“ሳታመኻኝ ብላኝ”
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል
.
.
አያ ዥቦ ልጁ ሞተበትና ለነ እንኮዬ አህዩት “ልጄ ሞቷልና አላቅሱኝ” ሲል መርዶ ነጋሪ ላከ።
ተረጅዎቹም “እንግዲህ ሰምተን ብንቀር ይጣላናል ብንሄድም ይበላናል። እንዴት ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ምክር ዠመሩ። ነገር ግን “ቀርተን ከሚጣላን ሄደን ቢበላን ይሻላል” ብለው ተነስተው ልብሳቸውን አሸራርጠው ሄዱ።
ከለቅሶውም ቦታ እንደ ደረሱ አንደኛዋ ብድግ አለችና፣
“ምን አጥንት ቢሆን ይሰብራል ጥርስዎ
ምን ጨለማ ቢሆን እሾኽ አይወጋዎ
ምን ጥቍር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ
ያንን ጐራ ዞሮ ይሰማል ድምጥዎ
አሁን የርስዎን ልጅ ምን አገኘብዎ?” እያለች ሙሾ ታወርድ ዠመር።
እሱ ደግሞ ቀበል አለና፣
“አንችስ ደግ ብለሻል መልካም አልቅሰሻል
ይህ ሁሉ አዘንተኛ ምን ይብላ ብለሻል?” ሲል መለሰ።
እንዳልማራቸው ባወቁ ጊዜ እንግዲህ አለቀቀንም ምን ማድረግ ይሻለናል ብለው እነ እንኮዬ አህዩት ምክር ዠመሩ። አንዲት እናቷ የሞተችባት ውርንጭላ ከነርሱ ጋር ነበረችና ይህችን እንስጥና እንገላገል ብለው ሲነጋገሩ ግልገሏ አህያ ሰምታ፣
“ምነው እኔ ውርንጫ
ማ ይዞኝ በሩጫ” ብላ ተነስታ እልም አለች።
ከዚህ በኋላ ጭንቅ ያዛቸውና መቼስ ምን ይደረግ ለንቦጫችንን ሰጥተነው እንሂድ ብለው ተማከሩ። ወዲያው በል እንግዲህ የላይ የላይ ለንቦጫችንን ውሰድ አሉት። እሱም እንዳመለከቱት ለንጨጭ ለንጨጫቸውን ገነጣጠለና ለቀቃቸው።
በሦስተኛው ቀን ደግሞ እስቲ ዛሬ ሣልስቱ ነውና እመቃብሩ ላይ ደርሰን አያ ዥቦን ጠይቀን እንምጣ ብለው ቢሄዱ አያ ዥቦ ቀድሞ ከመቃብሩ ላይ ሲያለቅስ ደረሱ።
አያ ዥቦም ድዳቸውን ገልፍጠው ባየ ጊዜ፣
“ለካ የኔ ሐዘን ለናንተ ሰርግና ምላሽ ሆኖላችኋልና የኔ ልጅ ትላንትና ሞቶ ዛሬ እናንተ እየተሳሳቃችሁ የመጣችሁት በምን ምክንያት ነው?” ብሎ ተቆጣና ለወገኖቹ “ኧረ በሉ አንድ አንድዋን እየዘረጠጣችሁ ጣሉልኝ” አላቸው።
ከዚህ በኋላ የዥብ ወገን ያህያን ልጅ እየገነጣጠለ ጣለ ይባላል።
“አያ ዥቦ ሳታመኻኝ ብላኝ”
.
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል
.
[ምንጭ] – “እንቅልፍ ለምኔ”። 1952 ዓ.ም። ገጽ 43-44።
Thank you so much.
LikeLike