ግስ ዘመምህር ክፍሌ

ግስ ዘመምህር ክፍሌ

(መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ – ክፍል 2)

.

በኅሩይ አብዱ

.

(ከክፍል 1 የቀጠለ)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻) መላ ሕይወታችውን በትምህርትና ምርምር ዙርያ በአገራቸው እንዲሁም በስደት እንዳሳለፉ የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል። በዚህኛው ክፍል ደግሞ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የወጠኑት “ግስ” በ1948 ዓ.ም ለታተመው “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” እንዴት መሠረት ሊሆን እንደቻለ ለማሳየት እሞክራለሁ።

በቅድሚያ ግን ስለ የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ታሪካዊ አጀማመር እና በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ዘመን የነበረበትን ደረጃ በአጭሩ አቀርባለሁ።

 .

የግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት ታሪካዊ ሂደት

“መዝገበ ቃላት” በቁሙ የቃላት መሰብሰብያ፣ ማከማቻ ወይም መድበል ነው። ቁምነገሩ ግን እነዚህን በተለያየ ምክንያት የተሰባሰቡትን ቃላትን መፍታት ወይም መተርጎሙ ላይ ነው። ስለዚህ ስለ መዝገበ ቃላት ሲነሳ የትኞቹ ቃላት ተመርጠው እንደሚሰበሰቡ፣ ከዛም በምን መልክ እንደሚተረጎሙ አብሮ መታሰብ አለበት።

አብዛኞቹ የመጀመሪያዎቹ መዝገበ ቃላት በአንድ የጽሑፍ ቋንቋ (ለምሳሌ ግእዝ) የሚገኙትን ከባድና ያልተለመዱ ቃላት ወደ ጊዜው የንግግር ቋንቋ (ለምሳሌ አማርኛ) ለመተርጎም የተዘጋጁ ናቸው። “መዝገበ ቃላት” የሚለውም ቃል በ20ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ከመለመዱ በፊት ጽንሰ ሐሳቡ “ነገር” እና “መጽሐፈ ግስ” በተባሉት ቃላት ውስጥ ተካቶ ነበር።

የመጀመሪያዎቹ ከ1600ዎቹ በፊት የተዘጋጁ የግእዝ-አማርኛ መፍቻዎች ዓላማ በግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ከግሪክ ወይም እብራይስጥ የተገለበጡ ቃላትን ወደ አማርኛ መተርጎም ነበር። እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የማያሳዩ (ግስ ያልሆኑ) ቃላቶች በግእዝ ሰዋስው “ነባር” ይባላሉ። አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት፣

“ዘርነት የሌለው፣ ከዘር አንቀጽ የማይገኝ የቋንቋ ቤተሰብ እየኾነ በውጥንቅጥነት የሚገኝ ጥሬ ቃል ኹሉ ነባር ይባላል፤ ትርጓሜውም የማይፈልስ የማይናወጥ የማይጠፋ የማይለወጥ ስም ማለት ነው።”

እኒህም የነባር ቃላት መፍቻዎች በድሮ ዘመን (እንደ መጽሐፉ ዓይነት) “ጥሬ ኦሪት”፣ “ጥሬ ነገሥት” ይባሉ ነበር ። ለምሳሌ ከኦሪትና ከነገሥት የሚከተሉትን ማየት ይቻላል።

ሂጳጳታላቅ አሞራ፣ የማይበር (ዘዳግም 14፡17)

ለሮንይብራ ሦስት ጕተና ያለው (ዘዳግም 14፡15)

ልንጴኔአልጋ፣ መከዳ፣ ብርኩማ (1 ሳሙኤል 26፡5)

ሐሜላትመጠምጠምያ፤ ሕባኔ (1 ነገሥት 19፡13)

ሐንጶንእንዘዝ፣ አርጃኖ  (ዘሌዋ 11፡30)

በመቀጠል ከ17ኛው እስከ 19ኛው ክ/ዘመን በተዘጋጁ የሰዋስው ብራናዎች ላይ የምናገኘው “ነገር” በሚል ምደባ ቃላትን እየከፋፈለ ከግእዝ ወደ አማርኛ የሚተረጉም መዝገበ ቃላትን ነው።

ቃላቱንም ለመፍታት አብዛኞቹ ብራናዎች ይህን መሠረታዊ ቅርጽ ይጠቀማሉ፣

(ግእዝ ቃል) (አማርኛ ፍቺ)

(“ብ” ማለት “ብሂል ው የግእዝ ቃል ሲሆን ኛ “ማለት ወይም ሲል” ተብሎ ይተረጎማ)

ለምሳሌ፣ ውኂዝ ፈሳሽ

ወይም ባሁኑ አማርኛ “ውኂዝ ሲል ፈሳሽ ማለት ነው”።

አብዛኞቹ የ“ነገር” ብራናዎች ቀዳሚው ክፍላቸው “እጽሕፍ ነገረ ሰዋስው በማለት ይጀምርና

ሰዋስው (ማለት) መሸጋገርያ ወመሰላል ብሎ የመጀመርያውን ትርጉም ይሰጠናል።

ከዛም የተለያዩ የሰዋስው አገባብ ቃላትን ይፈታል፣

ላዕለ በላይ

ማዕዜ መቸ

አይቴ ወዴት ….

ቀጥሎም አንድ ዓይነት ትርጉም ያላቸውን የግእዝ ግሶች ይተረጉማል፣

ሖረ፣ አመልአ፣ ነገደ ሄደ

ሐለየ፣ ተዘከረ፣ አስተሐመመ አሰበ … የመሳሰሉት።

አብዛኞቹ “ነገር” ብራናዎች ከ30 በላይ ክፍል አላቸው። አብዛኛዎቹ ክፍሎች ከዚህ በፊት እንደተጠቀሱት “ጥሬ ኦሪት፣ ጥሬ ነገሥት” የመጽሐፍ ቅዱስን ነባርና ከባድ ቃላት ፍቺ ይሰጣሉ። ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም አብዛኞቹ የየራሳቸው ክፍል አላቸው፣

ለምሳሌ ያህል፣

እጽሕፍ ነገረ ሕዝቅኤል

እለ ቄጥሩ ዖፍ ዘራብዕ ርእሱ (ወፍ ባለአራት ራስ)

ተርሙስ አደንጓሬ ….

ሐዲስ ኪዳንም “ነገረ ወንጌል፣ ነገረ ጳውሎስ፣ ነገረ ሐዋርያት” በሚል መደቦች ተከፍሏል። በተጨማሪም ሌሎች የቤተ ክርስቲያኑ ዋና መጻሕፍት (ሲኖዶስ፣ ቄርሎስ …) የየራሳቸው ክፍል አላቸው። በተጨማሪም ስለ መላእክት፣ ሰማዕታት፣ ሐዋርያት፣ ወራ …. ነክ ቃላት ትርጉም የሚያስረዱ ክፍሎችም አሉ።

የተረፉትን ክፍሎች ደግሞ ሕይወት ካላቸው ነገሮች ጋር የሚገናኙ (እንደ ነገረ አራዊት፣ ነገረ አዕዋፍ፣ ነገረ ዕዋት፣ ነገረ አዝርዕት፣ ነገረ ሥጋ፣ ነገረ ሕዋሳት/መልክዕ፣ ነገረ ሕማም …) የመሳሰሉ ክፍሎች ይገኛሉ። ከነዚህ ውጭም እንደ ነገረ ርዓተ መንግስትአልባስ (ልብስ)፣ አጽር (አጥር)፣ ማያት (ውሃዎች)፣ ሐጻውንት (ብረቶች)፣ አብያት (ቤቶች)፣ አዕናቊ (ዕንቁዎች)፣ ወርቅ …. የመሳሰሉም ይገኛሉ፡፡

ለምሳሌ “ነገረ ሕማም” የተሰኘው ክፍል፣ በዚህ መልክ ህመም-ነክ ቃላትን፣ ግሶችንና ሀረጎችን ይፈታል፣

እጽሕፍ ነገረ ሕማም

ብድብድ ቸነፈር

ጼደናታት መጋኛ ጉስምት

ፈጸንት ተቅማጥ

በደዶ ፈንፃፃ

ዝልጋሴ ሕንጳጴ ቊስለ ሥጋ

ቀበር በድን እሬሳ

ዝኅር መቃብር

እንፎራ ሳውዕ ማር ካህን

አንኰለሎ አዞረው

ኖመ ኀለፈ ሞተ

ለይልየ ወይ እኔ

ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮ ለኔ

ነገረ ሕማም” ምንም እንኳ ከህመም ዓይነቶች (መጋኛ፣ ጉስምት …) ቢጀምርም፣ ህመሙ ሲብስ የሚመጣውን (አዞረው፣ ቁስለ ሥጋ፣ ሞተ …)፣ በማስከተልም ቀብርን (እሬሳ፣ መቃብር …)፣ የቀብሩን ሥርዓት አስተናጋጆች (ቄስ …)፣ እና በለቅሶ ወቅት የሚባለውንም (ወይ ለኔ፣ ወዮ ለኔ …) ያካትታል።

ታዲያ አንዳንድ የ18ኛ እና 19ኛ ክ/ዘመን “ነገር” ብራናዎች የተወሰኑትን ቃላት ብቻ “ነገር” ስር ከመደቧቸው በኋላ፣ የተቀሩትን ቃላት ደግሞ በሞላ በአንድ ትልቅ ክፍል ይከቷቸዋል። ይሄም ወደፊት ለሚመጣው “የቅኔ ቤት ግስ” መነሻ ሳይሆን አይቀርም።

የቅኔ ቤት ግሥ

የቅኔ ቤት ግሥ በአብዛኛው የሚገኘው በ19ኛው እና በ20ኛው ክ/ዘመን በተዘጋጁ ብራናዎች ላይ ነው። ይህ አይነት መዝገበ ቃላት የተዘጋጀው በቃላቱ መድረሻ ፊደል ቅደም ተከተል ስለሆነ ቅኔ እና ሌሎች ግእዝ ግጥሞችን ለመድረስ ይረዳል።

በዚህም ምክንያት እስካሁን ድረስ በቅኔ ቤት ተፈላጊነት ስላለው፣ ተማሪው ወይም በእጁ ይገለብጠዋል አሊያም ከታተሙት አንዱን “መጽሐፈ ግስ” ገንዘቡን አጠራቅሞ ይገዛል።

የግእዝ ፊደላት 26 ቢሆኑም የቅኔ ቤት ግስ 21 ክፍሎች አሉት። ምክንያቱም ሀ ሐ ኀ፣ ሠ ሰ፣ አ ዐእና ጸ ፀአብረው አንድ ክፍል ውስጥ ስለሚመደቡ ነው።

ከ19ኛ ክ/ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የሚገኙት የቅኔ ቤት ግስ ብራናዎች በቅድሚያ ቃላቱን በመድረሻ ፊደል ወደ የተለያየ ቤት ይመድባሉ (ለምሳሌ፣ ሰአ፣ ሠረ፣ ኖለ)። በመቀጠልም እያንዳንዱ ቤቱ ውስጥ (ለምሳሌ “”) ደግሞ ከእንደገና በቃላቱ መነሻ ፊደል ይደረደራሉ።

ለምሳሌ የ “” ቤት ቅደም ተከተሉ፣

ሥረ፣ ሐረረ፣ ብረ፣ ሖረ

ወረ፣ ለጠረ

ረ፣ መ

ረ፣ አረ፣

ብረ

ጠረ

መድረሻ ቤትም እንደተጨረሰ “ እያለ እስከ “ ድረስ ይቀጥላል፤

ለምሳሌ ላይ፣

ንኮሪ

ስሪ

ጌሪ

ባለፉት ሃያ አመታት የታተሙት የቅኔ ቤት ግሶች ደግሞ ተማሪው እንዲቀለው በማለት ከነጠላው ግስ በማስከተል ከግሱ የሚወጡትን ዘሮች (ቅጽሎች፣ ስሞች) ይደረድራሉ።

ለምሳሌ፣

መሀረ አስተማረ

ምሁር ስጠ ዘ (የተማረ)

መምህር ባዕድ ቅጽል (አስተማሪ)

መሀርት መድበል (አስተማሪዎች)

ትምህርት ባዕድ ከምዕላድ (በቁሙ፣ ትምህርት)

ትምህርታት በብ(ትምህርቶች)

.

የመምህር ክፍሌ ግስ አወጣጠ

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወደ ግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላቱ ሥራ እንዴት ሊገቡ እንደቻሉ፣ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” መግቢያ ላይ የመምህራቸውን ኑዛዜ እንዲህ አቅርበውታል፤

“…ኋላም በጊዜ ሞት አስር ዓመት ምሉ ከርሳቸው ጋራ ለነበረው ለሀገራቸው ልጅ ለተማሪያቸው እንዲህ ብለውታል፤ልጄ ሆይ ይህነን ግስ ማሳተም ብትፈልግ እንደ ገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረኽ ማፍረስና ማደስ አለብኽ፤ በመዠመሪያው አበገደን ጥፈኽ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው። አንባቦችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለኽ ዐጭር ሰዋስው አግባበት፤ የጐደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፤ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ፣ ዘር ኹን፣ ዘር ያድርግኽ፤ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ፤ ለሀገርኽ ያብቃኽ ብለው ተሰናበቱት።”

ዲልማን (August Dillmann) የተሰኘ ጀርመናዊ የቋንቋ እና መጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ በርካታ የግእዝ መጻሕፍትን በመመርመር በ1857 ዓ.ም “Lexicon Linguae Aethiopicae” የተሰኘ የግእዝ-ላቲን መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶ ነበር። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም የዲልማንን መዝገበ ቃላት አይተው፣ “ሥራን መንቀፍ በሥራ ነው እንጂ በቃል ብቻ መንቀፍ አይገባም” ብለው የጀርመናዊውን መዝገበ ቃላት በሥራ ነቅፈው አዲስ ግስ (መዝገበ ቃላት) የጀመሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚነገሩን ምጽዋ በስደት ሳሉ ነበር።

መምህር ክፍሌ በ1870ዎቹ መጀመርያ የግእዝ-አማርኛ ግሳቸውን (መዝገበ ቃላት) ረቂቅ ሲልኩ ይህንንም መልእክት አብረው ልከው ነበር፤

“የዚህ ግሥ ሥራው አልተጨረሰም፤ ስምና ግዕዘ ብሔር ቀርቶታል። ጊዜ ቢገኝ ሲታተም ይጨረሳል። ተራም ቤቱን ሳይለቅ አንዳንድ የፊደል ተራ ተዛውሮ ይገኛል። ኋላ ይቀናል። አማርኛው ለሰው እንዲሰማ የሀገረ ሰብ አማርኛ አለበት፤ ‘ሥር፣ ሥራ’ በብዙ አንድ አማርኛ ይሆናሉ። ሥራ ሲበዛ ሥሮች፣ ሥርም ሲበዛ ሥሮች ይባላል። እንዲህ ያለ ሲገኝ ያለ መምህር ለሁሉ አይሰማም። ስለዚህ ሥራ ብሎ በብዙ ‘ሥራዎች’ እንደ ማለት ያለ ይጥፋል። እንዲሰማ ነው እንጂ መልካም አማርኛ አይደለም።

“ሦስቱ ‘ሀሐኀ’፣ ሁለቱ ‘ሠሰ’፣ ሁለቱ ‘አዐ’ እንዳይሳሳቱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አለዚያ ተራ ይበላሻል። የፊደልም ተራ ‘ሀላዊ’ ሳይል ‘ሀለደ’ አይልም። ከ‘ላ’‘ለ’ ይቀድማል ብሎ ‘ሀለደ’ ይቅደም ቢል ከ‘ዊ’‘ደ’ አይቀድምም ይላሉ። ሁሉ እንዲህ ነው፣ ቤቱን ካለቀቀ ግዕዝ ሐምስ ቢቀዳደሙ ግድ የላቸውም። ሦስተኛው ፊደል ያለ ተራው እንዳይገባ ይጠብቃሉ።

ፍችም አእማሪ ‘ያወቀ’፣ አእማሪት ‘የወደደች’፣ እንዲህ ያለ ፍች አለው፡ ያንዱ ፍች ለሁሉ ይሆናል። የፊደል ግድፈት ተጠንቅቃችኁ ተመልከቱ፤ ዕለቱን ተጨርሶ ሳይታረም መጥቶላችኋል። ሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ አሜን።”

መምህር ክፍሌ ከምጽዋ የላኩት ‘ግስ’ በአሁኑ ወቅት በሦስት ግልባጭ ይገኛል።

ሁለቱ አቡነ አሥራተ ማርያም በ1920ዎቹ ያስገለበጡዋቸው ሲሆኑ በEthiopian Manuscripts Microfilm Library (EMML) በፕሮጀክቱ ፊልም ተነስተዋል – EMML 2334 እና EMML 2335 ይሰኛሉ። ሌላኛው ግልባጭ ደግሞ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተመራማሪ ፈረንሳዊው ኮኸን (Marcel Cohen) በ1915 ያስገለበጠው ሲሆን እሱ እንደሚለው ዋናው ኮፒ አሊቴና ሳይገኝ አይቀርም። ከዚህ በተጨማሪም አሁን የት እንዳለ ባናውቅም፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ከመምህር ክፍሌ የወረሱት እና በኋላ ያስፋፉት ሌላ ግልባጭ መኖሩንም ማስታወስ ያስፈልጋል።

.

ይዘት

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ግሳቸውን ከምጽዋ ሲልኩ “የዚህ ግሥ ሥራው አልተጨረሰም .. ጊዜ ቢገኝ ሲታተም ይጨረሳል … የፊደል ግድፈት ተጠንቅቃችኹ ተመልከቱ፤ ዕለቱን ተጨርሶ ሳይታረም መጥቶላችኋል” በማለት ነበር። ስለዚህ ግሱም መታየት ያለበት እንደ መጀመርያ ሙከራ (ረቂቅ) ነው።

ግሱ ከመጀመሩ በፊት ተጠቃሚውን እንዲረዳ መለስተኛ ርባ ቅምር (የግስ እርባታ አመል) የሆነ አጭር መግቢያ ተዘጋጅቷል። መግቢያውም፣

“ግሥ ከሁለት ፊደል አይወርድም፤ ከሰባት ፊደል አይወጣም” በማለት ይጀምራል።

በመቀጠልም ስለ ግስ አመሎች የተወሰኑ ፊደሎች (ሀ፣አ እና ወ፣የ) በግስ እርባታ ቅርጽ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ሲናገሩ፣ “እሊህ ያሉበት ግሥ ከቤቱ ዘር ጥቂት ጥቂት ይለወጣል” በማለት ምሳሌ ይሰጣል።

ቀጥሎም ሰላሳ ሁለቱን የግስ ሠራዊትና ስምንቱን የግስ አርዕስት (ቀተለ፣ ባረከ፣ ጥሕረ፣ ኖለወ፣ ቀደሰ፣ ደንገፀ፣ ተጋብአ፣ አናኅሰየ) ዘርዝሮ ሳቢዘር ስለሚገኝባቸው ግሶች ያወራል። በመጨረሻም ግሱ ውስጥ ስለሚገኙ ‘የግሥ ምልክት’ ( – የሚጠብቅ፣ – የሚላላ) በማለት ያስረዳል።

መምህር ክፍሌ ግሳቸውን ለመስራት ሲነሱ በቤት መምቻ ፊደል የተደረደረውን የዘመኑን የቅኔ ቤት ግሳቸውን በመያዝ ነው።

የቅኔ ቤት ግስ በቤት መምቻ ፊደል መሰደሩን እንዲሁም በአማርኛ ሞክሼ ፊደላት የሚባሉት መዳበላቸው ስላልተስማማቸው በአዲስ መልክ አዲስ ግስ ይሰራሉ። ከEMML 2335 መረዳት እንደምንችለው የቅኔ ቤት ግሱን ወስደው፣ አብረው የተዳበሉትን (ሀ፣ሐ፣ኀ)፣ (ሠ፣ሰ)፣ (አ፣ዐ) እና (ጸ፣ፀ) መለያየት ይጀምራሉ። ከያንዳንዱ ቤትም በ ‘ሀ’ የሚጀምሩትን ለብቻ፣ በ ‘ለ’ የሚጀምሩትን ለብቻ …. አድርገው ግሱ በመድረሻ ፊደል መደርደሩን ትቶ በመነሻ ፊደል መሰለፍ ይጀምራል።

አንድ ግስ የሚደረደረው በቀደማይ (ያለቀ ድርጊት – ‘ኖረ’) አንቀጹ ሲሆን፣ በመቀጠልም እዛው መስመር ላይ ካልኣይ (ያላለቀ ድርጊት – ‘ይኖራል’) እና ሣልሳይ አንቀጾች (ዘንድ/ትእዛዝ ‘ይኖር ዘንድ/ይኑር’) ነው። ከዚያም የግሱ አርእስት (ንዑስ አንቀጽ – ‘መኖር’) ይከተላል። ግሱም የሚተረጎመው በግሱ አርእስት መሠረት ነው።

ሀለወ፣ ይሄሉ፣ የሀሉ፣ ሀልዎት – መኖር

በመቀጠልም ሣልስ ውስጠ ዘ (‘ኗሪ’) እና ሌሎች ዘሮች (ዘመድ፣ ሳቢ፣ ጥሬ፣ መ ስም) ይተረጎማሉ። ግሱ አድራጊና ተደራጊ አምዶችም ካሉት (‘አኖረ’ ‘አስኖረ’ ‘ተኖረ’) እዛው ተተርጉመው ዘሮቻቸውም (‘ኑሮ’ ‘አኗኗር’) ይቀርባሉ።

ሀላዊዊት – ነዋሪ

ሀላውያንያት – ነዋሮች፣ የሚኖሩ

ሳድስ ውስጠ ዘ (ህልው ‘የሚኖር’) እና በሳድስ የሚጀምሩ ዘሮች (‘ህላዌ’ ‘ህልውና’) ግን በፊደል ተራቸው ሳድስ ፊደሉ (‘ህ’) ላይ ይደረደራሉ።

ህሉናአነዋዎ

ህሉትየምትኖር

ህልውየሚኖር

ህልዋንየሚኖሩ

ህልዋትየሚኖሩ፣ ኑዋሮች

ህላዌአነዋዎር፣ አካል፣ ባሕርይ

ህልውናአነዋዎር

በመቀጠልም የቃሉን አጠቃቀም ከግእዝ ሥነጽሑፍ በመጥቀስ ከትርጉሙ ይዘታዊ ዐውድ ጋር ያቀርባሉ።

፫ ህላዌ በአካላት፣ ፩ ህላዌ በመለኮት – አነዋዎር ሲል

ኢሐመ በህላዌ መለኮቱ – ባህርይ ሲል

አበዊነ ሰመይዎሙ ለህላውያት አካላተ – አካል ሲል።

መምህር ክፍሌ ለአብዛኛው ግሶች (ከ50 በመቶ በላይ) ምስክር ወይ ጥቅስ ይቀርባሉ። በብዛት ግን ጥቅሶቹ ከየት እንደሆኑ አይነግሩንም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑትን የተወሰኑትን ግን ምንጫቸውን ያቀርባሉ፣ ለምሳሌ መጽሐፈ ምሥጢር፣ ጾመ ድጓ፣ አቡሻክር … የመሳሰሉትን።

በተጨማሪም መዝገበ ቃላቱ በተሻለ መልክ እንዲነበብ አንዳንድ ማመላከቻዎችን አስገብተዋል።

በቊሙ – ትርጉሙ ካማርኛ አንድ ሲሆን።

ምሳሌ፣ ሃይማኖት – በቊሙ

ጥሬ – ከድሮ የቃላት ዝርዝር (ጥሬ ኦሪት፣ ጥሬ ነገሠት) ሲገኝ፣

ምሳሌ፣ ሐመድ – በጥሬ ኦሪት መድልው ይለዋል።

– ሌላ አጻጻፍ ሲኖረው፣

ምሳሌ፣ ሐሔሬኤል ሐኤሬኤል

ቋንቋ ምንጭ – አብዛኛው ጊዜ አረብኛ፣

ምሳሌ፣ ህላል – ሠርቀ ወርኅ (አረብ)

የግስ ቤት – ከ32 የግእዝ “ሰራዊት” ውስጥ በየት እንደሚመደብ

ምሳሌ፣ ለሐወ – የባልሐ ቤት ነው።

እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ገለጻ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስን ለመዝገበ ቃላት ሥራ ያነሳሳቸው ምንም እንኳ የዲልማን ሥራ (“Lexicon Linguae Aethiopicae” 1865) ነው ቢሉንም፣ የመምህር ክፍሌ ግስ በቃላት አመራረጥና አፈታት እንዲሁም በጥቅስ ምርጫው የራሱን መንገድ የቀየሰ ይመስላል።

የመምህር ክፍሌ “ግስ” ከዲልማን የግእዝ-ላቲን “ሌክሲኮን” እንዲሁም ከአለቃ ኪዳነ ወልድ “መዝገበ ቃላት” ጋር በተወሰኑ መስፈርቶች ከታች በሰንጠረዦች ተነጻጽሯል።

Table 2

የሆሄ ቅደም ተከተል – አገራዊ እንዲሁም የሳባ ቋንቋ የሚጠቀመውን “ሀ ለ ሐ መ” የፊደል ተራ ወይስ አረብኛና ዕብራይስጥ (እንዲሁም ግሪክና ላቲን) የሚጠቀሙትን “አ በ ገ ደ” ተራ እንደመረጠ ያሳያል።

የግስ ማግኛ ዘዴ – አንድን ቃል (ግስ፣ዘር) ለማግኘት በግሱ ኀላፊ ጊዜ (ቀዳማይ አንቀጽ) ወይስ በሌላ (አርእስት) እንደተመረጠ ያሳያል። ለምሳሌ “ጻፈ” የሚለውን ግስ ብናይ ኀላፊ ጊዜ ጸሐፈ ሲሆን አርእስት ደግሞ ጽሒፍ፣ ጽሒፎት – መጻፍ ነው።

የግስ ዘሮች አቀማመጥ – ከግስ የሚገኙ ዘሮች አብረው ይደረደራሉ ወይስ በተለያየ ቦታ ይገኛሉ? ለምሳሌ ጸሐፈ (ጻፈ) ከሚለው ግስ ጸሓፊ፣ ጽሑፍ፣ መጽሐፍ፣ ጽሕፈት … የመሳሰሉ ዘሮች የት የት ተደርድረዋል?

Table 3

ጥቅስ – የአንድን ቃል አጠቃቀም ለማሳየት ጥቅስ፣ ምስክር ይቀርባል ወይ?

ነባርና ግስ – ለነባር ቃላት ግስ ይፈለጋል ወይ? ለምሳሌ በተለምዶ ሀገር የሚለው ቃል ግስ የለውም። አለቃ ኪዳነ ወልድ ግን ሀገረ የሚል ግስ ያቀርባሉ።

የቋንቋ ንጽጽር – ቃሉ ከተዛማጅ ቋንቋዎች ጋር ይነጻጸራል ወይ?

.

Kifle 3

.

Kifle 4

.

ማሳረጊያ

thrinity 3

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በ1870 ዓ.ም አካባቢ ያዘጋጁትን “ግስ” በሕይወታቸው መጨረሻ በ1900 ዓ.ም ለተማሪያቸው ለኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአደራ መልክ እንዲህ ብለው አስረከቡ፣

የጐደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ ዘር ኹን ዘር ያድርግኽ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ፤ ለሀገርኽ ያብቃኽ።”

አለቃ ኪዳነ ወልድም የፊደሉን ተራ ቀይረው (‘ሀ ለ ሐ መ’ ወደ ‘አ በ ገ ደ’)፣ ረጅም ሰዋስው አስገብተው፣ መዝገበ ቃላቱንም አስፋፍተው አጠናከሩት። እሳቸውም በሕይወታቸው መጨረሻ ለተማሪያቸው ለደስታ ተክለ ወልድ በአደራ በ1936 ዓ.ም አስተላለፉ።

ደስታ ተክለ ወልድም የተሰጣቸውን መዝገበ ቃላት አርመውና አስተካክለው በ1948 ዓ.ም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ብለው በመሰየም በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት አሳተሙት … ይህ እንግዲህ ሌላ ታሪክ ነው፤ ታሪኩንም ወደፊት በአንድምታ ለማቅረብ እንሞክራለን።

.

ኅሩይ አብዱ

ግንቦት 2009 ዓ.ም

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (1817 – 1900)

በኅሩይ አብዱ

 .

በ1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ “መጽሐፈ ሰዋስው ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በገበያ ዋለ። ይህ የግእዝ-አማርኛ ሰዋስው እና መዝገበ ቃላት የሦስት ትውልድ ሊቃውንት የምርምርና የትጋት ውጤት ሲሆን ላለፉት ስድሳ ዓመታት ዋነኛው የግእዝ ቃላት መፍቻ ሆኖ አገልግሏል። እስከዛሬ ድረስም ቢሆን በአገራችን ምትክ የሚሆነው መጽሐፍ ሊገኝለት አልተቻለም።

በዚህ ጽሑፍ የዚህን ዕጹብ መዝገበ-ቃላት ሥራ ወጣኝ የነበሩትን የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስን የሕይወት እና የድርሰት ታሪክ አቀርባለሁ።

.

ተማነት (1817 – 1842)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ግንቦት 14፣ 1817 ዓ.ም በአንኮበር ተወለዱ። ከአርባ ቀንም በኋላ በሰኔ 23 ስለተጠመቁ ሰማዕቱ ጊዮርጊስን ለመዘከር ስማቸው “ክፍለ ጊዮርጊስ” ተባለ። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንደጻፉልን መምህር ክፍሌ አንኮበር ቢወለዱም አብዛኞቹ ዘመዶቻቸው ከሐር አምባ ናቸው (“አንኮበር ይእቲ ምድረ ሙላዱ ወሐር አምባ ርስተ ነገዱ።”)

አንኮበር

አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚነግሩን መምህር ክፍሌ የሕይወታቸውን የመጀመሪያ ሃያ አምስት ዓመታት ያሳለፉት በሸዋ ሲሆን አብዛኛውን የቤተ ክርስትያን ትምህርት የተማሩትም በዚሁ ወቅት በአንኮበር ነበር። ይህም ማለት ከመሠረታዊው ንባብና ጽሕፈት በመጀመር ዜማ ቤት፣ በመቀጠልም ቅኔ ቤት ገብቶ መማር ነው። የሚቀጥለው ደረጃ የአንድምታ (መጻሕፍት ቤት) ትምህርት ሲሆን፣ ለዚህም ጠለቅ ያለ የግእዝ ሰዋስው እውቀት ያስፈልጋል።

የግእዝ ሰዋስውን አገባብ እና የቅኔ መንገድ በመማር የቅኔ መምህርነት ደረጃ መድረስ ለአዲሱ የአንድምታ ትምህርት ጥሩ መሠረት ይሆናል። ተማሪው መጻሕፍት ቤት ገብቶ በመጀመርያ የሐዲስና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ትርጓሜ (አንድምታ) በቃል በመያዝ ይማራል። በመቀጠልም የመጻሕፍተ ሊቃውንትን (ቄርሎስዮሐንስ አፈወርቅሃይማኖተ አበውፍትሐ ነገሥት …) ትርጓሜ ይማራል። ፍላጎት ያለው ተማሪም በተጨማሪ የመጻሕፍተ መነኮሳትን (ማር ይስሐቅ ፊልክስዮስ፣ እና አረጋዊ መንፈሳዊ) አንድምታ በመማር የመጻሕፍት ቤትን ትምህርት ያጠናቅቃል።

የግዕዝ መምህርና ተማሪዎች 1840ዎቹ አካባቢ

በ1830ዎቹ እና 1840ዎቹ በአንኮበር በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አሰባሳቢነት ታላላቅ ሊቃውንት ይገኙ ነበር። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም ከላይ የተጠቀሱትን ትምህርት ዓይነቶች እዛው በአንኮበር በመጀመሪያ ሳያስኬዱ አልቀሩም። በሃይማኖትም ረገድ፣ ለደቀ መዝሙራቸው ለኪዳነ ወልድ እንደነገሩት “የጸጋ ልጆች” ትምህርትን በሕፃንነታቸው ያስተማሯቸው ዓይነ ስውሩ መምህር ወልደ ሥላሴ ናቸው።

.

 ምህር (1842 – 1867)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ቀጣዩን ሃያ አምስት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት ማዕከሎች እንዳሳለፉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይገልጻሉ (“ … ወዕሥራ ወኀምስቱ ዓመት በብሔረ ጐዣም ወዐምሐራ፣ በላስታ ወበቤጌምድር፣ በጐንደርሂ ወበስሜን፣ በትግሬሂ ወበሐማሴን።”) በዚህ ዘመን የታወቁት የአንኮበር ሊቃውንት (እነ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ተክለ ጽዮን፣ እንዲሁም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ) ከሞጣው ጊዮርጊሱ አራት ዓይና ጐሹ ተምረው በብሉይ ኪዳን መምህርነት እንደተመረቁ ይነገራል። የተማሩበትም ዘመን በደጃች ተድላ ጓሉ ጊዜ እንደመሆኑ እስከ 1850ዎቹ አጋማሽ ባለው ዘመን የነበረ ይመስለኛል።

ከአራት ዓይና ጐሹ ተምረው እንደጨረሱ የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጓደኛ ባለቅኔው ተክለ ጽዮን ዲማ ወርደው ቅኔ አስተማሪ ሲሆኑ፣ እሳቸው ደግሞ ወደ ጐንደር አቀኑ። እዛም ከታላቁ ሊቅ ከግምጃ ቤት ማርያሙ ከወልደአብ ወልደሚካኤል ዘንድ የአንድምታ ትምህርታቸውን (መጻሕፍተ ሐዲስና ሊቃውንትን) አስኬዱ።

ከዚህም በኋላ ስለ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ያለን መረጃ በአንኮበር ሚካኤል በሚገኝ ብራና ላይ ያለው የቤት ሽያጭ ውል ነው። ይህም ውል፣ “ይመር ጐጅ ለቄስ ክፍለ ጊዮርጊስ በ፫ ብር ከ፰ ጨው ሁለት ቤት ሸጠዋል” ይላል።

አንኮበር ሚካኤል 1830ዎቹ አካባቢ

ውሉ የተጻፈው በአጼ ቴዎድሮስ መንግሥት (1847-1860 ዓ.ም) በዘመነ ማቴዎስ ነው። ይህም ውሉ የተፈጸመበትን ዓመት 1849፣ 1853 አሊያም 1857 ዓ.ም. ያደርገዋል። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በጐዣም እና በጐንደር ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመት በትምህርት ሊያሳልፉ ስለሚችሉ ውሉ የተፈጸመበት ዘመን በ1853 ወይም በ1857 ቢሆን የበለጠ ያሳምናል።

ከጐዣም እና ጐንደር ቆይታቸው በኋላ ሁለቱ ጓደኛሞች (ተክለ ጽዮን እና ክፍለ ጊዮርጊስ) የብሉያትን አንድምታ አንኮበር ተመልሰው ማስተማር እንደጀመሩ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይናገራሉ። ለምን ያህል ጊዜ አብረው እንዳስተማሩ ባይታወቅም፣ አንደኛው ኦሪት ዘፍጥረት ሲተረጉም ሌላኛው የመሐፈ ነገሥትን አንድምታ እንደሚያስተምር፣ አንዱ ትንቢ ኢሳይያስን ሲተረጉም ሌላው ትንቢ ኤርምያ አንድምታ እንደሚያስኬድ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይነግሩናል።

ከዚህ ቀጥሎ ስለ መምህር ክፍሌ የምናገኘው መረጃ አለቃ ኪዳነ ወልድ ስለ መጽሐፈ ሕዝቅኤል ዘርና ትርጓሜ ፍለጋ ከመምህራቸው ሰምተው አንድ መጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራና ላይ (አሁን በኢየሩሳሌም በደብረ ገነት ቤተ መጻሕፍት የሚገኝ) በጻፉት መቅድም ውስጥ ነው። በዚህም ጽሑፍ ላይ እንደሚተረከው የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ትርጓሜ ትምህርት በአገሪቱ ውስጥ የሚሰጥበት ብቸኛ ቦታ ጐንደር ሆኖ ነበር። በጐንደርም ያሉት የአንድምታ መምህራን ትምህርቱን በድብቅ ቤት ዘግተው ለብቻቸው በማድረጋቸው እነሱ በተለያየ ምክንያት ሲሞቱ ትምህርቱም አብሮ ጠፋ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እንደሚሉት፣

“የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የሊቃውንትና የመነኮሳትን ትርጓሜ ትምህርት እንደጨረስኩ የነቢዩ ሕዝቅኤልን መጽሐፍ ፍለጋ አድባራትን፣ ገዳማትን፣ ደሴታትን ሳስስ ምንም አላረፍኩም።”

በዚህም ምክንያት መምህር ክፍሌ ‘ትክክለኛው’ ሕዝቅኤልን ፍለጋ ወደ ስሜን ወደ ደረስጌ ማርያም ያመራሉ። እዛም ሁለት የሕዝቅኤል መጽሐፎች ያገኛሉ። ብራናዎቹ ግን አላስደሰቷቸውም፣ በተለይ አንደኛው ብዙ የተቆራረጠና የተደላለዘ ነበር። ነገር ግን በመጽሐፈ ሕዝቅኤል ገለጻ ታላቅ ቦታ ያለውን “ሥዕለ ኤስከዴሬ” እና ትርጉሙን የያዘ አንድ ጥራዝ ስላገኙ ልክ የተቀበረ ሳጥን እንዳገኘ ሰው በመደሰት ጥራዙን በሞላ ገለበጡት። ይህ የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ፍለጋ ጉዞ ወደሚቀጥለው የሕይወታቸው ምዕራፍ ይወስደናል።

.

 ስደት (1867-1878)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራናን በማሰስ ላይ እንዳሉ የታላቁ ሊቅ የአለቃ ወልደአብ መጻሕፍት በከረን እንደሚገኙ ይሰማሉ። በዚህም ምክንያት ለሚቀጥሉት አስራ አንድ ዓመታት መጠለያ ወደሚሆናቸው ወደ ምጽዋ እና ከረን ካቶሊክ ሚሽን (ቤተ አፍርንጅ) ያመራሉ።

ምጽዋ እና አካባቢዋ (“ቤተ አፍርንጅ” ከመሀል)

በከረንም ተስተካክለው የተጻፉ፣ ያልተቆረጡ፣ ያልተደለዙ ሁለት የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራናዎችን አገኙ። ብራናዎቹንም በኋላ ለሚሰሩት የሕዝቅኤል አንድምታ ዘር እንዲሆን እንዳለ ገለበጡ። (ይህንንም መጽሐፈ ሕዝቅኤል” ተማሪያቸው አለቃ ኪዳነ ወልድ አደራ ተቀብለው፣ የእብራይስጡንም ዘር አካተው በ1916 ዓ.ም ያትሙታል)

አለቃ ኪዳነ ወልድ ግን ለመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ስደት ሌላም ምክንያት ያቀርባሉ። መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስመግቢያ ላይ ስለዚሁ ምክንያት ባጭሩ ጽፈው ነበር። ነገር ግን በ1948 ዓ.ም. መጽሐፉ ሲታተም አሳታሚው ደስታ ተክለወልድ ባልታወቀ ምክንያት ከመጽሐፉ አስቀርተውታል። ጽሑፉ እንዲህ ይል ነበር፤

“… የስደታቸውም ምክንያት ባጭር ቃል ይህ ነው። … ፬ኛው ሐፄ ዮሐንስ … መምህር ክፍሌንም እንደ ዋልድቤ እንግዳና እንደ ዙራንቤ እንግዳ እንደ መምህር ተክለ አልፋ ምላሳቸውን ለመቁረጥ፣ ለማሰር፣ ለመግረፍ፣ ወይም በጭራሽ ለመሰየፍ በግር በጥፍር ያስፈልጓቸው ነበሩና፤ በዚህ ምክንያት፣ ‘ከመሞት ይሻላል መሰንበት’፣ ‘ከመታሰር ይሻላል ማስተማር’ ብለው ምጽዋዕ ገብተው ከዚያ ሳይወጡ ፫ ዓመት ያህል ኑረዋል።”

እንግዲህ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት፣ አፄ ዮሐንስ ግንቦት 1870 ዓ.ም. ባካሄዱት የቦሩ ሜዳ የሃይማኖት ጉባኤ የ“ጸጋ ልጆች” ከተሸነፉም በኋላ፣ ንጉሡ የ“ጸጋ” አስተሳሰብን ተከታዮች (የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጓደኛን መምህር ተክለ ጽዮንን ጨምሮ) ያሳድዱ ስለነበር ከዚህ አደጋ ለማምለጥ መምህር ክፍሌ ወደ ምጽዋ ተሰደዱ።

ባለቅኔውም ተክለ ጽዮን የሁለቱን ጓደኛሞች የስደት ዕጣ በግእዝ መወድስ ቅኔ ዘግበው ነበር (ቅኔው ከነአማርኛ ትርጉሙ እነሆ)፤

በሰሚዐ ቃሉ ለሳውል ቢጸ ኤርምያስ 

ሠለስተ ዓመተ ኢነትገ አንብዕነ 

ለዝኒ ብካይ ሀገረ ሳውል ኢኮነ

ነግደ ወፈላሴ  

እስመ ሰብአ ቤቱ ለብካይ ንሕነ

ቀዳሚ ኀበ ለመድነ 

በላዕለ ትካዝ ትካዘ ወበላዕለ ሐዘን ሐዘነ  

ሶበሂ ተዘከርናሃ ለደብረ ሊባኖስ እምነ 

ህየ ውስተ አፍላጋ ነበርነ ወበከይነ 

እስመ ማየ ዕድሜነ ኀልቀ ከመ ንዘረው ኵልነ

መንፈቅነ በምሥራቅ እንዘ በምዕራብ መንፈቅነ።

.

“የኤርምያስ ጓደኛ የሆነው የጳውሎስን ቃል በመስማት፤

ሶስት ዘመን እንባችን አልጎደለም፤

ለዚህም ልቅሶ የጳውሎስ አገር እንግዳ አልሆነንም፤

የልቅሶ ቤተሰቦች ነንና፤

በትካዜ ላይ ትካዜን፣ በሐዘንም ላይ ሐዘንን ቀድሞ ከለመድን ዘንድ።

እናታችን ደብረ ሊባኖስንም በአሰብናት ጊዜ፤

በዚያ በወንዞች ተቀመጥንና አለቀስን፤

እኩላችን በምዕራብ እኩላችንም በምሥራቅ፤

ሁላችን እንድንበተን እድሜያችን አልቋልና።”

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም በምጽዋ ከአቡነ ዮሴፍ ሳሉ ከረን በሚገኘው የካቶሊክ ሚስዮን የግእዝ መምህር እንዲሆኑ ይጠየቃሉ። በሀሳቡም ከተስማሙ በኋላ ኢየሩሳሌምን ተሳልመው ሲመለሱ ከረን ማስተማር ይጀምራሉ። በከረንም ቆይታቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከማስተማር በተጨማሪ የተለያዩ መጻሕፍት ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ነበሩ።

በመጀመሪያ ያዘጋጁት መጽሐፍ የአባ ገብረ ሚካኤልን መጽሐፈ ሰዋስው ነበር። ከጥር 1871 እስከ ታኅሣሥ 1872 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከላዛሪስት ሚስዮን ማተሚያ ቤት የወጣው ይህ መጽሐፍ ስድስት ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው ክፍል “የርባታ ዓመል” ሲሆን (በአሁኑ ጊዜ ‘ርባ ቅምር’ ከምንለው ጋር ይቀራረባል) የተለያዩ የሰዋስው ደንቦችን ያስተምራል።

ሁለተኛው ክፍል “ሰዋስውና ቅጽል” ሲሆን ሰምና ወርቅ፣ ባለቤትና ዘርፍ፣ ቅጽል … የመሳሰሉትን ይዳስሳል። ሦስተኛው ክፍል “ዐቢይ አገባብ” (የግስ አገባብ ባሕርይ)፣ አራተኛውና አምስተኛ ክፍል ደግሞ “ንኡስ አገባብ” እና “ደቂቅ አገባብ” (የስሞች አገባብ ባሕርይ) ያቀርባሉ። ስድስተኛው ክፍል ስለ “አኃዝ” (ቁጥር) ካስረዳ በኋላ በመጨረሻ “አእመረ” እና “ይቤ” የተሰኙት የግእዝ ግሶችን እርባታ ያቀርባል። ይህ መጽሐፍ የአባ ገብረ ሚካኤልን ብቻ ሳይሆን የመምህር ክፍሌንም የግእዝ ሰዋስው እውቀት የሚያሳይ ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታትም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከካቶሊኩ ሚስዮናዊ ኩልቦ (Jean-Baptiste Coulbeaux) ጋር በመሆን በ1876 ዓ.ም ኢሚታስዮ – ክርስቶስን ስለ መምሰል፣ በ1880 ዓ.ም ደግሞ ትምህርተ ክርስትያን” የተሰኙ ድርሰቶችን ከላቲንና ጣሊያንኛ ወደ አማርኛ ተርጉመው በሚስዮኑ ማተሚያ ቤት አሳትመዋል። እንዲሁም በ1878 ዓ.ም. ያዘጋጁት መዝሙረ ዳዊት በከረን ታትሟል።

በቦሩ ሜዳ በጉባኤ ላይ በንጉሡ ዳኝነት ተረተው የተሰደዱትን “የጸጋ ልጆች” አስተሳሰብ መምህር ክፍሌ በ1875 ዓ.ም ሃይማኖተ ቅድስት ሥላሴ በሚል ርእስ አዘጋጁ። የረቂቁ የመጀመሪያ ሦስት ምዕራፎች የራሳቸውን የ“ጸጋ ልጆች” ቡድን አስተሳሰብ ሲያቀርብ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ የተቃዋሚዎቻቸውን “ካሮች” እና “ቅብዐቶች” አስተሳሰብ ያቀርባል።

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም ከከረን እና ምጽዋ አስራ አንድ ዓመታት ቆይታቸው በኋላ፣ ከሚስዮኑ አለቃ ከአባ ተክለሃይማኖት ጋር ብዙም ባለመስማማትና “ሮሜን ለማየት” ወደ ጣሊያን አገር ወደ ሮማ አመሩ።

.

ሕር ማዶ (1878 – 1889)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ሮም እንደደረሱ ቫቲካን (Vatican) ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ግእዝ ማስተማር ጀመሩ። በዚህም ወቅት ምጽዋ እና ከረን ሳሉ የጀመሩትን የሮማይስጥ (Latin) ቋንቋ ጥናት በማጠናከር ቀጠሉ። በቆይታቸውም ዘመን ከጣሊያኑ የቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ሊቅ ጒዲ (Ignazio Guidi) ጋር ይተዋወቃሉ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ኪዳነ ወልድ እንደተናገሩት፣

“ሮሜ ሄጄ ከፈረንጅ ሊቃውንት ሁሉ በእውቀት የሚበልጥ፣ የጽርዕ (Greek) እና እብራይስጥ (Hebrew)፣ እንዲሁም ሱርስት (Syriac) እና ዓረብ ዐዋቂ ሰው አገኘሁ። ይህም ሰው፣ ‘ኢትዮጵያዊ ሊቅ ሆይ! ግእዝና አማርኛ አስተምረኝ፣ እኔም የፈለግከውን አስተምርሃለሁ’ አለኝ።”

ይህም ትውውቅ ሁለቱ ሊቃውንት እርስ በርስ እንዲማማሩና ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ምሁራን ይከብድ የነበረውን የአማርኛ ጽሑፎችን ጥናት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እርዳታ ጒዲ ሊካንበት አስችሏል። ጒዲ በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እገዛ ካሳተማቸው ሥራዎቹ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ምሳሌዎች፣ ግጥሞች እና ተረቶች የተሰኘው ነው። ሌሎች በእሳቸው እገዛ ከወጡት ሥራዎች መካከል፣ የነገሥታት ግጥምመርሐ ዕዉርየኢትዮጵያ ቅኔዎችፍትሐ ነገሥት እና እንደዋና ሥራው የሚቆጠረውን “የአማርኛ-ጣሊያንኛ መዝገበ ቃላት መጥቀስ ይቻላል።

.

 መጨረሻ (1889 – 1900)

ከአስራ አንድ ዓመታት የጣሊያን ቆይታም በኋላ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ወደ ኢየሩሳሌም አመሩ። ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ዕድሜያቸው ሰባዎቹ ላይ ደርሶ ስለነበር ፍላጎታቸው የሕይወታቸውን የመጨረሻ ዓመታት በጸሎትና በጥናት ለማሳለፍ ነበር። እዛም ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን ለማካፈል ቢሞክሩም፣ ጥናትና ምርምር ላይ መስራት የሚፈልግ ሊያገኙ አልቻሉም።

ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ከሳቸው ጋር ለመስራት ችሎታና ፍላጎትም ከነበረው ከወጣቱ ኪዳነ ወልድ ጋር ይገናኛሉ። የሁለቱ መገናኘትም ያስገኘልን ትልቁ ነገር የ1948ቱ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘው የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ነው።

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ደስታ ተክለ ወልድ

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በኢየሩሳሌም አስራ አንድ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ጳጕሜ 3፣ 1900 ዓ.ም በሰማንያ ሦስት ዓመታቸው አረፉ። ከአንኮበር ጓደኛቸው ከባለቅኔው ተክለጽዮን አጠገብም ተቀበሩ።

.

(በክፍል 2 ይቀጥላል)

ኅሩይ አብዱ

ሚያዝያ 2009

 .

ምንጮች

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪወክ) – መዝገበ ቃላት – መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ አዲስ አበባ 1948 ዓ.ም ገጽ 7-8

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪወክ) – ሃይማኖተ አበው ቀደምት ውስተ Berhanou Abebbe (ed.) – Kidana Wald Kéfle, ሃይማኖተ አበው ቀደምት La foi des pères anciens, 1. Texte éthiopien. Enseignement de Mamher Kefla Giyorgis …, Stuttgart 1986 ገጽ 268-274

ሮጀር ካውሊ Roger Cowley, “A Geez Prologue concerning the Work of Mämhér Kéfla Giyorgis on the Text and Interpretation of the Book of Ezekiel”, ውስተ A STANISLAV SEGERT – ANDRAs J.E. BOOROGLIGETI (eds.), Ethiopian Studies: Dedicated to Wolf Leslau on the Occasion of his Seventy-Fifth Birthday, November 14th, 1981, by Friends and Colleagues, Wiesbaden 1983. ገጽ 99–114

ብርሃኑ አበበ – Berhanou Abebbe (ed.) – Kidana Wald Kéfle, ሃይማኖተ አበው ቀደምት La foi des pères anciens, 1. Texte éthiopien. Enseignement de Mamher Kefla Giyorgis …, Stuttgart 1986 ገጽ 7-17

ቮልክ እና ኖስኒትሲን – Ewa Wolk and Denis Nosnitsin, “Kéflä Giyorgis” ውስተ Encyclopaedia Aethiopica ቅጽ 3 ገጽ 370-371 

“እንዳለጌታ ከበደ” (ቃለመጠይቅ)

ቆይታ ከእንዳለጌታ ከበደ ጋር

(ከታኅሣሥ 1998 ዓ.ም እትማችን የተወሰደ)

.

ባለፉት አመታት ከደመቁት የስነጽሑፍ ኮከባት መሀል ወልቂጤ ያፈራችው እንዳለጌታ ከበደ አንዱ ነው። በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ፣ በ”እፍታ” እና “ክንፋም ህልሞች” መድበሎች ካቀረበው ሥራዎቹ ሌላ በ1996 ዓ.ም “ከጥቁር ሰማይ ሥር” እንዲሁም በ1998 “ዛጎል” የተሰኘ ረጅም ልብወለድን አቅርቦልናል። እንዳለጌታን በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በስልክ አግኝተነው ነበር።

እንዴትወደስነጽሑፍአለምገባህ? ከየትስጀመርክ?

ለመጀመሪያ ጊዜ ግጥም የጻፍኩት ሰባተኛ ክፍል እያለሁ ነው። አንድ ጓደኛችን ግጥም መድረክ ላይ አቀረበ። እና ያኔ ተጨበጨበለት፤ በጣም ሙገሳ በዛለት። እኔ ደግሞ ያቺ ግጥም ከጋዜጣ እንደተወሰደች አውቃለሁና እንዴት ባልሰራው ስራ የኔ ነው እያለ ጉራውን ይቸረችርብናል ብዬ ተናደድኩ። ጓደኞቼ ደግሞ “ታዲያ በዚህ እድሜው ከየት ሊያመጣ ይችላል፤ ከባድ እኮ ነው” ብለው መልሰው እኔን ተቆጡኝ። እኔም ይህን ያህል ከባድ አይደለም ብዬ አንድ ግጥም ጽፌ ለመምህሩ ሰጠሁ። መምህሩ ግን ከድርሰቱ ይልቅ የወደደው እጅ ጽሑፌን ነበር። ቢሆንም አበረታቶኝ ለወላጆች ቀን ዝግጅት አቀረብኩት።

እንዲሁም ቤት የምሰማውን ተረትና ታሪክ ቀይሬ አሻሽዬ ለሰው አወራ ነበር። አሁን ሳስበው ወደ ድርሰት ማዘንበሉ ያኔ የተጀመረ ይመስለኛል። ቤተ ክርስቲያንም አካባቢ እሄድ ስለነበር የቅዱሳን ገድልና ታሪካዊ ነገሮች አነብ ነበር – በተለይ ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ የሚያሳትሟቸውን። የጸሎት መጽሐፎቹ ግን የዛን የአራተኛ ክፍል ያለሁበትን ምኞቴን አልያዙም ነበር። ያኔ ምኞቴ በትምህርቴ በጣም ጎብዤ አባቴን ማስደሰት ነበር። የጸሎት መጽሐፎቹ ግን የሚሉት ጳጳሱን ባርክ እንዲያ የመሳሰለውን ነው። በልጅነት አእምሮዬ የጳጳሱ መባረክ ጥቅሙ ሰላልገባኝ ትናንሽ የጸሎት መጽሐፎች እጽፍ ጀመር – እኔ መሆን የምፈልገውን ቤተሰቦች ከኔ የሚጠብቁትን። “እግዚአብሔርዬ ከተማሪዎች ሁሉ የተሻለ ውጤት እንዲኖረኝ አባቴም በኔ ደስ እንዲለው አድርግልኝ” እያልኩ እጽፍ ነበር። ከዛም ቀስ በቀስ ወደ ልብወለድ ንባብ ገባሁ።

የትኞቹንየልብወለድጽሑፎችታነብነበር?

መጀመሪያ ያነበብኩት “ሽልንጌን” የሚል አማርኛ መጽሐፋችን ውስጥ የሚገኝ አጭር ልብወለድ ነበር። ከዛም ሳንቲም ሳገኝ – ያኔ መጽሐፎች 3.50 ወይም 4.50 ያወጡ ነበርና – ያገኘሁትን ሳላማርጥ አነብ ነበር። መጀመሪያ በጣም የወደድኩት አጭር ልብወለድ የስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን “አምስት ስድስት ሰባት” ነበር። እሱ ግን ታዋቂ መሆኑን ያወቅኩት አስረኛ ክፍል እያለሁ የአማርኛ መምህራችን ከታዋቂ ደራሲዎች አንዱ ስብሐት ነው ብሎ ሲነግረን ነው። ያኔ መምህሩ እኔ የምወደውን ደራሲ ሰላደነቀልኝ በጣም ደስ አለኝ። ቀጥሎም ወደእነ በዓሉ ግርማ …

ያኔበአካባቢህየስነጽሑፍክበብነበር?

እኔ ተወልጄ ያደግኩት ወልቂጤ ነው። እና ያኔ እንኳን ላይብረሪ ይቅርና መጽሐፍ መሸጫ መደብሮች  አልነበሩም። በየስንት ወሩ አንዴ ብቅ የሚል እየዞረ የሚሸጥ አንድ ሰው ነበር። እና ከሱ ነበር መጽሐፍ የምንገዛው። ታዲያ ሰው ቤት ስሄድ የመጀመሪያ ትኩረቴ መደርደሪያዎችን ማየት ነበር። ከዛም ካላነብኳቸው መጽሐፎች አንዱን መርጨ አነብ ነበር። በማንበብ ረሀብ ውስጥ ሰላደግኩ ነው መሰለኝ፣ ቆይ ሳድግ ትንሽም ቢሆን ቤተ መጻሕፍት እከፍታለሁ የሚል ስሜት ነበረኝ። አስራ ሁለተኛ ክፍል ስጨርስም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባ ነጥብ አልነበረኝም። እና ያኔ ትንሽዬ ክፍል ውስጥ መጽሐፎቼን አሰባስቤ ማከራየት ጀመርኩ – ለ24 ሰአት 25 ሳንቲም። እዛም ብዙ ሰዎች – ተማሪዎች መምህራን – ይመጣሉ፤ መወያየት ጀመርን። ከዛም “ተስፋ ቡክ ክለብን” ከፈትን፤ የስነጽሑፍ ሰዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም የቀለም ተማሪዎችን የሚያግዝ አንዳንድ ስራዎችን መስራት ላይ አተኩረን ነበር።

ወደአዲስአበባእንዴትመጣህ?

መጽሐፍ በማከራየት የሰበሰብኩትን ገንዘብ ይዤ ዕቁብ በመግባት አንድ ሶስት ሺ ብር ሲሞላ ወደ አዲስ አበባ ተጓዝኩ። ፍላጎቴ ስነጽሑፍ መማር ቢሆንም ይህን ዘርፍ የሚያስተምር የግል ተቋም ሰላልነበረ ዩኒቲ ኮሌጅ በመግባት ጆርናሊዝም እና ኮምዩኒኬሽን ተማርኩ።

የመጀመሪያመጽሐፍህስ?

መጀመሪያ ገንዘብ ስሰበስብ መማር ላይ አተኮርኩ። ቀጥሎ ደግሞ ወልቂጤ የነበረውን ስራ ወንድሞቼ ያግዙኝ ነበረ እና ገንዘቡ ሲጠራቀም የኔን ስም የያዘ መጽሐፍ ለማሳተም የነበረኝን ፍላጎት እውን ለማድረግ አሰብኩ። አንዳንድ አጫጭር ልብወለዶቼ ከዚህ በፊት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ወጥተው ነበር፤ ጓደኞቼ እንዲሁም የማከብራቸው ሰዎች ጥሩ አስተያየት ሰጥተውኝ ነበር። ነገር ግን እነዚህ አጫጭር ልብወለዶች ተሰባስበው አንድ የራሴ የሆነ ቀለም ማሳየት እፈልግ ነበር። እንዴት እንደማስብ ማሳየት እፈልግ ነበር። መጀመሪያ ግጥም ለማሳተም አሰብኩ። ያኔ ግን ብዙ ገጣሚዎች ስራዎቻቸውን ለንባብ ያበቁበት ጊዜ ነበረና አይ አጫጭር ልብወለድ ቢታተም በአመት አንዴ ነውና ለምን የኔዎቹን ሰብስቤ አላሳትማቸውም ብዬ አሰብኩ። ከዚህ በፊት ለንባብ ከበቁትና ከአዳዲሶቹም ጨምሬ አሥራ ስድስቱን አብሬ አሳተምኩ። “ከጥቁር ሰማይ ሥር”ንም ለማሳተም የፈጀብኝ 12 ሺ ብር ነው። ግማሹን ከኔ ግማሹን ተበድሬ።

ምንያህልኮፒአሳተምክ?

ሶስት ሺ። ሰዎች፣ እኔም ጭምር፣ አይሸጥም ብለን ፈርተን ነበር። መጀመሪያ የተበደርኩትን ገንዘብ ካስመለስኩ ጥሩ ይሆናል ብዬ አሰብኩ፤ ከዛም ካልከሰርኩ ጥሩ ነው አልኩ። ቀስ በቀስ ጋዜጦች ሰለመድበሉ መጻፍ ሲጀምሩ እንዲሁም ሰው ሲነጋገርበት ስመለከት አይ ትንሽ እንኳን ማትረፍ ብችል ማለት ጀመርኩ። አሁን መጽሐፉ ከወጣ ሁለት ዓመት አልፎታል። እና ገበያ ላይ አለ ማለት ያስቸግራል። ባለፈው አንድ ሱቅ ውስጥ ሁለት ሶስት አይቼ እራሴ ገዛኋቸው። እና አሁን አብዛኛው ጸሐፊ አንድ ወይም ሁለት ሺ በሚያሳትምበት ጊዜ ሶስት ሺ ማሳተሜ ብዙ ቢመስልም ከሰባ ሚልዮን ህዝብ በላይ ባለበት ሀገር እንዲህ መሆኑ ንባብ በጣም ማሽቆልቆሉን ያሳያል።

ከጥቁርሰማይሥርዋጋውአስርብርነው።ለመሆኑየአከፋፋዮቹድርሻእንዴትነው?

አከፋፋዮቹ 30 ከመቶ ያገኛሉ። የሽፋን ስዕሉንና Layout ለማሰራት፣ ታይፕ ለማስደረግ፣ እንዲሁም ለማሳተም ለእያንዳንዱ መጽሐፍ 4 ብር ወጥቷል። አከፋፋዮቹ ደግሞ 3 ብር ያገኛሉ። እኔ ደግሞ ለሰዎች በነፃ የሰጠሁትን እንዲሁም የተበላሹትን ኮፒዎች አስበህ ከእያንዳንዱ መጽሐፍ 2.80 አገኛለሁ።

በአንድጋዜጣላይምኞትህአንድአገራዊድርሰትበሚልዮንኮፒእንዲታተምመሆኑንገልጸህነበር።እዛለመድረስምንማድረግያስፈልጋል?

ምን መሰለህ! ብዙ ሰዎች መጽሐፍ የሚያነቡት በሌላው ጎትጓችነት ነው። በአሁኑ ሰዓት መጽሐፎች ውድ ናቸውና “ሳንቲሜን አውጥቼ ከገዛሁ በኋላ የፈለኩትን ያህል ደስታ ባላገኝበትስ? ዝም ብሎ እንቶ ፈንቶ ቢሆንስ?” የሚል አስተያየት አለ። አንዳንዶች “ለመሆኑ በአሁኑ ዘመን ጥሩ ደራሲ አለ ወይ?” ይላሉ። እናም በዚህ ጥርጣሬ አይገዛም ማለት ነው። የሰዉን ስሜት ስመለከት መምህሩ አንብቡ ያላቸውን መጽሐፍ ውለው ሳያድሩ ያነባሉ። ምክንያቱም ካላነበቡ የሚጎድልባቸው እንዳለ ሰለሚያውቁ ነው።

ሁለተኛ ደግሞ ያሉን የቤተ መጻሕፍት ቁጥር ብዛታቸው ስንት ነው ብንል መልሱ ያሳዝነናል። መጽሐፍ ሻጮችንም የሚያበረታታ አካል የለንም። ከሚልዮን በላይ ኮፒ ቢታተም ደስ ይለኛል ያልኩት ከምን አንጻር ነው ቢባል? እንግዲህ የህዝቡን ብዛት አስብ! በየጊዜው ደግሞ የመኃይማኑ ቁጥር ቀንሷል ነው የሚባለው። ይህን ህልም እውን ለማድረግ የንባብንና የውይይት ክበቦችን ማብዛት የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። ምክንያቱም ብዙዎቹ ያነቡና የሚያዋራቸው ሰው የለም። የሚያወያያቸው ሰውም የለም። በአሁኑ ሰዓት  የአንባቢው ቁጥር አንሷል ማለት አስቸጋሪ ነው። ሰዉ ወደ ጋዜጣና መጽሔት፣ የዕለት ተዕለት ወደሆነ ኑሮ የሚያተኩሩ ዜናዎችን ለማንበብ ነው የሚረባረበው። መንግሥት በየቀበሌው ካሉት የመዝናኛ ማዕከሎች መሐል የተወሰኑትን ለንባብ አገልግሎት እንዲውሉ ቢያደርግ የአንባብያንን ቁጥር ማብዛት ይቻላል። ምክንያቱም ወመዘክር ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብትሄድ ሰልፉ ሌላ ነው። እንኳንስ ቁጭ ብለህ ልታነብባቸው ይቅርና ሰው በዝቶባቸው የማይመቹ ቦታዎች ሆነዋል።

ከደራሲው ብዙ የሚጠበቅ አይመስለኝም – ማለት እንዲነበብለት። የውይይትና የንባብ ክበባት ይህንን ነገር ማጉላትና ማራመድ ይችላሉ። በመገናኛ ብዙኃን የጥበባት ፕሮግራምም አዳዲስ መጻሕፍት ሲወጡ በማስተዋወቅ የአንባብያን ቁጥር እንዲበዛ ማድረግ ይቻላል። የቴሌቪዥን ሚዲያ ስናይ የስዕል ኤግዚቢሽን ሲከፈት ሮጠው ያቀርባሉ። ጥሩ ነው ደስ ይላል። ደራሲያን መጽሐፍ በሚያስመርቁበት ሰዓት ግን ብዙ አይመጡም። አንባቢንና ድርሰትን ለማገናኘት የሚያደርጉት ጥረት የደከመ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። እነዚህ ሁሉ ድክመቶች መቀረፍ ቢችሉ በተወሰነ መንገድ የአንባብያንን ቁጥር ማብዛት እንደሚቻል አስባለሁ።

ሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም አንድ ዝግጅት ላይ ጥናት አቅርበው በደርግ ዘመን ብዙ አንባቢዎች ነበሩ ብለዋል። ለምሳሌ የሲሳይ ንጉሡ “ሰመመን” 70-80 ሺ ኮፒ ታትሞ ተሽጧል። አሁን ግን ደራሲዎች የሚያሳትሟቸው መጽሐፎች ከ5 ሺ ኮፒ ብዙም ፈቀቅ አይሉም። ለምንድነው? አስበው እንግዲህ የህዝብ ቁጥር ጨምሯል። ነገር ግን የአንባቢያን ቁጥር እየቀነሰ ነው። ያኔ ጎትጓች ነበረው። ያሁኑ ያህል ጋዜጦች አልነበሩም። ሚዲያ አልነበረም፤ ኢንተርኔት ጊዜን አያጣብብም ነበር። ሲኒማዎችም አልተበራከቱም። አቶ ሣህለሥላሴ ሲናገሩ ያኔ ጋዜጦች “ወታደሩ ሰለማያነብ ንቃተ ህሊናው አልዳበረም” እያሉ ይወርፉ ነበር። ወታደሩም እኛ ነን ወይ የማናነበው፤ እኛ ነን ወይ ንቃተ ህሊናችን ያልዳበረው በማለት መጽሐፍ ይገዛ ነበር። ይላክለትም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ወታደሩ እንዲያነብ ግፊት ስለሌለው የተወሰነ አንባቢዎችን አጥተናል ሲሉ ሰምቻለሁ።

አንተ፣ በዕውቀቱሥዩምናአማኑኤልመሃሪስትረዳዱይታያል።ከጥቁርሰማይስርውስጥያሉትንስዕሎችየሳለውምበዕውቀቱነው።የደራሲዎችመተባበርናአብሮመስራትንእንዴትታየዋለህ ?

አብሮ መስራት ስራውን የተሸለ ለማድረግ ምንም ጥርጥር በሌለው መልክ ያግዛል። ለምሳሌ በዕውቀቱ “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” የሚለውን መጽሐፉን ከማውጣቱ በፊት አንዳንድ ግጥሞቹን እንዲያወጣ መክረነው ሀሳባችንን ተቀብሏል። ይህ ትውልድ ውስጥ መንፈሳዊ የሆነ ስሜት አለ። እርስ በእርስ የመተጋገዝ ነገር አለ። ከሶስተኛው መጽሐፌ ቀደም ብሎ በዕውቀቱ መጽሐፍ ቢያወጣ ደስ ይለኛል። ሙሉ ትኩረታችንንም እዛ ላይ አድርገን ብንሰራም በጣም ደስ ይለኛል። ምክንያቱም እሱ የሚጽፋቸውን ነገሮች እወዳቸዋለሁ። የኔ መጽሐፎችንም ሳሳትም በዕውቀቱ የራሱ የሆነ እገዛዎች ነበሩት፤ አብዛኛዎቹን ሀሳቦቹን ተቀብያቸዋለሁ። ሰለዚህ የምጽፈው ጽሑፍ ወደ ህዝብ እንዲደርስ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በእኛ መሀከል መተጋገዙ ጥሩ ነገር ለህዝብ ለማቅረብ ከመጓጓት ስሜት ነው። ፍቅርህን የምትገልጸው የምትወደውን ነገር የሚወዱ ሰዎች በማብዛት ነው። እኔና ጓደኞቼ ጥበብን እንወዳለን። ኪነትም የተለየ ስሜት ይሰጠናል። በጣም ጥሩ ነገር ስናዘጋጅ እንቀባበላለን። ለምን ይሄ ነገር ጋዜጣ ላይ አይወጣም እንላለን። የህብረት መዝሙር ላይ ከሚሳተፉ ሰዎች መሃል እንደ አንዱ ነን። እያንዳንዱ ዘማሪ የራሱ የሆነ ድምጽ አለው። በሁሉም ባንመሳሰልም አንድ ላይ ስንደረደር ግን እራሱን የቻለ ጥዑመ ዜማ ሊወጣ እንደሚችል እንገምታለን። መተባበራችን እገዛ እንደሚያደርግ እገምታለሁ። ቢያንስ ቅንነትን ለተተኪው ትውልድ ማሳየት ነው።

እናመሰግናለን።

አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ”

“ቪላ አልፋ” አዲሱ መልክ

ከበዓሉ ግርማ

(1961 ዓ.ም)

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገውን፣ በመደረግ ላይ ያለውንና ወደፊት የሚደረገውን ሁሉ እንደመጠጥ ብርጭቆ አንስተው የማስቀመጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከተሜዎች አሉ። ሰሞኑንም ከሰላምታ በኋላ አርዕስተ ነገር አድርገው የያዙት ትችት ቢኖር ስለ አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጐድጓድ) አዲሱ የቪላ አልፋ መልክ ነው።

ትችቱ እንደተቺዎቹ የበዛ ቢሆንም አንዳንዶቹ፣

“ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ (በተለይ የፍሮይድን ሳይኮሎጂ ከእጅ ጣታቸው እንደዋዛ የሚያንቆረቁሩት ተቺዎች) የዚህን ዓለም ጉዳይ ወደጎን ብለው፣

“አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ።

“ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነገር ነው” የሚሉም አሉ።

ያም ሆነ ይህ የነቀፌታዎቹ መነሾ ሠዓሊው አፈወርቅ ቪላ በመሥራቱ አይደለም። ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን የገነቡት በሰው አፍ አልገቡም። በግል መኖሪያቸው የሰማኒያና የመቶ ሺህ ብር ዘመናይ ቪላዎችን የሠሩት ዓይን አልበላቸውም።

“ታዲያ የአፈወርቅ ስም እንደ ትኩስ ድንች እያንዳንዱ አፍ ውስጥ የሚገላበጥበት ምክንያት ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።

ጐንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነው ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው።

የዚህ አይነት ቤት (ወይም ካስል) በመሥራት አፈወርቅ በዘመናችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ቤቱን የቀየሰው መሐንዲስ G. Boscarino እንዳለው፤

“እንዲህ ያለው ቤት ውስጥ ከአፈወርቅ በስተቀር ሌላ ሰው ቢኖርበት፣ ቤቱ አሁን ያለውን ዋጋና ጥቅም ሊሰጥ አይችልም”።

አዎን፣ ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ የመሰለውን ቤት አልሞ የሚሰራ የለም። የሚሰጠውን ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱው ብቻ ነው።

እንዲህ የመሰለውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ምን እንዳሳሰበው፣ ከተሰራ በኋላ የሚሰጠውንም ጥቅም እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበር። ለማናገር ፈቃደኛ ቢሆንም ጊዜ አልነበረውም።

አናጢዎቹ በየደቂቃው ይጠሩታል።

በተመለሰ ቁጥር “የአገራችን አናጢዎች ለምን አንድ መስመር በትክክል ለመሥራት አይችሉም?” በማለት ይገረም ነበር።

እነሱም በበኩላቸው እሱ አሁን በቅርብ ጊዜ የሠራውን የእንሥራ ተሸካሚ ሥዕል፤ በተለይ ወተት መስሎ በጃኖ ጥለት የታጠረውን ቀሚሷን፣ አለንጋ የመሳሰሉትን ጣቶቿንና ሕልም መሳይ ውበቷን አይተው መገረማቸው አልቀረም።

ገና ተመልሶ ቁጭ ከማለቱም ቀለም ቀቢዎች ይጠሩታል።

አዎን፣ “የሰሜን ተራራ” የተባለውን ሥዕል (ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ሰላም የሚፈጥረውን) የሠራ ሰው ለተራ ቀለም ቀቢዎች ችሎታ ልዩ አድናቆት ሊኖረው አይችልም።

አሁንስ አፈወርቅን የሚጠራው ሰው የለም ብዬ በመተማመን ጥያቄዬን ወርውሬ፣ ብዕሬን ከወረቀት ለማገናኘት ስቃጣ፣ አንድ ጽጌረዳ አበባ የት እንደሚተክሉ የቸገራቸው፣ ወይም አበባ የያዘውን ሳጥን የት እንደሚያስቀምጡ ግራ የገባቸው ለምክር ይጠሩታል። ሳያማክሩት ያስቀመጡት፣ ወይም የተከሉት እንደሆነ ኋላ ማንሳታቸው አይቀርም።

አፈወርቅ ደጋግሞ እንደሚለው፣

“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው”።

ሠራተኞቹም ደከሙ። ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ያራውጣቸው ነበር።

ጥሪው እያነሰ ሄደ። ቁጭ ለማለት ቻልን።

“ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊው የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል” አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ።

በሁለት ወር ያልቃል ተብሎ የታሰበው ቤት አሁን አራተኛ ወሩን ሊጨርስ ነው። በአራት ወር ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕሎች ብቻ ነበር ለመሥራት የቻለው። የቀረውን ጊዜ ያዋለው በቤቱ ሥራ ላይ ነበር።

“ቪላ አልፋ” የተሠራው በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን ቤቱን ለመሥራት አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥቦ ነበር። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል።

ይሁንና በኔ በጠያቂው በኩል ሃያ ስድስት በሃያ ስድስት ሜትር ካሬ መሬት ላይ የተሠራው አዲሱ ቤት ይህን ያህል የሚያስደንቅ ወጭ የሚጠይቅ መስሎ አልታየኝም። አፈወርቅም ስንት ገንዘብ እንደጨረሰ ትክክለኛ ዋጋውን ሊገልጽልኝ አልፈቀደም።

ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስሎ ለመስራት ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽልኝ እንዲህ አለ፣

“ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም።”

አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው።

በቤቱ ውስጥ ያለ ምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው እሱ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። የቤቱ ቆርቆሮ ቀይ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። ቤቱ ነጭ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው።

አንድ ሥዕል አንድ ግድግዳ ላይ በአንድ በኩል እንዲሰቀል የተደረገበት ያለ ምክንያት አይደለም። ቤቱ የተሠራው ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ሌላ ምክንያት አለው። ቤቱም ቀለሙም አቀማመጡም – ሁሉም ባንድነት ተዋህደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው።

“ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ። የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ አውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር።”

“አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው።”

“ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ላንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትዕይንት ጠቃሚው ነው።”

አዎን፣ ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

ቤቱ አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው።

ሦስቱ መስኮቶች ሦስት አይነት ቀለማት የተቀቡበት ምክንያት አለው። የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንጸባርቁ ለማድረግ ነው።

የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው። እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሱም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው።

የምሥጢር በሩ ያለ ምክንያት አልተሠራም። አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው።

የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው።

አዎን፣ በአፈወርቅ ቤት ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

በዓሉ ግርማ

በዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – መነን (ሚያዝያ ፳፱፣ ፲፱፻፷፩)፤ ገጽ ፲፮-፲፯።

ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ

“ዳኛቸው ወርቁና መጽሐፎቹ”

በሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ማንኛውንም መጽሐፍ ገዝቼም ሆነ ተውሼ ከማንበቤ በፊት ማን እንደጻፈው፣ በኋላው አጎበር ምን እንደተጻፈ፣ መግቢያ ወይም መቅድም ካለው እዚያ ውስጥ ምን እንደተባለ፣ ማውጫ ካለውም በዚያ የሠፈረውን ገረፍ ገረፍ አድርጌ እመለከታለሁ።

ይህንን የማደርገው መጽሐፉን ከአጎበር እስከ አጎበር ማንበብ ከመጀመሬ በፊት “መነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው ወይንስ አይደለም?” የሚል ግምት ለመውሰድ ያህል ነው። አብዛኛውን ጊዜም ግምት ወስጄ በማነባቸው መጻሕፍት ከሞላ ጐደል እደሰታለሁ፤ የአእምሮ ብርሃን የሚሰጡ፣ ስለ ሕይወት ብዙ ነገር የሚያስተምሩ፣ የሚያዝናኑና የሚያስደስቱ ናቸው።

ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹን ብጠቅስ እወዳለሁ።

የሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” (1958)፣ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ” (1962)፣ የአፈወርቅ ገብረየሱስ “ልብወለድ ታሪክ [ጦቢያ]” (1900) እና “ዳግማዊ አጤ ምኒልክ” (1901)፣ የገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” (1916)፣ የአሰፋ ገብረማርያም “እንደወጣች ቀረች” (1946) … እና ሌሎችም።

ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የአገራችን ደራስያን የማውቃቸው በጽሑፎቻቸው አማካኝነት እንጂ በግንባር አይደለም። በግንባር ላያቸው ፍላጎት ቢኖረኝ ኖሮ እንኳ ባልተቻለኝም ነበር፤ እነሱ የኖሩበትና እኔ የምኖርበት ዘመን በጣም የተራራቁ በመሆናቸው።

ዳኛቸው ወርቁ ግን የዕድሜ አቻዬ በመሆኑና ሁለታችንም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመሆናችን እሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ብዙ ጊዜ የመገናኘትና የመጨዋወት ዕድል አጋጥሞናል።

የማልረሳው የመጀመሪያው ግንኙነታችንን ነበር።

ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ቀን፣ የቀድሞው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባልደረባዬና ወዳጄ የሆነውን ሰው ለመጠየቅ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እሄዳለሁ። ያ ወዳጄ በዚያን ሰዓት ከዳኛቸው ወርቁ ጋር ነበር፤ በቢሮው ውስጥ።

“እገሌ”፣ “እገሌ” ብሎ አስተዋወቀንና የ“አደፍርስ” ደራሲ መሆኑን ገለጸልኝ። “አደፍርስ” ስለሚባል መጽሐፍ ከዚያን ቀን በፊት ሰምቼ አላውቅም። ከታተመ አንድ አመት እንኳ የሞላው አይመስለኝም።

“በዚህ ርዕስ የሚታወቅ መጽሐፍ ካለ ምነው መጽሐፍ መሸጫ መደብር ውስጥ አይቼው አላውቅም?” ስል ጠየቅሁት ዳኛቸውን።

“ቀደም ብሎ እንኳ ከመጽሐፍ መሸጫ መደብር ይገኝ ነበር፤ አሁን ግን እኔ ዘንድ እንጂ ሌላ ቦታ አታገኘውም” አለኝ።

ሦስታችንም የመጻሕፍት አፍቃሪያን ስለነበርን ስለሥነጽሑፍና በጊዜው ታትመው ይወጡ ስለነበሩት መጻሕፍት ስንጨዋወት ቆየንና በመጨረሻም ዳኛቸውና እኔ ወዳጃችንን ተሰናብተን ወጣን።

“መጽሐፍህን ልገዛው እፈልግ ነበር። ነገር ግን እንዴት ነው የማገኘው?” አልኩት።

“ማግኘት እንኳ ታገኘዋለህ። ነገር ግን ዋጋው እንደቀድሞው አይደለም” አለኝ።

“ስንት ነው?” አልኩት።

“መጀመሪያ በአምስት ብር ነበር የሚሸጠው። ነገር ግን አልሄድ ስላለ አስር ብር አደረግሁት። አሁንም እንደገና አልሄድ አለ። ስለዚህ መሸጫ ዋጋውን አስራ አምስት ብር አድርጌዋለሁ” አለኝ።

ይህንን ስሰማ ሳቅ ወጥሮ ያዘኝ። ነገር ግን ከዚያ በፊት የማልተዋወቀውን ዳኛቸውን እንዳላስቀይመው በመፍራት ሳቄን ታግዬ አስቀረሁትና፣

“ለማንኛውም አንድ ኮፒ እፈልጋለሁ” አልኩት።

“እንግዲያውስ ተከተለኝ” ብሎኝ መኪናው ውስጥ ገባ። እኔም በያዝኩት መኪና ተከተልኩት።

በፒያሳ አድርገን አራት ኪሎ ስንደርስ ወደታች ተጠምዘን ወደ ምኒልክ ግቢ አቅጣጫ አመራን። እዚያ ሳንደርስ ከፓርላማ ወደ እሪ በከንቱ የሚያመራውን መንገድ አቋርጠን ትንሽ ከሄድን በኋላ ወደ ቀኝ ታጥፈን በጠባብ ኮረኮንች መንገድ ተጓዝን። ከዚያም በኋላ ከመኪናችን ወርደን በእግራችን ወደ መኖርያ ቤቱ አመራን።

ከጽሕፈት ቤቱ ስንገባ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ በብዙ ረድፍ የተደረደሩ የመጻሕፍት ክምር ይታያል። ሄድ ብሎ ከአንዱ እሽግ አንድ ኮፒ መዞ አወጣና “ይኸውልህ” አለኝ። ተቀብዬው፣ ሂሳቡንም ከፍዬ ተሰናብቼው ወጣሁ።

ዳኛቸው ወርቁ ልዩ ባህሪ ያለው ሰው መሆኑን ያን ቀን ነው የተረዳሁት።

ከዚያም በኋላ ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል፤ ተቀራርበናልም። እኔ እንደማውቀው በጣም ሰዓት አክባሪ ሰው ነበር። አንድ ቀን እቢሮው ተቃጠርንና ከዚያ ስሄድ እሱ ከቢሮው ወጥቶ ወደ መኪናው ሲያመራ አየሁና፤

“ዳኛቸው! ዳኛቸው!” ብዬ ተጣራሁና፤ “ምነው? እረሳህ እንዴ? ቀጠሮ ነበረንኮ!” አልኩት።

“ቀጠሮውንማ አፍርሰህብኝ ወደ ሌላ ጉዳዬ መሄዴ ነበር” አለኝ፤ መለስ ብሎ።

እጅግ በጣም ተገርሜ ሰዓቴን ብመለከት ያሳለፍኩት ጊዜ ሦስት ደቂቃ ብቻ ነበር!

በሌላ ቀንም ኩራዝ መጻሕፍት መደብር እንድንገናኝ ተቃጠርን። በቀነ ቀጠሮው ከዚያ ብሄድ ዳኛቸው የለም። አስራ አምስት ደቂቃ ያህል ጠበቅሁትና አለመምጣቱን ሳይ አንዳች እክል ቢያጋጥመው ነው እንጂ አይቀርም ነበር አልኩና ወደ ሌላ ጉዳዬ ሄድኩ።

ከዚያ በኋላ በሌላ ቀን በአጋጣሚ ስንገናኝ በቀጠሮአችን ቀን ለምን ሳይመጣ እንደቀረ ጠየቅሁት።

“እኔማ ከተቃጠርንበት መጻሕፍት መሸጫ መደብር ሄጄ ነበር። እንዲያውም ሰዓት አሳልፋለሁ ብዬ ስከንፍ መኪናዬን ገጨኋት። አንተ ግን በቀጠሮው ቦታ አልነበርክም” አለኝ።

“ኧረ እኔስ ከዚያ ነበርኩ! አንተ ነህ ቀጠሮ ያፈረስከው” አልኩት።

“ወደ የትኛው መደብር ነበር የሄድከው?”

“ኤንሪኮ ባር ፊት ለፊት ያለው … ቸርችል ጐዳና”

“አዬ! ለካስ ያልተግባባነው ከቦታው ኖሯል! እኔ ደሞ የሄድኩት አምስት ኪሎ ካለው መደብር ነው” አለኝና ሁለታችንም በሠራነው ስሕተት ተሳስቀን ተለያየን።

ዳኛቸውን ከሌሎች ሰዎች ለየት የሚያደርገው ሰዓት አክባሪነቱ ብቻ አልነበረም። እኔ እንደማውቀው እውነተኛ ሰው ሆኖ ተጠራጣሪም ነበር – “ሰውን ውደደው እንጂ አትመነው” እንደሚባለው አይነት!

የሆነ ሆኖ ወደ መጻሕፍት እናምራ።

“አደፍርስ” በርካታ ምሁራንን በሰፊው ያነታረከ መጽሐፍ ስለሆነ እኔም ተጨማሪ ንትርክ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለሁም። ስለምንነቱ ጥቂት ሳልል ግን ለማለፍ አይቻለኝም።

“አደፍርስ” በሌሎች ልብ ወለዶች የምናየው ዓይነት አንድ ወጥ የሆነና የጐለበተ ፈጠራ ታሪክ የለውም። በዚህ ፈንታ ቁርጥራጭ ትርኢቶች ነው የሚታዩበት።

ትረካውን ይፋትንና ጥሙጋን ከጣርማ በር ተራራ ላይ ሆነው ሲመለከቱት ምን እንደሚመስል የሙዚቃ ቃና ባለው ቋንቋ ይጀምራል፤

“ቁንዲ አንገቷን አስግጋ ቃፊርነት የቆመች መስላለች። የዓዋዲና የጀውሃ ጅረቶች ደረታቸውን ለፀሐይ ሰጥተው ይምቦገቦጋሉ። ሰማይና ምድር የተገናኘበት፣ ሕይወት ያሸለበችበት የሚመስለውን በስተግርጌ የሚታይ ሜዳ አቧራ ረግቶበታል … የይፋትና ጥሙጋ አውራጃን ጣርማበር ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከቱት እግዚአብሔር ዓለምን ሠርቶ ሲያበቃ የተረፈውን ትርክምክም ያጐረበት እቃ ቤቱ ይመስላል – ሸለቆው፣ ጉባው፣ ተራራው፣ ገመገሙ፣ ጭጋጉ፣ አቧራው ሕይወትን አፍኗት ተኝታለች – ያቺ በሌላው አገር የምትጣደፈው፣ የምትፍለቀለቀው፣ የምትምቦለቦለው ሕይወት እዚህ እፎይ ብላለች – በርጋታ፣ በዝግታ ታምማለች፤ በተገማሸረ መስክ ውስጥ እንደሚብሰከሰክ ውሃ …” (ገጽ ፭)

ገጠሩን በተዋበ ቋንቋ ከገለጸልን በኋላ ወ/ሮ አሰጋሽ የተባሉ የገጠር እመቤት ከጢሰኛቸው ጋር ቲያትር መሰል የንግግር ልውውጥ ሲያደርጉ ያሳየናል። ጢሰኛው የዘንጋዳ ዘር አጥቶ ሊበደር ወደ እመቤቱ ዘንድ መጥቶ ይለምናል። ወ/ሮ አሰጋሽ በተባ አንደበት የጢሰኛቸውን ሞራል አንኮታኩተው ከሰበሩት በኋላ ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ ሰጥተውት በመኸር ወራት አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይነግሩታል።

የ”አደፍርስ” ጀርባ ሥዕል (በታዬ ወልደ መድኅን)

አራጣው በጣም የበዛ መሆኑ በተሰበረ ድምፅ ይገልጽላቸውና እንዲራሩለት ይማጸናቸዋል። ወ/ሮ አሰጋሽ ግን በአራጣው ከተስማማ ዘጠኙን ቁና እንዲወስድ፣ አራጣው በዛ ካለም እንዲተወው ርህራሄ በሌለው አንደበት ቁርጥ አድርገው ይነግሩታል።

ሌላ ምርጫ ስለሌለው እመቤቱ ለሚሰጡት ዘጠኝ ቁና ዘንጋዳ አስራ አምስት ቁና እንዲመልስ ይስማማል። ወ/ሮ አሰጋሽም ይህንን ገፈፋ ውለታ እንደዋሉለት በመቁጠር በመሬታቸው ላይ የበቀለውን የድርቆሽ ሳር (ሰማንያ ሸክም ይሆናል) አጭዶ፣ ተሸክሞ አምጥቶ ከደጃቸው እንዲከምረው ይነግሩታል። እሱም ትእዛዛቸውን ለመፈጸም የቃል ውል ከገባ በኋላ ዘንጋዳው ተሰፍሮለት አህያውን እየነዳ ከግቢያቸው ይወጣል።

በዚህ ክፍል ያለው ድንቅ ትርኢት በመድረክ ላይ የሚታይ ትርኢት እንጂ ሌላም አይመስል።

ታሪኩ በዚሁ ይቀጥላል ብለን ስንጠባበቅ ሳለን የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ ይከፈትና ሌሎች ባህርዮች ሲጨዋወቱ እናያለን።

ምሽት ይሆንና “የፌንጣ ሲርሲርታ፣ የዝንብ ዝዝታ፣ የንቦች እምምታ” እንሰማለን። ጨረቃ ትወጣለች። የወ/ሮ አሰጋሽ አገልጋይ የሆነውን የወርዶፋ ዋሽንት ሙዚቃ እናዳምጣለን።

በዚህ መልክ የመድረኩ መጋረጃ ተዘግቶ እንደገና እየተከፈተ እስከ መጨረሻው ድረስ የተለያየ ትርኢት እናያለን።

ከዚህ ቀደም እንዳልኩት መጽሐፉ ከልብ ወለድነት ይልቅ ወደ ድራማነት የተጠጋ ነው … አንዳንዴ አስቸጋሪ ቢሆንም በውብ ቋንቋ የተደረሰ ድራማ።

የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ዐቢይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት እንግሊዝ አገር የታተመውና “The Thirteenth Sun” የተሰኘው መጽሐፍ በብዙ የአውሮጳውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንደታተመም ዳኛቸው ራሱ አጫውቶኛል።

መሠረተ ሀሳቡ ከ“አደፍርስ” ጭብጥ እጅግም የራቀ አይደለም።

በጥንታዊት ኢትዮጵያ አስተሳሰብና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ (በቀድሞው ትውልድ እምነትና በዛሬው ትውልድ አመለካከት) መሀከል ባለው ግጭት ላይ የተገነባ ልብወለድ ነው። በእኔ አስተያየት በትረካው ረገድ “The Thirteenth Sun” ከ“አደፍርስ” ላቅ ያለ ሲሆን በቋንቋው ውበት ግን አደፍርስ ይበልጣል።

ከዳኛቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበትን ቀን ምንጊዜም አልረሳውም ብዬ ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ አስከሬኑን የሸኘኹበትንም ቀን አልረሳውም።

ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ምሽት ላይ ሁለት ደራሲያን ወዳጆቼ በተለያየ ሰዓት ስልክ ደውለው ዳኛቸው ወርቁ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱንና በማግስቱ ማለዳ ከ11 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ አስከሬኑ ወደ ትውልድ አገሩ፣ ደብረሲና እንደሚሸኝ ገለጹልኝ።

ከሌሊቱ በ11 ሰዓት ተነስቼ ምኒልክ ግቢ አጠገብ ወደሚገኘው ቤቱ አመራሁ።

እዚያ ስደርስ አምስት የሚሆኑ የግል አውቶሞቢሎችና ከሠላሳ የማይበልጡ በጣም ጥቂት ሰዎች (አብዛኞቹ የሠፈር ሴቶች መሰሉኝ) በአካባቢው ቆመው አየሁ። ሌሎች አስር የሚሆኑ ሰዎች ደሞ ከዚያው አጠገብ ከቆመው መለስተኛ አውቶቡስ ውስጥ ገብተው ተቀምጠዋል።

የአስከሬኑ ሳጥን በአውቶቡሱ ጣርያ ላይ በሸራ ተሸፍኖ ታስሯል። በአካባቢው አንድ ሰው ብቻ ሲነፋረቅና እንባውን ሲጠርግ ተመለከትሁ። ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ ብመለከት አንድም የማውቀው ሰው የለም። ትናንትና ደውለው ያረዱኝ ወዳጆቼም በዚያ የሉም።

እጅግ በጣም ተገረምኩ፤ አዘንኩም።

“አደፍርስ” እና “The Thirteenth Sun” የሚያህሉ ድርሰቶችን ያቀረበልን የብዕር ሰው አስከሬኑ የሚሸኘው በዚህ ሁኔታ ነው ወይ? ወይንስ ዳኛቸው ወርቁ ራሱን አግልሎ ስለሚኖር ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹና ደራስያኑ ጭምር ዜና ዕረፍቱን በጊዜ ሳይሰሙ ቀሩ? ስል አሰብኩ።

የሆነ ሆኖ ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ ሲሆን አስከሬኑን የጫነው መለስተኛ አውቶቡስ ወደ ደብረሲና ለመጓዝ መንቀሳቀስ ሲጀምር በሀሳቤ፣

“ነፍስህን ይማረው። የዘላለም እረፍት አግኝ” ብዬ ተሰናብቼው ወደ ቤቴ አቅጣጫ አመራሁ።

ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም

(1988 ዓ.ም)

በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – “ሹክታ” (፲፱፻፺፪)፤ ገጽ 6-20።

.

.

 

“በራሪ ወፎች” (የሥዕል እይታ)

“በራሪ ወፎች” – የሥዕል ኤግዚቢሽን

በሕይወት ከተማ

 

በየካቲት ወር፣ በብሔራዊ ሙዚየም ጋለሪ የስናፍቅሽ ዘለቀ “በራሪ ወፎች” የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ተዘጋጅቶ ነበር። ትዕይንቱንም ለአንድ ሰዓት ያህል ከአንድ ወዳጄ ጋር ተመልክተን ስንወጣ ራሷን ስናፍቅሽን በር ላይ አገኘናት።

ስለ ሥዕሎቿ አንዳንድ ነገሮችን አወራርተን እንዳበቃን፣ ስናፍቅሽ (ዐውደ ርዕዩን በማስመልከት ነው መሰለኝ) “ሰው የደገሰውን መጥተው ሲበሉለት ደስ ይለዋል” አለችን። ወዳጄ ግን፣ “አይ ሰው እንኳ ባይመጣ እኔስ እራሴ እበላዋለሁ” ብሏት ተሳሳቅን።

ስናፍቅሽ ዘለቀ በ1977 ዓ. ም. ከአዲስ አበባ የሥነጥበብ ት/ቤት በቀለም ቅብ ተመረቀች። በ1979 የመጀመሪያዋን የግል ኤግዚብሽን በአልያንስ (Alliance EthioFrançaise) አሳየች። በርካታ ዐውደ ርዕዮችንና የሥነ ጥበብ ውይይቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለማዘጋጀትም በቃች። እንዲሁም “ፏ ብዙነን” የተባለውን የሴቶች ሰዓሊያን ማህበር አቋቁማለች። በሕንድ ት/ቤትም (Indian National School) የሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ መምህርት ሆና ለረጅም ዓመታት አስተምራለች።

ስናፍቅሽ የሥዕል ዐውደ ርዕይ ለሠላሳ አመታት ያህል ስታቀርብ የቆየች ባለሙያ ናት። በማህበራዊ ጉዳይ ባተኮሩ ስራዎቿም ስትታወቅ በተለይም የሴቶችን ትግል የሚያሳዩ በርካታ ሥዕሎችን ለእይታ አቅርባለች። በራሷም አገላለጽ “…ሴት ልጅ የቤተሰብ ኃላፊ ከሆነች እንደ እናትም ብዙ ኃላፊነት አለባት።  ልጅ ሲወለድ ብሩሽና ሸራ መቀመጥ የለበትም” ትላለች።

በአሁኑ ዐውደ ርዕይ ግን ስናፍቅሽ በከፊል አዲስ አትኩሮት የያዘች ይመስላል። እራሷ እንደነገረችኝም፣ ካለፈው አመት ጀምሮ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተለየ መልክ እየያዘ ሄዷል። “በጨለማ ውስጥ ብርሃንን፣ በመኖር ውስጥ አለመኖርን፣ በማጣት ውስጥ ማግኘትን … አብረው ተቆላልፈው ማየት ጀምርያለሁ” ትላለች።

እናም የሕይወት “ዙር ጥምጥም” (ሙሉ ክብነት) በብዛት እየታያት መምጣት እንደጀመረ ትናገራለች። ይህንንም ፍልስፍናዋን በሥዕሎቿ ላይ ለማሳየት እንደሞከረች ይታያል።

በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡት ወደ 40 ከሚጠጉ ሥዕሎቿ ውስጥ ግማሾቹ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ ግማሾቹ ደግሞ “ምናባዊ” (Abstract) ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በአዲሱ የሕይወት ፍልስፍናዋ የተቀረጹት ደንገዝና ጨለም ብለው “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) የሆኑት ሥዕሎቿ ቀልቤን ስበውታል።

መቼም የሥዕል ፎቶ ቅጂዎች የዋናውን ሥዕል ግርማ ሞገስ እንደማይገልጹ የታወቀ ነው። የዚህም ዐውደ ርዕይ በብዛት የተሰራበት አክሪሊክ (Acrylic) ቀለም ደግሞ በተፈጥሮው በፎቶ ሲታይ ልጥፍ (Flat) የመሆን ባሕርይ አለው። በዚህ ምክንያት የሥዕሉን መልክ በትክክል ማሳየት የሚችል ምስል ማንሳት አስቸጋሪ ነው። እናም፣ ሁሌም ቢሆን ሥዕሎችን ራሳቸውን በአካል ሄዶ ማየት አጥብቆ ይመከራል።

እስቲ፣ ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹን “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) ሥዕሎቿን እንያቸው።

ይህ ሥዕል ጨለም ያለ ድባብ (Background) ላይ የተመሰረተ ሲሆን በቀጥታ መስመሮችና ክቦች ተገንብቶ የተለያዩ ቀለማትን በመስመር ፈርጆ ያሳያል። የቅርጾቹ ቀላልነት (Simplicity)፣ የክቦቹ አቀማመጥ፣ የመስመሮቹ ጥራት፣ እና የቅርጾቹ አነባበር (Depth) ደስ የሚል የመውደቅን ወይም የማሽቅልቆልን ስሜት ይሰጣል። ሠዓሊዋ አስቸጋሪ የሆነውን ጥቁር ቀለም ስትጠቀም ገጽታው ልጥፍ እንዳይሆንና ንብብር እንዲኖረው በተለያዩ ቀለማት መደገፏ ይታያል። ከሥዕሉ በታች በኩል የሚታየውን ጭስ ጠገብ ሰማያዊ ምሕዋሩን (Space) ያስተውሏል። ይህ ተንጠልጣይ ቦታ የመንሳፈፍን፣ የመምጠቅን ስሜት አሳድሮብኛል … ብቻ የሥዕል እይታ እንደተመልካች ይለያያልና ለእናንተ የተለየ ስሜት ይፈጥርባችሁ ይሆናል።

“መስመሮችና ቅርጾች በምሽት”

Acrylic on Canvas

100 x 75 cm


ይህኛውም ከላይ እንዳየነው በጥቁር ድባብ የተመሰረተ፣ ብዙ የተለያየ መጠን ያላቸውን ክቦች ያዋቀረ ነው። የተለያዩት ቀለሞች ግን እንደፊተኛው በመስመሮች የታገዱ ሳይሆን በነጻነት የሚፈሱ ናቸው። ሥዕሉም በውስጡ ውስብስብ ድርብርብነት (Layering) ይታይበታል። እነዚህ ድርብርብ ቀለማት ከክቦቹ ጋር ተዋህደው የሥዕሉን ሙሉነት ይገልጻሉ። እያንዳንዱ ክብ ሆነም ወፍ የራሱ የሆነ ገጽታ (Expression) በፊቱ ላይ ይታያል። ለምሳሌ፣ በመሀል ያለውን ትልቁን ክብ/ወፍ ብንመለከት፣ የወፉ አይን ውስጥ የሚታየው እይታ ምሰጣ ውስጥ መግባትን የሚገልጽ ይመስላል።

“በራሪ ወፎች”

Acrylic on Canvas

95 x 50 cm


ይህኛው ደግሞ በአፈርማ (መሬታዊ) ቀለማት ተገንብቶ አንድ ክብን በማማከል ወደ ውጭ የሚፈሱ (Radiating) መስመሮችን የያዘ ነው። የመስመሮቹ ጥራት አሁንም የሚደነቅ ነው። እዚህ ላይ ስናፍቅሽ የተጠቀመችው ስልት ቀለማቱን ከመደራረብ ይልቅ እያንዳንዱን “መስኮት” የተለያየ ቀለም ወይም “ጥለት” (Pattern) መስጠት ነው። ህብረ ቀለሙ በመስመሮቹ ቢታሰርም ከመስመሮቹ መፍሰስ ጋር በጋራ ሲታይ የተሟላ ሥዕል እንዲሆን አድርጎታል። የሥዕሉ አሰዳደር (Composition) እንዲሁም የመስመሮቿ አካሄድ ሌጣ ቢመስልም ምሕዋሩን በሚገባ ተጠቅማበታለች።

.

“ክብና መስኮቶች”

Acrylic on Canvas

95 x 71 cm


ይህ ሥዕል ከአሁኑ “ዙር ጥምጥም” የአሰራር ስልቷ ወጣ ብሎ የ“ሴትነት” እይታ የያዘ ይመስላል። ሥዕሉ የጠንካራ ሴትን ገጽታ የሚገልጽ ይመስላል። ሴቲቷ “ኮስታራነት” ተላብሳ ዓለሟን አሸንፋ በራሷ መንገድ መሄድን የመረጠች መስላ ትታያለች። አሁንም የሥዕሉ መስመሮች እንደተለመደው ግልጽ ናቸው። ይህችንም ሴት ለመሳል የተጠቀመችው እኒህኑ ጠንካራ መስመሮቿን ነው። ባጠቃላይ የሴትየዋን ፊት “ቅርጻዊ” (ጂኦሜትሪክ) በማድረግ ጠንካራ የፊት ገጽታ ለመፍጠር ችላለች። በሴቲቷ ፊት ላይ የሚታዩትን ቀጫጭን መስመሮች ያስተውሏል። በእሳታማ ቀለማት አጠቃቀሟም ተጨማሪ ሙቀት ለሥዕሉ ሰጥታዋለች።

.

.

“Concentration”

Acrylic on Canvas

92 x 62 cm


ይህኛውም የፊት ገጽን በቅርጽ እያሳየ በመሬታማ ቀለማት የተሰራ ነው። ጥሩ የብርሃንና ጥላ አጠቃቀም ይታይበታል። የእናትነት ገጽታ በሚገባ በመቀረፁ ደግነትንና እንክብካቤን በአንገቷና በአይኖቿ እናያለን። አሁንም የስናፍቅሽ አቀራረብ በተለየ ሁኔታ “ቅርጻዊ” ነው። በመስመሮችና በቅርጾች የምትፈልገውን ሁሉ በሥዕሎቿ ማስተላለፍን የተካነችበት ይመስላል።

.

.

.

“እናትና ልጅ”

Acrylic on Canvas

72 x 63 cm


የስናፍቅሽ የአሳሳል ጥንካሬ በ“ቅርጻዊ” ስልት ሸራዋን ማድመቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። መስመሮቿን በሚገባ ትስላለች። ቀለሞቿን ደግሞ አነባብራ ትጠቀማለች። ሰፋ ያለ ምሕዋር (Space) መፍጠርንም የግሏ አድርጋዋለች።

ዛሬም ቢሆን ስናፍቅሽ የምትሰራው በዚህ “ምናባዊ” (Abstract) ስልት ብቻ አይደለም። ዐውደ ርዕዩ ላይ በመጠኑ “ተፈጥሯዊ” (Realistic)፣ አንዳንዴም “ገጽታዊ” (Expressionist) የሆኑ ሥዕሎችም ለእይታ ቀርበዋል። እነዚህ ሥዕሎቿ ግን ከተለመደው የአሳሳል ስልት እምብዛም ወጣ ያላሉ በብዛትም “ጌጣዊ” (Decorative) የሚመስሉ ናቸው። የሰዎቹ ፊትና ገጽታ ተመሳሳይና ስሜት አልባ ይመስላሉ። የሥዕሎቿን ጥንካሬ እምብዛም አናይባቸውም።

እስቲ ከእነዚህ ሥዕሎች ለምሳሌ አንድ እንይ፦

“ወደ ገበያ”

Acrylic on Canvas

92 x 62 cm

.

በአዲስ መልክ እየተጠቀመችው ያለው “ቅርጻዊ” የሆነው “ዙር ጥምጥም” ስልቷ ግን ቀልብ ይስባል። በዚህ ስልት ክቦቿ እውነትም መስመር የያዙላት ይመስላሉ፤ የምትስላቸው ገጻዊ ሥዕሎችም እጅግ ገላጭ ናቸው።

ስናፍቅሽን ለምን ይህን አዲስ አቅጣጫ እንደቀየሰችም ጠይቄአት ነበር። “ምናልባትም በሰል ማለት ይሆናል … ለምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም … አሁን ግን የሚሰማኝ እንደሱ ነው” አለችኝ።

እግረ መንገዴን ስለ ጥቁር ቀለም አጠቃቀሟ ጠይቄአት ስትናገር፣ “ትምህርት ቤት እያለን ጥቁር ቀለምን እንድንጠቀም አያበረታቱንም ነበር። አንደኛ፣ ‘ያቆሽሻል’ ይሉናል፤ ሁለተኛ፣ የተለያዩ ቀለሞችን በመደበላለቅ የሚመጣ ስለሆነ እምብዛም በቀጥታ አንጠቀምበትም። አሁን ግን ለመድፈር ወስኜ እየሰራሁበት ነው። የተለያየ የጨለማ ደረጃም ላመጣበት ችያለሁ” ትላለች።

በመጨረሻም፣ ከስናፍቅሽ ጋር በሥዕል አርእስት አወጣጥ ዙርያ ተወያይተን ነበር። እኔም፣ “መጀመሪያ አርእስት አስበሽ ነው ሥዕሉን የምትሰሪው? ወይስ ከሰራሽው በኋላ ነው የምትሰጭው?” ብዬ ጠየኳት። እሷም በተራዋ፣ “እንደሁኔታው … አንዳንዴ መጀመሪያ፣ አንዳንዴ መሃል አንዳንዴም መጨረሻ ነው” አለችኝ።

የጥበብ ሰዎች በሥራቸው ፍልስፍና ላይ ብዙ ሲንገላቱ አያለሁ። የትኛው ይሆን የሚቀድመው … ጥበብን  መፍጠር? ወይስ ለመፍጠር ፍልስፍናን ማጠንከር? … አንድ የጥበብ ሥራ መልዕክት ሊኖረው የግድ ነውን? … ጥበብ ያለ ፍልስፍና ወይም መልዕክት ሌጣውን በራሱ ብቻ መደነቅስ ይችላል? … አንዳንድ ጊዜ “ሥዕሎች ምነው አርእስት ባይኖራቸው?” ያስብለኛል።

ስናፍቅሽ ብዙ የጥበብ ውይይቶችን እንደምታዘጋጅ፣ የህዝቡንም የሥዕል ንቃተ ኅሊና ከፍ ለማድረግ (እንደ መምህርነቷ) ሃላፊነት እንደሚሰማት ትናገራለች። ስለዚህም በዐውደ ርዕዮቿ ላይ በመገኘት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ተመልካች ያልገባውን ለማስረዳት እንደምትሞክር ገልጻልኛለች። የጥበብ ሰዎች የሥዕል ድግሳቸውን ስለሚቋደሱ ተመልካቾች ምን ያህል መጨነቅ እንዳለባቸው ያሳስበኛል።

ወደፊት ሥራዋ ወዴት እንደሚመራት ለማየት ጓጉቻለሁ።

.

ተጨማሪ

ሌሎች ሥዕሎቿን ለማየት

 ቃለመጠይቅ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ‹‹ሥዕልን ያን ያህል የተገነዘበ ማኅበረሰብ አለን ለማለት ያስቸግራል››

የኤግዚቢሽን ዘገባ ከሪፖርተር ጋዜጣ  በ‹‹በራሪ ወፎች›› ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ

“በራሪ ወፎች Catalogue” የካቲት 2009

የግዕዝ ሊቃውንት እና አዲሱ ዘመን

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 5)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል አራት የቀጠለ)

 

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ትውልዳቸው ሸዋ ትምህርታቸው ጎንደር ነው። ዕድሜያቸው 60 ዓመት ይሆናል። በኢትዮጵያ መጻሕፍት ካላቸው ከሰፊው ዕውቀታቸው በላይ፣ ላገራችን መጻሕፍት ምሥጢርና ታሪክ አስፈላጊ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን ዕብራይስጥ ጨምረውበታል። የሕዝቅኤልን ትንቢት ዕብራይስጡን ወደ አማርኛ ገልብጠው ባማርኛ የጨመሩበት መግለጫ፣ ከሁሉ በፊት ላገራችን ሊቃውንት ከግሪክ ተተርጕሞ በግዕዝ ተቀብለውት የሚኖሩትን የብሉያትን መጻሕፍት፣ ዋናውን አብነት ዕብራይስጡን እያዩ ማቃናት እንዳለባቸው አነቃቅተዋቸዋል። ዳግመኛ ትምህርቱም መጠነኛ ቢሆን አማርኛ ያወቀ ሁሉ ሊያስተውለውና ሊያጣጥመው በሚችል ንግግር በመግለጣቸው ተራውን ሕዝብ ሳይቀር ከሊቃውንቱ ዕውቀት እንዲካፈል አድርገውታል። እግረ መንገዳቸውንም ልዩ ለሆነው ከባድ ዕውቀት፣ ልዩ የሆነና ያጌጠ አማርኛ ፈጥረውለታል።

kidane-photo

እርሳቸው ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት ኢየሩሳሌም ሒደው ዕብራይስጥ የተማሩበት ዘመን የነበረውን ችግር ያስተዋለ ሰው ብቻ ድካማቸውን ሊመዝነውና ሞያቸው ትልቅ መሆኑን ሊረዳ ይችላል። ፍቅርና አንድነት በተሰበከበት አገር በኢየሩሳሌም ጠብና መለያየት ተዘርቶበት ነበር። ዛሬውንም ገና አላለፈበትም። ከዚያ የነበረው የኢትዮጵያ መነኮሳት ማኅበር፣ ከጸሎት በቀር፣ ትምህርት መቀጠል የማያስፈልግ ሥራ ሁኖ ሲታየው፣ እስራኤላዊ ደግሞ በዓለም ያለ ሕዝብ አሥር ቢማር እንደማያፈቅረው ተረድቶት ቋንቋውን ሊማርለት የመጣውን ክርስቲያን መርዳት፣ እባብን ከመቀለብ ይቆጥረው ነበር። ስለዚህም አለቃ ኪዳነ ወልድ ዕብራይስጥ የተማሩት በሁለት ፊት ሥቃያት እያዩ ነው። ይህ ሁሉ ድካማቸው በክርስቲያን ሊቃውንት ጭምር ስለ ብሉያት መጻሕፍትና ታሪክ ያመጡትን አዲስ መግለጫ ለመከታተል ቢቸግራቸው፣ አማርኛው ከተሰናዳው መግለጫቸውም በክርስቲያንነታቸው የጸኑት ሊቃውንት ከደረሱበት የታሪክና የትርጕም አዲስ አካሔድ ለመድረስ ቢያቅታቸው አይፈረድባቸውም።

kidane-hizqel

የኢትዮጵያን የጥንቱን ትምህርት ከሚያውቁት ሊቃውንት አማርኛንና ግዕዝን ለማጣራት፣ ያለቃ ኪዳነ ወልድን ያህል የሚደክም ብዙ አልተገኘም። አማርኛ ለግዕዝ ልጁ በመሆኑ፣ ከግዕዝ የተቀበላቸውን ቃላት ልክ እንደ ግዕዝ አድርጎ መያዝ አለበት የሚል አሳብ ስላለባቸው፣ ይህንኑ ውሳኔ ለመግለጥ የታተመና ያልታተመ ብዙ መጽሐፍ ጽፈዋል። አሳባቸውን ተቀብሎም ለማስተዋል የሚጣጣር በያገሩ ብዙ ደቀመዛሙርት አውጥተዋል። ሠላሳ ዓመት ያህል የደከሙበት ዋናው መጽሐፋቸው ግዕዙን ባማርኛ የሚተረጕም መዝገበ ቃላት ነው።

ጠላት አገራችንን በወረረበት ዘመን እርሳቸው ሲታሠሩ ሲጋዙ ያን ያህል የደከሙበት ሥራ የሚከውነው አጥቶ የብልና የምስጥ ምግብ ሁኖ መቆነጻጸሉ ጕዳቱ የራሳቸውና የመላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወሰን ሳያግደው ሰንደቅ ዓላም ሳይለየው፣ ወገን ለሆነው በዓለም ላለው የትምህርት ወዳጅ ለሆነው ሰው ሁሉ ነው። ከሰው ተለይተው፣ ፈቃድ አጥተው ሲኖሩ ሳለ ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ከችግር አስጥለዋቸው የነበሩ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። ዛሬም ንጉሠ ነገሥታችን የኢትዮጵያን አልጋ መልሰው ሲይዙ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድን አስፈልገው የዕለት እንጀራቸውን በመዓርግ እንዲያገኙና ያቋረጡትን ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋልና ፈቃዱ ሁኖ የኢትዮጵያ ወጣቶች የግዕዝን ቋንቋ ከሥር እስከ መሠረቱ ለማወቅ ከገዛ አገራቸው ሊቅ በተጻፈው መዝገበ ቃላት ይመረምሩታል እያልን ተስፋ እናደርጋለን።kidane-dictionary

የግጥም ባሕል

በግጥም ወይም ቤት ሳይመታ፣ ቃሉ ያላጋደለ፣ የተመዛዘነ በሆነ ንግግር አሳብን መግለጥ፣ ሰው አንደበት ከፈታ ጀምሮ የነበረ ልማድ ነው። በጽሕፈት ያልገባው ያገራችን የጥንት ወግና ታሪክ፣ ብዙ ግጥም አለበት። ሌላ የቀድሞ ሕዝብ የቤተ መንግሥቱን ሕግ ሳይቀር ቤት እያስመታ ጽፎ፣ በተማሪ ቤት በዜማ እንዲማሩት አድርጓል። በኢትዮጵያ ማናቸውንም የግዕዝ መጽሐፍ ስንኳ በዜማ ማንበብ ልምድ ቢሆን፣ ሕግን በግጥም መጻፍ አልተለመደም። ነገር ግን ቤት የሚመታ የሕግ ዓይነት ምሳሌ አይጠፋም። “ይካስ የበደለ፣ ይሙት የገደለ”፣ “ያባት ዕዳ ለልጅ፣ ያፍንጫ እድፍ ለእጅ”፣ “አልሞት ባይ፣ ተጋዳይ”።

ይህንንም የሚመስል ባንድ ፊት ምሳሌ፣ እግረ መንገዱን ደግሞ ሕግ ሁኖ የሚጠቀስ፣ ቤት የሚመታ ብዙ ንግግር አለ። በቀድሞ ዘመን አንዳንድ ጊዜ ከሳሽና ተከሳሽ ተከራክረው ሲጨርሱ፣ አጭር ሁኖ ቤት የሚመታ ንግግር ጉዳያቸውን ለዳኛ ያቀርቡ ነበር። ከትችት ላይ ዛሬውንም ቢሆን በግጥም የሚተች አለ። የበገናና የመሰንቆ፣ ልዩ ልዩ ዝማሬ፣ ባላገሩ ለአምላክና ለድንግል ማርያም፣ ለመልአክና ለጻድቅ የሚያቀርበው ልመናና ምስጋና በግጥም ነው። ቀረርቶና ዘፈን፣ እንጕርጕሮና ልቅሶ ሁሉም በግጥም ነው።

ነገር ግን ልዩ ልዩ ሕዝብ ፊት አስቀድሞ ቤት እየመታ ወይም በሕግ በተወሰነ ሚዛን አሳቡን የሚገልጥበትን ጽሑፍ ሥራው ሲደራጅ፣ ባገራችን ጽሑፍ ሥራ ግጥም የኋሊት ቀርትዋል። ስለሆነም አሁን በቅርቡ ጊዜ ብዙዎች ሰዎች በግጥም መጻፍ ጀምረዋል። አብዛኛው ስላልታተመ ስለ አማርኛ ግጥም ብዙ የምናመለክተው የለንም።

ያሳተሙትና ያላሳተሙት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች በግጥም የሚገልጡት አሳብ አብዛኛውን ጊዜ ምክር ነው። የሰውን ኀዘንና ደስታ የሚገልጠው እጅግ በጥቂቱ ሁኖ፣ የወንድንና የሴትን ፍቅር የሚያነሳ በጭራሽ የለበትም። የጣልያኖች ወረራ፣ ስለ አገርና ስለ ንጉሠ ነገሥት ፍቅር፣ ዓመፀኝነት ስለሚሠራው ግፍ፣ ስለነፃነትም ናፍቆት በግጥም የሚያናግር አሳብ ቀስቅስዋል። የተጻፈው ገና ስላልተመረመረ፣ የሚያምረውን ከማያምረው ለመለየት ለጊዜው አልተቻለኝም።

ስለ አማርኛ የቅኔ ባሕርይ ግን ከዚህ በፊት እንዳመለከትነው፣ ብዙ “ስለምን” ወይም “አማርኛ” ይወዳል። አብዛኛውን ጊዜ አያሌውን መስመር ባንድ ፊደል ቤት ያስመታል። አንዱን መስመር በሁለት ሐረግ ከፍሎ፣ ላንዳንዱ ሐረግ ፮፣ ለሁለቱ ሐረግ (ላንዱ መስመር) ፲፪ ፊደል ይሰጣል። ፊደል ሲቆጥር አብዛኛውን ጊዜ እንደ ዕብራይስጡ ቅኔ ሳድሱን ከሌለ ይቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሳቡና በንግግሩ ስንኳ ቅኔ ወዳጅና ቅኔ ፈጣሪ ሁኖ ቢታይ፣ ባማርኛ እስከ ዛሬ ጽፈው ካሳተሙት ግጥም ገጣሚዎች፣ ትዕግሥት ሰጥትዋቸው፣ ሽሕ መቶ ሽሕ መሥመር የጻፉና ያሳተሙ ያሉ አይመስሉንም። በርከት አድርጎ የጻፈ ቢኖርባቸው ለፍርድ ይመች ነበር።

ወጣቱ ከበደ ሚካኤል

ይሁን እንጂ አጭርም ቢሆን፣ እኔ ለራሴ ሥራቸውን የማደንቅላቸውና የማመሰግንላቸው ብዙ ወጣቶች አሉ። ከነዚህም አንዱ ከበደ ሚካኤል ነው። ቅኔ፣ ምሳሌ፣ ተረት ከውጭ አገር ደራሲ (ከፈረንሳይ) በሚተረጕምበት ጊዜ አሳቡና ንግግሩ አማርኛ ሁኖ ከተረጐመበት ቋንቋ ጋር ሲያስተያዩት አንዳንድ ጊዜ ተወዳዳሪው፣ አንዳንድ ጊዜም አርሞ ያቃናው ሁኖ ይገኛል።

ምክንያቱን ከራሱ አፍልቆ የሚፈጥረው ግጥም ከልብ የወጣ ከልብ ይገባል እንደተባለው ሁሉ፣ ልብን የማይነካ የሚገኝበት ሁኖ አልታየኝም። አብዛኛውን ጊዜ ካገራችን ባለ ቅኔዎች ግዕዝን ወይም የውጭ አገርን ቋንቋ እጅ ያደረጉ ሲሆኑ ወደዚያው እየሳባቸው ንግግራቸውን ለማስተዋል እንቸገርበታለን። ወይም ደግሞ፣ ሌላ ባለ ግጥም ያወጣውን ንግግር፣ አማርኛው ካማረ ብለው ያለ ቦታው ሲጥሉት ቅር ያሰኛሉ። “ስለምን” ያልሁትን ንግግር አምጥተው አንባቢ በቶሎው እንዳያስተውለው ያደረጉ እንደሆን፣ ሰው ሊያስተውለው ያልቻለ ጥልቅ ጥበብ የተገለጠላቸው ይመስላቸዋል። ከበደ ሚካኤል፣ ሌሎች ካበጁት ወይም ከውጭ አገር ንግግር ሳይጨምር በራሱ አማርኛ፣ ሁሉም ሊያስተውለው የሚችል አገላለጥ በመምረጡ ለወደፊት ለሚነሱት ያማርኛ ባለ ቅኔዎች አብነታቸው ለመሆን ተስፋ የሚያስደርግ ልጅ ነው።

kebede-berhane-hilinakebede-nibab

ማጠቃለያ

ለንግግራችን ፍጻሜ ስንሰጥም ደግመን የምናስታውሰው፣

 1. በአማርኛ መጻፍ ከጀመርን ስድስት መቶ ዓመት ስንኳ ቢሆን፣ በብዙው የተጻፈበት ዘመን ከ1600 ዓ.ም. በኋላ መሆኑን።
 2. ከ1600 ዓ.ም. ጀምሮ ባማርኛ የሚጻፈው አብዛኛው የሃይማኖት መጽሐፍ ሁኖ ከንግግሩና ከአሰካኩ ከግዕዝ ነፃ ያልወጣ ብዙ አካሔድ እንደነበረበት፤ ይህንም የአጻጻፍና የንግግር አካሔድ ዛሬውን ሳይቀር አንዳንድ ጸሐፊዎች እንደሚከተሉት።
 3. አማርኛን ራሱን አስችለው መጻፍ የጀመሩት ደራስያን በአጤ ቴዎድሮስ ዘመን (1847-1860) መሆኑን ጭራሽ እየተጣራ የሔደበት ግን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን።
 4. አማርኛ ጽሑፍ ሥራውን በግጥም ጀምሮ፣ ይኸው የግጥም ሥራ ዛሬ የኋሊት መቅረቱን።
 5. የዛሬ ዘመን ደራስያን ከሚጽፉት አብዛኛው መጽሐፋቸው የታሪክና፣ የሃይማኖት፣ የልብ ወለድ ታሪክም መሆኑን፣ የሁሉን አሳብ ትምህርትን ሥራንና ልማድን እያሻሻሉ መሔድ ዋና መሆኑን።
 6. የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍጥረቱ የቅኔ መንፈስ ያደረበትና በግጥም አሳቡን እንደገለጠ መኖሩን፣ ሙግቱንና ትቹን ሳይቀር በግጥም ማምጣት ልማዱ መሆኑን በዚኸውም የተፈጥሮ ልማዱ ቤት እያስመታ የሚሔድ ደራሲ በብዙው መገኘቱን፣ ነገር ግን ባማርኛ ያወጣውን ግጥም ያሳተመ ደራሲ ጥቂት መሆኑን ነው።

ተአምራት አማኑኤል

1936 ዓ.ም

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 4)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል ሶስት የቀጠለ)

 

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ትውልዳቸው ሸዋ የሞቱበት አገር (+1931) በባት ከተማ በእንግሊዝ አገር ነው። በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ትምህርት ፈጽመው በቤተ ክህነት ሲያገለግሉ ኑረው ሠላሳ ዓመት ያህል በቤተ መንግሥት ልዩ ልዩና ከፍ ያለ ሹመት ተቀብለው ከባድ የሆነ የኀላፊነት ሥራ የፈጸሙ ሰው ናቸው። የአሁኑ ማስታወሻ ስለ ደራሲነታቸው ብቻ የሚናገር በመሆኑ በሹመታቸው ስላስኬዱት ትላልቅ ሥራ ከዚህ ማንሣት የለብንም።

heruy-medal

ከጽሑፍ ሥራቸውም ዋና ሁነው የሚታዩን “ወዳጄ ልቤ”፣ “ጎሐ ጽባሕ” እና “ሀገረ ጃፓን” በመሆናቸው የቀሩት መጻሕፍቶቻቸው ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስንኳ በብዙው ቢጠቅሙት፣ አሳባቸውንና ደራሲነታቸውን በሦስቱ መጻሕፍት ማግኘት ስለ ተቻለ ስለነርሱ ብቻ ባጭሩ እናመለክታለን።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ በጻፉት ሁሉ ዋና አሳባቸው፤

 1. በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው ሁሉ በፈጣሪውና በመንግሥት ዘንድ አኳያ መሆኑን ነው። የውነት ነው። ሲፈጠር ብልህና ሞኝ ሁንዋል፤ በሥራ ዕውቀትና ዕድለኛ በመሆን ከሰው የተሠራ አስፈላጊ የሆነ የመዓርግ ከፍተኝነትና ዝቅተኝነት ይህንንም የመሰለ ብዙ ልዩነት አለ። ነገር ግን በምንፈርድለትና በምንፈርድበት ጊዜ መሠረት ልናደርገው የሚገባን ሁሉም ትክክል መሆኑን ነው።
 2. በዘርና በሃይማኖት የመጣውን ልዩነትም እርስ በርሳችን ተቻችለን ከሌለ መቍጠር ይገባናል።
 3. የክርስቲያን ሃይማኖት በዓለም ከታወቁት ሃይማኖቶች ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ኑሮ የሚስማማ ነው።
 4. ሰው በማናቸውም ሰዓት ሞት እንደሚመጣበት ማሰብ ይገባዋል።
 5. ሰው የልማድ ባርያ ሳይሆን በነፃነት ሕጉንና ሥርዓቱን እያሻሻለ መሔድ አለበት።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከጻፍዋቸው መጻሕፍት ከሁሉ ይልቅ ዕድለኛ ሁኖ ሕዝቡ አንብቦ የማይጠግበው “ወዳጄ ልቤ” ነው። እንዲህ ያለውን መጽሐፍ የሚጽፍ የእንግሊዙን ደራሲ የዮሐንስ ቡንያንን መጽሐፍ ያነበበ ሰው ብቻ መሆኑን የምንረዳው የዚሁኑ ደራሲ “የክርስቲያን መንገድ” የተባለውን መጽሐፉን ስናነብ ነው። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ግን ንድፉን ስንኳ ከእንግሊዙ ደራሲ ቢቀበሉ፣ የጽሑፋቸውን ሕንፃ መልክና ጠባይ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ያውም የሚያምር ኢትዮጵያዊ አድርገውታል።

heruy-wedaje

ባሳባቸው የፈጠሩት “ወዳጄ ልቤ” የተባለው ሰው የርሳቸው ራሳቸው ወይም ክርስቲያን ሁኖ የክርስቲያንን ሕግ ለመጠበቅ የሚታገል ሰው ምሳሌ ነው። ወዳጄ ልቤ ለብቻው ሁኖ የእግዚአብሔርን ህላዌና የሕዝበ አዳምን፣ በተለየም የነፍስን ሁኔታ በሚያስብበት ጊዜ፣ ወይም እግር ጥሎት ከልዩ ልዩ ሰዎች ጋር ተገናኝቶ ክፋታቸውንና በጎነታቸውን በሚገልጥበት ጊዜ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ በተለየም በክርስቲያን ላይ የሚመጣበትን መከራ ሲያስታውስ፣ ተስፋ ሊቆርጥ ሲቃጣና፣ በርትቶ ሲታገል፣ ከባልንጀሮቹ ጋርና ለብቻው መሰንቆውን ይዞ ሲያንጐራጕር፣ በሠርግ አስመስሎ ስለ ክርስቲያን ሃይማኖት አጀማመርና፣ ድል እየነሣ በሔደበት፣ በሚሔድበትም ዘመን ሁሉ ያለበትን መከራ ሲተርክ፣ ፍጹም ክርስቲያናዊ ነው።

ወዳጄ ልቤ፣ “ሰው በየሱስ ክርስቶስ ካመነ በኋላ ከኃጢአት ላለመውደቅ ምን ቢሠራ ይሻላልን?” ብሎ የሚጠይቅ ወይም የዚህን አሳብ የሚያሳድር ሁኖ ይታያል። አንባቢው፣ ቁልፉን ወይንም መልሱን አገኘሁ! መጽሐፉ ሊነግረኝ ነው! ብሎ ሲጓጓ፣ “ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ” ብሎ ያሰናብተዋል።

heruy-goh

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስለ ሃይማኖትና ስለ ፖሊቲካ ስለ ልዩ ልዩ ጉዳይም ያሰቡትን ሁሉ ካንድ ላይ ሰብስበው ጽፈው ያወጡትን መጽሐፍ “ጎሐ ጽባሕ” ብለው ሰይመውታል። ጎሐ ጽባሕ ስለ ሃይማኖት የሚገልጠው አሳብ ንግግሩም ልዩ ቢሆን ከ”ወዳጄ ልቤ” አይለይም። ሕግንና ልማድን ማሻሻል ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ሥራዬ ብለው የቆሙበት ዋና አሳብ በመሆኑ፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ቍጥር፣ ስለ ምንኵስናና ስለ ጋብቻ ሥርዓት፣ ስለ ጸሎትና ስለ ንስሐ ከጻፉት ክፍል፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ሥርዓት እየተሻሻለ የሚሔድበትን መንገድ መሠረት ባለው አካሔድ አስረድተዋል። ከቤተ ክህነት፣ ቤተ መንግሥትን መምራት ይገባኛል እያለ፣ በመንፈሳዊና በሥጋዊ ጕዳይ ሁሉ የበላይ አስተዳዳሪ ልሁን የሚል እንደማይጠፋ ስለ ተረዱት፣ የሁለቱንም ሥልጣን ወስነው ሁሉም በየክፍሉ፣ በየሥራው አላፊነት እንዳለበት፣ የሁሉ በላይ ግን መንግሥት መሆኑን አደላድለው ወስነዋል። ወገን ለሌለው፣ በዘር በሃይማኖት ለተለየ ሰውና ለእንስሳ ርኅራኄ እንዲገባ በብዙው ሰብከዋል። ለዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያዊ አንዳንዱ ስንኳ የዚህ ዓይነት ምክር ባያስፈልገው፣ ካገራችን ሕዝብ ላብዛኛው አዲስ ነገር ሁኖ ታይቶት ከአሳባቸው አንዳንዱ ለመቀበል የሚያስቸግር ሁኖ ሳይታየው የማይቀር ነው፣ መጽሐፉ ለእንዲህ ያለው ክፍል ብርቱ አሳብ የሚያሳድርበትና ጥቅም ያለው ክርክር የሚያነሣ ነው።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ገና ወደ ጃፓን አገር የመንግሥት መልእክተኛ ሁነው ሳይሔዱና ከዚያ በኋላ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ስላይዋቸው አገሮች ሁነታ የጻፉዋቸው መጻሕፍት አሉ። በተስተካከለ አማርኛና ያላዩትን አገርና ሕዝብ ካዩት በሚያስቆጥር አነጋገር የመንገዳቸውን አካኋን የገለበጡበት መጽሐፍ ግን “ማኅደረ ብርሃን” (ሀገረ ጃፓን) ብለው የሰየሙት ነው።

heruy-japan

መጽሐፉ ከማያስፈልግና ከሚያታክት ዝርዝር ሳይገባ በወሬ የምናውቀው የጃፓን አገርና ሕዝቡ፣ ሃይማኖቱ፣ ያገሩ ልማድ፣ ሥልጣኔውና አስተዳደሩ ምን እንደሆነ ነግሮ የሚያጠግብ ነው። ደራሲው የተላኩበት ሥራ ከሕዝብና ከትላልቅ ሰው፣ ከንጉሠ ነገሥቱና ከንግሥቲቱ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የሆቴሉንና የባላገሩን፣ የሚኒስትሮችንና የቤተ መንግሥቱን እልፍኝ ታዳራሽ ወገኑንና ሥርዓቱን አይተዋል። ያዩትንም ላላየነው፣ ካየነው እንድንቆጥረው አድርገው ጽፈዋል። ከዚህም ሁሉ ጋራ ጃፓን ሕዝብ መሆን ከጀመረበት ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታሪኩን እንድናውቀው ከሌላ ባለ ታሪክ እየጠቀሱ ባጭሩ ተርከውልናል። የባሕሩንና የመሬቱን፣ የጫካውንና ያትክልቱን ሁኔታ የሚነግረው ክፍል፣ ደኅና ሥዕል ሳይ፣ በሚስማማ ቀለም ነድፎ ያቀረበው ሰሌዳ ይመስላል። ክርስቲያኑ ኅሩይ፣ ክርስቲያን ያይደሉትን ወገኖች የአምልኮና ባህል የሚያዩት እጅግ ከፍ ባለ አስተያየት ነው። የጃፓን አምልኮም እንደ ሌላው አምልኮ፣ የእግዚአብሔርን ምስጢር ለማግኘት የሚጣጣር ሁኖ ስለታያቸው፣ ያገራችን ሕዝብ ደግሞ ባይቀበለውም በሰፊው እንዲመለከተው አድርገው ገልጠውታል።

ከዚያ በፊት ልዩ ልዩ መጻሕፍት በመጻፍ ብዙ ትግል ያየው የብላቴን ጌታ አእምሮና አማርኛ፣ “ሀገረ ጃፓን”ን በጻፈበት ጊዜ፣ ደርጅቶ ከፋ ካለ ደረጃ የደረሰ ሁኖ ይታያል።

አማርኛ ማሠሪያ አንቀጹን አርቆ፤ ከማህሉ ልዩ ልዩ አሳብ ጣልቃ ማግባት የተፈጥሮ ጠባዩ ነው ብለናል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ አብዛኛውን ጊዜ ይህን ሳይከተሉ ንግግሩን ባጭር ባጭሩ ማሠር ልዩ ባሕርያቸው ነው። ከአማርኛ መርማሪዎች አንዳንድ ሰው ብላቴን ጌታ ኅሩይ አማርኛን በውጭ አገር (በኤውሮጳ) ንግግር ዓይነት እንጂ በተፈጥሮ ጠባዩ አያስኬዱትም ብሎ ጽፎባቸዋል። ነገሩም እውነት ይሆናል፤ ግን ደግሞ ደራሲ መከተልና ማሻሻል የሚገባው የሚጽፍበትን ቋንቋ ጠባይ ነው ስለ ተባለ፣ ይኸው ደራሲ የሚጽፈው፣ የንግግር ጣዕም ያለውና በፍጥነት የሚያስተውሉት ከሆነ፣ ከተራው ሕዝብ ተለይቶ መዓርግ ያለው ደራሲ ነው መባልን አያግደውም።

heruy-sikwarብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሕፃናትና አእምሮ ለዋጭ የሚሆኑ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ትተውልናል። እንዲያውም ከመጻሕፍት ዓይነት በጽሕፈት ለመግለጥ ያልሞከሩት ጥቂት ነው ለማለት ይቻላል። በሥራ የተፈተነው የተፈጥሮ ባሕርያቸው ትዕግሥተኛ ሲሆን፣ ጽሕፈት ሲልዋቸው ፍጥነታቸው የመኪና ያህል ስለ ነበረ፣ ካማርኛቸው በቀር በወጣቱ ኢትዮጵያዊ ላንዳንዱ የጻፉት ታሪክና ልብ ወለድ ታሪክ፣ ሌላውም ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ ውዝፍ ሁኖ ይታየዋል።

ምክንያቱም በቤተ መንግሥት የነበረባቸው ከባድ ሥራ፣ ለሚጽፉት መጽሐፍ የተገባውን ምርመራ ለማጥለቅና ለማስፋፋት ፋታ አልሰጣቸው ስላለና ላገራቸው ሕዝብ በነበረባቸው ፍቅር፣ እርሳቸው ካወቁት ከብዙው ጥቂቱን ሳያስታውቁት ቢቀሩ “ዘደፈነ ወርቀ እግዚኡ” እንዳይሆኑ ሲሉ ይሆናል።

የሒሳብና የፍልስፍና የሕክምና የሥነ ፍጥረት ይህንንም የመሰለው ልዩ ልዩ ዕውቀት የተጻፈበትን ጽሑፍ ሥራ ቋንቋው የተጣራ ቢሆን፣ ያንኑ ዕውቀት የተማረ ሰው ካልሆነ በቀር፣ በሌላ ዕውቀትም ሊቅ የሆነ ሰው አያስተውለውም። የድርሰት ስጦታቸው አንዳንድ ሰዎች ግን፣ እንኳንስና የተማረ ሰው ተራው ሕዝብ ሳይቀር በሚያስተውለው ንግግር ልዩ ዕውቀታቸውን ለመጻፍ ተችልዋቸዋል። ቃለ እግዚአብሔር የሚያስተምሩና የሃይማኖትን መጻሕፍት የሚተረጕሙ፣ ስለ ሃይማኖትም የሚጽፉት ሊቃውንት፣ ምሥጢሩ ግድ እያላቸው ንግግራቸው ወይም አጻጻፋቸው አማርኛ አወቅሁ ለሚል ሁሉ የማይደፈር ሁኖ ይኖራል። ደግሞም ትምህርት ሲባል፣ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ያገር፣ የመንግሥት ወሰን የማያግደው አገሩና መንግሥቱም ቢለያዩ ሰንደቅ ዓላማው፣ ወይም ወገኑ አንድ የሆነ ነው። ለጊዜው ያገራችን ሊቃውንት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ያለው ትምህርትና ዕውቀት ባዕድ ሁኖባቸዋል።

 

(በክፍል አምስት ይቀጥላል …)

ማቲክ ኬዎርኮፍ – አርመኑ ነጋዴ

 የፒያሳው ኬዎርኮፍ ሕንጻ

(ክፍል 3)

በሕይወት ከተማ

(… ከክፍል ሁለት የቀጠለ)

አራዳ የመዲናችን ንግድ ማዕከል በነበረችበት ዘመን ትላልቆቹን ሱቆች የሚያስተዳድሩት የውጭ ዜጎች (ግሪኮች፣ አረቦች፣ አርመኖችና ህንዶች) ነበሩ። ከነዚህም የናጠጡ ነጋዴዎች መካከል አርመናዊው Matig Kevorkoff (እንዳገሬው አጠራር ማቲክ ኬዎርኮፍ) አንዱ ነበር።

ጥቂት ስለ ማቲክ ኬዎርኮፍ

 

ኬዎርኮፍ በ1859 ዓም ኢስታምቡል ውስጥ ተወለደ። በቆንስጣንጢኖስም (Constantinople) በአርመን ትምህርት ቤት ተምሮ ወደ ግብጽ ተጓዘ። ለአጭር ጊዜ ግብጽ ውስጥ ቆይቶ በ1888 (በአድዋ ድል ወቅት) ወደ ጅቡቲ አመራ። በጅቡቲም ቆይታው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ እና የፈረንሳይም ዜጋ ለመሆን በቃ።

16463652_1413657838645249_4225349741114144258_o
ማቲክ ኬዎርኮፍ  (ምንጭ – “L’Empire D’Ethiopie” by Adrien Zervos)

ኬዎርኮፍም ከአጎቱ ጋር በመሆን ከጅቡቲ ትንባሆ ወደ ፈረሳይ ሐገር በመላክ ትልቅ ንግድ ጀመሩ። ቀስ እያለም ንግዱን ወደ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ እና አዲስ አበባ አስፋፋ። ጎራዴ፣ ሰይፍ፣ ጩቤ እና የመሳሰሉትን በ1890ዎቹ በሐረር ያመርት እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

picture 19
የኬዎርኮፍ ጎራዴ (የኢንተርኔት ምንጮች)

ጥይትና መሳሪያም በማስመጣት በአዲስ አበባ ሱቁ ይሸጥ እንደነበር የቀድሞ ደብዳቤዎች ያሳያሉ፤

“ይድረስ ከነጋድራስ ይገዙ – ማቲክ ጊዎርኮፍ መቶ ሳጥን የፉዚግራ ጥይት ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ አምቷልና እንዳይከለከል ይሁን።”

[ግንቦት 4 ቀን 1899 ዓ.ም. አዲስ አበባ]

በጣልያን ወራራ ዋዜማ ግንቦት 29, 1927 ዓ.ም. የወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣም ይህንንኑ ይጠቁማል።

guns
የመሳርያ ማስታወቂያ  (ብርንሃና ሰላም ጋዜጣ፣ ግንቦት 29 1927)

የትንባሆ ንግድ በጣም አዋጪ ሆኖም ስላገኘው በአዲስ አበባ የትንባሆ ብቸኛ አስመጪ ሞኖፖል ይዞ ንግዱን በሰፊው ተያያዘው። በመጋቢት 1921 ዓ.ም. አእምሮ ጋዜጣ ስለ አገሪቱ የትንባሆ ሞኖፕል ለተጻፈበት ትችት መልስ ሲሰጥም እዚህ ይነበባል።

ከዚህም በተጨማሪ ጥጥ፣ ሐር፣ መጠጥ፣ ዘይት፣ ሳሙና፣ የህንጻ መሳሪያዎች፣ ብትን ጨርቅ፣ ስጋጃ፣ ሰዓት እና የመሳሰሉትን አስመጭና ላኪ ሆኖ ይሰራ ነበር።

picture 26
ማቲክ ኬዎርኮፍ በሱቁ ውስጥ (ምንጭ – Fasil & Gerald – Plate 504)

 

 

omega 2.JPG
የኬዎርኮፍ ሰዓት ማስታወቂያ (ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ፤ መጋቢት 29፣ 1919)
cognac
የኮኛክ ማስታወቂያ (ብርንሃና ሰላም ጋዜጣ፤ ሐምሌ 21፣ 1919)

እንዲሁም ኬዎርኮፍ የኮኛክና የተለያዩ መጠጦች ዋነኛ አስመጪ እንደነበር ምንጮች ያሳያሉ።

“መገን ያራዳ ልጅ ጠመንጃም የላቸው፤

በየደረሱበት ብርጭቆ ግምባቸው።

… ውስኪና ኮኛኩ ሲረጭ እንደውሃ፤

እንዴት ነሽ አራዳ የውቤ በረሃ።”

ለዚህ ሁሉ የንግድ ሥራው ይሆን ዘንድ ነበር በአራዳ የሚገኘውን ኬዎርኮፍ ህንጻ ያሰራው። ይህም የኬዎርኮፍ ሕንጻ የትምባሆ ሞኖፖል (“Tobacco Regie”) ዋና ቢሮ ሆኖ አገልግሏል። (ሕንጻው በአሁኑ ጊዜ “ሮያል ኮሌጅ”፣ “አቢሲኒያ ባንክ” ፣ “ካስቴሊ ሬስቶራንት” እና ሁለት ቡቲኮችን በመያዝ እያገለገለ ነው።)

ኬዎርኮፍ ሕንጻ

የኬዎርኮፍ ህንጻ ከመሰራቱ በፊት ኬዎርኮፍ አራዳ ውስጥ በሁለት ሌሎች ሱቆች ውስጥ ንግዱን ያካሂድ እንደነበር ምንጮች ያሳያሉ። ከደጎል አደባባይ ፊት ለፊት ከአያሌው ሙዚቃ ቤት በስተቀኝ በነበረ (አሁን የፈረሰ) ጥንታዊ ህንጻ ውስጥ ኬዎርኮፍ ሱቅ እንደነበረው ይታያል።

cp-michel-29-recto-2
የቀድሞ የኬዎርኮፍ ሱቅ  (ከፖስትካርድ የተገኘ)

ከዚህም በተጨማሪ እስከ 1920ቹ የፖስታ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ህንጻ የነበረው (የአሁኑ “ሲኒማ ኢትዮጵያ” እና “ትራያኖን ካፌ”) በ1900ዎቹ ዓ.ም. መጀመሪያ የኮዎርኮፍ ሱቅ እንደነበረ ይታያል።

picture 24
የቀድሞ የኬዎርኮፍ ሱቅ (ከፖስትካርድ የተገኘ)

ኬዎርኮፍ ከዚህም ሌላ የሚታወቀው በፈረንሳይ ሌጌሲዎን ውስጥ የዲፕሎማሲና የማስተርጎም ስራዎችን በመሥራት ነበር። ከአንደኛው አለም ጦርነት በኋላም የትውልድ ሃገሩ አርሜንያ ስትመሰረት ብዙ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። በ1911 ዓ.ም. ከጓደኞቹ ጋር በመሆን 1000 የእንግሊዝ ባውንድ አዋጥተው ለአዲሲቷ አርሜንያ አውሮፕላን አበርክተው ነበር። በ1911 ዓ.ም. ደግሞ ለአርሜኒያ በኢትዮጵያ ተወካይ (እንደ አምባሳደር) ሆኖ ተመርጦ ነበር። ኬዎርኮፍ የፈረንሳይ እና የኢትዮጵያ መንግሥቶች የክብር ኒሻን ተሸላሚ እንደነበርም የወቅቱ ጋዜጦች ዘግበዋል።

በ1919 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ውስጥ አርመን ኮሚኒቲ ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል። ቀደም ብሎም በ1915 ዓ.ም. በአርመን ፖለቲካ ልዩነት የተነሳ ሶስት ቦታ ተከፋፍሎ የነበረውን የአርመን ትምህርት ቤቶች በማዋሃድ አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት (National Armenian Kevorkoff School) ብሎ ሰይሞ አቋቁሞት ነበር። እስካሁንም ይህ ትምህርት ቤት በአራት ኪሎ አርመን ሰፈር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እንዲሁም የኢትዮጵያ ባንክ (Bank of Abyssinia) ቦርድ አባል እና የሎተሪ ኮሚሽን አማካሪ ሆኖ አገልግሏል።

በጣልያን ወረራ ዋዜማ ኬዎርኮፍና ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጋ ነጋዴዎች በአንድነት ግማሽ ሚሊዮን ብር አዋጥተው ለኢትዮጵያ የጦርነት ወጪ ድጋፍ ይሆን ዘንድ ለቀዳማዊ ኀይለሥላሴ አበርክተው ነበር። ይህንንም ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ በታህሳስ 2 1928 ዓ.ም. እትሙ ዘግቦታል።

በ1928 ዓ.ም. ጣልያን አዲስ አበባ በገባ ጊዜ በፈረንሳዊነቱ ምክንያት ንብረቱ በሙሉ “የጠላት ንብረት” ተብሎ እንደተወረሰበት ይነገራል። በዚህም የተነሳ ወደ ፈረንሳይ ተሰዶ፣ በማርሴይ ውስጥ እንደሞተ ይነገራል።

ታዲያ እሱ ቢያልፍም፣ አሻራውን በአዲስ አበባችን ኪነ ሕንጻ ላይ ትቶልን አልፏል።

.

የጽሑፍ ምንጮች

 1. “The City and Its Architectural Heritage Addis Ababa 1886-1941” by Fasil Giorghis and Denis Gerard
 2. “Old Tracks in the New Flower – A Historical Guide to Addis Ababa” by Milena Batistoni and Gian paolo Chiari
 3. “L’Empire D’Ethiopie : le Miroir de l’ethiopie moderne 1906-1935”  by Adrien Zervos
 4. “ይምጡ በዝና፤ አዲስ አበባ” በያሬድ ገብረ ሚካኤል (1958 ዓ.ም)
 5. “Urban Africa: Changing Contours of Survival in the City”  by Abdou Maliq Simone & Abdelghani Abouhani
 6. “Out of Africa and into America, The Odyssey of Italians in East Africa” by Enzo Centofanti
 7. “Moderns Abroad: Architecture, Cities and Italian Imperialism” by Mia Fuller
 8. “La fanfare du Négus”  by Boris Adjemian
 9. “The Dramatic History of Addis Ababa  The Capital’s Armenians” by Richard Pankhurst
 10. “ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ” – ግንቦት 29 1927፣ መጋቢት 29 1919፣ ሐምሌ 21 1919 እትሞች
 11. “አእምሮ ጋዜጣ” – መጋቢት 14፣ 1921 እትም
 12. “አጤ ምኒልክ በሐገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች” በጳውሎስ ኞኞ 2003 ዓ.ም.

የኢንተርኔት ምንጮች

 1. http://armenianweekly.com/2015/05/06/remembering-the-armenians-of-ethiopia/
 2. http://www.failedarchitecture.com/le-corbusiers-visions-for-fascist-addis-ababa/
 3. http://www.africantrain.org
 4. https://gasparesciortino.wordpress.com/
 5. http://senato.archivioluce.it/senato-luce/home.html
 6. http://www.samilitaria.com/SAM/

የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ደራሲዎች

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 3)

በተአምራት አማኑኤል

[1936 ዓ.ም]

(… ከክፍል ሁለት የቀጠለ)

የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ደራሲዎች

፩ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ የሱስ

አለቃ ታየ ሲጽፉና ሲያስተምሩ በነበሩበት ጊዜ፣ ፊት ኤውሮጳ ኋላም ኢትዮጵያ ሁነው ላማርኛ አጻጻፍና ንግግር ብዙ ትጋት ያሳዩ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ የሱስ ናቸው። በወጣትነታቸው ለትምህርት ወደ ኤውሮጳ በመሔዳቸው፣ በነገር አስተያየትም መልክ ባለው ንግግር አሳብን በጽሕፈት በመግለጥ ልዩ ስጦታ ያላቸው ደራሲ ናቸው። የሕይወታቸው ታሪክ ግን እጅግ የሚያሳዝን ነው።

የዛሬ 50 ዓመት አቅራብያ ዕድለኛ ሁነው ከጃንሆይ ካጤ ምኒልክ ተመርጠው ለትምህርት ወደ ኤውሮጳ ተላኩ። የጣልያን የጦር አለቃ ባራቲዬሪ (1888 ዓ.ም) መልሶ ወደ ሮማ እስኪልካቸው ድረስ፣ ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ተሰልፈው ዓዲግራት ድረስ መጡ። ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሳትረሳ፣ ይቅርታ አድርጋ፣ በልጅ ኢያሱ አልጋ ወራሽነት ጊዜ ለትልቅ ሥራ አጨቻቸው።

ለዚህ ወረታ ወጣቱን የኢትዮጵያን አልጋ ወራሽ ልጅ ኢያሱን በሚያምር ንግግር በማሞገስ ደስታቸውን ገለጡ። በእውነትም ልጅ ኢያሱ ባልሆኑ ካጤ ምኒልክ ጋራ የሠሩት መሳፍንትና መኳንንት ሁሉ ተቀይመዋቸው ነበር። አሳባቸውም የነበረ በቤተ መንግሥት ሥራ ለማስያዝ ይቅርና የኢትዮጵያን መሬት እንዳይረግጡ ለማድረግ ነበር። የኢትዮጵያ ባላባቶች የልጅ ኢያሱ ሥራ አጀማመር ብዙ የሚያሠጋ ሁኖ ታይትዋቸው ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ባስገደድዋቸው ጊዜ፣ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከዚያ ሁሉ ሰው አብልጠው ለኢትዮጵያ የተቈረቈሩ መሆናቸውን ለማስረዳት፣ የሚያምረውን ግጥማቸውን የልጅ ኢያሱ መስደቢያ በማድረጋቸው አበላሹት።

እንኳን ይህን፣ ከጠላት ጋር አገራቸውን ሊወጉ የተሰለፉትን በደል የቤተ መንግሥት አስተዳደሮች ትተውላቸው ነበር። አሁንም ንግሥት ዘውዲቱና ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ ሁነው የመንግሥቱን ሥራ ሲያካሒዱበት በነበረ ጊዜ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ተቀበሉ። ከቶውንም በሚኒስትርነት ሥራ ወደ ሮም ተላኩ። ጠላት አገራችንን ሲያጠፋት፣ አሁንም ተመልሰው ለጣልያን ዋና ሠራተኛ ሆኑለት። አገርን ለያዘ ጠላት ሳያስፈልግ ማገልገል እንኳ ከመነቀፍ ቢያደርስ፣ ይህ አልበቃ ብሎ ለጠላት ታማኝነታቸውን ለመግለጥ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ጀምረው እስከ ተራው አርበኛ ድረስ የማይጠጋውና ያልሆነ ቃል በመጻፍ ብዕራቸውን አበላሹ።

ተራ ጸሐፊ ቢሆኑ የሚያሳዝነውን የሕይወታቸውን ታሪክ ሳላነሣው በቀረሁ። ነገር ግን ፕሮፌሰር አፈወርቅ እኛ ላለንበት ትውልድ ዋና ደራሲው ናቸው።

afework-grammarafework-grammar-2

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ባማርኛ ከጻፍዋቸው መጻሕፍት፣ “የአጤ ምኒልክ ታሪክ” እና “ልብ ወለድ ታሪክ” ዋና ሁነው ይታዩናል። የነርሱን አኳኋን ከማስታወቃችን በፊት የአማርኛ ቋንቋ ሕጉንና ሕዝቡ የሚወደውን የንግግር ወይም ያጻጻፍ ዓይነት እናመልክት። ከሕጉም ርቀው አዲስ አካሔድ የሰጡን ደራስያንና የተለምዶውን ንግግርና አጻጻፍ ሳይለቁ ጣዕም ያለበት ለማድረግ የቻሉትን ካልቻሉት ለመለየት ይረዳናል።

የአማርኛ ቋንቋ ከብዙው ሕገጋቱ አንዱ፣ ማሰርያ አንቀጽን ከንግግር መጨረሻ ማግባት ነው። ከጽሕፈት ላይ ባንድ ማሰርያ አንቀጽ ውስጥ ባሉት ቃላት ማኽል ጣልቃ እያገባ ልዩ ልዩ አሳብና ንግግር በሚጨምርበት ጊዜ፣ ዋናውንና ጣልቃ የገባውን ከውኖ ለማስተዋል እንዲመች ሊያደርጉ የቻሉ ስጦታ ያላቸው ደራስያን ብቻ ናቸው። ደራሲው ሙሉውን ንግግር ባማርኛ ባሕርይ በሚያስኬድበት ጊዜ ደግሞ ሰነፍ አንባቢ እንዳይታክተው ለማድረግ ያሰበበት እንደሆነ፣ ንግግሩን ባጭር ባጭሩ በማሰሩ ላንባቢ መመቸቱ እርግጥ ነው።

ቢሆንም ደራሲ በፊተኛው (በረጅሙ) አካሔድ ሲጽፍ አንባቢው በውጥን ጭርስ አካሔድ አስሮ ለንግግሩ ደራሲው ያላሰበውን አሳብ ከመስጠት የሚደርስበት ጊዜ አለ። ደራሲው በሁለተኛው አካሔድ (ባጭሩ) ሲጽፍ አንባቢው አሁን ካመለከትነው ስሕተት አይደርስም። ግን ንግግሩን ባንድ ማሰሪያ አንቀጽ ሊጠቀልል ሲሽል ደራሲው እያቋረጠ በመናገር አንደበቱን ያልረታ ሕፃን ሊመስል ነው። ንግግሩንም በመጠኑ ካማርኛ ባሕርይ የራቀ ሊያደርገው ነው። ዋና ደራሲ የምንለው፣ በረጅሙም ሆነ ባጭሩ አካሔድ ጽፎ፣ ንግግሩ ግልጽ እና ጣዕም ያለው ሲሆን ነው።

afework-guide
የአፈወርቅ ገብረየሱስ “Guide de Voyage”

በኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ሲበዛም ሲያንስም በልዩ ልዩ ሕዝብ (ይልቁንም በምሥራቃውያን) የተለመደ አካሔድ በሁለት፣ በሦስት ፍች የሚተረጎም ቃል እየፈለጉ ከንግግር ማግባት ነው። እንዲህ ያለው አካሔድ “አማርኛ” ወይም “ስለምን” ይባላል። ይህም በኢትዮጵያ እጅግ የተወደደና የተለመደ ንግግር ነው። እንዲህ ያለውን ንግግር የሚያመጣንም ሰው ሁሉ የንግግር ዕውቀት ያለው ሰው በመሆኑ የሚከራከርበት አይገኝም።

ሁለተኛ፣ በአሳብ ከልብ ፈጥሮ ደጉንና ክፉውን በምሳሌ በሚገልጽበት ጊዜ፣ ክፉውንና ደጉን የሚገልጡበትን ሰዎች አንባቢው በግብራቸው ባሕርያቸውን እንኳ ቢለይ፣ ደራሲው በ”ምሳሌ ስም” በአሳቡ የፈጠራቸውን ሰዎች “አቶ ክፉ ሰው”፣ “አቶ ደግ ሰው”፣ “ወይዘሮ ዓለሚቱ” ይህንንም በመሰለ ስም ይሰይማቸዋል። እንዲህ ያለው አካሔድ አብዛኛውን ጊዜ ችክ ይላል። ስለሆነም በደራሲዎችና በሕዝቡ ተለምዷል፤ ተወዷልም።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከዚህ በላይ “ስለምን” እና “ምሳሌ ስም” ያልነውን አካሔድ በብዙው አይከተሉትም። በተከተሉበት ጊዜም፣ አንባቢው ሳይሰለች አሳባቸውን እንዲያስተውል አድርገዋል። ሙሉው ንግግራቸው ያማርኛን ባሕርይ እየተከተለ በረዘመበት ጊዜም ቢሆን፣ ግልጥና ያማረበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ብቻ ቅጽል ሲያበዙ ነገሩ ጉት ይሆንባቸዋል። ፕሮፌሰር አፈወርቅ በደራሲነታቸው ሙቀት ያለበት ንግግር ማምጣት ዋና ባሕርያቸው ነው። ሙቀቱም የሚገባ ወይም ተሸጋጋሪ በመሆኑ፣ አንባቢው አሳባቸውንም በማይቀበልበት ጊዜ መሞቁ አይቀርም። በጽሑፍ ሥራቸው የሚያነሡት ሰው ወይም እንስሳ፣ ጫካ ወይም በረኻ ሁሉም ሕይወት ያለበት ሁኖ ይታያል።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ “የአጤ ምኒልክ ታሪክ” እና አንድ ልብ ወለድ ታሪክ ጽፈዋል። የቀሩት በጣልያንና በፈረንሳይ ቋንቋ የጻፏቸው መጻሕፍት የአማርኛን ሰዋስውና የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያስታውቁ ናቸው።

afework-menelik

ፕሮፌሰር አፈወርቅ የአጤ ምኒልክን ታሪክ ሲጽፉ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ከደረሰባቸውና ከሠሩት ዝርዝር ሳይገቡ ዋና ዋናውን ብቻ አመልክተዋል። ጥቂት ዝርዝር ያለበት፣ ስለ አጤ ምኒልክና የኢጣልያ መንግሥት መልእክተኞች የሚናገረው ክፍል ነው። የአጤ ምኒልክን ታሪክ ባጭሩ ካመለከቱ በኋላ የጣልያን መንግሥት መልእክተኞች ፕሮፌሰር አፈወርቅን እንዲረዷቸው በገንዘብ ሳይቀር ሊያባብልዋቸው እንደሞከሩ፣ እርሳቸው ግን ሳይታለሉላቸው በመቅረታቸው የንጉሣቸውን ፖለቲካ እንደደገፉ ለማስረዳት ይጣጣራሉ። በንግግራቸው ለምኒልከና ለሸዋ ሲሆን፣ ቁልምጫውንና ቃለ አጋኖውን ማብዛታቸው፣ ለሌላው ወረዳ ባላባትና ሕዝብ ሲሆን፣ ማዋረዳቸውና መሳቂያ ለማድረግ መታገላቸው፣ ለባለ ታሪክ የተገባውን እውነተኛ ሚዛን የያዙ በመሆን ፈንታ፣ ከዳተኛ ካለቻቸው አገራቸው ጋር ለመቃረብና የመንግሥቱን ሥራ የያዙትን ደስ ለማሰኘት የተነሡ ያስመስላቸዋል። ግን ደግሞ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከባለ ታሪክ ልዩ ሥራ አንዳንዱን እንዳልዘነጉትና ለታሪክ ንግግር አዲስ መንገድ እንደ ጠረጉለት አጭሩ የምኒልክ ታሪክ እንደሚያስረዳ ማስታወቅ ይገባናል።

afework-tobya

“ልብ ወለድ ታሪክ” ለኢትዮጵያ የፈጠራ መጀመሪያ መጽሐፍዋ ነው። ከዚህ በፊት እንዳመለከትሁት ያገራችን ደራሲ አሳቡን በጽሕፈት ለመግለጥ ባሰበበት ጊዜ ባሳቡ የሚፈጥራቸው ሰዎች የግብራቸውን ስም የተጸውዖ ስም አድርጎ “አቶ መልካም ሰው”፣ “አቶ ክፉ ሰው” የሚሉትን አካሔድ ብቻ ይከታተል ነበር። የዛሬው ሰው የፕሮፌሰር አፈወርቅንና የኤውሮጳን መጻሕፍት በማንበቡ ልብ ወለድ ታሪክ ለመጻፍ ይጣጣራልና በር ከፋቹ ፕሮፌሰር አፈወርቅ በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋል።

የፕሮፌሰር አፈወርቅ ልብ ወለድ ታሪክ የሚነግረን የሁለት ወጣቶችን ፍቅር ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁነው፣ ሃይማኖታቸው የወንድየው እስላም የሴቲቱ ክርስቲያን ነው። ከሁለቱ በፍቅር ድል ሁኖ የወዳጁን ሃይማኖት የተቀበለ ወንድየው ነው። መጽሐፉ የፍቅር ኃይል ብርቱ መሆኑንና የንጹሕ ፍቅር አካሔድ እንዴት መሆን እንደሚገባው ይተርካል። እግረ መንገዱን ደግሞ፣ የዛሬ ሰባት ወይም ስምንት መቶ ዓመት በኢትዮጵያ ሲደረግ ከነበረው ሥራ ከብዙው ጥቂቱን ያመለክተናል።

ደራሲው የጽሕፈት አገላለጣቸው ደግ ሲሆን፣ ምክንያት ለመፍጠር ብዙ መንገድ አልተገለጠላቸውም። ባሳባቸው የፈጠሯቸው ሰዎች ለሚፈጽሙት ሁለት ሦስት ልዩ ልዩ ሥራ አንድ ምክንያት ሰጥተው፣ ያንኑ አንዱን ምክንያት ሳይለውጡ፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ደጋግመውታል። ይህንና ሌላውን ያደራረግ ብልሐት (የቴክኒክ ጣጣ) የዋናው ሥራቸው ንድፍ ተስተካክሎ በመሔዱ አንባቢው እንደሌለ ይቆጥረዋል። ይህም አንድ ኪነ ጥበብ ነው።

ፕሮፌሰር አፈ ወርቅ ሁለት ሦስት ያህል ቲያትር ጽፈዋል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሰው በቲያትር ጨዋታ አላያቸውም ደግሞም አልታተሙም።

እንደዚኸው ሁሉ ብዙ ደራስያን ጽፈው ያላሳተሙ አሉና ሥራቸው በሕዝብ ስላልታወቀ ስለነርሱ ለመጻፍ ከዚህ ሥፍራው አይደለምና እንተወዋለን። ቢሆንም ከነዚህ ያንዱን የበጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትን ስም ማስታወስ የተገባ ነው።

፪ በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም

teklehawaryat-photo-2

አገራቸው ሸዋ፣ የተወለዱበት ዘመን ደግሞ 1875 ዓ.ም ግድም ነው። እርሻና የወታደርነት ሥራ በሞስኮብና በፈረንሳይ አገር ተምረው በኢትዮጵያ መንግሥት ከፍ ባለ ልዩ ልዩ ሹመት ላይ ኑረዋል። በመጨረሻ ጊዜም በፓሪስና በዤኔቭ የኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስትር ሁነው ነበር። ፍጹም አማርኛ በሆነ ግጥም ጥቂት ተረት ጽፈው ካሳተሙና በተረት ዓይነት ቲያትር ከጻፉ በኋላ፣ አሁንም ንጹሕ በሆነ አማርኛ ስለ እርሻ ትምህርት ጽፈዋል።

teklehawaryat-ershaበዚህም መጽሐፍ በአማርኛ ቃል ላልተገኘለት ለኬሚስትሪና ለሌላው ዕውቀት የተመረጠ ቃል በመገኘቱ ዕውቀትን በእውነት እጅ ካደረጉት ለደራሲ ቋንቋን እንደልቡ ማዘዝ እንደማያስቸግር ያስረዳል። በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ለኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መግለጫ የተናገሩትና የጻፉት ደግሞ የተሰወረን አሳብ ለመግለጥ ችሎታ እንዳላቸው ያስረዳል።

፫ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ

ነጋድራስ ገብረሕይወት ትውልዳቸው ትግሬ ሲሆን ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ሙተዋል። በልጅነታቸው ነምሳ (ኦስትሪያ) አገር ብዙ ተቀምጠው በትምህርታቸው ተጠቅመዋል። ከጻፉት አብዛኛው ጠፍቶ በሕይወታቸው ሳሉ ስለ አጤ ምኒልክና የኢትዮጵያ ሕዝብ በኤርትራ ሲታተም ከነበረ ጋዜጣ አሳትመዋል። “የመንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” ብለው የሰየሙትን መጽሐፍ ከሞቱ በኋላ ወዳጆቻቸው አሳትመውታል።

በሁለቱም ሁሉ መጻሕፍት ኢትዮጵያዊ በሚረዳው አካሔድ የቤተ መንግሥቱ ሥራ ማሻሻል እንዳለበት ሰብከዋል። ሁለቱም መጻሕፍት ደራሲው በልበ ሙሉነት ስለሚገልጡት ከፍተኛ አሳብና ስለ ንግግራቸው ጥራት ምስክር ናቸው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ብዙ ጉዳይ ለማሠራትና፣ ለወደፊት ሕግንና ልማድን እያሻሻሉ ለማደስ ስላለብን ሥራ፣ ብርቱ አሳብ የሚያሳድሩ የሚያስፈጽሙም መጻሕፍት ናቸው።

(በክፍል አራት ይቀጥላል …)