“እስቲ ሙዚቃ!” (ልብወለድ)

“እስቲ ሙዚቃ!”

በሌሊሳ ግርማ

.

[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]

.

.

የፍቅርን ዋና ትርጉም ለመረዳት ይመስለኛል፣ አንዳንድ ጊዜ የምጽፈው፡፡ ፍቅርን ለመረዳት ብጽፍም ተረድቼው አላውቅም፡፡ የማውቀው ነገር ግን አለ፡፡ ፍቅርን ባላውቅም የማውቀው ነገር አለ፡፡ ይኼውም የፍቅር ተቃራኒ ፍርሐት መሆኑን ነው፡፡ የጨዋታው ህግ ይሄ ብቻ ነው፡፡

ባለፈው ወር አንድ ፒያኖ የሚጫወት ሰውዬ ትርኢት ባሳየበት ምሽት ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ ሰውዬው መጫወት ሲጀምር ገና ነው ፍርሃት እንደሌለበት የገባኝ፡፡ ሰውዬው ሳይሆን ፒያኖውን የሚጫወተው ፒያኖው ነው ለሰውየው እየተጫወተለት ያለው፡፡

ሰውዬው ፒያኖውን ከሚወደው በላይ ፒያኖው ሰውየውን ያፈቅረዋል፡፡ ፒያኖው ሰውየውን ያፈቀረበት ምክንያትም ግልፅ ነው፡፡ ሰውየው አንዳችም ፍርሃት የለበትም፡፡ እርግጠኛ ነው፡፡ ፒያኖውን መጫወት ስለመቻሉ አንዳችም ጥርጣሬ አድሮበት እንደማያውቅ ያስታውቃል፡፡ ፒያኖ ደግሞ በተፈጥሮው የሴት ባህርይ ያለው መሳሪያ ነውና፤ እርግጠኛ የሆነ ሰው ያለ ፍርሐት ሊነካካት ከቀረበ ነፃ ሆና መጫወቷ አይቀርም፡፡ ፍርሃት ካሸተተች ግን ሴቷም ሆነች ፒያኖዋ ፍቅሯን ትከለክላለች፡፡ እንዲነካኳትም አትፈቅድም፡፡ ቢነካኳትም የምታወጣው ድምጽ የእንቢታ ነው፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ከፍቅር እንጂ ከእንቢታ ውስጥ አይወጣም፡፡

እናም ባለፈው ወር ሰውየው ገና መቀመጫውን ስቦ ፒያኖዋ ስር እንደተቀመጠ እጁን ሳያሳርፍባት በፊት መሳሪያዋ ጥዑመ ዜማዋን ለቀቀችው፡፡ የፒያኖውን ቁልፎች እየጐረጐረ አልነበረም ሙዚቃውን የሚያፈልቀው፡፡ በመጐርጐርማ መኪናም የሞተር ድምጽ ከተኛበት ተቀስቅሶ ያወጣል፡፡ ሰውየው የፒያኖው ቁልፎች ላይ የተቀመጠለትን ሙዚቃ… በሁለት እጆቹ ማፈስ ነው የጀመረው፡፡ በሁለት መዳፎቹ ከጥግ እስከ ጥግ እየተመላለሰ ፒያኖዋ የምትሰጠውን ፍቅር ሙዚቃ አስመስሎ አፈሰ፡፡ ጉያዋን፣ ደረቷን፣ ዳሌዋን እያሸ ዜማዋን አስጨረሳት፡፡

በመጨረሻ በአንድ እጁ ጭንዋ ውስጥ ገብቶ ሲቀር … እና ፒያኖዋም ተንሰቅስቃ ዜማዋን ስትጨርስ … አዳራሹ በጭብጨባ መሃል ለመሀል ተገመሰ፡፡ ፒያኖዋን መጫወት ያላስፈራው ሰውዬ በጭብጨባው ተደናበረ፡፡

ደነገጠ፡፡ ከመደንገጡ የተነሳ ከወገቡ ሁለት… ሶስት ጊዜ ታጠፈ፡፡ ጭብጨባው ነጐድጓድ ሲሆንበት… በሩጫ ከመጋረጃው ጀርባ ገብቶ ተደበቀ፡፡ ፒያኖውን ቢደፍርም የጭብጨባ ነጐድጓድ እና ሕዝብን ግን ይፈራል ለካ!

ለካ፤ ሁሉም የሚፈራው ነገር አለው፡፡ ሕዝብ ፒያኖውን መንካት ቢፈራም ሰውየውን ግን ለመንካት ይደፍራል፡፡ ሰውየው ደግሞ በተገላቢጦሽ ልበ ሙሉነቱ ወደ ፒያኖው እንጂ ለህዝባዊ ፍቅር ቦቅቧቃ ነው፡፡

የፍቅርን ትርጉም አላውቅም፡፡ የማውቀው ፍቅር ከፍርሃት ጋር ዝንተ ዓለም ጠላት መሆኑን ብቻ ነው፡፡

***

ኤስን ትዝ ይለዋል፤ ምናልባት የአስር አመት ልጅ ቢሆን ነው፡፡ አባቱ ከእነ ቮልስዋገኑ ድልድይ ውስጥ የገባ ጊዜ ሆስፒታል ከእናቱ ጋር ይመላለስ ነበር፡፡ ሆስፒታሉ ሳይሆን የሆስፒታሉ ሽታ ከአደገም በኋላ ስሜቱ ሲጐዳ ወይንም … ተስፋው በየትኛው ኪሱ ውስጥ አስቀምጦት እንደነበር ፈልጐ ባጣው ጊዜ ሁሉ የዚያ የሆስፒታል ሽታ ይመጣበታል፡፡

ከሆስፒታሉ ሽታ ቀጥሎ ደግሞ በላስቲክ … አባቱ አናት ላይ ይንጠለጠል የነበረው እርጐ መሳዩ ደም ዓይኑ ላይ ይደቀንበታል፡፡

***

እናቱ እንደዚያ መሳቅ እንደምትችል አያውቅም ነበር፡፡ የሆስፒታሉ ሽታ፣ እርጐ መሳዩ ደም እና የእናቱ ሳቅ ከመንፈስ ዝቅታ ጋር እንደ ሰንሰለት ተቀጣጥለው የሚመጡበት ነገሮች ናቸው፡፡ የዓይን ትዝታ በደም፣ የጆሮ ትዝታ በሳቅ፣ የአፍንጫ ትዝታ በሆስፒታሉ ሽታ፡፡

ይመስለዋል እንጂ … መሳሳቱን አያውቅም፡፡ የትዝታ ጥፍሮች ከአስርት አመታት በላይ ወደኋላ ሄደው ሲቧጥጡ ጊዜ እና ቦታን ያዛንፋሉ፡፡ ይመስለዋል እንጂ፤ የእናቱ ሳቅ የተሰማው በሆስፒታሉ ሽታ እና በተንጠለጠለው እርጐአማ ደም መሀል ሳይሆን … በክፍለ ሀገር አውቶብስ እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ያኔ፤ እድሜውም አስር ሳይሆን ስምንት ቢሆን ነው፡፡

በክፍለ ሀገር አውቶብስ የእናቱን ዘመዶች ለመጠየቅ በሄዱበት የክረምት ወቅት፣ አባቱ ገና ድልድይ ጥሶ ለመግባት ሁለት አመት ገደማ ይቀረው ነበር፡፡ በስምንት አመቱ ላይ የገጠመውን ድንጋጤ እና በአስር ዓመቱ የተጋፈጠውን መከራ ያስተሳሰረው በራሱ ስሜት አማካኝነት እንጂ በጊዜ ቅደም ተከተሉ መሰረት አይደለም፡፡ (እንዳይደለ ግን እኛ እንጂ እርሱ አያውቅም፡፡)

በክፍለ ሀገር አውቶቡስ ወደ አርባ ምንጭ እየሄዱ ነው፡፡ እናቱ እናት እንጂ ልጃገረድ መስላው አታውቅም ነበር፡፡

እየተጓዙ ብዙ ጥያቄ ይጠይቃታል፡፡ የተቻላትን ያህል ትመልስለታለች፡፡ ጥያቄው አሁን ለሱ ትዝ ባይለውም እኛ ግን እናስታውሰዋለን፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ዘፈን ተከፍቷል፡፡ ሾፌሩ ከመንገዱ ጋር እየተወዛወዘ ትሪ የሚያክለውን መሪ ወደግራ፣ ወደቀኝ ይለዋል፡፡

“ኢንፌዱ ምን ማለት ነው?” አላት እናቱን፡፡

“አልፈልግም ማለት ነው” ባለመፈለግ ውስጥ ብዙ አመታት የተንገላታ መልክ አላት፡፡

“ኢንተሁስ?”

“አይሆንም”

“ኢ-ሰብአዊ ማለትስ?”

“ለሰዎች የማይሆን ማለት ነው”

“ኢ … ካለበት አፍራሽ አረፍተ ነገር ነው ብሎኛል አባባ”

“አባባ ምን ያውቃል ስለ አማርኛ”

“ኢ – ትዮጵያ ማለትስ?”

“አንተ ደግሞ … አጉል አትፈላሰፍ!”

ይህንን በመሳሰሉ ጥያቄ እና መልስ የመንገዱን አሰልቺነት ሲገዘግዙ ድንገት አውታንቲው ዱካ መሳይ በርጩማ ስቦ እናቱ መቀመጫ ጐን ተቀመጠ፡፡ አውታንቲው እንደተቀመጠ፣ በድፍረት አንድ እጁን እናቱ ጭን ላይ አስቀምጦ በማይሰማ ድምጽ ወደ ጆሮዋ ተጠግቶ አንሾካሾከ፡፡ ይሄኔ ነው … እናቱ ከዚህ በፊት አሰምታው የማታውቀውን ሳቅ የለቀቀችው፡፡

ስቃ ሳትጨርስ አሁንም ወደ ጆሮዋ ተጠግቶ አንሾካሾከ፡፡ ባላለቀው ሳቋ ላይ አዲስ ሳቅ ቀጠለችበት፡፡ እየሳቀች፤ በዱካ የተቀመጠው ሰውዬ እጇን በመዳፉ ላይ ደርቦ በሌላ መዳፉ እየመታ (“ሙች”) ይምልላታል፡፡ በተማለ እና በተሳቀ ቁጥር እናቱ እድሜ የቀነሰች ልጃገረድ እየመሰለች መጣች፡፡ ሻሽዋ ውስጥ አብሮ የታሰረው ጆሮዋ ከእነ ጆሮ ጌጡ ብቅ አለ፡፡

ኤስ የስምንት አመት ልጅ ቢሆንም ሲደነግጥ ትዝ ይለዋል፡፡ ምናልባት ልጅነት የዋህነት ስለሆነ ሊሆን ይችላል የደነገጠው፡፡ በአውቶቡሱ ውስጥ የነበሩት … ተሳፋሪዎቹ፣ ሌሎቹ አዋቂዎች በእናቱ ሳቅ ሳቢያ ከንፈራቸው በፈገግታ ፈልቀቅ ብሎ ነበር፡፡ ምናልባት … አዋቂ ሆኖ ቢሆን እናቱን አባቱ ብቻ ማሳቅ ወይንም መንካት መብት አለው ብሎ ባላሰበ ነበር፡፡ ግን ያኔ ልቡ ደነገጠበት፡፡ በዱካ የተቀመጠውን ሰውዬ ጠላው፡፡ ቢጠላውም ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡

አዋቂ ቢሆን ኖሮ “ማነህ … የት ታቃታለህ?” ማለት በቻለ ነበር፡፡ ሰው ለማስወረድ ብቻ ከተቀመጠበት አልፎ አልፎ ከመነሳት በስተቀር የጉዞውን ጊዜ እናቱ ስር በዱካ ተቀምጦ አውታንቲው በማይሰማ ድምጽ ሲያንሾካሹክላት እንደነበር ኤስን አሁን ትዝ አይለው ይሆናል፡፡ ግን እያንዳንዱ ክስተት ቢዘነጋውም ሳቋ ግን እድሜ ልኩን ይከተለዋል፡፡

“ኢ-እናታዊ” ብሎ ጉሮሮው ላይ የተጠራቀመውን ሳግ እየዋጠ፣ በአውቶብሱ መስኮት ጋራና ሸንተረሩን እንባ በሞላው አይኑ እያየ ማጉተምተሙ ለእኛ እንጂ ለእርሱ ተዘንግቶታል፡፡

እንደ ፒያኖ ተጫዋቹ ለእናቱ የሳቅ ዜማ ማመንጨት ዋናው ምክንያት የአውታንቲው ድፍረት ነበር፡፡ በድፍረቱ ምክኒያት እናቱ ተሸነፈችለት፡፡ ጥርጣሬ ቢያሳይ ኖሮ ሊጫወታት ወይንም ሊያጫውታት ባልቻለ ነበር፡፡ በዚህ ሰውዬ ፍርሃት አልባ ድፍረት ምክኒያት ከሁለት ኣመት በኋላ አባቱ አብዝቶ መጠጣት በመጀመሩ ድልድይ ውስጥ ገባ፡፡ ድልድይ ውስጥ ከመግባቱ፤ ሆስፒታል ገባ፡፡

ሆስፒታል ከመግባቱ፣ የአውታንቲው እና የእናቱ ግንኙነት ጠነከረ፡፡ ግንኙነታቸው በመጠንከሩ፣ አባቱ ከእናቱ ጋር የነበራቸው በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ትዳር ተበጠበጠ፡፡ በመበጥበጡ ተለያዩ፡፡ እሱም የድሮው ሰፈሩን፣ የድሮው ት/ቤቱን፣ የድሮ ጓደኞቹን ከአባቱ ጋር ጥሎ ወደ አዲስ ህይወት ከእናቱ ጋር ተንቀሳቀሰ፡፡

***

ፒያኖ ተጫዋቹ እና አውታንቲው አንድ ናቸው፡፡ ፒያኖ ተጫዋቹ የሚጫወተው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡

አውታንቲውም ለአጭር ጊዜ የእናቱን ፍቅር አፈሰ … የእናቲቱን እንጂ የልጁን ፍቅር ግን አላገኘም፡፡

በአውቶብሱ ውስጥ ሳሉም አውታንቲው ፒያኖውን ሲጫወት ተሳፋሪው በሙሉ አጨብጭቦለት ነበር፤ ደፋር፣ የዋህ እና እውነተኛ ይመስል ነበርና፡፡ ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉም ወደውታል፡፡ ከአንድ ሰው በስተቀር በተጫወተው ሙዚቃ ሁሉም ተደንቋል፡፡ ያ አንድ ሰው ብቻ አውታንቲው በተጫወተው ሙዚቃ ህይወቱ በዘላቂነት ተበጥብጧል፡፡ ያ አንድ ሰው በዚያ ወሳኝ ወቅት አንድ ፍሬ ልጅ ነበረ፡፡ የስምንት ዓመት ልጅ፡፡

ስለዚህም ነው፤ የእናቱን ሳቅ፣ ከሆስፒታሉ ሽታ፣ ከአባቱ አናት በላይ ከተሰቀለው እርጎ መሳይ ደም ጋር የሚያስተሳስረው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ተበጣጥሶ የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በእይታ እና በሳቅ ድምፅ ቅላፄ፡፡ ፒያኖ ተጫዋቹ የመጨረሻውን ዜማ ፒያኖው ጭን ውስጥ ሰተት ብሎ በመግባት እንዳፈለቀው፣ በአውቶብሱ መስኮት እየተመለከተ የነበረው የስምንት ዓመት ልጅም የመጨረሻውን እና የመጀመሪያውን የእንባ ዘለላ ብዥ ካለው አይኑ ላይ የጠረገው … እናቱ ወረቀት ጽፋ በርጩማ ላይ ለተቀመጠው ጎልማሳ ስታቀብለው አይቶ ነው፡፡ ጭን ውስጥ መግባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ዝርዝሩ ባይገባውም … ጭኗ ውስጥ እንደሚገባ ግን እርግጠኛ ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖ እንደነበር እሱ ራሱ ትዝ ላይለው ይችላል።

ብዙ ዓመታት አልፈዋል ይኼ ታሪክ ከተከሰተ፡፡ እኔ እና እናንተ ግን ከእሱ በተሻለ የተከሰተውን ሁሉ እናስታውሳለን።

የፒያኖ ተጫዋቹ፣ የአድማጩ እና የጨዋታው ህግ እንዴት እንደሚሰሩ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

.

ሌሊሳ ግርማ

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] – “እስቲ ሙዚቃ”። 2009 ዓ.ም። ገጽ 239-243።

4 thoughts on ““እስቲ ሙዚቃ!” (ልብወለድ)

  1. አጭር ግን በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ሰፍነው ያሉ ስሜቶችን በተዋሐደ ንፅፅር በረጅሙ ያመለከተ ፅሁፍ። በጉጉት የሚገል

    Like

  2. እያንዳንዱ ቃል ምስል ይከስታል፡ ታሪኩን ይተርካል ፡ እንቅስቃሴውን ፍንትው አድርጎ ያስቃኛል፡ እምቅ ነው፣ ከተባለው በላይ እንድናስብ እንገደዳለን፣ ስሜታችንን የሚይዝ ግዙፉን ተፈጥሯዊ ክስተት ፍቅርና ፍርሃትን ባንዲት ሽራፊ በምታክል ቅንጭብ ሕይወት አስቃኝቶናል፣ ግሩም ሥራ ሌሊሳ።

    Like

አስተያየት ለመስጠት