ፈጠራ ድርሰት/ጥበባዊ ዜና/አስተያየት ላኩልን
አዲስ አዲስ ድርሰት ድረሱ
የግፈኛው የፋሽስት መንግሥት አገዛዝ ከሀገራችን ጠፍቶ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በእግዚአብሔር ኃይል ጠላታቸውን ድል አድርገው ተመልሰው በዙፋናቸው በመቀመጣቸው ይህን የደስታ ዘመን ተከትሎ አዲስ የመጻሕፍት የድርሰት ዘመን መጥቷል ለማለት ይቻላል።
ነቢዩ ኢዩኤል “እግዚአብሔር በሕዝቡ ልብ የእውቀት መንፈስ ያሳድርበታል፤ ስለዚህ ወጣቶች ጉልማሶችና ቈነጃጅት ደናግል ራእይ ያያሉ፣ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ እንደተናገረ ዛሬም በግርማዊ ጃንሆይ ስለተደረገልን ታላቅ ክብርና ነፃነታችን ስለተመለሰልን የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሉ አዲስ አዲስ ድርሰት ለመድረስና ጥዑም ጥዑም የሆነ ግጥም ለማጻፍ አእምሮዋቸው ታድሶ፣ ሕሊናቸው ተቀስቅሶ፣ ይህንኑ መልካም ሐሳብ ሲከታተሉ እናያለን።
ይህንም ለማስረዳት ግርማዊ ጃንሆይ አዲስ አበባ ከገቡ ጀምሮ የቃል ንግግር የጅ ጽሕፈት የሚያውቁ ብዙ ወጣቶች በፊትም ስማቸው የታወቀው ጸሐፊዎች ብዙ ዓይነት ግጥምና ልዩ ልዩ ዓይነት ድርሰት እያመጡ እንዲታተምላቸው ጥያቄ ያደርጋሉ። ከነዚህም መካከል ድርሰታቸው እየታተመ ያለዋጋ ለሕዝብ እንዲታደልላቸው የሚፈቅዱት ይበዛሉ።
ይልቁንም የጊዜው ክብርና የንጉሠ ነገሥታችን ፍቅር ስለተሰማቸው ከሴቶችም መካከል ብዙዎቹ በዚሁ ነገር ሐሳባቸው ስለተነሣሣ የደስታቸው መግለጫ የሚሆን ድርሰት ሊጽፉ ስለቻሉ ከላይ እንዳልነው ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረው ቃል ለዛሬው ጊዜ ተስማሚ ሁኗል። ይህንም አድራጊው የሀገርና የንጉሥ ፍቅር ነው። ከዚህ ከሚያስገርመው ከአእምሮ ንቃት የተነሣ መንግሥታችንን በጣም ደስ ብሎት ሊያነቃቃቸውና ሊያተጋጋቸው ፈቃዱ ሁኗል።
ይህም የተሰበሰበው ግጥምና ድርሰት ሁሉ በየጸሐፊው ስም እየታተመ ለአዋቂዎች አእምሮ የእውቀት መክፈቻና ለሕፃናቱም የአፍ መፍቻ እንዲሆን የሚታተምበት ዱሮ የአእምሮ ጋዜጣ ማተሚያ ቤት መከፈቱን ለጸሐፊዎቹና ለደራሲዎቹ ስንነግራቸው መጻሕፍትን ለመመልከትና የሥልጣኔን ሥራ ለመከተል ፈቃድ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በጣም ደስ እንዲላቸው እንተማመናለን።
በውነትም ይህ ሐሳብ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው። በምሳሌ “በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” ተብሎ እንደሚነገረው ሁሉ ይህ የዛሬው አዲስ ታሪክ በግጥምም ሆነ በንባብ ተጽፎ ታትሞ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲነበብ የኖረ እንደሆነ የዘመን ሐውልት ሁኖ ይኖራል።
ይሁን እንጂ ይህም የድርሰት ትንሣኤ ንባቡ ከምሥጢሩ፣ አጻጻፉ ከመስመሩ የወጣ እንዳይሆንና ደንቡን እንዲጠብቁት፤ ይልቁንም ፍሬ ነገሩ ከቁም ነገር እንዲደርስ ደራሲዎቹ ያጻጻፉን አኳኋን በሥርዓት እንዲመለከቱትና እንዲአስቡበት ያስፈልጋል። ቤቱ እንዳይፈርስ ሲባል የመጨረሻውን ፊደል ብቻ ቢከተሉ ምሥጢሩ ይፈርሳል። ስለዚህ በግጥም አጣጣል ላይ ታላቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
እኛም እስካሁን የተቀበልናቸው ግጥሞችና ድርሰቶች ሁሉ የሐሳባቸው ግንኙነትና የምሥጢራቸው አካሔድ ዓይነቱ አንድ ነው። እንዲሁም ለመሆኑ የሚበቃና የሚገባ ምክንያት አለው።
ግርማዊ ጃንሆይ ለሕዝባቸውና ለነፃነታችን ሲሉ ከሔዱበት ተመልሰው ጠላታችንን ድል አድርገው በታላቅ ግርማ ከዙፋናቸው ስለተቀመጡና በመሣሪያ ብዛት ከሚበልጧቸው ጠላቶች ጋራ ስለነፃነታችን አምስት ዓመት ሙሉ ታግለው ያንኑ ጥንታዊ ጠላት ጥለው ኢትዮጵያን ከወደቀችበት ስላስነሷትና ትንሣኤዋን ስላሳዩን ጸሐፊዎቹ በአጻጻፋቸው አልተሳሳቱም።
ስለዚህም የተገጠሙት ግጥሞችና ድርሰቶች ሁሉ ምንም አነጋገራቸው ቢለይ ሐሳባቸውና ውስጠ ምስጢራቸው አንድ ነው። ስለዚህ እነዚህ ስለ አዲሱ ዘመንና ስለ ግርማዊ ጃንሆይ ድል አድራጊነት የተገጠሙት ግጥሞችና ድርሰቶች አንድነት ተሰብስበው እንደ ምዕላድ ወይም እንደ መዝገበ ቃላት ሁነው በመጽሐፍ አኳኋን ታትመው፣ በጥራዝ ተያይዘው፣ በመልካም ተሰርተው አሁን በቅርቡ ጊዜ ይወጣሉ። አንድነትም ተሰብስበው መታተማቸውና በጥራዝ መገናኘታቸው የያንዳንዱ ጸሐፊ ሐሳብ በተፈለገ ጊዜ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ በቶሎ እንዲገኝና ለየብቻው የሆነ እንደሆነ ከማነሱ የተነሣ ጥራዝ ሳይኖረው ቀርቶ ተቆነጻጽሎ የትም እንዳይወድቅ ነው።
ወደፊት ግን የሚጻፉት ግጥሞችና ድርሰቶች ከልዩ ልዩ ታሪኮችና ከሌሎችም ሐሳቦች የተስማሙና የተቀመሙ እንዲሆኑ ይገባል። እኛም እንደዚህ ያለ ሐሳብ ሲመጣ በደስታ ተቀብለን እንዲታተም እናደርጋለን። ያጻጻፉንም አኳኋን ከዚህ በታች በጥቂቱ እናሳያለን።
መቼም ሁሉ ነገር ሊሠራና ሊጻፍ የሚቻለው ሥነ ፍጥረትንና ታሪክን መሪ በማድረግ ስለሆነ ስለ ሀገራቸው ቁንጅናና ስለ ማናቸውም ፍጥረት ውበት ወይም ስለ ሰው ሕይወትና በዚህ ዓለም በሰው ላይ ስለሚፈራረቁ ሐዘንና ደስታ፣ ስለሚመጣበትም መከራ ሁሉ በፍልስፍና ሐሳብና በመርማሪ አእምሮ አዲስ አዲስ አይነት ድርሰት መጻፍ ብዙ ዓይነት ምሥጢር ይገልጻል። ልቡናንም ያራቅቃል። በሰው ፍቅርና በማኅበር ደንብ በወንድና በሴቶች መካከል ይህንም በመሰለው የደስታ ምክንያት በሚሆነው ሁሉ ያለው አኳኋን በልብ ወለድ ሲጻፍ ጥሩ የሆነ አንድ ዓይነት መጽሐፍ ሊወጣው ይችላል።
ከነዚህም ሌላ ብዙ ስልትና ዓይነት የሚገኝባቸው ሐሳቦች ይገኛሉና በጥልቅ እየመረመሩና እየተመራመሩ ከፈላስፎችና ከሊቃውንቶች መጻሕፍት ጋራ እያስተባበሩና እያገናዘቡ ጽፎ ማቅረብ አጥንት የሚያለመልምና ልቡና የሚያራቅቅ ይሆናል። ስለዚህ ለድርሰት የሚሆኑትን ቃሎች አስቀድሞ በሐሳብ ማደራጀትና ያጻጻፉን ሥርዓት በመልክ በመልኩ ማሰቀመጥ ያስፈልጋል። እንዲህ የሆነ እንደሆነ የቃሉና የነጥቡ አጣጣል ትክክለኛ ይሆናል፤ ይህም ከተካከለ ምሥጢሩም ሆነ ንባቡ አይቃወስም።
ግጥም ድርሰት
ከዚህ ቀድሞ በተቀበልናቸው በብዙዎቹ ድርሰቶች ውስጥ በነጥቡ አጣጣልና በሐሳቡ ድርድር ውስጥ አንድ አንድ ድርሰትነቱ ያልተስማማ አካሄድ ይገኝበታል። በግጥሞቹም ውስጥ አንድ ላይ ሊጠቀለሉ የሚገባቸው መሥመሮች በደምብ ሳይጠቀለሉ መለየት የሚገባቸው በሥርዓት ሳይለዩ ይገኛሉ።
ስለዚህ የግጥም ጸሐፊዎች ሁሉ አንዱን ካንዱ ሳያቃውሱ ባንድ ግጥም ውስጥ አንድ ዓይነት አጻጻፍ መከተል ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም አሳታሚዎቹ የሚሰጡት ምክር ለአጻጻፉ ደንብና ሥርዓት እንዲኖረው ብቻ ነው እንጂ የጽሕፈቱን ዓይነትና ስልት የሚመርጠው ደራሲው ነው።
ለምሳሌ፣ የግጥም ደራሲዎች እንደምሥጢሩ መርዘምና ማጠር አንዳንዱን ሐሳብ በሁለትና በሦስት ወይም ባራት መስመሮች ሊወስኑት ይችላሉ። አለዚያም እያዘዋወሩ ለማከናወንና ግጥምነቱን ለማስማማት ይቻላል። ይሁን እንጂ ባንድ ድርሰት ውስጥ አንድ ዓይነት አጻጻፍና ላጻጻፉም ደንብ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አለመዘንጋት ነው።
ከዚህም ሌላ ለደራሲዎቹ የምናስታውቃቸው ነገር እንዲህ ነው። ግጥም ሲጻፍ ቃሉን ለማሳመርና አቀማመጡን ብቻ ለማስተካከል ሲባል ሐሳቡ እንዳይፋለስ ወይም እንዳይሰባጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ግጥም የሚመሰገነው ቃሎቹ ወይም ፊደሎቹ በትክክል በመግጠማቸውና የዜማቸው ቃና ለጆሮ በመጣፈጡ ብቻ አይደለም።
በውነቱ የተመለከትን እንደሆነ የግጥሙ ቋንቋ ቤት ሳይመታ እንደ መዝሙረ ዳዊት በመስመር ብቻ ሊጻፍ ይችላል። ይህንም ለመረዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥና የኢዮብን መጽሐፍ ብቻ መመልከት ይበቃል። ስለዚህ የግጥሙን ደረጃዎች ከዚህ በላይ እንደተባለው መከታተል ይቻላል። ይህን ትቶ ለቤት ተብሎ የመጨረሻውን ፊደል ብቻ ለመከታተል ሐሳቡን ማፍረስና የሚጠቅመውን ሐሳብ መተው አስፈላጊ አይደለም።
ግጥም የሚመሰገነው መጀመሪያ ስለ ሐሳቡ ትክክለኛነት፣ ሁለተኛ ይህንኑ ትክክለኛውን ሐሳብ ባማረ ቋንቋ በመጻፍ ነው እንጂ የቤት አመታቱን በፊደል እንከተላለን ሲባልና የመዝሙሩን ቃና እናሳምራለን ሲባል ንባቡንና ምሥጢሩን ሳያስተካክሉ ሐሳቡን በእንዲህ ያለ አኳኋን በመግለጽ ብቻ አይደለም። ስለዚህ ለደራሲዎቹ የምናስታውቃቸው በግጥማቸውና በሐሳባቸው ትክክለኛውን ሚዛን ብቻ እንዲጠብቁ ነው።
ትያትር ድርሰት
እስካሁን ድረስ በቀረቡልን ድርሰቶች መካከል የትያትር መጽሐፍ ጽፎ ያቀረበልን አንድም የለም። ወደፊት ግን ጸሐፊዎቹ ሁሉ የትያትር መጽሐፍ በልዩ ልዩ ዓይነት ሐሳብ እየጻፉ እንዲያመጡልን እንተማመናለን።
ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በግፍ ወርረው አዳዲሶቹን ድርሰቶች ከማጥፋታቸው አስቀድሞ በኢትዮጵያ የትያትር ድርሰት ተስፋፍቶ ጥቅሙም ታውቆ ነበር። ይኸውም ሊታወቅ ከነ አቶ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ከነሐዲስ ዓለማየሁ፣ ከነ አቶ መልአኩ በጎሰው፣ ከሌሎችም ብልሆች ሁሉ ተደርሰው የነበሩት የትያትር መጻሕፍቶች ሥራቸውም ምሥጢራቸውም ብዙ ዓይነት መንገድ ያመለክት ነበር።
ይኸውም በእንግሊዝ አገር በንግሥት ኤልሳቤጥ ዘመን እነ ሼክስፒርና እነ ቤን ጆንሰን፣ በፈረንሣዊ አገር በ14ኛው ሉዊ ዘመን እነ ሞዬርና እነ ራሲን ያስነሷት እንደ መስከረም ፀሐይ የምታንጸባርቀው የትያትር ዘመን ተጀምራ እንደነበረው ነበር። በዚህ ምክንያት ከኢትዮጵያና ከኢጣልያ ጦርነት አስቀድሞ በትያትር ድርሰት ከፍ ያለ ጥበብ ለማሳየትና ብዙ የሥልጣኔ እርምጃ ለማመልከት ባለትያትሮቹና የትያትር ሠራተኞቹ በሥራው ስለሠለጠኑበት ዘመኑ አዲስ ዘመን ሆኖ ነበር።
አሁንም ይህ የተጀመረው ታላቅ ሥራ እንዲቀጥልና ፍሬውን እንዲያሳይ ምኞታችን ስለሆነ ረቂቅ ሐሳብ ያላቸውና ተመልካች አእምሮ ያደረባቸው ሁሉ በግጥምም ሆነ በተራ ንባብ፣ በልዩ ልዩ ዓይነት ምሳሌና ተረት፣ ወይም በልብ ወለድና በፍልስፍና ሐሳብ እየጻፉ እንዲልኩልን በተስፋ እንጠብቃለን።
የትያትር ጥቅሙ በብዙ ወገን ስለሆነና በቁም ነገሩ ውስጥ ማጣፈጫና የደስታ ፊት መግለጫ የሆነ ሐሳብ ስለሚገኝበት ሐዘን ያስረሳል። የሥራውም አኳኋን በዓለም ላይ ስላለው ስለማናቸውም ነገር ስለሆነ የተሠወረውን ጥበብ በምሳሌ ሲገልጽ ደስ ያሰኛል። ደግሞም ለፍጡር በጣም ጥጋብ እንዳይሰማው ባለትሕትና የሚያደርገውን መንፈሳዊ ሐሳብ በጨዋታ አስመስሎ ሲገልጸው የሰውን ልብ አዛኝና ርኅሩኅ ያደርጋል።
ይሁን እንጂ፣ ለግጥምና ለሌሎቹ ድርሰቶች እንደተባለው ሁሉ ለትያትር አጻጻፍም ሐሳብ ማሻሻልና ያጻጻፉን ደንብ ማስተዋል ያስፈልጋል።
ከዚህ ቀደም የተጻፉት ትያትሮቻችን ሁሉ በጊዜው ፖለቲካና በሕዝብ አኗኗር በክርቲክ ላይ መጻፋቸውን አንርሳ። አሁንም ቢሆን ጸሐፊዎቹ ለማሻሻል የሚያስፈልገውን የፖለቲክ አካሄድና የሕዝብ አኗኗር ወይም አስተዳደር ክርቲክ እያደረጉ ሐሳባቸውን አይስጡ ማለታችን አይደለም። ነገር ግን ይህቺ ዘመን በኢትዮጵያ ወደፊት ሥራ የሚሠራባት ጊዜ ናትና “ይህ ሥራ አላማረም”፣ “ለዚህ ክፍል ይህ ይጐድለዋል” ከሚለው ዓይነት ድርሰት ይልቅ “እንደዚህ ይደረግ”፣ “ለዚህ ክፍል ይህ ቢጨመር ይሻላል” እያለ አዲስ ሐሳብ ለሚአቀርበው ዓይነት መጽሐፍ መጀመሪያውን ቦታ ለቆ ሁለተኛውን ቦታ ቢይዝ ይሻላል።
የጥበብ መጻሕፍት ደራሲዎች በማናቸውም ዘመንና በማናቸውም አገር ለአዲስ የሥልጣኔ እርምጃ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ አዋጅ ነጋሪና መሪ ስለሆኑ የኢትዮጵያ ጸሐፊዎች ይህን ተግባራቸውን ተረድተውት ሕዝባቸው አዲስ ሐሳብ እንዲአስብና ላዲስ ለሥልጣኔ ወይም ለጥበብ ሥራ ቀዳሚ መሪ እንዲሆኑት ይገባቸዋል። ባለፉት በስድስት ዓመቶች ውስጥ ሁላችንም የኖርነው በመከራ ስለነበረ በሕዝባችን ሐሳብ የመረረ ነገር ሞልቶበታል። ደግሞም በነዚሁ ዘመናት ውስጥ በሕዝባችን ልብ ውስጥ የተተከለውን ጥልቅ የሆነ ኀዘን የዛሬው ደስታ ቢአሸንፈው እንኳ ፈጽሞ እስኪነቀል ድረስ ጥቂት ጊዜ ማለፉ አይቀርም። ይሁን እንጂ የጨለማ ቀኖች አልፈውልናልና ወደፊት ያለችውን የብርሃን ዘመን በሥራና በተስፋ ለማሳለፍ እንድንሞክር ያስፈልጋል።
እንግዲህ ከዚህ ቀደም ስለደረሰብን መከራ ወደፊት ፈጣሪአችንን እንዳናማርር ኀዘናችንን የሚአስረሳንና ልባችንን ወደ ሥራና ወደ ደስታ የሚመሩ፣ የትካዜ ሰዓት አልፎ የደስታ ጊዜ እንደደረሰ የሚናገሩ ትያትሮች ያስፈልጉናል። የትካዜ ጊዜ አልፋለችና ሕይወታችን እንድትታደስ ትንሽ የጥርስ ፍልቅቅታና የፊት ፈገግታ ያስፈልገናል።
እንግሊዞች ሲተርኩ የሚያስቅ ነገር የሕይወት ጨው ነው ይላሉና ወደፊት ትያትር የሚጽፉልን ደራሲዎች ከዚህ ቀደም ካደረጉት የበለጠ የሕይወት ጨው እንዲጨምሩበት በተስፋ እንጠብቃለን።
የትያትር ደራሲዎች ትያትራቸውን ሲጽፉ ሥራቸውን ለሕዝብ የሚገልጸው በተጨዋቾቹና ጨዋታው በሚደረግበት መንበር፣ ለጨዋታውም በሚለበስ ልብስ በኩል መሆኑን አስታውሰው ለዚሁ እንዲመች አድርገው እንዲጽፉት እናሳስባቸዋለን።
ታሪክ ድርሰት
በዚህ በዘመናችን በጣም ከሚአስፈልጉት መጻሕፍት አንድ አንዱ ታሪክ ነውና የታሪክ ድርሰት ያለው ሰው እንዳለ በደስታ እንቀበላለን። ታሪክ ትልቅ ነገር ነውና ከፍ ባለ ሐሳብ መጻፍ ያስፈልጋል። ታሪኩን የሚጽፉ ሰዎች ሁሉ በውነተኛነትና በትክክለኛነት፣ አድልዎ ሳያደርጉ መጻፍ ያስፈልጋቸዋል። በሐቅ ካልተጻፈ ግን የታሪክ ድርሰት ዋጋውን ያጣና ታሪክ መሆኑ ይቀራል። ስለዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ ትክክለኛውን መንገድ እየተመለከቱ እውነቱን ብቻ የሚገልጸውን ትርጉም ሊሰጡት ይገባቸዋል።
በውነት ላይ መጨመር፣ ወይም ከውነቱ ማጉደል፣ አድልዎም ማድረግ ለታሪክ ጸሐፊዎች የተገባ ነገር አለመሆኑን ባለማዋቅ አንድ አንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በጠባብ ሐሳብ ያንዱን ሕዝብ አኗኗርና አስተያየት ብቻ ተከትለው የጻፉ አሉ። ሌሎች ግን የዓለምን ሕዝብ ሁሉ ሐሳብና አኗኗር ተመልክተው ትርጉሙን አስፋፍተው ይጽፋሉ።
ዛሬ የዓለምን የፖለቲካ የኤኮኖሚክና የሕዝብ አኗኗርን ስንመለከት ጸሐፊዎችን በጠባብ አስተያየት ታሪክ እንዲጽፉ አንመክራቸውም። ለሕዝብ ከሌላው ዓለም ሁሉ ተለይታችሁ ለብቻችሁ የምትኖሩ ናችሁ ብሎ መስበክ ስሕተት ያመጣል። የዓለም ሕዝብ ሁሉ ዛሬ በሥራቸውም በትዳራቸውም እየተጋገዙና እየተባበሩ ነው የሚኖሩት።
የዛሬውም ጦርነት የመጣው ናዚዎችና ፋሽስቶች ለሕዝባቸው ታሪክ ካስተማሩበት አኳኋን ነው። ፋሽስቶችና ናዚዎች “በአገራችሁ ሁሉም ነገር ይገኛል፤ በንግድና በኤኮኖሚክ ከሌሎቹ አገሮች ጋር ሳትተባበሩ ራሳችሁን ችላችሁ መኖር ትችላላችሁ” እያሉ የኢጣሊያንና የጀርመንን ሕዝብ በማታለል የሰበኩት፣ በውጭ ፖለቲካም በጥጋብና በእምቢተኛነት አኳኋን ከቀረው ዓለም ጋር አንተባበርም እያሉ ሲያውኩ ኖሩ። በዚህም ምክንያት ያገራቸውን ሕዝብ ከብርቱ ችግር ላይ ጣሉት። በፖሊቲካም አኳኋን መንግሥታቸውን ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ ጋር አጣሉት። ከዚያም በኋላ ሕዝባቸውን እንደከብት ነድተው ከዓለም ጦርነት ውስጥ ጨመሩት።
ሕዝብ ከመተባበር የሚአገኘውን ጥቅም ለማስረዳት ዛሬ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መንግሥት መካከል ካለው ወዳጅነት የተሻለ ምሳሌ አይገኝም። እነዚህ ሁለቱ አገሮች በጅዎግራፊ በጣም ይራራቃሉ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ፋሽስቶች ከጫኑባት ቀምበር ነፃ ለማውጣት የሁለቱ መንግሥታት መተባበር አስፈለገ። እንደዚሁም ደግሞ የሁለቱም መንግሥታት ጠላት የሆኑትን ናዚዎችና ፋሽስቶች ለማሸነፍ የኢትዮጵያ ወገኖች ለእንግሊዝ ትልቅ እርዳታ እንደሚሆኑት አይጠረጠርም።
ልብወለድ
በሀገራችን እስከዛሬ ድረስ ተዘንግቶ የቆየ ሌላ ዓይነት ድርሰት ልብወለድ የሚባለው ድርሰት ነው። ይህም ዓይነት መጽሐፍ ድርሰቱ አዲስ ዓይነት ነው። ዛሬ በዓለም ሁሉ ላይ በብዙው እየታተመ ስለሚሸጥ አእምሮውን ለማንቃትና የሚበልጠውን ጊዜ ለማሳለፍ አንባቢውም የሚአነበው ደስታ ለማግኘት ስለሆነ የልብወለድ ድርሰት ብዙ ጥቅም ያለበት መጽሐፍ ነው። ለጊዜ ማሳለፍና ለደስታ የሚአነበው ሕዝብ ለመመራመርና ጥበብን ሊፈልጋት ከሚአነበው ክፍል በጣም ይበዛል።
ይሁን እንጂ አንባቢው አዲስ ትምህርት አገኝበታለሁ ብሎ ቢአነበው እንኳ መጽሐፍ ካነበቡት መጥቀሙና ማስተማሩ አይቀርም። ስለዚህ የልብወለድ መጻሕፍቶች ለሕዝቡ ብዙ ትምህርት እንደሚሰጡትና እንደሚአሠለጥኑት አይጠረጠርምና ጸሐፊዎቻችን የልብወለድ ድርሰት እየደረሱ እንዲልኩልን አጥብቀን አናስታውሳቸዋለን።
የድርሰት ጥቅምና አገልግሎቱ የጸሐፊው መንፈስ የቀሰቀሰውን ሐሳብ ለሕዝቡ በማመልከቱ በመግለጹና በማስረዳቱ ነው። መንፈሱን የቀሰቀሰው ሐሳብና ሕይወት ያስተማራቸውን ትምህርት ለሕዝቡ ለማካፈል እንዲችል ድርሰቱም የጥበብ ሥራ እንዲሆንለት ለጸሐፊው የቋንቋ እውቀት ያስፈልገዋል።
ስለዚህ የሚጽፍበትን ቋንቋ ማርቀቅና ማሳመር የቻለ ደራሲ የልቡን ብርሃን ለማብራት ችሎታ ያለው ጸሐፊ ነው ሊባል ይቻላል።
(ይልማ ዼሬሳ – ሰኔ ፲፱፻፴፫)