ቆይታ ከበዕውቀቱ ሥዩም ጋር
(ከመስከረም 1998 ዓ.ም እትማችን የተወሰደ)
.
በዕውቀቱ ሥዩም የስነጽሑፍ ተስፋችንን ከጣልንባቸው ወጣት ጸሐፊዎች አንዱ ነው። “በክንፋም ህልሞች” ውስጥም የመጽሐፉን ርዕስ የያዘውን አጭር ልብወለድ ደራሲ ነው። ስለሱም ከመጽሐፉ ያገኘነው እንዲህ ይላል – “… በጎጃም ማንኩሳ በምትባል ገጠር ቢጤ ከተማ ተወለደ። ደብረ ማርቆስም ተማረ። በ1995 ዓ.ም. ‘ኗሪ አልባ ጎጆዎች’ የሚል የግጥም ስብስብና በ 1996 ‘በራሪ ቅጠሎች’ የሚል የሽርፍራፊ ታሪኮች መድበል አሳትሟል። … በ1993 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን በጽሑፍ ስራ ይተዳደራል።” በ1997 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በስልክ አግኝተነው ነበር።
አንብበህየወደድከውየመጀመሪያውመጽሐፍምንነበር?
ትዝ የሚለኝ የሐዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ነው። ከውጭ ደግሞ 3ኛ ነው 4ኛ ክፍል ያነበብኩት አንድ የኬንያ ጽሑፍ … አርእስቱ ጠፋኝ … ኸ … ታሪኩ ስለ ማሳዮች ነበር። አዎ ‘The Chiefs Shadow’ መሰለኝ።
የምትወደውየሐገርደራሲ?
ሀዲስ አለማየሁና ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር።
ገጣሚስ?
ዮፍታሔ ንጉሤና ዮሐንስ አድማሱ።
ኢትዮጵያውያንማንበብአለባቸውየምትላቸውሶስትመጽሐፎችየትኞቹናቸው?
መጀመሪያ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ን እመርጣለሁ። መጽሐፉ የኢትዮጵያን ስነጽሑፍ ወደፊት አሻግሯል። የአለም ስነጽሑፍ ደረጃን የጠበቀ የአገራችን የመጀመሪያው ድርሰት ነው – ግን ኢትዮጵያዊነቱን ሳይለቅ። ቀጥሎ የምመርጠው የስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን ‘ሌቱም አይነጋልኝ’ን ነው። ብዙ ሰው ስብሐትን የሚያውቀው Controversial ነገሮችን ስለሚያነሳ ነው። ነገር ግን አጻጻፉ ራሱ ጥንካሬ አለው ፤ ነፃ ሆኖ የጊዜውን የስነጽሑፍ ህግጋቶች Transcend አድርጓል – አልፏል። ከግጥም መጽሐፎች የዮሐንስ አድማሱን ‘እስኪ ተጠየቁ’ን እመርጣለው። በተጨማሪም የዕጓለ ገብረ ዮሐንስን “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተዋጣለት ሐተታ አቀራረቡ እመርጠዋለሁ።
ከውጭጸሐፊዎችእነማንንትወዳለህ?
ሚላን ኩንዴራን አደንቃለሁ፤ ‘The Unbearable Lightness of Being’ እና ‘Book of Laughter and Forgetting’ የሚባሉ መጽሐፎች አሉት – አራት አምስት ጊዜ ደጋግሜ ነው ያነበብኳቸው። ከዛ በፊት ረጅም ልብወለድ ደጋግሞ የሚነበብ አይመስለኝም ነበር። አንዴ ከተነበበ ታሪኩ ስለሚታወቅ ለምን ይደገማል እል ነበር። እንዲሁም ቪክቶር ሁጎን፣ ቻርልስ ዲክንስን እና ፍሬዴሪክ ኒቸን እወዳለሁ።
ለመሆኑለማነውየምትጽፈው? አንባቢህማነው?
እኔ እንኳ ለአንባቢ ብዬ ሳይሆን ለራሴ ነው የምጽፈው። ከዛም ጓደኞቼን አስነብባለሁ። እነሱ ከወደዱት እንዲወጣ ይደረጋል።
ዮሐንስአድማሱንብዙጊዜበጽሑፎችህታነሰዋለህ።የምትወደውንምያህልአንዳንዴትቀልድበታለህ።እንዴትነውነገሩ?
(ሳቅ ብሎ) የምቀልድበት ስለምወደው ይመስለኛል። ዮሐንስ ሀያሲነቱን በጣም አደንቃለሁ፤ ሂሶቹን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች አቅርቧል። ዘመናዊ ገጣሚነቱንም እስከነድክመቶቹ አደንቃለሁ።
ድክመቶቹ?
ድክመቶቹ – ለምሳሌ እንደነ ‘እስኪ ተጠየቁ’ የመሳሰሉት ግጥሞች ከመጠን በላይ ረዝመዋል፤ ስሰማ በዛ ጊዜ የነበሩ ጸሐፊዎች የአማርኛ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ዘዴ ነበር። በዛው ልክ የአማርኛ ግጥምን አሳድጓል። ከሱ በፊት የነበሩ ዘመናዊ ገጣሚዎች (እንደነ ከበደ ሚካኤል የመሳሰሉት) አንብበው ወይም ሰምተው የሳባቸውን ሀሳብ ቅርፁን ወደ ወል ግጥም ቀይረው ለሰው ያቀርቡ ነበር። ዮሐንስ ግን የራሱን የሚገርሙ እይታዎች በራሱ ቅርፅ!
መጽሐፎችህበራስህስእሎችየታጀቡናቸው።በአገራችንያልተለመደነገርነው፤እንዴትጀመርከው?
ወደ ሥነጽሑፍ ከመግባቴ በፊት ሥዕል እሞክር ነበር። አሁንም አቢሲኒያ ሥዕል ኮሌጅ ገብቼ እማራለሁ። ሥዕሎችን ከጽሑፋቸው ጋር በማዋሃድ የሳቡኝ ካሊል ጊብራንና በተለይም ዊልያም ብሌክ ናቸው። ሥዕሎቹ ለግጥሞቹ ወይም ለታሪኩ እንደ ማስረጃ ወይንም ምትክ እንዲሆኑ ብዬ አይደለም። በራሳቸው መንገድ እንደ ቅኔ እንደ ሀሳብ እንዲታዩ ነው።
እንደ “ክንፋምህልሞች” ገጸባህሪያትከማንኩሳወደደብረማርቆስከዛምወደአዲስአበባተሸጋግረሃል።አሁንስአሜሪካልትመጣነወይ?
(እየሳቀ) አይመስለኝም። አሜሪካን ለናንተ ትቻለሁ። አዎ ‘ክንፋም ህልሞች’ን ስጽፍ ከተወለድኩበት ማንኩሳ እስከ አዲስ አበባ ያለፍኩበትን የሕይወት ልምድ ተጠቅሜበታለሁ። የፈራሁት ግን የአሜሪካውን ደብዳቤ ነበር።
እንዴት?
አይ ለአሜሪካ መንፈስ ባእድ ስለሆንኩ በትክክል ላላቀርበው እችላለሁ ብዬ ፈርቼ ነበር።
እናመሰግናለን።
እኔም አመሰግናለሁ።
እንደ በዕውቀቱ ሥዩም ያሉ ደራሲዎች ለኢትዮጵያ ብዙ ያስፈልጋታል። ምክንያቱም የንባብ ባህል ብዙ ባልዳበረባት አገራችን በዕውቀቱ ሥዩም የሚያነሳቸው አይዲያዎች ስለ ሥነጽሑፍ ብዙም ጠለቅ ያለ እውቀት ለሌላቸውም ሆነ በመስኩ የተካኑተም የአፃፃፍ ስልቱ እና አቀራረቡ ለሁሉም እንዲገባ አድርጎ ስለሆነ በአገርኛ አባባል ወድጀዋለሁ። (Like)
LikeLike
በውቄ ይመቸኛል በአንድ ዘመን ላይ ስላለንም ለተጠራጣሪዋ ነፍሴም እፎይታ ነው
LikeLike
በዕውቀቱ ግሩም የሥነጽሑፍ ሰው ነው። ግጥሞቹና ልብወለዶቹ ምንጊዜም ቢነበቡ የማይሰለቹና ሁልጊዜም አዲስ ናቸው። ጽሑፎቹ ከማዝናናታቸውን በላይ የአንባቢውን ንቃታዊ ኅሊና የሚጨምሩና እንዲሁም የማህበረሰቡን ወግና ልማድም ድፍረትና ጉልበት ባለው የቋንቋ አገላለጽ የሚፈትሹ ናቸው።
LikeLike
በዕውቀቱ ግሩም የሥነጽሑፍ ሰው ነው። ግጥሞቹና ልብወለዶቹ
ምንጊዜም ቢነበቡ የማይሰለቹና ሁልጊዜም አዲስ ናቸው።
በተለይ ወቅታዊና በድሮ ታሪኮች ላይ የሚፅፈዉ ነገር ለኔ በቃ አቻ የማይገኝለት ነው ሁሉንም ሰው የሚያዝናና በተጨማሪም ቁምነገር የሚያስጨብጡ ናቸው።
LikeLike
Bewketu fegegta ena kumneger yazele mirt tsehafi new. Enwedhalen Berta.
LikeLike
የበዕውቀቱን መፅሃፍት እወዳቸዋሉ በዕውቀቱን እጅግ አመሰግናሉሁ….. እባካቸሁ በራሪ ቅጠሎችን የሚለውን የሚያውሰኝ…..
LikeLike