“የኮሌጅ ቀን ግጥሞች”

የኮሌጅ ቀን ግጥሞች

.

ኅሩይ አብዱ

.

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የወርቅ ኢዮቤልዮውን (50ኛ አመት) ባከበረበት በ1993 ዓ.ም.  “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር። ዩኒቨርስቲው ከ1951 እስከ 1960 ዓ.ም. ለውድድር ከቀረቡት ግጥሞች ከፊሉን ለንባብ አብቅቷል። ለመሆኑ እነዚህ የኮሌጅ ቀን ግጥሞች የትኞቹ ናቸው? ገጣሚያኑስ እነማን ናቸው?

ግጥሞቹ በዚህ ስም የተጠቃለሉት በየአመቱ ግንቦት ወይም ሰኔ በሚከበረው የኮሌጅ (ከ1954 በኋላ “ዩኒቨርስቲ”) ቀን ሰለቀረቡ ነው። ከኮሌጅ ምሥረታ ጀምሮ የግጥም ክበብ እንደነበረና ቅዳሜ ቅዳሜ ገጣምያን ስንኞቻቸውን በት/ቤቱ ምግብ አዳራሽ ያቀርቡ እንደነበረ ይነገራል። ት/ቤቱ ውስጥ በሚያደረገውም የግጥም ውድድር ላይ የሚቀርቡት ግጥሞች እየተሻሻሉ ሰለመጡ ለኮሌጅ ቀን ዝግጅት ለማቅረብ ታሰበ። በዚህም መሰረት በ1951 ዓ.ም. ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት የወጡት ገጣሚዎች ለኮሌጅ ቀን ግጥሞቻቸውን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ሌሎች ባለሥልጣናት በተገኙበት እንዲያነቡ ተደረገ። ንጉሡም በግጥሞቹ በተለይም ተገኘ የተሻወርቅ ባቀረበው “ሰው እንቆቅልሽ ነው” ሰለተደሰቱ በትምህርት ሚኒስቴር ግጥሞቹ እንዲባዙ አዘዙ።

ንገሩኝ እናንተ ገባን የምትሉ

ይሄ ነው ብላችሁ የሰው ልጅ ባህሉ

ክፋቱን ጥፋቱን ባንድ ፊት አርጉና

ልማት ደግነቱን ወደዚህ ለዩና

አንፍሱ አንጓሉና ብጥር አድርጋችሁ

ንገሩኝ የሰው ልጅ ይሄ ነው ብላችሁ።

                            (ተገኝ የተሻወርቅ፣ “ሰው እንቆቅልሽ ነው” ገጽ 1)

ከዛን ጊዜ ጀምሮ የግጥም ንባብ ከኮሌጅ ቀን ዝግጅት ጋር ተጣመረ። ለሚቀጥሉት ሁለት አመታትም ሶስቱ አሸናፊ ግጥሞች ከተነበቡ በኃላ ለታዳሚው አምስት አምስት ሳንቲም ይሸጡ ጀመር። የቅዳሜ ግንቦት 12 1959 ዓ.ም. ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቀን ፕሮግራም እንደሚያሳየውም ሶስቱ አሸናፊ ግጥሞች የሚነበቡት ከሰአት በኋላ ነበር። የተለያዩ የስፖርትና የመዝናኛ ትርኢቶች ከቀረቡ በኋላ ሶስተኛው የወጣው ግጥም ይነበባል። ከዛም የተለያዩ የተማሪ ማሕበሮች አመታዊ ዘገባ ያቀርቡና ሁለተኛው ግጥም ይቀርባል። የቀኑ ዝግጅት የሚጠናቀቀው አሸናፊው ግጥም ተነቦ ሽልማቶችም ከተሰጡ በኋላ ነበር።

 

1953

1953 ዓ.ም የሚታወሰው በታኅሣሡ ግርግር ነው። በሁለት ወንድማማቾች (ግርማሜና መንግስቱ ነዋይ) የተጠነሰሰው የመንፈቅለ መንግስት ሙከራ የከሸፈበት ጊዜ ነበር። መፈንቅለ መንግስቱ 6 ወር ሳይሞላው ስርአቱን የሚወርፍ ግጥም በኮሌጅ ቀን ዝግጅት ላይ   ቀረበ። ገጣሚው ታምሩ ፈይሳ፣ ንጉሱና አጃቢዎቻቸው በተሰበሰቡበት “በድሀው” አንደበት እንዲህ አለ።

ያችን አህያዬን የገዛሃትን

አርፎባታል አሉ የጅቦች አይን።

ብለቃት ይሻላል እንዳው ዝም ብዬ

ላስጥላት አልችልም ከጅብ ተታግዬ

ጅቡ ሲቦድሳት እንዳትጮህ ደግሞ

ልታናፋ አትችልም አፏ ተለጉሞ።

                                (ታምሩ ፈይሳ፣ “ድሀው ይናገራል” ገጽ 7)

ህዝቡ በታምሩ ድፍረት በመገረም ቶሎ ግጥሙን ለመግዛት ይጣደፍ ጀመር። ቀን አምስት ሳንቲም ሲሸጥ የነበረው ግጥም ማታ ሊገኝ ሰላልቻለ በአንዳንድ ቡና ቤቶች እስከ አምስት ብር እንደተሸጠ ይነገራል።

የግጥሙ ዝና ከአዲስ አበባ አልፎ ከተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ግጥሙ እንዲላክላቸው በደብዳቤ የሚጠይቁ ብዙ ነበሩ።

“በድሀው ይናገራልም” ምክንያት የሚቀጥለው አመት ለኮሌጅ ቀን የሚቀርቡት ግጥሞች እንዲሁም ተውኔቶች በቤተ መንግስት መጀመሪያ መታየት እንዳለባቸው ለተማሪው ማኅበር ትእዛዝ ተላለፈ። ይህም ቅድመ ሁኔታ ካልተሟላ ንጉሠ ነገሥቱ በዝግጅቱ ላይ እንደማይገኙ ቤተ መንግስቱ አሳሰበ። የተማሪው ማኅበር አመራርም የቤተ መንግሥቱን ማስጠንቀቂያ ከምን ሳይቆጥረው ቅድመ ሁኔታውን እንደማይቀበል አሳወቀ። በዚህ አጣባቂ ሁኔታ አመታዊው ዝግጅት በቅዳሜ ሰኔ 2 1954 ዓ.ም. ንጉሡና አጃቢዎቻቸው በሌሉበት ተካሄደ።

የቀረቡት ግጥሞች የይልማ ከበደ “ኑሮ” የመላኩ ተገኝ “ሜዳ የቀረኸው”ና የዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” ነበሩ። ዘውድን በመዳፈርና በግጥሞቹም ይዘት ምክንያት ከተማሪው ማኅበር የአመራር ቡድን አምስቱ ከት/ቤት ሲባረሩ ሶስቱ ገጣሚዎች ደግሞ ለአንድ አመት ከትምህርት ገበታ እንዲወገዱ ተወሰነ። ግጥሞቹንም አሸናፊ ብለው የመረጡት ዳኞች (ዓለማየሁ ሞገስ፣ አብርሃም ደሞዝና ሥርግው ሐብለ ሥላሴ) መቀጫ ብር እንዲከፍሉ ታዘዙ።

 

እስኪ ተጠየቁ?

በ1954 ዓ.ም ከቀረቡት ግጥሞች የዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” የበለጠ ዝና አግኝቷል። አንደኛው ምክንያት አገሪቷን ወደ ኋላ አስቀርቷታል የሚላቸውን ነገሮች አብጠርጥሮ ሰለሚወቅስ ነው። ወቀሳውንም የሚያካሄደው ወደ ሙት አለም ሲጓዝ “እናንተ ጋር ሁኔታዎች እንደኛው አገር ተበላሽተዋል ወይ?” በማለት ነው።

ሰለ ነጻነት ሲያነሳ፣

በመቃብር ዓለም አለ ወይ በውነት

በስም አጠራሩ ሚባል ነፃነት

ነፃነት ምትሉት ከውጭ አጥቂ ጠላት መጠበቁን ነው

ወይንስ በርግጡ ሌላ ፍቺ አለው።

የውስጥ ነፃነትስ በመሀል በናንተ

ዘየው ሳይታወቅ ከንቱ የሻገተ

ከዝምታ ብዛት ለብዙ ዘመን

ምርምር ሳይገባው ሳይተነተን

ዋጋውን አጥቷል ወይ በናንተ ዝንጋታ

በእናንተ ዝምታ

ወይንስ ንቁ ነው እጅግ የበረታ።

                              (ዮሐንስ አድማሱ፣ “እስኪ ተጠየቁ” ገጽ 40)

ሌላው “እስኪ ተጠየቁ” የሚታወቀው በርዝማኔው ነው። ደራሲው በዕውቀቱ ሥዩም በራሪ ቅጠሎች ላይ በአሽሙር እንዲህ አቅርቦታል።

“የረጅምነት ታሪክ ሲነሳ በድሮ ውስጥ ነገሮች ሁሉ የመርዘማቸው ጉዳይ ያልተፈታ ጥያቄ ሆኖብኛል። የማቱሳላ ዕድሜ የአቦዬ ጣዲቁ ፂም … በኪነጥበብም እንዲሁ ነው። ጥንታዊ የስነጽሑፍ አፍቃሪያን ወደ መታደሚያ አዳራሽ ለመሄድ በማለዳ ሲነሱ ‘ዛሬ እስኪ ተጠየቁ የሚባል ግጥም ስሰማ ሰለምውል ለምሳ እንዳትጠብቁኝ’ የሚሉ ይመስለኛል።”

                                      (“ተራራው ያድጋል” ገጽ 35)

አዎ የሃያ ገጽ ግጥም ረጅም ነው። ነገር ግን የግጥሙን እርዝማኔ ማየት ያለብን በቀረበበት መቼት ነው። ያኔ ከ 3-4 ሺ ህዝብ በተሰበሰበበት የስርአቱን ችግሮች በዲስኩር መዘርዘር የማይታሰብ ነገር ነበር። ታዲያ ዮሐንስ በግጥም ለመተንፈስ መሞከሩ ነበር። እርዝማኔው ከዚህ አኳያ ነው መገምገም ያለበት።

በረከተ መርገም

አብዛኛው ሰው ሰለ ኮሌጅ ቀን ግጥሞች ባሰበ ቁጥር ትዝ የሚለው የኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) 1959 ዓ.ም “በረከተ መርገም” ግጥም ነው። የተሸከመው ለየት ያለ እጅ አዙር ወቀሳ ይሁን አጻጻፉ ግጥሙ እስካሁን ድረስ የአንባቢውን አእምሮ አልለቀቀም። ገሞራው “በረከተ መርገም”ን በመጽሐፍ መልክ በ1966 ዓ.ም ባሳተመው ጊዜ የግጥሙን መልዕክት እንዲህ ገልጿል።

 “… የአንዲቱ ምድራችን ሊቃውንት ለሰው ልጅ ዘር ያበረከቱት ከፍተኛ የጥበብ ጸጋ ለሁሉና ለእያንዳንዱ እንዲዳረስ አድርገው ያልፈለሰፉት ከሆነ በኔ ግምት አሁንም ቢሆን ሰዎችን ለመለያየት ያቀዱበት ተንኮል ነውና ወንጀለኞች ናቸው ባይ ነኝ። ለዚህም ወንጀላቸው መርገም ሲያንሳቸው ነው። እንደማየው ከሆነ ጥበባቸውና ከፍተኛው የሥልጣኔ ረድኤታቸው ለጥቂት ውሱን የሰው ልጆች ብቻ ሊያገለግል እስከቻለ ድረስ የጠቅላላውን የሰውን ልጆች መሠረታዊ እኩልነት እስከኅልቀተ ዓለም እንዳደበዘዘው ሊኖር ነው። ይህ እንዳይሆን ኡኡ ማለት ሊያስፈልግ ነው። ከኡኡታዎቹም አንዱ ይህች ግጥም እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ።”

                                            (ገሞራው፣ “በረከተ መርገም” ገጽ ረ)

ታዲያ የገሞራውን ኡኡታ ሁሉም እኩል አልሰማም። የሱን አስተሳሰብ ከማይቀበሉት ውስጥ አንዳንድ ተማሪዎች የሳይንስ ሊቆች በመሰደባቸው ተናደው ነበር። ገሞራው እንደሚስታውሰው።

“ግጥሟ በተነበበችበት ሰሞን ለጊዜው ስሙንና ምልኩን የማላስታውሰው አንድ የሳይንስ ፋካልቲ ደቀ መዝሙር የሚመልካቸው ሊቃውንተ ሳይንስ ለምን ተረገሙ? በሚል ምክንያት የበቀለ ሠንጋ ፈረሱን ጭኖ ካለሁበት በመምጣት ሊጣላኝ እንደከጀለ ሁሉ ትዝ ይለኛል።”

                                    (ገሞራው፣ “በረከተ መርገም” ገጽ ሠ)

ገሞራው አንዳንዴ በግጥሙ በቀጥታ ይዘልፋል። ለምሳሌ፣ ሰለ ፓርላማ ሲያወራ

“… ያልተደረገውን፣ ከፅንፍ እስከ አድማስ ጊዜን ጊዜ ገጭቶት፣

ይወልደው ይመስል፣ መዋቲውን መንፈስ ከቶ መመሥረትህ፣

በደል ለማጽደቂያ የውሸት ምክር ቤት፣

በተስማምቻለሁ ለማድለብ ከሆነ የሰዎችን ሙክት

ጮማ ለማይወጣው ከአኞ በስተቀር ልፋጭ ሊያበረክት

አስበህ ከሆነ እንዲያ እነደዲያ ማድረግህ የሰው ልጅ ለማወክ

መንጋ ማጎሪያውን ፓርላማ ነው ብለህ ለኛ ሰላሳለፍክ

ያንግሎ ሳክሶኑ ለፍዳዳው ዊልያም ዘርህ አይባረክ።

             ……..

ከጥንት ጀምሮ እኛ እንዳየነው

ሲቃጠል የሚሥቅ ዘለዓለም እሳት ነው።

                              (ኃይሉ ገ/ዮሐንስ፣ “በረከተ መርገም”፣ ገጽ 129)

አንዳንዴ ደግሞ ምጸትን ይጠቀማል። እንደ ቤተሰብ ሰለማይርቁን ችግሮች ሲያወራ፣

“ዝግጅቱ አምሮ ሁሉም እንዲደርሰው ትምህርት ቢስፋፋ

ለብዙ ዘመናት ከኖረበት ሀገር ዘመድ ድንቁርና እንዴት ድንገት እንዴት ይጥፋ?

በሥራ ደርጅተን ሥልጣኔን ይዘን ገናና ብንባል

ላያሌ ዓመታት ጠብቀን ያኖርነው ድህነት ባህላችን ይቃወስብናል።

የያንዳንዱ ጤና እንዲጠበቅለት ሐኪም ቤት ቢቋቋም።

ሲወርድ ሲዋረድ ትውልድ ያወረሰን የቆየው በድካም

በሽታ ቅርሳችን እንዴት ባንዴ ይውደም…?”

                          (ኃይሉ ገ/ዮሐንስ፣ “በረከተ መርገም” ገጽ 135)

አንዳንዴ ከበድ ያለውን መልዕክት በቅኔ መልክ ያስተላልፋል።

“ግን ያሰብከው ዓላማ አልሆን ብሎህ ሲከሽፍ

ሁኔታው ሲጠጥር ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር።”

                           (ኃይሉ ገ/ዮሐንስ፣ “በረከተ መርገም” ገጽ 137)

መንግስት ገጣሚው ያለ ይሉኝታ የዘረዘረውን የወቀሳ መአት በቀላሉ አላሳለፈለትም። በዚህ ግጥም ምክንያት የደረሰበትን ሲያትት፣

“ይህች መለስተኛ ግጥም ከተጻፈች ስምንት ዓመታት ያህል አልፏታል። ያስከተለችብኝ የሚያመረቅዘው ጦሷ ግን አሁንም አለቀቀኝም። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲና በመንግስቱ ባለሥልጣኖች ብዙ ጊዜ አስለክፋኝ ከትምህርቴ እስከ መባረርና እስከመታሠርም አድርሳኛለች።”

(ገሞራው፣ “በረከተ መርግም” ገጽ መ)

የግጥሙን ርዝማኔ አይታችሁ አዬ ጣጣዬ ይህን ሳነብ ራት ሊያመልጠኝ ነው ትሉ ይሆናል። ነገር ግን በዛ ታሪካዊ መድረክ ላይ ሀሳቡን በሰፊው ዘርዝሮ እንደዚህ ባይገልጽ ኖሮ ይህን ግጥም እናስታውስ ነበር?

“እራስን መውቀስ!”

የኮሌጅ ቀን ገጣምያን የአገሪቱን ችግር መንግስት ላይ ማላከክ ብቻ ነው የሚያውቁት ወይንስ ራሳቸውንም ይመረመራሉ ትሉ ይሆናል። አንዳንዶቹ ገጣምያን ትኩረታቸው ጓደኞቻቸው ላይ ነበር። ለምሳሌ መሐመድ ኢድሪስ ከከተማ ወጥተው መስራት ስለማይፈልጉት ጓደኞቹ እንዲህ ይላል።

“ምሁር የተባለው ያገሬ ፈላስማ

ኤ ቢ ሲ ዲ ብለው ወጥተው ከጭለማ፣

በገበሬ ጫንቃ በነጋዴ ኮቴ

ተምረው ተምረው ዲግሬ ተቀብለው አልወጣም ከቤቴ።

ከአዲስ አበባ ከሞቀው ከተማ

ወጥቼ አላበራም ያገሬን ጨለማ፣

ገጠር ምን በወጣን ቧንቧ በሌለበት

መብራት በሌለበት ሐኪም በሌለበት

ክዮስክ ቤተክሲያን አልሳለምበት

እያለ ይኖራል እንዲህ በመታከት።”

(መሐመድ ኢድሪስ፣ “ከምሽት እስከ ጎሕ” ገጽ 117)

ዮናስ አድማሱ ደግሞ ተማሪው በመጤ አስተሳሰብ እንዲሁም በወሬ ራሱን ከህዝቡ አርቋል ይላል፣

“ የአንተ አገር ‘ፋሽን’ ላንተ ትምህርት ወጉ፣

‘ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር’

ብሎ ማውራት ሁኖ መቅረቱ ነወይ፣

ያንተ ዲሞክራሲ

ያንተ ማርክሲዝም

ኢንፎርሜሽን ኦርደር

ጨርሶ አይገባውም፣ ለጀሌው ገበሬ፣ ለጀሌው ባላገር

ኧረ ወኔው የወጣቱ

ኧረ ፍሬው የትምህርቱ፣

ለምንድነው ነው ባፉ ብቻ መስፋፋቱ፣”

(ዮናስ አድማሱ፣ ‘እስከ ማእዜኑ’፣ ገጽ 101)

“አሁንስ?”

ለመሆኑ የያኔው የኮሌጅ ቀን ገጣሚያን አሁን የት ይገኛሉ? ስለሁሉም ማወቅ ቢያዳግትም ስለጥቂቶቹ የማውቀውን አካፍላለሁ። ሁሉንም አንተ ልበልና፣ ተገኘ የተሻወርቅ በኅይለ ሥላሴ መንግስት ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ በኋላም ደርግ ሕዳር 1967 ዓ. ም. በግፍ ከገደላቸው ባለስልጣናት አንዱ ነበር። አበበ ወርቄ ከጠበቃነት እስከ ከፍተኛ ዳኝነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢመሰጉ) መስራችና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ።

ዮናስ አድማሱ በገጣሚነት ከቀጠሉት አንዱ ሲሆን በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ክፍል አስተማሪ ነበር። ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተጻፉትን ግጥሞቹን ‘ጉራማይሌ’ በሚል መድበል በ1980 ዓ. ም. በአሜሪካ አሳትሟል። ዮሐንስ አድማሱ በስልሳዎቹ ለእድገት በህብረት ዘመቻ ሂርና ሄዶ እያለ ታሞ ሞተ። ወንድሙ ዮናስ የተበታተኑትን ግጥሞቹን ‘እስኪ ተጠየቁ’ በሚል መድብል አሰባስቦ በ1990 ዓ. ም. አሳትሞታል።

ጸጋዬ ገ/መድህን (ደብተራው) በተማሪው ንቅናቄ ጊዜ የታገል (Struggle) ዋና አዘጋጅ ነበር። እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)ን ከመሰረቱት አንዱ እንደሆነና በኋላም የጦሩ መሪ ሆኖ ከሰማኒያዎቹ ዓ. ም. ታስሮ የት እንደገባ እንደማይታወቅ ይነገራል (www.debteraw.com)። መጽሐፍ ባያሳትምም ብዙ ገጥሟል። ከማይረሱትም ቅኔዎቹ አንዱ

“ቁማር ጨዋታ ተጫውቼ

አጨብጭቤ ቀረሁ ተበልቼ

ምንኛ እድሌ በሰመረ

ዘውዱን ገልብጨ በነበረ”

በመጨረሻም ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ከግጥም አለም ጋር ተሳስሮ ኖሮ ነበር። ከኮሌጅ ቀን ግጥሞቹ በኋላም ሥራዎቹን በ‘ፍንዳታ’ ርዕስ እያሳተመ ቆይቶ ነበር። አብዮት ከፈነዳም በአገር ወጥቶ በስደት ከቻይና ኖርዌይ በመጨረሻም ደግሞ በስዊድን ነበር። ብዙ የግጥም መጻሕፍትን አሳትሟል። ከሚታወቁት ግጥሞቹ ውስጥ ‘አንደበት ላጣ ህዝብ’፣ ‘የበሰለው ያራል’፣ ‘ዜሮ ፊታውራሪ’፣ ‘የማዳም ቀበቶ’፣ ‘ፊጋና ፓሪሞድ’፣ ‘ዲግሪማ ነበረን’ … የመሳሰሉት ይገኛሉ። የራሱንና የሌላውንም የዲግሪ ማካበት ተግባር ላይ አለመዋል እንዲህ ይተቸዋል።

ዲግሪማ ነበረን፣ ሁሉም በያይነቱ

ከቶ አልቻልንም እንጂ፣ ቁንጫን ማጥፋቱ።

ታዲያ እነዚህ በግጥሙ አለም የገፉት አራቱ፣ የኮሌጅ ቀን ግጥሞቻቸው ላይ የግዕዝ ተጽእኖ ይታያል። እንዲሁም የአበበ ወርቄ ‘ምላሴን ተውልኝ’ በተቃራኒው የሰውነት አካላት እየዘረዘረ ሰውን ቢያወግዝም፣ ቅርጹ የግዕዙን መልክዐ ዘርፍ ተጽዕኖ ያሳያል። እና ወደፊት የኮሌጅ ግጥሞቹን አብጠርጥረው ለሚያጠኑ በላያቸው ላይ ግዕዝ ያለውን አስተዋጽኦ ቢመረመሩ አዳዲስ እይታዎች ሊያገኙ ይችላሉ።

.

ኅሩይ አብዱ

.

ምንጮች

ከዩንቨርስቲ ቀን ፕሮግራም ሌላ የRandi Balsvikን Haile Selassie’s Students: The Intellectual and Social Background to Revolution. 1952-1977 እና የR Greeenfieldን A Note on a Modern Ethiopian Protest Poem ስለጊዜው ለመረዳት ተጠቅሜባቸዋለሁ።

2 thoughts on ““የኮሌጅ ቀን ግጥሞች”

  1. በኅሩይ አብዱ የቀረበው የኮሌጅ ቀን ግጥሞች ወደድኩት።ከተጻፈ ሰንበት ብሏልና አንድምታ ላይ ከመቅረቡ በፊት አበበ ወርቄ በስደት መገኘቱ፡ዮናስ አድማሱና ኃይሉ ገ/ዮሐንስ በሕይወት ያለመኖራቸው ቢገለጽ መልካም ነበር።በተረፈ አጠር አጠር ያሉትን የኮሌጅ ቀን ግጥሞችን ሙሉውን አልፎ አልፎ ብታቀርቡልን መልካም ነው።ለምሳሌ “ማነው ኢትዮጵያዊ?” የተሰኘው ግጥም ከእጥረቱ ባሻገር ወቅታዊም ነው።ገጣሚው ባልሳሳት ይብሳ ጉተማ ከኢትዮጵያ ሌላ አገር ለማቋቋም ቀና ደፋ እያለ በስደት የሚኖር ይመስለኛል።በጊዜው “ማነው ኢትዮጵያዊ”? ጥያቄ በራሱ ላይ ማንነት የጫረበት ነበር ማለት ነው። ፖለቲካና ጥበብ መለያያ መስመሩ አለው እንዴ?የሚል ጥያቄም እኛም ልናነሳ እንችላለን።
    አንድምታዎች ደህና ሁሉልኝ።

    Liked by 1 person

Leave a Reply to tarik miskeru Cancel reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s