“አለቃና የምኒልክ እናት” (ወግ)

“ትዝታ ዘአለቃ ለማ”

መንግስቱ ለማ እንደጻፈው

.

(ቅንጫቢ)

.

*** አለቃ ለማ የታላቁ ባለቅኔ የመንግስቱ ለማ አባት ናቸው። በቤተክህነት እጅግ ብዙ የተማሩ ሊቅ ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸውን በአንደበታቸው በሚያወጉን “ትዝታ ዘአለቃ ለማ” ከሚባለው መጽሐፋቸው የተቀነጨበ ወግ። ***

ዕንግዲት ፤ ያባቴ እናት – እንደርሷ ያለ፣ ወንድ እንኳ የለም እንኳን ሴት። ብርታቷ፣ ምክር ስታውቅ! ንብረት የተሰናከለበት እንደሆነ ‘ወይዘሮ ዕንግዲት ይምከሩህ፣ ከሳቸው ምክር ተቀበል’ ይባል ነበር። የተናገረችው ነገር ይሆንላታል። ባል አግቢ ሲሏት ጊዜ፣ እምቢ አለች፣ ቁርባኔን አላፈርስም አለች። ሟቹ የልጃገረድ ባሏ ናቸውና፤ ባል አላገባም አለች። በብዙ ወገን ያም ይመጣል፣  ያም ይመጣል፣ አይሆንም ትላለች።

ውሽን ገብረ ሚካኤል ልጅ የላቸውምና ትወልድልኝ መስሏቸው አገባለሁ እቆርባለሁ አሉ። ማይም ናቸው፤ ያርሳሉ ባለጠጋ ናቸው።

ያባቴ እናት ልታገባ ስትል ያባት ዘመዶች ‘እኛ ልጃችን የንጀራ አባት አያይምና እንወስዳለን! ልጃችን በንጀራ አባት አያድግም’ አሉና መጡ ሊወስዱ።

‘እኔ ከልዤ አልለይም!’ – እናቲቱ – ‘እኔ ልዤን አልሰጥም ባል አላገባም ይቅርብኝ!’

ኋላ እኒያ አቡነ አሮኖች፣ ካህናቱም መምሩም ሽማግሌው ሁሉ ‘ምነው እንዲህ ታረጋላችሁ? እንዴት በልጅነት ባል ሳታገባ እንዲህ ሁና ትቀር?’ አለና ሽማግሌ ተቈጣቸው።

ልጁን ይዤ እሄዳለሁ ብለዋል ትኩ ፈንታ (የሟቹ ባል ዘመድ) የንጀራ አባት አያሳድገውም ብለው ነው።

ከብት ቀረበ (የሟቹ ባል ንብረት)፤ ሃያ አራት ሆኑ ከብቶቹ። አስራ ሁለት ያባት አሥራ ሁለት የናት ሆነ። ዕጣ ወደቀ ተከፍሎ። የሷማ እሷው አለች፤ ያባቱ ፈንታ ለልጁ ነው።

ተቈጠረና፤ ያ ባል የተባለው ቀረበ የሚያገባት።

“ይኸ ከብት ይኸው፣ የላሟ ወተት የበሬው ጉልበት ለልጁ ደመወዙ ነውና፤ ዝንጀሮ እንዳይጠብቅ ከብት እንዳይጠብቅ እንዲማር ብቻ። ከተማሪ ቤት በቀር ከምንም ከምንም ከትእዛዝ እንዳይገባ” ተብሎ ለልጁ ተሰጠ። ተነጋግሩ በዚህ አለቀ።

እኒያ ትኩ ፈንታ ሚስታቸው ለምለም ገብረሥላሴ ትባል ነበር። ‘ልጁን ይዤ እመጣለሁ ብያት ነበረ ለምለምን። ባዶ እጄን ስሄድ ትሰቀቃለች’ አሉና ከዚይ ከቀረበው ከብት አንዷን ጥጃ ያዙና – ያን ጊዜ ያገራችን ድግ ይኸ መቀነቱ አርባ አርባ ክንድ ነበረ የሚታጠቁት – ድጉን ፈቱና ኻንገቷ ታሠረ፤ አሽከር ያዘ፤ በዚያ ተጐትታ እንደ ፍየል ይዘው ሄዱ።

ዕንግዲት በብዙ ብዙ ጭቅጭቅ ውሽን ገብረሚካኤልን አገባች። ማኅፀኗ አርሮ ቀርቷል በዚያ በባሏ ኅዘን፤ ምንም ሳትወልድ ቀረች።

ውሽን ገብረ ሚካኤል ያጤ ምኒልክ አጎት መሆናቸው ነው በናታቸው – የናታቸው ወንድም ናቸው። ያጤ ምኒልክ እናት የኛ አገር ሴት አይደሉም ባባታቸው? አድያሞ ለማ፣ እሱ አይደለም ያጤ ምኒልክን እናትን የወለደ? አባትየው የላስታ ተወላጅ የመቄት ተወላጅ ናቸው። በጌምድር ወርደው – ደብረታቦር አጠገብ ነው፤ አሞራ ገደል ይባላል – የዚያን ባላባት ልጅ አግብተው አድያሞ ለማን ወለዱ።

እንግዴህ ያን ጊዜ አገራችንን የሚገዙ ወረሴኾች ይባላሉ – የጆች ይገዛሉ። ይኸ አድያሞ ለማ ከየጆች ሰው ገደለ፤ ባምባጓሮ ተጣላና አንዱን ወረሴኽ ገደለ። የጆች አገረ ገዦች ናቸውና ያን ጊዜ ባገር ለመኖር የማይቻለው ሆነ። በዚያ አመለጠና፤ ተሰደደና፣ ሸዋ መጣ። እዚህ ሎሌነት ገባ ለሣህለሥላሴ አያት።

ሲኖር ያ አድያሞ ለማ ከመንዝ ሴት ወልዷት ያጤ ምኒልክን እናት፤ ‘በደሙ ታርቀናልና ና’ አሉት ተነስቶ ሄደ። ‘መጥቼ ልጄን እወስዳለሁ’ ብሎ ሄደ፣ ኸዚያ ወዲያው እንዳለ ቀረ ቀረ። እንግዲህ የምኒልክ እናት ባባቷ መቄት ናት።

መጣችና ኻለቃ ምላት ቤት ግርድና ገባች። ያንኮበር ሚካኤል አለቃ ናቸው፤ አለቃ ምላት በዚህ አገር ክቡር ናቸው እንደ ጳጳስ። ልጅ እግር ናት፣ ማለዳ ግብር ውሀ ወጥተዋል ከጓደኞቿ ጋራ

“ዛሬ እንዲያው ሲጫዎትብኝ አደረ ቅዠት።”

“ምንድነው?”

“ኧረ እንዲያው ምኑን አውቀዋለሁ? – ከብልቴ ጠሐይ ወጣች” አለች

እነዚያ ልጃገዶች ሣቅ! ሃይ! ሃይ! ሣቅ!። እየተሳሳቁ እቤት ገቡ። ጠሐይ ከብልቴ ወጣች አለች ሲሉ ያ የቤቱ ምስለኔ ሰማ። ኻለቃ ምላት ዘንድ ገባ፤

“ኧረ ጌታዬ ይች ዕንግዳ ገረዳችን ጉድ አመጣች!”

“ምን አረገች – ምን አረገች”

“ጠሐይ በብልቴ ወጣች አለች። አሁን አሽከሮቻችን ሁሉ ይሳሳቃሉ” ብሏቸዋል።

“እህ! ታዲያ ይች ከኛ ዘንድ ምን አላት? ኸላይኛው ቤት ውጪ በሏት” አሉ።

አንኮበር ቤተ መንግስቱ ኸላይ ነው፤ ጉባ ነው ቤተ መንግስት ያለበት። (አንኮ ኦሮሞይቱ ባላባት ናት፤ የሷ ከተማ ናት አንኮበር። እሷን ወግተው አስለቅቀው የሣህለ ሥላሴ አያታቸው ገቡ።)

ተመለሰ ሄደና

“ኧረ ጌታ እኮ መልካም ተረጎሙላት”

“ምናሉ?”

“ኸላይኛው ቤት ውጪ በሏት፤ ከኛ ምናላት? ብለው አሉ”።

ጓደኞቿ ሁሉ ሰምተዋል ተሳሳቁ።

ውሀ እሚቀዱት ከቤተ መንግሥቱ ጋር ካንድ ነው እታች ከሚካኤል ግርጌ ነው። ይችም ዕንግዳዋ ወንዝ ወረደች አንድ ቀን። እነዚያ የቤተ መንግሥቱ ሥራ ቤቶች የማያውቋት ናቸውና

“ይችም የናንተ ናት?”

“አዎ”

“የየት አገር ናት?”

“ኧረ ይቺማ ጉድ ያላት ናት! ከብልቴ ጠሐይ ወጣች ብላ እልም አይታ፣ ጌታ ቢሰሙ ኸላይኛው ቤት ውጪ ብለው አሏት ተባለ ትርጓሜው”።

አለቃ ምላትን መላው ሸዋ ይጠብቃቸዋል አነጋገራቸውን። እኒያ ሥራ ቤቶች ሰሙና ወጡ፤

‘ኧረ አለቃ ምላት ቤት አንዲት ገረድ ገብታለች! … እንዲህ እንዲህ ብላ አለመች አሉ…ኸላይኛው ቤት ውጪ ብለው ተረጎሙ አሉ’ ብለው ማውራት። የሣህለ ሥላሴ ባለቤት የነኃይለ መለኮት የነሰይፉ እናት ሰምተው፤

“ጥሩልኝ ያችን ልጅ” ተጠራች። መጣች።

“አገርሽ የት ነው?”

“መንዝ”

“ኸኔ ጋር አትቀመጭም ልጄ?”

“ምን ከፋኝ”

“ተቀመጭ። በሉ ጥጥ አምጡላት – የጅ ስራ ታግባ”

ዛዲያ የሸዋ ሴት ለእጅ ሥራ የጥጥ ነገር እንዲያ ነው፤ ደስ አሰኝቷቸዋል። ምንጣፉን ልብሱን እሳቸው ካሉበት ተኝ ብለው ሰጧት።

ኸልጆቻቸው ሰይፉን ነው የሚወዱ ሴቲቱ። ያ ጠሐይ ከሰይፉ እንዲወለድላቸው፤ ‘እንዲህ ያለች ልጅ ይዤልሃለሁ – እንዲህ ያለች እንዲህ ያለች’ ብለውታል ለሰይፉ።

ሰነበተች። አንድ ቀን ‘ማታ እልክለሃለሁ’ ብለውታል። እንግዴህ ከሣህለ ሥላሴ ቤት ግብር ይበላሉ ልጆቹ ኻባታቸው ቤት። በልተው ጠጥተው፤ ሽንጥም ታናሽም ቢሆን ደሞ ይጨመርና ጠጁ ይሆንና መሶቡ ወጡ መጥቶ – የልጆች ቤት አለ – በላይ ኃይለ መለኮት ይቀመጣል፤ ቀጥሎ ሰይፉ ነው፤ በወዲያ በኩል ዳርጌ፣ ደሞ ኃይሉ ነበሩ የይፋት – እነዚያ ይቀመጣሉ። ባለሟሎች ይቀመጣሉ። የቀረው ይቆማል። እንደገና ግብር ይገባል፤ ቅልጥ ይላል።

እናቱ ያቺን ሴት ለሰይፉ ወሰዱና ሰጡ – ሄዳችሁ ኸሰይፉ ምኝታ አስቀምጧት አሉና፤ ላኩለትና፤ መጥታ ተቀምጣለች። ሰማ። ሰይፉ የሚወዳት ሌላ ሴት አለችው።

“ወንድሜ የምትመጣ ሴት አለችብኝ?” አለ ኃይለ መለኮትን።

“የለችብኝም።”

“እሜቴ አንዲት ሴት መርተውብኛል። የኔ እገሊት ትመጣለች፤ አሁን ተመልሳ ሁለተኛ አላገኛት፤ እባክህ አንተ ውሰድልኝ።”

“እኔ ምን ቸገረኝ!” ኃይለመለኮት።

ወጣችና ልጅቱ ከኃይለመለኮት ምኝታ ገባች። በበነጋውም መጣች፣ ኸዚያው። በበነጋውም መጣች፣ ኸዚያው። ምኒልክ ተጸነሰ።

ከሰይፉ ጸነሰችልኝ ብለው ደስ ብሏቸው ሳለ እናትዮዋ፤

“ከኃይለ መለኮት እኮ ነው የጸነሰችው!” አሏቸው ሥራ ቤቶቹ።

“እንደምን?!”

“ሰይፉ አይሆንም ብሎ”

“ጥሯት” አሉ።

“አንቺ ከማን ነው ያረገዝሽው? ምነው እኔ የሰደድኩሽ ከሰይፉ አይደለም ወይ?”

“እሱማ ሌላ አለችብኝ ብሎ ለኃይለ መለኮት ሰጠኝ።”

በእግር ብረት! ታሠረች።

ኋላ እኛ አማችየው የሣህለ ሥላሴን ሴት ልጅ ያገቡ ሰሙ።

“ምነው እመቤቴ! ምነው በሴት ልጅ እንዴት ይጫወታሉ!”

“እ! ወንድማማቾቹን ልታጋድል – ከኃይለ መለኮት አረገዝኩ ትላለች!”

“ታዲያ እነሱ ይተዋወቃሉ … ሰይፉ አይሆንም ሲል ጊዜ  ምንታርግ .. ” አሉ፣ አስለቀቁ።

ሣህለ ሥላሴ ሰሙ፤ መጸነሷን ሰሙ። ምኒልክ ተወለደ። ስትወልድ ጊዜ፤ ጐረቤላ (ኻንኮበር ማዶ ጉባው ነው) ቦታ አደረጉና ድርጎ አመላላሽ አርገው፣ ጠባቂ ሁሉን አደረጉ፤ እዚያ አስቀመጡ። ሰንብተው ‘አምጡ አሳዩኝ’ አሉ። መጣ ያ ልጅ።

አዩ “ምን ይልህ” ያሉ ሣህለ ሥላሴ ናቸው። “እንግዲህ አንተን ሸዋ ምን ይልህ? ሸዋ ምን ይልህ!” አሉ። ‘ምኒልክ’ ያለ ተማሪ ነው – ለቅኔ – በድሮው ምኒልክ። እሳቸው ያሉ ‘ምን ይልህ’ ነው።

ምኒልክ ያስራ ሁለት ዓመት ልጅ ናቸው እጃቸውን ሲሰጡ ለቴዎድሮስ። ቴዎድሮስ

“አባትህ ምናለህ? ምናለህ እንዲያው ምን ነገረህ?” ቢሏቸው፤

“ምንም የነገረኝ የለ፤ ይችን” – ካንገታቸው ክታብ – “ይችን ሰው አይይብህ ብለውኛል እንጂ።”

አለቃ ለማ

1959 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ። ፲፱፻፶፱። ገጽ ፭-፲፪።

“ወደ አዲስ አበባ” (ወግ)

“ወደ አዲስ አበባ”

በሣህለ ሥላሴ ብርሃነማርያም

.

.

አባ ፍራንሷ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ ከመጡ በኋላ ዘመድ ቤት አስቀምጠውኝ ያን ጊዜ “ሐኪም ቦራ” ተብሎ ይጠራ በነበረው፣ በዛሬው ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል እንድታከም አደረጉ። ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እሳቸው የሚያርፉት ካቴድራል (ልደታ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን) ስለሆነ እዚያ ቆዩ። የበሽታዬ ዓይነት ምን እንደነበረ ባይነገረኝም ባጭር ጊዜ ውስጥ ታክሜ ተፈወስኩ።

ከዚያ በኋላ ከአባ ጋር ወደ እምድብር ለመመለስ በምጠባበቅበት ጊዜ ወደ ክፍላቸው አስጠርተውኝ፣

“ልጄ … ወደ እምድብር ለመመለስ ትፈልጋለህ ወይስ እዚሁ አዲስ አበባ ቀርተህ ለመማር ትሻለህ?” ሲሉ ጠየቁኝ።

የሚቀልዱብኝ መስሎኝ ዝም ብዬ ተመለከትኳቸው። ፍጹም ያላሰብኩትና ሊሆን ይችላል ብዬ ያልገመትኩት ነበር። ከእምድብር ሚሲዮን ንፍሮ ተገላግዬ እዚህ አዲስ አበባ ልቀር? እንደ አዲስ አበባ ሰው ሁሉ እንጀራና ወጥ ብቻ ሳይሆን ያንን የቀመስኩትን የፈረንጅ ፉርኖ እየገመጥሁ ጣፋጩን ሻይ እየጠጣሁ ተንደላቅቄ ልኖር? ፈጽሞ አልመስልህ አለኝ።

“እዚህ ለመቅረት ከፈለግህ ላዛሪስት ሚሲዮን አስገባሃለሁ ልጄ” አሉኝ፤ “እና ምን ይመስልሃል?”

ደስታ ፈንቅሎኝ፤ “እውነትዎን ነው ወይ አባ?” አልኳቸው።

ያን ከፊታቸው የማይጠፋውን ፍልቅልቅታ እያሳዩኝ፤

“አዎን ልጄ … ላዛሪስት ሚሲዮን ውስጥ ላንተ የሚሆን አንድ ቦታ አይጠፋም” አሉኝ።

“ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ አባ!”

በማግስቱ ይሁን በሠልስቱ ወደ ላዛሪስት ሚሲዮን ለመጓዝ ከካቴድራል ወጣ ብለን ጋሪ አስቆምን። የዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ ዋናው የሕዝብ ማመላለሻ ጋሪ ነበር። እነ ኩርኩር (ባለ ሦስት ጎማው ማጓጓዣ)፣ እነ አውቶቡስ፣ እነ ሚኒባስና ውይይት ገባ አልገቡም። ፈረንጆችና ጥቂት ዘበናይ ኢትዮጵያውን ሹማምንት በታክሲ ይጓዙ እንደሆነ ነው እንጂ ሌላው የከተማው ነዋሪ በሙሉ፣ ከእግረኛው በስተቀር፣ በጋሪ ነበር የሚጓጓዘው … ከፒያሳ መርካቶ፣ ከለገሐር ጉለሌ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና፣ ከመርካቶ ኮልፌ፣ ወዘተርፈ።

ፈረሶቹ አስፋልቱን መንገድ ከኮቴአቸው ሥር በተገጠመላቸው የብረት መጫሚያ እያንቋቁ ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ የሚል ድምፅ እያሰሙ ሲያልፉ እስከ ዛሬ ድረስ በውስጥ ጆሮዬ ሲያስተጋባ ይሰማኛል። ስንቱን ጀግና ከጦር ሜዳ እንዳላደረሱ ሁሉ፣ የስንቱን ንጉሥ ስም አባ ዳኘው፣ አባ ዲና፣ አባ ታጠቅ፣ አባ ጠቅል እያሰኙ እንዳላስጠሩ ሁሉ እነ ዳማ፣ እነ ጉራች፣ እነ ቦራ፣ እነ ሻንቆ፣ ጣሊያን ባመጣው አዲሱ ሥልጣኔ ተዋርደው የጋሪ ጐታች ሆነው ቀሩ።

ፊት ለፊት እንጂ ግራና ቀኝ እንዳያዩ ለዓይናቸው ከለላ ይደረግላቸዋል። የጋሪዎቹ መቀመጫዎች በኋላ ዘመን በአሥመራ ከተማ እንዳየኋቸው የሚደሉ ባይሆኑም ለክፉ የሚሰጡ አልነበሩም። ባለጋሪዎቹ ከአናታቸው ቆብ፣ ከእጃቸው ጅራፍ አይለያቸውም። ደሞም ይዘፈንላቸዋል፤ “ባለጋሪው … ባለጋሪው … ቶሎ ቶሎ ንዳው …” እየተባለ። አቤት ዘፈኑ ለጆሮ ደስ ሲል!

አንዱን ባለጋሪ አስቁመን አባና እኔ ጋሪው ላይ ተሳፍረን ጉዞ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሆነ። ላዛሪስት ሚሲዮን የሚገኘው ከእንጦጦ ጋራ ሥር ነበር። “ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ … ቂብ ቂብ” የሚል ድምፅ እያሰማ ተጉዞ ተጉዞ ከሚሲዮኑ መግቢያ በር አደረሰን። አባ ሂሳቡን ከፈሉትና ወደ ምድረ ግቢው አመራን።

ከእኔ በፊት ከየቦታው ተመልምለው መጥተው እዚያ የሚኖሩ ወጣት ተማሪዎች ምድረ ግቢው መሐል ላይ ባለው ሜዳ የእግር ኳስ እየለጉ ሲጫወቱ አየን። ይንጫጫሉ። አንዳንዶቹ በእኔው እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። አንዳንዶቹ ያበጡ ጐረምሶች ሲሆኑ የተቀሩት ከእኔ የሚያንሱ ትንንሽ ልጆች ናቸው።

አባና እኔ ኳስ ጨዋታውን መልከት ካልን በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ክፍል አመራን። እዚያ የነበሩት ፈረንጅ ካህንና አባ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሲጨዋወቱ እኔ ዝም ብዬ እሰማቸዋለሁ። የፈረንሳይኛ ፊደል የቆጠርኩ ቢሆንም በዚያን ጊዜ ቋንቋው አይገባኝም። ይሁን እንጂ አባና ሌላኛው ካህን ሲነጋገሩ ቋንቋው የተለምዶው ሙዚቃዊ ቃና ነበረው።

አባ ተነጋግረው ሲጨርሱ እኔው ተዚያው ትተውኝ ወደ ካቴድራል ማረፊያቸው ተመለሱ። ግቢውን የሚያስተዋውቀኝ ልጅ ተሰጥቶኝ እየተዘዋወርን ሚሲዮኑን ያስጐበኘኝ ጀመር። ጸሎት ቤቱን፣ የመኝታና የጥናት ክፍሎቹን፣ ቤተ መጻሕፍቱን፣ በሲሚንቶ የተሰሩ ንጽሕና ቤቶቹን አንድ በአንድ አስጐበኘኝ።

ከዚያን ቀን ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ያህል አብረን መኖር የጀመርነው ወጣቶች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጣን ነበርን። እና ሁላችንም አብረን ውለን አብረን እናድራለን። ወደ ተፈሪ መኰንን ት/ቤት እየተመላለስን እንማራለን። እሁድ እሁድ ወደ እንጦጦ እየወጣን ወይም ሸጎሌ ወደተባለው ሜዳ እየኼድን የእግር ኳስ እንጫወታለን።

የሚያስተዳድሩንና ተንከባክበው የሚያሳድጉን ካህናት አምስቱ ፈረንሳውያን ሲሆኑ አንዱ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፤ አባ ዢማላክ፣ አባ ብርዬ፣ አባ ሊሙዘን፣ አባ ጃንካ፣ አባ ማርሴ እና አባ አጽብሐ።

አባ ጃንካ በጣም ጉልበተኛ ሰው ነበሩ። እኛ ሁለት ወይም ሦስት ሆነን ተጋግዘን ማንሳት የማንችለውን ሸክም እሳቸው በአንድ እጃቸው፣ ያውም በግራ እጃቸው ብድግ ያደርጉት እንደነበረ አስታውሳለሁ። ቁመታቸው መሐከለኛ ሆኖ አጥንታቸው ሰፊ፣ ምንም ነገር ሊነቀንቃቸው የማይችል የግንብ አጥር የመሰሉ ነበሩ። ታንክ በመሰለ ከባድ መኪና ለሚሲዮኑ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ገዝተው የሚያመጡት እሳቸው ናቸው። እሁድ እሁድ ወደ እንጦጦ ጋራ ወይም ወደ ሸጎሌ ሜዳ በምንጓዝበት ጊዜ የፈረንጅ ኮርቻ በተጫነ ፈረስ ላይ ተቀምጠው የሚመሩን እሳቸው ናቸው።

አባ ማርሴ በሚሲዮናችን ብቻ ሳይሆን በተፈሪ መኰንን ት/ቤት ጭምር በጣም ዝነኛ ሰው ነበሩ። አባ ማርሴ የፈረንሳይ ተወላጅ ቢሆኑም አማርኛና ግእዝ አሳምረው ያውቁ ነበር። እንዲያውም በተፈሪ መኰንን ት/ቤት፣ ያውም በሁለተኛው ደረጃ፣ የአማርኛ ሰዋስው መምህር ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በአንዱ ብብታቸው ሸጉጠው፣ ከዘራቸውን በአንድ እጃቸው ይዘው ቢስኪሌታቸው ላይ ወጥተው እያሽከረከሩ ነበር ወደ ተፈሪ መኰንን ት/ቤት የሚጓዙት። እኛ ግን ወደ እዚያ የምንኼደውና ከዚያም ወደ ማታ ጊዜ የምንመለሰው አርባ አምስት ደቂቃ ያህል በእግር እየተጓዝን ነበር።

በመንገዳችን ካኪ ዩኒፎርም የለበሱ ልጃገረዶች ያጋጥሙናል። መጽሐፎቻቸውንና ደብተሮቻቸውን እንደ ሕፃን ልጅ በደረታቸው ታቅፈው ዱብ ዱብ እያሉ ያልፉናል። እኛ ሚሲዮን ቀጥቅጦ ያሳደገን በመሆናችን ቀና ብለን ልናያቸው ባንደፍርም እነሱ ግን ፈጽሞ አያፍሩንም ነበር። እየተሳሳቁ፣ የአቧራ ብናኝ እያስነሱ ወደ እቴጌ መነን ት/ቤት ያመራሉ። እቴጌ መነን ት/ቤትና ተፈሪ መኰንን ት/ቤት ቅርብ ለቅርብ ናቸው። በዚያን ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በተለያየ ት/ቤት እንጂ በአንድ ት/ቤት፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ጐን ለጐን ተቀምጠው መማር የማይታሰብ ነበር … በኋላ ዘመን ቢሻርም ቅሉ!

በትምህርት ቀናት ለምሳ ወደ ሚሲዮናችን ለመመለስ ሰዓቱ ስለማይበቃን እነ አባ ማርሴ ከተፈሪ መኰንን ት/ቤት አቅራቢያ ሆቴል ተኮናትረውልን ምሳችንን እዚያ እንበላ ነበር። ለእያንዳንዳችን ሃያ አምስት ሳንቲም ይሰጠን ነበር። ለምሳ መብያ። ያ ሃያ አምስት ሳንቲም ተአምር ይሰራ ነበር ለማለት እደፍራለሁ … ከዛሬው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር።

ሙሉ እንጀራ በሽሮ ወጥ በአስር ሳንቲም፣ በክንድ የሚለካ ፉርኖ በአስር ሳንቲም፣ በስንዝር የሚለካው በአምስት ሳንቲም፣ አንድ ብርጭቆ ሻይ በአምስት ሳንቲም ይገዛ ነበር። ሙሉ እንጀራ በሥጋ ወጥ ለመብላት የሚሻ በሃያ አምስት ሳንቲም አዝዞ ጥስቅ አድርጎ ይበላ ነበር። የዚያም ዓይነት ዓለም ነበር … በሺ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ!

በተፈሪ መኰንን ት/ቤት የሚማሩት ባልደረቦቻችን፣

“የአባ ማርሴ ልጆች

አንሶላ ለባሾች!”

እያሉ ያፌዙብን ነበር።

ይህም ከበስተጀርባው ታሪክ አለው። በበጋው ወራት በተለይም በታህሳስ ወር ጠዋት ጠዋት በጣም ይበርድ ነበር። በዚህ ምክንያት አሳዳጊዎቻችንን አስፈቅደን ለመኝታ የምንጠቀምበትን ነጭ አንሶላ ደርበን ነበር ወደ ትምህርት ቤታችን የምንጓዘው። ካፖርት እንዳንገዛ ከአቅማችንና ከደረጃችን በላይ ነው። ሌላም የብርድ መከላከያ አልነበረንም።

ታዲያ በአዳሪነት፣ ያውም ያለ ክፍያ ተሞላቅቀው የሚኖሩት ባልደረቦቻችን ችግራችንን ባለመረዳት ”የአባ ማርሴ ልጆች፤ አንሶላ ለባሾች“ እያሉ ያፌዙብን ነበር።

እነሱ አላወቁም እንጂ ሌላም የብርድ መከላከያ ነበረን። በዚያን ጊዜ ከመሐከላችን ጫማ የሚያደርግ ማንም የለም። ሁላችንም በባዶ እግር ነበር የምንኼደው። ወደ ት/ቤት ስንጓዝ በመንገዳችን የሚገኝ አንድ ደረቅ ወንዝ ስለነበረ በታህሳስ ወር ከዚያ ስንደርስ ቅዝቃዜው በጣም ስለሚበረታ ከሚሲዮናችን ስንነሳ አሮጌ ጨርቅ ይዘን እንመጣና እግራችንን በዚያ ጨርቅ ሸፍነን ሰርጓዳውን ስፍራ እናልፋለን።

ጨርቁን ወደ ትምህርት ቤታችን ይዘን ብንኼድ የባሰውን መሳቂያ ስለምንሆን ደረቁን ወንዝ ከተሻገርን በኋላ ጥሻ ውስጥ ወሽቀነው እንኼድና ማታ ስንመለስ ይዘነው ወደ ሚሲዮናችን እናመራ ነበር።

.

ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

.

[ምንጭ] – “ፍኖተ ሕይወት”። 2001 ዓ.ም። ገጽ 51-56።

“የፈላስፋው ውሃ” (ወግ)

“የፈላስፋው ውሃ”

.

.

አንድ ንጉሥ እጅግ አጥብቆ የሚወደው ፈላስፋ ነበረው። አብሮት የሚጋበዝ፣ የሆነውን የሚሆነውንም ሁሉ የሚያማክረው።

በጤናና በስምምነት አያል ወራት አያል ዘመናት ሲኖሩ አንድ ቀን ከገበታ ላይ ለምግብ ተቀምጠው ሳለ ፈላስፋኑ አንስቶ “አዬ!” አለና እጅግ ተከዘ። ወደ ምግቡም እምብዛም ነፍሱ አልፈቀደ። በዚህን ጊዜ ንጉሡ ደንግጦ ያመመው መስሎት “ምነው በደህናህን?” ብሎ ጠየቀው።

ፈላስፋኑ እየመላለሰ ‘አዬን’ ብቻ ያዘ።

ንጉሡም “ደሞ አመመህን?” ቢለው እንኳን “አላመመኝም” ብሎ መለሰለት። “እንግድያውስ አሁንም አሁንም እየተከዝህ ‘አየ’ የምትለው ምን ብትሆን ነው?” ብሎ መረመረው።

ቀጥሎም ‘አዬን’ ብቻ ያዘ።

ንጉሡም ገሚሱ ቁጣ በገሚሱ ጭንቀት “እንደዚህ ያለ ምንድር ነው? ሯ!እባክህን ንገረኝ ምንድር ነው ብልሃቱ?” ብሎ ቢለው

“ክፉ ዘመን የሚመጣብን ቢሆን ነው እንዲህ የምሆነውን የማዝነው” ብሎ ፈላስፋኑ አለው።

የባሰውን ንጉሡ በዚህ ነገር ተጨንቀ። ንጉሡም በፍጥነት ነገሩን እንዲረዳው ፈለገ። ፈላስፋው ግን መልሶ ‘አዬውን’ ያዘ። ተዚህ ወዲህ ንጉሡ አጥብቆ ፈራ። “ሯ! እባክህን ውሃ አታርገኝ ንገረኝ” አለው።

“እስከ ሦስት ዓመት እንደለመድነው ጊዜ ሁሉ ነው። ቀጥሎ ግን የሚዘንበው ዝናብ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ሰውም ሆነ እንስሳም ሆነ ፍጡር የተባለ ሁሉ ይመርዛል። ውሃን የጠጣ ሁሉ ያብዳል። ወንዙ ምንጩ ባሕሩ ዝናቡ ሲዘንብበት ይመረዛልና። ስለዚህ ውሃ የጠጣ ሁሉ ያብዳል። ተዚህ የበለጠ ምን የሚያሳዝንና የሚያስተክዝ አለ?” ብሎ አረዳው።

ንጉሡም እንደ ፈላስፋው አንገቱን ደፍቶ ተራውን ይተክዝ ጀመረ። ቀጥሎ ጥቂት ጥቂት ተንፍሶ “ስማ እንደዚህ ያለ የማይቻል መዓት ሲመጣብነ ጊዜ ምን ይበጀናል?” ብሎ አማከረው።

“ለዚህማ መቼስ ምን አቅም አለኝ! ያሳየኝ ይህ ነው። ባዋጅ ‘የደህናውን ዝናብ ውሃ ጉድጓድ እያበጀህ አስቀምጥ’ ተብሎ ማስታወቅ ይሻል ይመስለኛል … ለክፉው ዘመን መውጫ እንዲሆን” ብሎ የተቻለውን ምክር መከረ።

አዋጁም ሳይውል ሳያድር ተመታ። ከሕዝቡ የፈራ ጉድጓድ ይምስ ጀመር። ነገሩን የናቀ ግን፣

“ተወው! አመሉ ነው። ሁልጊዜም አዋጅ ይመታልና መቼ አንድ ነገር ሁኖ ያውቃል? ደግሞ ያሁኑስ የሚያስደንቅ አዋጅ ነው! ተእግዜር ጋራ ተማክረዋልን? ” እያለ ያፌዝ ጀመር።

ከቤተ መንግሥቱ ደሞ ጉድጓድ ሁሉ ተሰናድቶ ተምሶ የደኅናውን ዝናብ አከማቹበት። በቁልፍም ተቆለፈ። የፈሩትም እንደዚሁ አደረጉ።

ያ ቀን መድረሱ አልቀረምና ደረሰ። ገና መዝነብ ሲጀምር በየወንዙ በየምንጩ በየባሕሩ ሲጥልበት ጊዜ ተመረዘ። ያን ውሃ የጠጣ ሁሉ ማበድ ጀመረ። ሲል ሲል እብደቱ እየባሰ ሄደ። የእብደት ብዛት እየገነነ ሄደ።

ነጋዴ ንግድነቱን ትቶ ወደ ሌላ ሆነ። አራሽም እርሻውን ትቶ ወደ ሌላ ሆነ። ልጅም አባት እየተወ ወደ ሌላ ሆነ። ካህናትም ክህነታቸውን ትተው ወደ ሌላ ሆነ። ቁም ነገር የነበረው ጨዋ ሆነ መኳንንትም ሆነ ሊቃውንትም ውልን ትተው ወደ ሌላ ሆነ። ለእብደቱ ዲካ ጠፋበትና ሁሉም ዝብርቅርቁ ወጣ።

ተዚህ ወዲህ በጐራ በጐራ እየተለየ፣

“ነጋሪት ምንድር ነው? ቆሪ እንጨት አይዶለምን? በሉ ነጋሪቱንም ጠፍሩ! መለከቱንም እምቢልቴውንም አብጁ!” አሉ።

በየጐራው አበጀ። ሁሉም ተተበጀ በኋላ ነጋሪቱን እየጐሸመ፣ መለከቱን እያንጠራራ፣ እምቢልቴውን እየነፋ … ሕዝቡ ሁሉ መቸም አብዷልና፣

“ንጉሥ አልነበረነም ወይ? አለ እንጂ! ወዴት ነው? ከግቢው ተቀምጦ ይንፈላሰሳል!” አሉ።

ይህነን ሁሉ ንጉሡም ፈላስፋውም ያያሉ ይሰማሉም።

ሕዝቡም እንዳልነው ጐራ እየለየ ነጋሪቱን እያስጐሸመ፣ መለከቱን እያንጠራራ፣ እምቢልቴውን እያስነፋ፣

“ንጉሣችን ወዴት ነው? በል ሳብ ወደ ግቢ!” እያለ ይስብ ጀመር።

ገቢዎች ይኼንን ነገር ባዩ ጊዜ በንጉሡ ታዛዥ የግቢ በር ሁሉ እንዲዘጋ ታዘዘ። እነዝያም እብዶች በደረሱ ጊዜ በሩ ተዘግቶ አገኙ።

“ደሞ ዘግቶታልና! አዎን ሊተርፈን? ሯ!” … በድንጊያም በዱላም ያን መዝጊያ ተለቀቁበት።

ንጉሡም ይኼንን ባየ ጊዜ ለፈላስፋኑ “አንተ! እነዚህ እብዶች ሊገሉን ሊፈጁን ደረሱብን! ምን ይበጀን ትላለህ?” ብሎ አማከረው።

“ንጉሥ ሆይ! እኔማ በጉድጓድ ደኅናውን ውሃ እናጠራቅም ለክፉው ዘመን መውጫ እንዲሆን ብየ መክሬ ነበር። ለሕዝቡም ይኼነኑን አስታወቅነ ይሆናል ብየ ነበር። ሳይሆን ሲቀርማ ያነኑ የሚያሳብደውን ውሃ ጠጥተን አንድ እንምሰል!” አለ።

እነሱም ያነኑ የሚያሳብደውን ውሃ ልጅ ተሾልኮ ይሂድና በቅምጫና ይዞልን ይምጣ ተብሎ ሰደዱት። ሄዶ ይዞ መጣ። እንደ ጠበል ተሻምተው ጠጡ። ወዲያውም አበዱ።

ንጉሥ መዝለልና መቀባጠር ጀመረ። ወዲያውም ወደ ግቢው በር ሂዶ፣

“ይኼንን በር ማን አባቱ ነው የዘጋው?” አለ … እርሱ ራሱ ዝጉ ብሎ ሲያበቃ!

ወዲያው ብዋ አርገው ከፈቱ። ንጉሡ እየዘለለ እየለፈለፈ እንደነሱ መስሎ በሩን በወጣ ጊዜ የተሰበሰበው ፍጡር ሁሉ መንገድ ለቆ ገለል ብሎ ዳር እስከ ዳር “እልል!” አሉ። ገሚሱ ያልሰማ “ምንድር ነው ነገሩ?” ብለው ሲጠይቁ፣

“ንጉሣችን አብደው ነበር ሽረዋል” ተባለ … ዳር እስከ ዳር እልልታውን አቀለጠው!

ክፉውን ዘመን ሁሉ ሲያብዱ ኖሩ።

ደኅናው ዘመን ሲገባ ሁሉም እየስፍራው እየሙያው እየደምቡ ገባ። መንግሥቱም አገሩም ሁሉም ረጋ።

.

[ምንጭ] – Major J. Eadie. 1924. “An Amharic Reader”. pp. 29-33.

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ” (ክፍል 2)

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ”

በደብተራ ኀይሉና በሐጅ አሊ

(1800 ዓ.ም)

.

(ከክፍልአንድ የቀጠለ)

.

.

ከዚህ በኋላ ከዛር ንጉሥ ሊዋጉ ሔዱ። ገና ሳይደርሱ ላኩባት። ሲልኩባት፣

“በዦሮ የሰሙን በዓይን ሳያዩት አይቀርምና … ታዪን መጣሁ” ብለው ላኩባት።

እርሷም ስትመልስ፣

“የኔም ሰው በነፍጥ ያልቃል። የርስዎም ሰው በሟርት ያልቃል። እኔም አልሞትም እርስዎም አይሞቱ … ምነው በፍቅር ብንለያይ አይሻልም?” ብላ ግብር ሰደደችልዎ።

ከዝያ በኋላ “ክፉ የተናገረች ታየኝን ነበረች!” ብለው ተመለሱ። ከቤታቸው በወጡ በ፯ ዓመት ቤታቸውን ገቡ።

ዳግመኛ የእስክንድርያ ንጉሥ የአሕዛብ ጸላት ቢነሣበት ዜናዎን ሰምቶ ነበርና “መጥተህ እርዳን” ብሎ ላከበዎ።

ተነሡና ሲሔዱ የ፫ ቀን መንገድ እንደሔዱ ዘንዶ እባብ ያለበት አገር ደረሱ። እየረገጡት የሚሔዱ ነው።

ከዚህ በኋላ ቤት የሚያህል አሞራ በኢየሩሳሌም አለ ያነን አስነድተው አመጡት። በእግዜር ፈቃድ ያነን በፊተዎ አደረጉትና ቢሔዱ እባቡና ዘንዶውን እየለቀመው ይሔዱ ዠመረ። የእባቡንና የዘንዶውን ምድር ሲጨርሱ ከደህናው ምድር ሲደርሱ ያም ጠላቱ መምጣተዎን ቢሰማ ሸሸ ‘ይዩልኝ’ ብሎ። የላከውም ሸሸ ‘እኔን ይጨምሩኛል’ ብሎ።

ከዚህ በኋላ ያሰቡትን ሳይደርሱ የማይቀሩ ንጉሥ ናቸው “ቀራንዮን ስሜ ኢየሩሳሌምን አይቼ አመጣለሁና እሔዳለሁ” አሉ።

ሹማንምቱ ገብተው “አይሂዱ ይቅሩ” ብለው መከሩ።

“ተቀረሁ በኢየሩሳሌም ለውዝ ገውዝ የሚሉ ሽቱ አለ ብለውኛልና ልመለስ አምጡልኝ” ቢሉ ሒደው አመጡልዎ ተመለሱ።

ከዚህ በኋላ የንጉሥን ብርታት ቢሰማ የሮም ንጉሥ “ልጅዎን ይስጡን” ብሎ ላከ። ማጫዎን ፵፰፼ መድፍ፣ ነፍጥ፣ ቁጽር የሌለው እቃ የማይታወቅ ሰጠ። ብዙ ነው። እጅግ የሚወዱዋት ልጅ ነበረችና ለርሱ ዳሩዋት።

ሲዘምቱም በ፼ በ፼ ነፍጡ መድፉ እየተቈጸረ ያሲዙ ነበረ። ፵ ፵፼ አኽያ በዳውላ ወርቅ እየተጫነ ከየደረሱበት እያሳመኑ የወርቅ ቤተ ክርስቲያን እየሰሩ፣ ደጅ አዝማች እየሾሙ፣ መምሕር ካህናት እየሰሩ ይሔዱ ነበርና ከባሕር ወዲህ ያለን ሁሉ አገር አሳመኑት። ከኢትዮጵያ ምድር አንድ አልቀረዎም ሁሉን አሳመኑት።

ክፉ ወንድ ልጅ ነበረዎ።

‘እሱ ይነግሣል’ የሚሉ ንግር ነበረና አይወዱትም ነበረ። ሀብተዎን ሁሉ ስለዚህ ምክንያት ለሴት ልጅዎ ይሁን ብለው ሮም ሰደዱት።

“እርሱም በሀብቱ ይንገሥ” አሉ።

እርሱም መጥቶ ነገሠ። የርስዎም እቃ ተመልሶ ሮም ወረደ።

ተፈጸመታሪክዘጸሐፎኃይሉወዘአጽሐፎሐጅአሊ።

.

ደብተራ ኀይሉ እና ሐጅ አሊ

1800 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – Bibliothèque Nationale። Eth Ms 144። ቅጠል 19-20።

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ” (ወግ)

“ያጼ ዳዊት ጀብዱ”

በደብተራ ኀይሉና በሐጅ አሊ

(1800 ዓ.ም)

.

ክፍል አንድ

.

አጼ ዳዊት በነገሡ ጊዜ ግብጽ ያለው የስጥንቡል ንጉሥ፣

“ትገብር እንደሆን ገብር አትገብር እንደሆን አታመልጠኝም ቻለኝ መጣሁ” አለና ላከብዎ … በአጼ ዳዊት።

እርስዎም “ብትመጣ ጦር አለኝና እችልሃለሁ” ብለው ላኩበት።

እርሱም ሳይነሳ የኢትዮጵያን ውሀ ሁሉ በኖራ መልሰው አድርቀው ወደ ምሥራቅ ሰደዱትና ውሀ አጡ ግብጻውያን ሁሉ። ከዚህ ወዲያ ማረኝ ሲል ላከ።

“መማለጃኸንም በ፼ ግመልና በቅሎ አኽያ የተጫነ ወርቅ ብርና ግምጃ ተቀበለኝ። በውሀ ጥም አንለቅ። ግዱን በፈጠረህ አምላክ ማረኝ” ብሎ ላከ።

እርስዎም ሲልኩ፣

“ማረኝስ ታልኸኝ ብር ወርቅ ግምጃ ምን ይሆነኝ? መማለጃየንስ ጌታዬ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል እቃውን ሁሉ፣ የሰማዕታትን ዓጽም፣ ስዕርተ ሐናን፣ የሙሴን ጎሞር ከነጎፍላው፣ የዮሐንስን መስቀል፣ ሉቃስ ወንጌላዊ የሳላቸውን ስዕል፣ የቀራንዮን መሬት ከሊቀ ጳጳሱ ዘንድ ልከህ አስመጣልኝ። እንታረቅ ውሀውንም ልመልስልህ። ይህ ሁሉ ያልሁህ ታልገባልኝ ውሀውንም አልመልሰልህም” ብለው ላኩ።

እርሱም ሉል አደረገና የግብር መዠመርያ ግማደ መስቀሉን፣ ኵርዓተ ርእሱን፣ የተገረፈበትን አለንጋ፣ ራሱን የተመታበትን ብትር፣ ከለሜዳውን፣ ሐሞት የጠጣበትን ቢናግሬ፣ እግሩን እጁን የተቸነከረበትን፣ የቀራንዮን መሬት ደሙ የፈሰሰበትን ጭነው። የቅዱስ ጊዮርጊስን አጽምን፣ የፈረሱን ጭራ ቢሰፍሩት ፵፪ ክንድ ሆነ። የ፳፭ አጽመ ሰማዕታት፣ ስእርተ ሐናን፣ ዮሐንስ ያጠመቀበትን መስቀል፣ ሉቃስ ወንጌላዊ የሳላቸውን ስእላት፣ የሙሴን ጎሞር ከነጎፍላው፣ ከዚኽም የሚበዛ ብዙ እቃ ሰደደልዎና ታረቁ።

ውሀንም መልሰው ሰደዱላቸው። ስለዚህ ኢየሩሳሌምን ግብጽንም አስገበሩት።

ከዚያ ወዲያ የዘንዶ ንጉሥ አለ ቢሏቸው ሠራዊታቸውን ክተት አሉና ዘመቱ እዋጋለሁ ብለው። ዘንዶም አፉን ይከፍትና ፼ ዝሆን እየገባ ሲከማች ጊዜ አፉን ይገጥመዋል። በዚህ ይኖር ነበር። ያን ጊዜ ቢደርሱ አፉን ለቆ አገኙት። ዋሻ አገኘነ ብለው ንጉሥ ከለሠራዊታቸው ገቡ።

ሲገቡ ነፍጥ ቢያስተፉ ፪ ዛሮች ተከሠቱ።

“የዘንዶ ንጉሥ አሉ ይላሉ ወዴት?” ብለው ጠየቋቸው።

“ይህ የገባችሁበት አይዶለውም” አሏቸው።

ንጉሥ ደንግጸው ከለሠራዊትዎ  ወጡ። ከዝያ ወዲያ ፰ ቀን በመድፍና በነፍጥ ቢደበድቡት አልላወስ አልቀሳቀስ ብሎ በግድ ሞተ።

ከዝያ በኋላ ምሥራቅ ምድር ሔዱ … ከፀሐይ ጋር እዋጋለሁ ብለው። ለንጉሥ የ፰ ቀን ጐዳና ሲቀረዎ ፊታውራሪው አጠገቧ ሲደርስ፣ እርሷም ከመስኮቷ ስትወጣ፣ ያነን የሰፈውን ፊታውራሪ ሠራዊት እንደ ሰም አቅልጣ ፈጀችው … ንጉሥ ሳይደርሱ።

ከዝያ በኋላ አንድስ የሚሉት አውሬ ከገደል ስር የሚኖር አለ አሏቸው … ሊዋጉ ሔዱ። የ፰ ቀን መንገድ ሲቀረዎ ፊታውራሪው ከገደሉ አፋፍ ሲደርስ፣ ገና ሳይወጣ ድምጡን ቢሰሙ፣ ግማቱ ቢሸታቸው ፊታውራሪው ከለሠራዊቱ አለቀ።

‘አንድስ አንድስ ይሸታል’ የሚሉት ከዚህ የተነሣ ነው።

(በክፍል 2 ይቀጥላል … )

ደብተራ ኀይሉ እና ሐጅ አሊ

1800 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – Bibliothèque Nationale። Eth Ms 144። ቅጠል 18-19።

“ያጼ በካፋ በግ” (ወግ)

“ያጼ በካፋ በግ”

.

.

አፄ በካፋ አንድ የሚወዱት ለማዳ በግ ነበራቸው። ሲቀላውጥ ይውልና አዳሩ ከእልፍኛቸው ነው የሚያድር። የመወደዱ ብዛት አዋጅ ወጣለት። “ያጼ በካፋ በግ በገባበት ቤት ሳይጋበዝ የቀረ እንደሆነ አይቀጡ ቅጣት እቀጣለሁ” ተባለ።

እንደ አቀማጠሉት ታውቆት ቅልውጡ ባሰበት። በቅልውጡ የተነሳ ሰው አጥብቆ ተመረረ። ቅልውጡ ቀርቶ ከደጅ የሚሰጣውን ያወድማል።

እንዲህ እያስለቀሰ ሲኖር አንድ ቀን ሲፈርድበት ከአንድ ደብተራ ቤት ዘው አለ። ደብተራው “እንኳ የመጣህልኝ” ብሎ ሲያበቃ ደጁን ዘግቶ እንክት አርጎ አረደው። ሥጋውን ዘልዝሎ ኸጓዳው ሰቀለ። የበጉ አመል የትም ሲቀላውጥ ውሎ አዳሩ ከንጉሡ እልፍኝ ነበር። ሲጠፋ ጊዜ በያለበት ፈልጉ ተባለ።

ወደ ተንኮለኛ ደብተራ እንመለስ።

የበጉን ደበሎ ብራና ፋቀው። ቀጥሎ ብራናውን በትንንሽ ቆራርጦ በቍራጮቹ፣

“የንጉሡን በግ እኔ ነኝ አርጄ የበላሁት። ጮማ ነበር። መጣፈጡም ግሩም ነው። መታረዱም ይገባዋል። መክለፍለፍ አብዝቶ ድሀ አስለቅሷልና”

ብሎ ጽፎ ቁራጮቹን ወስዶ በስውር ሰው እንዳያየው አርጎ ካደባባይ በተናቸው።

መቸም በከተማው የንጉሥ ባለሟል ጠፍቷል ተብሎ በያለበት ፍለጋ ተይዟል። ሁለት ወይ ሦስት ሰዎች ቁራጮች አይተው አንስተው አንብበው ለንጉሡ አደረሱ።

በተነበበ ጊዜ ንጉሡ እጅግ አጥብቀው ተቆጡ፡

“እንዴት አባቱ ያለ ደፋር ነው! ተማረዱ ጽፎ አደባባይ ብራናውን መበተኑ። ቆይ ሳትያዝ የቀረህ እንደሆነ”

አሉና በምስጢር አርገው፤

“ስስ ወርቅ አምጡና መዝኑ። ተተመዘነ በኋላ ወስዳችሁ ከግቢው አደባባይ ዠምራችሁ እስከ አውራው ጐዳና በትኑት። ቀጥላችሁ የታመነ የታመነ ዘበኛ ተተነሰነሰው ወርቅ እልፍ ብለው ቆባ ብለው አጐንብሶ የሚያነሳውን ሰው ይያዙ” ብለው አዘዙ።

መቼም ሌባና አጥፊ እንቅልፍ የለው የሚወራውን የሚሆነውን ሁሉ ተጠንቅቆ እህ ይላል። በብልሃቱ ብዛት የበጋቸው ሌባ የወርቅ ወጥመድ መጠመዱን አወቀ።

“ቆይ እዚህማ ብልሃት አለኝ” ይልና ቶሎ መጫምያ አሰፍቶ ታቹን ምድር የሚረግጠውን ወገን በሰም መረገው። ቀጥሎ መጫምያውን አጥልቆ ጥምጥሙን አሳምሮ ጠምጥሞ መቋምያውን ይዞ አንጓቦ ወርቅ በተዘራበት መንገድ አረጋገጡን ወደ ምድር ጫን እያደረገ እየረገጠ ወርቁ ከሰሙ ውስጥ እንዲጠልቅ ነው ብልሃቱ።

እንደዚህ እየሆነ እየተንደላቀቀ ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላለሰ። ከቤቱ እየገባ የተለጠፈውን ወርቅ እያነሳ እያስቀመጠ አንድም ሰው ሳያውቅበት ማታ በሆነ ጊዜ “እስኪ ወርቁን አንሱትና መዝኑት” ተባለ። ቢመዝኑት ቅምጥል ብሎ ጐደለ። ለንጉሡ ይኼንን ቢያሰሙ የባሰውን ተናደዱ።

ዘበኞቹም “እኛ ኩስትር ብለን ነው የጠበቅነ ዳሩ ግን አንድም ሰው አጐንብሶ ሲያነሳ አላየነ” አሉ።

ንጉሡ ቢቸግራቸው “ጠንቋዮች ጥሩ” ብለው አስመጡ። “እንደዚህ ያለ ሥራ የሚሰራ የት ነው የተቀመጠው?“ ብለው ጠየቋቸው። ከገሌ አፈር ላይ ነው ብለው አሉ።

ወታደር ሂዱ ያዙ ተብሎ ታዞ ይሄዳል ግን ማንም አያገኙ። ስለምን ደብቴ እጅግ ብልህ ነውና የሚያረጉትን ሁላ አውቆታል። ለዚህ ብልሃት ተአራት አምስት አገር አፈር አስመጥቶ ከቤቱ ውስጥ አስቀምጦ ከዝያ ላይ ይቀመጥበታል። ያገሩን አፈር እያለዋወጠ ማለት ወታደር ታዞ ሲሄድ ጠንቋዮቹ በመሯቸው ስፍራ ሰውየውን ያጡታል። የተቀመጠበትን አፈር ትቶ ከሌላ አፈር ላይ ይቀመጣል። ወታደሩም በከንቱ ማሰኑ ጠንቋዮቹም ተነቀፉ።

ንጉሡም የባሰውን ተናደዱ። ከዚህ ወዲህ ቆይ ሌላ ብልሃት አለኝ ብለው ሚስጢርዎን በሆድዎ ከተው ድግስ ደገሱ። አለቆች፣ ካህናት፣ ተማሪ፣ ደብተራ የተባለ ሁሉ ትምህርት የጠቀሰ ሁሉ ግብር እንዲበላ አዘዙ። በዚህ ማኽል የታመኑ የታመኑ ሰዎች በምስጢር አርገው መርጠው አሰናዱ።

“ድግሱ በደረሰ ጊዜ እነዚህን የተመረጡትን ሰዎች ካህናቱ ሁሉ ገብተው ሲበሉ ሲጠጡ መጠጡን በገፍ አርጋችሁ ስፍራውን ተከፋፍላችሁ ይዛችሁ ኮስተር ብላችሁ ጠብቁ። በመጠጥ ብዛት የተነሳ ያ ተንኮለኛ ለባልንጀራው ሳይለፈልፍ አይቀርምና በሰማችሁ ጊዜ ለምለም ዦሮውን በስለት ቀንጥቦ ምልክት እንዲሆን ነው” ብለው አዘዙ። “ካህናቱ ጠዋት ሲወጡ ከዦሮው ምልክት ያለበት እንዲያዝ” አሉ።

እውን እንዳሉትም በመጠጥ ብዛት የተነሳ ደብቴ ተቸነፈና ለባልንጀራው ተበጉ መታረድ ጀምሮ እስከ ወርቁ እስከ ጠንቋዮቹ ድረስ የሆነውን ሁሉ ዘከዘከለት። ይህን ሁሉ ሲዘከዝክ በዠርባው በኩል የቆመው ሰላይ ወደነሱ ዦሮውን ጣል አርጎ ኑሮ አንዱ ሳያመልጠው ሁሉን ሰምቷል። በስካር ብዛት የተነሳ ሁሉም ተረፍርፎ እንቅልፍ ወስዷቸው ያ የሰማው ሰላይ ይህን ጊዜ ነው ብሎ ለምለም ዦሮውን ቀነጠበ።

ደብቴ ብዙ እንቅልፍ ተተኛ በኋላ ዦሮው ቆጠቆጠው። በጁ ቢዳብስ ዦሮው ተቀንጥባ “አሁን ገና ተያዝሁ” ይልና አያሌ ተማሪዎችና ደብተሮች ከተረፈረፉት ለምለም ዦሮዋቸውን ቀነጠበ። እንዳይነጋ የለም ነጋ። መቼም ያ ሰላይ የደብቴን ዦሮ የቀነጠበ ለሽልማቱ ሲል የምስራችን አድርሷል። ንጉሡም ደስ ብሏቸው “ምንየ በነጋ” ብለው ቸኩለዋል።

ሲነጋ “በሉ እንግዴህ ካህናቱንና ተማሪውን ሁሉ አስወጡ። ያ ለምለም ዦሮውን የተቆረጠውን ያዙና አምጡ” ብለው አዘዙ። ካህናት በወጣ አያሌ ለምለም ዦሮዋቸው ተቆርጦ ይህንን ነገር ለንጉሡ ባስታወቁ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናደዱ። ቀጥለውም የምስራች ቀናኝ ብሎ ያለኝን ይጠራ አሉ።

በመጣ ጊዜ “በል አንተ አብደሃልን? ይህን ሁሉ ያዛውንት ጆሮ ቁረጥልኝ ብየኻለሁን” አሉት።

“እኔስ ንጉሥ ሆይ ያንድ ተማሪ ለምለም ዦሮውን ብቻ ነው የቆረጥሁት” አለ።

ንጉሡም “እንግድያውስ ይህ ሸረኛ ደብተራ ሲነቃ የሰራውን ሥራ ዦሮው አስታውሶት ተነስቶ የነዚህን ሁሉ ተማሪ ዦሮ መንድቧል” አሉ።

ተዚህ ወዲህ በደብቴ ብልሃት ተገርመው እንደዚህ ያለ ብልህ ተመቅጣት ይልቅስ ሸልሞ መሾም ይበልጣል ለመንግሥት ይጠቅማል ብለው አውጥተው አውርደው አስበው፣

“ነጋሪት ይውጣ አዋጅ ንገሩ የንጉሥን በግ የበላ ደብተራ ምሬአለሁ። ከቶም ሸልሜ እሾመዋለሁ። ላልከዳ ምያለሁ። ይምጣ አይስጋ ብላችሁ አስታውቁ” ብለው አዘዙ።

አዋጁም ተነገረ።

ደብቴ ይኼንን አዋጅ በሰማ ጊዜ አጥብቆ ደስ ብሎት ጌጡን አጋጊጦ ሲደለቅ ወደ አደባባይ ብቅ ብሎ ላጋፋሪ ለንጉሡ መምጣቱን እንዲያስታውቅለት ለመነ። አስታወቀ ተጠርቶ ገባ።

“ስማ ተጀምሮ እስከ ድግሱ ድረስ እንደምን አደረግህ” ብለው በመልካም ዓይን አይተውት ጠየቁት።

እርሱም ተጀምሮ እስኪጨርስ ያደረገውን ሁሉ አፈሰሰ።

ንጉሡም ቃሉን ሁሉ ሰምተው ተገረሙ። ወድያውም ሾሙት።

.

[ምንጭ] – Major J. Eadie. 1924. “An Amharic Reader”. pp. 7-11.

ዘመን ቊጥርና ስሌት

“ዘመን ቊጥርና ስሌት”

(ክፍል 1) 

በኅሩይ አብዱ

.

የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች ጥንታዊ ሰነዶችን እንደ መረጃ ሲጠቀሙ፣ ሰነዱ የተጻፈበትን ጊዜ ማወቅ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር መንገዶች ካሁኑ ስለሚለዩ የጽሑፉን ዘመን በቀላሉ ማወቅ ያዳግታል። ለምሳሌ በ14ኛው ክ/ዘመን የመጀመርያ አጋማሽ ላይ የተጻፈው የዐጼ ዓምደ ጽዮን ታሪክ እንዲህ ይላል፣

ዓምደ ጽዮን ንጉሠ ኢትዮጵያ … በዓሠርቱ ወሠመንቱ ዓመተ መንግሥቱ እምዘ ነግሠ ወዓመተ ምሕረትሂ ፭፻፲ወ፮።

[ትርጉም] የኢትዮጵያ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን … በነገሠ በ 18 ዓመት፣ በ516 ዓመተ ምሕረት።

(516 ዓመተ ምሕረት?! ይህ እንዴት ይሆናል? ያኔ የአክሱም ዘመን አልነበር? የጸሓፊው ስሕተት ነው ወይስ ያልተረዳነው ነገር አለ?)

ሌላ ምሳሌ ደግሞ፣

በ፴ወ፭ ዓመተ ምሕረት ወበመዋዕሊሁ ለንጉሥነ ዘርአ ያዕቆብ … ወእምአመ ነግሠ በ፳ወ፭ ዓመት ..

[ትርጉም] በ35 ዓመተ ምሕረት በንጉሣችን በዘርአ ያዕቆብ ዘመን … ከነገሠ በ25 ዓመት

(የ15ኛው ክ/ዘመን አፄ ዘርአ ያዕቆብስ ወደ አንደኛው ክ/ዘመን ምን ሊሰራ ሄደ?)

ይባስ ብሎ ሌላ በ14ኛ ክ/ዘመን የተዘጋጀ ብራና፣

ዓመተ ምሕረት በ፷፻፰፻፸፬ … (በ6874 ዓመተ ምሕረት)

(ይህንስ ማለቱ ስምንተኛው ሺ የሚያስብል ነው።)

እነዚህን አደናጋሪ የዘመን አቆጣጠር ምሳሌዎች ወደፊት ለመፍታት ይሞከራል። በመጀመርያ በዚህኛው ክፍል ስለ ግዕዝ ቁጥሮችና ስሌቶች አጭር ገለጻ አቀርባለሁ።

በሚቀጥሉት ወራት በሚቀርቡ ክፍሎች ደግሞ ከዘመነ አክሱም እስከ 20ኛው ምዕት ዓመት የዘመን አቆጣጠር ታሪካዊ ቅኝት ቀርቦ፣ በመጨረሻም የተወሰኑ የዘመን አቆጣጠር ዓይነቶች ከታሪካዊ ምሳሌዎችና የሒሳብ ስሌቶች ጋር ይታያሉ።

 .

የግእዝ ቊጥር (አኀዝ)

በግእዝ ሰዋስው አኀዝ የተባለ ራሱን የቻለ ክፍል አለ። ስለ አኀዝ ሰፋ ያለ ትንተና ከምናገኝባቸው ቀደምት ሥራዎች መካከል፣ አባ ገብረ ሚካኤል በ1850ዎቹ አዘጋጅተውት በኋላ በ1872 ዓ.ም. በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ አርታዒነት በላዛሪስት ሚሽን ማተምያ ቤት ከረን የታተመው መጽሐፈ ሰዋስው ነው።

በ1882 ዓ.ም. በአለቃ ታዬ የተዘጋጀውም መጽሐፈ ሰዋስው ተመሳሳይ ትንተና ስለ አኀዝ ምንነት ያቀርባል። ጽሑፉም እንደሚለው አኀዝ መጀመሪያ፣ መቋሚያ፣ መያዣ ዋስ፣ ቊጥር እና ድምበር ተብሎ ይተረጎማል። የአኀዝንም ፍቺ በአንድምታ የትንተና ስልት እንደዚህ አቅርበውታል።

aleqa taye
አለቃ ታየ ገብረማርያም

መጀመሪያ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ ሁሉ በቊጥር ይጀመራል ይጨርሳልና መጀመሪያ ተባለ።

አኀዝን መቋሚያ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ የነገር ሁሉ መቋሚያ አለው፤ አኀዝም የነገር ሁሉ መቋሚያ ነውና…።

መያዣ ዋስ ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ በመያዣ በዋስ ያለ እንዳይጠፋ በቊጥርም ያለ አይጠፋምና መያዣ ዋስ ተባለ።

አኀዝን ቊጥር ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ፣ በቊጥር የተወሰነ ይወሳል። ያልተወሰነ ይረሳልና ቊጥር ተባለ።

ድምበር ያሰኘው ምንድር ነው ቢሉ ድምበር የእህል የሣር መለያ ነው። ቊጥርም የሁሉ መታወቂያ ነውና ድምበር ተባለ። አንድም ከአኀዝ ወዲያ ቅጽል የለምና ድምበር ተባለ።”

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በታላቁ መጽሐፋቸው፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ስለ አኀዝ ጠለቅ ያለ ትንተና ያቀርባሉ። ስለ የተለያዩ የአኀዝ ዓይነቶች ሲያስረዱ፣ አኀዝ በጥቅሉ መዘርጋት፣ መተርተር፣ መከፈል፣ መታጠፍ፣ መጠቅለል እንደሚችል ይገልጻሉ። ሲተነተኑም፣

Kidane Photo
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ

መዘርጋት፣ ብዛትንና ስንትነትን እንደ ነዶና እንደ ችቦ አስሮ ሰብስቦ የሚያሳይ የጅምላ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ ፩፣ ፪፣ ፲፣ እንዲሁ።

መተርተር፣ ስንትነታቸው ከታወቀ ከብዙዎች ማኽል ስንተኛነትን ለይቶ የሚያሳይ የተራ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ ፩ኛ፣ ፪ኛ፣ ፲ኛ፣ እንዲሁ።

መክፈል፣ የክፍሎችን ስም እንደ ተራ ቊጥር እየለየ በየማዕርጉ የሚያሳይ ክፋለዊ ቊጥር ነው። ምሳሌ፤ መንፈቅ፣ ሣልሲት፣ ራብዒት።

ማጠፍ፣ ጅምላውን ቊጥር ዐጥፎ ደርቦ እያሳየ በመንታ መንገድ የሚወስድ ያጸፋ ቊጥር ነው። ምሳሌ፣ አሐዳት፣ አው ካዕበተ አሐዱ፣ ፩ ዕጽፍ። ክልኤታት፣ አው ካዕበተ ክልኤቱ፣ ፪ ዕጽፍ፣፬ ነጠላ፤ ወከማሁ።

መጠቅለል፣ እንዳራቱ ክፍሎች አኀዝ ሳይኖረው፣ በቅጽልነቱ ማነስና መብዛት ሕጸጽና ምልአት የሚያሳይ፣ የአኀዝ ቅጽሎች ሰብሳቢና ከታች የሚኾን መድበል ቊጥር ነው፤ ያውም ኅዳጥ ብዙኅ ኵሉ፣ ይህን የመሰለ።

የግእዝ ቊጥሮችንም ከአንድ እስከ ምእልፊት (መቶ ሚልዮን) ይዘረዝሩና፣ ከተፈለገም እስከ እልፍ  ምእልፊት (ትሪልዮን)  … እንዲሁም ከዛም በላይ መቊጠር (መጻፍ) እንደሚቻል ያስረዳሉ። አለቃ ኪዳነወልድ ከአንድ (1) እስከ እልፍ ምእልፊት (በአሁኑ አቆጣጠር ትሪልዮን 1‚000‚000‚000‚000) በግእዝ አኀዝ ለመጻፍ እንደ ቊጥር የሚያገለግሉ አስራ ዘጠኝ የተለያዩ ምልክቶችን ተጠቅመዋል። እነዚህም በአሁኑ ባላቸው መልክ የሚከተሉት ናቸው።

፩ ፪ ፫ ፬ ፭ ፮ ፯ ፰ ፱ ፲ ፳ ፴ ፵ ፶ ፷ ፸ ፹ ፺ ፻

(1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 20 30 40 50 60 70 80 90 100)

እነዚህን 19 ምልክቶች በተለያየ መልክ በማጣመርም ሌሎች ቁጥሮችን መፍጠር ይቻላል።

ለምሳሌ ፳፻፲፯፣ 2017 (20 መቶ እና 10 እና 7) ይሆናል።

ስለዚህ የግዕዝ የቊጥር ስርዓት በ19 ምልክቶች ላይ የተመሰረተ ነው (በአንፃሩ በዓለም በሰፊው የተሰራጨው የሂንዱ-አረብ የቊጥር ስርዓት አስር ምልክቶችን ይጠቀማል።)

የግዕዝ የቊጥር ስርዓት ለዜሮ ቊጥር ምልክት የለውም፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ ለአስር፣ ለሀያ … እስከ መቶ ላሉት ቁጥሮች ተጨማሪ ምልክቶች ያስፈልገዋል። ምንም እንኳ የዜሮ ምልክት በቁጥሩ ስርዓት ውስጥ ባይኖርም፣ የዜሮ ጽንሰ ሐሳብ ግን ለብዙ መቶ ዓመታት አልቦ (ሲያጥር አል ወይም ) በሚለው ቃል ውስጥ ተካቶ እናያለን፣ በተለይ የማካፈል ስሌት ውጤቶች ውስጥ።

.

የቊጥሮች መልክ መቀያየር

ከላይ የሚታዩት ያሁኑ ዘመን የቊጥር ምልክቶች በመደበኝነት በዚህ ቅርጻቸው የጸኑት በ19ኛው ክ/ዘመን ለኅትመት ሲባል በብረት መቀረጽ ሲጀምሩ ነው፣ አሁን ደግሞ በኮምፕዩተር ፕሮግራሞች ያንኑ መልክ ይዘው ቀጥለዋል። ከታች የቀረበው ሰንጠረዥ የተወሰኑ የግዕዝ ቁጥሮችን የጊዜ ሂደት ለውጥ ያሳያል።

Hiruy Numbers Evolution

ከሰንጠረዡ ማየት እንደሚቻለው በዋነኝነት በጊዜ ሂደት መልካቸው ሊያሳስት የሚችለው ቊጥር 1 እና 4፣ እንዲሁም ቊጥር 6 እና 7 ናቸው።

የአክሱም ዘመን፣ የ14/15 ምዕት ዓመት እና በ17ኛ ክ/ዘመን ሉዶልፍ ያስቀረጸው ቊጥር 1 ያሁኑን ዘመን ቊጥር 4 (፬) ይመስል ነበር፣

የቀድሞው ቊጥር 4  ሦስት ማዕዘናዊ ነበር።

ስለዚህ ሁለቱን ለመለየት ሲባል ያሁኑ ዘመን ቊጥር 1 (፩) ከላዩ ትንሽ ቅጥያ ተጨምሮለታል።

የአክሱም ዘመን፣ የ14/15 ምዕት ዓመት እና በ17ኛ ክ/ዘመን ሉዶልፍ ያስቀረጸው ቊጥር 6 ያሁኑን ዘመን አነስተኛ ቊጥር 7 (፯) ይመስል ነበር፣ ስለዚህ ሁለቱን ለመለየት ሲባል ያሁኑ ዘመን ቊጥር 6 (፮) የስረኛው ቅጥያ ወደ ቀለበት ተቀይሯል።

 .

የሒሳብ ስሌቶች

በጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት ባሕረ ሐሳብ የሚባል የዕውቀት ክፍል አለ። የትምህርቱም ዓላማ ከዓመት ዓመት ተንቀሳቃሽ የሆኑ በዓላትና አጽዋማት (ፋሲካ፣ የሁዳዴ ጾም … ወዘተ)  መቼ እንደሚውሉ ማስላት ነው። የባሕረ ሐሳብ ዐዋቂ ለመሆን የሚያስፈልገው የአራቱ መደብ የቊጥር ስሌት (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈል) እንዲሁም የአንዳንድ የዘመን መለኪያ የስሌት ቃላትን ትርጉም መረዳት ነው።

የስሌትን አጠቀላይ ተግባር ለመግለጽ የተለያዩ የግዕዝና የአማርኛ ቃላት በሥነ ጽሑፍ ይገኛሉ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፣

ቈጠረ፣ ቀመረ፣ ሠፈረ፣ መጠነ፣ ሐሰበ (ዐሰበ) – ሒሳብ፣ አሰላ – ስሌት፣ …

በተጨማሪም፣

በዘተአምር (እንድታውቅ)፣

አእምሮ አዝማን (ዘመንን ማወቅ)፣

ትእኅዝ (ትይዛለህ)፣

ተኀሥሥ (ትፈልጋለህ፣ ትሻለህ) … የሚባሉ ሙያዊ ቃላቶችም አሉ።

የስሌቱ ውጤት እንዲህ ይሆናል ለማለት ደግሞ፣

ይዔሪ (ይተካከላል፣ እኩል ይሆናል)፣

ይከውነከ (ይሆንልሃል) … የመሰሳሉትን እናገኛለን።

ከታች ያለው ሰንጠረዥ አራቱ መደበኛ የቊጥር ስሌቶች (መደመር፣ መቀነስ፣ ማባዛት እና ማካፈል) በግዕዝ እና አማርኛ የባሕረ ሐሳብ ብራናዎች በምን ቃላት እንደሚገለጹ ዝርዝር ያቀርባል።

Terms Table

.

ማካፈል

በባሕረ ሐሳብ ትምህርት በመደጋገም የምናገኘው ስሌት ማካፈል ነው፤ በተለይም መግደፍ ለሚባለው ስሌት በጣም አስፈላጊ ነው። ማካፈልን በዘመናዊ መልኩ ስናየው፣ አንድ ቊጥር በሌላ ሲካፈል የማካፈሉ ውጤት ድርሻ (quotient) እና ቀሪ (remainder) ይሰጣል።

ለምሳሌ ሰላሳን በሰባት ብናካፍል

Division Figure

የማካፈሉ ውጤት – ድርሻ አራት (4) ይደርስና (4 × 7 =28) ቀሪው ሁለት (2) ይሆናል።

.

መግደፍ 

በባሕረ ሐሳብ ትምህርት ላይ መግደፍ የሚባል ከአራቱ መደብ የቊጥር ስሌት ትንሽ ለየት ያለ የሒሳብ ስሌት አለ። መግደፍ ማለት አንድን ቊጥር በሌላ አካፍሎ የሚተርፈውን ቊጥር (ቀሪ) እንደ ውጤት መያዝ ነው። የላይኛውን ምሳሌ ከእንደገና ብናይ፣ ሰላሳን (30) በ ሰባት (7) መግደፍ ቢያስፈልግ፣ መጀመርያ ሰላሳን በሰባት እናካፍላለን – የዚህም ውጤት አራት ይደርስና (4 × 7 =28) ቀሪው ሁለት (2) ይሆናል።

ስለዚህ ቀሪው ሁለት (2)፣ ሰላሳን በሰባት መግደፍ ለተባለው የሒሳብ ስሌት ውጤት መሆኑ ነው። በዘመናዊ የሒሳብና የኮምፒዩተር ስሌት መግደፍ Modulo (MOD) ከሚባለው ስሌት ጋር አቻ መሆኑ ነው።

የመግደፍን ውጤት የሚተነትኑ ቃላትም አሉ፤

ጥንቁቀ ተከፍለ (በትክክል ተከፍሏል – ቀሪ የለውም ለማለት)፣

ወዘተርፈከ (የተረፈህም)፣

ወዘዘኢከለ (ያልበቃውም – የተረፈውም)፣

እስከ ትዌድእ (እስከ ትጨርስ ድረስ … ‹ማካፈሉን›)፣ (ይህን ያህል) …ደርሶ …(ይህን ያህል) ይቀራል፣ ይተርፋል ….

መግደፍ በሰፊው በባሕረ ሐሳብ ስሌቶች ውስጥ፣ እንዲሁም ከ16ኛ ክ/ዘመን ጀምሮ በተስፋፋው በዓውደ ነገሥት የዕጣ-ፈንታ ስሌት ውስጥም ይገኛል።

.

መጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት፣  … መጠነ _ _ _

ከማካፈል ስሌት ጋር በተገናኘ፣ ቀሪው እላይ እንደታየው መግደፍ ለተባለው ስሌት ሲጠቅም፣ ድርሻው ደግሞ አሁን ለምናያቸው መጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት … ስሌቶች ይጠቅማል። መጠነ ሳብዒት የአንድን ቊጥር በሰባት የማካፈል ድርሻ ሲይዝ፣ መጠነ ራብዒት ደግሞ የአንድን ቊጥር በአራት የማካፈል ድርሻ ይወስዳል። የላይኛውን ምሳሌ ከንደገና ብናይ፣

የሰላሳ መጠነ ሳብዒት፣ ሰለሳን በሰባት አካፍሎ (30 ÷ 7፣ ድርሻው 4፣ ቀሪው 2)  ድርሻውን አራት (4) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰለሳ መጠነ ሳብዒት አራት (4) ነው።

የሰላሳ መጠነ ራብዒት፣ ሰለሳን ባራት አካፍሎ ድርሻውን ሰባት (7) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰለሳ መጠነ ራብዒት ሰባት (7) ነው።

ይህ መጠነ — የሚለው ስሌት ከአራት እና ሰባት በተጨማሪ ለሌላ ቁጥሮችም ማስላት ይቻላል። ለምሳሌ፣ መጠነ ሳድሲት በስድስት የማካፈልን ድርሻ ይይዛል። የሰላሳ መጠነ ሳድሲት (30 ÷ 6፣ ድርሻው 5፣ ቀሪው 0) ድርሻውን አምስት (5) ይይዛል፣ ስለዚህ የሰላሳ መጠነ ሳድሲት አምስት (5) ነው።

.

(ውጤቱ) እንዲህ ከሆነ … ይህን አድርግ … 

አለዚያ … ያንን አድርግ

በዘመናዊ የሒሳብና የኮምፒዩተር ስሌት Conditional IF ከሚባለው ስሌት ጋር አቻ መሆኑ ነው።

If 1 Then  Do A,

If 2 Then  Do B …

Else … Do X

የአንድ የመግደፍ ስሌት ውጤት ከታወቀ በኋላ፣ እንደውጤቱ ዓይነት የተለያዩ የድርጊት ምርጫዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ በባሕረ ሐሳብ፣ መስከረም 1 በምን ዕለት እንደሚውል በሚደረገው ስሌት፣ ድምሩ በሰባት ይገደፍና፣ ቀሪው ውጤት አበቅቴ ፀሐይ ተብሎ ይያዛል። የሚገደፈው በሰባት ስለሆነ ያሉትም ምርጫዎች ሰባት ይሆናሉ። ሰነዱ እንደሚለው፣

            ወእምዝ ትገደፍ በበ፯ ወዘተረፈከ ውእቱኬ አበቅቴ ፀሐይ።

(ከዛም በ7 ትገደፋልህ፤ የተረፈህም (ውጤት) አበቅቴ ፀሐይ ነው።)

ለእመ ኮነ ኍልቈ አበቅቴ ፀሐይ

የአበቅቴ ፀሐይ ልኬት (ቊጥር) 1 ከሆነ)

ይከውን ቀዳሚተ ሠርቀ መስከረም በዕለተ ረቡዕ

(መስከረም 1 ረቡዕ ዕለት ይሆናል (ይውላል)።)

       ለእመ ኮነ ኍልቈ አበቅቴ ፀሐይ

(የአበቅቴ ፀሐይ ልኬት (ቊጥር) 2 ከሆነ)

 ይከውን ቀዳሚተ ሠርቀ መስከረም በዕለተ ኀሙስ

(መስከረም 1 ሐሙስ ዕለት ይሆናል (ይውላል)።)

… እያለ እስከ ቊጥር ሰባት ድረስ ይዘልቃል።

ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ባሳተሙት ሐተታ መናፍስት ወዓውደ ነገሥት ደግሞ፣ ለምሳሌ ሓሰበ ኑሮ ወዕድል የሚለውን ክፍል ብንወስድ፤ በመጀመርያ፣ ‹ስምና የእናትን ስም በ፱ ግደፍ› ይላል። የሚገደፈው በዘጠኝ ሰለሆነ ያሉትም ምርጫዎች ዘጠኝ ናቸው። ከዛም እንደ ሎተሪ፣

፩፤ ሲወጣ በሹመት ይኖራል።

፪፤ በንግድ ይኖራል።

በዙረት ይኖራል።

በእጀ ስራ ይኖራል

በወታደርነት ይኖራል።

በብክንክን ይኖራል።

በቤተ መንግሥት ይኖራል።

በዙረትና ልፋት ይኖራል።

በንግድና በእርሻ ይኖራል።›

.

ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገደብ (ወሰን)

የአንድ ስሌት ውጤት ከዚህ ቊጥር መብለጥ ወይንም ከዚህ ቊጥር ማነስ የለበትም፣ የሚለውን ሐሳብ ለማስረዳት በባሕረ ሐሳብ ትምህርት የሚከተሉት ቃላት ይገኛሉ። ዝቅተኛው ገደብን (በሒሳብ እና ኮምፕዩተር ትምህርት Lower Limit) ለመግለጽ፣

ኢይውኅድ (አይቀንስም)፣

ኢይወርድ (አይወርድም)፣

ኢይቴሐት (አያንስም)፤

ከፍተኛውን ገደብ (በሒሳብ እና ኮምፕዩተር ትምህርት Upper Limit) ለመግለጽ ደግሞ፣

ኢይበዝኅ (አይበዛም)፣

ኢይዐዱ (አያልፍም)፣

ኢይትሌዐል (አይተልቅም)።

እላይ ካየናቸው ከአራቱ መደበኛ ስሌቶች፣ ከመግደፍመጠነ ሳብዒት፣ መጠነ ራብዒት …፣ ከ ‹(ውጤቱ) እንዲህ ከሆነ … ይህን አድርግ‹ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ገደብ› በተጨማሪ ሌሎች የሒሳብ ስሌቶችና ብያኔዎች አሉ።

ሁሉንም ለመዘርዘር እና ለመተንተን ግን ሰፋ ያለ ጥናት ያስፈልጋል። የ14ኛው ክ/ዘመን የባሕረ ሐሳብ ሊቅ እንዳለው፣

ዘንተ ዕቀቡ

በጥንቃቄ ሐስቡ 

ጥያቄ አዝማን ከመ ትርከቡ። 

(የዘመንን ምርመራ ታገኙ ዘንድ፣ ይህንን ያዙ፤ በጥንቃቄ አስሉ።)

.

ኅሩይ አብዱ

ሐምሌ ፳፻፱

መሰንቆ እና ብትር (ወግ)

“መሰንቆ እና ብትር”

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ …”

አዝማሪ ጣፋጭ [1845 ዓ.ም]

.

የዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ጎሹ እና የቋራው ፋኖ ደጃዝማች ካሳ በኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም ጉራምባ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ካሳ፣ ከጥቂት ታማኝ ጭፍሮቻቸው ፊት ተሰልፈዋል። ጎሹም፣ በተለመደው የጀብድ መንገድ ከሰራዊታቸው ፊት ለፊት ቀድመው፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ ውለዋል። ውጊያው እንደተፋፋመ፣ ደጃች ጎሹ በጥይት ተመትተው ወደቁ። የመሪውን መውደቅ እንደተረዳ የዳሞት ጦር ፀንቶ መመከት ተሳነው። ወዲያው የንቧይ ፒራሚድ ሆነ። ያለቀው አልቆ ቀሪው ተማረከ።

ከምርኮኞች አንዱ፣ አዝማሪው ጣፋጭ ነበር።

ጣፋጭ፣ የደጃች ጎሹ አዝማሪ ስለነበር በብዙ ጦር ሜዳ ላይ ውሏል። በጌታው ጠላት እጅ ሲወድቅም የመጀመሪያው አይደለም። በራስ ይማም ዘመንም እንዲሁ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ የተባለ መስፍን ደጃዝማች ጎሹን ድል በነሳ ጊዜ፣ ከጌታው ጋር ተማርኮ ነበር።

ይሁን እንጂ ያኔ ዝንቡን እሽ ያለው አልነበረም። ጣፋጭ፣ የደጃች ማጠንቱ ምርኮኛ ቢሆንም፣ የእግር ብረት አልገባበትም። እንዲያውም፣ በድል አድራጊው አዳራሽ ውስጥ ያሻውን ከማንጎራጎር አልተከለከለም ነበር። በወቅቱም፣ አዝማሪው ጣፋጭ ይህንን ገላጋይ ዝማሬ አቅርቦ ነበር፤

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

ጣፋጭ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ በጦር ሜዳ ላይ ስምንት ወታደር መግደሉን አስታውሶ፣ አሁን ተማራኪውን ቢገድል የሚጨመርለት ክብር እንደሌለ አስታወሰው። በሁለት መስመር ግጥም ለድል አድራጊው የሚገባውን መወድስ ሳይነፍግ፣ የጌታውን ሕይወት ለመታደግ ጥሯል። ድል አድራጊው ደጃች ማጠንቱም ጎሹን ሳይገድለው ቀረ።

በዚህ በኅዳር ዕለት ጦርነት ግን፣ አዝማሪው ጣፋጭ በቋረኛው ካሳ ጦር ተማርኳል። ተስፋና ፍርሀት ከፊቱ ተደቅነዋል። ባንድ በኩል፣ አዝማሪን መግደል ነውር የሚያደርገው ባህል ጋሻ ሁኖት ከክፉ እንደሚታደገው ተስፋ ያደርጋል። በሌላ በኩል፣ ደጃዝማች ካሳ ይህን ደምብ ለማክበራቸው ርግጠኛ አይደለም።

እነሆ፣ አዝማሪው በካሳና በጭፍሮቻቸው ፊት ቆሟል። ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ የሚተርኩልን ለዘመኑ ቅርብ የነበሩት አለቃ ወልደማርያም ናቸው፤

“አዝማሪ ጣፋጭ … ተይዞ በቀረበ ጊዜ ባደባባይ አቁመው ደጃች ካሳ ‘እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ’ ቢሉት እጅግ ተጨነቀ፤ እንዴህም አለ፤

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

እንዲህም ቢል ሞት አልቀረለትም፤ በሽመል ገደሉት።”

አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ከሁለት ትውልድ በኋላ በጣፉት የጎጃም ታሪክ ውስጥ ደግሞ የሚከተለውን ተጨማሪ መስመር እናገኛለን፤

“አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

ከመቶ አመት በኋላ ታዋቂው ዘመናይ የታሪክ ጸሐፊ ተክለጻድቅ መኩሪያ በጻፉት ጥናትም “ብትር” የሚለውን “ሽመል” በሚል ቃል ከመተካት በስተቀር ያለቃ ተክለየሱስን ቅጂ ማስተጋባት መርጠዋል፣

“እወይ ያምላክ ቁጣ

ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

.

ጣፋጭ፣ የደጃች ካሳን ምሕረት አጥብቆ የሚፈልግ ምርኮኛ ሆኖ ሳለ፣ እንዴት ተሽቀዳድሞ በራሱ ይፈርዳል? እንዴት “ሽመል/ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ” ብሎስ ራሱን ለቅጥቀጣ ያቀርባል?

የጣፋጭን ፍርድ በመመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት አለቃ ወልደማርያም ታሪክ ውስጥ መደምደሚያው ስንኝ አለመጠቀሱ አንድ ነገር የሚጠቁም ይመስለኛል። ስንኙ ምናልባት ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ይሆናል።

የኔ ግምት እንዲህ ነው … አዝማሪ ጣፋጭ በደጃዝማች ካሳና አጃቢዎቻቸው ፊት ይቀርባል፤

ደጃች ካሳ፤   እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ?

ጣፋጭ፣ በጦርነቱ ዋዜማ በደጃች ካሳ ላይ ያወረደውን ዘለፋ እዚህ ቢደግም፣ የድል አድራጊውን ቁጣ ከማቀጣጠል ውጭ የሚፈይድለት ነገር የለም። ስለዚህ የመጨረሻ መሳሪያውን ለመጠቀም ወሰነ። ቧልት! …. ካሳና ጣፋጭ በጎሹ ቤት በሎሌነት ሲኖሩ፣ ካሳ ቀልድና ፈሊጥ እንደሚወድ ያውቃል። ጣፋጭ መሰንቆውን ቃኝቶ ይህን በግለ ሂስ የተሞላ የቧልት ዘፈን ዘፈነ፤

ጣፋጭ፤   ህምም …

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ሥራ ሲያጣ።

ካሳ አልሳቀም። አዝማሪው የከፈተውን ተውኔት እንዴት መቀጠል እንዳለበት እያሰበ ይሆናል። ደጃዝማች ካሳ፣ ራሱን የመለኮት ተውኔት ፍሬ አድርጎ ስለሚቆጥር ፍርዱን ሳይቀር ተውኔታዊ ማድረግ ይወድ ነበር። የራስ አሊን እናት በማረከም ጊዜ “ገረድ ትሰለጥናለች እመቤት ትፈጫለች” የሚለውን የፍካሬ የሱስ ትንቢት ለማስፈጸም ወይዘሮ መነን ባቄላ እንድትፈጭ ፈርዶባት ነበር። “የኮሶ ሻጭ ልጅ” ብሎ የሰደበው ቀኛዝማች ወንድይራድን ደግሞ “እናቴ ከገበያ ሳይሸጥላት የቀረ ኮሶ ስላለ እሱን ተጋበዝ” ብሎ፣ ከመጠን ያለፈ ኮሶ አስግቶ ለመቅጣት የሆነ የተውኔት ስጦታ ያስፈልጋል። ያገራችን ጸሐፌ ተውኔቶች በፍቅሩ የነሆለሉት ብጤያቸው ስለሆነ መሆን አለበት።

ደጃች ካሳ፤   (ወደ አጃቢዎቹ ዞሮ)

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ።

.

ጣፋጭ በቧልት የጀመረውን … ካሳ በትራጀዲ ደመደመው።

.

* * *

ጣፋጭን ለድብደባ የዳረገው ዝማሬ ግጥም ይሄ ነበር …

አያችሁት ብያ፥ የኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞ፥ ጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂ፥ መች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት፥ በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ ፥ በነ ጉንጭት ለምዶ።”

* * *

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ” [መስመር ፩]

ብያ” ዛሬ ለመረሳት ከደረሱት ያማርኛ ጥንታዊ ቃላት አንዱ ሲሆን “እኮ፣ አይደል” ማለት ነበር። “አያችሁት ብያ” ሲልም “አይታችሁታል አይደል?” ማለት ነው። ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሱን ገድሎ በወደቀ ማግስት ከወረዱ የሙሾ ግጥሞች አንዱ፣ “አያችሁት ብያ ያንበሳውን ሞት” የሚል ስንኝ አለው። ይህም በጊዜው ቃሉ የተለመደ እንደነበር ያመለክታል።

“እብድ” ተብሎ ካሳ በይፋ ሲጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የምንሰማው ከአዝማሪ ጣፋጭ ሳይሆን አይቀርም። ጣፋጭ ይህን ሲል፤ የጊዜውን አስተያየት እያስተጋባ ነው? ወይስ በራሱ ምርመራ የደረሰበት ነበር? አላውቅም። አለቃ ተክለየሱስ ከግማሽ መቶ አመት በኋላ በጐንደር ሲወርድ የነበረውን ግፍ ዘግቦ፣ የሕዝቡን ምላሽ ምን እንደነበር ሲጽፍ፣ “ከዚህ በኋላ፣ የበጌምድር ሰው ‘ይህስ የደህንነትም አይደለ’ እያለ አመል አወጣ … ንጉሡንም ጠላው። ሌሊት በተራራ እየቆመ፣ እንደ ሳሚ ወልደ ጌራ ‘እብዱ ገብረኪዳን’ እያለ ተሳደበ” ይላል። (“ገብረኪዳን” የአፄ ቴዎድሮስ የክርስትና ስም እንደነበረ ባልታወቀ ደራሲ ተጽፎ Fusella ባሳተመው ዜና መዋዕል ተጠቅሷል።)

.

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ [መስመር ፪]

ጋሞች” የሚላቸው ባለ አፍላ እድሜ ላይ ያሉትን ጋሜዎች ነው። ባዝማሪው አይን ሲመዘኑ የደጃዝማች ካሳ አጃቢዎች እድሜያቸው ለጋ፣ ቁጥራቸውም ጥቂት ነው። በርግጥም የካሳ ጭፍሮች ማነስ ለባላጋራዎች ግራ የሚያጋባ ነበር። ባነጋገር ፈሊጣቸው የታወቁት ራስ አሊ የቋራው ካሳን ሰራዊት ከሩቅ አይተው ከገመቱት በታች ቢሆንባቸው፣ “ጦረኛ እንዳንለው አነሰ፤ ሰርገኛ እንዳንለው በዛ” ብለው ነበር።

ጉራምባ” (ጉር አምባ) በዛሬው የደንቢያ ወረዳ፣ ጎርጎራ በተባለው ንኡስ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው። ደጃዝማች ካሳ ይህን ስፍራ የመረጡት ለመከታ የሚያመች አምባ ሆኖ ስላገኙት ሳይሆን አይቀርም። አዝማሪው ጣፋጭ በግጥሙ ውስጥ “ጉር አምባ” የሚለውን ነባር ስም “ጉራምባ” ብሎ አሸጋሽጎታል። ይህን ያደረገው ስፍራውን “ጉራ መንፊያ” ብሎ ለመተርጎም እንዲያመቸው ይመስላል። ጣፋጭም የቋራው ካሳን ለይስሙላ እንጂ የምር መዋጋት የማይሆንለት ጦረኛ አድርጎ ይገምተው እንደነበር ቀጣዩ መስመር ያሳያል።

.

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋ ካሳ” [መስመር ፫]

ያንጓብባል” የሚለው ቃል “አጊጦ በመልበስ ቄንጥ ባለው አካሄድ ይሄዳል፣ ዳር ዳር ይላል” ማለት ነው። ቃሉን የሚከተለው ከአለቃ ዘነብ “መጽሐፈ ጨዋታ” የተቀነጨበ አንቀጽ የበለጠ ያብራራዋል፣

“ሰማይ ከዚያ ላይ ሆኖ አንጓቦብን የሚኖር ከቶ ምንድር ነው? ቀን ፀሐይን ሌሊት ጨረቃንና ከዋክብትን ተሸልሞ ዘወትር እኔን እኔን እዩኝ እዩኝ እያለ ያደክመናል … እንደዚህ የኮራ እንደ ሰም ለመቅለጥ ነው እንጂ ፊቱን እንዴት ያየው ይሆን? ኩራቱም ምድር አስለቅቆታል። ምን ይሆናል እንደሚያልፍ አያውቅምን?”   [ክፍል 15፤ አንቀጽ 16]

ይህ ዳር ዳር ማለት የቋራው ካሳ ጠላቶቹን የሚያዘናጋበት ልዩ የጦር ስልት ነበር። በጠላቶቹ አይን ግን እንደ ፍርሀት ይቆጠር ነበር። ለአብነት ያክል፣ አለቃ ወልደማርያም በደጃች ካሳና በራስ አሊ መሐል የተደረገውን ውጊያ አስመልክተው ሲጽፉ፤ “ራስ አሊ አይሻል በሚባል ሜዳ ጦርዎን ሰርተው ተቀምጠው ሳሉ ደጃች ካሳም ዳር ዳሩን ይዞሩ ጀመሩ። ሰውም የፍርሀት መስሎት ‘ተመልሶ ሊሄድ ነው’ ይል ጀመረ።”

መች ይዋጋል …” የቋራው ካሳ ደፋርና ጽኑ ተዋጊ ቢሆንም ጉልበቱን መዝኖ መሸሽም ያውቅ ነበር። ደጃዝማች ጎሹ በ1840 ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሚካኤል አባዲ በጻፉት ደብዳቤ “ተካሳ ጋራ የተዋጋነ እንደሆነ ጎንደር እገባለሁ እንገናኛለን፤ ወደ ቆላ የሸሸ እንደሆነ …” ያሉት ይህን ስለሚያውቁ ይመስላል። እንደገመቱት፣ ካሳ ወደ ትውልድ ቦታው አፈግፍጎ ከርሟል። አዝማሪው ጣፋጭ “… መች ይዋጋል ካሳ” ያለው ይህን ሁኔታ በማጤን መሆን አለበት። ይሁን እንጂ፣ ካሳ ለጣፋጭ ያልተገለጠለት ጠንካራ ጎን ነበረው። ጠላቶቹ ሽሽቷል ብለው ሲዘናጉ እንደገና አፈር ልሶ ተነስቶ ማጥቃትና ማሸነፍ ይችል ነበር።

.

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ [መስመር ፬]

ወርደህ” የሚለውን ቃል አዝማሪው በዚህ ዝማሬ ውስጥ ሁለቴ ተጠቅሞበታል። መስመር 2 ላይ “ጉራምባ ሲወርድ” ብሎ ካሳን የገለጠውን ያክል “ወርድህ ጥመድበት” ብሎ ጎሹን ይጎተጉተዋል። የመፋለሚያውን ቦታ ቆላነት ያሳስባል፤ ወደ ቆላ ወረደ ይባላልና። “ጥመድ” በአማርኛ ብዙ ትርጉም አለው፤ ከግጥሙ ዐውድ ጋር የሚሄደው “አሽክላን ዘረጋ፣ ወይም የጠፋ ሰውን አጥምዶ ሸምቆ ለመያዝ በጎደጎደ አደባ” የሚለውን ነው። ስለማይዋጋ ካሳን አድብቶ መያዝ እንደሚያዋጣ ጣፋጭ ሀሳብ እያቀረበ ነው።

በሽንብራው ማሳ” ሲል አዝማሪ ጣፋጭ ስለየትኛው ነው የሚያወራው? “ካሳ” ከሚለው ቃል ጋር እንዲገጥመለት ይሆን? የለም፤ እኔ እንደሚመስለኝ ቃሉ ታስቦበት የተመረጠ ነው። ደጃች ጎሹ የቋራውን ደጃች ካሳ አባርረው ደንቢያን በጃቸው ባስገቡበት ዘመን ከምግብ ሁሉ የሚወደውን የሽንብራ አዝመራ አውድመውበታል ይባላል። ጣፋጭ “ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ” ያለው ያንን አስታውሶ ይመስለኛል። አለቃ ዘነብ፣ “ያን ጊዜም ቋራ ሁሉ ጠፍ ሆኖ ነበር። ልጅ ካሳም ለባላገሩ ሁሉ ብዙ ብር ሰጡት። መቆፈርያ ግዛ ብለው … ከወታደሩ ጋር ብዙም ቆፍረው ዘሩ” ያሉት የሚታወስ ነው።

.

ወዶ ወዶ!” [መስመር ፭]

ወዶ ወዶ …” ጣፋጭ ይህን የተጠቀመው ለማሽሟጠጥ ነው፤ “ወድያ ወድያ” እንደማለት ነው። በዛሬ አማርኛ ብንመልሰው “ድንቄም ድንቄም” እንል ነበር።

.

በሴቶቹ በነ ጉንጭት ምዶ” [መስመር ፮]

ጉን” ለጉንጫም ሴት የሚሰጥ ቅጥል ነው። ጣፋጭ “በነ ጉንጭት” ሲል ደጃዝማች ካሳን በዘመኑ ያጅቡ ከነበሩት ቅሬዎች (ጋለሞቶች) አንዷን ጉንጫም አስታውሶ ይሆን?  “በነ ጉንጭት ምዶ …” ካሳ ከሴቶቹ ከነጉንጭት የለመደው ምንድነው? በጣፋጭ እይታ መሽቀርቀር፣ የእዩኝ እዩኝ ማለትን ተግባሮች ሁሉ ድምር የሆነው “ማንጓበብ” መሆኑ ነው።

ጣፋጭም ሆነ ካሳ፣ ወንድን እንደ መለኮት ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ ሴትን እንደ ጉድፍ የሚያጣጥል ማኅበረሰብና ዘመን ፍሬዎች ናቸው። በዚህ አይነቱ ዘመን አንድ ጦረኛ ጀብዱው ከከተሜ ቅሬዎች ተግባር ጋር መነጻጸሩን ሲሰማ ደም ብቻ እንደሚያጸዳው ውርደት አድርጎ ቢቆጥረው አይገርምም።

የጣፋጭን ፍጻሜ የወሰነችውም ይቺ የመጨረሻዋ መስመር ሳትሆን አትቀርም።

.

አዝማሪ ጣፋጭ (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም)

እና ድርሰቶቹ

*

“እወይ ያምላክ ቁጣ፣ እወይ የግዜር ቁጣ፤

አፍ ወዳጁን ያማል፣ ሥራ ሲያጣ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* *

“ክፉ የክፉለት፣ ይሆን የነበረ፤

ብሩን ‘ይሙት’ ብሎ፣ አለ የመከረ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * *

አያችሁት ብያየኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂመች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ  በነ ጉንጭት ለምዶ፤

(ሐሩ ቋዱ፣ ለውዙ ገውዙ አለ ቋራ፤

መንገዱ ቢጠፋ፣ እኔ ልምራ።)”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * * *

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ፤ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

[1820 ዓ.ም – ቋሚ ጨርቅ]

.

በዕውቀቱ ሥዩም

ሰኔ 2009 ዓ.ም

.

ምንጮች

ስለ አዝማሪ ጣፋጭ ሕይወት (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም) ያሉን ቀጥተኛ ምንጮች ሁለት ብቻ ናቸው። ቀዳሚው፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመን (1875 ዓ.ም) የቴዎድሮስ ታሪክን የጻፈው አለቃ ወልደማርያም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን (1917 ዓ.ም) የጐጃምን ታሪክ የጻፈው አለቃ ተክለየሱስ ነው። ሁለቱም ስለ ጣፋጭ የጻፉት በጣም በጥቂቱ፣ ለዚያውም ባለፍ ገደም ነው። ጣፋጭም ለትውስታ የበቃው፣ አሳዛኝ እጣው ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ስለተቆራኘ መሆን አለበት።

ተሰማ ሀብተ ሚካኤል። (፲፱፻፶፩)። “ከሳቴ ብርሃን የዐማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 266፣ 821።

ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ)። [፲፱፻፲፯]። “የኢትዮጵያ ታሪክ” አርታዒ፤ ስርግው ገላው (2002 ዓ.ም)፤ ገጽ 94-102

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፴፮]። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ“፤ (9ኛ እትም፤ ገጽ ፮-፯)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፹፩]። “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት“፤ ገጽ 125-127።

ወልደማርያም (አለቃ)። [፲፰፻፸፭]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Mondon-Vidailhet, Cassimir (1904)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፪]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Littmann, Enno (1902).

(ያልታወቀ ደራሲ)። [፲፰፻፸ዎቹ]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Fusella, Luigi (1959).

ደስታ ተክለወልድ። (፲፱፻፷፪)። “ዐዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 169፣ 217።

Blanc, Henry (1868) “A Narrative of Captivity in Abyssinia“, p. 178.

Lejean, Guillaume (1865) “Théodore II: Le Nouvel Empire d’Abyssinie“.

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (1817 – 1900)

በኅሩይ አብዱ

 .

በ1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ “መጽሐፈ ሰዋስው ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በገበያ ዋለ። ይህ የግእዝ-አማርኛ ሰዋስው እና መዝገበ ቃላት የሦስት ትውልድ ሊቃውንት የምርምርና የትጋት ውጤት ሲሆን ላለፉት ስድሳ ዓመታት ዋነኛው የግእዝ ቃላት መፍቻ ሆኖ አገልግሏል። እስከዛሬ ድረስም ቢሆን በአገራችን ምትክ የሚሆነው መጽሐፍ ሊገኝለት አልተቻለም።

በዚህ ጽሑፍ የዚህን ዕጹብ መዝገበ-ቃላት ሥራ ወጣኝ የነበሩትን የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስን የሕይወት እና የድርሰት ታሪክ አቀርባለሁ።

.

ተማነት (1817 – 1842)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ግንቦት 14፣ 1817 ዓ.ም በአንኮበር ተወለዱ። ከአርባ ቀንም በኋላ በሰኔ 23 ስለተጠመቁ ሰማዕቱ ጊዮርጊስን ለመዘከር ስማቸው “ክፍለ ጊዮርጊስ” ተባለ። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንደጻፉልን መምህር ክፍሌ አንኮበር ቢወለዱም አብዛኞቹ ዘመዶቻቸው ከሐር አምባ ናቸው (“አንኮበር ይእቲ ምድረ ሙላዱ ወሐር አምባ ርስተ ነገዱ።”)

አንኮበር

አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚነግሩን መምህር ክፍሌ የሕይወታቸውን የመጀመሪያ ሃያ አምስት ዓመታት ያሳለፉት በሸዋ ሲሆን አብዛኛውን የቤተ ክርስትያን ትምህርት የተማሩትም በዚሁ ወቅት በአንኮበር ነበር። ይህም ማለት ከመሠረታዊው ንባብና ጽሕፈት በመጀመር ዜማ ቤት፣ በመቀጠልም ቅኔ ቤት ገብቶ መማር ነው። የሚቀጥለው ደረጃ የአንድምታ (መጻሕፍት ቤት) ትምህርት ሲሆን፣ ለዚህም ጠለቅ ያለ የግእዝ ሰዋስው እውቀት ያስፈልጋል።

የግእዝ ሰዋስውን አገባብ እና የቅኔ መንገድ በመማር የቅኔ መምህርነት ደረጃ መድረስ ለአዲሱ የአንድምታ ትምህርት ጥሩ መሠረት ይሆናል። ተማሪው መጻሕፍት ቤት ገብቶ በመጀመርያ የሐዲስና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ትርጓሜ (አንድምታ) በቃል በመያዝ ይማራል። በመቀጠልም የመጻሕፍተ ሊቃውንትን (ቄርሎስዮሐንስ አፈወርቅሃይማኖተ አበውፍትሐ ነገሥት …) ትርጓሜ ይማራል። ፍላጎት ያለው ተማሪም በተጨማሪ የመጻሕፍተ መነኮሳትን (ማር ይስሐቅ ፊልክስዮስ፣ እና አረጋዊ መንፈሳዊ) አንድምታ በመማር የመጻሕፍት ቤትን ትምህርት ያጠናቅቃል።

የግዕዝ መምህርና ተማሪዎች 1840ዎቹ አካባቢ

በ1830ዎቹ እና 1840ዎቹ በአንኮበር በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አሰባሳቢነት ታላላቅ ሊቃውንት ይገኙ ነበር። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም ከላይ የተጠቀሱትን ትምህርት ዓይነቶች እዛው በአንኮበር በመጀመሪያ ሳያስኬዱ አልቀሩም። በሃይማኖትም ረገድ፣ ለደቀ መዝሙራቸው ለኪዳነ ወልድ እንደነገሩት “የጸጋ ልጆች” ትምህርትን በሕፃንነታቸው ያስተማሯቸው ዓይነ ስውሩ መምህር ወልደ ሥላሴ ናቸው።

.

 ምህር (1842 – 1867)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ቀጣዩን ሃያ አምስት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት ማዕከሎች እንዳሳለፉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይገልጻሉ (“ … ወዕሥራ ወኀምስቱ ዓመት በብሔረ ጐዣም ወዐምሐራ፣ በላስታ ወበቤጌምድር፣ በጐንደርሂ ወበስሜን፣ በትግሬሂ ወበሐማሴን።”) በዚህ ዘመን የታወቁት የአንኮበር ሊቃውንት (እነ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ተክለ ጽዮን፣ እንዲሁም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ) ከሞጣው ጊዮርጊሱ አራት ዓይና ጐሹ ተምረው በብሉይ ኪዳን መምህርነት እንደተመረቁ ይነገራል። የተማሩበትም ዘመን በደጃች ተድላ ጓሉ ጊዜ እንደመሆኑ እስከ 1850ዎቹ አጋማሽ ባለው ዘመን የነበረ ይመስለኛል።

ከአራት ዓይና ጐሹ ተምረው እንደጨረሱ የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጓደኛ ባለቅኔው ተክለ ጽዮን ዲማ ወርደው ቅኔ አስተማሪ ሲሆኑ፣ እሳቸው ደግሞ ወደ ጐንደር አቀኑ። እዛም ከታላቁ ሊቅ ከግምጃ ቤት ማርያሙ ከወልደአብ ወልደሚካኤል ዘንድ የአንድምታ ትምህርታቸውን (መጻሕፍተ ሐዲስና ሊቃውንትን) አስኬዱ።

ከዚህም በኋላ ስለ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ያለን መረጃ በአንኮበር ሚካኤል በሚገኝ ብራና ላይ ያለው የቤት ሽያጭ ውል ነው። ይህም ውል፣ “ይመር ጐጅ ለቄስ ክፍለ ጊዮርጊስ በ፫ ብር ከ፰ ጨው ሁለት ቤት ሸጠዋል” ይላል።

አንኮበር ሚካኤል 1830ዎቹ አካባቢ

ውሉ የተጻፈው በአጼ ቴዎድሮስ መንግሥት (1847-1860 ዓ.ም) በዘመነ ማቴዎስ ነው። ይህም ውሉ የተፈጸመበትን ዓመት 1849፣ 1853 አሊያም 1857 ዓ.ም. ያደርገዋል። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በጐዣም እና በጐንደር ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመት በትምህርት ሊያሳልፉ ስለሚችሉ ውሉ የተፈጸመበት ዘመን በ1853 ወይም በ1857 ቢሆን የበለጠ ያሳምናል።

ከጐዣም እና ጐንደር ቆይታቸው በኋላ ሁለቱ ጓደኛሞች (ተክለ ጽዮን እና ክፍለ ጊዮርጊስ) የብሉያትን አንድምታ አንኮበር ተመልሰው ማስተማር እንደጀመሩ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይናገራሉ። ለምን ያህል ጊዜ አብረው እንዳስተማሩ ባይታወቅም፣ አንደኛው ኦሪት ዘፍጥረት ሲተረጉም ሌላኛው የመሐፈ ነገሥትን አንድምታ እንደሚያስተምር፣ አንዱ ትንቢ ኢሳይያስን ሲተረጉም ሌላው ትንቢ ኤርምያ አንድምታ እንደሚያስኬድ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይነግሩናል።

ከዚህ ቀጥሎ ስለ መምህር ክፍሌ የምናገኘው መረጃ አለቃ ኪዳነ ወልድ ስለ መጽሐፈ ሕዝቅኤል ዘርና ትርጓሜ ፍለጋ ከመምህራቸው ሰምተው አንድ መጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራና ላይ (አሁን በኢየሩሳሌም በደብረ ገነት ቤተ መጻሕፍት የሚገኝ) በጻፉት መቅድም ውስጥ ነው። በዚህም ጽሑፍ ላይ እንደሚተረከው የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ትርጓሜ ትምህርት በአገሪቱ ውስጥ የሚሰጥበት ብቸኛ ቦታ ጐንደር ሆኖ ነበር። በጐንደርም ያሉት የአንድምታ መምህራን ትምህርቱን በድብቅ ቤት ዘግተው ለብቻቸው በማድረጋቸው እነሱ በተለያየ ምክንያት ሲሞቱ ትምህርቱም አብሮ ጠፋ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እንደሚሉት፣

“የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የሊቃውንትና የመነኮሳትን ትርጓሜ ትምህርት እንደጨረስኩ የነቢዩ ሕዝቅኤልን መጽሐፍ ፍለጋ አድባራትን፣ ገዳማትን፣ ደሴታትን ሳስስ ምንም አላረፍኩም።”

በዚህም ምክንያት መምህር ክፍሌ ‘ትክክለኛው’ ሕዝቅኤልን ፍለጋ ወደ ስሜን ወደ ደረስጌ ማርያም ያመራሉ። እዛም ሁለት የሕዝቅኤል መጽሐፎች ያገኛሉ። ብራናዎቹ ግን አላስደሰቷቸውም፣ በተለይ አንደኛው ብዙ የተቆራረጠና የተደላለዘ ነበር። ነገር ግን በመጽሐፈ ሕዝቅኤል ገለጻ ታላቅ ቦታ ያለውን “ሥዕለ ኤስከዴሬ” እና ትርጉሙን የያዘ አንድ ጥራዝ ስላገኙ ልክ የተቀበረ ሳጥን እንዳገኘ ሰው በመደሰት ጥራዙን በሞላ ገለበጡት። ይህ የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ፍለጋ ጉዞ ወደሚቀጥለው የሕይወታቸው ምዕራፍ ይወስደናል።

.

 ስደት (1867-1878)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራናን በማሰስ ላይ እንዳሉ የታላቁ ሊቅ የአለቃ ወልደአብ መጻሕፍት በከረን እንደሚገኙ ይሰማሉ። በዚህም ምክንያት ለሚቀጥሉት አስራ አንድ ዓመታት መጠለያ ወደሚሆናቸው ወደ ምጽዋ እና ከረን ካቶሊክ ሚሽን (ቤተ አፍርንጅ) ያመራሉ።

ምጽዋ እና አካባቢዋ (“ቤተ አፍርንጅ” ከመሀል)

በከረንም ተስተካክለው የተጻፉ፣ ያልተቆረጡ፣ ያልተደለዙ ሁለት የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራናዎችን አገኙ። ብራናዎቹንም በኋላ ለሚሰሩት የሕዝቅኤል አንድምታ ዘር እንዲሆን እንዳለ ገለበጡ። (ይህንንም መጽሐፈ ሕዝቅኤል” ተማሪያቸው አለቃ ኪዳነ ወልድ አደራ ተቀብለው፣ የእብራይስጡንም ዘር አካተው በ1916 ዓ.ም ያትሙታል)

አለቃ ኪዳነ ወልድ ግን ለመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ስደት ሌላም ምክንያት ያቀርባሉ። መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስመግቢያ ላይ ስለዚሁ ምክንያት ባጭሩ ጽፈው ነበር። ነገር ግን በ1948 ዓ.ም. መጽሐፉ ሲታተም አሳታሚው ደስታ ተክለወልድ ባልታወቀ ምክንያት ከመጽሐፉ አስቀርተውታል። ጽሑፉ እንዲህ ይል ነበር፤

“… የስደታቸውም ምክንያት ባጭር ቃል ይህ ነው። … ፬ኛው ሐፄ ዮሐንስ … መምህር ክፍሌንም እንደ ዋልድቤ እንግዳና እንደ ዙራንቤ እንግዳ እንደ መምህር ተክለ አልፋ ምላሳቸውን ለመቁረጥ፣ ለማሰር፣ ለመግረፍ፣ ወይም በጭራሽ ለመሰየፍ በግር በጥፍር ያስፈልጓቸው ነበሩና፤ በዚህ ምክንያት፣ ‘ከመሞት ይሻላል መሰንበት’፣ ‘ከመታሰር ይሻላል ማስተማር’ ብለው ምጽዋዕ ገብተው ከዚያ ሳይወጡ ፫ ዓመት ያህል ኑረዋል።”

እንግዲህ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት፣ አፄ ዮሐንስ ግንቦት 1870 ዓ.ም. ባካሄዱት የቦሩ ሜዳ የሃይማኖት ጉባኤ የ“ጸጋ ልጆች” ከተሸነፉም በኋላ፣ ንጉሡ የ“ጸጋ” አስተሳሰብን ተከታዮች (የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጓደኛን መምህር ተክለ ጽዮንን ጨምሮ) ያሳድዱ ስለነበር ከዚህ አደጋ ለማምለጥ መምህር ክፍሌ ወደ ምጽዋ ተሰደዱ።

ባለቅኔውም ተክለ ጽዮን የሁለቱን ጓደኛሞች የስደት ዕጣ በግእዝ መወድስ ቅኔ ዘግበው ነበር (ቅኔው ከነአማርኛ ትርጉሙ እነሆ)፤

በሰሚዐ ቃሉ ለሳውል ቢጸ ኤርምያስ 

ሠለስተ ዓመተ ኢነትገ አንብዕነ 

ለዝኒ ብካይ ሀገረ ሳውል ኢኮነ

ነግደ ወፈላሴ  

እስመ ሰብአ ቤቱ ለብካይ ንሕነ

ቀዳሚ ኀበ ለመድነ 

በላዕለ ትካዝ ትካዘ ወበላዕለ ሐዘን ሐዘነ  

ሶበሂ ተዘከርናሃ ለደብረ ሊባኖስ እምነ 

ህየ ውስተ አፍላጋ ነበርነ ወበከይነ 

እስመ ማየ ዕድሜነ ኀልቀ ከመ ንዘረው ኵልነ

መንፈቅነ በምሥራቅ እንዘ በምዕራብ መንፈቅነ።

.

“የኤርምያስ ጓደኛ የሆነው የጳውሎስን ቃል በመስማት፤

ሶስት ዘመን እንባችን አልጎደለም፤

ለዚህም ልቅሶ የጳውሎስ አገር እንግዳ አልሆነንም፤

የልቅሶ ቤተሰቦች ነንና፤

በትካዜ ላይ ትካዜን፣ በሐዘንም ላይ ሐዘንን ቀድሞ ከለመድን ዘንድ።

እናታችን ደብረ ሊባኖስንም በአሰብናት ጊዜ፤

በዚያ በወንዞች ተቀመጥንና አለቀስን፤

እኩላችን በምዕራብ እኩላችንም በምሥራቅ፤

ሁላችን እንድንበተን እድሜያችን አልቋልና።”

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም በምጽዋ ከአቡነ ዮሴፍ ሳሉ ከረን በሚገኘው የካቶሊክ ሚስዮን የግእዝ መምህር እንዲሆኑ ይጠየቃሉ። በሀሳቡም ከተስማሙ በኋላ ኢየሩሳሌምን ተሳልመው ሲመለሱ ከረን ማስተማር ይጀምራሉ። በከረንም ቆይታቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከማስተማር በተጨማሪ የተለያዩ መጻሕፍት ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ነበሩ።

በመጀመሪያ ያዘጋጁት መጽሐፍ የአባ ገብረ ሚካኤልን መጽሐፈ ሰዋስው ነበር። ከጥር 1871 እስከ ታኅሣሥ 1872 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከላዛሪስት ሚስዮን ማተሚያ ቤት የወጣው ይህ መጽሐፍ ስድስት ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው ክፍል “የርባታ ዓመል” ሲሆን (በአሁኑ ጊዜ ‘ርባ ቅምር’ ከምንለው ጋር ይቀራረባል) የተለያዩ የሰዋስው ደንቦችን ያስተምራል።

ሁለተኛው ክፍል “ሰዋስውና ቅጽል” ሲሆን ሰምና ወርቅ፣ ባለቤትና ዘርፍ፣ ቅጽል … የመሳሰሉትን ይዳስሳል። ሦስተኛው ክፍል “ዐቢይ አገባብ” (የግስ አገባብ ባሕርይ)፣ አራተኛውና አምስተኛ ክፍል ደግሞ “ንኡስ አገባብ” እና “ደቂቅ አገባብ” (የስሞች አገባብ ባሕርይ) ያቀርባሉ። ስድስተኛው ክፍል ስለ “አኃዝ” (ቁጥር) ካስረዳ በኋላ በመጨረሻ “አእመረ” እና “ይቤ” የተሰኙት የግእዝ ግሶችን እርባታ ያቀርባል። ይህ መጽሐፍ የአባ ገብረ ሚካኤልን ብቻ ሳይሆን የመምህር ክፍሌንም የግእዝ ሰዋስው እውቀት የሚያሳይ ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታትም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከካቶሊኩ ሚስዮናዊ ኩልቦ (Jean-Baptiste Coulbeaux) ጋር በመሆን በ1876 ዓ.ም ኢሚታስዮ – ክርስቶስን ስለ መምሰል፣ በ1880 ዓ.ም ደግሞ ትምህርተ ክርስትያን” የተሰኙ ድርሰቶችን ከላቲንና ጣሊያንኛ ወደ አማርኛ ተርጉመው በሚስዮኑ ማተሚያ ቤት አሳትመዋል። እንዲሁም በ1878 ዓ.ም. ያዘጋጁት መዝሙረ ዳዊት በከረን ታትሟል።

በቦሩ ሜዳ በጉባኤ ላይ በንጉሡ ዳኝነት ተረተው የተሰደዱትን “የጸጋ ልጆች” አስተሳሰብ መምህር ክፍሌ በ1875 ዓ.ም ሃይማኖተ ቅድስት ሥላሴ በሚል ርእስ አዘጋጁ። የረቂቁ የመጀመሪያ ሦስት ምዕራፎች የራሳቸውን የ“ጸጋ ልጆች” ቡድን አስተሳሰብ ሲያቀርብ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ የተቃዋሚዎቻቸውን “ካሮች” እና “ቅብዐቶች” አስተሳሰብ ያቀርባል።

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም ከከረን እና ምጽዋ አስራ አንድ ዓመታት ቆይታቸው በኋላ፣ ከሚስዮኑ አለቃ ከአባ ተክለሃይማኖት ጋር ብዙም ባለመስማማትና “ሮሜን ለማየት” ወደ ጣሊያን አገር ወደ ሮማ አመሩ።

.

ሕር ማዶ (1878 – 1889)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ሮም እንደደረሱ ቫቲካን (Vatican) ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ግእዝ ማስተማር ጀመሩ። በዚህም ወቅት ምጽዋ እና ከረን ሳሉ የጀመሩትን የሮማይስጥ (Latin) ቋንቋ ጥናት በማጠናከር ቀጠሉ። በቆይታቸውም ዘመን ከጣሊያኑ የቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ሊቅ ጒዲ (Ignazio Guidi) ጋር ይተዋወቃሉ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ኪዳነ ወልድ እንደተናገሩት፣

“ሮሜ ሄጄ ከፈረንጅ ሊቃውንት ሁሉ በእውቀት የሚበልጥ፣ የጽርዕ (Greek) እና እብራይስጥ (Hebrew)፣ እንዲሁም ሱርስት (Syriac) እና ዓረብ ዐዋቂ ሰው አገኘሁ። ይህም ሰው፣ ‘ኢትዮጵያዊ ሊቅ ሆይ! ግእዝና አማርኛ አስተምረኝ፣ እኔም የፈለግከውን አስተምርሃለሁ’ አለኝ።”

ይህም ትውውቅ ሁለቱ ሊቃውንት እርስ በርስ እንዲማማሩና ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ምሁራን ይከብድ የነበረውን የአማርኛ ጽሑፎችን ጥናት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እርዳታ ጒዲ ሊካንበት አስችሏል። ጒዲ በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እገዛ ካሳተማቸው ሥራዎቹ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ምሳሌዎች፣ ግጥሞች እና ተረቶች የተሰኘው ነው። ሌሎች በእሳቸው እገዛ ከወጡት ሥራዎች መካከል፣ የነገሥታት ግጥምመርሐ ዕዉርየኢትዮጵያ ቅኔዎችፍትሐ ነገሥት እና እንደዋና ሥራው የሚቆጠረውን “የአማርኛ-ጣሊያንኛ መዝገበ ቃላት መጥቀስ ይቻላል።

.

 መጨረሻ (1889 – 1900)

ከአስራ አንድ ዓመታት የጣሊያን ቆይታም በኋላ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ወደ ኢየሩሳሌም አመሩ። ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ዕድሜያቸው ሰባዎቹ ላይ ደርሶ ስለነበር ፍላጎታቸው የሕይወታቸውን የመጨረሻ ዓመታት በጸሎትና በጥናት ለማሳለፍ ነበር። እዛም ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን ለማካፈል ቢሞክሩም፣ ጥናትና ምርምር ላይ መስራት የሚፈልግ ሊያገኙ አልቻሉም።

ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ከሳቸው ጋር ለመስራት ችሎታና ፍላጎትም ከነበረው ከወጣቱ ኪዳነ ወልድ ጋር ይገናኛሉ። የሁለቱ መገናኘትም ያስገኘልን ትልቁ ነገር የ1948ቱ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘው የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ነው።

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ደስታ ተክለ ወልድ

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በኢየሩሳሌም አስራ አንድ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ጳጕሜ 3፣ 1900 ዓ.ም በሰማንያ ሦስት ዓመታቸው አረፉ። ከአንኮበር ጓደኛቸው ከባለቅኔው ተክለጽዮን አጠገብም ተቀበሩ።

.

(በክፍል 2 ይቀጥላል)

ኅሩይ አብዱ

ሚያዝያ 2009

 .

ምንጮች

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪወክ) – መዝገበ ቃላት – መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ አዲስ አበባ 1948 ዓ.ም ገጽ 7-8

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪወክ) – ሃይማኖተ አበው ቀደምት ውስተ Berhanou Abebbe (ed.) – Kidana Wald Kéfle, ሃይማኖተ አበው ቀደምት La foi des pères anciens, 1. Texte éthiopien. Enseignement de Mamher Kefla Giyorgis …, Stuttgart 1986 ገጽ 268-274

ሮጀር ካውሊ Roger Cowley, “A Geez Prologue concerning the Work of Mämhér Kéfla Giyorgis on the Text and Interpretation of the Book of Ezekiel”, ውስተ A STANISLAV SEGERT – ANDRAs J.E. BOOROGLIGETI (eds.), Ethiopian Studies: Dedicated to Wolf Leslau on the Occasion of his Seventy-Fifth Birthday, November 14th, 1981, by Friends and Colleagues, Wiesbaden 1983. ገጽ 99–114

ብርሃኑ አበበ – Berhanou Abebbe (ed.) – Kidana Wald Kéfle, ሃይማኖተ አበው ቀደምት La foi des pères anciens, 1. Texte éthiopien. Enseignement de Mamher Kefla Giyorgis …, Stuttgart 1986 ገጽ 7-17

ቮልክ እና ኖስኒትሲን – Ewa Wolk and Denis Nosnitsin, “Kéflä Giyorgis” ውስተ Encyclopaedia Aethiopica ቅጽ 3 ገጽ 370-371 

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

በተአምራት አማኑኤል

(ክፍል 1)

.

የጥንቱ የኢትዮጵያ አፈ ታሪክ “አንድ ሽሕ ዓመት ያህል ከልደተ ክርስቶስ በፊት፣ ባገራችን ሊቃውንትና መምህራን ነበሩበት … እስከ ዛሬ ድረስም ሊቅ፣ መምህርና ደራሲ አልጠፉበትም” ይላል። ቢሆንም አፈ ታሪኩ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከብሉያት በቀር ሌላ ዓይነት መጻሕፍት መኖር አለመኖራቸውን አያመለክትም።

አፈ ታሪካችን በሰሎሞን ዘመን ከሕዝበ እስራኤል ጋራ ግንኙነት እንደነበረን፣ ንግሥተ ሳባ ዛሬ ኢትዮጵያ (ሐበሻ) የምንለውንና ከዓረብ አገር የደቡቡን ክፍል ትገዛ እንደነበረች፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ሒዳ ከሰሎሞን ጋር ተዋውቃ ከርሱ ቀዳማዊ ምኒልክ የተባለ ወንድ ልጅ እንደወለደች፣ ቀዳማዊ ምኒልክም እስከ ዛሬ ድረስ ላሉት ነገሥታቶቻችን አባት መሆኑን፣ እርሱም አባቱን ሰሎሞንን ለማየት ሒዶ ከኢየሩሳሌም ሲመለስ፣ ጽላተ ሙሴንና እስከ ሰሎሞን ዘመን ከእስራኤላውያን የተጻፉትን መጻሕፍተ ብሉያትን ይዞ እንደመጣ ይነግራል።

ይህን አፈ ታሪክ የሚነግሩ መጻሕፍት ባገራችን መጻፍ የጀመሩት ከ1300ኛው ዓመተ ምሕረት ወዲህ ነው። ሽሕ ዓመት ከዚያ በፊት ለሕዝቡ ወንጌል ተሰብኮለት ነበር። በሽሕ ዓመት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ፣ በአሕዛብነት የነበረበትን ዘመን እንዲጠየፈው፣ የሕዝበ እሥራኤልን መጻሕፍትና አሳብ እንዲወድ አድርጎት ስለ ነበረ፣ ጥቂት በጥቂት የገዛ ራሱን ታሪክ እየዘነጋ፣ የእስራኤል ልጅ ነኝ ከማለትና የእስራኤል ሕዝብ የጻፋቸውን መጻሕፍት፣ አያቶቼ የጻፏቸው ናቸው ከማለት ደርሷል።

በሰሎሞን ዘመን የእስራኤልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ኖሯቸው ይሆናል ቢባል፣ ማስረጃው እንኳ ባይገኝ፣ ሳይሆን አይቀርም በማለት በተቀበልነው። በሰሎሞን ዘመን ከብሉያት መጻሕፍት አንዳንዶቹ እስከ ኢትዮጵያ ደርሰው በዚያው ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀብሎ የሃይማኖት ሥራ አስይዟቸዋል ለማለት ግን ማስረጃው እስኪገኝ ድረስ ልብ ወለድ የመጣ አሳብ ነው እንላለን።

የዛሬው ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሙሴ የሚባሉት አምስቱ ብሔረ ኦሪት ተሰብስበው ባንድነት መገኘት የጀመሩት በሰሎሞን ዘመን ብቻ ነው ይለናል። የዚህ ክርክር ገና ሳይጨረስ፣ አፈ ታሪካችን፤ “መጽሐፈ ኦሪት በሰሎሞን ዘመን ካገራችን ደርሰው ነበር” ሲል፣ ለራሱ ክብር በመጓጓት፣ ታሪክ ጥሶ የተራመደ ሁኖ ይታየናል። ይህም ከወገን ለጊዜው የበለጠ መስሎ የታየውን እየመረጡ “ወገኔ ነው” ማለት፣ የዛሬ ሳይሆን የጥንት፣ የኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የደረሰና፣ ታሪክ ተመርምሮ ወሬው ትክክለኛ አለመሆኑ ሲታይ የሚቀር ነው።

በግሪኮች ሥልጣኔ ንጹሕ ቅናት ያደረባቸው ሮማውያን፣ የግሪኮች መዓረግ ተካፋይ ለመሆን፣ የ”ኤኔአ”ን ተረት ፈጥረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕዝበ እስራኤል የተነገረው ሁሉ ደስ ሲያሰኛቸው ከነበሩት እንግሊዞች፣ አንዳንዱ ባለ ታሪክ፣ “ስደት የሔዱት የአስሩ ነገደ እስራኤል የልጅ ልጆች ነን” ሲል ነበር። ዛሬ ግን፣ ሮማውያንም ከግሪኮች ጋር ዝምድና እንኳ ቢኖራቸው፣ ባለ ታሪክ ሌላ ማስረጃ ያመጣል እንጅ የ”ኤኔአ”ን ተረት መሠረት አያደርገውም። የባለ ታሪክ ስምና መዓረግ ያለው ሰው ደግሞ፣ “በእንግሊዝ ደሴቶች ከምሥራቅ የመጣ ሕዝብ ሰፍሮበት ኑሮ ይሆናል” እንኳ ቢል፣ “አንግሎ ሳክሶን የአስሩ ነገደ እስራኤል ልጆች ናቸው” አይልም።

እንደዚኸው ሁሉ የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲሱ የምርመር አካሔድ የሚከታተል ሰው፣ ታሪኩን በሌላ መንገድ ያስረዳል እንጂ፣ ስለ ንግሥት ሳባና ስለ ሰሎሞን የሚነገረውን መሠረት አያደርግም። ስለዚህም ከልደተ ክርስቶስ በፊት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ኑረው እንደሆነ የደረሱበትን ለማወቅ ቸግሮናል እንላለን እንጅ (ሕዝበ እስራኤል በሰሎሞን ዘመን የሙሴን መጻሕፍት መሰብሰብ ገና ሲጀምር) እነዚህ መጻሕፍት ድሮ ባገራችን ነበሩ ለማለት ይቸግረናል።

በውቅሮ አቅራቢያ የተገኘው የአልሙቃሕ ቤተ ጸሎት

ጽሑፍ ሥራ በኢትዮጵያ ገና ከልደተ ክርስቶስ በፊት ተጀምሮ ነበር እንላለን። ማስረጃው ግን በጣም ችግር ነው። እርግጥ የምናውቀው ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን አቅራብያ በትግሬ አውራጃ ከሐውልትና ከጸሎት ቤት የተጻፈ አንዳንድ ቃል መገኘቱን ነው። ቀደምት የተባሉት ጽሕፈቶች የሚገኙት በሳባና በግሪክ ቋንቋ ነው። ከክርስቶስ ልደት በኋላ 300ኛው ዘመን ሲጀምር ግን፣ ጽሕፈቱና ንግግሩ የተጣራ፣ በግዕዝ ቋንቋ ከሐውልት ላይ የተጻፈ መታሰብያ አለ። ስለዚህም ከሊቃውንት አንዳንዱ እንዲህ ይላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፣

           ፊት፤                ግሪክ፣

          ቀጥሎ፤              ሳባ፣

           ኋላ፤                ግዕዝ

king-ezana-s-inscription
የንጉሥ ኤዛና የድል ሐውልት በአክሱም

ለዚህ አሳብ ብዙ ተቃራኒ አልተነሣበትም። ነገር ግን ገና የመንን ሳይለቅ ባገሩ ቋንቋና ፊደል ሲጽፍ የነበረ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለምን በግሪክ ጻፈ? ደግሞም እስከ ዛሬ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ሥራ የተያዘበት ሴማዊ የሆነው የግዕዝ ቋንቋ እጅግ የተጣራ በመሆኑ፣ ለግሪክና ለላቲን ቋንቋ ተወዳዳሪ ሊሆን ይቃጣዋል። ይህን የመሰለ ቋንቋ እያለው ባገር ውስጥ ላለው ጕዳይ ለምን በግሪክ ይጽፋል? የዚህ ምክንያቱ እስኪገለጥ ድረስ ከዚህ በላይ የተነገረው አሳብ ትክክለኛ ነው ላይባል ነው።

በርሱ ፈንታም ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን አሳብ መናገር ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽሕፈት ቋንቋው፤

           ፊት፤                ሳባ፣

           ቀጥሎ፤            ግዕዝ

የግሪክ ቋንቋ ከእስክንድር ጀምሮ ሮማውያን ግብጽን እስከያዙበትና ከዚያም በኋላ እስከ ብዙ ዘመን ለግብፅና ለታናሽ እስያ ሕዝብ ዋና ቋንቋ ሁኖ ነበረ። ለኢትዮጵያ ደግሞ ከሠለጠነው ዓለም ጋር መገናኛ ቋንቋ ሁኖላት ለደብዳቤ፣ አላፊ አግዳሚ ለሚያየው ሐውልትዋ፣ ባሕር ተሻግሮ ለሚገበያዩበት ገንዘብዋ፣ ይህንንም ለመሰለ ልዩ ጕዳይ የጽሕፈት ቋንቋዋ ኑሮ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ከ400ኛው ዓመተ ምሕረት በፊት (ይህ ማለት ወንጌል ባገሩ ሳይሰበክ) በሳባ ሆነ በግሪክ፣ በግዕዝም ሆነ ወይም በሌላ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ኑሮ እንደሆን ወሬው ከኛ አልደረሰም። ዛሬ በጃችን ያሉት መጻሕፍት ከ400ኛው እስከ 1700ኛው ዓ ም በግዕዝ፣ ከዚያ እስከ ዛሬ በግዕዝና በአማርኛ የተጻፉ ናቸው። ግዕዝ የሴም ቋንቋ መሆኑን ከዚህ በፊት አመልክተናል። ከዓረብ በስተደቡብ ከነበሩት ሴማውያን ያንዱ ነገድ ቋንቋ ኑሮ ይሆናል ይባላል። ምናልባትም ከዚሁ ነገድ አንድ ክፍል ዛሬ ዓጋሜ በምንለው አውራጃ ግድም ይኖር ኖሯል። ድንገት ደግሞ ከትግሬ አውራጃ ካሉት ነገዶች አንዳንዶች ይነጋገሩበት ኑረው ይሆናል። “በኢትዮጵያ ያሉት የሴም ቋንቋዎች (ትግርኛ፣ ትግረ፣ አማርኛ፣ ወዘተ) ከርሱ የመጡ ናቸው” የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ይህን አሳብ የማይቀበሉ በዚህ ፈንታም፣ “ከዓረብ በስተደቡብ ሲኖሩ ከነበሩት የሴም ነገዶች አንዳንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ ኖሯቸው፣ የእያንዳንዱ ነገድ ቋንቋ ራሱን እንደቻለ፣ በሆነለት መጠን እየደረጀ ሄዷል እንጅ፣ ግዕዝ በኢትዮጵያ ላለው ልዩ ልዩ የሴም ቋንቋ አባቱ አይደለም” የሚሉ አሉ።

img0042
በቀደምትነቱ የሚታወቀው የአባ ገሪማ ወንጌል

በግዕዝ ከተጻፉት በብዙ ሽሕ ከሚቆጠሩት መጻሕፍቶቻችን ጥቂቶች ሲቀሩ፣ አብዛኛው ከክርስትያናዊ ግሪክና ዓረብ ከሌላም ቋንቋ የተተረጐሙ ናቸው። ደግሞም የዓለምንና የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚነግሩት ከጥቂቶች መጻሕፍት በቀር ሁሉም የሃይማኖት መጻሕፍት ናቸው። ስለዚህ የኢትዮጵያዊነታችንን አሳብ የሚገልጥ መጽሐፍ በብዛት አይገኝባቸውም። ዋናው መጽሐፋችን “መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። ይኸውም ብሉይና ሐዲሱ እግዚአብሔር በዓለምና በእስራኤል ላይ የሠራውንና የሚሠራውን እስራኤላውያን በታያቸው ዓይነት የሚገልጽ መጽሐፍ መሆኑን፣ ሁሉ ያውቀዋል። ምስጋና ለዚህ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በሃይማኖትና በምግባር ከፍ ካለ ደረጃ ደርሶ፣ በያዘው መንገድ እየገፋበት እንዲሔድ ብርቱ ኃይል ተሰጥቶታል።

ደግሞም የግዕዝ ቋንቋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወዳገራችን ሳይመጣ ገና ፊት አስቀድሞ ራሱን የቻለ እንደነበረ በሐተታ እንኳ ብንረዳው፣ የግዕዝ ቋንቋ ጽሑፍ ምስክሩ ባለቤቶቹ የጻፉት መጽሐፍ መሆኑ ቀርቶ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የሌሎች መጻሕፍት ትርጕም ነው። ማናቸውም የሠለጠነ ሕዝብ ለቋንቋው፣ ለሰዋስው ማስረጃ ባለቤቶቹ የጻፉትን ሲጠቅስ፣ ግዕዝ ለሰዋስው ማስረጃ የሚጠቅስ ከባዕድ ቋንቋ የተተረጐሙትን መጻሕፍት ነው። በግዕዝ ከጻፉት ካገራችን ደራስያን ይቅርና በአሳብ፣ በአጻጻፍ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል ሳይከተሉ የጻፉ የሚገኙ አይመስለኝም። ይህም ልምድ የሃይማኖት አሳባቸውን የሚገልጹበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ አገራችን ታሪክና ማናቸውንም ጕዳይ በሚጽፉበት ጊዜ ጭምር ነው። ይህም የአጻጻፍ አካሔድ ኢትዮጵያ ገንዘብ ካደረገችው ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር የተስማማ ንግግር ለማምጣት የተመቸ ከመሆኑ በላይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሳንቀበል ከነበረብን አሕዛባዊ ከሆነ ምሳሌና ንግግር አርቆናል።

ይሁን እንጅ ኢትዮጵያዊ የሆነ አሳብ፣ ኢትዮጵያዊ በሆነ ንግግር የመግለጹ ዕድል ለግዕዝ ቀርቶበት ለአማርኛ ሆኗል። ዛሬ ዘመን በግዕዝ እግር ተተክቶ፣ የመንግሥትና የሕዝብ ጕዳይ የሚሠራበት የአማርኛ ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባማርኛ መጻፍ ከጀመረ ስድስት መቶ ዓመታት ሁኖታል። አማርኛ ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን አካሔድ በ፫ ዘመን ቢከፍሉት ይሆናል።

፩ኛውን ዘመነ ዓምደ ጽዮን (1336-1599 ዓ ም)

፪ኛውን ዘመነ ሱስንዮስ (1599-1847 ዓ ም)

፫ኛውን ዘመነ ቴዎድሮስ (1847-1936 ዓ ም)

በ፩ኛው ዘመን በአማርኛ የተጻፈው ሥራ እጅግ ጥቂት ነው። የተጻፈውም ላንዳንድ ነገሥታት ምስጋና ደራሲው ባልታወቀ የተገጠመ ቅኔ ነው። ቅኔውም በዘመናት ውስጥ አንድ ቋንቋ እንደምን ሁኖ እየተለዋወጠ ለመሄዱ ዋና ምስክር ከመሆኑ በላይ በዚያ ዘመን የነገሥታቱ ሥልጣን የተዘረጋበት የሰፊው አገር ሁኔታ እንዴት እንደነበረ፣ ለታሪክም ለዦግራፊም ማስረጃ ለመሆን ይረዳል።

pages-from-bruce-88-bodleian-library-oxford
በአማርኛ የተጻፈ የነገሥታት ግጥም (የ1600ዎቹ ቅጂ)

አማርኛው ዛሬ ዘመን የማንናገርበትና የማንጽፈው፣ ለማስተዋሉም የሚያስቸግረንና የሰዋስው አካሔዱ የተለዋወጠ ብዙ ቃልና አገባብ አለበት። እርሱን የመሰለ አማርኛም በየዘመኑ እየተጻፈ ምናልባት እስከ 1599 ደርሶ ይሆናል። ነገር ግን ከ1555 እስከ 1599 ዓ.ም ባማርኛ የተጻፈ ምስክር አይገኝም፤ ቢገኝም ከዚህ በፊት ያመለከትሁትን የመሰለ ግጥም ሳይሆን አይቀርም።

ከ1500ኛው ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወገን ለይቶ አልጋ ለመያዝ እርስ በርሱ ሲዋጋ፣ ባንድ ወገን ደግሞ ቱርኮችና ፖርቱጋሎች በቀይ ባሕር ሥልጣናቸውን ለመዘርጋት ይፈካከሩ ነበር። ቱርኮች በቀይ ባሕር ዙርያ ላለው ፖሊቲካቸው የኢትዮጵያን እስላም ሲረዱ፣ ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የፖርቱጋልን እርዳታ መለመን ግድ ሆነበት። አራት መቶም ያህል ጠበንጃ የያዙ ፖርቱጋሎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተዋጉበት ጊዜ፣ ድል ለክርስቲያኑ ወገን ሆነ።

የፖርቱጋል መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋራ ግንኙነት ሲጀምር ያገሩ ካህናት በኢትዮጵያ ለማስተማር እንዲፈቀድላቸው ተነጋግሮ ነበርና በስምምነታቸው የካቶሊክ ካህናት በኢትዮጵያ ማስተማር ጀመሩ። የሚያስተምሩበትና የሚጽፉበት ቋንቋ አማርኛ ነበርና የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ደግሞ ሕዝቡ ካቶሊክ እንዳይሆንበት ግዕዝን ሳይተው ባማርኛ መተርጐምና መጻፍ ጀመረ። በዚያው ዘመን ለመጻሕፍት ትርጕምና ለስብከት የተጀመረው አማርኛ ገና ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ፣ አንዳንዱም ንግግር ግዕዝ ላልተማረ ሰው በፍጹም የማይሰማ ነበር። እንደዚኽው ሁሉ በዚያው ዘመን ሲጻፍ የነበረው የነገሥታት ታሪክ ግዕዙ አማርኛ ቅልቅል ነበር።

old-amharic
በ1760ዎቹ የተጻፈ የአማርኛው መሐልየ መሐልይ ዘሰሎሞን

ያም ሁሉ ሁኖ እንኳንስና ለውጭ አገር ሕዝብ የሚተርፍ፣ ካገራችን ውስጥ ከፍተኛ አሳብ የሚያሳድር በታረመ አማርኛ የተጻፈ መጽሐፍ ለማግኘት ችግር ነው። መጻሕፍቱ የፈጸሙት ጕዳይ፣ በሕዝቡ ላይ ከመጣበት ከሃይማኖት ተወዳዳሪ መከላከልና የባላገር ቋንቋ የነበረውን አማርኛን ጽሑፍ ሥራ ለማስያዝ መጀመራቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ለትሕትና ሲል ስሙን አያመለክትም ነበርና የመጻሕፍቱን ፍሬ ነገር መዘርዘር፣ ደራሲው ወይም ተርጓሚው ማን እንደነበር መርምሮ የሕይወቱን ታሪክ ማመልከት ይቸግረናል።

(በክፍል ሁለት ይቀጥላል …)

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም