰዎች የየትኛው መጽሐፏ ትርጉም እንደሆነ ጥያቄ ስላበዙ፣ ይህንንም አንድላይ አርመናል። እንዲህ አይነት ትናንሽ እርማቶች ናቸው እንጂ ይዘቱ ላይ የተደረገ ለውጥ የለም።
ከትርጉም ሥራዎች በተጨማሪ የራስሽ ወጥ ድርሰቶች እንዳሉ ትንሽ ብታጫውቺን …
በአሁኑ ሰዓት አቋርጬው የነበረ አንድ ረቂቅ የረጅም ልብወለድ ስራ እጄ ላይ አለ። በቅርቡ እመለስበትና እጨርሰዋለሁ ብዬ አስባለሁ። ያለፈው አርባ አመት የፖለቲካ ታሪካችን በሁለት ትውልድ ደጋግሞ የሚበጠብጠው ቤተሰብ ታሪክ ነው ባጭሩ።
የትርጉም ሂደትሽና የድርሰት አጻጻፍሽ ስልትሽ እንዴት ይለያል?
ከአሰራር ልማድ (routine) አንጻር ልዩነት የለውም። ከክህሎት አንጻር ግን አሁን ጀማሪ ተርጓሚ አይደለሁም፤ ግን ጀማሪ ደራሲ ነኝ፤ ሙልጭ ያልኩ አማተር። ስልቴን ገና እያፈላለግኩት ነው። ኀሠሣ ስልት ላይ ነኝ ማለት ይቻላል።
የሚቀጥለው ሥራሽ ምን ላይ የሚያተኩር ነው?
ወጥ ስራን በተመለከተ፣ ከላይ በአጭሩ አስቀምጬዋለሁ። ትርጉምን በተመለከተ፣ በአሁኑ ሰዓት ቅርብ ጊዜ ገበያ ላይ ውሎ ተወዳጅነት ያተረፈውን የዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉን “መንገደኛ” ወደ እንግሊዘኛ እየመለስኩ እገኛለሁ። ሌሎችም ልተረጉማቸው የምፈልግ መጻሕፍት አይጠፉም።
እናመሰግናለን።
እኔም አመሰግናለሁ
ሕይወት ታደሰ
(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)
መስከረም 2010 ዓ.ም