“ልብወለድ ታሪክ” (ክፍል 3)

“ልብወለድ ታሪክ”

በአፈወርቅ ገብረየሱስ

(1900 ዓ.ም)

.

(ከክፍል ሁለት የቀጠለ)

.

ዋህድ እንደገና በረታ። ከዚያ መደበር ሳይነጋ በፊት ለመድረስ ተመኘ። ጊዜው ግን ተዋርዷል ተመንፈቅ ሌሊት ዝቅ ብሏል። ዋህድ እንደ ባልንጀራ አድርጎ ሲወዳቸው የነበሩት እነ ስድስቶም ጠፉ። ጨለማውም እጅግ በረታ። ነገር ግን አንድ ጊዜ ተመንገዱ ሲወጣ አንድ ጊዜም ጥቃሽ ሲአገኝ ሲሄድ ሲሄድ የመንደር እሳት ይታየው ጀመርና ደስ ብሎት እየተበራታ ሲጓዝ ታንድ ወንዝ ቁልቍለት ደረሰ። ጥቂት ዝቅ እንዳለ የሰፈሩም እሳት ላይኑ በሸጡ ጀርባ ተሰወረው።

ጨረቃ የለ የንጋት ኮከብ እንኳ ገና አልወጣች ምንም ሌቱ ቢዋገድ ጨለማው ይልቁን ባሰ እንጂ አልተሻለም። በዚያው ላይ ደግሞ የግራና ቀኙ የወንዛወንዙ ገረንገብ ጥላ ታከለበትና ጨለማው ዓይን ቢወጉ አይታይ ሆነ። ዋህድ በዚህ ጊዜ ቁልቍለቱን ተዳፋ። መንገዱ ግን ጠፋው ምን ይሁን ሳልደርስ አልቀርም ብሏልና በፈከረው ለመድረስ በዚያ ጥቅጥቅ ድንጉር ጨለማ ቍልቁለቱን በጁና በግሩ እየተተማተመ በቅምጡ ሲንኳተት በንብርክኩም ሲድህ።አንዳንድ ጊዜም አልሆንለት ሲል ጊዜ ፊቱን ወደመጣበት አዙሮ እግሩን ወደሚሄድበት አስረዝሞ ማጭድ እረስቶ እንደመጣ ለጓሚ በጁ እሳር ቅጠሉን እየጨበጠና እየሟጠጠ እየጓጠጠ እሾህም አይቀረው እንደሀር ጐፍላ እየጨባበጠ በደረቱ ሲሳብ ሲጋፍ ሲጐተት ተወራጁ ወንዝ ደረሰ።

ያ ወራጅ ውሀ ለዋህድ ጥሩም ይሁን ይደፍርስ አልታወቀውም ግና በጥማት ልሳኑ ታስሮ ነበርና ተጐንብሶ እንደገልዳ ጠጅና እንደገፈታማ ጠላ ለስም ያህል ተላይ ያሰፈፈውን አረንጓዴና ስልባቦት እፍ እፍ እያለ በትንፋሹ ገፋፋና የተቻለውን ያህል አንስቶ ጥማቱ እንዳለፈ “ተመስገን ጌታየ” አለና ተኹል ደንጊአ ላይ ቁጭ ብሎ የመሻገሪአውን መልካ ያይ ጀመረ።

ቢመለከት ሁሉም ጥልቅ መሰለው። ቋም ይሁን ጠሊቅ ይሁን ውሀው አልታወቅህ አለው። ዝም ብሎ እንዳይገባ ዋህድ የዋና ነገር አያውቅም ነበረና ፈራ። ይልቁንም ያ ወንዝ ፉአፉአቴ አልነበረውምና “ዝም ያለ ወራጅ ውሀ ሙሉ ነው” ሲሉት ሰምቶ ፈራ። “ምን ላድርግ” እያለ ገና በልቡ ሲአመናምን እንዳጋጣሚ እንደሱ ውሀ ጥም የተባሰች በቅሎ ከመደብር ችካሏን ነቅላ አምልጣ ከወንዙ ደረሰች። ዋህድ “አውሬን ይሆን” ብሎ ሲደናገጥ አፍንጫዋንና ከንፈሩአን ስታማታ በቅሎነቷን አውቆ ሲረጋጋ ያችው በቅሎ ገስግሳ ከውሀው እስተንቢአዋ ገብታ ተነክራ ተዚአ ውሀ ትግፍለት ጀመር። በዚህ ጊዜ ዋህድ በዚያች በቅሎ ምክኛት የውሀውን ግልብነት ቋምነቱን አወቀ አስረገጠና “ቶሎ በቅሎይቱ ጠጥታ የጠገበች እንደሆነ አትያዘኝም ታመልጠኛለች” ሲል ወደ በቅሎይቱ አንጣር አድርጎ ውሀውን በዘንጉ እየለካ ተሻገረና ተማዶው ደረሰ።

የዚያን ጊዜ በቅሎይቱ አንድ አፍታ ተዚያው ውሀ ግፋለት አንገቷን አቅንታ ጆሮዋን እያርገበገበች ለሁለተኛው ገና “ልበልን ልተው ይብቃኝን አይብቃኝ” ስትል ዋህድ ተሎ ብሎ “አንቺ አንቺ” እያለ እያባበለ ቀረበና ያዛት። እሷም ገራም ነበረች። ትራገጥ መስሎት አስቀድሞ በጁ ይዳስሳት ጀመር። በቅሎይቱ ግን የዋህድን መድከም አውቃ “ይረፍብኝ” ብላ ያዘነችለት መስላ ዝም አለችው። መገረሟን አስረገጠና ዋህድ ወደ ትልቅ ደንጊአ ስቦ አቀረበና ተቀመጠባት። ቀጥሎም ወደመጣችበት ወገን አቃንቶ “እንግዴህ እንዳወቅሽ ወደ ሰፈርሽ ውሰጅኝ” አለና አሳቡን በሷ ላይ ጣለው።

በቅሎይቱም ዋህድ የሚለው ሁሉ ነገር እንደገባት ሁሉ የመደብሩን መንገድ ይዛ ሳትነቃነቅ ይዛው ትጓዝ ጀመር። ብቻ አንዳንድ ጊዜ ለምለም እሣር ባየች ጊዜ ትቆም ትነቻችፍና እሷን የጠዳት ጊዜ እንደገና ተባልንጀሮቿ ለመደባለቅ መንገዱአን ትይዛለች። ዋህድ ግን ቀስ አርጎ እንዳይወድቅ ብቻ ጋማዋን ተመጨበጥ በቀር አይኰለኵላት “ሂጅ መጭ” አይላት እንዲያው እሷ እንዳለች ተዋት። ስለምን እሷ በፈቃዷ ነውና የተያዘችለት መጭ እያለ በግሩ መጐሳሰሙ ወረታዋን ማጥፋት መሰለው።

“አሁንስ ቢሆን የማን እንግዳ በተቀባዩ ቤት ገብቶ ያዝዛል” እያለ ያስብ ነበር። ያች የዋህ በቅሎ ግን ተሁሉም ሳትደርስ እያዘገመች ስትወስደውና ከሰፈሩ ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ያችኑ በቅሎ ሲፈልጉ የነበሩ ጐረደማኖች ዱካ ሰምተው ሲሮጡ ደረሱ። በዚህ ጊዜ ዋህድ አለገንዘቡ በሰው በቅሎ መቀመጡን ያውቃልና ፈርቶ ተበቅሎይቱ ወረደና ለመሸሸግ አሰበ። ነገር ግን ጐረደማኖቹ በቅሎይቱን ከበው በመጫኛ ሲይዙ እሱም ከዚያው ተገኘና ተያዘ። እንዳያመልጥ እግሩ በጣመን ተሳስሮ ነበርና ቸገረው።

ጐረደማኖች ግን ተበቅሎይቱ አጠገብ ባገኙት ጊዜ እሷን ተችካል አውልቆ ሰርቆ ሊሄድ ሳለ ደረስንበት መስሏቸው “አንት ሌባ የታባትህ” እያሉ አስረው በየቆመጣቸው ይቸበችቡት ፍዳውን ያሳዩት ይሰድቡት ጀመር። ዋህድ ግን እባካችሁ አንድ ጊዜ ስሙኝ ሌባም አይደለሁ እያለ ቢጮህ ቢቀባጥር ማን ይስማው። ምላሹ አንት ሌባ አንት ቀጣፊ ስትሰርቅ ደርሰንብህ ሌባም አይደለሁ ትል ጀመር ብቻ ሆነ።

ከዚህማ ወዲአ እየገፋፉ ወደ መደብሩ አደረሱና ገሚሶቹ በቅሎይቱን በካስማ ሲአስሩ ገሚሶቹ ዋህድን የፊጥኝ ገለበጡና አሰሩ። ያን የመሰለ ቀንበጥ ለጋ ልጅ የፊጥኝ ተገልብጦ ምን ይቻል። መተንፈስም አቃተው። ትንፋሹም ባጭር ባጭሩ ሆነ ቅትት ቅትት የሚል። የዚያን ጊዜ ላየው ሰው ዋህድ እጅግ ያስለቅስ ነበር።

የፊጥኝ ባሏለበት ነገር ተገልብጦ እንደሚታረድ ፍየል እጅና እግሩን ተኮድኵዶ ተጋድሞ በቅሎዎች አንዳንድ እግራቸውን ብቻ በገመድ ታስረው ጥሬ ተዘርግፎላቸው ሲበሉ ዋህድ ተተጋደመበት እንደሆነ አየና “ምነው ባይሆን እንኳ እንደናንተ እግሬን ብቻ ባሰሩና እንደናንተ ትንፋሸን በሙሉ በተነፈስሁ” እያለ በበቅሎዎች ሳይቀር ይቀና ጀመር። መተንፈስ ግን የማይሆንለት ሁኖ ሊፈነዳ ሆነ። ያን የንጋት ኮከብ የመሰለ ዓይኑን እያንከዋለለ ዙሪአውን ሰው ቢፈቅድ ማን ይገላግለው ማን ያማልደው ማን ጥቂት እንኳ ገመዱን ያላላለት። በከንቱ ነው። መከራው ስቃዩ ተገድሉ ሲነበብ እንደሚሰማው እንደሰማዕታት ስቃይ ሆነ እንጂ ተዚያም አያንስ። ያ ወደል ወደል ነጋዴ ሁሉ በክርንም በጡጫም በርግጫም ሲተካክዝበት እንዳይነጋ የለምና ለዋህድ ነጋለት።

ሲነጋ ደግሞ ተኝቶ የነበር ነጋዴ ሁሉ እየተነሣ እየመጣ ያን በከንቱ የታማ ሌባ እንደቀረመት ፍሪዳ በዙሪአው ከቦ ሲአይ ፀሐይ ብልጭ አለችና ሌሊቱን ሁሉ በሾህና በጋሬጣ የተበላሸውን ገላውን በደም የተበከለ ጋቢውን ቁልቍለቱን ሲወጣ ሲወርድ የተገጣጠበውን ጕልበቱን ደረቱን ጀርባውን አዩና እርግጥ በሌባነቱ አቆሙት። “ተሌላም ስፍራ እንደዚሁ ሲሰርቅ ተገኝቶ ገርፈው ለቀውታል” ተባለ። ከነዚያው ሰዎች እኩሉም እንደታሰረ ላገሩ ሹም ለማቀበል ተመኘ። እኩሉም አስረን ተኛው ጋር እናጉዘው አለ። ዋህድ ግን ዓይኑን መክፈት እስቲአቅተው ድረስ ደክሞ መተንፈስ እንኳ አቅቶታል። እንኳን ቁሞ ከነሱ ጋር ይጓዝ። እውነትም የዚያን ጊዜ ገሚሱ ነጋዴ ለሹም እናስረክበው ወይ አስረን ተበቅሎ ጋራ እንንዳው እያለ ሲከራከር እኮሌቶቹ በግራቸው እየጐሳሰሙ ማን ትባላለህ ከወዴት መጣህ እያሉ ቢጠይቁት እንኳን መመለስ ይሆንለት ያን ያህል ሲረግጡትም ገላውን ስቅቅ አይለውም ሆነ።

እንደበድን ወዲህና ወዲአም ቢአገላብጡት ቢአንከባልሉት እንደሬሳ ሆነ። በዚህ ጊዜ ይበልጠው ሰው “ተዉ እንፍታና እንተወው የሞተ እንደሆነ ስበቡ በኛ ነው እዳ እንሆናለን አለ። ወዲህም ረፈደባቸውና ከብት ማዋዛት ተጀመረ። ወዲአውም ጫጫኑና ለሹሙ ማሳለፍ እረፈደና አላዳርሳቸው ብሎ ዋህድን ፈትተው ተዚአው እንደተጋደመ ትተውት ተጓዙ። ከመደበሩ ላይ አጋሰስ ታረከሰው ሣርና ከሱ በቀር ምንም አልቀረ። ከዚያው ላይ ያው ያልታደለ ዋህድ አለስንቅ አለውሀ አለዘመድ አለደጋፊ ወድቆ ቀረ። ሌሊቱን ሁሉ ውርጭና አመዳይ አድሮበት በዚአው ስፍራ ደረቅ ፀሐይ ተተክቶ ልብ ልቡን ግንባር ግንባሩን ያከስለው ጀመር። ተነሥቶ ወደ ጥላ እንዳይጠጋ በምን ጕልበቱ በምን አቅሙ።

ቀን ተሌት መንገድ መቶት ቀጥሎም የጐረደማን ሁሉ እርግጫው ጥፊው ጡጫው መንዶው ጐመዱ ግፊው ስድቡ ከዚያም ወዲአ እስራቱ እሄ ሁሉ መከራ ወርዶበት እህል ተቀመሰ ሁለት ቀኑ ሁኖ ተዚህ ሁሉ በኋላ እንደምን መንቀሳቀስ ይቻለው እንዲአው ዝም ብሎ ፀሐይ እያቆረናው ውሀ ጥማት እያከረረው በሞቱ ቆርጦ ተዘረረ።

አትሙት ያለው ሰው መቸም አለቀኑ አይሞትምና እንዳጋጣሚ ሁሉ ኩበት ለቃሚ አንዲት ባልቴት ተሩቅ ተጋድሞ አየችው። ተመጀመሪያው ነጋዴ ተመደብር የረሳው እቃ መሰላት። እያደረች ስትቀርብ ስትቀርብ የሰው አካል መሰላት። በጥፍሩአ ቁማ ስታስተውል ጊዜ በሩቁ የተጋደመ እሬሣ መሰላትና መቅረቡን ፈራች። ወደኋላዋም እንዳትመለስ እርግጡን ነገሩን ሳታይ መሄዷን ጠላች። በዚህ ጊዜ ስትፈር ስትቸር ቀስ እያለች እያጠቀሰች ትቀርብ ጀመር። ምንም አትኩራ ብታይ ግን ሲንቀሳቀስ አላየው አለችና እሬሳ ነው ብላ ጠረጠረች። ከዚህ ወዲአ ግን ያደረ የዋለ ሬሳ እንደሆን ብላ ፈርታ አፍንጫዋንና አፉአን በጨርቋ አፍና ይዛ በጣም እየቀረበች

“ምን ሰው ነህ ምን የሆንህ ሰው ነህ ኧረ”

እያለች ብትጠራው አይናገር አይጋገር ዝም ብሎ አየችው። እሷ ግን “ድንገት የማውቀው ሰው ሙቶ እንደሆነ” ብላ ለማወቅ ቀረበችና ባየች ጊዜ የዋህድ ዓይን ጥቂት ገርበብ ብሎ ነበርና “አይዞሽ ገና ነብሴ አሎጣችምና ቀርበሽ ብሶቴን እይኝ። ቢቻልሽ እገዢኝ” የሚል መስሎ ታያትና ጥቂት መንቀሳቀሱን ባየች ጊዜ ቀስ ብላ

“ምን ሁነሀል ወንድሜ?” አለችው።

እንዳልመለሰላት ባየች ጊዜ ደረቷን እየደቀደቀች እያለቀሰች ስትሮጥ ሄደችና ተቤቷ ባንድ እጁአ ወተት ባንድ እጁአ ውሀ ያዘችና ያች ደግ ባልቴት ደረሰች። የወተቱን ቋጫ አኖረችና ባንድ እጇ አንገቱን ቀና አድርጋ ከደረቷ ላይ አስጠግታ ውሀውን “ጕረሮህን እስቲ አርጥበው ልጀ” አለችና ተከንፈሩ ለገተችለት።

ዋህድም በዚያ ውሀ ከንፈሩን ቢነካክር እንጂ ለጊዜው መሳቡ አልሆነለትም። የተሰነጣጠቀው ከንፈሩ እንደራሰለት አይታ የቋጫውን ወተት ለገተችለት። ወተቱን አንድ ሁለት ጊዜ ጕረጉጭ እንዳደረገ ዓይኑን መግለጥና እንደልቡ መተንፈስ ጀመረ። ያች ደግ ሴት ነብሱ እንደገባለት አወቀችና የኩበት መልቀሚአ ያመጣችውን እንቅብ ደፍታ አንተራሰችውና እራቅ ብላ ከፍ ታለ ዲብ ላይ ወጥታ በቅርብ ጠምዶ ሲአርስ የነበረውን ባሏን ጠርታ

“ወዲህ ና የምታግዘኝ ሥራ አለ” አለችው።

ባሉአም ጥማዱን አቁሞ ሲሮጥ ደረሰ። ነገሩ ምንድር ነው ብሎ እስቲጠይቃትም አላቆየችው ብቻ

“እባክህ እሄን ጐበዝ ተጋግዘን እንውሰድና ተቤታችን እናስታመው” አለችው።

እሱም እሱአም እየተጋገዙ ወስደው ተገዛ አልጋቸው አስተኙና እንደናትና እንዳባት ያማረውን ነገር ሁሉ ሳያሳጡ እነሱ ከመሬት እየተኙ አስታመው አዳኑት። ዋህድም የነዚህን ባልና ምሽት ደግነትና የጐረደማኖቹን ጨካኝነት እያመዛዘነ በዚህ ዓለም ስንትስ ክፉ ስንትስ በጎ ሰው አለበት እያለ ለብቻው ተደመመና

“እግዚአብሔር ካሳችሁን አያስቀርባችሁ ተምስጋና በቀር እኔ የማደርግላችሁ ነገር የለኝም። አሁንም እሄው ጕልበቴ በናንተ ቼርነት ጠነከረልኝ ልሂድ” አላቸው።

እነሱም ስንቁን ሰንቀው መንገዱን አሳይተው ሸኝተው ሲጨርሱ እንዲህ ብለው መከሩት።

“ተዛሬ በፊት ያገኘህን መከራ አትርሳ ሰው ክፉ ነው ለንግዴሁ ተጠንቀቅ ብቻህን አትሂድ። ለኛ አንድ ልጅ በቁሙ በወርዱ አንድ ልጅ ብቻ ነበረነ። እሄኑን ልዣችነን አንድ ቀን ተመንገድ ብቻውን አግኝተውት እስላሞች ነጋዴዎች አፍነው ይዘው ሸጡት። እኛም እሄው ደጋፊ ጧሪ ወራሽ ቆራሽ አጥተን ቀረነ። አንተም ገና ያልባለቅህ ልዥ በሰው እጅ እንዳትወድቅና እንዳትሸጥ ተጠንቀቅ” ብለው ተሰነባበቱ።

ዋህድም ከዚአው ላይ ሲሰነባበት የሁለቱንም ስም የተሸጠውን ልጃቸውን ስም ያገራቸውንም ስም አስተውሎ ጠይቆ በቃሉ አጥንቶ ይጓዝ ጀመር።

ሲጓዝ ሲጓዝ ተመሸበት ሲአድር ሲሄድ ሲሄድ ተመሸበት ሲአድር ነገር ግን ዋህድ የሚደርስበትን ስፍራ የሚሄድበትን አገር ቈላም ይሁን ደጋም ይሁን አያውቅም ነበር። ብቻ የነጋዴ ወሬ እየጠየቀ በዚህ አለፈ ከዚህ ሰፈረ ሲሉት ያን ያሉትን መንገድ ይዞ መጓዝ ነው። እንዲህ እንዲህ ሲል ሳያውቀው ያገሩን ደንበር ዘሎ የሚፈልገውን ያን ሀብታም ነጋዴ ሳያገኝ ተሰው አገር ገባ።

ሰውን አስቀድሞ ባየ ጊዜ ቋንቋውም ልብሱም ስራቱም ምኑም ተለየበት። ዋህድ መጨነቅ ጀመረ። ወደ ኋላውም እንዳይመለስ እንዴት ብሎ። እግሩ እንደመራው ሲጓዝ ኑሮ የመጣበትን ስፍራ ቢአይም አገር ምድሩ ዞረበት። የፀሐዩ መግቢአና መውጫ አንድ ሆነበት። በዚህ ቅጡ ጠፍቶት ሲጨነቅ ምድር መሸበትና በቁሜ አውሬ ሲበላኝ ባይሆን ሰው ይልቅ እንዳደረገ ያርገኝ አለና ተመንገዱ ዳር ታለው ተማንላቸውም ቤት ሄደና እባካችሁ አሳድሩኝ አለና ለመነ። ባለቤቶችም እንደ ብርቅ ከበው እየሳቁ ያዩት ጀመር። ዋህድ የተናገረው ነገር አልገባቸውም። ነገር ግን በመላ አሳድሩኝ ማለቱን አወቁና ደስ ብሏቸው በግራና በቀኝ ሁነው ከሩቅ ዘመቻ እንደተመለሰ ዘመዳቸው እጁን ይዘው እየደጋገፉ ከቤታቸው አገቡት። ምግቡንም አሳመሩና ከስቶ እንዳያድርና ዋጋ እንዳያፋርስባቸው አበሉት አጠጡት።

ዋህድን የመሰለው የደግነትና የግዚአብሔርን እንግዳ ለማክበር ለማስተናገድ መስሎት ይመርቃቸው ጀመረ። እነሱ ግን ወዲአው በልቶ እንደጨረሰ ያን በጨለማ ሲሄድ ያደረ ለት የተላላጠውንና ከነጋዴ መደበር የተደበደበውን ሰውነቱን ቆስሎ ሽሮ ሲአዩ ጊዜ ዙሪአውን ከበው እየደሳሰሱ ያስተውሉ ጀመር። ድሮ እነሱ ዋጋ ያዋርድብነን አያዋርድብነ እያሉ ለነገው ገብያ ማሰናዳታቸው ነበር። ዋህድ ግን ያን ሁሉ አላወቀ በቅን ልቦናው የዳነውን ቍስሉን ድፍጥጥ ድፍጥጥ እያደረጉ እያዩ ሲነጋገሩ ሲአያቸው ጊዜ ያዘኑለት እየመሰለው አሁንስ ድኛለሁ አያመኝም ይላቸዋል። እነሱ ግን የሚለውን አይሰሙ አያውቁ ዝም ብለው የነገውን ገቢአቸውን ምን ያህል ብለን እንሽጠው እያሉ ያሰናዳሉ።

አስተኝተው እንዳይሾልክና እንዳይጠፋቸው ሲጠብቁ አሳደሩና እጅግ ማለዳ ተነስተው ገንፎ አገንፍተው ዋህድ የሚጣፍጥ እንቅልፍ ከተኛበት ቀሰቀሱና ያበሉት ጀመር። በልቶ እንደጠገበ ወዲአው ሁለንተናውን በቅልጥም ያሻሹት ገቡ። ዋህድ ግን ምንም ቢሆን የጌታ ልጅ ነበርና ባይሆን እንኳ በሰንደል ሀጥር የተጣፈጠ ቅቤ ነው እንጂ ሰው እንዳሮጌ መጫኛና እንደገረረ ጀንዲ በቅልጥምና በሞራ ሲጨማለቅ አይቶ አያውቅም። ስለዚህ “አይሆንም አታስነኩኝ” እያለ ተናገረ። እነሱም ምንም ቋንቋውን ባያውቁ ባኳኋኑ ባተያዩ መጠየፉንና አለመውደዱን አውቀውበታል። ነገር ግን አወዛዝተውና ሆዱን በገንፎ ነትረው ለገዡ ሲያሳዩት ብዙ ገንዘብ እንዲአስነችፋቸው ያውቃሉና እያደናቆሩ ምንም ብል በዚአ በሚገማ ስብ ሁለንተናውን በካከሉት።

ዋህድ ግን የማይተውት ሲሆን ባየ ጊዜ ተረታና ዝም አላቸው። ደግሞም የመሰለው ጣመኑ እንዲለቀውና ያ የተገጣጠበው በውል እንዲድን ብለው ለሱ ደግ ውለታ መዋላቸው መስሎታል። እየጊዜው ወይ ግሩም እንዴት የግዚአብሔር እንግዳ የተወደደበት አገር ነው እያለ አገር ይመርቃል። ወይ አለመተዋወቅ።

እነዚያው ያሳደሩት ሰዎች ወደ ደረቅ እረፋዱ ሲሆን ዋህድን ባይን ጥቅሻ ተነስ ተከተለነ አሉትና ተጣጥቀው ወጡ። እሱም እንደ መልካም ዙረት እሽ ብሎ በመካከላቸው አድርገውት ሲሄዱ ሲሄዱ ካንድ ትልቅ መንደር ደረሱ። ያ መንደር በትልቅ እርድ እንደ ምሽግ ተከልሏል። በዚያ እርድ ውስጥ ትልቅ የደንጊአ ቅጥር ተክቦበታል። በዚያ እድሞ ላይ አጋም እሾህና የግራር እሾህ ሰው እንዳይዘለው ተመስጎበታል። ከዚያ መካከል ትልልቅ ሰቀላ ቤትና ሁለት ትልልቅ ቤተንጉሥ አዳራሽ ተገጥግጦበታል። የዚያ ቅጥር በሩ ሁለት ብቻ ነው። ከሁለቱ በር አንዱ ጠባብ ነው። አንደኛው ግን በፈረስ ተዛንቶ ለመግባት የተመቸ ነው። ከዚያው ካውራው በር አንድ ጥብልያኮስን የመሰለ ጥቁር ሰው ደረቱ በክንድ የሚሰፈር የመሰለ ቁመቱ አምድ የመሰለ ዓይኑ እንሶስላ የሞቀ የመሰለ አፍንጫው መርግ የተንከባለለበት የመሰለ የመዳብና የቈርቆሮ አንባሩን የዘሆን መዳፍ በመሰለ ክንዱ ደርድሮ ባራት ማዝን የተሳለ ጉዶውን የመስከረም ዘተር ዱባ በመሰለ በራቁት ሆዱ ላይ አሸንጦ በቀኝ እጁ ጐመዱን አጠንክሮ ይዞ ያልተፈቀደለትን ሰው ለመከልከለ ተገትሮ ቁሞ ነበር። እሄን እያየ ዋህድ ያገሩ ገዥ ያለበት ይሆናል እያለ ሲአስብ እነዚያ ይዘውት የመጡ ሰዎች ለባለቤቱ ልከው ኑረው ግቡ ተባሉ። ዋህድን በመካከል አድርገው ተቅጥሩ እንደገቡ በዚያም በዚያም እንደሱ የሚሸጡ የመጡትን የሚአስለቅስም የሚተክዝም ሰው ነበረባቸውና በሰው እየተከበቡ እንደሱ ሲገቡ ዋህድ አየ።

ከዚህ ወዲአ ግን ሰውነቱ ጠረጠረበት። ያ ሁሉ መከብከቡ ለቅንነት አለመሆኑን አወቀው። ነገር ግን መጨረሻውን ለማየት ዝም ብሎ ይከተል ጀመር። መሆንማ ነገሩንስ ቢአውቅ ብቻውን ተማያውቀው ሰዎች መሀል ሁኖ ምን ሊአደርግ ፣  ቋንቋቸውን እንኳ አያውቅ። እንደ ፋሲካ በግ ዝም ብሎ ባይኑ መቀላወጥ ብቻ ሆነ። ያው ትልቅ ቅጥር ያው ሁሉ ምሽግ ያው ሁሉ አጋም እሾህ ያ ሁሉ ጥንካሬ ያንድ የትልቅ የባሪአ ነጋዴ ቤት ኑሮ ያ እየተያዘ የሚመጣው ባሪአ እየዘለለ በሌትም ይሁን በቀን እንዳይጠፋና እንዳያመልጥ ኑሮአል።

ያ ዋናው የባርያ ነጋዴ ታዳራሹ ወጣና ለመሸጥ ከተሰበሰበው ሰው ዋህድም ታለበት መካከል ሆነና ተመካከሉ እየዞረ ያይ ዋጋውንም ይጠይቅ ጀመር። እንዲህ እንዲህ ሲል ተዋህድ ደረሰ። እንደ መልካም ወጌሳ እያገላበጠ ክንዱንም እግሩንም እንደ ልጅ ጥርስ እያነቃነቀ ያይ ጀመር። ካመጡቱ ሰዎች ጋር የዋጋውን ነገር ጨረሰና ብር ቆጥሮ ሲሰጥ ሲቀባበሉ እሱው ዋህድ ራሱ እንደ እማኝ ሁኖ ሲአስተውል ዋለና እንግዴህ መሸጡን ባርያነቱን አወቀ። እነዚያ የግዜር እንግዳ አክባሪዎችም ወርቅና ብራቸውን በዋህድ ጫንቃ ያፈሩትን እያንሆጫሆጩ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ዋህድም ካዲሱ ጌታው ቀረ።

ይቀጥላል …

አፈወርቅ ገብረየሱስ

1900 ዓ.ም

2 thoughts on ““ልብወለድ ታሪክ” (ክፍል 3)

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s