“የትና የት?” (ግጥም)

“የትና የት?”

ከከበደች ተክለአብ

.

[በደራሲዋ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

.

የትና የት ምኞቴማ

ምኞቴማ የትና የት

የፍላጐቴ ምጥቀት

እንደ መንኰራኩር መጥቆ

ሕዋውን እየዳሰሰ

ግድቡን እያፈረሰ

ተራራን እያፈለሰ

ይብላኝ እንጂ ለአካሌ

ሕሊናዬስ ገሠገሠ

የወዲያኛውን ዓለም

በመዳፎቹ ዳሰሰ።

.

በመዋዕለ እንስሳት

እንደ ኢምንቶች ካኖረው

ማስተዋሉን ዝቅ አድርጎ

ከአራዊት ከደመረው

የሕይወት ክፋይ እንዳይደለ

ከሕይወት ጣዕም የለየው

ጣፋጭ ፍሳሹን አቅርሮ

መራራ አተላ ከጋተው

የሰው አምሳል ሰው እንዳይሆን

ከሰዎች ዓለም ገፍቶ

በደመ ነፍስ ከሚጓዘው

የቦዘ አካል ተለይቶ

ከነባራዊው ሁኔታ

ሕሊናዬ የሸሸበት

የትየለሌ ርቀቱ!

የትና የት! የትና የት!

.

ምኞቴማ የትና የት

ሰው ሊያደርገኝ የቃጣበት

የጠወለገው የተስፋ ዕፅ

በምኞት ካቆጠቆጠ

የተጣለው መጋረጃ

በተስፋ ከተገለጠ

የትና የት! የትና የት!

አካሌ ተወሰነ እንጂ

በነባራዊው ሒደት!!

.

ከበደች ተክለአብ

1977 ዓ.ም

ሐዋይ የእስረኞች ካምፕ፣ ሶማሊያ

.

(በደራሲዋ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “የትነው?”። 1983 ዓ.ም። ገጽ 57-58።

One thought on ““የትና የት?” (ግጥም)

  1. የከበደችን መፅሐፍ ካነሱ ማስቀመጥ አይቻልም። አንብቦ ከመጨረስ በቀር። መፅሐፉዋ ከያዘችው ሃስብ አንፃር ግን እንደ ባለብዙ ገፅ ጥራዝ መፅሐፍ ተደጋግማ ብትነበብ ዘወትር አዲስ ናት። “የትና የት” ወሰደችን?

    Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s