“ወደ አዲስ አበባ”
በሣህለ ሥላሴ ብርሃነማርያም
.
.
አባ ፍራንሷ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ ከመጡ በኋላ ዘመድ ቤት አስቀምጠውኝ ያን ጊዜ “ሐኪም ቦራ” ተብሎ ይጠራ በነበረው፣ በዛሬው ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል እንድታከም አደረጉ። ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እሳቸው የሚያርፉት ካቴድራል (ልደታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን) ስለሆነ እዚያ ቆዩ። የበሽታዬ ዓይነት ምን እንደነበረ ባይነገረኝም ባጭር ጊዜ ውስጥ ታክሜ ተፈወስኩ።
ከዚያ በኋላ ከአባ ጋር ወደ እምድብር ለመመለስ በምጠባበቅበት ጊዜ ወደ ክፍላቸው አስጠርተውኝ፣
“ልጄ … ወደ እምድብር ለመመለስ ትፈልጋለህ ወይስ እዚሁ አዲስ አበባ ቀርተህ ለመማር ትሻለህ?” ሲሉ ጠየቁኝ።
የሚቀልዱብኝ መስሎኝ ዝም ብዬ ተመለከትኳቸው። ፍጹም ያላሰብኩትና ሊሆን ይችላል ብዬ ያልገመትኩት ነበር። ከእምድብር ሚሲዮን ንፍሮ ተገላግዬ እዚህ አዲስ አበባ ልቀር? እንደ አዲስ አበባ ሰው ሁሉ እንጀራና ወጥ ብቻ ሳይሆን ያንን የቀመስኩትን የፈረንጅ ፉርኖ እየገመጥሁ ጣፋጩን ሻይ እየጠጣሁ ተንደላቅቄ ልኖር? ፈጽሞ አልመስልህ አለኝ።
“እዚህ ለመቅረት ከፈለግህ ላዛሪስት ሚሲዮን አስገባሃለሁ ልጄ” አሉኝ፤ “እና ምን ይመስልሃል?”
ደስታ ፈንቅሎኝ፤ “እውነትዎን ነው ወይ አባ?” አልኳቸው።
ያን ከፊታቸው የማይጠፋውን ፍልቅልቅታ እያሳዩኝ፤
“አዎን ልጄ … ላዛሪስት ሚሲዮን ውስጥ ላንተ የሚሆን አንድ ቦታ አይጠፋም” አሉኝ።
“ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ አባ!”
በማግስቱ ይሁን በሠልስቱ ወደ ላዛሪስት ሚሲዮን ለመጓዝ ከካቴድራል ወጣ ብለን ጋሪ አስቆምን። የዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ ዋናው የሕዝብ ማመላለሻ ጋሪ ነበር። እነ ኩርኩር (ባለ ሦስት ጎማው ማጓጓዣ)፣ እነ አውቶቡስ፣ እነ ሚኒባስና ውይይት ገባ አልገቡም። ፈረንጆችና ጥቂት ዘበናይ ኢትዮጵያውን ሹማምንት በታክሲ ይጓዙ እንደሆነ ነው እንጂ ሌላው የከተማው ነዋሪ በሙሉ፣ ከእግረኛው በስተቀር፣ በጋሪ ነበር የሚጓጓዘው … ከፒያሳ መርካቶ፣ ከለገሐር ጉለሌ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና፣ ከመርካቶ ኮልፌ፣ ወዘተርፈ።
ፈረሶቹ አስፋልቱን መንገድ ከኮቴአቸው ሥር በተገጠመላቸው የብረት መጫሚያ እያንቋቁ ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ የሚል ድምፅ እያሰሙ ሲያልፉ እስከ ዛሬ ድረስ በውስጥ ጆሮዬ ሲያስተጋባ ይሰማኛል። ስንቱን ጀግና ከጦር ሜዳ እንዳላደረሱ ሁሉ፣ የስንቱን ንጉሥ ስም አባ ዳኘው፣ አባ ዲና፣ አባ ታጠቅ፣ አባ ጠቅል እያሰኙ እንዳላስጠሩ ሁሉ እነ ዳማ፣ እነ ጉራች፣ እነ ቦራ፣ እነ ሻንቆ፣ ጣሊያን ባመጣው አዲሱ ሥልጣኔ ተዋርደው የጋሪ ጐታች ሆነው ቀሩ።
ፊት ለፊት እንጂ ግራና ቀኝ እንዳያዩ ለዓይናቸው ከለላ ይደረግላቸዋል። የጋሪዎቹ መቀመጫዎች በኋላ ዘመን በአሥመራ ከተማ እንዳየኋቸው የሚደሉ ባይሆኑም ለክፉ የሚሰጡ አልነበሩም። ባለጋሪዎቹ ከአናታቸው ቆብ፣ ከእጃቸው ጅራፍ አይለያቸውም። ደሞም ይዘፈንላቸዋል፤ “ባለጋሪው … ባለጋሪው … ቶሎ ቶሎ ንዳው …” እየተባለ። አቤት ዘፈኑ ለጆሮ ደስ ሲል!
አንዱን ባለጋሪ አስቁመን አባና እኔ ጋሪው ላይ ተሳፍረን ጉዞ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሆነ። ላዛሪስት ሚሲዮን የሚገኘው ከእንጦጦ ጋራ ሥር ነበር። “ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ” የሚል ድምፅ እያሰማ ተጉዞ ተጉዞ ከሚሲዮኑ መግቢያ በር አደረሰን። አባ ሂሳቡን ከፈሉትና ወደ ምድረ ግቢው አመራን።
ከእኔ በፊት ከየቦታው ተመልምለው መጥተው እዚያ የሚኖሩ ወጣት ተማሪዎች ምድረ ግቢው መሐል ላይ ባለው ሜዳ የእግር ኳስ እየለጉ ሲጫወቱ አየን። ይንጫጫሉ። አንዳንዶቹ በእኔው እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። አንዳንዶቹ ያበጡ ጐረምሶች ሲሆኑ የተቀሩት ከእኔ የሚያንሱ ትንንሽ ልጆች ናቸው።
አባና እኔ ኳስ ጨዋታውን መልከት ካልን በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል አመራን። እዚያ የነበሩት ፈረንጅ ካህንና አባ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሲጨዋወቱ እኔ ዝም ብዬ እሰማቸዋለሁ። የፈረንሳይኛ ፊደል የቆጠርኩ ቢሆንም በዚያን ጊዜ ቋንቋው አይገባኝም። ይሁን እንጂ አባና ሌላኛው ካህን ሲነጋገሩ ቋንቋው የተለምዶው ሙዚቃዊ ቃና ነበረው።
አባ ተነጋግረው ሲጨርሱ እኔው ተዚያው ትተውኝ ወደ ካቴድራል ማረፊያቸው ተመለሱ። ግቢውን የሚያስተዋውቀኝ ልጅ ተሰጥቶኝ እየተዘዋወርን ሚሲዮኑን ያስጐበኘኝ ጀመር። ጸሎት ቤቱን፣ የመኝታና የጥናት ክፍሎቹን፣ ቤተ መጻሕፍቱን፣ በሲሚንቶ የተሰሩ ንጽሕና ቤቶቹን አንድ በአንድ አስጐበኘኝ።
ከዚያን ቀን ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ያህል አብረን መኖር የጀመርነው ወጣቶች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጣን ነበርን። እና ሁላችንም አብረን ውለን አብረን እናድራለን። ወደ ተፈሪ መኰንን ት/ቤት እየተመላለስን እንማራለን። እሁድ እሁድ ወደ እንጦጦ እየወጣን ወይም ሸጎሌ ወደተባለው ሜዳ እየኼድን የእግር ኳስ እንጫወታለን።
የሚያስተዳድሩንና ተንከባክበው የሚያሳድጉን ካህናት አምስቱ ፈረንሳውያን ሲሆኑ አንዱ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፤ አባ ዢማላክ፣ አባ ብርዬ፣ አባ ሊሙዘን፣ አባ ጃንካ፣ አባ ማርሴ እና አባ አጽብሐ።
አባ ጃንካ በጣም ጉልበተኛ ሰው ነበሩ። እኛ ሁለት ወይም ሦስት ሆነን ተጋግዘን ማንሳት የማንችለውን ሸክም እሳቸው በአንድ እጃቸው፣ ያውም በግራ እጃቸው ብድግ ያደርጉት እንደነበረ አስታውሳለሁ። ቁመታቸው መሐከለኛ ሆኖ አጥንታቸው ሰፊ፣ ምንም ነገር ሊነቀንቃቸው የማይችል የግንብ አጥር የመሰሉ ነበሩ። ታንክ በመሰለ ከባድ መኪና ለሚሲዮኑ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ገዝተው የሚያመጡት እሳቸው ናቸው። እሁድ እሁድ ወደ እንጦጦ ጋራ ወይም ወደ ሸጎሌ ሜዳ በምንጓዝበት ጊዜ የፈረንጅ ኮርቻ በተጫነ ፈረስ ላይ ተቀምጠው የሚመሩን እሳቸው ናቸው።
አባ ማርሴ በሚሲዮናችን ብቻ ሳይሆን በተፈሪ መኰንን ት/ቤት ጭምር በጣም ዝነኛ ሰው ነበሩ። አባ ማርሴ የፈረንሳይ ተወላጅ ቢሆኑም አማርኛና ግእዝ አሳምረው ያውቁ ነበር። እንዲያውም በተፈሪ መኰንን ት/ቤት፣ ያውም በሁለተኛው ደረጃ፣ የአማርኛ ሰዋስው መምህር ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በአንዱ ብብታቸው ሸጉጠው፣ ከዘራቸውን በአንድ እጃቸው ይዘው ቢስኪሌታቸው ላይ ወጥተው እያሽከረከሩ ነበር ወደ ተፈሪ መኰንን ት/ቤት የሚጓዙት። እኛ ግን ወደ እዚያ የምንኼደውና ከዚያም ወደ ማታ ጊዜ የምንመለሰው አርባ አምስት ደቂቃ ያህል በእግር እየተጓዝን ነበር።
በመንገዳችን ካኪ ዩኒፎርም የለበሱ ልጃገረዶች ያጋጥሙናል። መጽሐፎቻቸውንና ደብተሮቻቸውን እንደ ሕፃን ልጅ በደረታቸው ታቅፈው ዱብ ዱብ እያሉ ያልፉናል። እኛ ሚሲዮን ቀጥቅጦ ያሳደገን በመሆናችን ቀና ብለን ልናያቸው ባንደፍርም እነሱ ግን ፈጽሞ አያፍሩንም ነበር። እየተሳሳቁ፣ የአቧራ ብናኝ እያስነሱ ወደ እቴጌ መነን ት/ቤት ያመራሉ። እቴጌ መነን ት/ቤትና ተፈሪ መኰንን ት/ቤት ቅርብ ለቅርብ ናቸው። በዚያን ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በተለያየ ት/ቤት እንጂ በአንድ ት/ቤት፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ጐን ለጐን ተቀምጠው መማር የማይታሰብ ነበር … በኋላ ዘመን ቢሻርም ቅሉ!
በትምህርት ቀናት ለምሳ ወደ ሚሲዮናችን ለመመለስ ሰዓቱ ስለማይበቃን እነ አባ ማርሴ ከተፈሪ መኰንን ት/ቤት አቅራቢያ ሆቴል ተኮናትረውልን ምሳችንን እዚያ እንበላ ነበር። ለእያንዳንዳችን ሃያ አምስት ሳንቲም ይሰጠን ነበር። ለምሳ መብያ። ያ ሃያ አምስት ሳንቲም ተአምር ይሰራ ነበር ለማለት እደፍራለሁ … ከዛሬው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር።
ሙሉ እንጀራ በሽሮ ወጥ በአስር ሳንቲም፣ በክንድ የሚለካ ፉርኖ በአስር ሳንቲም፣ በስንዝር የሚለካው በአምስት ሳንቲም፣ አንድ ብርጭቆ ሻይ በአምስት ሳንቲም ይገዛ ነበር። ሙሉ እንጀራ በሥጋ ወጥ ለመብላት የሚሻ በሃያ አምስት ሳንቲም አዝዞ ጥስቅ አድርጎ ይበላ ነበር። የዚያም ዓይነት ዓለም ነበር … በሺ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ!
በተፈሪ መኰንን ት/ቤት የሚማሩት ባልደረቦቻችን፣
“የአባ ማርሴ ልጆች
አንሶላ ለባሾች!”
እያሉ ያፌዙብን ነበር።
ይህም ከበስተጀርባው ታሪክ አለው። በበጋው ወራት በተለይም በታህሳስ ወር ጠዋት ጠዋት በጣም ይበርድ ነበር። በዚህ ምክንያት አሳዳጊዎቻችንን አስፈቅደን ለመኝታ የምንጠቀምበትን ነጭ አንሶላ ደርበን ነበር ወደ ትምህርት ቤታችን የምንጓዘው። ካፖርት እንዳንገዛ ከአቅማችንና ከደረጃችን በላይ ነው። ሌላም የብርድ መከላከያ አልነበረንም።
ታዲያ በአዳሪነት፣ ያውም ያለ ክፍያ ተሞላቅቀው የሚኖሩት ባልደረቦቻችን ችግራችንን ባለመረዳት ”የአባ ማርሴ ልጆች፤ አንሶላ ለባሾች“ እያሉ ያፌዙብን ነበር።
እነሱ አላወቁም እንጂ ሌላም የብርድ መከላከያ ነበረን። በዚያን ጊዜ ከመሐከላችን ጫማ የሚያደርግ ማንም የለም። ሁላችንም በባዶ እግር ነበር የምንኼደው። ወደ ት/ቤት ስንጓዝ በመንገዳችን የሚገኝ አንድ ደረቅ ወንዝ ስለነበረ በታህሳስ ወር ከዚያ ስንደርስ ቅዝቃዜው በጣም ስለሚበረታ ከሚሲዮናችን ስንነሳ አሮጌ ጨርቅ ይዘን እንመጣና እግራችንን በዚያ ጨርቅ ሸፍነን ሰርጓዳውን ስፍራ እናልፋለን።
ጨርቁን ወደ ትምህርት ቤታችን ይዘን ብንኼድ የባሰውን መሳቂያ ስለምንሆን ደረቁን ወንዝ ከተሻገርን በኋላ ጥሻ ውስጥ ወሽቀነው እንኼድና ማታ ስንመለስ ይዘነው ወደ ሚሲዮናችን እናመራ ነበር።
.
ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም
.
[ምንጭ] – “ፍኖተ ሕይወት”። 2001 ዓ.ም። ገጽ 51-56።
ሙሉ እንጀራ በሽሮ ወጥ በአስር ሳንቲም፣ በክንድ የሚለካ ፉርኖ በአስር ሳንቲም፣ በስንዝር የሚለካው በአምስት ሳንቲም፣ አንድ ብርጭቆ ሻይ በአምስት ሳንቲም ይገዛ ነበር። ሙሉ እንጀራ በሥጋ ወጥ ለመብላት የሚሻ በሃያ አምስት ሳንቲም አዝዞ ጥስቅ አድርጎ ይበላ ነበር። የዚያም ዓይነት ዓለም ነበር … በሺ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ!
LikeLike
1/ ታሪክ ራሱን ይደግማል? ኩርኩር (ባለ ሦስት ጎማ ማጓጓዣ) ባጃጅ ሆና ተመልሳ መጣች?
2/ “ስንቱን ጀግና ከጦር ሜዳ እንዳላደረሱ ሁሉ፣ የስንቱን ንጉሥ ስም አባ ዳኘው፣ አባ ዲና፣ አባ ታጠቅ፣ አባ ጠቅል እያሰኙ እንዳላስጠሩ ሁሉ እነ ዳማ፣ እነ ጉራች፣ እነ ቦራ፣ እነ ሻንቆ፣ ጣሊያን ባመጣው አዲሱ ሥልጣኔ ተዋርደው የጋሪ ጐታች ሆነው ቀሩ።”
አንድምታዎች፦ ከ “ፍኖተ ሕይወት” በተከታታይ ለማተም አስባችኋል?
LikeLike
Tiliq misgana lemaqreb neew. Mitawetuwachew tsihufoch hulu bizu eyastemarun yigegnalu.
LikeLike