“ቆይታ ከሌሊሳ ግርማ ጋር”
(ቃለመጠይቅ)
.
[ከአንድምታጋርየተደረገውይይት]
.
[ሌሊሳ ግርማን አብዛኞቻችን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ባቀረባቸው አጫጭር ልብወለዶቹ እናውቀዋለን። ከዛም ባሻገር በርካታ የልብወለድ እና ወግ አዘል መጣጥፍ ድርሰቶችን በመጽሐፍ መልክ አቅርቦልናል። ባለፈው ዓመት መገባደጃም “እስቲሙዚቃ!” የተሰኘ 38 አጫጭር ታሪኮችን የያዘ አዲስ የልብወለድ መጽሐፍ አሳትሟል። አንድምታ ሌሊሳን በቅርቡ በሥነጽሑፍ ዙርያ አነጋግራው ነበር።]
.
በልጅነትህምንአይነትመጻሕፍትንታነብ ነበር?
መጀመሪያ እናታችን ልጅ ሳለን ብዙ ተረት ታወራልን ነበር። … እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ከትምህርት ውጭ ምንም ንባብ ስለማድረጌ አሁን ትዝ አይለኝም። … ምናልባት ብዙ ስዕል ያለባቸው የተረት መፅሐፍት አገላብጬ ሊሆን ይችላል። … አራተኛ ክፍል በአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ መፅሐፍት ከት/ቤቱ ላይብረሪ እየወሰድን ማንበብ እና ያነበብነውን ለአስተማሪው ማስረዳትን የሚጠይቅ መርሐ ግብር ተጀምሮ ነበር። ምናልባት ያኔ ነው የአማርኛ መፅሐፍትን ማንበቡ የጀመረው ወይንም የቀጠለው። .. የተማርኩት የግል ትምህርት ቤት ስለነበር በሳምንት አንድ ፔሬድ በላይብረሪ ውስጥ መፅሐፍ ወስደን ለአርባ አምስት ደቂቃ የመረጥነውን መፅሐፍ ስናገላብጥ ለመቆየት እንገደድ ነበር።
… አዎ እንገደድ ነበር ነው ያልኩት። ብዙ ስዕል ያለበትን መፅሐፍ ቀድሞ የያዘው ብዙም ሳይሰለቸው ፔሬዱን ያጠናቅቃል። “ጣፋጭ ታሪክ” የሚባል መፅሐፍ ትዝ ይለኛል። ታሪኩ የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው። መፅሐፉ ላይ ያሉ ስዕሎች በጣም ይመስጡኝ እንደነበር እንጂ መፅሐፉ ውስጥ ያለው ንባብ ላይ ብዙም አልተሳተፍኩም።
… እኔ ከንባብ ጋር በእውነት ትውውቅ የጀመርኩት በት/ቤት ሳይሆን በቤቴ ነው። መንስኤውም አባቴ ነበር። አባቴ መሀንዲስ ቢሆንም ከራሱ የሞያ ክልል ውጭ በብዙ ዘርፍ ላይ የእውነተኛ ንባብ ያደርግ የነበረ ሰው ነው። በፊት ብቻ ሳይሆን አሁንም በሀይል በማንበብ ላይ ይገኛል። (ስድስተኛ መፅሃፉን በቅርቡ አሳትሞአል)
… አባቴ መፅሐፍ ሲያነብ እና የአባቴን “ጥናት ቤት” (Library) የማይጨምር የልጅነት የመጀመሪያ ትዝታ የለኝም።
ስለዚህ፤ አባቴ አራተኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ላይ ለእኔ ለወንድሞቼ እና እህቴ አንዳንድ መፅሐፍ መርጦ ሰጠን። ለእኔ የመረጠልኝ የአንቶኒ ሆፕን “The Prisoner of Zenda” ነበር፤ ትዝ ይለኛል። … የመረጠልንን መፅሐፍ ጮክ ብሎ እያነበበ ይተረጉምልናል። ለእያንዳንዳችን ከተመረጠው መፅሃፍ ላይ አንድ አንድ ምዕራፍ … በየእለቱ። አነባበቡ እና ቃላቱን የሚተረጉምበት መንገድ በፍፁም ከአእምሮ የሚጠፋ አይደለም። … እሱ ማታ ያነበበልንን ቀን ስንደግም እንውላለን። ወደፊት ገፍተን ለማንበብም እንሞክራለን። ያልገባንን እሱ አቃንቶ እንደገና ማታ ይቀጥላል። መፅሐፉ ተነቦ እስኪያልቅ ድረስ። መፅሀፉ በአባቴ እና በእኔ ትብብር ተነቦ ሲያልቅ ከወንድሞቼ እና እህቴ ጋር መፅሐፍ እንለዋወጣለን። … መፅሐፍቱ ለጀማሪ አንባቢዎች ተብለው አጥረው የተዘጋጁ (Abridged) ናቸው። ብዙዎቹ “Longman’s series” የሚያዘጋጃቸው ነበሩ።
ብቻ ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል እነዚህ አይነት መፅሐፍትን ሳላውቀው ብዙ አንብቢያለሁኝ። (The Coral Island, Round the World in Eighty Days, Treasure Island, The Lost World, Beau Geste, The Thirty Nine Steps…ወዘተ)
በተለይ “Montezuma’s Daughter” ራይደር ሀጋርድ በሚባል ደራሲ የተፃፈው … ትዝ ይለኛል። … የአባቴ … ሌላ ጊዜ ደግሞ የአጎቴ … የመተረክ እና የማስረዳት አቅም ባይታከልበት እነዚህን መፅሐፍት ወደ መውደድ አልደርስም ነበር።
ከፍ እያልኩ ስመጣ ሙሉ ፊክሽኖችን ማንበብ ጀምሬአለሁ። ወደ እነ አጋታ ክሪስቲ … እና ሸርለክ ሆምስ … ምናምን። … ሰው ትምህርቱን ነበር የሚያጠናው እኔ ፊክሽን ነበር የማነበው።… እነ ሉድለምን … እነ ሀሮልድ ሮቢንሰን። በኋላ ደግሞ “Western” (Cowboy) ድርሰቶችን ወደ መጨፍጨፍ ገባሁ። … ቤት ውስጥ Zane Grey የሚባል ደራሲ የተቆጣጠረው ሼልፍ ነበር (አሁንም አለ)።
… አሁን ይገርመኛል እንዴት እነዛን መደዳዎች ሁሉ በዛው ዘመን ጨርግጄ እንደጨረስኩኝ። አሁን በምንም አይነት ያንን ያህል ፊክሽን ደግሜ ለማንበብ አልችልም። … በዘመኑ የሚወጡ የአማርኛ መፅሃፍትን ከእንግሊዘኛው እኩል ነበር የማነበው። “ሳቤላ” እና “East Lynne” ጎን ለጎን ማንበቤ ትዝ ይለኛል። አማርኛው ከእንግሊዘኛው ተሽሎኛል። በሁለቱም ቋንቋ … መፅሐፉ እኔን አላስለቀሰኝም። … ምናልባት ማልቀሴ እንደማይቀር ቃል ስለተገባልኝ ሊሆን ይችላል። …
… ትርጉመ ቢስ ከሚመስል ድራማ እና አድቬንቸር እየወጣሁ ስመጣ A.J Cronin የሚባል የአየርላንድ ደራሲ ተቀበለኝ። …. መጀመሪያ “Hatters Castle” በሚል ጨለምተኛ ድርሰት ነው የተዋወቅሁት።
ስለመጀመሪያ የድርሰት ሙከራህ ምን ትዝ ይልሃል?
የድርሰት ሙከራዬ ከሀያ አመቴ በኋላ በግጥም ነው የጀመረው። በእንግሊዘኛ ግጥም። ከመጠን ያለፈ የቪክቶሪያዊ ገጣሚዎችን ስራ አመነዥግ ነበር። የነ ቴኒሰንን፣ የነ ኪፕሊንግን፣ የነ ብራውኒንግን … የነ ኬትዝን …
ስለዚህ የእነሱን የመሰለ ግጥም መፃፍ ጀመርኩኝ። ሀሳብ እና ስሜት ማብቀል ብቻ ሳይሆን ያንን የማንፀባርቅበት መንገድ ያገኘሁ መሰለኝ። ብዙ እስክፅፍ ለማንም አላሳይም ነበር። በኋላ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ጓደኞች ሳገኝ መናበብ ጀመርን። የእነሱን ሙከራ ማንበብ የእኔንም ማስነበብ። አንዲት ግጥም የኢትዮጵያን ኤርላይንስ የአብራሪዎች ምርቃት በማስመልከት በተዘጋጀ መፅሔት ላይ ወጣችልኝ። ከዛ የልብ ልብ ተሰማኝ። … ግጥሞቼን ይዤ የእንግሊዘኛ ጋዜጦች ላይ መሄድ ጀመርኩኝ። ”The Sun” የሚባል ጋዜጣ ብዙ ግጥም እንዳወጣልኝ ትዝ ይለኛል። … ከግጥሞቹ በኋላ የእንግሊዘኛ አጭር ልብ ወለዶችን መሞከር ያዝኩኝ። … የአጭር ልብ ወለዶቹ እስካሁን በህትመት ተፈትነው አያውቁም።
… ከዛ የመፃፍ ግፊቱ እና ፍላጎቱ እየጨመረ መጣ። በመምጣቱም የተነሳ ሌላ አይነት ተግባር ወይንም እንቅስቃሴ ሁሉ ትርጉም የሌለው ይመስለኝ ጀመር። የሙሉ ሰአት ፀሀፊ መሆን አለብኝ ብዬ ቆረጥኩኝ። … ተው ቢሉኝም ልተው አልቻልኩም። … አማርኛን ለመፃፍ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረኩት ጋዜጣ ላይ ፅሁፍ በማውጣት ለመተዳደር ስወስን ነው። … መጀመሪያ የእንግሊዘኛ አጭር ልብ ወለዶችን ወደ አማርኛ በመመለስ ጅማቴን አጠነከርኩኝ። የቋንቋ አቅሜን ከፍ አደረግሁኝ።… ከዛ መጣጥፍ ወደ መፃፍ ገባሁኝ። ከመጣጥፉ በኋላ አጭር ልብ ወለድ መፃፍ ጀመርኩኝ። አማርኛ ላይ የምፅፈው ፅሁፍ ሲበዛ እንግሊዘኛ ላይ የጀመርኩት ፅሁፍ እያሽቆለቆለ ሄደ። … አለማቀፍ ፀሀፊ ለመሆን ያለኝ ህልም ሀገራዊ ፀሀፊ በመሆን ተቋጨ።
ወደአጭርልብወለድ ድርሰትየበለጠለማተኮርለምንወሰንክ?
… የአጭር ልብ ወለድን ቅርፅ እወደዋለሁኝ። ከድሮውም አጭር ድርሰቶች ተተርጉመውም ሆነ በወጥነት አግኝቼ ሳነብ በጣም ደስ ይሉኛል። … ያው ማንም ፀሀፊ እኮ ማድረግ የሚቀለውን እና የማይችለውን ያውቃል። የሚቀለውን ብቻ ሳይሆን ከእሱ ፍላጎት ጋር የሚሄደውን ሚዲየም ይመርጣል።
እኔ ደግሞ በአማርኛ ግጥም ከመፃፍ አጭር ልብ ወለዱ ይቀርበኛል፤ ግዛቴ ይመስለኛል። … ማለት የምፈልገው ሀሳብ ወይንም ስሜት በልብ ወለድ ቅርፅ ተቀምጦ ይታየኛል። … በብዛት የማይገኝ ብርቅም ይመስለኛል። እና መፃፍ ፈልጌ ብዕር ስሰነዝር በቀላሉ ምናባዊ እና አጭር ፅሁፍ ይሆንብኛል። መሆኑንም አልጠላውም። እኔ ባነብ የምወደውን አይነት ፅሁፍ ብፅፍ ደስ ይለኛል እንጂ አይከፋኝም። ምናልባት ወደፊት ከሰለቸኝ ላስወግደው እና ሌላ አይነት አማራጭ ለመፈለግ ልወጣ እችላለሁኝ።
የአዲሱመጽሐፍህየአጻጻፍሂደትምንይመስልነበር?
የአፃፃፌ ሂደቴ ጋዜጣ ፅሁፍ ሳዘጋጅ እንደማደርገው በቀን ቢያንስ አንድ ሺ ቃላት ቢበዛ ሁለት ሺ ቃላት በመፃፍ ነው። በእኔ እጅ ፅሁፍ በልሙጥ ወረቀት ላይ የሚከናወን ነው።
የሁሉም ገፀ ባህሪዎች መነሻ ፤ ከአብዮቱ በኋላ የተወለዱ የእኔን ዘመን ተጋሪዎች እና የከተማን መቼት የሚመለከት ነው። እነዚህ ገፀ ባህሪዎች ምናልባት በእውቀቱ “የተካደ ትውልድ” የሚላቸው አይነት መሆናቸው ነው። የተለያየ ርእዮተ አለም እና የተለያ ሱስ የተቀባበላቸው ናቸው።
“ኤስ” የተሰኘው ገጸባህሪ የዚህ ትውልድ ተወካይ ነው። ሁሉንም ነገር ለመሞከር የሚደፍር እና በሞከረው ነገር ላይ ሁሉ ብልጫ የሚያሳይ … ዘመኑ ከነፈገው በላይ የሚፈልግ የጂኒየስ አዝማሚያን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያሳይ ገፀ ባህርይ ነው። “እሸቱ” የተሰኘው ገጸባህሪ ደግሞ ደራሲ ነው። እሸቱ ኤስን ይፅፈዋል አንዳንድ ቦታ። ሌላ ቦታ ኤስ ስለ ራሱ በአንደኛ መደብ ተራኪ ይናገራል። እሸቱ ኤስን ሲፅፈው የራሱን እምነት እና ፍላጎት ያላክክበታል።
የኤስን ታሪኮች መፃፍ የጀመርኩት ሁለት ሺ ሰባት መጀመሪያ ላይ ነው። እያንዳንዱ ታሪክ በአንድ ቀን ይፃፋል። ከእያንዳንዱ የእለት ታሪክ ጋር አንድ vignette (ገላጭ ሀረግ) በታሪኩ አናት ላይ አስቀምጫለሁኝ። ቪኜቱ ከታሪኩ ጋር ግንኙነት የለውም። አንድ ሀሳብ ወይ ምስል ወይንም ሌላ ቅንጭብ የፈጠራ አጋጣሚን የሚያሳይ ነው። ቪኜቶቹ ከ ኤስ ታሪኮች ጋር ግንኙነት የላቸውም። ወደ ሁለት ወር አካባቢ ብዙ የኤስ ታሪኮችን ፃፍኩኝ። እያንዳንዱ እለታዊ ፅሁፍ አጭር ልብ ወለድ እንዲሆን አቅጄ ነው የፃፍኩት። ሁሉም ታሪኮች በራሳቸው የሚቆሙ እና ከሌላ መሰላቸው ጋር በመጠነኛ ምልክቶች የሚገናኙ እንዲሆኑ ነበር የወጠንኩት።
ሁለት ወር ከፃፍኩት በኋላ ብዙም አካሄዱ አላማረኝም። የኤስን ታሪክ ለመፍጠር የእኔን ግለታሪክ በጣም እየታከኩ እንደሆነ ሲገባኝ አቆምኩት። ብዙ ገፅ ከተፃፉት የተወሰኑትን ብቻ መርጬ ሌላውን አስቀመጥኩት። ይመስለኛል … ሀሳብ ነበር ያጠረኝ። ይሄንን ካራክተር (ኤስ) የሚሸከም ሀሳብ ስላላገኝሁ ተውኩት።
ግን ልቦለዶቹ መጀመሪያ እንዳሰብኩት ሳይሆን … ማለትም ኤስን የሚከተሉ ሳይሆን … በኤስ ዙሪያ የሚካሄዱ በመሆናቸው እንደ ነጠብጣብ የተፈነጣጠሩ ናቸው። ነጠብጣቦቹን ገጣጥሞ የሚያይ ሰው፤ ስለ ኤስ እና እሸቱ ሳይሆን ስለ ዘመኑ መንፈስ አንዳች ምስል ሊያገኝ ይችላል። የሚያገኘው ምስል ግን፤ እንደ አብስትራክት ስዕል መልሶ ፍንጥርጣሪ ነጠብጣብ ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል። ይሄ ነው የመፅሀፉ ጥቅል ትልም።
አንዳንዶቹ የ“እስቲ ሙዚቃ“ መፅሐፍ መሰረታዊ መያያዣዎች ከመፅሐፉ ውጭ የሚገኙ ናቸው። … እንዲሁ ሌሎች አያያዥ ታሪኮች ደግሞ በመፅሀፍም ላይ ያልሰፈሩ፤ በወረቀት ከፃፍኳቸው በኋላ ንቄ ያስቀመጥኳቸውም አሉ። ለምሳሌ “Ace” የሚል አንድ አጭር ልብወለድ የሆነ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ መፅሀፍ ላይ ግን ያላካተትኩት አለ።
ምስሎቹ እንደ ጂግ ሶ ፐዝል ግጥምጥም እንዲሉ የታቀዱ አይደሉም። በአንድ እርምጃ እና በሌላው መሀል ክፍተት እየተውን እንደምንራመደው ሁሉ የኤስ ታሪኮችም በቂ የእርምጃ ዱካ እየተዉ … ግን በእየዱካው መሀል ባለው ክፍተት ከአንድ መቼት እና ጭብጥ ወደ ቀጣዩ የሚሻገሩ ናቸው። የጥቅል ታሪኩን “Tip of the Iceberg” ብቻ እንዲያሳዩ እንዲሆኑ ሆን ተብለው የተቀረፁ ናቸው።
እያንዳንዱ ታሪክ ራሱን ችሎ የሚቆም … ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዘመን መንፈስን በማሳየት ለጥቅሉ መቼት እና ጭብጥ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው።
“ኤስ” ስለተሰኘውገጸባህሪእስቲጥቂትብትለን …
“እስቲሙዚቃ” ላይ በጥቂቱ ማየት የሚቻለው ኤስ የስምንት አመት ልጅ እያለ የተከሰተውን አጋጣሚ ነው። አጋጣሚውን የሚተርከው እሸቱ ወይንም ሌላ ሦስተኛ ሰው ሊሆን ይችላል። ኤስ አዋሽ ሰፈርን በእናት እና አባቱ ጥል ለመልቀቁ የመነሻውን ምክንያት መጠነኛ ምስል የሚሰጥ ታሪክ ነው።
“የምርጥ ውሻ አጭር ታሪክ” የሚለው ደግሞ እሸቱ የኤስን ማንነት/እምነት ከአሳለፈው ታሪክ ጋር በግርድፉ የሚናገርበት ነው ማለት ይቻላል። ታሪኩ ላይ ኤስ ከልጅነት ጉጉቱ እስከ ተስፋ መቁረጫው ዘመን … ገጣሚ የመሆን ፍላጎቱን እስከሚያጣበት ከወፍ በረር የሚያስቃኝበት ነው።
ኤስ ከእናት እና አባቱ መለያየት በኋላ እናቱን ተከትሎ ለመኖር እንደሄደ “ማህሌት” በምትባል ልጅ ከትምህርት ገበታው ከተሰናበተ በኋላ ባለው አመት ቴክኒሻን ሆኖ ነበር።
“እየሱሳዊ ሽጉጥ” የተሰኘው ታሪክ ሞትን መናቅ የጀመረበትን አጋጣሚ ለማሳየት የሚጥር ነው። “ሰው ሲሸነፍ” በሚለው ታሪክ ኤስ ራሱን ለመግደል ሲሞክር ይታያል። ግን ሳያደርገው ይቀራል። ኢትዮ-ኤርትራ የጦርነት ግጭትን ተከትሎ ጦር ሜዳ እውነተኛውን ሞት ለመሻት ወይ ለማሽተት ይሄዳል።
ተመልሶ ሲመጣ ተለውጦ ነው። ከደራሲው እሸቱ ጋር የሚተዋወቁት ይሄኔ ነው። ትውውቃቸውን የሚያሳየው የታሪኩ ክፍል ግን “እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች” የሚለው መድብል ላይ ሳይሆን ያለው “አማሌሌ እና ሌሎች” የሚለው መፅሀፍ ላይ ነው።
ይህንልዩገጸባህሪበሌሎችድርሰቶችመልሰህታቀርበውይሆን?
“ኤስ“ ራሱን ችሎ እንዲከሰት አንድ ታላቅ እምነት ወይንም ሀሳብን ሰንቆ መምጣት መቻል ይኖርበታል። ይሄንን እምነት ወይንም ሀሳብ ደግሞ ደራሲው (እኔ) ከገፀባህሪው ቀድሜ ማግኘት ይኖርብኛል። ያገኘሁ ለት ኤስ የተባለውን ገፀባህርይ ይሄንን ተልዕኮ ሰጥቼ እመልሰዋለሁኝ።
አሁን በተደጋጋሚ “እስቲ ሙዚቃ”ን ባገላበጡ አንባቢዎች የሚሰነዘረው አስተያየት … ኤስ አፈንጋጭ ገፀባህርይ ነው። የብዙሀኑን አንባቢ ወይንም የማህበረሰብ ድምፅ የሚወክል እንዳልሆነ ነው የምሰማው። “Weird” ነው። ስለዚህ ሙሉ ወጥ መፅሀፍ ይሄንን አፈንጋጭ ገፀባህርይ ያለ ግብ ቀርፆ ማንከራተት … ለገፀባህርይውም ሆነ ለአንባቢ ትርፍ ያለው አይመስለኝም።
ወጥ የሆነ አላማ እና እምነት ሲገኝ ግን ገፀባህርይውን ወልውዬ እንደገና እንዲመለስ ለማድረግ እሞክራለሁ።
ለወደፊት ምንአይነትሥራዎችንለማቅረብአቅደሃል?
የሚቀጥሉት አመታት የምሞክረው ወጥ የልብወለድ ድርሰትን ለማሳካት ነው። የአጭር ልብወለድ ፀሀፊ በመሆኔ ወደ ረጅም ልብወለድ መሻገር … እንደ መመኘት ቀላል አይሆንም። ግን በቂ ሰላም እና የፈጠራ ፀጥታ ካገኘሁ ይሄንን ግብ ለማሳካት ነው ምኞቴ። ወግ፣ አጭር ልብወለድ እና መጣጥፍ መፃፌን ጎን ለጎን እቀጥላለሁ። የፃፍኩትን የሚቀበል ጋዜጣ ካገኘሁም አትሜ አስነብባለሁኝ።
ለሁሉም ግን የኑሮ እና የፖለቲካ ሰላም መኖሩ ለእኔ ለፀሀፊውም ሆነ ለአንባቢው ቁልፍ ጉዳይ ይመስለኛል።
.
ሌሊሳ ግርማ
(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)
ጥቅምት 2010 ዓ.ም
.
ahun lemin yeLelisan tshufoch endemwedachew gebtognal.
yebizu nebab wuTetoch selehonu new.
Arif interview new indehulgizew
LikeLiked by 1 person