“የእኩለ ሌሊት ወግ” (ልብወለድ)

“የእኩለ ሌሊት ወግ”

በመሐመድ ኢድሪስ

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

.

አራት ሰዎች ነን። በአንደኛው ጓደኛችን ቤት ውስጥ ተቀምጠናል፤ ጫት እየቃምን።

የመሸግነው ደግሞ አውቶቡስ ተራ ነው። ጊዜው፣ የረመዳን ጾም ወቅት ስለኾነ፤ ገንዘብ ካለ፥ ኻያ አራት ሰዐት ጫት መግዛት የሚቻልበት ሰፈር ነው፤ አውቶቡስ ተራ። ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ላይ፥ ሦስተኛውን ዙር ጫት፥ አንዱ ጓደኛችን ይዞ መጣ።

እንዳጋጣሚ ኾኖ፣ የወሬያችን አርእስት ሁሉ ስለ ሞት ነበር። አንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙኀን አርእስት ኾኖ የሰነበተውንና የገዛ ሚስቱን ገድሎ እራሱን ያጠፋውን ሰውዬ አንሥተን ብዙ ከተጫወትን በኋላ ግን የጨዋታችን መንፈስ ተቀየረ።

እኔ፣ ‘በቅርቡ የሞተው ጓደኛችንም፣ መጠጥ ቤት በተፈጠረ አምባጓሮ ውስጥ ባይገባ ኖሮ፥ አይሞትም ነበር’ ስል፤ ሁለቱ ጓደኞቻችን፣ የተለያየ አቋም ይዘው፥ መነታረክ ጀመሩ። አንደኛው ጓደኛችን፣ ‘ሰው፣ ተጠንቅቆና እራሱን ለጥቃት ሳያጋልጥ ከኖረ፥ ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል’ የሚል፤ ሌላኛው ጓደኛችን ደግሞ፣ ‘ማንኛውም ሰው፣ የቱንም ያህል ቢጠነቀቅና ቢታገስ፥ ከተጻፈለት ቀን ሊያመልጥ አይችልም’ የሚል አቋም ይዘው ነበር።

ሦስተኛው ጓደኛችን ግን፣ በተመስጦ ሲጋራውን እያጬሰ፥ ዝም ብሎ ያዳምጥ ነበር፤ ይሥሐቅ ይባላል።

ይሥሐቅ፣ ረጅምና ወፍራም የሽያጭ ሠራተኛ ነው። ብዙ መጻሕፍትን አንብቧል። ለብዙ ዓመታት አውሮፓ ውስጥ ኖሯል። አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በእንግሊዝ ሀገር ውስጥ ነው።

“እሺ፤ አንተስ ምን ትላለህ?” ስል፤ ጠየቅሁት።

በዕድሜ፣ በዕውቀትና በሕይወት ልምድ ስለሚበልጠን፤ እሱ የሚለው፣ ሁላችንንም ሊያስማማን እንደሚችል አስቤያለሁ።

“ከዚያ በፊት፣ አንድ እውነተኛ ታሪክ ላጫውታችሁና እራሳችሁ ትፈርዳላችሁ።” አለ።

ሁላችንም፣ የሚለውን ለመስማት፥ ድምፃችንን አጠፋን። ክፍሉ፣ ጸጥ-እረጭ አለ። ጊዜው፣ ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ከዐሥር ነበር።

“…በደቡባዊ ለንደን የሚኖር አጎት ነበረኝ…” ሲል ጀመረ።

“…ልክ እንደኔው ወፍራም። ዕድሜው ወደ ስድሳ ይጠጋል። በጣም የተማረ፣ ከልክ ያለፈ የዊስኪና የሲጋራ ሡሠኛ ነበር። ሌላው ቀርቶ፣ እመንገድ ላይም እንኳ ቢኾን ባሰኜው ጊዜ ሁሉ እንዳይቀርበት፥ ከአሉሚነም የተሠራ የዊስኪ መያዣ ዕቃ ነበረው። ዊስኪውን በዚያ ቆርቆሮ ውስጥ ይገለብጥና ቀኑን ሙሉ ሲያንደቀድቅ ይውላል። ይታያችሁ፤ በረዶና ሶዳ እንኳን አይጠቀምም፤ ደረቅ ዊስኪ ነው እንደ ውኃ የሚጨልጠው…

“…አንድ ቀን፣ የመረመረው ዶክተር፥ ‘ባጭር ጊዜ ውስጥ መጠጥና ሲጋራ ካላቆምህ፥ ሕይወትህ አደጋ ላይ ነው!’ ይለዋል፤ ‘ከባድ የልብ ድካም በሽታ ስላለብህ፥ ከመጠን ያለፈ የአካል እንቅስቃሴ አታድርግ’ም ይለዋል። እኔ፣ እስካኹን የሱን ያህል ሞትን የሚፈራ ሰው አላየሁም። የሚገርማችሁ፣ የዶክተሩን ማስጠንቀቂያ ከሰማ በኋላ፥ ሲጋራ፣ እርግፍ አድርጎ ተወ፤ ከልክ ያለፈ የአካል እንቅስቃሴ ላለማድረግም ይጠነቀቅ ነበር። መጠጥ ግን፣ ሊያቆም አልቻለም።…

“…አንድ ቀን ጠዋት፣ ስልክ ይደወልለትና፤ ጓደኛው፣ እቤት ውስጥ በተፈጠረ የእሳት ቃጠሎ፥ ተለብልቦ፤ ለመሞት እያጣጣረ እንደኾነ ይነገረዋል። በፍጥነት ወደ ተባለው ሆስፒታል ይሄዳል። ጓደኛው፣ በፋሻ ተጠቅልሎ፥ አልጋ ላይ ተኝቷል። ምንም አልተረፈም፤ ፊቱ የሌላ ፍጡር መስሏል። አጎቴ፣ ጓደኛው፣ በደቂቃዎች ዕድሜ ውስጥ እንደሚሞት አወቀ።…

“…ቀስ ብሎ ጆሮውን ሲያስጠጋ፤ ‘አየሁት!’ ይለዋል ጓደኛው፤ ትንፋሹ ከፍና ዝቅ እያለ። አጎቴ፣ ጓደኛው የሚቃዥ ይመስለውና ሊያረጋጋው ፈልጎ፥ ‘አይዞህ! ሐኪሞቹ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ትድናለህ!’ ይለዋል። ጓደኛው ግን፣ በተስፋ መቁረጥ ፈገግ ብሎ፥ ‘አልድንም! ምክንያቱም አይቼዋለሁ!’ ይለዋል።”

… “ማንን ነው ያዬው?” ሲል፤ ከሦስታችን መሀል፥ አንደኛው ጓደኛችን፥ ጠየቀ።

ይሥሐቅ፣ ሲጋራ ለኮሰ። ሦስታችንም፣ ዐይን ዐይኑን እያዬን ነበር። የጫቱ መንፈስ ይኹን የሚያወራው ወሬ አላውቅም፣ ፍርሃት ቢጤ ተሰምቶኝ ነበር። ሰዐቴን ተመለከትሁ፤ ሰባት ሰዐት ከሩብ ይላል። ይሥሐቅ፣ ሲጋራውን አንዴ ማግ አድርጎ፥ ጨዋታውን ቀጠለ።

“…አጎቴም የጠየቀው ይኽንኑ ነበር።… ‘ማንን ነው ያየኸው?’… ሲል ጠየቀው። ጓደኛው፣ ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ፥ በረጅሙ ተነፈሰና፥ ‘ሲጋራ ላጬስ፣ መስኮቱጋ ተደግፌ ክብሪት ልመታ ስል፤ የመስኮቱ መስተዋት ላይ አየሁት። የራሴው መልክ ነበር። እኔ እንዳልኾንሁኝ ግን እርግጠኛ ነበርሁ። ጥላው፣ እክብሪቱ ቀፎ ላይ አርፎ ነበር። ክብሪቱን ለኮስሁ። ግን… ሻይ ልጥድ የከፈትሁትን ጋዝ እረስቼው ነበር። ድንገት፣ ተያያዘና ፈነዳ። አለና በረጅሙ አቃሰተ። ከዚያ፣ በእሳት በተለበለበ እጁ የአጎቴን ኮት ጨምድዶ ይዞ፣ ወደሱ አስጠጋውና፥ ‘ጥላው… ጥላው ያረፈበት…’ ብሎ ሳይጨርስ፣ ዐይኑ ፈጥጦ፣ አፉ እንደተከፈተ ደርቆ ቀረ።” አለ ይሥሐቅ፤ ሲጋራውን እመተርኮሻው ላይ እየደፈጠጠ።

“ሞተ?” አልሁኝ፤ ይሥሐቅን አፍጥጬ እያዬሁ።

“አዎ፤ ሞተ!”

“ያዬው ነገር ግን ምን ነበር?”

“እራሱን ነው ያዬው። ግን፣ የገረጣውንና መንፈስ የመሰለውን፤ እራሱን ሳይኾን ሌላ ነገር…”

“እያልከኝ ያለኸው፣ ሞትን አየው ነው?” አልሁና ሣቅ አልሁኝ።

እሱ ግን አልሣቀም። ድርቅና ፍጥጥ ብሎ ተመለከተኝ። ወዲያው፣ ፈገግታዬ ጠፍቶ፥ በውስጤ ፍርሃት ነገሠ። ሁለቱ ጓደኞቻችንም፣ ዐይኖቻቸውን አፍጥጠው፥ ይሥሐቅን ይመለከቱታል።

ይሥሐቅ ቀጠለ።

“…አጎቴ፣ ጓደኛው በቀላሉ የሚረበሽና ዘባራቂ ሰው እንዳልኾነ አሳምሮ ያውቃል። እንዲያውም፣ በጣም የተረጋጋና በምንም ዓይነት አፈ ታሪክና የማይጨበጡ ወሬዎች የማያምን ሰው እንደኾነም ያውቃል። ከመሞቱ በፊት አጓጉል ቀልድ ሊቀልድ እንደማይቃጣም ግልጽ ነው። የኾነ ኾኖ፣ የአጎቴ ጓደኛ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ነገሩ እየተረሳ መጣ። ነገሩ አልፎ ረጅም ጊዜ ቢቆይም አጎቴ ግን አንድ ነገር አልረሳም፤ ጓደኛው፣ ከመሞቱ በፊት፥ የተናገረውን፤ ‘ጥላው!’…

“…አዎ! ያ፣ የራስህን መልክ ይዞ፥ ሞት ይኹን መልአከ ሞት ሳይለይ፥ በሚያንጸባርቅ ነገር ላይ እንደጥላ አርፎ የሚታይህ ነገር፣ የመሞቻህ መንሥኤ መኾኑን። አጎቴ፣ ይኽንን አልረሳም።”

“የራስህን መልክ ነው የምታዬው?” ሲል፤ አንዱ ጓደኛችን ጠየቀ።

“አዎን፤ ግን አንተ አይደለህም። ምክንያቱም፣ ያ፥ አንተን የሚመስል ነገር፣ የሞት መንፈስ ያረፈበት ነው።” አለ ይሥሐቅ፤ ሲጋራ አውጥቶ እየለኮሰ።

ሲጋራ ሲስብ፣ ትንሽ ሰከንድ ወሰደ። በበኩሌ፣ የታሪኩን መጨረሻ ለማወቅ ብጓጓም፥ ከመጠን በላይ ፈርቻለሁ። በአራታችን መሀል ያረፈው ድባብም ይኸው ነበር። ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ከኻያ ላይ፣ እንደዚህ ዓይነት ወሬ ሲወራ ሰምቼ አላውቅም።

“…አጎቴ፣ ለረጅም ጊዜ በጥንቃቄ እራሱን እየጠበቀ ሲኖር ቆዬ። እንደነገርኋችሁ፣ እንደሱ ሞትን የሚፈራ ሰው አልተፈጠረም። አንድ ቀን ምሽት፣ የመኪናው የፍሬን ሸራ ተበላሽቶ፥ ሊያስጠግን ወደ ጋራዥ ይሄድና ሜካኒኩን አጥቶት ይመለሳል። መኪናውን፣ አፓርታማው ሥር በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ያቆምና ወደ ቤቱ ይገባል። በእጁ፣ ከሱፐር ማርኬት የገዛውን ሦስት ኪሎ ሙዝ ይዞ ነበር። ገላውን ለመታጠብ ሻወሩን ሲከፍት፣ ውኃ አልነበረም። በስጨት ብሎ፣ ለመጠባበቂያ ውኃ ይዞ ከተቀመጠ በርሜል ይቀዳና ድስት ላይ ሞልቶ፤ የጋዝ ምድጃ ላይ ይጥደዋል። ውኃውን እያሞቀ፣ ሙዝ ልጦ ይበላና ልጣጩን የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ላይ፥ እንደ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች፥ ይወረውራል። ልጣጩ፣ ዒላማውን ይስትና እመሬት ላይ ያርፋል።…

“…አዲስ የገዛው ሸሚዝ እንዳማረበትና እንዳላማረበት ለማዬት፣ እግድግዳ ላይ ወደተሰቀለ መስተዋት ጠጋ ብሎ ይመለከታል። ከሰውነቱ ጋር ልክክ ብሏል። አንዱ የሸሚዙ ቁልፍ ግን፣ የተለዬ ሕብር እንዳለው በመስተዋቱ ውስጥ ይመለከታል። ጎንበስ ብሎ፣ ሸሚዙን ያዬዋል፤ ልክ ነው። ምንም የተለየ ሕብር የለውም። እንደገና ቀና ብሎ፣ መስተዋቱን ይመለከታል፤ አኹን አዬው።” አለ ይሥሐቅ፤ ሲጋራውን እመተርኮሻው ላይ እየደፈጠጠ።

“ሞትን?” አልሁኝ፤ ድምፄን የሹክሹክታ ያህል ቀንሼ።

ሁላችንም፣ ጸጥ-እረጭ ብለናል። ይሥሐቅ፣ ትኩር ብሎ ተመለከተኝና፤

“አዎን፤ ሞትን!” አለኝ።

ከዙርባው ላይ፣ አንድ ዘለላ የጫት ዕንጨት መዘዘና መቀንጠስ ጀመረ።

“…አጎቴ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠነቀቅ ኖሯል፤ እራሱንም ሲጠብቅ። አኹን እመስተዋቱ ውስጥ ያዬው የራሱ ምስል ግን ያበጠና ላብ በላብ የኾነ ፊት ያለው ከመኾኑም በላይ፤ እፊቱ ላይ የፌዝ ፈገግታ ይታይበት ነበር። አጎቴ፣ በድንጋጤ በርግጎ ወደ ኋላ ያፈገፍግና ለመሮጥ ይሞክራል። የዛ፥ እመስተዋቱ ላይ ያረፈው ምስል፥ ጥላ የት እንዳረፈ በዐይኑ እየፈለገ በመደናበር መሮጥ ይጀምራል። ነገር ግን፣ እግሩ ለመሮጥ አየር ላይ በተነሣበት ቅጽበት፥ ጥላው ያረፈው የሙዙ ልጣጭ ላይ እንደኾነ ያስተውላል። ምን ዋጋ አለው…! እግሩን የሙዙ ልጣጭ ላይ ከማሳረፍ ውጪ አማራጭ አልነበረውም።…

“…ጥንቁቅ የኾነውና ሞትን አጥብቆ የሚፈራው አጎቴ፣ እንደምንም ብሎ ሚዛኑን ይጠብቅና ተፈናጥሮ የሙዝ ልጣጩን ይዘልለዋል። የሙዙን ልጣጭ ቢረግጠው ኖሮ፣ ተንሸራትቶ በጀርባው ይወድቅና፤ ከብረት የተሠራው የውኃ መያዣ በርሜል አናቱን ይመታው ነበር። ለጊዜው አመለጠ፤ ግን አምልጦ አላመለጠም፤ የጋዝ ምድጃውን ተደግፎ እመሬት ላይ ሲቀመጥ፣ ምድጃውን በኀይል ነቅንቆት ነበር።” አለ ይሥሐቅ፤ የቀነጠሰውን ጫት አፉ ውስጥ እየከተተ።

“…ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የጋዝ ምድጃው ላይ ያስቀመጠውና ቅድም ውኃ የቀዳበት የብረት ኩባያ ላይ፥ ምስሉን እንደገና ያዬዋል፤ ጥላው ያረፈው እድስቱ ላይ ነበር። አኹን ግን የፌዝ ፈገግታ እፊቱ ላይ አይታይበትም፤ ቁጣ እንጂ። አጎቴ፣ እመሬት ላይ ተንከባልሎ ቦታውን ይለቅቃል። ምድጃውን ተደግፎ ሲቀመጥ የነቀነቀው ድስት ይወድቅና አጎቴ እነበረበት ቦታ ላይ ይገለበጣል፤ ሲንተከተክ የነበረው ውኃም ይደፋል። ነገሩ አላማረውምና ያንን ቤት ለቅቆ መውጣት፣ የትም ይኹን የት መራቅ እንዳለበት ይወስናል።…

“…እየሮጠ በሩን ከፍቶ ይወጣል። ደረጃውን ወርዶ ያቆመውን መኪና አስነሥቶ በከባድ ፍጥነት እየነዳ ይፈተለካል። ትንሽ ርቀት እንደተጓዘ፣ አኹንም ያዬዋል፤ የመኪናው ስፖኪዮ ላይ። ጥላው፣ ፍሬኑ ላይ አርፎ ነበር። ያን ጊዜ ነው የባነነው፤ ለካ የመኪናው ፍሬን አይሠራም። ደጋግሞ ቢረግጠውም የመኪናው ፍጥነት አልቀነስም አለው።…

“…የመኪናውን ማርሽ በፍጥነት ይቀያይርና መኪናውን ከመንገዱ ጠርዝ ጋር እያላተመና ጎማውን ከጠርዙ ጋር እያስታከከ አብርዶ ዘልሎ ይወርዳል። መኪናው ሄዶ ከአንድ ዛፍ ጋር ይጋጫል። ቁና ቁና እየተነፈሰ፣ መኪናው ወደተጋጨበት ዛፍ እያመራ ሳለ፤ በድንጋጤና በድካም ሰውነቱ ዝሎ ኖሮ፥ ተዝለፍልፎ እዛፉ ሥር ይቀመጥና ደርቆ ይቀራል። ምክንያቱም፣ ያ፣ ያበጠ ፊት ያለውና ላብ በላብ የኾነው፣ የራሱ ሞት ያንዣበበበት ፊት፥ ከቆርቆሮው ላይ ተንጸባርቆ ታይቶት ነበርና። ጥላውም፣ በደረቱ ላይ አርፎ ነበር።” አለና ሁላችንንም ትኩር ብሎ አየን።

“ከደረቱ ላይ?!” አልሁኝ።

“አዎ፤ ከደረቱ ላይ!

“…ጠዋት በዚያ የሚያልፉ ሰዎች፣ ደርቆ የወደቀውን አጎቴን አገኙትና ወደ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ። ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ፣ እኔን አስጠርቶ፥ በጻዕረ ሞት ውስጥ ኾኖ፥ እንደምንም እየታገለ፥ አሁን ያወጋኋችሁን ታሪክ፣ ለእኔ፥ ነገረኝ። ረፋድ ላይ ሕይወቱ አለፈች። የመረመረውም ዶክተር፣ የሞቱ ምክንያት፣ ከፍተኛ የልብ ድካም እንደኾነ ነገረን።

“…እኔም፣ ከዛን ጊዜ ጀምሮ፥ ይኼው፥ አካባቢዬን ኹሉ፣ በጥርጣሬና በሥጋት እየቃኜሁ፥ በሰቀቀን አለሁ።” አለና፤ ሦስታችንንም እየተመለከተ፤

“…ክርክራችሁ፣ ‘ሰው ሞትን ማምለጥ ይችላል ወይስ አይችልም?’ በሚል የተጀመረ ነበር አይደል?” በማለት ጠየቀ።

“አዎ!” አልሁት።

“እኔ ምን አውቃለሁ፤ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው!” አለና፤ አንድ ዘለላ ጫት መዘዘ።

እኔም፣ አንድ ዘለላ ጫት መዘዝሁ። የኾነ ጥላ በአካባቢዬ እንዳላረፈ እርግጠኛ ለመኾን፣ የጎሪጥ እያዬሁ፥ ሰዐቴን ተመለከትሁ።

… ከሌሊቱ ሰባት ሰዐት ተኩል ይላል።

.

መሐመድ ኢድሪስ

2009 ዓ.ም

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] “ሣልሳዊው ዐይን”። 2009 ዓ.ም። ገጽ 1-6።

.

 

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s