“ልብወለድ ታሪክ” (ጦቢያ)

“ልብወለድ ታሪክ”

በአፈወርቅ ገብረየሱስ

(1900 ዓ.ም)

.

ደግ አድራጊ አበደረ ክፉ አድራጊ ተገደረ።

ለጋስ ቢለግስ አበደረ እንጂ አልሰጠም።

.

ኦሪት ተሽራ ወንጌል መሰበክ በተጀመረ ዘመን እስላሙ ከፍ ብሎ ክርስቲያኑ ዝቅ ይል ነበር። ድሉ ግን አንድ ጊዜ ለክርስቲያኑ ሲሆን አንድ ጊዜም ለእስላሙ ሲሆን ይኖር ነበር። ነገር ግን ከነዚህም ወገን ከነዚያም ወገን ከቶ እርቅ የሚፈልግ አንድም ሰው አልነበረ። ብቻ በየጊዜውና በየወርሁ በያመቱ ሲዋጉ ሲፋተጉ ሲተራረዱ ሲተላለቁ ይኖሩ ነበር።

እንደዚሁ ሁሉ አንድ ጊዜ የእስላም ጦር እንደልማዱ መጣ በተባለ ጊዜ የክርስቲያኑ ንጉሥ ተፋጥኖ ጦሩን ባዋጅ አስከትቶ ባራት ደጃዝማቾች እግር አሳዝዞ ሂድ ተዋጋ ብሎ ሰደደ። ከነዚያ ከሄዱት ካራቱ ደጃዝማቾች ሶስቱ ከውጊያው ላይ ሞቱ። አንደኛው ግን ተያዘ። ሰዉም ሁሉ ከዚያው ላይ እንደጉድ እየተሳመጠ እየተናነቀ እየተራኰተ ሞተ አለቀ። የቀረውም ጥቂት ሰው ተማረከ። አንድ ለዘር ወዳገሩ ሸሽቶ ያመለጠ ሰው ግን አልተገኘም። የእስላሙ ጦር ግን ከድሉ በኋላ እንደፈከረው ገብቶ ከብቱንና ምርኮውን ይዞ ወዳገሩ ተመለሰ።

ይሄ ወሬ በያገሩ ተዘራና ሁሉም በየዘመዱ መሞት መማረክ ይላቀስ ፊቱን ይነጭ ጠጕሩን ይቈረጥ ጀመር። የክርስቲያኑ ንጉሥም የጦሩን ማለቅ የሶስቱንም ደጃዝማቾች መሞት፣ ያንደኛውንም ደጃዝማች መታሰር፣ ያገሩንም መዘረፍና መጥፋት በሰማ ጊዜ ወዲያው በሀዘንና በድንጋጤ ታሞ ከጥቂት ቀን ወዲያ አለቀኑ ተቀሰፈ ሞተ። የክርስቲያንም አገር ባንድ ጊዜ ንጉሥ አጣ፣ ገዢ ጠፋበት። አገሩም ምድረ በዳ ሆነ።

ያ ተማርኮ የቀረው ደጃዝማችም የእስላሙ ጦር አገሩን እንደ ተመለሰ በማረከው ሰው እጅ ተሸጠ። ማራኪው ሰው ግን ሲማርከውም ሲሸጠውም ትልቅ ሰው መሆኑን ሳያውቅ እንዲያው እንደማንም ሰው ነው የሸጠው። ያነኑ መከረኛ ደጃዝማች የገዛ እስላም ግን ቁመቱን ዛላውን አምሮ ባየ ጊዜ ‘ማለፊያ ብርቱ ባሪያ አገኘሁ’ ሲል ደስ አለውና ብርቱ ብርቱ ስራ እያዘዘ፣ እንደለጓሚ ሣር ያሳጭደው፣ እንደቋሚ እንጨት ያስፈልጠው፣ እንደጐረደማን ድንኳን ያስጭነው፣ ተራዳ ያስሸክመው ጀመር።

እሱ ግን ያልለመደው ነገር ነውና ከዚህ ሁሉ ሥራ አንድ የሚሆንለት ነገር አጣ። ሣር ልጭድ ቢል የለሰለሰው የጨዋ እጁ እንደሽንኵርት ተላጠ። ብርጭቆ ብርሌ በሚጨብጥበት በነበረው ጣቱ ምሳር ቢጨብጥበት ጉብር አወጣ። ያም ሆነ ያም ሆነ ያው የጥንት ደጃዝማች የዛሬው ባሪያ አዲሱ ጌታው እንዳይቈጣው ምናልባችም ባልተወለደ አንጀቱ እንዳይገርፈው እየተጋጠጠ ሥራውን አልሁህ አልሁህ ይል ጀመር። ነገር ግን ያኰረሰው እጁ ጭራሹን ተሞሸለቀ። ተራዳ የሚሸከምበት ጫንቃውም አጕርቦ የነበረው ሁሉ ተገሸለጠና የማይሆንለት ሆነ። ጌታው ግን ለሥራ ተለገመ መስሎት ይቈጣውና ለመግረፍ ያንገራግረው ጀመረ። ይሄው አዲስ ገብ ባርያ ግን “እንግዴህ የምታረገውን አድርገኝ እንጂ ተችሎኝ የምሰራልህ ነገር አላገኝም” አለና ጫንቃውንም እጁንም አሳየው።

ያም ጌታው ባየው ጊዜ እውነትም መስራት እንዳይሆንለት አየና የጨዋ ልጅ ነው ይሆን ብሎ ጠረጠረ። በዚህ የተነሳ የማረከውን ሰው “የሸጥህልኝን ባሪያ ስትማርከው ምን ለብሶ አገኘኸው” ብሎ ጠየቀ። ያም ሰው “ብዙ ጌጥ ነበረው ገፍፌ ብሸጠው ብዙ ወርቅ አመጣልኝ” አለና ነገረው።

እሄን አዲስ ወሬ በሰማ ጊዜ ያ የገዛው ጌታው ደስ አለውና የዚያን ደጃዝማች ነገር ትልቅ ሰው መሆኑን አወቀና መቸም ስራው ታልጠቀመኝ ብሎ ገንዘብ ያተርፍበት ዘንድ ፈለገ። ከዚህ በኋላ ጠራና እንዲህ አለው።

“አንተ ባሪያ … እኔ ተማረከህ ሰው ብዙ ወርቅ አፍስሸ ገዛሁህ። አሁን የፈቀደኝን ብሰራህ ይቻለኛል ነገር ግን ታሳዝነኛለህ። አሁንም ከዘመዶችህ ላክና እልፍ ወቄት ወርቅ አስመጥተህ ስጠኝና አገርህን እንድትሄድ እለቅሃለሁ።”

ያ ደጃዝማች ግን እንኳን አገሩ ጠፍቶ፣ ንጉሡ ሙቶ፣ ከብቱ ተዘርፎ፣ በሬው ላሙ ተነድቶ፣ እሄም ባይሆን ታገሩ በጌትነቱ ሳለ ለጀግና መስጠት፣ ለደሀ መርጠብ፣ ለተራበ ማብላት፣ ለታረዘ ማልበስ እንጂ ገንዘቡን ወደኋላ ማረግ ለነገ ማለት አያውቅም ነበረና “

“የምከፍለውም የለኝ ደሀ ነኝ እንደ ወደድህ አድርገኝ” ብሎ መለሰለት።

የዚሁ ደጃዝማች ሎሌዎች ሁሉ አብረውት ሲዋጉ ከዚያው ተፊቱ አልቀዋል። ንጉሡም ሙቷል። አንድ ደጋፊ አንድ ተስፋ ታገሩ አልነበረውም። ብቻ ተቤቱ ምሽቱና መንታ የተወለዱ ሁለት ልጆች አንድ ወንድ አንድ ሴት ልጆች ነበሩት።

እነዚሁ ልዦች የዚያን ጊዜ አሥራ ስድስት ዓመት ሁኖአቸው ነበር። ወንዱ ዋህድ፣ ሴቲቱ ጦቢያ ይባሉ ነበር። ሁለቱም ልጆቹ እጅግ ያማሩ እጅግ የተዋቡ ነበሩ። መንታ ስለሆኑ ሁለቱም መልካቸው አንድ አካል አንድ አምሳል ሁኖ ላይን ያሳስቱ ነበረ። ታለባበሳቸው በቀር ወንዱም ገና ጢም አላቀነቀነም ነበርና ሌላ ምንም የሚለያዩበት ነገር አልነበረም።

ለነዚሁ ልጆቹና ለምሽቱ ፊት እሱን ሞተ ብለው አርድተዋቸው ነበር። ኋላ ግን ታንዱ ወዳንዱ ሲል እሄው አባታቸው ተማርኮ ተሽጦ ኑሮ ያው የገዛው ጌታው ‘እልፍ ወቄት ወርቅ አምጣና ልልቀቅህ አለው’ ሲባል ወሬው ደረሰላቸው። ምንም ባለመሞቱ ደስ ቢላቸው ወዲህም እንደባሪያ በመሸጡ ወዲህም ሰጥተው የሚያስለቅቁበት ገንዘብ በማጣታቸው እንደገና ይላቀሱ ጀመር።

ንጉሡ ሙቶ አገር ጠፍቶ እነሱ ለራሳቸው ደህይተው ወዴት ገንዘብ ይገኝ? ምን ሰጥተው ያድኑት? እንዲያው መላቀስ እንዲያው መጨነቅ ብቻ ሆነባቸው። ልጅየው ዋህድ “ልሂድና ባባቴ ፈንታ እኔው ባሪያ ልሁንና አባቴ አገሩን እንዲመለስ ላድርግ” ቢል እናቲቱ “ያው እስላም ሁለቱንም ይዞ ያስቀርብኛል” ብላ ፈርታ አለቀው አለች።

በመጨረሻው ግን እናቲቱና እነዚያ መንቶች ዋህድና ጦቢያ እንዲህ ብለው ተማከሩ። እናቲቱ ቶሎ ቶሎ የሙያ እየፈተለች ገንዘብ ልታጠራቅም። ወንዱ ልጇ ዋህድ የጌታ አድሮ ደመወዙን እያመጣ ሊያጠራቅም። ሴቲቱ ጦቢያ ግን እንጨት ለቅማ ውሀ ቀድታ የሚበሉትን እያሰናዳች ልታቀርብ። ቤተሰቡን ሎሌውን ገረዱን የሚሰጡት ገንዘብ የለምና ሊያሰናብቱ አሰቡና ተማከሩ።

እውነት ነው የሞያ ተፈትሎ የሎሌነት ደመወዝ ተቀብሎ እልፍ ወቄት ወርቅ ለማጠራቀም ተረት ነው። ነገር ግን ምን ያድርጉ የቀራቸው ነገር እሄ ብቻ ነው ሌላ የሚቻላቸው ነገር አልነበረም።

ከዚህ ወዲያ እናቲቱ ቶሎ ቶሎ ትፈትል ጀመር። ዋህድም እየዞረ የሚያድርለት ጌታ ይፈልግ ጀመረ። ጦቢያም እያንጐራጐረች እንጨቷን ትለቅም፣ ውሀዋን ትቀዳ፣ ቅጠላ ቅጠሉን ትለቅም ጀመር። ምግባቸውም ቅጠል ብቻ ሆነ። የምግባቸው ነገር በጦቢያ በኵል ተከተተ። እሷ አሉማውን፣ እህል ገቡን፣ ማገጡን፣ አሞጩም ሳይቀር እንዲህ እንዲህ ያለውን ስራስሩን ቅጠላቅጠሉን እያጠራቀመች እያበሳሰለች አቅርባ አንድነት ተጠራቅመው አባታቸውን እናቲቱም ባሏን እያሰቡ እየተከዙ መበላላት ሆነ። በማግስቱ ሁሉም እየስራቸው ይሰማራሉ። ወንዱ ልጅ ዋህድ ገና የሚያድርለት ጌታ አላገኘም ነበርና ሲፈልግ ሲፈልግ ወሬ ሲጠይቅ ሲያስጠይቅ ታንድ ትልቅ ከተማ ደረሰ።

ተዚያ ከተማ ዳር ተመስክ ላይ መደበሩን መትቶ፣ ወገኑን አሰማርቶ የሰፈረ ነጋዴ አየና ከዚያው ለመሄድ ፊቱን ወደ መደበሩ አቀና። ተመደበሩ ሳይደርስ በፊት ወገን ጠባቂውን አየና አስቀድሞ ወሬውን ከሱ ለማግኘት ቀረበ። ቀጥሎም “ያ መደበር የምን ነጋዴ ነው ወዴትስ ሂያጅ ነው” አለና ጠየቀ። እረኛውም “ሰፈሩም ያንድ የትልቅ ነጋዴ ነው። እሄው ነጋዴ የሚነግድበትም በወርቅ በዝባድ በዝሆን ጥርስ በቡን ነው። አሁን የሚሄድበትም ወደ ምስር ነው” አለና አወራለት።

ዋህድም እግዚአብሔር ይስጥህ አለውና ሲያቆም “ጫኝ ሎሌ ቢያገኝ ባስገባ ይሆን?” አለና ጠየቀው። ከብት ጠባቂውም ተሎ ብሎ “እንዴታ ታልህስ ተጐረደማኖቹ መሀል ንዳድ በሽታ ገብቶ ታመውበት የሚነሣበቱ ጊዜ ዘግይቶበት ተጨንቋል። እንዳይነሣ ጫኝ አጣ አሁን ቢቸግረው እጥፍ ደመወዝ እሰጣለሁና ጐረደማን ፈልጉልኝ እያለ ይፈልጋል ያስፈልጋል። ከብቱም እንደምታየው እልቅ የለውም” አለና ነገረው።

በዚህ ጊዜ ዋህድ ደስ አለውና ቸኵሎ ደህና ዋል እንኳ አላለውም ወደ መደበሩ ይሮጥ ጀመረ። ከሰፈሩ እንደደረሰ የዋናውን ድንኳን በትልቅነቱ አወቀና ቀርቦ አጋፋሪውን “ጫኝ እሆን ብየ መጥቻለሁና ለጌታው ንገርልኝ” አለው። አጋፋሪው ግን ያለባበሱንም ያለሳለሱንም ያነጋገሩንም ያኳኋኑንም ነገር አየና ነገሩ የማይመስለው ሆነ።

ነገር ግን ለሁሉም ነገር አጋፋሪ ነውና አልነግርም ይል ዘንድ አይቻለውምና የጌታውንም ጫኝ ማጣት ያውቅ ስለነበረ በግዱ ገብቶ ለጌታው “ጫኝ እሆናለሁ የሚል አንድ ደህና ጐበዝ መጥቷል” ብሎ ነገረው። ባለቤቱም ‘ደህና ጐበዘ መጥቷል’ን በሰማ ጊዜ አጋፋሪውን ተቈጣና “ደህና ጐበዝ መጥቷል የምትለኝ የታመመ ጐበዝ ስፈልግ ሰምተኸኝ ኑሮአል። የታመመማ ተቤቴስ ተርፎኝ የለም እንደምታየው” አለና አፈፍ ብሎ ቸኵሎ ታጋፋሪው ቀድሞ ግፋን ወደዚያ ጐበዝ ሄደ። አጋፋሪው ግን “ኧረ ደህና ጐበዝ ማለቴ ለጭነት የተገባ ሰውም አይመስል ማለቴ ነበር” ብሎ ሊናገር ሲል ባለቤቱ ጊዜ ሳይሰጠው ተነሣ።

እሱም አጋፋሪው ‘ኧረን … ባፉ እንዳንጠለጠለ በኋላ በኋላው ተከተለ። ባለቤቱ ግን ተድንኳኑ ደጃፍ እንደደረሰ ወዲያና ወዲህ ቢያይ ተዚያ ማለፊያ ገና ወጣት ልጅ ተዋህድ በቀር ሌላ ለጐረደማንነት የተገባ ሰው ከደጁ አጣ። ቀጥሎ ወደ በረኛው ዙሮ “ለጫኝነት የመጣው ሰው ወዴት ነው” አለና ጠየቀ።

ገና በረኛው ሳይመልስ ዋህድ እጅ ነሳና “ጌታው እኔው ነኝ። ይወዱ እንደሆን እርስዎን ለመከተል ለርስዎ ጐረደማን ልሆን መጥቻለሁና ይፍቀዱልኝ” አለ። ባለቤቱ ግን ዋህድን ተግር እስከ ጥፍሩ ከራሱ እስተጠጉሩ አመሳቅሎ አየውና ደንቆት “እንዴታ ጐረደማን እንዲህ ኑሮ! ጫኝ እንዲህ ነው እንጂ! ምንኛውን!” እያለ ለብቻው ይጕተመተም ገባ።

ዋህድም ነገሩን እንደናቀበት እንዳልተቀበለው ባየ ጊዜ እንዲህ አለው፣ “ጌታው ተወፍራም አባያ የቀና ኮሳሳ በሬ አብልጦ ያርሳልና ለጋነቴን አይተው አይናቁኝ ጭነት አይቸግረኝም።”

ያው ሀብታም ነጋዴ ግን እንዲህ ያለ ቃል ከዚህ ሕፃን ከዋህድ ሲወጣ በሰማ ጊዜ ወዲያው ወቃቢው ወደደውና እንዲህ አለው። “ምነው እንዳንት ያለ የደህና ሰው ልጅ ተማዕርጉ ወጥቶ ጫኝነት ይመኛል? ንግግርህ ያማረ አለባበስህ የተዋበ ስራህ የጌታ ወቃቢህም ሁለንተናህም የጌታ እንዴት የገንዘብ ስስት አድሮብህ እንዳንት ያለ ሰው ጫኝ ለመሆን ይመኛል?” አለና ተናገረው።

ዋህድ ግን ዝም ብሎ ሰምቶ ሲጨርስ “ጌታየ ኧረ የገንዘብ ስስት አድሮብኝ አይደለ። የኔን መከራ የኔን አይቶ ማጣት ቢሰሙ ባልፈረዱብኝም ነበር” አለ። ባለቤቱም አንስቶ “እስቲ ዋይህን ንገረኝ ሰው የላዩን አይቶ ይፈርዳል እንጂ የውስጡን ያውቅ ዘንድ አይቻለውም። ስለዚህ እኔም ሳላውቅ አጥፍቸ ይሆናልና ንገረኝ” አለው።

ቀጥሎም ያው ሀብታም “እስኪ ለሁሉም ነገር በቅሎየን ጫንልኝና ወደ ውጭ እንሂድ” አለው። ዋህድም ባንድ አፍታ በቅሎውን ጫነለትና ሁለቱም አብረው ወጡ። ከድንኳኑ ጥቂት እንደራቁ ባለቤቱ “በል እስቲ የመከፋትህን ነገር አጫውተኝ” አለው። ዋህድም ግራ ክንዱን ባለቤቱ ከተቀመጠባት በቅሎ ከደሀራዩ ላይ ጣል አርጎ በግሩ እየተከተለ ጌትዮው እያሰገረ እንዲህ ብሎ የሀዘኑን ታሪክ ጀመረለት።

“ጌታው የደህና ሰው ዘር ያሉኝም እውነትዎ ነው። የደጃዝማች ልጅ ነኝ በመዓርግ በጌትነት እኖር ነበር። ነገር ግን እርስዎም እንደሚያውቁት የእስላም ጦር መጣ በተባለ ጊዜ ንጉሣችን ባዋጅ አስከትቶ ባራት ደጃዝማቾች እግር አሳዝዞ ተዋጋ ብሎ ጦሩን ሰደደ። ከነዚያ አራት ደጃዝማቾች አንዱ የኔ አባት ነበረ።

እስላሞቹና ክርስቲያኖቹ በተዋጉም ጊዜ እግዚአብሔር ሳይል ጊዜ ድሉ የእስላም ሆነ። ሰውም የሞተው ሞተ የተማረከውም ተማርኮ ተሸጠ። ካራቱ ደጃዝማቾችም ሶስቱ ከጦርነቱ ሞቱ። የኔ አባት ግን ተማርኮ እንደባሪያ ተሸጠ። አሁን ግን ያ የገዛው እስላም ገና ጌታ ሳይሆን አይቀርም ብሎ ቀለሙን አይቶ ጠርጥሮ ‘እልፍ ወቄት ወርቅ አምጣና ልልቀቅህ አለው’ ሲሉ ወሬ ደረሰልነ።

እሄን ወሬ በሰማነ ጊዜ በናቴም በቴም በኔም እጅግ የመረረ ሀዘን ገባብነ። አምጣ ያለውን ገንዘብ ሰደን እንዳናስለቅቀው እሄን ያህል ወርቅ ከጃችን የለ። ደግሞም አባቴ ጥንቱም ቢሆን መስጠት መለገስ ያውቅ ነበር እንጂ ገንዘብ መቈጠብ አያውቅም ነበርና ገንዘብ ወዴት እናገኝ አሁን? ንጉሡ ሰጥቶ እንዳያስፈታው እንደሚያውቁት በሀዘን ሞተ። አገር ጠፍቶ ሰዉ አልቆ ከብቱ ተነድቶ ክምሩ ተቃጥሎ ገንዘብ ወዴት ይገኝ?

አሁን ቅጡ ቢጠፋነ እቴ ቅጠል እያበሰለች እንበላለን። እናቴ የሙያ እየፈተለች እኔ ሎሌነት ገብቼ ገንዘብ አጠራቅመን ተቀን ብዛት አባቴን ለማስለቀቅ ተስፋ አድርገን እሄው እንደሚያዩኝ ለጌታ አዳር መጣሁ። እኔንስ ደስ የሚለኝ የነበር እኔው ሄጄ ባባቴ ስፍራ ተተክቼ እኔው ባሪያ ሁኜ አባቴ ወዳገሩ እንዲመለስ ማድረግ ነበር። አባቴ እጅግ አሳምሮ ከብክቦ ተጨንቆ አሳደገኝ። እኔም በዚህ ጊዜ ስለሱ እኔው ባርያ ሁኜ ወረታውን ብከፍል ደስታየ ነበር። ነገር ግን እናቴ ‘ባባትህ መከራ ሳለቅስ አንተ ደግሞ ሂደህ ታባትህ ጋራ ባርያ ሁነህ ትቀርና በመከራ ላይ መከራ ይጨመርብኝ’ ብላ እንዳልሄድ ከለከለችኝ በቄስ አስገዘተችኝ። አሁንም እሄውልዎ ጌታየ ከዚህ ያደረሰኝ የሰው ሎሌነት ያስመኘኝ እሄ ነው ነገሩ አይፍረዱብኝ” አለና ነገሩን ጨረሰ።

ያው ሀብታም ነጋዴም እያዘነ የዋህድን ታሪክ አስተውሎ አዳመጠና ሲጨርስ “እኔ ጉዳይ አለብኝና ወደ ድንኳኔ እመለሳለሁ አንተም ወደ ቤትህ ተመለስ። እግዚአብሔር ይሁንህ” አለና ነጋዴ መቸም ለምናልባች ከጁ ገንዘብ አይለይምና ይዞት የነበረውን ገንዘብ እስተቀረጢቱ ተጁ ላይ ጣለለት። ሳይለያዩ በፊት ግን ያው ሀብታም ለዋህድ “ያባትህ ስም ማነው? የገዛውስ አረመኒ ማን ይባላል? ያለበት አገርስ ወዴት ነው?” አለና ጠየቀ።

ዋህድም ያን ቀረጢት ወርቅ እንደሞላበት በጁ እንደያዘ ደስ ብሎት ከንፈሩም እየተንቀጠቀጠ አንደበቱም እየተርበደበደ ያባቱንም ስም የገዛውን አረመኒ ስሙን እስተቦታው እስከምልክቱ ነገረውና ሁለቱም ተለያዩና እየስፍራቸው ሄዱ። ዋህድ ግን ያላሰበውን ሲሳይ በድንገት ሲያገኝ ጊዜ እጅግ ደስ አለውና እንኳን የዚያን ለጋስ ስሙንና አገሩን ለመጠየቅ እግዚአብሔር ይስጥህ ሊለው አላደረሰውም እንዲያው ወደ ቤቱ ከነፈ።

ነገር ግን ከዚያ ለጋስ ሰው ፊት የተቀበለውን ለማየትና ለመቍጠር አፍሮ አላየውም ነበርና ወዲያው እንደተለያዩ አንድ የሚሸሸግበት ቍጥቋጦ መሳይ ባየ ጊዜ ዋህድ የቀረጢቱን ወርቆ ቶሎ ከሸማው ላይ ዘረገፈና ሲቈጥር ጊዜ ፵ ወቄት ወርቅ አገኘበት። በዚህ ጊዜ ይልቁንም በደስታው ላይ ደስታ ተጨመረለትና እየፈነደቀ ሲሮጥ ሲሮጥ ከቤቱ ገባና ለናቱና ለቱ ወስዶ ያን ወርቅ ሆጭ አደረገላቸው ነገሩንም ሁሉ ነገራቸው።

እናቱም እቱም ነገሩን ሰምተው የነጋዴውንም ደግነት የተሸጠውን ሰዋቸው የመለቀቁን ነገር ባሰቡ ጊዜ በደስታም ይሁን በሀዘን በንባ ይታነቁ ጀመር። ያው ሀብታም ነጋዴ ጥንቱንም ዋህድን በቅሎየን ጫንልኝ ተከተለኝ ማለቱ ድንገት የሚረጥቡት ሰው እንደሆነ ለሱም ለመርጠብ ምክንያት እንዲሆነው ለተቀባዩም ሳያገለግል አለስበብ መቀበሉ ውርደት እንዳይሆንበት ብሎ ነበር።

ሁሉም ሆኖ ግን ይኸው የተገኘው ገንዘብ አባታቸውን ለመለቀቂያ አምጣ ታለው ወርቅ አይደርስምና በጐደለው ለመሙላት እናቲቱም ጦቢያም ዋህድም እንደፊተኛቸው ሁሉም እያሳባቸው ገቡ። ሁሉም እየተግባራቸው ይውሉና ማታ ማታ ያን ቅጠላ ቅጠላቸውን ለመብላት ይጠራቀማሉ።

(በክፍልሁለትይቀጥላል)

.

አፈወርቅ ገብረየሱስ

1900 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ልብወለድ ታሪክ”። ፲፱፻ ዓ.ም። ገጽ ፩-፲።

4 thoughts on ““ልብወለድ ታሪክ” (ጦቢያ)

አስተያየት ለመስጠት