“ስለ ቅኔ ባህል” (ወግ)

“ስለ ቅኔ ባህል”

(በምስጢር የተሞላ)

.

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

.

በዚህ መጣጥፍ ውስጥ የምናገረው ስለ ኢትዮጵያዊ የሀሳብ ዘይቤ (ቅኔ) ቢሆንም ለማነፃፀሪያነት ከባሕር ማዶ መጥቀሴ አይቀርም። ስለጐንጁ ተዋነይ ተናግሬ ስለአውሮጳ ሊቃውንትም አነሳለሁ። ይህ በኔ ግምት ተገቢ ነው። ሰዎች ከአንድ በላይ ዜግነት ይዘው በሚኖርበት ዓለም ከማዶም ከወዲህም እያቆላለፉ ማውጠንጠን ያዋጣል።

አንድም፣ የሌሎችን ሀሳብ ማስታወስ የራስን በተሻለ መንገድ ለመገንዘብ የሚያመችበት አጋጣሚ አለ። ለጊዜው ‘አውሮጳ ተኮር ጥበብ’፣ ‘አፍሪቃ ተኮር ሥልጣኔ’፣ ‘አፍሪቃዊው ሶቅራጥስ’፣ ‘ጥቁሩ አውግስጢኖስ’ በሚለው እሰጥ-አገባ ውስጥ ተሳታፊ የምሆንበት አቅም የለኝም።

አንዳንዶቹ “የኛን” ሀሳቦች ከሌሎች ጋራ ተበርዘው ልዩ መልካቸው እንዳይደመሰስ በመፍራት አጥረው ያስቀምጧቸዋል። በሌላ በኩል የሌሎች ሀሳብ “እንዳይውጣቸው” በመስጋት የሚከላከሉ ይኖራሉ። በውጤት ሀገርኛ ሀሳቦች ከሌሎች ጋራ የማይውሉ የማይወዳደሩ ዓይናፋር የቤት ልጆች ሁነው ቀሩ። ከማዶ የሚያንኳኩ ዘይቤዎች ደግሞ በዝጋ ብርሃን ፖሊሲ ምክንያት ወደ ውጭ ተጥለው ቀሩ። ይህ አይነቱ ልማድ ግን የማያዛልቅ መሆኑን የተረዱ ሊቃውንት አልጠፉም።

ለዚህ መጣጥፍ ማዳመቂያ አለፍ አለፍ እያልኩ የምጠቅሳቸው ዕጓለ ገብረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው የሚከተለውን ብለዋል፤

“… የሥልጣኔ መንፈስ ወደ ፈቀደበት ይነፍሳል። ለመቃወም አይቻልም፤ የሚገባም አይደለም። ምክንያቱም የሥልጣኔ ሀብታት ከሰው የኅሊና ጥረት የሚገኙ ስለሆነ በየትም ቢወለዱ ዘመዳሞች ናቸው። ለመዓት ወይም ለምሕረት የሚቸኩል ሰው ሳይሆን፣ አስተዋይ ተመልካች የሆነ እኒህን ዘመዳሞች የሚያስተዋውቅ ሽማግሌ ያስፈልጋል።”

ቅኔ በሀሳብ በሰዋስው መምህራን አማካኝነት ከግዕዝ ጋራ ብቻ ተቆራኝቶ ቆይቷል። በኔ ግምት በሌሎች ቋንቋዎች የመቀጠል ዕድል አላጣም። ይህም በሀሳቡ ላይ ባለን ፍቺ ስምምነት የሚወሰን ይሆናል። በቅኔ ምንነት ዙሪያ የሰዋስው ምሁራንና ሀሳብ አመንጭ ሊቃውንት የተለያየ አቋም አላቸው። ሁሉም ግን “ምስጢር የተሞላ” በሚለው መስፈርት ይስማማሉ። “ምስጢር መሞላት” ማለት በሰምና ወርቅ ሀሳብን መሸሽግና መግለጥን አያመለክትም። ሰምና ወርቅ ቅኔ፣ ወርቁ የተገለጠ ቀን ምስጢርነቱ ያከትማል። የተጋረደብንን የህልውና ዕውቀት የሚገልጥልንን ምጥን የጽሑፍ ዘይቤ በዚህ ስም ልንጠራው እንችላለን።

በዚህ ረገድ ከፍ ያለ ጥበብ ያለውን ግጥም ሁላ ቅኔ ልንለው እንችላለን። ሰሎሞን ዴሬሣ ባንድ ወቅት እንደጻፈው በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ፈሊጥ ውስጥ ስድ ጽሑፍ የቅኔን ያክል አላደገም ወይም የዝርው ጽሑፍ ሥርዓት ለቅኔ የተሰጠውን “ምስጢር የተሞላ” የተባለ ማጎላመሻ አላገኘም። የቅኔን ያክል ተደጋግመው የሚነበቡ ዝርው ጽሑፎች አሉ። የራሱ የሰሎሞን ‘የልጅነት መግቢያ’ በኔ ግምት ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። ቤት ባይመታም ላቅ ያለ ሀሳብና ጥበብ ያለው በምስጢር የተሞላ ዘይቤ ሁላ ቅኔ ነው።

.

“ያልተጻፈ”

ሊቃውንትና ባልቴቶች ተባብረው እንደሚነግሩን የቅኔ አባት ተዋነይ ነው። ልክ የሙዚቃ አባት ያሬድ እንደ ሆነ። የኖረበትን ዘመን አጥኚዎች በ15ኛው ክፍለ ዘመን ያደርጉታል።

በነገራችን ላይ ተዋነይ የስሙን ገናናነት ያክል ብዙ ቅኔ አናነብለትም፤ አብዝቶ ስላልተቀኘ ሳይሆን አብዝቶ ስላልመዘገበ። በኢትዮጵያ የቅኔ ሥርዓት ትውፊት ውስጥ የምዝገባ ባህል ደካማ ነው። ደካማ የሚለውን ቃል በመጠኑ ላርመው። ታድያ የጥንቶቹ ደራሲዎች ቅኔያቸውን በጥንቃቄ መዝግበው ለምን አላስቀመጡልንም? መጀመሪያ ትሕትና መስሎኝ ነበር። በኋላ ግን ራሴን አረምኩ። አብዛኞቹ ታላላቅ ባለቅኔዎች እንደ ጻድቃን ትሑታን አልነበሩም። “ዕቡይ” የሚባል ቅጽል እስኪሰጣቸው ቀና ቀና ባይ ነበሩ።

ሌላው ምክንያት የጽሑፍ ባህል አለመዳበር ነው። ይኼ እንዲያውም ለውይይት የማይበቃ ሰበብ ነው። ጥንታውያኑ ጽፎ በማስቀመጥ ረገድ ወደር አልነበራቸውም። ኪዳነወልድ ክፍሌ እንዳሉት ከሆነ እንግሊዞች ብቻ ከቴዎድሮስ ቤተመጻሕፍት 375 መጻሕፍት ወስደዋል።

ለጊዜው የምገምተው ምስጢር የቅኔ ጠባይ ለምዝገባ ምቹ አለመሆኑ ነው። ቅኔ ለጥንቶቹ በንግግር የሚተባ ሀሳብ ነው። (ፈረንጆች፣ ለምሳሌ የArt That Heals ጸሐፊ Jacques Mercier ቅኔን “Rhetorical Poetry” የሚለው ለዚህ ነው።) በዚህ ምክንያት ለብራና የሚመጥን አይደለም። የጽርእ (ግሪክ) ሊቃውንት ይኼን ያውቁታል። ሃና አሪቲ አፍላጦንን (Plato) ጠቅሳ እንዳቀበለችን ዋናውና የክቱ ሀሳባችን ካፋችን የሚወጣው ሲሆን የሚጻፈው ግን ቢጤው፤ ወይም ጥላው ነው።

አንድም፣ ቅኔ የላቀ ጥበብነቱ ከሙዚቃ ያላነሰ አድርጎታል። ዓለማየሁ ሞገስ ቅኔ ምን እንደሆነ ሲነግሩን “ምስጢር የተጎናፀፈ መዝሙር” ብለው ነው። የምዕራብ ባለቅኔዎች ፈታውራሪ ኒቸ “ዛራቱስትራ”ን በዝርው ቅኔ እንደጻፈው ያውቃል። ግን ሥራውን ለመረዳት “ሙዚቃ የማጣጣም ጥበብ” እንደሚጠይቅ ተናግሯል።

ይህንን ይህንን ስናይ ጥሩ ባለቅኔ እንደሞዘቀ ይሰማናል። ዘርዓ ያዕቆብ የድምፁን ጎርናናነት እንዲያካክስ ያደረገው ልቦናው ለቅኔ ብሩህ መሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት ቅኔን መጻፍ መንፈሱን ማጉደል መሆኑ የተሰማቸው አበው ምዝገባውን ብዙ የተጨነቁበት አይመስለኝም። ከነተረታቸው “የቅኔ ቋንጣ የለውም”።

.

“ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”

ስለ ተዋነይ ታሪክ የሚነግሩን ተራኪዎች የእውነትና የተረት ቅልቅል ያቀርቡልናል። እውነቱም ተረቱም ግን ቅኔና ባለቅኔ የሥጋና የመንፈስ ታዛዥ መሆኑን የሚያጠያይቁ ናቸው። ተዋነይ ምትሐተኛ እንደነበረ፣ የአፄ እስክንደርን ሚስት አማልሎ እንዳስኮበለለ፣ በአጋንንት እርዳታ ልዩ ልዩ ጥበብ እንደፈጸመ፣ በማይታዩ ሴቶች አማካኝነት ወደ ጣና ደሴት ተጠልፎ እንደተወሰደ … ሌላም ሌላም ይተረካል።

ይህ የሚያነሳብን ጥያቄ አለ። ቅኔ በቤተክርስቲያን በኩል ነው የደረሰን፣ የቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ደግሞ መንፈሳዊነትን ማላቅ ነው። መንፈሳዊነትን የሚያጋንኑ ምሁራን የሥጋን ህልውና ቸል ይላሉ። ለምሳሌ ወሲብና መፀዳዳትን እንውሰድ። ወሲብ እስካሁን ያለው ስሙ ግብረ-ሥጋ ነው። የሥጋ ሥራ እንደማለት ነው። ስለዚህ የጻድቃንን አኗኗር ብናነብ ታሪካቸው ወይ የድንግልና ነው፤ አሊያም የመበለትነት ነው።

መፀዳዳትም እንዲሁ ነው። የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ታሪክ ሲነገረን የሚከተለውን እንሰማለን። አባ ጊዮርጊስ በሄደበት ሁሉ እመ ብርሃንን ያሞግሳታል። ከእለታት አንድ ቀን፣ ሽንት ቤት ቁጭ ብሎ ሲያመሰግናት ተገለጠችለትና ባረከችው። ከዚህ በኋላ “ይህ አይሁንብህ” አለችው። እሱም ከዚያ በኋላ ወደ መፀዳጃ ቤት አልተመለሰም።

ለአባ ጊዮርጊስ የተሰጠው ቡራኬ ከሥጋ ሥራ የሚያድን ነው … ወይም በተሻለ አባባል ከሥጋ የሚነጥል ነው። በዚህ ረገድ የቅኔ ትውፊት ከቤተክርስቲያን ቀኖና ይነጠላል። የቅኔ ትውፊት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ነው። ከስሙ ብንጀምር ተዋነይ ከመንፈሳዊው ምክር ያፈነግጣል። ተዋነይ በግዕዝ “ተጫዋች” ማለት ነው። ቀላጅና ቧልተኛ ልማዱን የሚያሳይ መጠሪያ ነው። ከሴቶች ጋር የተቆራኘው ገድሉ በወሲብ ላይ ያለውን አንክሮ ይጠቁመናል። ልክ ነው። ያለ ወሲብ፣ ቅድስና እንጂ ቅኔ የተሟላ ሊሆን አይችልም። ስለ “የነገሮች ባህሪይ” (De Rerum Natura) የጻፈው ሉቅርጢያስ (Lucretius) እንኳ ቅኔውን የሚጀምረው የግጥምን አምላክ ቸል ብሎ የወሲብን አምላክ በማሞገስ ነው።

.

“የስሜት ጡዘት” (Ecstasy)

ሊቃውንት ስለ ስሜት ጡዘት ሲያብራሩልን ቃል ሲያጥራቸው በአስረጅነት ወይ ሙዚቃን ይጠቅሱልናል፤ ወይ ከወሲብ ማጠናቀቂያ የእርካታ ሰከንዶችን እንድናስብ ይነግሩናል። በስሜት ጡዘት ውስጥ አካባቢን፣ እራስንና ጊዜን መቆጣጠር አዳጋች ነው። ይህን ኃይል በወሲብ ብቻ ሳይሆን በቅኔም ውስጥ እንደምናገኛቸው ከሀዲስ አለማየሁ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ሁለት ትረካዎችን ልጥቀስ፤ የመጀመሪያው  የበዛብህና የሰብለወንጌል ባፍ ውስጥ የመቅለጥ ትርኢት ነው።

“… ሁለቱ ንጹሐን ይህንን የተበላሸ፣ ይህንን በክፉ ነገር ያደፈ የጎደፈ አለም ጥለው ወደ ሌላ አለም ወደ አንድ አዲስ አለም ገቡ።”

በሌላ ቦታ፣ አለቃ ክንፉ የተባሉ ባለቅኔ ሲቀኙ እንዴት እንደሆኑ ሀዲስ እንዲህ ብለው ይተርካሉ፣

“… ከጉባኤ ቃና ጀምረው እመወድስ ሲደርሱ እንደ ሁልጊዜው ሞቅ አላቸው። ብድግ ብለው እንደ ፎካሪ ከወዲያ ወዲህ እየተንገዳገዱ ማዕበሉን ያወርዱት ጀመር … አለቃ ላባቸው እየተንጠፈጠፈ ደሞ እንደገና ‘ተቀበል!’ ብለው ጉባኤ ቃና ሲጀምሩ መምህራኑ ወደ ፎቅ ወጡና ለምነው ወደ ምኝታቸው ወስደው አስተኟቸው። ገላጋይ ባይደርስ ደክሟቸው እስኪወድቁ ድረስ ይዘርፉ ነበር … ቅኔ ሲያሰክራቸው፣ በዚህ አለም መኖራቸውን ሲረሱት፣ ከጻድቃን ከሰማዕታት ከምዕመናን ከመላእክት ጋር በሌላ አለም የሚጫወቱ ሲመስላቸው፣ ያን ጊዜ ሳያውቁት ሳይሰማቸው የሚያወርዱት የቅኔ ማዕበል የእውነተኛው የተዋነዩ ደቀመዝሙር አሰኝቷቸው ቀረ …”

የፍቅረኞቹ በአፍ ላፍ መቅለጥና የአለቃ ክንፉ የቅኔ ስካር እጅግ ተቀራራቢ ትርኢት ገልጧል። ፍቅረኞቹም ባለቅኔውም ከጊዜና ከቦታ እግረ ሙቅ ላፍታ ነጻ ወጥተዋል። ስሜታቸው ወደ ነበረበት ሲመለስ ሁሉም የሰውነት መዛልና መራድ ደርሶባቸዋል።

እንዲህ አይነቱ የስሜት ነውጥ በባለዛር እንጂ በባለቅኔ ውስጥ ይገኛል ብለን አንገምትም። ምናልባት ጥንታዊ ጽርአውያን ሊቃውንት (ይልቁንም ሶቅራጥስ) ቅኔን የመለኮት ኃይል ወይም የከያኒ መናፍስት ሀብት ነው ብሎ ማመኑ፣ ባለቅኔዎችም የኒህ መናፍስት መስፈሪያ ከመሆን ያለፈ እርግጥም የሆነ ዕውቀት እንደሌላቸው ማስተማሩ፣ ከዚህ አይነት ትርኢት በመነሳት ይሆናል። ሀዲስ አለማየሁ የአለቃ ክንፉ ቅኔ ሳያውቁትና ሳይሰማቸው የሚወርር መሆኑን በማመናቸው ከሶቅራጥስ ትይዩ ቆመዋል።

ከመለኮትም መጣ ከሰው ልቦና፣ ቅኔ ከወሲብ ጋር የሚመሳሰል የስሜት ንረት ማጎናጸፉ ለብርቅነቱና ለተወዳጅነቱ ሰበብ ሆኗል።

.

“ጽሙና”

ስለ ኃያልነቱና ስለ ድንገተኝነቱ ቅኔ በሀዲስ አለማየሁ ‘ማዕበል’ ተብሎ ተጠርቷል። እንዲያ ከሆነ ከማዕበሉ መውሰድ በፊት ባህሩ ፀጥ ማለት አለበት። የብዙ ባለቅኔዎች ገድል የጽሙና ገድል ነው። “ጽሙና” በኪዳነወልድ ክፍሌ ፍቺ፤ ‘ጭምትነት፣ ፀጥታ’ ማለት ነው። አበው እንደሚነግሩን ባለቅኔው እየተንጎራደደ ወይም ተቀምጦ ሲያውጠነጥን በዙርያው ያሉትን ሁሉ ሊዘነጋ ይችላል።

ክፍለ ዮሐንስ የተባለው ባለቅኔ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ በፊቱ በአጀብ ሲያልፉ ቅኔውን እያስተካከለ ስለነበር እጅ አይነሳም። ይኽኔ በወርቅ ጠጠሮች ወርውረው በመምታት ‘ከጽሙናው’ ቀሰቀሱት። እሱም እንደመባነን ብሎ፣

“ድንጋዮች ከእስጢፋኖስ ላይ ቢያልቁ፣ ኢያሱ ወገረኝ በወርቁ!” ብሎ ተቀኘ።

ተዋነይ ከጣና ደሴቶች ባንዱ (ደቅ) ገብቶ ለረጅም ጊዜ በጽሞና እስኪቆይ ድረስ የቅኔን ስልት የሚያሻሽልበት ጥበብ እንዳልተገለጠለት ሊቃውንት ይናገራሉ። ጽሞናና ብሕትውና ለባለቅኔ (ለሌላውም ከያኒ) እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን የተቹ ብዙ ጸሐፊዎች አሉ። ዕጓለ ገብረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ብለው በደረሱት መጽሐፍ ውስጥ የዛራቱስትራን የተራራ ላይ ቆይታ በማንሳት እንዲህ ብለው ነበር፤

“… ወደ ኋላ መሸሽ መሸሸግ፣ ወይም እንደ ዛራቱስትራ ወደ ተራራ ወጥቶ ከሳር ከቅጠሉ ከንስር ከእባቡ ጋር መኖር ከገዛ ራስ ጋር በመጠያየቅ፣ በመከራከር፣ በመወደስ መንፈስን ማደርጀት ያስፈልጋል። እንዲህ ያለ ዘዴ በሰዎች ዘንድ ቀርቶ በእንስሳት ዘንድ እንኳ ያለ ነው። በግና በግ እንኳ ተጣልተው ሲዋጉ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸው ቀጥሎም መንደርደራቸው አንድ ምክንያት አለው። ይህም ኃይል ጉልበት ለማግኘት ነው። ሰው የመንፈስ ጉልበት ለማከማቸት የሚችለው በዕለት ትርኪ ምርኪ ወዲያና ወዲህ በማለት መባከኑ ቀርቶ ወደ ራሱ ተመልሶ መንፈሱን የቆጠበ ያደረጀ እንደሆነ ነው።”

.

“የላቀ ንቃተ ኅሊና”

ኢትዮጵያ ከመልክአ ምድሯ በተሻለ በጊዜና በኃይል መፈራረቅ ምክንያት የማይዋዥቅ ሌላ ምስል አላት። እሱም የብዙ ጥንታዊ መናፍስት ማኅደርነቷ ነው። ኢትዮጵያ በጃርሶ ‘ሞትባይኖር’ ኪሩቤል የማያዳግም አገላለጽ “Mystical Entity” ናት። ይህ የዕውቀቷም፣ ያለማወቋም ምንጭ ተደርጎ የሚወሰድ ዕጣዋ ነው። የኢትዮጵያን የሀሳብ ታሪክ አብዝተው የሚያውቁት ያገርም ሆነ ያገር ውጭ ሊቃውንት ደግመው ደጋግመው የሚያትቱት ክርስትናዋን ነው። የኪነጥበብ ታሪኳ ግን የብዙ ውጥንቅጥ መናፍስት መናኽሪያ እንደነበረች ነው።

ቅኔ ለአያቶቻችን ወደ መለኮት የሚያሻግር መሰላል ነው። ይሁን እንኳ፣ መሰላሉ የሚሰበርበት ጊዜም ነበር። የተዋነይ አንዱ ቅኔ እንዲህ የሚል ነው፤

“የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ

ካልኣን እንዘ ይትኤዘዙ ይሰግዱ ቅድሜሁ

ለጠይቆ ዝኒ ነገር ከመ እስራኤል ይፍርሁ

ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ

ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።”

.

(ትርጉም)

“ዓለም ሁሉ ራሱ በፈጠረው ያምናል፤ ይገዛልም

ሌሎች እየታዘዙ በፊቱ ይሰግዳሉ

ይህንን ነገር በመረዳት እስራኤል እንዲፈሩት

ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ

ፈጣሪም እሱን መልሶ ፈጠረው።”

.

ይህ ቅኔ ተዋነይ ላለማመኑ የሰጠው ምክንያት ነው። እግዜርን የሙሴ እጅ ሥራ አድርጎ መግለጡ ብቻ ሳይሆን፣ የፈጠረውን መነሻ የማስገበር ፍላጎት መሆኑን ገምቷል። ይህንን ሀሳብ ከምእተ ዓመታተ በኋላ የተመለሰበት ኒቸ “The will of God is the preservation of priestly power” ይላል (“The Anti-Christ”)። ይሁን እንጂ እሱ እንደገመተው ሃይማኖት ከበላይነት ፈቃድ ጋራ የማገናኘቱን ዘይቤ በማግኘት የመጀመሪያው ሳይሆን ቀርቷል። አበው በቅኔ ቤት በኩል አስቀድመው ሰምተውታልና።

ይህንን ቅኔ ያገኘሁት በቤተክርስትያን የቅኔ ስብስብ ውስጥ መሆኑ እንቆቅልሽ ነው። ግን ቅኔ መሆኑ በቀኖና አክባሪ ሊቃውንት እንዳይሽቀነጠር አግዞታል። ቅኔ “በምስጢር የተሞላ” በመሆኑና በአሻሚኒቱ ከእምነት መፈክሮች ጋራ ተመሳስሎ የመቆየት ዕድል ነበረው። በዚህ አይነት ቅኔ ለዘመናዊ ንቃተ ኅሊና በር ከፍቷል።

.

“ሙሾ”

እዚህ አዲስ አበባ በቅኔ ላይ ውይይት በተካሄደ ቁጥር የወጣቶች ጉድለት ተብሎ የሚጠቀሰው “ጨለምተኝነት” ነው። በ“ኗሪ አልባ ጎጆዎች” የግጥም መድብሌ ላይ አስተያየታቸውን በሚድያ የገለጹልኝ ሰዎች ደግመው ደጋግመው “ስለ ጨለምተኝነቴ” ነግረውኛል። አንዳንዶቹ ለዚህ ምክንያቱ “የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ” መሆኑን በማብራራት ሊያግዙኝ ሞክረዋል። በበኩሌ ብያኔውም ሆነ ለብያኔው የተሰጠው ማስተባበያ ጉድለት አላቸው። ሀያሲዎች ጨለምተኝነት የሚሉት ሙሾ ሙሾ የሚለውን ሃዘን ያጠላበትን ግጥም ነው። ግንኮ ሊቃውንት በሊቃውንት መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለውን የቅኔ ፍቺ “ተቀነዬ፣ ሙሾ አወጣ፣ ግጥም ገጠመ፣ አራቆተ፣ ተናገረ፣ አዜመ፣ አንጎራጎረ” የሚል ነው። (ዓለማየሁ ሞገስ)

“የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ” ለጨለምተኝነት ሰበብ ሆኖ መጠቀሱ አያዋጣም። የአሜሪካ ሕዝብን ሃዘን በኢትዮጵያ ሕዝብ ሃዘን የሚያበላልጥ ቁና አለ ብዬ አላምንም።

“ሥልጣኔ ምንድነች?” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ከበደ ሚካኤል ጦርነት ለቅኔና ሙዚቃ ማደግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጽፈው ማንበቤን አስታውሳለሁ። ሰው ሆነን ስናስበው አባባሉ ያስደነግጣል፤ የኪነጥበብ ዘፍጥረት መርማሪያዎች ሆነን ስንነሳ ግን ብዙ እውነት እናገኝበታለን። የሰርግ ዘፈኖችና የሙሾ ግጥሞችን ብናወዳድር የተሻለ ጥበብ የምናገኘው በሙሾ ውስጥ ይመስለኛል። ጦርነት ላቅ ያሉ የሀሳብ ዘይቤዎችን ገላጭ ሆኖ የተወሰደው የነፍስ በር ከፋች የሆነውን ሞትን ስለሚያሳስብ ይሆን? (ዮፍታሔ ንጉሤ ያማሩ ግጥሞቻቸውን የጻፉ በሙሶሎኒ ጦርነት፣ ዘርዓ ያዕቆብ ሐተታውን የጻፈው በሃይማኖት እርስ በርስ ጦርነት ወቅት ነው።)

ጦርነት ሞትን፣ ሞት ደግሞ የህልውናን ምንነት ያመላልሳል። የሰው እውነተኛ ድምፅ የሚሰማው ከዚህ ክስተት ጋር ሲጋፈጥ ነው። በሰው ያመኑ እናቶች እንዲህ የሚል ግጥም ትተዋል፣

“ወይ እኛና ዶሮ፣ አሞራና ሞት

ሲመጣ መንጫጫት፣ ሲሄድ መርሳት።”

.

እኛ ኢትዮጵያውያን የፊደል ሰዎች ሁለት ምርጫ ያለን ይመስለኛል … ወይ ሁኔታችንን መለወጥ፣ ወይ ካለው ሁኔታ ውበትና ዕውቀትን መፈለግ።

.

በዕውቀቱ ሥዩም

.

[ምንጭ]አንድምታ ቁጥር 3። ግንቦት 1998 ዓ.ም። ገጽ 6-8።

.

 

“የጋሽ ጸጋዬ ግጥሞች ቅኝት”

“የጸጋዬ ገብረ መድኅን ግጥሞች”

ከነቢይ መኮንን

.

.

እውነት ለመናገር ስለ ስነግጥም ከመናገር መግጠም ይሻላል። በተለይ እንደ ጋሽ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ያለውን የግጥም ነዶው ተከምሮ የማያልቅ ገጣሚን ሥራ መናገር “ሂማሊያን በሁለት ቆራጣ እግር-አሊያም አባይን በጭልፋ” እንደማለት ያለ ነገር ነው። ራሱ ጋሽ ጸጋዬ እንደሚለውም “አንድ ምእመን የሃይማኖቱን ድንጋጌ ከማተቱ ይልቅ፤ በቀጥታ እግዚአብሔርን በእምነት ማገልገሉ እንደሚበልጥበት ሁሉ፤ ባለቅኔም የሥነ-ግጥሞችን የአደራደር ሥርዓትና ድንጋጌ (Form) ከማተቱ ይልቅ ቅኔውን ተቀኝቶ፣ ደርሶ፣ ፍሬ-ሃሳቡን (Content) ማበርከቱ ይበልጥበታል።”

አንድ የአገራችን አጭር ልብ ወለድ ጸሐፊ የጻፈውን ውርስ መነሻ በማድረግ አንድ ምሳሌ በመስጠት የግጥምን ባህሪ ለማሳየት ልሞክር –

“አንድ አይነ-ሥውር፣ መንገድ መሪውን ባንዲራችን ምን ዓይነት ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል። “አረንጓዴ ቢጫ ቀይ” ይለዋል መንገድ መሪው። ዓይነ ስውሩም “ቢጫ ምን ዓይነት ነው?” ሲል ደግሞ ይጠይቃል። መንገድ መሪውም ግራ ይገባውና አዘውትረው የሚሄዱበትን ጠጅ ቤት አስታውሶ “ቢጫ ቀለምማ ጠጅ የመሰለ ነው!” አለው። አይነ ስውሩ “አሃ!” ይላል በመደምደም።

ቀጥሎ ሌላ ጥያቄም ቀጥሏል። ለጉዳያችን እዚሁ ጋ ላቁመውና፣ እንዲያው የዓይነ ስውሩን ግንዛቤ ለማሰብ ብንሞክር – በጆሮው የሰማውን ጠጅ፣ በምላሱ በማጣጣም፣ የባንዲራው ቢጫ ምን መሳይ እንደሆነ በሚያውቀው ግንዛቤ ሊያስብ ነው የሞከረው ማለት ነው። ስለዚህም ባንዲራ ይጣፍጣል። ባንዲራ ያሰክራል። ከበዛ ደግሞ ያማል። ባንዲራ እንደተርጓሚው የግንዛቤ አቅም ይታያል። እንግዲህ ባንዲራ ይህን አይነት ግንዛቤ የመፍጠሩን ያህል፤ እንደሚታወቀው በውስጡ ግን ያለው ታሪክ፣ ዓላማ፣ ህብር … ብዙ የታጨቀ ነገር ነው።

ይሄው ባንዲራ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ወይ ጥሩነሽ ዲባባ በሩጫ ሲያሸንፉ በሰው አገር ላይ ከፍ ብሎ ስናየውና፤ የኢትዮጵያ መዝሙር ሲታከልበት፣ ልዩ ሳግና እንባ ጭምር እንዲፈጠርብን የሚያደርግ ግጥም ይሆናል። ባንዲራው ውስጥ የታመቀው ሃሳብ፣ የጨርቁና የሰንደቁ ምጣኔ፣ ቀለሙና የቀለሙ ህብር፣ ከዜማው ጋር ተዋህዶ ቢታሰብ፣ ግጥም ይባላል እንደማለት ነው። ስልተ-ምት ያለው፣ ውበት የተላበሰ፣ ቁጥብ፣ እምቅ፣ በተመረጡ ቃላት የተጻፈ፣ አይረሴና የጣፈጠ ግጥም!!

የጥበብ ሥራው ይዘት – ከቅርፅ የሰመረ ሆነ እምንለው ይሄንን ነው። ስለጋሽ ጸጋዬ የአጻጻፍ ዘይቤ ስንመለከት፣ ራሱ ጋሽ ጸጋዬ እንደሚለው፤

የወል ቤት፣ ቡሄ በሉ ቤት፣ ሰንጎ መገን ቤት የተለመዱት ሲሆኑ፣ እኔ በስምንት የስንኝ ስልት ድንጋጌ ላይ ነው የምደረድረው። ይህም በአደራደርና በሰረዝ ነጥብ ተከፍሎ ይታያል። አንዳንድ ምሁራን የዚህን ድንጋጌ ዘይቤ (ስታይል) ስም ስላላገኙለትና እኔም ስላልሰየምኩት ‘የጸጋዬ ቤት’ ይሉታል” ብሏል።

አስረጅ –

“… አበባው ምድሩን ሲንተራስ፣ ያፈር ፅዋ ረፍቱን ሲገድፍ

ቢራቢሮ ያንቺስ ሞገስ፣ ለምንድን ነው አብሮ እንደሚረግፍ?”

.

“የጸጋዬ ግጥምና የወል ግጥም ልማድ”

.

የጋሽ ጸጋዬን ግጥም በወል አነባበብ ዘዴ ልማድ የተካነ ሰው ሲያነበው ስሜት ሊያጣበት ይችላል። ትንፋሽ አወሳሰዱም ሊያቅተው ይችላል። ዜማው ሊሰበርበትም ይችላል። በዚህም ምክንያት ግጥሙ – ግጥም ግጥም አይልም። በአጠቃላይ የወልና የጸጋዬ አገጣጠም ካንድ ልማድ ወደ ሌላ የመሸጋገርን ያህል ሊከብድ ይችላል።

ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ጋሽ ጸጋዬ ለተዋንያን የሚያዘጋደውን ቃለ-ተውኔት በዝርው፣ በስድ ግጥም መልክ ወደ አግድም እየጻፈ እንዲቀልላቸው የሚያደርገው። መገንዘብ ያለብን ግን በጸጋዬ ቤት የተጻፈውን ግጥም ወደ ወል ግጥም ስልት መለወጥ መቻሉን ነው።

ለአብነት አንድ የጸጋዬን ግጥም እንይ – ዜማውን ልብ በሉ።

በጸጋዬ ቤት የተጻፈው – አዋሽ

“አዋሽ ህመምህ ምንድነው? ህመምክስ አንተስ ምንድነው?

ከውሃ ወዝ የተለየ፣ መቼስ ልዩ  ንግርት የለህ?

እንደ ሴቴ ሸረሪት ፅንስ፣ ራስክን በራስ ዋጥ ያለህ …”

.

ይህንኑ ግጥም ወደወል ቤት ስልት ስለውጠው፣

“አዋሽ ሆይ ህመምክስ፣ አንተሳ ምንድን ነህ

ከውሃ ወዝ ልዩ፣ መቼስ ንግርት የለህ?

የሴቴ ሸረሪት፣ ፅንስ ዘር እንዳለው

ራስክን በራስህ መዋጥህ ለምን ነው?” ተብሎ ሊቀርብ ይችል ነበር።

ያም ሆኖ በሁለቱም ዘይቤ ቢሆን ቃላትን መምረጡና ሐረጋትን መቀመሩ የራሱ የሆነ ግጥማዊ ክህሎትን ይጠይቃል። Metaphor በሚባለው ወይ ተኪ-ተምሳሌት በሚባለው አንጻር ጋሽ ጸጋዬን ሳየው ምንም እንኳ ከአስመስሎ ቃሉ (Simile) አንጻር ያነሰ ቢሆንም፤ ብዙ ጊዜ ሲጠቀምበት እናያለን።

አሁንም በጋሽ ጸጋዬ ልሳን ግጥምና ቃል እንዲህ ተገልጧል።

ገጣሚው “ውስጣዊና ህያዊ ባህርዩን፣ መርጦ፣ አቅንቶ፣ ውበት አክሎ፣ በአስተዋይ ህሊናችን ውስጥ ቁስሉን የመፈወሱን ጥረት፤ ያደርጋል … ቃል ኃይል ነውና። ቃል ሕይወት ነውና”። ገጣሚው እኛ ውስጥ ፈውሱን ያገኛል። ለእኛ ደግሞ በፈንታው ፈውስን ይሰጠናል ማለቱ ይመስለኛል።

“ግጥም እርቃነ ልቦናችንን ወደ አልባሌው ሰው የየዕለት ህይወት ገልጠን የምንቀምረው ነው…” – እንደሕፃን ንጹህ ልብ ይዘን እንቀርባለን ማለቱ ነው። “ሸክላ ሠሪ ጡቧን – ባለቅኔው ኪነትን  ከምርጥ ቃለ-ሕይወት ዳግመኛ ይፈጥራሉ” ይለናል። ቃላት መምረጥ ያለክህሎት፤ ያለሙያ ያለስል ብዕር ሊሆን እንደማይችል ሲያስገነዝበን ነው።

“ፀሐይ ግንባሯን ቀልሳ፣ ከጭለማ ክንፍ ስትሸሽ ብርሃኗ በሌት ተዳፍኖ ዓይኗም ፈገግታዋም ሲሰንፍ” የሚለውን በአስረጅነት ይገነዘቧል።

ከጭለማው ክንፉን ሲዘረጋ ፀሐይ ግንባሯን እንደምትቀልስ በተኪ-ተምሳሌት (Metaphor) (ክንፍ እና ግንባር) እንዳስቀመጠው እንይ። ዓይኗና ፈገግታዋ ሲከስም፣ ወይም ሲጠፋ የሚለውን የተለመደ ግሥ ሳይጠቀም አላለም፤ ይልቁንም “ሲሰንፍ” የሚል ቀሰ በቀስ የመፋዘዟን ነገር የሚጠቁም፣ ውብ ቃል ይጠቀማል። ምርጥ ቃለ-ሕይወት እንዲል።

.

የጋሽ ጸጋዬ የሥነ ግጥም ጭብጦች

በ “እሳት ወይ አበባ”

.

  1. ማህበረሰባዊ/ግለሰባዊ ችግሮች

‘የምታውቀኝ የማላውቅህ’

“ለሩቅ ገጠሬ ነባሩ

ለማላውቅህ ለዳር ዳሩ

… ከረን ነህ መለሎ ብሌን

ከሁመራ ነህ ወይስ ገለብ

ማነህ

አጋው ነህ ወይስ ሺናሻ

ቅማንቴ ነህ ወይ ፈላሻ

ስምህ የሆነብን ግርሻ …”

ቦታው የማይታወቀውን፣ ዘር-ሐረጉ የተረሳውን፣ የሩቅ ገጠሬ በመጠይቃዊ አጻጻፍ ህሊናችን ላይ እንዲከሰት በማድረግ በረቂቁ ይወቅሰናል።

ግራ ጎንደር ነህ መተከል

ባላዋቂ የምላስ ቅርስ

የዘር ንፍገት ስትቀበል

ያለዳህ ስምህ ሲበከል

እምትችል እምትቀበል፣ እማትሞት እማትነቀል።”

እያለም፤ ስሙን ማንነቱን የተበከለውንና የተነጠቀውን ሳያጤኑ መነፈጉን ይነግረናል።

“እረኛ ነህ የከብት አርቢ

ሐማል ነህ የግመል ሳቢ

አራሽ ነህ የአገር ቀላቢ”

እያለ ኑሮውን ለማሟላት ሲል ገጠሬው ደፋ-ቀና የሚልበትን ሙያ፣ እንጀራውን መሠረት አድርጎ ለምን ይበደላል ከሚል የተቆርቋሪነት መንፈስ ይሞግተናል። መቻሉን መቀበሉን ግና በምንም ዓይነት እሱን መንቀል አለመቻሉን የማይሞት ጥኑ ገጠሬ መሆኑን አበክሮ ይነግረናል።

‘አይ መርካቶ’፣ ‘ማነው ምንትስ’፣ ‘ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል’፣ ‘አስቀመጡህ አሉ’‘ጎል’ እንዲሁ የማህበራዊ ፍሬ ጉዳይ የሚያነሱ ናቸው።

.

  1. ጥበብን በተመለከተ ቁርቋሬ

‘የብዕር አሟሟት ሌላ’

‘መትፋት ያስነውራል’ … ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው

.

  1. ፖለቲካዊ ሸንቋጮች

የጋሽ ጸጋዬ ግጥሞች ሀገራዊ ጉዳዮችን በብዛት ያነሳሉ ለኤድዋርዶ ሞንድላንድ ለሞዛምቢኩ ታጋይ የጻፈው ጥሩ አብነት ይሆነናል።

እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ

“አልጠራቸውም አይጠሩኝ

አይንኩኝ ስሜን አያንሱኝ”

ብለህ እንዴት ትመኛለህ፣ እንደማይተዉህ ስታውቀው

የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው?

የጅምሩን ካልጨረሰው?”

ያ ታጋይ በዳሬሰላም አደባባይ ነው የተገደለው። ከዚያ ድረስ ተከታትለው ነው የገደሉት። ጋሽ ጸጋዬ ለሱ ተቆርቁሮ ብቻ ሳይሆን የተለመደውን ተረትም ሰብሮታል፤ ህጉን ጥሶታል። “የተወጋ በቅቶት ቢተኛ የወጋ መች እንቅልፍ አለው” ይለናል። የሚታወቀው አባባል “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” ነው። ጸጋዬ በግልባጩ ነው የገለጸው። የተወጋ በቃኝ ብሎ ቢተኛ የወጋው አይተኛልህም። ተከታትሎ ይጨርስሃል ነው የሚለን።

‘እግር እንይ’ በስላቃዊ ዘይቤ የጻፈልን ነው፣ ‘ምንም አልል’፣ ‘አዋሽ’ በሲምቦሊክ በምልክታዊ መልክ ያቀረበልን ነው። ‘እንዳይነግርህ አንዳች እውነት’፣ ሌሎችም በርካቶች አሉት።

.

  1. የፍቅር ጉዳይ

በፍቅር ፍሬ ጉዳይ ዙሪያም እንደብዙ ገጣምያን ጋሽ ጸጋዬም ተመስጦበታል። ከነዚህ ግጥሞቹ መካከል በወል የአጻጻፍ ዘይቤ የጻፈው ‘መውደድ አባ ፀፀት’ ይገኝበታል። ‘መሸ ደሞ አምባ ልውጣ’ ሌላው ነው። ‘ተወኝ’፣ ‘ጌራ’‘አብረን ዝም እንበል’፣ ‘ትዝታ’ እያለ ይቀጥላል።

[“አብረን ዝም እንበል”። ጸጋዬ ገብረ መድኅን። 1996 ዓ.ም።]

.

  1. የታሪክና ጀግንነት ጉዳይ

‘የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ’‘ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት’፣ ‘ቦረን’ (የሃዩ አላኬ ሊበን ቀረርቶ)፣ ‘ዋ ያቺ አድዋ!’

ለአብነት ያህል ‘መተማን በህልም’ የሚለውን እንይ

“… ከራስ ዳሽን አድማስ ግርጌ

ከዞብል መቃብር ማዶ

መተማ የተኛ ዘንዶ

ተምዘግዝጎ ጠረፍ ንዶ

እንደሰሎሜ ምሳሌ፣ እንደሄሮድስ ሴት ልጅ ሽንጥ

በኖባ ተራራ ጥምጥም፣ ሠራ አካሉን ቢያንቀጠቅጥ…”

የሴት ልጅ ሽንጥን ዙሪያና የኖባን ተራራ አመሳስሎ ከመሳልም ባሻገር ሠራ አካሉን የማንቀጥቀጡን ሥዕል እንዴት እንደተጠቀመበት ስናስተውል እጅግ ድንቅ ምስል እናያለን።

.

  1. የሕይወት ፍልስፍና

ከ‘ሕይወት ቢራቢሮ’ አንጻር አንድ ምሳሌ ቆንጽለን እንይ ፦

“… ምን አይተሻል ከቄጤማ፣ ምን አይተሻል ከለምለሙ

ቀን አብረሽ አብበሽ ውለሽ፣ ሲመሽ አብረሽ መስለምለሙ?…

አስተምሪኝ ቢራ ቢሮ፣ ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ …

ሲተረትም ሲወጋ፣ ከየብልጭታው ውጋገን

የሰው የአራዊት የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገደ-ጉንዳን

ሲነሳ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያዛባ ሚዛን

በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ የተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን

ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል

ልደቱ ዕድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዛል፤

ይኸ ይሆን አልፋ-ኦሜጋ? ይኸ ይሆን አስቀድሞ ቃል?”

በሕይወት ላይ መፈላሰፍ የየገጣሚው አመል ነው። ከሕይወት ጋር ያልተሳሰረ ምንም አይገኝም። ሕይወት ወረት ናት። ከሚያምረው ጋር አብራ አብባ፣ ከሚከስመው ጋር የምትጠወልግ መሆኗ ለምንድን ነው? ብሎ ይጠይቃል ጋሽ ጸጋዬ። በቢራቢሮም ይመስላታል። የአያሌ በሳል የዓለም ገጣሚያን ታላቅ ጥያቄ ሰው የተባለ ፍጡር ከየት መጣ? መድረሻውስ ወደየት ነው፤ ነው የሚለው። ጋሽ ጸጋዬ ዥጉርጉር ቀለም ያላትን ውብ ቢራቢሮ በሕይወት መስሎ ይሄንኑ ታላቅ ጥያቄ ያነሳባታል፤

“ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ” እያለ።

ፍጥረት ሁሉ በማይመጠን ግዙፍ ታላቅ የተፈጥሮ ኃይል የተፈጠረ ነው የሚለውን ንድፈ ሀሳብ እየነገረን ያም ቢሆን የውጋጋን ብልጭታ ታህል የሚነገር ተረት መሰል ነገር ነውም ይለናል። መውለድ፣ መኖርና መሞት ያለ የነበረ መሆኑን እያመላከተ ምናልባት የፍጥረት አልፋና-ኦሜጋ ይህ ነው ተብሎ ቀድሞ የተጻፈው ቃል ይሆን ወይ? ብሎም ይጠይቃል፣ እንድንመራመር ያተጋናል። ጋሽ ጸጋዬ ይሄን ሁሉ ከመልከ-ብዙዋ ቢራቢሮ እንደሚነጋገር አድርጎ ነው የሚያጫውተን። ተምሳሌታዊ ውክልናው በጣም ማራኪና ኃይለኛ ነው።

‘እሳት ወይ አበባ’ ‘ድንቅም አደል?’፣ ‘ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ’ ዓይነቶቹ ግጥሞች እያንዳንዱ ግጥሙ ውስጥ ፍልስፍና ያለውን ያህል ራሱ በፍልስፍና ላይ የተመሠረት ግጥምም እንደሚጽፍ ያሳያል።

.

  1. ባህላዊ እሴት

ባህላዊ እሴት ላይ ሲያተኩር ደግሞ ‘በራ የመስቀል ደመራ’ን ጽፏል። ‘በየት አባቱ ሞትም ይሙት!’ ደግሞ የጋሞ ባህላዊ ሥርዓት በሞት ላይ ድል መጎናጸፍ መሆኑን ያበስረናል።

‘ለኢልማ ጋልማ’ – አባ ጋዳ የጻፈው ‘ቦረን’ (የሙርቲ -ጸሎት – ጥሪ)

“ጸጥታ ይሁን ፈረሱን አቅና

እምቦሳን አጥባ

ጊደሩን አርባ

ኮርማውን አስባ” ብሎ በሥነ ግጥም ይባርከናል።

‘አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ’፤ 1962 – ባሌ ጎባ የተጻፈውን ተመልከቱ፤

“ለካ እንደትዝታ አስታምሞ

እንደዘነጉት የእናት- ጡት፣ ከዘመን ጋር አገግሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፣ እጄን በትዝታሽ ያዢኝ

በሕልም ጣቶችሽ ሳቢኝ

መቼም … በውን አልሆንሺም፣ እንዲያው በሰመመን ዳሺኝ”

ትዝታዋ ያጠመደውን የባሌ ኦሮሞ እስኪያመው ድረስ ይስታውሳታል። እጅ ለእጅ መያያዛቸውን ለማስታወስ ለትዝታ ነው ኃይሉን የሰጠው። ሩቅ ሃሳብ መሆኑን ለማሳየት ጣቶቿ ሁሉ የህልም ጣት እንዲሆኑ አድርጓል። ዳሰሳዋን እንደሰመመን ስስ አድርጎታል።

የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም

የኔ ክንድ እኮ ተልም አይተልምም

የኔ ጣት አረም አይነቅልም

በፊደል መፈደል በቀር፣ ጉልጓሎኮ አይጎለጉልም

ለስልሻለሁ፣ ሠልጥኛለሁ፣ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም።”

ጋሽ ጸጋዬ ‘ፊደል’ የሚለውን ስም ወደ ግሥ ለውጦ ‘መፈደል’ ማለቱ ሳያንስ ጭራሽ ከጉልጓሎ ጋር ያነጻጸረዋል። መሠይጠን፣ መሠልጠን መሆኑን፣ መሠልጠን ደግሞ መለስለስ መሆኑን፣ መናገሩ ሳያንስ፤ የዚህ ዓለም ሥልጣኔ በጥንት የባህልና የልማድ አብሮ-አደጎቻችን ላይ ዛሬ ክፉ መሥራት መሠይጠን መሆኑን ያስረዳናል።

“… የማር እሸት እንቁረጥ ተይ፣ የጥቅምት አበባ እንቅጠፍ

ነይ ሸጎዬ አብረን እንግዘፍ

ጣት ለጣት እንቆላለፍ

በዐይን ጥቅሻ እንገራረፍ

ከአውድማችን አፋፍ ለአፋፍ፣ በዳሰሳ እንጠላለፍ

ተይ ፍቅር እንዘራረፍ

በህልም እንኳ እንተቃቀፍ…

አዎን ዕድሜም ያማል ከርሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ።”

የማር እሸት እንቁረጥ ተይ በሚለው መስመር ውስጥ ተይ በሚለው የማማለያም፣ የመማጸኛም ቃል የልጅነት ጨዋታውን ሊነግረን ፈልጓል። “ሸጎዬ አብረን እንግዘፍ” ሲለንም እንቅስቃሴውን ለመግለጽም፣ ግዙፍ እንሁን ለማለትም፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ገድሏል። በዳሰሳ እንጠላለፍ ሲልም ጉዳዩን ወደ ህልም ሲለውጠው ነው። “ተይ ፍቅር እንዘራረፍ” ማለቱን አስተውሉ። ፍቅርን እንደቅኔም፣ እንደሚነጠቅ ንብረትም የማየት ቅኔያዊ ውበት ነው የሰጠው። በህልም እንኳ እንተቃቀፍ የሚለው ውብ አጻጻፍ የትዝታን አስተቃቀፍ የሚያጠናክርልን ነው።

የመጀመሪያውን ስንኝ የመጀመሪያ ሐረግ ከመጨረሻው ስንኝ ብናስተሳስረው የጅምሩንና የፍጻሜውን መጣጣም እናስተውላለን፤

ለካ እንደትዝታ አስታምሞ

እንደዘነጉት የእናት ጡት፣ ከዘመን ጋር አገግሞ (ይሄ የመጀመሪያው ስንኝ ነው)

አዎን ዕድሜም ያማል ከርሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ (ይሄ ደግሞ የግጥሙ መደምደሚያ ነው።)

.

  1. መልክዓ ምድራዊ ይዘት

መልክዓ ምድራዊ ይዘት ያላቸው እንደ ‘አባይ’ እና ‘ሊማሊሞ’ ያሉ ግጥሞችንም ጽፏል ጋሽ ጸጋዬ። ምስልና ማመሳሰያ ቃላት እንደልብ የሚያጠግበን በነዚህ ዓይነቶቹ ግጥሞቹ ነው። ከ‘ሊማሊሞ’ ጥቂት መስመሮቹን እንመልከት፤

“የሰማይ የምድሩ ኬላ፣ የየብስ የጠፈሩ ዋልታ

አይበገር የአለት ጣራ፣ አይመክተው መከታ

ሊማ-ሊሞ አድማስ ሰበሩ፣ በጎማ ፈለግ ይፈታ?

በትሬንታ እግር ይረታ?…”

ሊማሊሞን የጻፈው ለፈረደ ዘሪሁን ነው። ፈረደ ዘሪሁን እንግዲህ የታዋቂው ደራሲ የብርሀኑ ዘሪሁን ወንድም መሆኑ ነው።

ጸጋዬ በዚህ ግጥሙ ውስጥ ልዩ ልዩ እኩያ እየፈጠረ ሊማሊሞን እሱ ባየበት ዐይኑ ሲያሳየን እናገኘዋለን – ሊማሊሞ የምድር ኬላ ነው። ሊማሊሞ ለምድር ዘብ የቆመ ነው። ሊማሊሞ ለጠፈሩ ደግሞ ዋልታ ሆኖ የቆመ ነው። ሊማሊሞ የማይበገር አለት ነው። መከታና ጋሻ ነው። ሊማሊሞ በዐይናችን የምናየውን ሰፊ አድማስ ሰብሮአል።

ይሄ ሁሉ መሬት ቆመን ከኛ እያነጻጸርን ስናየው የሚፈጠርብን ስሜት ነው ማለቱ ነው። ወደ ሽቅብ ከሰማዩ ጋር ስናየው ደሞ ሊማሊሞን እንደቆመ ወንዲስ ሰው አድርገን እፊታችን እንድናይ ለማድረግ ከደመናው በላይ አልፎ ይታየናል ይለናል። አለፍ ብሎም ከሰማይ ጋር ይለካካል። ጉም እንደቀሚስ አጥልቋል። የፀሐይቱን ጨረር ደግሞ እንዳንገት ልብስ ሸብ አድርጎታል። ከአንገቱ ይጀምርልንና “በብብቱ ጉም ታቅፎ” እያለን፤ ግራና ቀኝ የጮራ ዘርፍ እንደሰራ በመጥቀስ ያሞካሸውና “ፍም አንጥፎ እንደስጋጃ” ብሎ እግርጌ ያደርሰናል።

በግዙፍ ተራራ መልክ የቆመ የሰው ምስል ነው የሰጠን። ሆኖም ይሄ የማይበገር ተራራ “በድማሚት ተፈልፍሎ፤ ድልድይ ይሁንና ይረፍ ወይ?” ብሎ ነው የሚደመድምልን። ሥልጣኔ የማይረታው የተፈጥሮ አካል የለም እንደማለት ነው የተጠቀመበት – ምስለታውን።

.

ነቢይ መኰንን

.

[ምንጭ]አዲስ አድማስ ጋዜጣ/ አንድምታ መጽሔት (ቁጥር 9)። ኅዳር 2000 ዓ.ም።

.

 

“የብዕር አሟሟት ሌላ” (ግጥም)

“የብዕር አሟሟት ሌላ”

ከጸጋዬ ገብረ መድኅን

.

(1959 ዓ.ም)

.

[በደራሲው ቤተሰብ ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

.

.

የቃለ – ልሣን ቅመሙ

የባለቅኔ ቀለሙ

ነጠበ እንጂ ፈሰሰ አንበል፣ ቢዘነበል እንኳ ደሙ

ሰከነ እንጂ ከሰለ አንበል፣ ቢከሰከስ እንኳን ዐፅሙ፤

የቃል እሳት ነበልባሉ

አልባከነምና ውሉ

የዘር – ንድፉ የፊደሉ

ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ።

እስካልተዳፈነ ፍሙ

እስካልተሰበረ ቅስሙ

እስካልተቀበረ ስሙ

የደራሲ ዐፅመ – ወዙ

የብዕር ቀስተ – መቅረዙ

ሕዋሳቱ እስካልቀዘዙ፤

አልፏልና ከሥጋ – ሞት

በቃሉ ሚጠት ስልባቦት

በፊደሉ አድማሰ – ፍኖት

በኅብረ ቀለሙ ማኅቶት

በሥነ – ግጥሙ ምትሃት

በግሱ ንጥረ – ልሳናት

በነባቢቱ ነፍስ እሳት፤

ይነዝራልና ደም – ሥሩ፣ አይሞትምና ፀዳሉ

ቢሞት እንኳ ሞተ አትበሉ …

የብዕር አሟሟት ሌላ

ሲፈስ የብሌኑ ኬላ

የፊደል መቅረዝ አሟሟት

ከውስጥ ነው እንደ ጋን መብራት

በቁም ነው እንደ ቁም ፍትሐት

የሚያጨልም የነፍስ እሳት፤

እንጂ ብዕር ሞተ አትበሉ፣ እሳቱን ሳያስለመልም

ነበልባሉን ሳያከስም

ውጋጋኑን ሳያጨልም።

ቃለ – ምንጩን ካልመሰነ፣ ስለቱን ካልጐለደፈ

መቅረዙን ካልተዳፈነ፣ ከፊደሉ ካልነጠፈ

ዐፅመ – ወዙን ካልደረቀ፣ ጧፉን ቀልጦ ካልሰፈፈ

ጡጦ እንደጠፋበት አራስ፣ ቁም ተዝካሩን ካልለፈፈ

ብዕሩ ቀርቶ ምላሱ፣ በሃሜት ካልተንጠፈጠፈ፤

የቃለ – እሳት ነበልባሉ

የድምፀ ብርሃን ፀዳሉ

የኅብረ ቀለማት ኃይሉ

አልባከነምና ውሉ

የዘር – ንድፉ የፊደሉ

ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ።

.

ጸጋዬ ገብረ መድኅን

.

 “ለካሳ ተሰማ”።

1959 ዓ.ም – ቆቃ።

.

(በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ]“እሳት ወይ አበባ”። 1966 ዓ.ም። ገጽ 37-38።

.

 

“ሙሉቀን መለሰ” (ቃለመጠይቅ)

“ከሻይ ቤት ሀርሞኒካ እስከ ዳህላክ ባንድ”

በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

(1973 ዓ.ም)

.

.

አንዳንድ ዘፈን አለ … ድንገት ደርሶ ድፍን አዲስ አበባን የሚያጥለቀልቅ። በየቡና ቤቱ፣ በየ መጠጥ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ በቴፕ ያሰሙታል። ካሴት ያላቸው ታክሲዎች ውስጥም ሲዘፈን ይሰማል። በመንገድ ጐረምሶች ዜማውን ያፏጩታል። ሴቶች ብቻቸውን ሆነው ልብስ እያጠቡ ወይም ወጥ እየሠሩ ለራሳቸው ይዘፍኑታል። ልጆች መንገድ ሲሄዱ ይዘፍኑታል … አልፎ አልፎ ባንድ እግራቸው ብቻ እየነጠሩ። ገና አፋቸውን የፈቱ ሕፃናትም ይኰላተፉበታል። የመንደር ሰካራሞችም ይንገዳገዱበታል። ባጭሩ፣ የከተማው ዘፈን እሱ ይሆናል።

ከጥቂት ወራት በፊት “ናኑ ናኑ ነይ፣ ናኑ ናኑ ነይ፣ ካንቻለኝ ጉዳይ!” እያለ ሲያስተጋባ ነበር የአዲስ አበባ ሕዝብ … ከሙሉቀን መለሰ ተቀብሎ ነበር የዘፈነው።

.

[“ናኑ ናኑ ነይ”። ሙሉቀን መለሰ። ዳህላክ ባንድ። 1972 ዓ.ም።]

.

አንድ የሥራ ጓደኛዬ እድሜዋ ሶስት ዓመት ተኩል የሆነ ልጅ አለችው። አንድ ቀን፣

“አባዬ! ያቺ ኮ ስሟ ናኑ ነው” አለችው ወደ አንዲት ኰረዳ እያመለከተች።

“ኧረ?” ሲላት፣

“አዎን” አለች፤ “ብትፈልግ ትላንትና ‘ናኑ ናኑ ነይ፣ ካንቻለኝ ጉዳይ’ ስል ጊዜ መጣች!”

ጓደኛዬ ይህን ከነገረኝ በኋላ፣ “ያንን ሙሉቀንን ባወቅኩት እቺን አጫውተው ነበር” አለኝ።

Muluken 1973b

ሙሉቀን መለሰ አጠር ያለ፣ ወፈር ያለ፣ በጣም ቀይ የሆነ የሃያ ስምንት ዓመት ጐረምሳ ነው። ለሁለት ሰዓት ይህል ሲያነጋግረን እንደገመትኩት ሙሉቀን ሀሳቡን በቀጥታ የሚናገር ሰው ነው። ማለቴ፣ “እንዲህ ያልኩ እንደሆነ እንደዚህ ተብሎ ሊተረጐምብኝ ይችላል” የሚል ሥጋት የለበትም።

“ሙሉቀን ብለው ስም ያወጡልህ ለምንድነው?” አልነው።

“እህቴ ነች ያወጣችልኝ። እናቴ ‘ሙሉሰው’ ነው የምትለኝ። ከኔ በፊት አስወርዷት ነበር። ደሞ ታላላቆቼ አራቱም ሲወለዱ ምጥ ይበዛባት ነበር። እኔ ስወለድ ግን ይህ ችግር አልነበረም። ለዚህ ነው ‘ሙሉሰው’ ያለችኝ። ‘ስማቸው’ ይለኛል አባቴ። የመሬት ሙግት ነበረበት። ጠላቶች ነበሩት። እነሱን ስማቸው ማለቱ ነው።”

ሙሉቀን መለሰ በጐጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም ተወለደ። አሥር ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ፣ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አጐቱ እንዲማር ብለው አመጡት። ኰልፌ ሰፈር ጳውሎስ ትምህርት ቤት ገባ። ግን ብዙ አልተማረም። ያጐቱ ሚስት ይጠሉት ስለነበረ ብስጭት በዛበት።

እንግዲህ ኰልፌ አንድ የጡረታ ቤት ነበረ። ባንድ ጐኑ የልጆች ማሳደጊያ ነበረው። የሚረዱ አሉ ሲባል ሰምቶ ሙሉቀን ሄዶ ጠየቀ። ተቀበሉት።

“የበላይ አስተዳዳሪዋ ይወዱኝ ነበር። ‘ኤልቪስ’ ነበር የሚሉኝ። በሁለት ወር እንደዚህ ልብስ ይዘውልኝ ይመጡ ነበር። ውጭ አገር ልኬ አስተምርሃለሁ ብለውኝም ነበር። ይንከባከቡኝ ነበር። እወዳቸው ነበር። ውለታቸው በጣም ትዝ ይለኛል።”

እዚያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተከፈተ። አቶ ተፈራ አቡነ ወልድ ነበሩ አስተማሪው።

Muluken Melesse (1964) - Yemiaslekes Fikir & Hedech Alu (AE 440) 1b

ሙሉቀን ስድስት ወር ያህል እንደተማረ እህቱ ስለታመመች ወደ አገር ቤት ሄደ። ያን ጊዜ ነው አዲስ አበባ ውስጥ አክስት እንዳሉት ያወቀው። እሳቸው ይዘውት መጡና ከሳቸው ጋር መኖር ጀመረ። ቤታቸው የካ ሚካኤል ነው። እንግዲህ ሙሉቀን ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አልተመለሰም።

አክስቱ የወታደር ሚስት ናቸው፣ ጠላም ይነግዳሉ። ኑሮአቸው ጐስቋላ ነው። ልጁ አልተመቸውም።

አንድ ቀን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ሄደ። ሊቀጠር። አልተቀበሉትም። ግን በእርዳታ መልክ ሻይ የማፍላት ሥራ ሰጡት።

“ምድጃዋ የኤሌክትሪክ ነበረች። ባንድ ቀን ውስጥ ሶስት ጊዜ ኮረንቲ ያዘኝ” አለ።

ስድስት ወር ያህል ከሰራ በኋላ ትቶት ወጣ። ጥቂት ወራት ተንከራተተ።

ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወረድ ብሎ አንድ ሻይ ቤት ነበረ። የሻይ ቤቱ ባለቤት ሙሉቀንን ይወደዋል፤ ይረዳዋል። ሀርሞኒካ የሚጫወት ጓደኛ አለው ሙሉቀን። ሻይ ቤቱ ቁጭ ይሉና ጓደኛው ሀርሞኒካውን ይጫወታል። ሙሉቀን ይዘፍናል።

abunepetros1-620x310

አንድ ቀን ሙሉቀንና ጓደኞቹ አብረው ሲጫወቱ ያመሹና ወደ ሶስት ሰዓት ላይ አንዱን ጓደኛቸውን ለመሸኘት ይነሳሉ። ደጃች ውቤ ሰፈር ሲደርሱ የውቤ በርሀ ልዩ ልዩ ቀለማት መብራቶች በርተው ሙሉቀንን በጣም ያስደንቁታል። አንዱ ቤትማ ከሌሎቹም የበለጠ አሸብርቋል። ጓደኛሞቹ ይኸ ቤት ምንድነው ብለው ሲጠያይቁ፣ ይኸማ ‘ፈጣን ኦኬስትራ’ የሚጫወትበት ‘ፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ’ ነው ይሏቸዋል።

ፊት ለፊቱ ካለው ሱቅ ሄደው፣

“ባለቤቱ ማነው የዚህ ናይት ክለብ?” ብለው ጠየቁ።

“ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ናቸው” አለ ባለሱቁ።

“ሥራ ይሰጡኝ ይሆን ወይ?” ብሎ ጠየቀ ሙሉቀን።

“ፃፍና ጠይቃቸው” አለው ባለሱቁ ወረቀትና እስክሪፕቶ እየሰጠው።

እዚያው ቆሞ ደብዳቤውን ፃፈ። ጓደኛሞቹ ከፍርሃት ጋር እየታገሉ ከዚያ ከአስደናቂ ቤት ገቡ። ሙሉቀን ደብዳቤውን ለኦኬስትራው መሪ ሰጠው።

አነበበውና ሳቀበት።

“ምንድነው እሱ?” አሉ ወይዘሮ አሰገደች ከወዲያ ቁጭ ብለው።

ሰውየው ነገራቸው። ደብዳቤውን ተቀብለው አነበቡ።

“ፈትነው። ካለፈ ጥሩ … አለዚያም ሌላ ሥራ እሰጠዋለሁ” አሉ። የልጅ መልኩና ጎስቋላ ሁኔታው ሀዘኔታቸውን ቀስቅሶ ሳይሆን አይቀርም።

ያን ጊዜ ሙሉቀን እንደ ጥላሁን ገሰሰና እንደ ዓለማየሁ እሸቴ እያደረገ ይዘፍን ነበር። ባዶ እግሩንና በቁምጣ ሱሪ መድረኩ ላይ ወጣና ‘ለውነት እሞታለሁ፣ አልሳሳም ለነብሴ’ን እና ‘እንክርዳድ’ን ዘፈነ።

የናይት ክለቡ ሴቶች (በጣም ብዙ ናቸው) ዘፈኑን ወደዱለትና ያን ጊዜውኑ አንድ አራት መቶ ብር የሚሆን አዋጡለት።

“በበነጋታው ካኪ ልብስ ተገዛልኝ፤ ሱፍ ልብስ ተለካሁ። ቢትልስ ጫማ አደረኩ … እግሬን ታጥቤ!” አለ።

Muluken 1973d
ሙሉቀን በ1960ዎቹ መጀመሪያ።

እዚያው ክፍል ተሰጠው። ምግብም ከዚያው ነው። የዘፈን ሥራ ጀመረ።

ወደ ናይት ክለቡ የሚመጣው ሰው እየበዛ ሄደ። ወይዘሮ አሰገደች ሙሉቀንን ኮንትራት (ውል) አስፈረሙት። እሱ ማታ ማታ ሊዘፍን፣ እሳቸው በወር ዘጠና ብር ሊከፍሉት።

“ዘጠና ብር! ሚልየኔር የሆንኩ ነው የመሰለኝ!” አለን።

የቀድሞው አሜሪካን ቤተ መጻሕፍት አጠገብ ‘ዙላ ናይት ክለብ’ የሚባል ነበር። የዚህ የዙላ ባለቤቶች መጥተው አነጋገሩት ሙሉቀንን። በወር ሦስት መቶ ብር እንክፈልህ፣ ለኛ ዝፈን አሉት። እሺ ብሎ ሄደ።

ሴትየዋ ኮንትራት አፍርሷል ብለው አሳሰሩት። ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ። አንዱ ፖሊስ እሳቸውን ለማስደሰት ብሎ ሙሉቀንን በጥፊ ሲለው ጊዜ ታዲያ በጣም ተቆጡት።

“እንድታስፈራሩልኝ ነው እንጂ እንድትጎዱት አይደለም” አሉ።

ከቤታቸው አልጋ መጣለትና ተረኛው መኰንን ክፍል ተነጥፎለት እዚያ አደረ። በነጋታው ተፈታ። ‘ዙላ ናይት ክለብ’ ገባ።

“ጋሽ ሰሎሞን ተሰማ የደረሰውን ‘የዘላለም እንቅልፍ’ እና አቡበከር አሸኬ የደረሰውን ‘ያላየነው የለም’ … ሁለቱን ዘፈን ይዤ በቴሌቪዥን ቀረብኩ።”

.

[“የዘላለም እንቅልፍ”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም/ዜማ) ሰለሞን ተሰማ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1961-1964 ዓ.ም።]

.

አዲስ አበባ ሙሉቀን መለሰን ሊያውቀው ጀመረ።

Muluken Melesse (1965) - Antarekm Wey & BeMistir Kiberign (PH 7-181) 1a

የፖሊስ ኦርኬስትራ አስተዋዋቂ ሻለቃ ወርቅነህ ዘለቀ (የቅጽል ስማቸው ‘ይቀጥላል’)፣

“አንድ አራት መቶ ብር እንክፈልህ፣ ና እኛጋ!” አሉት።

እሺ ብሎ ሄደ። የወር ደሞዙ ይመጣል ታድያ – አንድ መቶ ብር ብቻ!። እወጣለሁ ቢል ጊዜ፣ “ፈርመሃል!” ብለው አስፈራሩት። ልጅ ነዋ!

ሙሉቀን መለሰ ለፖሊስ ኦርኬስትራ በተቀጠረ በሦስት ቀኑ መቀሌ ከኦርኬስትራው ጋር የ “ወይዘሪት ትግራይ” የቁንጅና ውድድር ይደረግ ነበር። ሙሉቀን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈኖች ዘፈነ። በጣም ወደደው ሕዝቡ። የኦርኬስትራው አባሎችም አለማየሁ እሸቴ ሄዶባቸው ስለነበረ ሙሉቀንን “ምትኩ” አሉት።

ተስፋዬ አበበ የደረሳቸውን ሦስት ዘፈኖች (“እምቧይ ሎሚ መስሎ” “እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ” እና “ልጅነት” የተባሉትን) ሙሉቀን በሕዝብ ፊት ይዘፍን ጀመር። በነዚህ ዘፈኖች ታዋቂነትን አተረፈ። ጋዜጣ ላይም “ኮከብ ድምጻዊ ተጫዋች” ብለው ጻፉለት።

.

[“እምቧይ ሎሚ መስሎ”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም) ተስፋዬ አበበ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1961-1964 ዓ.ም።]

.

ከፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ሦስት ዓመት አገልግሎ ወጣ … የማታ ክበቦች እንደገና መጫወት ጀመረ።

Muluken 1973f

ዛሬ በግዮን ሆቴል በ‘ዳህላክ ባንድ’ እየታጀበ ይዘፍናል።

አንድ አስር የሚሆን የሙሉቀን መለሰ ሸክላ ወጥቷል። ከአብዮቱ ወዲህ ዘፈኖቹ በካሴት ተሰራጭተዋል።

ከዘፈኖችህ በጣም የምትወደው የትኞቹን ነው? ብለን ጠየቅነው።

“እኩል ነው የማያቸው። ግን … በጣም የሚያረኩኝ … በዜማውና በዘፈኑ … ‘ሰውነቷ’ እና ‘ሆዴ ነው ጠላትሽ’ … እ …… በሙዚቃ ጥራትና ባሠራር ደግሞ፣ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀነባበራቸውና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈንኳቸው ‘ቼ በለው’ እና ‘ውቢት’።”

Muluken Melesse (1967) - Chebelew & Wubit (A 004) 1b

[“ቼ በለው”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም/ዜማ) ተስፋዬ ለማ። Equators Band። 1967 ዓ.ም።]

[“ሰውነቷ”። ሙሉቀን መለሰ። ዳህላክ ባንድ። 1971 ዓ.ም።]

.

ከድምፃውያን ተጫዋቾች ማንን ታደንቃለህ? አልነው።

“ዓለማየሁ እሸቴን። ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው። ካሉን ዘፋኞች ሁሉ የበለጠ የሙዚቃ እውቀት አለው። ሁላችንም በዘልማድ የምንዘፍን ሲሆን፣ እሱ ግን ሙዚቃን በማወቅ ከኛ ብልጫ አለው። ፕሮፌሽናል ኢንተርናሽናል (በአለም አቀፍ ደረጃ ባለሙያ) ዘፋኝ ያለን እሱ ነው ብዬ የምኰራበት ሰው ነው።

“በድምፅ ደሞ እንደ ምኒልክ ወስናቸው ያለ ዘፋኝ የለንም። የኦፔራ ዘፋኝ ድምጽ ነው ያለው … ጥላሁን፣ ዓለማየሁ፣ ምኒልክ፣ ብዙነሽ፣ ሂሩት፣ ማህሙድ – እነዚህን የሚተኩ ድምጻውያን መብቀል አለባቸው። ይኸ የአገሪቱ ኃላፊነት ነው … ይህን ሙያ ሲበዛ ነው የምወደው። በየዕለቱ ይበልጥ እያወቅከው … እየተማርከው ትሄዳለህ። ማቆሚያ የለውም … ሙዚቃን በትምህርት ሳይሆን በልማድ ነው የማውቀው።

Muluken 1973a

“አንደኛ የሚባል ዘፋኝ የለም። ሊኖርም አይችልም። ቢበዛ ‘የዓመቱ ኮከብ’ መባል ይችላል እንጂ … እያንዳንዱ ዘፋኝ የራሱ አይነት ልዩ ተሰጥዎ አለው።”

.

[“ላንቺ ብዬ”። ጥላሁን ገሰሰ። (ግጥም/ዜማ) ምኒልክ ወስናቸው። All-Star Band። 1963 ዓ.ም።]

[“እሩቅ ያለሽው”። ዓለማየሁ እሸቴ። (ግጥም) ኃይሉ መኩሪያ። ዓለም-ግርማ ባንድ። 1965 ዓ.ም።]

[“የእንጆሪ ፍሬ”። ምኒልክ ወስናቸው። ቀኃሥ ቴአትር ኦርኬስትራ። 1960ዎቹ።]

[“አትራቀኝ”። ብዙነሽ በቀለ። (ግጥም/ዜማ) ተዘራ ኃ/ሚካኤል። ዳህላክ ባንድ። 1969 ዓ.ም።]

[“እውነተኛ ፍቅር”። ሂሩት በቀለ። (ግጥም) ተስፋዬ አበበ (ዜማ) ንጉሤ ዳኜ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1969 ዓ.ም።]

[“ትዝታ”። ማሕሙድ አህመድ። (ግጥም) ሸዋልዑል መንግሥቱ። አይቤክስ ባንድ። 1967 ዓ.ም።]

 [“መውደዴን ወደድኩት”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም) ዓለምፀሐይ ወዳጆ። ዳህላክ ባንድ። 1971 ዓ.ም።]

.

ሙሉቀን መለሰ

(ቃለመጠይቅ በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር)

1973 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ኪነት ዓምድ”። ፀደይ መጽሔት። ኅዳር ፲፱፻፸፫ ዓ.ም። ገጽ 12-14፣ 20።

.

 

“ሌቱም አይነጋልኝ” (ልብወለድ)

“ሌቱም አይነጋልኝ”

በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

.

.

ምዕራፍ 3

(ገድለ ጥላሁን)

“አያ በለው በለው

አያ በለው በለው

አያ በለው በለው”

.

ታዲያ ዓይናችን አገልጋያችን ነው ትለኛለህ? አገልጋያችን ከሆነ ለምን ትርሲትን ፈልግ ስለው ሄዶ ኃይለሚካኤል ላይ ያርፋል?

ኃይለሚካኤል አንድ የውቤ በረሃ ጀግና ነው። ሰውነቱ ግዙፍ፣ መልኩ ቀይ፣ አፍንጫው ደፍጣጣ፣ ፀጉሩ በጣም ሉጫና በቅባት የሚያብለጨልጭ፣ በጡንቻው የታወቀ ነው። አሁንም ሳየው ሮዛን እጇን ጠምዞ የቀልድ እያስመሰለ ቂጧን በጥፊ ይመታታል። ሮዛ እንዳትስቅ አመማት፣ እንዳታመር የባሰውን እንዳይደበድባት ፈራች። ስለዚህ በውሸት ሳቅና በእውነት ንዴት መሃል፣

“ጋሼ ኃይልዬ! እባክህን ተወኝ ያማል!” ትላለች።

አልተዋትም። ውቤ በረሀ የሚመጣው ሴቶቹን ለመደብደብ ወይም ወንዶቹን ለመገላመጥ ነው።

አንድ ማታ ለምሳሌ ከአንድ ፈረንጅ ጋር ዝናሽ ቤት መጣ። ይኼ ፈረንጅ ፀሐይን ሁለት ውስኪ ጋበዛትና እንሂድ አላት። ሰው አለኝ አለችው። ኃይለሚካኤል ታዲያ ብድግ አለና፣

“የኔን እንግዳ? አንቺ ቂንጥራም!”

እያለ በጥፊ – በእርግጫ – በክርን – በጡጫ ሲያጣድፋት ጊዜ አፍንጫዋ ደማ፣ ዐይኗ አበጠ። አምስት ቀን ተኛች ስትተነፍስ ጎኗን እያመማት ብዙ ተሰቃየች። እስከ ዛሬ በደንብ አልዳነችም፤ ስትስል ወይም ስትስቅ ጎኗን ያማታል። የኃይለሚካኤል ጡንቻ ነው።

ተኝታ ሳለ ልጠይቃት ገብቼ ስናወራ፣

“ለምን አትከሺውም?” አልኳት።

“አንተ ደሞ! ከመቼ ወዲህ ነው ሸርሙጣ ተረገጥኩ ብሎ ‘ሚከሰው?” አለችና ማልቀስ ጀመረች። “ደሞ ብከሰውም እኔ ነኝ ምታሰረው። ወንድሙ የፖሊስ ሻለቃ ነው።”

ኃይለሚካኤል ሲያጠቃ ሴቶችን ብቻ አይደለም። ወንዶችንም ነው። አሀዝ ሲነግረኝ (አሀዝም ራሱ ጉልበተኛ ነው – ብቻ ሴቶቹን አይነካም) አንድ ማታ ሁለቱም አብረው መርካቶ ሾፌሮች ቡና ቤት ገቡ። እዚያ አንድ ጠብዚራ ክብር ዘበኛ ነበር። ስክር ብሎ መጠጥ መቅጃው ባንኮኒ ዘንድ ቆሞ ስለኮርያ ዘመቻ – ስለቶኪዮ ይለፈልፋል። ኃይለሚካእል አሀዝን፣

“አቦ ይኼ ቡፋ ምን ጡሩንባውን ይነፋብናል?” አለው።

“ካማረህ ዝም አታሰኘውም?” አለ አሀዝ።

ኃይለሚካኤል “ተመልከት እንግዲህ” አለውና ጮክ ብሎ፣

“አቦ እዚህ ጩኸት በዛ!” አለ።

ክብር ዘበኛው “ታዲያ ጆሮህን  አትዘጋም?” አለው። ኃይለሚካኤል “አንተ አፍህን አትዘጋም?” አለና እጆቹን ጨብጦ ቀረብ አለው።

“ጆሮሽን ነው በጥፊ ብዬ ‘ምደፍንልሽ”

ኃይለሚካኤል ጠጋ ብሎ ፊቱን ለጥፊ አመቻችቶ ሰጠውና፣

“እስቲ?” አለው።

ክብር ዘበኛው “እንቺ!” አለና አንዴ በጥፊ ወለወለው። ኃይለሚካኤል ፊቱን እያሻሸ፣

“ታዲያ ይኼ የሚገባ ነገር ነው?” አለውና፣ ወንበር ፈልጎ ለብቻው ቁጭ አለ።

አሀዝን አኮረፈው።

ታዲያ ቅድም እንዳልኩት፣ ማሚት እሹሩሩ ቤት ውስጥ ኃይለሚካኤል ሮዛን የቀልድ ሲያጎሳቁላት ከቆየ በኋላ፣ ድንገት እርግፍ አድርጎ ተዋትና፣ ሰዎች መሀል መንገድ እየከፈተ ወደ በሩ በኩል ሄዶ ጥላሁንን ጨበጠው።

ጥላሁን በውቤ በረሀ የታወቀ ረብሸኛ እንደመሆኑ መጠን፣ ልክ ሲገባ እንዳየኸው ሄደህ ካልጨበጥከውና “እንደምነህ ጥላሁን? የት ጠፋህ ባክህን?” ካልልከው ኮራህ ብሎ ይቀየምሃል፤ ትንሽ የጠጣ ጊዜ ነገር ይፈልጋሃል።

ሱሪውን በክንዶቹ ከጎንና ጎኑ ከፍ እያደረገ፣ መፋቂያውን አፉ ውስጥ ከግራ ወደ ቀኝ እያዘዋወረ፣ ደም የለበሱ ትልልቅ ዓይኖቹን እያፈጠጠ፣ በሚያስፈራ ድምጽ “ፈረሰኛውን!” እያለ ይመጣብሃል።

ስለዚህ ኃይለሚካኤልና ሌሎችም የበረሀ ጀግኖች መጥተው ጨበጡት፣ አንገቱን አቀፉት፣ ጀርባውን መታ አደረጉት። በውቤ በረሀ ሥነ ሥርዓት ገበሩለት። አሁን ከኃይለሚካኤል ጋር አብረው እየተሽቆጠቆጡ ጥላሁንን ሰላምታ የሰጡት ጀግኖች፣ ምናልባት ከጥቂት ደቂቃ በፊት ኃይለሚካኤልን ራሱን እየተሽቆጠቆጡ ሰላምታ ሰጥተውታል …

ውቤ በረሀ እንዲያው መጥቶ ደንሶ ገንዘብ ከፍሎ ሴት ተኝቶ የሚኬድበት ቦታ አይደለም። ወንዶች የተሰበሰቡበት ማንኛውም ቦታ ውስጥ አንዱ ከሁሉም መብለጡ መታወቅ አለበት። ከብቶችም መሀል፣ ውሾችም፣ ሰዎችም መሀል፣ አብዛኛው በማህበር የሚኖር ፍጡር መሀል እንደዚህ ነው። የተፈጥሮ ሕግ ሳይሆን አይቀርም። በዶሮ፣ በዝንጀሮና በሌሎችም አንዳንድ ፍጥረቶች መሀል ይህ ህግ ከመጠን በላይ ይሠራል።

አንድ ወንድ ከሌሎቹ ሁሉ በላይ መሆኑ እንዳይበቃው፣ ሌሎቹን ሁሉ ወንዶች ልጅነታቸውን ጨርሰው ሴቶቹን ማሽተት ሲጀምሩ ቢገድላቸው ይፈቅዳል። አንዳንዱማ በሕፃንነታቸው ይገድላቸዋል። እናቶቻቸው አንዳንዶቹን እንደ ሙሴ ደብቀው ያሳድጓቸዋል። ሲያድጉ መጥተው አውራውን ገድለው (አሁን ሸምግሏል) ቦታውን ይወስዳሉ። ተራቸውን እስኪገደሉ ድረስ ይነግሳሉ።

ለምንድን ነው? ያልክ እንደሆነ፣ ለሴቶቹ ነው። ‘እኔ ግን ለሴቶቹ ብዬ አይደለም፣ ለወንድነቱ ነው’ ትላለህ። ራስህን አታለልክ። ወንድ ስትል ከጎኑ ሴት ውስጠ ታዋቂ ነው። ስለዚህ ስማ፣ ውቤ በረሀ መጥተህ ስትጣላ ስትደባደብ የፍጥረትን ህግ መከተለህ ነው። በህጉ መሠረት እንዳሸናፊትህ መጠን ሴትህን ወይም ሴቶችህን ትመርጣለህ። ካንተ ቀጥሎ ከሌሎቹ የሚበልጠው ከቀሩት ሴቶች ውስጥ ይመርጣል።

መጨረሻ የቀረው ወንድ መጨረሻ ይመርጣል፣ ወይም የቀረችውን አንዲት ይወስዳል፣ ምንም ሴት ካልተረፈ ቀረበት። ምናልባት አንተን ተደብቆ ይከተለህና ሴትህን ከጠገብካት በኋላ ለጥቂት ጊዜ ትተሃት አደን ስትሄድ በስርቆሽ ይተኛታል። ግን ዘርህን ቀድመኸው ዘርተሃልና የሚወለደው ልጅ ያንተ ነው፣ ጉልበት የሌለው ዘር ሳይተው ይሞታል። ይህ የፍጥረት ህግ ነው። ብርቱውን ማባዛት፣ ደካማውን ማጥፋት። ክርስቶስም ብሎታል “ላለው ይጨመርለታል፣ የሌለው ግን ያ ያለውም ይወሰድበታል”።

የሰው ስልጣኔ ይህን የጉልበት ህግ ጥሶታል። ግን ላይ ላዩን ነው እንጂ ውስጥ ውስጡን ይህ ህግ አሁንም ይሰራል። እዚህ በረሀ ውስጥ ብታስተውል ጉልበተኛው ነው የፈለጋትን ሴት የሚያገኝ። አንዳንዴ ባለ ገንዘቡ ነው። ለምን? ህገ-ወጥ የሆነው የሰው ስልጣኔ በጉልበትህ እንዳትጠቀምበት ይከለክልሃል። ግን አሁንም ላይ ላዩን ነው እንጂ ውስጡን ብትመለከት እንዴት ነው? ገንዘቡ ከጉልበትህ የበለጠ ጉልበት ነው። የሚገዛውን ጠበቃ፣ የሚያስከትለውን እስራት አስብ – ይኼ ጉልበት አይደለም?

አንድ ማታ ማሚት እሹሩሩ ቤት እኔ፣ ክንፈ፣ አሥራት ዕንቁ እና ጥላሁን ባንኮኒው ዙሪያ ቆመን ስናወራ፣ ጥላሁን እየሳቀ፣

“ለመሆኑ ለምንድን ነው እዚህ በረሀ ጥል የሚበዛው?”

ብሎ ጠየቀና፣ ይህን የፍጥረት ህግ ከዘበዘብኩለት በኋላ፣ በቁጣ ዓይነት ድምፅ፣

“እንግድያው አንተ ለምን እንደ ህጉ መሠረት አትደባደብም?” አለኝ።

 እየሳቅኩ፣

“እኔ ወንድ መቼ ሆንኩ?” አልኩት።

ሌሎቹም ከኔ ጋር ሳቁ። ጥላሁን ግን አፈጠጠብኝ። ስሜት ይጎድልሃል፣ ሰው አይደለህም ብሎ ሁልጊዜ እንደነቀፈኝ ነው። አሁን ግን የተቀየመኝ ከልቡ የጠየቀኝን ጥያቄ ወደ ቀልድ ስላዞርኩበት ነው።

ወደ መደነሻው ወለል እየተመለከተ፣ አፉ ውስጥ መፋቂያውን ከግራ ወደ ቀኝ እያዛወረ፣

“ትርሲትንና ብርሃኑ ተመልከት” አለኝ።

ሁላችንም አየናቸው። ጥብቅ ብለው ተቃቅፈው ታንጎ ይደንሳሉ። የሱ ፀጉር (ከአባቶቹ የወረሰው ረዥም ሉጫ ፀጉር) ከግንባሩ በኩል ወድቆ ከሷ ፀጉር ጋር ተደባልቋል።

“ብርሃኑ እንደምታየው ኮሳሳ ቢጤ ነው” አለ ጥላሁን … “በጉልበትም ቢሆን እዚህ የሚመጡት ወንዶች ብዙዎቹ ያሸንፉታል። በገንዘብም ቢሆን ብዙዎቹ ይበልጡታል። ግን ማንም ቢሆን ትርሲትን ሊወስድበት አይችልም። እውነቴን ነው? You agree?”

“አዎን”

“ታዲያ የዳርዊን Natural Law የምትለው የታል የሚሠራው?”

ረታሁ ብሎ ደስ ብሎታል። በቆንጆ ነጭ ጥርሶቹ ፈገግታ አሳየኝ።

“እንድያውም እዚህ ላይ ነው በግልጽ የሚሠራው” አልኩት።

“እንዴት?”

“እዚህ ቤት ከሚመጡት ወንዶች ሁሉ ከእያንዳንዳቸው ጋር ቢመዛዘን፣ የብርሃኑ ወንድነት እጥፍ ወይም አስር እጅ ነው”

“ኤድ !” አለኝ።

‘የማነህ ቀርፋፋ?!’ እንደማለት ያህል “ድ” ላይ ድምፁን ጫን ብሎ ጎተተው። ሌሎቹ ደስ ብሏቸው ዝም ብለው ያዳምጣሉ። ጥላሁን መጨረሻ ላይ እንደሚቆጣኝ ያውቃሉ።

“አስብ እንግዲህ” አልኩት … “ከብርሃኑ ሌላ ማን ወንድ ነው ደፍሮ ሸርሙጣ ይዞ ፒያሳ መሀል የሚንሸራሸር? ማነው በየቡና ቤቱ ይዟት የሚገባ? ሌሎቻችን እንዲያው እዚህ ስንሆን ቂጣቸውን እየላስን፣ ውጪ ስናገኛቸው እንደማናውቃቸው እናልፋቸዋለን። ማን ነው ሸርሙጣ ወዳጁ ስትታመም ራሱ በቀን ውቤ በረሀ መጥቶ ሀኪም ቤት የሚወስዳት? ገንዘብ መክፈሉንስ ምናልባት የሚከፍል አይጠፋም እንበል። ማነው በየቀኑ እየሄደ አብሯት የሚውል? ማነው የአስታማሚ ፈቃድ አስወጥቶ አልጋዋ አጠገብ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ የሚያድር?”

“ከብርሃኑ ሌላ ማን ጎበዝ ነው ፓርቲ በተደረገ ቁጥር ያችኑ ሸርሙጣ ይዞ ሄዶ ልክ እንደ ልጃገረድ የሚያከብራት? ደሞ ‘ይህን የሚያደርገው ትርሲት ልዩ ስለሆነች ነው፤ በየሄደችበት እንደ ሸርሙጣ ሳይሆን እንደ ጨዋ ሴት ስለምትሆንለት ነው’ እንዳትለኝ፣ እንደ ሸርሙጣ መሆን ትታ እንደ ሴት ወይዘሮ የምትሆንበት ምክንያት ብርሃኑ ሸርሙጣነቷን ስለሚያስረሳት ነው። ሽርሙጥናን እንደ እድፍ ወይም እንደ ብረት ልብስ ብንቆጥረው፣ ካንዲት ሸርሙጣ ላይ እድፏን ለማጠብ ወይም የብረት ልብሱን ቀድዶ ለመጣል ምን ያህል ወንድነት የሚጠይቅ ይመስልሃል? ታውቃለህ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተኛት ገንዘብ አልከፈላትም። እስካሁንም ቢሆን ሊተኛት ሲል ወይም ከተኛት በኋላ ገንዘብ ሰጥቷት አያውቅም።”

ጥላሁን “ኧረ ባክህን?” አለኝ። አሁን ክርክራችንን ረስቷል። የትርሲትና የብርሃኑ ነገር ደግ ቅን ልቡን ነክቶታል።

“በፍጹም ከፍሏት አያውቅም” አልኩት … “ልብስ ሲያስፈልጋት – ሲያምራት ማለቴ – የጨርቁንና የሰፊውን ዋጋ ትነግረዋለች። ይሰጣታል። አስተውል፣ የፍቅር ስጦታ ነው እንጂ የእምስ ዋጋ አይደለም። አንዳንዴ ለምን እንደሚጨቃጨቁ ልንገርህ? እሱ ገንዘብ ሲሰጣት እሷ አልፈልግም ስለምትለው ነው። ወይም ትንሽ ወስዳ ከዛ በላይ አያስፈልገኝም ስትለው። ለምሳሌ ለፀጉር መሠሪያ ስትጠይቀው አስር ብር ነው ‘ሚሰጣት። እሷ አምስት ብር ይበቃኛል ትለዋለች። ወረፋ ስትጠብቂ ኬክና ጀላቲ ያስፈልግሻል ይላታል። እንግድያው ስድስት ብር ይበቃኛል ትለዋለች። እንግዲህ አትጨቅጭቂኝ ይልና አስቱን ብር በግድ ይሰጣታል።

ትርሲትና ብርሃኑ ዳንሳቸውን አብቅተው አንድ ሶፋ ላይ ተቃቅፈው ቁጭ ብለው እየተሳሳቁ ያወራሉ። ጥላሁን እንደ እናት ደስታና ፍቅር በሞላው ገጽ ይመለከታቸዋል። እኔ ዝም ስል ጊዜ ክርክራችንን አስታወሰና፣

“መጀመሪያ’ኮ ወንድነት አላልክም ጉልበት ነው ያልከው” አለኝ።

“ጉልበትስ ቢሆን ጥላሁን? እንደዚህ ተመልከተው እስቲ? አሁን አንድ ጉልበተኛ ጠብዚራ መጥቶ በጥፊ ብሎት ትርሲትን ቢቀማው አንተ ዝም ብለህ ታያለህ?” አልኩት።

ሱሪውን በሁለት ክንዶቹ ከፍ እያደረገና የወይራ መፋቂያውን አፉ ውስጥ ከግራ ወደ ቀኝ እያዛወረ “አይሆንም!” አለ። ለጠብ ሲዘጋጅ ነው። በሳቃችን መሀል፣

“ይኸውልህ፣ ብርሃኑ የራሱ ጉልበትና ያንተ ጉልበት አንድ ላይ አለው ማለት ነው። የሌሎችም” አልኩት።

“እኔ ምልክ፣ የነዚህ ልጆች ፍቅር እውነተኛ ፍቅር ነው በለኛ” አለ።

“እንዲህ አይምሰልህ!” አልኩና ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን አጫወትኩት።

አንድ ሰኞ ማታ ወደ ሁለት ሰዓት ላይ ወንዶች ገና መምጣት ስላልጀመሩ ቤቱ ባዳውን ነበር። ብርሃኑ እዚያ ጥግ ሶፋ ላይ ብቻውን ቁጭ ብሎ ሲጋራ ያጨሳል። እዚህ ጋ ትርሲት፣ ከበቡሽ፣ አስቴር፣ ሦስቱ ካንድ ሰውዬ ጋር ቁጭ ብለው ስለ በረሀ ፍቅር ያወራሉ። (ሌላ ማንም ሰው የለም፣ ሌሎቹ ሴቶች እውስጥ እራታቸውን ይበላሉ) በወሬያቸው መሀል፣ ሰውዬው አንገቱን ወደ ብርሃኑ በኩል ጣል እያደረገ፣

“ያ ክልስ ከማንኛችሁ ጋር ነው ፍቅር የያዘው? በመጣሁ ቁጥር …” ዐረፍተ ነገሩን ሳይጨርስ አፉን እንደከፈተ ቀረ። ትርሲት የቢራ ጠርሙስ ይዛ ከላዩ ቆማ እንደ ቁጣ አምላክ ትገላምጠዋለች።

“ያንቺ ነው እምዬ?” አላት ደንግጦ።

ስትናደድ ዓይኗ ያስፈራል። ሳትጮህ፣ ግን በቁጣ፣

“አንት የውሻ ክልስ! ውጣ!” አለችው። የጠርሙሱን አንገት የጨበጠው እጇ ይንቀጠቀጣል። ሰውዬው ፈርቶ ብድግ አለ።

ግን ሲነሳ ጊዜ ትንሽ ሆነችበት። እሱ ቀጭ እንዳለ እሷ ወደ ታች ስታፈጥበት ደነገጠ እንጂ፣ አሁን እሱ ከላይ ሆኖ ወደ ታች ሲያያት ፍርሀቱ ለቀቀው። ተራውን እየገላመጣት በሚያንቋሽሽ ድምፅ፣

“ምን ሆነሻል? ግም ሸርሙጣ!” አላት።

ደግነቱ ይህን ጊዜ ብርሃኑ ከኋላዋ መጥቶ ያዛት። ዓይን ዓይኗን በቀጥታ እያየ ጠርሙሱን ቀስ አድርጎ ከእጇ ነጥቆ ለከበቡሽ እያቀበለ፣

“ምንድን ነው?” አላት።

“ምንም” አለችው።

ገባው፣ ፊቱ ደም ለበሰ። ለማረጋገጥ ያህል ሰውዬውንና እነ ከበቡሽን እያየ፣

“ምንድን ነው?” አለ።

ከበቡሽ “ኧረ የለም፣ እዚህ እኔና አስቴር …”

“ውሸታም!” አላት ለመሳቅ እየሞከረ።

ወደ ነጭነት የሚያደላ ፊቱ አሁን ሳምባ መስሏል። ሰውዬውን፣

“ክልስ አልከኝ መሰለኝ” አለው።

ሰውዬው ግዙፍ፣ ኩሩ ቢጤ ነው። ብርሃኑን በንቀት እያየ፣

“ኧ … በእውነቱ ወንድም”

“ወንድምህ አይደለሁም። ክልስ ብለኸኛል?”

“ብልህስ?”

“ትችላለህ። ግን እሷን ግም ሸርሙጣ ስትላት የሰማሁህ መሰለኝ”

“ብላትስ?”

“አትችልም። እሷን እንዳንተ ያለ ግም አቃጣሪ አይሰድባትም”

አስቴር “ብርሃኑ” ብላ ልትይዘው ስትል መነጨቀና ወደዚያ ገፋት። ክበቡሽ ደንግጣ አፈገፈገች። ትርሲት እንደቆመች ቀረች። ሌሎቹ ሴቶች እውስጥ እራታቸውን ይበላሉ። ማንም ሌላ ሰው የለም። ሙዚቃው ይዘፍናል።

ሰውየው “ንፍጣም ክልስ! ሴቶቹ ያግዙልኛል ብለህ ነው መቼስ እንዲህ ሰው እምትደፍረው” አለው።

ብርሃኑ “ለምን ሴቶች የሌሉበት አንሄድም?” አለው።

“ማን ቀድሞ ይውጣ?” አለ ሰውዬው።

“እኔ”

“ሽንታም ክልስ! ልትፈተለኪ ፈልገሽ ነው?”

“እሺ አንተ ቀድመህ ውጣ”

“ቅዘናም ነጭ! በጓሮ ልትሸሺ! እግሬ አውጪኝ ልትይ? መች አጣንሽ?”

“ኦ-ዎህ! እሺ አብረን እንውጣ”

“ሴቶቹ አይፈቅዱልሽማ!”

ብርሃኑ ቃል ሳይጨምር ወደ በሩ ሄደና መጋረጃውን ከፍቶ ጠበቀው። አብረው ወጡ። ብርሃኑ እዚችው አጥር ግቢ ውስጥ ያለችውን ትንሽ ሜዳ እያሳየ፣

“እዚህ ትፈልጋለህ?” አለው።

“ሴቶቹ መጥተው እንዲያግዙልሽ ነው?”

ካጥር ግቢው ወጡና ባቡር መንገድ ሲደርሱ ብርሃኑ፣

“እዚህስ?” አለው።

“ገላጋይ አይጠፋም። ወይ የማሚት እሹሩሩ ዘበኞች ተልከው ይመጡና ያግዙልሻል”

ብርሃኑ ተበሳጨ። ሊያለቅስ ምንም አልቀረው።

“ታዲያ የት እንሂድ?”

“እንጃልህ!” አለው ሰውዬው።

“ጊዮርጊስ ጓሮ እንሂድ?”

“እሺ ምን ከፋኝ?”

ወደ ጊዮርጊስ በኩል ትንሽ እንደተራመዱ ሰውየው ቆመ፣

“አህ! ገባኝ ለካ! …” አለ።

“ምኑ?” አለ ብርሃኑ።

“ጊዮርጊስ ጓሮ ወስደህ በማጅራት መቺ ልታስመታኝ አቅደህ ነው። እኔ ግን እንደዚህ በቀላሉ አልታለልም። መልአኩ ይጠብቀኛላ!”

ብርሃኑ ስልችት አለው።

“እንዲዋጣልን ትፈልጋለህ ወይስ አትፈልግም?” አለው።

“አልፈልግም”

ብርሃኑ በመገረም፣

“ለምን?” አለ።

“ንጹሕ አየር ሲመታኝ ጊዜ ሴጣኔ አለፈልኝ”

ብርሃኑ ዝም አለ።

“ሴጣናም ነኝ ልንገርህ። ሴጣኔ ሲመጣ የሚመልሰኝ የለም። አምስት ስድስቱን ከመሬት ጋር ደባልቄ ቤቴ የምገባበት ጊዜ አለ። ታዲያ ሴጣኔ ሲያልፍልኝ የሠራሁት ሥራ ይቆጨኛል። የገዛ ሀገሬን ልጆች፣ የገዛ ወንድሞቼን መደብደቤ ኃይለኛ ፀፀት ያሳድርብኛል። አንተ ግን እድለኛ ነህ። ሴጣኔ ቶሎ ለቀቀኝ”

“ሴጣንህ ክልስ ሲያይ ይፈራል እ?”

“ይቅርታ አድርግልኝ ወንድሜ። በውነቱ ለክፉ ያልኩት አልነበረም”

ብርሃኑ ይሄ ሰውዬ ሌሎችንም ክልሶች እንደሚያስቸግር ታየው። ስለዚህ እንደ አብዛኞቹ ጉረኞች ፈሪ መሆኑን አውቆ እንዲህ አለው።

“ሰማህ ወንድም፣ ለወደፊቱ ክልሶችን ለማጥቃት ባትሞክር ይሻልሃል። ምክንያቱም የምታየው ክልስ ሁሉ (ከኔ ጭምር) ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ እንዳንተ ያሉ ደደቦች ‘ክልስ! አህያ መልስ! እየበዳህ አልቅስ!’ እያሉ ሲያበሳጩት እየተደባደበ ያደገ ስለሆነ ጥል እንጀራው ነው። ሩቅ ሳንሄድ እኔን ተመልከት። ብትፈልግ እንወራረድና፣ አልቢትሮ ጠርተን፣ እንዳንተ ያሉ ሌሎች ሁለት ጨምረህ፣ ሦስታችሁ ለብቻዬ ኑልኝ። አፈር አስገባችኋለሁ። አስተውል፣ ጉልበት ስላለኝ አይደለም። ክልስ በመሆኔ መደባደብ በግዴታ ስለተማርኩ ነው። ገባህ? በል አሁን እንመለስና ልጅቷን ይቅርታ ለምናት”

“ኧ … ሰማህ ወንድም፣ ምንስ ቢሆን …”

“ወይም ይዋጣልን”

“ምንስ ብሳሳት፣ ራሴው በድዬ ሰው አስቀይሜ ይቅርታ ሳልጠይቅ የምሄድ ሰው እመስላለሁ እንዴ?”

ከዚያ ተመለሱና ሰውዬው ትርሲትን ይቅርታ አድርጊልኝ ብሎ ቢራ ጋበዛት። ብርሃኑም ቢራ ጋብዞት፣ ሲያወራላቸው አምሽቶ ሄደ እልሃለሁ። ከዚያ ማታ ወዲህ እዚህ በመጣ ቁጥር ትርሲትን ጠርቶ “እሳተ ጎመራይቱ! ዛሬ ምን ልጋብዝሽ?” ብሎ አንድ ቢራ ሳይጋብዛት አይሄድም።

ያን ዕለት ማታ ጥላሁን ማሚት እሹሩሩን አስፈቅዶ ወይም አስገድዶ ትርሲትንና ብርሃኑን ቀ.ኃ.ሥ ቲያትር ናይት ክለብ ወሰዳቸው። እና ብርሃኑ “ከትርሲት ጋር ደንስ” አለው።

“የለም፣ እናንተ ስትደንሱ ደስ ይለኛል። የሚዋደዱ ሰዎች ሳይ፣ እንደ’ናንተ ያለ እውነተኛ ፍቅር ሳይ ልቤ በደስታ ይሞታል – ይመታል ማለቴ” አለና የሁለቱንም እጅ ይዞ ሳመ። ሰክሯል … “ደስ ትሉኛላችሁ” አለ።

ትርሲት “ደስ ካልንህ ከኛ ጋር ለምን አትደንስም?” አልችና አስነሳችው። ሲደንስ ጠጋ አደረጋት። ሲቆምበት ተሰማት። አፈረች። እሱም አፈረ። የበለጠውን እያስጠጋት፣

“ትርሲትዬ ይቅርታ አድርጊልኝ” አላት … “ሰክሬያለሁ። ፀጉርሽ ብቻ ሳይሆን ጸባይሽም ጭምር ደስ ይለኛል። ስለዚህ ይቅርታ ካላረግሽልኝ ኩነኔ እገባለሁ። አንቺ ጥሩ ልጅ ነሽ። እኔ ግን ውሻ ነኝ። ከሰከርኩ ከእህቴም ጋር ብደንስ ይቆምብኛል። ብቻ እህት የለኝም። እህቴ አንቺ ነሽ። ግን ልቤ ንጹሕ ነው። ቁላዬ ያልተቆነጠጠ ባለጌ ሆኖ ነው’ንጂ፣ እኔስ እንደ እህቴ ነው የማይሽ። ተቀየምሽኝ?”

“የለም”

“ጥሩ ልጅ ነሽ። እኔ’ኮ ‘ሚቆምብኝ የድሮው ትዝ እያለኝ ነው። አደራ ለብርሃኑ እንዳትነግሪው”

“አልነግረውም”

ከናይት ክለቡ ሲወጡ በጣም ሰክሮ ስለነበረ፣ ከተማውን እንዳይረብሽና እሱም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በማለት ከኛ ጋር እደር አሉት።

“ከናንተ ጋር ባድር ደስ ይለኛል። ከናንተ ጋር ባድር ኩራት ይሰማኛል። ከናንተ ጋር ባድር ከፍቅር ጋር እንዳደርኩ እቆጥረዋለሁ። ከናንተ ጋር ባድር ከናንተ ከወጣቶቹ ጋር አድራለሁ። ከናንተ ጋር ባድር …” አላቸው።

ቤት ሲደርሱ መሀላቸው ደግፈውት አንገታቸውን አቅፎ ተራ በተራ ጉንጫቸውን እየሳመ፣

“በጣም በጣም ነው እምወዳችሁ፣ እዚች ዓለም ላይ እንደ’ናንተ እምወደው የለም። መፋቂያዬስ?” እያለ ወደ ቤት ገቡ።

ትርሲትን መሀል አርገዋት ተኙ።

ሩብ ሰዓት ካለፈ በኋላ ብርሃኑ ቀስ ብሎ “ጥላሁን” አለ። መልስ የለም። ጥላሁን ተኝቷል ማለት ነው። ቀስ ብለው መተቃቀፍና መተሻሸት ጀመሩ።

“ትርሲትዬ!”

“ወዬ የኔ ብርሃን!”

“ሻሽሽን አውልቂልኝ”

“እምቢዮ!”

“እባክሽን!”

“ቆንጆ አርገህ ሳመኝና” ሲባባሉ …

“ቃ!” አለና ድንገት መብራቱ በራ። ጥላሁን ማብሪያውን እንደ ቀይ ሲጋራ በጣቶቹ መሀል ይዞ፣ ደም የለበሱ ጉልህ ዓይኖቹን ክፍት ክድን እያደረገ …

“እኔ ምላችሁ” አለ “እንደዚህ ሆናችሁ ፍቅራችሁን ስትገላለጹ ቁላችሁና እምሳችሁ የቱ የማን እንደሆነ ይታወቃችኋል?” መኖሩን ረስተው ስለነበር ከመደንገጣቸው የተነሳ እንደተቃቀፉ ትንፋሻቸውን እንደዋጡ ቀሩ።

“ማለቴ፣ ከመዋደዳችሁ የተነሳ ቁላው የማንኛችሁ እምሱስ የማንኛችሁ እንደሆነ አይጠፋችሁም ወይ?”

“ምን ማለትህ ነው?” አለ ብርሃኑ

“አየህ ብርሃኑ፣ እንደዚህ ነው። እኔ ፍቅር ፍለጋ ላይ ነው ያለሁት። የፍቅር አዳኝ ይሉሃል ማን ነው? ጥልዬ ነው። ሌላ መልስ የለውም። ፍቅር ማለት እንግዲህ ምንድን ነው? አንድ መሆን ነው። አንድ ታውቅ የለ? ሁለት መሆን ቀርቶ አንድ ትሆናላችሁ። አንድ። የምትተቃቀፉት ለዚህ ነው። አንድ ስትሆኑ እንግዲህ ቁላውም የሁለታችሁ ነው፣ እምሱም የሁለታችሁ ነው። ገባህ?”

ብርሃኑ ዝም ሲል ጊዜ …

“እኔ ‘ምፈልገው ፍቅር ነው። ፍቅር። አስናቀችን ስበዳት በጣም ጣፍጧት በኀይል ስታቅፈኝ፣ ‘ምንድነው ሚገባብሽ?’ ስላት ‘መርዘኛው ቁላህ ነዋ ጥልዬ!’ ትለኛለች። እበሽቃለሁ። እኔ የምፈልገው ‘ቁላችን ነዋ!’ እንድትለኝ ነበር። ‘ይሄ እምስ የማን ነው?’ ስላት ‘ያንተ ነዋ!’ ትለኛለች … ‘የኛ ነዋ!’ እንደማለት። ገባህ? ዳሩ ምን ይገባሃል? ቁላ ሲነሳ አንጎል ይተኛል።”

“ትርሲትዬ፣ ይቅርታ አርጊልኝ ስላቋረጥኳችሁ” አለ።

ቀጥሎ፣

“መፋቂያዬን ጣልኳት ወይስ አስቀመጥኳት? ያለ ‘ሷ ምን ዘመድ አለኝ?” አለና መብራቱን አጥፍቶ ተኛ …

.

ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

(1960ዎቹ)

.

[ምንጭ]“ሌቱም አይነጋልኝ” [እንደወረደ]። ፲፱፻፺፰ ዓ.ም። ገጽ 48-56።

 

“ባንዶቹ” (ራስ ባንድ)

“ባንዶቹ”

(ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቡድኖች)

.

በሳይም ኦስማን

.

(ራስ ባንድ)

.

ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ‘ወርቃማ ዘመን’ ስናወራ እነዚያን መሳጭ ሙዚቃዎች ከዘፋኞች ኋላ ሆነው ስላቀነባበሩት ስለ ባንዶቹ ሳናነሳ አናልፍም።  በዚህ ጽሑፍ (እና በቀጣዮቹ ክፍሎች) የዋና ዋናዎቹን ዘመናዊ ባንዶች ታሪክ እና ባንዶቹን ስላቋቋሙት ሙዚቀኞች አጠር አድርጌ አቀርባለሁ።

በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በጣም ተወዳጅ የነበሩት የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ፣ የፖሊስ ባንድ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ኦርኬስትራ፣ እና የምድር ጦር ኦርኬስትራ ነበሩ። በ1953 ዓ.ም የታህሳሱ ግርግር የኃይለሥላሴን መንግስት ለመገልበጥ የተሞከረበት ጊዜ፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሁለተኛ ምዕራፍን ከፈተ። በዚህም ወቅት የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራ ለበርካታ ወራት ለመበተን በቃ። ብዙዎቹ አባላቶቹም ከኦኬስትራው እየለቀቁ ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖችን (ፖሊስ፣ ምድር ጦር እና ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ቴያትር) መቀላቀል ጀመሩ። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ኦኬስትራዎች ቀስ በቀስ ወደ ብዙ ትናንሽ ባንዶች እየተቀየሩ መጡ።

እነዚህም ትናንሽ ባንዶች መጀመሪያ ስራ የጀመሩት በተለያዩ የአዲስ አበባ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ነበር። ለዚህም ይመስላል የባንድ ስማቸውን በሆቴሎቹ ስም ያደረጉት … እንደ “ራስ ባንድ”፣ “ግዮን ባንድ”፣ “ሸበሌ ባንድ” የመሳሰሉት። ብዙም ሳይቆይ ሆቴሎቹ በጣም ታዋቂ መዝናኛ ቦታዎች እየሆኑ መጡ። በተለይም አርብ ማታ እነዚህን የሙዚቃ ድግሶች ለመታደም የማይቀርበት ቦታ ሆኑ።

ras hotel 1950s
ራስ ሆቴል በ1950ዎቹ መባቻ።

.

ራስ ባንድ

.

የመጀመሪያው ራስ ባንድ የተቋቋመው በ1953 ዓ. ም ነበር። ባንዱንም የመሠረቱት ተፈራ መኮንን (ፒያኖ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክስፎን)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ባህታ ገብረሕይወት (አማርኛና ትግርኛ ድምፃዊ)፣ ግርማ በየነ (እንግሊዘኛ ድምፃዊ) እና ገብረአብ ተፈሪ (አስተናባሪና ገጣሚ) በመሆን ነበር። በዛሬ ዘመን በሕይወት በመሀከላችን የሚገኙት ጌታቸው ወልደሥላሴ፣ ባህታ ገብረሕይወት እና ግርማ በየነ ናቸው።

Ras Band 3
ራስ ባንድ በራስ ሆቴል (1953-1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 1|

የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ ናቸው። እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስም ሶስቱ አባላት የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ተምረው ነበር። በክቡር ዘበኛ ኦሮኬስትራ ውስጥ ተፈራ መኰንን ቤዝ ሲጫወት ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ ደግሞ ድራም ተጫዋቾች ነበሩ። በ1953 ዓ.ም አጋማሽም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲበተን ተጨማሪ ሙዚቀኞችን (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) እና ሁለት ድምፃውያንን ይዘው ወደ ራስ ሆቴል አመሩ።

“አርብ ማታ በራስ ሆቴል የሚያስደስት ጊዜ ነበር” ይላል ባህታ ገብረሕይወት – Addis Live ራዲዮ ኢንተርቪው ላይ፣ ባህታ የሆቴሉን ድባብ ሲያስታውስ ሁሉም የባንዱ አባላት በሚገባ ዘንጠው መገኘት ነበረባቸው። እያንዳንዱም የሆቴል ተጠቃሚ አለባበሱን አስተካክሎ መገኘት የሆቴሉ ህግ ነበር። በሚገባ አለባበሱ አልተስተካከለም ብለው ለሚያስቡት ተጠቃሚ ክራቫት ይሰጠው ነበር። ብቻቸውን የሚመጡ ተስተናጋጆች እምብዛም ናቸው። ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኖ ይደንስ ነበር።

Ras Band
ራስ ባንድ በአክሱም አዳራሽ መክፈቻ በዓል (ታኅሣስ 4፣ 1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ባህታ ገብረሕይወት (ድምፅ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 2|

ራስ ባንድ ውስጥ እያለ ነበር ባህታ ብዙዎቹን ስራዎቹን ያበረከተልን። እነ “አንቺም እንደ ሌላ”፣ “ደግሞ እንደምን አለሽ”/“ካላጣሽው አካል”፣ “ስቃይ ዝክኣል’ዩ”፣ “የጥላቻ ወሬ”፣ “ያ ያ” እና “ወደ ሀረር ጉዞ” የመሳሰሉትን።

[“ካላጣሽው አካል”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

ባህታ የትግርኛ ዘፈኖቹን ግጥም የጻፈው እራሱ ሲሆን፣ ብዙዎቹን የአማርኛ ዘፈኖች ግጥም ደግሞ ገብረአብ ተፈሪ ነበር የሚጽፋቸው። ሙዚቃዎቹን የሚጽፈውና የሚያቀናብረው ፒያኖ ተጫዋቹ ተፈራ መኰንን ነበር። ባህታም በዚህ ዘመን ከጻፋቸው ሙዚቃዎች ዜማ አንዱ እና ግርማ በየነን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ታዋቂ ያደረገው ዘፈን ‘ይበቃኛል’ የተሰኘው ነበር።

AE690c Bahta

በዚሁ ራስ ባንድ በሚሰራበት ጊዜም ነበር ባህታ በትርፍ ጊዜው ተምሮ አካውንቲንግ ያጠናው። በ1964 ዓ.ም ከሙዚቃ ዓለም ሲርቅ ለግዮን ሆቴል እና ለፊልም ኮርፖሬሽን የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ባህታ እንደሚለው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አካሄድ አላምር ብሎት ነበር ከሙዚቃ አለም የራቀው። በታህሳስ 1996 ዓ.ም ከብዙ አመታት በኋላ ባህታ ገብረሕይወት ‘አንቺም እንደሌላ’ን Either Orchestra ከሚባል ቦስተን ከሚገኝ የጃዝ ቡድን ጋር አቅርቦ ነበር።

[“አንቺም እንደሌላ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን/ራስ ባንድ)። 1957-1960 ዓ.ም።]

የመጀመሪያው የራስ ባንድ የተመሰረተው ከ1953 ዓ.ም ነበር። ታዲያ በ1956 ዓ.ም አጋማሽ ሁለቱ የባንዱ አባላት (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) በሌሎች ሙዚቀኛች የተተኩ ይመስላል። ወዳጄነህ ፍልፍሉ ከዚህ ወቅት ጀምሮ ሳክሰፎን በመያዝ፣ አሰፋ ባይሳ ደግሞ ትራምፔት በመጫወት ራስ ባንድን ተቀላቀሉ። በሐምሌ 1956 ዓ.ም አካባቢም እንግሊዘኛ ድምፃዊው ግርማ በየነ ራስ ባንድን ለቀቀ። ብዙም ሳይቆይ በ1957 ዓ.ም የባንዱ አባላት ከራስ ሆቴል ወጥተው በግዮን ሆቴል ለተወሰኑ ዓመታት “ግዮን ባንድ” ተሰኝተው ተጫውተዋል።

Ras Band 2
ራስ ባንድ በነሐሴ 1956 ዓ.ም። [ከግራ ወደ ቀኝ] ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ አሰፋ ባይሳ (ትራምፔት)፣ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባሕታ ገብረሕይወት (ድምፃዊ)፣ እና ወዳጄነህ ፍልፍሉ (ሳክሰፎን)። |ምስል 3|

በድምፃዊነት እና በፐርከሽን ከሦስት ዓመት በላይ “ራስ ባንድ” ከተጫወተ በኋላ ግን ወጣቱ ግርማ በየነ በተራው የራሱን ባንድ ለማቋቋም ወሰነ።

Girma Beyene (old)
ግርማ በየነ በ1956 ዓ.ም መገባደጃ። |ምስል 4|

.

.

(ይቀጥላል)

.

ሳይም ኦስማን

.

[ትርጉም] – ሕይወት ከተማ

.

[ምንጭ] – Sayem Osman. (Ethio Jazz). “Bandochu.” 2006. Bernos.com

ትምክሕት ተፈራ መኰንን። የግል ምስሎች ስብስብ። [ምስል 1]

 “የአዲስ አበባ ትዝታ”። vintageaddis.com [ምስል 2]

ሰለሞን ተሰማ። “አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው።” የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1957 ዓ.ም። [ምስል 3፣ 4]

Peter Roth. “Modern Ethiopian Music Discographies”. http://www.funkfidelity.de

Francis Falceto. “Abyssinie Swing – Pictorial History of Modern Ethiopian Music.” 2001.

.

.

ተጨማሪ

የራስ ባንድ ሥራዎች

.

[“ወደ ሐረር ጉዞ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

[“ወደ ሐረር ጉዞ – 2”። ባሕታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ። 1957-1960 ዓ.ም።]