“ልብወለድ ታሪክ”
በአፈወርቅ ገብረየሱስ
(1900 ዓ.ም)
.
ይሄው አዲስ ጌታው ግን እንደውነቱ ለዋህድ ክፉ ሰውም አልሆነበት ይልቁንም በወቃቢውና በመልኩ በጠባዩ በለጋነቱም ወደደውና አልነግደበትም ብሎ ተገዛ ልጆቹ ጋራ እንደቤት ልጅ እንዲቀመጥ ስራ እንዳይሰራ አደረገው። ዋህድም ምንም በሰው እጅ ቢሆን ዘመዶቹንና ያን ደግ አድራጊየን ነጋዴ ሳላይ እንደምን ክርስቶስ ተሰው አገር ቤት ያስቀረኛል እያለ ያስብ ነበር።
ሲኖር ሲኖር ግን ታለበቱ ቤት ብዙ ክርስቲያኖች ተሽጠው ባሪያ ሁነው ያለበቱኑ ጌታ ሲያገለግሉ ሲኖሩ ኑረው በቋንቋቸው አወቃቸውና ይቀራርባቸው ጀመረ። አዩኝ አላዩኝ እያለ እየፈራ ነገሩን የተሸጡበትን ጊዜውንም አገራቸውንም ስማቸውንም ጠይቆ አወቀ።
ተነዚአው መሀል ግን እንዳጋጣሚ ሁሉ የነዚያን ነጋዴ ደብድቦ ጥሎት ተሄደበት ስፍራ አንስተው አስታመው ያዳኑትን ልጅ እነሱው መሸጡንና ስሙን ነግረውት ነበርና እሱ በገዛ አንደበቱ ስሙንም አገሩንም አሻሻጡንም ቢነግረው አወቀው። እጅግ ደስ አለው። ተዚህ በኋላ ዋህድም ተቤቱ ታሞ መዳኑን የናት አባቱንም ወሬ በሱ ነገር ዘወትር መላቀሳቸውን ነገረው። ከዚያ ወዲያ ግን ሁለቱ በፍቅር ተጠመዱ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኑ። ምስጢራቸውም ተስፋቸውም አንድ ሆነ። አገራቸውንም ለመግባት አርቀው እያሰቡ በተስፋው ይኖሩ ጀመር።
ዋህድ ተቤቱ ተወጣ ዓመት ሁኖት ነበረና እናት አባቱ እቱም ወሬውና የሄደበቱ ዳብዛው ጠፍቷቸው ሲላቀሱ ባጁ ከረሙ።
በኋላ ግን የዋህድ አባት ልዤ ጠፍቶ ሲቀር ዝምን ብየ ተሞቀ ቤቴ እቀመጣለሁ ሂጀ በሄትም ብየ ልፈልገው እንጂ አለና ስንቁን ያ ደግ ነጋዴ ተተሸጠበት አርነት ያስወጣው ጊዜ ላገሩ መመለሻ የሰደደለትን ፈረስ ጭኖ በኋላው ወድሎ ሊነሣ ሆነ። ነገር ግን አንድ የሚከተለው ሰው አልነበረም። ስለምን ከጦርነቱ አሽከሮቹ ሁሉ እኩሌታዎችም ተፊቱ እየተጣበሱ አለቁ እኩሌታዎቹም እንደሱ ተማርከው ተሽጠዋል።
እሱም አገሩን ቢመለስ ሰዉ አልቆ ንጉሡ ሙቶ ከብቱ ተነድቶ መሬቱ ጠፍ ሁኖ ቆይቶት በድህነት ላይ ወድቋል። ብቻውን መሄዱን ባየች ጊዜ እሴት ልጁ ጦቢያ በወጣበት ጠፍቶ እንደ ወንድሟ እንደ ዋህድ እንዳይቀርባት ፈርታ ታለቅስ ጀመር። ቀጥላም እንዲህ አለችው።
“አባየዋ አንተ በጌትነት የለመድህ እንዴት አላንድ ሰው ብቻህን መሄድ ይቻልሀል። ፈረስህንስ ማን እሣር አጭዶ ያበላልሀል። ውሀስ በጊዜው ማን ያጠጣልሀል። አሁንም እባክህ ልከተልህ ትተኸኝ አትሂድ። ባይሆን እንኳ አፍህን አካፍትሀለሁ ፈረሱንም በለኮው ይዠ ተመስክ አግጥልሀለሁ። ምንም ቢሆን ጥለኸኝ አትሂድ” እያለች አልቅሳ ነገረችው።
እሱ ግን የሷን ጭንቀት የሷን ትበት የሷን ልቅሶ ባየ ጊዜ እጅግ አዘነና እንደሷው እያለቀሰ፣
“ልጄ ወዳጄ ይሄ ነገር የማይሳካ የማይወጠን ነገር ነው አንቺ ሴት ልጅ ገና ጮርቃ ነሽ። አንቺን ፀሐይና ብርድ አግኝቶሽ መንገድ መትቶሽ ውሀ ጥማትና እርሀብ ተጨምሮብሽ እንዴት ችለሽ ተኔ ጋራ አገር ላገር መዞር ይሆንልሻል? አይሆንም አትምጭ!” አለና ከለከላት።
ጦቢያ ግን አይሆንም አልቀርም እያለች እያለቀሰች ለመነችው። አባትዮው ግን ነገሩን አይቶ ጠንክሮ፣
“እንቢ! እንኳን ታግዢኝ ይልቱንም ትደክሚና ተመንገድ ወንድምሽን ዋህድን እንዳልፈልግ ታረጊኛለሽ። ደግሞም ጦቢያ አንቺ ገና ቀንበጥ ለጋ ልጅ ተከብክበሽ በጌታነት ጠጁ ተጕሮሮሽ ብርሌው ተጅሽ ሳይለይ ያደግሽ አሁን ጠጁ ቢቀር ውሀ አጥተሽ ዝጋጃና ወላንሳ በረገጥሽበት እግርሽ እሾህ አሜከላ አቃቅማ የፀሐይ እረመጥ እረግጠሽበት እንዴት ትችይና ትመጫለሽ። አሁንም አርፈሽ ተናትሽ ጋራ ቅሪ!”
አለና ሊስማትና ሊነሣ ባየች ጊዜ ጦቢያ ይልቁንም ክንዱን ተጠምጥማ ይዛ እያስለቀች እንዲህ አለችው።
“አባየ ለኔ አትስብ እንኳን ድህነት ጌትነት ይለመዳል። ሁሉንም ልዥ ነኝና እለምዳለሁ። ደግሞም ባለጌ ጌታ ሲሆን አያውቅበትም እንጂ ሀብታም የጨዋ ልጅ ቢያጣም መከራና ድህነት አይከፋበትም ቶሎ ይለምደዋል። እኔም ቶሎ ለመልመድ አይሳነኝምና ውሰደኝ። ደግሞም ለኔ ከዚህ ቀርቸ ባንተ በደጉ አባቴና በምወደው ወንድሜ አሳብ ተመጨነቅ ካንተ ጋራ አገር ላገር እየዞርሁ የሆንሁትን ብሆን ይሻለኛል” አለችው።
በዚህ ጊዜ አባትዮው፣
“እኔስ እስቲ አንቺ እንዳልሽ እሺ ብየ ልውሰድሽ ኧረ ላንች ምን በመሰለሽ እናትሽን ለብቻዋ ታንድ ቤት ዘግተናት ስንሄድ እሄን ነገር ብናረግ ለሰዉስ ምን በመሰለው” አለና በተናገረ ጊዜ እናቲቱ ቶሎ ብላ እንዲህ አለች።
“ሰውም ያለውን ይበል ለኔ አታስብ ደግሞም የምታስተዳድረኝ አንድ ባልቴት መሳይ አላጣም ብቻ እኔ የምፈራው ልጂቱ ካንተ ጋራ መገስገስ ያልተቻላት እንደሆነ ብየ ነው እንጂ እሷ ተተቻላት ኑሮአል ለኔ መታሰቡ። ለኔ የሚያሳስብ ነገር የለም አትስብ” አለችና ወደ ልጇ ዙራ እንዲህ አለች።
“ልጄ እርግጥ የጕልበትሽን ነገር ትተማመኚዋለሽ?”
ጦቢያም ተሎ ብላ፣
“አወን እናቴ አንቺ ተፈቀድሽልኝ አንቺ ለብቻሽ መሆኑን ታልሰጋሽ መሄድ ይሆንልኛል። አባቴን ብቻ እሺ እንዲለኝ እገዢኝ” አለች።
ቀጥላም ገና አባቷ ይሁንም አይሁንም ብሎ ሳይመልስላት ጦቢያ አሳቡን አቋረጠችና፣
“አባቴ አንድ ነገር ብቻ” አለችና ልትናገረው አፍራ ሳትጨርሰው እንደ መዳዳት አለች።
በዚህ ጊዜ ማፈሯን አባትዮው አወቀና፣
“ምን ሆንሽ ልጀ እስኪ ንገሪኝ” አለ።
ጦቢያም አነሣችና፣
“አባየ ካንድ ሁለት ይሻላል። እንኳን የሰው ጠላት አንበሣ እንኳን ሁለት ሲያይ ሰው ያከብራል አይናካም። ነገር ግን ሁለቱም ሰዎች ወንድ ቢሆኑ ነው የሚፈሩ እንጂ ጠላት እሴትን ተቁም ነገር አይጥፋትም። ስለዚህ አንተን ስከተል የሴት ልብሴ ቀርቶብኝ እንደ እንደ እንደ …”
እያለች የምትለውን ለመጨረስ አፈረችና አንገቷን ወደ ምድር አዘንብላ ዝም አለች።
አባቷ አወቀባትና፣
“እንደ እንደ የምትይው እንደ ወንድ ልልበስና ልከተልህ ማለትሽ ይሆን?” አላት።
ጦቢያም አፍራ ይልቁንም በሁለቱም እጇ ፊቷን ጋርዳ ቃሏን አቅጥና፣
“ይሻል መስሎኝ ነዋ አባቴ” አለች።
አባትዮውም እሷ እርግጥ በመነሣቷ እንደቈረጠች አየና፣
“እሺ ተወደድሽው ምን ይደረጋል ተሰናጅና ተሎ እንነሣ” አለ።
ጦቢያ ደስ አላትና የሀር ነዶ የመሰለ እሳዱላዋን እንደ ወንድ ተቈረጠችና የወንድ ሙሉ ልብስ ለበሰችና እናቷን አይዞሽ ብላ አረጋግታ ሁሉም ተሰነባብተው ተለያዩ።
እንግዴህ አባትና ልጁ እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉ እየተበረታቱ ሲሄዱ ሲሄዱ ተመሸባቸው ሲያድሩ ሲጓዙ ሲጓዙ ተመሸባቸው ሲያድሩ ዋህድ ሲነሳ እሄድበታለሁ ብሎ ታመለከታቸው ከተማ ደረሱ። ተዚያው እንደደረሱ ግን ማነን ይጠይቁ። ብቻ በያደባባዩም በየገበያውም እየዞሩ ቢፈልጉ ዋህድ ወዴት ይገኝ። እንዲያው ተረት ሆነባቸው።
በኋላ ግን ዋህድ ያነን ደግ ሀብታም ነጋዴ ለመፈለግ ነውና የሄደው ያገሩ ሁሉ ነጋዴ ወደ ስናር ተሚአልፍበት ተበሩ እንቀመጥና የሚወጣ የሚወርደውን ነጋዴ ሁሉ እንመልከት ዋህድ ወይ ያን ነጋዴ አግኝቶት አብሮ ተምስር ሲመለስ እናየዋለን ወይ ገና ሲፈልግ እናገኘዋለን አሉና እሄን ተስፋ አድርገው ወደዚያ ትልቅ በር እየጠየቁ ሲሄዱ ሲሄዱ መንገዱ ጠልፎ ወዳላሰቡበት ወሰዳቸው።
አፈወርቅ ገብረየሱስ
1900 ዓ.ም
.
[ምንጭ] – “ልብወለድ ታሪክ”። ፲፱፻ ዓ.ም። ገጽ ፳፱-፴፫።