“ያጼ በካፋ በግ” (ወግ)

“ያጼ በካፋ በግ”

.

.

አፄ በካፋ አንድ የሚወዱት ለማዳ በግ ነበራቸው። ሲቀላውጥ ይውልና አዳሩ ከእልፍኛቸው ነው የሚያድር። የመወደዱ ብዛት አዋጅ ወጣለት። “ያጼ በካፋ በግ በገባበት ቤት ሳይጋበዝ የቀረ እንደሆነ አይቀጡ ቅጣት እቀጣለሁ” ተባለ።

እንደ አቀማጠሉት ታውቆት ቅልውጡ ባሰበት። በቅልውጡ የተነሳ ሰው አጥብቆ ተመረረ። ቅልውጡ ቀርቶ ከደጅ የሚሰጣውን ያወድማል።

እንዲህ እያስለቀሰ ሲኖር አንድ ቀን ሲፈርድበት ከአንድ ደብተራ ቤት ዘው አለ። ደብተራው “እንኳ የመጣህልኝ” ብሎ ሲያበቃ ደጁን ዘግቶ እንክት አርጎ አረደው። ሥጋውን ዘልዝሎ ኸጓዳው ሰቀለ። የበጉ አመል የትም ሲቀላውጥ ውሎ አዳሩ ከንጉሡ እልፍኝ ነበር። ሲጠፋ ጊዜ በያለበት ፈልጉ ተባለ።

ወደ ተንኮለኛ ደብተራ እንመለስ።

የበጉን ደበሎ ብራና ፋቀው። ቀጥሎ ብራናውን በትንንሽ ቆራርጦ በቍራጮቹ፣

“የንጉሡን በግ እኔ ነኝ አርጄ የበላሁት። ጮማ ነበር። መጣፈጡም ግሩም ነው። መታረዱም ይገባዋል። መክለፍለፍ አብዝቶ ድሀ አስለቅሷልና”

ብሎ ጽፎ ቁራጮቹን ወስዶ በስውር ሰው እንዳያየው አርጎ ካደባባይ በተናቸው።

መቸም በከተማው የንጉሥ ባለሟል ጠፍቷል ተብሎ በያለበት ፍለጋ ተይዟል። ሁለት ወይ ሦስት ሰዎች ቁራጮች አይተው አንስተው አንብበው ለንጉሡ አደረሱ።

በተነበበ ጊዜ ንጉሡ እጅግ አጥብቀው ተቆጡ፡

“እንዴት አባቱ ያለ ደፋር ነው! ተማረዱ ጽፎ አደባባይ ብራናውን መበተኑ። ቆይ ሳትያዝ የቀረህ እንደሆነ”

አሉና በምስጢር አርገው፤

“ስስ ወርቅ አምጡና መዝኑ። ተተመዘነ በኋላ ወስዳችሁ ከግቢው አደባባይ ዠምራችሁ እስከ አውራው ጐዳና በትኑት። ቀጥላችሁ የታመነ የታመነ ዘበኛ ተተነሰነሰው ወርቅ እልፍ ብለው ቆባ ብለው አጐንብሶ የሚያነሳውን ሰው ይያዙ” ብለው አዘዙ።

መቼም ሌባና አጥፊ እንቅልፍ የለው የሚወራውን የሚሆነውን ሁሉ ተጠንቅቆ እህ ይላል። በብልሃቱ ብዛት የበጋቸው ሌባ የወርቅ ወጥመድ መጠመዱን አወቀ።

“ቆይ እዚህማ ብልሃት አለኝ” ይልና ቶሎ መጫምያ አሰፍቶ ታቹን ምድር የሚረግጠውን ወገን በሰም መረገው። ቀጥሎ መጫምያውን አጥልቆ ጥምጥሙን አሳምሮ ጠምጥሞ መቋምያውን ይዞ አንጓቦ ወርቅ በተዘራበት መንገድ አረጋገጡን ወደ ምድር ጫን እያደረገ እየረገጠ ወርቁ ከሰሙ ውስጥ እንዲጠልቅ ነው ብልሃቱ።

እንደዚህ እየሆነ እየተንደላቀቀ ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላለሰ። ከቤቱ እየገባ የተለጠፈውን ወርቅ እያነሳ እያስቀመጠ አንድም ሰው ሳያውቅበት ማታ በሆነ ጊዜ “እስኪ ወርቁን አንሱትና መዝኑት” ተባለ። ቢመዝኑት ቅምጥል ብሎ ጐደለ። ለንጉሡ ይኼንን ቢያሰሙ የባሰውን ተናደዱ።

ዘበኞቹም “እኛ ኩስትር ብለን ነው የጠበቅነ ዳሩ ግን አንድም ሰው አጐንብሶ ሲያነሳ አላየነ” አሉ።

ንጉሡ ቢቸግራቸው “ጠንቋዮች ጥሩ” ብለው አስመጡ። “እንደዚህ ያለ ሥራ የሚሰራ የት ነው የተቀመጠው?“ ብለው ጠየቋቸው። ከገሌ አፈር ላይ ነው ብለው አሉ።

ወታደር ሂዱ ያዙ ተብሎ ታዞ ይሄዳል ግን ማንም አያገኙ። ስለምን ደብቴ እጅግ ብልህ ነውና የሚያረጉትን ሁላ አውቆታል። ለዚህ ብልሃት ተአራት አምስት አገር አፈር አስመጥቶ ከቤቱ ውስጥ አስቀምጦ ከዝያ ላይ ይቀመጥበታል። ያገሩን አፈር እያለዋወጠ ማለት ወታደር ታዞ ሲሄድ ጠንቋዮቹ በመሯቸው ስፍራ ሰውየውን ያጡታል። የተቀመጠበትን አፈር ትቶ ከሌላ አፈር ላይ ይቀመጣል። ወታደሩም በከንቱ ማሰኑ ጠንቋዮቹም ተነቀፉ።

ንጉሡም የባሰውን ተናደዱ። ከዚህ ወዲህ ቆይ ሌላ ብልሃት አለኝ ብለው ሚስጢርዎን በሆድዎ ከተው ድግስ ደገሱ። አለቆች፣ ካህናት፣ ተማሪ፣ ደብተራ የተባለ ሁሉ ትምህርት የጠቀሰ ሁሉ ግብር እንዲበላ አዘዙ። በዚህ ማኽል የታመኑ የታመኑ ሰዎች በምስጢር አርገው መርጠው አሰናዱ።

“ድግሱ በደረሰ ጊዜ እነዚህን የተመረጡትን ሰዎች ካህናቱ ሁሉ ገብተው ሲበሉ ሲጠጡ መጠጡን በገፍ አርጋችሁ ስፍራውን ተከፋፍላችሁ ይዛችሁ ኮስተር ብላችሁ ጠብቁ። በመጠጥ ብዛት የተነሳ ያ ተንኮለኛ ለባልንጀራው ሳይለፈልፍ አይቀርምና በሰማችሁ ጊዜ ለምለም ዦሮውን በስለት ቀንጥቦ ምልክት እንዲሆን ነው” ብለው አዘዙ። “ካህናቱ ጠዋት ሲወጡ ከዦሮው ምልክት ያለበት እንዲያዝ” አሉ።

እውን እንዳሉትም በመጠጥ ብዛት የተነሳ ደብቴ ተቸነፈና ለባልንጀራው ተበጉ መታረድ ጀምሮ እስከ ወርቁ እስከ ጠንቋዮቹ ድረስ የሆነውን ሁሉ ዘከዘከለት። ይህን ሁሉ ሲዘከዝክ በዠርባው በኩል የቆመው ሰላይ ወደነሱ ዦሮውን ጣል አርጎ ኑሮ አንዱ ሳያመልጠው ሁሉን ሰምቷል። በስካር ብዛት የተነሳ ሁሉም ተረፍርፎ እንቅልፍ ወስዷቸው ያ የሰማው ሰላይ ይህን ጊዜ ነው ብሎ ለምለም ዦሮውን ቀነጠበ።

ደብቴ ብዙ እንቅልፍ ተተኛ በኋላ ዦሮው ቆጠቆጠው። በጁ ቢዳብስ ዦሮው ተቀንጥባ “አሁን ገና ተያዝሁ” ይልና አያሌ ተማሪዎችና ደብተሮች ከተረፈረፉት ለምለም ዦሮዋቸውን ቀነጠበ። እንዳይነጋ የለም ነጋ። መቼም ያ ሰላይ የደብቴን ዦሮ የቀነጠበ ለሽልማቱ ሲል የምስራችን አድርሷል። ንጉሡም ደስ ብሏቸው “ምንየ በነጋ” ብለው ቸኩለዋል።

ሲነጋ “በሉ እንግዴህ ካህናቱንና ተማሪውን ሁሉ አስወጡ። ያ ለምለም ዦሮውን የተቆረጠውን ያዙና አምጡ” ብለው አዘዙ። ካህናት በወጣ አያሌ ለምለም ዦሮዋቸው ተቆርጦ ይህንን ነገር ለንጉሡ ባስታወቁ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናደዱ። ቀጥለውም የምስራች ቀናኝ ብሎ ያለኝን ይጠራ አሉ።

በመጣ ጊዜ “በል አንተ አብደሃልን? ይህን ሁሉ ያዛውንት ጆሮ ቁረጥልኝ ብየኻለሁን” አሉት።

“እኔስ ንጉሥ ሆይ ያንድ ተማሪ ለምለም ዦሮውን ብቻ ነው የቆረጥሁት” አለ።

ንጉሡም “እንግድያውስ ይህ ሸረኛ ደብተራ ሲነቃ የሰራውን ሥራ ዦሮው አስታውሶት ተነስቶ የነዚህን ሁሉ ተማሪ ዦሮ መንድቧል” አሉ።

ተዚህ ወዲህ በደብቴ ብልሃት ተገርመው እንደዚህ ያለ ብልህ ተመቅጣት ይልቅስ ሸልሞ መሾም ይበልጣል ለመንግሥት ይጠቅማል ብለው አውጥተው አውርደው አስበው፣

“ነጋሪት ይውጣ አዋጅ ንገሩ የንጉሥን በግ የበላ ደብተራ ምሬአለሁ። ከቶም ሸልሜ እሾመዋለሁ። ላልከዳ ምያለሁ። ይምጣ አይስጋ ብላችሁ አስታውቁ” ብለው አዘዙ።

አዋጁም ተነገረ።

ደብቴ ይኼንን አዋጅ በሰማ ጊዜ አጥብቆ ደስ ብሎት ጌጡን አጋጊጦ ሲደለቅ ወደ አደባባይ ብቅ ብሎ ላጋፋሪ ለንጉሡ መምጣቱን እንዲያስታውቅለት ለመነ። አስታወቀ ተጠርቶ ገባ።

“ስማ ተጀምሮ እስከ ድግሱ ድረስ እንደምን አደረግህ” ብለው በመልካም ዓይን አይተውት ጠየቁት።

እርሱም ተጀምሮ እስኪጨርስ ያደረገውን ሁሉ አፈሰሰ።

ንጉሡም ቃሉን ሁሉ ሰምተው ተገረሙ። ወድያውም ሾሙት።

.

[ምንጭ] – Major J. Eadie. 1924. “An Amharic Reader”. pp. 7-11.

“አሞራ … የዳዊት አሞራ” (ግጥም)

“አሞራ … የዳዊት አሞራ”

በዣን ተኵላ

.

[1400 ዓ.ም]

.

Dawit 1

Dawit 2

Dawit 3

Dawit 4

Dawit 5

Dawit 6

.

.

በዘመናችን አማርኛ …

(ትርጉምና አሰናኝ)

በዕውቀቱ ሥዩም

.

.

“አሞራ የዳዊት አሞራ

ተከተለኝ ከኋላ፤

.

ላቅርብልህ ሥጋ ብላ

ላጠጣህ ወይ ደም መራራ

ተከተለኝ እኔ ልምራ፤

.

እየመተርሁ በካራ

እየወጋሁ በጦር ጣምራ።

.

ብንበላብህ አደራ

በገላችን ጦር ይዘራ፤

ክንፍ አውጥተን ብንሸሽም

ቀስትህ ትውጋን ተወርውራ።

.

ምንም ሆድ ቢብሰን እኛ አንበላም መሐላ

ገላችን ይምሰል እንጂ የፈጠጋር አምባራ

አፋችን ይምሰል እንጂ ባልቴት ምትሞቀው እንሶስላ

ጣታችንም ይምሰል ጭራ የጎረሰ ደም አበላ፤

.

ጭፍሮች ነነ የዣን ተኵላ

እኛስ አንበላም መሐላ!”

.

.

.

[በ1400ዎቹ አማርኛ በድጋሚ]

.

“አሞራ የዳዊት አሞራ

ተኸተለኝ በኋላ፤

.

ሥጋ አበላኽ ሐበላ (ከበላ)

የደም አጠጣኽ ነተራ (መራራ)

ተኸተለኝ በኋላ፤

.

ወግዕቼ በቃራ (በካራ)

ሰኽቼ በጸመራ። (በጣምራ)

.

እኛስ ብንበልዓኽ መሐላ

ለጾር ይስጠን ለወርወራ፤ (ውርወራ)

የከንፍ ብናደርግ ጽላ

ለቀስት ይስጠን ለቀፈራ። (ለወጠራ)

.

ምን ከበአሰን ንበልአኹ መሐላ (እንበላለን)

ገላችን ከመሰል የፈጠጋር እምብላ (አምባር)

አፈችን ከመሰል በዓልቴት የገባች እንሶስላ

ፀዓታችን የመሰል በደም የዘራ ጭራ (ጣታችን)

.

ስማችን የዣን ተኵላ

አንበልዓም መሐላ። (አንበላም)

.

የዣን ተኩላ

[ከአፄ ዳዊት ሠራዊቶች የአንዱ ስም]

(1400ዎቹ)

.

[ምንጭ] – Ms Bruce 88። Oxford Bodleian Library። ቅጠል 37ሀ።

 

“መሐመድ ኢድሪስ” (ቃለመጠይቅ)

“ቆይታ ከመሐመድ ኢድሪስ ጋር”

(ቃለመጠይቅ)

.
[ከአንድምታ ጋር የተደረገ ውይይት]

.

[አብዛኞቻችን መሐመድ ኢድሪስን በተወዳጁ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ በሚያቀርባቸው አጫጭር ልብወለዶቹ እናውቀዋለን። ከአጭር ልብወለዶች ባሻገር በርካታ የፊልም ጽሑፎችን ደርሷል። ባለፈው ዓመትም “ሣልሳዊው ዐይን” የተሰኘ ግሩም የአጭር ልብወለዶች ስብስብ መጽሐፍ አሳትሟል። አንድምታ መሐመድን በቅርቡ በሥነጽሑፍ ዙርያ አነጋግራው ነበር።]

.

እስቲ ስለ ልጅነትህ ትንሽ ብታጫውተን?

የልጅነት ጊዜዬ፣ በጣም ወርቃማ ነበር። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያስተላልፋቸው የነበሩትን “ሙን ላይቲንግ”፣ “ፔሪ ማሰን”፣ “ትዋይላይት ዞን” የመሳሰሉትን ተከታታይ ፊልሞች እያዬሁ ነበር ያደግሁት።

ሰፈሬ አምባሳደር ሲኒማ ቤትም እገባ የነበረው፣ ከስድስት እስከ ዐሥራ ኹለት ሰዐት፥ ሦስት ፊልም፣ በሦስት ብር፥ በነበረበት ጊዜ ነበር። የቻርለስ ሑስተን እና የዮል ብሬነርን “ዘ ቴን ኮማንድመንት” ከሠላሳ አምስት ዓመት በፊት ነበር ያዬሁት። ያኔ ያዬኋቸው ፊልሞች፣ የሥነ ጽሑፍ እና የሲኒማ ፍቅር፡ እንዲሁም ደግሞ፥ ዕውቀት ሰጥተውኛል።

የመጀመሪያ አጭር ልቦለዴን የጻፍሁት፣ ስድስተኛ ክፍል እያለሁ ሲኾን፤ “ፀሐይን የጎበኘው ሰው” የተሰኜ ሳይንስ ፊክሽን ነበር።

ከ “አዲስ አድማስ“ ጋዜጣ ጋር እንዴት ግንኙነት ጀመርክ?

እኔ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፥ መጻፍ የጀመርሁት በ1993 ዓ·ም ነው። የመጀመሪያ ጽሑፌም፣ “ውዱ ስጦታ” የሚል አጭር ልቦለድ ነበር። በዛ ወቅት፣ አሰፋ ጎሣዬ በጣም ያበረታታኝ ነበር።

ወደ አጭር ልብወለድ ደራሲነት እንዴት ልታመዝን ቻልክ?

የአጭር ልቦለድ ጸሐፊ የኾንሁት፣ አስቸጋሪና ጥበብ የሚጠይቅ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ስለኾነና ስለሚያስደስተኝም ጭምር ነው። የታሪኮቼ ፍሰት፣ እንደፊልም የሚኾነው፥ ስጽፍ የሚታዬኝ፡ እንደዛ ስለኾነ ነው።

“ሣልሳዊው ዐይን“ የተሰኘው መጽሐፍህ አዘገጃጀት ሂደት እንዴት ነበር?

“የሣልሳዊው ዐይን” ዝግጅት፣ በጣም ጥሩ ነበር። በዋናነት፣ ከዚህ በፊት ጋዜጣ ላይ ወጥተው የነበሩትን ታሪኮች፣ ማስፋት ያስፈልግ ነበር። አድካሚ ቢኾንም፤ አስደሳች ነበር። ጥሩ ኤዲተር ስላገኘሁ፥ ሥራው፣ ሊሳካ ችሏል።

“የእኩለ ሌሊት ወግ“ እና ”የጉንዴ ቀለበት“ የተሰኙት ልብወለዶችህ ጀርባ ስላለው ታሪክ እስቲ ብታጫውተን …

“የእኩለ ሌሊት ወግ” የተጻፈው፣ «የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ፣ በፈጣሪ የተጻፈ ነው» ከሚለው፣ የእስልምና አስተምህሮ፥ ተነሥቶ ነው። “የጉንዴ ቀለበት” ደግሞ፣ ከራሴ የግል ሕይወት ተነሥቼ፥ የጻፍሁት ታሪክ ነው። ጉንዴ፣ በኔ ሕይወት ውስጥ ያለች፥ ጓደኛዬ ነች። ጉንዴን፣ በአጭር ልቦለድ መጻፍ፥ ከባድ ቢኾንም፤ ለማሳየት ግን ሞክሬያለሁ።

ከቀጣይ ስራዎችህስ ምን እንጠብቅ …የትኛውስ ቀድሞ ይወጣል?

በቅርቡ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወጣ፥ “ሞያተኛው ቀብር አስፈጻሚ” የተሰኘ አጭር ልቦለድ አለ። በቀጣይም፣ “የበጋዋ እመቤት” በሚል ርእስ፥ ሌላ አጭር ልቦለድ ይቀጥላል። ከአኹን በኋላ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፥ በየዐሥራ አምስት ቀን፥ ለመጻፍ ዕቅድ አለኝ።

በመጽሐፍ ደረጃ ደግሞ፣ “ሞገደኛው” የሚል ሳይንሳዊ ልቦለድ ለመጻፍ አስቤያለሁ፤ በፈጣሪ ፈቃድ።

እናመሰግናለን።

እኔም አመሰግናለሁ!

.

መሐመድ ኢድሪስ

(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)

መስከረም 2010 ዓ.ም

.

“የእኩለ ሌሊት ወግ” (ልብወለድ)

“የእኩለ ሌሊት ወግ”

በመሐመድ ኢድሪስ

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

.

አራት ሰዎች ነን። በአንደኛው ጓደኛችን ቤት ውስጥ ተቀምጠናል፤ ጫት እየቃምን።

የመሸግነው ደግሞ አውቶቡስ ተራ ነው። ጊዜው፣ የረመዳን ጾም ወቅት ስለኾነ፤ ገንዘብ ካለ፥ ኻያ አራት ሰዐት ጫት መግዛት የሚቻልበት ሰፈር ነው፤ አውቶቡስ ተራ። ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ላይ፥ ሦስተኛውን ዙር ጫት፥ አንዱ ጓደኛችን ይዞ መጣ።

እንዳጋጣሚ ኾኖ፣ የወሬያችን አርእስት ሁሉ ስለ ሞት ነበር። አንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙኀን አርእስት ኾኖ የሰነበተውንና የገዛ ሚስቱን ገድሎ እራሱን ያጠፋውን ሰውዬ አንሥተን ብዙ ከተጫወትን በኋላ ግን የጨዋታችን መንፈስ ተቀየረ።

እኔ፣ ‘በቅርቡ የሞተው ጓደኛችንም፣ መጠጥ ቤት በተፈጠረ አምባጓሮ ውስጥ ባይገባ ኖሮ፥ አይሞትም ነበር’ ስል፤ ሁለቱ ጓደኞቻችን፣ የተለያየ አቋም ይዘው፥ መነታረክ ጀመሩ። አንደኛው ጓደኛችን፣ ‘ሰው፣ ተጠንቅቆና እራሱን ለጥቃት ሳያጋልጥ ከኖረ፥ ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል’ የሚል፤ ሌላኛው ጓደኛችን ደግሞ፣ ‘ማንኛውም ሰው፣ የቱንም ያህል ቢጠነቀቅና ቢታገስ፥ ከተጻፈለት ቀን ሊያመልጥ አይችልም’ የሚል አቋም ይዘው ነበር።

ሦስተኛው ጓደኛችን ግን፣ በተመስጦ ሲጋራውን እያጬሰ፥ ዝም ብሎ ያዳምጥ ነበር፤ ይሥሐቅ ይባላል።

ይሥሐቅ፣ ረጅምና ወፍራም የሽያጭ ሠራተኛ ነው። ብዙ መጻሕፍትን አንብቧል። ለብዙ ዓመታት አውሮፓ ውስጥ ኖሯል። አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በእንግሊዝ ሀገር ውስጥ ነው።

“እሺ፤ አንተስ ምን ትላለህ?” ስል፤ ጠየቅሁት።

በዕድሜ፣ በዕውቀትና በሕይወት ልምድ ስለሚበልጠን፤ እሱ የሚለው፣ ሁላችንንም ሊያስማማን እንደሚችል አስቤያለሁ።

“ከዚያ በፊት፣ አንድ እውነተኛ ታሪክ ላጫውታችሁና እራሳችሁ ትፈርዳላችሁ።” አለ።

ሁላችንም፣ የሚለውን ለመስማት፥ ድምፃችንን አጠፋን። ክፍሉ፣ ጸጥ-እረጭ አለ። ጊዜው፣ ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ከዐሥር ነበር።

“…በደቡባዊ ለንደን የሚኖር አጎት ነበረኝ…” ሲል ጀመረ።

“…ልክ እንደኔው ወፍራም። ዕድሜው ወደ ስድሳ ይጠጋል። በጣም የተማረ፣ ከልክ ያለፈ የዊስኪና የሲጋራ ሡሠኛ ነበር። ሌላው ቀርቶ፣ እመንገድ ላይም እንኳ ቢኾን ባሰኜው ጊዜ ሁሉ እንዳይቀርበት፥ ከአሉሚነም የተሠራ የዊስኪ መያዣ ዕቃ ነበረው። ዊስኪውን በዚያ ቆርቆሮ ውስጥ ይገለብጥና ቀኑን ሙሉ ሲያንደቀድቅ ይውላል። ይታያችሁ፤ በረዶና ሶዳ እንኳን አይጠቀምም፤ ደረቅ ዊስኪ ነው እንደ ውኃ የሚጨልጠው…

“…አንድ ቀን፣ የመረመረው ዶክተር፥ ‘ባጭር ጊዜ ውስጥ መጠጥና ሲጋራ ካላቆምህ፥ ሕይወትህ አደጋ ላይ ነው!’ ይለዋል፤ ‘ከባድ የልብ ድካም በሽታ ስላለብህ፥ ከመጠን ያለፈ የአካል እንቅስቃሴ አታድርግ’ም ይለዋል። እኔ፣ እስካኹን የሱን ያህል ሞትን የሚፈራ ሰው አላየሁም። የሚገርማችሁ፣ የዶክተሩን ማስጠንቀቂያ ከሰማ በኋላ፥ ሲጋራ፣ እርግፍ አድርጎ ተወ፤ ከልክ ያለፈ የአካል እንቅስቃሴ ላለማድረግም ይጠነቀቅ ነበር። መጠጥ ግን፣ ሊያቆም አልቻለም።…

“…አንድ ቀን ጠዋት፣ ስልክ ይደወልለትና፤ ጓደኛው፣ እቤት ውስጥ በተፈጠረ የእሳት ቃጠሎ፥ ተለብልቦ፤ ለመሞት እያጣጣረ እንደኾነ ይነገረዋል። በፍጥነት ወደ ተባለው ሆስፒታል ይሄዳል። ጓደኛው፣ በፋሻ ተጠቅልሎ፥ አልጋ ላይ ተኝቷል። ምንም አልተረፈም፤ ፊቱ የሌላ ፍጡር መስሏል። አጎቴ፣ ጓደኛው፣ በደቂቃዎች ዕድሜ ውስጥ እንደሚሞት አወቀ።…

“…ቀስ ብሎ ጆሮውን ሲያስጠጋ፤ ‘አየሁት!’ ይለዋል ጓደኛው፤ ትንፋሹ ከፍና ዝቅ እያለ። አጎቴ፣ ጓደኛው የሚቃዥ ይመስለውና ሊያረጋጋው ፈልጎ፥ ‘አይዞህ! ሐኪሞቹ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ትድናለህ!’ ይለዋል። ጓደኛው ግን፣ በተስፋ መቁረጥ ፈገግ ብሎ፥ ‘አልድንም! ምክንያቱም አይቼዋለሁ!’ ይለዋል።”

… “ማንን ነው ያዬው?” ሲል፤ ከሦስታችን መሀል፥ አንደኛው ጓደኛችን፥ ጠየቀ።

ይሥሐቅ፣ ሲጋራ ለኮሰ። ሦስታችንም፣ ዐይን ዐይኑን እያዬን ነበር። የጫቱ መንፈስ ይኹን የሚያወራው ወሬ አላውቅም፣ ፍርሃት ቢጤ ተሰምቶኝ ነበር። ሰዐቴን ተመለከትሁ፤ ሰባት ሰዐት ከሩብ ይላል። ይሥሐቅ፣ ሲጋራውን አንዴ ማግ አድርጎ፥ ጨዋታውን ቀጠለ።

“…አጎቴም የጠየቀው ይኽንኑ ነበር።… ‘ማንን ነው ያየኸው?’… ሲል ጠየቀው። ጓደኛው፣ ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ፥ በረጅሙ ተነፈሰና፥ ‘ሲጋራ ላጬስ፣ መስኮቱጋ ተደግፌ ክብሪት ልመታ ስል፤ የመስኮቱ መስተዋት ላይ አየሁት። የራሴው መልክ ነበር። እኔ እንዳልኾንሁኝ ግን እርግጠኛ ነበርሁ። ጥላው፣ እክብሪቱ ቀፎ ላይ አርፎ ነበር። ክብሪቱን ለኮስሁ። ግን… ሻይ ልጥድ የከፈትሁትን ጋዝ እረስቼው ነበር። ድንገት፣ ተያያዘና ፈነዳ። አለና በረጅሙ አቃሰተ። ከዚያ፣ በእሳት በተለበለበ እጁ የአጎቴን ኮት ጨምድዶ ይዞ፣ ወደሱ አስጠጋውና፥ ‘ጥላው… ጥላው ያረፈበት…’ ብሎ ሳይጨርስ፣ ዐይኑ ፈጥጦ፣ አፉ እንደተከፈተ ደርቆ ቀረ።” አለ ይሥሐቅ፤ ሲጋራውን እመተርኮሻው ላይ እየደፈጠጠ።

“ሞተ?” አልሁኝ፤ ይሥሐቅን አፍጥጬ እያዬሁ።

“አዎ፤ ሞተ!”

“ያዬው ነገር ግን ምን ነበር?”

“እራሱን ነው ያዬው። ግን፣ የገረጣውንና መንፈስ የመሰለውን፤ እራሱን ሳይኾን ሌላ ነገር…”

“እያልከኝ ያለኸው፣ ሞትን አየው ነው?” አልሁና ሣቅ አልሁኝ።

እሱ ግን አልሣቀም። ድርቅና ፍጥጥ ብሎ ተመለከተኝ። ወዲያው፣ ፈገግታዬ ጠፍቶ፥ በውስጤ ፍርሃት ነገሠ። ሁለቱ ጓደኞቻችንም፣ ዐይኖቻቸውን አፍጥጠው፥ ይሥሐቅን ይመለከቱታል።

ይሥሐቅ ቀጠለ።

“…አጎቴ፣ ጓደኛው በቀላሉ የሚረበሽና ዘባራቂ ሰው እንዳልኾነ አሳምሮ ያውቃል። እንዲያውም፣ በጣም የተረጋጋና በምንም ዓይነት አፈ ታሪክና የማይጨበጡ ወሬዎች የማያምን ሰው እንደኾነም ያውቃል። ከመሞቱ በፊት አጓጉል ቀልድ ሊቀልድ እንደማይቃጣም ግልጽ ነው። የኾነ ኾኖ፣ የአጎቴ ጓደኛ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ነገሩ እየተረሳ መጣ። ነገሩ አልፎ ረጅም ጊዜ ቢቆይም አጎቴ ግን አንድ ነገር አልረሳም፤ ጓደኛው፣ ከመሞቱ በፊት፥ የተናገረውን፤ ‘ጥላው!’…

“…አዎ! ያ፣ የራስህን መልክ ይዞ፥ ሞት ይኹን መልአከ ሞት ሳይለይ፥ በሚያንጸባርቅ ነገር ላይ እንደጥላ አርፎ የሚታይህ ነገር፣ የመሞቻህ መንሥኤ መኾኑን። አጎቴ፣ ይኽንን አልረሳም።”

“የራስህን መልክ ነው የምታዬው?” ሲል፤ አንዱ ጓደኛችን ጠየቀ።

“አዎን፤ ግን አንተ አይደለህም። ምክንያቱም፣ ያ፥ አንተን የሚመስል ነገር፣ የሞት መንፈስ ያረፈበት ነው።” አለ ይሥሐቅ፤ ሲጋራ አውጥቶ እየለኮሰ።

ሲጋራ ሲስብ፣ ትንሽ ሰከንድ ወሰደ። በበኩሌ፣ የታሪኩን መጨረሻ ለማወቅ ብጓጓም፥ ከመጠን በላይ ፈርቻለሁ። በአራታችን መሀል ያረፈው ድባብም ይኸው ነበር። ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ከኻያ ላይ፣ እንደዚህ ዓይነት ወሬ ሲወራ ሰምቼ አላውቅም።

“…አጎቴ፣ ለረጅም ጊዜ በጥንቃቄ እራሱን እየጠበቀ ሲኖር ቆዬ። እንደነገርኋችሁ፣ እንደሱ ሞትን የሚፈራ ሰው አልተፈጠረም። አንድ ቀን ምሽት፣ የመኪናው የፍሬን ሸራ ተበላሽቶ፥ ሊያስጠግን ወደ ጋራዥ ይሄድና ሜካኒኩን አጥቶት ይመለሳል። መኪናውን፣ አፓርታማው ሥር በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ያቆምና ወደ ቤቱ ይገባል። በእጁ፣ ከሱፐር ማርኬት የገዛውን ሦስት ኪሎ ሙዝ ይዞ ነበር። ገላውን ለመታጠብ ሻወሩን ሲከፍት፣ ውኃ አልነበረም። በስጨት ብሎ፣ ለመጠባበቂያ ውኃ ይዞ ከተቀመጠ በርሜል ይቀዳና ድስት ላይ ሞልቶ፤ የጋዝ ምድጃ ላይ ይጥደዋል። ውኃውን እያሞቀ፣ ሙዝ ልጦ ይበላና ልጣጩን የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ላይ፥ እንደ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች፥ ይወረውራል። ልጣጩ፣ ዒላማውን ይስትና እመሬት ላይ ያርፋል።…

“…አዲስ የገዛው ሸሚዝ እንዳማረበትና እንዳላማረበት ለማዬት፣ እግድግዳ ላይ ወደተሰቀለ መስተዋት ጠጋ ብሎ ይመለከታል። ከሰውነቱ ጋር ልክክ ብሏል። አንዱ የሸሚዙ ቁልፍ ግን፣ የተለዬ ሕብር እንዳለው በመስተዋቱ ውስጥ ይመለከታል። ጎንበስ ብሎ፣ ሸሚዙን ያዬዋል፤ ልክ ነው። ምንም የተለየ ሕብር የለውም። እንደገና ቀና ብሎ፣ መስተዋቱን ይመለከታል፤ አኹን አዬው።” አለ ይሥሐቅ፤ ሲጋራውን እመተርኮሻው ላይ እየደፈጠጠ።

“ሞትን?” አልሁኝ፤ ድምፄን የሹክሹክታ ያህል ቀንሼ።

ሁላችንም፣ ጸጥ-እረጭ ብለናል። ይሥሐቅ፣ ትኩር ብሎ ተመለከተኝና፤

“አዎን፤ ሞትን!” አለኝ።

ከዙርባው ላይ፣ አንድ ዘለላ የጫት ዕንጨት መዘዘና መቀንጠስ ጀመረ።

“…አጎቴ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠነቀቅ ኖሯል፤ እራሱንም ሲጠብቅ። አኹን እመስተዋቱ ውስጥ ያዬው የራሱ ምስል ግን ያበጠና ላብ በላብ የኾነ ፊት ያለው ከመኾኑም በላይ፤ እፊቱ ላይ የፌዝ ፈገግታ ይታይበት ነበር። አጎቴ፣ በድንጋጤ በርግጎ ወደ ኋላ ያፈገፍግና ለመሮጥ ይሞክራል። የዛ፥ እመስተዋቱ ላይ ያረፈው ምስል፥ ጥላ የት እንዳረፈ በዐይኑ እየፈለገ በመደናበር መሮጥ ይጀምራል። ነገር ግን፣ እግሩ ለመሮጥ አየር ላይ በተነሣበት ቅጽበት፥ ጥላው ያረፈው የሙዙ ልጣጭ ላይ እንደኾነ ያስተውላል። ምን ዋጋ አለው…! እግሩን የሙዙ ልጣጭ ላይ ከማሳረፍ ውጪ አማራጭ አልነበረውም።…

“…ጥንቁቅ የኾነውና ሞትን አጥብቆ የሚፈራው አጎቴ፣ እንደምንም ብሎ ሚዛኑን ይጠብቅና ተፈናጥሮ የሙዝ ልጣጩን ይዘልለዋል። የሙዙን ልጣጭ ቢረግጠው ኖሮ፣ ተንሸራትቶ በጀርባው ይወድቅና፤ ከብረት የተሠራው የውኃ መያዣ በርሜል አናቱን ይመታው ነበር። ለጊዜው አመለጠ፤ ግን አምልጦ አላመለጠም፤ የጋዝ ምድጃውን ተደግፎ እመሬት ላይ ሲቀመጥ፣ ምድጃውን በኀይል ነቅንቆት ነበር።” አለ ይሥሐቅ፤ የቀነጠሰውን ጫት አፉ ውስጥ እየከተተ።

“…ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የጋዝ ምድጃው ላይ ያስቀመጠውና ቅድም ውኃ የቀዳበት የብረት ኩባያ ላይ፥ ምስሉን እንደገና ያዬዋል፤ ጥላው ያረፈው እድስቱ ላይ ነበር። አኹን ግን የፌዝ ፈገግታ እፊቱ ላይ አይታይበትም፤ ቁጣ እንጂ። አጎቴ፣ እመሬት ላይ ተንከባልሎ ቦታውን ይለቅቃል። ምድጃውን ተደግፎ ሲቀመጥ የነቀነቀው ድስት ይወድቅና አጎቴ እነበረበት ቦታ ላይ ይገለበጣል፤ ሲንተከተክ የነበረው ውኃም ይደፋል። ነገሩ አላማረውምና ያንን ቤት ለቅቆ መውጣት፣ የትም ይኹን የት መራቅ እንዳለበት ይወስናል።…

“…እየሮጠ በሩን ከፍቶ ይወጣል። ደረጃውን ወርዶ ያቆመውን መኪና አስነሥቶ በከባድ ፍጥነት እየነዳ ይፈተለካል። ትንሽ ርቀት እንደተጓዘ፣ አኹንም ያዬዋል፤ የመኪናው ስፖኪዮ ላይ። ጥላው፣ ፍሬኑ ላይ አርፎ ነበር። ያን ጊዜ ነው የባነነው፤ ለካ የመኪናው ፍሬን አይሠራም። ደጋግሞ ቢረግጠውም የመኪናው ፍጥነት አልቀነስም አለው።…

“…የመኪናውን ማርሽ በፍጥነት ይቀያይርና መኪናውን ከመንገዱ ጠርዝ ጋር እያላተመና ጎማውን ከጠርዙ ጋር እያስታከከ አብርዶ ዘልሎ ይወርዳል። መኪናው ሄዶ ከአንድ ዛፍ ጋር ይጋጫል። ቁና ቁና እየተነፈሰ፣ መኪናው ወደተጋጨበት ዛፍ እያመራ ሳለ፤ በድንጋጤና በድካም ሰውነቱ ዝሎ ኖሮ፥ ተዝለፍልፎ እዛፉ ሥር ይቀመጥና ደርቆ ይቀራል። ምክንያቱም፣ ያ፣ ያበጠ ፊት ያለውና ላብ በላብ የኾነው፣ የራሱ ሞት ያንዣበበበት ፊት፥ ከቆርቆሮው ላይ ተንጸባርቆ ታይቶት ነበርና። ጥላውም፣ በደረቱ ላይ አርፎ ነበር።” አለና ሁላችንንም ትኩር ብሎ አየን።

“ከደረቱ ላይ?!” አልሁኝ።

“አዎ፤ ከደረቱ ላይ!

“…ጠዋት በዚያ የሚያልፉ ሰዎች፣ ደርቆ የወደቀውን አጎቴን አገኙትና ወደ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ። ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ፣ እኔን አስጠርቶ፥ በጻዕረ ሞት ውስጥ ኾኖ፥ እንደምንም እየታገለ፥ አሁን ያወጋኋችሁን ታሪክ፣ ለእኔ፥ ነገረኝ። ረፋድ ላይ ሕይወቱ አለፈች። የመረመረውም ዶክተር፣ የሞቱ ምክንያት፣ ከፍተኛ የልብ ድካም እንደኾነ ነገረን።

“…እኔም፣ ከዛን ጊዜ ጀምሮ፥ ይኼው፥ አካባቢዬን ኹሉ፣ በጥርጣሬና በሥጋት እየቃኜሁ፥ በሰቀቀን አለሁ።” አለና፤ ሦስታችንንም እየተመለከተ፤

“…ክርክራችሁ፣ ‘ሰው ሞትን ማምለጥ ይችላል ወይስ አይችልም?’ በሚል የተጀመረ ነበር አይደል?” በማለት ጠየቀ።

“አዎ!” አልሁት።

“እኔ ምን አውቃለሁ፤ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው!” አለና፤ አንድ ዘለላ ጫት መዘዘ።

እኔም፣ አንድ ዘለላ ጫት መዘዝሁ። የኾነ ጥላ በአካባቢዬ እንዳላረፈ እርግጠኛ ለመኾን፣ የጎሪጥ እያዬሁ፥ ሰዐቴን ተመለከትሁ።

… ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ተኩል ይላል።

.

መሐመድ ኢድሪስ

2009 ዓ.ም

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] “ሣልሳዊው ዐይን”። 2009 ዓ.ም። ገጽ 1-6።

.

 

“ሳይቸግር ጤፍ ብድር” (ወግ)

“ሳይቸግር ጤፍ ብድር”

ከሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

.

አንድ ሰሞን ሰባት ገጽ ከሩብ የኾነ የአንድ ሥራ-ሀላፊን ያማርኛ ጥያቄና መልስ (ቃለመጠይቅ) ጽሑፍ አንብቤ ነበር። ሃያ ሦስት የእንግሊዝኛ ቃላት/ሐረጎች ተቀላቅለውበት አገኘሁ! ይህ የጽሑፉ 1.06% መሆኑ ነው።

ታዲያ “ይቺ ምን አላትና ሰው ታስተቻለች?” ያሰኝ ይሆናል።

ጉዳዩ ግን መጠኑ አይደለም – ሌላ ነው። አንደኛ፣ ሰው ሀላፊ ኾኖ ባደባባይ ንግግሩ እንግሊዝኛን ካማርኛ እያቃየጠ ሲናገር ላድማጮቹ ኹሉ አብነት ይኾናል። ኹለተኛ፣ አቀያይጦቱ “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” መሆኑ ነው።

ቀጥዬ ከጽሑፉ የለቀምኩዋቸውን አማርኛና-እንግሊዝኛ ቅይጥይጥ ንግግር አመጣለሁ።

.

ቅይጡ ቃል                በጽሑፉ ያለው አጠቃቀም       (በጎ የሚሆነው)

Albergo             “አንድ ቦታ ነበር ቤርጎ የያዝነው”   (አንድ ቦታ ነበር ሆቴል የያዝነው)

Already              “ኦረዲ ወስነናል”   (ዱሮ ወስነናል)

Chair                  “ቸር ማድረጉንም”   (ስብሰባውን መምራቱንም)

Chairperson       “ለዋናው ቸርፐርሰን”   (ለዋናው ሊቀመንበር)

Cross-check            “ይህንኑ ክሮስቼክ አደረግን”   (ይህንኑ አመሳከርን)

Excessive Force         “ይህ ኤክሴሲቭ ፎርስ ነው”   (ይህ መጠኔለሽ ኃይል ነው)

Extension                  “ለምን ኤክስቴንሽን አይጠይቁም”   (ለምን የጊዜ ተራዝሞ አይጠይቁም)

Information               “ኢንፎርሜሽን በሚስጥር እያወጣ”   (መረጃ በሚስጥር እያወጣ)

Interrogate                “ኢንተሮጌት አድርጓቸዋል”   (እሳቸውንም ጠይቋቸዋል)

I Think                       “አይቲንክ”   (ይመስለኛል)

Leads                         “የካሴት ሊዶችን ለማትረፍ”   (የካሴት መረጃዎችን ለማትረፍ)

Legal Adviser         “ሌጋል አድቫይዘር በመሆን”   (የሕግ አማካሪ በመሆን)

Organization          “ከማንም ኦርጋናይዜሽን ጋር”   (ከማንም ድርጅት ጋር)

Pressure                  “ፕሬዠሩን በመፍራት”   (ጫናውን በመፍራት)

Property Damage        “የደረሰባቸውን የፕሮፐርቲ ዳሜጅ”   (የደረሰባቸውን የሀብት ጥፋት)

Region                     “የደቡብ ሪጅን”   (የደቡብ ቀጣና/ክፍለ ሀገር)

Replace                    “በሕጉ ምክትሉ ሪፕሌስ ያደርጋል”   (በሕጉ ምክትሉ ይተካል)

Report                     “የናንተን ውሳኔ ሪፖርት”   (የናንተን ውሳኔ ዘገባ)

Resign                      “አንዱ ሪዛይን አድርጎ”   (አንዱ ሥራውን ለቆ)

Scholarship             “እስኮላርሺፕ አግኝቶ ነው”   (የትምህርት ድጎማ አግኝቶ ነው)

Statement                “የራሴን ስቴትመንት ሳደርግ”   (የራሴን ቃል ስሰጥ)

Supreme Court       “ሱፕሪም ኮርት ቢሮ ስንደርስ”   (ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢሮ ስንደርስ)

Trust                         “ትረስት ለማድረግ ሞክረን”   (ለማመን ሞክረን)

.

እዚህ ላይ በተጠቅሞቴ (ለምሳሌ) Albergoን “ሆቴል” ብያለሁ። በፈረንጅኛነቱ በቅየማ ሊያስከስስ ይችላል። ይህ ቃል ግን አማርኛ ኾኑዋል።

ለምሳሌ “Apple” ባማርኛ ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ ማንም “ፖም” ይላል – ከፈረንሳይኛ በመጣ ቃል። በዚህ መልክ ብዙ የውጭ ቃላት ወደ አማርኛ መጥተው፣ በዘመን ብዛት አማርኛ የኾኑ አሉ – ሆቴልም የዚያ ዐይነት ነው።

ከላይ የተዘረዘሩት የሃያ ሦስቱ ፈረንጅኛ ቃላት/ሐረጎች ጉዳይ ግን ሌላ ነው … ሀሳባቸው በአማርኛ በቀላሉ ይገኛልና።

.

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

(1999 ዓ.ም)

.

[ምንጭ] – አንድምታ ክበብ። ቁጥር 6። የካቲት 1999። ገጽ 8።