“ገብረ ክርስቶስ ገጣሚው”

“ገብረ ክርስቶስ ገጣሚው”

በሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

.

ገበረ ክርስቶስን የማውቀው ከሐረር ትምህርት ቤቱ ጀምሬ ነው። እዚያ ባዶ እግራችንን፣ በቴኒስ ኩዋስ ኩዋስ ተጫውተናል። ገብረክርስቶስ፣ የእግር ጣቶቹ እኩል ስለሆኑ፣ ኳሱን የሚመታ በእግር ኩርኩም ነበር – ኹሌ የከረረች ምት።

ከእለታት ባንዱ ቀን ግን፣ ዕረፍት ወጥተን፣ ግማሹ በሚሯሯጥበት፣ ግማሹም ኳስ በሚጫወትበት ሽብር ኹኔታ ውስጥ፣ ገብረክርስቶስ ጥጋት ተቀምጦ፣ ቁምጣ ሱሪውን አጋልጦ ባዶ ጭኑ ላይ ሥዕል ሲሠራ እንዳየሁት አስታውሳለሁ። እና አሁን መለስ ብዬ ሳስብ ሥዕል ምንኛ ከልጅነቱ ከጭንቅላቱ ገብቶ ኖሯል እላለሁ። ለዚህም የአባቱ የአለቃ ደስታ ነገዎ የድጉሥ፣ የቁም ጽሕፈትና የብራና መጻሕፍት ላይ ሥዕል ምን ያኽል ተፅዕኖ አድርጎበት ነበር ይሆን? በምንስ መንገድ? እላለሁ።

ያ ያ እንዳለ ኾኖ ግን፣ ገብረ ክርስቶስን እዚህ እማንቀራብጥ በሠዓሊነቱ ሳይሆን በገጣሚነቱ ነው።

የገብረ ክርስቶስን ግጥሞች አንዴ ወጥቻቸው የግጥም መድበል መጽሐፉን (“መንገድ ስጡኝ ሰፊ” 1998 ዓ.ም) እንዳጠፍኩ፣ ገብረ ክርስቶስ ባሳብ አካቶው ምንኛ አይጠገቤ ነው። በእይታ ስንዘራውም ምንኛ አራዝሜ ነው፤ በሌላ ምንኛ … ምንኛ … ምንኛ አልኩ። ይህን ይህን ብዬ ነው የሚከተሉትን ግጥሞች የመረጥኩ እነሁዋችሁ፤

አይጠገብ ወንዝ

አባ በሽበሽ

አይሞላ ልቃቂት

ደናሽ

ሞልቶ እስኪፈስ

ገስጋሽ

የመጨረሻዋን ስንኝ አንጋሽ።

(“ትዝታ” ፣ ገጽ 52)

.

ዘላይ ነው ዘላይ

መጣቂ

ከምብርቷ ዘላቂ

ምጥቃለምን

አይለቅ መንገዱን።

(“የጠፈር ባይተዋር” ገጽ 114)

.

መሔድ፣ መሔድ መሔድ

ከጨረቃ በላይ

ከኮከቦች በላይ

ከሰማይ በላይ

መጓዝ ወደ ሌላ ባዶ ቦታ መግባት።

(“ሥዕል” ገጽ 98)

.

“አሰነኛኘት”

ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ዘጠና በመቶውን ወል ግጥም ገጣሚ ነው። ይህን የግጥም ዘርፍ በስንኞች አቀማመጥ ልዩ ልዩ መልክ ይሰጠዋል። ከኒህ የመልክ ዐይነቶች፣ ዋና ዋናዎች ያልኩዋቸውን፣ ልዩ ልዩ ስሞች እየሰጠሁ እንደሚከተለው አመጣቸዋለሁ።

.

[ሰያፍ ስንኝ]

እርሷን መርሳት አልችል

እፈልጋታለሁ

እከተላታለሁ

እጠብቃታለሁ

(ገጽ 100)

.

[ስንኝ-አጠፍ ስንኝ]

ስንኝ – አጠፍ፣ አንዱን ሙሉ ውል ስንኝ ከሁለት ግጥማዊ ወይም ስንኛዊ እኩሌታ፣ ወይም ወል ገጽታውን ከማያሳጣ ቦታ ማጠፍ ነው። የስንኝ-አጠፍ ስንኝ – ምናልባት – የመጀመሪያው ተጠቃሚ ከበደ ሚካኤል ናቸው።

ደስታና ሐዘን

እየቀላቀልኩ

ልቤን ብዙ ዘመን

ስመገበው ኖርኩ።

(‘ብርሃነ ኅሊና’ – 1961 ዓ. ም. – ገጽ 100።)

ከዚህ አንጻር፣ የገብረክርስቶስ ስንኝ-አጠፍ ስንኝ ስልት መሥመሮች ያዛንፋል፣ በቤት አመታትም ነጻነት ይሰማዋል። ለዚህ እነሆ ምሳሌ፤

እምቢኝ እሻፈረኝ

አሻፈረኝ እምቢ

መቅደስ ነው አገሬ

አድባር ነው አገሬ።

(ገጽ 134)

.

[ቁልቁሎሽ ስንኝ]

በ ‘መንገድ ስጡኝ ሰፊ’ እንደሚታየው፣ ቁልቁሎሽ ስንኝ፣ ወል ግጥምን ስንኝ በስንኝ ወስዶ፣ ቃላቱን ቃል በቃል እያሉ አንድ አንዱን ቁልቁል መጻፍ ነው። በተራው እንዲህ አንዳንዱን የተጻፈውን ወስዶ መልሶ ደምበኛውን የወል ግጥምም መጻፍ ይቻላል። እነሆ የሁለቱም ምሳሌዎች፤

(ነጠላ ነጠላውን)

በገና

ቢቃኙ

ሸክላ

ቢያዘፍኑ

ክራር

ቢጫወቱ

ለሚወዱት

ምነው

ሙዚቃ

ቢመቱ።

(ገጽ 96)

.

(ወል ቅንብሩን)

በገና ቢቃኙ ሸክላ ቢያዘፍኑ ክራር ቢጫወቱ

ለሚወዱት ምነው ሙዚቃ ቢመቱ።

.

“ቤት ምትና ተምሳሌት”

የገብረክርስቶስ ግጥሞች – በመሠረቱ – ወል ስልታቸውን ቤት የሚመቱ ናቸው፤ አልፈው አልፈው ግን ቤት ሳይመቱም ይገኛሉ። ለምሳሌ “የሞት አለም ሞት” (ገጽ 109) የዚሁ ብጤ ነው። ርዕስ የሌለው፣ የዚሁ የገጽ 163 ግጥም ደሞ ቤት ይመታል፣ ግን ብቸኛ የወል ግጥም ያልሆነ ግጥም ነው።

የገብረክርስቶስ ቤት መምቺያ ፊደሎች፣ ገና ሰፊ የጥናት ሥራ የሚጠይቁ ቢሆኑም የ ለ፣ ሰ፣ ረ፣ ተ፣ ነ ቤቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ማለት ይቻላል።

ገብረክርስቶስ የተምሳሌት ባለጸጋ ነው። ይህን የጸጋ በሽበሽ ግን እንዲህ ባለ መጣጥፍ አሟጥጬ ላጤን አልችልም። ስለዚህ – በምትኩ የግጥሙን ጉልህ ገጽታ ወስጄ፣ የዚያን ውስጥ ተምሳሌቶች ላጤን እሞክራለሁ።

ገብረክርስቶስ ግጥሞች ውስጥ ያለው ጉልሁ ገጽታ ሮማንስ ነው። ይህ ገጽታ መድበሉ ውስጥ 12% ይሆናል። ሙከራዬም በመልክእ ስልት – አካላተ እንስትን እንዴት እንደገለጻቸው ማየት ይኾናል – እሱም እነሆ፤

ጠጉር            “ዞማ”

ዐይን            “የጡዋት ጨረር”

ጉንጭ            “ጽጌረዳ”

አፍ             “ማር ወለላ”

ከንፈር           “ብርቱካን፣ የማር እንጎቻ”

ትንፋሽ           “የጋለ”

ምላስ            “የፋመ”

ጡት            “ተዋጊ”

ባት             “የሚጫን”

ሰውነት           “ሎጋ”

ድምጽ           “ሙዚቃ”

.

“የሐሳብ ይዘት”

ገብረክርስቶስ፣ እንደ ገጣሚ፣ የሐሳብ እምብርቱ ሰው ነው፤ ያገርና የወገን ፍቅር ነው፣ ሙዚቃ ነው፣ ዳንስ ነው፣ ተፈጥሮ ነው፣ ሮማንስ ነው፣ የባህል ፍቅር እና ወዘተ ነው። ዝርዝሩ ይሄ ኾኖ ሳለ ወሳኝ ሐሳቦችን የያዙት ግጥሞች የሚከተሉትን ጭብጦች ያካተቱ ስንኞችን ያቁለጨልጫሉ – እናንብባቸው፤

የልጅነት ጊዜ ትምጣ ትዝታዬ

ድሮ የሠራችኝ አሁን መኖሪያዬ።

(“ትዝታ”፣ ገጽ 53-54)

.

ዕንቆቅልሽ ነፍሴ ንገሪኝ በርጋታ

ጨንቆኛል ጠቦኛል ያለሽበት ቦታ።

(“ምንድነሽ”፣ ገጽ 61)

.

“አንድ ነገር ሲሆን ግዴታ መነሻው

መኖር ይገባዋል የሚቀሰቅሰው

ሰውንም ያስገኘ

መኖር ግድ አለበት ዓለምን የናኘ”

በማለት ብዙዎሽ ሲያቀርቡ ክርክር

እስማማለው በዚህ ያለመጠራጠር።

(“ደብዳቤ”፣ ገጽ 126-7)

.

ሞትን ያሸንፋል

ሁሉን ሲቆጣጠር እግዚአብሔር ይኾናል

ወዴት አለ እንቅፋት

የት አለና ዳገት

ለዚህ ትንሽ ተባይ

ገና ይራመዳል።

(“ይራመዳል”፣ ገጽ 132)

.

ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ

እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ

ሳስብ እሄዳለሁ ቢሰበርም እግሬ

አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ

አለብኝ ቀጠሮ

ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ።

(“አገሬ”፣ ገጽ 140)

.

እኒህ ስንኞች፣ የሰአሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ነገዎን ዐጽም – በዳንቴ አሊጊዬሪ (1235-1321) ጣልያናዊ ገጣሚ አብነት – ላገሩ ዐፈር አብቁት እያሉ ይጮኻሉ … በሕይወቱ ብቻ ሳይሆን በሞቱም ለብዙዎች የራእይ ንቃት ሊሰጥ ለሚችልበት ለአገሩ አፈር እናብቃው።

.

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

.

[ምንጭ] – አንድምታ ልሳን ቁጥር 7 (ግንቦት 1999 ዓ.ም)። ገጽ 2-7።

4 thoughts on ““ገብረ ክርስቶስ ገጣሚው”

  1. ምስጋና ለሰይፉ መታፈሪያ። ስለ ገብረክርስቶስ ደስታ ጥሩ መንደርደሪያ እውቀት የሚሰጥ መግለጪያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። መታደል ሆኖ ገብረክርስቶስ ስዕሎቹንም ከትምህርት ቤቴ ጉዋሮ ጎራ እያልኩ የተደሰትኩባቸው ሲሆን፣ ግጥሞቹንም በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያነብ በቅርብ ለማዳመጥ ችያለሁ። ወርቅዬ ጥበበኛ ነበር። #ሰሎሞንገብሬ

    Like

  2. ከገብረክርስቶስ ግራና ቀኝ የተቀመጡት እነማን ናቸው? ሰይፉ፣ የገብረክርስቶስን ዐጽም ላገሩ አፈር እናብቃው ላለው ምን እየተደረገ ነው? አንድምታ ልታስተባብር ትችላለች? ከጤና ጥበቃ፣ ከህግ፣ ወዘተ አንጻር መመልከት ስለሚጠይቅ በዚህ የሠለጠኑ ወገኖቻችን ሊረዱ ይችላሉ። በማጓጓዙ አየር መንገዳችን ቢጠየቅ። አገር ቤት ካሉት ወገኖቻችን ጋር ምክክር ቢጀመር አንድ ቁምነገር መሥራት ይቻል ይመስለኛል። ይኸ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በትክክል ከተደረገ የባህላችንና የአንድነታችን ማንሠራሪያ አንደኛው መንገድ ነው።

    Like

አስተያየት ለመስጠት