“ዐፅም” (ግጥም)

“ዐፅም”

በገብረ ክርስቶስ ደስታ

(1950 ዓ.ም)

.

(ገብረ ክርስቶስ ግጥሙን ሲያነብ ለማዳመጥ)

.

.

ማነህ የተኛኸው?

እንቅልፍ የደበተህ ሥጋህን ጥለኸው።

.

ምን ኖረኻል አንተ?

ንጉሥ ኖረኻል ወይ፣ ኖረኻል ወይ ጌታ

ወይ ቁሩንጮ ለባሽ፣ ለማኙ ከርታታ

ሚኒስትር ደጃዝማች፣ ወይም ፊታውራሪ

ባለብዙ ገንዘብ፣ አሽከር አሳዳሪ

ኖረኻል ወይ አንተ?

አጥንትህ ወላልቆ እንዲህ የሻገተ።

.

ሥራህ ምን ነበረ? ቤትህ የት ነበረ?

እርስትህ የት ቀረ?

የተመራመረ አዋቂ ፈላስፋ

ብዙ መሰናክል ካለም ላይ የገፋ

ሳትሆን አልቀረህም

ጉድ ነው መልክህ የለም።

.

ማነሽ ማነህ አንተ?

ማናችሁ እናንተ?

.

ማነሽ በዘመንሽ የውበት እመቤት

ሆነሽ የገዛሽው የወንዶችን ጉልበት

በክንድሽ ያለቀው

ወጣቱ ጐልማሳ የት ነው የወደቀው?

.

ምን ኖረሻል አንቺ አጥንትሽ ይናገር

እንጨት ተሸካሚ

ወይ ኩበት ለቃሚ

ወይ ልብስሽ ያደፈው ጥሬዋ ባላገር

ወይም ሽቅርቅሯ እስቲ ተናጋሪ

ሽቱሽ የጎረፈው መንጭቶ ከፓሪ

በወርቅና ባልማዝ በሉል እንደሆነ

ተጫውተሽ የሄድሽው ዝናሽ የገነነ።

.

እስቲ ተናገሪ ቋሚ ያዳምጣል

አንቺ ለመሆንሽ ምስክርሽ የታል?

.

ያሻኻል ምስክር

ሞተህ ስትቀበር

ድንጋይ ላይ ተጽፎ የሚናገርልህ

ምልክት የሚሰጥ አንተ ለመሆንህ

ሐውልት የሚያቆይህ

ዘመድ ያስፈልጋል ከሌላው ለይቶ

መንገደኛ እንዲያውቅህ ቆሞ ተመልክቶ።

.

“እገሌ ነው” ብሎ ታሪክ የሚያወራ

እንዲደነቅልህ ቀሪው ያንተ ሥራ

ተነስ አንተው ጥራ!

.

እጐንህ ከተኙት ዐፅሞች በጉድጓድ

አለ ወይ ዘመድህ የምታውቀው ጓድ?

ወዴት ነው አባባ የታለች እማዬ

ጋሼ ወዴት ይሆን የት ቀረች እትዬ?

.

ጠፍቷል ምልክቱ

አጥንትና ሥጋህ ሲሰነባበቱ።

.

ከሙታን ማኅበር በመዝገብ ገብተሃል

ማንኛውም አጥንት አስክሬን ሆነኻል

የሞት ጠባሳ ነህ አስታዋሽ ሥራውን

ከንቱ ነው የምትል አወይ ፍጡር መሆን!

 .

የተንቀራፈፈው እጅ እግሩ ሸምበቆ

የተከፋፈለው ሰረሰሩ ለቆ

ጥርሱ ያገጠጠ ዐይኑ የወለቀ

ጐድኑ ተቆጥሮ ጅማቱ ያለቀ

የተገጣጠመ የተሰራ ባጥንት

ሥጋ ወዝ የሌለው የሰው ዘር ምልክት።

.

ሆነህ የተኛኸው

የማትታወቀው …

ምን ኖረኻል አንተ?

.

ገብረ ክርስቶስ ደስታ

.

[ምንጭ] – “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ”። መስከረም 10፣ 1950 ዓ.ም።

.

5 thoughts on ““ዐፅም” (ግጥም)

አስተያየት ለመስጠት