“ጦር አውርድ” (ልብወለድ)

“ጦር አውርድ”

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

.

… ከዘመናት ባንዱ ዘመን የሀበሻ መዲና በነበረችው አክሱም በጐረቤቶቿ በኑብያና በየመን ሰላም ነገሠ … ይልቁንም በአክሱም ብልፅግና ሰፈነ፤ ሁሉም እንጀራና ወይን ጠገበ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከተመሰገኑት ያክሱም ሊቃውንት አንዱ ንጉሡ በተገኙበት ጉባኤ ‘ልቦናዬ ያሳየኝን ልናገር’ አሉ።

ተፈቀደላቸው።

“ግርማዊ ጃንሆይ” አሉ ባማረ ድምፃቸው … “ግርማዊ ጃንሆይ አክሱም የምትገኝበት ሁኔታ ለረጋው ሕሊናየ ሥጋት ፈጥሮብኛል፤ ይሄ ሥጋት ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ወገኖቼ መጋባቱ አይቀርም።”

“ምንድን ነው የሥጋትህ ምንጭ?” አሉ ንጉሡ።

ሊቁ ማብራራት ጀመሩ።

“እንደምናየው በመንግሥታችን ሰላም አለቅጥ ሰፍኗል … የባሩድ መዓዛ ከሸተተን ብዙ ዘመን ሆነን … የሽለላ የፉከራ ዜማዎቻችን ተዘነጉ። እረኞቻችንን ስሟቸው … በዜማዎቻቸው ውስጥ የብልግናና የፍቅር እንጂ የጉብዝናና የጀግንነት ስንኝ አይገኝም። ጋሻዎቻችን በተሰቀሉበት ድር አደራባቸው … ጦሮቻችን ዶልዱመዋል … ሀኔዎቻችን ዛጉ … ነጋሪቶቻችን ዳዋ ዋጣቸው … ሰላም ልማዶቻችንና ትውፊታችንን አጠፋብን። ሕንፃ ያለ ጡብ ያለ ጣሪያ ሕንፃ እንደማይሆን እኛም ያለ ነውጣችን ያለ ሽለላችን ያለ ድላችን እና ያለ ሽንፈታችን እኛ አይደለንም።

“ግርማዊነትዎ እንደሚያውቁት አንበሳ ከሚዳቋ ጋር ተኝቶ ማየት ለጊዜው የሚያስደስት ትዕይንት ሊሆን ይችላል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ይሰለቻል። የሁሉም ዓይን አንበሳው ሚዳቆዋን ሲያሳድዳት … ሰብሮም ሲገነጣጥላት ለማየት ይናፍቃል።

“ጃንሆይ … ‘እርግቦች በሰገነቶቻችን ላይ ሰፍረዋል፤ የዘንባባ ዛፎች በጓሮአችን በቅለዋል’ ብለው የሚያዘናጉትን አይስሟቸው! … ብርቱ መንግሥት ከርግቦች ላባ ፍላፃ ያበጃል … ከዘንባባዎች ዝንጣፊ የጦር ሶማያ ይሰራል።

“ለራሳችን ብርቱዎች ነን ብለን እንጃጃላለን … ካልታገሉ ሀቅንም ማወቅ አይቻልም። ጐረቤቶቻችን ከፈገግታቸው ባሻገር ምን እያሴሩ እንደሆኑ አናውቅም። የጐረቤቶቻችን በር ተዘግቷል … በዚህ ምክንያት በእልፍኛቸው ውስጥ ምን እየተሰራ እንደሆነ አናውቅም … የጐረቤቶቻችንን ልክ አለማወቅ በቤታችን ላይ ሥጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል።

“ጃንሆይ! የምንኖረው ፈተና በሌለበት ዘመን ነው። ፈተና የሌለበት ዘመን የተፈጥሮን ሕግ ያዛባል። እስቲ ጐረምሶቻችንን እይዋቸው! … እንደ ሴት ዳሌና ጡት ማብቀል ጀምረዋል … በምትኩ ፂማቸውን ካገጫቸውና ከከንፈራቸው ጠርዝ አርግፈዋል … መዳፎቻቸው ከሐር ጨርቅ ይለሰልሳሉ … እግራቸውን ዘርግተው የባልቴት ተረት በመተርተር ጊዜያቸውን ያጠፋሉ … የደም ቀለም አያውቁም!

“አያቶቻችን ፍላፃ የወጠሩባቸው ደጋኖች የሴት ልጆቻችን የጥጥ መንደፊያ ሆኑ … ስለዚህ የምንለብሰው ሸማ በውርደት አድፏል። ይሄን እድፍ ከደም በቀር የሚያነፃው ምን አለ?”

ንጉሡ ከመኳንንቱ ጋር ይሄን አድምጠው፣ “ታዲያ ምን ይሻላል?” አሉ።

“ኑብያዎችን ለምን አንወጋም?” አሉ ሊቁ።

“ኑብያዎች ምን አደረጉን?”

“ሁለታችንን በሚለየው ድንበር ላይ ዋርካ ተክለዋል!”

“እና ቢተክሉስ?”

“ዋርካዎች እየሰፉ በመጡ ቁጥር የኛን መሬት መውሰዳቸው አይቀርም!”

“እና ምን ይሻላል?”

“እናቅምሳቸው!” አሉ ሊቁ።

“እንበላቸው!” አሉ መኳንንት።

“በሏቸው” አሉ ንጉሡ።

***

ሁኔታዎች ተቀያየሩ።

ሴቶች ቆሎ በማመስ ጭብጦ በማሰናዳት ተጠመዱ። ወንዶች ኢላማ ልምምዱን አጣደፉት። አሮጌ ጋሻዎች ከተሰቀሉበት ወረዱ። ደጋኖች ተወለወሉ። ፍላፃዎች ተሳሉ። የጐበዞች አረማመድ ተለወጠ። የእረኞች የፍቅር ዘፈን አንደበታቸው ላይ ሟሟ።

የደም ቃና ያላቸው ዜማዎች መስኩን ዱሩን ጋራውን ሞሉት። የአክሱም ባንዲራ ከእንቅልፏ ተቀሰቀሰች።

***

ጥቂት ወራት አለፈ።

ከወደ ኑብያ ግድም ደብዳቤ መጣ።

ዛቲጦማርዘተፈነወትኀበንጉሠአክሱም

የየመንሊቃውንትአንድመረጃነገሩንእናንተ አክሱሞች በኛ ላይ ሠራዊት ልታዘምቱ እንደተሰናዳችሁ ሰምተን አዝነናል። ይሁን እንጂ የጠባችን ምክንያት በድንበሮቻችን ላይ የተተከሉት የዋርካ ዛፎች መሆናቸውን በማወቃችን ለሰላም የሚበጀውን አድርገናል። ከዛሬ ጀምሮ ዋርካዎች እንዲቆረጡ ትእዛዝ አስተላልፈናልይቅርታ አድርጉልን!”

የሚታይ ማህተም

ደብዳቤው ከደረሳቸው በኋላ ንጉሡ ሊቁን አስጠሩ።

“ምን ይሻለናል? ኑብያዎች ሳንወጋቸው ዋርካዎችን ቆረጡ! እንግዲህ ምን ሰበብ እንፈጥራለን?” አሉ በቅሬታ።

“ግርማዊ ሆይ!” አሉ ሊቁ “የሰማነው ዜና በእውነቱ የሚያስቆጣ ነው። እንደሚያውቁት ሠራዊት ለማደራጀት ብዙ ገንዘብ ብዙ ጉልበት ብዙ ጊዜ ፈጅተናል። ጐበዞቻችንን ከሙያቸው አፈናቅለን አስታጥቀናቸዋል። ሴቶቻችን ቡሃቃቸውን አሟጠው ስንቅ ሰርተዋል። ይሄ ሁሉ ያለ አንዳች ተግባር ብላሽ መሆን የለበትም ጃንሆይ!” አሉ በመማፀን ድምፅ።

“ታድያ ምን አድርግ ነው የምትለኝ?”

“የዘመቻችንን እቅድ ሰልሎ ለኑብያዎች የነገራቸው የየመን መንግሥት ነው።”

“እናስ?”

“በዚህ ምክንያት የመኖች የኛን ሉዐላዊነት ደፍረዋል። ስለዚህ ለምን ዘመቻውን ወደ የመን አናዛውረውም?”

አማራጭ አልተገኘም።

በማግስቱ አዋጅ ተነገረ፤

ጠላታችን ወደሆነው ወደ የመን ሀገር ዝመቱ። በዚያ ሕያው የሆነውን ሁሉ ፍጁ! … ከተሞቻቸውንም ወደ ፍርስራሽ ለውጡ! …” 

.

በዕውቀቱ ሥዩም

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “በራሪቅጠሎች። 1996 ዓ.ም። ገጽ 76-81።

“የትና የት?” (ግጥም)

“የትና የት?”

ከከበደች ተክለአብ

.

[በደራሲዋ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

.

የትና የት ምኞቴማ

ምኞቴማ የትና የት

የፍላጐቴ ምጥቀት

እንደ መንኰራኩር መጥቆ

ሕዋውን እየዳሰሰ

ግድቡን እያፈረሰ

ተራራን እያፈለሰ

ይብላኝ እንጂ ለአካሌ

ሕሊናዬስ ገሠገሠ

የወዲያኛውን ዓለም

በመዳፎቹ ዳሰሰ።

.

በመዋዕለ እንስሳት

እንደ ኢምንቶች ካኖረው

ማስተዋሉን ዝቅ አድርጎ

ከአራዊት ከደመረው

የሕይወት ክፋይ እንዳይደለ

ከሕይወት ጣዕም የለየው

ጣፋጭ ፍሳሹን አቅርሮ

መራራ አተላ ከጋተው

የሰው አምሳል ሰው እንዳይሆን

ከሰዎች ዓለም ገፍቶ

በደመ ነፍስ ከሚጓዘው

የቦዘ አካል ተለይቶ

ከነባራዊው ሁኔታ

ሕሊናዬ የሸሸበት

የትየለሌ ርቀቱ!

የትና የት! የትና የት!

.

ምኞቴማ የትና የት

ሰው ሊያደርገኝ የቃጣበት

የጠወለገው የተስፋ ዕፅ

በምኞት ካቆጠቆጠ

የተጣለው መጋረጃ

በተስፋ ከተገለጠ

የትና የት! የትና የት!

አካሌ ተወሰነ እንጂ

በነባራዊው ሒደት!!

.

ከበደች ተክለአብ

1977 ዓ.ም

ሐዋይ የእስረኞች ካምፕ፣ ሶማሊያ

.

(በደራሲዋ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “የትነው?”። 1983 ዓ.ም። ገጽ 57-58።

“ሳታመኻኝ ብላኝ” (ወግ)

“ሳታመኻኝ ብላኝ”

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል

.

.

አያ ዥቦ ልጁ ሞተበትና ለነ እንኮዬ አህዩት “ልጄ ሞቷልና አላቅሱኝ” ሲል መርዶ ነጋሪ ላከ።

ተረጅዎቹም “እንግዲህ ሰምተን ብንቀር ይጣላናል ብንሄድም ይበላናል። እንዴት ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ምክር ዠመሩ። ነገር ግን “ቀርተን ከሚጣላን ሄደን ቢበላን ይሻላል” ብለው ተነስተው ልብሳቸውን አሸራርጠው ሄዱ።

ከለቅሶውም ቦታ እንደ ደረሱ አንደኛዋ ብድግ አለችና፣

“ምን አጥንት ቢሆን ይሰብራል ጥርስዎ

ምን ጨለማ ቢሆን እሾኽ አይወጋዎ

ምን ጥቍር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ

ያንን ጐራ ዞሮ ይሰማል ድምጥዎ

አሁን የርስዎን ልጅ ምን አገኘብዎ?” እያለች ሙሾ ታወርድ ዠመር።

እሱ ደግሞ ቀበል አለና፣

“አንችስ ደግ ብለሻል መልካም አልቅሰሻል

ይህ ሁሉ አዘንተኛ ምን ይብላ ብለሻል?” ሲል መለሰ።

እንዳልማራቸው ባወቁ ጊዜ እንግዲህ አለቀቀንም ምን ማድረግ ይሻለናል ብለው እነ እንኮዬ አህዩት ምክር ዠመሩ። አንዲት እናቷ የሞተችባት ውርንጭላ ከነርሱ ጋር ነበረችና ይህችን እንስጥና እንገላገል ብለው ሲነጋገሩ ግልገሏ አህያ ሰምታ፣

“ምነው እኔ ውርንጫ

ማ ይዞኝ በሩጫ” ብላ ተነስታ እልም አለች።

ከዚህ በኋላ ጭንቅ ያዛቸውና መቼስ ምን ይደረግ ለንቦጫችንን ሰጥተነው እንሂድ ብለው ተማከሩ። ወዲያው በል እንግዲህ የላይ የላይ ለንቦጫችንን ውሰድ አሉት። እሱም እንዳመለከቱት ለንጨጭ ለንጨጫቸውን ገነጣጠለና ለቀቃቸው።

በሦስተኛው ቀን ደግሞ እስቲ ዛሬ ሣልስቱ ነውና እመቃብሩ ላይ ደርሰን አያ ዥቦን ጠይቀን እንምጣ ብለው ቢሄዱ አያ ዥቦ ቀድሞ ከመቃብሩ ላይ ሲያለቅስ ደረሱ።

አያ ዥቦም ድዳቸውን ገልፍጠው ባየ ጊዜ፣

“ለካ የኔ ሐዘን ለናንተ ሰርግና ምላሽ ሆኖላችኋልና የኔ ልጅ ትላንትና ሞቶ ዛሬ እናንተ እየተሳሳቃችሁ የመጣችሁት በምን ምክንያት ነው?” ብሎ ተቆጣና ለወገኖቹ “ኧረ በሉ አንድ አንድዋን እየዘረጠጣችሁ ጣሉልኝ” አላቸው።

ከዚህ በኋላ የዥብ ወገን ያህያን ልጅ እየገነጣጠለ ጣለ ይባላል።

“አያ ዥቦ ሳታመኻኝ ብላኝ”

.

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል

.

[ምንጭ] – “እንቅልፍ ለምኔ”። 1952 ዓ.ም። ገጽ 43-44።

 

“ግማሽ 1/2” (ልብወለድ)

“ግማሽ 1/2”

በሌሊሳ ግርማ

.

[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]

.

.

በአራቱም መአዘን ግንቡ ላይ ዓይኑ ስንጥቅ ፈልጎ ያገኘው በአንዱ በኩል ብቻ ነው። ስንጥቁ በግድግዳ ጠርዝ ላይ ቢሆን ኖሮ ቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር ለማየት በቀለለው ነበር። ግን አልሆነም። አልተመቸም። ስለዚህም በአንደኛው ግድግዳ ላይ በተገኘው ትንሽ ሽንቁር ወደ ውስጥ ተመለከተ። የሚታየውን ለማየት።

ዓይኑ ያረፈበት ነገር ሁሉ ግማሹ ብቻ ነበር የሚታየው። የአልጋው ግራ ግማሽ፤ የሶፋው ጀርባ ግማሽ፤ የሚስትየው ግማሽ እግር – ትከሻ፣ በግማሽ እጅ የሚበጠረው የሚስትየው ፀጉር፣ ግማሽ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው የሕንድ ማርያም ስዕል ግማሽ። እማይንቀሳቀሱት ህይወት አልባ የሆኑት ነገሮች በሙሉ በስንጥቁ ዓይን ሲታዩ ዘላለም ግማሽ ሆነው እንደቀሩ ግልፅ ነው። ሙሉ እንዲሆኑ የግድግዳው ስንጥቅ ዓይን ወይ መስፋት አለበት አለበለዚያ ሌላ የተመቸ ቦታ ላይ ሄዶ መሰንጠቅ አለበት።

ለነገሩማ ከቤቱ ውጭ ሆኖ የሚያየው ዓይንም ከሁለት ዓይኑ በግማሽ ነበር እያየ የነበረው። የሚታየው አለም ግማሽ ጎዶሎ ሆኖት ተንከራተተ። ግድግዳ ላይ ያለው ስንጥቅ፣ የኔን ጽናት ይስጥህ ብሎ የመከረው መሰለውና ዓይኑ ለጽናት ልክ ሰውነት ክብደቱን ከአንዱ እግር ወደ ሌላው አስተላልፎ እንደሚያርፈው፤ አይኑም ከአንዱ አይን ወደ ሌላው ትዕግስቱን አቀያይሮ፣ እንደገና በሽንቁሩ ውስጥ አሳልፎ ወደ ቤቱ ውስጥ ማየቱን ቀጠለ። ሽንቁሩ ግን የሚያሳርፈውም ክብደት የሚቀያይረው ዓይን ስለሌለው፣ እንደ አሳ አይን ሁሌ በማይዘጋ ብሌኑ ውስጥ ሌላ ዓይን ሲሰልልበት ያለ ተቃውሞ ተባበረ።

በዛ ሁሉ ነገር ግማሽ በሆነበት ክፍል ውስጥ፣ አንድ የሆነች ነገር እየቦረቀች በግማሹ አልጋ፣ በግማሽ ሶፋ እና በግማሽ ሚስት መሀል ገብታ ሙሉ ስትሆን፣ በዚህ ሙሉ ነገር ደስታ ሙሉነቷን ለማድነቅ ዓይኑን የተቻለውን ያህል ከፈተ። ግን ዓይን ብቻ ስለሆነ ቤቱ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር መስማት አይችልም ነበር። የግድግዳውም ሽንቁር በዚህ ረገድ ሊተባበረው አልቻለም። ወይንም አልፈለገም።

ልጅቷ እናቷን የሆነ ነገር እያለቻት ነበር። ትንሽ ቆይቶ እናትየው በግማሽ እጇ ስታበጥረው የነበረውን ግማሽ ፀጉሯን ማበጠሪያውን እላዩ ላይ ትታ፣ ሌባ ጣቷን እጇ ላይ እያውለበለበች ቆይታ መልሳ ግማሽ ሶፋ ላይ ፀጉሯን ነስንሳ ማበጠር ቀጠለች።

የልጅቷ ፊት ላይ የተሳለው ፈገግታ በድንገት ተሰርዞ፣ መጀመሪያ እንደ ነጭ ገጽ ባዶ ሲሆን፤ ቆይቶ ደግሞ ሁለት ወይ ሶስት ቀን ለመሙላት እንደ ቀራት ትንሽ ጨረቃ ሞለል፣ ረዘም ሲል ሽንቁሩም ዓይኑም ታዘቡ። ልጅቷ ለጥቂት ሰከንዶች ቆማ ግድግዳ ግድግዳውን ሽንቁር ሽንቁሩን ስታይ ቆይታ፣ ድንገት ዞራ እየቦረቀች ወደ መጣችበት አቅጣጫ ተመልሳ ተሰወረች፣ መጀመሪያ ግማሽ ሆና ከዛ እሩብ … ከዛ ምንም።

ሚሚ በተሰወረችበት ቦታ ላይ ተጋርዶ የነበረ አዲስ ነገር ተተካበት። ግማሽ የመጽሐፍ መደርደሪያ ሼልፍ። ሼልፉ ግማሽ ይሁን እንጂ መጻሕፍቶቹ ሙሉ ሆነው ለዓይኑ ታዩት። ከዛ ርቀት አርእስታቸውን ማንበብ ባይችልም እንደ መጠጥ ጠርሙሶች የስካር መጠናቸውን፤ የአልኮል ይዞታቸውን ዓይኑ ያውቀዋል። አጣጥሟቸዋል። ሰክሮባቸዋል። እንደ ጣዕማቸው፣ እንደ ይዘታቸው፣ እንደ ጥንካሬአቸው ሙሉ የሆኑት ሙሉ ሆነው ባይታዩት እንኳን ሙሉነታቸው ይሰማዋል፤ ግማሽ የሆኑት ግማሽ፤ ግማሽ ሆነው ያልታዩት ደግሞ ጠፍተዋል። ዓይኑ ቀዳዳውን አደነቀው። ሽፋሽፍቶቹን እያርገበገበ ለሀቅ የሚሰጠውን ምስጋና ለገሰው። እውነት እንዲህ ነው የሚታየው ለካ!

ሚስትየዋ ፀጉሯን ይዛ ቦታ ለቀቀች። የማይንቀሳቀሱት ግማሽ ነገሮች ብቻቸውን ቀሩ። ሽንቁሩ እንደሚያቃቸው። ሳይሞካሹ።

ሚሚ ተመልሳ መጣች። አሁንም ግን ሙሉ ነች። ከነሁሉ ትንሽ ነገሯ። ስትመጣ ሙሉ ነች። ከሌለች ግን የለችም። የትልቅ ሰው ጫማ አድርጋለች። የአባቷን፤ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው መስታወት ጎን ተጠግታ እየተሸከረከረች ራሷን አደነቀች። ትንንሽ ደስ የሚሉ ጥርሶቿን ብልጭ እያደረገች። እጇን አፏ ላይ ከድና ፍርስ ብላ ሳቀች። እንደገና ተሰወረችና እንደገና ተከሰተች። የእናቷን ጌጥ እና ሊፕስቲክ ይዛለች። መስታወቱ ጋ ቆማ ቶሎ ብላ ከንፈሯን ከማዳረሷ በፊት ድምፅ እንደሰማች አይነት ከንፈሯን በፍጥነት በእጅጌዋ ጠረገችው። ጀርባዋን ወደ መስታወቱ አድርጋ ጌጡንና የከንፈር ቀለሙን አልጋ ስር ወረወረችው።

ግማሽ ሚስት፣ ግማሽ ዳሌዋን እያውረገረገች መጥታ ሚሚን ጋረደቻት። ግማሽ እጅ ወደ ላይ እየተነሳ ሲወርድ ቆይቶ፣ ግማሽ አጅ አልጋ ስር ራሱን ሰዶ የተጣለውን እቃ አነሳ። የማይታየው ግማሽ ሶፋ ላይ ሚስት ሄዳ ተሰወረች። ሶፋው ሲውረገረግ ዓይኑ እንደተቀመጠች አወቀ።

ሚሚ ድምፅ የሌለውን ለቅሶዋን ስታሰማ እንኳን ሙሉ ነበረች። የማይሰማው ለቅሶዋ እንኳን ሙሉ ነው። በእጇ አይኗን ሸፍና። በደንብ ያልተጠረገው ከንፈሯ … አገጯን ጨምሮ እንደቀለሙ ቀልቶ። ዓይኗን የማይታየው የሶፋ ጠርዝ ላይ ተክላ ትንሰቀሰቃለች። ሶፋው “ዝም በይ እንዳልደግመሽ!” የሚል ይመስላል። ሚሚ ትዕዛዝ በመቀበል አይነት አኳኋን የአባቷን ጫማ በፍጥነት አውልቅ አልጋ ስር መለሰች። ቀና ብላ ሶፋውን እያየች ለተጨማሪ ትዕዛዝ ተዘጋጀች።

 አሁን፤ ሚሚ በግራው አልጋ ጎን ወጥታ ዓይኗን ጨፈነች። አባቷን እየናፈቀች እንደነበር ሁሉ ነገሯ ይናገራል። ዓይኑ ከውጭ በግድግው ስንጥቅ እየተመለከተ ‹‹እራቷን ሰጥተዋት ይሆን?›› ብሎ አሰበ። ሚሚ ብዙም ሳትቆይ እንቅልፍ ወሰዳት። ስትተኛ እንኳን ሙሉ ነች።

ዓይኑን ከስንጥቁ ሲነጥል፤ እማይሰማ፣ በጨረፍታ የሚያይ ዓይን መሆኑ ቀርቶ ሰው ሆነ፤ አባት ሆነ፤ ባል ሆነ።

የቤቱን ጓሮ ዞሮ በመግቢያው በኩል አንኳኳ፤ ሚስቱ ከፈተችለት። ፀጉርዋ አሁን ተበጥሮ ተስተካክሏል። አስተያየቷ እንዳለፉት ሳምንታት የጥላቻ ነው። ሰላም አላላትም ወደ ውስጥ ሲገባ። የተኛችው ሚሚ ጎን አልጋው ላይ ተቀመጠ። እራቷን በልታለች ወይ? ብሎ ሊጠይቅ አሰበና ግማሽ መልስ እንደሚሰጠው ስለሚያውቅ ተወው።

ለነገሩ እሱም አልበላም። የሱ እንኳን የታወቀ ነው። በኋላ እጇን ሲያገላብጥ ወጥ ነክቶት ስላየ በልታለች ብሎ ደመደመ። እምትበላው በማንኪያ ቢሆንም እጇ ዝቅ ብሎ ማንኪያ ቂጥ ስለሚይዝ የበላችው ነገር ሁሉ እጇ ላይ ምልክቱ ይቀራል።

ሚሚን ወስዶ የራሷ ትንሽ አልጋ ውስጥ ከቷት ተመልሶ መጥቶ ሶፋ ላይ መጽሐፍ ይዞ ቁጭ አለ። ሚስቱ በአግቦ እያወራች ቆይታ መጽሐፍ ቅዱሷን ይዛ በአልጋው ቀኝ ገብታ ጸለየች። ተኛች።

ባልየው በንባቡ መሐል ትዝ ብሎት ወደ ግድግዳው ፊቱን መልሶ ያንን ትዕግስተኛ ሽንቁር ፈለገው። ሊያገኘው አልቻለም። ከሶፋው ላይ ተነስቶ ሄዶ በቅርበት መረመረ። በጭቃው ግድግዳ ላይ ብዙ ስንጥቆች ቢኖሩም አንዱም ወደ ውጭ ሊያሳየው አልቻለም።

‘እንደ አምላክ ነብሴን ከውጭ ሆኜ ሳይ ነበር እንዴ?’ የሚል ጥያቄ መሰል ሐሳብ እንደ ወፍ በቃናው ላይ ተወንጭፎ ሲያልፍ የተሰማው መስሎት ነበር፤ ግን እርግጠኛ መሆን አልቻለም። ተመልሶ ሄዶ መጽሐፉን ማንበብ ቀጠለ።

.

ሌሊሳ ግርማ

.

(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] – “እስቲ ሙዚቃ”። 2009 ዓ.ም። ገጽ 36-39።

“ባይተዋር ወጣቱ” (ግጥም)

“ባይተዋር የሆነው ብቸኛው ወጣት”

ከዮሐንስ አድማሱ

(1957)

.

.

ባይተዋር የሆነው ብቸኛው ወጣት

ሕሊናና ምኞት የተማቱበት

ተወጥሮ ያለ በሁለት ዓለም

ቆዳው እየሳሳ ነፍሱ ስትከስም፤

ባይተዋር

ባይተዋር

ብቸኛው ወጣት፤

የዘመን ከርታታ ቋንቋ ቸግሮት

ስሜቱን መግለጹ አድርጎ በስልት

ይኸው ተስኖት

ሐሳብ አነሁሎት አይለይም ከንክ

ወይንም በሙያ ወይንም በመልክ።

.

ተቀምጦ በድንገት ይዘምታል ሐሳቡ

ድንገት ሳያስበው ይዝላል ልቡ፤

ወጣቱ

ወጣቱ

የሚኖር በከንቱ፤

ሰው የለውም አሉ፣ በስሙ እንዳልጠራው እንዳይል አቤት

እገሌ እንኳ አይባልም እሱም በዝቶበት፤

ገና ገና

ገና ወጣት ሲሆን ስሙ ጠፍቶበት፤

ይማኩሳል

ይወጣል ይወርዳል

ከቅል እቀንድ ይላል ቃል ስም ለማግኘት

የነፍስ ብዝባዜ የነፍስ ፈተና

ስም አጥቶ ፍለጋ መማታት አገና።

.

ባይተዋር ወጣቱ

የባይተዋርነት ፍጹም አብነቱ

ለስም ብቻ አይደለም ትግሉ ብዙ ነው አለው ብዙ ዋልታ

በነዚህ መካከል ትካዝና ሐዘን ጋርና ዋይታ፤

ባንድ በኩል መስቀል ባንድ በኩል ጦር

ይኸም ተለውጦ መስቀል ከሰላጢን አብሮ ሲጣመር

(ወይንም)

ይህ ይለወጥና አለመቁረጥ ፍዳ

የመዋለለ ዕዳ፤

ባንድ በኩል ደግሞ ማተቡን በጥሶ

ሁሉን ነገር ጥሶ

ይመኛል ሊኖር

ወጣት ባይተዋር።

.

ሁሉንም አንድነት መጨፍለቅ አውኮት

ወይ የራሱን እምነት

(እንዳለው ምናልባት)

ማስረገጥ ቢሳነው ጸንቶ በኔነቱ

(ምናልባት እንዳለው ሰው የመሆን ልዩ … ልዩ ምልክቱ)፤

ገባ ወህኒ አምባ

ገባ ወህኒ አምባ

ባይተዋር ወጣቱ የብቸኝነቱን ዕንቡን እያነባ

ገባ ወህኒ አምባ፤

ኑሮ ከሽልላበት ሥሯ ተመዝምዞ

ፍሬዋ ጎምዝዞ

ፍሬ ፍች አጥቶባት ገባ ወህኒ አምባ

ገባ ወህኒ አምባ።

.

ዮሐንስ አድማሱ

.

[ምንጭ] – “እስኪ ተጠየቁ …”። 1990 ዓ.ም። ገጽ 78-79።

“ወደ አዲስ አበባ” (ወግ)

“ወደ አዲስ አበባ”

በሣህለ ሥላሴ ብርሃነማርያም

.

.

አባ ፍራንሷ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ ከመጡ በኋላ ዘመድ ቤት አስቀምጠውኝ ያን ጊዜ “ሐኪም ቦራ” ተብሎ ይጠራ በነበረው፣ በዛሬው ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል እንድታከም አደረጉ። ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እሳቸው የሚያርፉት ካቴድራል (ልደታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን) ስለሆነ እዚያ ቆዩ። የበሽታዬ ዓይነት ምን እንደነበረ ባይነገረኝም ባጭር ጊዜ ውስጥ ታክሜ ተፈወስኩ።

ከዚያ በኋላ ከአባ ጋር ወደ እምድብር ለመመለስ በምጠባበቅበት ጊዜ ወደ ክፍላቸው አስጠርተውኝ፣

“ልጄ … ወደ እምድብር ለመመለስ ትፈልጋለህ ወይስ እዚሁ አዲስ አበባ ቀርተህ ለመማር ትሻለህ?” ሲሉ ጠየቁኝ።

የሚቀልዱብኝ መስሎኝ ዝም ብዬ ተመለከትኳቸው። ፍጹም ያላሰብኩትና ሊሆን ይችላል ብዬ ያልገመትኩት ነበር። ከእምድብር ሚሲዮን ንፍሮ ተገላግዬ እዚህ አዲስ አበባ ልቀር? እንደ አዲስ አበባ ሰው ሁሉ እንጀራና ወጥ ብቻ ሳይሆን ያንን የቀመስኩትን የፈረንጅ ፉርኖ እየገመጥሁ ጣፋጩን ሻይ እየጠጣሁ ተንደላቅቄ ልኖር? ፈጽሞ አልመስልህ አለኝ።

“እዚህ ለመቅረት ከፈለግህ ላዛሪስት ሚሲዮን አስገባሃለሁ ልጄ” አሉኝ፤ “እና ምን ይመስልሃል?”

ደስታ ፈንቅሎኝ፤ “እውነትዎን ነው ወይ አባ?” አልኳቸው።

ያን ከፊታቸው የማይጠፋውን ፍልቅልቅታ እያሳዩኝ፤

“አዎን ልጄ … ላዛሪስት ሚሲዮን ውስጥ ላንተ የሚሆን አንድ ቦታ አይጠፋም” አሉኝ።

“ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ አባ!”

በማግስቱ ይሁን በሠልስቱ ወደ ላዛሪስት ሚሲዮን ለመጓዝ ከካቴድራል ወጣ ብለን ጋሪ አስቆምን። የዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ ዋናው የሕዝብ ማመላለሻ ጋሪ ነበር። እነ ኩርኩር (ባለ ሦስት ጎማው ማጓጓዣ)፣ እነ አውቶቡስ፣ እነ ሚኒባስና ውይይት ገባ አልገቡም። ፈረንጆችና ጥቂት ዘበናይ ኢትዮጵያውን ሹማምንት በታክሲ ይጓዙ እንደሆነ ነው እንጂ ሌላው የከተማው ነዋሪ በሙሉ፣ ከእግረኛው በስተቀር፣ በጋሪ ነበር የሚጓጓዘው … ከፒያሳ መርካቶ፣ ከለገሐር ጉለሌ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና፣ ከመርካቶ ኮልፌ፣ ወዘተርፈ።

ፈረሶቹ አስፋልቱን መንገድ ከኮቴአቸው ሥር በተገጠመላቸው የብረት መጫሚያ እያንቋቁ ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ የሚል ድምፅ እያሰሙ ሲያልፉ እስከ ዛሬ ድረስ በውስጥ ጆሮዬ ሲያስተጋባ ይሰማኛል። ስንቱን ጀግና ከጦር ሜዳ እንዳላደረሱ ሁሉ፣ የስንቱን ንጉሥ ስም አባ ዳኘው፣ አባ ዲና፣ አባ ታጠቅ፣ አባ ጠቅል እያሰኙ እንዳላስጠሩ ሁሉ እነ ዳማ፣ እነ ጉራች፣ እነ ቦራ፣ እነ ሻንቆ፣ ጣሊያን ባመጣው አዲሱ ሥልጣኔ ተዋርደው የጋሪ ጐታች ሆነው ቀሩ።

ፊት ለፊት እንጂ ግራና ቀኝ እንዳያዩ ለዓይናቸው ከለላ ይደረግላቸዋል። የጋሪዎቹ መቀመጫዎች በኋላ ዘመን በአሥመራ ከተማ እንዳየኋቸው የሚደሉ ባይሆኑም ለክፉ የሚሰጡ አልነበሩም። ባለጋሪዎቹ ከአናታቸው ቆብ፣ ከእጃቸው ጅራፍ አይለያቸውም። ደሞም ይዘፈንላቸዋል፤ “ባለጋሪው … ባለጋሪው … ቶሎ ቶሎ ንዳው …” እየተባለ። አቤት ዘፈኑ ለጆሮ ደስ ሲል!

አንዱን ባለጋሪ አስቁመን አባና እኔ ጋሪው ላይ ተሳፍረን ጉዞ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሆነ። ላዛሪስት ሚሲዮን የሚገኘው ከእንጦጦ ጋራ ሥር ነበር። “ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ” የሚል ድምፅ እያሰማ ተጉዞ ተጉዞ ከሚሲዮኑ መግቢያ በር አደረሰን። አባ ሂሳቡን ከፈሉትና ወደ ምድረ ግቢው አመራን።

ከእኔ በፊት ከየቦታው ተመልምለው መጥተው እዚያ የሚኖሩ ወጣት ተማሪዎች ምድረ ግቢው መሐል ላይ ባለው ሜዳ የእግር ኳስ እየለጉ ሲጫወቱ አየን። ይንጫጫሉ። አንዳንዶቹ በእኔው እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። አንዳንዶቹ ያበጡ ጐረምሶች ሲሆኑ የተቀሩት ከእኔ የሚያንሱ ትንንሽ ልጆች ናቸው።

አባና እኔ ኳስ ጨዋታውን መልከት ካልን በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል አመራን። እዚያ የነበሩት ፈረንጅ ካህንና አባ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሲጨዋወቱ እኔ ዝም ብዬ እሰማቸዋለሁ። የፈረንሳይኛ ፊደል የቆጠርኩ ቢሆንም በዚያን ጊዜ ቋንቋው አይገባኝም። ይሁን እንጂ አባና ሌላኛው ካህን ሲነጋገሩ ቋንቋው የተለምዶው ሙዚቃዊ ቃና ነበረው።

አባ ተነጋግረው ሲጨርሱ እኔው ተዚያው ትተውኝ ወደ ካቴድራል ማረፊያቸው ተመለሱ። ግቢውን የሚያስተዋውቀኝ ልጅ ተሰጥቶኝ እየተዘዋወርን ሚሲዮኑን ያስጐበኘኝ ጀመር። ጸሎት ቤቱን፣ የመኝታና የጥናት ክፍሎቹን፣ ቤተ መጻሕፍቱን፣ በሲሚንቶ የተሰሩ ንጽሕና ቤቶቹን አንድ በአንድ አስጐበኘኝ።

ከዚያን ቀን ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ያህል አብረን መኖር የጀመርነው ወጣቶች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጣን ነበርን። እና ሁላችንም አብረን ውለን አብረን እናድራለን። ወደ ተፈሪ መኰንን ት/ቤት እየተመላለስን እንማራለን። እሁድ እሁድ ወደ እንጦጦ እየወጣን ወይም ሸጎሌ ወደተባለው ሜዳ እየኼድን የእግር ኳስ እንጫወታለን።

የሚያስተዳድሩንና ተንከባክበው የሚያሳድጉን ካህናት አምስቱ ፈረንሳውያን ሲሆኑ አንዱ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፤ አባ ዢማላክ፣ አባ ብርዬ፣ አባ ሊሙዘን፣ አባ ጃንካ፣ አባ ማርሴ እና አባ አጽብሐ።

አባ ጃንካ በጣም ጉልበተኛ ሰው ነበሩ። እኛ ሁለት ወይም ሦስት ሆነን ተጋግዘን ማንሳት የማንችለውን ሸክም እሳቸው በአንድ እጃቸው፣ ያውም በግራ እጃቸው ብድግ ያደርጉት እንደነበረ አስታውሳለሁ። ቁመታቸው መሐከለኛ ሆኖ አጥንታቸው ሰፊ፣ ምንም ነገር ሊነቀንቃቸው የማይችል የግንብ አጥር የመሰሉ ነበሩ። ታንክ በመሰለ ከባድ መኪና ለሚሲዮኑ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ገዝተው የሚያመጡት እሳቸው ናቸው። እሁድ እሁድ ወደ እንጦጦ ጋራ ወይም ወደ ሸጎሌ ሜዳ በምንጓዝበት ጊዜ የፈረንጅ ኮርቻ በተጫነ ፈረስ ላይ ተቀምጠው የሚመሩን እሳቸው ናቸው።

አባ ማርሴ በሚሲዮናችን ብቻ ሳይሆን በተፈሪ መኰንን ት/ቤት ጭምር በጣም ዝነኛ ሰው ነበሩ። አባ ማርሴ የፈረንሳይ ተወላጅ ቢሆኑም አማርኛና ግእዝ አሳምረው ያውቁ ነበር። እንዲያውም በተፈሪ መኰንን ት/ቤት፣ ያውም በሁለተኛው ደረጃ፣ የአማርኛ ሰዋስው መምህር ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በአንዱ ብብታቸው ሸጉጠው፣ ከዘራቸውን በአንድ እጃቸው ይዘው ቢስኪሌታቸው ላይ ወጥተው እያሽከረከሩ ነበር ወደ ተፈሪ መኰንን ት/ቤት የሚጓዙት። እኛ ግን ወደ እዚያ የምንኼደውና ከዚያም ወደ ማታ ጊዜ የምንመለሰው አርባ አምስት ደቂቃ ያህል በእግር እየተጓዝን ነበር።

በመንገዳችን ካኪ ዩኒፎርም የለበሱ ልጃገረዶች ያጋጥሙናል። መጽሐፎቻቸውንና ደብተሮቻቸውን እንደ ሕፃን ልጅ በደረታቸው ታቅፈው ዱብ ዱብ እያሉ ያልፉናል። እኛ ሚሲዮን ቀጥቅጦ ያሳደገን በመሆናችን ቀና ብለን ልናያቸው ባንደፍርም እነሱ ግን ፈጽሞ አያፍሩንም ነበር። እየተሳሳቁ፣ የአቧራ ብናኝ እያስነሱ ወደ እቴጌ መነን ት/ቤት ያመራሉ። እቴጌ መነን ት/ቤትና ተፈሪ መኰንን ት/ቤት ቅርብ ለቅርብ ናቸው። በዚያን ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በተለያየ ት/ቤት እንጂ በአንድ ት/ቤት፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ጐን ለጐን ተቀምጠው መማር የማይታሰብ ነበር … በኋላ ዘመን ቢሻርም ቅሉ!

በትምህርት ቀናት ለምሳ ወደ ሚሲዮናችን ለመመለስ ሰዓቱ ስለማይበቃን እነ አባ ማርሴ ከተፈሪ መኰንን ት/ቤት አቅራቢያ ሆቴል ተኮናትረውልን ምሳችንን እዚያ እንበላ ነበር። ለእያንዳንዳችን ሃያ አምስት ሳንቲም ይሰጠን ነበር። ለምሳ መብያ። ያ ሃያ አምስት ሳንቲም ተአምር ይሰራ ነበር ለማለት እደፍራለሁ … ከዛሬው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር።

ሙሉ እንጀራ በሽሮ ወጥ በአስር ሳንቲም፣ በክንድ የሚለካ ፉርኖ በአስር ሳንቲም፣ በስንዝር የሚለካው በአምስት ሳንቲም፣ አንድ ብርጭቆ ሻይ በአምስት ሳንቲም ይገዛ ነበር። ሙሉ እንጀራ በሥጋ ወጥ ለመብላት የሚሻ በሃያ አምስት ሳንቲም አዝዞ ጥስቅ አድርጎ ይበላ ነበር። የዚያም ዓይነት ዓለም ነበር … በሺ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ!

በተፈሪ መኰንን ት/ቤት የሚማሩት ባልደረቦቻችን፣

“የአባ ማርሴ ልጆች

አንሶላ ለባሾች!”

እያሉ ያፌዙብን ነበር።

ይህም ከበስተጀርባው ታሪክ አለው። በበጋው ወራት በተለይም በታህሳስ ወር ጠዋት ጠዋት በጣም ይበርድ ነበር። በዚህ ምክንያት አሳዳጊዎቻችንን አስፈቅደን ለመኝታ የምንጠቀምበትን ነጭ አንሶላ ደርበን ነበር ወደ ትምህርት ቤታችን የምንጓዘው። ካፖርት እንዳንገዛ ከአቅማችንና ከደረጃችን በላይ ነው። ሌላም የብርድ መከላከያ አልነበረንም።

ታዲያ በአዳሪነት፣ ያውም ያለ ክፍያ ተሞላቅቀው የሚኖሩት ባልደረቦቻችን ችግራችንን ባለመረዳት ”የአባ ማርሴ ልጆች፤ አንሶላ ለባሾች“ እያሉ ያፌዙብን ነበር።

እነሱ አላወቁም እንጂ ሌላም የብርድ መከላከያ ነበረን። በዚያን ጊዜ ከመሐከላችን ጫማ የሚያደርግ ማንም የለም። ሁላችንም በባዶ እግር ነበር የምንኼደው። ወደ ት/ቤት ስንጓዝ በመንገዳችን የሚገኝ አንድ ደረቅ ወንዝ ስለነበረ በታህሳስ ወር ከዚያ ስንደርስ ቅዝቃዜው በጣም ስለሚበረታ ከሚሲዮናችን ስንነሳ አሮጌ ጨርቅ ይዘን እንመጣና እግራችንን በዚያ ጨርቅ ሸፍነን ሰርጓዳውን ስፍራ እናልፋለን።

ጨርቁን ወደ ትምህርት ቤታችን ይዘን ብንኼድ የባሰውን መሳቂያ ስለምንሆን ደረቁን ወንዝ ከተሻገርን በኋላ ጥሻ ውስጥ ወሽቀነው እንኼድና ማታ ስንመለስ ይዘነው ወደ ሚሲዮናችን እናመራ ነበር።

.

ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

.

[ምንጭ] – “ፍኖተ ሕይወት”። 2001 ዓ.ም። ገጽ 51-56።

“ልብወለድ ታሪክ” (ክፍል 2)

“ልብወለድ ታሪክ”

በአፈወርቅ ገብረየሱስ

(1900 ዓ.ም)

.

(ከክፍል አንድ የቀጠለ)

.

አንድ ቀን ግን ማታ ምድር ጦቢያ ቅጠሉን አብስላ ሰባብቃ፣ ከምንቸቱ ወደ ቆሬው ዘርግፋ፣ እንደልማዳቸው ሶስቱም ቀርበው ሲበላሉ የዝያን ለጋስ ነጋዴ ነገር እያደነቁ፣ ወዲአውም ‘እሄ ገንዘብ መቸ ተጠራቅሞልን መቸ ገንዘቡን ሰደን እስተመቸ ታባታችን ጋር ዓይን ላይን እንተያይ ይሆን ገና ነውና ነገሩ’ እያሉ እየናፈቁ በየጊዜው ምግባቸውን እያቋረጡ ሲነጋገሩ ከሄት መጣ ሳይባል የተገደበውን መዝጊያ ገፋ አድርጎ ገብቶ አንድ ሰው ተፊታቸው ቀጥ አለ።

ሶስቱም ደነገጡና ቀና አድርገው ቢያዩ ያው የሚመኙት ተሽጦ የነበረው ሰዋቸው ሆነ። ነገር ግን ህልም መሰላቸው እንጂ በውናቸው የሚያዩት አልመስላችሁ አላቸው። እሱም እንደገባ ምሽቱንም ልጆቹንም አንድነት ባየ ጊዜ በናፍቆትና በነዚያው ፍቅር ስስት ፈዘዘና እንባ እያነቀው መናገር ተሳነው። እነሱም መብረክረክ እንዲያው መፋዘዝ እንጂ ለጊዜው ለመነሣትም ለመነጋገርም አልሆነላቸው።

ቆይተው ቆይተው ግን ህልምነቱ ቀርቶ በውነት እሱ አባታቸው መሆኑን አወቁና ነብስ ገዝተው ምሽቱም ልዦቹም አንድነት ተነሥተው እየተላቀሱ ባንገቱ ላይ ይረባረቡበት ጀመረ። ተነዚአው ተሶስቱ ተወገቡም የተጠመጠመ ታንገቱም የተንጠለጠለ ጉልበቱንም የታቀፈ አለ። የዚአን ጊዜ ላያቸው ሰው እንኳን ለተወለዳቸው ላልተዘመዳቸው ለጠላታቸውም ቢሆን ያሳዝኑ ያስለቅሱ ነበር። አባትዮውም የዚህን ጊዜ ቃሉን እንባ እያቋረጠው አንዱን አንድ ጊዜ፣ አንዱን አንድ ጊዜ በየራሳቸው አቅፎ እየያዘ እንዴት ናችሁ እንደምን ናችሁ ይላቸው ጀመር።

ቀጥሎም ለሁሉም አንድነት አድርጎ እንባውን በመሀርሙ እየጠራረገ

“ያን ያህል ወርቅ ወዴት አገኛችሁና ሰዳችሁ ከባርነቴ ከተሸጥሁበት አስለቃቅችሁኝ። እኔ እንኳ ገንዘብ ማጠራቀም አላውቅ ነበር ወዴት አገኛችሁት” አላቸው።

እነሱ ግን ለገናው ገንዘቡን ቢሆንላቸው አጠራቅመው ሰደው ለማስለቀቅ እንጂ ከዚያ በፊት አለመስደዳቸውን አውቀው ነገሩ አረቀቀባቸውና የሚመልሱት ቃል አጡ። ብቻ እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር። በዚሁ መሀል አንድ ቃል የሚመልስለት ባጣ ጊዜ አባትዮው ወደ ዋህድ ዞረና፣

“አንተ ትሆን ልዤ ወዴት አገኘኸው” አለና ጠየቀው።

በዚህ ጊዜ ዋህድ ምን ይመልስ እሱ እንዳልሰደደ ያውቅ ነበር። በኋላ ግን ገና አባትዮው ዓይን ዓይኑን እየተመለከተ ምላሽ ሲጠብቅ ዋህድ የዚያ ለጋስ ሰው ነገር ውል አለውና፣

“አሁንስ ገንዘብ የሰደደውና አንተን ያስለቀቀህን ሰው አወቅሁት። አባየ እኔ አልምሰልህ”

አለና ታሪኩን የዚያን ለጋስ ነጋዴ ነገር ለሱም ገንዘብ መስጠቱን ኋላም ያባቱን ስም የገዛውን አረመኒም ስም ያለበትን ያገሩንም ስም መጠየቁን ሁሉንም ተረከለት።

አባትዮውም ነገሩን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ደነቀውና ከላይም ክርስቶስን ከታችም ያን ለጋስ ያመሰግን ይመርቅ ጀመር። ከዚህ ቀጥሎም እሄው የጥንት ደጃዝማች ለዋህድ እንዲህ አለው።

“ልጀ ያ ለጋስ እኔን ሳያውቅ ሳይጠይቅ ሳይወለደኝ ሳይዘመደኝ ያን ያህል ገንዘቡን አጥፍቶ ለገዛኙ ጌታ ከፍሎ አስለቀቀ። ወዳገሬ ስመለስ እንዳልደክም ጮሌውን ፈረስ አድርጎ፣ እንዳልራብ ስንቁን ጨምሮ ሰዶ፣ እሄው ላገሬ ለወንዜ ለቤቴ ለምሽቴ ለልጆቸ አበቃኝ፣ ደስታየን ዓለሜን አሳየኝ። ስለዚህ እኔም አሁን ምንም ትልቅ ወረታ ባልመልስለት ባይሆን እንኳ ሂጀ ታለበት እግዚአብሔር ይስጥህ እንድለው ወዳለበት ምናልባች ወደ ንግዱ አልሄደ እንደሆነ ምነው ብትመራና ብትወስደኝ። አሁንም ቶሎ ውሰደኝ” አለና ነገረው።

ዋህድ ግን ተመልኩ በቀር የዚያን ሀብታም ነጋዴ እንኳን ስሙን አገሩንም ለይቶ አያውቅ አልጠየቀምም ነበርና ተጨነቀ።

“እንግዴህ ያን ደግ ሰው ያን መሳይ ለጋስ ሰው፣ ያባቴን ታዳጊ፣ የናቴን የቴን የኔን እንባ አድራቂ፣ ወዴቱን መልሸ ብሄድ አገኘዋለሁ። እሱን ለማግኘት ምን ባረግ በተሻለኝ” እያለ ተጨነቀና በመጨረሻ “እሱን ታላገኘሁና ያባቴን በደህና መድረስ፣ የኛን ደስታ የኛን ዓለም ታልነገርሁት እግሬ እስቲነቃ እስትሞትም ቢሆን ዓለሙን እየዞርሁ እፈልገዋለሁ እንጂ ተቤቴ አልቀመጥም”

ብሎ ሲያቆም ዋህድ ስንቁን ቋጥሮ ዘንጉን ይዞ በማግስቱ ከዘመዶቹ ተላቅሶ ተለያይቶ ፍለጋ ተነሣ።

ዋህድ ከቤቱ እንደተነሣ መንገዱን ያን ሀብታም ነጋዴ ታንድ ትልቅ ከተማ ዳር ሰፍሮ ነውና ያገኘው ወደዚያው ከተማ አቀና። ከዚያውም በደረሰ ጊዜ ተከተማው ሳይገባ በፊት ዓይኑን ያቀና የዚያ ነጋዴ መደበር ወደነበረበቱ መስክ ነው። የመደበሩን ስፍራ እያየ ያን ደግ አድራጊውን ሰው እያሰበ ልቡ ተዋለለበት። እንባውም ባይኑ ተንቸረፈፈበትና ተቆመበት ላይ ቁጭ አለ።

ከዚያው አለቃቀሰና ሲነሣ ያን አሮጌ መደበር አጕድኖ እያየ አንገቱን እስቲጣምነው እግሩንም እንቅፋት እያከሰለው ሁሉንም ቁም ነገር ሳይል ፊቱን ወደዚያው አሮጌ ሰፈር እንዳዞረ ተከተማው ገባ። ነገር ግን ከዚያው ከተማ ገብቶ ምን ያድርግ። የዚያን ሰው ስም አያውቅ እገሌ ብሎ አይጠይቅ። ቤቱን አያውቅ ወደ ቤቱ አይሄድ። ምን ያድርግ ድሮ ዋህድ አሳቡ ሁሉ ተልከሰከሰበት።

እንዲያው እንደ ሞኝ እንደ ንክ ታውራ መንገድ መካከል ቆመና የሚሄድበቱን ሳያውቅ ይዋልል ጀመር። የቤት ልጅ ነው መከራ ከጥቂት ጊዜ በቀር አይቶት አያውቅ። በዚህ ጊዜ ውሀ ጥም ታከለበት እራብም ይመተልገው ጀመረ። ቶሎ ቶሎም ያንቧቅስ፣ ዓይኑም እንባ ይቋጥር ጀመር። እሄ ሁሉ ሲሆን ዋህድ ባደረገው ነገር አይጠጠትበትም። ያን ደግ ሰው ለመፈለግ እድሜውንም ልክ ቢሆን እንዳይገበዝ አንድ ጊዜ በልቡ ቆርጦ ፈክሮ ተነሥቷል።

እራቡና ጥሙ ሲበረታበት ጊዜ ዋህድ ምንጭ ፈለገና ከዚያ ምንጭ አጠገብ በመቍነን ተስንቁ በላና ከምንጩ ተደፍቶ ጠጣና ተመስገን ጌታዬ ብሎ ወደ ፍለጋው ተነሣ። ከዚህ ወዲያ ያን ነጋዴ ለማግኘት ዋህድ በያደባባዩም፣ በየገበያውም፣ በየጐዳናውም፣ በየደጀ ሰላሙም፣ በየቤቱ በየበሩ፣ በየመጋቢያው፣ በየቤተክርስቲያኑም እየገባ እየዞረ ቢፈልግ አጣው የማይሆንለት ሆነ። ዋህድ ተስፋውን ቆረጠ።

ከዚያ ከተማ መፈለግ ተጀመረ አሥራምስት ቀኑ ሆነ። እሄን አሥራ አምስት ቀን ሙሉ ዋህድ ቀን ቀኑን ሲፈልግ እየዋለ ማታ ማታውን ጅብ እንዳይበላው ከየቤተ ክርስቲያኑ ዚነጋባ እየገባ ነበር የሚያድር። ያ ሀብታም ነጋዴ ከዚያ ከተማ አለመኖሩን እርግጡን ተረዳውና እንግዴህ ወዴት ሂጄ ልፈልገው ሲል አሳብ ገባው። አስቦ አስቦ የተሻለ ነገር ያገኘው በየነጋዴው መደበር በየነጋዴው ጉዞ እየሄደ እየዞረ መፈለግ ብቻ ሆነ። የዋህድ አሳብ በዚህ ቆመ።

እሄን በመከረ በማግስት ዋህድ ከዚያ ከተማ ወጣና በሄትም ሳይል አንዱን መንገድ ይዞ መደበር ፍለጋ ይጓዝ ጀመር። ይሄድ ይሄድና ከጉብታ ላይ ወጥቶ ባገሩ ዙሪያ ወይ መደበር ወይ የነጋዴ ጉዞ ለማየት ይመለከታል።

ሰውም ተመንገድ ሲገጥመው መደበርና ነጋዴ ብቻ ነው የሚጠይቅ። ነጋዴ በዚህ አለፈ ከዚህ ሰፈረ ያሉት እንደሆነ ወደዚያው ሲሮጥ እየሄደ ከነጋዴው መሀል ያን ደግ አድራጊውን ነጋዴ ይፈልጋል። መልኩን ካላየው በቀር ስሙን አያውቅምና የሚፈልገውን ሰው ተነጋዴዎቹ አንዱ ‘እገሌ ወዴት ነው ወዴት ደረሰ’ ብሎ መጠየቅ አይሆንለትም ነበር።

ከዚያ መደበር ሳያገኘው ጊዜ ወደ ሌላው መደበር ፍለጋ ሲሄድ ሲሄድ ተመሸበት ሲያድር ዋህድ ሆየ አንድ ቀን ሲጓዝ ውሎ መንደር ተሌለበት ከምድረ በዳ ደረሰ። ከዚያው ምድረበዳ መሀል በሩቁ ትልቅ የነጋዴ ሰፈር አየ። ነጋዴ መሆኑንም በመደበሩ ለየው። ዋህድ ያነን መደበር ባየ ጊዜ ነገሩ አደባበሩም መጠኑም ያን ሀብታም ነጋዴ ያየ ጊዜ ያየውን መደበር መሰለውና ለጊዜው ደስ አለው። ተዚያ ሰፈር ለመድረስ አሰበና ይባክን ይሮጥ ጀመረ። ወንዛወንዝ የበዛበት ሜዳ ነበርና ቢለው ቢለው እርቀቱ ያው ነው። መደበሩ በመጫኛ አስሮ ወደኋላ እንደጐተቱት ሁሉ ወደኋላ የሚርቅ እንጂ የሚቀርብ አልመስለው አለ። መንገዱ ቢሄደው ቢሄደው አልገፋህ አለው። ጊዜው ግን ተማሸ ፀሐይቱም ተቆለቆለች።

ዋህድ ግን ከመደበሩ ሳልደርስ አላድርም ብሎ ፈክሮ ተሎ ተሎ ይራመድ ይሮጥ ጀመር። ነገር ግን ሳይደርስ በፊት ምድር መሸበት። በመሀል ቤት ጀንበር ጠለቀችና ድንግዝግዝ አለ። ቀጥሎም ጨለመና ላይን ነሳ። በወፎች ጫጫታ ስፍራ የፌንጣው ድምጥና የጓጕንቸሩ በያረንቋው በየረግረጉ ያለው ጕርጥ ዋካታ ተተካበት። ይልቁንም በዚሁ መሀል ባንድ ወገን ተኵላው፣ ባንድ ወገን ቀበሮው ሲጯጩአህ ሳለ፣ ባንድ ወገን ጅቡ እሙኝ ይል፣ ነብሩ ያጓጉር፣ አንበሳው ይገስል ጀመር።

እሄ ሁሉ ሲሆን ዋህድ ብቻውን በጨለማው ከምድረበዳው መካከል ሁኖ በፍርሀት ይንቀጠቀጣል። ወደ ምሽቱ አቅራቢያ የወፎች ጫጫታ እንደ ባልንጀራ ሁኖት ነበር። ኋላ ግን ያራዊት ድምጥ በቀኝና በግራው ከበበው ተጨነቀ። ከዚያው እንዳያነጋ ቤት የለ ተምን ይጠጋና ይደር። ተሜዳው ላይ እንዳያድር አራዊት ሊናጠቁት ሆነ። ዋህድ በዚህ ጊዜ ምን ያድርግ። ከዚያው ተኝቶ አውሬ ሲበላውስ ቢሆንለት በቁሙ እየተከላከለ መጓዙን መረጠና ምንም ቢሆን ታየሁት መደበር ሳልደርስ አላድር ብሎ ሲሄድ ሲሄድ ጨለማው እያደር ባሰ። ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ሆነበትና መንገዱም ጠፋው ልቡም መባባት ጀመረ።

በቀኝም በግራም በፊትም በኋላማ ቢያይ ሁሉ ጅብ ሁሉም ነብር ሁሉም አንበሳ መሰለው። ታሁንን አሁን ጅቡ ሳላየው መጥቶ ጐኔን ይዘበትረኛል፣ ነብሩም ዘሎ ያንቀኛል፣ ወይ አንበሳው ይሰብረኛል። ወይኔ ሆየ ዛሬ ታንዱ ባመልጥ መቸም ታንዱ አላመልጥ እያሉ ነብሱ ብንን ብንን ማለት ብቻ ሆነ ሥራው። ምን ያድርግ ዋህድ ፍርዱ ነው። ደግሞም ገና ጮርቃ ልጅ ነው።

ዋህድ እሄ ሁሉ ሲሆን ያን መደበር ያየበትን አንጣር ይዞ ቀስ ቀስ እያለ መጓዙን አልተወም ነበር። አንድ ጊዜ ግን በጨለማው አሻግሮ አንድ ቍጥቋጦ መሳይ አየና አራት እግር ያለው የውነተኛው አንበሳ መሰለውና ነብስና ሥጋው ተለያየበት። ጕልበቱ እየተብረከረከ ትክ ብሎ ሲያየው ጊዜ ያው በፍርሀት የተፈጠረ አንበሳ የሚንቀሳቀስ ዘሎም ሊይዘው ልበልን ልተው የሚል መሰለው። በዚህን ጊዜ ዋህድ ብልሀት ያገኘ መስሎት ለዚያ አንበሳ ብዙ ሰው የመጣበት እንዲመስለው ብሎ ድምጡን ባሥር ባስራምስት አይነት እያደረገ።

አንድ ጊዜ ቃሉን ከፍ፣ አንድ ጊዜ ዝቅ፣ አንድ ጊዜ ቀጭን፣ አንድ ጊዜ ጐርናና እያደረገ እንዳንድ መንጋ ሰው እየጮኸ “ክበብ አያምልጥህ አይዞህ በዚያ እለፍ” እያለ ድምጡን አንዱን ባንዱ ላይ እያነባበረ ይጯጯህ ገባ። ዋህድ ግን ብቻውን አንድ ፍጥሩን ነበረ። ከጨለማው ጋር እየተደባለቀ ይሳከር ተነበረው ተገዛ ጥላው በቀር የዚያን ጊዜ ምንም ባልንጀራ አብሮት አልነበረ።

ያ በከንቱ የታማ ቍጥቋጦ ምንም ባንበሳ ስም ቢጠራ ነብስ የለውምና አልሸሽለት ሲል ጊዜ ዋህድ መንገድ ሰብሮ ይሄድ ጀመር። ዙሮ ባየው ጊዜ ግን ያው በገዛ ፍርሀቱ የፈጠረው የቍጥቋጦ አንበሳ የሚከተለው መሰለው። ዋህድ ሆየ ጕልበቱም በፍራት እየተብረከረከበት መሄድ ተሳነው። ከዛፍ ላይ ተሰቅሎም እንዳያመልጥ ከዚያ ምድረበዳ እንዳጋጣሚ ሁሉ እንኳን ትልቅ ዛፍ፣ የምጣድ መሰቅሰቂያ የሚሆን እንጨትም አልነበረ።

ተዚህማ ወዲያ ለዋህድ ጨነቀው። ፍርሀቱም እያደረ ነገሠበት። የሚያየውም ጥቁር ነገር ሁሉ አውሬ ብቻ መሰለው። ከፍና ዝቅ እያለ በዳባቱ እያየ መንገድ እየለወጠ ሲሄድ ሲሄድ በግራው በኩል አንድ ትንሽ ዋሻ መሳይ ላይኑ ደርሶ ገች አለበትና ዋህድ መብረክረኩ ባሰ። በድንጋጤ ቀጭን ላብ መጣና በገላውም በፊቱም ተሰረጨበት። ታንዱ አንበሳ ባመልጥ ታንደኛው ደግሜ ደረስሁ። አሁንስ ቁርጥ ነው አላመልጥም እያለ ዋህድ ይጨነቅ ጀመር።

ቁሞ እንደ ቄጠማ እያረገረገ ድምጡን እንደ ፊተኛው በያይነቱ ከፍና ዝቅ እያደረገ በውሀ ጥማት የከረረው ጕረሮው እስቲነቃና እስቲሰነጠቅ ድረስ “ክበብ አያምልጥህ” እያለ ይጮህ ጀመር። ነገር ግን ሲያየው ጊዜ ምንም አይሸሽለት። የናቀኝ ይመስለውና እንደገና አጥብቆ ተንጠራርቶ ሲጮህ ጊዜ ያው ነው።

ኋላ ግን ድምጡም ሰለለበት፣ ጕረሮውም ይብሰውን ተዘጋበት። ከዚያ ታሥር ታሥራምስት አይነቱ ድምጡ አንዱንም አይነት ለመጮህ ቸገረው። ያው የውሸት አንበሳም ንቆት ዝም ያለው መሰለው። ዋህድ ከዚህ በኋላ መጠርጠር ጀመረ። ድንገት ሌላ ነብስ የሌለው ጥቁር ነገር ይሆን ማለት ጀመረ። ቀጥሎ በውል ለማስተዋል በጕልበቱ ተንበረከከና ትክ ብሎ አሁንን አሁን ይንቀሳቀስ ይሆን እያለ ሲመለከት ጥቂት ጥቂት የሚንቀሳቀስ መሰለው።

በዚህን ጊዜ ውልውሉ ቀረና የውነት አውሬ መሰለው። ዓይኑን ሳያጥፍ ትኩር ብሎ እንደገና ባስተዋለ ጊዜ ይልቁንም ተመንቀሳቀሱ ወደሱ መራመድ የጀመረ መሰለው። ዓይኑን ሳያጥፍ ትኩር ብሎ እንደገና ባስተዋለ ጊዜ ይልቁንም ተመንቀሳቀሱ ወደሱ መራመድ የጀመረ መሰለው። ዓይኑ ትኩር ብሎ በማየት የተነሣ እንባ ሞላበት። ዋህድ ግን ጊዜ የጠፋሁ መስሎት እንባውን መጥመቅ ትቶ ባየ ጊዜ ይልቁንም ያ እንባው እያደናገረው የዚያ አውሬ አረማመዱ ወደሱ የተፋጠነ አስመሰለው።

በመጨረሻ ግን ዋህድ ዓይኑን ከዚያው አውሬ ላይ እንደተከለ ባባና ተተንበረከከበት ጠጠር አፍሶ ወደ ፊቱ ብትን አደረገ። ለመከራ አጋዥ አይታጣምና ዋህድ ላደረገው ሁሉ ነገር ምስክር ሁና ተሸሽጋ ስታይ የነበረች አንድ ድርጭት ተተሸሸግሁበት ተገለጥሁ ብላም እንደሆነ አይታወቅ እሳር ቅጠሉን በክንፉያ አስሸብራ ተነሥታ በረረች። ዋህድም ያው አውሬ ደርሶ አነቀኝ መስሎት ትንፋሹን አቋርጦ እንደሞተ ታለበት ተንዘራጋና መንቀሳቀሱም ቀረ።

ቆይቶ ቆይቶ ግን ነብሴ አለችን ሙቻለሁ ብሎ አሰበ። ቀጥሎም ታውሬው መነከስና አለመነከሱን ለማወቅና ለመረዳት በጆሮው ቢያንቋቋ ምንም አልሰማህ አለው። ዓይኑን ግን አውሬው ሲነክሰው ጨክኖ ማየቱን ቢፈራ ጨፍኖት ነበርና ሲፈር ሲቸር ገርበብ አርጎ ቢያይ ተፊቱ እንኳን አንበሳ ምንም ጥንቸል እንኳ አልነበረም።

ዋህድ ከዚህ ወዲያ ነብስ አጋባና ጫን ተንፍሶ ተነሣ። አሻግሮ ባየ ጊዜ ያ አውሬ ጥንት ተነበረበቱ አይንቀሳቀስ፣ ምን አይል፣ ዝም ብሎ አየው። ዋህድ ከዚህ ወዲህ ትልቅ አሳብ ገባውና፣

“ወይስ ምንም አውሬ አልመጣም ኑሮዋል ወይስ አውሬም አይደል ኑሮዋል። ለዚያውም ሲመጣ ባይኔ አይቸዋለሁ። ወይስ ነካክሶ ጥሎኝ ሄደ” እያለ ገላውን ቢዳስስ አልተነካም።

“ምን ይሆን በገዛ ፍራቴ ባብቸ ኑሮአል መውደቄ። እንኳም ሰው አላየኝ በገዛ ፍርሀቱ ወንድ ልጅ ሁኖ እንዴ ይወድቃል!”

እያለ እየተደመመ እንደገና ጉዞውን ያዘ።

.

አፈወርቅ ገብረየሱስ

1900 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ልብወለድ ታሪክ”። ፲፱፻ ዓ.ም። ገጽ ፲-፲፱።