“ያጼ በካፋ በግ” (ወግ)

“ያጼ በካፋ በግ”

.

.

አፄ በካፋ አንድ የሚወዱት ለማዳ በግ ነበራቸው። ሲቀላውጥ ይውልና አዳሩ ከእልፍኛቸው ነው የሚያድር። የመወደዱ ብዛት አዋጅ ወጣለት። “ያጼ በካፋ በግ በገባበት ቤት ሳይጋበዝ የቀረ እንደሆነ አይቀጡ ቅጣት እቀጣለሁ” ተባለ።

እንደ አቀማጠሉት ታውቆት ቅልውጡ ባሰበት። በቅልውጡ የተነሳ ሰው አጥብቆ ተመረረ። ቅልውጡ ቀርቶ ከደጅ የሚሰጣውን ያወድማል።

እንዲህ እያስለቀሰ ሲኖር አንድ ቀን ሲፈርድበት ከአንድ ደብተራ ቤት ዘው አለ። ደብተራው “እንኳ የመጣህልኝ” ብሎ ሲያበቃ ደጁን ዘግቶ እንክት አርጎ አረደው። ሥጋውን ዘልዝሎ ኸጓዳው ሰቀለ። የበጉ አመል የትም ሲቀላውጥ ውሎ አዳሩ ከንጉሡ እልፍኝ ነበር። ሲጠፋ ጊዜ በያለበት ፈልጉ ተባለ።

ወደ ተንኮለኛ ደብተራ እንመለስ።

የበጉን ደበሎ ብራና ፋቀው። ቀጥሎ ብራናውን በትንንሽ ቆራርጦ በቍራጮቹ፣

“የንጉሡን በግ እኔ ነኝ አርጄ የበላሁት። ጮማ ነበር። መጣፈጡም ግሩም ነው። መታረዱም ይገባዋል። መክለፍለፍ አብዝቶ ድሀ አስለቅሷልና”

ብሎ ጽፎ ቁራጮቹን ወስዶ በስውር ሰው እንዳያየው አርጎ ካደባባይ በተናቸው።

መቸም በከተማው የንጉሥ ባለሟል ጠፍቷል ተብሎ በያለበት ፍለጋ ተይዟል። ሁለት ወይ ሦስት ሰዎች ቁራጮች አይተው አንስተው አንብበው ለንጉሡ አደረሱ።

በተነበበ ጊዜ ንጉሡ እጅግ አጥብቀው ተቆጡ፡

“እንዴት አባቱ ያለ ደፋር ነው! ተማረዱ ጽፎ አደባባይ ብራናውን መበተኑ። ቆይ ሳትያዝ የቀረህ እንደሆነ”

አሉና በምስጢር አርገው፤

“ስስ ወርቅ አምጡና መዝኑ። ተተመዘነ በኋላ ወስዳችሁ ከግቢው አደባባይ ዠምራችሁ እስከ አውራው ጐዳና በትኑት። ቀጥላችሁ የታመነ የታመነ ዘበኛ ተተነሰነሰው ወርቅ እልፍ ብለው ቆባ ብለው አጐንብሶ የሚያነሳውን ሰው ይያዙ” ብለው አዘዙ።

መቼም ሌባና አጥፊ እንቅልፍ የለው የሚወራውን የሚሆነውን ሁሉ ተጠንቅቆ እህ ይላል። በብልሃቱ ብዛት የበጋቸው ሌባ የወርቅ ወጥመድ መጠመዱን አወቀ።

“ቆይ እዚህማ ብልሃት አለኝ” ይልና ቶሎ መጫምያ አሰፍቶ ታቹን ምድር የሚረግጠውን ወገን በሰም መረገው። ቀጥሎ መጫምያውን አጥልቆ ጥምጥሙን አሳምሮ ጠምጥሞ መቋምያውን ይዞ አንጓቦ ወርቅ በተዘራበት መንገድ አረጋገጡን ወደ ምድር ጫን እያደረገ እየረገጠ ወርቁ ከሰሙ ውስጥ እንዲጠልቅ ነው ብልሃቱ።

እንደዚህ እየሆነ እየተንደላቀቀ ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላለሰ። ከቤቱ እየገባ የተለጠፈውን ወርቅ እያነሳ እያስቀመጠ አንድም ሰው ሳያውቅበት ማታ በሆነ ጊዜ “እስኪ ወርቁን አንሱትና መዝኑት” ተባለ። ቢመዝኑት ቅምጥል ብሎ ጐደለ። ለንጉሡ ይኼንን ቢያሰሙ የባሰውን ተናደዱ።

ዘበኞቹም “እኛ ኩስትር ብለን ነው የጠበቅነ ዳሩ ግን አንድም ሰው አጐንብሶ ሲያነሳ አላየነ” አሉ።

ንጉሡ ቢቸግራቸው “ጠንቋዮች ጥሩ” ብለው አስመጡ። “እንደዚህ ያለ ሥራ የሚሰራ የት ነው የተቀመጠው?“ ብለው ጠየቋቸው። ከገሌ አፈር ላይ ነው ብለው አሉ።

ወታደር ሂዱ ያዙ ተብሎ ታዞ ይሄዳል ግን ማንም አያገኙ። ስለምን ደብቴ እጅግ ብልህ ነውና የሚያረጉትን ሁላ አውቆታል። ለዚህ ብልሃት ተአራት አምስት አገር አፈር አስመጥቶ ከቤቱ ውስጥ አስቀምጦ ከዝያ ላይ ይቀመጥበታል። ያገሩን አፈር እያለዋወጠ ማለት ወታደር ታዞ ሲሄድ ጠንቋዮቹ በመሯቸው ስፍራ ሰውየውን ያጡታል። የተቀመጠበትን አፈር ትቶ ከሌላ አፈር ላይ ይቀመጣል። ወታደሩም በከንቱ ማሰኑ ጠንቋዮቹም ተነቀፉ።

ንጉሡም የባሰውን ተናደዱ። ከዚህ ወዲህ ቆይ ሌላ ብልሃት አለኝ ብለው ሚስጢርዎን በሆድዎ ከተው ድግስ ደገሱ። አለቆች፣ ካህናት፣ ተማሪ፣ ደብተራ የተባለ ሁሉ ትምህርት የጠቀሰ ሁሉ ግብር እንዲበላ አዘዙ። በዚህ ማኽል የታመኑ የታመኑ ሰዎች በምስጢር አርገው መርጠው አሰናዱ።

“ድግሱ በደረሰ ጊዜ እነዚህን የተመረጡትን ሰዎች ካህናቱ ሁሉ ገብተው ሲበሉ ሲጠጡ መጠጡን በገፍ አርጋችሁ ስፍራውን ተከፋፍላችሁ ይዛችሁ ኮስተር ብላችሁ ጠብቁ። በመጠጥ ብዛት የተነሳ ያ ተንኮለኛ ለባልንጀራው ሳይለፈልፍ አይቀርምና በሰማችሁ ጊዜ ለምለም ዦሮውን በስለት ቀንጥቦ ምልክት እንዲሆን ነው” ብለው አዘዙ። “ካህናቱ ጠዋት ሲወጡ ከዦሮው ምልክት ያለበት እንዲያዝ” አሉ።

እውን እንዳሉትም በመጠጥ ብዛት የተነሳ ደብቴ ተቸነፈና ለባልንጀራው ተበጉ መታረድ ጀምሮ እስከ ወርቁ እስከ ጠንቋዮቹ ድረስ የሆነውን ሁሉ ዘከዘከለት። ይህን ሁሉ ሲዘከዝክ በዠርባው በኩል የቆመው ሰላይ ወደነሱ ዦሮውን ጣል አርጎ ኑሮ አንዱ ሳያመልጠው ሁሉን ሰምቷል። በስካር ብዛት የተነሳ ሁሉም ተረፍርፎ እንቅልፍ ወስዷቸው ያ የሰማው ሰላይ ይህን ጊዜ ነው ብሎ ለምለም ዦሮውን ቀነጠበ።

ደብቴ ብዙ እንቅልፍ ተተኛ በኋላ ዦሮው ቆጠቆጠው። በጁ ቢዳብስ ዦሮው ተቀንጥባ “አሁን ገና ተያዝሁ” ይልና አያሌ ተማሪዎችና ደብተሮች ከተረፈረፉት ለምለም ዦሮዋቸውን ቀነጠበ። እንዳይነጋ የለም ነጋ። መቼም ያ ሰላይ የደብቴን ዦሮ የቀነጠበ ለሽልማቱ ሲል የምስራችን አድርሷል። ንጉሡም ደስ ብሏቸው “ምንየ በነጋ” ብለው ቸኩለዋል።

ሲነጋ “በሉ እንግዴህ ካህናቱንና ተማሪውን ሁሉ አስወጡ። ያ ለምለም ዦሮውን የተቆረጠውን ያዙና አምጡ” ብለው አዘዙ። ካህናት በወጣ አያሌ ለምለም ዦሮዋቸው ተቆርጦ ይህንን ነገር ለንጉሡ ባስታወቁ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናደዱ። ቀጥለውም የምስራች ቀናኝ ብሎ ያለኝን ይጠራ አሉ።

በመጣ ጊዜ “በል አንተ አብደሃልን? ይህን ሁሉ ያዛውንት ጆሮ ቁረጥልኝ ብየኻለሁን” አሉት።

“እኔስ ንጉሥ ሆይ ያንድ ተማሪ ለምለም ዦሮውን ብቻ ነው የቆረጥሁት” አለ።

ንጉሡም “እንግድያውስ ይህ ሸረኛ ደብተራ ሲነቃ የሰራውን ሥራ ዦሮው አስታውሶት ተነስቶ የነዚህን ሁሉ ተማሪ ዦሮ መንድቧል” አሉ።

ተዚህ ወዲህ በደብቴ ብልሃት ተገርመው እንደዚህ ያለ ብልህ ተመቅጣት ይልቅስ ሸልሞ መሾም ይበልጣል ለመንግሥት ይጠቅማል ብለው አውጥተው አውርደው አስበው፣

“ነጋሪት ይውጣ አዋጅ ንገሩ የንጉሥን በግ የበላ ደብተራ ምሬአለሁ። ከቶም ሸልሜ እሾመዋለሁ። ላልከዳ ምያለሁ። ይምጣ አይስጋ ብላችሁ አስታውቁ” ብለው አዘዙ።

አዋጁም ተነገረ።

ደብቴ ይኼንን አዋጅ በሰማ ጊዜ አጥብቆ ደስ ብሎት ጌጡን አጋጊጦ ሲደለቅ ወደ አደባባይ ብቅ ብሎ ላጋፋሪ ለንጉሡ መምጣቱን እንዲያስታውቅለት ለመነ። አስታወቀ ተጠርቶ ገባ።

“ስማ ተጀምሮ እስከ ድግሱ ድረስ እንደምን አደረግህ” ብለው በመልካም ዓይን አይተውት ጠየቁት።

እርሱም ተጀምሮ እስኪጨርስ ያደረገውን ሁሉ አፈሰሰ።

ንጉሡም ቃሉን ሁሉ ሰምተው ተገረሙ። ወድያውም ሾሙት።

.

[ምንጭ] – Major J. Eadie. 1924. “An Amharic Reader”. pp. 7-11.

8 thoughts on ““ያጼ በካፋ በግ” (ወግ)

  1. ይህ ወግ ማህበራዊ ገፀ ባሕርያችንን እንዴት ይገልጸው ይሆን? የሰው ንብረት የሰረቀ ተሾመ። ማቸነፍ እንጂ እንዴት እንዳቸነፈ አይገድም። ሰክሮ በተኛበት ጆሮውን ቢቆርጥ፤ ነቅቶ በተኙበት የሁሉንም ጆሮ ቆረጠ። ለራሱ ወንጀል መሸፈኛ ሲያበጅለት ነው። የአንደኛውን ብቻ ጆሮ ባይቆርጥና ከሥቃይ ቢያድነው ምን ነበረ?

    አፄ በካፋን ዙፋን ላይ እንዳይወጣ ለማገድ አፍንጫውን ቆረጡት፤ በካፋ ግን ወንድሙ ሲሞት በደጋፊዎቹ ብዛት ዙፋን ላይ ወጣ። እንደ ኢትዮጵያውያን ፍትኅ ተጓደለ ብሎ የሚጮህ የለም። ያሰብናትን ለማድረግ ሲሆን ግን ፍትኅን አንታመንባትም፤ የጠንቋይ ይሁን የ[ወታደር] ኃይል ሳይቀር እንጠቀማለን። ከ250 ዓመት በኋላ ምን ያህል ከዚህ ወግ መሠረት ፈቅ ብለናል?

    ሌላው ጉዳይ፣ አውሮጳውያን [Major J. Eadie] ምን ያህል ወጋችንን ከጥንቱ አጥብቀው ሲያጠኑ እንደ ኖሩ ነው። አንደኛው ምክንያት የራሳቸውን ሊያጎለብቱበት፤ ሌላኛው፣ ንግድ ይሁን ዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችን ሲፈጥሩ፤ ጦርነት ሲፈልጉን። ብሪቲሽ ካውንስል፣ ገርተ ኢንስቲትዩት፣ ዩ ኤስ ኢንፎርሜሽን ኤጄንሲ፣ ወዘተ ተልእኮአቸው ይኸው ነው። አንድምታዎች ወጋችንን ስላስታወሳችሁን ምሥጋና ይገባችኋል። ያለፈው ታሪካችንን ችላ ብለን ዛሬን በሚገባ መረዳትና ማሸነፍ አንችልምና።

    Like

  2. የታሪኩ ጭብጥ ለእኔ እንደገባኝ ለነበረው አንድ አገረ ገዢ በጭፍን ከመገዛት ይልቅ በልጦ በመገኘት ተፅእኖ መፍጠርና ንጉሡ እሱን መሸለመቻው ደግሞ ዴሞክራሳውያውነትን የሚያመላክት ይመስለኛል በምሁራን ቋንቋ ዲኮንስትራክሽን የእይታ ወይም የምልከታ መንገድ ማለት ነው፡፡

    Like

  3. የዘመኑን ህይወትና ብልሃት የሚያሳይ ሽጋ ወግ ነው። ዘመን የተሻገረ ምንጭ መገኘቱም እጅግ የሚያስደንቅ ነው። እኔ ይህን ታሪክ በአፈታሪክ እንደማውቀው እንደዚህ ረጅም የታሪክ ሰንሰለት የለውም። ንጉሡ “እኔን የሚደፍር እስቲ ማን ነው?” በሚል ከበጉ አንገት ላይ የተሳለ ቢለዋ(ካራ) ያስሩለት እንደነበርና ደብተራውም በዚህ ቢለዋ በጉን አርዶ እንደተመገበ በሁዋላም ንጉስ በመደፈራቸው ተናደው መቼም ጥጋብና ስካር የማያደርገው የለምና ብለው ድግስ ደግሰው ሰውን ሁሉ ጋብዘው ቢከታተሉ ደብተራው በመጠጥ ብዛት የሰራውን ሲቀባጥር ተገኘ። ደብተራውም “ንጉሡ ቢለዋ አስረው አርዳችሁ ብሉልኝ ያሉትን እኔ የንጉሥ የግብዣ እንዴት ብዬ ንቄ ልተው?”ብሎም ስላቅ ተናገረ። በሉ ይህንን ደፋር ጧት ስካሩ ሲበርድ አምጡልኝ ስለድፍረቱ የምቀጣውን አውቃለሁ ብለው አዘዙ። ደብተራው ጧት ላይ ስካሩ በርዶለት ልብ ቢል የሰራውን ስህተት አስተዋለ። ከችሎት ቀርቦ ንጉሡ “በል ትናንት የተናገርከውን እስቲ ድገምልኝ ?” አሉት። ደብተራውም “አይ ትናንት ብቻየን አልነበርኩም ጓደኞቼ ይጠሩልኝና እናገራለሁ” ብሎ መልስ ሰጠ።ንጉሡም ተገርመው ” ደግሞ ትናንት ከነማን ጋር ነበርክ ብቻህን ነው ስትቀባጥር የነበረው” ቢሉት “አይ ብቅልና ጌሾ አብረውኝ ነበሩ” ብሎ መልስ ሰጠ። ንጉሡም በመልሱ ተገርመው ይህስ ብልሃተኛ ነው ምህረት የይገባዋል” ብለው ነፃ እንደለቀቁት አፈ ታሪክ ይናገራል ። ስለተሟላው የታሪክ ወግ ግብዣችሁ እናመሰግናለን።

    Like

  4. አንድምታዎች፣
    ጥሩ ሥራ እየሠራችሁ ነው፤ መጽሔቱ የተሻለ እንዲሆን ከተፈለገ ግን፣ የሁሉም ጥረት ሊታከልበትና አስተያየት ለመቀበል ፈቃደኛነት ሊኖር ይገባል። ያልተስማማንን አስተያየት ማስተናገድ ግድ ነው፤ አለዚያ በቡድን ስሜት መነዳት ይሆንና መጽሔቷንና ጥበብን ማቀጨጭ ይከተላል፤
    1/ የአታሚው፣ የቦርድ አባላትና የለት ተለት ሥራ አስኪያጆች ስም በግልጽ ይታወቅ፤ ባለቤት የሌለው ቤት እንዳይመስልና ኃላፊነትን ላለመቀበል ሰበብ እንዳይገኝ፤
    2/ አስተያየት ሰጭዎች ጥያቄ ቢያነሱና ምላሽ ሳያገኝ ቢቀር ምላሽ የሚሰጥ ማነው?
    3/ አንባቢው “ዋው” “ተመቸኝ” “እንወድሃለን” “አድናቂህ ነኝ” ከማለት ባለፈ የውይይት ባህሉን እንዲያዳብር ምን ብልሃት ይፈጠር?
    ይህን አስተያየት እንደምታትሙ ተስፋ አደርጋለሁ።

    Like

  5. ይቅርታ፣ “ስለ መጽሔቷ” ሥር የሦስት ሰዎች ስም የተጠቀሱትን አይቻለሁ። ማን አታሚ፣ ማን ምን እንደሆነ ይገለጽ ማለቴ ነው። ሌሎች አስተዋጽኦ ካላቸው እንደዚሁ ይጠቀሱ፤ እንደ መደበኛ የጥበብ መጽሔት ማለት ነው። ፕሮፌሽናል ቢመስል ተኣማኒነትን/ክብደት ይኖረዋል።

    Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s