“ጉማ ላሎ” (ግጥም)

“ጉማ ላሎ”

ከሰሎሞን ዴሬሳ

(1963 ዓ.ም)

.

.

ቅኔ ነው ተባለ መሰረቱ

በብራና ቃላት መታሰሩ፤

እየተፍጠረጠረ ዝምብስ ይሞት የለ

እልባት መሃከል፤

ጉማ ሳይከፈል?

.

ቅኔ ነው አላችሁ መሰረቱ

ሰማእታት ከስሜት እንዳልተወለዱ

ቤትና ቤት ማምታታቱ፤

ቡሄ በሉ ልጆች ሁሉ

የቡሄን አደራ አንች አሞራ

.

መነጠር ሆነ ሸለቆ ተራራ

ቋንቋን አርጐ ባላጋራ

ድብብቆሽ መጫወቱ

ማግና ድሩን እያጣጡ

የማይገባ መጣፍ ካልገለጡ …

.

ልግለጥ ታድያ፣ ልግለጥ?

ኦኪ ዶክ …

ሳጠል ቆኜ፣ ፊደል ዋሬ

ቤንቴ ካራማሹኔ፣ ሲቡ ዳርጌ

አቡ ጊዳ፣ ራፉ ጂዻ

ቴኜ ዹግና፣ ኛኔ ሙግና

ሳጠል ቆኜ፣ ወዘተርፈ ለግእዙ

ቤንቴ ካራማሹኔ፣ ሲቡ ዳርጌ … 

ምን ይፈጠር

ልጅነት አይሰቀል

ምን ይፈጠር?

.

ከበሮ ነው ብልስ መነሻዬ

የረኛ ዋሽንት መጓዣዬ

ኰረዳይቱ መድረሻዬ

ያረረ ለቅሶ የራእይ ፊርማዬ

የኰረዳ ምላስ መሰቀያዬ

ብልስ?

ምን ትሆኑ?

ዝግባ አትቆርጡ

ሳታስፈቅዱ

ምን ትሆኑ?

.

በሌባ ጣቴ እምብርቴን

አጥቅሼ

የሌለ ብራና አለስልሼ

እንደ ትግራይ እንጉርጉሮ

ብልስ?

ጉማ ላሎ

ነያ ጉማ ላሎ

ጉማ ላሎ

መንኰራኩር መጣች በጪስ ተሸፍና

ጉማ ላሎ

ነያ ጉማ ላሎ

ጉማ ላሎ

የናትህ ልጅ ደፍታለች አንገቷን፣ ታለቅስልሃለች

ጉማ ላሎ

ነያ ጉማ ላሎ

ጉማ ላሎ

ምሽትህ ድርብ አሸንክታብ አጣፍታለች

ጉማ ላሎ

ነያ ጉማ ላሎ

ጉማ ላሎ

ብታቅማማ፣ ባታቅማማ

አትል ግጥም አይደል

ዱዳ ካልሆንህ የማትሰማ

.

ልጓም ካለ ለፍትወቱ

ሀሳብ ካለ ቸርነቱ

ብትሰማ

ባትሰማ

ብፈነዳ

ባልፈነዳ

ብቀኝ

ባልቀኝ

ባልመቀኝ

ባዳምጥህ ትዝብት ሁነኝ

.

ድንጋይ ሳልቈጥር

ቃላት ሳልቋጥር

ስንኝ ሳላዛውር

ግጥም ነው ቋንቋ ነኝ

ምን ታረጉኝ

.

ሰሎሞን ዴሬሳ

.

[ምንጭ]ልጅነት። ፲፱፻፷፫። ገጽ 41-43።

.

“የፈላስፋው ውሃ” (ወግ)

“የፈላስፋው ውሃ”

.

.

አንድ ንጉሥ እጅግ አጥብቆ የሚወደው ፈላስፋ ነበረው። አብሮት የሚጋበዝ፣ የሆነውን የሚሆነውንም ሁሉ የሚያማክረው።

በጤናና በስምምነት አያል ወራት አያል ዘመናት ሲኖሩ አንድ ቀን ከገበታ ላይ ለምግብ ተቀምጠው ሳለ ፈላስፋኑ አንስቶ “አዬ!” አለና እጅግ ተከዘ። ወደ ምግቡም እምብዛም ነፍሱ አልፈቀደ። በዚህን ጊዜ ንጉሡ ደንግጦ ያመመው መስሎት “ምነው በደህናህን?” ብሎ ጠየቀው።

ፈላስፋኑ እየመላለሰ ‘አዬን’ ብቻ ያዘ።

ንጉሡም “ደሞ አመመህን?” ቢለው እንኳን “አላመመኝም” ብሎ መለሰለት። “እንግድያውስ አሁንም አሁንም እየተከዝህ ‘አየ’ የምትለው ምን ብትሆን ነው?” ብሎ መረመረው።

ቀጥሎም ‘አዬን’ ብቻ ያዘ።

ንጉሡም ገሚሱ ቁጣ በገሚሱ ጭንቀት “እንደዚህ ያለ ምንድር ነው? ሯ!እባክህን ንገረኝ ምንድር ነው ብልሃቱ?” ብሎ ቢለው

“ክፉ ዘመን የሚመጣብን ቢሆን ነው እንዲህ የምሆነውን የማዝነው” ብሎ ፈላስፋኑ አለው።

የባሰውን ንጉሡ በዚህ ነገር ተጨንቀ። ንጉሡም በፍጥነት ነገሩን እንዲረዳው ፈለገ። ፈላስፋው ግን መልሶ ‘አዬውን’ ያዘ። ተዚህ ወዲህ ንጉሡ አጥብቆ ፈራ። “ሯ! እባክህን ውሃ አታርገኝ ንገረኝ” አለው።

“እስከ ሦስት ዓመት እንደለመድነው ጊዜ ሁሉ ነው። ቀጥሎ ግን የሚዘንበው ዝናብ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ሰውም ሆነ እንስሳም ሆነ ፍጡር የተባለ ሁሉ ይመርዛል። ውሃን የጠጣ ሁሉ ያብዳል። ወንዙ ምንጩ ባሕሩ ዝናቡ ሲዘንብበት ይመረዛልና። ስለዚህ ውሃ የጠጣ ሁሉ ያብዳል። ተዚህ የበለጠ ምን የሚያሳዝንና የሚያስተክዝ አለ?” ብሎ አረዳው።

ንጉሡም እንደ ፈላስፋው አንገቱን ደፍቶ ተራውን ይተክዝ ጀመረ። ቀጥሎ ጥቂት ጥቂት ተንፍሶ “ስማ እንደዚህ ያለ የማይቻል መዓት ሲመጣብነ ጊዜ ምን ይበጀናል?” ብሎ አማከረው።

“ለዚህማ መቼስ ምን አቅም አለኝ! ያሳየኝ ይህ ነው። ባዋጅ ‘የደህናውን ዝናብ ውሃ ጉድጓድ እያበጀህ አስቀምጥ’ ተብሎ ማስታወቅ ይሻል ይመስለኛል … ለክፉው ዘመን መውጫ እንዲሆን” ብሎ የተቻለውን ምክር መከረ።

አዋጁም ሳይውል ሳያድር ተመታ። ከሕዝቡ የፈራ ጉድጓድ ይምስ ጀመር። ነገሩን የናቀ ግን፣

“ተወው! አመሉ ነው። ሁልጊዜም አዋጅ ይመታልና መቼ አንድ ነገር ሁኖ ያውቃል? ደግሞ ያሁኑስ የሚያስደንቅ አዋጅ ነው! ተእግዜር ጋራ ተማክረዋልን? ” እያለ ያፌዝ ጀመር።

ከቤተ መንግሥቱ ደሞ ጉድጓድ ሁሉ ተሰናድቶ ተምሶ የደኅናውን ዝናብ አከማቹበት። በቁልፍም ተቆለፈ። የፈሩትም እንደዚሁ አደረጉ።

ያ ቀን መድረሱ አልቀረምና ደረሰ። ገና መዝነብ ሲጀምር በየወንዙ በየምንጩ በየባሕሩ ሲጥልበት ጊዜ ተመረዘ። ያን ውሃ የጠጣ ሁሉ ማበድ ጀመረ። ሲል ሲል እብደቱ እየባሰ ሄደ። የእብደት ብዛት እየገነነ ሄደ።

ነጋዴ ንግድነቱን ትቶ ወደ ሌላ ሆነ። አራሽም እርሻውን ትቶ ወደ ሌላ ሆነ። ልጅም አባት እየተወ ወደ ሌላ ሆነ። ካህናትም ክህነታቸውን ትተው ወደ ሌላ ሆነ። ቁም ነገር የነበረው ጨዋ ሆነ መኳንንትም ሆነ ሊቃውንትም ውልን ትተው ወደ ሌላ ሆነ። ለእብደቱ ዲካ ጠፋበትና ሁሉም ዝብርቅርቁ ወጣ።

ተዚህ ወዲህ በጐራ በጐራ እየተለየ፣

“ነጋሪት ምንድር ነው? ቆሪ እንጨት አይዶለምን? በሉ ነጋሪቱንም ጠፍሩ! መለከቱንም እምቢልቴውንም አብጁ!” አሉ።

በየጐራው አበጀ። ሁሉም ተተበጀ በኋላ ነጋሪቱን እየጐሸመ፣ መለከቱን እያንጠራራ፣ እምቢልቴውን እየነፋ … ሕዝቡ ሁሉ መቸም አብዷልና፣

“ንጉሥ አልነበረነም ወይ? አለ እንጂ! ወዴት ነው? ከግቢው ተቀምጦ ይንፈላሰሳል!” አሉ።

ይህነን ሁሉ ንጉሡም ፈላስፋውም ያያሉ ይሰማሉም።

ሕዝቡም እንዳልነው ጐራ እየለየ ነጋሪቱን እያስጐሸመ፣ መለከቱን እያንጠራራ፣ እምቢልቴውን እያስነፋ፣

“ንጉሣችን ወዴት ነው? በል ሳብ ወደ ግቢ!” እያለ ይስብ ጀመር።

ገቢዎች ይኼንን ነገር ባዩ ጊዜ በንጉሡ ታዛዥ የግቢ በር ሁሉ እንዲዘጋ ታዘዘ። እነዝያም እብዶች በደረሱ ጊዜ በሩ ተዘግቶ አገኙ።

“ደሞ ዘግቶታልና! አዎን ሊተርፈን? ሯ!” … በድንጊያም በዱላም ያን መዝጊያ ተለቀቁበት።

ንጉሡም ይኼንን ባየ ጊዜ ለፈላስፋኑ “አንተ! እነዚህ እብዶች ሊገሉን ሊፈጁን ደረሱብን! ምን ይበጀን ትላለህ?” ብሎ አማከረው።

“ንጉሥ ሆይ! እኔማ በጉድጓድ ደኅናውን ውሃ እናጠራቅም ለክፉው ዘመን መውጫ እንዲሆን ብየ መክሬ ነበር። ለሕዝቡም ይኼነኑን አስታወቅነ ይሆናል ብየ ነበር። ሳይሆን ሲቀርማ ያነኑ የሚያሳብደውን ውሃ ጠጥተን አንድ እንምሰል!” አለ።

እነሱም ያነኑ የሚያሳብደውን ውሃ ልጅ ተሾልኮ ይሂድና በቅምጫና ይዞልን ይምጣ ተብሎ ሰደዱት። ሄዶ ይዞ መጣ። እንደ ጠበል ተሻምተው ጠጡ። ወዲያውም አበዱ።

ንጉሥ መዝለልና መቀባጠር ጀመረ። ወዲያውም ወደ ግቢው በር ሂዶ፣

“ይኼንን በር ማን አባቱ ነው የዘጋው?” አለ … እርሱ ራሱ ዝጉ ብሎ ሲያበቃ!

ወዲያው ብዋ አርገው ከፈቱ። ንጉሡ እየዘለለ እየለፈለፈ እንደነሱ መስሎ በሩን በወጣ ጊዜ የተሰበሰበው ፍጡር ሁሉ መንገድ ለቆ ገለል ብሎ ዳር እስከ ዳር “እልል!” አሉ። ገሚሱ ያልሰማ “ምንድር ነው ነገሩ?” ብለው ሲጠይቁ፣

“ንጉሣችን አብደው ነበር ሽረዋል” ተባለ … ዳር እስከ ዳር እልልታውን አቀለጠው!

ክፉውን ዘመን ሁሉ ሲያብዱ ኖሩ።

ደኅናው ዘመን ሲገባ ሁሉም እየስፍራው እየሙያው እየደምቡ ገባ። መንግሥቱም አገሩም ሁሉም ረጋ።

.

[ምንጭ] – Major J. Eadie. 1924. “An Amharic Reader”. pp. 29-33.

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ” (ክፍል 2)

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ”

በደብተራ ኀይሉና በሐጅ አሊ

(1800 ዓ.ም)

.

(ከክፍልአንድ የቀጠለ)

.

.

ከዚህ በኋላ ከዛር ንጉሥ ሊዋጉ ሔዱ። ገና ሳይደርሱ ላኩባት። ሲልኩባት፣

“በዦሮ የሰሙን በዓይን ሳያዩት አይቀርምና … ታዪን መጣሁ” ብለው ላኩባት።

እርሷም ስትመልስ፣

“የኔም ሰው በነፍጥ ያልቃል። የርስዎም ሰው በሟርት ያልቃል። እኔም አልሞትም እርስዎም አይሞቱ … ምነው በፍቅር ብንለያይ አይሻልም?” ብላ ግብር ሰደደችልዎ።

ከዝያ በኋላ “ክፉ የተናገረች ታየኝን ነበረች!” ብለው ተመለሱ። ከቤታቸው በወጡ በ፯ ዓመት ቤታቸውን ገቡ።

ዳግመኛ የእስክንድርያ ንጉሥ የአሕዛብ ጸላት ቢነሣበት ዜናዎን ሰምቶ ነበርና “መጥተህ እርዳን” ብሎ ላከበዎ።

ተነሡና ሲሔዱ የ፫ ቀን መንገድ እንደሔዱ ዘንዶ እባብ ያለበት አገር ደረሱ። እየረገጡት የሚሔዱ ነው።

ከዚህ በኋላ ቤት የሚያህል አሞራ በኢየሩሳሌም አለ ያነን አስነድተው አመጡት። በእግዜር ፈቃድ ያነን በፊተዎ አደረጉትና ቢሔዱ እባቡና ዘንዶውን እየለቀመው ይሔዱ ዠመረ። የእባቡንና የዘንዶውን ምድር ሲጨርሱ ከደህናው ምድር ሲደርሱ ያም ጠላቱ መምጣተዎን ቢሰማ ሸሸ ‘ይዩልኝ’ ብሎ። የላከውም ሸሸ ‘እኔን ይጨምሩኛል’ ብሎ።

ከዚህ በኋላ ያሰቡትን ሳይደርሱ የማይቀሩ ንጉሥ ናቸው “ቀራንዮን ስሜ ኢየሩሳሌምን አይቼ አመጣለሁና እሔዳለሁ” አሉ።

ሹማንምቱ ገብተው “አይሂዱ ይቅሩ” ብለው መከሩ።

“ተቀረሁ በኢየሩሳሌም ለውዝ ገውዝ የሚሉ ሽቱ አለ ብለውኛልና ልመለስ አምጡልኝ” ቢሉ ሒደው አመጡልዎ ተመለሱ።

ከዚህ በኋላ የንጉሥን ብርታት ቢሰማ የሮም ንጉሥ “ልጅዎን ይስጡን” ብሎ ላከ። ማጫዎን ፵፰፼ መድፍ፣ ነፍጥ፣ ቁጽር የሌለው እቃ የማይታወቅ ሰጠ። ብዙ ነው። እጅግ የሚወዱዋት ልጅ ነበረችና ለርሱ ዳሩዋት።

ሲዘምቱም በ፼ በ፼ ነፍጡ መድፉ እየተቈጸረ ያሲዙ ነበረ። ፵ ፵፼ አኽያ በዳውላ ወርቅ እየተጫነ ከየደረሱበት እያሳመኑ የወርቅ ቤተ ክርስቲያን እየሰሩ፣ ደጅ አዝማች እየሾሙ፣ መምሕር ካህናት እየሰሩ ይሔዱ ነበርና ከባሕር ወዲህ ያለን ሁሉ አገር አሳመኑት። ከኢትዮጵያ ምድር አንድ አልቀረዎም ሁሉን አሳመኑት።

ክፉ ወንድ ልጅ ነበረዎ።

‘እሱ ይነግሣል’ የሚሉ ንግር ነበረና አይወዱትም ነበረ። ሀብተዎን ሁሉ ስለዚህ ምክንያት ለሴት ልጅዎ ይሁን ብለው ሮም ሰደዱት።

“እርሱም በሀብቱ ይንገሥ” አሉ።

እርሱም መጥቶ ነገሠ። የርስዎም እቃ ተመልሶ ሮም ወረደ።

ተፈጸመታሪክዘጸሐፎኃይሉወዘአጽሐፎሐጅአሊ።

.

ደብተራ ኀይሉ እና ሐጅ አሊ

1800 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – Bibliothèque Nationale። Eth Ms 144። ቅጠል 19-20።

“ሌሊሳ ግርማ” (ቃለመጠይቅ)

“ቆይታ ከሌሊሳ ግርማ ጋር”

(ቃለመጠይቅ)

.
[ከአንድምታጋርየተደረገውይይት]

.

[ሌሊሳ ግርማን አብዛኞቻችን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ባቀረባቸው አጫጭር ልብወለዶቹ እናውቀዋለን። ከዛም ባሻገር በርካታ የልብወለድ እና ወግ አዘል መጣጥፍ ድርሰቶችን በመጽሐፍ መልክ አቅርቦልናል። ባለፈው ዓመት መገባደጃም “እስቲሙዚቃ!” የተሰኘ 38 አጫጭር ታሪኮችን የያዘ አዲስ የልብወለድ መጽሐፍ አሳትሟል። አንድምታ ሌሊሳን በቅርቡ በሥነጽሑፍ ዙርያ አነጋግራው ነበር።]

.

በልጅነትህምንአይነትመጻሕፍትንታነብ ነበር?

መጀመሪያ እናታችን ልጅ ሳለን ብዙ ተረት ታወራልን ነበር። … እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ከትምህርት ውጭ ምንም ንባብ ስለማድረጌ አሁን ትዝ አይለኝም። … ምናልባት ብዙ ስዕል ያለባቸው የተረት መፅሐፍት አገላብጬ ሊሆን ይችላል። … አራተኛ ክፍል በአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ መፅሐፍት ከት/ቤቱ ላይብረሪ እየወሰድን ማንበብ እና ያነበብነውን ለአስተማሪው ማስረዳትን የሚጠይቅ መርሐ ግብር ተጀምሮ ነበር። ምናልባት ያኔ ነው የአማርኛ መፅሐፍትን ማንበቡ የጀመረው ወይንም የቀጠለው። .. የተማርኩት የግል ትምህርት ቤት ስለነበር በሳምንት አንድ ፔሬድ በላይብረሪ ውስጥ መፅሐፍ ወስደን ለአርባ አምስት ደቂቃ የመረጥነውን መፅሐፍ ስናገላብጥ ለመቆየት እንገደድ ነበር።

… አዎ እንገደድ ነበር ነው ያልኩት። ብዙ ስዕል ያለበትን መፅሐፍ ቀድሞ የያዘው ብዙም ሳይሰለቸው ፔሬዱን ያጠናቅቃል። “ጣፋጭ ታሪክ” የሚባል መፅሐፍ ትዝ ይለኛል። ታሪኩ የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው። መፅሐፉ ላይ ያሉ ስዕሎች በጣም ይመስጡኝ እንደነበር እንጂ መፅሐፉ ውስጥ ያለው ንባብ ላይ ብዙም አልተሳተፍኩም።

… እኔ ከንባብ ጋር በእውነት ትውውቅ የጀመርኩት በት/ቤት ሳይሆን በቤቴ ነው። መንስኤውም አባቴ ነበር። አባቴ መሀንዲስ ቢሆንም ከራሱ የሞያ ክልል ውጭ በብዙ ዘርፍ ላይ የእውነተኛ ንባብ ያደርግ የነበረ ሰው ነው። በፊት ብቻ ሳይሆን አሁንም በሀይል በማንበብ ላይ ይገኛል። (ስድስተኛ መፅሃፉን በቅርቡ አሳትሞአል)

… አባቴ መፅሐፍ ሲያነብ እና የአባቴን “ጥናት ቤት” (Library) የማይጨምር የልጅነት የመጀመሪያ ትዝታ የለኝም።

ስለዚህ፤  አባቴ አራተኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ላይ ለእኔ ለወንድሞቼ እና እህቴ አንዳንድ መፅሐፍ መርጦ ሰጠን። ለእኔ የመረጠልኝ የአንቶኒ ሆፕን “The Prisoner of Zenda” ነበር፤ ትዝ ይለኛል። … የመረጠልንን መፅሐፍ ጮክ ብሎ እያነበበ ይተረጉምልናል። ለእያንዳንዳችን ከተመረጠው መፅሃፍ ላይ አንድ አንድ ምዕራፍ … በየእለቱ። አነባበቡ እና ቃላቱን የሚተረጉምበት መንገድ በፍፁም ከአእምሮ የሚጠፋ አይደለም። … እሱ ማታ ያነበበልንን ቀን ስንደግም እንውላለን። ወደፊት ገፍተን ለማንበብም እንሞክራለን። ያልገባንን እሱ አቃንቶ እንደገና ማታ ይቀጥላል። መፅሐፉ ተነቦ እስኪያልቅ ድረስ። መፅሀፉ በአባቴ እና በእኔ ትብብር ተነቦ ሲያልቅ ከወንድሞቼ እና እህቴ ጋር መፅሐፍ እንለዋወጣለን። … መፅሐፍቱ ለጀማሪ አንባቢዎች ተብለው አጥረው የተዘጋጁ (Abridged) ናቸው። ብዙዎቹ “Longman’s series” የሚያዘጋጃቸው ነበሩ።

ብቻ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል እነዚህ አይነት መፅሐፍትን ሳላውቀው ብዙ አንብቢያለሁኝ። (The Coral Island, Round the World in Eighty Days, Treasure Island, The Lost World, Beau Geste, The Thirty Nine Steps…ወዘተ)

በተለይ “Montezuma’s Daughter” ራይደር ሀጋርድ በሚባል ደራሲ የተፃፈው … ትዝ ይለኛል። … የአባቴ … ሌላ ጊዜ ደግሞ የአጎቴ … የመተረክ እና የማስረዳት አቅም ባይታከልበት እነዚህን መፅሐፍት ወደ መውደድ አልደርስም ነበር።

ከፍ እያልኩ ስመጣ ሙሉ ፊክሽኖችን ማንበብ ጀምሬአለሁ። ወደ እነ አጋታ ክሪስቲ … እና ሸርለክ ሆምስ … ምናምን። … ሰው ትምህርቱን ነበር የሚያጠናው እኔ ፊክሽን ነበር የማነበው።… እነ ሉድለምን … እነ ሀሮልድ ሮቢንሰን። በኋላ ደግሞ “Western” (Cowboy) ድርሰቶችን ወደ መጨፍጨፍ ገባሁ። … ቤት ውስጥ Zane Grey የሚባል ደራሲ የተቆጣጠረው ሼልፍ ነበር (አሁንም አለ)።

… አሁን ይገርመኛል እንዴት እነዛን መደዳዎች ሁሉ በዛው ዘመን ጨርግጄ እንደጨረስኩኝ። አሁን በምንም አይነት ያንን ያህል ፊክሽን ደግሜ ለማንበብ አልችልም። … በዘመኑ የሚወጡ የአማርኛ መፅሃፍትን ከእንግሊዘኛው እኩል ነበር የማነበው። “ሳቤላ” እና “East Lynne” ጎን ለጎን ማንበቤ ትዝ ይለኛል። አማርኛው ከእንግሊዘኛው ተሽሎኛል። በሁለቱም ቋንቋ … መፅሐፉ እኔን አላስለቀሰኝም። … ምናልባት ማልቀሴ እንደማይቀር ቃል ስለተገባልኝ ሊሆን ይችላል። …

… ትርጉመ ቢስ ከሚመስል ድራማ እና አድቬንቸር እየወጣሁ ስመጣ A.J Cronin የሚባል የአየርላንድ ደራሲ ተቀበለኝ። …. መጀመሪያ “Hatters Castle” በሚል ጨለምተኛ ድርሰት ነው የተዋወቅሁት።

ስለመጀመሪያ የድርሰት ሙከራህ ምን ትዝ ይልሃል?

የድርሰት ሙከራዬ ከሀያ አመቴ በኋላ በግጥም ነው የጀመረው። በእንግሊዘኛ ግጥም። ከመጠን ያለፈ የቪክቶሪያዊ ገጣሚዎችን ስራ አመነዥግ ነበር። የነ ቴኒሰንን፣ የነ ኪፕሊንግን፣ የነ ብራውኒንግን … የነ ኬትዝን …

ስለዚህ የእነሱን የመሰለ ግጥም መፃፍ ጀመርኩኝ። ሀሳብ እና ስሜት ማብቀል ብቻ ሳይሆን ያንን የማንፀባርቅበት መንገድ ያገኘሁ መሰለኝ። ብዙ እስክፅፍ ለማንም አላሳይም ነበር። በኋላ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ጓደኞች ሳገኝ መናበብ ጀመርን። የእነሱን ሙከራ ማንበብ የእኔንም ማስነበብ። አንዲት ግጥም የኢትዮጵያን ኤርላይንስ የአብራሪዎች ምርቃት በማስመልከት በተዘጋጀ መፅሔት ላይ ወጣችልኝ።  ከዛ የልብ ልብ ተሰማኝ። … ግጥሞቼን ይዤ የእንግሊዘኛ ጋዜጦች ላይ መሄድ ጀመርኩኝ። ”The Sun” የሚባል ጋዜጣ ብዙ ግጥም እንዳወጣልኝ ትዝ ይለኛል። … ከግጥሞቹ በኋላ የእንግሊዘኛ አጭር ልብ ወለዶችን መሞከር ያዝኩኝ። … የአጭር ልብ ወለዶቹ እስካሁን በህትመት ተፈትነው አያውቁም።

… ከዛ የመፃፍ ግፊቱ እና ፍላጎቱ እየጨመረ መጣ። በመምጣቱም የተነሳ ሌላ አይነት ተግባር ወይንም እንቅስቃሴ ሁሉ ትርጉም የሌለው ይመስለኝ ጀመር። የሙሉ ሰአት ፀሀፊ መሆን አለብኝ ብዬ ቆረጥኩኝ። … ተው ቢሉኝም ልተው አልቻልኩም። … አማርኛን ለመፃፍ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረኩት ጋዜጣ ላይ ፅሁፍ በማውጣት ለመተዳደር ስወስን ነው። … መጀመሪያ የእንግሊዘኛ አጭር ልብ ወለዶችን ወደ አማርኛ በመመለስ ጅማቴን አጠነከርኩኝ። የቋንቋ አቅሜን ከፍ አደረግሁኝ።… ከዛ መጣጥፍ ወደ መፃፍ ገባሁኝ። ከመጣጥፉ በኋላ አጭር ልብ ወለድ መፃፍ ጀመርኩኝ። አማርኛ ላይ የምፅፈው ፅሁፍ ሲበዛ እንግሊዘኛ ላይ የጀመርኩት ፅሁፍ እያሽቆለቆለ ሄደ። … አለማቀፍ ፀሀፊ ለመሆን ያለኝ ህልም ሀገራዊ ፀሀፊ በመሆን ተቋጨ።

ወደአጭርልብወለድ ድርሰትየበለጠለማተኮርለምንወሰንክ?

… የአጭር ልብ ወለድን ቅርፅ እወደዋለሁኝ። ከድሮውም አጭር ድርሰቶች ተተርጉመውም ሆነ በወጥነት አግኝቼ ሳነብ በጣም ደስ ይሉኛል። … ያው ማንም ፀሀፊ እኮ ማድረግ የሚቀለውን እና የማይችለውን ያውቃል። የሚቀለውን ብቻ ሳይሆን ከእሱ ፍላጎት ጋር የሚሄደውን ሚዲየም ይመርጣል።

እኔ ደግሞ በአማርኛ ግጥም ከመፃፍ አጭር ልብ ወለዱ ይቀርበኛል፤ ግዛቴ ይመስለኛል። … ማለት የምፈልገው ሀሳብ ወይንም ስሜት በልብ ወለድ ቅርፅ ተቀምጦ ይታየኛል። … በብዛት የማይገኝ ብርቅም ይመስለኛል። እና መፃፍ ፈልጌ ብዕር ስሰነዝር በቀላሉ ምናባዊ እና አጭር ፅሁፍ ይሆንብኛል። መሆኑንም አልጠላውም። እኔ ባነብ የምወደውን አይነት ፅሁፍ ብፅፍ ደስ ይለኛል እንጂ አይከፋኝም። ምናልባት ወደፊት ከሰለቸኝ ላስወግደው እና ሌላ አይነት አማራጭ ለመፈለግ ልወጣ እችላለሁኝ።

የአዲሱመጽሐፍህየአጻጻፍሂደትምንይመስልነበር?

የአፃፃፌ ሂደቴ ጋዜጣ ፅሁፍ ሳዘጋጅ እንደማደርገው በቀን ቢያንስ አንድ ሺ ቃላት ቢበዛ ሁለት ሺ  ቃላት በመፃፍ ነው። በእኔ እጅ ፅሁፍ በልሙጥ ወረቀት ላይ የሚከናወን ነው።

የሁሉም ገፀ ባህሪዎች መነሻ ፤ ከአብዮቱ በኋላ የተወለዱ የእኔን ዘመን ተጋሪዎች እና የከተማን መቼት የሚመለከት ነው። እነዚህ ገፀ ባህሪዎች ምናልባት በእውቀቱ “የተካደ ትውልድ” የሚላቸው አይነት መሆናቸው ነው። የተለያየ ርእዮተ አለም እና የተለያ ሱስ የተቀባበላቸው ናቸው።

“ኤስ” የተሰኘው ገጸባህሪ የዚህ ትውልድ ተወካይ ነው። ሁሉንም ነገር ለመሞከር የሚደፍር እና  በሞከረው ነገር ላይ ሁሉ ብልጫ የሚያሳይ … ዘመኑ ከነፈገው በላይ የሚፈልግ የጂኒየስ አዝማሚያን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያሳይ ገፀ ባህርይ ነው። “እሸቱ” የተሰኘው ገጸባህሪ ደግሞ ደራሲ ነው። እሸቱ ኤስን ይፅፈዋል አንዳንድ ቦታ። ሌላ ቦታ ኤስ ስለ ራሱ በአንደኛ መደብ ተራኪ ይናገራል። እሸቱ ኤስን ሲፅፈው የራሱን እምነት እና ፍላጎት ያላክክበታል።

የኤስን ታሪኮች መፃፍ የጀመርኩት ሁለት ሺ ሰባት መጀመሪያ ላይ ነው። እያንዳንዱ ታሪክ በአንድ ቀን ይፃፋል። ከእያንዳንዱ የእለት ታሪክ ጋር አንድ vignette (ገላጭ ሀረግ) በታሪኩ አናት ላይ አስቀምጫለሁኝ። ቪኜቱ ከታሪኩ ጋር ግንኙነት የለውም። አንድ ሀሳብ ወይ ምስል ወይንም ሌላ ቅንጭብ የፈጠራ አጋጣሚን የሚያሳይ ነው። ቪኜቶቹ ከ ኤስ ታሪኮች ጋር ግንኙነት የላቸውም። ወደ ሁለት ወር አካባቢ ብዙ የኤስ ታሪኮችን ፃፍኩኝ። እያንዳንዱ እለታዊ ፅሁፍ አጭር ልብ ወለድ እንዲሆን አቅጄ ነው የፃፍኩት። ሁሉም ታሪኮች በራሳቸው የሚቆሙ እና ከሌላ መሰላቸው ጋር በመጠነኛ ምልክቶች የሚገናኙ እንዲሆኑ ነበር የወጠንኩት።

ሁለት ወር ከፃፍኩት በኋላ ብዙም አካሄዱ አላማረኝም። የኤስን ታሪክ ለመፍጠር የእኔን ግለታሪክ በጣም እየታከኩ እንደሆነ ሲገባኝ አቆምኩት። ብዙ ገፅ ከተፃፉት የተወሰኑትን ብቻ መርጬ ሌላውን አስቀመጥኩት። ይመስለኛል … ሀሳብ ነበር ያጠረኝ። ይሄንን ካራክተር (ኤስ) የሚሸከም ሀሳብ ስላላገኝሁ ተውኩት።

ግን ልቦለዶቹ መጀመሪያ እንዳሰብኩት ሳይሆን … ማለትም ኤስን የሚከተሉ ሳይሆን … በኤስ ዙሪያ የሚካሄዱ በመሆናቸው እንደ ነጠብጣብ የተፈነጣጠሩ ናቸው።  ነጠብጣቦቹን ገጣጥሞ የሚያይ ሰው፤ ስለ ኤስ እና እሸቱ ሳይሆን ስለ ዘመኑ መንፈስ አንዳች ምስል ሊያገኝ ይችላል።  የሚያገኘው ምስል ግን፤ እንደ አብስትራክት ስዕል መልሶ ፍንጥርጣሪ ነጠብጣብ ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል። ይሄ ነው የመፅሀፉ ጥቅል ትልም።

አንዳንዶቹ የ“እስቲ ሙዚቃ“ መፅሐፍ መሰረታዊ መያያዣዎች ከመፅሐፉ ውጭ የሚገኙ ናቸው። … እንዲሁ ሌሎች  አያያዥ ታሪኮች ደግሞ በመፅሀፍም ላይ ያልሰፈሩ፤ በወረቀት ከፃፍኳቸው በኋላ ንቄ ያስቀመጥኳቸውም አሉ። ለምሳሌ “Ace” የሚል አንድ አጭር ልብወለድ  የሆነ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ መፅሀፍ ላይ ግን ያላካተትኩት አለ።

ምስሎቹ እንደ ጂግ ሶ ፐዝል ግጥምጥም እንዲሉ የታቀዱ አይደሉም። በአንድ እርምጃ እና በሌላው መሀል ክፍተት እየተውን እንደምንራመደው ሁሉ የኤስ ታሪኮችም በቂ የእርምጃ ዱካ እየተዉ … ግን በእየዱካው መሀል ባለው ክፍተት ከአንድ መቼት እና ጭብጥ ወደ ቀጣዩ የሚሻገሩ ናቸው። የጥቅል ታሪኩን “Tip of the Iceberg” ብቻ እንዲያሳዩ እንዲሆኑ ሆን ተብለው የተቀረፁ ናቸው።

እያንዳንዱ ታሪክ ራሱን ችሎ የሚቆም … ግን  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዘመን መንፈስን በማሳየት ለጥቅሉ መቼት እና ጭብጥ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው።

ኤስስለተሰኘውገጸባህሪእስቲጥቂትብትለን

እስቲሙዚቃ ላይ በጥቂቱ ማየት የሚቻለው ኤስ የስምንት አመት ልጅ እያለ የተከሰተውን አጋጣሚ ነው። አጋጣሚውን የሚተርከው እሸቱ ወይንም ሌላ ሦስተኛ ሰው ሊሆን ይችላል። ኤስ አዋሽ ሰፈርን በእናት እና አባቱ ጥል ለመልቀቁ የመነሻውን ምክንያት መጠነኛ ምስል የሚሰጥ ታሪክ ነው።

“የምርጥ ውሻ አጭር ታሪክ” የሚለው ደግሞ እሸቱ የኤስን ማንነት/እምነት ከአሳለፈው ታሪክ ጋር በግርድፉ የሚናገርበት ነው ማለት ይቻላል። ታሪኩ ላይ ኤስ ከልጅነት ጉጉቱ እስከ ተስፋ መቁረጫው ዘመን … ገጣሚ የመሆን ፍላጎቱን እስከሚያጣበት ከወፍ በረር የሚያስቃኝበት ነው።

ኤስ ከእናት እና አባቱ መለያየት በኋላ እናቱን ተከትሎ ለመኖር እንደሄደ “ማህሌት” በምትባል ልጅ ከትምህርት ገበታው ከተሰናበተ በኋላ ባለው አመት ቴክኒሻን ሆኖ ነበር።

“እየሱሳዊ ሽጉጥ” የተሰኘው ታሪክ ሞትን መናቅ የጀመረበትን አጋጣሚ ለማሳየት የሚጥር ነው። “ሰው ሲሸነፍ” በሚለው ታሪክ ኤስ ራሱን ለመግደል ሲሞክር ይታያል። ግን ሳያደርገው ይቀራል። ኢትዮ-ኤርትራ የጦርነት ግጭትን ተከትሎ ጦር ሜዳ እውነተኛውን ሞት ለመሻት ወይ ለማሽተት ይሄዳል።

ተመልሶ ሲመጣ ተለውጦ ነው። ከደራሲው እሸቱ ጋር የሚተዋወቁት ይሄኔ ነው። ትውውቃቸውን የሚያሳየው የታሪኩ ክፍል ግን “እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች” የሚለው መድብል ላይ ሳይሆን ያለው “አማሌሌ እና ሌሎች” የሚለው መፅሀፍ ላይ ነው።

ይህንልዩገጸባህሪበሌሎችድርሰቶችመልሰህታቀርበውይሆን?

“ኤስ“ ራሱን ችሎ እንዲከሰት አንድ ታላቅ እምነት ወይንም ሀሳብን ሰንቆ መምጣት መቻል ይኖርበታል። ይሄንን እምነት ወይንም ሀሳብ ደግሞ ደራሲው (እኔ) ከገፀባህሪው ቀድሜ ማግኘት ይኖርብኛል። ያገኘሁ ለት ኤስ የተባለውን ገፀባህርይ ይሄንን ተልዕኮ ሰጥቼ እመልሰዋለሁኝ።

አሁን በተደጋጋሚ “እስቲ ሙዚቃ”ን ባገላበጡ አንባቢዎች የሚሰነዘረው አስተያየት … ኤስ አፈንጋጭ ገፀባህርይ ነው። የብዙሀኑን አንባቢ ወይንም የማህበረሰብ ድምፅ የሚወክል እንዳልሆነ ነው የምሰማው። “Weird” ነው። ስለዚህ ሙሉ ወጥ መፅሀፍ ይሄንን አፈንጋጭ ገፀባህርይ ያለ ግብ ቀርፆ ማንከራተት … ለገፀባህርይውም ሆነ ለአንባቢ ትርፍ ያለው አይመስለኝም።

ወጥ የሆነ አላማ እና እምነት ሲገኝ ግን ገፀባህርይውን ወልውዬ እንደገና እንዲመለስ ለማድረግ እሞክራለሁ።

ለወደፊት ምንአይነትሥራዎችንለማቅረብአቅደሃል

የሚቀጥሉት አመታት የምሞክረው ወጥ የልብወለድ ድርሰትን ለማሳካት ነው። የአጭር ልብወለድ ፀሀፊ በመሆኔ ወደ ረጅም ልብወለድ መሻገር … እንደ መመኘት ቀላል አይሆንም። ግን በቂ ሰላም እና የፈጠራ ፀጥታ ካገኘሁ ይሄንን ግብ ለማሳካት ነው ምኞቴ። ወግ፣ አጭር ልብወለድ እና መጣጥፍ መፃፌን ጎን ለጎን እቀጥላለሁ። የፃፍኩትን የሚቀበል ጋዜጣ ካገኘሁም አትሜ አስነብባለሁኝ።

ለሁሉም ግን የኑሮ እና የፖለቲካ ሰላም መኖሩ ለእኔ ለፀሀፊውም ሆነ ለአንባቢው ቁልፍ ጉዳይ ይመስለኛል።

.

ሌሊሳ ግርማ

(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)

ጥቅምት 2010 ዓ.ም

.

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ” (ወግ)

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ”

በደብተራ ኀይሉና በሐጅ አሊ

(1800 ዓ.ም)

.

ክፍል አንድ

.

አጼ ዳዊት በነገሡ ጊዜ ግብጽ ያለው የስጥንቡል ንጉሥ፣

“ትገብር እንደሆን ገብር አትገብር እንደሆን አታመልጠኝም ቻለኝ መጣሁ” አለና ላከብዎ … በአጼ ዳዊት።

እርስዎም “ብትመጣ ጦር አለኝና እችልሃለሁ” ብለው ላኩበት።

እርሱም ሳይነሳ የኢትዮጵያን ውሀ ሁሉ በኖራ መልሰው አድርቀው ወደ ምሥራቅ ሰደዱትና ውሀ አጡ ግብጻውያን ሁሉ። ከዚህ ወዲያ ማረኝ ሲል ላከ።

“መማለጃኸንም በ፼ ግመልና በቅሎ አኽያ የተጫነ ወርቅ ብርና ግምጃ ተቀበለኝ። በውሀ ጥም አንለቅ። ግዱን በፈጠረህ አምላክ ማረኝ” ብሎ ላከ።

እርስዎም ሲልኩ፣

“ማረኝስ ታልኸኝ ብር ወርቅ ግምጃ ምን ይሆነኝ? መማለጃየንስ ጌታዬ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል እቃውን ሁሉ፣ የሰማዕታትን ዓጽም፣ ስዕርተ ሐናን፣ የሙሴን ጎሞር ከነጎፍላው፣ የዮሐንስን መስቀል፣ ሉቃስ ወንጌላዊ የሳላቸውን ስዕል፣ የቀራንዮን መሬት ከሊቀ ጳጳሱ ዘንድ ልከህ አስመጣልኝ። እንታረቅ ውሀውንም ልመልስልህ። ይህ ሁሉ ያልሁህ ታልገባልኝ ውሀውንም አልመልሰልህም” ብለው ላኩ።

እርሱም ሉል አደረገና የግብር መዠመርያ ግማደ መስቀሉን፣ ኵርዓተ ርእሱን፣ የተገረፈበትን አለንጋ፣ ራሱን የተመታበትን ብትር፣ ከለሜዳውን፣ ሐሞት የጠጣበትን ቢናግሬ፣ እግሩን እጁን የተቸነከረበትን፣ የቀራንዮን መሬት ደሙ የፈሰሰበትን ጭነው። የቅዱስ ጊዮርጊስን አጽምን፣ የፈረሱን ጭራ ቢሰፍሩት ፵፪ ክንድ ሆነ። የ፳፭ አጽመ ሰማዕታት፣ ስእርተ ሐናን፣ ዮሐንስ ያጠመቀበትን መስቀል፣ ሉቃስ ወንጌላዊ የሳላቸውን ስእላት፣ የሙሴን ጎሞር ከነጎፍላው፣ ከዚኽም የሚበዛ ብዙ እቃ ሰደደልዎና ታረቁ።

ውሀንም መልሰው ሰደዱላቸው። ስለዚህ ኢየሩሳሌምን ግብጽንም አስገበሩት።

ከዚያ ወዲያ የዘንዶ ንጉሥ አለ ቢሏቸው ሠራዊታቸውን ክተት አሉና ዘመቱ እዋጋለሁ ብለው። ዘንዶም አፉን ይከፍትና ፼ ዝሆን እየገባ ሲከማች ጊዜ አፉን ይገጥመዋል። በዚህ ይኖር ነበር። ያን ጊዜ ቢደርሱ አፉን ለቆ አገኙት። ዋሻ አገኘነ ብለው ንጉሥ ከለሠራዊታቸው ገቡ።

ሲገቡ ነፍጥ ቢያስተፉ ፪ ዛሮች ተከሠቱ።

“የዘንዶ ንጉሥ አሉ ይላሉ ወዴት?” ብለው ጠየቋቸው።

“ይህ የገባችሁበት አይዶለውም” አሏቸው።

ንጉሥ ደንግጸው ከለሠራዊትዎ  ወጡ። ከዝያ ወዲያ ፰ ቀን በመድፍና በነፍጥ ቢደበድቡት አልላወስ አልቀሳቀስ ብሎ በግድ ሞተ።

ከዝያ በኋላ ምሥራቅ ምድር ሔዱ … ከፀሐይ ጋር እዋጋለሁ ብለው። ለንጉሥ የ፰ ቀን ጐዳና ሲቀረዎ ፊታውራሪው አጠገቧ ሲደርስ፣ እርሷም ከመስኮቷ ስትወጣ፣ ያነን የሰፈውን ፊታውራሪ ሠራዊት እንደ ሰም አቅልጣ ፈጀችው … ንጉሥ ሳይደርሱ።

ከዝያ በኋላ አንድስ የሚሉት አውሬ ከገደል ስር የሚኖር አለ አሏቸው … ሊዋጉ ሔዱ። የ፰ ቀን መንገድ ሲቀረዎ ፊታውራሪው ከገደሉ አፋፍ ሲደርስ፣ ገና ሳይወጣ ድምጡን ቢሰሙ፣ ግማቱ ቢሸታቸው ፊታውራሪው ከለሠራዊቱ አለቀ።

‘አንድስ አንድስ ይሸታል’ የሚሉት ከዚህ የተነሣ ነው።

(በክፍል 2 ይቀጥላል … )

ደብተራ ኀይሉ እና ሐጅ አሊ

1800 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – Bibliothèque Nationale። Eth Ms 144። ቅጠል 18-19።

“ልብወለድ ታሪክ” (ጦቢያ)

“ልብወለድ ታሪክ”

በአፈወርቅ ገብረየሱስ

(1900 ዓ.ም)

.

ደግ አድራጊ አበደረ ክፉ አድራጊ ተገደረ።

ለጋስ ቢለግስ አበደረ እንጂ አልሰጠም።

.

ኦሪት ተሽራ ወንጌል መሰበክ በተጀመረ ዘመን እስላሙ ከፍ ብሎ ክርስቲያኑ ዝቅ ይል ነበር። ድሉ ግን አንድ ጊዜ ለክርስቲያኑ ሲሆን አንድ ጊዜም ለእስላሙ ሲሆን ይኖር ነበር። ነገር ግን ከነዚህም ወገን ከነዚያም ወገን ከቶ እርቅ የሚፈልግ አንድም ሰው አልነበረ። ብቻ በየጊዜውና በየወርሁ በያመቱ ሲዋጉ ሲፋተጉ ሲተራረዱ ሲተላለቁ ይኖሩ ነበር።

እንደዚሁ ሁሉ አንድ ጊዜ የእስላም ጦር እንደልማዱ መጣ በተባለ ጊዜ የክርስቲያኑ ንጉሥ ተፋጥኖ ጦሩን ባዋጅ አስከትቶ ባራት ደጃዝማቾች እግር አሳዝዞ ሂድ ተዋጋ ብሎ ሰደደ። ከነዚያ ከሄዱት ካራቱ ደጃዝማቾች ሶስቱ ከውጊያው ላይ ሞቱ። አንደኛው ግን ተያዘ። ሰዉም ሁሉ ከዚያው ላይ እንደጉድ እየተሳመጠ እየተናነቀ እየተራኰተ ሞተ አለቀ። የቀረውም ጥቂት ሰው ተማረከ። አንድ ለዘር ወዳገሩ ሸሽቶ ያመለጠ ሰው ግን አልተገኘም። የእስላሙ ጦር ግን ከድሉ በኋላ እንደፈከረው ገብቶ ከብቱንና ምርኮውን ይዞ ወዳገሩ ተመለሰ።

ይሄ ወሬ በያገሩ ተዘራና ሁሉም በየዘመዱ መሞት መማረክ ይላቀስ ፊቱን ይነጭ ጠጕሩን ይቈረጥ ጀመር። የክርስቲያኑ ንጉሥም የጦሩን ማለቅ የሶስቱንም ደጃዝማቾች መሞት፣ ያንደኛውንም ደጃዝማች መታሰር፣ ያገሩንም መዘረፍና መጥፋት በሰማ ጊዜ ወዲያው በሀዘንና በድንጋጤ ታሞ ከጥቂት ቀን ወዲያ አለቀኑ ተቀሰፈ ሞተ። የክርስቲያንም አገር ባንድ ጊዜ ንጉሥ አጣ፣ ገዢ ጠፋበት። አገሩም ምድረ በዳ ሆነ።

ያ ተማርኮ የቀረው ደጃዝማችም የእስላሙ ጦር አገሩን እንደ ተመለሰ በማረከው ሰው እጅ ተሸጠ። ማራኪው ሰው ግን ሲማርከውም ሲሸጠውም ትልቅ ሰው መሆኑን ሳያውቅ እንዲያው እንደማንም ሰው ነው የሸጠው። ያነኑ መከረኛ ደጃዝማች የገዛ እስላም ግን ቁመቱን ዛላውን አምሮ ባየ ጊዜ ‘ማለፊያ ብርቱ ባሪያ አገኘሁ’ ሲል ደስ አለውና ብርቱ ብርቱ ስራ እያዘዘ፣ እንደለጓሚ ሣር ያሳጭደው፣ እንደቋሚ እንጨት ያስፈልጠው፣ እንደጐረደማን ድንኳን ያስጭነው፣ ተራዳ ያስሸክመው ጀመር።

እሱ ግን ያልለመደው ነገር ነውና ከዚህ ሁሉ ሥራ አንድ የሚሆንለት ነገር አጣ። ሣር ልጭድ ቢል የለሰለሰው የጨዋ እጁ እንደሽንኵርት ተላጠ። ብርጭቆ ብርሌ በሚጨብጥበት በነበረው ጣቱ ምሳር ቢጨብጥበት ጉብር አወጣ። ያም ሆነ ያም ሆነ ያው የጥንት ደጃዝማች የዛሬው ባሪያ አዲሱ ጌታው እንዳይቈጣው ምናልባችም ባልተወለደ አንጀቱ እንዳይገርፈው እየተጋጠጠ ሥራውን አልሁህ አልሁህ ይል ጀመር። ነገር ግን ያኰረሰው እጁ ጭራሹን ተሞሸለቀ። ተራዳ የሚሸከምበት ጫንቃውም አጕርቦ የነበረው ሁሉ ተገሸለጠና የማይሆንለት ሆነ። ጌታው ግን ለሥራ ተለገመ መስሎት ይቈጣውና ለመግረፍ ያንገራግረው ጀመረ። ይሄው አዲስ ገብ ባርያ ግን “እንግዴህ የምታረገውን አድርገኝ እንጂ ተችሎኝ የምሰራልህ ነገር አላገኝም” አለና ጫንቃውንም እጁንም አሳየው።

ያም ጌታው ባየው ጊዜ እውነትም መስራት እንዳይሆንለት አየና የጨዋ ልጅ ነው ይሆን ብሎ ጠረጠረ። በዚህ የተነሳ የማረከውን ሰው “የሸጥህልኝን ባሪያ ስትማርከው ምን ለብሶ አገኘኸው” ብሎ ጠየቀ። ያም ሰው “ብዙ ጌጥ ነበረው ገፍፌ ብሸጠው ብዙ ወርቅ አመጣልኝ” አለና ነገረው።

እሄን አዲስ ወሬ በሰማ ጊዜ ያ የገዛው ጌታው ደስ አለውና የዚያን ደጃዝማች ነገር ትልቅ ሰው መሆኑን አወቀና መቸም ስራው ታልጠቀመኝ ብሎ ገንዘብ ያተርፍበት ዘንድ ፈለገ። ከዚህ በኋላ ጠራና እንዲህ አለው።

“አንተ ባሪያ … እኔ ተማረከህ ሰው ብዙ ወርቅ አፍስሸ ገዛሁህ። አሁን የፈቀደኝን ብሰራህ ይቻለኛል ነገር ግን ታሳዝነኛለህ። አሁንም ከዘመዶችህ ላክና እልፍ ወቄት ወርቅ አስመጥተህ ስጠኝና አገርህን እንድትሄድ እለቅሃለሁ።”

ያ ደጃዝማች ግን እንኳን አገሩ ጠፍቶ፣ ንጉሡ ሙቶ፣ ከብቱ ተዘርፎ፣ በሬው ላሙ ተነድቶ፣ እሄም ባይሆን ታገሩ በጌትነቱ ሳለ ለጀግና መስጠት፣ ለደሀ መርጠብ፣ ለተራበ ማብላት፣ ለታረዘ ማልበስ እንጂ ገንዘቡን ወደኋላ ማረግ ለነገ ማለት አያውቅም ነበረና “

“የምከፍለውም የለኝ ደሀ ነኝ እንደ ወደድህ አድርገኝ” ብሎ መለሰለት።

የዚሁ ደጃዝማች ሎሌዎች ሁሉ አብረውት ሲዋጉ ከዚያው ተፊቱ አልቀዋል። ንጉሡም ሙቷል። አንድ ደጋፊ አንድ ተስፋ ታገሩ አልነበረውም። ብቻ ተቤቱ ምሽቱና መንታ የተወለዱ ሁለት ልጆች አንድ ወንድ አንድ ሴት ልጆች ነበሩት።

እነዚሁ ልዦች የዚያን ጊዜ አሥራ ስድስት ዓመት ሁኖአቸው ነበር። ወንዱ ዋህድ፣ ሴቲቱ ጦቢያ ይባሉ ነበር። ሁለቱም ልጆቹ እጅግ ያማሩ እጅግ የተዋቡ ነበሩ። መንታ ስለሆኑ ሁለቱም መልካቸው አንድ አካል አንድ አምሳል ሁኖ ላይን ያሳስቱ ነበረ። ታለባበሳቸው በቀር ወንዱም ገና ጢም አላቀነቀነም ነበርና ሌላ ምንም የሚለያዩበት ነገር አልነበረም።

ለነዚሁ ልጆቹና ለምሽቱ ፊት እሱን ሞተ ብለው አርድተዋቸው ነበር። ኋላ ግን ታንዱ ወዳንዱ ሲል እሄው አባታቸው ተማርኮ ተሽጦ ኑሮ ያው የገዛው ጌታው ‘እልፍ ወቄት ወርቅ አምጣና ልልቀቅህ አለው’ ሲባል ወሬው ደረሰላቸው። ምንም ባለመሞቱ ደስ ቢላቸው ወዲህም እንደባሪያ በመሸጡ ወዲህም ሰጥተው የሚያስለቅቁበት ገንዘብ በማጣታቸው እንደገና ይላቀሱ ጀመር።

ንጉሡ ሙቶ አገር ጠፍቶ እነሱ ለራሳቸው ደህይተው ወዴት ገንዘብ ይገኝ? ምን ሰጥተው ያድኑት? እንዲያው መላቀስ እንዲያው መጨነቅ ብቻ ሆነባቸው። ልጅየው ዋህድ “ልሂድና ባባቴ ፈንታ እኔው ባሪያ ልሁንና አባቴ አገሩን እንዲመለስ ላድርግ” ቢል እናቲቱ “ያው እስላም ሁለቱንም ይዞ ያስቀርብኛል” ብላ ፈርታ አለቀው አለች።

በመጨረሻው ግን እናቲቱና እነዚያ መንቶች ዋህድና ጦቢያ እንዲህ ብለው ተማከሩ። እናቲቱ ቶሎ ቶሎ የሙያ እየፈተለች ገንዘብ ልታጠራቅም። ወንዱ ልጇ ዋህድ የጌታ አድሮ ደመወዙን እያመጣ ሊያጠራቅም። ሴቲቱ ጦቢያ ግን እንጨት ለቅማ ውሀ ቀድታ የሚበሉትን እያሰናዳች ልታቀርብ። ቤተሰቡን ሎሌውን ገረዱን የሚሰጡት ገንዘብ የለምና ሊያሰናብቱ አሰቡና ተማከሩ።

እውነት ነው የሞያ ተፈትሎ የሎሌነት ደመወዝ ተቀብሎ እልፍ ወቄት ወርቅ ለማጠራቀም ተረት ነው። ነገር ግን ምን ያድርጉ የቀራቸው ነገር እሄ ብቻ ነው ሌላ የሚቻላቸው ነገር አልነበረም።

ከዚህ ወዲያ እናቲቱ ቶሎ ቶሎ ትፈትል ጀመር። ዋህድም እየዞረ የሚያድርለት ጌታ ይፈልግ ጀመረ። ጦቢያም እያንጐራጐረች እንጨቷን ትለቅም፣ ውሀዋን ትቀዳ፣ ቅጠላ ቅጠሉን ትለቅም ጀመር። ምግባቸውም ቅጠል ብቻ ሆነ። የምግባቸው ነገር በጦቢያ በኵል ተከተተ። እሷ አሉማውን፣ እህል ገቡን፣ ማገጡን፣ አሞጩም ሳይቀር እንዲህ እንዲህ ያለውን ስራስሩን ቅጠላቅጠሉን እያጠራቀመች እያበሳሰለች አቅርባ አንድነት ተጠራቅመው አባታቸውን እናቲቱም ባሏን እያሰቡ እየተከዙ መበላላት ሆነ። በማግስቱ ሁሉም እየስራቸው ይሰማራሉ። ወንዱ ልጅ ዋህድ ገና የሚያድርለት ጌታ አላገኘም ነበርና ሲፈልግ ሲፈልግ ወሬ ሲጠይቅ ሲያስጠይቅ ታንድ ትልቅ ከተማ ደረሰ።

ተዚያ ከተማ ዳር ተመስክ ላይ መደበሩን መትቶ፣ ወገኑን አሰማርቶ የሰፈረ ነጋዴ አየና ከዚያው ለመሄድ ፊቱን ወደ መደበሩ አቀና። ተመደበሩ ሳይደርስ በፊት ወገን ጠባቂውን አየና አስቀድሞ ወሬውን ከሱ ለማግኘት ቀረበ። ቀጥሎም “ያ መደበር የምን ነጋዴ ነው ወዴትስ ሂያጅ ነው” አለና ጠየቀ። እረኛውም “ሰፈሩም ያንድ የትልቅ ነጋዴ ነው። እሄው ነጋዴ የሚነግድበትም በወርቅ በዝባድ በዝሆን ጥርስ በቡን ነው። አሁን የሚሄድበትም ወደ ምስር ነው” አለና አወራለት።

ዋህድም እግዚአብሔር ይስጥህ አለውና ሲያቆም “ጫኝ ሎሌ ቢያገኝ ባስገባ ይሆን?” አለና ጠየቀው። ከብት ጠባቂውም ተሎ ብሎ “እንዴታ ታልህስ ተጐረደማኖቹ መሀል ንዳድ በሽታ ገብቶ ታመውበት የሚነሣበቱ ጊዜ ዘግይቶበት ተጨንቋል። እንዳይነሣ ጫኝ አጣ አሁን ቢቸግረው እጥፍ ደመወዝ እሰጣለሁና ጐረደማን ፈልጉልኝ እያለ ይፈልጋል ያስፈልጋል። ከብቱም እንደምታየው እልቅ የለውም” አለና ነገረው።

በዚህ ጊዜ ዋህድ ደስ አለውና ቸኵሎ ደህና ዋል እንኳ አላለውም ወደ መደበሩ ይሮጥ ጀመረ። ከሰፈሩ እንደደረሰ የዋናውን ድንኳን በትልቅነቱ አወቀና ቀርቦ አጋፋሪውን “ጫኝ እሆን ብየ መጥቻለሁና ለጌታው ንገርልኝ” አለው። አጋፋሪው ግን ያለባበሱንም ያለሳለሱንም ያነጋገሩንም ያኳኋኑንም ነገር አየና ነገሩ የማይመስለው ሆነ።

ነገር ግን ለሁሉም ነገር አጋፋሪ ነውና አልነግርም ይል ዘንድ አይቻለውምና የጌታውንም ጫኝ ማጣት ያውቅ ስለነበረ በግዱ ገብቶ ለጌታው “ጫኝ እሆናለሁ የሚል አንድ ደህና ጐበዝ መጥቷል” ብሎ ነገረው። ባለቤቱም ‘ደህና ጐበዘ መጥቷል’ን በሰማ ጊዜ አጋፋሪውን ተቈጣና “ደህና ጐበዝ መጥቷል የምትለኝ የታመመ ጐበዝ ስፈልግ ሰምተኸኝ ኑሮአል። የታመመማ ተቤቴስ ተርፎኝ የለም እንደምታየው” አለና አፈፍ ብሎ ቸኵሎ ታጋፋሪው ቀድሞ ግፋን ወደዚያ ጐበዝ ሄደ። አጋፋሪው ግን “ኧረ ደህና ጐበዝ ማለቴ ለጭነት የተገባ ሰውም አይመስል ማለቴ ነበር” ብሎ ሊናገር ሲል ባለቤቱ ጊዜ ሳይሰጠው ተነሣ።

እሱም አጋፋሪው ‘ኧረን … ባፉ እንዳንጠለጠለ በኋላ በኋላው ተከተለ። ባለቤቱ ግን ተድንኳኑ ደጃፍ እንደደረሰ ወዲያና ወዲህ ቢያይ ተዚያ ማለፊያ ገና ወጣት ልጅ ተዋህድ በቀር ሌላ ለጐረደማንነት የተገባ ሰው ከደጁ አጣ። ቀጥሎ ወደ በረኛው ዙሮ “ለጫኝነት የመጣው ሰው ወዴት ነው” አለና ጠየቀ።

ገና በረኛው ሳይመልስ ዋህድ እጅ ነሳና “ጌታው እኔው ነኝ። ይወዱ እንደሆን እርስዎን ለመከተል ለርስዎ ጐረደማን ልሆን መጥቻለሁና ይፍቀዱልኝ” አለ። ባለቤቱ ግን ዋህድን ተግር እስከ ጥፍሩ ከራሱ እስተጠጉሩ አመሳቅሎ አየውና ደንቆት “እንዴታ ጐረደማን እንዲህ ኑሮ! ጫኝ እንዲህ ነው እንጂ! ምንኛውን!” እያለ ለብቻው ይጕተመተም ገባ።

ዋህድም ነገሩን እንደናቀበት እንዳልተቀበለው ባየ ጊዜ እንዲህ አለው፣ “ጌታው ተወፍራም አባያ የቀና ኮሳሳ በሬ አብልጦ ያርሳልና ለጋነቴን አይተው አይናቁኝ ጭነት አይቸግረኝም።”

ያው ሀብታም ነጋዴ ግን እንዲህ ያለ ቃል ከዚህ ሕፃን ከዋህድ ሲወጣ በሰማ ጊዜ ወዲያው ወቃቢው ወደደውና እንዲህ አለው። “ምነው እንዳንት ያለ የደህና ሰው ልጅ ተማዕርጉ ወጥቶ ጫኝነት ይመኛል? ንግግርህ ያማረ አለባበስህ የተዋበ ስራህ የጌታ ወቃቢህም ሁለንተናህም የጌታ እንዴት የገንዘብ ስስት አድሮብህ እንዳንት ያለ ሰው ጫኝ ለመሆን ይመኛል?” አለና ተናገረው።

ዋህድ ግን ዝም ብሎ ሰምቶ ሲጨርስ “ጌታየ ኧረ የገንዘብ ስስት አድሮብኝ አይደለ። የኔን መከራ የኔን አይቶ ማጣት ቢሰሙ ባልፈረዱብኝም ነበር” አለ። ባለቤቱም አንስቶ “እስቲ ዋይህን ንገረኝ ሰው የላዩን አይቶ ይፈርዳል እንጂ የውስጡን ያውቅ ዘንድ አይቻለውም። ስለዚህ እኔም ሳላውቅ አጥፍቸ ይሆናልና ንገረኝ” አለው።

ቀጥሎም ያው ሀብታም “እስኪ ለሁሉም ነገር በቅሎየን ጫንልኝና ወደ ውጭ እንሂድ” አለው። ዋህድም ባንድ አፍታ በቅሎውን ጫነለትና ሁለቱም አብረው ወጡ። ከድንኳኑ ጥቂት እንደራቁ ባለቤቱ “በል እስቲ የመከፋትህን ነገር አጫውተኝ” አለው። ዋህድም ግራ ክንዱን ባለቤቱ ከተቀመጠባት በቅሎ ከደሀራዩ ላይ ጣል አርጎ በግሩ እየተከተለ ጌትዮው እያሰገረ እንዲህ ብሎ የሀዘኑን ታሪክ ጀመረለት።

“ጌታው የደህና ሰው ዘር ያሉኝም እውነትዎ ነው። የደጃዝማች ልጅ ነኝ በመዓርግ በጌትነት እኖር ነበር። ነገር ግን እርስዎም እንደሚያውቁት የእስላም ጦር መጣ በተባለ ጊዜ ንጉሣችን ባዋጅ አስከትቶ ባራት ደጃዝማቾች እግር አሳዝዞ ተዋጋ ብሎ ጦሩን ሰደደ። ከነዚያ አራት ደጃዝማቾች አንዱ የኔ አባት ነበረ።

እስላሞቹና ክርስቲያኖቹ በተዋጉም ጊዜ እግዚአብሔር ሳይል ጊዜ ድሉ የእስላም ሆነ። ሰውም የሞተው ሞተ የተማረከውም ተማርኮ ተሸጠ። ካራቱ ደጃዝማቾችም ሶስቱ ከጦርነቱ ሞቱ። የኔ አባት ግን ተማርኮ እንደባሪያ ተሸጠ። አሁን ግን ያ የገዛው እስላም ገና ጌታ ሳይሆን አይቀርም ብሎ ቀለሙን አይቶ ጠርጥሮ ‘እልፍ ወቄት ወርቅ አምጣና ልልቀቅህ አለው’ ሲሉ ወሬ ደረሰልነ።

እሄን ወሬ በሰማነ ጊዜ በናቴም በቴም በኔም እጅግ የመረረ ሀዘን ገባብነ። አምጣ ያለውን ገንዘብ ሰደን እንዳናስለቅቀው እሄን ያህል ወርቅ ከጃችን የለ። ደግሞም አባቴ ጥንቱም ቢሆን መስጠት መለገስ ያውቅ ነበር እንጂ ገንዘብ መቈጠብ አያውቅም ነበርና ገንዘብ ወዴት እናገኝ አሁን? ንጉሡ ሰጥቶ እንዳያስፈታው እንደሚያውቁት በሀዘን ሞተ። አገር ጠፍቶ ሰዉ አልቆ ከብቱ ተነድቶ ክምሩ ተቃጥሎ ገንዘብ ወዴት ይገኝ?

አሁን ቅጡ ቢጠፋነ እቴ ቅጠል እያበሰለች እንበላለን። እናቴ የሙያ እየፈተለች እኔ ሎሌነት ገብቼ ገንዘብ አጠራቅመን ተቀን ብዛት አባቴን ለማስለቀቅ ተስፋ አድርገን እሄው እንደሚያዩኝ ለጌታ አዳር መጣሁ። እኔንስ ደስ የሚለኝ የነበር እኔው ሄጄ ባባቴ ስፍራ ተተክቼ እኔው ባሪያ ሁኜ አባቴ ወዳገሩ እንዲመለስ ማድረግ ነበር። አባቴ እጅግ አሳምሮ ከብክቦ ተጨንቆ አሳደገኝ። እኔም በዚህ ጊዜ ስለሱ እኔው ባርያ ሁኜ ወረታውን ብከፍል ደስታየ ነበር። ነገር ግን እናቴ ‘ባባትህ መከራ ሳለቅስ አንተ ደግሞ ሂደህ ታባትህ ጋራ ባርያ ሁነህ ትቀርና በመከራ ላይ መከራ ይጨመርብኝ’ ብላ እንዳልሄድ ከለከለችኝ በቄስ አስገዘተችኝ። አሁንም እሄውልዎ ጌታየ ከዚህ ያደረሰኝ የሰው ሎሌነት ያስመኘኝ እሄ ነው ነገሩ አይፍረዱብኝ” አለና ነገሩን ጨረሰ።

ያው ሀብታም ነጋዴም እያዘነ የዋህድን ታሪክ አስተውሎ አዳመጠና ሲጨርስ “እኔ ጉዳይ አለብኝና ወደ ድንኳኔ እመለሳለሁ አንተም ወደ ቤትህ ተመለስ። እግዚአብሔር ይሁንህ” አለና ነጋዴ መቸም ለምናልባች ከጁ ገንዘብ አይለይምና ይዞት የነበረውን ገንዘብ እስተቀረጢቱ ተጁ ላይ ጣለለት። ሳይለያዩ በፊት ግን ያው ሀብታም ለዋህድ “ያባትህ ስም ማነው? የገዛውስ አረመኒ ማን ይባላል? ያለበት አገርስ ወዴት ነው?” አለና ጠየቀ።

ዋህድም ያን ቀረጢት ወርቅ እንደሞላበት በጁ እንደያዘ ደስ ብሎት ከንፈሩም እየተንቀጠቀጠ አንደበቱም እየተርበደበደ ያባቱንም ስም የገዛውን አረመኒ ስሙን እስተቦታው እስከምልክቱ ነገረውና ሁለቱም ተለያዩና እየስፍራቸው ሄዱ። ዋህድ ግን ያላሰበውን ሲሳይ በድንገት ሲያገኝ ጊዜ እጅግ ደስ አለውና እንኳን የዚያን ለጋስ ስሙንና አገሩን ለመጠየቅ እግዚአብሔር ይስጥህ ሊለው አላደረሰውም እንዲያው ወደ ቤቱ ከነፈ።

ነገር ግን ከዚያ ለጋስ ሰው ፊት የተቀበለውን ለማየትና ለመቍጠር አፍሮ አላየውም ነበርና ወዲያው እንደተለያዩ አንድ የሚሸሸግበት ቍጥቋጦ መሳይ ባየ ጊዜ ዋህድ የቀረጢቱን ወርቆ ቶሎ ከሸማው ላይ ዘረገፈና ሲቈጥር ጊዜ ፵ ወቄት ወርቅ አገኘበት። በዚህ ጊዜ ይልቁንም በደስታው ላይ ደስታ ተጨመረለትና እየፈነደቀ ሲሮጥ ሲሮጥ ከቤቱ ገባና ለናቱና ለቱ ወስዶ ያን ወርቅ ሆጭ አደረገላቸው ነገሩንም ሁሉ ነገራቸው።

እናቱም እቱም ነገሩን ሰምተው የነጋዴውንም ደግነት የተሸጠውን ሰዋቸው የመለቀቁን ነገር ባሰቡ ጊዜ በደስታም ይሁን በሀዘን በንባ ይታነቁ ጀመር። ያው ሀብታም ነጋዴ ጥንቱንም ዋህድን በቅሎየን ጫንልኝ ተከተለኝ ማለቱ ድንገት የሚረጥቡት ሰው እንደሆነ ለሱም ለመርጠብ ምክንያት እንዲሆነው ለተቀባዩም ሳያገለግል አለስበብ መቀበሉ ውርደት እንዳይሆንበት ብሎ ነበር።

ሁሉም ሆኖ ግን ይኸው የተገኘው ገንዘብ አባታቸውን ለመለቀቂያ አምጣ ታለው ወርቅ አይደርስምና በጐደለው ለመሙላት እናቲቱም ጦቢያም ዋህድም እንደፊተኛቸው ሁሉም እያሳባቸው ገቡ። ሁሉም እየተግባራቸው ይውሉና ማታ ማታ ያን ቅጠላ ቅጠላቸውን ለመብላት ይጠራቀማሉ።

(በክፍልሁለትይቀጥላል)

.

አፈወርቅ ገብረየሱስ

1900 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ልብወለድ ታሪክ”። ፲፱፻ ዓ.ም። ገጽ ፩-፲።

“እስቲ ሙዚቃ!” (ልብወለድ)

“እስቲ ሙዚቃ!”

በሌሊሳ ግርማ

.

[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]

.

.

የፍቅርን ዋና ትርጉም ለመረዳት ይመስለኛል፣ አንዳንድ ጊዜ የምጽፈው፡፡ ፍቅርን ለመረዳት ብጽፍም ተረድቼው አላውቅም፡፡ የማውቀው ነገር ግን አለ፡፡ ፍቅርን ባላውቅም የማውቀው ነገር አለ፡፡ ይኼውም የፍቅር ተቃራኒ ፍርሐት መሆኑን ነው፡፡ የጨዋታው ህግ ይሄ ብቻ ነው፡፡

ባለፈው ወር አንድ ፒያኖ የሚጫወት ሰውዬ ትርኢት ባሳየበት ምሽት ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ ሰውዬው መጫወት ሲጀምር ገና ነው ፍርሃት እንደሌለበት የገባኝ፡፡ ሰውዬው ሳይሆን ፒያኖውን የሚጫወተው ፒያኖው ነው ለሰውየው እየተጫወተለት ያለው፡፡

ሰውዬው ፒያኖውን ከሚወደው በላይ ፒያኖው ሰውየውን ያፈቅረዋል፡፡ ፒያኖው ሰውየውን ያፈቀረበት ምክንያትም ግልፅ ነው፡፡ ሰውየው አንዳችም ፍርሃት የለበትም፡፡ እርግጠኛ ነው፡፡ ፒያኖውን መጫወት ስለመቻሉ አንዳችም ጥርጣሬ አድሮበት እንደማያውቅ ያስታውቃል፡፡ ፒያኖ ደግሞ በተፈጥሮው የሴት ባህርይ ያለው መሳሪያ ነውና፤ እርግጠኛ የሆነ ሰው ያለ ፍርሐት ሊነካካት ከቀረበ ነፃ ሆና መጫወቷ አይቀርም፡፡ ፍርሃት ካሸተተች ግን ሴቷም ሆነች ፒያኖዋ ፍቅሯን ትከለክላለች፡፡ እንዲነካኳትም አትፈቅድም፡፡ ቢነካኳትም የምታወጣው ድምጽ የእንቢታ ነው፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ከፍቅር እንጂ ከእንቢታ ውስጥ አይወጣም፡፡

እናም ባለፈው ወር ሰውየው ገና መቀመጫውን ስቦ ፒያኖዋ ስር እንደተቀመጠ እጁን ሳያሳርፍባት በፊት መሳሪያዋ ጥዑመ ዜማዋን ለቀቀችው፡፡ የፒያኖውን ቁልፎች እየጐረጐረ አልነበረም ሙዚቃውን የሚያፈልቀው፡፡ በመጐርጐርማ መኪናም የሞተር ድምጽ ከተኛበት ተቀስቅሶ ያወጣል፡፡ ሰውየው የፒያኖው ቁልፎች ላይ የተቀመጠለትን ሙዚቃ… በሁለት እጆቹ ማፈስ ነው የጀመረው፡፡ በሁለት መዳፎቹ ከጥግ እስከ ጥግ እየተመላለሰ ፒያኖዋ የምትሰጠውን ፍቅር ሙዚቃ አስመስሎ አፈሰ፡፡ ጉያዋን፣ ደረቷን፣ ዳሌዋን እያሸ ዜማዋን አስጨረሳት፡፡

በመጨረሻ በአንድ እጁ ጭንዋ ውስጥ ገብቶ ሲቀር … እና ፒያኖዋም ተንሰቅስቃ ዜማዋን ስትጨርስ … አዳራሹ በጭብጨባ መሃል ለመሀል ተገመሰ፡፡ ፒያኖዋን መጫወት ያላስፈራው ሰውዬ በጭብጨባው ተደናበረ፡፡

ደነገጠ፡፡ ከመደንገጡ የተነሳ ከወገቡ ሁለት… ሶስት ጊዜ ታጠፈ፡፡ ጭብጨባው ነጐድጓድ ሲሆንበት… በሩጫ ከመጋረጃው ጀርባ ገብቶ ተደበቀ፡፡ ፒያኖውን ቢደፍርም የጭብጨባ ነጐድጓድ እና ሕዝብን ግን ይፈራል ለካ!

ለካ፤ ሁሉም የሚፈራው ነገር አለው፡፡ ሕዝብ ፒያኖውን መንካት ቢፈራም ሰውየውን ግን ለመንካት ይደፍራል፡፡ ሰውየው ደግሞ በተገላቢጦሽ ልበ ሙሉነቱ ወደ ፒያኖው እንጂ ለህዝባዊ ፍቅር ቦቅቧቃ ነው፡፡

የፍቅርን ትርጉም አላውቅም፡፡ የማውቀው ፍቅር ከፍርሃት ጋር ዝንተ ዓለም ጠላት መሆኑን ብቻ ነው፡፡

***

ኤስን ትዝ ይለዋል፤ ምናልባት የአስር አመት ልጅ ቢሆን ነው፡፡ አባቱ ከእነ ቮልስዋገኑ ድልድይ ውስጥ የገባ ጊዜ ሆስፒታል ከእናቱ ጋር ይመላለስ ነበር፡፡ ሆስፒታሉ ሳይሆን የሆስፒታሉ ሽታ ከአደገም በኋላ ስሜቱ ሲጐዳ ወይንም … ተስፋው በየትኛው ኪሱ ውስጥ አስቀምጦት እንደነበር ፈልጐ ባጣው ጊዜ ሁሉ የዚያ የሆስፒታል ሽታ ይመጣበታል፡፡

ከሆስፒታሉ ሽታ ቀጥሎ ደግሞ በላስቲክ … አባቱ አናት ላይ ይንጠለጠል የነበረው እርጐ መሳዩ ደም ዓይኑ ላይ ይደቀንበታል፡፡

***

እናቱ እንደዚያ መሳቅ እንደምትችል አያውቅም ነበር፡፡ የሆስፒታሉ ሽታ፣ እርጐ መሳዩ ደም እና የእናቱ ሳቅ ከመንፈስ ዝቅታ ጋር እንደ ሰንሰለት ተቀጣጥለው የሚመጡበት ነገሮች ናቸው፡፡ የዓይን ትዝታ በደም፣ የጆሮ ትዝታ በሳቅ፣ የአፍንጫ ትዝታ በሆስፒታሉ ሽታ፡፡

ይመስለዋል እንጂ … መሳሳቱን አያውቅም፡፡ የትዝታ ጥፍሮች ከአስርት አመታት በላይ ወደኋላ ሄደው ሲቧጥጡ ጊዜ እና ቦታን ያዛንፋሉ፡፡ ይመስለዋል እንጂ፤ የእናቱ ሳቅ የተሰማው በሆስፒታሉ ሽታ እና በተንጠለጠለው እርጐአማ ደም መሀል ሳይሆን … በክፍለ ሀገር አውቶብስ እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ያኔ፤ እድሜውም አስር ሳይሆን ስምንት ቢሆን ነው፡፡

በክፍለ ሀገር አውቶብስ የእናቱን ዘመዶች ለመጠየቅ በሄዱበት የክረምት ወቅት፣ አባቱ ገና ድልድይ ጥሶ ለመግባት ሁለት አመት ገደማ ይቀረው ነበር፡፡ በስምንት አመቱ ላይ የገጠመውን ድንጋጤ እና በአስር ዓመቱ የተጋፈጠውን መከራ ያስተሳሰረው በራሱ ስሜት አማካኝነት እንጂ በጊዜ ቅደም ተከተሉ መሰረት አይደለም፡፡ (እንዳይደለ ግን እኛ እንጂ እርሱ አያውቅም፡፡)

በክፍለ ሀገር አውቶቡስ ወደ አርባ ምንጭ እየሄዱ ነው፡፡ እናቱ እናት እንጂ ልጃገረድ መስላው አታውቅም ነበር፡፡

እየተጓዙ ብዙ ጥያቄ ይጠይቃታል፡፡ የተቻላትን ያህል ትመልስለታለች፡፡ ጥያቄው አሁን ለሱ ትዝ ባይለውም እኛ ግን እናስታውሰዋለን፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ዘፈን ተከፍቷል፡፡ ሾፌሩ ከመንገዱ ጋር እየተወዛወዘ ትሪ የሚያክለውን መሪ ወደግራ፣ ወደቀኝ ይለዋል፡፡

“ኢንፌዱ ምን ማለት ነው?” አላት እናቱን፡፡

“አልፈልግም ማለት ነው” ባለመፈለግ ውስጥ ብዙ አመታት የተንገላታ መልክ አላት፡፡

“ኢንተሁስ?”

“አይሆንም”

“ኢ-ሰብአዊ ማለትስ?”

“ለሰዎች የማይሆን ማለት ነው”

“ኢ … ካለበት አፍራሽ አረፍተ ነገር ነው ብሎኛል አባባ”

“አባባ ምን ያውቃል ስለ አማርኛ”

“ኢ – ትዮጵያ ማለትስ?”

“አንተ ደግሞ … አጉል አትፈላሰፍ!”

ይህንን በመሳሰሉ ጥያቄ እና መልስ የመንገዱን አሰልቺነት ሲገዘግዙ ድንገት አውታንቲው ዱካ መሳይ በርጩማ ስቦ እናቱ መቀመጫ ጐን ተቀመጠ፡፡ አውታንቲው እንደተቀመጠ፣ በድፍረት አንድ እጁን እናቱ ጭን ላይ አስቀምጦ በማይሰማ ድምጽ ወደ ጆሮዋ ተጠግቶ አንሾካሾከ፡፡ ይሄኔ ነው … እናቱ ከዚህ በፊት አሰምታው የማታውቀውን ሳቅ የለቀቀችው፡፡

ስቃ ሳትጨርስ አሁንም ወደ ጆሮዋ ተጠግቶ አንሾካሾከ፡፡ ባላለቀው ሳቋ ላይ አዲስ ሳቅ ቀጠለችበት፡፡ እየሳቀች፤ በዱካ የተቀመጠው ሰውዬ እጇን በመዳፉ ላይ ደርቦ በሌላ መዳፉ እየመታ (“ሙች”) ይምልላታል፡፡ በተማለ እና በተሳቀ ቁጥር እናቱ እድሜ የቀነሰች ልጃገረድ እየመሰለች መጣች፡፡ ሻሽዋ ውስጥ አብሮ የታሰረው ጆሮዋ ከእነ ጆሮ ጌጡ ብቅ አለ፡፡

ኤስ የስምንት አመት ልጅ ቢሆንም ሲደነግጥ ትዝ ይለዋል፡፡ ምናልባት ልጅነት የዋህነት ስለሆነ ሊሆን ይችላል የደነገጠው፡፡ በአውቶቡሱ ውስጥ የነበሩት … ተሳፋሪዎቹ፣ ሌሎቹ አዋቂዎች በእናቱ ሳቅ ሳቢያ ከንፈራቸው በፈገግታ ፈልቀቅ ብሎ ነበር፡፡ ምናልባት … አዋቂ ሆኖ ቢሆን እናቱን አባቱ ብቻ ማሳቅ ወይንም መንካት መብት አለው ብሎ ባላሰበ ነበር፡፡ ግን ያኔ ልቡ ደነገጠበት፡፡ በዱካ የተቀመጠውን ሰውዬ ጠላው፡፡ ቢጠላውም ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡

አዋቂ ቢሆን ኖሮ “ማነህ … የት ታቃታለህ?” ማለት በቻለ ነበር፡፡ ሰው ለማስወረድ ብቻ ከተቀመጠበት አልፎ አልፎ ከመነሳት በስተቀር የጉዞውን ጊዜ እናቱ ስር በዱካ ተቀምጦ አውታንቲው በማይሰማ ድምጽ ሲያንሾካሹክላት እንደነበር ኤስን አሁን ትዝ አይለው ይሆናል፡፡ ግን እያንዳንዱ ክስተት ቢዘነጋውም ሳቋ ግን እድሜ ልኩን ይከተለዋል፡፡

“ኢ-እናታዊ” ብሎ ጉሮሮው ላይ የተጠራቀመውን ሳግ እየዋጠ፣ በአውቶብሱ መስኮት ጋራና ሸንተረሩን እንባ በሞላው አይኑ እያየ ማጉተምተሙ ለእኛ እንጂ ለእርሱ ተዘንግቶታል፡፡

እንደ ፒያኖ ተጫዋቹ ለእናቱ የሳቅ ዜማ ማመንጨት ዋናው ምክንያት የአውታንቲው ድፍረት ነበር፡፡ በድፍረቱ ምክኒያት እናቱ ተሸነፈችለት፡፡ ጥርጣሬ ቢያሳይ ኖሮ ሊጫወታት ወይንም ሊያጫውታት ባልቻለ ነበር፡፡ በዚህ ሰውዬ ፍርሃት አልባ ድፍረት ምክኒያት ከሁለት ኣመት በኋላ አባቱ አብዝቶ መጠጣት በመጀመሩ ድልድይ ውስጥ ገባ፡፡ ድልድይ ውስጥ ከመግባቱ፤ ሆስፒታል ገባ፡፡

ሆስፒታል ከመግባቱ፣ የአውታንቲው እና የእናቱ ግንኙነት ጠነከረ፡፡ ግንኙነታቸው በመጠንከሩ፣ አባቱ ከእናቱ ጋር የነበራቸው በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ትዳር ተበጠበጠ፡፡ በመበጥበጡ ተለያዩ፡፡ እሱም የድሮው ሰፈሩን፣ የድሮው ት/ቤቱን፣ የድሮ ጓደኞቹን ከአባቱ ጋር ጥሎ ወደ አዲስ ህይወት ከእናቱ ጋር ተንቀሳቀሰ፡፡

***

ፒያኖ ተጫዋቹ እና አውታንቲው አንድ ናቸው፡፡ ፒያኖ ተጫዋቹ የሚጫወተው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡

አውታንቲውም ለአጭር ጊዜ የእናቱን ፍቅር አፈሰ … የእናቲቱን እንጂ የልጁን ፍቅር ግን አላገኘም፡፡

በአውቶብሱ ውስጥ ሳሉም አውታንቲው ፒያኖውን ሲጫወት ተሳፋሪው በሙሉ አጨብጭቦለት ነበር፤ ደፋር፣ የዋህ እና እውነተኛ ይመስል ነበርና፡፡ ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉም ወደውታል፡፡ ከአንድ ሰው በስተቀር በተጫወተው ሙዚቃ ሁሉም ተደንቋል፡፡ ያ አንድ ሰው ብቻ አውታንቲው በተጫወተው ሙዚቃ ህይወቱ በዘላቂነት ተበጥብጧል፡፡ ያ አንድ ሰው በዚያ ወሳኝ ወቅት አንድ ፍሬ ልጅ ነበረ፡፡ የስምንት ዓመት ልጅ፡፡

ስለዚህም ነው፤ የእናቱን ሳቅ፣ ከሆስፒታሉ ሽታ፣ ከአባቱ አናት በላይ ከተሰቀለው እርጎ መሳይ ደም ጋር የሚያስተሳስረው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ተበጣጥሶ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በእይታ እና በሳቅ ድምፅ ቅላፄ፡፡ ፒያኖ ተጫዋቹ የመጨረሻውን ዜማ ፒያኖው ጭን ውስጥ ሰተት ብሎ በመግባት እንዳፈለቀው፣ በአውቶብሱ መስኮት እየተመለከተ የነበረው የስምንት ዓመት ልጅም የመጨረሻውን እና የመጀመሪያውን የእንባ ዘለላ ብዥ ካለው አይኑ ላይ የጠረገው … እናቱ ወረቀት ጽፋ በርጩማ ላይ ለተቀመጠው ጎልማሳ ስታቀብለው አይቶ ነው፡፡ ጭን ውስጥ መግባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ዝርዝሩ ባይገባውም … ጭኗ ውስጥ እንደሚገባ ግን እርግጠኛ ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖ እንደነበር እሱ ራሱ ትዝ ላይለው ይችላል።

ብዙ ዓመታት አልፈዋል ይኼ ታሪክ ከተከሰተ፡፡ እኔ እና እናንተ ግን ከእሱ በተሻለ የተከሰተውን ሁሉ እናስታውሳለን።

የፒያኖ ተጫዋቹ፣ የአድማጩ እና የጨዋታው ህግ እንዴት እንደሚሰሩ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

.

ሌሊሳ ግርማ

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] – “እስቲ ሙዚቃ”። 2009 ዓ.ም። ገጽ 239-243።

“ገብረ ክርስቶስ ገጣሚው”

“ገብረ ክርስቶስ ገጣሚው”

በሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

.

ገበረ ክርስቶስን የማውቀው ከሐረር ትምህርት ቤቱ ጀምሬ ነው። እዚያ ባዶ እግራችንን፣ በቴኒስ ኩዋስ ኩዋስ ተጫውተናል። ገብረክርስቶስ፣ የእግር ጣቶቹ እኩል ስለሆኑ፣ ኳሱን የሚመታ በእግር ኩርኩም ነበር – ኹሌ የከረረች ምት።

ከእለታት ባንዱ ቀን ግን፣ ዕረፍት ወጥተን፣ ግማሹ በሚሯሯጥበት፣ ግማሹም ኳስ በሚጫወትበት ሽብር ኹኔታ ውስጥ፣ ገብረክርስቶስ ጥጋት ተቀምጦ፣ ቁምጣ ሱሪውን አጋልጦ ባዶ ጭኑ ላይ ሥዕል ሲሠራ እንዳየሁት አስታውሳለሁ። እና አሁን መለስ ብዬ ሳስብ ሥዕል ምንኛ ከልጅነቱ ከጭንቅላቱ ገብቶ ኖሯል እላለሁ። ለዚህም የአባቱ የአለቃ ደስታ ነገዎ የድጉሥ፣ የቁም ጽሕፈትና የብራና መጻሕፍት ላይ ሥዕል ምን ያኽል ተፅዕኖ አድርጎበት ነበር ይሆን? በምንስ መንገድ? እላለሁ።

ያ ያ እንዳለ ኾኖ ግን፣ ገብረ ክርስቶስን እዚህ እማንቀራብጥ በሠዓሊነቱ ሳይሆን በገጣሚነቱ ነው።

የገብረ ክርስቶስን ግጥሞች አንዴ ወጥቻቸው የግጥም መድበል መጽሐፉን (“መንገድ ስጡኝ ሰፊ” 1998 ዓ.ም) እንዳጠፍኩ፣ ገብረ ክርስቶስ ባሳብ አካቶው ምንኛ አይጠገቤ ነው። በእይታ ስንዘራውም ምንኛ አራዝሜ ነው፤ በሌላ ምንኛ … ምንኛ … ምንኛ አልኩ። ይህን ይህን ብዬ ነው የሚከተሉትን ግጥሞች የመረጥኩ እነሁዋችሁ፤

አይጠገብ ወንዝ

አባ በሽበሽ

አይሞላ ልቃቂት

ደናሽ

ሞልቶ እስኪፈስ

ገስጋሽ

የመጨረሻዋን ስንኝ አንጋሽ።

(“ትዝታ” ፣ ገጽ 52)

.

ዘላይ ነው ዘላይ

መጣቂ

ከምብርቷ ዘላቂ

ምጥቃለምን

አይለቅ መንገዱን።

(“የጠፈር ባይተዋር” ገጽ 114)

.

መሔድ፣ መሔድ መሔድ

ከጨረቃ በላይ

ከኮከቦች በላይ

ከሰማይ በላይ

መጓዝ ወደ ሌላ ባዶ ቦታ መግባት።

(“ሥዕል” ገጽ 98)

.

“አሰነኛኘት”

ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ዘጠና በመቶውን ወል ግጥም ገጣሚ ነው። ይህን የግጥም ዘርፍ በስንኞች አቀማመጥ ልዩ ልዩ መልክ ይሰጠዋል። ከኒህ የመልክ ዐይነቶች፣ ዋና ዋናዎች ያልኩዋቸውን፣ ልዩ ልዩ ስሞች እየሰጠሁ እንደሚከተለው አመጣቸዋለሁ።

.

[ሰያፍ ስንኝ]

እርሷን መርሳት አልችል

እፈልጋታለሁ

እከተላታለሁ

እጠብቃታለሁ

(ገጽ 100)

.

[ስንኝ-አጠፍ ስንኝ]

ስንኝ – አጠፍ፣ አንዱን ሙሉ ውል ስንኝ ከሁለት ግጥማዊ ወይም ስንኛዊ እኩሌታ፣ ወይም ወል ገጽታውን ከማያሳጣ ቦታ ማጠፍ ነው። የስንኝ-አጠፍ ስንኝ – ምናልባት – የመጀመሪያው ተጠቃሚ ከበደ ሚካኤል ናቸው።

ደስታና ሐዘን

እየቀላቀልኩ

ልቤን ብዙ ዘመን

ስመገበው ኖርኩ።

(‘ብርሃነ ኅሊና’ – 1961 ዓ. ም. – ገጽ 100።)

ከዚህ አንጻር፣ የገብረክርስቶስ ስንኝ-አጠፍ ስንኝ ስልት መሥመሮች ያዛንፋል፣ በቤት አመታትም ነጻነት ይሰማዋል። ለዚህ እነሆ ምሳሌ፤

እምቢኝ እሻፈረኝ

አሻፈረኝ እምቢ

መቅደስ ነው አገሬ

አድባር ነው አገሬ።

(ገጽ 134)

.

[ቁልቁሎሽ ስንኝ]

በ ‘መንገድ ስጡኝ ሰፊ’ እንደሚታየው፣ ቁልቁሎሽ ስንኝ፣ ወል ግጥምን ስንኝ በስንኝ ወስዶ፣ ቃላቱን ቃል በቃል እያሉ አንድ አንዱን ቁልቁል መጻፍ ነው። በተራው እንዲህ አንዳንዱን የተጻፈውን ወስዶ መልሶ ደምበኛውን የወል ግጥምም መጻፍ ይቻላል። እነሆ የሁለቱም ምሳሌዎች፤

(ነጠላ ነጠላውን)

በገና

ቢቃኙ

ሸክላ

ቢያዘፍኑ

ክራር

ቢጫወቱ

ለሚወዱት

ምነው

ሙዚቃ

ቢመቱ።

(ገጽ 96)

.

(ወል ቅንብሩን)

በገና ቢቃኙ ሸክላ ቢያዘፍኑ ክራር ቢጫወቱ

ለሚወዱት ምነው ሙዚቃ ቢመቱ።

.

“ቤት ምትና ተምሳሌት”

የገብረክርስቶስ ግጥሞች – በመሠረቱ – ወል ስልታቸውን ቤት የሚመቱ ናቸው፤ አልፈው አልፈው ግን ቤት ሳይመቱም ይገኛሉ። ለምሳሌ “የሞት አለም ሞት” (ገጽ 109) የዚሁ ብጤ ነው። ርዕስ የሌለው፣ የዚሁ የገጽ 163 ግጥም ደሞ ቤት ይመታል፣ ግን ብቸኛ የወል ግጥም ያልሆነ ግጥም ነው።

የገብረክርስቶስ ቤት መምቺያ ፊደሎች፣ ገና ሰፊ የጥናት ሥራ የሚጠይቁ ቢሆኑም የ ለ፣ ሰ፣ ረ፣ ተ፣ ነ ቤቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ማለት ይቻላል።

ገብረክርስቶስ የተምሳሌት ባለጸጋ ነው። ይህን የጸጋ በሽበሽ ግን እንዲህ ባለ መጣጥፍ አሟጥጬ ላጤን አልችልም። ስለዚህ – በምትኩ የግጥሙን ጉልህ ገጽታ ወስጄ፣ የዚያን ውስጥ ተምሳሌቶች ላጤን እሞክራለሁ።

ገብረክርስቶስ ግጥሞች ውስጥ ያለው ጉልሁ ገጽታ ሮማንስ ነው። ይህ ገጽታ መድበሉ ውስጥ 12% ይሆናል። ሙከራዬም በመልክእ ስልት – አካላተ እንስትን እንዴት እንደገለጻቸው ማየት ይኾናል – እሱም እነሆ፤

ጠጉር            “ዞማ”

ዐይን            “የጡዋት ጨረር”

ጉንጭ            “ጽጌረዳ”

አፍ             “ማር ወለላ”

ከንፈር           “ብርቱካን፣ የማር እንጎቻ”

ትንፋሽ           “የጋለ”

ምላስ            “የፋመ”

ጡት            “ተዋጊ”

ባት             “የሚጫን”

ሰውነት           “ሎጋ”

ድምጽ           “ሙዚቃ”

.

“የሐሳብ ይዘት”

ገብረክርስቶስ፣ እንደ ገጣሚ፣ የሐሳብ እምብርቱ ሰው ነው፤ ያገርና የወገን ፍቅር ነው፣ ሙዚቃ ነው፣ ዳንስ ነው፣ ተፈጥሮ ነው፣ ሮማንስ ነው፣ የባህል ፍቅር እና ወዘተ ነው። ዝርዝሩ ይሄ ኾኖ ሳለ ወሳኝ ሐሳቦችን የያዙት ግጥሞች የሚከተሉትን ጭብጦች ያካተቱ ስንኞችን ያቁለጨልጫሉ – እናንብባቸው፤

የልጅነት ጊዜ ትምጣ ትዝታዬ

ድሮ የሠራችኝ አሁን መኖሪያዬ።

(“ትዝታ”፣ ገጽ 53-54)

.

ዕንቆቅልሽ ነፍሴ ንገሪኝ በርጋታ

ጨንቆኛል ጠቦኛል ያለሽበት ቦታ።

(“ምንድነሽ”፣ ገጽ 61)

.

“አንድ ነገር ሲሆን ግዴታ መነሻው

መኖር ይገባዋል የሚቀሰቅሰው

ሰውንም ያስገኘ

መኖር ግድ አለበት ዓለምን የናኘ”

በማለት ብዙዎሽ ሲያቀርቡ ክርክር

እስማማለው በዚህ ያለመጠራጠር።

(“ደብዳቤ”፣ ገጽ 126-7)

.

ሞትን ያሸንፋል

ሁሉን ሲቆጣጠር እግዚአብሔር ይኾናል

ወዴት አለ እንቅፋት

የት አለና ዳገት

ለዚህ ትንሽ ተባይ

ገና ይራመዳል።

(“ይራመዳል”፣ ገጽ 132)

.

ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ

እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ

ሳስብ እሄዳለሁ ቢሰበርም እግሬ

አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ

አለብኝ ቀጠሮ

ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ።

(“አገሬ”፣ ገጽ 140)

.

እኒህ ስንኞች፣ የሰአሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎን ዐጽም – በዳንቴ አሊጊዬሪ (1235-1321) ጣልያናዊ ገጣሚ አብነት – ላገሩ ዐፈር አብቁት እያሉ ይጮኻሉ … በሕይወቱ ብቻ ሳይሆን በሞቱም ለብዙዎች የራእይ ንቃት ሊሰጥ ለሚችልበት ለአገሩ አፈር እናብቃው።

.

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

.

[ምንጭ] – አንድምታ ልሳን ቁጥር 7 (ግንቦት 1999 ዓ.ም)። ገጽ 2-7።

“ዐፅም” (ግጥም)

“ዐፅም”

በገብረ ክርስቶስ ደስታ

(1950 ዓ.ም)

.

(ገብረ ክርስቶስ ግጥሙን ሲያነብ ለማዳመጥ)

.

.

ማነህ የተኛኸው?

እንቅልፍ የደበተህ ሥጋህን ጥለኸው።

.

ምን ኖረኻል አንተ?

ንጉሥ ኖረኻል ወይ፣ ኖረኻል ወይ ጌታ

ወይ ቁሩንጮ ለባሽ፣ ለማኙ ከርታታ

ሚኒስትር ደጃዝማች፣ ወይም ፊታውራሪ

ባለብዙ ገንዘብ፣ አሽከር አሳዳሪ

ኖረኻል ወይ አንተ?

አጥንትህ ወላልቆ እንዲህ የሻገተ።

.

ሥራህ ምን ነበረ? ቤትህ የት ነበረ?

እርስትህ የት ቀረ?

የተመራመረ አዋቂ ፈላስፋ

ብዙ መሰናክል ካለም ላይ የገፋ

ሳትሆን አልቀረህም

ጉድ ነው መልክህ የለም።

.

ማነሽ ማነህ አንተ?

ማናችሁ እናንተ?

.

ማነሽ በዘመንሽ የውበት እመቤት

ሆነሽ የገዛሽው የወንዶችን ጉልበት

በክንድሽ ያለቀው

ወጣቱ ጐልማሳ የት ነው የወደቀው?

.

ምን ኖረሻል አንቺ አጥንትሽ ይናገር

እንጨት ተሸካሚ

ወይ ኩበት ለቃሚ

ወይ ልብስሽ ያደፈው ጥሬዋ ባላገር

ወይም ሽቅርቅሯ እስቲ ተናጋሪ

ሽቱሽ የጎረፈው መንጭቶ ከፓሪ

በወርቅና ባልማዝ በሉል እንደሆነ

ተጫውተሽ የሄድሽው ዝናሽ የገነነ።

.

እስቲ ተናገሪ ቋሚ ያዳምጣል

አንቺ ለመሆንሽ ምስክርሽ የታል?

.

ያሻኻል ምስክር

ሞተህ ስትቀበር

ድንጋይ ላይ ተጽፎ የሚናገርልህ

ምልክት የሚሰጥ አንተ ለመሆንህ

ሐውልት የሚያቆይህ

ዘመድ ያስፈልጋል ከሌላው ለይቶ

መንገደኛ እንዲያውቅህ ቆሞ ተመልክቶ።

.

“እገሌ ነው” ብሎ ታሪክ የሚያወራ

እንዲደነቅልህ ቀሪው ያንተ ሥራ

ተነስ አንተው ጥራ!

.

እጐንህ ከተኙት ዐፅሞች በጉድጓድ

አለ ወይ ዘመድህ የምታውቀው ጓድ?

ወዴት ነው አባባ የታለች እማዬ

ጋሼ ወዴት ይሆን የት ቀረች እትዬ?

.

ጠፍቷል ምልክቱ

አጥንትና ሥጋህ ሲሰነባበቱ።

.

ከሙታን ማኅበር በመዝገብ ገብተሃል

ማንኛውም አጥንት አስክሬን ሆነኻል

የሞት ጠባሳ ነህ አስታዋሽ ሥራውን

ከንቱ ነው የምትል አወይ ፍጡር መሆን!

 .

የተንቀራፈፈው እጅ እግሩ ሸምበቆ

የተከፋፈለው ሰረሰሩ ለቆ

ጥርሱ ያገጠጠ ዐይኑ የወለቀ

ጐድኑ ተቆጥሮ ጅማቱ ያለቀ

የተገጣጠመ የተሰራ ባጥንት

ሥጋ ወዝ የሌለው የሰው ዘር ምልክት።

.

ሆነህ የተኛኸው

የማትታወቀው …

ምን ኖረኻል አንተ?

.

ገብረ ክርስቶስ ደስታ

.

[ምንጭ] – “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ”። መስከረም 10፣ 1950 ዓ.ም።

.