“አበባየሆሽ” (ሥነ ቃል)

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን

ጌቶች  አሉ ብለን

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን

እሜቴ አሉ ብለን

እውዬ (እኸ) እዋውዬ ካሽከር ተዋውዬ
ጌቶች አሉ ብዬ ገባሁ ሰተት ብዬ

አበባየሆሽ (ለምለም)

ባልንጀሮቼ (ለምለም) ቁሙ በተራ (ለምለም)
እንጨት ሰብሬ (ለምለም) ቤት እስክሰራ (ለምለም)
እንኳን ቤትና (ለምለም) የለኝም አጥር (ለምለም)
እደጅ አድራለሁ (ለምለም) ኮከብ ስቆጥር (ለምለም)
ኮከብ ቆጥሬ (ለምለም) ስገባ ቤቴ (ለምለም)
ትቆጣኛለች (ለምለም) የንጀራ እናቴ (ለምለም)
የንጀራ እናቴ (ለምለም) ሁለ’ልጅ አላት (ለምለም)
ለነሱ ፍትፍት (ለምለም) ለኔ ድርቆሽ (ለምለም)
ከሆዴ ገብቶ (ለምለም) ሲንኮሻኮሽ (ለምለም)
አበባማ አለ (ለምለም) በየውድሩ (ለምለም)
ባልንጀሮቼ (ለምለም) ወልደው ሲድሩ (ለምለም)
እኔ በሰው ልጅ (ለምለም) ማሞ እሹሩሩ (ለምለም)

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ

ከገዳይ ጋራ (ለምለም) ስጫወት ውዬ (ለምለም)
ራታችንን (ለምለም) ንፍሮ ቀቅዬ (ለምለም)
ድፎ ጋግሬ (ለምለም) ብላ ብለው (ለምለም)
ጉልቻ አንስቶ (ለምለም) ጎኔን አለው (ለምለም)
ከጎኔም ጎኔ (ለምለም) ኩላሊቴን (ለምለም)
እናቴን ጥሯት (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም)
እሷን ካጣችሁ (ለምለም) መቀነቷን (ለምለም)
አሸተዋለሁ (ለምለም) እሷን እሷን (ለምለም)
አባቴን ጥሩ (ለምለም) መድሃኒቴን (ለምለም)
እሱን ካጣችሁ (ለምለም) ጋሻ ጦሩን (ለምለም)
አሸተዋለሁ (ለምለም) እሱን እሱን (ለምለም)

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ

እቴ አበባ ሽታ አበባዬ (አዬ እቴ አበባዬ)
እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ (አዬ እቴ አበባዬ)
ጥላኝ ሄደች ባምሌ ጨለማ (አዬ እቴ አበባዬ)
እቴ አበባሽ እቴ እያለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ጋሻ ጦሬን ወስዳ አሸጠቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
እንኳን ጋሻ ይሸጣል በሬ (አዬ እቴ አበባዬ)
ከናጥንቱ ከነገበሬ (አዬ እቴ አበባዬ)

ሄሎ ሄሎ የገደል ሄሎ (አዬ እቴ አበባዬ)
ማን ወለደሽ እንዲህ መልምሎ (አዬ እቴ አበባዬ)
ወለደቺኝ መለመለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ላፈንጉስ ዳርኩሽ አለቺኝ (አዬ እቴ አበባዬ)
ካፈንጉስ አምስት ወልጄ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ዳኛ ያውም መልከኛ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ቄስ ቆሞ ቀድስ (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ቂል ንፍሮ ቀቅል (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዷ ሴት የሺመቤት (አዬ እቴ አበባዬ)
አንዱ ሞኝ ቂጣ ለማኝ (አዬ እቴ አበባዬ)

ይሸታል ዶሮ ዶሮ  የማምዬ ጓሮ
ይሸታል ጠጅ ጠጅ  የጌቶችም ደጅ

ሻሽዬ (እኸ) ሻሽ አበባ
ደሞም ሻሽ አበባ
እራስ ዩም ግቢ ይታያል ሲኒማ
የማነው ሲኒማ ያፀደ ተሰማ

ሻሽዬ (እኸ) ሻሽ አበባ
ደሞም ሻሽ አበባ
ትራሷም ባላበባ
ፍራሹም ባላበባ
እርግፍ እንደወለባ

የማምዬ ቤት (ለምለም) ካቡ ለካቡ (ለምለም)
እንኳን ውሻቸው (ለምለም) ይብላኝ እባቡ (ለምለም)

ከብረው ይቆዩን ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሃምሳ ጥገቶች አስረው
ከብረው ይቆዩን ከብረው

ከብረው ይቆዩን በፋፋ
የወለዱት ልጅ ይፋፋ
ከብረው ይቆዩን በስንዴ
ወንድ ልጅ ወልደው ነጋዴ
ከብረው ይቆዩን ከብረው

(የህዝብ ግጥም)

(ምስል)  ሕይወት ከተማ 

“ዓለም እና ጊዜ” (ግጥም)

“ዓለም እና ጊዜ”

በከበደ ሚካኤል

.

.

እኔማ አቶ ጊዜ፥ ከጥንት ዠምሬ፣

ለፍጥረት ታዛቢ፥ ሆኜ በመኖሬ፣

እጅግ በረዘመው፥ በራቀው መንገዴ፣

ቸኩዬ በፍጥነት፥ ሳልፍ እንደ ልማዴ፣

መቼም አይቀርና፥ አይቶ መመልከት፣

ትልቅ ግቢ አይቼ፥ ባለ ብዙ ቤት፣

ከደጅ ሲተራመስ፥ ሰዉ ከቤት ተርፎ፣

ይመስል ነበረ፥ ንብ ያለበት ቀፎ።

ያጥሮቹ አሠራር፥ የግቢውም መድመቅ፣

የቤቶቹም ብዛት፥ በጣም የሚደነቅ፣

እንደዚህ ግቢውን፥ ሠርቶ ያሳመረ፣

ማን ይሆን? አልኩና፥ ከዚህ የሰፈረ፣

ደንቆኝ ስመለከት፥ በጣም ተገርሜ፣

ሰው አገኘሁና፥ አልኩት “በል ወንድሜ፣

የዚህ የውብ ግቢ፥ ባለቤቱ ማነው?”

“ያባት ያያቱ ርስት፥ ያንድ ከበርቴ ነው፣

ርስቱም ዘላለም፥ አለ ሳይነካ”፣

ብሎ መለሰልኝ፥ ኰርቶ እየተመካ።

 

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

 

ከዚያ ካጥር ግቢ፥ ከዚያ ሁሉ ቤት፣

ከቁመቱ ርዝመት፥ ከጐኑ ስፋት፣

አንድ ድንጋይ እንኳን፥ ጠፍቶ ምልክት፣

ያ ያየሁት ሁሉ፥ እንዳልነበር ሆኖ፣

ከግቢው ቦታ ላይ፥ አየሁ ትልቅ መስኖ።

የለመለመበት፥ አንድ ትልቅ ጨፌ፣

ተመለከትኩና፥ ልሄድ ስል አልፌ፣

አንድ ትልቅ ዛፍ ሥር፥ ተጠግቶ ጥላ፣

አንድ እረኛ አገኘሁ፥ ከብቶች ሣር ሲያበላ።

“እንደዚህ ያለ ሣር፥ የበቀለበት፣

ከመቼ ወዲህ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤

እሱም ቁጭ እንዳለ፥ ቀና ብሎ አይቶኝ፣

“ዘለዓለም ለከብቶች፥ ግጦሽ የሚገኝ፣

ከዚሁ መስኖ ነው” ሲል መለሰልኝ።

 

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

 

መስኖውም ጠፋና፥ ጨፌነቱ ቀርቶ፣

ከመስኩ ቦታ ላይ፥ ከተማ ተሠርቶ፣

የቤቱ መበርከት፥ የመንገዱ ማማር፣

የከተማው ጥዳት፥ የግንቡም አሠራር፣

የሕዝቡ አበዛዝ፥ የገበያው መድመቅ፣

ታይቶ እማይጠገብ፥ እጅግ የሚደነቅ።

ያማረች ከተማ፥ የጥበብ መዝገብ፣

ጠንተው የቆሙባት፥ ዐዋጅና ደንብ፣

ውበቷን አድንቄ፥ ስመለከታት፣

ዕድሜው የጠና ሰው፥ አግኝቼ ድንገት፣

“መች ነው የተሠራች?” ብዬ ጠየቅሁት።

እሱም መለሰልኝ፥ በጣቱ አመልክቶ፣

“ይች ትልቅ ከተማ፥ ከጥንትም አንሥቶ፣

መልኳ እየታደሰ፥ ውበቷ እያበራ፣

ይኖራል ዘለዓለም፥ ሥልጣኗ እንደ ኰራ”።

 

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

 

ከዚያች ከከተማ፥ ጠፍቶ ምልክት፣

አየሁ ከዚያ ቦታ፥ ጫካ በቅሎበት፤

ሲተራመሱበት፥ ዥብ ነበር አንበሳ፣

በያይነቱ አውሬ፥ አዕዋፍ እንስሳ፣

ሁሉም በየቋንቋው፥ ድምፁን እያሰማ፣

ለጫካው ሲሰጡት፥ የሚያስፈራ ግርማ፣

የዛፉ አበዛዝ፥ ያውሬው መበርከት፣

እጅግ አስደናቂ፥ ሆኖ አገኘሁት።

ደኑን ተመልክቼ፥ እያየሁ ስሄድ፣

አገኘሁ ያገር ሰው፥ ድንገት በመንገድ፤

“ዛፍ እንጨቱ፥ በቅሎ ጫካው የደመቀው፣

ከመቼ ወዲህ ነው?” ብዬ ብጠይቀው፣

ትክ ብሎ እያየ፥ ጫካ ጫካውን፣

እንዲህ መለሰልኝ፥ እሱም ተራውን፤

“ይህን መጠየቅህ፥ እንግዳ ነህ ለካ፣

ጥድ የሚበቅልበት፥ ግራርና ወርካ፣

ጥንቱንም ደን ነው፥ የዘላለም ጫካ”።

 

አንዱ ስፍራ ሲለቅ፥ አንዱ እየተተካ፣

ሁሉም ርስቴ ነች፥ እያለ ሲመካ፣

ሞኝነት አድሮብን፥ ሳናስበው እኛ፣

ዓለም ሰፈር ሆና፥ ሕዝቡ መንገደኛ፣

ትውልድ ፈሳሽ ውሃ፥ መሬቷም ዥረት፣

መሆኑን ዘንግቶ፥ ይህ ሁሉ ፍጥረት፣

ስትመለከቱት፥ በሰልፍ ተጉዞ፣

ሁሉም በየተራው፥ ያልፋል ተያይዞ።

.

ከበደ ሚካኤል

(1936 እና 1956 ዓ.ም)

.

[ምንጭ] – “የቅኔ አዝመራ”። ፲፱፻፶፮። ገጽ 4-8።

“ባሻ አሸብር በአሜሪካ” (ግጥም)

“ባሻ አሸብር በአሜሪካ”

ከመንግሥቱ ለማ

.

 

የዛሬ አሥር ዓመት፥ በታላቅ ሹመት

አሜሪካ ልኮኝ፥ ነበረ መንግሥት፤

ዋሽንግቶን ገብቼም፥ ዋልሁ አደርሁኝና

ሽር ሽር ስል ሳለ፥ ባንድ አውራ ጐዳና

አላፊ አግዳሚውን፥ ጥቁሩን ነጩን

ሳይ ስመለከተው፥ በኢትዮጵያዊ ዐይን

የውሀ ጥም ደርሶ፥ ስላረገኝ ቅጥል

ከመንገድ ዳር ካለች፥ ካንድ ትንሽ ውቴል

ጐራ አልኩና፥ ገና ከወምበር ላርፍ ስል

ተንደርድሮ መጣ፥ የውቴሉ ጌታ

አማረው ቋመጠ፥ ከጀለው ሊማታ፤

“አብዷል ሰክሯል እንዴ? ምንድን መሆኑ ነው?

በል ንካኝ በዱላ፥ ግንባርህን ላቡነው!”

ብዬ ስነጋገር፥ ሰምቶ ባማርኛ

አሳላፊው ሆነ፥ አስታራቂ ዳኛ፤

ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፥ እንዳገራችን ሕግ

አክብሮ ጠየቀኝ፥ ምን እንደምፈልግ፤

እኔም ጐራ ያልሁት፥ የሚጠጣ ነገር

ለመሻት መሆኑን፥ ነግሬ ከወንበር

“ይቅርታዎን ጌታ፥ አዝናለሁ በጣሙ

ምናምኒት የለም፥ በከንቱ አይድከሙ”

አለና እጅ ነሣኝ፥ ሳቁን እየቻለ

“ውሀም የለ?” ብለው፥ በሳቅ ገነፈለ፤

ቤቱን የሞላው ሰው፥ ሁሉም አጨብጭቦ

“ብራቮ!” ተባለ፥ “ብራቮ! ብራቮ!”

በጣም ተገርሜ፥ ደንቆኝ ‘ያየሁት

ከዘራየን ይዤ፥ ሄድሁኝ ወጣሁት፤

ሀሳብ ገብቶኝ እደጅ፥ ሳሰላስል ቁሜ

ያን ቂዛዛ መስኮት፥ ባስተውለው አግድሜ

አራዳ ግሪኮች፥ እንደሚሸጡት

ያለ በያይነቱ፥ አየሁኝ ብስኩት፤

ትዝ አለኝ “አራዳ አዲሳባ ሆይ

አገርም እንደ ሰው፥ ይናፍቃል ወይ?” …

አጐመዠኝ በሉ፥ ሳይርበኝ ጠግቤ

አስተውለው ጀመረ፥ መስኮቱን ቀርቤ፤

የምገዛውንም፥ በልቤ ቆጥሬ

ዳግም ልገባ ስል፥ በስተበሩ ዞሬ

ዘወር ብዬ አያለሁ፥ የውቴሉ ጌታ

ተኩሮ  ያየኛል፥ ወደኔም ተጠጋ

“ስንት ነው ሰውዬ፥ ያንዱ ብስኩት ዋጋ?”

የያዘው አባዜ፥ ብሎት አላናግር

ዐይኑ ደም ለበሰ፥ ይጉረጠረጥ ጀመር፤

“ዓለም ሁሉ ያውቃል፥ መሆኔን ታጋሽ …

ትግሥቴ አሁን አልቋል

ጥፋ ብረር ሽሽ! …

አገጭህን በቦክስ፥ ሳላፈራርሰው

ይህ ፈጠጤ ዐይንህን፥ እዚህ ሳላፈሰው

እሱቄ መግባትህ፥ አንሶህ አሁንስ

መስኮቴ ፊት ደሞ፥ ልትልከሰከስ?!

ገበያ አላገኝም! ደምበኛዎቼም

እዚህ አንተን ካዩ፥ ዳግመኛ አይመጡም

ሥራ ሥራ እኮ ነው፥ አይገባህም እንዴ?

ወግድ! አትገተር፥ ይቋረጣል ንግዴ!”

ይህንን እንዳለ፥ ቁጣው ጠና ጋለ

አገጨና ጉንጨም፥ በቡጢ ነገለ

በቦክስም አይለኝም፥ መልሶ መልሶ!

እስኪሸረፍ ድረስ፥ ጥርሴ በደም ርሶ!

ዠለጥ አደረግሁት፥ በያዝሁት ከዘራ

ግና አልጠቀመውም፥ ዘበኛ ተጣራ፤

ፖሊስ ቢሮ ሄድን

እሱ ተለቀቀ

አሸብር ከልካይ ግን፥ እወህኒ ማቀቀ፤

ማን ሊሰማኝ እዚያ፥ ዘሬን ብቆጥር

ብሸልል ባቅራራ፥ ወይስ ብፈክር

ደረቴ ላይ ያለው፥ ያገሬ ባንዲራ

ያምራል ተባለ እንጂ፥ ከብሮም አልተፈራ!

የሞጃው ተወላጅ፥ የጠራሁት መንዜ

ሸጐሌ ሻንቅላ፥ ተብዬ መያዜ

በግፍ እንደሆነ፥ ባሰት በውሸት

አቃተኝ ማነንም፥ ከቶ ማስረዳት፤

ሲቸግረኝ ጊዜ፥ አንዱን ተጠግቼ

‘ሻንቆን’ እንዲህ አልሁት፥ ነገሬን አስልቼ፤

“ሰማኸኝ ወንድሜ፥ አላሳዝንህም

በሰው ጠብ ገብቼ፥ በከንቱ ስደክም?

“አውቃለሁ ከጥንትም፥ ነጭና ሻንቅላ

በቂም እንደኖረ፥ ሲዋጋ ሲጣላ

እኔ ግን ሐበሻው፥ ምን ወገን ልለይ

በማይነካኝ ነገር፥ ለምን ልሰቃይ?

እንካ … ጠጉሬን እየው፥ … ሸጐሌ አይደለሁም

ፊቴን ተመልከተው … እንዳንት አልጠቆርኩም

ቀይ ዳማ ነኝ … እየኝ፥ ይሁን ጠይም ልባል …

እኔን መቁጠሪያ ራስ፥ የሚለኝ ሰው አብዷል!

“ዘራችንም ቢሆን፥ ከነገደ ሴም

ሲወርድ የመጣ ነው፥ ከዳዊት ካዳም

የንግሥተ ሳባን ታሪክ፥ ሰምተህ የለ?

ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ ተባለ …

ዛጔማ ከገረድ፥ ነው የተወለደ …

አያወጣው ወጥቶ፥ ከዙፋን ወረደ፤

የካም ልጆች ናችሁ፥ እናንተ ጥቁሮች

ፈንጆችም ናቸው፥ የያፌት ልጆች …”

ብዬ እንደጀመርኩኝ፥ ታሪክን ላስጠናው

ባጭሩ አቋረጠኝ፥ ትግሥት አጣ ሰሚው፤

“እንዲህ ያል ንግግር፥ ያሰኛል አላቲ!

ባሻ አሸብር ከልካይ፥ ልጠይቅህ እስቲ

ገና አንተ ነህና፥ ኢትዮጵያዊ

አይደለሁም ልትል፥ ጥቁር አፍሪካዊ?!

“ምን ይሆናል እንጂ፥ አንተን ላይዘልቅህ

ነበረኝ ባያሌው፥ ብዙ እምነግርህ …

“ቁጥርህ ከማን እንደሁ፥ ከነጭ ወይ ጥቁር

ማወቅ ቢፈልግህ፥ ወዳጄ አሸብር

እነጮች ቡና ቤት፥ ገብተህ ቡና ጠጣ

ወይ በባቡር ስትሄድ፥ አብረህ ተቀመጣ!

ይህም ባይቻልህ፥ ሞክር ባልደረባ

ነጮች እገቡበት፥ ሆቴል ልትገባ፤

“ባንተ አልተጀመረም፥ ያዳሜ ምኞት

ከተጠቃው ‘መራቅ’፥ አጥቂን ‘መጠጋት’

ኀይለኛውን ‘መውደድ’፥ ደካሙን ‘መጥላት’ …

ሰው ባያቱ ይምላል፥ አባቱ ሳይከብር

ማነው የድሀ ልጅ፥ ዘሩን የማይቆጥር?”

እስከ ዛሬ ድረስ፥ ይህ አነጋገር

ሲታወሰኝ አለ፥ ባሰብሁት ቁጥር፤

ይመስገነው ገባኝ፥ ከጊዜ በኋላ

‘አማራ’ ‘ጊሚራ’፥ ቢባልም ‘ሻንቅላ’

‘ሱማሌ’ ‘ኪኩዩ’፥ ‘ሡዋሂሊ’ ‘ባንቱ’

‘ኩኑኑሉሉ’ ‘ማሣይ’፥ ‘ኔግሮ’ ‘ባማንጓቱ’

ማለት እንደሆነ፥ ስልቻ ቀልቀሎ፤

ቀልቀሎ ስልቻ፥ ስልቻ ቀልቀሎ

ስልቻ ስልቻ፥ ቀልቀሎ ቀልቀሎ።

.

መንግሥቱ ለማ

(1950ዎቹ)

.

[ምንጭ] – “ባሻ አሸብር ባሜሪካ”። ፲፱፻፷፯። ገጽ ፲-፲፫።

 

ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ጋር

“ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን ጋር”

ከግርማ መኮንን

.

በአካልም በስሜትም ከሀገሬ በጣም መራራቅ ጀመርኩ መሰለኝ ትዝታዎቼ ከአምስቱም የስሜት ሕዋሳቶቼ መፍለቅ ጀምረዋል።

ሰው ሁሉ አፍንጫውን ዘግቶ መንገድ ለመሻገር እንደመንጋ ሲንጋጋ እኔ እርምጃዬን ገታ አደርግና ፖሊሱ ወደተቀመጠበት ፈረስ አቅራቢያ ስደርስ ደረቴ እስኪወጠር ድረስ አየሩን እስባለሁ። የፋንድያው ሽታ እኔን የሚያስታውሰኝ ሰፈሬን ሽሮሜዳን ነዋ! እሱም ቢሆን እኮ ይናፍቃል። አዘውትሬ የምሄድበት ቡና ቤትም በአንድ ጥግ በኩል ኮርኒሱ ተቦርድሷል … ያደግኩበት ቤትም እንደዚሁ።

ጆሮዬም ቢሆን የሚናፍቀው የራሱ የሆነ ትዝታ አለው።

አሁን አሁን የእግር ኳስ ጨዋታን እምብዛም ባልከታተልም አንዳንዴ የስፖርት ዘጋቢዎቹ “ጎል!” ብለው ሲጮሁ ለመስማት እጓጓለሁ። እሷን በሰማኹ ቁጥር ትዝ የሚለኝ አባቴ ነው። እኔና ወንድሜ ሕፃን እያለን በሳምንት እንዴ የሚተላለፈው የእንግሊዞች ኳስ ጨዋታ እንዳያመልጠን ተንደርድረን ከሶፋው ላይ ጉብ እንላለን። የኛም ልብ እንደተሰቀለ አይቀርምና አንድ ጎል ይገባል። ደስታችን ገና በጩኸት ሳይመነዘር በፊት አባታችን ጎል ብሎ ይጀምራል …

“… እንዲያ ነው ጎል! …

ከዚያማ ጎል አባ ቁርጡ

ያንን ሁዳድ ሙሉ ጀግና፥ ከገላገለው ከምጡ …

ምኑ ቅጡ! ምኑ ቅጡ!”

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፻፲፩)

አባታችን ዘወትር ቅድሜና እሑድ ጠዋት፣ መኝታ ቤታችን ድረስ እየመጣ ከሚያነብልን ግጥሞች መሐል ተቀንጥባ እንደወጣች እናውቃለን። ሁሌም ጎል በገባ ቁጥር ስለሚላት ጭፈራ ወይ ሐዘን ከመጀመራችን በፊት የሱን አፍ እንጠብቅ ነበር።

Esat wey Abebaተለቅ ስንል ግን እሱን መጠበቅ አቆምን። ታዲያ የሁለት ሳምንቱን ሸመታ ለማካሄድ በሶማሌ ተራ አድርገን፣ የተክለ ሃይማኖትን መንገድ አሳብረን፣ በጠመዝማዛ መንገድ ተጠማዘን፣ ቅቤና ቡላ ከሚቸረቸርበት መደዳ ደርሰን፣ እናቴ ለብቻዋ ከመኪና ስትወርድ እኔ የአባቴን አፍ መከታተል እጀምራለሁ። እንደለመደው ግራና ቀኙን ካየ በኋላ አንድ ቁም ነገር እንዳስታወሰ ሁሉ ወሬ ሊጀምር ሲል እቀድምና፣

“መርካቶ ያገር ድግሱ

የገጠር ስንቅ አግበስብሱ

ለከተሜው ለአባ ከርሱ …” እላለሁ።

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፴፩)

አባቴም ኮራ እያለ፣

“እሱን ግጥም ምን እንደጻፈው ታውቃለህ?” ብሎ ይጠይቃል ።

“አፍንጮን የጻፈው ሰውዬ ነዋ” ብዬ መሳቅ እጀምራለሁ።

አባቴም “አንበሳ ሲያረጅ…” እንደሚባለው ቀልዱ በሱ ላይ መሆኑ ይገባዋል። የሱም ጥየቃ የዘልማድ ሆኖ እንጂ ጋሽ ጸጋዬን እንደማውቃቸው ያውቃል – ዳዊት ሳልደግም አይደል “እሳት ወይ አበባን” ያስደገመኝ!

IMG_4952እኔም አውቃቸዋለሁ ስል እንደ አሕዛብ ሁሉ አንዳንድ ሥራዎቻቸውን አንብቤ ወይም ሰምቼ እንጂ በቁም አይቻቸውም አላውቅም ነበር። ታዲያ አሜሪካ ከመጣሁ ከደርዘን ዓመታት በኋላ እምግብ ቤት በራፍ ላይ በቁም አገናኘን።

እሳቸው ከምግብ ቤቱ ሲወጡ፣ እኔ ደሞ ሊጐበኘኝ ከመጣው ታናሽ ወንድሜና ከጓደኞቼ ጋራ ርሃባችንን ለማስታገስ ስንቻኮል። በራፍ ላይ ስለነበርን ሁላችንን ሰላም ብለው ሊያልፉ ሲሉ ከኛው መሐል አንዱ ወደኔና ወንድሜ እየጠቆመ፣

“እነዚህ ደሞ ወንድማማቾች ናቸው። አይመሳሰሉም?” ብሎ ሲያዳንቅ፣

“ለመመሳሰልማ አይጦች ሁሉ ይመሳሰሉ የለ እንዴ?” ብለውን አለፉ።

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ነክ የሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ስሄድ በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ አያቸው ነበር። ሦስት ዓመታት ያኽል እንዲህ አለፉና እንደገና እሳቸውን የማገኝበት ሁኔታ ተፈጠረ። “አንድምታ” የመጽሐፍ ክበብን ወክዬ ጋሽ ጸጋዬን እንዳነጋግር ተጠየኩኝ። እኔም በተራዬ በልጃቸው በኩል ቀጠሮ ያዝኩኝ።

IMG_4942ጋሽ ጸጋዬ ጋር ከቡና ቤት እንድንገናኝ ነበርና ቀጠሮ የተያዘው እኔም እንዳይረፍድብኝ በማሰብ ከቤቴ ቀደም ብዬ ወጣሁ። ግና ሌሊቱን ሰማዩ የበረዶ ገለባ ሲበትን አድሮ ኖሮ፣ ጠዋት ከቤት ስወጣ መንገዱና መኪናው ሁሉ ይህንኑ ሦስት አራት ድርብ ጥጥ ለብሷል። ቀጠሮዬ መሰናከሉ ገብቶኝ አጠገቤ ያየሁትን ነገር ሁሉ መስደብ ስጀምር ከቀበቶዬ ያነገብኩት ስልክ ጥሪ እንዳለ አስታወቀኝ።

“ሃሎ፣ የምጽአት ቀን ዛሬ ናት መሰለኝ….” አልኩ ልጃቸውን።

“የቀጠሮውን ሰዓት ብትረሳው ይሻላል። ግን ቤት ድረስ መምጣት ትችላለህ?” አለችኝ።

የተቃጠርነው ከጠዋቱ 4 ሰዓት መሆኑን ሳልዘነጋ እኔም በ6 ሰዓት ከቤታቸው። የጋሽ ጸጋዬን ባለቤት ወይዘሮ ላቀችን ከሳሎን እንደተቀመጡ ሰላም ብዬ የምትመራኝን ልጃቸውን ተከትዬ በስተቀኝ በኩል ወዳለው መኝታ ቤት ዘው ብዬ ገባሁ።

በቀኝ በኩል ጠረጴዛ፣ በላዩ ላይ ደግሞ ኮምፒውተር – በግራ በኩል አመቺ ወንበር፣ በላዩ ላይ ደግሞ ጋሽ ጸጋዬ፣ ከእጃቸው ላይ ደግሞ ስልክ ተቀምጠዋል። አንድ ወንበር ጐተት አደረኩና ከፊታቸው ቁጭ ብዬ የስልክ ጥሪውን እስኪጨርሱ መጠበቅ ጀምርኩ።

TSEGAYE GEBRE-MEDHINየምሽት ልብሳቸውን እንደለበሱ ነው ቁጭ ያሉት። ቤቱ ውስጥ ባይበርድም ጋቢ ደርበዋል። ከጭንቅላታቸው የደፏት የሹራብ ኮፍያ ለአመል እንጂ በአግባቡ የተደረገች አትመስልም። ይህን የመሳሰሉትን የአለባበስ ዘዬዎች ሳስተውል ስልክ ጥሪያቸውን ጨርሰው ኖሮ አተኩረው ተመልክተውኝ፤

“ከዚህ በፊት ተገናኝተን አናውቅም?” አሉኝ

“እናውቃለን እንጂ ቂም ብይዝ እኮ ነው ቤቶ ድረስ የመጣሁ።”

“እንዴት?”

“ከሦስት ዓመታት በፊት ወንድሜንና እኔን ከአይጦች ጋራ አመሳስለው ነበር። ረሱት እንዴ?”

ፈገግ አሉና፣

“እሱማ የኛኑ ቤተሰብ ትመስላለህ ለማለት ነበር … አንዳንዴ ሰው አይቼ እኔን ይመስሉኝና እደነግጣለሁ። እንዲሁ አንድ ጊዜ የሆነ ልጅ ስድስት ኪሎ አካባቢ አይቼ የኛን ቤተሰብ መምሰሉ በጣም ገረመኝና ተጠግቼ ጠየቅኩት” ብለው ዝም አሉ።

ብጠብቅ አሁንም ዝም።

“ምን ብለው ጠየቁት” አልኩኝ መጠበቅ አላስችል ቢለኝ።

“እናትህ ጐረቤት ነበረች ወይ ነዋ!” ብለው በራሳቸው ቀልድ ራሳቸውንም እኔንም አስቀው ወሬያችንን ቀጠልን።

በደንቡ መሠረት ወደ ቁም ነገር ሰተት ተብሎ አይገባምና እኔና እሳቸውም የባጥ የቆጡን ማውራት ቀጠልን – ወቅቱ ስላመጣው ዝናብና በረዶ፤ ስለ ሰፈሬ እንጦጦ ብርድ፣ ከኒው ዮርክ በፊት ስለኖርኩበት ከተማ፣ በአሁኑ ጊዜ ምን እንደምሰራ ወዘተ… ይኽንንም ያንንም እየዳሰስን ቀስ በቀስ ወደመጣሁበት ጉዳይ ማዘንበላችን አልቀረም።

እኔም ያለመዳዳት “አንድምታ ክበብ” ከሐሳበ ጽንሰት እስከ ጉርምስና እንዴት እንደደረሰ አስረዳሁ። በጥሞና ከሰሙኝ በኋላ፣

“በኛ ቋንቋ ከተጻፉ ሥራዎች በቅርቡ ያነበብከው ጥሩ ነው የምትለው አግኝተሃል?” በማለት ጥያቄ አቀረቡ።

ለአባቴ ድሮ እንደምመልስለት አፍንጮ ልላቸው አሰብኩና ቀልዱን ለማስረዳት ብዙ ጊዜ እንደሚወስድብኝ ገምቼ ተውኩት። ሆኖም የሳቸው ጥያቄ ለ15 ደቂቅ ያኽል ራሱን የቻለ ውይይት ውስጥ ከተተን። ለጥያቄያቸው ቀጥተኛ መልስ ባልሰጣቸውም የፈላስፋው ዘርአ ያዕቆብን ሥራ ለራሴ አንብቤ መገምገም በመቻሌ ጽሑፉን ተርጉመውና አቀነባብረው ላቀረቡልን ምስጋናዬን እንደማቀርብ ተናገርኩ።

እሳቸውም አጠፋውን ሲመልሱ፣

“አየህ ሼክስፒር ለእንግሊዝ ትልቅ ቅርስ ነው። እንደ ትልቅነቱም ቅርሱ እንዳይበላሽ በመንግሥት ደረጃ ይጠበቃል። የሼክስፒር ሥራዎች ሌላ ሀገር በመድረክ ላይ ሲቀርቡ በትክክል ካልተሰሩ፣ ባህሉን አቃውሰው ካሳዩ፣ ዝግጅታቸው ጥሩ ካልሆነ፣ ጉዳዩ በአምባሳደሩ ደረጃ ተመክሮበት ነገሩ እንዲስተካከል ተብሎ ‘እርዳታ እናድርግላችሁ’ ብለው እንግሊዞች ይጠይቃሉ። ይኽም የሚሆንበት ምክንያት የሼክስፒር ሥራዎች የእንግሊዝን ታሪክና ባህል ስለሚወክሉ እንደ ቅርስ ተቆጥረው ነው። ምነው የኛ ሀገር ቅርሶች ታዲያ እንዲያ አይያዙም? እነ ያሬድን እነ ዘርአ ያዕቆብን ማን እንደዚህ የሚንከባከባቸው አለ?”

ሊሰነዝሩት ያሰቡት ነጥብ አላመለጠኝም። እሳቸው ግን ቀጠሉ፣

IMG_4943

“ትልቅ ዋጋ እንሰጣቸው የነበሩ ነገሮች በጣም ረክሰው ስናያቸው መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅም ይታክታል። በአፄ ምኒልክ ጊዜ እንግሊዞች ቱርካና ሐይቅ አካባቢ ዝሆን ያድኑ ነበርና አንዴ አደናቸውን ተከትለው ሲገሰግሱ ከኢትዮጵያ ኬላ ደርሰው ኖሮ ድንበር አላሳልፍ ካሉ የኬላ ጠባቂዎች ጋራ ተኩስ ይከፈትና ከአዳኞች አንዱ በዚሁ ምክንያት ይሞታል። እንግሊዞችም አቤቱታ ያሰሙና ነገሩ የጦር የሚስቴር ከነበሩት ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዘንድ ይደረሳል። እንግሊዞቹ ያላግባብ ሰው እንደተገደለባቸው አመልክተው የደም ካሳ እንዲሆናቸው ከኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው ነበር የጠየቁት።

“ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ነገሩን ያጠኑና ችግር እንደሌለው ለእንግሊዞች ይገልጻሉ። ‘ነገሩ ከመፈጸሙ በፊት ግን ይኽ ሕግ እናንተ ሀገርም እንደሚሰራበት ማየት ስለምንሻ በሰነድ መልክ ረቂቁ ካለ እስቲ እንየው። እውነት የእንግሊዝ ሰው የዌልስን ሰው ቢገድል እንግሊዝ ከመሬቷ ለዌልስ የምትሰጥ ከሆነ እኛም እንሰጣለን። እሱም የሚሆነው ለተገደለብን የኬላ ጠባቂ ካሳ የሚሆን ከቱርካና ሐይቅ አካባቢ መሬት ከተረከብን ይሆናል።’ ብለው መለሷቸው” አሉ።

እንዲህ እንዲያ እያልን የተጀመረው ወሬ በኢትዮጵያ ቅርስ ደጃፍ አቋርጦ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ጓሮ ዞሮ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያንን ነካ ነካ አድርጎ ከራሴው ቤት ፊት ለፊት ጣለኝ። ወሬያችን ከአንድ ርእስ ወደ ሌላ ሲሸጋገር በተያያዙ ነጥቦች ስለቤተሰቤ ድንገት ሲጠይቁኝ ምን አስመርኩዘው እንደሆነ አልታወቀኝም። አባቴ የሳቸውን ግጥም ያነብልን እንደነበር ተገልጾላቸው ይሆን?

ያም ሆነ ይኽ ስለቤተሰቤ ተናግሬ ስጨርስ እስቲ የኔን ጽዋ ይቅመሱት ብዬ በምትኩ አዲስ የተጻፈች እንዲት አጭር ታሪክ አነበብኩላቸው – ታሪኩ መኸል እሳቸው የጻፏት “ሕይወት ቢራቢሮ” የተሰኘችው ግጥም ቅንጣቢ ነበረች። የራሳቸው ግጥም አንድ ነገር አስታውሷቸው ልክ ታሪኩን አንብቤ ስጨርስ፣

“እሷ ግጥም በጋዜጣ ታትማ በወጣች ማግስት መንግስቱ ለማ ከቢሮዬ መጥቶ ‘ቢራውን እስቲ አምጣው ወይስ ዝም ብለህ ነው ቢራ ቢሮ ያልከው’ ብሎ እንደቀለደብኝ ትዝ ይለኛል” አሉኝ።

ትንሽ ተከዝ አሉና፣

“ምን የመሰለ ደማም ቋንቋ የነበረው ሰው ነበር። አሁን እኮ ደማም ቋንቋ የሚናገር ሰው ሁሉ ጠፋ።” ብለው እንደገና ትክዝ አሉ።

እኔም አዝማሚያው አላማረኝም። ምክንያቱም የመንግስቱ ለማን ሥራዎችም ቢሆን አባቴ ቅዳሜና እሑድ እንደ ዳዊት ይደግምልን ስለነበር በጣም እያደነቅኩት ነው ያደግኩት። ስለዚህ ስለሱ ማውራት ብንጀምር አዳሬም ከሳቸው ቤት እንደሚሆን በመረዳት እዚህ ላይ ልሰናበታቸው ወሰንኩ።

የአንድምታን መሥራች አባላት ይዤ መጥቼ እንደገና በሰፊው እንደምንወያይ ነግሬያቸው ልወጣ ስል ያዝ አረጉኝና ግንባሬ ላይ ሳሙኝ። ብዙ ባላስቀይማቸው ነው ብዬ ገምቼ ነበር።

IMG_4953

ግን ለካ ወደ ፊት ወጣ ያለው ግንባሬ ቀድሞ ከንፈራቸውን አግኝቶት ኖሯል።

… እኛኑ ትመስላለህ ብለውኝ የለ!

.

ግርማ መኰንን

1998 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “አንድምታ” ቅፅ ፫ – መጋቢት-ግንቦት ፲፱፻፺፰። ገጽ 1፣ 4፣ 10።

 

መሰንቆ እና ብትር (ወግ)

“መሰንቆ እና ብትር”

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ …”

አዝማሪ ጣፋጭ [1845 ዓ.ም]

.

የዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ጎሹ እና የቋራው ፋኖ ደጃዝማች ካሳ በኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም ጉራምባ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ካሳ፣ ከጥቂት ታማኝ ጭፍሮቻቸው ፊት ተሰልፈዋል። ጎሹም፣ በተለመደው የጀብድ መንገድ ከሰራዊታቸው ፊት ለፊት ቀድመው፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ ውለዋል። ውጊያው እንደተፋፋመ፣ ደጃች ጎሹ በጥይት ተመትተው ወደቁ። የመሪውን መውደቅ እንደተረዳ የዳሞት ጦር ፀንቶ መመከት ተሳነው። ወዲያው የንቧይ ፒራሚድ ሆነ። ያለቀው አልቆ ቀሪው ተማረከ።

ከምርኮኞች አንዱ፣ አዝማሪው ጣፋጭ ነበር።

ጣፋጭ፣ የደጃች ጎሹ አዝማሪ ስለነበር በብዙ ጦር ሜዳ ላይ ውሏል። በጌታው ጠላት እጅ ሲወድቅም የመጀመሪያው አይደለም። በራስ ይማም ዘመንም እንዲሁ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ የተባለ መስፍን ደጃዝማች ጎሹን ድል በነሳ ጊዜ፣ ከጌታው ጋር ተማርኮ ነበር።

ይሁን እንጂ ያኔ ዝንቡን እሽ ያለው አልነበረም። ጣፋጭ፣ የደጃች ማጠንቱ ምርኮኛ ቢሆንም፣ የእግር ብረት አልገባበትም። እንዲያውም፣ በድል አድራጊው አዳራሽ ውስጥ ያሻውን ከማንጎራጎር አልተከለከለም ነበር። በወቅቱም፣ አዝማሪው ጣፋጭ ይህንን ገላጋይ ዝማሬ አቅርቦ ነበር፤

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

ጣፋጭ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ በጦር ሜዳ ላይ ስምንት ወታደር መግደሉን አስታውሶ፣ አሁን ተማራኪውን ቢገድል የሚጨመርለት ክብር እንደሌለ አስታወሰው። በሁለት መስመር ግጥም ለድል አድራጊው የሚገባውን መወድስ ሳይነፍግ፣ የጌታውን ሕይወት ለመታደግ ጥሯል። ድል አድራጊው ደጃች ማጠንቱም ጎሹን ሳይገድለው ቀረ።

በዚህ በኅዳር ዕለት ጦርነት ግን፣ አዝማሪው ጣፋጭ በቋረኛው ካሳ ጦር ተማርኳል። ተስፋና ፍርሀት ከፊቱ ተደቅነዋል። ባንድ በኩል፣ አዝማሪን መግደል ነውር የሚያደርገው ባህል ጋሻ ሁኖት ከክፉ እንደሚታደገው ተስፋ ያደርጋል። በሌላ በኩል፣ ደጃዝማች ካሳ ይህን ደምብ ለማክበራቸው ርግጠኛ አይደለም።

እነሆ፣ አዝማሪው በካሳና በጭፍሮቻቸው ፊት ቆሟል። ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ የሚተርኩልን ለዘመኑ ቅርብ የነበሩት አለቃ ወልደማርያም ናቸው፤

“አዝማሪ ጣፋጭ … ተይዞ በቀረበ ጊዜ ባደባባይ አቁመው ደጃች ካሳ ‘እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ’ ቢሉት እጅግ ተጨነቀ፤ እንዴህም አለ፤

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

እንዲህም ቢል ሞት አልቀረለትም፤ በሽመል ገደሉት።”

አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ከሁለት ትውልድ በኋላ በጣፉት የጎጃም ታሪክ ውስጥ ደግሞ የሚከተለውን ተጨማሪ መስመር እናገኛለን፤

“አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

ከመቶ አመት በኋላ ታዋቂው ዘመናይ የታሪክ ጸሐፊ ተክለጻድቅ መኩሪያ በጻፉት ጥናትም “ብትር” የሚለውን “ሽመል” በሚል ቃል ከመተካት በስተቀር ያለቃ ተክለየሱስን ቅጂ ማስተጋባት መርጠዋል፣

“እወይ ያምላክ ቁጣ

ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

.

ጣፋጭ፣ የደጃች ካሳን ምሕረት አጥብቆ የሚፈልግ ምርኮኛ ሆኖ ሳለ፣ እንዴት ተሽቀዳድሞ በራሱ ይፈርዳል? እንዴት “ሽመል/ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ” ብሎስ ራሱን ለቅጥቀጣ ያቀርባል?

የጣፋጭን ፍርድ በመመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት አለቃ ወልደማርያም ታሪክ ውስጥ መደምደሚያው ስንኝ አለመጠቀሱ አንድ ነገር የሚጠቁም ይመስለኛል። ስንኙ ምናልባት ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ይሆናል።

የኔ ግምት እንዲህ ነው … አዝማሪ ጣፋጭ በደጃዝማች ካሳና አጃቢዎቻቸው ፊት ይቀርባል፤

ደጃች ካሳ፤   እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ?

ጣፋጭ፣ በጦርነቱ ዋዜማ በደጃች ካሳ ላይ ያወረደውን ዘለፋ እዚህ ቢደግም፣ የድል አድራጊውን ቁጣ ከማቀጣጠል ውጭ የሚፈይድለት ነገር የለም። ስለዚህ የመጨረሻ መሳሪያውን ለመጠቀም ወሰነ። ቧልት! …. ካሳና ጣፋጭ በጎሹ ቤት በሎሌነት ሲኖሩ፣ ካሳ ቀልድና ፈሊጥ እንደሚወድ ያውቃል። ጣፋጭ መሰንቆውን ቃኝቶ ይህን በግለ ሂስ የተሞላ የቧልት ዘፈን ዘፈነ፤

ጣፋጭ፤   ህምም …

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ሥራ ሲያጣ።

ካሳ አልሳቀም። አዝማሪው የከፈተውን ተውኔት እንዴት መቀጠል እንዳለበት እያሰበ ይሆናል። ደጃዝማች ካሳ፣ ራሱን የመለኮት ተውኔት ፍሬ አድርጎ ስለሚቆጥር ፍርዱን ሳይቀር ተውኔታዊ ማድረግ ይወድ ነበር። የራስ አሊን እናት በማረከም ጊዜ “ገረድ ትሰለጥናለች እመቤት ትፈጫለች” የሚለውን የፍካሬ የሱስ ትንቢት ለማስፈጸም ወይዘሮ መነን ባቄላ እንድትፈጭ ፈርዶባት ነበር። “የኮሶ ሻጭ ልጅ” ብሎ የሰደበው ቀኛዝማች ወንድይራድን ደግሞ “እናቴ ከገበያ ሳይሸጥላት የቀረ ኮሶ ስላለ እሱን ተጋበዝ” ብሎ፣ ከመጠን ያለፈ ኮሶ አስግቶ ለመቅጣት የሆነ የተውኔት ስጦታ ያስፈልጋል። ያገራችን ጸሐፌ ተውኔቶች በፍቅሩ የነሆለሉት ብጤያቸው ስለሆነ መሆን አለበት።

ደጃች ካሳ፤   (ወደ አጃቢዎቹ ዞሮ)

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ።

.

ጣፋጭ በቧልት የጀመረውን … ካሳ በትራጀዲ ደመደመው።

.

* * *

ጣፋጭን ለድብደባ የዳረገው ዝማሬ ግጥም ይሄ ነበር …

አያችሁት ብያ፥ የኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞ፥ ጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂ፥ መች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት፥ በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ ፥ በነ ጉንጭት ለምዶ።”

* * *

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ” [መስመር ፩]

ብያ” ዛሬ ለመረሳት ከደረሱት ያማርኛ ጥንታዊ ቃላት አንዱ ሲሆን “እኮ፣ አይደል” ማለት ነበር። “አያችሁት ብያ” ሲልም “አይታችሁታል አይደል?” ማለት ነው። ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሱን ገድሎ በወደቀ ማግስት ከወረዱ የሙሾ ግጥሞች አንዱ፣ “አያችሁት ብያ ያንበሳውን ሞት” የሚል ስንኝ አለው። ይህም በጊዜው ቃሉ የተለመደ እንደነበር ያመለክታል።

“እብድ” ተብሎ ካሳ በይፋ ሲጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የምንሰማው ከአዝማሪ ጣፋጭ ሳይሆን አይቀርም። ጣፋጭ ይህን ሲል፤ የጊዜውን አስተያየት እያስተጋባ ነው? ወይስ በራሱ ምርመራ የደረሰበት ነበር? አላውቅም። አለቃ ተክለየሱስ ከግማሽ መቶ አመት በኋላ በጐንደር ሲወርድ የነበረውን ግፍ ዘግቦ፣ የሕዝቡን ምላሽ ምን እንደነበር ሲጽፍ፣ “ከዚህ በኋላ፣ የበጌምድር ሰው ‘ይህስ የደህንነትም አይደለ’ እያለ አመል አወጣ … ንጉሡንም ጠላው። ሌሊት በተራራ እየቆመ፣ እንደ ሳሚ ወልደ ጌራ ‘እብዱ ገብረኪዳን’ እያለ ተሳደበ” ይላል። (“ገብረኪዳን” የአፄ ቴዎድሮስ የክርስትና ስም እንደነበረ ባልታወቀ ደራሲ ተጽፎ Fusella ባሳተመው ዜና መዋዕል ተጠቅሷል።)

.

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ [መስመር ፪]

ጋሞች” የሚላቸው ባለ አፍላ እድሜ ላይ ያሉትን ጋሜዎች ነው። ባዝማሪው አይን ሲመዘኑ የደጃዝማች ካሳ አጃቢዎች እድሜያቸው ለጋ፣ ቁጥራቸውም ጥቂት ነው። በርግጥም የካሳ ጭፍሮች ማነስ ለባላጋራዎች ግራ የሚያጋባ ነበር። ባነጋገር ፈሊጣቸው የታወቁት ራስ አሊ የቋራው ካሳን ሰራዊት ከሩቅ አይተው ከገመቱት በታች ቢሆንባቸው፣ “ጦረኛ እንዳንለው አነሰ፤ ሰርገኛ እንዳንለው በዛ” ብለው ነበር።

ጉራምባ” (ጉር አምባ) በዛሬው የደንቢያ ወረዳ፣ ጎርጎራ በተባለው ንኡስ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው። ደጃዝማች ካሳ ይህን ስፍራ የመረጡት ለመከታ የሚያመች አምባ ሆኖ ስላገኙት ሳይሆን አይቀርም። አዝማሪው ጣፋጭ በግጥሙ ውስጥ “ጉር አምባ” የሚለውን ነባር ስም “ጉራምባ” ብሎ አሸጋሽጎታል። ይህን ያደረገው ስፍራውን “ጉራ መንፊያ” ብሎ ለመተርጎም እንዲያመቸው ይመስላል። ጣፋጭም የቋራው ካሳን ለይስሙላ እንጂ የምር መዋጋት የማይሆንለት ጦረኛ አድርጎ ይገምተው እንደነበር ቀጣዩ መስመር ያሳያል።

.

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋ ካሳ” [መስመር ፫]

ያንጓብባል” የሚለው ቃል “አጊጦ በመልበስ ቄንጥ ባለው አካሄድ ይሄዳል፣ ዳር ዳር ይላል” ማለት ነው። ቃሉን የሚከተለው ከአለቃ ዘነብ “መጽሐፈ ጨዋታ” የተቀነጨበ አንቀጽ የበለጠ ያብራራዋል፣

“ሰማይ ከዚያ ላይ ሆኖ አንጓቦብን የሚኖር ከቶ ምንድር ነው? ቀን ፀሐይን ሌሊት ጨረቃንና ከዋክብትን ተሸልሞ ዘወትር እኔን እኔን እዩኝ እዩኝ እያለ ያደክመናል … እንደዚህ የኮራ እንደ ሰም ለመቅለጥ ነው እንጂ ፊቱን እንዴት ያየው ይሆን? ኩራቱም ምድር አስለቅቆታል። ምን ይሆናል እንደሚያልፍ አያውቅምን?”   [ክፍል 15፤ አንቀጽ 16]

ይህ ዳር ዳር ማለት የቋራው ካሳ ጠላቶቹን የሚያዘናጋበት ልዩ የጦር ስልት ነበር። በጠላቶቹ አይን ግን እንደ ፍርሀት ይቆጠር ነበር። ለአብነት ያክል፣ አለቃ ወልደማርያም በደጃች ካሳና በራስ አሊ መሐል የተደረገውን ውጊያ አስመልክተው ሲጽፉ፤ “ራስ አሊ አይሻል በሚባል ሜዳ ጦርዎን ሰርተው ተቀምጠው ሳሉ ደጃች ካሳም ዳር ዳሩን ይዞሩ ጀመሩ። ሰውም የፍርሀት መስሎት ‘ተመልሶ ሊሄድ ነው’ ይል ጀመረ።”

መች ይዋጋል …” የቋራው ካሳ ደፋርና ጽኑ ተዋጊ ቢሆንም ጉልበቱን መዝኖ መሸሽም ያውቅ ነበር። ደጃዝማች ጎሹ በ1840 ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሚካኤል አባዲ በጻፉት ደብዳቤ “ተካሳ ጋራ የተዋጋነ እንደሆነ ጎንደር እገባለሁ እንገናኛለን፤ ወደ ቆላ የሸሸ እንደሆነ …” ያሉት ይህን ስለሚያውቁ ይመስላል። እንደገመቱት፣ ካሳ ወደ ትውልድ ቦታው አፈግፍጎ ከርሟል። አዝማሪው ጣፋጭ “… መች ይዋጋል ካሳ” ያለው ይህን ሁኔታ በማጤን መሆን አለበት። ይሁን እንጂ፣ ካሳ ለጣፋጭ ያልተገለጠለት ጠንካራ ጎን ነበረው። ጠላቶቹ ሽሽቷል ብለው ሲዘናጉ እንደገና አፈር ልሶ ተነስቶ ማጥቃትና ማሸነፍ ይችል ነበር።

.

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ [መስመር ፬]

ወርደህ” የሚለውን ቃል አዝማሪው በዚህ ዝማሬ ውስጥ ሁለቴ ተጠቅሞበታል። መስመር 2 ላይ “ጉራምባ ሲወርድ” ብሎ ካሳን የገለጠውን ያክል “ወርድህ ጥመድበት” ብሎ ጎሹን ይጎተጉተዋል። የመፋለሚያውን ቦታ ቆላነት ያሳስባል፤ ወደ ቆላ ወረደ ይባላልና። “ጥመድ” በአማርኛ ብዙ ትርጉም አለው፤ ከግጥሙ ዐውድ ጋር የሚሄደው “አሽክላን ዘረጋ፣ ወይም የጠፋ ሰውን አጥምዶ ሸምቆ ለመያዝ በጎደጎደ አደባ” የሚለውን ነው። ስለማይዋጋ ካሳን አድብቶ መያዝ እንደሚያዋጣ ጣፋጭ ሀሳብ እያቀረበ ነው።

በሽንብራው ማሳ” ሲል አዝማሪ ጣፋጭ ስለየትኛው ነው የሚያወራው? “ካሳ” ከሚለው ቃል ጋር እንዲገጥመለት ይሆን? የለም፤ እኔ እንደሚመስለኝ ቃሉ ታስቦበት የተመረጠ ነው። ደጃች ጎሹ የቋራውን ደጃች ካሳ አባርረው ደንቢያን በጃቸው ባስገቡበት ዘመን ከምግብ ሁሉ የሚወደውን የሽንብራ አዝመራ አውድመውበታል ይባላል። ጣፋጭ “ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ” ያለው ያንን አስታውሶ ይመስለኛል። አለቃ ዘነብ፣ “ያን ጊዜም ቋራ ሁሉ ጠፍ ሆኖ ነበር። ልጅ ካሳም ለባላገሩ ሁሉ ብዙ ብር ሰጡት። መቆፈርያ ግዛ ብለው … ከወታደሩ ጋር ብዙም ቆፍረው ዘሩ” ያሉት የሚታወስ ነው።

.

ወዶ ወዶ!” [መስመር ፭]

ወዶ ወዶ …” ጣፋጭ ይህን የተጠቀመው ለማሽሟጠጥ ነው፤ “ወድያ ወድያ” እንደማለት ነው። በዛሬ አማርኛ ብንመልሰው “ድንቄም ድንቄም” እንል ነበር።

.

በሴቶቹ በነ ጉንጭት ምዶ” [መስመር ፮]

ጉን” ለጉንጫም ሴት የሚሰጥ ቅጥል ነው። ጣፋጭ “በነ ጉንጭት” ሲል ደጃዝማች ካሳን በዘመኑ ያጅቡ ከነበሩት ቅሬዎች (ጋለሞቶች) አንዷን ጉንጫም አስታውሶ ይሆን?  “በነ ጉንጭት ምዶ …” ካሳ ከሴቶቹ ከነጉንጭት የለመደው ምንድነው? በጣፋጭ እይታ መሽቀርቀር፣ የእዩኝ እዩኝ ማለትን ተግባሮች ሁሉ ድምር የሆነው “ማንጓበብ” መሆኑ ነው።

ጣፋጭም ሆነ ካሳ፣ ወንድን እንደ መለኮት ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ ሴትን እንደ ጉድፍ የሚያጣጥል ማኅበረሰብና ዘመን ፍሬዎች ናቸው። በዚህ አይነቱ ዘመን አንድ ጦረኛ ጀብዱው ከከተሜ ቅሬዎች ተግባር ጋር መነጻጸሩን ሲሰማ ደም ብቻ እንደሚያጸዳው ውርደት አድርጎ ቢቆጥረው አይገርምም።

የጣፋጭን ፍጻሜ የወሰነችውም ይቺ የመጨረሻዋ መስመር ሳትሆን አትቀርም።

.

አዝማሪ ጣፋጭ (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም)

እና ድርሰቶቹ

*

“እወይ ያምላክ ቁጣ፣ እወይ የግዜር ቁጣ፤

አፍ ወዳጁን ያማል፣ ሥራ ሲያጣ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* *

“ክፉ የክፉለት፣ ይሆን የነበረ፤

ብሩን ‘ይሙት’ ብሎ፣ አለ የመከረ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * *

አያችሁት ብያየኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂመች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ  በነ ጉንጭት ለምዶ፤

(ሐሩ ቋዱ፣ ለውዙ ገውዙ አለ ቋራ፤

መንገዱ ቢጠፋ፣ እኔ ልምራ።)”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * * *

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ፤ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

[1820 ዓ.ም – ቋሚ ጨርቅ]

.

በዕውቀቱ ሥዩም

ሰኔ 2009 ዓ.ም

.

ምንጮች

ስለ አዝማሪ ጣፋጭ ሕይወት (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም) ያሉን ቀጥተኛ ምንጮች ሁለት ብቻ ናቸው። ቀዳሚው፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመን (1875 ዓ.ም) የቴዎድሮስ ታሪክን የጻፈው አለቃ ወልደማርያም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን (1917 ዓ.ም) የጐጃምን ታሪክ የጻፈው አለቃ ተክለየሱስ ነው። ሁለቱም ስለ ጣፋጭ የጻፉት በጣም በጥቂቱ፣ ለዚያውም ባለፍ ገደም ነው። ጣፋጭም ለትውስታ የበቃው፣ አሳዛኝ እጣው ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ስለተቆራኘ መሆን አለበት።

ተሰማ ሀብተ ሚካኤል። (፲፱፻፶፩)። “ከሳቴ ብርሃን የዐማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 266፣ 821።

ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ)። [፲፱፻፲፯]። “የኢትዮጵያ ታሪክ” አርታዒ፤ ስርግው ገላው (2002 ዓ.ም)፤ ገጽ 94-102

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፴፮]። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ“፤ (9ኛ እትም፤ ገጽ ፮-፯)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፹፩]። “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት“፤ ገጽ 125-127።

ወልደማርያም (አለቃ)። [፲፰፻፸፭]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Mondon-Vidailhet, Cassimir (1904)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፪]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Littmann, Enno (1902).

(ያልታወቀ ደራሲ)። [፲፰፻፸ዎቹ]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Fusella, Luigi (1959).

ደስታ ተክለወልድ። (፲፱፻፷፪)። “ዐዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 169፣ 217።

Blanc, Henry (1868) “A Narrative of Captivity in Abyssinia“, p. 178.

Lejean, Guillaume (1865) “Théodore II: Le Nouvel Empire d’Abyssinie“.

የግዕዝ ሊቃውንት እና አዲሱ ዘመን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 5)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል አራት የቀጠለ)

 

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትውልዳቸው ሸዋ ትምህርታቸው ጎንደር ነው። ዕድሜያቸው 60 ዓመት ይሆናል። በኢትዮጵያ መጻሕፍት ካላቸው ከሰፊው ዕውቀታቸው በላይ፣ ላገራችን መጻሕፍት ምሥጢርና ታሪክ አስፈላጊ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ዕብራይስጥ ጨምረውበታል። የሕዝቅኤልን ትንቢት ዕብራይስጡን ወደ አማርኛ ገልብጠው ባማርኛ የጨመሩበት መግለጫ፣ ከሁሉ በፊት ላገራችን ሊቃውንት ከግሪክ ተተርጕሞ በግዕዝ ተቀብለውት የሚኖሩትን የብሉያትን መጻሕፍት፣ ዋናውን አብነት ዕብራይስጡን እያዩ ማቃናት እንዳለባቸው አነቃቅተዋቸዋል። ዳግመኛ ትምህርቱም መጠነኛ ቢሆን አማርኛ ያወቀ ሁሉ ሊያስተውለውና ሊያጣጥመው በሚችል ንግግር በመግለጣቸው ተራውን ሕዝብ ሳይቀር ከሊቃውንቱ ዕውቀት እንዲካፈል አድርገውታል። እግረ መንገዳቸውንም ልዩ ለሆነው ከባድ ዕውቀት፣ ልዩ የሆነና ያጌጠ አማርኛ ፈጥረውለታል።

kidane-photo

እርሳቸው ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት ኢየሩሳሌም ሒደው ዕብራይስጥ የተማሩበት ዘመን የነበረውን ችግር ያስተዋለ ሰው ብቻ ድካማቸውን ሊመዝነውና ሞያቸው ትልቅ መሆኑን ሊረዳ ይችላል። ፍቅርና አንድነት በተሰበከበት አገር በኢየሩሳሌም ጠብና መለያየት ተዘርቶበት ነበር። ዛሬውንም ገና አላለፈበትም። ከዚያ የነበረው የኢትዮጵያ መነኮሳት ማኅበር፣ ከጸሎት በቀር፣ ትምህርት መቀጠል የማያስፈልግ ሥራ ሁኖ ሲታየው፣ እስራኤላዊ ደግሞ በዓለም ያለ ሕዝብ አሥር ቢማር እንደማያፈቅረው ተረድቶት ቋንቋውን ሊማርለት የመጣውን ክርስቲያን መርዳት፣ እባብን ከመቀለብ ይቆጥረው ነበር። ስለዚህም አለቃ ኪዳነ ወልድ ዕብራይስጥ የተማሩት በሁለት ፊት ሥቃያት እያዩ ነው። ይህ ሁሉ ድካማቸው በክርስቲያን ሊቃውንት ጭምር ስለ ብሉያት መጻሕፍትና ታሪክ ያመጡትን አዲስ መግለጫ ለመከታተል ቢቸግራቸው፣ አማርኛው ከተሰናዳው መግለጫቸውም በክርስቲያንነታቸው የጸኑት ሊቃውንት ከደረሱበት የታሪክና የትርጕም አዲስ አካሔድ ለመድረስ ቢያቅታቸው አይፈረድባቸውም።

kidane-hizqel

የኢትዮጵያን የጥንቱን ትምህርት ከሚያውቁት ሊቃውንት አማርኛንና ግዕዝን ለማጣራት፣ ያለቃ ኪዳነ ወልድን ያህል የሚደክም ብዙ አልተገኘም። አማርኛ ለግዕዝ ልጁ በመሆኑ፣ ከግዕዝ የተቀበላቸውን ቃላት ልክ እንደ ግዕዝ አድርጎ መያዝ አለበት የሚል አሳብ ስላለባቸው፣ ይህንኑ ውሳኔ ለመግለጥ የታተመና ያልታተመ ብዙ መጽሐፍ ጽፈዋል። አሳባቸውን ተቀብሎም ለማስተዋል የሚጣጣር በያገሩ ብዙ ደቀመዛሙርት አውጥተዋል። ሠላሳ ዓመት ያህል የደከሙበት ዋናው መጽሐፋቸው ግዕዙን ባማርኛ የሚተረጕም መዝገበ ቃላት ነው።

ጠላት አገራችንን በወረረበት ዘመን እርሳቸው ሲታሠሩ ሲጋዙ ያን ያህል የደከሙበት ሥራ የሚከውነው አጥቶ የብልና የምስጥ ምግብ ሁኖ መቆነጻጸሉ ጕዳቱ የራሳቸውና የመላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወሰን ሳያግደው ሰንደቅ ዓላም ሳይለየው፣ ወገን ለሆነው በዓለም ላለው የትምህርት ወዳጅ ለሆነው ሰው ሁሉ ነው። ከሰው ተለይተው፣ ፈቃድ አጥተው ሲኖሩ ሳለ ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ከችግር አስጥለዋቸው የነበሩ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ዛሬም ንጉሠ ነገሥታችን የኢትዮጵያን አልጋ መልሰው ሲይዙ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድን አስፈልገው የዕለት እንጀራቸውን በመዓርግ እንዲያገኙና ያቋረጡትን ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋልና ፈቃዱ ሁኖ የኢትዮጵያ ወጣቶች የግዕዝን ቋንቋ ከሥር እስከ መሠረቱ ለማወቅ ከገዛ አገራቸው ሊቅ በተጻፈው መዝገበ ቃላት ይመረምሩታል እያልን ተስፋ እናደርጋለን።kidane-dictionary

የግጥም ባሕል

በግጥም ወይም ቤት ሳይመታ፣ ቃሉ ያላጋደለ፣ የተመዛዘነ በሆነ ንግግር አሳብን መግለጥ፣ ሰው አንደበት ከፈታ ጀምሮ የነበረ ልማድ ነው። በጽሕፈት ያልገባው ያገራችን የጥንት ወግና ታሪክ፣ ብዙ ግጥም አለበት። ሌላ የቀድሞ ሕዝብ የቤተ መንግሥቱን ሕግ ሳይቀር ቤት እያስመታ ጽፎ፣ በተማሪ ቤት በዜማ እንዲማሩት አድርጓል። በኢትዮጵያ ማናቸውንም የግዕዝ መጽሐፍ ስንኳ በዜማ ማንበብ ልምድ ቢሆን፣ ሕግን በግጥም መጻፍ አልተለመደም። ነገር ግን ቤት የሚመታ የሕግ ዓይነት ምሳሌ አይጠፋም። “ይካስ የበደለ፣ ይሙት የገደለ”፣ “ያባት ዕዳ ለልጅ፣ ያፍንጫ እድፍ ለእጅ”፣ “አልሞት ባይ፣ ተጋዳይ”።

ይህንንም የሚመስል ባንድ ፊት ምሳሌ፣ እግረ መንገዱን ደግሞ ሕግ ሁኖ የሚጠቀስ፣ ቤት የሚመታ ብዙ ንግግር አለ። በቀድሞ ዘመን አንዳንድ ጊዜ ከሳሽና ተከሳሽ ተከራክረው ሲጨርሱ፣ አጭር ሁኖ ቤት የሚመታ ንግግር ጉዳያቸውን ለዳኛ ያቀርቡ ነበር። ከትችት ላይ ዛሬውንም ቢሆን በግጥም የሚተች አለ። የበገናና የመሰንቆ፣ ልዩ ልዩ ዝማሬ፣ ባላገሩ ለአምላክና ለድንግል ማርያም፣ ለመልአክና ለጻድቅ የሚያቀርበው ልመናና ምስጋና በግጥም ነው። ቀረርቶና ዘፈን፣ እንጕርጕሮና ልቅሶ ሁሉም በግጥም ነው።

ነገር ግን ልዩ ልዩ ሕዝብ ፊት አስቀድሞ ቤት እየመታ ወይም በሕግ በተወሰነ ሚዛን አሳቡን የሚገልጥበትን ጽሑፍ ሥራው ሲደራጅ፣ ባገራችን ጽሑፍ ሥራ ግጥም የኋሊት ቀርትዋል። ስለሆነም አሁን በቅርቡ ጊዜ ብዙዎች ሰዎች በግጥም መጻፍ ጀምረዋል። አብዛኛው ስላልታተመ ስለ አማርኛ ግጥም ብዙ የምናመለክተው የለንም።

ያሳተሙትና ያላሳተሙት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች በግጥም የሚገልጡት አሳብ አብዛኛውን ጊዜ ምክር ነው። የሰውን ኀዘንና ደስታ የሚገልጠው እጅግ በጥቂቱ ሁኖ፣ የወንድንና የሴትን ፍቅር የሚያነሳ በጭራሽ የለበትም። የጣልያኖች ወረራ፣ ስለ አገርና ስለ ንጉሠ ነገሥት ፍቅር፣ ዓመፀኝነት ስለሚሠራው ግፍ፣ ስለነፃነትም ናፍቆት በግጥም የሚያናግር አሳብ ቀስቅስዋል። የተጻፈው ገና ስላልተመረመረ፣ የሚያምረውን ከማያምረው ለመለየት ለጊዜው አልተቻለኝም።

ስለ አማርኛ የቅኔ ባሕርይ ግን ከዚህ በፊት እንዳመለከትነው፣ ብዙ “ስለምን” ወይም “አማርኛ” ይወዳል። አብዛኛውን ጊዜ አያሌውን መስመር ባንድ ፊደል ቤት ያስመታል። አንዱን መስመር በሁለት ሐረግ ከፍሎ፣ ላንዳንዱ ሐረግ ፮፣ ለሁለቱ ሐረግ (ላንዱ መስመር) ፲፪ ፊደል ይሰጣል። ፊደል ሲቆጥር አብዛኛውን ጊዜ እንደ ዕብራይስጡ ቅኔ ሳድሱን ከሌለ ይቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሳቡና በንግግሩ ስንኳ ቅኔ ወዳጅና ቅኔ ፈጣሪ ሁኖ ቢታይ፣ ባማርኛ እስከ ዛሬ ጽፈው ካሳተሙት ግጥም ገጣሚዎች፣ ትዕግሥት ሰጥትዋቸው፣ ሽሕ መቶ ሽሕ መሥመር የጻፉና ያሳተሙ ያሉ አይመስሉንም። በርከት አድርጎ የጻፈ ቢኖርባቸው ለፍርድ ይመች ነበር።

ወጣቱ ከበደ ሚካኤል

ይሁን እንጂ አጭርም ቢሆን፣ እኔ ለራሴ ሥራቸውን የማደንቅላቸውና የማመሰግንላቸው ብዙ ወጣቶች አሉ። ከነዚህም አንዱ ከበደ ሚካኤል ነው። ቅኔ፣ ምሳሌ፣ ተረት ከውጭ አገር ደራሲ (ከፈረንሳይ) በሚተረጕምበት ጊዜ አሳቡና ንግግሩ አማርኛ ሁኖ ከተረጐመበት ቋንቋ ጋር ሲያስተያዩት አንዳንድ ጊዜ ተወዳዳሪው፣ አንዳንድ ጊዜም አርሞ ያቃናው ሁኖ ይገኛል።

ምክንያቱን ከራሱ አፍልቆ የሚፈጥረው ግጥም ከልብ የወጣ ከልብ ይገባል እንደተባለው ሁሉ፣ ልብን የማይነካ የሚገኝበት ሁኖ አልታየኝም። አብዛኛውን ጊዜ ካገራችን ባለ ቅኔዎች ግዕዝን ወይም የውጭ አገርን ቋንቋ እጅ ያደረጉ ሲሆኑ ወደዚያው እየሳባቸው ንግግራቸውን ለማስተዋል እንቸገርበታለን። ወይም ደግሞ፣ ሌላ ባለ ግጥም ያወጣውን ንግግር፣ አማርኛው ካማረ ብለው ያለ ቦታው ሲጥሉት ቅር ያሰኛሉ። “ስለምን” ያልሁትን ንግግር አምጥተው አንባቢ በቶሎው እንዳያስተውለው ያደረጉ እንደሆን፣ ሰው ሊያስተውለው ያልቻለ ጥልቅ ጥበብ የተገለጠላቸው ይመስላቸዋል። ከበደ ሚካኤል፣ ሌሎች ካበጁት ወይም ከውጭ አገር ንግግር ሳይጨምር በራሱ አማርኛ፣ ሁሉም ሊያስተውለው የሚችል አገላለጥ በመምረጡ ለወደፊት ለሚነሱት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች አብነታቸው ለመሆን ተስፋ የሚያስደርግ ልጅ ነው።

kebede-berhane-hilinakebede-nibab

ማጠቃለያ

ለንግግራችን ፍጻሜ ስንሰጥም ደግመን የምናስታውሰው፣

  1. በአማርኛ መጻፍ ከጀመርን ስድስት መቶ ዓመት ስንኳ ቢሆን፣ በብዙው የተጻፈበት ዘመን ከ1600 ዓ.ም. በኋላ መሆኑን።
  2. ከ1600 ዓ.ም. ጀምሮ ባማርኛ የሚጻፈው አብዛኛው የሃይማኖት መጽሐፍ ሁኖ ከንግግሩና ከአሰካኩ ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ ብዙ አካሔድ እንደነበረበት፤ ይህንም የአጻጻፍና የንግግር አካሔድ ዛሬውን ሳይቀር አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደሚከተሉት።
  3. አማርኛን ራሱን አስችለው መጻፍ የጀመሩት ደራስያን በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን (1847-1860) መሆኑን ጭራሽ እየተጣራ የሔደበት ግን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን።
  4. አማርኛ ጽሑፍ ሥራውን በግጥም ጀምሮ፣ ይኸው የግጥም ሥራ ዛሬ የኋሊት መቅረቱን።
  5. የዛሬ ዘመን ደራስያን ከሚጽፉት አብዛኛው መጽሐፋቸው የታሪክና፣ የሃይማኖት፣ የልብ ወለድ ታሪክም መሆኑን፣ የሁሉን አሳብ ትምህርትን ሥራንና ልማድን እያሻሻሉ መሔድ ዋና መሆኑን።
  6. የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍጥረቱ የቅኔ መንፈስ ያደረበትና በግጥም አሳቡን እንደገለጠ መኖሩን፣ ሙግቱንና ትቹን ሳይቀር በግጥም ማምጣት ልማዱ መሆኑን በዚኸውም የተፈጥሮ ልማዱ ቤት እያስመታ የሚሔድ ደራሲ በብዙው መገኘቱን፣ ነገር ግን ባማርኛ ያወጣውን ግጥም ያሳተመ ደራሲ ጥቂት መሆኑን ነው።

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም