“ሁለተኛው ራስ ባንድ” (ባንዶቹ)

“ባንዶቹ”

(ሁለተኛው ራስ ባንድ)

.

በሳይም ኦስማን

.

.

(ከክፍል አንድ የቀጠለ)

.

Girma Closeup AE170cግርማ በየነ በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዛው በካቴድራል ት/ቤት በሚከታተልበት ወቅት ነበር የሙዚቃ ፍቅር ሥር የሰደደበት። ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ለጊዜው ተቀጥሮ በመድረክ በድምፃዊነት መቅረብ ጀመረ። የማዜም እና የመዝፈን ፍቅሩም ሲብስበት በ1953 ዓ.ም ትምህርቱን ከልዑል መኰንን ት/ቤት አቋርጦ ከታኅሣስ ግርግር በኋላ የተመሰረተውን “ራስ ባንድ” በምዕራባዊ ዘፈን አቀንቃኝነት ተወዳድሮ ተቀላቀለ።

ግርማ በራስ ባንድ ቆይታው ከእንግሊዝኛ ዘፈን አቀንቃኝቱ ባሻገር የሙዚቃ መሳሪያ ችሎታውን አዳበረ። በፐርከሽን መሳሪያዎች (ማራካስ እና ድራምስ) ጀምሮም ቀስ በቀስ ፒያኖ የመጫወት ልምድ አካበተ። ከሦስት አመት ተኩል ቆይታ በኋላም በሐምሌ 1956 ዓ.ም ራስ ባንድን በራሱ ፈቃድ ለመልቀቅ ወሰነ።

ግርማ ለተወሰኑ ወራት በተለያዩ የአዲስ አበባ ምሽት ክበቦች (እነ La Mascotte እና Domino Club) ከግርማ ዘማርያም (ድራምስ) ጋር ፒያኖ እየተጫወተ መዝፈኑን ተያያዘው። በሁለቱ ግርማዎች የተቋቋመውን ባንድ “The Girmas” በመባል ይጠራ ነበር።

[ትወጅኝ እንደው። ግርማ በየነ  እና ግርማ ዘማርያም። (ዜማ/ግጥም) ግርማ በየነ። The Girmas። 1957 ዓ.ም።]

.

ይህም ባንድ ቁጥሩን በርከት በማድረግ ጌታቸው ደገፉ (ኦርጋን)፣ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክስ) እና ፈለቀ ነጋሽን (ትራምፔት) ወደ ቡድኑ ጨመረ። በጊዜው ከተጫወቷቸው ዜማዎች መሀከልም ትወጅኝ እንደው”/“ቁርጡን ንገሪኝጥሩልኝ ቶሎ”/“ፍፁም ፍፁምእናሮኬት ቢሰራ”/“እቅጩን ንገሪኝ ይጠቀሳሉ።

[ሮኬት ቢሰራ። ግርማ በየነ።  (ዜማ) Sam Cooke። The Girmas/ራስ ባንድ። 1957 ዓ.ም።]

.

ከጥቂት ጊዜም በኋላ የቀድሞው “ራስ ባንድ” ወደ ግዮን ሆቴል በ1957 ዓ.ም ሲዛወር ግርማ በየነ በተራው ሁለተኛውን “ራስ ባንድ“ በዚያው በራስ ሆቴል አቋቋመ። ይህም ባንድ ለአምስት ዓመታት ያህል በርካታ ሥራዎችን በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ሲያቀርብ ቆየ። በዚህኛውም ራስ ባንድ ውስጥ የነበሩት ግርማ በየነ (ፒያኖ እና እንግሊዘኛ ዘፈን)፣ ግርማ ዘማርያም (ድራምስ)፣ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክሰፎን)፣ ፈለቀ ነጋሽ (ትራምፔት) እንዲሁም ሁለቱ ድምፃውያን ምኒልክ ወስናቸው እና ሰይፉ ዮሐንስ ነበሩ።

2nd Ras Band
ሁለተኛው ራስ ባንድ በ1960 ዓ.ም መገባደጃ። [ከግራ ወደ ቀኝ] ግርማ ዘማርያም (ድራምስ)፥ ምኒልክ ወስናቸው (ድምፅ)፥ ግርማ በየነ (ፒያኖ/ድምፅ)፥ ሰይፉ ዮሐንስ (ድምፅ)፥ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ) እና ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክሰፎን)

ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ ከቅፅል ስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሰውነቱ ግዙፍ ነበረ። ኃይሉ በግሩም ቤዝ ተጫዋችነቱ ከራስ ባንድ አባልነቱ ባሻገር በ1960ዎቹ ከግርማ በየነ ጋር በAll-Stars Band እና ዓለም-ግርማ ባንዶች ውስጥ አባል ሆኖ ነበር። ለተወሰነ ጊዜም በዝነኛው Soul Ekos ባንድ ተጫውቷል። ከአብዮቱ በኋላም በሀገር ፍቅር ማህበር በሙዚቀኝነት አገልግሏል።

ተስፋማርያም ኪዳኔ ተወልዶ ያደገው ኤርትራ ውስጥ ነው። ተስፋማርያም ሳክሰፎን መጫወት የጀመረው ከአሥመራ ፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ነበር። ሁለተኛው ራስ ባንድን ከተቀላቀለም በኋላም ከግርማ በየነ እና ኃይሉ ከበደ ጋር በመሆን All-Star ባንድ ውስጥ አብሮ ተጫውቷል።

AE590c

አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ምኒልክ ወስናቸው የሙዚቃ ጅማሬው በ1951 ዓ.ም በተቀጠረበት ዝነኛው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር ኦርኬስትራ ነበር። በዛም ብዙ ምርጥ ዘፈኖችን ዘፍኖ ነበር – እነ “ፍቅር በአስተርጓሚ”፣ “ፍቅር አያረጅም”፣ “ስኳር ስኳር” እና የመሳሰሉትን። ምኒልክ ራስ ባንድን በ1957 ዓ.ም ከተቀላቀለ በኋላም “ውብ ናት” እና ሌሎችን ግሩም ዘፈኖች ተጫውቶ ነበር። ውብ ናት” ላይ በአጃቢነት የሚቀበለው ግርማ በየነ ነው።

[ውብ ናት። ምኒልክ ወስናቸው። (ዜማ) ምኒልክ ወስናቸው (ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]

.

Seifu Venus 1970

ወጣቱ ሰይፉ ዮሐንስም ከሁለተኛው ራስ ባንድ ጋር ለበርካታ ዓመታት ተጫውቶ ነበር። በዚህ ዘመን በጣም ከታወቁለት ሥራዎቹ መካከልም “ጽጌረዳ”፣ “ቆንጅትዬ”፣ “ሃና”፣ እና “መለወጥሽ ምነው” ናቸው። የሰይፉም ታላቅ እህት ተወዳጅዋ ዘፋኝ ራሔል ዮሐንስ ናት። ለሬድዮ ፋና አንድ ጊዜ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ አባታቸው በሰይፉ ዘፋኝነት እጅግ ይበሳጭ እንደነበረና ልጄ አይደለህም ብሎ እስከመካድ ደርሶ በሽማግሌዎች ልመና ይቅርታ እንዳደረገለት ተናግራ ነበር።

ሰይፉ ጽጌሬዳቆንጅትዬእናመለወጥሽ ምነው የተሰኙትን የተጫወተው ሁለተኛው ራስ ባንድ ጋር ሳለ ሲሆን ድርሰቶቹን የጻፈውና ያቀናበረው ግርማ በየነ ነበር። ሰይፉ ከራስ ባንድ ቆይታውም በኋላ በየምሽት ክበቦቹ (ዙላ፣ ቬኑስ) በመጫወት ዝነኛው ሶውል ኤኮስ (Soul Ekos) ባንድን ተቀላቀለ።

.

[ቆንጂትዬ። ሰይፉ ዮሐንስ። (ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]

[መለወጥሽ ምነው። ሰይፉ ዮሐንስ። (ዜማ/ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]

.

ከነዚህ ሙዚቀኞች ባሻገርም፣ በተለይ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከባሕር ማዶ የተመለሰው ወጣቱ ሙላቱ አስታጥቄ ባንዱን ተቀላቅሎ ከራስ ባንድ ጋር በአዲስ አበባ እና ሐረር ራስ ሆቴል መድረኮች ላይ ዛይሎፎን እና ኮንጐ ድራምስ ተጫውቷል።

.

Ras Band 1961
ራስ ባንድ በ1961 ዓ.ም መባቻ። [ከግራ ወደ ቀኝ] ግርማ በየነ (ፒያኖ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክሰፎን)፣ ሙላቱ አስታጥቄ (ዛይሎፎን/ኮንጎ ድራምስ)፣ ኃይሉ ከበደ (ቤዝ ጊታር/ኰንትሮ ባስ)፣ ፈለቀ ኪዳኔ (ትራምፔት)፣ ግርማ ዘማርያም (ጃዝ ድራምስ)

.

በመጨረሻም፣ ዝነኛው ራስ ባንድ በ1961 ዓ.ም (በመበታተኑ ዋዜማ እና መባቻ) በአምኃ እሸቴ “ሐራምቤ ሙዚቃ ቤት“ አሳታሚነት የግርማ በየነ፣ ሙላቱ አስታጥቄ እና ዓለማየሁ እሸቴን ሙዚቃዎች በሸክላ ለማስቀረጽ ችሎ ነበር።

.

AE100c

[ያ ታራ!”። ዓለማየሁ እሸቴ። ራስ ባንድ። 1961 ዓ.ም።]

.

AE160bc

[ይበቃኛል። ግርማ በየነ። (ግጥም/ዜማ) ባሕታ ገ/ሕይወት። ራስ ባንድ። 1961 ዓ.ም።]

.

.

(ይቀጥላል)

.

ሳይም ኦስማን

.

[ትርጉም] – ፅዮን ዮሐንስ

.

[ምንጭ] – Sayem Osman. (Ethio Jazz). “Bandochu.” 2006. Bernos.com

ሰለሞን ተሰማ።አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው።” የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1957 ዓ.ም።

የሙዚቃ መጽሔት። የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1961 ዓ.ም።

Peter Roth. “Modern Ethiopian Music Discographies”http://www.funkfidelity.de

Francis Falceto. “Éthiopiques Series Volume 1-30 Liner Notes.” 1998-2017.

.

.

Ras Band 1968 Poster

“ሙሉቀን መለሰ” (ቃለመጠይቅ)

“ከሻይ ቤት ሀርሞኒካ እስከ ዳህላክ ባንድ”

በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

(1973 ዓ.ም)

.

.

አንዳንድ ዘፈን አለ … ድንገት ደርሶ ድፍን አዲስ አበባን የሚያጥለቀልቅ። በየቡና ቤቱ፣ በየ መጠጥ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ በቴፕ ያሰሙታል። ካሴት ያላቸው ታክሲዎች ውስጥም ሲዘፈን ይሰማል። በመንገድ ጐረምሶች ዜማውን ያፏጩታል። ሴቶች ብቻቸውን ሆነው ልብስ እያጠቡ ወይም ወጥ እየሠሩ ለራሳቸው ይዘፍኑታል። ልጆች መንገድ ሲሄዱ ይዘፍኑታል … አልፎ አልፎ ባንድ እግራቸው ብቻ እየነጠሩ። ገና አፋቸውን የፈቱ ሕፃናትም ይኰላተፉበታል። የመንደር ሰካራሞችም ይንገዳገዱበታል። ባጭሩ፣ የከተማው ዘፈን እሱ ይሆናል።

ከጥቂት ወራት በፊት “ናኑ ናኑ ነይ፣ ናኑ ናኑ ነይ፣ ካንቻለኝ ጉዳይ!” እያለ ሲያስተጋባ ነበር የአዲስ አበባ ሕዝብ … ከሙሉቀን መለሰ ተቀብሎ ነበር የዘፈነው።

.

[“ናኑ ናኑ ነይ”። ሙሉቀን መለሰ። ዳህላክ ባንድ። 1972 ዓ.ም።]

.

አንድ የሥራ ጓደኛዬ እድሜዋ ሶስት ዓመት ተኩል የሆነ ልጅ አለችው። አንድ ቀን፣

“አባዬ! ያቺ ኮ ስሟ ናኑ ነው” አለችው ወደ አንዲት ኰረዳ እያመለከተች።

“ኧረ?” ሲላት፣

“አዎን” አለች፤ “ብትፈልግ ትላንትና ‘ናኑ ናኑ ነይ፣ ካንቻለኝ ጉዳይ’ ስል ጊዜ መጣች!”

ጓደኛዬ ይህን ከነገረኝ በኋላ፣ “ያንን ሙሉቀንን ባወቅኩት እቺን አጫውተው ነበር” አለኝ።

Muluken 1973b

ሙሉቀን መለሰ አጠር ያለ፣ ወፈር ያለ፣ በጣም ቀይ የሆነ የሃያ ስምንት ዓመት ጐረምሳ ነው። ለሁለት ሰዓት ይህል ሲያነጋግረን እንደገመትኩት ሙሉቀን ሀሳቡን በቀጥታ የሚናገር ሰው ነው። ማለቴ፣ “እንዲህ ያልኩ እንደሆነ እንደዚህ ተብሎ ሊተረጐምብኝ ይችላል” የሚል ሥጋት የለበትም።

“ሙሉቀን ብለው ስም ያወጡልህ ለምንድነው?” አልነው።

“እህቴ ነች ያወጣችልኝ። እናቴ ‘ሙሉሰው’ ነው የምትለኝ። ከኔ በፊት አስወርዷት ነበር። ደሞ ታላላቆቼ አራቱም ሲወለዱ ምጥ ይበዛባት ነበር። እኔ ስወለድ ግን ይህ ችግር አልነበረም። ለዚህ ነው ‘ሙሉሰው’ ያለችኝ። ‘ስማቸው’ ይለኛል አባቴ። የመሬት ሙግት ነበረበት። ጠላቶች ነበሩት። እነሱን ስማቸው ማለቱ ነው።”

ሙሉቀን መለሰ በጐጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም ተወለደ። አሥር ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ፣ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አጐቱ እንዲማር ብለው አመጡት። ኰልፌ ሰፈር ጳውሎስ ትምህርት ቤት ገባ። ግን ብዙ አልተማረም። ያጐቱ ሚስት ይጠሉት ስለነበረ ብስጭት በዛበት።

እንግዲህ ኰልፌ አንድ የጡረታ ቤት ነበረ። ባንድ ጐኑ የልጆች ማሳደጊያ ነበረው። የሚረዱ አሉ ሲባል ሰምቶ ሙሉቀን ሄዶ ጠየቀ። ተቀበሉት።

“የበላይ አስተዳዳሪዋ ይወዱኝ ነበር። ‘ኤልቪስ’ ነበር የሚሉኝ። በሁለት ወር እንደዚህ ልብስ ይዘውልኝ ይመጡ ነበር። ውጭ አገር ልኬ አስተምርሃለሁ ብለውኝም ነበር። ይንከባከቡኝ ነበር። እወዳቸው ነበር። ውለታቸው በጣም ትዝ ይለኛል።”

እዚያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተከፈተ። አቶ ተፈራ አቡነ ወልድ ነበሩ አስተማሪው።

Muluken Melesse (1964) - Yemiaslekes Fikir & Hedech Alu (AE 440) 1b

ሙሉቀን ስድስት ወር ያህል እንደተማረ እህቱ ስለታመመች ወደ አገር ቤት ሄደ። ያን ጊዜ ነው አዲስ አበባ ውስጥ አክስት እንዳሉት ያወቀው። እሳቸው ይዘውት መጡና ከሳቸው ጋር መኖር ጀመረ። ቤታቸው የካ ሚካኤል ነው። እንግዲህ ሙሉቀን ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አልተመለሰም።

አክስቱ የወታደር ሚስት ናቸው፣ ጠላም ይነግዳሉ። ኑሮአቸው ጐስቋላ ነው። ልጁ አልተመቸውም።

አንድ ቀን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ሄደ። ሊቀጠር። አልተቀበሉትም። ግን በእርዳታ መልክ ሻይ የማፍላት ሥራ ሰጡት።

“ምድጃዋ የኤሌክትሪክ ነበረች። ባንድ ቀን ውስጥ ሶስት ጊዜ ኮረንቲ ያዘኝ” አለ።

ስድስት ወር ያህል ከሰራ በኋላ ትቶት ወጣ። ጥቂት ወራት ተንከራተተ።

ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወረድ ብሎ አንድ ሻይ ቤት ነበረ። የሻይ ቤቱ ባለቤት ሙሉቀንን ይወደዋል፤ ይረዳዋል። ሀርሞኒካ የሚጫወት ጓደኛ አለው ሙሉቀን። ሻይ ቤቱ ቁጭ ይሉና ጓደኛው ሀርሞኒካውን ይጫወታል። ሙሉቀን ይዘፍናል።

abunepetros1-620x310

አንድ ቀን ሙሉቀንና ጓደኞቹ አብረው ሲጫወቱ ያመሹና ወደ ሶስት ሰዓት ላይ አንዱን ጓደኛቸውን ለመሸኘት ይነሳሉ። ደጃች ውቤ ሰፈር ሲደርሱ የውቤ በርሀ ልዩ ልዩ ቀለማት መብራቶች በርተው ሙሉቀንን በጣም ያስደንቁታል። አንዱ ቤትማ ከሌሎቹም የበለጠ አሸብርቋል። ጓደኛሞቹ ይኸ ቤት ምንድነው ብለው ሲጠያይቁ፣ ይኸማ ‘ፈጣን ኦኬስትራ’ የሚጫወትበት ‘ፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ’ ነው ይሏቸዋል።

ፊት ለፊቱ ካለው ሱቅ ሄደው፣

“ባለቤቱ ማነው የዚህ ናይት ክለብ?” ብለው ጠየቁ።

“ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ናቸው” አለ ባለሱቁ።

“ሥራ ይሰጡኝ ይሆን ወይ?” ብሎ ጠየቀ ሙሉቀን።

“ፃፍና ጠይቃቸው” አለው ባለሱቁ ወረቀትና እስክሪፕቶ እየሰጠው።

እዚያው ቆሞ ደብዳቤውን ፃፈ። ጓደኛሞቹ ከፍርሃት ጋር እየታገሉ ከዚያ ከአስደናቂ ቤት ገቡ። ሙሉቀን ደብዳቤውን ለኦኬስትራው መሪ ሰጠው።

አነበበውና ሳቀበት።

“ምንድነው እሱ?” አሉ ወይዘሮ አሰገደች ከወዲያ ቁጭ ብለው።

ሰውየው ነገራቸው። ደብዳቤውን ተቀብለው አነበቡ።

“ፈትነው። ካለፈ ጥሩ … አለዚያም ሌላ ሥራ እሰጠዋለሁ” አሉ። የልጅ መልኩና ጎስቋላ ሁኔታው ሀዘኔታቸውን ቀስቅሶ ሳይሆን አይቀርም።

ያን ጊዜ ሙሉቀን እንደ ጥላሁን ገሰሰና እንደ ዓለማየሁ እሸቴ እያደረገ ይዘፍን ነበር። ባዶ እግሩንና በቁምጣ ሱሪ መድረኩ ላይ ወጣና ‘ለውነት እሞታለሁ፣ አልሳሳም ለነብሴ’ን እና ‘እንክርዳድ’ን ዘፈነ።

የናይት ክለቡ ሴቶች (በጣም ብዙ ናቸው) ዘፈኑን ወደዱለትና ያን ጊዜውኑ አንድ አራት መቶ ብር የሚሆን አዋጡለት።

“በበነጋታው ካኪ ልብስ ተገዛልኝ፤ ሱፍ ልብስ ተለካሁ። ቢትልስ ጫማ አደረኩ … እግሬን ታጥቤ!” አለ።

Muluken 1973d
ሙሉቀን በ1960ዎቹ መጀመሪያ።

እዚያው ክፍል ተሰጠው። ምግብም ከዚያው ነው። የዘፈን ሥራ ጀመረ።

ወደ ናይት ክለቡ የሚመጣው ሰው እየበዛ ሄደ። ወይዘሮ አሰገደች ሙሉቀንን ኮንትራት (ውል) አስፈረሙት። እሱ ማታ ማታ ሊዘፍን፣ እሳቸው በወር ዘጠና ብር ሊከፍሉት።

“ዘጠና ብር! ሚልየኔር የሆንኩ ነው የመሰለኝ!” አለን።

የቀድሞው አሜሪካን ቤተ መጻሕፍት አጠገብ ‘ዙላ ናይት ክለብ’ የሚባል ነበር። የዚህ የዙላ ባለቤቶች መጥተው አነጋገሩት ሙሉቀንን። በወር ሦስት መቶ ብር እንክፈልህ፣ ለኛ ዝፈን አሉት። እሺ ብሎ ሄደ።

ሴትየዋ ኮንትራት አፍርሷል ብለው አሳሰሩት። ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ። አንዱ ፖሊስ እሳቸውን ለማስደሰት ብሎ ሙሉቀንን በጥፊ ሲለው ጊዜ ታዲያ በጣም ተቆጡት።

“እንድታስፈራሩልኝ ነው እንጂ እንድትጎዱት አይደለም” አሉ።

ከቤታቸው አልጋ መጣለትና ተረኛው መኰንን ክፍል ተነጥፎለት እዚያ አደረ። በነጋታው ተፈታ። ‘ዙላ ናይት ክለብ’ ገባ።

“ጋሽ ሰሎሞን ተሰማ የደረሰውን ‘የዘላለም እንቅልፍ’ እና አቡበከር አሸኬ የደረሰውን ‘ያላየነው የለም’ … ሁለቱን ዘፈን ይዤ በቴሌቪዥን ቀረብኩ።”

.

[“የዘላለም እንቅልፍ”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም/ዜማ) ሰለሞን ተሰማ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1961-1964 ዓ.ም።]

.

አዲስ አበባ ሙሉቀን መለሰን ሊያውቀው ጀመረ።

Muluken Melesse (1965) - Antarekm Wey & BeMistir Kiberign (PH 7-181) 1a

የፖሊስ ኦርኬስትራ አስተዋዋቂ ሻለቃ ወርቅነህ ዘለቀ (የቅጽል ስማቸው ‘ይቀጥላል’)፣

“አንድ አራት መቶ ብር እንክፈልህ፣ ና እኛጋ!” አሉት።

እሺ ብሎ ሄደ። የወር ደሞዙ ይመጣል ታድያ – አንድ መቶ ብር ብቻ!። እወጣለሁ ቢል ጊዜ፣ “ፈርመሃል!” ብለው አስፈራሩት። ልጅ ነዋ!

ሙሉቀን መለሰ ለፖሊስ ኦርኬስትራ በተቀጠረ በሦስት ቀኑ መቀሌ ከኦርኬስትራው ጋር የ “ወይዘሪት ትግራይ” የቁንጅና ውድድር ይደረግ ነበር። ሙሉቀን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈኖች ዘፈነ። በጣም ወደደው ሕዝቡ። የኦርኬስትራው አባሎችም አለማየሁ እሸቴ ሄዶባቸው ስለነበረ ሙሉቀንን “ምትኩ” አሉት።

ተስፋዬ አበበ የደረሳቸውን ሦስት ዘፈኖች (“እምቧይ ሎሚ መስሎ” “እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ” እና “ልጅነት” የተባሉትን) ሙሉቀን በሕዝብ ፊት ይዘፍን ጀመር። በነዚህ ዘፈኖች ታዋቂነትን አተረፈ። ጋዜጣ ላይም “ኮከብ ድምጻዊ ተጫዋች” ብለው ጻፉለት።

.

[“እምቧይ ሎሚ መስሎ”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም) ተስፋዬ አበበ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1961-1964 ዓ.ም።]

.

ከፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ሦስት ዓመት አገልግሎ ወጣ … የማታ ክበቦች እንደገና መጫወት ጀመረ።

Muluken 1973f

ዛሬ በግዮን ሆቴል በ‘ዳህላክ ባንድ’ እየታጀበ ይዘፍናል።

አንድ አስር የሚሆን የሙሉቀን መለሰ ሸክላ ወጥቷል። ከአብዮቱ ወዲህ ዘፈኖቹ በካሴት ተሰራጭተዋል።

ከዘፈኖችህ በጣም የምትወደው የትኞቹን ነው? ብለን ጠየቅነው።

“እኩል ነው የማያቸው። ግን … በጣም የሚያረኩኝ … በዜማውና በዘፈኑ … ‘ሰውነቷ’ እና ‘ሆዴ ነው ጠላትሽ’ … እ …… በሙዚቃ ጥራትና ባሠራር ደግሞ፣ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀነባበራቸውና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈንኳቸው ‘ቼ በለው’ እና ‘ውቢት’።”

Muluken Melesse (1967) - Chebelew & Wubit (A 004) 1b

[“ቼ በለው”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም/ዜማ) ተስፋዬ ለማ። Equators Band። 1967 ዓ.ም።]

[“ሰውነቷ”። ሙሉቀን መለሰ። ዳህላክ ባንድ። 1971 ዓ.ም።]

.

ከድምፃውያን ተጫዋቾች ማንን ታደንቃለህ? አልነው።

“ዓለማየሁ እሸቴን። ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው። ካሉን ዘፋኞች ሁሉ የበለጠ የሙዚቃ እውቀት አለው። ሁላችንም በዘልማድ የምንዘፍን ሲሆን፣ እሱ ግን ሙዚቃን በማወቅ ከኛ ብልጫ አለው። ፕሮፌሽናል ኢንተርናሽናል (በአለም አቀፍ ደረጃ ባለሙያ) ዘፋኝ ያለን እሱ ነው ብዬ የምኰራበት ሰው ነው።

“በድምፅ ደሞ እንደ ምኒልክ ወስናቸው ያለ ዘፋኝ የለንም። የኦፔራ ዘፋኝ ድምጽ ነው ያለው … ጥላሁን፣ ዓለማየሁ፣ ምኒልክ፣ ብዙነሽ፣ ሂሩት፣ ማህሙድ – እነዚህን የሚተኩ ድምጻውያን መብቀል አለባቸው። ይኸ የአገሪቱ ኃላፊነት ነው … ይህን ሙያ ሲበዛ ነው የምወደው። በየዕለቱ ይበልጥ እያወቅከው … እየተማርከው ትሄዳለህ። ማቆሚያ የለውም … ሙዚቃን በትምህርት ሳይሆን በልማድ ነው የማውቀው።

Muluken 1973a

“አንደኛ የሚባል ዘፋኝ የለም። ሊኖርም አይችልም። ቢበዛ ‘የዓመቱ ኮከብ’ መባል ይችላል እንጂ … እያንዳንዱ ዘፋኝ የራሱ አይነት ልዩ ተሰጥዎ አለው።”

.

[“ላንቺ ብዬ”። ጥላሁን ገሰሰ። (ግጥም/ዜማ) ምኒልክ ወስናቸው። All-Star Band። 1963 ዓ.ም።]

[“እሩቅ ያለሽው”። ዓለማየሁ እሸቴ። (ግጥም) ኃይሉ መኩሪያ። ዓለም-ግርማ ባንድ። 1965 ዓ.ም።]

[“የእንጆሪ ፍሬ”። ምኒልክ ወስናቸው። ቀኃሥ ቴአትር ኦርኬስትራ። 1960ዎቹ።]

[“አትራቀኝ”። ብዙነሽ በቀለ። (ግጥም/ዜማ) ተዘራ ኃ/ሚካኤል። ዳህላክ ባንድ። 1969 ዓ.ም።]

[“እውነተኛ ፍቅር”። ሂሩት በቀለ። (ግጥም) ተስፋዬ አበበ (ዜማ) ንጉሤ ዳኜ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1969 ዓ.ም።]

[“ትዝታ”። ማሕሙድ አህመድ። (ግጥም) ሸዋልዑል መንግሥቱ። አይቤክስ ባንድ። 1967 ዓ.ም።]

 [“መውደዴን ወደድኩት”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም) ዓለምፀሐይ ወዳጆ። ዳህላክ ባንድ። 1971 ዓ.ም።]

.

ሙሉቀን መለሰ

(ቃለመጠይቅ በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር)

1973 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ኪነት ዓምድ”። ፀደይ መጽሔት። ኅዳር ፲፱፻፸፫ ዓ.ም። ገጽ 12-14፣ 20።

.

 

“ባንዶቹ” (ራስ ባንድ)

“ባንዶቹ”

(ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቡድኖች)

.

በሳይም ኦስማን

.

(ራስ ባንድ)

.

ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ‘ወርቃማ ዘመን’ ስናወራ እነዚያን መሳጭ ሙዚቃዎች ከዘፋኞች ኋላ ሆነው ስላቀነባበሩት ስለ ባንዶቹ ሳናነሳ አናልፍም።  በዚህ ጽሑፍ (እና በቀጣዮቹ ክፍሎች) የዋና ዋናዎቹን ዘመናዊ ባንዶች ታሪክ እና ባንዶቹን ስላቋቋሙት ሙዚቀኞች አጠር አድርጌ አቀርባለሁ።

በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በጣም ተወዳጅ የነበሩት የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ፣ የፖሊስ ባንድ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ኦርኬስትራ፣ እና የምድር ጦር ኦርኬስትራ ነበሩ። በ1953 ዓ.ም የታህሳሱ ግርግር የኃይለሥላሴን መንግስት ለመገልበጥ የተሞከረበት ጊዜ፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሁለተኛ ምዕራፍን ከፈተ። በዚህም ወቅት የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራ ለበርካታ ወራት ለመበተን በቃ። ብዙዎቹ አባላቶቹም ከኦኬስትራው እየለቀቁ ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖችን (ፖሊስ፣ ምድር ጦር እና ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ቴያትር) መቀላቀል ጀመሩ። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ኦኬስትራዎች ቀስ በቀስ ወደ ብዙ ትናንሽ ባንዶች እየተቀየሩ መጡ።

እነዚህም ትናንሽ ባንዶች መጀመሪያ ስራ የጀመሩት በተለያዩ የአዲስ አበባ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ነበር። ለዚህም ይመስላል የባንድ ስማቸውን በሆቴሎቹ ስም ያደረጉት … እንደ “ራስ ባንድ”፣ “ግዮን ባንድ”፣ “ሸበሌ ባንድ” የመሳሰሉት። ብዙም ሳይቆይ ሆቴሎቹ በጣም ታዋቂ መዝናኛ ቦታዎች እየሆኑ መጡ። በተለይም አርብ ማታ እነዚህን የሙዚቃ ድግሶች ለመታደም የማይቀርበት ቦታ ሆኑ።

ras hotel 1950s
ራስ ሆቴል በ1950ዎቹ መባቻ።

.

ራስ ባንድ

.

የመጀመሪያው ራስ ባንድ የተቋቋመው በ1953 ዓ. ም ነበር። ባንዱንም የመሠረቱት ተፈራ መኮንን (ፒያኖ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክስፎን)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ባህታ ገብረሕይወት (አማርኛና ትግርኛ ድምፃዊ)፣ ግርማ በየነ (እንግሊዘኛ ድምፃዊ) እና ገብረአብ ተፈሪ (አስተናባሪና ገጣሚ) በመሆን ነበር። በዛሬ ዘመን በሕይወት በመሀከላችን የሚገኙት ጌታቸው ወልደሥላሴ፣ ባህታ ገብረሕይወት እና ግርማ በየነ ናቸው።

Ras Band 3
ራስ ባንድ በራስ ሆቴል (1953-1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 1|

የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ ናቸው። እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስም ሶስቱ አባላት የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ተምረው ነበር። በክቡር ዘበኛ ኦሮኬስትራ ውስጥ ተፈራ መኰንን ቤዝ ሲጫወት ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ ደግሞ ድራም ተጫዋቾች ነበሩ። በ1953 ዓ.ም አጋማሽም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲበተን ተጨማሪ ሙዚቀኞችን (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) እና ሁለት ድምፃውያንን ይዘው ወደ ራስ ሆቴል አመሩ።

“አርብ ማታ በራስ ሆቴል የሚያስደስት ጊዜ ነበር” ይላል ባህታ ገብረሕይወት – Addis Live ራዲዮ ኢንተርቪው ላይ፣ ባህታ የሆቴሉን ድባብ ሲያስታውስ ሁሉም የባንዱ አባላት በሚገባ ዘንጠው መገኘት ነበረባቸው። እያንዳንዱም የሆቴል ተጠቃሚ አለባበሱን አስተካክሎ መገኘት የሆቴሉ ህግ ነበር። በሚገባ አለባበሱ አልተስተካከለም ብለው ለሚያስቡት ተጠቃሚ ክራቫት ይሰጠው ነበር። ብቻቸውን የሚመጡ ተስተናጋጆች እምብዛም ናቸው። ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኖ ይደንስ ነበር።

Ras Band
ራስ ባንድ በአክሱም አዳራሽ መክፈቻ በዓል (ታኅሣስ 4፣ 1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ባህታ ገብረሕይወት (ድምፅ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 2|

ራስ ባንድ ውስጥ እያለ ነበር ባህታ ብዙዎቹን ስራዎቹን ያበረከተልን። እነ “አንቺም እንደ ሌላ”፣ “ደግሞ እንደምን አለሽ”/“ካላጣሽው አካል”፣ “ስቃይ ዝክኣል’ዩ”፣ “የጥላቻ ወሬ”፣ “ያ ያ” እና “ወደ ሀረር ጉዞ” የመሳሰሉትን።

[“ካላጣሽው አካል”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

ባህታ የትግርኛ ዘፈኖቹን ግጥም የጻፈው እራሱ ሲሆን፣ ብዙዎቹን የአማርኛ ዘፈኖች ግጥም ደግሞ ገብረአብ ተፈሪ ነበር የሚጽፋቸው። ሙዚቃዎቹን የሚጽፈውና የሚያቀናብረው ፒያኖ ተጫዋቹ ተፈራ መኰንን ነበር። ባህታም በዚህ ዘመን ከጻፋቸው ሙዚቃዎች ዜማ አንዱ እና ግርማ በየነን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ታዋቂ ያደረገው ዘፈን ‘ይበቃኛል’ የተሰኘው ነበር።

AE690c Bahta

በዚሁ ራስ ባንድ በሚሰራበት ጊዜም ነበር ባህታ በትርፍ ጊዜው ተምሮ አካውንቲንግ ያጠናው። በ1964 ዓ.ም ከሙዚቃ ዓለም ሲርቅ ለግዮን ሆቴል እና ለፊልም ኮርፖሬሽን የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ባህታ እንደሚለው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አካሄድ አላምር ብሎት ነበር ከሙዚቃ አለም የራቀው። በታህሳስ 1996 ዓ.ም ከብዙ አመታት በኋላ ባህታ ገብረሕይወት ‘አንቺም እንደሌላ’ን Either Orchestra ከሚባል ቦስተን ከሚገኝ የጃዝ ቡድን ጋር አቅርቦ ነበር።

[“አንቺም እንደሌላ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን/ራስ ባንድ)። 1957-1960 ዓ.ም።]

የመጀመሪያው የራስ ባንድ የተመሰረተው ከ1953 ዓ.ም ነበር። ታዲያ በ1956 ዓ.ም አጋማሽ ሁለቱ የባንዱ አባላት (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) በሌሎች ሙዚቀኛች የተተኩ ይመስላል። ወዳጄነህ ፍልፍሉ ከዚህ ወቅት ጀምሮ ሳክሰፎን በመያዝ፣ አሰፋ ባይሳ ደግሞ ትራምፔት በመጫወት ራስ ባንድን ተቀላቀሉ። በሐምሌ 1956 ዓ.ም አካባቢም እንግሊዘኛ ድምፃዊው ግርማ በየነ ራስ ባንድን ለቀቀ። ብዙም ሳይቆይ በ1957 ዓ.ም የባንዱ አባላት ከራስ ሆቴል ወጥተው በግዮን ሆቴል ለተወሰኑ ዓመታት “ግዮን ባንድ” ተሰኝተው ተጫውተዋል።

Ras Band 2
ራስ ባንድ በነሐሴ 1956 ዓ.ም። [ከግራ ወደ ቀኝ] ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ አሰፋ ባይሳ (ትራምፔት)፣ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባሕታ ገብረሕይወት (ድምፃዊ)፣ እና ወዳጄነህ ፍልፍሉ (ሳክሰፎን)። |ምስል 3|

በድምፃዊነት እና በፐርከሽን ከሦስት ዓመት በላይ “ራስ ባንድ” ከተጫወተ በኋላ ግን ወጣቱ ግርማ በየነ በተራው የራሱን ባንድ ለማቋቋም ወሰነ።

Girma Beyene (old)
ግርማ በየነ በ1956 ዓ.ም መገባደጃ። |ምስል 4|

.

.

(ይቀጥላል)

.

ሳይም ኦስማን

.

[ትርጉም] – ሕይወት ከተማ

.

[ምንጭ] – Sayem Osman. (Ethio Jazz). “Bandochu.” 2006. Bernos.com

ትምክሕት ተፈራ መኰንን። የግል ምስሎች ስብስብ። [ምስል 1]

 “የአዲስ አበባ ትዝታ”። vintageaddis.com [ምስል 2]

ሰለሞን ተሰማ። “አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው።” የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1957 ዓ.ም። [ምስል 3፣ 4]

Peter Roth. “Modern Ethiopian Music Discographies”. http://www.funkfidelity.de

Francis Falceto. “Abyssinie Swing – Pictorial History of Modern Ethiopian Music.” 2001.

.

.

ተጨማሪ

የራስ ባንድ ሥራዎች

.

[“ወደ ሐረር ጉዞ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

[“ወደ ሐረር ጉዞ – 2”። ባሕታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ። 1957-1960 ዓ.ም።]

የአስናቀች ወርቁ ኪነጥበባዊ ሕይወት

የአስናቀች ወርቁ ኪነጥበባዊ ሕይወት

በኅሩይ አብዱ

“አስናቀችና ሙዚቃ”

ከቅጽበታዊው የተውኔት መድረክ ይበልጥ አብዛኞቻችን አስናቀችን የምናያይዛት ከክራሯና ከምታንጎራጉራቸው ዘፈኖቿ ጋር ነው። እንደ ኢየሩሳሌምን እንደምታስታውሱ ተስፋ አደርጋለሁ።

“እንደ ኢየሩሳሌም እንደ አኩስም ፅዮን ፣

ተሳልሜው መጣሁ አይንና ጥርሱን …”

asnakech-ethiopiquesየኢትዮጵክስ 16 – “The Lady With the Krar” – ሲዲ አስናቀች በ1966ና 1968 ዓ. ም. ያወጣቻቸውን ሸክላ ዘፈኖች የድምጽ ጥራት አሻሽሎ ለገበያ ቀርቧል። ኢትዮጲክስ 16 ሃያ ሁለት ዘፈኖችን አሰባስቧል፣ ዘፈኖቹ በሕዝባዊ ዜማዎች ላይ ተመስርተው ሰባቱ ግጥሞች በአስናቀች ሲደረሱ ሌሎቹ በጌታቸው ደባልቄ፣ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ተስፋዬ ለማና፣ ሸዋልዑል መንግስቱ የተገጠሙ ናቸው።

አስናቀች በክራር ራሷን አጅባ በምታንጎራጉራቸው ዘፈኖች የምታተኩረው ተቀጣጥሎ ያልተፋፋመ ወይንም የሰከነ ፍቅር ላይ ነው። ለአብነት ‘እንደ ኢየሩሳሌምን’ና ‘እሱ ርቆ ሄዶ’ን መመልከት ነው። የፍቅር ጉዞዋ በዘፈኖቿ ውስጥም ይታያል። የምታፈቅራቸው ሰዎች አያዛልቋትም፤ የሰው ሰው ሊሆኑ ይችላሉ ወይንም ስሜታቸው አብሯት አይፈካም። ለዚህም ነው ፍቅረኞቿን “ይፋ የማይወጣ ሰው”፣ “ፍቅር የማይገባው አጉል ሰው” እያለች የምትጠራቸው። አስናቀች ለወደደችው ፍቅሯን ከመግለጽ አትቆጠብም፣ ከመለማመጥም አትመለስም። አንዴ ፍቅሩ ከሰከነ ግን እርግፍ አድርጋ ትተዋለች። ሕይወቷም ዘፈኖቿም ምስክሮች ናቸው።

“መሞከር ይሻላል ሁሉንም መሞከር፣

ይፈጠር ይሆናል አንድ ደህና ነገር።”

መንገደኛው ልቤ 1966 ዓ. ም.

asnakech-musicአስናቀች ወርቁ እነዚህን ስንኞች ስታንጎራጉር የሕይወቷን ሚስጥር የምታካፍለን ይመስላል። አስናቀች ዘወትር ሕይወቷን ወደ አዲስ መንገድ እንደመራችው ነው። ከልጅነት ወደ ትዳር፣ ከአንዱ ትዳር ወደ ሌላ፣ ያም ሲፈርስ ወደ አዲስ ፍቅረኛ፣ ከዛም ወደ ሌሎች ፍቅረኞች ተሻግራለች። ብዙ ነገር ሆናለች፤ ማንም ያልደፈረውን የሴት ተዋናይ፣ ከዛም አልፋ የሙዚቃ (ክራር) ተጨዋች ፣ ዘፋኝ (አንጎራጓሪ)፣ እንዲሁም የባሕልና የዘመናዊ ሙዚቃ ተወዛዋዥ፣ ሁሉንም ሆናለች።

“አስናቀችና ቴያትር”

አስናቀች “የፍቅር ጮራ” ተውኔት ውስጥ ከመሳተፏ በፊት የሴትን ገጸባህሪ የሚጫወቱት ወንዶች ነበሩ። የሚመረጡትም ጺም ገና ያላወጡ ፣ መልከ መልካም ወጣቶች – እንደ ተስፋዬ ሣህሉ (አባባ ተስፋዬ)፣ መርአዊ ስጦት፣ ተፈራ አቡነወልድ … የመሳሰሉት – ነበሩ። ምንም መልከ መልካም ቢሆን፣ ድምጽንም እንደፈለገ መቀያየር ቢችል፣ ወጣቱ አባባ ተስፋዬ (ወይንም ሌላ ወንድ ተዋናይ) የቧልት እንጂ ውስብስብ የሴት ገጸባህሪይ መጫወት የሚችል አይመስለኝም። በአስናቀች ፋና ወጊነት የሴቶችን ገጸባህሪ ሴቶች ራሳቸው ይጫወቱት ጀመረ፤ የሚሰሩትም ተውኔቶች ተአማኒነታቸው እየጨመረ ሄደ።

img_4762የዚህችን ሁለገብ ጠበብት ሕይወት የሚዳስስ መጽሐፍም በቅርቡ ታትሟል። አስናቀች መድረክ ላይ የምትጫወተውን የባለታሪክ ባህርይ ሙሉ በሙሉ እንደምትላበስ ደራሲው ይናገራል። ለምሳሌ የፍቅር ጮራ ላይ ከመድረክ ፍቅረኛዋ ጋር የነበራት ግንኙነት እውነተኛ በመምሰሉ ትርኢቱን የምትመለከተው የተዋናዩ ፍቅረኛ እያለቀሰች ዝግጅቱን አቋርጣ ወጥታለች (ገጽ 23)። በሌላ መድረክ ላይ “ሴተኛ አዳሪዋ” አስናቀች ኑሮዋን የመረጠችው እንደሌላው ስራ ዘመድ፣ ትምህርት ወይንም ጉቦ ስለማያስፈልገው እንደሆነ ትናገራለች። እውነታው የከነከናቸው የውቤ በረሃ ቆነጃጅት እንዲሁም ሌላው ተመልካች ገጸባህሪዋን (ወይንስ አስናቀችን?) በጭብጨባ ደግፈዋታል (ገጽ 36)።

አስናቀች ምን ያህል ተውኔቶች ውስጥ እንደተሳተፈች አላውቅም። መጽሐፉም አይናገርም። ደራሲው የፍቅር ጮራ ፣ እኔና ክፋቴ ፣ ዳዊትና ኦሪዮን ፣ ስነ ስቅለት ፣ ኦቴሎ ፣ እናት አለም ጠኑና ኤሪስ በጎንደር የተባሉትን ዘርዝሯል። የነዚህን ከአምስት እጥፍ በላይ እንደሰራች አልጠራጠርም። ነገር ግን ተጽፎ ካልተቀመጠ ይረሳልና፣ ደራሲው የወደፊት እትም ላይ ቦታ ቢሰጠው መጽሐፉን ያሳድገዋል። ገጣሚውና ጸሐፌ ተውኔቱ ጸጋዬ ገብረ መድህን በበልግ መጽሐፉ ፣ “በመስከረም 19 ቀን 1954 ዓ. ም. ዓርብ ማታ በተከፈተ (የበልግ ተውኔት) ጊዜ፣ … ጌታቸው ደባልቄ እንደ ወፈፌው ሰዓሊ እንደ ኅሩይ፣ … አስናቀች ወርቁ እንደ ብኩኗ ቆንጆ እንደ ጽዮን ሆነው ተጫውተው ነበር” በማለት ዘግቧል። በተጨማሪም አውራስ መጽሔት 1985 ዓ.ም. ቁጥር 1 ላይ እንዳየሁትም “ደመ መራራ”ና “ዋናው ተቆጣጣሪ” የተባሉ ተውኔቶች ውስጥ ተሳትፋለች።

“መጽሐፉ”

img_4761የአስናቀች ትዝታዎቹን በጽሑፍ አዘጋጅቶ ያቀረበልን ጌታቸው ደባልቄ ነው። ጌታቸው ላለፉት 50 አመታት ከዘመናዊ የኢትዮጵያ ቴያትር አብሮ ድኾ፣ አድጎ፣ ጎልምሷል – እንደ ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ደራሲ እንዲሁም አስተዳዳሪ። በተጨማሪም ጌታቸው ስለ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃና ቴያትር አጀማመርና ሂደት ማወቅ ለፈለጉ የመረጃ ምንጭ ኧረ ወንዝም ነው። የሰበሰባቸው ፎቶዎችና ሰነዶች፣ እንዲሁም ለጠየቁት በደስታ የሚያወጋቸው ትዝታዎቹ፣ ከመጽሔቶች ተርፈው ሙሴ ፋልሴቶ አዘጋጅቶ የሚያቀርባቸውን የኢትዮጲክስ (Ethiopiques) ሲዲዎች እያጀቡ ነው።

ደራሲው ከባለታሪኳ ጋር የተዋወቀው በ1945 ዓ.ም. ነበር። ጌታቸውም እንደሚለው፣ “ስለሷ ሕይወት መጠነኛ ታሪክ ለማስቀረት ምኞት ካደረብኝ ቆይቷል” ለምንስ መጽሐፉን ጻፈ? “… ለነገዎቹ የኪነጥበብ ሰዎችና ታሪክ ጸሐፊዎች” ለማስተላለፍ ይመስላል።

asniመጽሐፉ አራት ክፍሎች አሉት፤ እነሱም ልደትና እድገት – ውስብስብ ሕይወት ፣ የጥበብ ጮራ ፣ ከጠባቡ ወደ ሰፊው የኪነጥበብ አለምና፣ ጡረታና ትዝታ ናቸው። አባቷን የማታውቅ፣ እናቷም በሕጻንነቷ የሞቱባት አስናቀች፣ ልጅነቷን ያሳለፈችው አንዱ ዘመድ ወደ ሌላው እየተቀባበላት ነበር። በብቸኛው የአዲስ አበባ የሴቶች ት/ቤት የመማር እድሏን ስለተነፈገች፣ ምርጫ ሆኖ የታየው ለትዳር መዘጋጀት ብቻ ነበር። አክስቷም ጣሊያን አገር ሚስትና ልጆቹን ላስቀመጠው ለአንዱ ዳሯት። ልጅነቷን ያልጠገበችው አስናቀች ግን የትዳር ማተብ ሊያስራት እንዳልቻለ በመጀመሪያው ክፍል እናያለን።

ሁለተኛው ክፍል የዘመናዊን ቴያትር አጀማመር በትንሹ ዳስሶ አስናቀችም በምን መልክ “የፍቅር ጮራ” ተውኔት ላይ የመጀመሪያዋ የሴት ተዋናይት እንደሆነች ይተርካል። የሚቀጥለው ክፍል የአስናቀችን በ“ዳዊትና ኦሪዮን” (ለአፄ ኃይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዮ የተዘጋጀ ተውኔት) የተዋጣለት ትወና፣ እንዲሁም ከክራሯ ጋር የመሰረተችውን ፍቅር አጀማመር ያወሳል። የመጨረሻው ላይ ክፍል ከጡረታ ይልቅ ሁሌ የሚፋጀው የአስናቀች ፍቅር ላይ ያተኩራል፤ የፍቅር ሕይወቷ ለብቻው አንድ ተውኔት ሳይወጣው አይቀርም። በኢትዮጲክስ አዘጋጅ ከቀረበው አጭር የሕይወት ታሪክ በኋላም መጽሐፉ በሁለት የታወቁ የአስናቀች የዘፈን ግጥሞች ይደመደማል።

asnaketch-costume

የሽፋኑም ምስሎች ፣ የደራሲውንም ጉርድ ፎቶ ጨምረን መጽሐፉ ከሃያ በሚበልጡ ፎቶዎች አሸብርቋል። የናንተን ባላውቅም እኔ በበኩሌ ፎቶ ወይንም ምስሎች የተነሰነሱበት መጽሐፍ ይስበኛል። ምስሎች ከታሪክ ጋር በአግባቡ ሲዋሀዱ ጽሑፍን ያጣፍጣሉ፤ ምናባችንንም “በፈረሱም ይኸው ሜዳውም ይኸው” እያሉ ያደፋፍራሉ። አዘወትረን በሀገራችን መጽሐፎች እንደምናየው ፎቶዎቹ ደብዝዘው ሰው ከሰው የማይለይበት ደረጃ አልደረሱም። እነዚህዎቹ ጥርት ብለው ወጥተዋል ፤ ደራሲውና አሳታሚው ምስሎቹን ታሪካዊነት ፋይዳ ስለሰጡ ፎቶዎቹን ከደህና ምንጭ ቀድተው ለፎቶ በሚስማማ ወረቀት አሳትመዋል።

የፊት ሽፋኑን ፎቶ ብትመልከቱት፤ ለብቻው ስንት ታሪክ ይናገራል! መቸስ አስናቀች ባሕላዊነትን ከዘመናዊነት ጋር ያለ ግጭት ካዋሐዱ ጥቂቶች አንዷ መሆን አለባት። የእድሜ ባለፀጋዋ ወጣትነት ከልብ ትኩሳት እንጂ ከቁጥር ማነስ እንደማይገኝ የምታምን ትመስላለች፤ ወይንስ ትዝታዋን የሙጥኝ መያዟ ነው? የአይኖቿ ከኛ መደበቅስ? ብዙ ሚስጥር በሆዷ ይዛ ነውን? እኛን አፍራ ሳይሆን ሸክሙ እንዳይከብደን ያዘነች ትመስላለች። ይሄ በሙላ ከአንድ ፎቶ!

asnakech-kirar

ፎቶዎቹ ሌላም ብዙ ታሪክ ያወሳሉ። አስናቀች የመጀመሪያዋ የሴት ተዋናይ ከመሆኗ በፊት የሴትን ገጸባህሪ ማን ይጫወት ነበር? ገጽ 19 ያለውን ፎቶ ይመልከቱ። በ1945 ዓ. ም. ሁለተኛ ማዕረግ ተቀምጦ ቴያትር ለመመልከት ስንት ብር ያስፈልግ ነበር? ምን ያህልስ የተውኔት ማስተዋወቂያ ይታተም ነበር? መልሱን ገጽ 21 ያገኙታል። ሞኝና ወረቀት … ልበል መሰለኝ።

ጌታቸው ደባልቄ በዚህ አነስተኛ መጽሐፍ ስለሚወዳት ጓደኛው ያሉትን ትውስታዎች አስተላልፎልናል። በተጨማሪም ስለ ቴያትርና ሙዚቃ አጀማመር፣ ወጣቷንም አዲስ አበባን ለመተዋወቅ ለሚፈልጉ ጥሩ እይታ ይሰጣል። ይህን መጽሐፍ እንደተለመዱት በዓመተ ምህረትና በመረጃዎች እንደተሞሉ የሕይወት ስራዎች አላየሁትም። ከዚያ ይልቅ በትውስታ/ትዝታ ዘርፍ ቢመደብ አንባቢውንም አያደናግርም።

ምን ይጨመር? ምንስ ይቀነስ? አስናቀች የተሳተፈችባቸውን ተውኔቶች፣ የዘፈነችባቸውን የሙዚቃ ሸክላዎች ቢዘረዘሩ የበለጠ የምናውቃት ይመስለኛል። የመጽሐፉ መጀመሪያና አራተኛው ክፍል በባለታሪኳ ድምጽ ቢተረክ ቋንቋዋም ስሜቷም የሚዋሐደን ይመስለኛል። መጽሐፉ በመታተሙ እጅግ ተደስቻለሁ፤ በሕይወት ያሉ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጊዜ መጽሐፍ አይጻፍላቸውምና!

እንደ መጽሐፉ መዝጊያ ዓረፍተ ነገሮች …

“ይህ የኔ ጽሑፍ ለመጭዎች ጸሐፊዎች መግቢያ በር ይሆናል። ሊያባዙት ሊያሳጥሩት ቀና መንገድ ይሆናል። በበኩሌ የዘለልኩትን ዘልዬ ያሳጠርኩትን አሳጥሬ በዚህ ሁኔታ ደምድሜዋለሁ።”