“ልብወለድ ታሪክ”
በአፈወርቅ ገብረየሱስ
(1900 ዓ.ም)
.
.
አንድ ቀን ግን ማታ ምድር ጦቢያ ቅጠሉን አብስላ ሰባብቃ፣ ከምንቸቱ ወደ ቆሬው ዘርግፋ፣ እንደልማዳቸው ሶስቱም ቀርበው ሲበላሉ የዝያን ለጋስ ነጋዴ ነገር እያደነቁ፣ ወዲአውም ‘እሄ ገንዘብ መቸ ተጠራቅሞልን መቸ ገንዘቡን ሰደን እስተመቸ ታባታችን ጋር ዓይን ላይን እንተያይ ይሆን ገና ነውና ነገሩ’ እያሉ እየናፈቁ በየጊዜው ምግባቸውን እያቋረጡ ሲነጋገሩ ከሄት መጣ ሳይባል የተገደበውን መዝጊያ ገፋ አድርጎ ገብቶ አንድ ሰው ተፊታቸው ቀጥ አለ።
ሶስቱም ደነገጡና ቀና አድርገው ቢያዩ ያው የሚመኙት ተሽጦ የነበረው ሰዋቸው ሆነ። ነገር ግን ህልም መሰላቸው እንጂ በውናቸው የሚያዩት አልመስላችሁ አላቸው። እሱም እንደገባ ምሽቱንም ልጆቹንም አንድነት ባየ ጊዜ በናፍቆትና በነዚያው ፍቅር ስስት ፈዘዘና እንባ እያነቀው መናገር ተሳነው። እነሱም መብረክረክ እንዲያው መፋዘዝ እንጂ ለጊዜው ለመነሣትም ለመነጋገርም አልሆነላቸው።
ቆይተው ቆይተው ግን ህልምነቱ ቀርቶ በውነት እሱ አባታቸው መሆኑን አወቁና ነብስ ገዝተው ምሽቱም ልዦቹም አንድነት ተነሥተው እየተላቀሱ ባንገቱ ላይ ይረባረቡበት ጀመረ። ተነዚአው ተሶስቱ ተወገቡም የተጠመጠመ ታንገቱም የተንጠለጠለ ጉልበቱንም የታቀፈ አለ። የዚአን ጊዜ ላያቸው ሰው እንኳን ለተወለዳቸው ላልተዘመዳቸው ለጠላታቸውም ቢሆን ያሳዝኑ ያስለቅሱ ነበር። አባትዮውም የዚህን ጊዜ ቃሉን እንባ እያቋረጠው አንዱን አንድ ጊዜ፣ አንዱን አንድ ጊዜ በየራሳቸው አቅፎ እየያዘ እንዴት ናችሁ እንደምን ናችሁ ይላቸው ጀመር።
ቀጥሎም ለሁሉም አንድነት አድርጎ እንባውን በመሀርሙ እየጠራረገ
“ያን ያህል ወርቅ ወዴት አገኛችሁና ሰዳችሁ ከባርነቴ ከተሸጥሁበት አስለቃቅችሁኝ። እኔ እንኳ ገንዘብ ማጠራቀም አላውቅ ነበር ወዴት አገኛችሁት” አላቸው።
እነሱ ግን ለገናው ገንዘቡን ቢሆንላቸው አጠራቅመው ሰደው ለማስለቀቅ እንጂ ከዚያ በፊት አለመስደዳቸውን አውቀው ነገሩ አረቀቀባቸውና የሚመልሱት ቃል አጡ። ብቻ እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር። በዚሁ መሀል አንድ ቃል የሚመልስለት ባጣ ጊዜ አባትዮው ወደ ዋህድ ዞረና፣
“አንተ ትሆን ልዤ ወዴት አገኘኸው” አለና ጠየቀው።
በዚህ ጊዜ ዋህድ ምን ይመልስ እሱ እንዳልሰደደ ያውቅ ነበር። በኋላ ግን ገና አባትዮው ዓይን ዓይኑን እየተመለከተ ምላሽ ሲጠብቅ ዋህድ የዚያ ለጋስ ሰው ነገር ውል አለውና፣
“አሁንስ ገንዘብ የሰደደውና አንተን ያስለቀቀህን ሰው አወቅሁት። አባየ እኔ አልምሰልህ”
አለና ታሪኩን የዚያን ለጋስ ነጋዴ ነገር ለሱም ገንዘብ መስጠቱን ኋላም ያባቱን ስም የገዛውን አረመኒም ስም ያለበትን ያገሩንም ስም መጠየቁን ሁሉንም ተረከለት።
አባትዮውም ነገሩን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ደነቀውና ከላይም ክርስቶስን ከታችም ያን ለጋስ ያመሰግን ይመርቅ ጀመር። ከዚህ ቀጥሎም እሄው የጥንት ደጃዝማች ለዋህድ እንዲህ አለው።
“ልጀ ያ ለጋስ እኔን ሳያውቅ ሳይጠይቅ ሳይወለደኝ ሳይዘመደኝ ያን ያህል ገንዘቡን አጥፍቶ ለገዛኙ ጌታ ከፍሎ አስለቀቀ። ወዳገሬ ስመለስ እንዳልደክም ጮሌውን ፈረስ አድርጎ፣ እንዳልራብ ስንቁን ጨምሮ ሰዶ፣ እሄው ላገሬ ለወንዜ ለቤቴ ለምሽቴ ለልጆቸ አበቃኝ፣ ደስታየን ዓለሜን አሳየኝ። ስለዚህ እኔም አሁን ምንም ትልቅ ወረታ ባልመልስለት ባይሆን እንኳ ሂጀ ታለበት እግዚአብሔር ይስጥህ እንድለው ወዳለበት ምናልባች ወደ ንግዱ አልሄደ እንደሆነ ምነው ብትመራና ብትወስደኝ። አሁንም ቶሎ ውሰደኝ” አለና ነገረው።
ዋህድ ግን ተመልኩ በቀር የዚያን ሀብታም ነጋዴ እንኳን ስሙን አገሩንም ለይቶ አያውቅ አልጠየቀምም ነበርና ተጨነቀ።
“እንግዴህ ያን ደግ ሰው ያን መሳይ ለጋስ ሰው፣ ያባቴን ታዳጊ፣ የናቴን የቴን የኔን እንባ አድራቂ፣ ወዴቱን መልሸ ብሄድ አገኘዋለሁ። እሱን ለማግኘት ምን ባረግ በተሻለኝ” እያለ ተጨነቀና በመጨረሻ “እሱን ታላገኘሁና ያባቴን በደህና መድረስ፣ የኛን ደስታ የኛን ዓለም ታልነገርሁት እግሬ እስቲነቃ እስትሞትም ቢሆን ዓለሙን እየዞርሁ እፈልገዋለሁ እንጂ ተቤቴ አልቀመጥም”
ብሎ ሲያቆም ዋህድ ስንቁን ቋጥሮ ዘንጉን ይዞ በማግስቱ ከዘመዶቹ ተላቅሶ ተለያይቶ ፍለጋ ተነሣ።
ዋህድ ከቤቱ እንደተነሣ መንገዱን ያን ሀብታም ነጋዴ ታንድ ትልቅ ከተማ ዳር ሰፍሮ ነውና ያገኘው ወደዚያው ከተማ አቀና። ከዚያውም በደረሰ ጊዜ ተከተማው ሳይገባ በፊት ዓይኑን ያቀና የዚያ ነጋዴ መደበር ወደነበረበቱ መስክ ነው። የመደበሩን ስፍራ እያየ ያን ደግ አድራጊውን ሰው እያሰበ ልቡ ተዋለለበት። እንባውም ባይኑ ተንቸረፈፈበትና ተቆመበት ላይ ቁጭ አለ።
ከዚያው አለቃቀሰና ሲነሣ ያን አሮጌ መደበር አጕድኖ እያየ አንገቱን እስቲጣምነው እግሩንም እንቅፋት እያከሰለው ሁሉንም ቁም ነገር ሳይል ፊቱን ወደዚያው አሮጌ ሰፈር እንዳዞረ ተከተማው ገባ። ነገር ግን ከዚያው ከተማ ገብቶ ምን ያድርግ። የዚያን ሰው ስም አያውቅ እገሌ ብሎ አይጠይቅ። ቤቱን አያውቅ ወደ ቤቱ አይሄድ። ምን ያድርግ ድሮ ዋህድ አሳቡ ሁሉ ተልከሰከሰበት።
እንዲያው እንደ ሞኝ እንደ ንክ ታውራ መንገድ መካከል ቆመና የሚሄድበቱን ሳያውቅ ይዋልል ጀመር። የቤት ልጅ ነው መከራ ከጥቂት ጊዜ በቀር አይቶት አያውቅ። በዚህ ጊዜ ውሀ ጥም ታከለበት እራብም ይመተልገው ጀመረ። ቶሎ ቶሎም ያንቧቅስ፣ ዓይኑም እንባ ይቋጥር ጀመር። እሄ ሁሉ ሲሆን ዋህድ ባደረገው ነገር አይጠጠትበትም። ያን ደግ ሰው ለመፈለግ እድሜውንም ልክ ቢሆን እንዳይገበዝ አንድ ጊዜ በልቡ ቆርጦ ፈክሮ ተነሥቷል።
እራቡና ጥሙ ሲበረታበት ጊዜ ዋህድ ምንጭ ፈለገና ከዚያ ምንጭ አጠገብ በመቍነን ተስንቁ በላና ከምንጩ ተደፍቶ ጠጣና ተመስገን ጌታዬ ብሎ ወደ ፍለጋው ተነሣ። ከዚህ ወዲያ ያን ነጋዴ ለማግኘት ዋህድ በያደባባዩም፣ በየገበያውም፣ በየጐዳናውም፣ በየደጀ ሰላሙም፣ በየቤቱ በየበሩ፣ በየመጋቢያው፣ በየቤተክርስቲያኑም እየገባ እየዞረ ቢፈልግ አጣው የማይሆንለት ሆነ። ዋህድ ተስፋውን ቆረጠ።
ከዚያ ከተማ መፈለግ ተጀመረ አሥራምስት ቀኑ ሆነ። እሄን አሥራ አምስት ቀን ሙሉ ዋህድ ቀን ቀኑን ሲፈልግ እየዋለ ማታ ማታውን ጅብ እንዳይበላው ከየቤተ ክርስቲያኑ ዚነጋባ እየገባ ነበር የሚያድር። ያ ሀብታም ነጋዴ ከዚያ ከተማ አለመኖሩን እርግጡን ተረዳውና እንግዴህ ወዴት ሂጄ ልፈልገው ሲል አሳብ ገባው። አስቦ አስቦ የተሻለ ነገር ያገኘው በየነጋዴው መደበር በየነጋዴው ጉዞ እየሄደ እየዞረ መፈለግ ብቻ ሆነ። የዋህድ አሳብ በዚህ ቆመ።
እሄን በመከረ በማግስት ዋህድ ከዚያ ከተማ ወጣና በሄትም ሳይል አንዱን መንገድ ይዞ መደበር ፍለጋ ይጓዝ ጀመር። ይሄድ ይሄድና ከጉብታ ላይ ወጥቶ ባገሩ ዙሪያ ወይ መደበር ወይ የነጋዴ ጉዞ ለማየት ይመለከታል።
ሰውም ተመንገድ ሲገጥመው መደበርና ነጋዴ ብቻ ነው የሚጠይቅ። ነጋዴ በዚህ አለፈ ከዚህ ሰፈረ ያሉት እንደሆነ ወደዚያው ሲሮጥ እየሄደ ከነጋዴው መሀል ያን ደግ አድራጊውን ነጋዴ ይፈልጋል። መልኩን ካላየው በቀር ስሙን አያውቅምና የሚፈልገውን ሰው ተነጋዴዎቹ አንዱ ‘እገሌ ወዴት ነው ወዴት ደረሰ’ ብሎ መጠየቅ አይሆንለትም ነበር።
ከዚያ መደበር ሳያገኘው ጊዜ ወደ ሌላው መደበር ፍለጋ ሲሄድ ሲሄድ ተመሸበት ሲያድር ዋህድ ሆየ አንድ ቀን ሲጓዝ ውሎ መንደር ተሌለበት ከምድረ በዳ ደረሰ። ከዚያው ምድረበዳ መሀል በሩቁ ትልቅ የነጋዴ ሰፈር አየ። ነጋዴ መሆኑንም በመደበሩ ለየው። ዋህድ ያነን መደበር ባየ ጊዜ ነገሩ አደባበሩም መጠኑም ያን ሀብታም ነጋዴ ያየ ጊዜ ያየውን መደበር መሰለውና ለጊዜው ደስ አለው። ተዚያ ሰፈር ለመድረስ አሰበና ይባክን ይሮጥ ጀመረ። ወንዛወንዝ የበዛበት ሜዳ ነበርና ቢለው ቢለው እርቀቱ ያው ነው። መደበሩ በመጫኛ አስሮ ወደኋላ እንደጐተቱት ሁሉ ወደኋላ የሚርቅ እንጂ የሚቀርብ አልመስለው አለ። መንገዱ ቢሄደው ቢሄደው አልገፋህ አለው። ጊዜው ግን ተማሸ ፀሐይቱም ተቆለቆለች።
ዋህድ ግን ከመደበሩ ሳልደርስ አላድርም ብሎ ፈክሮ ተሎ ተሎ ይራመድ ይሮጥ ጀመር። ነገር ግን ሳይደርስ በፊት ምድር መሸበት። በመሀል ቤት ጀንበር ጠለቀችና ድንግዝግዝ አለ። ቀጥሎም ጨለመና ላይን ነሳ። በወፎች ጫጫታ ስፍራ የፌንጣው ድምጥና የጓጕንቸሩ በያረንቋው በየረግረጉ ያለው ጕርጥ ዋካታ ተተካበት። ይልቁንም በዚሁ መሀል ባንድ ወገን ተኵላው፣ ባንድ ወገን ቀበሮው ሲጯጩአህ ሳለ፣ ባንድ ወገን ጅቡ እሙኝ ይል፣ ነብሩ ያጓጉር፣ አንበሳው ይገስል ጀመር።
እሄ ሁሉ ሲሆን ዋህድ ብቻውን በጨለማው ከምድረበዳው መካከል ሁኖ በፍርሀት ይንቀጠቀጣል። ወደ ምሽቱ አቅራቢያ የወፎች ጫጫታ እንደ ባልንጀራ ሁኖት ነበር። ኋላ ግን ያራዊት ድምጥ በቀኝና በግራው ከበበው ተጨነቀ። ከዚያው እንዳያነጋ ቤት የለ ተምን ይጠጋና ይደር። ተሜዳው ላይ እንዳያድር አራዊት ሊናጠቁት ሆነ። ዋህድ በዚህ ጊዜ ምን ያድርግ። ከዚያው ተኝቶ አውሬ ሲበላውስ ቢሆንለት በቁሙ እየተከላከለ መጓዙን መረጠና ምንም ቢሆን ታየሁት መደበር ሳልደርስ አላድር ብሎ ሲሄድ ሲሄድ ጨለማው እያደር ባሰ። ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ሆነበትና መንገዱም ጠፋው ልቡም መባባት ጀመረ።
በቀኝም በግራም በፊትም በኋላማ ቢያይ ሁሉ ጅብ ሁሉም ነብር ሁሉም አንበሳ መሰለው። ታሁንን አሁን ጅቡ ሳላየው መጥቶ ጐኔን ይዘበትረኛል፣ ነብሩም ዘሎ ያንቀኛል፣ ወይ አንበሳው ይሰብረኛል። ወይኔ ሆየ ዛሬ ታንዱ ባመልጥ መቸም ታንዱ አላመልጥ እያሉ ነብሱ ብንን ብንን ማለት ብቻ ሆነ ሥራው። ምን ያድርግ ዋህድ ፍርዱ ነው። ደግሞም ገና ጮርቃ ልጅ ነው።
ዋህድ እሄ ሁሉ ሲሆን ያን መደበር ያየበትን አንጣር ይዞ ቀስ ቀስ እያለ መጓዙን አልተወም ነበር። አንድ ጊዜ ግን በጨለማው አሻግሮ አንድ ቍጥቋጦ መሳይ አየና አራት እግር ያለው የውነተኛው አንበሳ መሰለውና ነብስና ሥጋው ተለያየበት። ጕልበቱ እየተብረከረከ ትክ ብሎ ሲያየው ጊዜ ያው በፍርሀት የተፈጠረ አንበሳ የሚንቀሳቀስ ዘሎም ሊይዘው ልበልን ልተው የሚል መሰለው። በዚህን ጊዜ ዋህድ ብልሀት ያገኘ መስሎት ለዚያ አንበሳ ብዙ ሰው የመጣበት እንዲመስለው ብሎ ድምጡን ባሥር ባስራምስት አይነት እያደረገ።
አንድ ጊዜ ቃሉን ከፍ፣ አንድ ጊዜ ዝቅ፣ አንድ ጊዜ ቀጭን፣ አንድ ጊዜ ጐርናና እያደረገ እንዳንድ መንጋ ሰው እየጮኸ “ክበብ አያምልጥህ አይዞህ በዚያ እለፍ” እያለ ድምጡን አንዱን ባንዱ ላይ እያነባበረ ይጯጯህ ገባ። ዋህድ ግን ብቻውን አንድ ፍጥሩን ነበረ። ከጨለማው ጋር እየተደባለቀ ይሳከር ተነበረው ተገዛ ጥላው በቀር የዚያን ጊዜ ምንም ባልንጀራ አብሮት አልነበረ።
ያ በከንቱ የታማ ቍጥቋጦ ምንም ባንበሳ ስም ቢጠራ ነብስ የለውምና አልሸሽለት ሲል ጊዜ ዋህድ መንገድ ሰብሮ ይሄድ ጀመር። ዙሮ ባየው ጊዜ ግን ያው በገዛ ፍርሀቱ የፈጠረው የቍጥቋጦ አንበሳ የሚከተለው መሰለው። ዋህድ ሆየ ጕልበቱም በፍራት እየተብረከረከበት መሄድ ተሳነው። ከዛፍ ላይ ተሰቅሎም እንዳያመልጥ ከዚያ ምድረበዳ እንዳጋጣሚ ሁሉ እንኳን ትልቅ ዛፍ፣ የምጣድ መሰቅሰቂያ የሚሆን እንጨትም አልነበረ።
ተዚህማ ወዲያ ለዋህድ ጨነቀው። ፍርሀቱም እያደረ ነገሠበት። የሚያየውም ጥቁር ነገር ሁሉ አውሬ ብቻ መሰለው። ከፍና ዝቅ እያለ በዳባቱ እያየ መንገድ እየለወጠ ሲሄድ ሲሄድ በግራው በኩል አንድ ትንሽ ዋሻ መሳይ ላይኑ ደርሶ ገች አለበትና ዋህድ መብረክረኩ ባሰ። በድንጋጤ ቀጭን ላብ መጣና በገላውም በፊቱም ተሰረጨበት። ታንዱ አንበሳ ባመልጥ ታንደኛው ደግሜ ደረስሁ። አሁንስ ቁርጥ ነው አላመልጥም እያለ ዋህድ ይጨነቅ ጀመር።
ቁሞ እንደ ቄጠማ እያረገረገ ድምጡን እንደ ፊተኛው በያይነቱ ከፍና ዝቅ እያደረገ በውሀ ጥማት የከረረው ጕረሮው እስቲነቃና እስቲሰነጠቅ ድረስ “ክበብ አያምልጥህ” እያለ ይጮህ ጀመር። ነገር ግን ሲያየው ጊዜ ምንም አይሸሽለት። የናቀኝ ይመስለውና እንደገና አጥብቆ ተንጠራርቶ ሲጮህ ጊዜ ያው ነው።
ኋላ ግን ድምጡም ሰለለበት፣ ጕረሮውም ይብሰውን ተዘጋበት። ከዚያ ታሥር ታሥራምስት አይነቱ ድምጡ አንዱንም አይነት ለመጮህ ቸገረው። ያው የውሸት አንበሳም ንቆት ዝም ያለው መሰለው። ዋህድ ከዚህ በኋላ መጠርጠር ጀመረ። ድንገት ሌላ ነብስ የሌለው ጥቁር ነገር ይሆን ማለት ጀመረ። ቀጥሎ በውል ለማስተዋል በጕልበቱ ተንበረከከና ትክ ብሎ አሁንን አሁን ይንቀሳቀስ ይሆን እያለ ሲመለከት ጥቂት ጥቂት የሚንቀሳቀስ መሰለው።
በዚህን ጊዜ ውልውሉ ቀረና የውነት አውሬ መሰለው። ዓይኑን ሳያጥፍ ትኩር ብሎ እንደገና ባስተዋለ ጊዜ ይልቁንም ተመንቀሳቀሱ ወደሱ መራመድ የጀመረ መሰለው። ዓይኑን ሳያጥፍ ትኩር ብሎ እንደገና ባስተዋለ ጊዜ ይልቁንም ተመንቀሳቀሱ ወደሱ መራመድ የጀመረ መሰለው። ዓይኑ ትኩር ብሎ በማየት የተነሣ እንባ ሞላበት። ዋህድ ግን ጊዜ የጠፋሁ መስሎት እንባውን መጥመቅ ትቶ ባየ ጊዜ ይልቁንም ያ እንባው እያደናገረው የዚያ አውሬ አረማመዱ ወደሱ የተፋጠነ አስመሰለው።
በመጨረሻ ግን ዋህድ ዓይኑን ከዚያው አውሬ ላይ እንደተከለ ባባና ተተንበረከከበት ጠጠር አፍሶ ወደ ፊቱ ብትን አደረገ። ለመከራ አጋዥ አይታጣምና ዋህድ ላደረገው ሁሉ ነገር ምስክር ሁና ተሸሽጋ ስታይ የነበረች አንድ ድርጭት ተተሸሸግሁበት ተገለጥሁ ብላም እንደሆነ አይታወቅ እሳር ቅጠሉን በክንፉያ አስሸብራ ተነሥታ በረረች። ዋህድም ያው አውሬ ደርሶ አነቀኝ መስሎት ትንፋሹን አቋርጦ እንደሞተ ታለበት ተንዘራጋና መንቀሳቀሱም ቀረ።
ቆይቶ ቆይቶ ግን ነብሴ አለችን ሙቻለሁ ብሎ አሰበ። ቀጥሎም ታውሬው መነከስና አለመነከሱን ለማወቅና ለመረዳት በጆሮው ቢያንቋቋ ምንም አልሰማህ አለው። ዓይኑን ግን አውሬው ሲነክሰው ጨክኖ ማየቱን ቢፈራ ጨፍኖት ነበርና ሲፈር ሲቸር ገርበብ አርጎ ቢያይ ተፊቱ እንኳን አንበሳ ምንም ጥንቸል እንኳ አልነበረም።
ዋህድ ከዚህ ወዲያ ነብስ አጋባና ጫን ተንፍሶ ተነሣ። አሻግሮ ባየ ጊዜ ያ አውሬ ጥንት ተነበረበቱ አይንቀሳቀስ፣ ምን አይል፣ ዝም ብሎ አየው። ዋህድ ከዚህ ወዲህ ትልቅ አሳብ ገባውና፣
“ወይስ ምንም አውሬ አልመጣም ኑሮዋል ወይስ አውሬም አይደል ኑሮዋል። ለዚያውም ሲመጣ ባይኔ አይቸዋለሁ። ወይስ ነካክሶ ጥሎኝ ሄደ” እያለ ገላውን ቢዳስስ አልተነካም።
“ምን ይሆን በገዛ ፍራቴ ባብቸ ኑሮአል መውደቄ። እንኳም ሰው አላየኝ በገዛ ፍርሀቱ ወንድ ልጅ ሁኖ እንዴ ይወድቃል!”
እያለ እየተደመመ እንደገና ጉዞውን ያዘ።
.
አፈወርቅ ገብረየሱስ
1900 ዓ.ም
.
[ምንጭ] – “ልብወለድ ታሪክ”። ፲፱፻ ዓ.ም። ገጽ ፲-፲፱።
One thought on ““ልብወለድ ታሪክ” (ክፍል 2)”