“ሳታመኻኝ ብላኝ” (ወግ)

“ሳታመኻኝ ብላኝ”

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል

.

.

አያ ዥቦ ልጁ ሞተበትና ለነ እንኮዬ አህዩት “ልጄ ሞቷልና አላቅሱኝ” ሲል መርዶ ነጋሪ ላከ።

ተረጅዎቹም “እንግዲህ ሰምተን ብንቀር ይጣላናል ብንሄድም ይበላናል። እንዴት ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ምክር ዠመሩ። ነገር ግን “ቀርተን ከሚጣላን ሄደን ቢበላን ይሻላል” ብለው ተነስተው ልብሳቸውን አሸራርጠው ሄዱ።

ከለቅሶውም ቦታ እንደ ደረሱ አንደኛዋ ብድግ አለችና፣

“ምን አጥንት ቢሆን ይሰብራል ጥርስዎ

ምን ጨለማ ቢሆን እሾኽ አይወጋዎ

ምን ጥቍር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ

ያንን ጐራ ዞሮ ይሰማል ድምጥዎ

አሁን የርስዎን ልጅ ምን አገኘብዎ?” እያለች ሙሾ ታወርድ ዠመር።

እሱ ደግሞ ቀበል አለና፣

“አንችስ ደግ ብለሻል መልካም አልቅሰሻል

ይህ ሁሉ አዘንተኛ ምን ይብላ ብለሻል?” ሲል መለሰ።

እንዳልማራቸው ባወቁ ጊዜ እንግዲህ አለቀቀንም ምን ማድረግ ይሻለናል ብለው እነ እንኮዬ አህዩት ምክር ዠመሩ። አንዲት እናቷ የሞተችባት ውርንጭላ ከነርሱ ጋር ነበረችና ይህችን እንስጥና እንገላገል ብለው ሲነጋገሩ ግልገሏ አህያ ሰምታ፣

“ምነው እኔ ውርንጫ

ማ ይዞኝ በሩጫ” ብላ ተነስታ እልም አለች።

ከዚህ በኋላ ጭንቅ ያዛቸውና መቼስ ምን ይደረግ ለንቦጫችንን ሰጥተነው እንሂድ ብለው ተማከሩ። ወዲያው በል እንግዲህ የላይ የላይ ለንቦጫችንን ውሰድ አሉት። እሱም እንዳመለከቱት ለንጨጭ ለንጨጫቸውን ገነጣጠለና ለቀቃቸው።

በሦስተኛው ቀን ደግሞ እስቲ ዛሬ ሣልስቱ ነውና እመቃብሩ ላይ ደርሰን አያ ዥቦን ጠይቀን እንምጣ ብለው ቢሄዱ አያ ዥቦ ቀድሞ ከመቃብሩ ላይ ሲያለቅስ ደረሱ።

አያ ዥቦም ድዳቸውን ገልፍጠው ባየ ጊዜ፣

“ለካ የኔ ሐዘን ለናንተ ሰርግና ምላሽ ሆኖላችኋልና የኔ ልጅ ትላንትና ሞቶ ዛሬ እናንተ እየተሳሳቃችሁ የመጣችሁት በምን ምክንያት ነው?” ብሎ ተቆጣና ለወገኖቹ “ኧረ በሉ አንድ አንድዋን እየዘረጠጣችሁ ጣሉልኝ” አላቸው።

ከዚህ በኋላ የዥብ ወገን ያህያን ልጅ እየገነጣጠለ ጣለ ይባላል።

“አያ ዥቦ ሳታመኻኝ ብላኝ”

.

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል

.

[ምንጭ] – “እንቅልፍ ለምኔ”። 1952 ዓ.ም። ገጽ 43-44።

 

“ሳይቸግር ጤፍ ብድር” (ወግ)

“ሳይቸግር ጤፍ ብድር”

ከሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

.

አንድ ሰሞን ሰባት ገጽ ከሩብ የኾነ የአንድ ሥራ-ሀላፊን ያማርኛ ጥያቄና መልስ (ቃለመጠይቅ) ጽሑፍ አንብቤ ነበር። ሃያ ሦስት የእንግሊዝኛ ቃላት/ሐረጎች ተቀላቅለውበት አገኘሁ! ይህ የጽሑፉ 1.06% መሆኑ ነው።

ታዲያ “ይቺ ምን አላትና ሰው ታስተቻለች?” ያሰኝ ይሆናል።

ጉዳዩ ግን መጠኑ አይደለም – ሌላ ነው። አንደኛ፣ ሰው ሀላፊ ኾኖ ባደባባይ ንግግሩ እንግሊዝኛን ካማርኛ እያቃየጠ ሲናገር ላድማጮቹ ኹሉ አብነት ይኾናል። ኹለተኛ፣ አቀያይጦቱ “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” መሆኑ ነው።

ቀጥዬ ከጽሑፉ የለቀምኩዋቸውን አማርኛና-እንግሊዝኛ ቅይጥይጥ ንግግር አመጣለሁ።

.

ቅይጡ ቃል                በጽሑፉ ያለው አጠቃቀም       (በጎ የሚሆነው)

Albergo             “አንድ ቦታ ነበር ቤርጎ የያዝነው”   (አንድ ቦታ ነበር ሆቴል የያዝነው)

Already              “ኦረዲ ወስነናል”   (ዱሮ ወስነናል)

Chair                  “ቸር ማድረጉንም”   (ስብሰባውን መምራቱንም)

Chairperson       “ለዋናው ቸርፐርሰን”   (ለዋናው ሊቀመንበር)

Cross-check            “ይህንኑ ክሮስቼክ አደረግን”   (ይህንኑ አመሳከርን)

Excessive Force         “ይህ ኤክሴሲቭ ፎርስ ነው”   (ይህ መጠኔለሽ ኃይል ነው)

Extension                  “ለምን ኤክስቴንሽን አይጠይቁም”   (ለምን የጊዜ ተራዝሞ አይጠይቁም)

Information               “ኢንፎርሜሽን በሚስጥር እያወጣ”   (መረጃ በሚስጥር እያወጣ)

Interrogate                “ኢንተሮጌት አድርጓቸዋል”   (እሳቸውንም ጠይቋቸዋል)

I Think                       “አይቲንክ”   (ይመስለኛል)

Leads                         “የካሴት ሊዶችን ለማትረፍ”   (የካሴት መረጃዎችን ለማትረፍ)

Legal Adviser         “ሌጋል አድቫይዘር በመሆን”   (የሕግ አማካሪ በመሆን)

Organization          “ከማንም ኦርጋናይዜሽን ጋር”   (ከማንም ድርጅት ጋር)

Pressure                  “ፕሬዠሩን በመፍራት”   (ጫናውን በመፍራት)

Property Damage        “የደረሰባቸውን የፕሮፐርቲ ዳሜጅ”   (የደረሰባቸውን የሀብት ጥፋት)

Region                     “የደቡብ ሪጅን”   (የደቡብ ቀጣና/ክፍለ ሀገር)

Replace                    “በሕጉ ምክትሉ ሪፕሌስ ያደርጋል”   (በሕጉ ምክትሉ ይተካል)

Report                     “የናንተን ውሳኔ ሪፖርት”   (የናንተን ውሳኔ ዘገባ)

Resign                      “አንዱ ሪዛይን አድርጎ”   (አንዱ ሥራውን ለቆ)

Scholarship             “እስኮላርሺፕ አግኝቶ ነው”   (የትምህርት ድጎማ አግኝቶ ነው)

Statement                “የራሴን ስቴትመንት ሳደርግ”   (የራሴን ቃል ስሰጥ)

Supreme Court       “ሱፕሪም ኮርት ቢሮ ስንደርስ”   (ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢሮ ስንደርስ)

Trust                         “ትረስት ለማድረግ ሞክረን”   (ለማመን ሞክረን)

.

እዚህ ላይ በተጠቅሞቴ (ለምሳሌ) Albergoን “ሆቴል” ብያለሁ። በፈረንጅኛነቱ በቅየማ ሊያስከስስ ይችላል። ይህ ቃል ግን አማርኛ ኾኑዋል።

ለምሳሌ “Apple” ባማርኛ ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ ማንም “ፖም” ይላል – ከፈረንሳይኛ በመጣ ቃል። በዚህ መልክ ብዙ የውጭ ቃላት ወደ አማርኛ መጥተው፣ በዘመን ብዛት አማርኛ የኾኑ አሉ – ሆቴልም የዚያ ዐይነት ነው።

ከላይ የተዘረዘሩት የሃያ ሦስቱ ፈረንጅኛ ቃላት/ሐረጎች ጉዳይ ግን ሌላ ነው … ሀሳባቸው በአማርኛ በቀላሉ ይገኛልና።

.

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው

(1999 ዓ.ም)

.

[ምንጭ] – አንድምታ ክበብ። ቁጥር 6። የካቲት 1999። ገጽ 8።

 

“አበባየሆሽ” (ሥነ ቃል)

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን

ጌቶች  አሉ ብለን

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን

እሜቴ አሉ ብለን

እውዬ (እኸ) እዋውዬ ካሽከር ተዋውዬ
ጌቶች አሉ ብዬ ገባሁ ሰተት ብዬ

አበባየሆሽ (ለምለም)

ባልንጀሮቼ (ለምለም) ቁሙ በተራ (ለምለም)
እንጨት ሰብሬ (ለምለም) ቤት እስክሰራ (ለምለም)
እንኳን ቤትና (ለምለም) የለኝም አጥር (ለምለም)
እደጅ አድራለሁ (ለምለም) ኮከብ ስቆጥር (ለምለም)
ኮከብ ቆጥሬ (ለምለም) ስገባ ቤቴ (ለምለም)
ትቆጣኛለች (ለምለም) የንጀራ እናቴ (ለምለም)
የንጀራ እናቴ (ለምለም) ሁለ’ልጅ አላት (ለምለም)
ለነሱ ፍትፍት (ለምለም) ለኔ ድርቆሽ (ለምለም)
ከሆዴ ገብቶ (ለምለም) ሲንኮሻኮሽ (ለምለም)
አበባማ አለ (ለምለም) በየውድሩ (ለምለም)
ባልንጀሮቼ (ለምለም) ወልደው ሲድሩ (ለምለም)
እኔ በሰው ልጅ (ለምለም) ማሞ እሹሩሩ (ለምለም)

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ

ከገዳይ ጋራ (ለምለም) ስጫወት ውዬ (ለምለም)
ራታችንን (ለምለም) ንፍሮ ቀቅዬ (ለምለም)
ድፎ ጋግሬ (ለምለም) ብላ ብለው (ለምለም)
ጉልቻ አንስቶ (ለምለም) ጎኔን አለው (ለምለም)
ከጎኔም ጎኔ (ለምለም) ኩላሊቴን (ለምለም)
እናቴን ጥሯት (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም)
እሷን ካጣችሁ (ለምለም) መቀነቷን (ለምለም)
አሸተዋለሁ (ለምለም) እሷን እሷን (ለምለም)
አባቴን ጥሩ (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም)
እሱን ካጣችሁ (ለምለም) ጋሻ ጦሩን (ለምለም)
አሸተዋለሁ (ለምለም) እሱን እሱን (ለምለም)

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ

እቴ አበባ ሽታ አበባዬ (አዬ እቴ አበባዬ)
እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ (አዬ እቴ አበባዬ)
ጥላኝ ሄደች ባምሌ ጨለማ (አዬ እቴ አበባዬ)
እቴ አበባሽ እቴ እያለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ጋሻ ጦሬን ወስዳ አሸጠቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
እንኳን ጋሻ ይሸጣል በሬ (አዬ እቴ አበባዬ)
ከናጥንቱ ከነገበሬ (አዬ እቴ አበባዬ)

ሄሎ ሄሎ የገደል ሄሎ (አዬ እቴ አበባዬ)
ማን ወለደሽ እንዲህ መልምሎ (አዬ እቴ አበባዬ)
ወለደቺኝ መለመለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ላፈንጉስ ዳርኩሽ አለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ካፈንጉስ አምስት ወልጄ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ዳኛ ያውም መልከኛ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ቄስ ቆሞ ቀድስ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ቂል ንፍሮ ቀቅል (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዷ ሴት የሺመቤት (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ሞኝ ቂጣ ለማኝ (አዬ እቴ አበባዬ)

ይሸታል ዶሮ ዶሮ  የማምዬ ጓሮ
ይሸታል ጠጅ ጠጅ  የጌቶችም ደጅ

ሻሽዬ (እኸ) ሻሽ አበባ
ደሞም ሻሽ አበባ
እራስ ዩም ግቢ ይታያል ሲኒማ
የማነው ሲኒማ ያፀደ ተሰማ

ሻሽዬ (እኸ) ሻሽ አበባ
ደሞም ሻሽ አበባ
ትራሷም ባላበባ
ፍራሹም ባላበባ
እርግፍ እንደወለባ

የማምዬ ቤት (ለምለም) ካቡ ለካቡ (ለምለም)
እንኳን ውሻቸው (ለምለም) ይብላኝ እባቡ (ለምለም)

ከብረው ይቆዩን ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሃምሳ ጥገቶች አስረው
ከብረው ይቆዩን ከብረው

ከብረው ይቆዩን በፋፋ
የወለዱት ልጅ ይፋፋ
ከብረው ይቆዩን በስንዴ
ወንድ ልጅ ወልደው ነጋዴ
ከብረው ይቆዩን ከብረው

(የህዝብ ግጥም)

(ምስል)  ሕይወት ከተማ 

ዘመን ቊጥርና ስሌት

“ዘመን ቊጥርና ስሌት”

(ክፍል 1) 

በኅሩይ አብዱ

.

የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች ጥንታዊ ሰነዶችን እንደ መረጃ ሲጠቀሙ፣ ሰነዱ የተጻፈበትን ጊዜ ማወቅ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር መንገዶች ካሁኑ ስለሚለዩ የጽሑፉን ዘመን በቀላሉ ማወቅ ያዳግታል። ለምሳሌ በ14ኛው ክ/ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ ላይ የተጻፈው የዐጼ ዓምደ ጽዮን ታሪክ እንዲህ ይላል፣

ዓምደ ጽዮን ንጉሠ ኢትዮጵያ … በዓሠርቱ ወሠመንቱ ዓመተ መንግሥቱ እምዘ ነግሠ ወዓመተ ምሕረትሂ ፭፻፲ወ፮።

[ትርጉም] የኢትዮጵያ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን … በነገሠ በ 18 ዓመት፣ በ516 ዓመተ ምሕረት።

(516 ዓመተ ምሕረት?! ይህ እንዴት ይሆናል? ያኔ የአክሱም ዘመን አልነበር? የጸሓፊው ስሕተት ነው ወይስ ያልተረዳነው ነገር አለ?)

ሌላ ምሳሌ ደግሞ፣

በ፴ወ፭ ዓመተ ምሕረት ወበመዋዕሊሁ ለንጉሥነ ዘርአ ያዕቆብ … ወእምአመ ነግሠ በ፳ወ፭ ዓመት ..

[ትርጉም] በ35 ዓመተ ምሕረት በንጉሣችን በዘርአ ያዕቆብ ዘመን … ከነገሠ በ25 ዓመት

(የ15ኛው ክ/ዘመን አፄ ዘርአ ያዕቆብስ ወደ አንደኛው ክ/ዘመን ምን ሊሰራ ሄደ?)

ይባስ ብሎ ሌላ በ14ኛ ክ/ዘመን የተዘጋጀ ብራና፣

ዓመተ ምሕረት በ፷፻፰፻፸፬ … (በ6874 ዓመተ ምሕረት)

(ይህንስ ማለቱ ስምንተኛው ሺ የሚያስብል ነው።)

እነዚህን አደናጋሪ የዘመን አቆጣጠር ምሳሌዎች ወደፊት ለመፍታት ይሞከራል። በመጀመርያ በዚህኛው ክፍል ስለ ግዕዝ ቁጥሮችና ስሌቶች አጭር ገለጻ አቀርባለሁ።

በሚቀጥሉት ወራት በሚቀርቡ ክፍሎች ደግሞ ከዘመነ አክሱም እስከ 20ኛው ምዕት ዓመት የዘመን አቆጣጠር ታሪካዊ ቅኝት ቀርቦ፣ በመጨረሻም የተወሰኑ የዘመን አቆጣጠር ዓይነቶች ከታሪካዊ ምሳሌዎችና የሒሳብ ስሌቶች ጋር ይታያሉ።

 .

የግእዝ ቊጥር (አኀዝ)

በግእዝ ሰዋስው አኀዝ የተባለ ራሱን የቻለ ክፍል አለ። ስለ አኀዝ ሰፋ ያለ ትንተና ከምናገኝባቸው ቀደምት ሥራዎች መካከል፣ አባ ገብረ ሚካኤል በ1850ዎቹ አዘጋጅተውት በኋላ በ1872 ዓ.ም. በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ አርታዒነት በላዛሪስት ሚሽን ማተምያ ቤት ከረን የታተመው መጽሐፈ ሰዋስው ነው።

በ1882 ዓ.ም. በአለቃ ታዬ የተዘጋጀውም መጽሐፈ ሰዋስው ተመሳሳይ ትንተና ስለ አኀዝ ምንነት ያቀርባል። ጽሑፉም እንደሚለው አኀዝ መጀመሪያ፣ መቋሚያ፣ መያዣ ዋስ፣ ቊጥር እና ድምበር ተብሎ ይተረጎማል። የአኀዝንም ፍቺ በአንድምታ የትንተና ስልት እንደዚህ አቅርበውታል።

aleqa taye
አለቃ ታየ ገብረማርያም

መጀመሪያ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ ሁሉ በቊጥር ይጀመራል ይጨርሳልና መጀመሪያ ተባለ።

አኀዝን መቋሚያ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ የነገር ሁሉ መቋሚያ አለው፤ አኀዝም የነገር ሁሉ መቋሚያ ነውና…።

መያዣ ዋስ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ በመያዣ በዋስ ያለ እንዳይጠፋ በቊጥርም ያለ አይጠፋምና መያዣ ዋስ ተባለ።

አኀዝን ቊጥር ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ በቊጥር የተወሰነ ይወሳል። ያልተወሰነ ይረሳልና ቊጥር ተባለ።

ድምበር ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ ድምበር የእህል የሣር መለያ ነው። ቊጥርም የሁሉ መታወቂያ ነውና ድምበር ተባለ። አንድም ከአኀዝ ወዲያ ቅጽል የለምና ድምበር ተባለ።”

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በታላቁ መጽሐፋቸው፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ስለ አኀዝ ጠለቅ ያለ ትንተና ያቀርባሉ። ስለ የተለያዩ የአኀዝ ዓይነቶች ሲያስረዱ፣ አኀዝ በጥቅሉ መዘርጋት፣ መተርተር፣ መከፈል፣ መታጠፍ፣ መጠቅለል እንደሚችል ይገልጻሉ። ሲተነተኑም፣

Kidane Photo
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ

መዘርጋት፣ ብዛትንና ስንትነትን እንደ ነዶና እንደ ችቦ አስሮ ሰብስቦ የሚያሳይ የጅምላ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ ፩፣ ፪፣ ፲፣ እንዲሁ።

መተርተር፣ ስንትነታቸው ከታወቀ ከብዙዎች ማኽል ስንተኛነትን ለይቶ የሚያሳይ የተራ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ ፩ኛ፣ ፪ኛ፣ ፲ኛ፣ እንዲሁ።

መክፈል፣ የክፍሎችን ስም እንደ ተራ ቊጥር እየለየ በየማዕርጉ የሚያሳይ ክፋለዊ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ መንፈቅ፣ ሣልሲት፣ ራብዒት።

ማጠፍ፣ ጅምላውን ቊጥር ዐጥፎ ደርቦ እያሳየ በመንታ መንገድ የሚወስድ ያጸፋ ቊጥር ነው። ምሳሌ፣ አሐዳት፣ አው ካዕበተ አሐዱ፣ ፩ ዕጽፍ። ክልኤታት፣ አው ካዕበተ ክልኤቱ፣ ፪ ዕጽፍ፣፬ ነጠላ፤ ወከማሁ።

መጠቅለል፣ እንዳራቱ ክፍሎች አኀዝ ሳይኖረው፣ በቅጽልነቱ ማነስና መብዛት ሕጸጽና ምልአት የሚያሳይ፣ የአኀዝ ቅጽሎች ሰብሳቢና ከታች የሚኾን መድበል ቊጥር ነው፤ ያውም ኅዳጥ ብዙኅ ኵሉ፣ ይህን የመሰለ።

የግእዝ ቊጥሮችንም ከአንድ እስከ ምእልፊት (መቶ ሚልዮን) ይዘረዝሩና፣ ከተፈለገም እስከ እልፍ  ምእልፊት (ትሪልዮን)  … እንዲሁም ከዛም በላይ መቊጠር (መጻፍ) እንደሚቻል ያስረዳሉ። አለቃ ኪዳነወልድ ከአንድ (1) እስከ እልፍ ምእልፊት (በአሁኑ አቆጣጠር ትሪልዮን 1‚000‚000‚000‚000) በግእዝ አኀዝ ለመጻፍ እንደ ቊጥር የሚያገለግሉ አስራ ዘጠኝ የተለያዩ ምልክቶችን ተጠቅመዋል። እነዚህም በአሁኑ ባላቸው መልክ የሚከተሉት ናቸው።

፩ ፪ ፫ ፬ ፭ ፮ ፯ ፰ ፱ ፲ ፳ ፴ ፵ ፶ ፷ ፸ ፹ ፺ ፻

(1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 20 30 40 50 60 70 80 90 100)

እነዚህን 19 ምልክቶች በተለያየ መልክ በማጣመርም ሌሎች ቁጥሮችን መፍጠር ይቻላል።

ለምሳሌ ፳፻፲፯፣ 2017 (20 መቶ እና 10 እና 7) ይሆናል።

ስለዚህ የግዕዝ የቊጥር ስርዓት በ19 ምልክቶች ላይ የተመሰረተ ነው (በአንፃሩ በዓለም በሰፊው የተሰራጨው የሂንዱ-አረብ የቊጥር ስርዓት አስር ምልክቶችን ይጠቀማል።)

የግዕዝ የቊጥር ስርዓት ለዜሮ ቊጥር ምልክት የለውም፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ ለአስር፣ ለሀያ … እስከ መቶ ላሉት ቁጥሮች ተጨማሪ ምልክቶች ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ የዜሮ ምልክት በቁጥሩ ስርዓት ውስጥ ባይኖርም፣ የዜሮ ጽንሰ ሐሳብ ግን ለብዙ መቶ ዓመታት አልቦ (ሲያጥር አል ወይም ) በሚለው ቃል ውስጥ ተካቶ እናያለን፣ በተለይ የማካፈል ስሌት ውጤቶች ውስጥ።

.

የቊጥሮች መልክ መቀያየር

ከላይ የሚታዩት ያሁኑ ዘመን የቊጥር ምልክቶች በመደበኝነት በዚህ ቅርጻቸው የጸኑት በ19ኛው ክ/ዘመን ለኅትመት ሲባል በብረት መቀረጽ ሲጀምሩ ነው፣ አሁን ደግሞ በኮምፕዩተር ፕሮግራሞች ያንኑ መልክ ይዘው ቀጥለዋል። ከታች የቀረበው ሰንጠረዥ የተወሰኑ የግዕዝ ቁጥሮችን የጊዜ ሂደት ለውጥ ያሳያል።

Hiruy Numbers Evolution

ከሰንጠረዡ ማየት እንደሚቻለው በዋነኝነት በጊዜ ሂደት መልካቸው ሊያሳስት የሚችለው ቊጥር 1 እና 4፣ እንዲሁም ቊጥር 6 እና 7 ናቸው።

የአክሱም ዘመን፣ የ14/15 ምዕት ዓመት እና በ17ኛ ክ/ዘመን ሉዶልፍ ያስቀረጸው ቊጥር 1 ያሁኑን ዘመን ቊጥር 4 (፬) ይመስል ነበር፣

የቀድሞው ቊጥር 4  ሦስት ማዕዘናዊ ነበር።

ስለዚህ ሁለቱን ለመለየት ሲባል ያሁኑ ዘመን ቊጥር 1 (፩) ከላዩ ትንሽ ቅጥያ ተጨምሮለታል።

የአክሱም ዘመን፣ የ14/15 ምዕት ዓመት እና በ17ኛ ክ/ዘመን ሉዶልፍ ያስቀረጸው ቊጥር 6 ያሁኑን ዘመን አነስተኛ ቊጥር 7 (፯) ይመስል ነበር፣ ስለዚህ ሁለቱን ለመለየት ሲባል ያሁኑ ዘመን ቊጥር 6 (፮) የስረኛው ቅጥያ ወደ ቀለበት ተቀይሯል።

 .

የሒሳብ ስሌቶች

በጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት ባሕረ ሐሳብ የሚባል የዕውቀት ክፍል አለ። የትምህርቱም ዓላማ ከዓመት ዓመት ተንቀሳቃሽ የሆኑ በዓላትና አጽዋማት (ፋሲካ፣ የሁዳዴ ጾም … ወዘተ)  መቼ እንደሚውሉ ማስላት ነው። የባሕረ ሐሳብ ዐዋቂ ለመሆን የሚያስፈልገው የአራቱ መደብ የቊጥር ስሌት (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈል) እንዲሁም የአንዳንድ የዘመን መለኪያ የስሌት ቃላትን ትርጉም መረዳት ነው።

የስሌትን አጠቀላይ ተግባር ለመግለጽ የተለያዩ የግዕዝና የአማርኛ ቃላት በሥነ ጽሑፍ ይገኛሉ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፣

ቈጠረ፣ ቀመረ፣ ሠፈረ፣ መጠነ፣ ሐሰበ (ዐሰበ) – ሒሳብ፣ አሰላ – ስሌት፣ …

በተጨማሪም፣

በዘተአምር (እንድታውቅ)፣

አእምሮ አዝማን (ዘመንን ማወቅ)፣

ትእኅዝ (ትይዛለህ)፣

ተኀሥሥ (ትፈልጋለህ፣ ትሻለህ) … የሚባሉ ሙያዊ ቃላቶችም አሉ።

የስሌቱ ውጤት እንዲህ ይሆናል ለማለት ደግሞ፣

ይዔሪ (ይተካከላል፣ እኩል ይሆናል)፣

ይከውነከ (ይሆንልሃል) … የመሰሳሉትን እናገኛለን።

ከታች ያለው ሰንጠረዥ አራቱ መደበኛ የቊጥር ስሌቶች (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈል) በግዕዝ እና አማርኛ የባሕረ ሐሳብ ብራናዎች በምን ቃላት እንደሚገለጹ ዝርዝር ያቀርባል።

Terms Table

.

ማካፈል

በባሕረ ሐሳብ ትምህርት በመደጋገም የምናገኘው ስሌት ማካፈል ነው፤ በተለይም መግደፍ ለሚባለው ስሌት በጣም አስፈላጊ ነው። ማካፈልን በዘመናዊ መልኩ ስናየው፣ አንድ ቊጥር በሌላ ሲካፈል የማካፈሉ ውጤት ድርሻ (quotient) እና ቀሪ (remainder) ይሰጣል።

ለምሳሌ ሰላሳን በሰባት ብናካፍል

Division Figure

የማካፈሉ ውጤት – ድርሻ አራት (4) ይደርስና (4 × 7 =28) ቀሪው ሁለት (2) ይሆናል።

.

መግደፍ 

በባሕረ ሐሳብ ትምህርት ላይ መግደፍ የሚባል ከአራቱ መደብ የቊጥር ስሌት ትንሽ ለየት ያለ የሒሳብ ስሌት አለ። መግደፍ ማለት አንድን ቊጥር በሌላ አካፍሎ የሚተርፈውን ቊጥር (ቀሪ) እንደ ውጤት መያዝ ነው። የላይኛውን ምሳሌ ከእንደገና ብናይ፣ ሰላሳን (30) በ ሰባት (7) መግደፍ ቢያስፈልግ፣ መጀመርያ ሰላሳን በሰባት እናካፍላለን – የዚህም ውጤት አራት ይደርስና (4 × 7 =28) ቀሪው ሁለት (2) ይሆናል።

ስለዚህ ቀሪው ሁለት (2)፣ ሰላሳን በሰባት መግደፍ ለተባለው የሒሳብ ስሌት ውጤት መሆኑ ነው። በዘመናዊ የሒሳብና የኮምፒዩተር ስሌት መግደፍ Modulo (MOD) ከሚባለው ስሌት ጋር አቻ መሆኑ ነው።

የመግደፍን ውጤት የሚተነትኑ ቃላትም አሉ፤

ጥንቁቀ ተከፍለ (በትክክል ተከፍሏል – ቀሪ የለውም ለማለት)፣

ወዘተርፈከ (የተረፈህም)፣

ወዘዘኢከለ (ያልበቃውም – የተረፈውም)፣

እስከ ትዌድእ (እስከ ትጨርስ ድረስ … ‹ማካፈሉን›)፣ (ይህን ያህል) …ደርሶ …(ይህን ያህል) ይቀራል፣ ይተርፋል ….

መግደፍ በሰፊው በባሕረ ሐሳብ ስሌቶች ውስጥ፣ እንዲሁም ከ16ኛ ክ/ዘመን ጀምሮ በተስፋፋው በዓውደ ነገሥት የዕጣ-ፈንታ ስሌት ውስጥም ይገኛል።

.

መጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት፣  … መጠነ _ _ _

ከማካፈል ስሌት ጋር በተገናኘ፣ ቀሪው እላይ እንደታየው መግደፍ ለተባለው ስሌት ሲጠቅም፣ ድርሻው ደግሞ አሁን ለምናያቸው መጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት … ስሌቶች ይጠቅማል። መጠነ ሳብዒት የአንድን ቊጥር በሰባት የማካፈል ድርሻ ሲይዝ፣ መጠነ ራብዒት ደግሞ የአንድን ቊጥር በአራት የማካፈል ድርሻ ይወስዳል። የላይኛውን ምሳሌ ከንደገና ብናይ፣

የሰላሳ መጠነ ሳብዒት፣ ሰለሳን በሰባት አካፍሎ (30 ÷ 7፣ ድርሻው 4፣ ቀሪው 2)  ድርሻውን አራት (4) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰለሳ መጠነ ሳብዒት አራት (4) ነው።

የሰላሳ መጠነ ራብዒት፣ ሰለሳን ባራት አካፍሎ ድርሻውን ሰባት (7) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰለሳ መጠነ ራብዒት ሰባት (7) ነው።

ይህ መጠነ — የሚለው ስሌት ከአራት እና ሰባት በተጨማሪ ለሌላ ቁጥሮችም ማስላት ይቻላል። ለምሳሌ፣ መጠነ ሳድሲት በስድስት የማካፈልን ድርሻ ይይዛል። የሰላሳ መጠነ ሳድሲት (30 ÷ 6፣ ድርሻው 5፣ ቀሪው 0) ድርሻውን አምስት (5) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰላሳ መጠነ ሳድሲት አምስት (5) ነው።

.

(ውጤቱ) እንዲህ ከሆነ … ይህን አድርግ … 

አለዚያ … ያንን አድርግ

በዘመናዊ የሒሳብና የኮምፒዩተር ስሌት Conditional IF ከሚባለው ስሌት ጋር አቻ መሆኑ ነው።

If 1 Then  Do A,

If 2 Then  Do B …

Else … Do X

የአንድ የመግደፍ ስሌት ውጤት ከታወቀ በኋላ፣ እንደውጤቱ ዓይነት የተለያዩ የድርጊት ምርጫዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ በባሕረ ሐሳብ፣ መስከረም 1 በምን ዕለት እንደሚውል በሚደረገው ስሌት፣ ድምሩ በሰባት ይገደፍና፣ ቀሪው ውጤት አበቅቴ ፀሐይ ተብሎ ይያዛል። የሚገደፈው በሰባት ስለሆነ ያሉትም ምርጫዎች ሰባት ይሆናሉ። ሰነዱ እንደሚለው፣

            ወእምዝ ትገደፍ በበ፯ ወዘተረፈከ ውእቱኬ አበቅቴ ፀሐይ።

(ከዛም በ7 ትገደፋልህ፤ የተረፈህም (ውጤት) አበቅቴ ፀሐይ ነው።)

ለእመ ኮነ ኍልቈ አበቅቴ ፀሐይ

የአበቅቴ ፀሐይ ልኬት (ቊጥር) 1 ከሆነ)

ይከውን ቀዳሚተ ሠርቀ መስከረም በዕለተ ረቡዕ

(መስከረም 1 ረቡዕ ዕለት ይሆናል (ይውላል)።)

       ለእመ ኮነ ኍልቈ አበቅቴ ፀሐይ

(የአበቅቴ ፀሐይ ልኬት (ቊጥር) 2 ከሆነ)

 ይከውን ቀዳሚተ ሠርቀ መስከረም በዕለተ ኀሙስ

(መስከረም 1 ሐሙስ ዕለት ይሆናል (ይውላል)።)

… እያለ እስከ ቊጥር ሰባት ድረስ ይዘልቃል።

ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ባሳተሙት ሐተታ መናፍስት ወዓውደ ነገሥት ደግሞ፣ ለምሳሌ ሓሰበ ኑሮ ወዕድል የሚለውን ክፍል ብንወስድ፤ በመጀመርያ፣ ‹ስምና የእናትን ስም በ፱ ግደፍ› ይላል። የሚገደፈው በዘጠኝ ሰለሆነ ያሉትም ምርጫዎች ዘጠኝ ናቸው። ከዛም እንደ ሎተሪ፣

፩፤ ሲወጣ በሹመት ይኖራል።

፪፤ በንግድ ይኖራል።

በዙረት ይኖራል።

በእጀ ስራ ይኖራል

በወታደርነት ይኖራል።

በብክንክን ይኖራል።

በቤተ መንግሥት ይኖራል።

በዙረትና ልፋት ይኖራል።

በንግድና በእርሻ ይኖራል።›

.

ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገደብ (ወሰን)

የአንድ ስሌት ውጤት ከዚህ ቊጥር መብለጥ ወይንም ከዚህ ቊጥር ማነስ የለበትም፣ የሚለውን ሐሳብ ለማስረዳት በባሕረ ሐሳብ ትምህርት የሚከተሉት ቃላት ይገኛሉ። ዝቅተኛው ገደብን (በሒሳብ እና ኮምፕዩተር ትምህርት Lower Limit) ለመግለጽ፣

ኢይውኅድ (አይቀንስም)፣

ኢይወርድ (አይወርድም)፣

ኢይቴሐት (አያንስም)፤

ከፍተኛውን ገደብ (በሒሳብ እና ኮምፕዩተር ትምህርት Upper Limit) ለመግለጽ ደግሞ፣

ኢይበዝኅ (አይበዛም)፣

ኢይዐዱ (አያልፍም)፣

ኢይትሌዐል (አይተልቅም)።

እላይ ካየናቸው ከአራቱ መደበኛ ስሌቶች፣ ከመግደፍመጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት …፣ ከ ‹(ውጤቱ) እንዲህ ከሆነ … ይህን አድርግ‹ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገደብ› በተጨማሪ ሌሎች የሒሳብ ስሌቶችና ብያኔዎች አሉ።

ሁሉንም ለመዘርዘር እና ለመተንተን ግን ሰፋ ያለ ጥናት ያስፈልጋል። የ14ኛው ክ/ዘመን የባሕረ ሐሳብ ሊቅ እንዳለው፣

ዘንተ ዕቀቡ

በጥንቃቄ ሐስቡ 

ጥያቄ አዝማን ከመ ትርከቡ። 

(የዘመንን ምርመራ ታገኙ ዘንድ፣ ይህንን ያዙ፤ በጥንቃቄ አስሉ።)

.

ኅሩይ አብዱ

ሐምሌ ፳፻፱

“መጽሐፈ ጨዋታ” (ቅንጫቢ)

“መጽሐፈ ጨዋታ” (ቅንጫቢ)

አለቃ ዘነብ

(አንድምታ መጻሕፍት – 2010 ዓ.ም – ገጽ 27-30። )

.

[ይሄ ድርሰት ከ150 አመታት በፊት የተጻፈ ውብ የአማርኛ ወግ መጽሐፍ ነው … ለቅምሻ ያህል ከአዲሱ የአንድምታ እትም እነሆ  …]

.

ክፍል 1

እግዚአብሔር እስቲሻር ሚካኤል እስቲሞት ምነው በኖርሁኝ? ገብርኤል ሲያንቀላፋ ሩፋኤል ሲደክም ሐሰተኛው ዲያብሎስ ንስሐ ይገባል።

ክረምት ሲመጣ ሰማይ እንዲከብድ የጠሉትም ሰው ሲመጣ እንደዚያ ይከብዳል። ዘወትር ከሚያጋድል አህያ ተሸክሞ መሄድ ይሻላል። ከማያስተካክል መላክተኛ የማለዳ ወፍ ትሻላለች ምነው ቢሉ ንጋቱን ትነግራለችና።

ድንጋይና ጭቃ ቢቀጣጠሉ ታላቅ ቤት ረጅም ቅጥር ይሆናሉ። እናንተም መሬታውያን ሰዎች እንደዚህ ብትረዳዱ ጥበባችሁና ኀይላችሁ ከሰማይ በደረሰ።

ኮሶና ክረምት ፊት ይመራል ኋላ ግን ደስ ያሰኛል። ድሪ ምንድር ነው ገንዘብን ለመቆራኘት የተሠራ ሰንሰለት ነው። እሬት መብላት ቢለመድ ባልተለቀቀም ነበር። ዝሙትም ላለመደው ሰው እንደዚህ ነው።

ጣዝማ እጅግ ብልሕ ናት። መሬት ቀዳ ገብታ እንደዚያ ያለ መድኃኒት የሚሆን ማር ትሠራለች። ምነው እናንተ ሰዎች ወይ ከፈጣሪ ወይም ከሰው ብልሐትን አትፈልጉምን?

የምሥራች ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ የሰው ልብ በደስታ ባሕር ይሰጥማል። እርጎን ከፍቶ ቢተውት ዝንብና ድመት ይጫወትበታል። አገርንም አቅንቶ ሰው ካላስቀመጡበት ተመልሶ ዱር ይሆናል።

ባባቱ የሚኮራ ሰው ጅል ነው። የሰው አባቱ አንድ አዳም አይደለምን? ሴትን ወንድ አንድ ጊዜ ይደርስባታል መንታ ትወልዳለች። እህልም አንዲት ፍሬ ተዘርታ ብዙ ታፈራለች። ይህ ነገር ከቶ እንዴት ነው? እንጃ ማን ያውቀዋል። ያ የጠቢቦች ጠቢብ ያውቀው እንደሆነ ነው እንጂ።

ፈረስ በብረት ልጓም ይገታል። የሕዝብም ልጓሙ ንጉሥ ነው። መቃብር መልካም ጐታ ነው ብስሉንና ጥሬውን ይከታልና። ወዳጅ ቢወዱት ይወዳል መሬትም ቢበሉት ይበላል።

በርበሬ ላይን ቀይ ሆኖ ይታያል ምነው ቢሉ በብልሐት ገብቶ ሊለበልብ። ክፉ ሰውም ቀስ ብሎ ገብቶ ኋላ ነገሩን ያመጣል።

ቸር ሰው ለወዳጁ ጠጅ ነው ፍቅሩ ያሰክራልና። ዝናም ከዘነመ በኋላ ቡቃያ ያበቅላል። ንጉሥም ከወደደ በኋላ ይሾማል።

ሸክላ እጅግ ክፉ ነው ውሀ አርሶ አሠርቶት መከታ እየሆነ እሳትን ያስወጋዋል። ክፉም ሰው እንደዚያ ነው። ወንፊት ዱቄትን እንዲነፋ ዘርዛራም ሸማ ጠጅን እንዲያወርድ ባለቤቱም ያልቻለውን ምሥጢር ሌላው ሰው አይችለውም።

ቅቤ ካይብና ካጓት እንዲለይ በላይም እንዲሆን ጻድቅም ሰው እንደዚያ ነው።

.

ክፍል 2

ደመና ሰማይን እንዲሸፍነው ንጉሥም በሰራዊቱ እንደዚያ ነው። ሳማና አብላሊት ለምለም መስለው እንዲለበልቡ መናፍቃንም ሲቀርቧቸው እንደዚያ ናቸው።

በቀስታና በዝግታ የተበጀ መዘውር ኋላ ጉልበት ይሆናል። ወረቀት መልካም እርሻ ነው ብዙ ነገር ይዘራልና። ጐታም አይሻ እርሱ ከቶት ይኖራልና።

ማር ሁለት ጊዜ ያገለግላል አንድ ጊዜ መጠጥ አንድ ጊዜ መብራት ሆኖ። ምነው ቢሉ የብልሕ ሥራ ነውና አሰርም የለው።

ሕዝብና ሕዝብ ደጋና ቆላ ናቸው ንጉሡ ግን ገበያ ነው ሁሉን ያገናኛልና። ሸክላ ከተሰበረ በኋላ ገል ነው መኳንንትም ከተሻሩ በኋላ ሕዝብ ናቸው።

ክፉ ሰው ሽንቱን በሸና ጊዜ ኋላ ጉንፋን ይሆናል ምነው ቢሉ ግብሩ ተጉድፍ የተዋሐደ ነውና። ማርና እሬትን ቢመዝኑ ማን ይደፋል እሬት ምነው ቢሉ ክፉ መራራ ነውና።

ከብዙ ቀን ደስታ ያንድ ቀን መከራ ይበልጣል። ንጉሥ ምሰሶ ነው ሠራዊት ግድግዳ ናቸው መኳንንት ግን ማገር ናቸው። ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው።

ጨው በዓለሙ ሁሉ ይዞራል ምናልባት ሰልችተው ይተውኛል ብሎ ነውን? ከሬት ጋራ ይጋባ እንደሆነ ነው እንጂ የሚለቀው የለም።

አንድ ዓይንና አንድ ዓይን ያላቸው ተጋብተው ሁለት ዓይን ያለው ልጅ ወለዱ። ይህ ነገር ምንድር ነው? አንድ ካባቱ አንዱ ከናቱ ነዋ። የዚህ ዓለም ትርፉ ምንድር ነው? መብላት መጠጣት ጥጋብና ኩራት ነው። ኩራት ምንድር ነው? እንደርሱ ሆኖ የተፈጠረውን ሰው መናቅ ነው።

ሰው ፍሪዳን አብልቶ አብልቶ ያሰባዋል በመጨረሻውም ይበላዋል። ምነው ቢሉ አብልቶ መብላት እንጂ ገበያ ነው። ወርቅ ቢያብረቀርቅ ብር ያብለጨልጫል ምነው እናንት መናፍቃን ጥቂት ጥቂት ብልሐት አታዋጡምን።

የዝንብ ብልሐቷ ምንድር ነው ሌላው የሠራውን መብላት ነው። ሰነፎች ሰዎችም እንደዚሁ ሌላ ሰው የሠራውን መብላት ይወዳሉ።

ድሀ ከመሆን ሀብታም መሆን ይሻላል ምነው ቢሉ አይቸግርምና። በምድር ከመኖር በሰማይ መኖር ይሻላል ምነው ቢሉ የዚህ ዓለም መከራው ብዙ ነውና።

ከባለጌ ፍቅር የንጉሥ ቁጣ ይሻላል። የረሀብ ጌትነቱ መቼ ነው እህል በታጣ ጊዜ ነው ምነው ቢሉ የሌለውን አምጡ ይላልና። የማጣትስ ጌትነቱ መቼ ነው የፈለጉት ነገር በታጣ ጊዜ ነው። የጥጋብስ ጌትነቱ መቼ ነው መብልና መጠጥ በተገኘ ጊዜ ነው። የመብላትስ ትርፉ ምንድር ነው ጥጋብ ነው።

.

አለቃ/ደብተራ ዘነብ

1856 ዓ.ም.

[ምንጭ] – “መጽሐፈ ጨዋታ”። አንድምታ መጻሕፍት። ፳፻፲። ገጽ 27-30።

.

(የቃላት መፍቻ)

[ከሣቴ] = ተሰማ ሀብተ ሚካኤል። (፲፱፻፶፩)። “ከሣቴ ብርሃን የዐማርኛ መዝገበ ቃላት”

.

ለንቋጣ = የሚምለገለግ፣ ልጥ ያለው አንድ አይነት ሐረግ መሳይ [ከሣቴ፤ ገጽ ፲፱]

“ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው” (ክፍል 2፤ አንቀጽ 6)

ማለገ = ሳይፈተግ ተቆልቶ የተወቀጠውና የተበጠበጠው ተልባ ተዝለገለገ፣ ልሀጭ የሚመስል ዛህል ወጣው [ከሣቴ፤ ገጽ ፻፵]

“ለንቋጣ ልጡ እንዲማልግ እንጨቱም ቀሊል እንደሆነ ወስላታም ወዳጅ እንደዚያ ነው” (ክፍል 2፤ አንቀጽ 6)

.

ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን

ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን

(ሂሳዊ ንባብ)

በተአምራት አማኑኤል

(1926 ዓ.ም)

.

የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይን “ማኅደረ ብርሃን – ሀገረ ጃፓን” የሚባለውን መጽሐፍ ባነበብሁ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ ውጭ ያለውን አገራችንን (ተማሪ ቤት፣ ስልክ፣ ባቡር የሌለበትን)፣ እንኳንስና ከውቅያኖስ ማዶ ያሉትን አገሮች የኢትዮጵያን ወሬ የማያገኝበትን ወረዳ ነው ያሰብሁ።

እኒህን ቃላት ለመጻፍ ያነሳሳኝም ለተራበ ሕዝብ ጐተራውን ከፍቶ እህሉን እንደሚናኝ ባለጸጋ፣ ደራሲው ያዩትን የሰሙትን ያወቁትን ላገራቸው ልጆች ለማካፈል የጻፉትን መጽሐፍ በሩቅ አገር የሚኖሩት አንባቢዎች ወሬውን እንዲሰሙት፣ ሰምተውም መጽሐፉን እንዲያነቡት ስል ነው እንጂ “ሰብሕዎ ለኅሩይ” ለማለት አይደለም።

ይህን ብል ኃጢአት ኑሮበት አይደለም። ነገር ግን አመስጋኝ ያላጡትን ሰዎች፣ ይልቁንም ከቤተ መንግሥት ከፍ ካለ ማዕረግ የደረሱትን ሰዎች፣ በሚገባቸው ጊዜ ስንኳ ቢሆን እነሱን ማሞገስ (ያውም በጋዜጣ) ከከንቱ ድካም እቈጥረዋለሁ። “ሥራህ ጥሩ ነው አይዞህ በርታ ግፋበት” የሚባል እግር እንዳልተከለ ልጅ ታቴ የሚለውን ድኃ ነው።

በዓለም አንድ ተብለው ከሚቆጠሩት ቅኔ አዋቂዎች ፍሪዱዚ ያገሩን የፋርስን ነገሥታት ታሪክ “ሻ ናሜ” ብሎ ሰይሞ በግጥም ጽፎት መጽሐፉ በፈረንሣይ ቋንቋ በተተረጐመበት ዘመን ስለዚሁ መጽሐፍ አንድ የፈረንሣይ ደራሲ ጋዜጣ ሲያወጣ እንዲህ ይላል፣

“አንዳንድ ጊዜ ደጅ መውጣት ያላዩትን አገር ማየት ደግ ነው፤ አእምሮህን ያሰፋልሃል። ከማን አንሳለሁ የሚያሰኝህን ተራራ የሆነውን ትዕቢትህን አንስቶ ከመሬት ያፈርጠዋል። ካገርህ ሳትወጣ ከቤትህ ተሸጉጠህ ትልቅነት ገናናነት አንደኛ ነው እንጂ የምትለው አሳብህ ሁሉ ምስኪን መሆኑንና የሌላውን ነገር ሁሉ ልኩን የምታገኘው ደጅ ስትወጣ ነው።”

ዋና ሰው ነኝ እያሉ በሚመናቸኩበት ሰዓት ትዕቢትን ለማብረድ ስለ ፋርስ ስለ ሺን አገር መንገደኞቹ የጻፉትን መጽሐፍ ከማንበብ በቀር ሌላ መድኃኒት አይታየኝም። ያውልህ እልፍ አእላፋት ሕዝብና ነገድ ወሬህን ሰምተው የማያውቁ ለወደፊቱም ዜናህን ሳይሰሙት እድሜያቸውን የሚያሳልፉ ወሬህን ባለመስማታቸውም ጠጠት የማያድርባቸው … ያንጊዜም በገዛ እጅህ እንደ ፈላስፋው ብሌዝ ፓስካል “ስንትና ስንት መንግሥታት ሳያውቁ ይኖራሉ” ከማለት ትደርሳለህ።

አዲስ አበባን ቅሉ ካላዩት ካንዳንድ ያገሬ ልጆች መኳንንትና ወይዛዝር (እንጀራና ሹመት መሳይ ካላቸው ሰዎች ጋራ) ስነጋገርበት በነበረ ጊዜ እኒህ ሰዎች ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያለው ፍጥረት ሁሉ ያወቃቸው፣ የሚኮሩበትን አባትና ሹመትም ዓለም ሁሉ የተረዳላቸው ይመስላቸው እንደነበረ ስላየሁት ነው። ከዚህ በላይ ያለውን ቃል የጠቀስኩ ከጐንደር ተነሥታ ባምብሎ ስትደርስ “ትግሬ ማለት ይኸ ነው?” አለች እየተባለ ባንዲት ሴት ወይዘሮ ሲተረት አውቃለሁ።

በውነት እብድ ይመስል ሰው ሁሉ ቤቱን እየጣለ ይዙር ይንከራተት ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ካለበት ሁኖም ትምህርቱ ይስፋ፣ “ጌታ ነኝ ወይዘሮ ነኝ ጀግና ነኝ” የምትለው ሁሉ ተማር … ትምህርትህ ጌትነትህን ውይዝርናህን ጀግንነትህን አያጐልብህም። ይህ ሁሉስ ቢቀር ከትምህርት የበለጠን መሰለህ? “ጉልበት ማለት እውቀት ነው” ይሉሃል ላቲኖችና እውቀትን አታጐጥጠው እባክህ።

አሁንም “ማኅደረ ብርሃን” መጽሐፋቸውን አንብብና ብዙ ሳትደክም አንገረብን ሳትሻገር በብዙ ደስታ ከምድር ዳር ደርሰህ ትመለሳለህ። ደራሲውን ተከተላቸው … በባሕሩ በየብሱ በተራራው በደሴቱ ይመሩሃል። ተግተህ ከሰማሃቸውም ከቤትህ ሳትወጣ ጃፓን ርስት ልታካፍል ስንትም አይቀርህ። “እሳት ተነሳ፣ ቋያ ተቃጠለ” ስትል ቅጠለ-ቀይ ዛፍ ነው ይሉሃል፤ “ጥጥ ነው አመልማሎ ነው” ስትል ነጭ አበባ ነው ይሉሃል።

“እሺ ይሁን” በላቸው … ቀሚሱን እስከ እግር ጣቱ ሰዶ ወንዱንም ሴቱንም በቶኪዩ ጐዳና ድምቡል ድምቡል ሲል ያሳዩሃል። እንዲህ አስተዋውቀውህ ከቤቱ ሲወስዱህ ተንበርክኮ ይቆይሃል፤ “ንበር ሊለኝ ነው ሊነሳልኝ ነው” ስትል ፍግም ብሎ መሬት ይስምልሃል። አደግድግ አንተም … እንዳገርህ ‘ክበር ተከባበር’ ነውና እጅ ንሳ።

ከዚያ አልፈህ ከነቡዳሃ ከነሽንቶ ሽራይን (መቅደስ) ስትገባ አልባሳታቸው ብቻ የሚያስገርምህ ካህናትንና ደናግልን ሲያለዝቡ ሲያመረግዱ ታገኛለህ። አንተም አሸብሽብ … በሞቱ ከምድር አድማስ ነው ደርሰህ ያለ። ደራሲው በጠራ በማይሰለች አማርኛ ንግግር፣ አጭር ሳለ ብዙ ፍሬ ነገር በያዘ ቃል ያዩትን የሰሙትን ነገር ሁሉ ይነግሩሃል። ጃፓን ከተባለ እስከዛሬ ድረስ ያለውን ታሪኩንና ሕግጋቱን ሃይማኖቱንና ሥርዓቱን ይገልጹልሃል። ታሪኩ ይሰለችህ እንደሆነ ዝም ብለህ ተከተላቸው።

በኢትዮጵያና በጃፓን ሰንደቅ ዓላማ ተጋርደህ በሕዝብና በተማሪ ታጅበህ “ባንጃሂ ባንጃሂ” እየተባለልህ የደስታ ውካታና ጭደራ እየቀለጠ በየት አለፈ እስቲ እንየው እየተባልህ በብዙ ደጅ ጥናት ከማታገኘው ከነገሥታት እልፍኝ ያገቡሃል። መሳፍንቱና ወይዛዝሩ፣ የውስጥ አሽከሮቹና ደንገጥሮቹ ገና አይተው ሳይጠግቡህ እጅ ነሥተህ ዘወር በል። ለራት ለምሳ ግብዣ ተጠርተሃልና ካንዱ ሁሉ ግንብ መግባት አለብህ።

ከዚያም ከፍራሽ ላይ እየተዘናፈልክ፣ ክራር እየተመታልህ ባንድ እጅህ ሳኬ የሞላበትን ጽዋህን ጨብጠህ፣ ሹል ሁኖ አጊጦ በተበጀ ዝሆን ጥርስ (ወይም ድብልብል እንጨት) እየያዝህ ልጃገረዶች የሚያቀርቡልህን ምግብ ኮምኩም። ጃፓን እንግዳህ ቢሆን አንተም ለጃፓን ብርቁ ነህና ብዙ የምትጠይቀው አለብህ። አንተም በተራህ ጠይቅ። የጃፓን ሕዝብ ከባለጌነት በጣም የራቀ ጨዋ የጨዋ ልጅ ነውና በጠየቀኸው ሁሉ በፍቅር በማክበር ይመስልሃል።

ያገሩ፣ የወንዙ፣ የሰዉ ስም ላንደበትህ የቸገረ ፍጹም ግራ ሁኖ ይታይሃል። ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ወድያው ይለመድሃል። የሃይማኖቱ አሳብ እንግዳ ይሆንብሃል – ላንተ እንግዳ ይሁንብህ እንጂ ደራሲው ከሰሎሞን ጋራ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ይሉሃል። ይህን ብለውም አይቀሩ ጃፓን በሃይማኖቱ ሰማንያ አሐዱን ከተቀበለ ሕዝብ ጋራ በብዙ ነገር እንዲስማማ ያስረዱሃል። መጽሐፋቸውን አንብብው። ካነበብኸው ጃፓንን አየኸው ያዝኸው ጨበጥኸው።

ጃፓን ሥራ ወዳጅ ነው። በፋብሪካ የሚሠራው ወንዱም ሴቱም በሚሊዮን ነው የሚቆጠር። የሠራውም እቃ ከብዛቱ የተነሳ ገበያ አልበቃው ብሎ መድረሻ አጥቶ ተቀምጧል። ጃፓን ጀግና ነው። እንኳንስና ሊሰጋ ሕዝቡ ሰላማዊ ነው እንጂ እንዳይመጣብን እያሉ የሚፈሩት አይጠፉም። ጃፓን ብልህ፣ ቁም ነገረኛ፣ ፍቅሩ የሚፈለግ ሕዝብ ነው። ጃፓን ሊቅ ነው። በትምህርት ራሱን ችሎ ለሌላ ሊተርፍ ስንትም ያልቀረው ደቀ መዝሙር ነው። የሥልጣኔው ታሪክ የትላንትና ይባላል እንጂ እንደ እውነቱ የዛሬ ሺህ ተስድስት መቶ ዓመት ባገሩ ሲሰራ የነበረው እቃና የተደረሰው ቅኔ ረቂቅ ሕዝብ እንደነበረ ይመሰክርለታል።

የድርሰቱን የቅኔውን ሥራ ያገሬ ባላገር የደካማ ሥራ ብሎ ለደብተራ ብቻ ንቆ እንደሚተውለት ብልሁን ጃፓን ቃትቶት አያውቅም። የመጻሕፍቱን ታሪክ ብታየው ወይዛዝሩና መኳንንቱ፣ ንግሥታቱና ነገሥታቱ፣ ጀግኖች ወታደሮቹና መንፈሳውያን ካህናቱ “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ” የሚፈካከሩበት ነው የሚመስልህ። ጥሩ ቅኔና ድርሰት የጀመሩ ከልደት በኋላ በ285 ዓመት ነው ይሉናል። ከዚያ አንስቶም እስከ ዛሬ ደራሲና ባለቅኔ አቋርጦ አያውቅም።

ንጉሠ ነገሥቱ ሙሺሂቶ ዘመነ መንግሥታቸው ሜይጂ ዖ (ሰላማዊ ብርሃን) የተባለው፣ የዛሬው ንጉሠ ነገሥት አባት ዋና ባለ ቅኔ ነበሩ። ቢሆንም የትርጉም ትርጉም ሲሆን የቅኔያቸው መልኩ ሊበላሽብኝ ሆነ እንጂ፣ ከግርማዊ ሙሺሂቶ ቅኔ አንዲቱን አጭሯን ከጣልያን ቋንቋ ልተርጉምልህና “ማኅደረ ብርሃን“ን አንብብ እያልሁ ፍቀድልኝ ልሰናበትህ፤

ጐበዝ ላገርህ ለወንዝህ

እኔ ንጉሥህ ጌታህ

ውጋ ምታ ስል አዘዝሁህ

በለው አሁንም ውጋ

ዋናውን ፍቅርን አትዘንጋ

ቢሆንብህ የግድ

ላገርህ ለወንዝህ ማረድ

ፍቅርን መውደድን አትካድ።

.

ተአምራት አማኑኤል

1926 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ፤ መስከረም ፲፰፣ ፲፱፻፳፮

የጃፓን ባህል ቅኝት

“የጃፓን ባህል ቅኝት”

ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

(1924 ዓ.ም)

.

የጃፓን አገር ቀስት መስሎ ከምሥራቅ ወደ ሰሜን ምዕራብ በቀጭኑ የተዘረጋና የተከፋፈለ ደሴት ነው። እየዞርን ያየናቸው አውራጃዎች ሁሉ የሚበዙት ተራራሞች ናቸው። በየተራሮቹም ቄድሮስ (Cedar) የሚባለው ዛፍና ሌላም ልዩ ልዩ ዛፎች በብዙ ይታያሉ። ስለ ተራሮችም ብዛት ትልልቆች ወንዞች ሞልተዋል። ስለዚህም በየዘብጡ መሬት ሩዝ ለመዝራትና ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶች ለመትከል ይመቻቸዋል።

አሁን እኛ ወደ ጃፓን በደረስንበት ወራት የሩዝ አጨዳ ነበር። ስለ መሬቱም እርጥባምነት የታጨደው ሩዝ እንዳይበሰብስ በየነዶው እያሰሩ ረጃጅም እንጨት በባላ እያጋደሙ እንደ ሥጋ ቋንጣ ይሰቅሉታል እንጂ በመሬት ላይ አይከምሩትም። አንዳንዱም በገመድ እያሰሩ በየዛፉ ላይ ያንጠለጥሉታል።

እኛ በዞርንበት በጃፓን ምዕራብና ደቡብ በግና ፍየል ሌላም የቀንድ ከብት በዱር ተሰማርቶ የሚበላ አላየንም። ምናልባት እነዚህን የመሰሉት እንስሶች የሚረቡት በጃፓን ምሥራቅና ሰሜን ይሆናል እንጂ ባገሩ ውስጥ በግና የቀንድ ከብት የለም ለማለት አይቻልም።

በጃፓን አገር በያውራጃው የሚከበረው በዓል ብዙ ነው። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ የገብርኤል፣ የራጉኤል፣ የጊዮርጊስ፣ የተክለ ሃይማኖት፣ የገብረመንፈስ ቅዱስ ታቦት ባለበት አገር በየሰበካው እንደሚከበረው ነው። አሁን የምጽፈው ግን በመላው ጃፓን አገር የሚከበረውን ትልልቁን በዓላት ብቻ ነው። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ መስቀል፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ፋሲካ እንደሚባለው ነው።

ኅዳር 23 ቀን የሩዝ መከር በዓል ነው። በዚህም ቀን ከሩዙ ጥቂት ጥቂት እየያዙ ወደ ሽራይን (Shrine) እየሄዱ እንደ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበት ቀን ነው። በቤተ መንግሥቱም ከአዲሱ ሩዝ የሚቀመሰው በዚሁ ቀን ነው።

Japan Images_Page_14

ጥር 1 ቀን የዘመን መለወጫ በዓላቸው ነው። የካቲት 3 ቀን የክረምት ማጋመሻ በዓል ይባላል። በዚህም በዓል ቤተ ዘመዱ ሁሉ በየቤቱ እየተሰበሰበ ቆሎ እየተቆላ ቆሎውን እየዘገነ ‘ሰይጣንና ክፉ ነገር ውጣ’ እያለ ወደ ውጭ ይበትናል። ‘ሲሳይና ጤና ወደ ቤት ግባ’ እያለ ወደ ቤት ውስጥ ይበትናል፤ የተረፈውንም ይበሉታል። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ በየባላገሩ ለእንቁጣጣሽና ለግንቦት ልደታ እንደሚደረገው ነው።

መጋቢት 3 ቀን ‘ያሻንጉሊት በዓል’ የሚባለውን ያከብራሉ። በዚህም ቀን ከነገሥታቱ ልጆች ጀምሮ እስከ ሕዝቡ ድረስ ያሉት ሴቶች ልጆች ዋጋው ውድ የሆነ አሻንጉሊት እየገዙ ለንጉሠ ነገሥቱና ለእቴጌይቱ፣ ለሚኒስትሮችና ለመኳንንቶች፣ ለየትልልቁም ሰው ሁሉ እየወሰዱ ይሰጣሉ። ይኸውም እየተሰበሰበ እንደ አንቲካ በክብር እየሆነ ይቀመጣል። ባገራችን በኢትዮጵያ ሴቶች ልጆች ለእንቁጣጣሽ እንግጫ፣ ለመስቀል ደግሞ አበባ እየወሰዱ ለየትልልቁ ሰው እንደሚሰጡት ነው።

ግንቦት 5 ቀን ‘የባንዲራ በዓል’ ይባላል። ይኸውም በሙሉ በጃፓን አገር ይከበራል። በዚህም ቀን ወንዶች ልጆች ሁሉ የልብስ፣ ያላገኙም የወረቀት ባንዲራ እያበጁ ይይዛሉ። የወረቀት ባሎንም እያበጁ ወደ ሰማይ ይወረውራሉ። ደግሞ ካንዱ ቤት ወዳንዱ ቤት ገመድ እየተዘረጋ የወረቀት ባንዲራ ይደረደራል። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ በየቆላው አገር ሁሉ ወንዶች ልጆች የማሽላ አገዳ (አሜራ) እየላጡ በክር እየሰኩ አላማ እያሉ ለከተራ ታቦት ሲወጣ እየያዙ ወደ ጥምቀተ ባሕር እየወረዱ በማግሥቱ ታቦት ሲመለስ ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያኖሩት ነው።

ሐምሌ 13 ቀን የሰው ሁሉ የሞቱት ዘመዶች ነፍሳት መታሰቢያ በዓል ነው። በዚሁም ቀን የሞቱት መቃብራቸውንና የድሮ ቤታቸውን ይጎበኛሉ ይባላልና ሕያዋኑ ዘመዶቻቸው የመቃብሩን ስፍራ ሁሉ ንጹሕ ያደርጋሉ። ቤታቸውንም ሁሉ ያስጌጣሉ። ድግስም እየተደገሰ በየመቅደሱ ይላካል። ካህናቱም ጸሎት ያደርጋሉ፤ በየደጃቸውም ላይ ነፍሳትን ለመቀበል የጪስ እንጨት ያጨሳሉ። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ ክብረ ቅዱሳን ተዝካረ ሙታን እንደሚባለው ነው።

በተረፈ በሽንቶ ሽራይንም በቡድሃ መቅደስም አንዳንድ የቅዱሳኖቻቸው በዓላት ይከበራሉ። ይኸውም ባገራችን በኢትዮጵያ ታቦት በተተከለበት ስፍራ ሁሉ የታቦቱን በዓል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆኑ የሰበካው ሕዝብ ብቻ እንደሚያከብሩት ነው።

በጃፓኖች ቤት ሁለት ዓይነት መብል ይዘጋጃል። አንደኛው ዓይነት ያገራቸው መብል፣ ሁለተኛው ዓይነት የአውሮጳ ወጥ ነው። የአገራቸው መብል ከአታክልት፣ ከዓሳ፣ ከሥጋ፣ ከሩዝ የሚሰናዳ ነው። ዳቦ ወይም ሌላ ዓይነት እንጀራ የለም። መብሉ ለስላሳና ጣፋጭ ነገር ነው። ለውጭ አገር ሰው እጅግ ደስ አያሰኝም። የዓሳና የዶሮ ሥጋ ኮምጣጤ የሚመስል ከቅመም የተሰራ መረቅ ቀርቦ በዚያ እየተነከረ እርጥቡን ይበላል።

መብል ሲቀርብ ለያንዳንዱ ሰው በተለየ እቃ ነው እንጂ ለብዙ ሰዎች ባንድ እቃ አይቀርብም። ወጡም በትንንሽ ሳህን ለየብቻው እየቀረበ ባለቤቱ እየመረጠ ይበላል። የሚበላውም በማለፊያ ሆኖ በታነጸ በሁለት ድብልብል እንጨት (Chopstick) እየተጣበቀ ነው እንጂ እጅ አይነካውም። ጌታ ጌታው ከዝሆን ጥርስ የተሰራ ማጣበቂያ አለው።

የጃፓን ነገሥታት ታሪክ በጣም የሚያስደንቅ ነው። መጀመሪያ በጃፓን የነገሠው ‘ጂሙ ቴኖ’ ይባል ነበር። ‘ቴኖ’ ማለት በቋንቋቸው ንጉሠ ነገሥት ማለት ነው። ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩትን የነገሥታቱን ስም ሲጠይቋቸው “አማልክት ይገዙን ነበር” ይላሉ። ትርጓሜው ግን ታሪኩ አልተገኘም አልታወቀም ማለት ይመስላል።

የዚህ ንጉሥ ዘር ከወዴት የመጣ ነው ሲሏቸው “ፀሐይ ‘አማቴራሱ’ የተባለች ሴት ልጅ ነበረቻትና ከእሷ ዘር የመጣ ሰባተኛ ትውልድ ነው። ፀሐይም አምላክ ናትና ነገሥታቶቻችን የአምላክ ልጆች ስለ መሆናቸውና ሰውነታቸው የተቀደሰ ስለ መሆኑ እንሰግድላቸዋለን” ይላሉ። ምናልባት ይህች ‘አማቴራሱ’ ያሏት እኛ ሔዋን የምንላትን ይሆናል።

ይህም ልማድ በጃፓን አገር ብቻ አይደለም። ነገር ግን በቀድሞ ዘመን በምሥራቅ አገር፣ በባቢሎንና በፋርስ፣ በህንድም በሽንም የነበሩ ሰዎች አምላካችን ፀሐይ ነው እያሉ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። ባገራችን በኢትዮጵያም ምንም እንኳን በብሉይ ኪዳን ተጽፎ ባናገኘው ካባቶቻችን ቃል ለቃል ተያይዞልን እንደመጣው ታሪክ አብርሃም እንደ አባቶቹ በፀሐይ ለማምለክ ኅሊናው እምቢ ቢለው “አምላከ ፀሐይ ተናበበቢ (የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ)” አለ ይባላል።

በጃፓን አገር ነገሥታቱም የፀሐይ ልጆች ናቸው እየተባሉ በታላቅ ክብር እየተከበሩ ይሰገድላቸዋል። ከቀድሞ ካባቶቻቸው ጀምሮ እንደ ዘውድ እየተወራረሰ የመጣላቸው ያልማዝ ቀለበታቸውና ሰይፋቸው፣ መስተዋታቸውም እንደ ንዋየ ቅድሳት ይቆጠራል። የሰውነታቸውም መከበር ይቅርና ፎቶግራፋቸው በታየ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይሰግዳሉ።

ስለ ክብሩም ማንም ቢሆን የንጉሠ ነገሥቱን ፎቶግራፍ ደፍሮ በቤቱ የሚሰቅል አይገኝም። ለየትልልቅ ሰዎችም እንደ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ እንደሆነ በትልቅ የብረት ሳጥን ውስጥ እያገቡ ቆልፈው ያስቀምጡታል። በውጭ አገርም ለተሾሙት የጃፓን አምባሳደሮችና ሚኒስትሮች የተሰጠ እንደሆነ ነፋስ እንዳይነፍስበት፣ ትቢያ እንዳይበንበት፣ የእሳትም አደጋ እንዳያገኘው እየተባለ በብረት ሳጥን ውስጥ ይቀመጣል እንጂ በሌጋሲዮኑ አይሰቀልም። ያለፈቃድም ፎቶግራፉን ኮፒ ለማንሳት አይቻልም።

ይህም በእኔ በራሴ ደርሶብኛል።

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መልእከተኛ ስለ መሆኔ የጃፓን ንጉሠ ነገሥትና እቴጌይቱ ፎቶግራፋቸውን እየፈረሙ ሰጥተውኝ ነበር። ያገሩንም ሕግ ሳላውቅ ወደ አንድ ሠራተኛ ወስጄ “ይኸን ፎቶግራፍ ኮፒ አንስተህ በመጽሐፍ የሚገባ ክሊሼ ስራልኝ” ብለው ፎቶግራፉን ተቀብሎ አይቶ፣ “የተቀደሰውን የንጉሣችንን ፎቶግራፍ ክሊሼ ለመስራት ከግርማዊነታቸው ልዩ ፈቃድ ካላገኘሁ አልችልም” ብሎ ፎቶግራፉን መልሶ ሰጠኝ።

የዛሬው የጃፓን ንጉሥ ነገሥት የእንግሊዝና የፈረንሣዊ ቋንቋ ያውቃሉ። ነገር ግን የኦፌሴል ጉዳይ የሆነውን ሁሉ በአስተርጓሚያቸው ካልሆነ በቀር አውቃለሁ ብለው በውጭ አገር ቋንቋ አያነጋግሩም።

ይኸውም የጃፓንን ቋንቋ ለማስከበር የተደረገ ይመስላል።

.

ኅሩይ ወልደሥላሴ

(1924 ዓ.ም)

.

[ምንጭ] – “ማኅደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን”። ፲፱፻፳፬። ገጽ ፻፴፭-፻፶፭።

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

በተአምራት አማኑኤል

(ክፍል 1)

.

የጥንቱ የኢትዮጵያ አፈ ታሪክ “አንድ ሽሕ ዓመት ያህል ከልደተ ክርስቶስ በፊት፣ ባገራችን ሊቃውንትና መምህራን ነበሩበት … እስከ ዛሬ ድረስም ሊቅ፣ መምህርና ደራሲ አልጠፉበትም” ይላል። ቢሆንም አፈ ታሪኩ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከብሉያት በቀር ሌላ ዓይነት መጻሕፍት መኖር አለመኖራቸውን አያመለክትም።

አፈ ታሪካችን በሰሎሞን ዘመን ከሕዝበ እስራኤል ጋራ ግንኙነት እንደነበረን፣ ንግሥተ ሳባ ዛሬ ኢትዮጵያ (ሐበሻ) የምንለውንና ከዓረብ አገር የደቡቡን ክፍል ትገዛ እንደነበረች፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ሒዳ ከሰሎሞን ጋር ተዋውቃ ከርሱ ቀዳማዊ ምኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ እንደወለደች፣ ቀዳማዊ ምኒልክም እስከ ዛሬ ድረስ ላሉት ነገሥታቶቻችን አባት መሆኑን፣ እርሱም አባቱን ሰሎሞንን ለማየት ሒዶ ከኢየሩሳሌም ሲመለስ፣ ጽላተ ሙሴንና እስከ ሰሎሞን ዘመን ከእስራኤላውያን የተጻፉትን መጻሕፍተ ብሉያትን ይዞ እንደመጣ ይነግራል።

ይህን አፈ ታሪክ የሚነግሩ መጻሕፍት ባገራችን መጻፍ የጀመሩት ከ1300ኛው ዓመተ ምሕረት ወዲህ ነው። ሽሕ ዓመት ከዚያ በፊት ለሕዝቡ ወንጌል ተሰብኮለት ነበር። በሽሕ ዓመት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ፣ በአሕዛብነት የነበረበትን ዘመን እንዲጠየፈው፣ የሕዝበ እሥራኤልን መጻሕፍትና አሳብ እንዲወድ አድርጎት ስለ ነበረ፣ ጥቂት በጥቂት የገዛ ራሱን ታሪክ እየዘነጋ፣ የእስራኤል ልጅ ነኝ ከማለትና የእስራኤል ሕዝብ የጻፋቸውን መጻሕፍት፣ አያቶቼ የጻፏቸው ናቸው ከማለት ደርሷል።

በሰሎሞን ዘመን የእስራኤልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ኖሯቸው ይሆናል ቢባል፣ ማስረጃው እንኳ ባይገኝ፣ ሳይሆን አይቀርም በማለት በተቀበልነው። በሰሎሞን ዘመን ከብሉያት መጻሕፍት አንዳንዶቹ እስከ ኢትዮጵያ ደርሰው በዚያው ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀብሎ የሃይማኖት ሥራ አስይዟቸዋል ለማለት ግን ማስረጃው እስኪገኝ ድረስ ልብ ወለድ የመጣ አሳብ ነው እንላለን።

የዛሬው ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሙሴ የሚባሉት አምስቱ ብሔረ ኦሪት ተሰብስበው ባንድነት መገኘት የጀመሩት በሰሎሞን ዘመን ብቻ ነው ይለናል። የዚህ ክርክር ገና ሳይጨረስ፣ አፈ ታሪካችን፤ “መጽሐፈ ኦሪት በሰሎሞን ዘመን ካገራችን ደርሰው ነበር” ሲል፣ ለራሱ ክብር በመጓጓት፣ ታሪክ ጥሶ የተራመደ ሁኖ ይታየናል። ይህም ከወገን ለጊዜው የበለጠ መስሎ የታየውን እየመረጡ “ወገኔ ነው” ማለት፣ የዛሬ ሳይሆን የጥንት፣ የኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የደረሰና፣ ታሪክ ተመርምሮ ወሬው ትክክለኛ አለመሆኑ ሲታይ የሚቀር ነው።

በግሪኮች ሥልጣኔ ንጹሕ ቅናት ያደረባቸው ሮማውያን፣ የግሪኮች መዓረግ ተካፋይ ለመሆን፣ የ”ኤኔአ”ን ተረት ፈጥረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕዝበ እስራኤል የተነገረው ሁሉ ደስ ሲያሰኛቸው ከነበሩት እንግሊዞች፣ አንዳንዱ ባለ ታሪክ፣ “ስደት የሔዱት የአስሩ ነገደ እስራኤል የልጅ ልጆች ነን” ሲል ነበር። ዛሬ ግን፣ ሮማውያንም ከግሪኮች ጋር ዝምድና እንኳ ቢኖራቸው፣ ባለ ታሪክ ሌላ ማስረጃ ያመጣል እንጅ የ”ኤኔአ”ን ተረት መሠረት አያደርገውም። የባለ ታሪክ ስምና መዓረግ ያለው ሰው ደግሞ፣ “በእንግሊዝ ደሴቶች ከምሥራቅ የመጣ ሕዝብ ሰፍሮበት ኑሮ ይሆናል” እንኳ ቢል፣ “አንግሎ ሳክሶን የአስሩ ነገደ እስራኤል ልጆች ናቸው” አይልም።

እንደዚኸው ሁሉ የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲሱ የምርመር አካሔድ የሚከታተል ሰው፣ ታሪኩን በሌላ መንገድ ያስረዳል እንጂ፣ ስለ ንግሥት ሳባና ስለ ሰሎሞን የሚነገረውን መሠረት አያደርግም። ስለዚህም ከልደተ ክርስቶስ በፊት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ኑረው እንደሆነ የደረሱበትን ለማወቅ ቸግሮናል እንላለን እንጅ (ሕዝበ እስራኤል በሰሎሞን ዘመን የሙሴን መጻሕፍት መሰብሰብ ገና ሲጀምር) እነዚህ መጻሕፍት ድሮ ባገራችን ነበሩ ለማለት ይቸግረናል።

በውቅሮ አቅራቢያ የተገኘው የአልሙቃሕ ቤተ ጸሎት

ጽሑፍ ሥራ በኢትዮጵያ ገና ከልደተ ክርስቶስ በፊት ተጀምሮ ነበር እንላለን። ማስረጃው ግን በጣም ችግር ነው። እርግጥ የምናውቀው ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን አቅራብያ በትግሬ አውራጃ ከሐውልትና ከጸሎት ቤት የተጻፈ አንዳንድ ቃል መገኘቱን ነው። ቀደምት የተባሉት ጽሕፈቶች የሚገኙት በሳባና በግሪክ ቋንቋ ነው። ከክርስቶስ ልደት በኋላ 300ኛው ዘመን ሲጀምር ግን፣ ጽሕፈቱና ንግግሩ የተጣራ፣ በግዕዝ ቋንቋ ከሐውልት ላይ የተጻፈ መታሰብያ አለ። ስለዚህም ከሊቃውንት አንዳንዱ እንዲህ ይላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፣

           ፊት፤                ግሪክ፣

          ቀጥሎ፤              ሳባ፣

           ኋላ፤                ግዕዝ

king-ezana-s-inscription
የንጉሥ ኤዛና የድል ሐውልት በአክሱም

ለዚህ አሳብ ብዙ ተቃራኒ አልተነሣበትም። ነገር ግን ገና የመንን ሳይለቅ ባገሩ ቋንቋና ፊደል ሲጽፍ የነበረ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለምን በግሪክ ጻፈ? ደግሞም እስከ ዛሬ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ሥራ የተያዘበት ሴማዊ የሆነው የግዕዝ ቋንቋ እጅግ የተጣራ በመሆኑ፣ ለግሪክና ለላቲን ቋንቋ ተወዳዳሪ ሊሆን ይቃጣዋል። ይህን የመሰለ ቋንቋ እያለው ባገር ውስጥ ላለው ጕዳይ ለምን በግሪክ ይጽፋል? የዚህ ምክንያቱ እስኪገለጥ ድረስ ከዚህ በላይ የተነገረው አሳብ ትክክለኛ ነው ላይባል ነው።

በርሱ ፈንታም ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን አሳብ መናገር ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፤

           ፊት፤                ሳባ፣

           ቀጥሎ፤            ግዕዝ

የግሪክ ቋንቋ ከእስክንድር ጀምሮ ሮማውያን ግብጽን እስከያዙበትና ከዚያም በኋላ እስከ ብዙ ዘመን ለግብፅና ለታናሽ እስያ ሕዝብ ዋና ቋንቋ ሁኖ ነበረ። ለኢትዮጵያ ደግሞ ከሠለጠነው ዓለም ጋር መገናኛ ቋንቋ ሁኖላት ለደብዳቤ፣ አላፊ አግዳሚ ለሚያየው ሐውልትዋ፣ ባሕር ተሻግሮ ለሚገበያዩበት ገንዘብዋ፣ ይህንንም ለመሰለ ልዩ ጕዳይ የጽሕፈት ቋንቋዋ ኑሮ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ከ400ኛው ዓመተ ምሕረት በፊት (ይህ ማለት ወንጌል ባገሩ ሳይሰበክ) በሳባ ሆነ በግሪክ፣ በግዕዝም ሆነ ወይም በሌላ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ኑሮ እንደሆን ወሬው ከኛ አልደረሰም። ዛሬ በጃችን ያሉት መጻሕፍት ከ400ኛው እስከ 1700ኛው ዓ ም በግዕዝ፣ ከዚያ እስከ ዛሬ በግዕዝና በአማርኛ የተጻፉ ናቸው። ግዕዝ የሴም ቋንቋ መሆኑን ከዚህ በፊት አመልክተናል። ከዓረብ በስተደቡብ ከነበሩት ሴማውያን ያንዱ ነገድ ቋንቋ ኑሮ ይሆናል ይባላል። ምናልባትም ከዚሁ ነገድ አንድ ክፍል ዛሬ ዓጋሜ በምንለው አውራጃ ግድም ይኖር ኖሯል። ድንገት ደግሞ ከትግሬ አውራጃ ካሉት ነገዶች አንዳንዶች ይነጋገሩበት ኑረው ይሆናል። “በኢትዮጵያ ያሉት የሴም ቋንቋዎች (ትግርኛ፣ ትግረ፣ አማርኛ፣ ወዘተ) ከርሱ የመጡ ናቸው” የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ይህን አሳብ የማይቀበሉ በዚህ ፈንታም፣ “ከዓረብ በስተደቡብ ሲኖሩ ከነበሩት የሴም ነገዶች አንዳንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ ኖሯቸው፣ የእያንዳንዱ ነገድ ቋንቋ ራሱን እንደቻለ፣ በሆነለት መጠን እየደረጀ ሄዷል እንጅ፣ ግዕዝ በኢትዮጵያ ላለው ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ አባቱ አይደለም” የሚሉ አሉ።

img0042
በቀደምትነቱ የሚታወቀው የአባ ገሪማ ወንጌል

በግዕዝ ከተጻፉት በብዙ ሽሕ ከሚቆጠሩት መጻሕፍቶቻችን ጥቂቶች ሲቀሩ፣ አብዛኛው ከክርስትያናዊ ግሪክና ዓረብ ከሌላም ቋንቋ የተተረጐሙ ናቸው። ደግሞም የዓለምንና የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚነግሩት ከጥቂቶች መጻሕፍት በቀር ሁሉም የሃይማኖት መጻሕፍት ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያዊነታችንን አሳብ የሚገልጥ መጽሐፍ በብዛት አይገኝባቸውም። ዋናው መጽሐፋችን “መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። ይኸውም ብሉይና ሐዲሱ እግዚአብሔር በዓለምና በእስራኤል ላይ የሠራውንና የሚሠራውን እስራኤላውያን በታያቸው ዓይነት የሚገልጽ መጽሐፍ መሆኑን፣ ሁሉ ያውቀዋል። ምስጋና ለዚህ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በሃይማኖትና በምግባር ከፍ ካለ ደረጃ ደርሶ፣ በያዘው መንገድ እየገፋበት እንዲሔድ ብርቱ ኃይል ተሰጥቶታል።

ደግሞም የግዕዝ ቋንቋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወዳገራችን ሳይመጣ ገና ፊት አስቀድሞ ራሱን የቻለ እንደነበረ በሐተታ እንኳ ብንረዳው፣ የግዕዝ ቋንቋ ጽሑፍ ምስክሩ ባለቤቶቹ የጻፉት መጽሐፍ መሆኑ ቀርቶ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የሌሎች መጻሕፍት ትርጕም ነው። ማናቸውም የሠለጠነ ሕዝብ ለቋንቋው፣ ለሰዋስው ማስረጃ ባለቤቶቹ የጻፉትን ሲጠቅስ፣ ግዕዝ ለሰዋስው ማስረጃ የሚጠቅስ ከባዕድ ቋንቋ የተተረጐሙትን መጻሕፍት ነው። በግዕዝ ከጻፉት ካገራችን ደራስያን ይቅርና በአሳብ፣ በአጻጻፍ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል ሳይከተሉ የጻፉ የሚገኙ አይመስለኝም። ይህም ልምድ የሃይማኖት አሳባቸውን የሚገልጹበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ አገራችን ታሪክና ማናቸውንም ጕዳይ በሚጽፉበት ጊዜ ጭምር ነው። ይህም የአጻጻፍ አካሔድ ኢትዮጵያ ገንዘብ ካደረገችው ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር የተስማማ ንግግር ለማምጣት የተመቸ ከመሆኑ በላይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሳንቀበል ከነበረብን አሕዛባዊ ከሆነ ምሳሌና ንግግር አርቆናል።

ይሁን እንጅ ኢትዮጵያዊ የሆነ አሳብ፣ ኢትዮጵያዊ በሆነ ንግግር የመግለጹ ዕድል ለግዕዝ ቀርቶበት ለአማርኛ ሆኗል። ዛሬ ዘመን በግዕዝ እግር ተተክቶ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ጕዳይ የሚሠራበት የአማርኛ ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባማርኛ መጻፍ ከጀመረ ስድስት መቶ ዓመታት ሁኖታል። አማርኛ ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን አካሔድ በ፫ ዘመን ቢከፍሉት ይሆናል።

፩ኛውን ዘመነ ዓምደ ጽዮን (1336-1599 ዓ ም)

፪ኛውን ዘመነ ሱስንዮስ (1599-1847 ዓ ም)

፫ኛውን ዘመነ ቴዎድሮስ (1847-1936 ዓ ም)

በ፩ኛው ዘመን በአማርኛ የተጻፈው ሥራ እጅግ ጥቂት ነው። የተጻፈውም ላንዳንድ ነገሥታት ምስጋና ደራሲው ባልታወቀ የተገጠመ ቅኔ ነው። ቅኔውም በዘመናት ውስጥ አንድ ቋንቋ እንደምን ሁኖ እየተለዋወጠ ለመሄዱ ዋና ምስክር ከመሆኑ በላይ በዚያ ዘመን የነገሥታቱ ሥልጣን የተዘረጋበት የሰፊው አገር ሁኔታ እንዴት እንደነበረ፣ ለታሪክም ለዦግራፊም ማስረጃ ለመሆን ይረዳል።

pages-from-bruce-88-bodleian-library-oxford
በአማርኛ የተጻፈ የነገሥታት ግጥም (የ1600ዎቹ ቅጂ)

አማርኛው ዛሬ ዘመን የማንናገርበትና የማንጽፈው፣ ለማስተዋሉም የሚያስቸግረንና የሰዋስው አካሔዱ የተለዋወጠ ብዙ ቃልና አገባብ አለበት። እርሱን የመሰለ አማርኛም በየዘመኑ እየተጻፈ ምናልባት እስከ 1599 ደርሶ ይሆናል። ነገር ግን ከ1555 እስከ 1599 ዓ.ም ባማርኛ የተጻፈ ምስክር አይገኝም፤ ቢገኝም ከዚህ በፊት ያመለከትሁትን የመሰለ ግጥም ሳይሆን አይቀርም።

ከ1500ኛው ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወገን ለይቶ አልጋ ለመያዝ እርስ በርሱ ሲዋጋ፣ ባንድ ወገን ደግሞ ቱርኮችና ፖርቱጋሎች በቀይ ባሕር ሥልጣናቸውን ለመዘርጋት ይፈካከሩ ነበር። ቱርኮች በቀይ ባሕር ዙርያ ላለው ፖሊቲካቸው የኢትዮጵያን እስላም ሲረዱ፣ ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የፖርቱጋልን እርዳታ መለመን ግድ ሆነበት። አራት መቶም ያህል ጠበንጃ የያዙ ፖርቱጋሎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተዋጉበት ጊዜ፣ ድል ለክርስቲያኑ ወገን ሆነ።

የፖርቱጋል መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋራ ግንኙነት ሲጀምር ያገሩ ካህናት በኢትዮጵያ ለማስተማር እንዲፈቀድላቸው ተነጋግሮ ነበርና በስምምነታቸው የካቶሊክ ካህናት በኢትዮጵያ ማስተማር ጀመሩ። የሚያስተምሩበትና የሚጽፉበት ቋንቋ አማርኛ ነበርና የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ደግሞ ሕዝቡ ካቶሊክ እንዳይሆንበት ግዕዝን ሳይተው ባማርኛ መተርጐምና መጻፍ ጀመረ። በዚያው ዘመን ለመጻሕፍት ትርጕምና ለስብከት የተጀመረው አማርኛ ገና ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ፣ አንዳንዱም ንግግር ግዕዝ ላልተማረ ሰው በፍጹም የማይሰማ ነበር። እንደዚኽው ሁሉ በዚያው ዘመን ሲጻፍ የነበረው የነገሥታት ታሪክ ግዕዙ አማርኛ ቅልቅል ነበር።

old-amharic
በ1760ዎቹ የተጻፈ የአማርኛው መሐልየ መሐልይ ዘሰሎሞን

ያም ሁሉ ሁኖ እንኳንስና ለውጭ አገር ሕዝብ የሚተርፍ፣ ካገራችን ውስጥ ከፍተኛ አሳብ የሚያሳድር በታረመ አማርኛ የተጻፈ መጽሐፍ ለማግኘት ችግር ነው። መጻሕፍቱ የፈጸሙት ጕዳይ፣ በሕዝቡ ላይ ከመጣበት ከሃይማኖት ተወዳዳሪ መከላከልና የባላገር ቋንቋ የነበረውን አማርኛን ጽሑፍ ሥራ ለማስያዝ መጀመራቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ለትሕትና ሲል ስሙን አያመለክትም ነበርና የመጻሕፍቱን ፍሬ ነገር መዘርዘር፣ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ማን እንደነበር መርምሮ የሕይወቱን ታሪክ ማመልከት ይቸግረናል።

(በክፍል ሁለት ይቀጥላል …)

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም