“ባንዶቹ”
(ሁለተኛው ራስ ባንድ)
.
በሳይም ኦስማን
.
.
.
ግርማ በየነ በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዛው በካቴድራል ት/ቤት በሚከታተልበት ወቅት ነበር የሙዚቃ ፍቅር ሥር የሰደደበት። ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ለጊዜው ተቀጥሮ በመድረክ በድምፃዊነት መቅረብ ጀመረ። የማዜም እና የመዝፈን ፍቅሩም ሲብስበት በ1953 ዓ.ም ትምህርቱን ከልዑል መኰንን ት/ቤት አቋርጦ ከታኅሣስ ግርግር በኋላ የተመሰረተውን “ራስ ባንድ” በምዕራባዊ ዘፈን አቀንቃኝነት ተወዳድሮ ተቀላቀለ።
ግርማ በራስ ባንድ ቆይታው ከእንግሊዝኛ ዘፈን አቀንቃኝቱ ባሻገር የሙዚቃ መሳሪያ ችሎታውን አዳበረ። በፐርከሽን መሳሪያዎች (ማራካስ እና ድራምስ) ጀምሮም ቀስ በቀስ ፒያኖ የመጫወት ልምድ አካበተ። ከሦስት አመት ተኩል ቆይታ በኋላም በሐምሌ 1956 ዓ.ም ራስ ባንድን በራሱ ፈቃድ ለመልቀቅ ወሰነ።
ግርማ ለተወሰኑ ወራት በተለያዩ የአዲስ አበባ ምሽት ክበቦች (እነ La Mascotte እና Domino Club) ከግርማ ዘማርያም (ድራምስ) ጋር ፒያኖ እየተጫወተ መዝፈኑን ተያያዘው። በሁለቱ ግርማዎች የተቋቋመውን ባንድ “The Girmas” በመባል ይጠራ ነበር።
[“ትወጅኝ እንደው”። ግርማ በየነ እና ግርማ ዘማርያም። (ዜማ/ግጥም) ግርማ በየነ። The Girmas። 1957 ዓ.ም።]
.
ይህም ባንድ ቁጥሩን በርከት በማድረግ ጌታቸው ደገፉ (ኦርጋን)፣ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክስ) እና ፈለቀ ነጋሽን (ትራምፔት) ወደ ቡድኑ ጨመረ። በጊዜው ከተጫወቷቸው ዜማዎች መሀከልም “ትወጅኝ እንደው”/“ቁርጡን ንገሪኝ”፣ “ጥሩልኝ ቶሎ”/“ፍፁም ፍፁም” እና “ሮኬት ቢሰራ”/“እቅጩን ንገሪኝ” ይጠቀሳሉ።
[“ሮኬት ቢሰራ”። ግርማ በየነ። (ዜማ) Sam Cooke። The Girmas/ራስ ባንድ። 1957 ዓ.ም።]
.
ከጥቂት ጊዜም በኋላ የቀድሞው “ራስ ባንድ” ወደ ግዮን ሆቴል በ1957 ዓ.ም ሲዛወር ግርማ በየነ በተራው ሁለተኛውን “ራስ ባንድ“ በዚያው በራስ ሆቴል አቋቋመ። ይህም ባንድ ለአምስት ዓመታት ያህል በርካታ ሥራዎችን በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ሲያቀርብ ቆየ። በዚህኛውም ራስ ባንድ ውስጥ የነበሩት ግርማ በየነ (ፒያኖ እና እንግሊዘኛ ዘፈን)፣ ግርማ ዘማርያም (ድራምስ)፣ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክሰፎን)፣ ፈለቀ ነጋሽ (ትራምፔት) እንዲሁም ሁለቱ ድምፃውያን ምኒልክ ወስናቸው እና ሰይፉ ዮሐንስ ነበሩ።

ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ ከቅፅል ስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሰውነቱ ግዙፍ ነበረ። ኃይሉ በግሩም ቤዝ ተጫዋችነቱ ከራስ ባንድ አባልነቱ ባሻገር በ1960ዎቹ ከግርማ በየነ ጋር በAll-Stars Band እና ዓለም-ግርማ ባንዶች ውስጥ አባል ሆኖ ነበር። ለተወሰነ ጊዜም በዝነኛው Soul Ekos ባንድ ተጫውቷል። ከአብዮቱ በኋላም በሀገር ፍቅር ማህበር በሙዚቀኝነት አገልግሏል።
ተስፋማርያም ኪዳኔ ተወልዶ ያደገው ኤርትራ ውስጥ ነው። ተስፋማርያም ሳክሰፎን መጫወት የጀመረው ከአሥመራ ፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ነበር። ሁለተኛው ራስ ባንድን ከተቀላቀለም በኋላም ከግርማ በየነ እና ኃይሉ ከበደ ጋር በመሆን All-Star ባንድ ውስጥ አብሮ ተጫውቷል።
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ምኒልክ ወስናቸው የሙዚቃ ጅማሬው በ1951 ዓ.ም በተቀጠረበት ዝነኛው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር ኦርኬስትራ ነበር። በዛም ብዙ ምርጥ ዘፈኖችን ዘፍኖ ነበር – እነ “ፍቅር በአስተርጓሚ”፣ “ፍቅር አያረጅም”፣ “ስኳር ስኳር” እና የመሳሰሉትን። ምኒልክ ራስ ባንድን በ1957 ዓ.ም ከተቀላቀለ በኋላም “ውብ ናት” እና ሌሎችን ግሩም ዘፈኖች ተጫውቶ ነበር። “ውብ ናት” ላይ በአጃቢነት የሚቀበለው ግርማ በየነ ነው።
[“ውብ ናት”። ምኒልክ ወስናቸው። (ዜማ) ምኒልክ ወስናቸው (ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]
.
ወጣቱ ሰይፉ ዮሐንስም ከሁለተኛው ራስ ባንድ ጋር ለበርካታ ዓመታት ተጫውቶ ነበር። በዚህ ዘመን በጣም ከታወቁለት ሥራዎቹ መካከልም “ጽጌረዳ”፣ “ቆንጅትዬ”፣ “ሃና”፣ እና “መለወጥሽ ምነው” ናቸው። የሰይፉም ታላቅ እህት ተወዳጅዋ ዘፋኝ ራሔል ዮሐንስ ናት። ለሬድዮ ፋና አንድ ጊዜ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ አባታቸው በሰይፉ ዘፋኝነት እጅግ ይበሳጭ እንደነበረና ልጄ አይደለህም ብሎ እስከመካድ ደርሶ በሽማግሌዎች ልመና ይቅርታ እንዳደረገለት ተናግራ ነበር።
ሰይፉ “ጽጌሬዳ”፣ “ቆንጅትዬ” እና “መለወጥሽ ምነው” የተሰኙትን የተጫወተው ሁለተኛው ራስ ባንድ ጋር ሳለ ሲሆን ድርሰቶቹን የጻፈውና ያቀናበረው ግርማ በየነ ነበር። ሰይፉ ከራስ ባንድ ቆይታውም በኋላ በየምሽት ክበቦቹ (ዙላ፣ ቬኑስ) በመጫወት ዝነኛው ሶውል ኤኮስ (Soul Ekos) ባንድን ተቀላቀለ።
.
[“ቆንጂትዬ”። ሰይፉ ዮሐንስ። (ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]
[“መለወጥሽ ምነው”። ሰይፉ ዮሐንስ። (ዜማ/ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]
.
ከነዚህ ሙዚቀኞች ባሻገርም፣ በተለይ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከባሕር ማዶ የተመለሰው ወጣቱ ሙላቱ አስታጥቄ ባንዱን ተቀላቅሎ ከራስ ባንድ ጋር በአዲስ አበባ እና ሐረር ራስ ሆቴል መድረኮች ላይ ዛይሎፎን እና ኮንጐ ድራምስ ተጫውቷል።
.

.
በመጨረሻም፣ ዝነኛው ራስ ባንድ በ1961 ዓ.ም (በመበታተኑ ዋዜማ እና መባቻ) በአምኃ እሸቴ “ሐራምቤ ሙዚቃ ቤት“ አሳታሚነት የግርማ በየነ፣ ሙላቱ አስታጥቄ እና ዓለማየሁ እሸቴን ሙዚቃዎች በሸክላ ለማስቀረጽ ችሎ ነበር።
.
[“ያ ታራ!”። ዓለማየሁ እሸቴ። ራስ ባንድ። 1961 ዓ.ም።]
.
[“ይበቃኛል”። ግርማ በየነ። (ግጥም/ዜማ) ባሕታ ገ/ሕይወት። ራስ ባንድ። 1961 ዓ.ም።]
.
.
(ይቀጥላል)
.
ሳይም ኦስማን
.
[ትርጉም] – ፅዮን ዮሐንስ
.
[ምንጭ] – Sayem Osman. (Ethio Jazz). “Bandochu.” 2006. Bernos.com
ሰለሞን ተሰማ። “አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው።” የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1957 ዓ.ም።
“የሙዚቃ መጽሔት”። የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1961 ዓ.ም።
Peter Roth. “Modern Ethiopian Music Discographies”. http://www.funkfidelity.de
Francis Falceto. “Éthiopiques Series Volume 1-30 Liner Notes.” 1998-2017.
.
.
በጣም ጥሩ አድርጋችሁ ዘግባችሁታል ፤
LikeLike
የአ/አ ጆሊዎች ነበሩ።
LikeLike