አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ”

“ቪላ አልፋ” አዲሱ መልክ

ከበዓሉ ግርማ

(1961 ዓ.ም)

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገውን፣ በመደረግ ላይ ያለውንና ወደፊት የሚደረገውን ሁሉ እንደመጠጥ ብርጭቆ አንስተው የማስቀመጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከተሜዎች አሉ። ሰሞኑንም ከሰላምታ በኋላ አርዕስተ ነገር አድርገው የያዙት ትችት ቢኖር ስለ አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጐድጓድ) አዲሱ የቪላ አልፋ መልክ ነው።

ትችቱ እንደተቺዎቹ የበዛ ቢሆንም አንዳንዶቹ፣

“ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ (በተለይ የፍሮይድን ሳይኮሎጂ ከእጅ ጣታቸው እንደዋዛ የሚያንቆረቁሩት ተቺዎች) የዚህን ዓለም ጉዳይ ወደጎን ብለው፣

“አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ።

“ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነገር ነው” የሚሉም አሉ።

ያም ሆነ ይህ የነቀፌታዎቹ መነሾ ሠዓሊው አፈወርቅ ቪላ በመሥራቱ አይደለም። ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን የገነቡት በሰው አፍ አልገቡም። በግል መኖሪያቸው የሰማኒያና የመቶ ሺህ ብር ዘመናይ ቪላዎችን የሠሩት ዓይን አልበላቸውም።

“ታዲያ የአፈወርቅ ስም እንደ ትኩስ ድንች እያንዳንዱ አፍ ውስጥ የሚገላበጥበት ምክንያት ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።

ጐንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነው ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው።

የዚህ አይነት ቤት (ወይም ካስል) በመሥራት አፈወርቅ በዘመናችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ቤቱን የቀየሰው መሐንዲስ G. Boscarino እንዳለው፤

“እንዲህ ያለው ቤት ውስጥ ከአፈወርቅ በስተቀር ሌላ ሰው ቢኖርበት፣ ቤቱ አሁን ያለውን ዋጋና ጥቅም ሊሰጥ አይችልም”።

አዎን፣ ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ የመሰለውን ቤት አልሞ የሚሰራ የለም። የሚሰጠውን ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱው ብቻ ነው።

እንዲህ የመሰለውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ምን እንዳሳሰበው፣ ከተሰራ በኋላ የሚሰጠውንም ጥቅም እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበር። ለማናገር ፈቃደኛ ቢሆንም ጊዜ አልነበረውም።

አናጢዎቹ በየደቂቃው ይጠሩታል።

በተመለሰ ቁጥር “የአገራችን አናጢዎች ለምን አንድ መስመር በትክክል ለመሥራት አይችሉም?” በማለት ይገረም ነበር።

እነሱም በበኩላቸው እሱ አሁን በቅርብ ጊዜ የሠራውን የእንሥራ ተሸካሚ ሥዕል፤ በተለይ ወተት መስሎ በጃኖ ጥለት የታጠረውን ቀሚሷን፣ አለንጋ የመሳሰሉትን ጣቶቿንና ሕልም መሳይ ውበቷን አይተው መገረማቸው አልቀረም።

ገና ተመልሶ ቁጭ ከማለቱም ቀለም ቀቢዎች ይጠሩታል።

አዎን፣ “የሰሜን ተራራ” የተባለውን ሥዕል (ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ሰላም የሚፈጥረውን) የሠራ ሰው ለተራ ቀለም ቀቢዎች ችሎታ ልዩ አድናቆት ሊኖረው አይችልም።

አሁንስ አፈወርቅን የሚጠራው ሰው የለም ብዬ በመተማመን ጥያቄዬን ወርውሬ፣ ብዕሬን ከወረቀት ለማገናኘት ስቃጣ፣ አንድ ጽጌረዳ አበባ የት እንደሚተክሉ የቸገራቸው፣ ወይም አበባ የያዘውን ሳጥን የት እንደሚያስቀምጡ ግራ የገባቸው ለምክር ይጠሩታል። ሳያማክሩት ያስቀመጡት፣ ወይም የተከሉት እንደሆነ ኋላ ማንሳታቸው አይቀርም።

አፈወርቅ ደጋግሞ እንደሚለው፣

“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው”።

ሠራተኞቹም ደከሙ። ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ያራውጣቸው ነበር።

ጥሪው እያነሰ ሄደ። ቁጭ ለማለት ቻልን።

“ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊው የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል” አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ።

በሁለት ወር ያልቃል ተብሎ የታሰበው ቤት አሁን አራተኛ ወሩን ሊጨርስ ነው። በአራት ወር ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕሎች ብቻ ነበር ለመሥራት የቻለው። የቀረውን ጊዜ ያዋለው በቤቱ ሥራ ላይ ነበር።

“ቪላ አልፋ” የተሠራው በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን ቤቱን ለመሥራት አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥቦ ነበር። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል።

ይሁንና በኔ በጠያቂው በኩል ሃያ ስድስት በሃያ ስድስት ሜትር ካሬ መሬት ላይ የተሠራው አዲሱ ቤት ይህን ያህል የሚያስደንቅ ወጭ የሚጠይቅ መስሎ አልታየኝም። አፈወርቅም ስንት ገንዘብ እንደጨረሰ ትክክለኛ ዋጋውን ሊገልጽልኝ አልፈቀደም።

ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስሎ ለመስራት ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽልኝ እንዲህ አለ፣

“ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም።”

አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው።

በቤቱ ውስጥ ያለ ምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው እሱ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። የቤቱ ቆርቆሮ ቀይ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። ቤቱ ነጭ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው።

አንድ ሥዕል አንድ ግድግዳ ላይ በአንድ በኩል እንዲሰቀል የተደረገበት ያለ ምክንያት አይደለም። ቤቱ የተሠራው ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ሌላ ምክንያት አለው። ቤቱም ቀለሙም አቀማመጡም – ሁሉም ባንድነት ተዋህደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው።

“ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ። የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ አውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር።”

“አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው።”

“ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ላንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትዕይንት ጠቃሚው ነው።”

አዎን፣ ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

ቤቱ አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው።

ሦስቱ መስኮቶች ሦስት አይነት ቀለማት የተቀቡበት ምክንያት አለው። የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንጸባርቁ ለማድረግ ነው።

የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው። እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሱም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው።

የምሥጢር በሩ ያለ ምክንያት አልተሠራም። አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው።

የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው።

አዎን፣ በአፈወርቅ ቤት ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

በዓሉ ግርማ

በዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – መነን (ሚያዝያ ፳፱፣ ፲፱፻፷፩)፤ ገጽ ፲፮-፲፯።

“በራሪ ወፎች” (የሥዕል እይታ)

“በራሪ ወፎች” – የሥዕል ኤግዚቢሽን

በሕይወት ከተማ

 

በየካቲት ወር፣ በብሔራዊ ሙዚየም ጋለሪ የስናፍቅሽ ዘለቀ “በራሪ ወፎች” የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ተዘጋጅቶ ነበር። ትዕይንቱንም ለአንድ ሰዓት ያህል ከአንድ ወዳጄ ጋር ተመልክተን ስንወጣ ራሷን ስናፍቅሽን በር ላይ አገኘናት።

ስለ ሥዕሎቿ አንዳንድ ነገሮችን አወራርተን እንዳበቃን፣ ስናፍቅሽ (ዐውደ ርዕዩን በማስመልከት ነው መሰለኝ) “ሰው የደገሰውን መጥተው ሲበሉለት ደስ ይለዋል” አለችን። ወዳጄ ግን፣ “አይ ሰው እንኳ ባይመጣ እኔስ እራሴ እበላዋለሁ” ብሏት ተሳሳቅን።

ስናፍቅሽ ዘለቀ በ1977 ዓ. ም. ከአዲስ አበባ የሥነጥበብ ት/ቤት በቀለም ቅብ ተመረቀች። በ1979 የመጀመሪያዋን የግል ኤግዚብሽን በአልያንስ (Alliance EthioFrançaise) አሳየች። በርካታ ዐውደ ርዕዮችንና የሥነ ጥበብ ውይይቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለማዘጋጀትም በቃች። እንዲሁም “ፏ ብዙነን” የተባለውን የሴቶች ሰዓሊያን ማህበር አቋቁማለች። በሕንድ ት/ቤትም (Indian National School) የሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ መምህርት ሆና ለረጅም ዓመታት አስተምራለች።

ስናፍቅሽ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ለሠላሳ አመታት ያህል ስታቀርብ የቆየች ባለሙያ ናት። በማህበራዊ ጉዳይ ባተኮሩ ስራዎቿም ስትታወቅ በተለይም የሴቶችን ትግል የሚያሳዩ በርካታ ሥዕሎችን ለእይታ አቅርባለች። በራሷም አገላለጽ “…ሴት ልጅ የቤተሰብ ኃላፊ ከሆነች እንደ እናትም ብዙ ኃላፊነት አለባት።  ልጅ ሲወለድ ብሩሽና ሸራ መቀመጥ የለበትም” ትላለች።

በአሁኑ ዐውደ ርዕይ ግን ስናፍቅሽ በከፊል አዲስ አትኩሮት የያዘች ይመስላል። እራሷ እንደነገረችኝም፣ ካለፈው አመት ጀምሮ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተለየ መልክ እየያዘ ሄዷል። “በጨለማ ውስጥ ብርሃንን፣ በመኖር ውስጥ አለመኖርን፣ በማጣት ውስጥ ማግኘትን … አብረው ተቆላልፈው ማየት ጀምርያለሁ” ትላለች።

እናም የሕይወት “ዙር ጥምጥም” (ሙሉ ክብነት) በብዛት እየታያት መምጣት እንደጀመረ ትናገራለች። ይህንንም ፍልስፍናዋን በሥዕሎቿ ላይ ለማሳየት እንደሞከረች ይታያል።

በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡት ወደ 40 ከሚጠጉ ሥዕሎቿ ውስጥ ግማሾቹ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ ግማሾቹ ደግሞ “ምናባዊ” (Abstract) ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በአዲሱ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተቀረጹት ደንገዝና ጨለም ብለው “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) የሆኑት ሥዕሎቿ ቀልቤን ስበውታል።

መቼም የሥዕል ፎቶ ቅጂዎች የዋናውን ሥዕል ግርማ ሞገስ እንደማይገልጹ የታወቀ ነው። የዚህም ዐውደ ርዕይ በብዛት የተሰራበት አክሪሊክ (Acrylic) ቀለም ደግሞ በተፈጥሮው በፎቶ ሲታይ ልጥፍ (Flat) የመሆን ባሕርይ አለው። በዚህ ምክንያት የሥዕሉን መልክ በትክክል ማሳየት የሚችል ምስል ማንሳት አስቸጋሪ ነው። እናም፣ ሁሌም ቢሆን ሥዕሎችን ራሳቸውን በአካል ሄዶ ማየት አጥብቆ ይመከራል።

እስቲ፣ ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹን “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) ሥዕሎቿን እንያቸው።

ይህ ሥዕል ጨለም ያለ ድባብ (Background) ላይ የተመሰረተ ሲሆን በቀጥታ መስመሮችና ክቦች ተገንብቶ የተለያዩ ቀለማትን በመስመር ፈርጆ ያሳያል። የቅርጾቹ ቀላልነት (Simplicity)፣ የክቦቹ አቀማመጥ፣ የመስመሮቹ ጥራት፣ እና የቅርጾቹ አነባበር (Depth) ደስ የሚል የመውደቅን ወይም የማሽቅልቆልን ስሜት ይሰጣል። ሠዓሊዋ አስቸጋሪ የሆነውን ጥቁር ቀለም ስትጠቀም ገጽታው ልጥፍ እንዳይሆንና ንብብር እንዲኖረው በተለያዩ ቀለማት መደገፏ ይታያል። ከሥዕሉ በታች በኩል የሚታየውን ጭስ ጠገብ ሰማያዊ ምሕዋሩን (Space) ያስተውሏል። ይህ ተንጠልጣይ ቦታ የመንሳፈፍን፣ የመምጠቅን ስሜት አሳድሮብኛል … ብቻ የሥዕል እይታ እንደተመልካች ይለያያልና ለእናንተ የተለየ ስሜት ይፈጥርባችሁ ይሆናል።

“መስመሮችና ቅርጾች በምሽት”

Acrylic on Canvas

100 x 75 cm


ይህኛውም ከላይ እንዳየነው በጥቁር ድባብ የተመሰረተ፣ ብዙ የተለያየ መጠን ያላቸውን ክቦች ያዋቀረ ነው። የተለያዩት ቀለሞች ግን እንደፊተኛው በመስመሮች የታገዱ ሳይሆን በነጻነት የሚፈሱ ናቸው። ሥዕሉም በውስጡ ውስብስብ ድርብርብነት (Layering) ይታይበታል። እነዚህ ድርብርብ ቀለማት ከክቦቹ ጋር ተዋህደው የሥዕሉን ሙሉነት ይገልጻሉ። እያንዳንዱ ክብ ሆነም ወፍ የራሱ የሆነ ገጽታ (Expression) በፊቱ ላይ ይታያል። ለምሳሌ፣ በመሀል ያለውን ትልቁን ክብ/ወፍ ብንመለከት፣ የወፉ አይን ውስጥ የሚታየው እይታ ምሰጣ ውስጥ መግባትን የሚገልጽ ይመስላል።

“በራሪ ወፎች”

Acrylic on Canvas

95 x 50 cm


ይህኛው ደግሞ በአፈርማ (መሬታዊ) ቀለማት ተገንብቶ አንድ ክብን በማማከል ወደ ውጭ የሚፈሱ (Radiating) መስመሮችን የያዘ ነው። የመስመሮቹ ጥራት አሁንም የሚደነቅ ነው። እዚህ ላይ ስናፍቅሽ የተጠቀመችው ስልት ቀለማቱን ከመደራረብ ይልቅ እያንዳንዱን “መስኮት” የተለያየ ቀለም ወይም “ጥለት” (Pattern) መስጠት ነው። ህብረ ቀለሙ በመስመሮቹ ቢታሰርም ከመስመሮቹ መፍሰስ ጋር በጋራ ሲታይ የተሟላ ሥዕል እንዲሆን አድርጎታል። የሥዕሉ አሰዳደር (Composition) እንዲሁም የመስመሮቿ አካሄድ ሌጣ ቢመስልም ምሕዋሩን በሚገባ ተጠቅማበታለች።

.

“ክብና መስኮቶች”

Acrylic on Canvas

95 x 71 cm


ይህ ሥዕል ከአሁኑ “ዙር ጥምጥም” የአሰራር ስልቷ ወጣ ብሎ የ“ሴትነት” እይታ የያዘ ይመስላል። ሥዕሉ የጠንካራ ሴትን ገጽታ የሚገልጽ ይመስላል። ሴቲቷ “ኮስታራነት” ተላብሳ ዓለሟን አሸንፋ በራሷ መንገድ መሄድን የመረጠች መስላ ትታያለች። አሁንም የሥዕሉ መስመሮች እንደተለመደው ግልጽ ናቸው። ይህችንም ሴት ለመሳል የተጠቀመችው እኒህኑ ጠንካራ መስመሮቿን ነው። ባጠቃላይ የሴትየዋን ፊት “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) በማድረግ ጠንካራ የፊት ገጽታ ለመፍጠር ችላለች። በሴቲቷ ፊት ላይ የሚታዩትን ቀጫጭን መስመሮች ያስተውሏል። በእሳታማ ቀለማት አጠቃቀሟም ተጨማሪ ሙቀት ለሥዕሉ ሰጥታዋለች።

.

.

“Concentration”

Acrylic on Canvas

92 x 62 cm


ይህኛውም የፊት ገጽን በቅርጽ እያሳየ በመሬታማ ቀለማት የተሰራ ነው። ጥሩ የብርሃንና ጥላ አጠቃቀም ይታይበታል። የእናትነት ገጽታ በሚገባ በመቀረፁ ደግነትንና እንክብካቤን በአንገቷና በአይኖቿ እናያለን። አሁንም የስናፍቅሽ አቀራረብ በተለየ ሁኔታ “ቅርጻዊ” ነው። በመስመሮችና በቅርጾች የምትፈልገውን ሁሉ በሥዕሎቿ ማስተላለፍን የተካነችበት ይመስላል።

.

.

.

“እናትና ልጅ”

Acrylic on Canvas

72 x 63 cm


የስናፍቅሽ የአሳሳል ጥንካሬ በ“ቅርጻዊ” ስልት ሸራዋን ማድመቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። መስመሮቿን በሚገባ ትስላለች። ቀለሞቿን ደግሞ አነባብራ ትጠቀማለች። ሰፋ ያለ ምሕዋር (Space) መፍጠርንም የግሏ አድርጋዋለች።

ዛሬም ቢሆን ስናፍቅሽ የምትሰራው በዚህ “ምናባዊ” (Abstract) ስልት ብቻ አይደለም። ዐውደ ርዕዩ ላይ በመጠኑ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ አንዳንዴም “ገጽታዊ” (Expressionist) የሆኑ ሥዕሎችም ለእይታ ቀርበዋል። እነዚህ ሥዕሎቿ ግን ከተለመደው የአሳሳል ስልት እምብዛም ወጣ ያላሉ በብዛትም “ጌጣዊ” (Decorative) የሚመስሉ ናቸው። የሰዎቹ ፊትና ገጽታ ተመሳሳይና ስሜት አልባ ይመስላሉ። የሥዕሎቿን ጥንካሬ እምብዛም አናይባቸውም።

እስቲ ከእነዚህ ሥዕሎች ለምሳሌ አንድ እንይ፦

“ወደ ገበያ”

Acrylic on Canvas

92 x 62 cm

.

በአዲስ መልክ እየተጠቀመችው ያለው “ቅርጻዊ” የሆነው “ዙር ጥምጥም” ስልቷ ግን ቀልብ ይስባል። በዚህ ስልት ክቦቿ እውነትም መስመር የያዙላት ይመስላሉ፤ የምትስላቸው ገጻዊ ሥዕሎችም እጅግ ገላጭ ናቸው።

ስናፍቅሽን ለምን ይህን አዲስ አቅጣጫ እንደቀየሰችም ጠይቄአት ነበር። “ምናልባትም በሰል ማለት ይሆናል … ለምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም … አሁን ግን የሚሰማኝ እንደሱ ነው” አለችኝ።

እግረ መንገዴን ስለ ጥቁር ቀለም አጠቃቀሟ ጠይቄአት ስትናገር፣ “ትምህርት ቤት እያለን ጥቁር ቀለምን እንድንጠቀም አያበረታቱንም ነበር። አንደኛ፣ ‘ያቆሽሻል’ ይሉናል፤ ሁለተኛ፣ የተለያዩ ቀለሞችን በመደበላለቅ የሚመጣ ስለሆነ እምብዛም በቀጥታ አንጠቀምበትም። አሁን ግን ለመድፈር ወስኜ እየሰራሁበት ነው። የተለያየ የጨለማ ደረጃም ላመጣበት ችያለሁ” ትላለች።

በመጨረሻም፣ ከስናፍቅሽ ጋር በሥዕል አርእስት አወጣጥ ዙርያ ተወያይተን ነበር። እኔም፣ “መጀመሪያ አርእስት አስበሽ ነው ሥዕሉን የምትሰሪው? ወይስ ከሰራሽው በኋላ ነው የምትሰጭው?” ብዬ ጠየኳት። እሷም በተራዋ፣ “እንደሁኔታው … አንዳንዴ መጀመሪያ፣ አንዳንዴ መሃል አንዳንዴም መጨረሻ ነው” አለችኝ።

የጥበብ ሰዎች በሥራቸው ፍልስፍና ላይ ብዙ ሲንገላቱ አያለሁ። የትኛው ይሆን የሚቀድመው … ጥበብን  መፍጠር? ወይስ ለመፍጠር ፍልስፍናን ማጠንከር? … አንድ የጥበብ ሥራ መልዕክት ሊኖረው የግድ ነውን? … ጥበብ ያለ ፍልስፍና ወይም መልዕክት ሌጣውን በራሱ ብቻ መደነቅስ ይችላል? … አንዳንድ ጊዜ “ሥዕሎች ምነው አርእስት ባይኖራቸው?” ያስብለኛል።

ስናፍቅሽ ብዙ የጥበብ ውይይቶችን እንደምታዘጋጅ፣ የህዝቡንም የሥዕል ንቃተ ኅሊና ከፍ ለማድረግ (እንደ መምህርነቷ) ሃላፊነት እንደሚሰማት ትናገራለች። ስለዚህም በዐውደ ርዕዮቿ ላይ በመገኘት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ተመልካች ያልገባውን ለማስረዳት እንደምትሞክር ገልጻልኛለች። የጥበብ ሰዎች የሥዕል ድግሳቸውን ስለሚቋደሱ ተመልካቾች ምን ያህል መጨነቅ እንዳለባቸው ያሳስበኛል።

ወደፊት ሥራዋ ወዴት እንደሚመራት ለማየት ጓጉቻለሁ።

.

ተጨማሪ

ሌሎች ሥዕሎቿን ለማየት

 ቃለመጠይቅ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ‹‹ሥዕልን ያን ያህል የተገነዘበ ማኅበረሰብ አለን ለማለት ያስቸግራል››

የኤግዚቢሽን ዘገባ ከሪፖርተር ጋዜጣ  በ‹‹በራሪ ወፎች›› ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ

“በራሪ ወፎች Catalogue” የካቲት 2009