“ግማሽ 1/2”
በሌሊሳ ግርማ
.
[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]
.
.
በአራቱም መአዘን ግንቡ ላይ ዓይኑ ስንጥቅ ፈልጎ ያገኘው በአንዱ በኩል ብቻ ነው። ስንጥቁ በግድግዳ ጠርዝ ላይ ቢሆን ኖሮ ቤቱ ውስጥ ያለውን ነገር ለማየት በቀለለው ነበር። ግን አልሆነም። አልተመቸም። ስለዚህም በአንደኛው ግድግዳ ላይ በተገኘው ትንሽ ሽንቁር ወደ ውስጥ ተመለከተ። የሚታየውን ለማየት።
ዓይኑ ያረፈበት ነገር ሁሉ ግማሹ ብቻ ነበር የሚታየው። የአልጋው ግራ ግማሽ፤ የሶፋው ጀርባ ግማሽ፤ የሚስትየው ግማሽ እግር – ትከሻ፣ በግማሽ እጅ የሚበጠረው የሚስትየው ፀጉር፣ ግማሽ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው የሕንድ ማርያም ስዕል ግማሽ። እማይንቀሳቀሱት ህይወት አልባ የሆኑት ነገሮች በሙሉ በስንጥቁ ዓይን ሲታዩ ዘላለም ግማሽ ሆነው እንደቀሩ ግልፅ ነው። ሙሉ እንዲሆኑ የግድግዳው ስንጥቅ ዓይን ወይ መስፋት አለበት አለበለዚያ ሌላ የተመቸ ቦታ ላይ ሄዶ መሰንጠቅ አለበት።
ለነገሩማ ከቤቱ ውጭ ሆኖ የሚያየው ዓይንም ከሁለት ዓይኑ በግማሽ ነበር እያየ የነበረው። የሚታየው አለም ግማሽ ጎዶሎ ሆኖት ተንከራተተ። ግድግዳ ላይ ያለው ስንጥቅ፣ የኔን ጽናት ይስጥህ ብሎ የመከረው መሰለውና ዓይኑ ለጽናት ልክ ሰውነት ክብደቱን ከአንዱ እግር ወደ ሌላው አስተላልፎ እንደሚያርፈው፤ አይኑም ከአንዱ አይን ወደ ሌላው ትዕግስቱን አቀያይሮ፣ እንደገና በሽንቁሩ ውስጥ አሳልፎ ወደ ቤቱ ውስጥ ማየቱን ቀጠለ። ሽንቁሩ ግን የሚያሳርፈውም ክብደት የሚቀያይረው ዓይን ስለሌለው፣ እንደ አሳ አይን ሁሌ በማይዘጋ ብሌኑ ውስጥ ሌላ ዓይን ሲሰልልበት ያለ ተቃውሞ ተባበረ።
በዛ ሁሉ ነገር ግማሽ በሆነበት ክፍል ውስጥ፣ አንድ የሆነች ነገር እየቦረቀች በግማሹ አልጋ፣ በግማሽ ሶፋ እና በግማሽ ሚስት መሀል ገብታ ሙሉ ስትሆን፣ በዚህ ሙሉ ነገር ደስታ ሙሉነቷን ለማድነቅ ዓይኑን የተቻለውን ያህል ከፈተ። ግን ዓይን ብቻ ስለሆነ ቤቱ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር መስማት አይችልም ነበር። የግድግዳውም ሽንቁር በዚህ ረገድ ሊተባበረው አልቻለም። ወይንም አልፈለገም።
ልጅቷ እናቷን የሆነ ነገር እያለቻት ነበር። ትንሽ ቆይቶ እናትየው በግማሽ እጇ ስታበጥረው የነበረውን ግማሽ ፀጉሯን ማበጠሪያውን እላዩ ላይ ትታ፣ ሌባ ጣቷን እጇ ላይ እያውለበለበች ቆይታ መልሳ ግማሽ ሶፋ ላይ ፀጉሯን ነስንሳ ማበጠር ቀጠለች።
የልጅቷ ፊት ላይ የተሳለው ፈገግታ በድንገት ተሰርዞ፣ መጀመሪያ እንደ ነጭ ገጽ ባዶ ሲሆን፤ ቆይቶ ደግሞ ሁለት ወይ ሶስት ቀን ለመሙላት እንደ ቀራት ትንሽ ጨረቃ ሞለል፣ ረዘም ሲል ሽንቁሩም ዓይኑም ታዘቡ። ልጅቷ ለጥቂት ሰከንዶች ቆማ ግድግዳ ግድግዳውን ሽንቁር ሽንቁሩን ስታይ ቆይታ፣ ድንገት ዞራ እየቦረቀች ወደ መጣችበት አቅጣጫ ተመልሳ ተሰወረች፣ መጀመሪያ ግማሽ ሆና ከዛ እሩብ … ከዛ ምንም።
ሚሚ በተሰወረችበት ቦታ ላይ ተጋርዶ የነበረ አዲስ ነገር ተተካበት። ግማሽ የመጽሐፍ መደርደሪያ ሼልፍ። ሼልፉ ግማሽ ይሁን እንጂ መጻሕፍቶቹ ሙሉ ሆነው ለዓይኑ ታዩት። ከዛ ርቀት አርእስታቸውን ማንበብ ባይችልም እንደ መጠጥ ጠርሙሶች የስካር መጠናቸውን፤ የአልኮል ይዞታቸውን ዓይኑ ያውቀዋል። አጣጥሟቸዋል። ሰክሮባቸዋል። እንደ ጣዕማቸው፣ እንደ ይዘታቸው፣ እንደ ጥንካሬአቸው ሙሉ የሆኑት ሙሉ ሆነው ባይታዩት እንኳን ሙሉነታቸው ይሰማዋል፤ ግማሽ የሆኑት ግማሽ፤ ግማሽ ሆነው ያልታዩት ደግሞ ጠፍተዋል። ዓይኑ ቀዳዳውን አደነቀው። ሽፋሽፍቶቹን እያርገበገበ ለሀቅ የሚሰጠውን ምስጋና ለገሰው። እውነት እንዲህ ነው የሚታየው ለካ!
ሚስትየዋ ፀጉሯን ይዛ ቦታ ለቀቀች። የማይንቀሳቀሱት ግማሽ ነገሮች ብቻቸውን ቀሩ። ሽንቁሩ እንደሚያቃቸው። ሳይሞካሹ።
ሚሚ ተመልሳ መጣች። አሁንም ግን ሙሉ ነች። ከነሁሉ ትንሽ ነገሯ። ስትመጣ ሙሉ ነች። ከሌለች ግን የለችም። የትልቅ ሰው ጫማ አድርጋለች። የአባቷን፤ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው መስታወት ጎን ተጠግታ እየተሸከረከረች ራሷን አደነቀች። ትንንሽ ደስ የሚሉ ጥርሶቿን ብልጭ እያደረገች። እጇን አፏ ላይ ከድና ፍርስ ብላ ሳቀች። እንደገና ተሰወረችና እንደገና ተከሰተች። የእናቷን ጌጥ እና ሊፕስቲክ ይዛለች። መስታወቱ ጋ ቆማ ቶሎ ብላ ከንፈሯን ከማዳረሷ በፊት ድምፅ እንደሰማች አይነት ከንፈሯን በፍጥነት በእጅጌዋ ጠረገችው። ጀርባዋን ወደ መስታወቱ አድርጋ ጌጡንና የከንፈር ቀለሙን አልጋ ስር ወረወረችው።
ግማሽ ሚስት፣ ግማሽ ዳሌዋን እያውረገረገች መጥታ ሚሚን ጋረደቻት። ግማሽ እጅ ወደ ላይ እየተነሳ ሲወርድ ቆይቶ፣ ግማሽ አጅ አልጋ ስር ራሱን ሰዶ የተጣለውን እቃ አነሳ። የማይታየው ግማሽ ሶፋ ላይ ሚስት ሄዳ ተሰወረች። ሶፋው ሲውረገረግ ዓይኑ እንደተቀመጠች አወቀ።
ሚሚ ድምፅ የሌለውን ለቅሶዋን ስታሰማ እንኳን ሙሉ ነበረች። የማይሰማው ለቅሶዋ እንኳን ሙሉ ነው። በእጇ አይኗን ሸፍና። በደንብ ያልተጠረገው ከንፈሯ … አገጯን ጨምሮ እንደቀለሙ ቀልቶ። ዓይኗን የማይታየው የሶፋ ጠርዝ ላይ ተክላ ትንሰቀሰቃለች። ሶፋው “ዝም በይ እንዳልደግመሽ!” የሚል ይመስላል። ሚሚ ትዕዛዝ በመቀበል አይነት አኳኋን የአባቷን ጫማ በፍጥነት አውልቅ አልጋ ስር መለሰች። ቀና ብላ ሶፋውን እያየች ለተጨማሪ ትዕዛዝ ተዘጋጀች።
አሁን፤ ሚሚ በግራው አልጋ ጎን ወጥታ ዓይኗን ጨፈነች። አባቷን እየናፈቀች እንደነበር ሁሉ ነገሯ ይናገራል። ዓይኑ ከውጭ በግድግው ስንጥቅ እየተመለከተ ‹‹እራቷን ሰጥተዋት ይሆን?›› ብሎ አሰበ። ሚሚ ብዙም ሳትቆይ እንቅልፍ ወሰዳት። ስትተኛ እንኳን ሙሉ ነች።
ዓይኑን ከስንጥቁ ሲነጥል፤ እማይሰማ፣ በጨረፍታ የሚያይ ዓይን መሆኑ ቀርቶ ሰው ሆነ፤ አባት ሆነ፤ ባል ሆነ።
የቤቱን ጓሮ ዞሮ በመግቢያው በኩል አንኳኳ፤ ሚስቱ ከፈተችለት። ፀጉርዋ አሁን ተበጥሮ ተስተካክሏል። አስተያየቷ እንዳለፉት ሳምንታት የጥላቻ ነው። ሰላም አላላትም ወደ ውስጥ ሲገባ። የተኛችው ሚሚ ጎን አልጋው ላይ ተቀመጠ። እራቷን በልታለች ወይ? ብሎ ሊጠይቅ አሰበና ግማሽ መልስ እንደሚሰጠው ስለሚያውቅ ተወው።
ለነገሩ እሱም አልበላም። የሱ እንኳን የታወቀ ነው። በኋላ እጇን ሲያገላብጥ ወጥ ነክቶት ስላየ በልታለች ብሎ ደመደመ። እምትበላው በማንኪያ ቢሆንም እጇ ዝቅ ብሎ ማንኪያ ቂጥ ስለሚይዝ የበላችው ነገር ሁሉ እጇ ላይ ምልክቱ ይቀራል።
ሚሚን ወስዶ የራሷ ትንሽ አልጋ ውስጥ ከቷት ተመልሶ መጥቶ ሶፋ ላይ መጽሐፍ ይዞ ቁጭ አለ። ሚስቱ በአግቦ እያወራች ቆይታ መጽሐፍ ቅዱሷን ይዛ በአልጋው ቀኝ ገብታ ጸለየች። ተኛች።
ባልየው በንባቡ መሐል ትዝ ብሎት ወደ ግድግዳው ፊቱን መልሶ ያንን ትዕግስተኛ ሽንቁር ፈለገው። ሊያገኘው አልቻለም። ከሶፋው ላይ ተነስቶ ሄዶ በቅርበት መረመረ። በጭቃው ግድግዳ ላይ ብዙ ስንጥቆች ቢኖሩም አንዱም ወደ ውጭ ሊያሳየው አልቻለም።
‘እንደ አምላክ ነብሴን ከውጭ ሆኜ ሳይ ነበር እንዴ?’ የሚል ጥያቄ መሰል ሐሳብ እንደ ወፍ በቃናው ላይ ተወንጭፎ ሲያልፍ የተሰማው መስሎት ነበር፤ ግን እርግጠኛ መሆን አልቻለም። ተመልሶ ሄዶ መጽሐፉን ማንበብ ቀጠለ።
.
ሌሊሳ ግርማ
.
(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)
[ምንጭ] – “እስቲ ሙዚቃ”። 2009 ዓ.ም። ገጽ 36-39።
Wow! I like it keep it up.
LikeLike